Administrator

Administrator

አስከሬኑ እስከ ሰኞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል

ባለፈው እሁድ ሚያዚያ 15፣በሚኖርበት አሜሪካ፣ዳላስ፣ በሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ ያለፈው አንጋፋው የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ሊቅ አሰፋ ጫቦ አስከሬን፣በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባና የቀብር ሥነ ስርአቱም በትውልድ አካባቢው አሊያም በአዲስ አበባ እንደሚፈፀም ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የአሰፋ ጫቦ ትክክለኛ አሟሟት እስካሁን ያልተረጋገጠ ሲሆን ቤተሰቦቹም ለጥቂት ቀናት ታሞ ሆስፒታል መግባቱን እንጂ የሞቱን መንስኤ የሚያረጋግጥ ተጨባጭ የህክምና ማስረጃ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው እሁድ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ህይወቱ ማለፉን በቅርብ ዘመዳቸው በኩል እንደተረዱ፣ብቸኛ ሴት ልጁ እመቤት አሰፋ ለአዲስ አድማስ ገልጻለች፡፡  
ህይወቱ ከማለፉ ጥቂት ቀናት በፊት በየቀኑ በስልክ ይነጋገሩ እንደነበር የጠቀሰችው ወ/ሮ እመቤት፤አባቷ ከጉንፋን በቀር በሌላ በሽታ ታሞ እንደማያውቅ ጠቁማ፣የአሁኑ ህመሙም  ለከፋ ችግር እንደማይዳርገው ነግሯት እንደነበር አስታውሳለች፡፡
የህልፈቱ መርዶ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ የሚገኙ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለመላክ የገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ሲሆን ነዋሪነቱን በአሜሪካ ያደረገው የመጨረሻ ልጁ አለማየሁ አሰፋ፣ እስከ ሰኞ ድረስ አስከሬኑን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቀብር ሥነ ስርአቱ በትውልድ ሀገሩ ጨንቻ ወይም አዲስ አበባ የሚፈጸም ሲሆን እርግጠኛ ቦታው ሲወሰን ይፋ እንደሚያደርጉ
ቤተሰቦቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በ75 ዓመት ዕድሜው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አሰፋ ጫቦ፤ሦስት ወንድና አንድ ሴት ልጅ እንዲሁም ዘጠኝ የልጅ ልጆች እንዳፈራ ለመረዳት ተችሏል፡፡

   በድንገተኛ የልብ ህመም ህይወታቸው ያለፈው የሥነ ህዋ ሣይንስ ተመራማሪውና የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማህበር መስራች የነበሩት ዶ/ር ለገሠ ወትሮ፣የቀብር ሥነ ስርዓት ትናንት በአዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና የሥነ ህዋ ሣይንስ ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር ለገሠ ወትሮ፤ለበርካታ አመታት በሥነ ህዋ ሳይንስ ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የሬድዮ ፕሮግራም በማቅረብም ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚና የአፍሪካ አስትሮኖሚ ማህበር መስራችም ነበሩ፡፡
የአለማቀፍ የአስትሮኖሚ ማህበር አባል የነበሩት ዶ/ር ለገሠ፤460 አመት የቆየውን የጂኦማግኔቲክ ፊልድ ሪቨርሳል እንቆቅልሽን በመፍታት እንደሚታወቁ ተጠቁሟል፡፡

      “ግብፅ በኤርትራ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳላት አናውቅም” - (የውጭ ጉዳይ ሚ/ር)

   የሳኡዲ መንግስት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ህገ ወጥ ያላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች ሀገሪቱን በ90 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን አዋጅ ተከትሎ በየቀኑ እስከ 400 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ ነው ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያውያኑ መዘናጋት አሳሳቢ የነበረ ሲሆን አሁን በተፈጠረው ግንዛቤ፣የምህረት አዋጁን በመጠቀም ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ ለሚመለሱ ዜጎች 21 ዓይነት የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ መንግስት መፍቀዱን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡  ከሳኡዲ በአጠቃላይ 100 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ይመለሳሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን መንግስት ለተመላሽ ዜጎች ምን ያዘጋጀው የስራ እድል እንዳለ ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፤ “ጉዳዩ ለኛም ዱብእዳ ነው የሆነብን፤አዋጁ ይታወጃል ተብሎ አልታሰበም፤ነገር ግን ከክልሎች ጋር በመነጋገር የሥራ እድሎች በሚመቻቹበት ዙሪያ ምክክር ተደርጓል” ብለዋል፡፡ ከሳኡዲ ተመላሾች በአገር ውስጥ የተጀመረው የስራ እድል ማስፋፊያ ተቋዳሽ እንደሚሆኑም ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዜጎችን ከሳኡዲ የመመለስ ጉዳይ ብሄራዊ ጉዳይ ተደርጎ መወሰዱን ጠቁመው ሁሉም የመንግስት አካላት በችግሩ ላይ እየተረባረቡ ነው ብለዋል። ችግሩ ድንገተኛ እንደመሆኑ ከድንገተኛነቱ ጋር የሚመጣጠን ስራ እየተሰራ ነው ሲሉም አክለዋል፤ ቃል አቀባዩ፡፡  በሌላ በኩል ግብፅ በኤርትራ 30 ሺህ የሚደርስ ጦር ለማስፈር እንቅስቃሴ ጀምራለች መባሉን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ መለሰ፤”መገናኛ
ብዙኃን ስለ ጉዳዩ ከሚያቀርቡት ዘገባ ውጭ ግብጽ በኤርትራ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳላት አናውቅም” ብለዋል።

      በ2025 በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ 10 ምርጥ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን እየተጋ መሆኑን የሚገልፀው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ትናንት በሂልተን ሆቴል ባደረገው የብራንድና የንግድ ስያሜ ትውውቅ፤ ለ22 ዓመታት ሲጠቀምበት በነበረው የብራንድና የንግድ ስያሜ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቁ፡፡
የባንኩ የቢዝነስና ኦፕሬቲንግ ሞዴል መቀየሩን፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት በአዲስ መልክ መዋቀሩን፣ አዲስ የደንበኞች አመዳደብና አገልግሎት አሰጣጥ መዘጋጀቱን የጠቀሱት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፤ በባንኩ ሎጎ ወይም አርማና ቀለሞች ላይ ማሻሻያ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
አብዛኛው ኅብረተሰብና የባንኩ የቅርብ ባለድርሻ አካላት ባንኩን የሚጠሩት ‹‹አዋሽ ባንክ›› በማለት ስለሆነ የባንኩ ሕጋዊ የመዝገብ ስሙ ‹‹አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ›› ሆኖ እንዲቀጥል፣ የንግድ ምልክት ስያሜው ‹‹አዋሽ ባንክ›› ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
የባንኩ የኮርፖሬት ቀለሞች በሁለት ሙሉ ቀለም ማለትም ጥልቅ ሰማያዊና ብርቱካናማ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ አዲሱን ብራንድ የማስተዋወቅ ሥራ  በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በተለያዩ ጋዜጦች እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በ486 መሥራች ባለአክስዮኖች፣ በ23.1 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል፤ በ1987 ዓ.ም የተመሰረተው አዋሽ ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ3,600 በላይ፣ የባንኩ ካፒታል 2.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅላላ ሀብቱ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን፣ ተቀማጭ ገንዘብ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ፤ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን፤ በቅርንጫፎች ብዛትም ከ293 በላይ መድረሱን አቶ ፀሐይ

ሺፈራው አስታውቀዋል፡፡
አዋሽ ባንክ በአሁኑ ወቅት በጠቅላላ ሀብት፣ በካፒታል መጠን፣ በተቀማጭ ገንዘብ፤ በብድር፣ በትርፍ፣ በቅርንጫፎች ብዛትና በተለያዩ መስፈርቶች

የግል ባንኩን ኢንዱስትሪ እየመራ ነው ተብሏል፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በገጠር የሚኖር የናጠጠ ሀብታም ልጅ፤ የንጉሡን ልጅ ለማግባት ፈልጎ፤ ወደ ንጉሡ ከተማ ሽማግሌዎች ይልካል፡፡ የፋሲካ ማግሥት ነው ዕለቱ፡፡ ሽማግሌዎቹ ተፈቅዶላቸው ግቢ ይገባሉ፡፡ ንጉሡን ጨምሮ ልዑላኑና መኳንንቱ ተቀምጠዋል፡፡
ሽማግሌዎቹ ገብተው ከፊት ለፊት ቆሙ፡፡
‹‹ተቀመጡ እንጂ›› አሉ ንጉሡ፡፡
‹‹የለም፡፡ ጥያቄ አለንና፣ ጥያቄያችን ሳይመለስልን አንቀመጥም›› አሉ ሽማግሌዎቹን
‹‹መልካም፤ ጥያቄያችሁን እንስማ!›› አሉ ንጉሡ፡፡
ከሽማግሌዎቹ ጠና ያሉት ተነሱና፤
‹‹የመጣነው ልጃችሁን ለልጃችን ለጋብቻ ለመጠየቅ ነው፡፡ ፈቃዳችሁ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡››
‹‹ከየት ነው የመጣችሁት ከማንስ ቤተሰብ ነው የመጣችሁት?››
ሽማግሌው፤
‹‹ቤተሰባችን ጨዋ፣ የደራ የኮራ፣ ልጃችን የታረመ የተቀጣ፣ ምሁር ነው፡፡ የቤተክህነት ትምህርት  ጠንቅቆ ያቃል፡፡  የደጃች እከሌ ቤተሰብ ነን፡፡ ከሩቅ ገጠር ከለማው ቀዬ ነው የመጣነው፡፡ በማናቸውም መንገድ ከእናንተ ቤተሰብ ምንም ዓይነት ዝምድና እንደሌለ አጥርተን አውቀናል››
ንጉሡ፤
መልካም፡፡ ከሩቅ አገር መምጣታችሁን ገምተናል፡፡ ስለዚህ ብዙ አናመላልሳችሁም፡፡ እዚህ አካባቢ ቆየት ብላችሁ ተመለሱ፡፡ ልጃችንን እናናግራት፡፡ ዘመድ አዝማዱንም እናማክርና ጥያቄም ካለ ይቀርብላችኋል፡፡ እንደሚታወቀው ልጃችን ጠቢብ ናትና የምትጠይቀው አታጣም›› አሉ፡፡
ሽማግሌዎቹ እጅ ነስተው ወጡ፡፡ ከሰዓት በኋላ ተቀጥረዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ በየዘመድ አዝማድ ዘንድ እህል ውሃ ሲሉ ቆይተው፣ በተቀጠረው ሰዓት ተመልሰው መጡ፡፡ አሁን ጠርቀም ያለው የቤተሰብ ዘርፍ እልፍኝ ተሰባስቧል፡፡
ንጉሱ፤
‹‹አገር ሽማግሌዎች አጣደፋችሁንኮ፡፡ ዋናው ጉዳይ የእኛ ፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን የልጃችንም መቀበል ነው፡፡ ልጃችን ጥያቄ አቅርባለች፡፡ ጥያቄዋም፡- ‹እኔ ላገባው የምችለው ወንድ፣ ለእኔ ያለው ፍቅር፤
1ኛ/ እንደ እናቴ መቀነት
2ኛ/ እንደ አባቴ ጥይት
3ኛ/ እንደነብስ አባቴ ማተብ
ከሆነ ነው፡፡ የዚህን ፍቅር ፍቺ በወጉ ከተረዳ እሺ ብላለች በሉት” ብላናለች፡፡
እንግዲህ የዚህን ፍቺ በሁለት ቀን ውስጥ ከላከና የገባው ከሆነ ታገባዋለች” አሉ ንጉሡ፡፡
ሽማግሌዎቹ፤ “በሁለት ቀን መልስ ይዘን እዚሁ እንገኛለን” ብለው ሄዱ፡፡
በሁለተኛው ቀን ቤተ - መንግስት ቀረቡ፡፡
ንጉሡ፤
“እህስ ሁነኛ መልስ ይዛችሁልን መጣችሁ?”
ሽማግሌ፤
“አዎን፤ ንጉሥ ሆይ!”
ንጉሥ፤
“በሏ እንስማችሁ?”
ሽማግሌው ተነስተው፤
“ልጃችን ለአንደኛው ጥያቄ ያለው መልስ፡- የእናቴ መቀነት ማለቷ - የእናት መቀነት ተፈትሎ፣ ተከሮ፣ ተሸምኖ ነውና መቀነት የሚሆን ሥራ ወዳድ መሆኑን ፈልጋለች፡፡
አንድም ደግሞ እናት ሁሉን ዋጋ ያለው ነገር የምታኖረው መቀነቷ ውስጥ በመሆኑ ገንዘብና ንብረት ያዥና ቆጣቢ መሆን ያለብኝ መሆኔን ማመላከቷ ነው፤ ብሏል፡፡
ሁለተኛው ጥያቄዋ አዳኝ መሆኔን፣ ተኳሽ መሆኔን፣ ጀግና መሆኔን እንደምትወድ ስትገልፅልኝ ነው፡፡
ሶስተኛው ጥያቄዋ፤ ለትዳራችን ሁለታችንና ሁለታችን ብቻ ወሳኝ መሆናችንንና አንዳችን የአንዳችንን ምስጢር እንደነብስ አባት መጠበቅ እንዳለብን መንገሯ ነው፡፡
እኔ ደግሞ ሶስቱንም አክባሪ ነኝ” ብሏል አሉ፡፡
ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡
“በቃ ልጃችንን ለልጃችሁ ፈቅደናል፡፡ ወደገበታው እንቅረብና የምስራቹን፣ ቤት ያፈራውን እንቅመስ!” አሉ፡፡ ፋሲካው ደመቀ፡፡
*   *   *
በየትም ጊዜ፣ በየትም አገር ከውጣ - ውረድ ነፃ የሆነ ነገር የለም፡፡ ያለሥራ፣ ያለቁጠባ፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ያለ አላሚ - ተኳሽና ጀግና፣ ቤቱን አስከባሪ፣ ድንበሩን አክብሮ - አስከባሪ፤ በመጨረሻም የአገሩን ምሥጢር አክባሪ መሆን፤ ትዳርን በሀገር ለመተርጎም ለቻለ ሁሉ ወሳኝ ነው! እንደምን ቢሉ - የሀገር ምሳሌ ቤተሰብ ነውና!
ቤተሰብ በፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ይጀመርና እንደባህሉ በህግ ይታሰራል፡፡ እንደባህሉ ተከባብሮ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ፣ ግጭት ቢፈጠር ተወያይቶ፣ ችግርን ፈቶ፣ በእኩልነት የመተዳደርን ባህል አዳብሮ በፍቅር ይዘልቃል፡፡ ልጆች ቢወለዱም በዳበረው ልማድና ባህል ውስጥ መተዳደሪያቸው ተቀምሮላቸው፣ በግብረገብነት ታንፀው እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ ለአቅመ-አዳም ወይም ለአቅመ - ሄዋን ሲደርሱ ከቤተሰብ ወጥተው  ቤተሰብ ይመሰርታሉ፡፡ የራሳቸውን ደምብና ሥርዓት አበጅተው ህይወትን ይቀጥላሉ፡፡ የመተዳደሪያ ደምብ፣ የኢኮኖሚ ይዞታ፣ የልጅ አስተዳደግና ሥነ ምግባር ደምብ፣ የኢኮኖሚ ይዞታ፣ የልጅ አስተዳደግና ሥነ ምግባር፣ ከጎረቤት ጋር ያለ ባህላዊ ግንኙነት፣ የጤናና የትምህርት ሁኔታ፤ ወዘተ በቤተሰብ ውስጥ የምናያቸው ሥርዓተ-አኗኗሮች ሁሉ የአንድ አገር መንግሥት መዋቅር መሰረት ናቸው፡፡ በተለይ የኢኮኖሚ ሁኔታው እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን በቅርብ ተከታትሎ መሰረቱ እንዳይናድ፣ እንዳይመዘበር፣ ሥርዓት እንዳያጣ ተጠንቅቆ መምራት የአስተዳደሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አስተዳደሩ የፖለቲካው ዋና መዘውር ነው፡፡ ፖለቲካ የኢኮኖሚው አቅም ጥርቅም ገፅታ ነው (politics is the concentrated form of the economy) እንዲሉ ፈረንጆቹ) ቀለል አድርገን ብናየው “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንደምንለው ይሆናል፡፡ ኢኮኖሚው ሲበላሽ ፖለቲካው መናጋቱ፣ ህዝብ ጥያቄ ማንሳቱ፣ አመራሩ ሁነኛ መልስ ካልሰጠ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ፣ የመሰረታዊ ለውጥ አስፈላጊነት (Radical change) እየጎላ መምጣቱ አይቀሬ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በታሪክ እንደታየው ማንኛውም አመራር አካል በቸገረው ሰዓት፤ ሰዎችን ከመዋቅር መዋቅር ለመለወጥ ይሞክራል፡፡ ያ ካልተሳካ የመዋቅሩን ደም-ሥር እንዲመረምር ይገደዳል፡፡ ፍትሐዊ ሂደት መኖር አለመኖሩን ያጣራል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መኖር አለመኖሩን ይፈትሻል፡፡ መልካም አስተዳደር ሰንሰለታዊ ባህሪ አለው (Chain Reaction እንዲል መጽሐፍ) ለምሳሌ የመልካም አስተዳደርን ጉዳይ ብቻ ነጥለን እንመታለን ብሎ ማሰብ ከደን ውስጥ አንድ ዛፍ መፈለግ ዓይነት ነው፡፡ ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ተቋማዊ ብቃት፣ ባህላዊና ልማዳዊ አካሄድ፣ የአገር ሉአላዊነት፣ የአዕምሮ ውጤቶች አያያዝ፣ ማህበራዊና ሥነ ምግባራዊ ዕድገት ወዘተ ሁሉ በስፋትና በጥልቀት ሲኬድባቸውና ሲታዩ የመልካም አስተዳደር መጋቢ መንገዶች ናቸው፡፡ ድርና ማግ ናቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ ፍሬ አያፈሩም፡፡ ወንዝ አያሻግሩም፡፡ እነዚህን ሁሉ በወግና በሥነ ሥርዓት ቀንብቦ ለመያዝ በህግ የበላይነት አምኖና ተማምኖ መመራት ያስፈልጋል፡፡ “በህግ አምላክ” የማይባልበት አገር ዜጋ ተከባብሮና ሥርዓት ይዞ ለመኖር ያዳግተዋል፡፡ ሰላሙን በቀላሉ አያገኝም፡፡ የህግ የበላይነት የእኩልነት መቀነቻ ነው፡፡ የተገነባው እንዳይጠቃ፣ ዘራፍ - ባይ ቆራጭ ፈላጭ እንዳይፈጠር፣ ቀና ብለን የምናየው የህግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡ መኖሩን የሚያሳይ ተግባርም መታየት አለበት፡፡ የህግ የበላይነት በሥራ ተተርጉሞ ካልታየ ባዶ ነው፡፡
ከላይ ያነሳናቸው ፍሬ - ጉዳዮች እየተሟሉ ሲሄዱ የአገር ተስፋ ይለመልማል፡፡ ሆኖም ልምላሜው የሚገኘው በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ ተተኝቶ አይደለም፡፡ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ ውጣ ውረድ፣ አቀበት ቁልቁለት የበዛበት እሾሃማ መንገድ ነው፡፡ አንዴ ልምራው ተብሎ ከተገባ እሾኩን እየነቀሉ፣ አበባውን እየጠበቁ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ የነብርን ዥራት ከያዙ አይለቁም ነው ነገሩ፡፡ በመሰረቱ ለዘመናት በችግር የተተበተበችን አገር ውስብስብ ህልውና፤ በአንድ ጀንበር ማቅናት አይቻልም፡፡ ስኬታማነት ሊኖር ይችላል፡፡ ግን መሰናክሎችም አብረውት አሉ፡፡
“ችግር አለ፡፡ ችግሩንም ለመናገር ችግር አለ” በሚባልበት አገር ስኬት ብቻ ነው የሚታየኝ ማለት ወይ ሆነ ብሎ ዐይንን መጨፈን ነው፡፡ አሊያም “የፋሲካ ዕለት የተወለደች ሁል ጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” የሚለውን ተረት ውስጠ - ነገር አለመገንዘብ ነው፡፡ ከችግሩ ሁሉ ወጥተን ትንሳኤ እናገኝ ዘንድ በሁሉም ረገድ መልካም ትንሣኤ ይሁንልን፡፡  

Saturday, 15 April 2017 13:26

የ “ሥጋ ነገር …”

 በአለማቀፍ ደረጃ በሥጋ ፍጆታቸው አርጀንቲና፣ ኡራጋይ፣ ብራዚል፣ አሜሪካና አውስትራሊያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ቬትናም፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ቱርክና ኢንዶኔዢያ  የሥጋ ተመጋቢነት ባህል ስለሌላቸው ዝቅተኛ የስጋ ፍጆታ የሚጠቀሙ የዓለም ሀገራት መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
አብዛኛው አፍሪካዊ ሥጋ የመብላት ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም በአቅም ውስንነት ፍላጎቱን ማሟላት እንደማይችል ይኸው የፋኦ ጥናት የሚጠቁም ሲሆን አንድ ዴንማርካዊ በአመት 145 ኪ.ግ ሥጋ ሲመገብ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በአማካይ 8.9 ኪ.ግ ሥጋ ብቻ  በዓመት ይመገባል ይላል፡፡
ዜጎቻቸው ሥጋ መመገብ ብርቃቸው ካልሆነባቸው ሀገራት ኩዌት፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ ተጠቃሾች ሲሆኑ አንድ ሰው በአማካይ ከ110 ኪ.ግ እስከ 120 ኪ.ግ ሥጋ በዓመት ይመገባል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ13 ቢሊዮን እስከ 33 ቢሊዮን ዶላር የሥጋ ሽያጭ በማከናወን የሚታወቁ ኩባንያዎችም የሚገኙት በእነዚህ ሥጋ የዘወትር ቀለባቸው በሆኑ ሃገራት ነው፡፡
45 በመቶ ቻይናውያን  ከ5 እና 6 አመት በፊት የነበረው ሥጋ የመመገብ ፍላጎታቸውና አቅማቸው ወደ 80 በመቶ እያደገ መምጣቱ ተጠቁሟል፡፡
የአሜሪካውያን የሥጋ ፍላጎት በአንፃሩ በ5 አመት ውስጥ በ9 በመቶ ያሽቆለቆለ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በማህበረሠቡ ፅዩፍ የሆነው የፈረስ ሥጋ በሱፐር ማርኬት ከሌሎች ሥጋዎች ጋር እየተቀላቀለ ለሽያጭ ይቀርባል የሚለው አሉባልታ ነው ተብሏል፡፡
በአለም ሃገራት ሥጋ የመመገብ ባህል ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የአሣማ ሥጋ ነው፡፡ በአመት እስከ 3 ትሪሊዮን አሣማዎች የሚታረዱ ሲሆን አብዛኛው የአለም ህዝብም ይመገባቸዋል ተብሏል፡፡ በዓለም ላይ በዓመት ከ60 ትሪሊዮን ዶሮዎች በላይ የሚታረዱ ቢሆንም ከአሣማ አንፃር ተመጋቢዎቻቸው ውስን ናቸው፡፡ ከ300 ሚሊዮን ከብቶች በላይ እየታረዱ በየአመቱ ለሥጋ ተመጋቢዎች እንደሚቀርቡም የፋኦ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ እንደ አዲስ እየተለመደ የመጣው የባህር እንስሳትን እና የተለያዩ ጥቃቅን ነፍሳትን የመመገብ ባህል መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡

Saturday, 15 April 2017 13:23

ዝክረ ጃጋማ ኬሎ

  ከአዘጋጁ ፡-
    ታላቁ አርበኛ ሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ስነ ስርዓታቸውም ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞችና በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ
ነዋሪዎች በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን መከናወኑ
ይታወሳል፡፡

                 ኦፈን ያ ጃጋማ!!
ኦፈን ያ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ጣሊያን ግራ ገባው መብረቅ አይጨበጥ
ሲያስገመግም እንጂ አይታይ ሲያደፍጥ
ከቶ ምን ፍጥረት ነው እንዲህ የሚያራውጥ!!
ደንዲ አፋፉ ላይ ታይቷል ሲባል ጀግናው
ግንደበረት ወርዶ ጣልያንን አጨደው።
በቡሳ አቋርጦ… በሺ ላይ አድፍጦ
ዱከኖፍቱ አድሮ ጨሊያ ላይ ማልዶ…
ቦዳ አቦን ተሳልሞ ጊንጪ ላይ ብቅ አለ
በጠራራ ፀሐይ መብረቁን ነደለ።
‘ካፒቴኖ ጃጋማ… ካፒቴኖ’ ጣሊያን ቢማፀነው
አገሬን ሳትለቅ ሰላም የለም አለው።
ተመለስ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ባንዳ ተልከስክሶ ለጠላት ሊሸጣት
አገሬን ሲያስማማት
ክብሬን ሊያዋርዳት
‘ኢንተኡ ፣ ዲዴ’ ብሎ ጃጋማ ካለበት
በቁጣ ገንፍሎ መብረቁን ጣለበት።
ጠላትሽ ኢትዮጵያ ማደሪያ የለውም
የጃጋማ መብረቅ ምቾት አይሰጠውም።
የጠላት ጦር ሰፈር በጭንቅ ተሽመድምዶ
በጠራራ ፀሐይ መብረቅ መጣል ለምዶ
ጃጋማ ጃጋማ ጃጋማ ተወልዶ!!!
ኦፈን ያ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
         (ከታሪኩ አባዳማ ሚያዝያ 1 ቀን2009)
(ምንጭ፡- ጃጋማ ኬሎ - የበጋው መብረቅ/ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ)

የወለጋ፣ የሐረርና የቦረና ከብቶች ዘንድሮ ወደ አዲስ አበባ አልገቡም

በአቃቂ ለ12 ዓመታት በበሬና በበግ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ አስቻለው ሽመልስ፤ ከዓምናው የትንሳኤ በዓል ገበያ አንፃር ሲታይ የዘንድሮው በከብቶች ጥራትም ሆነ በዋጋ የተሻለ ነው ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዓምና በሬ አምራች በሆኑ እንደ አርሲና ሐረር አካባቢዎች፣ ድርቅ በመከሰቱ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡  ማተሚያ ቤት እስገባንበት ሐሙስ ድረስ በአቃቂ ባደረግነው የገበያ ቅኝት፤ መካከለኛ በሬ ከ8 ሺህ - 11 ሺህ ብር፣ ትልቅ በሬ  እስከ 30 ሺህ ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ የበግ ዋጋ ከወትሮው እምብዛም የዋጋ ጭማሪ ያላሳየ ሲሆን ትንሹ 1ሺ 200 ብር፣ሙክት የሚባለው እስከ 8 ሺህ ብር እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ ገበያ ዶሮ ከ300 ብር እስከ 350 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ በሾላ ገበያ ደግሞ በግ ከ1800 ብር  - 3100 ብር
እየተሸጠ ሲሆን በበዓሉ ዋዜማ የከብቶች ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
እዚያው ሾላ ሌሎች የበዓል ገበያዎችን እንመልከት፡- ቀይ ሽንኩርት በኪሎ፡- ከ10-12 ብር፣ ቲማቲም 15 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 60 ብር እየተሸጡ ሲሆን ቅቤ በኪሎ ከ160-250 ብር፣ ዶሮ ከ190-300 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አይብ በኪሎ ከ45-55 ብር፣ እንቁላል ከ3.50 እስከ 3 ብር ከ75 የሚገኝ ሲሆን የተፈጨ በርበሬ በኪሎ፡- ከ140 ብር እስከ 155 ብር ይሸጣል፡፡ የዳቦ ዱቄት በመደበኛ ሱቆች 1ኛ ደረጃ የሚባለው ኪሎው 14 ብር
እየተሸጠ ሲሆን በተለያዩ የሸማች ማህበራት ሱቆች በኪሎ እስከ 8 ብር እንደሚሸጥ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሆኖም በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ፣ በአራዳ፣ በየካ፣ በቦሌ ክ/ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ በአብዛኛዎቹ የሸማች ማህበራት ሱቆች፣ የዘይትና የዱቄት አቅርቦት በመቋረጡ፣ በመደበኛ ሱቆች በውድ ዋጋ ለመሸመት ተገድደዋል፡፡   ፈረንሳይ ለጋሲዮን፣ በተለምዶ ብረት ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአንድ ዓመት በፊት የተመሰረተው “ዳንኤል ኢዛናና ጓደኞቻቸው
የዶሮ እርባታ ሽርክና ማህበር” በበኩሉ፤ ለበዓሉ የምስራች አለኝ ይላል - እንቁላል በ2 ብር ከ50 እንደሚሸጡ በመግለጽ፡፡ ማህበሩ፤ከአንድ ሺህ በላይ ዶሮዎችን ለእንቁላል ምርት ብቻ በማዘጋጀት፣በቀን ከ900 በላይ እንቁላሎችን እንደሚያመርቱም አስታውቋል።  በከተማዋ የእንቁላል እጥረት እንዳለ በጥናት እንዳረጋገጡና ይህንን ክፍተት ለመሙላት ወደ ስራው እንደገቡ የሚገልጹት ወጣቶቹ፤ በበዓልም ሆነ በአዘቦት ቀናት ገበያ ላይ ከ3 ብር ከ50 እስከ 4 ብር የሚሸጠውን እንቁላል፣ በ2 ብር ከ50 እየሸጡ እንደሆነ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ
ተናግሯል፡፡ “እኛ የዶሮ እርባታችን ድረስ ለሚመጡ ግለሰቦችም ሆነ ለአከፋፋዮች በ2 ብር ከ50 እየሸጥን” ነው ያለው ስራ አስኪያጁ፤ በቅርቡ የዶሮዎቹን ብዛት ወደ ሁለት ሺህ በማድረስ፣ የእንቁላል ምርት በመጨመርና ዋጋውን አሁን ከሚሸጡበት በመቀነስ፣ ማህበረሰቡ እንዲጠቀም ለማድረግ ማሰባቸውንም ጠቁሟል። ለአዲስ ዓመትም ለስጋ ምርትነት የሚያገለግሉ ዶሮዎችን በማርባት 300 ብር እና ከዚያ በላይ የገባውን የዶሮ
ዋጋ ልክ እንደ እንቁላሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዳቀዱ የተናገረው አቶ ኢዛና፤ “አሁንም እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልግ ሰው የዶሮ እርባታ ቦታችን በሆነው ብረት ድልድይ አካባቢ በመምጣት፣ በ2 ብር ከ50 መግዛት ይችላል” ብሏል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ምንጮቻችንን እንደጠቆሙን፤ በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ከወትሮው በተለየ የጎንደር ከብቶች ገበያውን የተቆጣጠሩት ሲሆን የወለጋ፣ ቦረና፣ ክብረ መንግስትና የሐረር ከብቶች ለበዓሉ ወደ አዲስ አበባ አልመጡም ተብሏል፡፡ በስጋቸው
ጣፋጭነት በእጅጉ የተወደዱትና የተለመዱት የሐረርና የቦረና ከብቶች በዘንድሮ በዓል የት እንደገቡ ከአስተማማኝ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ፣ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን በግልና በመንግስት ለተቋቋሙ የከብት ማደለቢያ ማዕከላት በመሸጣቸው ሊሆን እንደሚችል የገለጹልን ምንጮቻችን፤ ብዙ ከብቶችም ወደ ውጪ ገበያ እየተላኩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ የንግድ ጽ/ቤት የቄራዎች የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተክኤ ግደይ፣ ለበዓሉ እስከ 2ሺ የሚደርሱ ከብቶች ወደ ገበያ ማዕከሉ እንደሚገቡ ጠቁመው፣ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል በአብዛኛው የጎንደርና የሰሜን ሸዋ ከብቶች ለሽያጭ መቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡• የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ “አዲስ አድማስ” ይቅርታ መጠየቅ አለበት አሉ
• በውሸት ወሬ ይነዛሉ ባሏቸው ወገኖች ላይ እርግማን አወረዱ

   የጋምቤላ ክልልና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ጽ/ቤት፥ መንበረ ጵጵስና በሆነችው የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል፣ “የወርቅ ጽላት የገባበት ጠፋ” መባሉን ሀገረ ስብከቱ ያስተባበለ ሲሆን፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው፤”ዘገባውን የሠራው የ”አዲስ አድማስ” ጋዜጠኛ፣ ይቅርታ ይጠይቀኝ” ብለዋል፡፡   
በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰው የአህጉረ ስብከቱ ማስተባበያ፣ “ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠው የጋምቤላ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ታቦት የደረሰበት ጠፋ” በሚል ርእስ፣ባለፈው መጋቢት 23 የቀረበው የአዲስ አድማስ ዘገባ፤“በቤተ ክርስቲያኗ መልካም ስምና ዝና ላይ የተፈጸመ የሐሰት ውንጀላና ስም ማጥፋት ነው” በማለት ተቃውሟል፡፡የኪዳነ ምሕረት ጽላት ሳይጠፋ ጠፍቷል፤በማለት ውሸት መነዛቱን የጠቀሰው ማስተባበያው፤ ጽላት መኖሩን አረጋግጠዋል የተባሉት፦ የካቴድራሉ
ቄሰ ገበዝና አገልጋዮች እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት፣በእማኝነት የፈረሙበትን ሰነድ አያይዞ አቅርቧል፡፡የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፣ ለአህጉረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ የታቦቱን መኖር በዓይን እማኝነት አረጋግጠዋል ያላቸውን አራት የካቴድራሉን ሓላፊዎችና አንድ የሌላ ወረዳና ደብር ሓላፊ እንዲሁም 12 የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን በእማኝነት አካቷል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ምእመናን ተወካዮች ጽላቱ ጠፍቷል በሚል ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባስገቡት አቤቱታ፤ አስቸኳይ ምርመራና ማጣራት እንዲካሔድ መማጸናቸው በዘገባው መጠቀሱን ያስታወሰው ማስተባበያው፤ “ምዕመናኑ ወደ
አዲስ አበባ ሳይሔዱ እንደሔዱ በማስመሰል የቀረበ የተሳሳተ መረጃ ነው” ብሏል፡፡ “መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው፣ በሃይማኖት ሽፋን በክልሉ ሁከትና ትርምስ እንዲፈጠር በሚፈልጉ ግለሰቦች የታቀደ ሐሰት ነው” ሲልም ማስተባበያው ጠቁሟል።  ዘገባው በወጣበት ሳምንት፣ የአህጉረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፣ እንደ አኮቦና ጂካዎ ባሉ ጠረፋማ
ወረዳዎች ቤተ ክርስቲያን በማሠራት ላይ እንደነበሩና በክልሉ 54 አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሳነፁ ያወሳው ማስተባበያው፣ አንድም የተዘጋ ቤተ ክርስቲያን እንደሌለና ዋና ሥራ አስኪያጁም፣ ከሕዝብና ከመንግሥት ጋራ በፍቅርና በሰላም ተግተው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል፣ እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቴድራሉ ጽላት ጉዳይ የሚመለከተው ቄሰ ገበዙንና አስተዳዳሪውን እንጂ እርሳቸውን እንዳልሆነ ባለፈው እሑድ የሆሣዕና በዓል ላይ ለምእመናን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ 17 ካህናትን ይዘው ገብተው ጽላቱ በመንበሩ ላይ መኖሩን
እንዳረጋገጡና በቃለ ጉባኤም እንደተፈራረሙ ተናግረዋል፡፡ “ከ107 በላይ ታቦታትን ለክልላችሁ በነጻ የሰጠሁ ነኝ፤ በገንዘብ ቢተመን ስንት ብር ያወጣል?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡  “ሃሰተኛ ወሬው የተነዛው ጋምቤላን በዚህ እናተረማምሳለን ብለው ባቀዱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሆኖም አልተሳካላቸውም ብለዋል፡፡ “የሚያተረማምሱት ስምንት ሰዎች ናቸው፤ ስምንቱንም እኔ ዐውቃቸዋለሁ” ያሉት መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፤ ከስምንቱ ተፈላጊዎችም፣ ሁለቱ ተይዘው ቦንጋ እስር ቤት መግባታቸውን ጠቁመው፤ “አንዱ ትላንት ማተሚያ ቤት ገብቶ አምልጧል፤ ሲመጣ እጠይቀዋለሁ” ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ለመንግሥት አሳልፈው መስጠታቸውንና የግለሰቦቹ ማንነትም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ይፋ እንደሚሆን
ለምዕመናኑ አክለው ገልጸዋል፡፡  የአገረ ስብከቱ የማስተባበያ ደብዳቤ ለዝግጅት ክፍሉ ከደረሰ በኋላ ሥራ አስኪያጁ በሆሳዕና በዓል ላይ ለምዕመናን ባደረጉት በዚህ ንግግራቸው፤ ዘገባውን የሰራው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ይቅርታ ካልጠየቀ፣ሀገረ ስብከቱ ፍርድ ቤት እንደሚገትረው ዝተዋል፡፡ “በውሸት ወሬ
ይነዛሉ፤ሃይማኖትንና ቤተ ክርስቲያንን ለማንኳሰስ ተነሣስተዋል” ሲሉ በወነጀሏቸው ማንነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ወገኖች ላይም እርግማን አውርደዋል- ሥራ አስኪያጁ፡፡ … በእኔ በአባ ተክለ ሃይማኖት ላይ ምንም አታገኙብኝም፤ አትድከሙ” ሲሉ በዐውደ ምሕረቱ ላይ ስለ ንጽሕናቸው መሟገታቸውን ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰው የድምጽ ማስረጃ ይጠቁሟል፡፡ አዲስ አድማስ፣ በመጋቢት 23 እትሙ፣ የጋምቤላ ከተማ ምእመናን ተወካዮች፣ የኪዳነ ምሕረት ጽላት በመንበሯ ላይ አለመኖሯን በመጠቆም፣ ለመንበረ ፓትርያርኩ ያደረሱትን አቤቱታ ጠቅሶ፣ የጽላቱን መጥፋት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የምእመናኑ ተወካዮች፥ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣
ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤትና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አቤቱታቸውን አስፈርመው የሰጡበት ሰነድ ለዝግጅት ክፍሉ የደረሰው ሲሆን፤ ጽላቱ በመንበሩ ላይ አለመኖሩን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስልም በማስረጃነት መቅረቡን መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ለተፈጠረው አለመግባባት የዝግጅት ክፍሉ
ይቅርታ ይጠይቃል፡፡

Page 7 of 335