Administrator

Administrator

የዋሽንግተን የጤና ዳይሬክተር ጆክሴል ጋርሺያ
የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የጤና ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ጆክሴል ጋርሺያ በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን በኢቦላ ምክንያት እየተገለሉ እንደሆኑ ዘ ዋሽንግተን ታይምስ ዘገበ፡፡
ስለ ኢቦላ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በተለይ በታክሲ ሾፌርነት በመስራት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችን እያገለሉ እንደሚገኙ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አሽከርካሪዎቹ አፍሪካውያን እንደሆኑ ሲያረጋግጡ ቫይረሱን ያስተላልፉብናል በሚል ስጋት ከመኪና እንደሚወርዱ ተናግረዋል፡፡
የመገኛኛ ብዙሃን ሰራተኛ የሆነ አንድ ግለሰብ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወደ አሜሪካ ሲገቡ ለምን የኢቦላ ምርመራ አይደረግላቸውም የሚል ጥያቄ እንዳቀረበላቸው ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ከሁለቱ አገራት ዜጎች ጋር የእጅ ሰላምታ የማይለዋወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዳይሬክተሩ፤ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴቸው በኢቦላ ሰበብ መገለል እንደሚደርስባቸው አስታውቀዋል፡፡
በዋሽንግተን ከሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

ጋለሪያ ቶሞካ በትላንትናው እለት “ግልፅና ድብቅ ከብርድልብስ ስር” በሚል ርዕስ ለሁለት ወራት የሚቆይ የስዕል አውደ ርዕይ ከፍቷል፡፡ ለአውደ ርዕይ የቀረቡት የሰዓሊ ዘላለም ግዛው የስዕል ስራዎች ሲሆኑ ብዛታቸው 30 ነው፡፡ ሥዕሎቹ በማህበራዊ ህይወት ላይ የሚያተኩሩ እንደሆኑና በብርድልብስ የተሸፈኑ  ግለሰባዊ የውስጥና የውጭ ችግሮችን አጉልተው እንደሚያሳዩ ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
ሰዓሊ ዘላለም ግዛው፤ በ1990 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “አለ ፈለገ ሰላም የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት” ዲፕሎማ እንዲሁም በ2003 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘ ሲሆን ከ20 ጊዜ በላይ በአገር ውስጥ አንድ ጊዜ ደግሞ በአየርላንድ ከሌሎች ሰዓሊዎች ጋር ስራዎቹን ለእይታ አብቅቷል፡፡ በግሉ  አውደ ርዕይ ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዶ/ር ወሮታው በዛብህ የተዘጋጀውና ከ70 የሚበልጡ ሥራ ፈጣሪዎችን ታሪክ የሚያስቃኘው “ለራስ ማን እንደራስ” የተሰኘ መጽሀፍ ሰሞኑን ለንባብ የበቃ ሲሆን የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአምባ ሆቴል ይመረቃል፡፡ መፅሀፉ በራስ ፈጠራ እንዴት መለወጥ እንደሚቻልና በመፅሀፉ የተካተቱ ከ70 በላይ ሰዎች እንዴት እንደተለወጡ የተርካል ተብሏል፡፡ በምረቃው ዕለት የጂኒየስ ማሰልጠኛ ተቋም ሰልጣኞች ምረቃ፣ የስኬታማ ሰዎች ልምድና ሌሎች ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል፡፡ መፅሀፉ በ60 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን የመፅሀፉ አዘጋጅ በሥራ ፈጠራና ብልፅግና ዙሪያ በርካታ መፃህፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል፡፡

በወጣቱ ገጣሚ አያሌው እውነቴ የተጻፈውና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ65 በላይ ግጥሞችን የያዘው “ቁምታም ጾም”  የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሃፍ፣ ከትናንት ጀምሮ በገበያ ላይ መዋሉን ገጣሚው ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
92 ገጾች ያሉት “ቁምታም ጾም” የግጥም ስብስብ መጽሃፍ፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በ42.50 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ለውጭ አገራት የመሸጫ ዋጋው 9 የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡
መጽሃፉ በቅርቡ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር እና በደብረ ማርቆስ በሚካሄዱ የስነ-ጥበብ ዝግጅቶች በይፋ እንደሚመረቅ የገለጸው ገጣሚው፣ በቀጣይም ለህትመት የተዘጋጁ ሌሎች የግጥምና የወግ ስብስብ ስራዎችን ለአንባብያን እንደሚያበቃ ገልጧል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍ ተማሪ በነበረበት ወቅት፣ በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል የተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ገጣሚው፣ ከ17 አመታት በፊትም ለህትመት የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “የበረከቱ አስኳል” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡

በይታገስ ጌትነት ገበየሁ የተፃፉ አጭር ልቦለዶችን የያዘ “የደመና መንገድ” የተሰኘ መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ አጫጭር ልብወለዶቹ በተለያዩ ማህበራዊ፣ አገራዊና የፍቅር ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ ተብሏል፡፡ በ124 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡  ደራሲው ከዚህ ቀደም “ጥቁር ነጥብ” እና “ደጅ ያደረ ልብ” የተሰኙ መፅሀፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡

Saturday, 15 November 2014 11:28

የፀሃፍት ጥግ

እችላለሁም አልችልምም ብለህ ብታስብ አልተሳሳትክም፡፡
ሔነሪ ፎርድ
ወንድ ሆኜ ብወለድ ኖሮ አውሮፓን አስገብራት ነበር፡፡
ሜሪ ባሽኪርትሴፍ
(ሩሲያዊ ሰዓሊ፤ ስለ ጥበብ ሥራዋ የተናገረችው)
ሥራ በቅጡ እንዲከወን ከፈለግህ፣ ባተሌ ሰው ምረጥ፤ ሌሎቹ ጊዜ የላቸውም፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
ዕድል የምታግዘው ለዝግጁ አዕምሮ ብቻ ነው፡፡
ሉዊስ ፓስተር
ከራሴ ግራ መጋባት ውጭ ለማንም ሰው የማበረክተው ነገር አልነበረኝም፡፡
ጃክ ኬሮአክ
ኤክስፐርት ማለት ማሰብ ያቆመ ሰው ነው፡፡ ለምን ያስባል? ኤክስፐርት ነዋ!
ፍራንክ ሊሎይድ ራይት
የምጠጣበት ብርጭቆ ትልቅ አይደለም፤ ግን ቢያንስ የራሴ ነው፡፡
አልፍሬድ ደ ሙሴ
ሰዎች ስለ ሥነጥበብ እኔ የማውቀውን ያህል ብቻ እንኳን ቢያውቁ፣ ሥዕሎቼን ፈጽሞ አይገዙኝም ነበር፡፡
ኤድዊን ሄንሪ ላንድሲር
ተሰጥኦ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ነው፡፡ ስለኤሌክትሪክ ነገረ - ሥራ አይገባንም፤ ግን እንጠቀምበታለን፡፡
ማያ አንጄሉ
ለንግድ ሥራ ተሰጥኦ አለኝ፡፡ ይሄን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልትማረው አትችልም፡፡
አላን ሹገር

አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ ይሆናልን?
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው ሲደፍሩ ምክንያታቸው ምንድነው?
ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ባለሙያዎች የሚሰጡት ምላሽ፡-
አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ አይደለም፡፡ ሰዎች በሚፋቀሩበት ጊዜ አንዱ ለአንዱ ከማሰብ ውጪ አካልንና ስነልቡናን የሚጎዳ ነገር በፍጹም አይፈጽሙም፡፡
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው የሚደፍሩበት ምክንያት ኃይልን ለማሳየት፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ተገዶ መደፈር እና ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑም እንደ ብቀላ በመሳሰለው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በአዳማ ከተማ በአንድ ወንድ ልጅ ላይ የደረሰ ተገዶ መደፈርን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ የሰጡትን ሐሳብም እናስነብባችሁዋለን፡፡
የልጁ ምስክርነት የሚከተለው ነው፡፡
“...ሰውየው አብሮኝ ለነበረው ሰው እንዲህ አለው፡፡ ...ያንን ጥቁር ልጅ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ስራ ስለአለኝ ለዛ ጉዳይ ስለምፈልገው ጥራልኝ... አለው፡፡ እኔም ላነጋግረው ስወጣ አስቀድሞ እጄን ነበር የያዘኝ፡፡ ጊዜው እኮ መሽቶአል ስለው ...ግድየለም... ዋጋ እንነጋገራለን...በለሊትም ሰው ከምንቀሰቅስ ከእኔ ጋር ብታድር ይሻልሀል አለኝ፡፡ እኔም ግድ የለም ዋጋ ንገረኝና እመለሳለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እቤቱ አስገብቶ በቃ...ልብስህን አውልቅ...ተኛ...የሚል ትእዛዝ ነው የሰጠኝ፡፡ በቃ... ስለፈራሁኝ ብቻ ልብሴን አውልቄ ተኛሁ...”
በአዳማ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ቢሮአቸው የሚገኘው የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ የልጁን ሁኔታ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
“...የዚህ ልጅ ታሪክ... እድሜው 18 አመት ሲሆን ተወልዶ ያደገው ባሌ ሮቤ አካባቢ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ወላጅ አባት በበሽታ ምክንያት በመሞቱ ምክንያት እናትየው ካገባችው ሰው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ጋር መግባባት ስላቃተው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ለተወለዱ ልጆች የሚደረገው እንክብካቤ እና ቤተሰቡ ለእርሱ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበረው በበጎ ፍቃድ አሳዳጊዎች ምክንያት ወደ አዳማ መጥቶአል፡፡ ይህ ልጅ ወደ አዳማ ከመጣ ገና አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖአል፡፡ አስገድዶ የደፈረው ሰው የልጁን ታሪክ በማጥናት እና በማባበል ...እኔ ሆቴል አለኝ... ስራ አስገባሀለሁ... በማለት ሊያግባባው ሞክሮአል፡፡ ከዚያም ባገኘው እለት አስገድዶ ሲደፍረው ልጁ የነበረውን ጉልበት ተጠቅሞ በላዩ ላይ የተቀዳደደ ልብሱን በእጁ ይዞ ... አምልጦ ...ማመን በሚያቅት ሁኔታ ነበር ወደነበረበት የሄደው...”
ወደተጎጂው ስንመለስ የሰውየውን አባባል እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
“...እኔ እኮ ወድጄህ ነው፡፡ አፈቅርሀለሁ፡፡ ገና ሳይህ ነው ልቤ የተሸበረው... ወዘተ ሲለኝ ...እኔ እኮ ሴት አይደለሁም፡፡ ለምን ታፈቅረኛለህ... ብዬ ገፍትሬው ነው ያመለጥኩት፡፡”
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...አስገድዶ መድፈር ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው ወንድ ሴት ልጅ ላይ በሚያደርሰው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት እንደሚስተዋለው ግን ወንድ ወንድን እንዲሁም ሴት ወንድን የሚደፍሩበት አጋጣሚ አለ፡፡”
ወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መኮንን ቤተሰብ ይህ ነገር ሲፈጸም ቅድሚያ የሚሰጡት ሁኔታውን ለማድበስበስ እና ለመካድ እንጂ ልጆቹ የስነልቡና ድጋፍ ወይንም ፍትህ፣ ሕክምና እንዲያገኙ አይደለም፡፡ ይህ ብዙዎች የሚያደርጉት ሙከራ ሲሆን አንዳንድ ወላጆች፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ግን በፍጥነት እርምጃ የሚወስዱ መሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡  
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...ብዙ ጊዜ ሬፕ (አስገድዶ መድፈር) የሚያደርጉ ሰዎች ከተመሳሳይ ጾታም ይሁን ከተቃራኒ ጾታ ባጠቃላይም ከሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መፍጠር የማይችሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ምክንያትም ከአስተዳደግ ወይንም ከተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር     ጥሩ የሆነ መግባባትና ግንኙነት መፍጠር የሚያቅታቸው ከሆነ እንደዚህ ያለውን (አስገድዶ መድፈር) የመሳሰለውን ወንጀል እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸዋል፡፡”
ተገዶ መደፈር የደረሰበት ልጅ እንደገለጸው፡-
“...ድርጊቱን ፈጻሚው ሰው በህግ እንዲጠየቅ በሚደረግበት ጊዜ... እኔ እነዚህን ሰዎች ከየት እንደመጡ አላውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጊትም አልፈጸምኩም፡፡ ልጁንም አልጠራሁትም ...እንዲያውም አላገኘሁትም በማለት ነበር የካደው..” ብሎአል፡፡
አቶ መኮንን እንደሚገልጹትም፡-
“...ልጁ የደረሰበት ጉዳት ከፍ ያለ ስለነበር በጊዜው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ በሚያገኝበት በዚህ ስፍራ ሲመጣ ባለሙያዎች በህግ አንጻርም ሆነ በህክምናው እንዲሁም በስነልቡናው ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኝ ጥረት አድርገዋል፡፡ አስገድዶ ደፋሪው ምንም እንኩዋን ለመካድ ቢሞክርም በወቅቱ ልጁ እራቁቱን ...የተቀዳደደውን ልብሱን በእጁ ይዞ መምጣቱ እና ሌሎች የተለያዩ መረጃዎች በመኖራቸው     እውነቱን ለማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡”
አቶ መኮንን የህግ ባለሙያዎችን እና የህብረተሰቡን ትብብር በሚመለከትም፡-
“...ፖሊሶች ለሙያቸው ስነምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ቢያምኑም በጣም የሚያሳዝነው ግን ...አንዳንድ ፖሊሶች ለወንጀለኛው የማገዝ ነገር ይታይባቸው ነበር፡፡ ተጎጂው ባለበት ሌላም ታዛቢ በሚገኝበት ካለምንም ፍርሀት ...እኔ ዋስ ሆኜ አስወጣዋለሁ... ምንም ችግር የለም ሲሉ የተስተዋሉ ነበሩ፡፡ አስገድዶ ደፋሪው በዚህ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የሚታማ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሕግ ሳይቀርብ የቆየ መሆኑን እያወቁ እንደዚህ ያለ ንግግር በተናገሩ ላይ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቢያዝኑም በሌላ በኩል ደግሞ  ለሙያቸው ተገዢ የሆኑ ጠንካራ የፖሊስ አባላት አቃቤ ሕጎች እና ዳኞች በመኖራቸው ጉዳዩን በጥንካሬ ይዘው ከዳር በማድረሳቸው ጥፋተኛው በስምንት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አስችለውታል፡፡ ምንም እንኩዋን ጉዳት የሚያደርሱ ባይታጡም ለትክክለኛው ስራቸው የቆሙትን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እወዳለሁ...” ብለዋል፡፡
ሌላው አነጋጋሪው ነገር ሽምግልና ነው፡፡
ተገዶ የተደፈረው ልጅ እንደገለጸው “...የእኔ ወገኖች በሽምግልና ሲጠየቁ አይሆንም... አንቀበልም በማለት አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥፋት ተደግሞ በሌላ ሰው ሊደርስ እንደማይገባ ማስተማሪያ እና ደፋሪው ሰው በህግ መጠየቁ ለተደፋሪውም የሞራል ካሳ ስለሆነ... የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም ገንዘብ እንክፈል... ሌላም ካሳ እንስጥ ሲባል... መልሳቸው አንቀበልም የሚል ስለነበር ወደህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ሆኖአል፡፡” አቶ መኮንን በዚህ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው፡፡ መድሀኒት የሚሆነው ግን ተገቢውንና በጎውን ነገር ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ግን ሰው ለሰው መድሀኒት መሆኑ ቀርቶ መርዝ ይሆናል፡፡ ሽምግልና በሰው ልጆች ዘንድ የታወቀ በጎ ባህርይ ቢሆንም አንዳድ ጊዜ የሚውልበት ቦታ ግን ጎጂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች ተገደው ሲደፈሩ አስገድዶ ደፋሪው በህግ እንዳይጠየቅ ገንዘብ እንክፈል... የሞራል ካሳ እንስጥ የሚባለው ነገር ምክንያቱ ከጥቅም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለማንኛውም... ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የስነልቡና፣ የሞራል፣ የአካል ደህንነታቸው የሚጠበቀው ጉዳት አድራሹ በሚከፍለው ገንዘብ ሳይሆን በህግ ተገቢውን ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡     እንደ አቶ መኮንን አባባል ሰው ሶስት ድህነቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡  
ሰው መንፈሳዊ ድህነትን ማሸነፍ ይገባዋል፡፡ ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ፈሪሀ እግዚአብሄር ሊያድርበት ይገባል፡፡ ልጆች ተገደው መደፈር ሲደርስባቸው ለጥፋት አድራሹ ወገንተኛ ሆኖ መቆምና ስለልጆቹ የወደፊት ሕይወት አለማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
ሰው ማህበራዊ ድህነትንም ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሰው ለገንዘብና ለጥቅም ሳይሆን  ለእውነት ተገዢ መሆን አለበት፡፡
ሰው በሶስተኛ ደረጃ ማሸነፍ ያለበት ድህነት የአእምሮ ድህነትን ነው፡፡ ሁሉም ሰው የተቻለውን ያህል እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሕይወት እራስዋ ትምህርት ቤት እንደመሆንዋ ማንኛውም ሰው እውቀት እንዲኖረው እራሱን ካዘጋጀ እውቀት ይኖረዋል፡፡
ስለዚህ ... እነዚህ ሶስቱ መበደር የማንችልባቸው ድህነቶች ሲሆኑ ተበድረን ልናሸንፍ የምንችለውን የኢኮኖሚ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ፍላጎት ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር ወይንም ወንጀልን ለመደበቅ ሙከራ ማድረግ ያስጠይቃል ...ሰው... ሽምግልናን ከአግባብ ውጪ ለመተግበር መሞከር የለበትም፡፡

ሰሞኑን  በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ በተካሄደው የእስያ ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ በስብሰባ ማዕከሉ ውስጥ ማስቲካ ሲያኝኩ መታየታቸው ቻይናውያንን ክፉኛ እንዳስቆጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ኦባማ ቤጂንግ ከደረሱበት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ፣ በወጡ በገቡ ቁጥር ማስቲካ ሲያኝኩ እንደነበር የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ይፋ መደረጋቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ የኦባማ ድርጊት የቻይናን ታዋቂ ምሁራን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን እንዳስቆጣ ጠቁሟል፡፡ኦባማ በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይ ማስቲካ ማኘካቸውን ቻይናውያን በንቀት እንደተረጎሙትና ሲና ዌቦ የተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽም፣ ኦባማን በሚተቹ አስተያየቶች መጥለቅለቁን ዘገባው ገልጧል፡፡“ገና ከመኪናቸው ሲወርዱ ጀምሮ፣ እንደ ስራ ፈት ማስቲካ እያኘኩ ነበር” ብለዋል በቢጂንግ ሲንጉሃ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ይን ሆንግ፣ ድርጊቱን በማውገዝ በጻፉት ጽሁፍ፡፡
ማስቲካ ማኘክ በአንዳንድ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት፣ እንደ ነውር እንደሚቆጠር የጠቆመው ዘገባው፣ ሲንጋፖር ማስቲካ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ የሚከለክል ህግ እንዳወጣችና በጃፓንም በስራ ላይ ማስቲካ ማኘክ ክልክል እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ቦኮ ሃራም በአንድ ቀን ብቻ 209 ትምህርት ቤቶችን አቃጥሏል
ፕሬዚዳንቱ ዳግም ከተመረጥኩ ቦኮ ሃራምንና ሙስናን አጠፋለሁ ብለዋል

          ባለፈው ሰኞና ረቡዕ  ዮቤ በተባለ የናይጀሪያ ግዛት በምትገኘው ፖቲስኩም ከተማና  ኮንታጎራ በተባለች ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ ላይ በአጥፍቶ ጠፊዎች በተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች  የሞቱትን ከ52 በላይ ተማሪዎች ጨምሮ፣ በአገሪቱ ባለፉት 18 ወራት ከ255 በላይ ተማሪዎች በአሸባሪዎች እንደተገደሉ ተዘገበ፡፡የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ዜጎችን ለህልፈት በመዳረግ ላይ የሚገኘውን ቦኮ ሃራም የተባለ ቡድንና ሙስናን ከአገሪቱ ለማጥፋት በሚል ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
የምዕራባውያን ትምህርት መቆም አለበት የሚል አቋም ይዞ የሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሃራም የተባለ የአሸባሪዎች ቡድን፣ በተለይ ካለፈው አመት ግንቦት ወር ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሽብር ጥቃት መፈጸሙን አጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞና ረቡዕ የተከሰቱት ጥቃቶችም በዚሁ አሸባሪ ቡድን እንደተፈጸሙ ይገመታል ብሏል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር በቺቦክ ከተማ ወደሚገኘው ትምህርት ቤታቸው በማምራት ላይ የነበሩ 276 ናይጀሪያውያን ልጃገረዶችን የጠለፈው አሸባሪ ቡድኑ፤ በተማሪዎች ላይ ግድያ መፈጸም ከጀመረ መቆየቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ቦኮ ሃራም ከሳምንታት በፊት ካንኮ በተባለች ከተማ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በከፈተው ተኩስ፣ 13 ያህል ተማሪዎችን መግደሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ሌሎች 15 ተማሪዎችን እንደገደለም  አክሎ ገልጧል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር በዮቢ ግዛት በሚገኝ የመንግስት ኮሌጅ ላይ ባደረሰው ጥቃት 59 ተማሪዎች መሞታቸውን፤ በመስከረም ወር ላይ በግብርና ማሰልጠኛ ተቋም 44 ተማሪዎችንና መምህራንን መግደሉን፤ በሃምሌ ወር በማሙዱ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ባደረሰው ጥቃት 29 ተማሪዎችና መምህራን መሞታቸውን አስታውሷል፡፡ ቦኮ ሃራም ባለፈው ወር፣ 209 ትምህርት ቤቶችን ማቃጠሉንና በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የንብረት ውድመት መፈጸሙን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ለቦኮ ሃራም ጥቃት ተገቢውን ምላሽ አልሰጡም በሚል በዜጎቻቸው እየተተቹ ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በበኩላቸው፤ ቦኮ ሃራምንና ሙስናን ከአገሪቱ የማጥፋት አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ አገሪቱንና ዜጎቿን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል ያሉት ጆናታን፣ ከተመረጡ ቡድኑ ያገታቸውን ልጃገረዶች እንደሚያስለቅቁና የሽብር ሰንሰለቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚበጣጥሱ ቃል ገብተዋል፡፡

ረጅም አመታት በውጭ አገራት ያሳለፈው ገጣሚ ሃይሉ ገ/ዮሃንስ (ጎሞራው)፤ ባደረበት ህመም በሚኖርባት ስዊድን በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ በተወለደ በ79 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡እ.ኤ.አ በ1935 በአዲስ አበባ የተወለደው ሃይሉ፤ የቤተክህነት ትምህርት እየተከታተለ ያደገ ሲሆን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከተማረ በኋላ፣ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የስነ መለኮት ትምህርት ተከታትሏል፡፡
በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ገብቶ የተማረው ገሞራው፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በግዕዝ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተለያዩ የስነጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ ታዋቂነትን አትርፏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ይካሄድ በነበረ የግጥም ውድድር ላይ ባሸነፈበት “በረከተ መርገም” የተሰኘ ግጥሙም  ይታወቃል፡፡ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት ይካፈል የነበረው ገጣሚው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከዩኒቨርሲቲው ተባርሯል፡፡
በ1957 ዓ.ም የጻፈው “በረከተ መርገም” የተሰኘ ግጥሙ በ1966 ዓ.ም የታተመለት ሲሆን በ1980 ዓ.ም በስዊድን በድጋሚ ታትሞለታል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ለንባብ ባበቃው “አንድነት” የሚል አነስተኛ መጽሃፍ ሳቢያ ለእስር የተዳረገው ሃይሉ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በቴክኒክና በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች በመምህርነት አገልግሏል፡፡
ወደ ቻይና በማምራትም በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ የቻይናን ስነጽሁፍ ያጠና ሲሆን የቻይንኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላትና የቻይንኛ-እንግሊዝኛ የሃረጋት መጽሃፍ አዘጋጅቷል፡፡ ወደ ኖርዌይ ሄዶ የፖለቲካ ጥገኝነት ካገኘ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ቆይቶ ወደ ስዊድን በመጓዝ ኑሮውን በስቶክሆልም አድርጎ ቆይቷል፡፡