Administrator

Administrator

 በአቶ ዮናስ ቦጋለ የተተረጎመውና የፖርቹጋላዊው ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬጽ ጥንታዊና ታሪካዊ መጽሐፍ
“አልቫሬጽ በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት ከ1520-1527 ወደ ኢትዮጵያ የተላከ የፖርቱጋል መልዕክት” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው አባ ፍራንሲስኮ አልቫሬጽ፣ በዶን ሮድሪጎ ዴ ሊማ መሪነት የፖርቹጋሉን ንጉሥስ ዳግማዊ ዦአም መልዕክት ለአቢሲኒያው ንጉሥ እንዲያደርስ ከተላከው ልዑክ ጋር ተካፋይ የነበረ ቄስ ሲሆን በኢትዮጵያ በቆየባቸው ሰባት ዓመታት ውስጥ የታዘበውንና የአገሪቱን ሁለንተናዊ ገጽታ “Narrative of the Portuguese Embassy to Abyssinia 1520-1527” ሲል ጽፎታል፡፡
    መጽሐፉ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ገጽታ፤ የፖለቲካ አቅም፤ የኢኮኖሚና የባሕል ጥንካሬዋን በግልጽ ከማሳየቱም በላይ ለታሪክ ተማሪዎች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ጸሐፍት፣ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ለማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች፣ ለጂኦግራፊ ጥናትና ለባህል ሰዎች ጠቃሚነቱ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያለውና ተመራጭ እንደሚሆን ይታመናል ተብሏል፡፡ መጽሐፉ በጠራ ቋንቋና በግሩም አተራርክ፤ በሁለት መግቢያ፣ በሁለት ክፍል፣ ከመቶ በላይ በሆኑ ምዕራፎች የተዘጋጀ ሲሆን በ450 ገፆች ተቀንብቦ በ120 ብር ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡

ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት አባላት ስልጠና በመስጠት
የሚታወቁት አቶ መላኩ ሙሉዓለም ያዘጋጁት የፓርላማን ቀደምት ታሪካዊ አመሰራረት፣ ምንነትና አሰራርን የሚተነትነው ‹‹ፓርላማ፣ ታሪክ፣ ዴሞክራሲና ዲፕሎማሲ›› የተሰኘው መፅሀፍ የፊታችን ማክሰኞ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ አምስት ኪሎ በሚገኘው በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መፅሀፉ በተለይም ፓርላማ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚኖረው ፋይዳና ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲን በሚመለከት ወቅታዊና ተጨባጭ መረጃዎችን አካትቶ ይተነትናል ተብሏል፡፡ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የሁለት ምክር ቤቶች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ባለሙያው ተስፋዬ ይመር የተፃፉ ከ50 በላይ ግጥሞችን ያካተተው ‹‹አዲስ መስመር›› የተሰኘ የግጥም መፅሀፍ ለንባብ በቃ፡፡ መድበሉ በፍቅር፣ በእውነትና በመተማመን ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ግጥሞችን የያዘ ሲሆን በ58 ገፆች ተቀንብቦ ለአገር ውስጥ በ40 ብር እና ለውጭ አገራት በ10 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 በደራሲ ጋዜጠኛና መምህር የኑስ መሐመድ የተዘጋጀው ‹‹አማርኛ ሰዋሰው እና ሥነ ፅሁፍ›› የተሰኘ
በአማርኛ ሰዋሰው፣ በስነ-ፅሁፍ አለባውያንና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነው መፅሀፍ ዛሬ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በራስ ሆቴል ይመረቃል፡፡
   በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ደራሲያን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚታደሙ ሲሆን በመፅሀፉ ላይ ዳሰሳ እንደሚካሄድና የስነ - ፅሁፍ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

 በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ አተኩሮ የተሰራውና 90 በመቶ ትዕይንቱ ሱዳን ካርቱም ውስጥ የተቀረፀው
“እንቆጳ” ፊ ልም በ ግብፁ ሉ ግዞር ኢንተርናሽናል ፊ ልም ፌስቲቫል ላይ ለእይታ ሊቀርብ ነው፡፡
    በደራሲ ተዋናይና ፕሮዲዩሰር ዩዲት ጌታቸው ተፅፎ በአለምፀሀይ በቀለና በአብርሀም ደምሴ ዳይሬክት የተደረገው ይሄው ፊልም፣ ለፌስቲቫሉ አዘጋጆች ከተለካ በኋላ ለ‹‹Official selection›› በመብቃቱ በፌስቲቫሉ ላይ ለመታየት ማክሰኞ ፊልሙ ወደ ካይሮ እንደሚያቀና ተገልጿል፡፡ በፊልሙ ላይ ሱራፌል ተካ፣ ዮዲት ጌታቸው፣ አለባቸው መኮንን፣ ደረጀ ደመቀና ሌሎችም እንደተሳተፉበት ታውቋል፡፡  

 በማትሪክስ ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ስራዎች በየ15 ቀኑ እየታተመ ለንባብ የሚበቃው ‹‹ሸገር ታይምስ›› አዲስ መፅሄት ዛሬ ከቀኑ 11 ሰአት ጀምሮ በአቤም ሆቴል ይመረቃል፡፡ መፅሄቱ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና
ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊና ለአንባቢ የሚመጥኑ ዘገባዎችን እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

 በኢኮኖሚ ባለሙያው ጸጋ ዘአብ ለምለም የተጻፈው “ሸክም የበዛበት ትውልድ” የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢያን ቀረበ፡፡ መጽሐፉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ የወጎች ስብስብ ነው ተብሏል፡፡
ጸሃፊው በመግቢያው ላይ “ትርጉም ያለው ሐሳብ እውነት ነው፤ ሐሳብ ዘር ነው፤ ዘርን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ዘርን ከማግኘት በላይ ዘር የሚዘራበትን ቦታ ማግኘት ደግሞ እጅጉን ፈታኝ ነው፡፡ በተለይ ቦታው የሰው ልቦና ሲሆን ክብደቱን የላቀ ያደርገዋል፤ ….. ስለሆነም ዘር በተገኘበት ቦታ አይዘራም፤ ዘር በማንኛውም ጊዜ አይዘራም፤ዘር ትክክለኛ ጊዜን ከባለቤቱ ትጋትና ከአስገኝው ጠባቂነት ጋር መቆራኘቱ ለፍሬያማነቱ የግድ ይላል…” ሲል አስፍሯል፡፡ በ280 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤አስራ አራት ክፍሎችና ሃያ አንድ ንዑሳን ክፍሎች ያሉት ሲሆን በ61 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ፖሊሲ ይተቻሉ
            በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውና ወደ 6 ሚሊዮን ገደማ ህዝብን ለአደጋ ያጋለጠው ድርቅ፤ህፃናት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ያናጠበ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ሰዎችንም ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፡፡
ለበርካታ ዓመታት ይህን የድርቅ አደጋና ስጋት ማሸነፍና ማስወገድ ያልተቻለው ለምንድን ነው? ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ አገራዊ ችግር ላይ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳብ ሲያቀርቡ እምብዛም አይስተዋልም፡፡
በወቅታዊው የድርቅ አደጋና ስጋቱ እንዲሁም በዘላቂ መፍትሄዎች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል፡፡

              “መንግስት ስለ ድርቁ ትክክለኛ መረጃ ሊያቀርብልን ይገባል”
                                 አቶ የሸዋስ አሰፋ (የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

       መንግስት ለተፈጠረው ድርቅ የሰጠው ትኩረት በኛ ፓርቲ በኩል አነስተኛ ነው የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡ ከ800 በላይ ት/ቤቶች ተዘግተው፤ በርካቶች ተሰደዋል ግን ስለ ጉዳዩ ብዙ ሲባል አይሰማም፡፡ ይሄ መደባበቅ ነው፡፡ ያለፉ መንግስታት ሲተቹ የነበረውኮ በዚህ የተነሳ ነው፡፡ መንግስት ችግሩን በቅጡ እንድናውቀው አላደረገንም፡፡ አሁን እንደ መረጃ የምንጠቀመው አለማቀፍ ተቋማት የሚያወጡትን ሪፖርት ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ መንግስት ጉዳዩን ሁሉም አውቆት የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ አለበት፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በድርቅ በተጎዱ አካባቢ ያሉ ሰዎችን አነጋግሮ መረጃ ለማግኘት ሞክሮ ነበር፡፡ እንደተረዳነው፤ በጥቅምት መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ በውሃና በግጦሽ እጦት ከብቶቻቸው እንዳለቁባቸውና እነሱም ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ ነው፡፡ በፓርቲያችን እምነት፤ በተደጋጋሚ በድርቅ ለሚጠቁ መሰል አካባቢዎች የሚሆን ተስማሚ ፖሊሲ አለመቀመጡ አደጋውን እስከ ዛሬ ላለመሻገራችን ምክንያት ነው፡፡ 6 ሚሊዮን ህዝብ በድርቅ ተጎዳ ማለት፣ የአንድ ሀገር ህዝብ ያህል ነው፡፡ ይሄን እንኳ በአግባቡ መንግስት ሊገልፀው አልፈለገም፡፡ ተቃዋሚዎች በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርገን፣ መንግስት ላይ ጫና እንዳናሳድር በአሁኑ ወቅት  በብዙ ጉዳዮች ተጠምደናል፡፡ በዚህ ሳምንት እንኳ 12 ሰዎች ታስረውብናል፡፡ ግን ቀንና ቀጠሮ የማይጠይቀው ይሄ ጉዳይ በሚገባው መጠን ንቅናቄ አልተደረገበትም፡፡ ምናልባት መንግስትም ሀገርም በብዙ ችግር መዋጣቸው፣ለጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው ማድረጉን አምናለሁ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ የእነዚህ ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች በድርቅ የመጎዳት ጉዳይ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ ሊደረግበት ይገባል፡፡ አሁንም መንግስት ከምንም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ፓርቲያችን በአቋም መግለጫው አሳስቧል፡፡ መንግስት በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎቻችን ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ፣የመታደግ ስራ ላይ መረባረብ አለበት፡፡
ድርቁ ራሱ መኖሩ ችግር አይደለም፤ ድርቁ ረሃብ ሲፈጥር ግን በግልፅ የመንግስት ፖሊሲ ችግር እንዳለ ያስረዳል፡፡ ለፖሊሲ ውድቀት ከዚህ በላይ ማስረጃ አይገኝም፡፡ በየ10 ዓመቱ ድርቅ እንደሚመጣ ይታወቃል፤ ለምን በቂ ዝግጅት አይደረግም? ዛሬ ከ800 በላይ ት/ቤቶች ተዘግተው፣ እንዴት ችግር ሳይፈጥር ድርቁን እየተቋቋምኩ ነው የሚል ሪፖርት ይሰጣል? ይሄ በቂ የአደጋ መከላከል ዝግጅት እንዳልተደረገ ማሳያ ነው፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፓርቲያችን መደረግ ያለበት ብለን የምናምነው፣በተለይ በተደጋጋሚ በድርቅ በሚጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ውሃ ወዳለበት የሀገሪቱ አካባቢ ማሰባሰብ ነው፡፡ በቀጣይ አርብቶ አደሩ በአንድ ምቹ አካባቢ ተረጋግቶ በመቀመጥ ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲለወጥ ተከታታይ ስራዎች መሰራት አለባቸው የሚለው ነው፡፡ ከመፍትሄዎቹ መካከል እነዚህ እንደ አማራጭ የሚቀመጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ለአስቸኳዩ ችግር ሁሉም አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል፡፡ መንግስት ስለ ድርቁ ጉዳይ ትክክለኛ መረጃ ሊያቀርብልን ይገባል፡፡ ሀቆች መደበቅ የለባቸውም፡፡

------------------

                        ‹‹ድርቅም ቢኖር ረሃብ ሊኖር አይገባም››
                        ዶ/ር ጫኔ ከበደ
                           (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

       በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ፓርቲዎች መንግስት ላይ ግፊት አላደረጉም፤ ነገር ግን በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል አጀንዳው ተነስቶ ውይይት ተደርጎበት ጥናት እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚመጣውን ውጤት እንጠብቃለን፡፡
በአቋም ደረጃ ግን ፓርቲያችን ከሚያራምደው ፕሮግራም አንፃር፣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንዲህ ያለው ድርቅ ሊያጠቃት የቻለው በአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ነገር ግን ድርቅም ቢኖር ረሃብ ሊኖር አይገባም የሚል አቋም ነው ያለን። ሌሎች ሃገሮች ከዚህም የከፋ ድርቅ ይመታቸዋል፤ ነገር ግን ዜጎቻቸው ሲራቡ አይተንም ሰምተንም አናውቅም፡፡ የፓርቲያችን ፕሮግራም በሊበራል የኢኮኖሚ ሲስተም የሚመራ እንደመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቋቋም ራስን በሚያስችል የመስኖ ልማት ውስጥ መገባት አለበት። ወንዞቻችን ከኛ አልፈው ለሌላው የሚተርፉ ናቸው።
ድርቅን ተከትለው የሚከሰቱ ችግሮችን መቋቋም አለመቻላችን የሚያሣየን፣ መንግስት በመስኖ ልማት የዚህችን ሃገር ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚገባው መጠን በቁርጠኝነት እየሰራ አለመሆኑን ነው፡፡ ድርቅን ተቋቁሞ ረሃብን ማጥፋት በሚቻልበት ዙሪያ ብዙ እንዳልተሰራ በየአመቱ ድርቅን ተከትሎ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች አስረጅ ናቸው፡፡
መንግስት ለሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደ ኢነርጂ ላሉት ትልቅ ትኩረት ሲሰጥ እናያለን፤ ነገር ግን በመስኖ ልማት ላይ የጠነከረ ስራ ሲሰራ አይታይም። ይህ መንግስት ከሚከተለው የልማት ፖሊሲ ደካማነት የመነጨ ነው፡፡ የሃገሪቱን ሃብቶች አሟጦ ከመጠቀምና ህዝቡን ከመሰል ችግሮች በዘላቂነት ከመታደግ አንፃር፣ አሁን መንግስት እየተከተለ ያለው ፖሊሲ የተሳሳተ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ለሃገሪቱ ጠቃሚ የሚሆነውና ህዝብን ከድርቅ አደጋ መታደግ የሚቻለው ለሌሎች ልማቶች የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለትላልቅ የመስኖ ልማቶች ሲሰጥ ብቻ ነው የሚል አቋም አለን፡፡ ይሄን ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ተፈጥሮ በየጊዜው እየተዛባ ባለበት ሁኔታ ህዝብን ከችግር መታደግ አይቻልም፡፡ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይም የራሱን አሉታዊ ተፅእኖ ያሳርፋል። ያለንበትን ጂኦግራፊያዊ ሁኔታ በሚገባ በጥናት በመለየት ለየዘርፉ ችግሮች ተመጣጣኝ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
ህዝቡ በመስኖ ልማት ውስጥ እንዲሳተፍ ሰፊ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ለምሳሌ በድርቅ ከተጎዱት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የሶማሌ ክልል ነው። ወደዚያ አካባቢ የሄደ ሰው በእጅጉ ያዝናል፡፡ ያንን የመሰለ ለም መሬት አቋርጠው ወደ ጎረቤት ሶማሊያ የሚፈሱ ወንዞችን ሲያይ በእጅጉ ይቆጫል፡፡ በጣም ነው የሚያስቆጨው፡፡
ወንዞቹ ያንን የመሰለ ለመስኖ ልማት ተስማሚ የሆነ ለም መሬት አቋርጠው ሶማሊያ ገብተው ጥቅም ሲሰጡ ለተመለከተ፣ በእርግጥስ ምንድን ነው ችግሩ የሚል ጥያቄ ያጭርበታል፡፡ ዛሬ ሶማሊያ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ የሙዝና የብርቱካን አቅራቢ የሆነችው፣ የኛን ለም መሬት አቋርጠው የሚሄዱ ወንዞችን ለመስኖ በመጠቀሟ ነው እንጂ ዝናብ የላትም፡፡ እኛ ከባሌ ተራራዎች እየፈለቁ ሶማሌ ክልልን እያቋረጡ የሚሄዱ ወንዞችን ሳንጠቀም፣ ሁልጊዜ የሶማሌ ክልል ህዝብ ተራበ የሚል ሪፖርት ነው የምንሰማው፡፡
ክልሉ ካለው ሰፊ የተፈጥሮ ፀጋ አንፃር እዚያው ሰብሉ ለምቶ፣ እዚያው በአግሮ ፕሮሰሲንግ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በማምረት ትልቅ የምግብ ምርት አካባቢ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ ግን በመንግስት የተሳሳተ ፖሊሲና ትኩረት ማነስ የተነሳ ይሄ እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ዛሬ በድርቅ አዙሪት ውስጥ ለመዳከራችንም ይሄው ነው ዋነኛ ምክንያቱ፡፡

---------------

                        “በድርቅ ለተጎሳቆለ ህዝብ አስፋልት ቢዘረጋለት ምኑ ነው?”
                                ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ ሊቀመንበር)

        ድርቅ ስለመኖሩና በዚህ ምክንያት በህዝብ ላይ ጉዳት እየደረሰ ስለመሆኑ ይሄ መንግስት ለአለማቀፉ ማህበረሰብ መረጃ ለማድረስ ትንሽ ይተናነቀዋል፡፡ መጀመሪያ ምንም ጉዳት እንደሌለ ተገልፆ ነው፣ ቀስ በቀስ የጉዳቱ መጠን ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄደው። “ሀገሪቷ አድጋለች ብዙ ለውጠናታል፤እንዴት ስለ ድርቅ ይወራል” በሚል መንግስት እውነታውን ለመናገር ድፍረት ያንሰዋል፡፡ እውነቱ ግን ይህቺ ሀገር ከድርቅ ጉዳት ለመላቀቅ የሚያስችል ስራ አልተሰራባትም። መንግስት መረጃ አሰጣጡ ላይ መታረም አለበት፡፡ በየዓመቱ ተመላልሶ የሚመጣ እንደመሆኑ ድርቁ ተተንባይ ነው፡፡ በዚህ ተተንባይ በሆነና የራሱ የታወቀ ጊዜ ባለው የተፈጥሮ አደጋ፣ ለምን ዜጎቻችን ይጎዳሉ? የሚለው በእውነቱ አነጋጋሪ ነው፡፡ ሁሉም ወገን ለዚህ ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት መስራት አለበት፡፡ ብዙ ገንዘብ በተለያዩ ብድሮችና እርዳታዎች እየመጣ፣ እዚያም እዚህም ሲበተን እናያለን፡፡
ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ከረሃብ ስጋት የሚያወጣ በቂ ስራ እስከዛሬ አለመሰራቱ በእውነት አስተዛዛቢ ነው። ለህዝቡና ለከብቶቹ በየቦታው ውሃ ማውጣት እንዴት ይከብዳል? ይሄ ከሁሉም መሰረት ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶት መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ለእነዚህ አይነት አካባቢዎች መሰረት ልማት ማለት በዋናነት መንገድ ብቻ አይደለም፤ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ውሃ ነው፡፡ የህዝቡ አኗኗር በእንስሳት ሃብት ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡ ለሱም ለከብቶቹም ውሃ ማግኘት አለበት፡፡ ይሄን መስራት እንዴት ይከብዳል? ውሃ ማቆር እየተባለ እንደ ፋሽን አንድ ሰሞን ይወራል፤ከዚያ እንደዘበት ይቀራል፡፡ አስፋልት ከሚለብሱ መንገዶች በፊት መጀመሪያ የሰው ህይወት መቅደም አለበት፡፡ ይሄንን ባለማድረግ መንግስት ትልቅ በደል እየፈፀመ ነው የሚል ነው የኛ አቋም፡፡
ውሃ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች ውሃ ማቅረብ ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለእንስሳትም ለሰውም ምግብ በበቂ ሁኔታ መድረስ አለበት፡፡ በቂ የእህል ክምችት አለን እየተባለ ነው፤ ታዲያ ለምን ህፃናት ተጎሣቁለው ትምህርት ያቋርጣሉ? ይሄ በእውነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከሁሉ በፊት ዜጎችን ከዚህ ጉስቁልና ማውጣት ያስፈልጋል። በድርቅ ለተጎሳቆለ ህዝብ ውሃ የመሰለ አስፓልት በአጠገቡ ቢዘረጋለት ምንም ስሜት አይሰጠውም፡፡ ለቪዲዮ ቀረፃ ብቻ የሚመቹ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የመኖር ዋስትና ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

-----------------

                        “መንግሥት ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ አለበት”
                          ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት)

       በ1966 እና በ1977 በዚህች ሀገር ያጋጠመው ድርቅ፣ ዜጎችን ለከፋ ረሃብ ዳርጎ፣ የዓለም ህዝብ ታድጎናል፡፡ በ1966 ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ውድቀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረው ድርቁና ረሀቡ ነው፡፡ ደርግም በድርቅ ብዙ ተፈትኗል፡፡ ይሄም መንግስት እየተፈተነ ነው፡፡ ዜጎች ዛሬም የረሃብ ስጋት ላይ በመውደቃቸው የእርዳታ እጅ ተዘርግቷል፡፡ በሌላ በኩል ለፖለቲካ ተብሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚገባው ለድርቁ ነው፡፡ መንግስት አሁን እየተቸገሩ ላሉት 6 ሚሊዮን ገደማ ዜጎቻችን እርዳታ እያቀረብኩ ነው ይላል፤ህዝቡ ደግሞ እየተራብኩ ነው ሲል በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየሰማን ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ከፖለቲካውም ጉዳይ ይልቅ ቅድሚያ ሰጥቶ በዚህ ችግር ላይ ርብርብ ማድረግ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም ጭምር፡፡
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በሚመሩት አማራጭ ኃይሎች ፓርቲ ውስጥ በነበርኩ ጊዜ በወቅቱ በሀገሪቱ ተከስቶ ለነበረው ድርቅ፣ እርዳታ አሰባስበን ለማቅረብ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበን ነበር፤ሆኖም ከመንግስት ቀና ምላሽ አላገኘንም ነበር፡፡ ሁሉም ነገር በፖለቲካ አይን መታየት የለበትም፡፡ ሠብአዊ ድጋፍ የፖለቲካ አቋም አይወስነውም፡፡
መንግስት ከጊዜያዊ እርዳታ ባለፈ በዘላቂ መፍትሄዎች ዙሪያ አማራጭ ሃሳቦችን ከተቃዋሚዎች መቀበል አለበት፡፡ ለምሳሌ ለምንድን ነው ዝናብ ጠባቂ የምንሆነው? ለምን ሰፋፊ መስኖ አይሰራም? ከሁሉም መሰረት ልማቶች ይሄ መቅደም አለበት፡፡ የውሃ አቅማችን ከፍተኛ ነው፤ለምን ይሄን ሃብት ለህዝባችን ጥቅም አናውለውም? ይሄ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡
የዛሬ 40 ዓመት ሩሲያ ሃገር ተማሪ በነበርኩ ሰአት አንድ የሩሲያ ፀሃፊ ስለ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው መፅሃፍ ላይ፣ኢትዮጵያን የአፍሪካ ገነት ይላታል፡፡ “ሃገሪቱ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ራሷን ከመገበች በኋላ ለትላልቅ 6 መንግስታት ህዝቦች የሚበቃ የእርሻ ምርት የማቅረብ አቅም ያላት ናት” ሲል በሰፊው ተንትኖ ፅፏል፡፡ እንግዲህ ዋናው ችግራችን ጥሩና ተስማሚ የፖሊሲ አማራጮችን በሚገባ ፈትሾ በስራ ላይ አለማዋል ነው፡፡  

----------------

                        “ከፖለቲካ በፊት የዜጎችን ህይወት መታደግ ይቀድማል”
                           አቶ ተሻለ ሰብሮ (የኢራፓ ፕሬዚዳንት)

       ከምንም በላይ የህዝብ አድን ስራዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል አቋም አለው፤ ፓርቲያችን፡፡ በየጊዜው ይህ ድርቅና ረሃብ መከሰቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ እስከዛሬም አለመቆሙ ሁነኛ መፍትሄ እንዳልተበጀለት አመላካች ነው፡፡ ድርቅን መቋቋም በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በቂ ልምድ እንዳልተቀሰመም መታዘብ ችለናል፡፡
ለምሳሌ እስራኤልና ግብፅ በረሃማ አካባቢን እንዴት ለሰው ልጆች እንዲመች አድርጎ መግራት እንደሚቻል ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ልምዶች በመቅሰም በሃገራችን ልንሰራበት ይገባ ነበር፡፡ ችግሩ በተፈጠረ ቁጥር የነፍስ አድን ስራ ላይ ብቻ መረባረብ ውጤት የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ የፖሊሲ ጥናት ተደርጎ፣ በልዩ ትኩረት አዋጭና ዘላቂ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ በፖለቲካ መጠላለፍና አተካሮ ሲኖር፣ እንዲህ ያሉ ወሳኝ የህዝብ ጉዳዮች ይዘነጋሉ፡፡ ዘንድሮ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በድርቅ አደጋ ላይ ሆኖ ትኩረት ያልተሰጠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡  
መንግስትም፣ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሄን በብሄራዊ መግባባት ማጤን አለባቸው። ከፖለቲካ በፊት የሰው ህይወትን መታደግና ዘላቂ ዋስትና ማስገኘት ይቀድማል፡፡ ተቃዋሚዎች ይሄን ጉዳይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት፣ህዝቡን እንዲታደግ ግፊት ማድረግ አለብን፡፡ አሁን እንኳ በተጀመረው ድርድር፣ ስለ ድርቅ አደጋ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት፣ በአጀንዳነት ለመወያየት ታስቦ እንደሆነ አናውቅም። ግን ይሄ የህዝባችን ዋነኛ ችግር ነው፡፡ ከፖለቲካም በላይ ነው፡፡ ይህ ተደጋጋሚ ችግር እንዴት እስከዛሬ ዘላቂ መፍትሄ አልተገኘለትም? ሰፊ ክርክርና ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በአባይ ጉዳይ ላይ ያለንን ሃገራዊ መግባባት በድርቅ ጉዳይ ላይ አናስተውልም፡፡
የዜጎችን ህይወት መታደግ ከአባይ ጉዳይም በላይ ነው፡፡ የተለያዩ ፖሊሲዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበው ሰፊ ክርክርና ውይይት ማድረግ አለብን፡፡ በብሄራዊ ደረጃ ይሄን የሚያስፈፅም ትልቅ ንቅናቄ ያስፈልጋል፡፡

   42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከሳምንት በኋላ በኡጋንዳዋ ከተማ ካምፓላ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፤ 66 አገራትን የወከሉ ከ600 በላይ አትሌቶች በአምስት አይነት የአገር አቋራጭ ውድድሮች ይሳተፉበታል፡፡ በሻምፒዮና ከፍተኛውን የውጤት ግምት ያገኙት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለሻምፒዮናው ከ1 ወር በላይ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሙሉ የቡድን ዝርዝር ባይታወቅም፤ በ34ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ በሁሉም የውድድር መደቦች ከ1 እስከ 4 ደረጃ ያገኙት እንዲሁም በወቅታዊ ብቃታቸው እና የጤንነት ደረጃ አስተማማኝ ሆነው የተገኙትን በ5ኛ እና በ6ኛ ደረጃ ለማካተት 40 አትሌቶች በዓለም አገር አቋራጭ ቡድኑ ጊዜያዊ ዝርዝር ተካትተዋል፡፡ በወንዶች ምድብ እነ ሙክታር ኢድሪስ፤  ኢብራሂም ጄይላን እንዲሁም ዮሚፍ ቀጀልቻ በሴቶች ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ ልምድ ካላቸው ምርጥ አትሌቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በ9 አሰልጣኞች እና ረዳቶቻቸው እየተዘጋጀ የሚገኘው  ቡድኑ በአራራት ሆቴል ተቀምጦ ከሚያደርጋቸው ስልጠናዎች ባሻገር በአዲስ አበባ ዙርያ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች የጎዳና ላይ እና የጫካ ልምምዶች እያደረገም ነው፡፡ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች በወንዶች ከ1981 እኤአ ጀምሮ እንዲሁም በሴቶች ከ1991 እኤአ ጀምሮ ሌሎች አገራትን ጣልቃ ሳያስገቡ በአሸናፊነቱ ላይ ተፈራርቀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ባሻገር በተለይ በአዋቂዎች ምድብ ምናልባትም በግል ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ አትሌቶችን እንደሚያሰልፉ የተወሳላቸው ከአፍሪካ አዘጋጇ ኡጋንዳ እና ኤርትራ እንዲሁም የቱርክ፤ የባህሬን፤ የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ የአየርላንድ እና የጃፓን አትሌቶች ናቸው፡፡ ውድድሩን የምታስተናግደው የካምፓላ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋን አረጋግጧል፡፡ ሻምፒዮናውን የሚያስተናግደው በ2014 እኤአ ላይ የአፍሪካ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ያስተናገደው የስፖርት ማእከል እንደሆነ ሲታወቅ፤ በከፍተኛ እድሳት ለውድድሩ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል  አይኤኤኤፍ እውቁን የኬንያ አትሌት ፖል ቴርጋ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና አምባሳደር አድርጎ ሾሞታል፡፡ በአይኤኤኤፍ እና በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባልነት የሚያገለግለው ፖል ቴርጋት በዓለም አገር አቋራጭ ከፍተኛ ውጤት ካመዘገቡ አትሌቶች አንዱ ሲሆን ለአምስት ጊዜያት በረጀም ርቀት 12 ኪሎ ሜትር በማሸነፍ የወርቅ ሜዳልያዎቹን ሰብስቧል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው  ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለቱም ጾታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር እንደሚኖርም ታውቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር በሻምፒዮናው በግልና በቡድን  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች እና አገራትም የገንዘብ ሽልማት ያበረክታል።  በአዋቂ አትሌቶች የሁለቱም ፆታዎች የውድድር መደቦች በግል  ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ በቡድን ውጤት ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ ለ1ኛ 20ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 16ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 8ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆንበሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር ለ1ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 8ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 6ሺ ዶላር፣ እንዲሁም ለ4ኛ 4ሺ ዶላር እንደሚሸለም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ2021 እ.ኤ.አ የ44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ?
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች በአንጋፋነቱ እና በፈታኝነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡  ከ1973 እኤአ ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፤ ከ2011 እ.ኤ.አ ወዲህ ግን በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ሆኗል፡፡ በተለይ ባለፉት 25 አመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድር መደቡ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በመቆጣጠር ያሳዩት የበላይነት  ባስከተለው ጫና ነው፡፡ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 5ኛው  ነው ማለት ነው፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በተሳትፎ ታሪኳ  ታላላቅ ውጤቶችን አስመዝግባለች፡፡ በኦሎምፒኮችና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶች የተገኙት ከፈታኙ የአገር አቋራጭ ሩጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዘንድሮ የሻምፒዮናውን መስተንግዶ በጐረቤቷ የምስራቅ አፍሪካ አገር ኡጋንዳ መቀደሟ የሚያስቆጭ ይመስላል፡፡    ሻምፒዮናውን በአፍሪካ አገር ሲካሄድ የዘንድሮው የኡጋንዳ፤ ካምፓላን መስተንግዶ ጨምሮ ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን ሞሮኮ ለሁለት ጊዜያት በ1975 እና በ1998 እኤአ፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996 እኤአ እንዲሁም ኬንያ በ2007 እኤአ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን አዘጋጅተዋል። ከአውሮፓ እንግሊዝ፤ ፖላንድ፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ፖርቱጋልና ጣልያን ከአንድ ጊዜ በላይ ውድድሩን ያስተናገዱ ከተሞች ሲሆኑ፤ አሜሪካም ከአንድ ግዜ በላይ አዘጋጅ ነበረች፡፡ ከኤስያ ጃፓን፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጆርዳን ሁሉ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን አስተናግደዋል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት እድሏ ሰፊ በመሆኑ በዚህ አቅጣጫ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከኡጋንዳዋ ካምፓላ ከተማ በኋላ በ2019 እኤአ ላይ 43ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ የዴንማርኳ አሩውስ ከተማ የተመረጠች ሲሆን፤  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቢያንስ   በ2021 እ.ኤ.አ ላይ 44ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጤት ታሪክ ባለፉት 41 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች
ባለፉት 41 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ በሁለቱም ፆታዎች በአዋቂዎች እና በወጣቶች የውድድር መደቦች የቡድን ውጤት ከቀረቡ 168 ሽልማቶች ኢትዮጵያ  123ቱን ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ በአዋቂዎች ምድብ በሁለቱም ፆታዎች በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች    19  የወርቅ ሜዳልያዎችን አስመዝግባለች።  በሻምፒዮናው የኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪክ በአዋቂዎች ምድብ የአጭርና ረጅም ርቀት ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አትሌት  ቀነኒሣ በቀለ ነው። ቀነኒሣ በአጭር ርቀት 4 ኪ.ሜ እና በረጅም ርቀት 12 ኪ.ሜ ውድድሮች በ5 ሻምፒዮናዎች በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን በ2008 እ.ኤ.አ ላይ በረጅም ርቀት 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቱ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በአዋቂዎች ምድብ ውጤታማ ከሆኑ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች መጠቀስ ያለባቸው ደራርቱ ቱሉ፤ ጌጤ ዋሚ፤ ጥሩነሽ ዲባባ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ ዋናዎቹ ናቸው፡፡  አትሌት ደራርቱ ቱሉ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት ያሸነፈች ሲሆን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በአዋቂዎች ምድብ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት 1 ጊዜ ማሸነፍ ከኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ትልቁን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1981 እ.ኤ.አ ላይ በአዋቂዎች ምድብ በወንዶች የ12 ኪ.ሜ ውድድር ሲሆን መሃመድ ከድር ባገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ አትሌት መሐመድ ከድር ከዓመት በኋላ በ1982 እኤአ በተመሳሳይ ረጅም ርቀት አሸንፎ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪሎሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 10 የወርቅ ሜዳልያዎች ስድስቱን ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ2002-2008 እ.ኤ.አ በተካሄዱት የዓለም ሻምፒዮናዎች ነው። ሌሎቹን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ደግሞ መሃመድ ከድር (በ1982 እ.ኤ.አ)፣ በቀለ ደበሌ (በ1983 እ.ኤ.አ)፣ ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም (በ2009 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ኢማና መርጋ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪ.ሜ የረጅም ርቀት ውድድር ደግሞ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያ የሜዳልያ የተገኘው በ1991 እ.ኤ.አ ደራርቱ ቱሉ በወሰደችው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ1995 እ.ኤ.አ ላይ አሁንም ደራርቱ ቱሉ የተጐናፀፈች ሲሆን ሌሎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ደግሞ በ1975 እና በ2000 እ.ኤ.አ አግኝታለች፡፡ በአዋቂ ሴቶች ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 ከጥሩነሽ ዲባባ (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) 2 በጌጤ ዋሚ (በ1996፣ በ1999 እ.ኤ.አ) እንዲሁም በወርቅነሽ ኪዳኔ (2003 እ.ኤ.አ) ተገኝተዋል፡፡
በርካታ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን በግል እና ከቡድን ጋር በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች መሪነቱ ላይ ተቀምጣለች። በግልና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያዎች ድምር የአለም አገር አቋራጭን የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች በግል ያገኛቸውን 12 ወርቅ ሜዳሊያዎች እና በቡድን ያገኛቸውን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ16 ወርቅ ሜዳሊያዎች ቀነኒሳ በቀለ መሪነቱን ሲይዝ፣ በሴቶችም በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ14 ወርቅ ሜዳሊያዎች በሴቶቹ ምድብ  አንደኛነቱን ይዛለች። በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪካቸው ቢያንስ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባት የኢትዮጵያ አትሌቶች ክብረወሰኑ አላቸው። እነሱም ሀይሉ መኮንን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ናቸው።

 አይኮግ ላብስ የተባለውና በወጣቶች የተቋቋመው የሶፍትዌር አማካሪ ድርጅቶች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሮች ጋር በመተባበር፣ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ግቢ ውስጥ በመቀሌና በአራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩልቲ ዩኒቨርስቲዎች መካከል የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድር ያካሂዳል፡፡ ድርጅቱ ባለፉት አምስት አመታት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በሮቦቲክስ ቢዝነስ ላይ ሲሰራ መቆየቱን ሰሞኑን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ የሚሰራው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦቲክስ ቢዝነስ በአገራችንም ሆነ በአፍሪካ ያልተደፈረ ስራ በመሆኑ ከውጭ ድርጅቶች ጋር ሲሰራ እንደነበር አስታውሶ፣ ነገር ግን ቢዝነሱ በአገር ውስጥ መተግበር ቢጀምር ችግር ፈቺ ይሆናል በሚል ሃሳብ ያለፈውን አንድ አመት ከ22 የአገራችን ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረሙን የአይኮግ ላብስ መስራቾች ተናግረዋል፡፡
ሳይንሱን ከጨዋታና ከመዝናናት ለመጀመር ከዩኒቨርስቲው የተውጣጡ ሁለት ሁለት ተማሪዎች መርጦ ስልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ተማሪዎቹ ውድድሩን በሮቦቶች ለማድረግ፣ ሮቦቶቹን ከመገጣጠም ጀምሮ ወደ ተቃራኒ ጎል እንዴት መምታት እንዳለበት፣ እንዴት ጎል ማስገባትና ኳስ ለቡድኑ ተጫዋች ማቀበል እንደሚችል ----- ሮቦቶቹን ፕሮግራም በማድረግ አዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡ ለፍፃሜ ውድድር ያለፉት መቀሌ ዩኒቨርስቲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ፋኩልቲ እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡  
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤”ወጣቶቹ በአገራችን ብቸኛ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦቲክ ቢዝነስ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም ለሥራቸው ከፍተኛ እውቅና በመስጠት ከሚኒስቴሩ ጋር በጋራ እንዲሰሩ አድርገናል” ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለፈጠራ ስራ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት የፈጠራ ባለሙያዎችን  ለማበረታታት በየዓመቱ ሽልማት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ዘንድሮም ለሰባተኛ ጊዜ ይህ ሽልማት ለፈጠራ ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
አይኮግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሂደው ‹‹አይኮግ ሜከርስ ሮቦ ሶከር ካፕ›› በየአመቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሮቦት እግር ኳስ ውድድሩን ለመጫወት 3 ሜ. በ 2 ሜ የሆነ ሜዳና ከእያንዳንዱ ቡድን ሶስት ሶስት ሮቦት እንደሚያስፈልጉ የተገለጸ ሲሆን ለአሸናፊው ቡድን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሽልማት ይበረከታል ተብሏል፡፡

Page 10 of 330