Administrator

Administrator

Saturday, 11 March 2017 12:53

መጫወቻ ፍለጋ

የሠፈር ልጆች ቅዳሜ-ቅዳሜ መጫወቻ ፍለጋ ዙረት እንሔድ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ ምርጫችን ፈረንጆች ቤት ጓሮ ማንጎዳጎድ ነበር፡፡ ፈረንጆቹ ከቤታቸው አጥር ግቢ ውጪ ጉድጓድ ቆፍረው ቆሻሻውን እዚያ ይጥሉታል፡፡ ዘበኞቻቸውም ጠቃሚ የሆነውን ዕቃ ይቃርማሉ፡፡ በተቀረው ላይ እሳት ለኩሰው ይለቁበታል፡፡ አንዳንዴ ከመቃጠሉ በፊት ደርሰን ደጋግ ዘበኞች ካጋጠመን ደስ ያለንን ዕቃ እንወስዳለን፡፡ ግን ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙን እርጉም ዘበኞች ስለነበሩ ያባርሩናል፡፡ ሸሽተን ከሌላ ቪላ ቤት ጓሮ ፍለጋችንን እናጧጡፋለን፡፡
ከዕለታቱ በአንዱ ቀን ብትንትኗ የወጣ አሻንጉሊት አገኘን፡፡ ቀጢሳው ከትከሻዋ እስከ ዳሌዋ ያለው የአሻንጉሊቷን አካል ሲያገኝ “ባትጋሩኝ! በትኩስ እንጀራ በመርፌ ቀዳዳ!” ብሎ ጮኸ፡፡
አሻንጉሊቷ ጭንቅላት፣ እጅና እግር እንደሌላት ካስተዋለ በኋላ “በእናታችሁ ልጆች! የተቀረውን አካሏን ካገኛችሁት ትሰጡኛላችሁ? የአሻንጉሊቷ ሙሉ አካል ከተገኘ ልብስ ሰፍተንላት ሁላችንም እንጫወትባታለን፡፡” አለ ቀጢሳው እየተለማመጠን።
ብዙም ሳይቆይ ኃይሉ ዶሮ “ባትጌ!” አለና ጮኸ። የአሻንጉሊትዋን እጆች ሽቅብ እንደ ዋንጫ ሰቅሎ እያሳየን፡፡
“ለቀጢሳው ስጠው!” እያልን ሁላችንም ለመነው፡፡ ሰጠው፡፡
“ዶሮ ደግ ልጅ ነው” አልን ሁላችንም፣ ቆሻሻውን ማገለባበጡን እየቀጠልን፡፡
የቆሻሻው ትንፋግ አይነሳ! አዋቂን ሰው ከአገር ያስለቅቃል፡፡ እኛ ግን መጫወቻው በልጦብን ያንን ክርፋት የልጅነት አፍንጫችን ችሎታል፡፡
ከጥቅም ውጭ የሆኑ የሕክምና ዕቃዎች፣ የምግብ ማሸጊያ ፓኮዎች፣ ቆርቆሮዎች፣ አርተፊሻል ፀጉር፣ የፀጉር ማስያዣ፣ ካርቶኖች፣ ፊኛዎች አገኘን። ፊኛውን እየተቀባበልን ነፋነውና ተጫወትንበት፡፡ (በበኋለኛው የሕይወት ዘመኔ ፊኛ እያልን ስንነፋው የነበረው ኮንዶም እንደነበረ ተገንዝቤያለሁ፡፡)
እዚያው ትንፋጉ ላይ ሆነን አስቂኝ ትዕይንት እየሰራን ያንን መራር ሕይወት እናጣፍጠው ነበር፡፡ ቀጢሳው ግማሽ ጎኑ የተቃጠለውን አርተፊሻል ፀጉር አናቱ ላይ አድርጎ፣ የተሰበረ የፀጉር ጌጥ ሰክቶበት እንደ ፈረንጅ ኮረዳ እየተሽኮረመመ “ዊስ ዋይስ” ብሎ በራሱ እንግሊዝኛ ተናገረ፡፡
ጎቢጥ ያንን አንድ ዓይኑ ላይ መስታወት የሌለውን መነፅሩን አደረገና አፉ ላይ የሲጋራ ቁራጭ ወትፎ እንደ ፈረንጅ ጎረምሳ ጎርነን ባለ ድምፅ፤ “ዋት ኢዝ ዊስ ዋይ?” አለ በብረት ዘንግ ቆሻሻውን እየቆፈረ፡፡ የአሻንጉሊትዋን እግሮች አገኘ፡፡ ለቀጢሳው ሰጠው።
ቀጢሳው ቻርሊ ቻፕሊን ፊልም ላይ ባየነው ስልት በደስታ ተውረግርጎ ሹል አፉን አሞጠሞጠና ሲሳይ ጎቢጥን ሳመው፡፡
ፍለጋችን ቀጠለ፡፡ ውሮ አንድ ነገር ደብቆን ኪሱ ሲከት ሴምላል አየውና፤ “ምን አገኘህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ ሁላችንም ካቀረቀርንበት ቀና አልን፡፡ ውሮ ቁንጮውን እያከከ “ምንም አላገኘሁም!” አለ፣ ኪሱን ጨብጦ ላለማስፈተሽ እየሞከረ፡፡
“እስኪ እናቴ ትሙት በልና ማል?!” ሲል ሴምላል ንፍጡን ሽቅብ እየሳበ ጠየቀው፡፡ ውሮ መማሉን ፈራ፡፡ በዚህ ምልልስ ወቅት መኩዬ ቀጫጫው እንደ እባብ ተስባ ከውሮ ኋላ ደርሳ ከኪሱ በፍጥነት አንድ ነገር ስትስብ የአሻንጉሊቷ ጭንቅላት መሬት ዱብ አለ፡፡
“ወይኔ አሻንጉሊቴን!” ሲል ውሮ ጩኸቱን አቀለጠው፡፡ መኩዬ ቀጫጫው የአሻንጉሊት ጭንቅላት ከመሬት አንስታ እየደባበሰች ለቀጢሳው እንዲሰጠው ለመነችው፡፡
ውሮ “እምቢ” አለ፡፡
ሁላችንም ብንለምነው ችክ አለ፡፡ እርሱም የራሱ አሻንጉሊት እንዲኖረው፣ የተቀረውን አካል በሽቦና በጨርቅ ሠርቶ ሊጫወትበት መፈለጉን በልቅሶ ዜማ አወራን፡፡ በዚህ ራስ ወዳድነቱ ሁላችንም አኮረፍነው፡፡ መኩዬ ቀጫጫውም የአሻንጉሊቷን ጭንቅላት አፍንጫው ላይ ወረወረችለት፡፡
(“ልጅነት” ከተሰኘው የደራሲ ዘነበ ወላ
መፅሀፍ ላይ የተቀነጨበ)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ - ዓይነ - ሥውር እናት የነበረችው አንድ ልጅ ነበረ፡፡ ይሄ ልጅ እናቱን አደባባይ ማውጣት አይፈልግም፡፡ ያፍርባታል፡፡ በሄደበት ቦታ ሁሉ ሌሎች ልጆች ስለ እናታቸው ሲያወሩ፣ እሱ አያወራም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሌሎቹ ስለ እናታቸው ደግነት ሲያወሩ እሱ እናቱን አያነሳም። እናቱ በእናትነቷ እስክትሸማቀቅና እስክትሸሸግ ድረስ በሰፈር ልጆች መሳቂያ መሳለቂያ እንድትሆን አደረጋት፡፡
በትምህርቱ እየገፋ ታዋቂ ልጅ እየሆነ ሲሄድ፣ ስለ እናቱ መናገሩን ጨርሶ ተወ - ያለ እናት የተወለደ እስኪመስል ድረስ፡፡ ውጪ አገር ሄዶ አድጎ ተመንድጎ፣ አንቱ ተብሎ ትልቅ ስራ ያዘ፡፡ እናቱን ረሳት፡፡ እናቱን የከዳና የናቀ መሆኑን ግን የሚያውቅ ማንም የለም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ትውልድ አገሩ ውስጥ ለሚደረግ ትልቅ ኮንፈረንስ ተጋበዘና ወደ ሀገሩ መጣ፡፡
ስብሰባው ሲያበቃ እስከ ዛሬ ረስቷት የነበረችውን እናቱን እስቲ ከመጣሁ አይቀር ልያት ብሎ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤት ግን የጠበቀችው እናቱ ሳትሆን፣ የእናቱ ታናሽ እህት፣ አክስቱ ናት፡፡
“እናቴስ ወዴት አለች?” አለና ጠየቀ እንደደረሰ፡፡
አክስቱም፤ “እናትህ የለችም?”
ልጅ፤ “ወዴት ሄደች?”
አክስት፣ “ወደማይቀረው አለም”
ልጁ ያልጠበቀው ነበረና ድንጋጤ ላይ ወደቀ፡፡ አለቀሰ፡፡
ሲረጋጋ፤ “እናትህ ከመሞቷ በፊት ‹ድንገት ልጄ ከመጣ ይሄን ደብዳቤ ስጪልኝ› ብላለች፡፡ እንካ ውሰደው” ብላ አክስቱ ትሰጠዋለች፡፡
ሲፈራ ሲቸር እጁ እየተንቀጠቀጠ ይቀበላትና ደብዳቤውን ከፍቶ ያነበዋል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ልጄ! አንድ ልጄ ሆይ!
ብትገፋኝም፣ ብትርቀኝም፣ ብትንቀኝም ብታስንቀኝም፣ ብትጠላኝም፣ ብታስጠላኝም፣ ብታኮርፈኝም፣ ሰዎች እንዲያፍሩብኝ ብታደርግም፣ አሁንም ያው አንድ ልጄ ነህ! ህይወቴ ከማለፉ በፊት አንድ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ፡-
ወጣት ሆነህ አንድ ዐይንህን ክፉኛ ያምህ ነበር፡፡ ሐኪም ቤት ወስጄህ ዶክተሩ ዐይንህ ሊጠፋ እንደሚችልና በቀዶ - ጥገና ሌላ ዐይን ካልተተከለልህ ተስፋ እንደማይኖርህ፣ ጨርሶም እንደሚጠፋ፣ ነገረኝ፡፡ የአንተ፣ የነገ ተስፋዬ፣ ገና ብዙ ማየት ያለብህ አንድ ልጄ፤ ዐይንህ - ብርሃንህ ከሚጠፋ የእኔ ዐይን ይጥፋ፤ ብዬ፣ የእኔ ዐይን ይጥፋና አንተ ብርሃን ይኑርህ ብዬ፣ ዐይኖቼን አስወልቄ ላንተ አስተከልኩልህ!! ዛሬ አንተ ሁለት ዐይን የኖረህና እኔ ዐይነ - ስውር የሆንኩት ለዚህ ነው! እይበት! ሰው ሁንበት ብዬ ነው!”
ልጅ በእጁ ይዞ የቀረው ፀፀትን ብቻ ነው!
*   *   *
እናትየውን ኢትዮጵያን አድርገን ብናይ ብዙ ነገር እንማራለን! የዛሬው ትውልድ ከላይ እንደተጠቀሰው ወጣት እንዳይሆን እንመኛለን፡፡
ዛሬም ወጣቱ የማያፍርበት አገር እንዳለው ልናሳውቀው ይገባል፡፡ ከራስ ወዳድነት የፀዳች አገር እንዳለችው በኩራት ማሰብ ይገባዋል፡፡ ጽጌረዳ ያለ እሾክ እንደማትኖር ልብ ይል ዘንድ ልንመክረው ይገባል!
ድርቅ እና የኑሮ ውድነት ዛሬም ከጫንቃችን ላይ አልወረዱም! “የደመናው ሎሌ” የሚለውን ግጥም ያስታውሰናል፡-
ለወትሮው ደመና ፊቱ እየጠቆረ
ዐይኖቹን አሻሽቶ ያነባ ነበረ
    ይዘንብ ነበረ
የዘንድሮ ሰማይ ፈጋግ ሰማያዊ
መልኩን አሳምሮ
ስንቱን ፈጀ በላ ከራብ ተመሳጥሮ
የምድር ከርስ አረረ
አገር ጦም አደረ
ሰው ምጡ ጠናና
ዐይኖቹን አቀና
እንዲሁ ከርተት ከርተት ሰማይ ለሰማይ
ውሃ የለሽ ህዋ ጠብታ-አልባ ጠፈር
ሰማይ አይታረስ በዐይን ብሌን ሞፈር
የዳመናው ሎሌ የዳመናው አሽከር
የዕለት ግብሩ ሆነ ጦም ውሎ ጦም ማደር
ዕንባውን እረጫት ሽቅብ ወደ ላይ ድንገት
ዝናብ ሆና ትወርድ ይሆን ወይ?!
ታህሣሥ 1977 ዓ.ም
(ለ1977 ድርቅ)
የመንግስት ሠራተኞች የተጨመረውን ደሞዝ መሰረት ያደረገ የነጋዴዎች የሸቀጥ ዕቃ ዋጋ መጨመር፤ ሌባና-ፖሊስ ጨዋታ አስገራሚ ነው! ህዝብና ነጋዴ አይጥና ድመት ሆነው መኖር የለባቸውም! ውስጠ-ነገሩ የሀገራችንን ነገር፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ሂደት፣ የየትውልዱን ማንነትና የፖለቲካ ተዋንያን ከእናት አገራቸው ጋር ያላቸውን ትሥሥር ሊያመላክተን የሚችል ነው፡፡ መልካም-ትውልድ የመሠረቱን አይረሳም፡፡ ሰፊውን የሀገሩን ሥዕል በሆደ ሰፊነት ያስተውላል፡፡ ከሀገር በፊት የሚመጣን ራስ ተኮርና ራስ ጠቀም አካሄድ ያስወግዳል፡፡ ከእርስ በእርስ መናቆርና መወጋገዝ፤ ከእኩይ ሙግት፣ ከእኔ ልግዘፍ ፖለቲካ፣ ከቀረርቶና ከሜዳሊያ ፍለጋ ሩጫ ራሱን ያገልላል ‹‹ከወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንባዩ ፍጥጥ›› ጨዋታ ራሱን በጊዜ ይገላግላል!
መጪው ትውልድ አርአያ ይሻል! አርአያ ልንሆነው ልባችን ይሙላ፣ ሁሉን ነገር ለመንግስት ጥለን አንችለውም! መንግሥት ያለውን ቢል ህዝብ እንደምን ተቀበለው ብሎ ጥናት ማካሄድ የነገራችን ሁሉ አልፋ- ኦሜጋ ነው፡፡ መንግሥት ሊሣሣት ይችላል፡፡ ማረሚያ ነጥቦቹ (Check-points) እኛ ነን!
ተሳስተሃል አቅጣጫህን ቀይር ማለት ኃላፊነታችን ነው (We are the watch-dogs) ይላሉ ፈረንጆቹ እንጂ ተረቱ እንደሚለው፤ ‹‹ንጉሥ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል›› እያልን ብዙ አንራመድም! በቀናነት ዕድሜውን ይስጠን!!

አሜሪካ በአመቱ የምትቀበላቸው ስደተኞች ቁጥር ከ110 ሺህ ወደ 50 ሺህ ዝቅ ተደርጓል

        የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሙስሊም አገራት ዜጎችን ተጠቂ ያደረገ ነው በሚል አለማቀፍ ተቃውሞ በገጠመውና ከአንድ ወር በፊት ባወጡት የጉዞ ገደብ ላይ የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረጉት አዲሱ የጉዞ ገደብ ትዕዛዝ፣ ከአገራትና ከተመድ ተቃውሞ እንደገጠመው እየተዘገበ ነው፡፡
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሱዳናውያን በአሜሪካ በተካሄዱ የሽብር ወንጀሎች ላይ ተሳትፈው እንደማያውቁ በማስታወስ፣ በመጪው ሳምንት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀውና ለሶስት ወራት ይቆያል በተባለው በዚህ የጉዞ ገደብ ትዕዛዝ ከልብ ማዘኑን መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ሱዳንን ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ በሚል ከዘረዘራቸው አገራት ተርታ ማሰለፉን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፤ ሱዳንን ከዝርዝሩ እንዲያወጣ በድጋሚ መጠየቁንም ዘገባው ገልጧል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ በበኩላቸው፣ አሜሪካ የጉዞ ገደቡን እንድታነሳ የጠየቁ ሲሆን፣ የጉዞ ገደቡ በቀጥታ ተጠቂ ከሚያደርጋቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች መካከል፣ በኬንያው ዳባብ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ሆነው ወደ አሜሪካ የሚገቡበትን ቀን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ 15 ሺህ ያህል ሶማሊያውያን ስደተኞች ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ 150 ሺህ ያህል ሶማሊያውያን ስደተኞች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጉልህ አወንታዊ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ያሉት ፎርማጆ፤ አገራቸው አልሻባብን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ የጀመረቺውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል በመግለጽ፣ የጉዞ ገደቡ ይህን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ፣ ስደተኞች በአገራቸው የገጠሟቸውን መከራና ስቃዮች ለማምለጥ አገራቸውን ጥለው ለመውጣት የተገደዱ ዜጎች እንጂ ወንጀለኞች አይደሉም፣ የትራምፕ ትዕዛዝ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የሃዋይ ግዛት አስተዳደር የትራምፕ የጉዞ ገደብ እንዳይተገበር የሚጠይቅ ክስ ባለፈው ማክሰኞ መመስረቱንና የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑ ሁለት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላትም የጉዞ ገደቡ ሙስሊሞችን ታላሚ ያደረገ አግላይ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ፣ ትዕዛዙ ተግባራዊ እንዳይደረግ ተግተው እንደሚታገሉ ማስታወቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ባወጡትና ተግባራዊ እንዳይደረግ በፍርድ ቤት ውሳኔ በታገደው የጉዞ ገደብ ትዕዛዝ ውስጥ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የተከለከሉት አገራት ኢራን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ የመን፣ ሶርያ፣ ሊቢያ እና ኢራቅ እንደነበሩ ያስታወሰው ዘ ጋርዲያን፣ ትራምፕ በአዲሱ ትዕዛዝ ኢራቅን ከዝርዝሩ ማውጣታቸውን ዘግቧል፡፡
በአዲሱ ትዕዛዝ ለውጥ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል፣ የስድስቱ አገራት ዜጎች የሆኑ ቋሚ ነዋሪዎች፣ ቪዛ ያላቸው፣ ከዚህ ቀደም በስደተኝነት የተመዘገቡ ወይም ጥገኝነት የተሰጣቸው እንዲሁም ሁለተኛ ዜግነት ያላቸው ሰዎች የጉዞ ገደቡ ሳይመለከታቸው ወደ አሜሪካ መግባት እንዲችሉ መፍቀዱ ይጠቀሳል፡፡
የአሜሪካ መንግስት በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ 110 ሺህ ያህል ስደተኞችን ለመቀበል አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ የትራምፕ የጉዞ ገደብ ግን በአመቱ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ቁጥር ከ50 ሺህ መብለጥ እንደሌለበት የሚያግድ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የዘንድሮው የአለም የሴቶች ቀን ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የሴቶች መብቶች እንዲከበሩና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ በሚጠይቁ እጅግ በርካታ ሴቶች የተሳተፉባቸው አድማዎችና የተቃውሞ ሰልፎች በአለም ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ አገራት ከተሞች ባለፈው ረቡዕ ተከብሮ ውሏል፡፡
በዕለቱ በማድሪድ ከ40 ሺህ በላይ ሴቶች አደባባይ ወጥተው የመብት ጥሰቶች እንዲቆሙ በተቃውሞ ሰልፍ የጠየቁ ሲሆን፣  ከአስር ሺህ በላይ የቱርክ ሴቶችም በመዲናዋ ኢስታንቡል ባደረጉት ሰልፍ “ወንዶች በሴቶች ላይ የሚፈጽሟቸው ጾታዊ ጥቃቶች ያብቁ” ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
በአሜሪካ አንዳንድ ከተሞች “አንድ ቀን ያለ ሴት” የሚል መሪ ቃል ባለው አድማ፣ በርካታ ሴቶች በዕለቱ ከስራ ገበታቸው በመቅረት የሴቶችን ሚና ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን ኒውዮርክንና ዋሽንግተንን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የአለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ሰልፍ እንደወጡ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አየርላንዳውያን ሴቶች በበኩላቸው፤ ውርጃን የሚከለክሉ የአገሪቱ ህጎችን በመቃወም ከስራ የማቆም አድማ ከማድረግ ባለፈ ቀኑን ሙሉ ጥቁር ልብስ ለብሰው ውለዋል፡፡ የፖላንድ ሴቶች የእግር ጉዞ በማድረግ መንግስታቸው የጾታ እኩልነትን እንዲያሰፍንና ጥበቃ እንዲያደርግ የጠየቁ ሲሆን፣ ለሴቷ ተገቢው ክብር እንዲሰጣትም ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
ከመቼውም ጊዜ በተለየ በበርካታ የአለማችን አገራት ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ለመብቶቻቸው መከበር አደባባይ በስፋት በመውጣት ድምጻቸውን ያሰሙበት ነው በተባለው በዘንድሮው የአለም የሴቶች ቀን፤ በሜክሲኮ፣ በፖላንድ፣ በኬንያ፣ በጀርመን፣ በዩክሬን፣ በየመንና በሌሎች የአለማችን አገራት የተለያዩ ሰልፎች፣ አድማዎችና ተቃውሞዎች ተከናውነዋል፡፡

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ ዘጠኝ አገራት በድምሩ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የርሃብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ ሶማሊያና
ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ ዘጠኝ አገራት የርሃብ አደጋ ከተጋረጠባቸውና አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 17 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መካከል 33 በመቶ ያህል የሚሆኑት ሶማሊያውያን መሆናቸውንና ከአገሪቱ ህዝብ ግማሽ ያህሉ የችግሩ ሰለባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ሶማሊያን የጎበኙት ጉቴሬዝ፣ የዝናብ እጥረትና ግጭት በአገሪቱ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ እያባባሰው እንደሚገኝ በመጠቆም፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ በሶማሊያና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት ለተከሰተው የርሃብ አደጋ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ታዋቂው ድረገጽ ጎግል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልጣናቸውን ያስረከቧቸውን አዲሱን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለማስገደል ሲያሴሩ ነበር በሚል ባለፈው እሁድ ያሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ፣ ብዙዎችን እያነጋገረ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
በድረገጾች አማካይነት የሚሰራጩ ሃሰተኛ ዜናዎችን እየተከታተለ እንደሚያጠፋና አሳሳች መረጃዎችን እንደሚቃወም ከወራት በፊት በይፋ ያስታወቀው ጎግል፤ ፊቸርድ ስኒፔትስ በተባለው ልዩ የድረገጽ የመረጃ አገልግሎቱ ኦባማ ከቻይና ጋር በመተባበር ትራምፕን ለማስገደል ሲያሴሩ ነበር የሚል ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ዌስተርን ሴንተር ፎር ጆርናሊዝም የተባለ ተቋም ይፋ ካደረገው ሚስጥራዊ ቪዲዮ አገኘሁት በሚል ጎግል ባለፈው እሁድ ይፋ ባደረገው በዚህ መረጃ፣ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ሰሞን ትራምፕን ለማስገደል ሲያሴሩ እንደነበር ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ ብዙዎችን ማነጋገር መጀመሩን ተከትሎ ጎግል መረጃው ሃሰተኛ ነው ሲል ማስተባበሉን ገልጧል፡፡
ጎግል ባወጣው የማስተባበያ መግለጫ ሆን ብሎ ሃሰተኛውን መረጃ እንዳላሰራጨ በመጥቀስ፣ ተጠቃሚዎች ለሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት ፊቸርድ ስኒፔትስ የተባለው ልዩ የመረጃ አገልግሎቱ፣ ምላሾችን የሚሰጠው ከተለያዩ ድረገጾች የሚያገኛቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ያልተረጋገጠው መረጃ ከተጠቃሚዎች ዘንድ ሊደርስ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ኦባማ በትራምፕ ላይ የግድያ ሴራ ሲያደርጉ ነበር የሚለው መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን በማረጋገጥ በአፋጣኝ ከድረገጹ እንዲወገድ ማድረጉን የጠቆመው ጎግል፤ ሃሰተኛው መረጃ በመሰራጨቱ ሳቢያ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት ይቅርታ እንደሚጠይቅም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

 ኩባንያው አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለቺውን ማዕቀብ ጥሷል ተብሏል

       የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለቺውን የንግድ ማዕቀብ በመጣስ በህገወጥ መንገድ የአሜሪካን የተለያዩ ምርቶች ለኢራን በመሸጡ ባለፈው ማክሰኞ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት እንደተጣለበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ኩባንያው የንግድ ማዕቀቡን በሚጥስ መልኩ የአሜሪካን የተለያዩ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ምርቶች ወደ ኢራን መላኩ እንዲሁም ህጋዊ የኤክስፖርት ፈቃድ ሳይኖረው የአሜሪካ ምርቶች የሆኑ የሞባይል ቀፎዎችን ወደ ሰሜን ኮርያ እየላከ መሸጡ በምርመራ በመረጋገጡ በድምሩ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል ቅጣት እንደተጣለበት ዘገባው ገልጧል።
ዜድቲኢ እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2016 በነበሩት አመታት 32 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የአሜሪካ የኮምፒውተር ራውተር፣ ማይክሮፕሮሰሰርና ሰርቨር ምርቶችን ወደ ኢራን መላኩ መረጋገጡን የጠቆመው ዘገባው፤ በርካታ የአሜሪካ የሞባይል ቀፎ ምርቶችንም ለሰሜን ኮርያ ገበያ ማቅረቡን አስታውሷል፡፡
በአሜሪካ አራተኛው ግዙፍ የስማርት ፎን ሽያጭ ኩባንያ የሆነው የዜድቲኢ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዣኦ ሢያንሚንግ፣ ኩባንያው ጥፋቱን መፈጸሙን በማመን ሃላፊነቱን እንደሚወስድ የገለጹ ሲሆን  ዜድቲኢ በቀጣይ የንግድ አሰራሩን ለማሻሻል እንደሚሰራ ማስታወቃቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡

ሰተቴ - ያልዘመርንለት ሌላኛው ጀግና
በቁም ለገደሏት ለሞተች ሀገሬ
ባንድ አይኔ አነባለሁ አንዱን አሳስሬ፡፡
(“ሰተቴ”፣ ገጽ 58)
“ሰተቴ”፣ በቅርቡ ለንባብ የበቃ አዲስ መፅሐፍ ነው፡፡ እንደ መነሻ በአንድ ግለሰብ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን የታሪክ ጥናትና የምርምር ውጤት ነው፡፡… ሐገራችን ላይ ሰተቴን ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ ውስጥ ያልዘመርንላቸውና ጨርሶም ያልተረዳናቸው ጀግኖቻችን ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ …ከሰተቴ ጋር በተያያዘም ከእስከዛሬው ቁርጥራጭና የተዛባ  አቀራረብ በተለየ መንገድ ከሰሞኑ ጠብሰቅ ብሎ የቀረበ የሚመስለው “ሰተቴ” መጽሐፍ ስለ ሰተቴ ማንነትና ስራዎች የተሻለ ምላሽ ይዞ መጥቷል።
“ሰተቴ” የተሰኘውን መጽሐፍ ያበረከቱልን ደራሲ ዲራዓዝ፣ በባለታሪኩ ሕይወት  ዙሪያ  ጥናታዊ  ምርምር  እንዲያካሂዱ  ያነሳሳቸውን ምክንያት በመፅሃፉ (ገፅ 20 ላይ) እንዲህ በማለት አስፍረዋል፡-
“ስለ ትናንት  ማንነታችን  የተሟላ   ምስል   እንዲኖረን ብቻ  ሳይሆን   እንድንማርበትም ካስፈለገ፣  ትናንትን  የምንመረምርበት የታሪክ  መነፅር  ከአንድ አይናነት  ወደ   ሁለት፣ ሶስት፣ አራት… አይናነት ሊሸጋገር፤  እንደ አዳኙ ሁሉ ከታዳኙም ግንባር፣  እንደ መሪው ሁሉ ከተርታው ሕዝብም አንፃር ሊጠና፣ ሊመረመር፣ ሊፃፍና ሊነበብ ይገባል፡፡ በምርጫ የተቀላቀልኩትንና  እስከ  መመረቅ  ድረስ    ታላቅ  ዋጋ  ሰጥቼ  የተከታተልኩት  የታሪክ ትምህርት፣ ይህን ሽግግር በሚደግፍ ጥናት  ማክተም እንዳለብኝ በማመን የመመረቂያ ጥናት  ፅሁፌን እጅግም ታሪክ   ትኩረት ባልሰጠውና ባልተዘመረለት   የጅማው   ከድር ሰተቴ ሕይወት ዙሪያ እንዲያጠነጥን የወሰንኩት በዚህ የተነሳ ነበር፡፡”
መልከ ብዙው ሰው…
እግር ጥሎት ጅማ የሄደ ሰው፣  ከቡናዋ ባልተናነሰ መልኩ ስለ አንድ ሰው ዝና ጎልቶ ይወራለታል፡፡ ስለ ሰተቴ የሰሙ ሰዎችም በአብዛኛው ከሳቅ የዘለለ ነገር ስለማትረፋቸው በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ … ብዙዎች ሰተቴን እብድ፣ ጭራሽም በእውኑ ዓለም ያልኖረ፣ በብልግና እና ደርግን በሚወርፉ ግጥሞቹ ብቻ መስለው ሊያቀርቡት ይሞክራሉ፡፡ የተቀሩት ጥቂቶች ደግሞ ሰተቴ አንዳች ተልዕኮ ያለውና ሊመረመር የሚገባው ጥልቅ ሰው እንደሆነ ያምናሉ፡፡  አሁን ላይ ስለ ሰተቴ በተሻለ መንገድ ሰፋ ያለ ሀተታ ያቀረቡት ደራሲው ዲራዓዝም ባካሄዱት ምርምር፣ የሰተቴን ትክክለኛ ማንነትና የበዙ መልኮች በመረጃ ጭምር ለማስደገፍ እየሞከሩ ያሳዩናል፡፡
ጣሊያን ኢትዮጵያን  በወረረች በ3ኛው ዓመት በ1931 ዓ.ም አካባቢ በጅማ መንደራ ውስጥ  የተወለደው ባለታሪኩ `ከድር መሐመድ  ሐሠን  ቢላል` በብዙዎች አጠራር ከድር ሰተቴ፤ እናቱ ሳዲያ ሀቢብ ትባላለች፡፡ እናትና አባቱ ከወለዷቸው አራት ወንድና ሁለት ሴቶች መካከል ከድር ቀዳሚውና የመጀመሪያ ልጅ ነው፡፡ ከድር ሁልጊዜም ዘናጭና እጅግ በተሳካ የንግድ ህይወት ውስጥ ጭምር ያለፈ ሰው ስለመሆኑ ደራሲው በማስረጃ ጭምር እያስደገፉ ይነግሩናል፡፡  የከድር የልጅነት ሕይወቱ፣ የተጓዘበት  የሕይወት መንገድ፣  የጅማ ነባራዊ ሁኔታ፣ የጥበብ ሰው ወይም ፈላስፋ ለመሆኑ ፍንጮች  ቢሰጥም፣ ደራሲው ከምንም ነገር  በፊት  ከድር  ከዘመኑ ቀድሞ ስለመፈጠሩና ልዩ ችሎታን  የታደለ የጥበብ ሰው ስለመሆኑ ማስረጃ ተደርጎ በብዙዎች  የሚቀርበው  ሃሳብ፣ ተቀምጦ ይሁን   አልያም  ሲዘዋወር  በድንገት የሚያስተውለውን  ክስተት  በተዋበ  ግጥም  ከሽኖ ያለ አንዳች ፍራቻ እዚያው በዚያው ማቅረብ በመቻሉ ነው ይላሉ፡፡
አልችል ብዬ መርገጥ፤ነፍሴን በግሬ ዳና
ስቃዬን አያለሁ፤ዘንድሮም እንዳምና፡፡
(ሰተቴ፣ ገጽ 45)
አብዮተኛው …  
ብዙዎች ሰተቴ ሲባሉ ወደ አፋቸው ቀድሞ የሚመጣው ግጥሙ፡-
ኢሰፓኮ
ባዶ ፓኮ
የሚለው ነው፡፡ ሰተቴ መሰል ግጥሞቹን ምንም ላይ ሳያሰፍራቸው ድንገት ከማውረዱ ባሻገር በአደባባይ ላይ ጮክ ብሎ ነበር የሚላቸው፡፡ ታዲያ ጊዜውን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ጊዜው አይደለም የፈለጉትን እንዲህ በአደባባይ ለመናገር ቀርቶ፣ ዝም ብሎ መኖር እንኳን ያስፈራ የነበረበት የደርግ ዘመን ነው፡፡ ከድር ሰተቴ ደርጎች ስልጣን ይዘው ከተረጋጉና የህዝብ አገልጋይና ሀቀኛ ነን በሚል ካኪያቸውን መልበስ በጀመሩበት ወቅት እንደ ልማዱ ማንንም ሳይፈራ አደባባይ ላይ ወጥቶ ድምጹን ሳይቆጥብ፡-
ልብሳቸው ሀቀኛ
ውስጣቸው ጠንቀኛ፡፡
ሲል ካኪ ለባሽ ደርጎችን በአደባባይ ያለ አንዳች ፍራቻ ሸንቁጧቸዋል፡፡  
በሃገራችን ረጅም  የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በሃይል ተደግፎ፤ በአመፃ  ታጅቦ፣ አገርና ምድሩን ከብዶ ከተጫነውና ጎልቶ ከሚቀነቀነው ተረክና ዜማ በተለየ መልኩ ወይም በተቃራኒው … በአደባባይ ለእውነት ጠበቃ   መቆም፤ መንግስታዊ  ግፍን በመቃወም  ከተጠቁትና ልሳናቸው  ከተለጎመው ወገኖች ጎን በመቆም  አንደበታቸው መሆን የእውቀት ቀንዶች፣ የጥበብ ሊቆች ድርሻና ሞራላዊ ኃላፊነት ተደርጎ ቢወሰድም በተግባር መሬቱ ላይ የምናገኘው ተጨባጭ እውነታ ግን ከሚባለው የሚገጥም  አይደለም፡፡  አልፎ  አልፎ  በዚህ  ደረጃና  ቁመት   ሊሰለፉ  የሚችሉ   ዜጎች   ኖረው ማለፋቸውን  የምንክደው  ባይሆንም  የአመዛኞቹ  አካሄድ  በዝምታ  ተሸብበው፣ በአድርባይነት ተከበው ከራሱ ከአፄ ቴዎድሮስ  ገበሬ ባልተለየ መልኩ፡-
ልጅ አሳድግ ብዬ
ከብት አረባ ብዬ
ለወታደር ዳርኳት
ሚሽቴን እቴ ብዬ ---
በሚል ቅኝት ቄሱም ጭጭ መፃፉም ጭጭ ብለው ዘመን መሻገራቸውን እናውቃለን፡፡ በተለይም   መንግስትን  በአደባባይ  ቀርቶ  በጓዳም  መውቀስና  መቃወም ወንጀል  ሆኖ በሚያሳስር፣ በሚያስገርፍና  በሚያስገድልበት  በዚያ  የጨለማ   የደርግ ዘመን፣ ከድር ሠተቴ ተለይቶ እንደምን ሊበቅል ቻለ ? ያጠያይቃል፡፡
እንደምን ደፍሮ ደርጉን  እስከ ዶቃ  ማሰሪያው በአደባባይ  ሊያስታጥቀው ቻለ? ከምንም  ነገር  በላይ መጽሐፉን  ስናነብ  ቀድሞ  ወደ አእምሯችን  የሚገባ  ጥያቄ  ነው፡፡  ደራሲው   በቀጥታ ወደ ድምዳሜ የምናመራበትን  መረጃ ከማቀበል ይልቅ  በጅማ ቆይታቸው ከከድር ወዳጅ ዘመዶች፣ አብሮ አደጎችና የጅማ ነዋሪዎች ያሰባሰቡትን መረጃና  እጃቸው የገቡትን የከድር ሠተቴ ሥራዎች በፈርጅ በፈርጅ በመከፋፈል   የባለታሪኩን አንድም ሁለትም ሶስትም ገጽታ በግጥም ስራዎቹ በኩል ያቀርቡልናል፡፡
ትቅደም ኢትዮጵያ!
አላችሁ…  አላችሁ…  ጫማ ቀየራችሁ፤
ትቅደም ኢትዮጵያ!
አላችሁ… አላችሁ…  ሱሪ ቀየራችሁ፤
ትቅደም ኢትዮጵያ!
አላችሁ… አላችሁ…  ሹራብ ቀየራችሁ፤
አቤቱ ወጋችሁ፤
ኢትዮጵያ ተረስታ፣ አየን ፊት ቆማችሁ፡፡
*   *   *
በአስተዳዳሪ፤  
ሁሉ ሆነ ታሳሪ፡፡
በኢሰፓ  ተጠሪ፤
ወላጅ አጣ ጧሪ፡፡
በወታደር  ኮሚሳር፤
ወጣት ታፍሶ ለአሳር፡፡
ያልተፈቱ እንቆቅልሾች    
እንዲህ ያለውን ከእውነት ይልቅ ለተረት የቀረበ የሚመስለውን ታሪክ ሰምተው ግራ የተጋቡ ሰዎች ናቸው ሰተቴን በምድር ላይ ኖሮ ያለፈ ሰው መሆኑን የሚክዱት፡፡ በተለያየ ማስረጃ በምድር ላይ ኖሮ ማለፉን ቢያምኑ እንኳን ሌላ ተቀጽላዎችን ይለጥፉበታል፡፡ እብድ፣ የጎዳና ተዳዳሪ፣ የኔ ቢጤ፣… ሲሉ ወደ ራሳቸው ድምዳሜ ለመድረስ ይቸኩላሉ፡፡
እኛው ራሳችን በተሳፈርንበት የጊዜ ታንኳ አብሮን ተሳፍሮ የነበረ ዜጋችንን   በምን ምክንያት ይህን ያህል ልናጣው ቻልን፣ ያጠያይቃል፡፡ የመገንባት ያህል ማፍረስ ባልተለየው ታሪካችን እንጂ ሌላ  ማንንም ተጠያቂ አድርገን ልንወስድ የምንችልበት መንገድ የለም፡፡ ማስረጃዎችን በዝርዝር የሚያቀብሉን ደራሲው ዲራዓዝ፤ ለከድር የተሰጠው ዥንጉርጉር ገፅታ ግራ ቢያጋባቸው፣ በአንድ ዘመን፣ በአንድ ከተማ ውስጥ ኖሮ ያለፈን ስጋ ለባሽ ፍጡር በምን ምክንያት አንድ ትውልድ ሶስት መልክ ሊሰጠው ቻለ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ (ገጽ 55)
በጣም የሚደንቀውና በዘመንም ላይ እንድናዝን  የሚያደርገን  የሠተቴ  መታወቂያ አሻራ  ሆነው የዘለቁት  ግጥሞቹ የላይኞቹ  አይደሉም።  በተቃራኒው  በሞት  ጥላ የተከበቡ፣ የኖረበትን ጊዜ  መራራ ግፍና በደል፣ ተስፋ መቁረጥና ሀዘን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ የጅማ  ነዋሪዎችም  ሠተቴን  የሚያውቁት  በአመፃ ግጥሞቹ እንጂ  ከላይ በሰፈሩት ግጥሞች እንዳልሆነ መጻፉ ከመተረኩ በተጨማሪ ለዚህ ያበቃውን ምክንያት የአብዮቱ  የጨለማ  ዘመኖች  በርካታ  የቅርብ  ወዳጅና  ተማሪ  ጓደኞቹን  በሞት የተቀማው ከድር ሰተቴ፣  ቀድሞ ከሚታወቅበት የወግ ግጥሞች በመውጣት፤ በደርግ ላይ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ የዓመፃ ግጥሞች ማውረድ የጀመረው `ከዚህ ጊዜ አንስቶ ነው` ይላሉ -  የሚያውቁት፤ ሲሉ ሹክ ይሉናል ደራሲው - በዚያ ሀዘንና ምሬት ከተጻፉ ግጥሞቹ ውስጥ አንዱን እንዲህ መዞ በማውጣት፡፡
ደምህን ላይልሰው፣  ስጋህን ላይበላ፤
ግፉ ልክ የለውም፣  ሰው ሰውን ሲጠላ፡፡
ደራሲው ለጥናትና ምርምራቸው የመረጡት የታሪክ ግንባር አዲስ ባይሆንም  መጽሐፉን ያቀረቡበት የጥበባዊ  ደረጃ    ከፍታ  ማለትም  የጠራ  የቋንቋ  አጠቃቀማቸው፣  መልዕክቱን  ለማስተላለፍ የተከተሉት የምዕራፍ አደረጃጀት፣ የማይደነቃቀፍ የሃሳብ ፍሰት፣… ልክ ልብወለድ የምናነብ ያህል አንዴ ከጀመርን ሳንጨርስ የማናስቀምጠው እንዲሆን ብርቱ አቅም አላብሶታል፡፡
ትንቢተኛው ሰተቴ
ሰተቴ አትመለሱም ብሎ በግልጽ የነገራቸው ሰዎች ሳይመለሱ በወጡበት ቀርተዋል፡፡ በግጥሞቹም መጪዎቹን ጊዜያት መተንበይ ችሏል። አቅጣጫዎችንም አመላክቷል፡፡ ለምሳሌም አንድን አጋጣሚ ለመጥቀስ ያህል ሰተቴ የ1977ቱ ድርቅ ከመከሰቱ ዓመታት ቀደም ብሎ ገጠመ የተባለውን ግጥም ብዙዎች የከድር መገለጫ አድርገው ያነሱታል፡፡
ሰባ ሰባት ፣
አንድ እንጀራ ለሰባት፤
እሱም ከተገኘ ምንአልባት!
ረሀቡን ተከትሎ በሚመጣው እልቂት የተነሳም የመቀበሪያ ቦታ ችግር እንደሚሆን በዚሁ ግጥም ላይ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ትንቢቱን እንደሚከተለው አስፍሯል፡፡
ሰባ ሰባት ፣
አንድ ጉድጓድ ለሰባት፤
እሱም ከተገኘ ምንአልባት!
ተጫዋቹና አሽሙረኛው ሰተቴ
ኮሎኔል ተድላ የተባሉ የጅማ ፖሊስ አዛዥ ነበሩ፡፡ ሰውዬው ከአብዮቱም በላይ ለሚስታቸው ቃል ታማኝና ታዛዥ ነበሩ ይባላል፡፡ ታዲያ ይህንን የተረዳው ሰተቴ እንደሚከተለው ይሸነቁጣቸዋል፡፡
የፍርድዎ ውሳኔ፣
በጓሮ በር በኩል
ከጓዳ ከመጣ፤
ዳኛ ቤትዎ ይቅሩ!
ሚስትዎ ችሎት ትምጣ፡፡
በሌላኛው ቀን አንድ ምሽት ላይ የደርግ ባለስልጣናት በልዩነት ከሚቀማምሱበት መሸታ ቤት ድንገት ሰተት ብሎ የገባው ሰተቴ፤ ባዶ እጁን በሽጉጥ ቅርጽ አስመስሎ “እጅ ወደላይ!” ብሎ ያዝረከርካቸዋል፡፡ በዚህ ምሽት ህዝብን ሲያሸኑ የከረሙ ቱባዎች ሁላ ሽንታም ሆኑ፡፡… ከቆይታ በኋላ ሽጉጥ አለመያዙን ሲረዱ እያዳፉ ወደ እስር ቤት ይወስዱታል፡፡  በእለቱ ቃል ይቀበል የነበረው ተረኛ ፖሊስ፤ “ዛሬ ደግሞ ማንን ተራግመህ መጣህ?” ቢለው፣ ሰተቴም ከአፉ በፍጥነት ቀበል ያደርግና ፡-
እኛ ያልነው ለፉገራ ፤
እነሱ የሚሉት የመግደል ሙከራ፡፡
ብሎ ይመልስለታል፡፡
በመነሻዬ ለመግለፅ እንደሞከርኩት “ሰተቴ” ልቦለድ አይደለም፡፡ በእውኑ ዓለም ኖሮ ያለፈን ሰው ታሪክ የሚመረምር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ሆኖም እንደ አንድ የታሪክ ጥናትና ምርምር ፅሁፍ ስንመዝነው፣ ከተዋበ መግቢያና መረጃ ማሰባሰብ ውጭ ወደ  ድምዳሜ ማድረስ የሚያስችል ምርመራና ትንተና ተካሂዶበታል ማለት አስቸጋሪ  ነው፡፡ የባለታሪኩ ናቸው የተባሉትን  ግጥሞች  በማሰባሰብ ለንባብ ማቅረብ መቻሉ ታላቅ  እርምጃ  ቢሆንም  ከቀረቡት  መሃል  የሰተቴን  ትክክለኛ  የአሻራ  መገለጫ  መስፈርት በማዘጋጀት የመለየት  ምርመራ  አለመካሄዱ የመጽሀፉ  ክፍተት  ተደርጎ  የሚወሰድ ነው፡፡  ቤተሰቦቹን በቀላሉ ማግኘት ተችሎ በማናገሩ ረገድ ግን እንዳልተሳካው ጥረት ሁሉ፣ ባለቤቱን እንዲሁም  በሕይወት ያሉ የደርጉ ፖሊሶችን፣ ዳኞችን አፈላልጎ በማነጋገር እይታቸውን ለማካተት ጥረት አለመደረጉ ሌላው የመጽሐፉ ተጨማሪ ድክመት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡  ምንግዜም ቢሆን ባለታሪኩን   ያለ ስሙ ስም  ላለመስጠት የምናደርገው ከፍተኛ ጥንቃቄ ለምርምራችን ውጤት ተዓማኒነት  ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ደራሲ  ዲራዓዝ    በ”ሰተቴ”  ሊያስተላልፉልን  የፈለጉትን  መልዕከት  በግልፅ  አስቀምጠው ነው ወደ ጥናትና ምርምር ስራቸው የገቡት፡፡ በመፅሃፉ  ገፅ 15 ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚያስረዳው፤ ሀሳባቸው   የቀድሞውን  ትውልድ ከመውቀስና ከማውገዝ ባሻገር በልኩና በመጠኑ እርሳቸውና የርሳቸው ትውልድ ታሪካችንን ለማቅናት ተጨባጭ እርምጃ ለመጓዝ ያደረገውን  ትግል በመረጃ ለማስደገፍ ከራስ ጋር የተገባ ቃል ነው፡፡
በእርግጥ ደራሲው ታሪክ ከገዢዎቻችን ግንባር ብቻ ሳይሆን ከተገዢዎችና ከተራ ተርታው ሕዝባችንም ሕይወት አንፃር ሊፃፍ መቻሉን በተዋጣለት ጥበባዊ መንገድ አስመስክረዋል፡፡…    ከምንም በላይ ግን፤ በዘርና ቀለም ተሳስበን፣ በእምነትና ፖለቲካ ተቧድነን ካልሆነ በቀር እንደ አንድ ዜጋ፣  እንደ አንድ ነጠላ ነፍስ ውጤቱ ምንም ሆነ ምን፣ ለእውነት መቆም ከእውቀት ቀንዶች ከጥበብ ሊቆች ዜጎች የሚጠብቁት ጥብቅና መሆኑንና በተዳከመው ሞራላዊ መሠረታችን ላይ ነፍስ ለመዝራት የተደረገ ጥረትና ሙከራ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በመጨረሻም “ሰተቴ” ከዚህም በላይ በመጓዝ የትናንት  ታሪካችንን የምንፈትሸው  የዛሬን አብሮነት የሚያፈርስ  ቂም ለመቆፈር  ሳይሆን  አብሮነታችንን  በላቀ   ሚዛናዊ  መሠረት  ላይ ለማኖር  መሆን  እንዳለበት አስተማሪም  አድርገን ብንቀበለው ያስኬዳልና ተደጋግሞ  ሊነበብ ይገባል።
በመጨረሻም ከድር ሰተቴ የማያልፉት ፈተና የሆነባቸው ደርጎች፣ እብድ በሚል ፍረጃ በ1981 ዓ.ም ከእብዶች ጋር ቀላቅለው ይረሽኑታል፡፡ እርግጥ ነው ከድር በራሱ ሞት ላይም ይተነብይ ነበር፡፡ ሞቱ እውን ሊሆን በተቃረበበት ሰሞን እንደሚከተለው ገጥሞ ነበር፡-
መቼ ነው የሞትኩት፣
ማነው የቀበረኝ
ምድር ቀረች ሲኦል፣
ከእንግዲህ ግድ የለኝ፡፡ (ገጽ 101)  

ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ” የተሰኘው የታዋቂዋ እንግሊዛዊት ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ እጅግ ተወዳጅ ቲያትር ለአመታዊው የለንደን ኦሊቨር የቲያትር ሽልማት በ11 ዘርፎች መታጨቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሽልማቱ ታሪክ በበርካታ ዘርፎች በመታጨት ቀዳሚነቱን የያዘውና ከመጽሃፍ ወደ ቲያትርነት የተቀየረው “ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ”፣ ምርጥ ዳይሬክተርና ምርጥ አዲስ ቲያትርን ጨምሮ በድምሩ በ11 ዘርፎች ለዘንድሮው ሽልማት ታጭቷል፡፡
ቲያትሩ በዘንድሮው የኦሊቨር ሽልማት በዕጩነት ከቀረበባቸው ሌሎች ዘርፎች መካከልም፣ የምርጥ የመድረክ ገጽ ዲዛይን፣ የምርጥ የብርሃን ዲዛይን፣ የምርጥ ድምጽ ግብዓትና የምርጥ አልባሳት ዘርፎች እንደሚገኝባቸው ዘገባው አስታውቋል፡፡
በመጽሃፍ መልክ ለገበያ የቀረበው “ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ” ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 አማዞን በተባለው ታዋቂ የድረ ገጽ ሽያጭ ተቋም በኩል በህጻናትም ሆነ በአዋቂዎች መጽሃፍት ዘርፍ በብዛት በአለማቀፍ ገበያ በመሸጥ ቀዳሚነቱን መያዙ ይታወሳል፡፡
የኦሊቨር ሽልማት ዋና ፕሮዲዩሰር ጁሊያን በርድ፤ በዕጩነት የቀረቡት ቲያትሮች የለንደን ቲያትሮች አለማቀፍ ለውጥ በተስተናገደበት አመትም የማዝናናትና አመለካከታችንን የመቀየር ብቃት እንዳላቸው ማሳያ ናቸው ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የሽልማት ስነስርዓቱ በመጪው ሚያዝያ ወር ለንደን በሚገኘው ሮያል አልበርት አዳራሽ እንደሚከናወንም አክሎ ገልጧል፡፡

በደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋፅዮን ጋሻነህ የተፃፈውና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው “ተልዕኮ አርማጌዶን” የተሰኘ ታሪካዊ ልቦለድ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡
     የመፅሀፉ ታሪክ መቼቱን ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ላይ አድርጎ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የአክሱም ፅዮን ታቦትን ለመዝረፍ በተደረገ ሙከራ ዙሪያ ያጠነጥናል። አንድነትና መቻቻል ለአገር ያለውን ከፍተኛ ፋይዳም እንደሚዳስስ የተነገረለት መፅሀፉ፤ መታሰቢያነቱ ለእውቁ የቀዶ ጥገና ሀኪምና ፖለቲከኛ ፕ/ር አሥራት ወልደየስ ተደርጓል፡፡ በ40 ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ176 ገፆች የተቀነበበው ይህ መፅሀፍ፤ በ67 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን ቀጣይ ክፍሉ በቅርቡ ለንባብ እንደሚበቃ ደራሲው ገልጿል፡፡

Page 9 of 330