Administrator

Administrator

የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ላለፉት 10 ወራት ያገለገሉት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፤ ከተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፊ ሰጪ አመራሮችና የካቢኔ አባላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው እንደለቀቁ ተናገሩ፡፡
ለዳያስፖራዎች ክብር እንዳላቸው የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ የተወሰኑ የዳያስፖራ የፓርቲው ድጋፍ ሰጪ አባላት አገር ውስጥ ባለው አመራር ጣልቃ በመግባት ማዘዝ እንደሚፈልጉ ጠቁመው ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ስለሚያደርጉ ብቻ ፓርቲውን የእነሱ ወኪል ለማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
“መውረድ አለብህ ብለው ጥያቄ ማቅረባቸውን አልቃወምም፤ ነገር ግን ተቃውሞዋቸውን በተቋማዊ መንገድ ማቅረብ አለባቸው” የሚሉት ኢንጂነር ግዛቸው፤ “እዚህ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርግ፣ እዚያ ቦታ ህዝባዊ ስብሰባ ጥራ እያሉ የሚያዙትን አልቀበልም” ብለዋል፡፡ “የሚሰጡትን ገንዘብ እንደ በጎ አድራጎት ማየት የለባቸውም፤ እንደ ግዴታ መውሰድ አለባቸው፤ እኔ ለእስርም ሆነ ለሞት ቅርብ እንደሆንኩት ሁሉ እነሱም ገንዘብ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው እንጂ በገንዘብ እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር የለባቸውም” ሲሉ ተናግረዋል - ኢንጂነሩ፡፡
“ግንኙነታቸውም ግለሰባዊ በመሆኑ ይህንን እቃወማለሁ” የሚሉት ኢንጂነሩ፤ እኔን ከስልጣን የማውረድ መብት ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ቢሆንም አተካሮ ውስጥ ገብቼ ፓርቲውን ላለመጉዳት ስል በገዛ ፈቃዴ መልቀቁን መርጫለሁ ብለዋል፡፡ አክለውም “አንዷለም አራጌ ታስሮ አንተ እቤት ቁጭ የማለት ሞራል አለህ ወይ? በሚል ግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁ በግፊት መውረድ አልፈልግም” ብለዋል፡፡
ከተወሰኑ የካቢኔ አባላት ጋር ያለመግባባት የተፈጠረው ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ በተደረገው ሙከራ መሆኑንም ኢ/ር ግዛቸው ገልፀዋል፡፡ ውህደቱ መኢአድ ውስጥ ባለ ችግር ምክንያት ሊሳካ አልቻለም ብለዋል፡፡
ለውጥ በህዝባዊ አመፅም ሆነ በትጥቅ ትግል ይመጣል ብለው እንደማያምኑ የገለፁት ኢንጅነሩ፤ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደርም ሆነ ላለመወዳደር ገና እንዳልወሰኑ ተናግረዋል፡፡

ህጻናትን በፍቅርና በሰላም ማሳደግ የሚቻለው ይበልጡኑ ወላጆች ኃላፊነት የሚሰማቸው እና ጥሩ ምሳሌ ሲሆኑ ነው፡፡ ቤተሰብህን በተሸለ ደረጃ መምራት ማለት አለምን በተሸለ ደረጃ ለመምራት ዝግጁ መሆን ማለት ነው የሚለው የጠበብት ንግግር ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ወላጅ ልጅን በማስተናገዱ ረገድ እራሱን ሊጠይቅ ከሚገባቸወ ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
* እኔ ወላጅ ከሆንኩኝ ልጄን በትክክል ለመርዳት የሚያስችል በቂ ጊዜ ሊኖረኝ ይገባል? ወይንስ በተጣበበ ጊዜ የማደርገው ነገር ትክክል ነው?
* ለመሆኑ ማድረግ የሚገባኝን እያደረግሁኝ ነውን?
* የትኛው ትምህርት ቤት ባስተምረው ጥሩ ይሆናል?
* ልጄን በሚያዝናና መንገድ እየረዳሁ ነውን? ወይንስ?
* በማደርገው ነገር ውስጤን በትክክል አምነዋለሁኝ? ወይንስ እየተጠራጠርኩ ነው?
የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለራስ በማቅረብ ልጆችን በተገቢው መንገድ ማሳደግ በሁሉም ወላጅ እና ቤተሰብ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ላይ የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡
የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 35 ማንኛውም አንድ ህፃን ሊኖረው የሚገቡ መብቶች ብሎ የሚከተሉትን በዝርዝር አስቀምጧል፡-
ሀ) በህይወት የመኖር፣
ለ) ስምና ዜግነት የማግኘት ፣
ሐ) ወላጆቹን ወይም በህግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣
መ) ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣በትምህርቱ፣በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስራዎችን እንዲሰራ ያለመገደድ ወይም ከመስራት መጠበቅ፣
ሠ.. በትምህርት ቤቶች ወይም በህፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈፀም ወይም ከጭካኔና ኢሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን፣ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መካከል ተራቁጥር (መ) እንዲሁም (ሠ) ህፃናትን ከተለያዩ አካላዊ ብሎም ስነልቦናዊ ጥቃቶች ለመከላከል ታስቦ የወጣ ነው፤እንደ ኢፌዲሪ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚንስ..ር አገልለፅ ለጥቃት ተጋላጭ ሆኑ የሚባሉት ህፃናት...
 ‹‹አስፈላጊው እንክብካቤ የማይደረግላቸው እንዲሁም ደህንነታቸው በተለያየ ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀና ህገመንግስቱ የደነገገላቸውን መብት መጠቀም ያልቻሉ ህፃናት ናቸው›› children advocacy center የሚለው ሕጻናትን ተንከባክቦ በማሳደግ ረገድ ለዚህ እትም መረጃ ያደረግነው ጽሁፍ ሲጀምር ተከታዮቹን ነጥቦች ይዘረዝራል፡፡
* ከትዳር አጋራችን ጋር የሚኖረን ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት፣
* የኢኮኖሚ ችግር ፣
* ከእፅ እና ከአልኮል ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲሁም፣
* በልጅነት ተከስቶ ያለፈ ጥቃት፣
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ለሚያደርሱት ጥቃት  እንደ መንስኤ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የቱንም ያህል ልጃቸውን የሚወዱ ወላጆች እን..ን ቢሆኑ እንደችግር ለተጠቀሱት ነጥቦች ትእግስትን ወይንም መቻልን ያጣሉ፡፡ children advocacy center የህፃናት ጥቃትን ለመከለላከል የሚያስችሉ መንገዶች ብሎ ካስቀመጣቸው ሀያ ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑትን ሀሳቦች እናስነብባችሁ፡
1/ጥሩ ምሳሌ ወይም አርአያ መሆን፣ ወላጆች ለሁሉም የቤተሰብ አባላት ተገቢውን ቦታ እና ክብር ሊሰጡ ይገባል፤ ልጆችን ትህትና     በተሞላበት መንገድ ማነጋገር ተገቢ ነው፡ አግባብ ያልሆነ ምግባር ሲያሳዩም  እነሱን ሳይሆን ድርጊታቸውን እንዳልወደዱት ከመንገር ባለፈ ፈፅሞ ልጆችን ለመምታት እንዳይሞክሩ ይመከራል፡፡፡
 መምታት ወይም ሌሎች አካላዊ     እርምጃዎችን መውሰድ ልጆች ሀይለኝነትን እንዲማሩ ያደርጋል፡፡ የተሳሳቱ መስሎ ተሰማዎት ይቅርታ ይጠይቁ ይህን በማድግዎ ለልጆ መልካም ባህሪን ያወርሳሉ፡፡
2/ልጅዎን ጓደኛ ማድረግ፣ልብ ይበሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን በቁጣ እና በንግግር ብቻ ማለፍ አለመግባባትን ለማቅለል ይረዳል፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን ደስታ እና ጥሩ ፊት ሲያዩ መልካም ምግባር ይኖራቸዋል ስለዚህ ከልጆችዎ ጋር መዝናናትን አሊያም የእግር ጉዞ ማድረግን     ያዘውትሩ፡፡
ይህን መሰል ድርጊቶች ድካምን ለመቀነስ ብሎም ከልጆችዎ ጋር የሚኖርዎትን ግንኙነት ለማጠንከር አይነተኛ መንገድ ነው፡፡
3/ልጆችን ማመስገን ወይም ማበረታታት፣    መጥፎ ቃላት ልጆች ዋጋቢስ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ጉዳቱም የእድሜ ልክ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ቀና ይሁኑ፡፡ ምን ያህል በእሱ/በእሷ ደሰተኛ እንደሆኑ እና     በእርስዎ ዘንድ ያላቸውን ቦታ ለልጆቾ አዘውትረው ይንገሯቸው፡፡
4/እርምጃ መውሰድ ወይም ሌሎች እስኪጀምሩ አለመጠበቅ፣በስራ ቦታ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች የህፃናት ጥቃትን በሚመለከት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ድርጊቱን ለማቆም በይበልጥ እንተጋለን፡፡
5/በጎ ፈቃደኛ መሆን ፣ ጊዜዎን በህፃናት ጥበቃ እንዲሁም ለልጆች ድጋፍ የሚሰጡ ፕሮግራሞችን ለመደገፍ     ያውሉት፡፡
6/ በህፃናት ማቆያ ማእከል ውስጥ ማገልገል፣  ጊዜዎን የተጎዱ እና ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናትን ለሚንከባከብ ማእከል የበጎፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ያውሉት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ህፃናትን ከሚረዱ ማእከላት ጋር     ህብረት በመፍጠር አብረው ይስሩ ፡፡
7/ ስለህፃናት ጥቃት እንዲሁም መከላከያ መንገዶቹ በቂ ግንዛቤ መያዝ፣
8/ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ወላጅ መሆን ፣ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም ነገርግን አንድ ህፃን ደህንነቱ ሲጠበቅ የሚሰማውን ሲያዩ እርካታዎ ከፍያለ ነው፡፡
9/ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ እና በህፃናት ደህንነት ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር መስራት፣
10/ የትኞቹ ህፃናት በይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ እንደሆኑ መረዳት፣ ምንም እን..ን የህፃናት ጥቃት ዘር እና ባህል ሳይለይ በሁሉም ህብረተሰብ ክፍል  የሚከሰት ቢሆንም አብዛኛዎቹ አካላዊ ጥቃቶች የሚከሰቱት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለቸው  የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ነው፡፡
የአእምሮ ህመም እንዲሁም የአካል ጉዳት ያለባቸው ታዳጊ ህፃናት ደግሞ ለድርጊቱ በይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡
11/ የጥቃቱን መገለጫዎች ለይቶ ማወቅ፣
በህፃናት ላይ የሚደርሱ አካላዊ እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት መገለጫዎችን ለይቶ ማወቅ     ድርጊቱን ለማወቅ በይበልጥ ይረዳል፡፡
12/  ለልጆች አስፈላጊ የሆኑ ስጦታዎችን አስቀድሞ ማዘጋጀት፣ ይህን ማድረግ ለልጆች ያለንን ፍቅርና እንክብካቤ ከመግለፅ አልፎ እነርሱን ለማሳደግ  ምን ያህ እግጁ እንደሆንን ያሳያል፡፡

በዳንኤል ቢሰጥ እቴቴ የተፃፉ ግጥሞች የተካተቱበት “አፈር ብላ” የተሰኘ የግጥም መድበል፤ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሽሙጦችና ፍልስፍና ነክ ግጥሞች እንዲሁም አገራዊ ፉከራና ሽለላ ቀመስ ግጥሞች የተካተቱበት መፅሃፉ፤ ፈገግና ዘና የሚያደርጉ ርእሰ ጉዳዮችንም ይዳስሳል፡፡
በ100 ገፆች ተቀንብቦ የተዘጋጀው “አፈር ብላ” የግጥም መድበል፤ በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መፅሃፉ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል (ፑሽኪን አዳራሽ) ይመረቃል ተብሏል፡፡

 በጉራጊኛ ዘፈኑና በማራኪ ውዝዋዜው የሚታወቀው የድምፃዊ መላኩ ቢረዳ “ዳነ” የተሰኘ አዲስ የጉራጊኛ ቪሲዲ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ የ14 ዘፈኖችን ቪዲዮ ያካተተው ይኸው ስራ፤ አብዛኞቹ ግጥሞችና ዜማዎች በራሱ በድምፃዊው የተሰሩ ሲሆን ቅንብሩ በዘሪሁን ሳህለማሪያም፣ ያሬድ አስናቀ፣ አሸናፊ ከበደና በሰለሞን ኢብራሂም ነው የተሰራው፡፡
ድምፃዊው በቪሲዲው ውስጥ “ትግርኛ ምት በጉራጊኛ”፣ “አውዳመት አማርኛ በጉራጊኛ ስልት”፣ “ጐንደር በጉራጊኛ”፣ “ሱዳንኛ በጉራጊኛ” እና “ትዝታ በጉራጊኛ” የሚሉትን በማካተት ለየት ባለ ሁኔታ የቀረበ ሲሆን ከዚህ ቀደም “ትዊስት በጉራጊኛ” የተሰኘ ቪሲዲ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ አዲሱ ቪሲዲ በዚያዳ ሪከርድስ ታትሞ እየተከፋፈለ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ድምፃዊ መላኩ ቢረዳ በአሁኑ ሰዓት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ ቤት አዳራሽ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በደራሲና አዘጋጅ ሙሉዓለም ጌታቸው ተሰናድቶ፣ በበርሄ ገ/መድህን ፕሮዱዩስ የተደረገው “ሚስቴን ቀሙኝ” የተሰኘ ኮሜዲ የፍቅር ፊልም፤ ነገ በመላ አገሪቱ በሚገኙ የግል ሲኒማ ቤቶች እንደሚመረቅ ፕሮዱዩሰሩ አቶ በርሄ ገ/መድህን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
በሜርሲ መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ለእይታ የሚቀርበውን ይሄን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ አመት እንደፈጀ የገለፁት ፕሮዱዩሰሩ፤ ከ600 ሺህ ብር በላይ እንደወጣበትና የ1ሰዓት ከ42 ደቂቃ ርዝማኔ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በፊልሙ ላይ ዮሐንስ ተፈራ (ዳረማኛ)፣ ቃልኪዳን ጥበቡ፣ ሰገን ይፍጠር፣ ካሳሁን ፍሰሃ (ማንዴላ)፣ አስራት ታደሰ፣ ፋንቱ ማንዶዬ፣ እንዳልካቸው ሰበታና ሌሎችም ወጣትና አንጋፋ ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡

Saturday, 11 October 2014 15:53

የፍቅር ጥግ

ሚስት ያላገባ ወንድ፣ አበባ አልባ የአበባ ማስቀመጫ እንደማለት ነው፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
የሚስትህን የልደት ቀን ለማስታወስ ትክክለኛው መንገድ አንድ ጊዜ መርሳት ነው፡፡
- ኤች.ቪ. ፕሮንችኖው
ፍቅር እውር ነው፤ ትዳር ግን የብርሃን ፀጋውን መልሶ ያጐናፅፈዋል፡፡
ሳሙኤል ሊችቴንበርግ
ትዳር፤ ከጠላትህ ጋር አንድ አልጋ የምትጋራበት ብቸኛው ጦርነት ነው፡፡
ፍራንሶይስ
ብዙ ቤተሰብ ባለበት ቤት ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ እውነት ለመናገር ሚስት እስካገባ ድረስ ብቻዬን ተኝቼ አላውቅም፡፡
ልዊስ ግሪዛርድ
ባል ማግባቴን እወደዋለሁ፡፡ በቀሪው ህይወታችሁ ልታበሽቁት የምትፈልጉት አንድ የራሳችሁ ሰው ማግኘት ድንቅ ነው፡፡
ሪታ ሩድነር
ትዳር እስከምይዝ በፍፁም በፍቺ አምኜ አላውቅም፡፡
ዲያኔ ፎርድ
ብቸኛ ለመሆን እርግጠኛው መንገድ ትዳር መያዝ ነው፡፡
ኖራ ኢፍሮን
ማንኛውም ያገባ ወንድ ስህተቶቹን መርሳት አለበት - ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ማስታወሳቸው ምንም ፋይዳ የለውም፡፡
ዱዌኔ ዴዌል
ትዳር ሌሊት ብቻቸውን መተኛት ለሚፈሩ ሰዎች ጥሩ ነው፡፡
ሴይንት ጄሮሜ
ከፍቅር የምንወደው ትኩሳቱን ነው፤ ትዳር ደግሞ አልጋ ላይ ያስተኛውና ይፈውሰዋል፡፡
ሚኞን ማክላውግሊን


Saturday, 11 October 2014 15:48

ማራኪ አንቀፅ

           በበረራ መማረክ የጀመርኩት ልጆች ሳለን አባቴ፣ እኔና እህቶቼን ወደ አየር ማረፊያ እየወሰደ አውሮፕላን ሲያርፍና ሲነሳ ያሳየን በነበረበት ወቅት ነው፡፡ አባቴ አውሮፕላኑን የሚያሳየን የአብራሪነት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብን አስቦ አይመስለኝም፡፡ በእኔ ልብ ውስጥ የአብራሪነት ፍላጎት ያደረገው ግን በዚያ ጊዜ ነበር፡፡ ግዙፎቹ አውሮፕላኖች ሰማዩን እየሰነጠቁ ሲከንፉ በደስታ ተጥለቅልቀን መመልከታችን፣ አባታችንን ሳይከነክነው እንደማይቀር አስባለሁ፡፡ አባታችን ሁላችንም እንደየፍላጎታችን እንድንጓዝ ከማበረታታት ችላ ያለበት ጊዜ ባይኖርም፤ ያ የየሳምንቱ የአየር ማረፊያው  ጉብኝታችን፣ እንዴት የበኩር ልጁ የእድሜ ልክ ሕይወትና ሙያ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡ የተወለድኩት በ1969 ዓ.ም ባህርዳር ከተማ ነበር፡፡ አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቼ፤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ደህና ገቢ የነበራቸውን ወላጆቼን በአርአያነት እየተመለከትኩ ነው ያደግሁት፡፡ አባትና እናቴ በራሴ እንድተማመንና ህልሜን ለማሳካት እንድጣጣር ያበረታቱኝ ነበር፡፡ “ሴት በመሆንሽ ገደብሽ እዚህ ድረስ ነው” ብለውኝ አያውቁም፡፡ ያደግሁበት ማህበረሰብም፣ ለዛሬው ማንነቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአካባቢያችን ሰው ሁሉ እንደራሱ ልጅ ነበር የሚያየኝ፡፡ የእለት ተዕለት እድገቴን ከመከታተልም ባሻገር በትምህርቴ በርትቼ እንድገፋ ያበረታቱኝ ነበር፡፡

አብራሪ የመሆን ፍላጎቴን ሁሉም ያውቁ ስለነበር የማያደንቀኝ አልነበረም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ፣ ሁለት ታንዛኒያውያን (አንድ ወንድና አንድ ሴት) የበረራ ሰልጣኞች እኛ ሰፈር ይኖሩ ነበር፡፡ እናም በዩኒፎርማቸው ተማርኬ ፈዝዤ እመለከታቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡
የሶስት ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ ቤተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በአሳይ የህዝብ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተልኩ፡፡ በ1987 ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቼ፣ ሥነ-ህንፃ (አርኪቴክቸር) መማር ጀመርኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የልጅነት ህልሜን አልዘነጋሁትም ነበር፡፡ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ወስጄ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተፈታኞች በመጀመርያ ሙከራቸው ይወድቁ ነበር፡፡ እኔም ሳላልፍ ቀረሁ፡፡ በእርግጥ በመግቢያ ፈተናው መውደቄ ተስፋ አለመቁረጥንና የበለጠ መጣርን አስተምሮኛል፡፡ የሥነ - ህንፃ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ የመግቢያ ፈተናውን በድጋሚ ወሰድኩና አለፍኩ፡፡ ክፋቱ ግን አስቸጋሪ ሰዓት ላይ ሆነብኝ፡፡ የበረራ ሥልጠናው በሚጀመርበት በመጋቢት ወር 1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነበር፡፡ እናም ለዓመታት የለፋሁበትን ትምህርት ገደል እንደመክተት ሆነብኝ፡፡ የማታ ማታ ግን በሐምሌ 1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ሥልጠናውን እንድጀምር ተፈቀደልኝ፡፡
ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደውን ሥልጠና አጠናቅቄ በአብራሪነት የተመረቅሁት በህዳር 1994 ዓ.ም ሲሆን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ተኩል በዘለቀው የሥራ ዘመኔም በረዳት አብራሪነት ለ4ሺ475 ሰዓታት አብርሬያለሁ፡፡ ከዚም ከተለያዩ ፈተናዎች፣ ምዘናዎችና ግምገማዎች በኋላ፣ እድገት ተሰጥቶኝ በዋና አብራሪነት (የካፒቴን) ሥልጠና ጀመርኩኝ፡፡ አስፈላጊውን የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና እንዳጠናቀቅሁም ከመጀመሪያ በረራዬ ከሰባት ዓመት ተኩል በኋላ በ2002 ዓ.ም ካፒቴን ሆንኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ከአንድ ሺ በላይ ሰዓታት አብርሬአለሁ፡፡ ..................
(“ተምሳሌት፡ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” ከተሰኘው አዲስ መፅሃፍ ላይ የተቀነጨበ፤ 2007 ዓ.ም)

                 የሙዚቃና የፊልም ባለሙያዎችን አወዳድሮ የሚሸልመው የ”ለዛ” ፕሮግራም መቼና እንዴት ተጀመረ?
ፕሮግራሙ ከተጀመረ አራት አመት ሆኖታል፡፡ የ“ለዛ” ፕሮግራም በተለይ የሀሙስ የምሳ ሰዓት ዝግጅት በኢትዮጵያ ስራዎች ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ደረጃቸውን የጠበቁ የኢትዮጵያ ሙዚዎችን እየመረጥን እናስተላልፋለን፡፡ የዛሬ አራት አመት ሁሉ ነገር ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ የወጡት አልበሞች ትንሽ ነበሩ፡፡ እኛም ፕሮግራማችን ላይ የምንሰማው አዲስ ስራ አጣን፡፡ አርቲስቶቹ ከስራቸው የሚያገኙት ገቢ ባያስደስታቸውም፣ የኮፒራይት ጉዳይ ፈር ባይዝም፣ የሰሩትን ስራ አድማጩ “ጥሩ ነው” ብሎ ሲመርጠው ይበረታቱ ይሆናል በሚል ነው ሽልማቱ የተጀመረው፡፡ ሰርፀ ፍሬስብሐትና ያሬድ ሹመቴ፤ በብሄራዊ ቴያትር ከሚያዘጋጁት ፕሮግራም ጋር ለምን አይደረግም ብለው ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት የመጀመርያው የሽልማት ፕሮግራም እዚያው ተደረገ፡፡ ሁለተኛውን በእምቢልታ ሲኒማ፣ ሶስተኛውን በጃዝ አምባና አራተኛውን የዛሬ ሳምንት በጣሊያን የባህል ተቋም አድርገናል፡፡
ፕሮግራሙ አላማውን አሳክቷል ትላለህ?
አዎ! የሰው ተሳትፎ በጣም ጨምሯል፤ ከመጀመሪያው በስተቀር የሌሎቹ ምርጫው የተከናወነው በኢንተርኔት ነው፡፡ በየእለቱ መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ዘንድሮ በያሁ ዶት ኮምና በሸገር ዌብሳይት ላይ ነው ድምፅ የተሰጠው፡፡ በሸገር ዌብሳይት ላይ ብቻ የተሰጠው ድምፅ ከ60ሺ በላይ ነው፡፡ ማን ከየት ሀገር ማንን እንደመረጠ ማየት ይቻላል፡፡
ተወዳዳሪዎችም ምን ያህል ድምፅ እንዳገኙ ያዩታል፡፡ በዚህ በአራተኛው ዙር ከበፊቶቹ ዙሮች በተለየ ከህዝብ ድምፅ በተጨማሪ የባለሙያዎች ግምገማም እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ስራዎች ህዝብ ስለወደዳቸው ብቻ ሳይሆን ኪነ-ጥበባዊ ፋይዳቸውም እንዲታይ በማለት ለህዝብ ድምፅ 60 በመቶ፣ ለባለሙያ ድምፅ 40 በመቶ ተደርጓል፡፡
የፐርሰንት ስሌቱ እንዴት ተሰራ?
ፕሮግራሙ ሲጀመር የአድማጮች ምርጫ ስለተባለ፣ አብላጫውን ለህዝብ ለመስጠት ሲባል 60 በመቶ ለህዝብ ድምፅ ሲሆን 40 በመቶው ለባለሙያ ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ትልቁ ክርክር ምን መሰለሽ? ህዝቡን መምራት ያለበትና ኪነ-ጥበባዊ ስራዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የመገምገም የመሪነቱን ሚና መጫወት ያለበት ባለሙያው ነው የሚል ነው፡፡
መስፈርቱ ምን ነበር?
 መስፈርቱ ግልፅ ነው፡፡ የሙዚቃ ስራዎችን ለመገምገም የሚችሉ ከበቂ በላይ ሙያተኞች አሉን፡፡ የፊልም ጥበብ ስራ ላይ ግን ገና ይቀረናል፡፡ ስራዎችን የሚገመግሙ በቂ ሙያተኞች የሉም፡፡ እንግዲህ በአገር ዳኛ ነው የሚዳኘው፡፡
በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ምንድን ናቸው?
ፕሮግራሙን ተረድቶት ላለፉት ዓመታት በብቸኝነት የረዳን “አኳ አዲስ” ነው፡፡ በጣም የሚገርመኝ የቢራ ፋብሪካዎች አልበም ስፖንሰር ያደርጋሉ፡፡ ስፖንሰር ያደረጓቸው አልበሞች በዚህ ውድድር ሲሳተፉ እያዩ፣ ይህን የውድድር መንፈስ ለማገዝ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ሌላው ችግር ፕሮግራሙ የሚዘጋጅበት ቦታ ማግኘት ነው፡፡ ብቸኛው ጥሩ አዳራሽ ብሔራዊ ትያትር ነው፤ ነገር ግን ነፃ የሚሆነው ሰኞ ብቻ ነው፡፡
የጣልያን የባህል ተቋም አዳራሽ ሰፊ ነው፤ ግራንድ ፒያኖና ብዙ ሰው የሚያስተናግድ ግቢ አለው፡፡ ይህንን የሚያሟላ ቦታ ለማግኘት ብዙ ምርጫ የለንም፡፡ መድረኩን እንደ አዲስ ነው የሰራነው፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ ገቢ አለው?
የለውም፤ እንዲያውም ከኪስ ያስወጣል፡፡ ፖስተሮችና በራሪ ወረቀቶች ላይ የሚታዩ ስፖንሰሮች ገንዘብ ሳይሆን የሚሰጡት ወጪዎችን ነው የሚችሉት፡፡ አንዱ የአዳራሽ ኪራይ ሲችል ሌላው የጥሪ ካርድ፣ ሌላው ውሃ፣ ሌላኛው ምግብ ያቀርባል፡፡ በዚያ መልክ ነው የዝግጅቱ ወጪ የሚሸፈነው፡፡
በአሸናፊዎቹ ምርጫ ላይ ቅሬታ ቀርቦ ያውቃል?
በፍፁም! ተወዳዳሪ ሁሉ በእርግጥ ማሸነፍ ይፈልጋል፤ ነገር ግን የድምፅ አሰጣጡ ሂደት መቶ በመቶ ግልፅ ነው፡፡ የተገኘው ድምፅ በግልፅ ይቀመጣል፡፡ እንዲያውም “አንተ አሪፍ ነው ያልከው ስራ አሸንፏል ወይ” ብትይኝ መልሴ አይደለም ነው፤ እኔ ጥሩ ያልኳቸው ያልተሸለሙ አሉ፤ ጥሩ አይደሉም ያልኳቸው የተሸለሙ አሉ፡፡
የውድድር ዘርፎቹ እንዴት ናቸው?
በአመት ውስጥ ምን ያህል የባህል ዘፈን ይወጣል? ምን ያህል ስራዎች በሙዚቃ ስልት ለመመደብ የተመቹ ናቸው ስትይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ አልበም ውስጥ የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶች አሉ፤ ስለዚህ ለምደባ አስቸጋሪ የሚሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ዜማና ግጥም የሚል ምድብ ለመጨመር እየታሰበ ነው፤ ዘንድሮ “ምርጥ የቪዲዮ ክሊፕ”፣ “አዲስ ድምፃዊ” እና “የህይወት ዘመን ተሸላሚ” የሚሉ ምድቦች ተካትተዋል፡፡
 በፊልም “ምርጥ ሳውንድ ትራክ” የሚል ምድብ ለመጨመር ታስቦ ምን ያህል ናቸው ኦርጂናል ሳውንድ ትራክ የሚጠቀሙት የሚለው ተገምግሞ ውድቅ ሆኗል፡፡  

ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
የእኔ ፍላጎት ኤፍቢአይ መሆን ነው፡፡ አንድ ቀን የፕሬዚዳንቱ ጠባቂ ሆኜ እመረጥ ይሆናል፡፡ ገና ልጅ ስለሆንኩ ግን ትንሽ ይቆያል፡፡
አርተር - የ11 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
የመጨረሻ ደብዳቤዬ ደርሶህ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በዚያ ደብዳቤ ላይ ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ጨረቃ የምጓዝ የመጀመሪያው ሰው መሆን እንደምፈልግ ፅፌልሃለሁ፡፡ ያን ጊዜ አንተ ፕሬዚዳንት ላትሆን ትችላለህ፤ ነገር ግን ወንድምህ ቦብ ኬኔዲ የሚሆን ከሆነ፣ ይሄን ደብዳቤ ለሱ ስጥልኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ስንታሊ - የ11 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
ባለቤትህ በጣም ቆንጆና በጣም ጥሩ ሴት ትመስለኛለች፡፡ በጣም ቀልደኛም ሳትሆን አትቀርም፡፡ ሁለታችሁንም እወዳችኋለሁ፡፡
ናንሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የገንዘብ ሚኒስትር እያሉህ፣ የህፃናት ሚኒስትር የሌለህ ለምንድነው? ህፃናትም እኮ ድምፅ መስጠት ይችላሉ፡፡ እነሱም መብት አላቸው፡፡
ቼሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡ በጣም ጎበዝ ነኝ፡፡ በትምህርቴም ጥሩ ውጤት ነው የማመጣው፡፡ እናቴ በጣም ንፁህና ጠንቃቃ እንደሆንኩ ትነግረኛለች፡፡ ስለዚህ ዋይት ሃውስን አላዝረከርክም፡፡
አቢጌል - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
አጎቴ ማርዮ ፀጉር አስተካካይ ነው፡፡ ዋይት ሃውስ መጥቶ ያንተን ፀጉር ማስተካከል ይፈልጋል፡፡ 50 ሳንቲም ብቻ ነው የሚያስከፍልህ፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ስለሆንክ አንተን ማስተካከል ብዙ ደንበኞች እንደሚያመጣለት ነግሮኛል፡፡
አልበርት - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
እኔ ገና መፃፍ ስለማችል ይሄን ደብዳቤ የፃፈችልኝ እናቴ ናት፡፡ አንድ ቀን ግን መፃፍ እችላለሁ፡፡ ያኔ ድምፅ መስጠት ስለምችል ድምፄን የምሰጠው ለአንተ ነው፡፡ ለደብዳቤዬ መልስ እንድትፅፍልኝ… እሺ፡፡ መፃፍ ባልችልም ማንበብ እችላለሁ፡፡
ሲድኒ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
ዋይት ሃውስ ውስጥ ሃላፊው ማነው? አንተ ነህ ወይስ ቀዳማዊት እመቤት? የእኛ ቤት ሃላፊ እናቴ ናት፡፡
ካርል - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
አባቴ ግብር ሲከፍል ነው እንጂ ሌላ ጊዜ በጣም ነው የሚወድህ፡፡
ብሩክ - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የሴት ጓደኛዬ አሊሳ ሪፐብሊካን ስትሆን እኔ ዲሞክራት ነኝ፡፡ አንድ ቀን መጋባታችን አይቀርም፡፡ ዲሞክራት ሪፐብሊካንን ማግባትና ደስተኛ መሆን ይችላል? እኔ 12 ዓመቴ ሲሆን ጓደኛዬ 11 ዓመቷ ነው፡፡ 18 ዓመት ሳይሞላን በፊት መልስህን እንፈልጋለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ሪያን - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የአብርሃም ሊንከንን ንግግሮች ማንበብ ያለብህ ይመስለኛል፡፡ ያን ጊዜ ሰዎች ያንተን ንግግር እየሰሙ ማንቀላፋት ይተዋሉ፡፡
ጂሚ - የ10 ዓመት ህጻን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
ከሚስትህ ጋር ከተጋባህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? አንተና ቀዳማዊት እመቤት ተጣልታችሁ ታውቃላችሁ? እናትና አባቴ ከተጋቡ 20 ዓመት ሲሆናቸው ሲተኙ ካልሆነ በቀር ሁልጊዜ እንደተጣሉ ነው፡፡
ካያ - የ13 ዓመት ህፃን

           የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሰባት አመታት በፊት በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በአገሪቱ ከተቀሰቀሰውና ከ1ሺህ 200 በላይ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት፣ 600 ሺህ ያህሉን ደግሞ ለመፈናቀል ከዳረገው የእርስ በርስ ግጭት ጋር በተያያዘ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት የተመሰረተባቸውን ክስ ባለፈው ረቡዕ በፍ/ቤቱ ቀርበው አደመጡ፡፡
በስልጣን ላይ እያሉ በአለማቀፉ ፍርድ ቤት የቀረበባቸውን ክስ ለማድመጥ በፈቃደኝነት የተገኙ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት የሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ዘ ሄግ በሚገኘው ፍ/ቤት በተዘጋጀው የቅድመ ፍርድ ሂደት ውይይት ላይ ተገኝተው የተመሰረቱባቸውን አምስት የወንጀል ክሶች ያደመጡ ሲሆን፣ ወንጀሎቹን አለመፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“የተመሰረቱብኝ ክሶች ከፖለቲካዊ ጥቅም ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ክሶቹ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል” ብለዋል ምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን በቦታቸው ወክለው፣ ክሱን ለማድመጥ ወደ ፍርድ ቤቱ የሄዱት ኬንያታ በሰጡት ምላሽ፡፡
በ2007 የኬንያ የምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በአገሪቱ በተከሰተው ግጭት ውስጥ እጃቸው አለበት፣ ሰብዓዊ መብቶችን በሚጥሱ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል በሚል በቀረቡባቸው አምስት ክሶች፣ የሚሊሺያ ወታደሮችን በገንዘብ በመደገፍ ለጥቃት አነሳስተዋል፤ ጉዳያቸው በመደበኛ ፍርድ ሂደት ይታይ አይታይ የሚለው  ሐሙስ የሚወሰን ይሆናል፡፡በዕለቱ አቃቤ ህግ፤ የኬንያ መንግስት በፕሬዚዳንቱ ላይ ከተመሰረተው ክስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁልፍ ማስረጃዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም በሚል ቢወነጅልም፣ ኬንያዊው ጠበቃ ጊቱ ሙጋይ ግን  ውንጀላውን አልተቀበሉትም፡፡ ፍርድ ቤቱ በቂ ማስረጃ ካላገኘ፣ ክሶቹ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ወንጀሎቹ  በፕሬዚዳንቱ መፈጸማቸውን የሚያረጋግጡ የስልክ ማስረጃዎችና ዘጠኝ ምስክሮች እንዳሉት አስታውቋል፡፡ፍርድ ቤቱ በኡሁሩ ኬንያታ ላይ የተመሰረተውን ክስ ውድቅ ማድረጉን አልያም የፍርድ ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት ሰሞኑን ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአፍሪካ በስልጣን ላይ እያሉ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ሌላው መሪ፣ የሱዳኑ ኦማር አልበሽር እንደሆኑ ያስታወሰው ዘገባው፤ በዳርፉር በተከሰቱ የጦርነት ወንጀሎች ተከስሰው  ፍርድ ቤቱ ያወጣባቸውን የእስር ትዕዛዝ አልቀበልም ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡በፍርድ ቤቱ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ባለፈው ሃሙስ ወደ አገራቸው የተመለሱት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ናይሮቢ በሚገኘው አየር ማረፊያ ሲደርሱ በባህላዊ ጭፈራና የወታደራዊ ማርሽ የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ከአየር ማረፊያ እስከተማዋ ማዕከላዊ አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውም ለፕሬዚዳንታቸው ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡
“አንድ ነን!... ኬንያ የተረጋጋች አገር ስለሆነች ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም!” ብለዋል ኬንያታ ለህዝቡ ባሰሙት አጭር ንግግር፡፡