Administrator

Administrator

          በአሁን ወቅት ወደ 300 የሚሆኑ የአውሮፓ ኩባንዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ሲሆን የአውሮፓ ኩባንያዎችን ይበልይ ወደ ሃገር ውስጥ ለመሳብ ጥረት እተደረገ ነው ተብሏል፡፡ “የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ማነቃት በሚል መርህ በአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ልኡክ እና በህብረቱ የቢዝነስ ዶርም አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በትናንትናው እለት ኢግዚብሽንና ኮንፈረንስ የተካሄደ ሲሆን በሃገሪቱ ተፈትሸዋል፡፡
የኮንፍረንሱ ዋነኛ አላማ አውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ የቢዝነስ ባለድርሻ አካላት በኢትዮጵያ ስላለው የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት አማራጭ እና ለችግሮቹ መፍትሄ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የነበረ ሲሆን በእለቱም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡ በኮንፈረንሱ ላይም በሃገሪቱ ለአውሮፓ ባለሃብቶች ተግዳሮት ናቸው በተባሉት ታክስ፣ ንግድ ፍቃድ፣ ግብር እና የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል በእለቱ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በምታደርገው ጥረት ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከንግድ ፍቃድ ጋር ተያይዞ ይውጭ ባለሃብቶች የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ወላጆች የጥርሳቸውን ጤንነት ሊከታተሉላቸው ይገባል

የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና ተመራማሪዎች፤ 54ሺ ገደማ የሚሆኑ ህፃናትን ጥርሶች ከመረመሩ በኋላ 12 በመቶ በሚሆኑት ህፃናት ላይ የጥርስ መበስበስ ምልክቶችን እንዳገኙ ይፋ አደረጉ፡፡ ህፃናቱ በአማካይ ሶስት ጥርሶቻቸው አንድም በስብሰዋል አሊያም ወልቀዋል ወይም ደግሞ ተሞልተዋል ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡ ከቦታ ቦታ የጥናት ውጤቱ ከፍተኛ ልዩነት ያሳየ ሲሆን በሌችስተር አካባቢ 34 በመቶ ያህሉ ህፃናት የጥርስ መበስበስ ሲስተዋልባቸው በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ 2 በመቶ ያህሉ ብቻ የችግሩ ተጠቂዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
አንዳንድ ህፃናት ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚከሰት የተለየ ዓይነት የጥርስ መበስበስ እንደተገኘባቸው ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ይሄ ችግር የሚያጠቃው የላይኛውን የፊት ጥርሶች ሲሆን በፍጥነትም ወደ ሌሎች ጥርሶች የሚሰራጭ እንደሆነ ታውቋል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የጥርስ መበስበስ ችግር በጡጦ ወይም በኩባያ ጣፋጭ አሊያም ስኳር የበዛባቸው ፈሳሾችን በመውሰድ የሚከሰት ነው ተብሏል፡፡
የእንግሊዝ የማህበረሰብ ጤና ተመራማሪዎች፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ጣፋጭ ምግቦችንና መጠጦችን አልፎ አልፎና በጣም በትንሹ መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የእናት ጡት ያቆሙ ህፃናት በሚወስዷቸው ምግቦችና መጠጦች ላይም ስኳር እንዳይጨምሩ ለወላጆች ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ወላጆችና ሞግዚቶች፤ ህፃናቱ የመጀመሪያ ጥርሳቸውን እንዳበቀሉ መቦረሽ መጀመር አለባቸው የሚሉት የህክምና ባለሙያዎች፤ ልጆቹ ሰባት ወይም ስምንት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስም የጥርስ ንፅህና አጠባበቃቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በእድሜያቸው የገፉ ሰዎችን የማሽተት ችሎታ በመለካት፣ በቀጣይ በህይወት የሚቆዩበትን ጊዜ ለመተንበይ እንደሚቻል በአሜሪካ የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተሰራ ጥናት ማረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተመራማሪዎች ከ57 እስከ 85 አመት እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 3ሺህ ሰዎች ላይ ያደረጉትን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ጥሩ የማሽተት ችሎታ ያላቸው ሰዎች፣ የማሽተት ችሎታቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ቀጣዮቹን 5 አመታት በህይወት የመቆየት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
ጥናቱ በተከናወነባቸው ሰዎች ላይ የተመዘገበው ውጤት እንደሚያሳየው፣ ዝቅተኛ የማሽተት ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ሲሞቱ፤ ጥሩ የማሽተት ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የሞቱት 10 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡
ተመራማሪዎቹ ለግለሰቦቹ የአሳ፣ የብርቱካን፣ የጽጌረዳ አበባ፣ የቆዳና የናና መዓዛዎችን በእስክርቢቶ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲያሸቱና የምን መዓዛ እንደሆነ እንዲለዩ በመጠየቅ የማሽተት ችሎታቸውን መዝግበዋል፡፡ ከአምስት አመታት በኋላም፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው ሰዎች፣ ምን ያህሉ በህይወት እንዳሉና ምን ያህሉ እንደሞቱ አረጋግጠዋል፡፡ በመቀጠልም የሞት መጠኑን ከማሽተት ችሎታ ጋር በማጣመር፣ በሁለቱ ነገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥናት ሞክረዋል፡፡
የማሽተት ችሎታ እየቀነሰ መምጣት በቀጥታ ለሞት እንደማይዳርግ የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ ይሄም ሆኖ ግን ክስተቱ እንደማስጠንቀቂያ ሊወሰድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
“የማሽተት አቅም መቀነስ በቀጥታ ለሞት አይዳርግም፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በግለሰቡ ጤንነት ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚያመላክት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ በምርምሩ ያገኘናቸው ውጤቶች በጤና ምርመራ ላይ እገዛ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ለአደጋ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ የሆኑ በሽተኞችን ለይቶ ለማወቅ የሚያግዝ ፈጣንና ወጪ የማይጠይቅ የምርመራ ዘዴ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል” ብለዋል የተመራማሪ ቡድኑ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃያንት ፒንቶ፡፡
በህይወት የመቆየት ዕድልን የሚወስኑ እርጅና፣ የምግብ አወሳሰድ፣ የሲጋራ ሱሰኝነት፣ ድህነትና አጠቃላይ የጤና ሁኔታን የመሳሰሉ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ የማሽተት ችሎታቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ለሞት የመዳረግ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን የማሽተት ችሎታ መቀነስ፣ በምን መንገድ በህይወት ላለመቆየት እድል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በግልጽ ባይታወቅም፣ ተመራማሪዎቹ በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የራሳቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
አነስተኛ የማሽተት ችሎታ መኖር፣ በግለሰቦች ሰውነት ውስጥ የሚገኙ ያረጁ ህዋሶች የሚታደሱበት መጠን አነስተኛ መሆኑን ሊያመላክት ይችላል ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡ ጤናማ የማሽተት ችሎታ እንዲኖር ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል፣ በአፍንጫ ውስጥ የሚገኙ ህዋሳት በየጊዜው መታደሳቸው ይጠቀሳል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሰዎች ዝቅተኛ የማሽተት ችሎታ ስላላቸው መጨነቅ እንደሌለባቸው የመከሩት ፕሮፌሰር ፒንቶ፤ ጉዳዩ ከጉንፋን፣ ከአለርጂክና ሳይነስን ከመሳሰሉ የጤና ችግሮች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ የማሽተት ችግሩ እየተባባሰ ከመጣ ግን፣ ሃኪማቸውን ማማከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑትና በጥናቱ ውስጥ ያልተሳተፉት ፕሮፌሰር ቲም ጃኮብ በበኩላቸው፤ በጥሩ ሁኔታ የተከናወነው ይህ ጥናት፣ የማሽተት ስሜትና ጤንነት በእጅጉ እንደሚቆራኙ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በሰውነት አጠቃላይ ሁኔታና በስነ-ልቦና መካከል ትስስር እንዳለ የጠቆሙት ጃኮብ፤ ለአብነትም ማሽተት አለመቻል ድብርት እንደሚፈጥር፣ ድብርትም በመስማት ችሎታ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

             በዓለም ላይ ከሚገኙ አገራት የትኞቹ ዕድሜያቸው ለገፉ አዛውንቶች ህይወት ምቹ እንደሆኑ ለማወቅ በ96 አገራት ላይ በተካሄደ ጥናት፣ ኖርዌይ ለአዛውንቶች ጤናማ ህይወት ቁጥር 1 ተመራጭ አገር ስትሆን አፍጋኒስታን በመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ግሎባል ኤጅዎች ኢንዴክስ፤ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የሆናቸው አዛውንቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት (ዋስትና) በመለካት ነው የአገራቱን ደረጃ ያወጣው፡፡ በተባበሩት መንግስታት የአዛውንቶች ቀን መፅሄት ላይ በወጣው መረጃ መሰረት፤ አውስትራሊያ፣ ምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ እድሜያቸው ለገፉ ዜጎች እጅግ ምቹ አገራት መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን አፍጋኒስታን ግን ለአዛውንቶች ህይወት የማትመች መሆኗ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

እ.ኤ.አ በ2050 ከዓለም ህዝብ ውስጥ 21 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች እንደሚሆኑ ሪፖርቱ ተንብይዋል፡፡ የኑሮ ምቹነትን የሚጠቁመው ኢንዴክስ፤ አራት ዘርፎችን የሚመዝን ሲሆን እነሱም የገቢ ዋስትና፣ ጤና፣ ግለሰባዊ አቅምና ሰውየው ሴትየዋ የሚኖሩት በ“ምቹ አካባቢ” ነው አይደለም የሚሉት ናቸው፡፡ ለአዛውንቶች ምቹ የመኖርያ ሥፍራ በመሆን በቀዳሚነት ከተጠቀሰችው ኖርዌይ ቀጥሎ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ካናዳና ጀርመን ይከተላሉ፡፡ በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት አገራት በ40 ያህሉ በ2050 ዓ.ም 30 በመቶ የሚሆነው ህዝብ 60 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያለው እንደሚሆን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ የተባበሩት መንግስታት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2030 ዓ.ም በዓለም ላይ ዕድሜው 60 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነው ህዝብ ቁጥር 1.4 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡

የኮበለሉ ጋዜጠኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበናል
ሥልጠናው ከምርጫ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም
የአቅም ግንባታ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ማስረጫ አይደለም

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተሰጠ ባለው ስልጠናና በአምስት የግል መጽሄቶችና በአንድ ጋዜጣ ላይ የተመሰረተውን ክስ ተከትሎ ከአገር በወጡት በርካታ ጋዜጠኞች ዙሪያ የአዲስ አድማስ  ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እውነቱ ብላታን  ሰሞኑን በፅ/ቤታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተዘጋጀው ስልጠና ዓላማ ምንድን ነው?
የስልጠናው ዋና ዓላማ፣ አንደኛ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በተቀላጠፈ መልኩ ማስቀጠል ነው፡፡ ሁለተኛ ሃገሪቱ በምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ዙሪያ እስካሁን የደረስንበት፣ እንዲሁም ከፊታችን የሚጠብቁን ተግዳሮቶችና ስራዎች ምን እንደሆኑ የጠራ ግንዛቤ ማስያዝ ነው፡፡ ሀገሪቱ ባለፉት 23 ዓመታት የተጓዘችባቸውን መንገዶች በተለይ ወጣቱ ትውልድ በደንብ እንዲያውቀውና የበኩሉን ሃገራዊ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጭምር ከየት ተነሳን ወዴት እየሄድን ነው የሚለውን ለማስጨበጥ ነው፡፡ ሌላው ሃገሪቱ እየተከተለች ባለችው ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ያሉ ክፍተቶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይቀረፋሉ? የመልካም አስተዳደር ትግላችን ምን ያህል ተጉዟል? ምንስ ይቀረዋል? በዚህ የመልካም አስተዳደር ጉዞ ውስጥ ከወጣቱና ከከተማው ህዝብ ምን ይጠበቃል? በአጠቃላይ ሃገሪቱ ለተያያዘቻቸው የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወጣቱ ሚናውን መጫወት በሚችል መልኩ ግንዛቤ ለመስጠት ተፈልጎ ነው ስልጠናው እየተሰጠ ያለው፡፡ ይሄ ስልጠና ዘንድሮ የተጀመረ አይደለም፤ በየጊዜው በየትምህርት ተቋማቱ ሲሰጥ የቆየ ነው፡፡ የዚያው ቀጣይ ፕሮግራም ነው፡፡
ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ለመንግስት ሰራተኞችም የሚሰጥ ነው፡፡ በህዝባዊ አደረጃጀቶች ውይይቶች እየተካሄዱ፣መንግስት በ5 ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ላይ የደረሰባቸው የእድገት ደረጃዎች የነበሩት ውጤታማ ተሞክሮዎች ምን ነበሩ? ከዚህ ምን ተምረን ለቀጣዩ እቅድ እንዴት እንሰራለን? የሚለውንና በአጠቃላይ ትልልቅ በሆኑ አገራዊ አጀንዳዎችና በህዳሴው ጉዞ ላይ  የሰፊውን ህዝብ  ተሣትፎ ለማጠናከር ታስቦ እየተካሄደ ያለ ስልጠና ነው፡፡ አሁን በዩኒቨርስቲዎች ለነባር ተማሪዎች ሁለተኛ ዙር ስልጠና እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ማለት ይህቺን አገር የሚረከበው ወጣቱ ሃይል የሚገኝበት ነው፡፡ ይሄ በእውቀት የተካነው ወጣቱ ሃይል፣ ነገ ወደ ስራ ሲሰማራ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችል ዘንድ በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተፈልጐ ነው ስልጠናው  የሚካሄደው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ያለው የተማረ ሃይል ስለብዝሃነት፣ ስለመቻቻል፣ ስለመከባበር የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው ጭምር ነው ስልጠናው እየተሰጠ ያለው፡፡
ስልጠናው በተማሪዎቹ ፍቃደኝነት ሳይሆን በግዴታ ነው የሚካሄደው የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡  እውነት በግዴታ ነው ?
ስልጠናው ግዴታ አይደለም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወዶና ፈቅዶ የሚሳተፍበትና ግንዛቤ የሚያገኝበት ነው፡፡ ተማሪው በአጠቃላይ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ የሚወያይበት ስለሆነ በግዴታ ላይ የተመሠረተ ነው የሚያስብለው ነገር የለም፡፡ ስልጠናው በፍፁም በግዴታ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡
ተማሪዎች በስልጠናው ተሳትፈው ሠርተፊኬት ካልተሰጣቸው ለትምህርት መመዝገብ እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል ይባላል፡፡ ይሄ ውሸት ነው ማለት ነው?
የአንድ ወይም የሁለት ሣምንት የተለመዱ ስልጠናዎች ይሠጣሉ፡፡ ማንኛውም ስልጠና ሲካሄድ ለማንኛውም ሠልጣኝ ሠርተፊኬት ይሰጣል፡፡ ስልጠናው ምን ያህል ገብቶታል ወይም የተሳትፎ ብቃቱ ምን ያህል ነው የሚለውን ለመመዘን አይደለም፡፡ እንኳንስ ለ15 ቀን በተከታታይ ሰፊ ስልጠና ተሰጥቶ ይቅርና ለሁለትና ሦስት ቀናት ስልጠናም ሠርተፊኬት ይሰጣል፡፡ ተማሪዎችም በትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ነው የተወያዩት፤ በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው መቻቻል፣ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአትን ተከትሎ መስራት ምን አንድምታ እንዳለው የሚዳስስ ሥልጠና ነው የወሰዱት፡፡ ትላልቅ አገራዊ አጀንዳ ላይ ለሠለጠነ አካል ሠርተፊኬት መስጠት አግባብ ነው፡፡ ሠርተፊኬቱ መሳተፉን ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ሠርተፊኬት መሰጠቱን እንደ ግዴታ ማሳያ ማድረግ ስህተት ነው፡፡ ማንም ተገዶ እንዲሰለጥን አይደረግም፡፡
የስልጠናው ውጤታማነትስ ምን ያህል ነው?
እኔም አሰልጣኝ ሆኜ ተሳትፌያለሁ፡፡ እንደውም አሁን ከመቱ መመለሴ ነው (ቃለምለልሱ የተደረገው ሃሙስ ከሰአት ነው) መጀመሪያ ላይ የተለያዩ ብዥታዎችን በማሠራጨት ስልጠናውን ለማደናቀፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ የተነሣ ተማሪውም ዘንድ በግንዛቤ ማጣት ከውጭ በሚነዙ አሉባልታዎች የመነዳት ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ችግሮች የመጀመሪያዎቹ ቀናት አካባቢ ድረስ ብቻ ነው የዘለቁት፡፡ የስልጠናውን ጠቃሚነትና አስፈላጊነት ከተረዳና ጥቅሙ ለራሱ፣ ለማህበረሰቡና ትምህርት ቤት ለላኩት ወላጆቹ መሆኑን ከተገነዘበ በኋላ ግን ስልጠናውን በፍላጎትና በተነቃቃ ስሜት ነው የተሳተፈው፡፡
 ከአንዳንድ ወገኖች ስልጠናውን የማደናቀፍ ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ስልጠናው የገቡት እንኳ መጨረሻ ላይ ራሳቸውን አጋልጠው “ይሄ የኔ ሃሳብ አይደለም፣ ይሄን ስልጠና ማዘግየታችሁ እኛን ለብዥታ እንድንጋለጥ አድርጐናል” ብለዋል፡፡ በስልጠናው ላይ መልካም መልካም ነገሮች  ብቻ አይደለም የቀረቡት፤የአገሪቱ ተግዳሮቶችና ማነቆዋች በሙሉ ተነስተዋል፡፡ በአፈፃፀም ሂደት የነበሩ ጉድለቶች፣ የስርአቱም ሆነ የዚህች አገር አደጋዎችና የአደጋ ስጋቶች ምን ምን እንደሆኑ ጎልተው ወጥተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ሁሉም ነገር ሳይደበቅ ግልጽ በሆነ አካሄድ ነው ስልጠናው የተሰጠው፡፡ እንደውም ወደ መጨረሻ ላይ ተማሪዎቹ በፍቅር እየወደዱት መጥተዋል፡፡
 እናም ውጤታማና በድል የተጠናቀቀ ስልጠና ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሠልጣኝም አስተባባሪም ስለነበርኩ በዚህ ረገድ ያየሁትን በሚገባ መመስከር እችላለሁ፡፡ ሌሎች አካባቢ ስለተደረጉት ስልጠናዎች አንደኛው ዙር ከተፈፀመ በኋላ ግምገማ ተካሂዷል፡፡ አፈፃፀማችን እንዴት ነበር? በቀጣይ የነበሩትን ጉድለቶች እንዴት እናስተካክል? የሚል አጠቃላይ ግምገማ ስለተካሄደ ውጤታማና ከጠበቅነው በላይ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ከተማሪዎቹም ዘንድ ሥልጠናው በአመት አንድ ጊዜ ቢካሄድ-- የሚል ሃሳብ ሲቀርብ ስለነበር እጅግ ውጤታማ የሆነ ስልጠና ነው፡፡
ኢህአዴግ የመንግስት ሃብትና ገንዘብን ለራሱ ርእዮተ ዓለም ማስፈፀሚያ እያዋለ ነው የሚል ትችት ይሰነዘራል፡፡ በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ መንግስት ይሄን ስልጠና የማከናወን ሙሉ መብትና ነፃነት አለው፡፡ አሁን ፓርቲውን በዚህ ለመክሰስ ተፈልጐ ከሆነ፣ ፓርቲው በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ላይ እስከሆነ ድረስ በመንግስት የሚሠራው አሸናፊው ፓርቲ የቀረፃቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የፓርቲው ፖሊሲዎች ከምርጫ በኋላ ወደ ስልጣን ሲመጣ፣ አገራዊ ፖሊሲ ሆነዋል፡፡ አገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂውን ደግሞ መንግስት በመላ አገሪቱ የማስፈፀም ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ አስታኮ ገዥውን ፓርቲ ለመክሰስ የሚደረገው ጥረት ውሃ አይቋጥርም፤ምክንያቱም የአገሪቱን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያስፈጽመው ፓርቲው ነው፡፡
 አሁን የተሰጠውና እየተሰጠ ያለው ስልጠና በመንግስት እንጂ በፓርቲው አይደለም፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱን የአቅም ግንባታ፣ መሠረተ ልማት፣ የአዕምሮ ግንባታንም ጭምር የመስራት ሙሉ ነፃነትና መብት ያለው መንግስት ነው፡፡ ይሄ አንዱ የአቅም ግንባታችን አካል ነው፡፡ የአቅም ግንባታው የሚሰጠው ደሞዝ ተከፋይ ለሆነውና በመንግስት ስልጣን ላይ ላለው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአርሶ አደራችን፣ ለተማሪዎችና ለተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ይህ የአቅም ግንባታ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ማስረጫ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ስለአገሪቱ እጣ ፈንታ የማወቅና የመወሰን ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የማድረግ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ታሪካዊ ሃላፊነት ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ ግዴታውም ነው፡፡ መንግስታዊ ሃላፊነትንና ግዴታን የመወጣት ጉዳይ ነው፡፡
ስልጠናው መጀመሪያ የታቀደ ሳይሆን ድንገት የመጣ አጣዳፊ ፕሮግራም ነው፤ እንደውም የግንቦቱን ምርጫ ታሳቢ ያደረገ ነው፤ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ የተለመደ ነው፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ የህዳሴው ግድብ ራሱ ለምርጫ ተብሎ እንጂ የታሰበበት አይደለም ሲባል ነበር፡፡ ነገር ግን የሚሠራውን የሚያስበው በስራው ላይ ያለው አካል ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው አካል ከመሬት ተነስቶ የታሰበበት አይደለም፤ መታሰቡንም አላውቅም ብሎ ሊበይን አይችልም፡፡ እነዚህ ወገኖች በመንግስት ውስጥ እስካልሆኑ ድረስ የታሰበውን ነገር ሁሉ አስቀድመው የሚያውቁበት እድል ሊኖር አይችልም፤ነቢያቶች እስካልሆኑ ድረስ፡፡
 ስለዚህ ስልጠናው በመንግስት እቅድ ውስጥ የነበረ እንጂ በዱብ እዳ የተሠራ አይደለም፡፡ ከምርጫ ጋርም የሚያቆራኘው ምንም ጉዳይ የለም፡፡ “ኢህአዴግን ብቻ ምረጡ” የሚል አረፍተ ነገር በአንዲት ቦታ ተብሎ ከሆነ፣ ይሄን በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ ይቻላል፤ ነገር ግን እንዲህ የተባለበት ቦታ የለም፡፡ ከምርጫ ጋር ፈጽሞ ሊያያዝ አይገባም፡፡ ይሄ ጉዳይ ከአንድ ዙር ምርጫ በላይ የዘለለ ነው፡፡ ስለ አገር ህልውና፣ በቀጣይ አገሪቱን ስለሚረከብ ዜጋ ጉዳይ ነው፡፡
 ስለ አገሪቷ እጣ ፈንታ ቀጣዩ ትውልድ እንዲገነዘብ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ትውልድን የመቅረጽ ጉዳይ ነው፡፡
 እነዚህ ነገሮች የተለመዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የስነ ዜጋ ትምህርት ሲጀመር ኢህአዴጋዊ ለማድረግ ነው ሲባል ነበር፤ስለዚህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም “ይሄ ነገር ለአገር በጐ ከማሰብ የተደረገ ነው” ቢባል ኖሮ ነበር በጣም የሚገርመው፡፡ የአሁኑ ግን የተለመደና መሠረተ ቢስ እንደሆነ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡
ከስልጠናው ምን ተገኘ? ወደፊትስ ምን  ታቅዷል  
በዩኒቨርስቲዎቹ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ግብአት አግኝተናል፡፡ በቀጣይም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአስተዳደር አካላት የአስር ቀናት ስልጠና ይሠጣል፡፡
በቅርቡ ከአገር የተሰደዱ ጋዜጠኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ እንዳቀረቡ ሰምቼአለሁ---
አዎ አቅርበናል፡፡
በምን መልኩ ነው ጥሪው የቀረበው?
በጋዜጠኞች ስልጠና ላይ የመክፈቻ ንግግር ሳደርግ አንዱ ያነሳሁት ጉዳይ ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍትህ ሚኒስቴር ከተከሰሱ 5 መጽሔቶችና 1 ጋዜጣ ጋር በተገናኘ የተሰደዱ ጋዜጠኞች አሉ የሚል ነገር በየቦታው ይወራል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች በክሱ ተደናብረው ከሃገር ኮብልለው ከሆነ፤ እነሱን ሊያስጠይቅ የሚችል ነገር ስለሌለ መኮብለላቸው አግባብ አይደለም፡፡ ብዥታው አግባብነት ስለሌለው በአስቸኳይ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ስራቸውን እንዲቀጥሉ ነው ጥሪ ያስተላለፍነው፡፡
አሁንም ደግሜ የምለው፤ ጋዜጠኞቹ ከአገር የወጡት በጋዜጣውና መጽሔቶቹ ክስ ምክንያት ከሆነ፣አግባብ ስላልሆነ  ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ስራቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመምህር ሃይማኖት ታደሰ አራጋው የተፃፈው “ያንዳንድ አጥንት እጣ” የተሰኘ የግጥም መድበል በገበያ ላይ ዋለ፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ተካተቱት ግጥሞች ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ፍልስፍናዊ ጉዳዮችን ያነሳሉ ተብሏል፡፡ 43 ግጥሞችን የያዘው መድበሉ፤ 48 ገፆች ያሉት ሲሆን በ20 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ደራሲው ከዚህ ቀደም “እንበለ ጥበብ” እና “የማርገዝ ነፃነት” የተሰኙ የግጥም መፅሃፍት ያሳተመ ሲሆን ከሌሎች ገጣሚያን ጋር በመሆንም “የማለዳ ነፍሶች” የተሰኘ የግጥም መድበል ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

“ድህረ አብዮት ሰልፍ ሜዳ ለሁለት ተከፍሎ፣ ቀበሌ ሃያ ዘጠኝና ቀበሌ ሰላሳ ተብሎ ተዋቀረ፡፡ ሰልፍ ሜዳ

የሚለው ስም የመጣውም ከአብዮቱ በኋላ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ ለሁሉ ነገር ይሰለፉ ነበር፡፡ ለዳቦ፣ ለጋዝ/ኪሮሲን፣

ለስኳር፣ ለዘይት፣ ለዱቤ ዱቄት፣ ለቦኖ ውሃ፣ የዕድር ሊቀመንበር ለመምረጥ… ሰልፍ….ሰልፍ….ሰልፍ ለሁሉም፡፡ …

የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ተስፋፊነትን ለማውገዝ፤ ለላቲን አሜሪካ ወዛደሮች ትግል አጋርነትን ለማሳየት፤… ነጋ

ጠባ፤ ዘመን መጣ፤ ዘመን … ሔደ… ሰልፍ! ሰልፍ! ሰልፍ! ሰልፍ! ነው! የሌላ ሠፈር ሰዎች፤ ሰልፍ እኛ ሰፈር ብቻ

ያለ ይመስል፤ “ሰልፍ ሜዳ” ሲሉ ጠሩት መንደራችንን፡፡ … እኛም የሰልፍ ሜዳ ልጆች ሆንን፡፡



ንዋይ ንዋይ የሚሸቱ የጥበብ ስራዎችን ዱካ ለማነፍነፍ ብዙ መድከም አይጠበቅብንም፡፡ በልባሳቸው መዥጎርጎር

አሊያም በሚመርጧቸው ርዕሶች በቀላሉ እንለያቸዋለን፡፡ ስገምት ነጋዴ ጸሐፍት ከመጽሐፍት ገበያ ትኩሳት ጋር

አብሮ ከፍ ዝቅ የሚል ርዕስና ርዕሰ-ጉዳይ ሲቃርሙ የሚውሉ ይመስለኛል፡፡ ስገምት ንግዱንም ትርፉንም

በሚገባ ያውቁበታል፡፡ ስገምት ቴሌቪዥን ማታ ማታ “ስግብግብ ነጋዴዎች…” ብሎ ዜና ባነበበ ቁጥር የሚበረግጉ

ይመስለኛል፡፡ ሁልጊዜም የሚከፋኝ ግን አንባቢ እነዚህን ንዋይ አፍቃሪ ጸሐፍት ፊት አለመንሳቱ ነው፡፡
ጥበበኛስ? ጥበበኛ ከነጋዴ ፀሐፍት ጋር ሆድና ጀርባ ነው፡፡ በገበያው ግርግር ውስጥ ተላላነት ያጠቃዋል፡፡

ትርፍና ንግድ በሚሉት ጉዳዮች ባይተዋርነቱ ያይላል፡፡ ተመስጦ ውስጥ ሆኖ በጥቂቶች ልብ ይበራል፡፡ ጥበበኛ

ቅድሚያ የሚሰጠው ለህሊናው ነፃነት ነው፡፡ ቅድምያ የሚሰጠው ለራሱ ስሜት ነው - ለመንፈሱ፡፡
ጥበበኛ ጥበብን ሲከውን እንደመተንፈስ ይቀለዋል፡፡ ዘና ማለቱ ለተደራሲያኑም ይተርፋል፡፡ በዚህ መሰሉ

መዝናናት የተበጃጀ የምናብ አብራክ ክፋይን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ከባድ ነው፡፡ እኔም ከሰሞኑ ከአራሙቻው

መሐል ጎንበስ ቀና የሚል እሸት ጥበብ፣ ከዓይኔ ሲገባ ዝምታን ወግድ ብዬ አንድ ሁለት ለማለት ፈለግሁ፡፡

ለትችትም ለሙገሳም የሚበቃ ንፁህ የጥበብ ሥራ ማግኘት አሁን አሁን እንደመታደል የሚቆጠር ሆኗል፡፡ ሰልፍ

ሜዳ ከእነዚህ ውስጥ የሚካተት የጥበብ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፌ ይሄን ልቦለድ ነው ለአንባቢያን ለማስቃኘት

የወደድኩት፡፡
የሰልፍ ሜዳ ሽፋን፤ ጽልመት የወረሰው፣ የኾነ የሚጨፈግግ  ቀንን የሚያስታውስ ነው፡፡ ጫፉ የማይታይ ጉም

የለበሰ ሰማይ ስር፣ ከሰው የተራቆተ ጎዳና፣ በደብዛዛ ብርሃን አንዲት ወልጋዳ ሰማያዊ ታክሲ እንደነገሩ

ትታያለች፡፡ ደራሲው ግርማ ተስፋው፤ ተደራሲያኑ ገና የመጽሐፉን ልባስ ማየት ሲጀምሩ በፈተና ሊቀበላቸው

የፈለገ ይመስላል፡፡ እንዴት? ቢሉ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ የድብርት ቆሌ አርብቦበታልና ነው፡፡
የመጽሐፍ ሽፋን የጎጆ በር ማለት ናት፡፡ ደራሲው ከመጽሐፉ ገጾች ሳቅና ጨዋታን እንዳንጠብቅ ጎጆዋን ከል

አልብሷታል፡፡ በ240 ገጾች የተቀነበበው ይህ ረዥም ልብወለድ፤ መቼቱ በደርግ መውደቂያ ዋዜማ ላይ ነው፡፡

መላ ታሪኩ ተጀምሮ የሚጠናቀቀው አዲሳባ ከምትገኝና ደራሲው በምናብ ከፈጠራት “ሰልፍ ሜዳ” ከተባለች

መንደር (ሰፈር) ነው፡፡ ይህ ምናባዊ ሰፈር “ሰልፍ ሜዳ” ለምን ተባለ ለምንል ተደራሲያን በገጽ 70 ላይ እንዲህ

ተብራርቶልናል፡-
“ድህረ አብዮት ሰልፍ ሜዳ ለሁለት ተከፍሎ፣ ቀበሌ ሃያ ዘጠኝና ቀበሌ ሰላሳ ተብሎ ተዋቀረ፡፡ ሰልፍ ሜዳ

የሚለው ስም የመጣውም ከአብዮቱ በኋላ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ ለሁሉ ነገር ይሰለፉ ነበር፡፡ ለዳቦ፣ ለጋዝ/ኪሮሲን፣

ለስኳር፣ ለዘይት፣ ለዱቤ ዱቄት፣ ለቦኖ ውሃ፣ የዕድር ሊቀመንበር ለመምረጥ… ሰልፍ….ሰልፍ….ሰልፍ ለሁሉም፡፡ …

የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ተስፋፊነትን ለማውገዝ፤ ለላቲን አሜሪካ ወዛደሮች ትግል አጋርነትን ለማሳየት፤… ነጋ

ጠባ፤ ዘመን መጣ፤ ዘመን … ሔደ… ሰልፍ! ሰልፍ! ሰልፍ! ሰልፍ! ነው! የሌላ ሠፈር ሰዎች፤ ሰልፍ እኛ ሰፈር ብቻ

ያለ ይመስል፤ “ሰልፍ ሜዳ” ሲሉ ጠሩት መንደራችንን፡፡ … እኛም የሰልፍ ሜዳ ልጆች ሆንን፡፡
በዚህ ማብራሪያ ደራሲው የሰልፋም ሰፈርነቱን (ሰሙን ማለት ነው) ያትት እንጂ ወርቁን ሊነግረን አልዳዳውም፡፡

ወርቁን ገጽ በገፋን ቁጥር፣ እንደ በቆሎ እየፈለፈልን እንድናገኘው ነው የፈለገው፡፡
ሰልፍ ሜዳ ዙሪያ ጥምጥም ነው፡፡ ወሰን ድንበር ፍጻሜው አይታየንም፡፡ ወትሮ እንደለመድናቸው የልብወለድ

ታሪኮች፣ የስሜት ከፍታን በእያንዳንዱ ኩርባ ላይ ለመቃረም ከዳዳን አይሳካልንም፡፡ እፍ ክንፍ ያለ የፍቅር

ታሪክ፣ ሴራ ጉንጎና፣ ልብ ሰቀላና የመሳሰሉት የሥነ-ፅሁፍ ጌጦች በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ብርቅ ናቸው፡፡ ለልብ

ሰቀላ ሲሉ መጽሐፍ ለሚያነቡ ተደራሲያን፣ ይህ መጽሐፍ ደመኛቸው ቢኾን አይገርምም፡፡ በሰልፍ ሜዳ ኩርባ

የሚባል ነገር የለም፡፡ የታሪክ መቋጫ ፍለጋ ከተንደረደርን፣አድማስ ጋር ሰዶ ማሳደድ እንገባለን፡፡
የመፅሐፉ አንኳር ጭብጦች
መጽሐፉ ስለብቸኝነት፣ ስለባዶነት፣ ስለከንቱነት----መብሰክሰክ ይበዛዋል፡፡ ገጸ-ባህርያቱ እዚህ ግቡ የማይባሉ

ተራ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደ ወይዘሮ ከድጃ አይነት ቡና ማፍያ የሚለምኑ፤ እንደ እሙ ከሴተኛ አዳሪ ተወልደው

ቆሎ የሚያዞሩ… ወዘተ፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሲኖሩ ትዝ የማይሉን፣ ነገር ግን ሲሞቱ ይበልጥ

የምናስታውሳቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ንጉሴ የተባለው ገጸ ባህሪ ወፍጮ አስፈጪ ነው፡፡ የሰልፍ ሜዳ ሰው፣ ንጉሴ

በህይወት መኖሩ ትዝ ያለው ለአካባቢው ዳቦ በምታድል መኪና የተገጨ ዕለት ነው፡፡ “… ንጉሴ ሰው ሳይሆን

የሰው ጥላ ይመስለኝ ነበር፤ በኑሮው ሳይኾን በሞቱ ሰው መስሎ ተሰማኝ” (ገጽ 8)፡፡
በገመናችን የሚዘባበቱት አያቱ!
“ስማ የእግዜር ቀልድ ይሉኝ ነበር አያቴ” በሚል ንግግሩ ነው የልቦለዱን ዋና ገፀ ባህሪ የምንተዋወቀው፡፡ ታሪኩ

ይባላል፡፡ በአንደኛ መደብ ሙሉ ታሪኩን የሚተርክልን ይኼ ገጸ ባህሪ ነው፡፡ የታሪኩ አያት ብርቱ ሰብእና

አላቸው፡፡ ብሽቀታቸውን መሸሸግ አይሆንላቸውም፡፡ በአገኙት አጋጣሚ ፈጣሪን በነገር ጎሸም ማድረግ

ይቀናቸዋል፡፡ ማህበረሰቡንም እንደዚያው፡፡ ጉሸማው ለሌላ አይደለም፡፡ የንቃ ዓይነት ደውል ነው፡፡
አዛውንቱ በገመናችን ይዘባበታሉ፡፡ በአመለካከታችን፣ በስንፈታችን፣ በጉብዝናችን፣ በእምነታችን፣ በክህደታችንና

በታሪካችን ላይ ክፉኛ ይሳለቃሉ፡፡ እኝህ አዛውንት የደራሲውን የብሽቀት ጥሪት ጠቅልለው የተሸከሙ

ይመስላሉ፡፡ በፈጣሪም በህብረተሰቡም ተሳላቂው አያት፤ ጣሊያንን ያንቀጠቀጡ ጎበዝ አርበኛ ነበሩ፡፡ ኋላ ላይ  

ወራሪው ኃይል ከሀገር ሲባረር፣ ወደ ጭቃ ረጋጭነት ሥራ ተሸጋገሩ፡፡ እርሳቸው በዱር በገደሉ ሲዋደቁ ግን

ባንዳዎች የፋሺስት ጫማ ይወልውሉ ነበር፡፡ ከድል በኋላ ጫማ ወልዋዮቹ ባንዳዎች ሹመት ሲሰጣቸው፣

እርሳቸው ግን ጭቃ ረጋጭ ሆነው ቁጭ አሉ፡፡
“ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡” የሚለውን ስንኝ ያስታውሰናል - የእሳቸው ታሪክ፡፡
የታሪኩ አያት ታሪክ ብቻ መርምረው አያበቁም፡፡ ስነልቦናችንን ይሰልላሉ፡፡  
የታሪኩ አያት ቄስ ቢኾኑም በአንድ አጋጣሚ ከታሪክ ጋር ሆነው በ “መታፈሪያ ጠጅ ቤት” ታድመዋል፡፡ የሰልፍ

ሜዳ “ጉልቤ” ተስፋሁን፤ አንድ ቦርጫም ጠጪን አንበርክኮ፣ እላዩ ላይ ጠጅ እያፈሰሰ ይንከተከታል፤

ይሳለቅበታል፤ ያዋርደዋል፡፡ ሰዎች በጉልቤው ተስፋሁን፣ እርር ድብን ቢሉም ማንም ለመናገር አይደፍርም፡፡

በሁኔታው የተናደዱ የሚመሰሉት ሽማግሌው የታሪኩ አያት፤ ከተቀመጡበት ብድግ ብለው ጉልቤው ተስፋሁንን

በቁጣ ገደሉት ሲባል፣ በተቃራኒው የተንበረከከውን ሰውዬ ከተስፋሁን ጋር ተደርበው መደብደብ ያዙ፡፡ ይበልጥ

የምንደመመው ግን ይህን ያደረጉበትን ምክንያት ሲገልጹ ነው፡፡ በገጽ 67 እና 68 ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
“… መንበርከክ እንደ ተስቦ ከሰው ሰው እንደሚጋባ አታውቅም? አናት አናቱን ማለትማ ተንበርካኪውን ነው!

ኧ---- ያኔ ነው ሰው የሚኾነው፡፡”
“ተንበርካኪ መቼ ምክንያት ያጣል፤ብትጠይቀው እኖር ብዬ፤ ልጅ አሳድግ ብዬ ይልኻል፡፡ የሰው ዝቃጭ፡፡ የኖረ

መስሎታል፡፡ ሞት አይቀር! ተረጋጭም የረጋጭን ያህል ጥፋተኛ ነው፡፡… ይበለው”
ጭቆናን አሜን ብሎ የሚኖር ሰብእና፣ የሀጢያት ዳፋው ከጨቋኙ በላይ ይገዝፍብናል፡፡ ተንበርካኪነትና ጎብጦ

የሚያዘግም ስነልቦናን ደራሲው እንዲህ ባለ ተራ የጠጅ ቤት ግጭት ሊያስዳስሰን ሲሞክር እንወደዋለን፤ እናም

አበጀህ እንለዋለን፡፡
አብደላ ሻይ ቤት እንደ ብሶት አደባባይ
ሳምቡሳ የሚጠበስበት ሻይ ቤት፣ በሰልፍ ሜዳ ላይ ታሪክን ለማንጎድ መደላደያውን ያመቻቸ ታንኳ ሆኖ

እናገኘዋለን፡፡ አብደላ ሻይ ቤት፣ የመጣው ሁሉ ብሶቱን የሚጥልበት ጉሮኖ ነው፡፡ ደራሲው ይህንን ስፍራ

በዋነኛነት ለመጠቀም የፈለገው ምን አልባትም ለአብዛኛው ህብረተሰብ ቅርብ የሆነ ስሜትን እፈጥርበታለሁ

በሚል ምናባዊ ጥንስስ ተገፋፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በአብደላ ሻይ ቤት ታሪክ ይወጣል ይወርዳል፡፡ ፍልስፍናን

በላይ በላይ እንመገባለን፡፡ ተፈላሳፊዎቹ ደሞ ማንም በማይገምተው መልኩ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን

ናቸው፡፡ አብዮት ተስፋ በሚባል ትምህርት ቤት ያስተምራሉ፡፡ አንባቢው እንዴት ይህን የመሰለ ጥልቅ

ፍልስፍናን ከመጀመሪያ ደረጃ መምህራን እናገኛለን? ብሎ ቢሞግት አይፈረድበትም፡፡ የጊዜ ስሌት ግን ሙግቱን

ውሃ እንዳይቋጥር ያደርገዋል፡፡ ተፈላሳፊዎቹ መምህራን ከአብዮቱ ግርግር ዘመን በፊት ነው የበቀሉት፡፡

መምህራኑ የደራሲው ምናባዊ ፈጠራ ቢኾኑም በዘመኑ የነበሩትን ታሪካዊ ኩነቶች እያነሱ የሚጥሉበት የአስተሳሰብ

ጥልቀት፣ የገሃዱ ዓለም አካል አድርገን እንድንቆጥራቸው ያስገድደናል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰልፍ ሜዳ

መምህራንን ከአሁን ዘመን መምህራን ጋር ለማነፃፀር ልኬት ውስጥ የምንገባባቸው አጋጣሚዎች ይበራከቱብናል፡፡
የሁለት መንትዮች ወግ
መንትዮቹ ቸርነትና አሸናፊ ይባላሉ፡፡ የታሪኩ የልብ ጓደኛ የለዓለም ወንድሞች ናቸው፡፡ ደራሲው የሁለቱን

መንትያዎች ስነልቦና የታሪካችን ማሳያ አድርጎ ቀርጾታል፡፡ እዚህ ጋ የደራሲውን ታሪክ አዋቂነት ልብ ይሏል፡፡

ቸርነት በአብዮቱ ዘመን አካባቢ የበቀሉ ልሂቃንን ይወክላል፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው፣ በአብዮቱ መባቻ ላይ

በፊት አውራሪነት የተሰለፉት ልሂቃን ስነልቦና ወጥ ነበር፡፡ ሁሉም፣ ጽንፈኝነትን ያነገቡ፣ ሁሉም እውቀትን

ሳይፈትሹ እንደወረደ የሚያጠልቁ ደብተራዎች ነበሩ፡፡ የቸርነትን ግልብ ስነልቦና በዘመኑ በነበሩት ዘውግ-ዘለል

የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ እናገኘዋለን፡፡ ቸርነትን ስንመለከት የማርክሲዝም ሌኒንዝምን ጥቅስ በቃል በማነብነብ

ብቻ ለአዋቂነታቸው ሚዛን የሚሰፍሩ ምሁራንን እናስታውሳለን፡፡ ቸርነት በማርክሲዝም ሌኒንዝም ከተጠመቀ

በኋላ፣የቤተሰቡን እምነት በአንዲት ጀምበር ለመናድ የሚጣደፍበት ሁኔታ ሀገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ

የሰደዷትን የአብዮቱን ዘመን የፖለቲካ ልሂቃን ያስታውሰናል፡፡ ለቸርነት ጽንፈኝነት ማሳያ መንትያ ወንድሙ

አሸናፊ በተቃራኒው ተስሏል፡፡ አሸናፊ ሚዛናዊ ነው፡፡ አማካይ ስፍራን መያዝ ይወዳል፡፡ የአርስቶትልን “Golden

Mean”  እዚህ ጋ እናስታውሳለን፡፡ “ዘ ጎልደን ሚን” አርስቶትል ሚዛናዊነትንና ክፍት ስነልቦናን የገለጸበት

መጠሪያ ነው፡፡ በእርግጥም አሸናፊ ይህ ስያሜ ይገባዋል፡፡
ጉዱ ካሳዊው - ለዓለም
ለዓለም መኩሪያ የደራሲው የምናብ ከፍታ ውላጅ ነው፡፡ በ“ፍቅር እስከ መቃብር” ከግርግሩ መሐል

በባይተዋርነት ቆሞ የሚሟገተውን ጉድ ካሳን በሰልፍ ሜዳ ላይ ለዓለም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዓለም ለእንቶ

ፈንቶው ፊት መንሳት ያውቅበታል፡፡ እጅግ የላቀ ቁርጠኝነትንና ጽናትን ከሚጠይቁ ጉዳዮች ጋር ሲጋፈጥ

እናስተውለዋለን፡፡ በገጽ 104፤ ለዓለም ከጓደኛው ታሪኩ ጋር በሚያደርገው ምልልስ የአመለካከቱን አስኳል

እናገኛለን፡-
“መፍራት ካለብህ ብቻውን መሆን የማይወድን ሰው ፍራ፡፡ ሰው በህብረት ሲሆን እምነት የለኝም፡፡ ታሪኩ፤ ሰው

ማህበራዊ እንስሳ ነው የሚሉህን አትስማቸው፡፡ ቆፈናሞች!! አፍንጫችሁን ላሱ በላቸው፡፡ በቡድን አደራጅተው፤

ከፋፍለው ከፋፍለው ለማጋደል፣ ለማሰርና ለመግዛት እንዲመቻቸው ነው፡፡ ሰው ብቸኛ እንስሳ ነው፡፡ ትልቁ

ትራጄዲ ብቸኝነቱን መሸሹና መፍራቱ ነው፡፡”
ይህ ዓይነቱ ከመንጋ የመነጠል አባዜ፣ የጉዱ ካሳ እምነትና አመለካከት፣ ቀኖና ውላጅ ነው፡፡ ለዓለም ግርግሩን

ለመሸሽ በሚያደርገው ጥረት፣ ከህዝበ ሰልፍ ሜዳ ብርቱ ወከባ ሲያጋጥመው እናስተውላለን፡፡
የመጽሐፉ ድክመቶች
ገጸ ባህሪን ከማስተዋወቅ አንጻር
ገፀ-ባህሪን ከተደራሲያኑ ጋር ከማስተዋወቅ አንጻር በመፅሃፉ ውስጥ ጉልህ ክፍተት ይታያል፡፡ በመጀመሪያው

ምዕራፍ መግቢያ አካባቢ፣ በመኪና አደጋ ለህልፈተ ህይወት የበቃው ንጉሴ፤ ድንገት ሞትን እንደ አልአዛር ድል

አድርጎ፣ በገጽ 93 በዳቦ ሰልፍ ላይ እናገኘዋለን፡፡ የንጉሴ ከአንባቢው ጋር ድንገት ፊት ለፊት መላተም፣ የታሪኩን

ፍሰት ያንገራግጨዋል፡፡ ስለንጉሴ ምንነት በቅጡ ለማወቅ ንባቤን ገታ አድርጌ፣ ያለፍኳቸውን ገጾች እንደገና

መመርመር ነበረብኝ፡፡ ይህ ግርታ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ተደራሲያን እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡
መቼት
ገፀ-ባህሪያቱ በጊዜና በቦታ መለኪያ ሲሰፈሩ በደንብ አልታሹም፡፡ አብደላ ሻይ ቤት በልብወለዱ ውስጥ

በጉልህነት ከሚነሱት ቦታዎች አንዱ ነው፡፡
በገጽ 11 ላይ፤ “አብደላ በቀይ ሽብር ዘመን በተባራሪ ጥይት የተገደለ የሙሰማ ታናሽ ወንድም ነው፤ በተባራሪ

ጥይት ለሞተ፣ ሐውልት የሚያቆምም የሚያጀግንም ስለሌለ፣ ይህን ምግብ ቤት በታናሽ ወንድሙ ስም ጠራው፤

የአብደላ ስምም በመላው ሰልፍ ሜዳና በዙሪያው ባሉ የአዲስ አበባ ሰፈሮች ሁሉ ታወቀ” ሲል ስለስያሜው

ያትታል፡፡
ደራሲው ስያሜው ከጊዜው ጋር ይጣጣም አይጣጣም ግድ የሰጠው አይመስልም፡፡ በቀይ ሽብር የተገደለን

ሰው፣በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፊት ለመዘከር ድኅረ ደርግና ቅድመ ደርግ ለየቅል መሆናቸውን ማንም ሊረዳው

የሚችል ሀቅ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር በቀበሌ ሹማምንት ዘንድ ይህ ተግባር ጥርስ የሚያስገባ ድፍረት ነው፡፡ ለዚህም

እራሱን ልብወለዱን ምስክር ማድረግ እንችላለን፡፡ ደራሲው የሰልፍ ሜዳ ህብረተሰብ የቀበሌውን ሊቀመንበር

ጓድ እንዳይላሉ መርሻን ሲመለከት፣ ብርክ እንደሚይዘው በመጀመሪያው ምዕራፍ ገጾች ላይ እየደጋገመ

እየነገረን፣ ሙሰማን እንደ ጸረ አብዮት በሚያስቆጥር ተግባር ላይ ደፋር ማድረጉ ከምን የመጣ ነው ብለን

እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ እዚህ ጋ ከግምት መጣፍ ያለብን የቤቱን ጭርንቁስነት ሳይሆን የጊዜውን እውነታ

ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳት፣ የቤቱ ስያሜን ተዓማኒነት እንደሚያጎድል መታሰብ ነበረበት፡፡
በእንግዳ ቃላት ማደናገር
ሰልፍ ሜዳ የቃላት ደሃ አይደለም፡፡ የቃላት ደሃ አለመሆኑ ግን ያዘናጋው ይመስላል፡፡ ደራሲው እንግዳ ቃላትን

ወይም አገላለጽን ያለ ማብራሪያ ዝም ብሎ ነው የሚያልፉቸው፡፡ ለአብነት ያህል በገጽ 175 ላይ እንዲህ የሚል

ስንኝ ሰፍሯል፡-
ቀነውኒ አደውየ ወእገርየ
ወኈለቍ ኩሉ አዕፀምትየ
ቀነውኑ እንደውየ ወአገርየ
ትንሽ አለፍ ብሎ “አምንስቲቲ ሙክርያ” የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ደራሲው የቃላቱን  ትርጉም በቅንፍ ጠቆም

አድርጎ ማለፍ ወይም የህዳግ ማጣቀሻ መጠቀም ይችል ነበር፡፡
በአጠቃላይ ግን ሰልፍ ሜዳ ባልተሄደበት ጎዳና ለመንጎድ የጀገነ፣ ግሩም የቋንቋ ዉበት ያለው፣ እንደወቅቱ

በድፍረት ተነስቶ ስለማያውቁት ጉዳይ መጽሐፍ የመጻፍ ደዌ ዉስጥ ያልተዘፈቀ፣ በስክነትና በእውቀት የተከተበ፣

ኩልል ያለ የጥበብ ስራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ደራሲው አንድ ተጨማሪ የጥበብ ስራ ከደገመን ምናልባት አዳም

ረታ ታናሽ የጥበብ ወንድም አገኘ ብለን ለማወጅ እንደፍር ይሆናል፡፡  

በበለጠ በላቸው ይሁን የተፃፈው “ጅቡቲ የጥገኝነታችን መስፈሪያ” የተሰኘ መጽሐፍ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ

ለንባብ በቃ፡፡ በስድስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ222 ገፆች የተመጠነው መጽሐፉ፤ ከአፄ ኃይለስላሴ መንግስት

ጀምሮ በበርካታ የኢትዮጵያና ጅቡቲ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ ያቀርባል፡፡ መጽሐፉ በ65 ብር ለገበያ እንደቀረበ

ለማወቅ ተችሏል፡፡

ላቭሊ የውበት ስራ ማሰልጠኛ ተቋም በተለያዩ የውበት ሥራ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ በግሎባል ሆቴል እንደሚያስመርቅ ስራ አስኪያጁ አቶ ፋሲል ሚካኤል አስታወቁ፡፡ በእለቱ የሚመረቁት ተማሪዎች በሞዴሊንግ፣ በፀጉርና በውበት ስራ፣ በፋሽን ሾው፣ እንዲሁም በሌሎች የፈጠራ ስራዎች የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትለው ያጠናቀቁ ሲሆን በየዘርፉ በትምህርት ብቃታቸው ብልጫ ላሳዩ ተማሪዎች ሽልማት እንደሚሰጥም ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ላቭሊ የውበት ማሰልጠኛ ተቋም ላለፉት 16 ዓመታት በዘርፉ ስልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በርካታ ዜጐችን የሙያ ባለቤት እንዳደረገም ተገልጿል፡፡

ውድ እግዚአብሔር፡-
ት/ቤት ሁሉም የራሱ ምርጥ ጓደኛ አለው፤ እኔ ብቻ ነኝ የራሴ ጓደኛ የሌለኝ፡፡ አንድ ጓደኛ ልትሰጠኝ ትችላለህ?

ግን ቶሎ ብለህ እሺ?!
ዴቭ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ሃና ከክፍላችን በጣም ቆንጆ ናት፡፡ ሳሚ ደግሞ በሩጫ የሚበልጠው የለም፡፡ ቲና ጥርሷ ያምራል፡፡ ለእኔ ግን

ምንም የተለየ ነገር አልሰጠኸኝም፡፡ ረስተኸው ነው?
ጁዲ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
እህቴ ባል እንድታገባ እባክህ ቆንጆ አድርጋት፡፡
ቤቲ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
የፕላስቲክ አበቦች ስታይ አትናደድም? እኔ አንተን ብሆን በጣም ነበር የምናደደው፡፡
ጆሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ታላቅ ወንድሜ እኔን እንደሚቆጣኝ፣ እኔም የምቆጣው ወንድም እፈልጋለሁ፡፡ ትንሽዬ ወንድም ትሰጠኛለህ?
ቶኒ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ሶፊ የሚያምር ጫማ አላት፡፡ እኔም የእሷ ዓይነት ጫማ እፈልጋለሁ፤ ግን ልሰርቃት አልፈለግሁም፡፡ አንተ

ልትሰጠኝ ትችላለህ?
ውድ እግዚአብሔር፡-
አንዳንዴ ጥርሴን የውሸት ስቦርሽ ታውቅብኛለህ አይደል? ግን ለማሚ እንዳትነግርብኝ እሺ!?
ካሌብ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ከዓለም ላይ መጥፎ ነገሮችን ካላስወገድክ በሚቀጥለው ጊዜ የምትመረጥ አይመስለኝም፡፡ እኔ እኮ ላንተ ብዬ

ነው፡፡ ወይስ መመረጥ አትፈልግም?
ኤርሚ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ከፃፍካቸው ታሪኮች ሁሉ የወደድኩት የኖህን ታሪክ ነው፡፡ እኔም በውሃ ላይ መጓዝ ደስ ይለኛል፡፡
ሳቤላ - የ8 ዓመት ህፃን