Administrator
በመጨረሻም ዋልያዎቹ ብራዚል መሄዳቸው አልቀረም
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ የብራዚል ጉዞ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ባይሳካም፤ ለሁለት ሳምንት ዝግጅት መሄዳቸው አልቀረም፡፡
በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ጥረት በብራዚል በካምፕ በአይነቱ የተለየ ዝግጅት የሚያደርጉት ዋልያዎቹ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ተሳታፊነት ብራዚልን በመርገጥ አስደናቂ ብቃት ያሳየችውን አልጄርያ ከመግጠማቸው በፊት ጥሩ ብቃት ላይ እንደሚደርሱ እየተነገረ ነው፡፡ ከብራዚል ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርገው ብሄራዊ ቡድኑ በቆይታው የሚያገኘው ጥቅም ያመዝናል። አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቋሚ ተሰላፊ ቡድናቸውን ለመለየት ያሰቡ ይመስላል፡፡ ባሬቶ በሃላፊነቱ በቆዩባቸው ጊዜያት ቋሚ አምበል አለመሾማቸው ሙሉ ቋሚ ተሰላፊዎች አለመለየታቸውን ያመለክታል፡፡ ፍቅሩ ተፈራ፤ አበባው ቡጣቆ እና ፍፁም ገብረማርያም አምበሎች እንደሚሆኑ እየተገመተ ነው፡፡ አዳነ ግርማ፤ ሳላዲን ሰኢድና መስኡድ መሃመድም ለሃላፊነቱ ብቁ መሆናቸውም ይገለፃል፡፡ 19 አባላትን ያካተተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመርያው ልዑክ ረቡዕ ወደ ብራዚል ተጉዟል፡፡ ቀሪዎቹ ዛሬ ይበራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በብራዚል በሚኖረው የ14 ቀናት ቆይታ 33 አባላት ያሉት ልዑክ ይኖረዋል። በብራዚሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት ከሰሜን ብራዚል ከመጣው ሬምዋ ከተባለ ክለብ ይጫወታል፡፡ የዛሬ ሳምንት ደግሞ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ጨዋታ አስተናግዶ በነበረው የማኔ ጋሪንቻ ስታድዬም ሁለተኛውን ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ከ2 ሳምንት በኋላ ደግሞ ሬዮ ግሬምዬ ከተባለ ክለብ ጋር ሶስተኛውን የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ሦስቱም የብራዚል ክለቦች በአገሪቱ የክለብ ውድድር በ4ኛ ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ጨዋታዎቹ አቋምን ከመፈተሽ ባሻገር ተጫዋቾቹን ለማስተዋወቅ ጥሩ እድል እንደሚፈጥር አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ተናግረዋል፡፡
በ2015 እኤአ ላይ ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚካሄድ የምድብ ማጣርያ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር ከመጫወቱ በፊት ቢያንስ ስምንት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዋልያዎቹ ባለፈው ሰሞን በሉዋንዳ ላፓላንካ ኔግራስ ከተባለው የአንጎላ ብሄራዊ ቡድን ጋር በመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታቸው ተገናኝተው 1ለ0 ተሸንፈዋል፡፡
በሉዋንዳ 11 ዲ ኔቨምብሮ ስታድዬም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንጎላ ያሸነፈችው ፍሬዲ የተባለ ተጨዋች በ16ኛው ደቂቃ ላይ ባገባት ብቸኛ ግብ። የአንጎላው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ የክብር እንግዳ ነበሩ፡፡
ከብራዚል መልስም በነሀሴ ወር ሁለት የደርሶ መልስ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ፈርኦኖቹ ከተባለው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለማድረግ ቀጠሮ መያዙም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 2 የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታው ጳጉሜ 2 ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከአልጄርያ ይገናኛል፡፡ አልጄርያና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ እና ዋና ውድድሮች 6 ጊዜ ተገናኝተዋል። እኩል አንዴ ተሸናንፈው በ4 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በምድብ 2 ከአልጄርያ፤ ከማሊ እና ከኢትዮጵያ ጋር ማጣርያ የምትገባው አራተኛ ቡድን ማላዊ ሆናለች፡፡ ማላዊ ምድቡን የተቀላቀለችው በሁለተኛ ዙር ቅድመ ማጣርያ ቤኒን ጥላ በማለፍ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙንሶኜ በሞሮኮው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመካከለኛው እና የምስራቅ ዞን አንድ ተወካይ መኖሩ አይቀርም ብለዋል። ከዞኑ አራት ቡድኖች በምድብ ማጣርያው የሚካፈሉ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በቀጥታ ወደ ምድብ ሲገቡ በቅድመ ማጣርያ ያለፉት ደግሞ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በማጣርያ በሜዳዋ በምታደርጋቸው ጨዋታዎች ባለፈው ሁለት ዓመት ያሳየችው ብቃት ለጥንካሬዋ ምክንያት እንደሚሆን ኒኮላስ ሙንሶኜ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የመካከከለኛው እና ምሰራቅአፍሪካ ሻምፒዮና አዘጋጅ እንደሆነች ይታወቃል።
አሜሪካ የደህንነት መረጃዎቼን የሚያወጣ ሌላ መንታፊ መጥቶብኛል አለች
ቁልፍ መረጃዎችን እያወጣ በዓለማቀፍ ደረጃ ክፉኛ ሲያሳጣት የከረመውን ኤድዋርድ ስኖውደን የተባለ ግለሰብ አሳድዳ ለመያዝና ለመፋረድ ደፋ ቀና ማለቷን የቀጠለችው አሜሪካ፣ አሁን ደግሞ ከእሱ የባሰ የብሄራዊ ደህንነት መረጃዎቼን እየዘረፈ በማውጣት ጉድ የሚሰራኝ ሌላ ሚስጥር መንታፊ ግለሰብ መጥቶብኛል ስትል ባለፈው ረቡዕ በይፋ መናገሯን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ስኖውደን የሚያወጣቸውን መረጃዎች እያተመ ለንባብ በማብቃት የሚታወቀው ዘ ኢንተርሴፕት የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ፣ ባለፈው ማክሰኞም ከዚህ ማንነቱ ያልተገለጸ ግለሰብ ያገኘውን የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት መረጃ ለንባብ ማብቃቱን ተከትሎ ነው የአሜሪካ መንግስት አሁንም ሌላ አዲስ መረጃ ዘራፊ እንደመጣበት ያመነው፡፡
ዘ ኢንተርሴፕት ለንባብ ያበቃው ጽሁፍ፣ በኦባማ የስልጣን ዘመን አሜሪካ በሽብርተኝነት ጠርጥራ የምትመዘግባቸው ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱንና የግለሰቦችን መረጃ በሚስጥር እያፈላለገች የመያዝና የመሰለል ስራዋን የበለጠ አጠናክራ መግፋቷን የሚያትት ነው ተብሏል፡፡
ጋዜጣው ግለሰቡ ያወጣቸው መረጃዎች አገሪቱ በሽብርተኝነት ጠርጥራ ከመዘገበቻቸው ዜጎች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያረጋግጡ ናቸው ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን ጋዜጣው ወጡ የተባሉትን የሚስጥር መረጃዎች በአግባቡ ካለመረዳት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረሱን መናገራቸውን አስረድቷል፡፡
ማንነቱ ባልተገለጸው ግለሰብ አማካይነት ወጡ ያላቸውን መረጃዎች ጠቅሶ ጋዜጣው እንዳስነበበው፣ አሜሪካ እስከ 2013 ነሃሴ ወር ድረስ 5ሺህ ያህል ዜጎቿን በከፍተኛ፣ 18 ሺህ ያህሉን ደግሞ በመለስተኛ ደረጃ በሽብርተኝነት ጠርጥራ የመዘገበች ሲሆን፣ 1ሺህ 200 የራሷን ዜጎች ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ 16 ሺህ የተለያዩ አገራት ዜጎችንም ‘በአየር መንገዶችና በድንበር አካባቢዎች ጥብቅ ፍተሻ ሊደረግባቸው የሚገቡ’ በማለት ስማቸውን መዝግባ ይዛለች፡፡
ግለሰቡ ያወጣቸው እነዚህ አዳዲስ መረጃዎች፣ ስኖውደን መረጃ በማውጣቱ ሰበብ ለእስር እንዳይዳረግ በመስጋት ከአሜሪካ አምልጦ ወደ ሩስያ ከኮበለለ በኋላ በነበረው ጊዜ በአገሪቱ ብሄራዊ የጸረ ሽብርተኝነት ማዕከል የተዘጋጁ እንደነበሩ መረጋገጡን ጠቁሞ፣ ይህም መረጃዎቹን ያወጣው ሌላ ግለሰብ መሆኑን የሚያሳይ ነው መባሉን ገልጿል፡፡ የአገሪቱ ባለስልጣናት የአዲሱን መረጃ መንታፊ ማንነት ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ግለሰቡ ምናልባትም በሚመለከታቸው የአገሪቱ የደህንነት መረጃ ተቋማት ውስጥ የሚሰራ ሊሆን እንደሚችል መገመቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ግለሰቡ ምን ያህል የሚስጥር መረጃዎችን እንዳወጣም ሆነ መረጃዎቹ አፈትልከው መውጣታቸው በአገሪቱ መንግስት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ የአገሪቱ መንግስት ያለው ነገር ባይኖርም፣ መረጃዎቹ ‘ሚስጥራዊና ለውጭ አገራት መንግስታት ተላልፈው የማይሰጡ መረጃዎች’ በሚል መለያ በአገሪቱ የደህንነት መረጃ ተመዝግበው እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
አዲሱ መንታፊ ያወጣቸው መረጃዎች ስኖውደን ከዚህ በፊት ካወጣቸው የደህንነት መረጃዎች ጋር ሲነጻጸሩ በሚስጥራዊነታቸው አነስተኛ እንደሆኑ ዘገባው ጠቁሞ፣ ስኖውደን ካወጣቸው 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአገሪቱ የደህንነት መረጃዎች አብዛኞቹ ‘ጥብቅ ሚስጥሮች’ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡
የቻይናው ዚያኦሚ “አዲሱ ‘የስማርት ፎኖች’ ንጉስ ነኝ!” እያለ ነው
የቻይናው የሞባይል ቀፎ አምራች የግል ኩባንያ ዚያኦሚ፣ የእነጋላክሲና አይፎን ዘመን አክትሟል፣ ከአሁን በኋላ ከማንም በላይ ከፍ ብዬ የምታየው የአገሬ ‘የስማርት ፎኖች’ ንጉስ እኔ ነኝ እያለ ነው፡፡
በአገረ ቻይና የስማርት ፎን ገበያ ዋነኛ ተፎካካሪው የነበረውን የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ በዘንድሮው ሁለተኛ ሩብ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሽያጭ ያስከነዳውና ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣው ዚያኦሚ፣ ይህ ስኬቱ በአገሩ ምድር የስማርት ፎን ገበያ መሪነቱን እንዳስጨበጠው ሲኤንኤን ሰሞኑን ከሆንግ ኮንግ ዘግቧል፡፡
ከአራት አመታት በፊት የተመሰረተው የቻይናው ስማርት ፎን አምራች ዚያኦሚ፣ በአገሪቱ ገበያ ያለውን ድርሻ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት በማሳደግና ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው የገበያ ድርሻ 240 በመቶ ጭማሪ በማድረግ በአሁኑ ወቅት 14 በመቶ ማድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሩብ አመቱ ለገበያ ያቀረባቸው ስማርት ፎኖች ቁጥርም 15 ሚሊዮን መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ዚያኦሚ በተጠቀሰው ጊዜ 97 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ለቻይና ገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ የካፒታል አቅሙም ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡
ሳምሰንግን ጨምሮ ዋነኛ ተፎካካሪዎች የነበሩት ሁዋዌ፣ ሌኖቮና ዩሎንግ በሩብ አመቱ በአማካይ 10 በመቶ የገበያ ድርሻ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዚያኦሚ በቻይና ቀዳሚውን የገበያ ድርሻ ቢይዝም ከአገር ውጭ እምብዛም እንደማይታወቅ አስታውሷል፡፡
ኩባንያው በአገር ውስጥ እያስመዘገበ ያለውን ስኬት በማስፋፋት በአለም አቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ተወዳዳሪና መሪ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን፣ ይህን እቅዱን ለማሳካት በሚችልበት መንገድ ዙሪያ ባለፈው አመት ከጎግል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር የጋራ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተዘግቧል፡፡
ዚያኦሚ ወደ አለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ዘልቆ ለመግባትና ንግስናውን ድንበር ለማሻገር የጀመረውን ጉዞ፣ ምርቶቹን ወደ ሩስያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ፣ ታይላንድና ቱርክ በመላክ ለመጀመር እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡
የኩባንያው ስማርት ፎኖች በአሁኑ የቻይና ገበያ በ130 ዶላር እየተሸጡ ሲሆን፣ ዋጋቸው ከአፕል ምርቶች ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሶስተኛ ያነሰ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ሳኡዲ የሌሎች አገራት ሴቶችን ለሚያገቡ ዜጎቿ ጥብቅ መመሪያ አወጣች
ትዳር መመስረት የፈለጉ ወንዶች ለመንግሰት ፕሮፖዛል ማቅረብ አለባቸው
የአገሪቱ ወንዶች ከ4 አገራት ሴቶች ጋር መጋባት አይችሉም
ሳኡዲ አረቢያ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር ትዳር መመስረት ለሚፈልጉ ዜጎቿ ጥብቅ የሆነ የትዳር መመሪያ ማውጣቷንና የአገሪቱ ወንዶች ከአራት አገራት ሴቶች ጋር እንዳይጋቡ መከልከሏን ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የሳኡዲ መንግስት ያወጣውን የትዳር መመሪያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር ትዳር መመስረት የሚፈልጉ ዜጎች፣ የትዳር ፕሮፖዛልና የሚኖሩበት ከተማ ከንቲባ ፊርማ ያረፈበት የነዋሪነት መታወቂያ ለአገሪቱ ፖሊስ ማቅረብና ማስገምገም ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመካ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት አሳፍ አልቁሪሽ እንዳሉት፣ መንግስት ትዳር ፈላጊዎች የሚያቀርቡለትን ፕሮፖዛል ገምግሞ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ አዲሱ መመሪያ እንደሚለው፤ ትዳር ፈላጊው ዕድሜው ከ25 ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ትዳር የነበረውና የተፋታ ከሆነ ደግሞ፣ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር አዲስ ትዳር መመስረት የሚችለው፣ ፍቺው ከተፈጸመ ከከ6 ወራት ጊዜ በኋላ ነው፡፡
“ዘ መካ” የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ ያወጣውን ዘገባ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደገለጸው፣ ትዳር ፈላጊው የቀድሞ ትዳሩን በህጋዊ ፍቺ ያላፈረሰ ከሆነ፣ አዲስ ትዳር መመስረት የሚችለው በመንግስት ከሚተዳደር ሆስፒታል የቀድሞ ሚስቱ በጸና መታመሟን ወይም መሃን መሆኗን የሚያረጋግጥ አልያም የቀድሞ ሚስቱ አዲስ ትዳር ቢመሰርት እንደማትቃወም የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርብ ነው፡፡ አዲሱ የሳኡዲ አረቢያ መንግሰት ለአገሪቱ ትዳር ፈላጊ ወንዶች ያወጣው የጋብቻ መመሪያ፣ ወንዶቹ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ተቀጥረው ከሚሰሩ የፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቻድ እና በርማ ሴቶች ጋር በፍጹም ትዳር መመስረት እንደማይችሉ ጥብቅ እገዳ የሚጥል መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፣ ዘጠኝ ሚሊዮን ከሚደርሱት ከእነዚህ የውጭ አገራት ሰራተኞች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ወይም 500 ሺህ ያህሉ የትዳር እገዳ ከተጣለባቸው አራቱ አገራት የመጡ ሴቶች መሆናቸውን ጨምሮ ገልጧል፡፡
የድረገጽ ሌቦች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ፓስ ዎርዶችን ሰረቁ
የሩስያ ዜግነት ያላቸው አባላትን የያዘ አለማቀፍ የድረገጽ ሌቦች ቡድን የአሜሪካን ግዙፍ ኩባንያዎች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ ድርጅቶችን፣ የንግድ ኩባንያዎችንና የግለሰቦችን የድረገጽ መረጃዎችና ፓስ ዎርዶችን (የሚስጥር ቁልፎች) መዝረፉን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ሆልድ ሴኪዩሪቲ የተባለውን ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ቡድኑ ከ420 ሺህ በላይ በሚሆኑ የኩባንያና የግለሰብ ድረገጾች ላይ የፈጸመው ይህ የስርቆት ተግባር፣ በዘርፉ በአለም ዙሪያ የተፈጸመ ትልቁ የመረጃ ዘረፋ ነው፡፡ ዘራፊዎቹ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢሜይል አድራሻዎችን የሚስጥር ቁልፍ በርብረው እንዳገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ መሰል ተግባር ከተፈጸመባቸው መካከልም በዓለማችን ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንደሚገኙበት የሆልድ ሴኪዩሪቲን መስራች አሌክስ ሆልደን መናገራቸውን አስረድቷል፡፡
አስር ያህል አባላትን የያዘው ይህ የዘራፊዎች ቡድን ተቀማጭነቱን ያደረገው፣ ከካዛኪስታንና ከሞንጎሊያ ጋር በሚዋሰነው የሩስያ ደቡብ ማዕከላዊ አካባቢ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አባላቱ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
የቡድኑ አባላት የራሳቸውን የኮምፒውተር ፕሮግራም በመፍጠርና የድረገጾችን መረጃ በመስረቅ በሚያገኙዋቸው የሚስጥር ቁልፎች አማካይነት የኩባንያዎችንና የግለሰቦችን የመረጃ ልውውጥና ሚስጥር በእጃቸው እንደሚያስገቡ ተገልጿል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ፣ቡድኑ የዝርፊያ ስራውን በረቀቀ መንገድ ማከናወን ከጀመረ ጥቂት አመታት እንደሆነው ገልጾ፣ የሚስጥር ቁልፎችን በመዝረፍ የሚያገኛቸውን የኩባንያዎችና የግለሰቦች ሚስጥሮች መደራደሪያ በማድረግ የገንዘብ ምንጭ አድርጎ እንደሚጠቀም ተነግሯል፡፡
“ከነፍስ እስከ ዩኒቨርስ” መፅሀፍ ለንባብ በቃ
በናትናኤል ፋንቱ የተፃፈው “ከነፍስ እስከ ዩኒቨርስ” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ መፅሀፉ በዋናነት በስነ ፈለክ ምርምር፣ በፕላኔቶች፣ በፀሐይና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ “ከነፍስ እስከ ዩኒቨርስ” ስለምንኖርባት ዓለም ምን ያህል እናውቃለን፣ ማወቁስ ለምን አስፈለገ? ስለክዋክብት ማወቅስ ምን ይጠቅማል ለሚሉትና ተያያዥ ጥያቄዎች መጠነኛ መልስ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለው መፅሀፉ፤ 156 ገፆች ያሉት ሲሆን በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ የመፅሀፉ አዘጋጅ ናትናኤል ፋንቱ ከዚህ ቀደም “የእኔ ስላሴዎች - ህይወት፣ ፍቅርና ሳቅ”፣ “ስለ አረንጓዴ አይኖች”፣ “ሴቶች ለምንድን ነው ወሬ የማያቆሙት?” እና “የአምላክነት ቅምሻ” የተሰኙ መፃህፍትን ማሳተሙ ይታወሳል፡፡
“ሰልፍ ሜዳ” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ
በቀድው የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ግርማ ተስፋው የተደረሰው “ሰልፍ ሜዳ” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ የልቦለዱ ማጠንጠኛ ከአብዮት በኋላ በሚያጋጥም የህይወት ፈተና ላይ በተዋቀረ በተለይም የሰው ልጆች በአብዮት ማግስት ለሚኖሩት ህይወት ትርጉም ማጣት፣ ብቸኝነት፣ ድብታና የባዶነት አዘቅት ውስጥ መስጠም በመፅሀፉ እንደ ዋንኛ ጭብጥ ተነስቷል፡፡
240 ገፆች ያሉት ልቦለዱ፤ በሊትማን መፃህፍት አከፋፋይነት የቀረበ ሲሆን በ49 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የጠፋችውን ከተማ ሐሰሳ” የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡
“የ‘ኛ ነገር” የግጥም መድበል ለንባብ በቃ
የጋዜጠኛ ግርማ ወ/ማርያም “የ ‘ኛ ነገር” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ ማህበራዊ ትዝብቶች፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ሌሎች ርዕሶች የተዳሰሱበት የግጥም መፅሀፉ፤ 76 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን በ70 ገፆች የተቀነበበ ነው፡፡ መፅሀፉ ድንገት ከቤቱ እንደወጣ ለቀረውና በጣም ለሚያከብረው ደራሲ በዓሉ ግርማ መታሰቢያነት ይሁንልኝ ብሏል፡፡ መድበሉ በ25 ብር ይሸጣል፡፡ ጋዜጠኛው ከዚህ በፊት “አለቃ ሙስና እና…” በሚል ርዕስ መፅሃፍ አሳትሟል፡፡
“ቼ ጉቬራያ የአብዮተኛው ህይወት” መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ
በነፃ አውጭ ታጋይነት ዓለም አቀፍ ዝናና አድናቆት ያተረፈውን የቼ ጉቬራን ህይወት የሚያስቃኝ “ቼ ጉቬራ! የአብዮተኛው ህይወት” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ገበያ ላይ ውሏል፡፡
መፅሀፉ ከጆን ሊ አንደርሰን “Che Guevara፡ A Revolutionary Life” እና ከሪቻርድ ኤል ሃሪስ “Che Guevara፡ A Biography” መፅሀፎች ተጠናቅሮ የተሰናዳ መሆኑን አዘጋጁ ብርሃነ መስቀል አዳሙ በመፅሃፉ መግቢያ ላይ ገልጿል፡፡
ድህረ ታሪኩን ጨምሮ በስድስት ምዕራፍ የተከፋፈለውና በ254 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ በ50 ብር ከ70 ለገበያ ቀርቧል፡፡
ማራኪ አንቀጽ
“..ምን ልርዳችሁ? ምን ፈልጋችሁ ነው?” አሉ ግራ ተጋብተው፡፡
ተዘጋጅተንበት ስለነበር ሁላችንም በአንድ ድምፅ
“ዜግነት!!! ዜግነት!!!...ነፃነት!!...አባት ሀገር!!...አባት ሀገር!!! Our father land!!...Father land!!!” እያልን መጮህ ጀመርን፡፡
ወንበር ላይ ወጥቼ እያጨበጨብኩ፤
“ነፃነት!! ዜግነት!! ነፃነት!! ዜግነት!!...” በማለት መዝፈን ስጀምር ሁሉም እኔን እየተከተሉ መዝፈንና ግድግዳ እየደበደቡ ሲረብሹ፣ አቶ ተስፋዬ የሚሰማቸው ስላጡ ቢሮውን ለቀው ወጡ፡፡ የኤምባሲው ሰራተኞች በሙሉ ደንግጠው ሲመለከቱን ጭራሽ ባሰብን፡፡ ከአስር ደቂቃ በኋላ አቶ ተስፋዬ አምባሳደሩን፣ ቆንስሉንና ሌሎች ነጭ ሆላንዳዊያንን አስከትለው መጡ፡፡
“እባካችሁ ተረጋጉና የምትፈልጉትን ንገሩን፡፡” ቢሉንም እኛ ግን መጮሃችንን ቀጠልን፡፡
“እንዲህ መሆናችሁ ጥቅም የለውም፡፡ ይልቁንስ አምባሳደሩ አጠገባችሁ ስለሚገኝ ይህን ዕድል ተጠቅማችሁ ጥያቄያችሁን ብታቀርቡ ይሻላል” አሉ አቶ ተስፋዬ፡፡
ይህን ስንሰማ ቀስ በቀስ ተረጋጋን፡፡ ወዲያውኑ አምባሳደሩ ንግግር ጀመረ፡፡ አቶ ተስፋዬ የአምባሳደሩን ንግግር ማስተርጐም ሲጀምሩ ከቆምኩበት ወንበር ላይ ዘልዬ ወረድኩ፡፡
“አቶ ተስፋዬ እንዲያስተረጉምልን አንፈልግም። እንግሊዘኛ ቋንቋ የሚችል ሰው አለን፡፡ አንተ እኛን ለማስፈራራት ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡” ብዬ ጮህኩኝ።
ኢዩኤል በእንግሊዝኛ መናገር ሲጀምር ፀጥታ ሠፈነ፡፡
“እኛ የተረሳን የሆላንድ ተወላጆች ነን። አባቶቻችን ጥለውን ጠፍተዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ሀገራችን መሄድ እንፈልጋለን! ጥያቄያችን ይህ ነው፡፡” አለና በእንግሊዝኛ የተናገረውን ወዲያው በአማርኛ ለእኛ ተረጐመልን፡፡ አምባሳደሩ የተናደደ መሰለ፡፡
“የሆላንድን ዜግነት በጉልበት ማግኘት ትችላላችሁ?! ሁላችሁም ከዚህ ቢሮ አሁኑኑ ለቃችሁ ውጡ! በፖሊስ ሃይል ተገዳችሁ ከመውጣታችሁ በፊት አሁኑኑ በሰላም ውጡ!” ብሎ ድምፁን ከፍ አድርጐ ተናገረ፡፡
በመቀጠል ቆንስሉ ወደ እኛ ተጠግቶ “በሉ ውጡ!” እያለ ሲንጐራደድ፣ ሁሉም ልጆች “ምን እናድርግ?” በሚል ስሜት ተመለከቱኝ፡፡
“በለው! በለው!” አልኩና ከባድ ግርግር አስነሳሁ። ሰለሞን ታይሰን አይኑን አፍጥጦ ቆንስሉን ሲጠጋው ቆንስሉ ወደ ውጪ ሮጠ፡፡
“ነፃነት! ዜግነት! ነፃነት! ዜግነት! ዜግነት!” የሚል ጩኸት ተጀመረ፡፡
ሁሉም ሸሽተውን በርቀት ይመለከቱናል። ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ አምስት የታጠቁ የኢትዮጵያ ፖሊሶች የእንጨት ዱላና ካቴና ይዘው መጡ፡፡ አምስቱም ፖሊሶች ተከታትለው ገብተው፤
“ፀጥ በል! ፀጥ በል! ለምንድነው የምትረብሹት?! ተነስ ውጣ! ውጣ!” እያሉ ያመናጭቁን ጀመር፡፡
ሳያስቡት ዘልዬ መጀመሪያ ወደኛ የተጠጋውን ፖሊስ ሁለቴ በቦክስ ስመታው፣ ተንገዳግዶ ጥግ ያዘ። ሰለሞን ሮጠና ጥግ የያዘውን ፖሊስ እግሩን ዘርጥጦ ጣለውና፣ በጉልበቱ ግንባሩን መቶት ራሱን አሳተው። የቀሩት ፖሊሶች ራሳቸውን ለመከላከል በያዙት ዱላ ሰለሞንን ፈነከቱት፡፡ በግብግቡ ውስጥ እንደምንም ብለው የተመታውን ፖሊስ ከቢሮ ጐትተው አወጡት። በመስታወት ውስጥ ቆመው ጠቡን የሚያዩት አምባሳደሩ፤ ቆንስሉና ሌሎችም ነጭ ሆላንዳዊያን በኛ ቁርጠኛነት ደንግጠዋል፡፡
በቢሮው ውስጥ የነበረውን አግዳሚ ወንበር አንስተን ለስድስት ተሸከምነውና ፊት ለፊት የሚያዩበትን መስታወት ለመስበር በወንበሩ መምታትና መደብደብ ጀመርን፡፡ በአምስተኛው ምት መስታወቱ ፈረሰ፡፡ ቢሮው ውስጥ የነበሩት አምባሳደሩ እና ሌሎች የኤምባሲው ሰራተኞች ቢሮውን ጥለው ከፖሊሶች ጋር ተቀላቀሉ። እንደማይቋቋሙን ሲረዱ ከሃያ በላይ የሚሆኑ ፖሊሶች አስጨምረው ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በኋላ ስለተዳከምን፣ ሁላችንንም በካቴና አስረው እየጐተቱ እና በዱላ እየቀጠቀጡ፣ በፖሊስ መኪና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ስንደርስ ካቴናችንን እየፈቱ፣ አንድ ቤት ውስጥ አስገብተው ቆለፉብን፡፡ ሁላችንም በጣም ደክሞን ስለነበር ወለሉ ላይ በጀርባችን ተዘርረን ተኛን፡፡ ማታ ራት አቀረቡልን፡፡ በነጋታው ሁላችንም ሻወር ወስደን እስር ቤት ውስጥ መጫወትና ያደረግነውን ትግል ጀብዱ፣ ድፍረት፣ ቆራጥነት ስናወራ፣ የፖሊስ ጣቢያው መርማሪዎችና መቶ አለቃው በሩን ከፍተው መሃላችን ቆሙ፡፡ ለሁለት ደቂቃ አዩንና
“አመፀኛው ክልስ የታል? የዚህ አመጽ መሪ አንተ ነህ?” ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ የቀሩት መርማሪ ፖሊሶች “አመፀኛው ክልስ ተነስ!! አመፀኛ!!” እያሉ በጥፊ እየመቱኝ፣ ለምርመራና ጥየቃ የመቶ አለቃው ቢሮ አስገቡኝ፡፡
“አመፀኛው ክልስ ስምህ ማነው” አለ መቶ አለቃ፡፡
“ዳንኤል ሁክ” አልኩት…
(ከዳንኤል ሁክ “አመፀኛው ክልስ”
እውነተኛ ታሪክ መፅሃፍ የተቀነጨበ -2005 ዓ.ም)

