Administrator

Administrator

Monday, 29 September 2014 08:40

የፍቅር ጥግ

ዝነኞች ስለጋብቻ የዛሬዋ ምሽት እጅግ ልዩ ናት፡፡ በፓሪስ የኤፍል ማማ ጫፍ ላይ ቃል ኪዳናችንን ዳግም ማደሳችን ምን ያህል እፁብ ድንቅ እንደሆነ ልገልፀው አልችልም፡፡ ማሪያ ኬሪ (አሜሪካዊት ዘፋኝ) ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢገጥመን ተደጋግፈን ማለፋችን ጠቅሞናል፡፡ ጃዳን የመሰለች ሴት በማግኘቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ እጅግ ግሩም ሴት፣ ሚስትና እናት ናት፡፡ ዊል ስሚዝ (አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ) ህፃናቱ እንድንጋባ ጫና አሳድረውብናል፡፡ የእኛ መጋባት ለእነሱ ምን ማለት እንደሆነ አልተገነዘብንም ነበር፡፡ ስንጋባ ግን ለእኛም ያለውን ትርጉም ተረድተነዋል፡፡ ብራድ ፒት (አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ) አሁንም ልክ መጀመሪያ ላይ ስንተዋወቅ እንደነበረው እንፋቀራለን፤ ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ልጆች አሉን … በጣም ደስተኞች ነን፡፡ የስራና የቤተሰብ ኃላፊነታችንን በማመጣጠን ህይወታችንን እንመራለን፡፡ ምንጊዜም ቅድምያ የምንሰጠው ለልጆቻችን ነው፡፡ ዴቪድ ቤክሃም (እንግሊዛዊ የእግር ኳስ ተጫዋች) ከ20 ዓመት በፊት ልታገባኝ የተስማማችው እቺ ሴት ባትኖር፣ ዛሬ የሆንኩትን አይነት ሰው አልሆንም ነበር፡፡ ይሄን ነገር በአደባባይ ልበለው፡- ሚሼል፤ እንዲህ አፍቅሬሽ አላውቅም፡፡ መላው የአሜሪካ ህዝብ በቀዳማዊት እመቤትነትሽ በፍቅር ሲወድቅልሽ እንደማየት የሚያኮራኝ ነገር የለም፡፡ ባራክ ኦባማ (የአሜሪካ ፕሬዚዳንት) ጋብቻ የሰመረ እንዲሆን ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ አንደኛው ለስኬታማነቱ መትጋት ነው፡፡ ሌላው ከእናንተ በላይ የሆነ ሰው ማግባት ነው፡፡ እኔ በሁለቱም ረገድ ተሳክቶልኛል፡፡ ቤን አፍሌክ (አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ) በእኔና በእሷ ግንኙነት ውስጥ ሁለት መመሪያዎች አሉን፡፡ የመጀመሪያው መመሪያ፤ ማናቸውንም ነገሮች እያገኘች እንደሆነ እንድታስብ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው መመሪያ ደግሞ፤ ማናቸውንም ነገሮች በራሷ መንገድ እንድታከናውን መፍቀድ ነው፡፡ ይሄ አሁን ድረስ እየሰራልን ነው፡፡ ጀስቲን ቲምበርሌክ (እንግሊዛዊ ዘፋኝ)

Monday, 29 September 2014 08:33

ገጣሚያን ስለህይወት


* ህይወት ስዕል መስራት እንጂ ሂሳብ ማስላት     አይደለም፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልምስ
* ህይወት ፈፅሞ እውን ለማይሆን ነገር የሚደረግ ረዥም ዝግጅት ነው፡፡
ዊሊያም በትለር ይትስ
* ነፃነት የሌለው ህይወት መንፈስ እንደሌለው ገላ ነው፡፡
ካህሊል ጂብራን
* ፍቅር የሌለው ህይወት አበባ ወይም ፍሬ እንደሌለው ዛፍ ነው፡፡
ካህሊል ጂብራን
* ህይወት ራሱ ጥቅስ ነው፡፡
ጆርጅ ሉይስ ቦርግስ
* ህይወት የተገነባው የሰው ልጅ ቀኑን ሙሉ ከሚያስባቸው ሃሳቦች ነው፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
* በ80 ዓመታችን ተወልደን ቀስ እያልን ወደ 18 ብንጠጋ ኖሮ፣ ህይወት በእጅጉ በደስታ የተሞላ ይሆን ነበር፡፡
ማርክ ትዌይን
*ህይወት የምንቆጥበው ሳይሆን የምንጠቀምበት ንብረታችን ነው፡፡
ዴቪድ ኸርበርት ሎውረንስ

* በትምህርት ቤትና በህይወት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ትምህርት ቤት፤ ትምህርት ትማርና ለፈተና

ትቀርባለህ፡፡ በህይወት ውስጥ ግን በቅድሚያ ትምህርት የምታገኝበት ፈተና ነው የሚሰጥህ፡፡
ቶም ቦዴት
* ላጣኸው ነገር ሁሉ ሌላ ነገር አግኝተሃል፤ ለምታገኘው ነገር ሁሉ ሌላ ነገር ታጣለህ፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
* በየቀኑ የምንከፍታቸውና የምንዘጋቸው      በሮች፣ የምንኖረውን ህይወት ይወስኑታል፡፡
ፍሎራ ዊትሞር

              የፅንስ ማቋረጥ ሕግ አተረገጓጎም... 551(ሀ) ‹‹በመደፈር ወይም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምክንያት ፅንሱ የተገኘ ሲሆን...›› የፅንሱ መቋረጥ የሚካሄደው እርጉዟ ሴት በምትሰጠው ቃል መነሻ መሰረት ነው፤ “ከአስገድዶ መድፈር ፣ ከቤተዘመድ ጋር በተደረገ ግንኙነት ምክንያት”.. ማለቷ በቂ ይሆናል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም ማስረጃ መስጠት አይጠበቅባትም፡፡ ይህም ቃሏ በሴትየዋ የህክምና ካርድ ላይ ይመዘገባል፡፡ 552 (ለ) የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱም ሆነ በፅንሱ ህይወት ወይም በእናቲቱ ጤንነት ላይ አደጋ የሚያስከትል ሲሆን ወይም የልጁ መወለድ በእናቲቱ ጤንነት ህይወት ላይ አደጋ የሚያመጣ ሲሆን.. 551(ሐ) “ፅንሱ ሊድን የማይችል ከባድ የአካል ጉድለት (deformed) ያለው ሲሆን” የጤና ባለሙያው አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ የማይድን የአካል ወይም የህብለዘር ጉድለት (genetic deformity) በፅንሱ ላይ ከታየ የፅንስ ማቋረጥ ሊካሄድ ይችላል፡፡

551 (መ) “አንዲት እርጉዝ ሴት የአካል ወይም የአእምሮ ጉዳት ያለባት በመሆኑ ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰች በመሆኗ የሚወለደውን ህፃን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጅት የሌላት ሲሆን” 551 (2) በፍጥነት በሚደረግ ህክምና ካልሆነ በስተቀር ሊወገድ የማይቻል ከባድና ጊዜ የማይሰጥ አደጋ ሲያጋጥም በህጉ አስገዳጅ ሁኔተ ተብሎ ስለሚቆጠር ..አንቀፅ 75.. ፅንስ ማቋረጥ አያስቀጣም፡፡ በአንቀፅ 551(2) በተደነገገው ሁኔታውስጥ ሆነው ለሚመጡ ሴቶች የፅንስ ማቋረጥ ተግባር ለመፈፀም ፈቃድ የተሰጣቸው ሁሉ በፍጥነት የፅንስ ማቋረጡን አገልግሎት መስጠት አለባቸው፡፡ የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስ..ር ሰኔ 1998 አዲስ አበባ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ መቋረጥን በሚመለከት ባለፈው እትም ለንባብ ያልነው ቀጣይ ይሆናል በዚህ አምድ የምናስነብባችሁ፡፡

ምንጮቻችን ዶ/ር ደመቀ ደስታ በአይፓስ ኢትዮጵያ ሲኒየር አድቫይዘር ፣ዶ/ር ጌትነት በቀለ ከበርጌስ ክሊኒክ ባለቤትና የህክምና ባለሙያ ከተክለ ሀይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ሲ/ር ነጻነት አባተ እና ሲ/ር አበባ ስለሺ ከበርጌስ ክሊኒክ ናቸው፡፡ እንደ ዶ/ር ደመቀ ማብራሪያ የአገልግሎቱ አሰጣጥ ልዩነት አለው ፡፡ “...የከተማና የገጠሩ ህዝብ በተለይ ደግሞ ወጣቶች በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች እና ሌላውን አካባቢ በምናነፃፅርበት ጊዜ ልዩነት አለው፡ ከተማ ውስጥ በተለይ የወጣቱ ክፍል ለስራ ፍለጋም፣ ከትምህርትም ጋር በተያያዘ ከገጠሩ ክፍል የሚመጡ ሲሆን እውቀቱና ግንዛቤው እንዲሁም አገልግሎቱም ስለማይኖር ብዙዎቹ ላልተፈለገ እርግዝና የተጋለጡ ናቸው ፡፡ ለምሳሌም ትልልቅ ኮንስትራክሽን የሚካሄድባቸው አካባቢዎች፣ ትልልቅ የእርሻ ጣቢያዎች በተለይም የአበባ እርሻ ያለባቸው አካባቢዎች እና ዩኒቨርስቲዎች ፣ ኮሌጆች ያሉባቸው አካባቢዎች የወጣቶች መሰባሰቢያዎች ሲሆኑ ፋሲሊቲዎቻችንን በምናይበት ጊዜ በቂ አገልግሎት እየሰጠን ነው ማለት አይቻልም፡፡ የገጠሩን የህብረተሰብ ክፍል በምናይበት ጊዜ ቁጥሩ አነስ ቢልም ለተጠቃሚዎች የተቻለውን ያህል አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተጠቃሚዎች አልጋ በመያዝም ይሁን ሙያተኛን ከመጋራት አንጻር ምን ያህል የህክምናው አሰራር ላይ ጫና ይፈጥራሉ? ለሚለው ሀሳብ ሲ/ር ነጻነት ከተክለሀይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል የሚከተለውን ገልጣለች፡፡

“...ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጣቸው ተጠቃሚዎች እንደሌላ ሕመምተኛ አልጋ አይይዙም ፡፡ እንደዚህ አይነት እናቶች ተስተናግደው ብዙም ሳይቆዩ የሚሸኙ ናቸው፡፡ ዋናው ነገር የምናየው ከጽንስ ማቋረጥ በሁዋላ የሚሰጣቸውን የምክር አገልግሎት ነው፡፡ ስለቤተሰብ ምጣኔ እዛው ትምህርቱ ይጀመርላቸዋል ፡፡ ሌላው ነገር የእሷን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥለውን ደም መፍሰስ ቆሟል ወይንስ አልቆመም የሚለውን ክትትል ማድረግ ነው ፡፡ ስለዚህ ከጽንስ ማቋረጥ በኋላ ያለውን ደም መፍሰስ እንዲሁም ከጽንስ ማቋረጥ በሁዋላ ያለው መመረዝ.. ሽቃሶስሰ..ሽቄቃ .. መኖር አለመኖር በተወሰኑ ሰአታት ከተረጋገጠ በበሁዋላ ወደ ቤትዋ እንድትሔድና በተሰጣት ቀጠሮ መሰረት እንድትታይ ትደረጋለች፡፡ ሲስተር አበባ ከበርጌስ ባስተላፈችው ምክር አዘል መልእክት... “.. የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ሴቶች በተቻለ መጠን ተጠቃሚ ቢሆኑ ጥሩ ነው፡፡ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንድ የማቋረጥ አገልግሎት በምንሰጥበት ጊዜ እግረ መንገዳችንን ስለቤተሰብ ምጣኔ አገልግት ምክር እንሰጣለን፡፡ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎቱን ምንም እንኩዋን ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ብንሰራውም አገልግሎት ፈላጊዋን ለመርዳት ሲባል እንጂ ደስ የማይል ነገር አለው፡፡

ነገር ግን ግዴታ ስለሆነ ደስ ባይለንም ስራውን እንሰራለን፡፡ ሴቶች አስቀድሞውኑ ያልተፈለገ እርግዝናን ቢከላከሉ ግን ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎትን ፈልገው አይመጡም ነበር ፡፡” ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ በትክክል ተግባር ላይ ውሎአልን? ለሚለው ዶ/ር ጌትነት በቀለ ከበርጌስ እንደሚሉት... .....ምንድነው ...ቀረ የምንለው ነገር ...በተለይ በመንግስት ተቋሞች ዙሪያ አንዳንድ ችግሮች ይታዩኛል፡፡ ለምሳሌ ...ለእኛ ቅርብ የሆኑ የመንግስት ጤና ጣቢያዎች፣ክሊኒኮችጋ ሊታዩ የሄዱ ሴቶች አንዳንድ ጊዜ ወደክሊኒንችን ይመጣሉ፡፡ ለምን ወደዚህ መጣችሁ? ተብለው ሲጠየቁ የተለያየ መልስ ይሰጣሉ፡፡ በእኛ በኩል ከአይፓስም ይሁን ከሜሪስቶፕስ የሚሰጠንን ድጋፍ በትክክል በመጠቀም ፣ለባለሙያዎች የሚሰጡ የተግባር ስልጠናዎችም ስለሚያግዙን አገልግሎቱን እንሰጣለን፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የህክምና ተቋም ጥያቄውን በትክክል ተቀብሎ ቢያስተናግድ መልካም ነው፡፡ በወደፊቱ አሰራርም መንግስትም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶት አሁን እየሰራን ያለነው ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ በቤተሰብ ጤና አገልግሎት እየተተካ የሚሄድበትን እና ሴቶችም በዚህ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሁኔታው ወደተሻሻለ ደረጃ ቢመጣ ጥሩ ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጡን በተመለከተ ዶ/ር ደመቀ ከአይፓስ እንደሚሉት... “...በተፈለገው መልኩ ሁሉም የጤና ተቋማት ይህን አገልግሎት እየሰጡ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በአብዛኛው ስራውን የሚሰሩት ድጋፍ የሚሰጣቸው የጤና ተቋማት ናቸው ፡፡ ስለዚህ በተቻለ አቅም አገልግሎቱ ለሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል ተደራሽ ሚሆንበት መንገድ መመቻቸት አለበት ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁን ጊዜ ወደ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ እና ከዛ በላይ ጤና ተቋማት ቢኖሩም አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ግን ምናልባት ቢበዛ ቢበዛ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ ወይንም ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ደህንነቱን የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ለህብረተሰቡ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም ፋሲሊቲዎች ላይ በሁሉም የጤና ተቋማት አገልግሎት ቢኖር እና ግንዛቤውን አስመልክቶ ህብረተሰቡ ምን ያህል ያውቃል የሚለውን መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ ዶ/ር ጌትነት በቀለ በስተመጨረሻ በሰጡት አስተያየት “...በአገልግሎት አሰጣጣችን በተለይም ደም እየፈሰሳት የምትመጣ ሴት ካጋጠመችን እስዋን ሳንረዳ ወደቤታችን አንሄድም፡፡ ይህ እንግዲህ እናቶች ደህንነቱ ባልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተቻለንን ለማድረግ ነው፡፡ ይህ አሰራር እርግጠኛ ባልሆንም በሌሎችም የሚተገበር ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ሴቶች ገንዘብ ሳይኖራቸው ይህ ችግር ስለሚገጥማቸው ክሊኒኩ በተቻለ መጠን ሁኔታውን እያየ በያዙት ገንዘብ ሳያጨናንቃቸው አገልግሎቱን እየሰጠ ይኛል፡፡

እስዊፍት የሚባል በጎ አድራጊ ድርጅት የጎዳና ልጆች እርዱልኝ እያለ ሲያመጣ የምንቀበል ሲሆን እንዲያውም በሳምንት ሶስት ሰው በነጻ እንዲታከሙ ፈቅደናል፡፡ለዚህ በተላያየ ቦታ ያሉ በዚህ ጉዳይ ችግር የሚገጥማቸው ሰዎች ካሉ እና ይህንን መልእክት የሰሙ መጥተው ቢያናግሩን አቅማችንን ባገናዘበ መልኩ የነፃ አገልግሎት ለመስጠት የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ዶ/ር ደመቀ ደስታ በስተመጨረሻ እንደገለጹት እንደ ውጭው አቆጣጠር በ2008/ የተጠና ጥናት እንደሚያሳየው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለአጠቃላይ የእናቶች ሞት የሚያስከትለው አስተዋፆ ወደ ዘጠኝ ኀ ነው፡፡ በአሀኑ ጊዜም ሌላ ሰፋ ያለ ጥናት በአገር ደረጃ ማለትም በአይፓስ ኢትዮጵያ ፣ጤና ጥበቃ ሚኒስ..ር ፣የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበ ESOG Ethiopian Public Health Association እየተሰራ ሲሆን ይህ ጥናት ሲያልቅ በትክክል በአሁን ወቅት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት ያለውን አስተዋጽኦ ለማወቅ ያስችላል፡፡

           ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለምዕራብ አፍሪካ ቀውስ ፈጣን ምላሽ ካልሰጠ፣ የኢቦላ ወረርሽኝ ተጠቂዎች ቁጥር እስከመጪው ጥር ወር አጋማሽ 1.4 ሚ. ሊደርስ እንደሚችል የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ተነበየ፡፡ ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት በኢቦላ እየተጠቁ እንደሆነ የጠቆመው ማዕከሉ፤ እስካሁን በቫይረሱ ተጠቅተዋል ተብሎ ከተነገረው በ2.5 እጅ የሚልቁ ተጠቂዎች እንዳሉ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡

በቅርቡ የተጀመረው ዓለምአቀፍ እርዳታ ከቀጠለ ግን ይሄ አስከፊ ሁኔታ ሊቀለብስ ይችላል ብለዋል - የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ቶም ፍሪይዴን፤ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በምዕራብ አፍሪካ 5800 የሚገመቱ ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን ከ2800 በላይ ሞተዋል፡፡ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል አዲሱ ሞዴል፤ የገዳዩን ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የኢቦላ በሽተኞችን ከጤነኞች መነጠል ባለው ፋይዳ ላይ ያተኩራል፡፡

እስካሁን የኢቦላ ተጠቂዎች ቁጥር በሁለቱ አገራት በየ20 ቀኑ በእጥፍ እየጨመረ እንደሆነ የጠቆመው ማዕከሉ፤ ለዚህም ምክንያቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከጤነኞች ጋር ባላቸው ንክኪ በቫይረሱ ስለሚበክሏቸው ነው ብሏል፡፡ ከአስሩ የኢቦላ በሽተኞች ሰባቱ በቤታቸው ወይም በህክምና ማዕከል ውስጥ ተነጥለው እንዲቀመጡ ቢደረጉ፣ በላይቤሪያና በሴራሊዮን ያለው ወረርሽኝ በጥር ወር አጋማሽ ላይ ሊገታ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ የመከላከያ ኃይል እንዲሁም ዩኤስኤይድ በምዕራብ አፍሪካ ገንዘብና የሰው ሃይላቸውን እያፈሰሱ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አገራትም የዚ ጥረት አካል እንደሆኑ የፕሁሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ልዩ ረዳትና የብሔራዊ ደህንነት ም/ቤት ከፍተኛ ዳይሬክተር ጋይሌ ስሚዝ ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዓለምአቀፍ የእርዳታ ጥረቶች እየጨመሩ ቢመጡም፤ ቫይረሱ ግን ስርጭቱን ቀጥሏል ያለው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ከችግሮቹ አንዱ በበሽታው ክፉኛ በተጠቁት ጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን በቂ የሆስፒታል አልጋዎች እንዲሁም የጤና ሰራተኞች፣ ወይም ሳሙናና ውሃ ሳይቀር አለመኖሩ ነው ብሏል፡፡

            ሥራዬን ላጣ እችላለሁ የሚል ስጋትና ጭንቀት በአስም የመያዝ አደጋን ሊጨምር እንደሚችል በአውሮፓ የተደረገ አዲስ ጥናት አመለከተ፡፡ ጥናቱ በጀርመን የሚገኙ ከ7ሺ በላይ ተቀጣሪ ሠራተኞችን ያሳተፈ እንደነበር ታውቋል፡፡ እነዚህ ተሳታፊዎች አውሮፓ የኢኮኖሚ ድቀት ባጋጠማት ወቅት (እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም) ስለመተንፈሻ አካላት መዛባትና በሁለት ዓመት ውስጥ ከሥራችን እንፈናቀላለን ብለው ያስቡ እንደሆነ ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጥናቱ በተካሄደባቸው ጊዜያት ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ከ100 በላይ የሚሆኑት አዲስ የአስም በሽታ እንደተቀሰቀሰባቸው ኸልዝዴይ ኒውስ ጥናቱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ከሥራ ጋር የተገናኘ ጭንቀት በ25 በመቶ ባደገ ቁጥርም በአስም የመያዝ አደጋ በ24 በመቶ እንደጨመረ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ሥራ የማጣት ዕድላችን ከፍተኛ ነው ብለው ያስቡ የነበሩት ተሳታፊዎችም በአስም የመያዝ ዕድላቸው ወደ 60 በመቶ ማሻቀቡን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡በሁለት ዓመት ውስጥ ሥራችንን የማጣት ዕድላችን ዝቅተኛ ነው ወይም ስጋት የለብንም ካሉት ይልቅ ሥራ የማጣት ዕድላችን ከፍተኛ ነው ያሉት በዕድሜ ወጣት፣ በትምህርት ብዙ ያልገፉ፣ ያላገቡና ዝቅተኛ ወርሃዊ ደሞዝ ያላቸው እንደነበሩ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ የስራ ማጣት ያሰጋቸው ተሳታፊዎች፤ ቋሚ የሥራ ኮንትራት የማግኘት ዕድላቸው እጅግ ዝቅተኛና በድብርት ለመሰቃየት የበለጠ የተጋለጡ እንደነበርም ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ የጥናት ውጤቱ ባለፈው ሳምንት “ጆርናል ኦፍ ኢፒዲሞሎጂ ኤንድ ኮሙኒቲ ኸልዝ” ላይ እንደወጣ ተገልጿል፡፡

ጥናቱ፤ ከስራ ጋር የተያያዘ ጭንቀት ለአስም መንስኤ እንደሆነ አላረጋገጠም ይላሉ - ተመራማሪዎቹ፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል በስነልቦና ጭንቀት ላይ የተደረገ ጥናትም ለአስም አደጋ የሚያጋልጥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ደርሰንበታል ብለዋል፡፡ “የጥናት ውጤቱ፤ በኢኮኖሚ ድቀቱ ወቅት ጊዜ በእንግሊዝ የመተንፈሻ አካላት መዛባት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበትን ምክንያትም ሊመልስ ይችላል” በማለት ተመራማሪዎቹ በጆርናሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስፍረዋል፡፡ ይሄ በዚህ እንዳለ የአባቶች አጫሺነት ህፃናትን ለአስም በሽታ እንደሚያጋልጥ በጀርመን የተካሄደ ጥናት ጠቁሟል፡፡ በተለይ አባት የረዥም ጊዜ አጫሽ ከሆነ፣ ህፃኑ በአስም የመያዝ ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ብለዋል - አጥኚዎቹ፡፡ ቀደም ሲል የአባት ማጨስ በህፃኑ ላይ ስለሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ማንም ትኩረት ሰጥቶት እንደማያውቅ ያወሱት ተመራማሪዎቹ፤ አዲሱ ጥናት የእናትየዋን ያህል አባትም በልጅ ጤና ላይ ይሄን ያህል ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ መታወቁ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡

      ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ለረዥም ዓመታት በመንግስት ብቻ ተይዞ በነበረው የአየር መንገድ ስራ ውስጥ የግል ባለሀብቶች መሳተፍ የጀመሩት በቅርቡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን እድል በመጠቀም ወደዘርፉ ከተሰማሩ ጥቂት የግል አየር መንገዶች መካከልም ናሽናል ኤርዌይስ አንዱ ነው፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት የተመሰረተው አየር መንገዱ፤ በዘርፉ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል፣ በ2003 ዓ.ም ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅን የከፈተ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ሰልጣኞችም ባለፈው ነሐሴ ወር አስመርቋል፡፡ ናሽናል ኤርዌይስ እንዴትና በእነማን ተቋቋመ፣ ምን ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል፣ የኮሌጁ አመሰራረትና የስልጠና ሂደቱ ምን ይመስላል በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ ዲን ከአቶ ገዛኸኝ ብሩ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

ስለ ናሽናል ኤርዌይስ አመሰራረት ሊነግሩኝ ይችላሉ? ናሽናል ኤርዌይስ በ2001 ዓ.ም ነው የተመሰረተው፡፡ የመሰረቱትም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አየር መንገድና በሌሎች አገራት አየር መንገዶች በአብራሪነት የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ካፒቴኖች ናቸው፡፡

አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ያወጣውን መስፈርትና መመዘኛ በማሟላት ኤር ኦፕሬተር ሰርተፍኬት ሊያገኝ ችሏል፡፡ በዚህ ሰርተፍኬት መሰረት የኤር አምቡላንስ፣ የቪአይፒ እንዲሁም የካርጎና የቻርተር በረራዎች አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ ቻርተርድ ኩባንያ አገር በቀል ቢሆንም የሚታገዘው በውጭ አገር ባለሙያዎች ጭምር በመሆኑ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የግል አየር መንገድ ለማቋቋም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን የሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች ምንድን ናቸው? በርካታ ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ ከፍተኛ ውጣ ውረድም አለው፡፡ ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለአየር መንገዱ የሚያስፈልጉ ክራፍቶችን ማሟላት፣ የውስጥ አሰራርና አደረጃጀትን ማጠናከር እንዲሁም በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከሚጠየቁት መስፈርቶች አንዱ ነው፡፡

ዘርፉ ትንሽ ከበድ ያለ እንደመሆኑ ከአገር ደህንነት፣ ከበረራ ደህንነትና ከአጠቃላይ ሴኩሪቲ አንጻር የሚደረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄዎች ያሉ ሲሆን ለዚህም በርካታ ነገሮችን ማሟላት የግድ ነው፡፡ በተለይ የገንዘብ አቅም ወሳኝ ነው፡፡ መስፈርቶቹን ለማሟላት የግድ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ናሽናል ኤርዌይስ እንግዲህ እነዚህን አሟልቶ ነው የተመሰረተው፡፡ የበረራ አገልግሎታችሁ በአገር ውስጥ የተገደበ ነው ወይስ ወደ ውጭም ትበራላችሁ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፤ የቪአይፒ እና የአንቡላንስ አገልግሎቶችን በአብዛኛው በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ነው የምንሰጠው፡፡ ከዚያ ውጭ ቻርተርድ በረራዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት መንገደኞችን ይዞ መጓዝ ነው፡፡ በብዛት የአገር ውስጥ በረራ እንሰራለን፡፡ ወደ ጎረቤት አገሮች ለምሳሌ ሶማሌላንድ፣ ጁባ፣ ናይሮቢና መካከለኛው አፍሪካ ድረስ የመብረር አቅም አለን፡፡ አየር መንገዱ በተለያዩ ኢትዮጵያዊያን አብራሪዎች መቋቋሙን ነግረውኛል፡፡ በዋናነት የሃሳቡ ጠንሳሽ ማን ነው? ሀሳቡን በመጠንሰስ እውን እስኪሆን ድረስ ተነሳሽነቱን የወሰዱት ካፒቴን አበራ ለሚ ይባላሉ፡፡ እኚህ ኢትዮጵያዊ ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ አየር መንገድን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ አየር መንገዱን ከሌሎች ሰዎች ጋር ካቋቋሙ በኋላ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት በማጤን ኮሌጁ እንዲመሰረት ሃሳብ ያፈለቁትም ካፒቴን አበራ ናቸው፡፡

እኚህ ሰው ድርጅቱን በመምራትና በማስተባበርም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ የመነሻ ካፒታላችሁ ምን ያህል ነው? በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱ ምን ያህል አውሮፕላኖች አሉት? ኢንቨስትመንቱ በጣም ከባድ ነው፤ አሁን እንዲህ ነው እንዲህ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እንኳንስ አንድ የግል አየር መንገድ ለመክፈት ቀርቶ አንድ አነስተኛ ምግብ ቤት ለመክፈት እንኳ ምን ያህል ፈተና እንዳለው ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በቁጥር ማስቀመጡ አስፈላጊ መስሎ ባይታየኝም እጅግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ልደብቅሽ አልችልም፡፡ ምን ያህል አውሮፕላኖች አላችሁ ለሚለው፣ አንድን አየር መንገድ ለማቋቋም የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላንባቸውን ያህል አሉን፡፡ አንዳንዴ ስራ ሲበዛና የእኛ ጥገና ላይ ሲሆኑ የሌሎችን የምንጠቀምበት ሁኔታ አለ፡፡ የካፒታል መጠኑንና የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ለመግለፅ ያልፈለጋችሁበት ምክንያት አልገባኝም… ወደፊት ይፋ እናደርጋለን፡፡ አሁን በራሳችን ምክንያት ግልፅ ማድረጉ አስፈላጊ መስሎ ስላልታየን ነው፡፡ እሺ-- ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ እንዴት ነው የተመሰረተው? ኮሌጁን የመሰረተው ናሽናል ኤርዌይስ ነው፡፡ የተመሰረተበት ምክንያት የናሽናል ኤርዌይስ ሰዎች አየር መንገዱን ከመሰረቱ በኋላ፣ በአገር ደረጃ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት እንደነበረ በመረዳታቸው፣ ለምን ኮሌጅ ከፍተን ችግሩን አናቃልልም በማለት ነው የመሰረቱት፡፡ እንደሚታወቀው የአቪየሽን ዘርፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እጅግ እያደገ ያለ ዘርፍ ነው፤ ሆኖም በአገራችን ብዙ ባለሙያዎች የሉም፡፡

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለራሱ የሚያሰለጥናቸው የአቪየሽን ባለሙያዎች አሉት፡፡ በግል ደረጃ ግን ከዚህ በፊት የለም፡፡ በመሆኑም ካፒቴን አበራ ለሚ ሃሳቡን ካዳበሩ በኋላ፣ ይህን የባለሙያ ችግር ለመቅረፍ ኮሌጁ ተቋቋመ፡፡ የመጀመሪዎቹ 140 ያህል ሰልጣኞችም ነሐሴ 3 ቀን ለምርቃት በቅተዋል፡፡ ኮሌጃችሁ በአቪየሽን ዘርፍ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች ምን ምን ናቸው? በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ስልጠና ለመስጠት ፈቃድ ስንጠይቅ፣ዘርፉ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ነው የተመደበው፡፡ ስልጠናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና ሰልጣኞቹ የትኛውም ዓለም ቢሄዱ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቀውና ካናዳ ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ኤር ትራንስፖርት አሶሴሽን (IATA) ጋር ለመስራት ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ የቆየን ሲሆን አሁን ተሳክቶልናል፡፡ አያታ የራሱ መስፈርትና መመዘኛ አለው፤ ያንን አሟልተን በእነሱ የተፈቀደልን የስልጠና ማዕከል ለመሆን ችለናል፡፡ በዋናነት በበረራ አስተናጋጅነት፣ ትኬቲንግ እና ሪዘርቬሽን፣ በካርጎ፣ በኤርፖርት ኦፕሬሽን ኤርላይን ከስተመር ሰርቪስና ሌሎች ዘርፎች ስልጠና እንሰጣለን፡፡ ሰልጣኞቻችን በአገር ደረጃ መስፈርቱን አሟልተው ከሰለጠኑ በኋላ፣ አያታ በአመት አራት ጊዜ ፈተናዎችን ይሰጣቸዋል፤ ያንን አሟልተው ሲገኙ አለም አቀፍ የምስክር ወረቀትና ዲፕሎማ ያገኛሉ፡፡

የመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎቹ በዚህ መልኩ ነው የተመረቁት? አዎ! በዚህ መልኩ ነው የተመረቁት፡፡ እነዚህ ልጆች ሰርተፍኬታቸውንና ዲፕሎማቸውን ይዘው የትኛውም ዓለም ላይ በሰለጠኑበት ዘርፍ መስራት ይችላሉ፡፡ ኮሌጃችሁን ለማሳደግና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመሸጋገር ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማችሁን ሰምቼ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ… እስካሁን በዘርፉ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ስልጠና ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ስናጠና ቆይተናል፡፡ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረምነው ከሶስት የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው፡፡ እነዚህን ዩኒቨርሲቲዎች የመረጥንበት ምክንያት በዘርፉ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት የሚታወቁ በመሆናቸው ነው፡፡ ክፍያቸው ተመጣጣኝና ከሌላው የተሻለ መሆኑ ሌላው ምክንያታችን ነው፡፡ ስለ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችና ስለሚሰጡት የሙያ ስልጠና ሊነግሩኝ ይችላሉ? አንደኛው ቫንጋይ ኤሮስፔስ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ተቋም በቻይና በጣም ግዙፍና ታዋቂ ነው፡፡ በኤሮኔቲካል ኢንጂነሪንግ፣ በኤሮክራፍት ማኑፋክቸሪንግና ዲዛይኒንግ፣ በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ፣ በኤሮክራፍት ቴክኒሺያን፣ በሲቪል ኢንጂነሪንግ… ባችለር ኦፍ አቪየሽን ሳይንስ ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ሊኒዋንግ ዩኒቨርሲቲ የሚባል ሲሆን ተቋሙ በፔትሮሊየም ኢንጂነሪንግ፣ በጋዝ ኢንጂነሪንግ በኢንቫይሮሜንታል ኢንጂነሪንግ… ስልጠና ይሰጣል፡፡ እኛ ፍላጎት በበዛበት ዘርፍ አብረን ስልጠና ለመስጠት አስበናል፡፡ ሶስተኛው ሊኒዋንግሸዋ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ተቋሙ በቢዝነስና ኢኮኖሚ ዘርፎች ለምሳሌ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት፣ በኢንተርናሽናል ትሬድና በመሳሰሉት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጥናሉ፡፡ ከእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረምነው፡፡ ስምምነታችሁ ምን ይመስላል? ወደተግባር ለመግባትስ ምን እየጠበቃችሁ ነው? ስምምነታችን በትብብር ለመስራት ነው፡፡ በአገራችን እነዚህን የስልጠና ማዕከላት ለመገንባት ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይህን ስልጠና ሊሰጡ የሚችሉ መምህራንም የሉንም፡፡

በተጨማሪም ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሟላት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ በትብብር ነው የምንሰራው፡፡ ትብብር ሲባል ለምሳሌ ስልጠናው አራት ዓመት ከሆነ፣ ተማሪዎች ሁለቱን ዓመት እዚህ ሰልጥነው፣ ቀሪውን ሁለት ዓመት በቻይና ሰልጥነው እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ ከዚያ አቅማችንን በማደራጀት የራሳችንን መምህራን ስናፈራና በቂ የስልጠና ማዕከላት ስንገነባ፣ ስልጠናው እዚሁ ተጀምሮ እዚሁ ይጠናቀቃል፡፡ ወደተግባር ለመግባት የምንጠብቀው የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲን እውቅና ነው፡፡ በአቪየሽን ዘርፍ እየሰራን ቢሆንም ከዘርፉ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው የሆቴል ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው በአገራችን እየሰፋና እያደገ ቢሄድም የሆቴል ዘርፍ የባለሙያ እጥረት አለ፡፡ እየተሰጠ ያለው ስልጠናም ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፤ ስለዚህ በዚህም ዘርፍ በአጭር ጊዜ ስልጠና ለመስጠት ኢንተርናሽናል ኮሜርሺያል ማኔጅመንት (ICM) ከተባለ የለንደን ድርጅት ጋር እየሰራን ነው፡፡ ሰልጣኞቹን እንደ አያታ ሰርቲፋይድ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚያም የትኛውም አገር ሲሄዱ ተቀባይነት አግኝተው ይሰሩበታል ማለት ነው፡፡ የከፈታችሁት ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ደረጃ ስልጠና ቢሰጥም በአገራችን እምብዛም የተለመደ ዘርፍ ባለመሆኑ የመምህራን ችግር እንደሚያጋጥማችሁ የታወቀ ነው፡፡

እንዴት ተወጣችሁት? እንዳልሽው መምህራን ማግኘት ፈታኝ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መምህራንን ከኬንያ ማስመጣት ነበረብን፤ ኬንያ በዚህ ዘርፍ የዳበረ ልምድ አላት፡፡ የማሰልጠኛ ተቋማቶቻቸው በመንግስትም በግልም ደረጃ ከኢትዮጵያ በጣም የተሻሉ ናቸው፡፡ ተማሪዎቻችንን ያሰለጠኑልን በአብዛኛው የኬኒያ መምህራን ናቸው፡፡ እነዚህን መምህራን በከፍተኛ ክፍያ ነው ያመጣናቸው፡፡ የኮሚዩኒኬሽንና የስነ-ልቦና ስልጠናዎችን የወሰዱት ግን በአገራችን መምህራን ነው፡፡ እንደስትራቴጂ የያዝነው ከእነዚህ መምህራን ልምድ በመውሰድ፣ከሰልጣኞችም አቅም ያላቸውን በማስቀረት በረጅም ጊዜ ሂደት በአገራችን መምህራን ለመተካት ነው፡፡ ለቀጣዮቹ አራትና አምስት ዓመታት ግን ኢትዮጵያዊ መምህራንን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንዴ እንደውም ናሽናል ኤርዌይስ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችንም ለመጠቀም እንገደዳለን፡፡ እናም በቀጣይ ላሰብናቸው የከፍተኛ ትምህርት ስልጠናዎች ከቻይና መምህራንን ማስመጣት ይኖርብናል፡፡ አሁን ካስመረቃችኋቸው ተማሪዎች ውስጥ ወደ ስራ የተሰማሩ አሉ? አዎ አሉ! ከተመረቁም በኋላ ሳይመረቁም የተቀጠሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ ሶስት ልጆች በበረራ አስተናጋጅ፣ በተለያዩ ዘርፎችም ብዙዎች ተቀጥረዋል፡፡

ዘርፉ የስራ ችግር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ብዙ አየር መንገዶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከፈቱ ነው፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅና ሌሎች አገራት ሄደው እየሰሩ ያሉም አሉ፡፡ ለስልጠናው ብዙ ወጪዎች እንደምታወጡ ነግረውኛል፡፡ ለምሳሌ ፋየር ፋይቲንግ ለማሰልጠን ለሲቪል አቪየሽን ትከፍላላችሁ፡፡ በመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ለማሰልጠን ወደ ቀይ መስቀል፣ ዋና ለማሰልጠን ደግሞ ወደ ትልልቅ ሆቴሎች ትሄዳላችሁ፡፡ የምታስተምሩባቸው መጻህፍትና ሞጁሎች ከውጭ ሲገቡ ይቀረጣሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ለስልጠናው የምትጠይቁት ክፍያ ውድ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነኝ ወይስ ተሳስቻለሁ? አንድ ሰው ወደ ትምህርት ዘርፍ ሲሰማራ፣ኢንቨስት ያደረገውን በአጭር ጊዜ አይመልስም፡፡ እንደ ማንኛውም ንግድ አይደለም፡፡ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ለትምህርት የሚከፈለው ክፍያ በጣም ርካሽ ነው፡፡ ድንገት ተነስተሽ የአቪየሽን ት/ቤት ልክፈት ብትይ አትችይም፡፡ ልጆቹ ብቃት እንዲኖራቸው ከውጭ ተቋማት ጋር ስምምነት ስናደርግም እነ አያታና አይሲኤም የሚያስከፍሉን ክፍያ አለ፡፡ ቅድም ከላይ የገለፅሻቸው ፋየር ፋይቲንግ፣ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ፣ የዋና ስልጠና ወዘተ የምንሰጠው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሲሆን የመማሪያ ግብአቶችን የምናስመጣውም ከውጭ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ስታስቢው አሁን የምናስከፍለው በጣም ትንሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እንደየስልጠናው አይነትና የጊዜ መጠን (ከ6-8 ወር ነው) ትንሹ ክፍያ ዘጠኝ ሺህ ብር ሲሆን ትልቁ ክፍያ 34ሺ ብር ነው፤ ነገር ግን ሰልጣኞች ተመርቀው ሲወጡ የሚቀጠሩት በጥሩ ደሞዝ ነው፤ ተፈላጊም ናቸው፡፡ በዘርፉ ዋና ዋና ፈተናዎች የሚባሉት ምንድን ናቸው? በርካታ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ራሱ በዘርፉ መሰማራት አንድ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በግል ዘርፍ ኮሌጅ ስትከፍቺ፣ የግንዛቤ እጥረት ስላለ በግል ተምረን ማን ይቀጥረናል የማለት አዝማሚያ ነበር፡፡ ይህን ለመለወጥ ብዙ ፈተናዎችን አልፈናል፡፡ ከውጭ የሚመጡ የስልጠና ግብአቶች ከፍተኛ ቀረጥ ይጣልባቸዋል፡፡ ብቻ በርካታ ችግሮች ነበሩ፤ አሁን በሂደት እየተቀረፉ ነው፡፡

            ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበር (ኮካኮላ) ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በገንዘብ ችግር ውጤታቸው እንዳይቀንስ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ ከአዲስ አበባ፣ ከባህርዳርና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረጡ ከ3.0 ነጥብ በላይ ውጤት ላላቸውና ለአነስተኛ ገቢ ቤተሰብ ተማሪዎች፣ለሶስት ዓመት የኪስ ገንዘብ እንደሚሰጥና ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ 1.2 ሚሊዮን ብር መመደቡን የኢትዮጵያ ኮካኮላ የሰው ኃይል ሀብት ማናጀር አቶ አንተነህ ተገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች 30 ሲሆኑ 11ዱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኩባንያው ሰራተኛ ልጆች ሲሆኑ የተቀሩት፣አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች መሆናቸውን የተመረጡበት ዩኒቨርሲቲዎች እንዳረጋገጡላቸው ጠቁመዋል፡፡በቀጣዩ ዓመት 15 ተማሪዎች እንደሚጨመሩና ገንዘቡም ወደ 1.8 ሚ ብር እንደሚያድግ የጠቀሱት አቶ አንተነህ፣ ለተማሪዎቹ በየወሩ 500 ብር የኪስ ገንዘብ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ አንድ ጊዜ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁስ እንደሚሟላላቸው፣ትምህርታቸውን እንዴት እየተከታተሉ እንደሆነ በኩባንያው ኃላፊዎች እንደሚጎበኙ፣ ለመመረቂያ ጽሑፍ ድጋፍ እንደሚደረግና በየዓመቱ መጨረሻ ት/ቤት ሲዘጋ ወደ ኩባንያው መጥተው እንደየትምህርታቸው በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር እንደሚለማመዱ፣ በዚህ ወቅትም ለምግብና ለትራንስፖርት ወጪ የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎቹ በመንግስት 70/30 የትምህርት ፖሊሲ መሰረት፤ ከሳይንስ ዘርፍ የተመረጡ (በአብዛኛው ከኢንጂነሪንግና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) መሆኑን የተናገሩት ማናጀሩ፣ እነዚህ የትምህርት ዘርፎች እነሱም የሚጠቀሙባቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ለ30ዎቹ ተማሪዎች በዓመት ከ400 እስከ 500 ሺህ ብር ወጪ ይደረጋል፡፡ኩባንያው የማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎን ለማጎልበት በጤና፣ በመጠጥ ውሃ፣ በስፖርት… ዘርፎች እየተሳተፈ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አንተነህ፤አሁን በትምህርት ዘርፍ የጀመሩት ተሳትፎ የአነስተኛ ገቢ ቤተሰብ ተማሪዎች፣ከፍተኛ ውጤት እያላቸው በገንዘብ ችግር ትምህርታቸውን እንዳይደናቀፍና ውጤታቸው እንዳይቀንስ በማለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አንተነህ፣ ይህ የኩባንያው እቅድ የሚሳካው በተማሪዎቹ፣ በዩኒቨርሲቲዎቹና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሆነ ገልጸው፣ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡ ባህሪያቸው ያማረና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ፋብሪካዎች ለሶስት ዓመት በሚያደርጉት የተግባር ልምምድ የሚሰጠውን ፈተና በሚገባ የሚያልፉት በኩባንያው እንደሚቀጠሩ አስታውቀዋል፡፡ ቅድስት ታደለና ቤዛዊት ዚያድ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኩባንያው ሰራተኞች ልጆች ናቸው፡፡ ቅድስት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ቤዛዊት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የ2ኛ ዓመት፣ ማተቡ ወርቁ ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ይህን ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዕድሉን ባያገኙ ኖሮ ለተግባር ልምምድ (አፓረንትሽፕ) የሚወጡት 4ኛ ዓመት ሲደርሱ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን ሶስት ዓመት የሚያደርጉት ልምምድ፤ ለእውቀታቸው መዳበርና ለውጤታቸው ማማር በእጅጉ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ችግሩ ከተስፋፋባቸው አገራት አንዷ ናት ተብሏል

          የአለማችን ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልገው የምግብ እህል ከሁለት እጥፍ በላይ ማምረት ቢቻልም፣ አሁንም ድረስ በተለያዩ የአለም አገራት የሚገኙ ከ800 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቂ ምግብ እንደማያገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡ባለፉት አስርት አመታት በአለማችን የርሃብ ችግር በተወሰነ መልኩ ቢቀንስም ባለፉት ሁለት አመታት 11 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ የምግብ እጥረት ተጠቂ እንደነበረ የጠቆመው ዘገባው፣ የምግብ እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚታይባቸው አገራት መካከልም፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ እንደሚገኙበት ገልጿ ል፡፡ በቂ ምግብ የማያገኙ በርካታ ዜጎች ካሏቸው አገራት አንዷ በሆነችው ኢራቅ፤ ከአራት ኢራቃውያን አንዱ የምግብ እጥረት ችግር ሰለባ መሆኑንም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳምንቱ መጀመሪያ ያወጣውን መረጃ በመጥቀስ ዘገባው ጠቁሟል ፡፡

የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዳለው፣ ምንም እንኳን በአለማችን በአሁኑ ወቅት ከሚያስፈልገው የምግብ እህል ከሁለት እጥፍ በላይ ማምረት ቢቻልም፣ ምርቱን ለተመጋቢዎች በማድረስ ረገድ ክፍተቶች በመኖራቸው የምግብ እጥረት ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ ምርታማነት ቢያድግም የተመረተውን የምግብ እህል ለሸማቾችና የችግር ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ማድረስ ካልተቻለ፣ የምግብ እጥረቱ እንደማይቀረፍ የገለጸው ድርጅቱ፣ ለዚህም ሴፍቲ ኔትና ሌሎች የማህበራዊ ዋስትና አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

ከሚሊኒየሙ የልማት ግቦች አንዱ በታዳጊ አገራት የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ዜጎች ቁጥር እስከ 2015 ድረስ በግማሽ መቀነስ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተመድ ሪፖርትም ግቡን ለማሳካት እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ማስታወቁን ጠቁሟል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራትና በመካከለኛው ምስራቅ የሚከሰቱ Yተፈጥሮ አደጋዎችና ግጭቶች፣ የአካባቢው አገራት ግቡን ለማሳካት የሚደርጉትን እንቅስቃሴ እያደናቀፉት እንደሚገኙ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

            ከ500 ሚ. በላይ ኮምፒውተሮችን ሊያጠቃ ይችላል

           በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ500 ሚሊዮን በላይ ኮምፒውተሮችንና ሰርቨሮችን ሊያጠቃ እንደሚችል የተነገረለት ‘ሼልሾክ’ የተባለ እጅግ አደገኛ የኮምፒውተር ቫይረስ ከሰሞኑ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡ የኮምፒውተር ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ይህ አዲስ አይነት አደገኛ ቫይረስ ባሽ ተብሎ በሚጠራውና በበርካታ የሌኑክስና ማክ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች ውስጥ በሚገኘው የሶፍትዌር አካል ላይ ላይ ተሰራጭቶ Yተገኘ ሲሆን፣ ማንኛውንም አይነት ሲስተም በርቀት ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው፡፡

በሱሬይ ዩኒቨርሲቲ የደህንነት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አለን ውድዋርድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ አዲሱ ቫይረስ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ተከስቶ ከነበረው ኸርትብሊድ የተባለ ቫይረስ በእጅጉ የከፋ እና ማንኛውንም የኮምፒውተር ሲስተም ሊቆጣጠር የሚችል ነው፡፡የአሜሪካ የኮምፒውተር አደጋ ዝግጁነት ቡድን፣ ከሰሞኑ የተከሰተውንና በርካታ ድረ ገጾችን ሊያጠቃ እንደሚችል የተነገረለትን ይህን አደገኛ ቫይረስ በተመለከተ ለተጠቃሚዎች አፋጣኝ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ ከቫይረሱ ጥቃት ሊታደጋቸው የሚችለውን ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መክሯል፡፡ የኢንተርኔት ወንጀለኞች ቫይረሱ የሚፈጥረውን ቀውስ በመጠቀም ኦፕሬቲንግ ሲስተሞችን ሊቆጣጠሩ፣ የሚስጥር መረጃዎችን ሊያገኙ፣ በመረጃዎቹ ላይ ለውጥ ሊፈጥሩና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉም ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

            አሜሪካ በድብቅ የያዘቻቸውን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያህል የብሄራዊ ደህንነት ሚስጥሮችና የተለያዩ ድብቅ መረጃዎችን በማውጣት ለአለም ይፋ ያደረገውና በአገሪቱ መንግስት ክስ የተመሰረተበት ኤድዋርድ ስኖውደን፣ ለፕሬስ ነጻነት ባበረከተው አስተዋጽኦ፣ አማራጭ የኖቤል ሽልማት በመባል የሚታወቀው ‘የስዊድን ራይት ላይቭሊሁድ ኦኖራሪ አዋርድ’ ተሸላሚ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ‘ራይት ላይቭሊሁድ ኦኖራሪ አዋርድ ፋውንዴሽን’ ስኖውደን የአሜሪካ መንግስት የዲሞክራሲያዊ ስርአት ሂደቶችንና ህገ መንግስታዊ መብቶችን በሚጥስ መልኩ የምታከናውነውን የመረጃ ክትትል ለማጋለጥ ባደረገው ጥረት ለሽልማቱ መመረጡን አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ሽልማቱን ለስኖውደን ከማበርከቱ በተጨማሪም፣ በቀጣይ ከአሜሪካ መንግስት ለሚገጥመው የወንጀል ክስ ህጋዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የመንግስት ንብረትን መዝረፍ፣ ብሄራዊ የመከላከያ መረጃዎችን በህገወጥ መንገድ ማሰራጨትና የስለላ መረጃዎችን ለማይገባቸው ሰዎች አሳልፎ መስጠት የሚሉ ክሶች ባለፈው አመት በአሜሪካ መንግስት የተመሰረተበት ስኖውደን፤ በዚያው አመት ከአሜሪካ ወጥቶ ወደ ሆንግ ኮንግ፣ ከዚያም ወደ ሩስያ አቅንቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሩስያ መንግስት በተሰጠው ለሶስት አመታት የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ በሞስኮ ይገኛል፡፡ በዘንድሮው ‘የስዊድን ራይት ላይ ቭሊሁድ ኦኖራሪ አዋርድ’፣ስኖውደን ያወጣቸውን መረጃዎች ለህትመት በማብቃት ትብብር ያደረጉት የታዋቂው ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አለን ራስብሪጀርም ተሸላሚ እንደሆኑ ዘገባው አስረድቷል፡፡