Administrator

Administrator

           ባለፈው ሳምንት በተካሄደው 41ኛው የበርሊን ማራቶን የ31 ዓመቱ ኬንያዊ ዴኒስ ኪሜቶ ርቀቱን ከ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያው ሰው ተብሎ ተደነቀ፡፡ ማራቶን መሮጥ ከጀመረ ገና የ5 ዓመታት ልምድ ያለው  ዴኒስ ኪሜቶ፤ ያስመዘገበው አዲስ የማራቶን ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሴኮንዶች ነው፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በሌላው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሳንግ ተይዞ ከነበረው ሪከርድ ላይ 26 ሰከንዶችን አሻሽሏል፡፡   ከ2 ሰዓት ከ4 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያው ሰው የነበረው በ2008 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡
በ41ኛው በርሊን ማራቶን ላይ ዴኒስ ኪሜቶ በሪከርድ ሰዓት ሲያሸንፍ የተሳትፎ እና የስፖንሰር ክፍያዎችን ሳይጨምር እስከ  154ሺ ዶላር ክፍያ ማግኘቱን የዘገበው ዴይሊ ኔሽን ነው፡፡ በውድድሩ አሸናፊነት 40ሺ ዶላር፤ ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች ስለገባ የ30ሺ ዶላር ቦነስ እንዲሁም ለሪከርዱ 50ሺ ዶላር ተከፍሎታል፡፡ ከወር በኋላ በሚደረገው የኒውዮርክ ማራቶን ላይ ከሚሳተፈው የቀድሞ ሪኮርድ ባለቤት እና የልምምድ አጋሩ ዊልሰን ኪፕሳንግ ጋር ለማራቶን ሊግ የ500ሺ ዶላር ሽልማትም ይፎካከራል፡፡ ዊልሰን ኪፕሳንግ በኒውዮርክ ማራቶን ካላሸነፈ ኪሜቶ የማራቶን ሊጉን በመሪነት ማጠናቀቁ የማይቀር ይሆናል፡፡ እንደኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘገባ በኤልዶሬት ከሰፈር ሰዎች ጋር ውድድሩን ትመለከት የነበረችው ካሮሊን ቼፕኩሪር የተባለች ሚስቱ ሪከርዱን በሰበረበት ወቅት ከደስታ ብዛት ራሷን ስታለች፡፡በማራቶን ስኬቱ ያገኘውን ሃብት በትውልድ አገሩ ትምህርት ቤት በመገንባት እና ወጣት የቤተሰቡ አባላት ከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እደግፍበታለሁ ብሏል፡፡ከዴኒስ ኪሜቶ አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በኋላ ርቀቱ ከ2 ሰዓት በታች ይገባል የሚለው አጀንዳም  በይበልጥ ማነጋገር ጀምሯል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት የተጠየቀው ዴኒስ ኪሜቶ የራሱን ሪከርድ የማሻሻል አቅም እንዳለው ተናግሮ፤  በሚቀጥለው ውድድር 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ልገባ እችላለሁ ብሏል፡፡ በበርካታ ጥናቶች በተሰሩ ትንታኔዎች 42.195 ኪሎሜትሮች (26 ማይሎች እና 385 ያርዶች) የሆነውን የማራቶን ርቀት ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  እስከ 30 ዓመታት ሊፈጅ ይችላል ተብሎ ነበር፡፡ ሰሞኑን ግን ቢያንስ በ10 ቢበዛ በ15 ዓመታት ውስጥ ሊሳካ እንደሚችል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተገልጿል፡፡
ይህን አስደናቂ የስፖርት ውጤት እንደሚያሳኩ ግምት ያገኙት ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኬንያና ኢትዮጵያ ቢሆኑም ግምቱ ወደ ኬንያ አጋድሏል፡፡በተያያዘ በ41ኛው የበርሊን ማራቶን በወንዶች ምድብ ለሶስትኛ ተከታታይ ጊዜ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በኬንያ አትሌቶች ሲሰበር በውድድር አይነቱ ከኢትዮጵያውያን ያላቸው ብልጫ በጋሃድ ተረጋግጧል፡፡ በሴቶች ግን ኢትዮጵያውያን እንደሚሻሉ የበርሊን ማራቶን አመልክቷል፡፡ በሴቶች  ያሸነፈችው ትርፌ ፀጋዬ በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች ከ18 ሰከንዶች ሲሆን ፈይሴ ታደሰ በ9 ሰከንዶች ዘግይታ ሁለተኛ ታደለች በቀለ እና አበበች አፈወርቅ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ በማግኘት የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በራድክሊፍ በለንደን ማራቶን የተመዘገበው ክብረወሰን 10 ዓመት ሆኖታል፡፡ ይህ ሪከርዷ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃዎች ከ25 ሰኮንዶች ነው፡፡
ዴኒስ ኪሜቶ ማነው?
በ14 ዓመቱ ትምህርቱን ያቋረጠው ዴኒስ ኪሜቶ አዘውትሮ አትሌቲክስን በቴሌቭዥን ይመለከት ነበር፡፡ በተለይ በ10ሺ ሜትር ኃይሌ ገብረስላሴና ፖል ቴርጋት በሲድኒ ኦሎምፒክ የነበራቸው ትንቅንቅ ወደ ስፖርቱ በደንብ አተኩሮ ለመግባት ምክንያት ሆኖታል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ገበሬ እና እረኛ ነበር፡፡በግብርናው  ድንች እና በቆሎ እያመረተ የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ ከአምስት አመት በፊት አንድ የቺካጎ ትሪቡን ጋዜጠኛ ወደ ማራቶን እንዲገባ ከመከረው በኋላ ግን ግብርናውን ትቶ በሳምንት እስከ 250 ኪሎሜትሮች በመሮጥ በከፍተኛ ትጋት ይለማመድ ነበር፡፡ የሚመገበው ደግሞ ጓሮ ያፈራውን ፍራፍሬ እና አታክልቶችን ብቻ ነው፡፡ ዴኒስ ኪሜቶ የማራቶን ስልጠናውን በመደበኛነት የሚያከናውነው ከኤልዶሬት ወጣ በምትገኝ ካፓንግኡቱኒ በተባለች የገጠር ከተማ ነው፡፡ ከ2008 እኤአ ጀምሮ  አብረው ልምምድ የሚሰሩት ደግሞ የማራቶንን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት በ2ኛ እና በ3ኛ ደረጃ የያዙት ኬንያውያኑ ጂኦፍሪ ሙታይ እና ዊልሰን ኪፕሳንግ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሶስቱ አትሌቶች ማራቶንን መሮጫ አማካይ ሰዓት 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ07 ሰከንዶች ነው፡፡ ዴኒስ ኬሚቶ ከ2012 ጀምሮ የማራቶን ሊግ አካል የሆኑ እና ሌሎች ትልልቅ ውድድሮችን ሮጧል፡፡ በ2012 በበርሊን ማራቶን ሁለተኛ ነበር፡፡ በ20014 የቦስተንን ማራቶንን አቋርጦ ወጥቷል፡፡ በ2013 የቶኪዮና የቺካጎ ማራቶኖች አሸንፏል፡፡ እንዲሁም ዘንድሮ የበርሊን ማራቶንን በሪከርድ ሰዓት በማሸነፍ በአጭር ግዜ የተሳካለት ዓለም አቀፍ ማራቶኒስት ሆኗል፡፡
ከ2 ሰዓት በታች የት እና መቼ?
ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ይገባባቸዋል ተብለው የተጠበቁ ውድድሮች የበርሊን እና የለንደን ማራቶኖች ናቸው፡፡ በተለይ የበርሊን ማራቶን ለውድድሩ አዳዲስ ሪከርዶች በተደጋጋሚ የሚመዘገቡበት አመቺ መድረክ ሆኖ  ቀጥሏል፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት 6  የዓለም ማራቶን ሪከርዶች በበርሊን ማራቶን ተሰብረዋል፡፡ በተለይ ያለፉት አምስት የማራቶን  ሪከርዶች ደግሞ የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች የተፈራረቁባቸው ናቸው ፡፡ በ2003 እኤአ ላይ ኬንያዊው ፖል ቴርጋት በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ55 ሴኮንዶች፤ በ2007 በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሴኮንዶችና በ2008 እኤአ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሴኮንዶች በኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገብረስላሴ በርሊን ላይ የተመዘገቡ የሪከርድ ሰዓቶች ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ኬንያውያን የሪከርድ መዝገቡን ተቆጣጥረውታል፡፡ በ2011 እኤአ በ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ38 ሴኮንዶች  ፓትሪክ ማኩ፤ በ2013 እኤአ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ23 ሴኮንዶች  ዊልሰን ኪፕሳንግ እንዲሁም በ2014 እኤአ በ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሴኮንዶች ዴኒስ ኪሜቶ ናቸው፡፡ መረጃዎች  እንደሚያመለክቱት ባለፉት 30 ዓመታት ከተመዘገቡ የማራቶን ሪከርዶች ስምንቱ በበርሊን ማራቶን  የተገኙ ናቸው፡፡ አራቱ በቺካጎና በለንደን አራት ሪከርዶች እንዲሁም  በሮተርዳም 3 የዓለም ማራቶን ሪኮርዶች ተመዝግበዋል፡፡
የዓለም ማራቶን ሪከርድ በአይኤኤኤፍ እውቅና ተሰጥቶት መፅደቅ የጀመረው በ2004 እኤአ ነው፡፡ ስለዚህም ባለፈው ሳምንት በዴኒስ ኪሜቶ የተመዘገበው በአይኤኤፍ የሚታወቅ እውቅና የሚያገኝ የዓለም ማራቶን ሪኮርድ ይሆናል፡፡ ከዚያን በፊት ክብረወሰኑ ይመዘገብ የነበረው ምርጥ ሰዓት እየተባለ ነበር፡፡ በ1908 እኤአ ላይ የተመዘገበው የመጀመርያው የማራቶን ምርጥ ሰዓት  2 ሰዓት ከ55 ደቂቃዎች ከ18 ሴኮንዶች ሲሆን ከዚያን በኋላ እስከ ዴኒስ ኪሜቶ ክብረወሰን ድረስ ከ45 በላይ የማራቶን ክብረወሰኖች ተመዝግበዋል፡፡
የማራቶን ሪከርድ በ1900  2፡40 ፤ በ1920ዎቹ 2፡32፤ በ1950ዎቹ 2፡15፤ በ1960ዎቹ 2፡08 ነበር፡፡ ከ1999 እኤአ ወዲህ በ3 ደቂቃዎች ተሻሽሎ 2፡05 ደረሰ፡፡ ከ2004 እኤአ ጀምሮ 2፡04 እና 2፡03 እያለ ቀጥሏል፡፡  ከ10 ዓመታት በፊት ከ2 ሰዓት 5 ደቂቃዎች በታች ማራቶን የሚገቡ ሁለት አትሌቶች ነበሩ፡፡ ባለንበት ጊዜ ግን በዚያ  ሰዓት የሚገቡት ከ35 በላይ ናቸው፡፡ ከ2 ሰዓት ከ06 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ ከ50 በላይ ማራቶኒስቶች ይገኛሉ፡፡ በ2013 እኤአ ላይ ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃዎች በታች ከገቡ 149 አትሌቶች 80ዎቹ የኬንያ ሲሆኑ የኢትዮጵያ 47 ናቸው፡፡
ብዙዎቹ የሁለቱ አገራት አትሌቶች በመጀመርያ ውድድራቸው ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች ውስጥ የሚገቡት 20 ደርሰዋል፡፡
ስፖርት ሳይንቲስት በድረገፁ በሰራው ትንተና የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች የሚገባ አትሌትን ለማግኘት ከ35 እሰከ 40 ዓመታት እንደሚፈጅ ገምቶ ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ በየዓመቱ የማራቶን ሪከርድ ሰዓት በአማካይ በ15 ሰከንዶች እየተሻሻለ መቀጠል አለበት የሚል ድምዳሜ ላይም ደርሷል፡፡በርግጥ የማራቶን ሪከርድ ሰዓትን ከ20 ሰከንዶች በላይ ማሻሻል ትልቅ የማራቶኒስት ስኬት ነው፡፡
ከዴኒስ ኪሜቶ አዲስ የማራቶን ሪከርድ በኋላ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት 157 ሴኮንዶች ይቀራሉ፡፡ እነዚህን ሴኮንዶች በማራገፍ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በርካታ ሁኔታዎች ወሳኝ ይሆናሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የማራቶኑን ርቀት ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚችሉት አትሌቶች ኬንያዊ ወይንም ኢትዮጵያ ዜገነት ያላቸው መሆኑ ይጠበቃል፡፡ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚችል አትሌት በሰዓት 13.1 ማይሎችን መሸፈን ይጠበቅበታል፤ ይህ ብቃት ያላቸው የሁለቱ አገራት አትሌቶች ብቻ መሆናቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ከእነዚህ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚወጣ አትሌት ከ7ሺ እስከ 8ሺ ጫማ ከፍተኛ አልቲትዩድ ባለበት አገር መኖሩ፤ ከ4ሺ ጫማዎች በታች ባለ ስፍራ  ልምምዱን መስራቱ ለሚያስፈልገው ብቃት አስፋላጊ ነው፡፡ ከዚያም አትሌቱ  ከባህር ጠለል በታች ዝቅተኛ በሚባል አገር ውድድሩን ማድረጉ ከ2 ሰዓት በታች የመገባቱን ሁኔታ ያጠናክረዋል፡፡
በሌላ በኩል ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት እንደ ዩሴያን ቦልት አይነት የላቀ ብቃት ያለው አትሌት መፈጠሩም ትረጉም ይኖረዋል፡፡ ከዩሴያን ቦልት በፊት መቶ ሜትርን በ9.6 ሰከንዶች ለመሸፈን ይቅርና በ9.7 ሰከንዶች አይገባም ይባል ነበር፡፡ በአጠቃላይ የሰው ልጅ በሚችለው ብቃት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  የስልጠና ሳይንስ እና ቴክኖሎጂም ለውጥ ይፈጥራል፡፡ 40 አመት በፊት የነበረው ስልጠና አሁን በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ እንደ አጋዥ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡አዲዳስ ለማራቶን ሯጮች የሚሰራቸው የመሮጫ ጫማዎች ለሪከርድ ሰዓቶች መመቸታቸው ሌላው አስተዋፅኦ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት እንኳን ዴኒስ ኪሜቶ ለሰበረው ሪከርድ አዲዮስቡስት የተባለው መሮጫ ጫማ ጠቅሞታል ተብሏል፡፡ ሌላው ኬንያዊ ፓትሪክ ማኩ ከ2 አመት በፊት ሪከርድ ያስመዘገበው በዚሁ መሮጫ ጫማ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የማራቶንን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡት አራት የኬንያ አትሌቶች እና ኃይሌ ገብረስላሴ ጨምሮ የሚጠቀሙት አዲዮስቡስት መሆኑ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚደረገውን ጥረት የአዲዳስ ምርት ሊያግዘው እንደሚችል እምነት አሳድሯል፡፡  አሯሯጮችም የሚያከናውኑት የቡድን ስራ ምክንያት እንደሚሆንም ተጠቅሷል፡፡ አሯሯጮቹ  ሙሉ ለሙሉ ማራቶን ቢሮጡ ሪከርዶች እና ፈጣን ሰዓት የማስመዝገብ ብቃት አላቸው፡፡ በ2011 እኤአ ላይ የኃይሌን ሪከርድ የነጠቀው ፓትሪክ ማኩ በፊት አሯሯጩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ብራዚል በሪዮዴጄኔሮ ከተማ ከምታዘጋጀው 30ኛው ኦሎምፒያድ በፊት አዲሱ የዴኒስ ኪሜቶ የማራቶን ሪከርድ ሊሰበር እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ ከ2 ሰዓት በታች የሚገባ አትሌት ደግሞ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይገኛል እየተባለ ነው፡፡
እነማን ታጭተዋል ኬንያዎች፤ ቀነኒሳ እና ሌሎች
ከሶስትና አራት የውድድር ዘመናት በፊት ከ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በታች ከሚገቡ 10 አትሌቶች ሰባቱ እድሜያቸው በአማካይ 24 የሆኑ ነበሩ፡፡ ባለፉት አምስት አመታት የታየው ግን ሪከርድ የመስበር እድል ያላቸው በእድሜያቸው በሰል ያሉ አትሌቶች ናቸው፡፡ በ2011 እኤአ ላይ የኃይሌን ሪከርድ የሰበረው ፓትሪክ ማኩ 29፤ አምና የፓትሪክ ማኩን ሪከርድ ያሻሻለው ሌላው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሳንግ 31 ዓመታቸው ነበር፡፡ በ2007 እና በ2008 እኤአ በቅደም ተከተል ለሁለት ጊዜ ሪኮርዶቹን የሰበረው ኃይሌ ገብረስላሴ በ34 እና 35 አመት እድሜው ነበር፡፡
እንደኦልአትሌቲክስ ድረገፅ ስታስቲካዊ መረጃ እና ደረጃ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ኬንያውያን በወንዶች ምድበ ከፍተኛ ብልጫ ሲኖራቸው ኢትዮጵያውያን በሴቶች ምድብ ይሻላሉ፡፡ በ2012 እና በ2013 ከተመዘገቡ የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች ኬንያውያን በወንዶች ምድብ ሲበዙ በሴቶች ኢትዮጵያውያን ይበዛሉ፡፡  በአሁኑ ጊዜ በ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ23 ሰከንዶች እስከ 2 ሰዓት ከ4 ዲቃዎች ከ05 ሰከንዶች የተመዘገቡ አራት ፈጣን ሰዓቶች የኬንያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከእነዚህ ፈጣን ሰዓቶች በመቀጠል የተመዘገቡትን አምስት ፈጣን ሰዓቶች አስመዝግበዋል፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውያን አንፃር ብልጫ ያላቸው ትልልቅ ማራቶኖችን ደጋግሞ በማሸነፍ እንጅ ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ አይደለም፡፡ በማራቶን ሪከርዶች ታሪክ 90 በመቶው ድርሻ በኬንያ እና ኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገበ መሆኑ ከእንግዲህ ለሚመዘገቡ የማራቶን ሪከርዶች ዋና እጩ ተደርገዋል፡፡
ከ2 ሰዓት በታች ማራቶንን ለመግባት ወይንም አዲስ የማራቶን ክብረወሰን ለማስመዝገብ ቅድሚያ ግምት ካገኙ አትሌቶች የመጀመርያው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ በፓሪስ የመጀመርያ ማራቶኑን በመሮጥ 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎችች ከ03 ሰከንዶች አስመዝግቦ የቦታውን ክብረወሰን ያሻሻለው የ31 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀለ ማራቶን ልዕልቷን ወደ ኢትዮጵያ ይመልሳል ተብሎ በብዙ ሚዲያዎች ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ቀነኒሳ በርሊን ላይ ከሮጠ ለሪከርዱ እድል ይኖረዋልም ተብሏል፡፡ ከቀነኒሳ ባሻገር ግምቱ ወደ ኬንያውያን አትሌቶች በብዛት ያጋደለ ነው፡፡
ከሳምንት በፊት በበርሊን ማራቶን ሁለተኛው የዓለም ፈጣን ሰዓ ያስመዘገበው ሌላው ኬንያዊ ጄፍሪ ሙታይ ግንባር ቀደም ግምቱን በመውሰድ ይጠቀሳል፡፡
በቆጂእና አካዳሚዎቻችን  የኬንያን ብልጫ እንዲመልሱ
የዓለም ምርጥ ማራቶኒስቶች ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ እየወጡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በቆጂ የምትባለዋ የክልል ከተማ በኬንያ ኤልዶሬት እና ኢቴን የተባሉ ከተማዎች ማራቶኒስቶችን በማውጣት በመላው ዓለም የሚስተካከላቸው የለም፡፡ ኦሮምያ ክልል አርሲ ውስጥ የምትገኘው የበቆጂ ገጠር ከተማ የትልልቅ የዓለም ማራቶኒስቶች መፍለቂያ በመሆኗ በየጊዜው ከፍተኛ ትኩረት እያገኘች በመላው ዓለም በሚሰራጩ ሚዲያዎች ተዳስሳለች፡፡ የበቆጂ ለጥ ያለ መልክዓ ምድር እና ተስማሚ  እና ተስማሚ አየር ንብረት  በርካታ የውጭ አገር አትሌቶችን እየሳበም ነው፡፡  ከወራት በፊት አንድ የቱርክ ጋዜጠኛ የበቆጂ ከተማን በመጎብኘት ያቀረበው ዘገባ ያቀረበው አሃዛዊ መረጃ የሚያስገርም ነው፡፡  17ሺ ነዋሪዎች ያሏት የበቆጂ ከተማ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ የዓለም ምርጥ አትሌቶች መገኛ ስትሆን፤ 7 የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖችን አፍርታለች፡፡ ቀነኒሳ በቀለ እና ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ በቀለ፤ ደራርቱ ቱሉ እና የእህቷ ልጆች የሆኑት የዲባባ እህትማማቾች፤ ፋጡማ ሮባ እና ቲኪ ገላና ትውልዳቸው ከበቆጂ መሆኑን የዘረዘረው የቱርኩ ጋዜጠኛ፤ የበቆጂ ሯጮች ባለፉት 20 ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ 16 ሜዳልያዎች 10 የወርቅ፤ ከ30 በላይ የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልያዎችን መሰብሰባቸውን ጠቅሷል፡፡ የበቆጂን አትሌቶች ስኬት በንፅፅር ሲያስቀምጠው 17ሺ ህዝብ ያላት የገጠር ከተማዋ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎቿ ብዛት 1.2 ቢሊዮን ህዝብ ካላት ህንድ ትበልጣለች፤ 247 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢንዶኔዥያ በሁሉም ኦሎምፒኮች በሁሉም ውድድሮች ባላት ተሳትፎ ካገኘችው የሜዳልያ ስብስብ በእጥፍ የሚል የሜዳልያ ስብስብም ካላት አሳይቷል፡፡ የዲባባ እህትማማቾች በኦሎምፒክ መድረክ ያገኟቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 22 ሚሊዮን ህዝብ ካላት ሲሪያ እና 28 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሳውዲ አረቢያ በድምር የሰበሰቡትን እንደሚበልጥ አመልክቶም ጥሩነሽ ዲባባ የሰበሰበችውን የወርቅ ሜዳልያ ብዛት 179 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ፓኪስታን አለማግኘቷን አውስቷል፡፡  አሁን በዓለም የጎዳና ሩጫዎች እና ማራቶኖች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ አትሌቶች ከበቆጂ የተገኙ መሆናቸው የከተማዋን የማራቶን ሯጮች መፍለቂያነት ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በዚህች ከተማ በስፋት አትሌቶችን ለማፍራት መንቀሳቀሳቸው ማራቶን ልዕልቷን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ወሳኝ ተግባር ይሆናል፡፡ እንደበቆጂ ሁሉ ኬንያም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮቿንና ማራቶኒስቶቿን የምታገኝባቸው ሁለት ልዩ አካባቢዎች ኤልዶሬት እና ኢቴን የተባሉት የገጠር ከተሞች ናቸው፡፡ በተለይ ኢቴን ከቅርብ አመታት ወዲህ የማራቶን ሯጮች መገኛ ብቻ ሳይሆን የዓለም ማራቶን ሯጮች መናሐርያ መሆንም ጀምራለች፡፡   ከሁለት ዓመት በፊት የኬንያ ምርጥ ማራቶን ሯጮች በሚፈልቁባት ኢቴን የተባለችው ከተማ በለንደን ማራቶን አዘጋጆች የሚደገፍ የማሰልጠኛ ትራክ ተሰርቶ ስራ ጀምሯል ባለፉት አምስት አመታት በርካታ የእንግሊዝ እና የአውሮፓ ሯጮች ከተማዋን መቀመጫቸው በማድረግ ትልልቅ የልምምድ ፕሮግራሞችን ያከናወናሉ፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በማንኛውም ወቅት በዚህች ኢቴን በተባለች ከተማ ቢያንስ እስከ 30 የውጭ አገር ሯጮች ይሰራሉ፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚመሩ ተቋማት በስፖርቱ ከፍተኛ ስኬትን ማግኘት፤ በኬንያ የተወሰደውን ብልጫ ለማስተካከል እንዲሁም በሪከርድ ሰዓቶች ውጤቱን የሚያጅብ ትውልድ ለመፍጠር በትጋት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ያሉ አዳዲስ አካዳሚዎች በሙሉ ራእይ እና አቅም መስራታቸው ግድ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተለይ ለአትሌተክስ ስፖርት ውጤታማነት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መታየቱ ይጠበቃል፡፡ ታዳጊዎች ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ከአካዳሚዎቹ በ2016 ሪዮዲጂኔሮ እስከምታስተናግደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ድረስ ምርጥ ወጣት አትሌቶችን በማፍራት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ከኬንያ እጅግ ወደኋላ እየራቀ የመጣበትን ሁኔታ መለወጥ  ይጠበቃል፡፡ አካዳሚዎቹ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ እድገት እና እንቅስቃሴን በሙሉ ፍላጎት በመከታተል በብሩህ ራዕይ የሚሰሩ ብቁ ባለሙያዎች ኖሯቸው መስራት አለባቸው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተሠሩት አካዳሚዎች ከመሠረተ ልማት ግንባታው ባሻገር ወደተግባራዊ ስልጠና መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአርሲ አካዳሚዎች የአትሌቶች መገኛ ለሀገራቸው በቆጂ እና በአርሲም ከተማ አሰላ ሁለት አካዳሚዎች በስፖርት ሚኒስትር ተገንብተዋል፡፡ ከ600 በላይ ታዳጊ አትሌቶችን ሲያሰለጥኑ የቆዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ታዳጊ አትሌቶች የኬንያን የበላይነት ለመስተካከል ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራባቸው ስኬታማ ለመሆን አይቸግርም፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ማራቶን ልዕልቷ ተብሎ ሲዘመር የኖረው የበላይነት ማራቶን ሃራምቤ ተብሎ በኬንያውያን የበላይነት ይቀጥላል፡፡

እየጮሁ ማውራትና መጨቃጨቅ ተከልክሏል
በሞባይል ወደ ውጭ አገራት መደወል አይፈቀድም
የሞባይል ባለቤት መሆን የሚችሉት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ብቻ ናቸው

የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በሚገኝባት ደቡብ ኮሪያ፣ በተጠቃሚዎች ላይ የሚታየውን የስነ-ምግባር ጉድለት ለመቅረፍ ሲባል አዲስ የአጠቃቀም መመሪያ መውጣቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ዮንሃፕ የተባለውን የደቡብ ኮሪያ የዜና ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የሞባይል ተጠቃሚዎች ላይ ከሚታዩ የስነ-ምግባር ጉድለቶች መካከል፣ ሰው በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ጮክ ብሎ ማውራትና መጨቃጨቅ ይገኙባቸዋል፡፡አዲሱ የአገሪቱ የሞባይል አጠቃቀም የስነ-ምግባር መመሪያ እንደሚለው፣ ተጠቃሚዎች ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው በትህትና መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡በሞባይል ስልክ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጭቅጭቆችን ለማስወገድ ሲባልም፣ የተደወለላቸው ሰዎች ጥሪያቸውን ሲመልሱ፣ ለደዋያቸው ማንነታቸውን ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
 የደዋያቸውን ማንነት እንዳወቁ መግለጽም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ደዋዩ ራሱን ለማስተዋወቅ ጊዜ እንዳይፈጅ ያግዘዋል ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ በሆነችው ደቡብ ኮሪያ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ2 ቢሊዮን በላይ እንደደረሰ የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ አለማቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ ክልክል ነው፡፡
የሞባይል ስልክ ባለቤት መሆን የሚችሉትም፣ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡

አብዛኞቹ የአገሪቱ ባለስልጣናት ፖሊሲ ሲያወጡ ጠንቋይ ያማክራሉ
የታይላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራዩዝ ቻኖቻ፣ ወደ ጠንቋዮች ጎራ ብሎ የመጪውን ጊዜ ዕጣ ፋንታ በተመለከተ የሚሰጡትን ትንቢትና ምክር መስማት ክፋት የለውም፤ ጥንቆላም ራሱን የቻለ ጥበብ ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
“ጠንቋዮች የሚነግሩኝን ትንቢት ልብ ብዬ እሰማለሁ፡፡ ምክራቸውንም እቀበላለሁ፡፡ እንዲያውም በቅርቡ በአገሪቱ ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጋር ግጭት ውስጥ ልገባ እንደምችል አስጠንቅቀውኛል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መገናኛ ብዙሃን መሪያችን ጠንቋይ ቤት ይሄዳሉ ሲሉ ያሰራጩት ዘገባም ትክክለኛ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ቻኖቻ በመገናኛ ብዙሃን ስለጠንቋይ አማኝነቴ የሰማችሁት ትክክል ነው ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠላቶቻቸው ካሰሩባቸው ድግምትና አስማት ለመንጻት ሲሉ፣ ከእግር እስከ ራሳቸው ጠበል መጠመቃቸውን በወሩ መጀመሪያ ላይ በይፋ መናገራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአገሪቱን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታክሲን ሺንዋትራን ጨምሮ በርካታ ደንበኞችን ወዳፈራው ኢት የተባለ የማይናማር ታዋቂ ጠንቋይ በመሄድ ምክር ይሰማሉ መባሉን ያስተባበሉት ቻኖቻ፣ ይሄም ሆኖ ግን ወደ ጠንቋዩ የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው አልደበቁም፡፡
ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች አብዛኞቹ፣ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ሲያስቡ ወደ ጠንቋዮች ሄደው፣ “ይበጃል፣ አይበጅም?” ብለው የማማከር ልማድ እንዳላቸው የጠቆመው ሮይተርስ፣  ታይላንድ ወደዘመናዊነት እየተሸጋገረች ያለች አገር ብትሆንም፣ ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ጥንቆላና መሰል የባዕድ አምልኮ አሁንም ድረስ በስፋት እንደሚከናወንባት አመልክቷል፡፡

ውድ እግዚአብሔር፡-
ወንድሜ ቶሎ ቶሎ ሽንቱን ይሸናል፡፡ እኔ ግን አይመጣብኝም፡፡ ለእኔ ብዙ ያልሰጠኸኝ አልቆብህ ነው?
ናቲ- የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ኤሊዬ ሞታብኛለች፡፡ ጓሮአችንም ቀብረናታል፡፡ አሁን ካንተ ጋር ናት እንዴ ?
ከሆነች ሰላጣ በጣም ትወዳለች እሺ፡፡
ዴቭ- የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ትልቅ ስሆን ቅርጫት ኳስ መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ በደንብ መጫወት እንድችል ቆዳዬን ጥቁር አድርግልኝ፡፡ ቁመቴንም በጣም አርዝምልኝ፡፡
አሌክስ- የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ወዳንተ ስፀልይ ደስ ይልሃል አይደል? እኔም ደስ ይለኛል፡፡
ጄሪ- የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
የሰንበት ት/ቤት አስተማሪዬ አንተ ሁልጊዜ እንደምትወደኝ ነግራኛለች፡፡ እውነቷን ነው? ትላንት ሳራ ላይ ያንን ነገር ካደረኩም በኋላ ትወደኛለህ? አውቀኸዋል አይደል?! በጣም አዝናለሁ፤ አሁንም ብትወደኝ ግን ደስ ይለኛል፡፡
ቤቲ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አያቴ ልትሞትብኝ ነው፡፡ አንተ እንደምትፈልጋት ነግራኛለች፤ እኔ ግን እዚህ አብራኝ እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ሌላ የፈለግኸውን ሰው መውሰድ ትችላለህ፡፡
ለእኔ ያለችኝ እሷ ብቻ ናት፡፡ እባክህን ከህመሟ ድና አብራኝ እንድትሆን አድርጋት፡፡
ጆኒ- የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ለምንድነው እባብና ሸረሪቶችን የፈጠርከው? በጣም እኮ ነው የምፈራቸው፡፡
ጄሪ- የ6 ዓመት ህፃን

         በአዲስ አበባ በየዓመቱ የሚካሄደው የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል ትላንት ዕለት ምሽት በ12 ሰዓት በጣልያን የባህል ማዕከል The Great Beautiful በተሰኘው የጣልያን ፊልም ተከፈተ፡፡
ለ15 ቀናት በሚዘልቀው የፊልም ፌስቲቫል ላይ የ15 አውሮፓ አገራት ፊልሞች ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን የጣልያን ባህል ማዕከልን ጨምሮ በገተ ኢንስቲቲዩትና በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ፊልሞቹ እንደሚታዩ ታውቋል፡፡
ሁሉም ፊልሞች በነፃ ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወይም በእንግሊዝኛ ትርጉም (subtitles) እንደተዘጋጁም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም The Selfish Giant በተሰኘው የእንግሊዝ ፊልም እንደሚጠናቀቅም ታውቋል፡፡

Monday, 06 October 2014 08:41

“መረቅ” ነገ ይመረቃል

በደራሲ አዳም ረታ የተጻፈው “መረቅ” የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የደራሲው አድናቂዎችና የጥበብ ቤተሰቦች በተገኙበት ነገ ጧት በሃገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
ለረጅም አመታት በውጭ አገራት የኖረው ደራሲ አዳም በሚገኝበት በሚከናወነው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ፣ የተለያዩ ስነ-ጽሁፋዊ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ስለደራሲው ስራዎችም ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
ለደራሲው ስምንተኛ ስራው የሆነውና 600 ገጾች ያሉት “መረቅ”፣ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም  120 ብር ነው፡፡

Monday, 06 October 2014 08:33

የፍቅር ጥግ

አንድ ወጣትና አንዲት ኮረዳ በሞተር ሳይክል ይጋልባሉ፡፡ ሞተሩ 100 ሜትር በሰዓት ይከንፋል፡፡
ኮረዳዋ፡- ቀስ በል በናትህ፤ በጣም ያስፈራል!
ወጣቱ፡- አይዞሽ፤ ደስ ይላል እኮ!
ኮረዳዋ፡- ምንም ደስ አይልም፤ በናትህ በጣም ነው የሚያስፈራው!
ወጣቱ፡- እንግዲያውስ እወድሃለሁ በይኝ፡፡
ኮረዳዋ፡- እሺ እወድሃለሁ፤ ግን ቀስ በል!
ወጣቱ፡- በይ ሄልሜቴን ውሰጂና ጭንቅላትሽ ላይ አጥልቂው፤ እኔን አስጨንቆኛል፡፡
በነጋታው በወጣ ጋዜጣ ላይ፡- አንድ ሞተር ሳይክል ፍሬን በጥሶ ከአንድ ህንፃ ጋር በመጋጨቱ ሞተሩ ላይ ከነበሩት ሁለት ሰዎች አንደኛው ህይወቱ ወዲያው አልፏል፡፡ የሆነው እንዲህ ነው፡- ጥንዶቹ ግማሽ መንገድ እንደከነፉ፣ ፍሬኑ እምቢ ማለቱን ወጣቱ ተገንዝቧል፡፡ ነገር ግን ፍቅረኛው ይሄን እንድታውቅ አልፈለገም፡፡
ይልቁንም ለመጨረሻ ጊዜ እወድሃለሁ የሚለውን ጣፋጭ ዜማዋን ማዳመጥ ስለፈለገ እንድትልለት ጠየቃት፡፡ ከዚያም ሄልሜቱን (ከአደጋ መከላከያውን) ከራሱ ላይ ወስዳ እንድታጠልቀው አደረጋት፡፡
ወጣቱ ሄልሜቱን ባለማድረጉ ለሞት እንደሚዳረግ ያውቅ ነበር፡፡ እሱን ያሳሰበው ግን የፍቅረኛው ህይወት ነው፡፡ ስለዚህም እሱ ሞቶ፤ እሷን አተረፋት፡፡  

Monday, 06 October 2014 08:32

የፀሐፍት ጥግ

ስለፖለቲካ

ፖለቲካ በጣም ብርቱ ጉዳይ ስለሆነ ለፖለቲከኞች የሚተው አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡
ቻርልስ ደጎል
በእኛ ዘመን ከፖለቲካ መራቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ጉዳዮች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ጆርጅ አርዌል
ፖለቲካ ፍልስፍናን በተካበት ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡
ጆሲ ማርያዲ ኢካዲ ኪውይሮዝ
ፖለቲከኛ፤ ጌታ ለመሆን አገልጋይ መስሎ ይቀርባል፡፡
ቻርልስ ደጎል
እውነት በአብላጫ ድምፅ አይወሰንም፡፡
ዶግ ግዊን
ለችግሮቻቸው የቀድሞውን አስተዳደር ያልወቀሱ ብቸኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን ናቸው፡፡
ያልታወቀ ፀሐፊ
ወግ አጥባቂ ማለት ምንም ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ መሰራት የለበትም ብሎ የሚያምን ሰው ነው፡፡
አልፍሬድ ኢ.ዊጋም
የከተማዋን መክፈቻ ቁልፎች ለፖለቲከኛ ከመስጠት ይልቅ መቆለፊያዎቹን መቀየር ሳይሻል አይቀርም፡፡
ዶውግ ላርሰን
እጅግ በጣም ጥቂት ሴት ፖለቲከኞች ያሉበት ምክንያት ሁለት ፊት ላይ ሜክአፕ መቀባት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
ማዩሪን መርፊ
የቤተሰብ ሐረግህን ለማስጠናት ለምን ገንዘብ ትከፍላለህ፤ ፖለቲካ ውስጥ ግባና ተቀናቃኞችህ ያጠኑልሃል፡፡
ያልታወቀ ፀሃፊ
አንድ አሜሪካዊ ለዲሞክራሲ ለመዋጋት ውቅያኖስ ይሻገራል፤ ለብሄራዊ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ግን ጎዳና አይሻገርም፡፡
ቢል ቫውግሃን
ድምፅ መስጠት (ምርጫው) አይደለም ዲሞክራሲ የሚባለው፤ የድምፅ ቆጠራው ነው፡፡
ቶም ስቶፓርድ

            መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በማዕከሉ ባዘጋጀው የመስቀል በአል አከባበር ስነስርአት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገች፡፡ በእለቱ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ከማዕከሉ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ በመስቀል አከባበር ስነስርአት ላይ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የመንግስት አካላት የተገኙ ሲሆን ዝግጅቱን በንግግር የጀመሩት የመቄዶንያ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ብርሀኔ ጸጋዬ እና የድርጅቱ መስራችን ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ ማዕከሉ በአራት ማዕከላት 650 በላይ ለሚሆኑ ተረጂ ወገኖች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልፀው ከመንግስት የጠየቀውን 30.000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሰጠው፣ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ የተረጂውን ቁጥር ወደ 10,000 /አስር ሺህ/ ለማሳደግ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉም የጎበኙትና 100.000 ብር የለገሱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ፓትሪያርክ ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብጹሃን ጳጳስ፣ ይህንን እርዳታ እንዲያደርጉ የረዳቸውን እግዚአብሔርን አመስግነው ማዕከሉ እያከናወነ ያለው ተግባር እግዚአብሔር የሚወደው መሆኑን የገለፁ ሲሆን እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ወደፊት በማስተባበርም ሆነ በገንዘብ እግዚአብሔር በሰጠን፣ አቅማችን በፈቀደ እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ይህ ተቋም ከሌሎች የተለየ እውቅናና ክብር እንድንሰጠው ያደረጉ ተግባሮችን እየሰራ ያለ ማዕከል ነው፡፡ ከማዕከሉ ጋር አብረን ለመስራት ፈቃደኛ መሆናችንን ማረጋገጥ እንወዳለን ያሉ ሲሆን፤ የወረዳ 9 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ በፈቃዱ በበኩላቸው፤ የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን እየተደረገ ያለውን ድጋፍና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እናደንቀዋለን፤ ከዚህም ባሻገር እንደ አስተዳደር ልንተጋገዝ የሚገባ ጉዳይ ሲገኝ ተጋግዘን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ
ምዝገባው የሚካሄደው የስራ አጡን ቁጥር ለማወቅ ነው ተብሏል

        በአዲስ አበባ  ቤት ለቤት የሚካሄደው የስራ አጦች ምዝገባ አላማ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለማወቅ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ ተብሏል፡፡ ወደ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተይዞለት ከመስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፤ በዋናነት በከተማዋ ምን ያህል ስራ አጥ አለ የሚለውን ለማወቅና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ፣ የስራ እድሎችን ለማመቻቸት የታቀደ ፕሮጀክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የሙያ ደህንነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ ስዩም ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ እንዲህ መሰሉ ምዝገባ ከዚህ ቀደምም በየጊዜው በከተማዋ እንደሚካሄድ አስታውሰው፣ የአለማቀፍ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ለአገራት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥነት ሁኔታ በተጠናከረ መረጃ የማደራጀት፣ የመተንተንና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተንተርሶ መፍትሄ የመስጠት አካል ነው ብለዋል፡፡ የስራ አጥነትን ሁኔታ አጥንቶ የስራ እድሎችን ማመቻቸት የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮው አንዱ ኃላፊነት እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ምዝገባው ከወር በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደታቀደ ጠቁመዋል፡፡ ቤት ለቤት እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፣ ተመዝጋቢዎች በምን አይነት የስራ መስክ ላይ ቢሰማሩ ይመርጣሉ የሚለውን ያካተተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳ፤ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ የተሰበሰበው መረጃ ተተንትኖ፣ ተመዝጋቢዎች በሚፈልጉት የስራ መስክ ስልጠና ወስደው የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
ቢሮው ስራና ሰራተኛን በነፃ የማገናኘት ኃላፊነቱን ለመወጣትም ራሱ ስራ አጦችንና ስራን ከማገናኘት ባለፈ ፍቃድ የተሰጣቸው ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስራ አጦችን ስራ በማስያዝ ተግባር እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ምዝገባው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት የሚያደርገው ጥናትን መሰረት አድርጎ የተለያዩ ማመላከቻዎችን መጠቀሙ እንደሆነ የገለፁት አቶ ካሣ፤ በከተማዋ ያሉ ስራ አጦች በየትኛው የስራ መስክ ነው የበለጠ መሰማራት የሚፈልጉት የሚለውን ለይቶ ለማወቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ መረጃውን በመጠቀምም የተለያዩ የመንግስት እና የግል የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና መስካቸውን እንዲፈትሹ አጋዥ ይሆናል ሲሉ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡
በምዝገባው ወቅት እድሜና የትምህርት ደረጃ የመሳሰሉትን ጨምሮ በትክክልም በአዲስ አበባ ነዋሪ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይሰበሰባሉ ተብሏል፡፡ በአለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት መስፈርት መሰረት እድሜያቸው ከ14-18 ዓመት ያሉት በወጣት ስራ ፈላጊነት ይመዘገባሉ ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ የእድሜ ክልል ላሉ በአቅማቸው ሊሰሩት የሚችሉት ስራ ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ በዚህ የምዝገባ ሂደት አይካተቱም ብለዋል - ኃላፊው፡፡ በየዓመቱ በርካታ የከተማዋ ስራ አጦች የስራ እድል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ካሣ፤ በ2006 ዓ.ም ከ230 ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ በዚህ የስራ አጦች ምዝገባ ፕሮጀክትም ከ350 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ይመዘገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ምዝገባው የቤት ሰራተኞችን ጨምሮ ማንኛውም ተቀጥሮ የሚሰራና ገቢ የሚያገኝ ግለሰብን አይመለከትም ተብሏል፡፡
ስራ አጦችን ለመመዝገብ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ እንደተገባ የተናገሩት ኃላፊው፤ 734 ሰራተኞች በኮንትራት ተቀጥረው በከፍተኛ አማካሪነት፣ በሱፐርቫይዘርነት፣ በአስተባባሪነት እና በመረጃ አሰባሰቢነት እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡ መረጃ ሰብሳቢዎችም በዲግሪ የተመረቁ እንደሆኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም የክልል ከተሞች በ2007 ዓ.ም በሃገሪቱ ምን ያህል ስራ አጦች አሉ የሚለውን በዘመናዊ መንገድ ለይቶ ለማወቅ ተመሳሳይ ምዝገባ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ቀደም በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ስራ አጦች እንዳሉ አመላካች የሆነ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መረጃ እንዳልነበረ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡