Administrator

Administrator

 የተመድ ማዕቀብ ያልገታት፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ውግዘት ያላስጨነቃት፣ የአሜሪካ ዛቻና ማስፈራሪያ ያላስበረገጋት ሰሜን ኮርያ፤ የሚሳኤልና የኒውክሌር ሙከራዎቿን በተጠናከረ መልኩ እንደምትገፋባቸውና በየሳምንቱ በቋሚነት የሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ ማቀዷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮርያ በቀጣይም ተጨማሪ የሚሳኤል ሙከራዎችን በመደበኛነት ለማካሄድ ማቀዷን ለቢቢሲ የተናገሩት የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃን ሶንግ ሪዮል፤ አሜሪካ ይህንን በመቃወም በእኛ ላይ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ እልቂት የሚያስከትል የኒውክሌር የአጸፋ እርምጃ እንወስዳለን፤ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጦርነትም ይቀሰቀሳል ማለታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡ ባለስልጣኑ ይህን ማለታቸውን ተከትሎ፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሉ ካንግ በሰጡት መግለጫ፤ አገራቸው ውጥረትን የሚያባብሰውን የሰሜን ኮርያን ድርጊትና ሃሳብ እንደምትቃወም ያስታወቁ ሲሆን ቻይና የሰሜን ኮርያ የኒውክሌርና የሚሳኤል ፕሮግራም በእጅጉ እንዳሳሰባት መግለጻቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለረጅም ጊዜያት የዘለቀው የሰሜን ኮርያና የአሜሪካ ወታደራዊ ውጥረት ባለፉት ሳምንታት እየተባባሰ መቀጠሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ አሜሪካ የባህር ሃይል ቡድን ወደ ኮርያ ልሳነምድር መላኳን ተከትሎ፣ ራሴን ለመከላከል ተዘጋጅቻለሁ ያለቺው ሰሜን ኮርያ፣ ባለፈው ቅዳሜ የጦር ሃይል አቅሟን የሚያሳይ ትርዒት ማቅረቧንና በነጋታውም የከሸፈ የሚሳኤል ሙከራ ማድረጓን ጠቁሟል፡፡

 አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1993 በሞቃዲሾ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ ከተካሄደውና 18 የልዩ ሃይል ወታደሮቿንና ሁለት የጦር ሄሊኮፕተሮቿን ካጣችበት ጦርነት በኋላ ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ መላኳን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ከአሜሪካ 101ኛ የአየር ወለድ ክፍለ ጦር የተመረጡት ወታደሮች፣ ለሶማሊያ ብሄራዊ የጦር ሃይል አልሻባብን በተሻለ ሁኔታ መታገል የሚችልበትን አቅም የሚፈጥር ወታደራዊ ስልጠና እና የማስታጠቅ ስራ እንደሚሰሩ አንድ የአሜሪካ ወታደራዊ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በሶማሊያ ሰፋ ያለ ወታደራዊ ሚና መጫወት የሚያስችል እቅድ ማጽደቃቸውንና ይህም በአልሻባብ ላይ የተጠናከረ የአየር ድብደባ ጥቃት ዘመቻ ለማካሄድ የታለመ እንደሆነም ዘገባው አክሎ ጠቁሟል፡፡
አዲሱ ሶማሊ-አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ ተቀማጭነቱን በሶማሊያ አድርጎ ምስራቃዊ አፍሪካን በሽብር በሚያተራምሰው ጽንፈኛው ቡድን አልሻባብ ላይ አዲስ የማጥቃት ዘመቻ ማወጃቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት የጀልባ ጉዞ ላይ የነበሩ 28 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ህገወጥ ስደተኞች፣ ሳባርታ ከተባለቺው የሊቢያ የጠረፍ ከተማ አቅራቢያ ሞተው መገኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ጀልባዋ ጉዞዋን ጀምራ ጥቂት እንደሄደች በደረሰባት አደጋ መሰበሯን የጠቆመው ዘገባው፤ በርሃብና በውሃ ጥም ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉት 28 ስደተኞች አስከሬንም በአንድ ሊቢያዊ አሳ አጥማጅ መገኘቱን የሊቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የደህንነት ክፍል ኮማንደር የሆኑት አህማይዳ ካሊፋ አምስላም ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡ በባህር ጉዞ ላይ የነበረቺው ጀልባ ሞተሯ ተበላሽቶ ከቆመች በኋላ ምግብና ውሃ በማጣት ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉትና አራቱ ሴቶች ከሆኑት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆሙት ባለስልጣኑ፤ የቀብር ስነስርዓታቸውም በሊቢያ በሚገኝ የህገወጥ ስደተኞች መካነ መቃብር እንደተፈጸመ ተናግረዋል፡፡
ሊቢያ በአፍሪካውያን ስደተኞች ዘንድ ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ተቀዳሚዋ የጉዞ መስመር መነሻ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፉት 3 አመታት ውስጥ ብቻ ከ150 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ በኩል ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ ጣሊያን መግባታቸውን አስታውሷል፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የቅንጦት መኪኖችን በማምረት የሚታወቀው ቴስላ የተባለው ኩባንያ፣ ለረጅም አመታት በታዋቂው ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ ተይዞ የቆየውን የአሜሪካ ቁጥር አንድ ሃብታም የመኪና አምራች ኩባንያነት ደረጃ መረከቡ ተዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አጠቃላይ የሃብት መጠኑ 51.54 ቢሊዮን ዶላር የደረሰውና በቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ የተቋቋመው ቴስላ፤ 50.22 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያለውን ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ በመብለጥ የአሜሪካ ቁጥር አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ለመሆን መብቃቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከ13 አመታት በፊት የተቋቋመው ቴስላ ኩባንያ የሃብት መጠኑ ከጄኔራል ሞተርስ ቢበልጥም በገበያ ድርሻ ግን አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ቴስላ በአሜሪካ የመኪና ገበያ ያለው ድርሻ 0.2 በመቶ ብቻ ሲሆን ጄኔራል ሞተርስ በበኩሉ፣ 17.3 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው ገልጧል፡፡
ቴስላ በ2016 ያመረታቸው መኪኖች 76 ሺህ ያህል ብቻ እንደነበርና ይህ ቁጥር ከጄኔራል ሞተርስ በእጅጉ ያነሰ  እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ ጄኔራል ሞተርስ በአመቱ 546 ሺህ ያህል መኪኖችን መሸጡን አስታውሷል፡፡ ቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ፣ ኩባንያውን የበለጠ በማስፋፋትና የማምረት አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ በቀጣዩ አመት ግማሽ ሚሊዮን ለማድረስ ማቀዳቸውም ተነግሯል፡፡

 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው 6ኛው የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን ነገ የአፍሪካን ትልቁን የኢንዱስትሪ ፓርክ እየገነባች በምትገኘው የሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል፡፡ የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ለአምስት ዓመታት ከተካሄደ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት አልተከናወነም ነበር። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ከCCECC ከተባለው የኮንስትራክሽ ተቋራጭ ኩባንያ  ጋር በመተባበር የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮያ ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የግማሽ ማራቶን ሩጫ እና ተያያዠ ውድድሮችን በስኬት ለማካሄድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
በ6ኛው የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን  በዋናው የ21 ኪሜ ውድድር ከ25 ክለቦች የተውጣጡ ከ150 በላይ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከ25 በላይ የጎዳና ላይ ሩጫ ስፖርተኞች ከተለያዩ አገራት በመምጣት ይሳተፉበታል፡፡  በተያያዘም የ7 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ  ሩጫ እና የህፃናት ውድድር  የተዘጋጀ  ሲሆን  ከ4500 በላይ ተሳታፊዎች ይኖራቸዋል፡፡ የግማሽ ማራቶን ውድደሩ በአገር ውስጥ ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር እድል የሚፈጥር በመሆኑና የሐዋሳ ከተማን የልማት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ ውጤታማ  እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡ ከአዲስ አበባ 275 ኪሎሜትር ርቃ የምትገኘው  የሐዋሳ ከተማ  በ1700 ሜትር ከፍታ  ላይ ናት፡፡ ከተማዋ የ57 ዓመታት እድሜ ያላት ስትሆን በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ እና ከ500ሺ በላይ ህዝብ የሚኖርባት  ናት፡፡

 በእርግዝና ወይንም ከወሊድ በሁዋላ የሚገጥም ድብርት ስያሜ ነው Postpartum Depression የሚባለው። ባለፈው እትም ያስነበብናችሁ ይህ በእናቶች ላይ የሚደርስ ከባድና ያልታወቀ ችግር በዚህ እትም እልባት ያገኛል። ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና ዶ/ር አታላይ አለም የአእምሮ ሐኪም የሰጡትን ጠቃሚ ሃሳብ እንዲሁም ሁለት እናቶች ከሰጡት ምስክርነት ጋር ለንባብ አቅርበነዋል።
“እኔ የሁለት ልጆች እናት ነኝ። እርግዝና ሲከሰት ወይንም ልጅ ሲወለድ እናትየው ስለሌላ ነገር እንዳታስብና በሰላም በደስታ የምትወልደውን ልጅ እንድታስብ እንዲሁም ቤተሰብዋ ቁጥሩ እየጨመረ ሲሄድ ማድረግ የሚገባትን ነገር ከባለቤትዋ እና ከቤተሰብዋ ጭምር በተረጋጋ ሁኔታ ዝግጅት እንድታደርግ መንገዱ ሊከፈትላት ይገባል ። ነገር ግን ይህ መሆኑ ቀርቶ እንዲያውም በፊት ከነበረው ይበልጥ ሌላ የሀሳብ ጫና የሚያድርባት ከሆነ ሁኔታው አስቸጋሪ ይሆናል። እኔ በተለይም የመጀመሪያ ልጄን በወለድኩበት ጊዜ ልገልጸው የማልችለው የጭንቀትና የድብርት ስሜት ነበረኝ። በሆነው ባልሆነው ነገር እበሳጭ ነበር። ሆድ ይብሰኝ ነበር። የዚህ ምክንያት ደግሞ ባለቤቴ ስለእኔ እርጉዝ መሆን ምንም ግድ የማይሰጠው እና ከእራሱ ፕሮግራም ውጭ ስለእኔም ሆነ ስለሚመጣው ልጅ ምንም የማይጨነቅ መሆኑ ነበር።
በእርግጥ ጠዋት ይወጣል ማታ ይገባል። ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ ባለቤ ልጅ ወለደችልኝ ብሎ እንክብካቤ አላደረገልኝም። በቅርቤ አልተገኘም። ስለዚህ አብረውኝ ያሉት ሰዎች ሁሉ ምንም ቢያደርጉልኝ ልወዳቸው አልቻልኩም። ያስጠሉኛል። ልክ እሱ ሲመጣ የነበረኝ ጭንቀት ሁሉ ይለቀኛል። ነገር ግን እቤቱ ከገባም በሁዋላ ወደእኔ ቀረብ ብሎ ማጽናናት ወይንም የደስታዬ ተካፋይ የመሆን ነገር... ልጁን ታቅፎ የማየት ሁኔታ ስላልነበረው ተመልሼ በጣም አዝን ነበር።ይህንን ነገር ለቤተሰቤ ፊት ለፊት ስላልተናገርኩኝ እናን ጨምሮ እህቶቼ መላው ቤተሰቡ ስለእኔ አልተጨነቀም ነበር። ለእኔ አጥሚት መስራት ገንፎ ማቅረብ በስተቀር ምን ያስፈልግሻል? ምን ሆነሻል? የሚያስደስትሽ ነገር ምንድነው? የሚለውን ነገር እነሱም አልጠየቁኝም። ምክንያቱም ስለዚህ ነገር ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። እኔም እራሴ ከባለቤጋር በተያያዘ ያለውን ነገር በሙሉ እጅግ አድርጌ ከመጥላት በስተቀር ለማንም ምንም መናገር አልቻልኩም። ምክንያቱም የደረሰብኝን ነገር ስላላወቅሁት ነው።
ሁለተኛውን ልጄን ስወልድ ግን በተቻለ መጠን ቀደም ባለው ጊዜ የደረሰብኝ ነገር እንዳይደርስብኝ ተጠንቅቄ ነበር። የሚያስደስቱኝን ነገሮች ከባለቤም ሆነ ከቤተሰቤ ሳልጠብቅ በእራሴ ለመወጣት በደንብ አድርጌ ነበር የተዘጋጀሁት። የኢኮኖሚ ችግር እንዳይገጥመኝ እቁብ ሰብስቤ ገንዘብ ያዝኩ። የምመገባቸውን ነገርች አስቀድሜ አዘጋጀሁ። ቤን ቀለም አስቀባሁ። የአልጋ ልብሶቼን ፒጃማዎቼን ሁሉ አስቀድሜ አዘጋጀሁ። ምክንያቱም ይህንን ሁሉ ስጠይቀው ባለቤ ምንድነው ብትወልጂ... በፊት በነበረው አትጠቀሚም? የምን ወጪ ማብዛት ነው እያለ እሱ ግን አንድ ቀን እንኩዋን ሳያቋርጥ እየጠጣና እየሰከረ ጭምር ይመጣ ስለነበር ያንን ጊዜ በፍጹም አልረሳውም። ድብርቱን በሐኪም ብርታት ተላቅቄአለሁ። ቂሙን ግን አልተላቀቅሁም። ስለዚህ ከዚህ በሁዋላ አልደግመውም በማለት እራሴ በራሴ ሁሉን ነገር አዘጋጅቼ ልጄን ወለድኩ።
ቤተሰቤ እንደእንግዳ ተስተናግዶ እንዲሄድ እንጂ ከጉዋዳዬ እንዲገቡ አልፈቀድሁም። ምክንያቱም በመጀመሪያው ስወልድ በሌለ ኢኮኖሚ እነእሱም ከቁጥር በላይ ሆነው እየተሰበሰቡ ባዶዬን ነበር ያስቀሩኝ። ስለዚህ ከእና በስተቀር የቀሩት እየመጡ እንዲሄዱ እንጂ ሌላ ኃላፊነት ውስጥ እንዲገቡ አልፈቀድሁም። ይህንን ደግሞ ለእናም ፊት ለፊት ነግሬአት እሱዋም ተስማምታ በፍቅር እና በክብር ቁጭ ብላ አረሰችኝ። ባለቤም... አ... ሀ... አሁን አድገሻል... ጭቅጭቅም አቁመሻል... ሲለኝ የፌዝ ሳቅ እየሳቅሁ ተወጣሁት። ስለዚህ ሴቶቹን እምመክረው በመጀመሪያ ሲያረግዙ ጀምሮ ይህ ድብርት የሚባለው በተለያየ ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ነው። ከሆነ ደግሞ ወደሐኪም መሔድ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ሁሉም ቢቻል ተግባብቶ... ካልተቻለ ደግሞ ረጋ ባለ መንፈስ አስፈላጊ ለሆነው ነገር ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ቢያደርጉ ከችግሩ አስቀድመው እራሳቸውን ያላቅቃሉ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ትልቁን ምክር መስጠት የምፈልገው ለባሎች ነው። ከእኔ ጉዳይ ስነሳ ባሎች አባቶች ሚስቶቻቸው ሲወልዱ ትልቁን ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
ባሎች... ሚስቶቻቸው ሲወልዱ ጊዜ ሰጥተው እቤት ውስጥ በመገኘት... ባለቤቱ በመውለዱዋ አመስግኖ... ሸልሞ... ወዘተ... እናትየውን የሚያስደስት ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል። እናትየው ልጅ በመውለድዋ ምክንያት ባልዋ የሰጠውን ክብደት በማየት... ለእርስዋ ያለውን ፍቅር የምታረጋግጥበት ወቅት በመሆኑ ከወለደች በሁዋላ ለሚፈጠረው የመንፈስ ጭንቀት አትጋለጥም። ስለዚህ ሚስት በምትወልድበት ጊዜ ባልየው በተቻለ መጠን በቅርብዋ መገኘት... ምን በላች... ምን ጠጣች... እስከሚለው ድረስ ቢንከባከባት... ሚስት በጣም ስለምትደሰት ለአእምሮ ጭንቀት ወይንም ድብርት አትጋለጥም ብዬ አስባለሁ። በእኔ ላይ የደረሰው ከመውለድ በሁዋላ የአእምሮ ጭንቀት ምክንያቱ ባለቤ ለእኔ ተገቢውን ድጋፍ አለማድረጉ ነው ብዬ አምናለሁ።”
 በእምነት ሲሳይ ከፒያሳ
ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ድብርት መገለጫዎቹ ብዙ ነገሮች ናቸው።
አንዳንድ እናቶች በወሊድ ወቅት በሰውነታቸው ላይ ለውጥ ያያሉ። ለምሳሌም በሰውነት ውስጥ ያለው የሆርሞን መጠን ሲቀንስ ወይንም የደም መጠን ማነስ ወይንም ግፊት መጨመርና የመሳሰሉት ነገሮች ለድካምና ለጸባይ መለዋወጥ ሊዳርጋቸው ይችላል። ይህ ባለበት ሁኔታ እናቶች በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች እንክብካቤና ድጋፍ ሲቀንስ ደግሞ ጉዳቱን ያባብሰዋል።
ሴቶች ብዙውን ጊዜ ማለትም በእርግዝና ጊዜ እንኩዋን ሳይቀር ስለውበታቸው ይጨነቃሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከወሊድ በሁዋላ እራስን ዞር ብሎ ማየት የሚያቅትበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህ ሲሆን ጤናማ ስላልሆነ አብሮ ያለ ሰው ምንድነው ምክንያቱ ብሎ መጨነቅ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ወላድዋ ስለመልክና ቁመናዋ መጨነቅ ካቆመችና ምንም ስሜት የማይሰጣት ከሆነ በህይወትዋም ላይ መወሰን አለመቻልዋን እንዲሁም ስጋት የመሳሰሉት ነገሮች እየጎሉ መምጣታቸውን ያሳያል ። ይህ መሆኑ ደግሞ ጭንቀትን የሚያባብስ ነው።
በቤት ውስጥ ስራን ለመስራት ድጋፍ የሚያደርግ ሰው አለመኖር ፣የኑሮ አጋርን ድጋፍ ማጣት ባል፣ በባህርይው አስቸጋሪ የሆነ ቀደም ብሎ የተወለደ ልጅ በቤት ውስጥ ካለና ካለእናቱ የሚዳኘው ሲጠፋ... በወላድዋ ላይ ጭንቀት ብስጭት እንዲሁም ድብርት ያስከትላል ።
አንድ ቤተሰብ ልጅ ለመውለድ ሲያስብ አስቀድሞ ስለኢኮኖሚው ጥያቄ ማንሳት ትክክለኛ እና ተገቢ ነው። የኢኮኖሚው ጉዳይ ሊያሳስብ የሚገባው እናትየው በምትወልድበት ጊዜ እሱዋን ጨምሮ ስለሚኖረው መስተንግዶ እና ከዚያም በሁዋላ ልጁ በምን እንደሚያድግ አስቀድሞ መጨነቅ ተገቢ በመሆኑ ነው። ይህ ጥያቄ መልስ የማያገኝ ከሆነ ባለው ሁኔታ እንዴት መኖር እንደሚቻል አስቀድሞ እቅድ ሊኖር ይገባል። ይህ ሳይሆን ከቀረነገሮች ሳይሙዋሉ ስለሚቀሩ እናትየው መበሳጨት እና መጨነቅዋ ወይንም መደበርዋ ግድ ነው።
ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ አንዲት እናት የደረሰባትን እንደሚከተለው አካፍላናለች።
 “እኔ ከመውለዴ በፊት ከባለቤ ጋር ብዙ ተነጋገርን። እባክህን ገንዘብ ሳይኖረን ሁለተኛ ልጅ ምን ያደርግልናል? ብዬ ስጠይቀው... ተይው... በቃ ይወለድ... የሚገጥመንን ምን ታውቂያለሽ? አለኝ። እኔም እየፈራሁ በጣም እያሰብኩ እንደምንም የእርግዝና ጊዜዬ አለቀ። ከዚያም ልክ ወልጄ ገና ከሆስፒታል ሳልወጣ ባለቤ ከመስሪያ ቤቱ በፖሊስ ተይዞ በሕግ ቁጥጥር ስር ዋለ። ምን አድርጎ ነው? ሲባል የመስሪያ ቤቱ አሽከርካሪ ስለነበር ከአሁን ቀደም በሄደበት የመስክ ስራ ሕገ ወጥ ሰዎችን ከነንብረታቸው በመኪናው ላይ ጭኖ ገንዘብ ሲሰራ በመገኘቱ ተከሶ ስለ ነበር በዋስ ተለቆ ሲከራከር ቆይቶ ውሳኔ የተሰጠበት ወቅት ነው።እኔ ደግሞ ይህንን ሁሉ ታሪክ አላውቅም። በሁዋላ ግን መለስ ብዬ ሳስበው እርግዝናው 7/ወር ካለፈው በሁዋላ ይህ ጽንስ ሊቋረጥ አይችልም? ብሎ ጠይቆኝ ከፍተኛ ጸብ መፈጠሩን አስታወስኩ። በጊዜው ለእኔ ሕይወት ምንም ግድ የለህም... አንተ ብትከለክለኝ እንኩዋን ለምኜም ቢሆን አሳድጋለሁ እንጂ አሁንማ ምንም አይደረግም ብዬዋለሁ። ወልጄ ስወጣ ባልተቤ እስር ቤት ነበር። የሶስት ወር እስራትና የተወሰነ ገንዘብ ቅጣት ተጥሎበት ነበር። በቃ... ትልቅ ችግር ውስጥ ነበር የወደቅሁት። ለሊት ተነስቼ ብጮህ ደስ ይለኛል። ሰው ማየት አስጠላኝ። የሽንት ጨርቅ ነጠላ መቅደድ ሆነ። የሚበላው በሰው በዘመድ ትብብር ሆነ። ከዚያ ወደ አንድ ወር ገደማ ሲሆነኝ ተመልሼ ሆስፒታል ነበር የገባሁት። በጣም ታመምኩ። ሐኪሞቹ ግን ድብርት ነው አሉኝ። አክመው አዳኑኝ። በጣም ብዙ ምክር ተሰጠኝ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ስቸገር ስሰቃይ እሱም የእስር ጊዜውን ጨርሶ ወጣ። ቀኑም አለፈ። አሁን ደህና ነን። ነገር ግን ሰው በሕይወቱ የሚመጣውን ለውጥ አስቀድሞ ቢገምት እና ቢጠነቀቅ መልካም ነው እላለሁ።”
 ሃና ተስፋዬ /ከአቧሬ
ቀጥሎ የተጠቀሱት ነጥቦች አንባቢ ልብ ሊላቸው የሚገቡ ናቸው። ከወሊድ በሁዋላ፡-
... የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት ፣ጥልቅ የሆነ ብስጭት፣ የፍቅር ግንኙነት መቀነስ ፣የደስተኝነት መጠን መቀነስ ፣በጣም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት፣ የእፍረት ስሜት ፣የጥፋተኝነት ስሜት መጨመር፣ የፀባይ መለዋወጥ፣ ከልጅ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር አለመቻል፣ እንዲሁም በእራስ ወይንም በተወለደው ልጅ ላይ ጉዳት ለማድረስ መሞከር... ወዘተ የሚታይ ከሆነ ያቺ እናት ድብርት (Postpartum Depression ) ይዟታል ማለት ነው።
ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚታየው ድብርት (Postpartum Depression ) ምክንያቱ
እርግዝናውና ጽንሱ የተፈለገ መሆን ያለመሆን ፣
ከትዳር ጉዋደኛ ጋር ያለው ግንኙነት ፣
ከሴት አማት ጋር ያለው ግንኙነት ፣
የገቢ መጠን ማነስ... ረሀብ፣
በወሊድ ጊዜ የሚጠብቁት ነገር ሳይሳካ ሲቀር፣
ድጋፍ ማጣት እና ስሜትን የሚጎዱ ችግሮች የደረሱባቸው ሴቶች ላይ በአብዛኛው ይታያል። ከዚህ በተጨማሪም... አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ፡-
ጥሩ ስሜት የማይሰማት ከሆነ፣
ለነገሮች ትኩረት ማጣትና ማሰብን ማቋረጥ፣
ልጅዋን በትክክል መንከባከብ ካቃታት፣
ለእራስዋ ተገቢውን ለማድረግና በየእለቱ ልትወጣው የሚገባትን ግዴታ መወጣት ሲያቅታት፣
ልጅዋን የመጉዳት ስሜት ሲፈጠርባት... ወዘተ
ድብርት (Postpartum Depression) ይዟት ሊሆን ስለሚችል በአስቸኩዋይ ወደሐኪም ቤት
መሔድ ይጠበቅባታል።

   ኢንሼቲቭ አፍሪካ በየዓመቱ የሚያዘጋጀውና ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ ሚያዚያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም በጣሊያን የባህል ማዕከል ይከፈታል፡፡ እስከ ሚያዚያ 25 በሚቆየው በዚህ ፌስቲቫል ላይ በተለይ በስደት፣ በወጣቶች የስነ ተዋልዶ ጤና፣ በአካባቢያዊ ደህንነት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በመሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የተሰሩ የአገር ውስጥና የውጭ ፊልሞች ለእይታ እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡
ከፊልሙም ባሻገር ከተለያዩ አለማት ተጋብዘው የሚመጡ እውቅ የፊልም ዳይሬክተሮች፣ አክተሮችና ፕሮዲዩሰሮች ለመገናኛ ብዙሀን፣ ለፊልም ሰሪዎች፣ ለፕሮዱዩሰሮችና ለተዋናዮች ሥልጠና ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን አገራዊ አጀንዳዎች ተዘጋጅተው ትልልቅ የውይይት ጉባኤ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ እነዚህ የተመረጡ ፊልሞች ከጣሊያን የባህል ማዕከል በተጨማሪ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትም ለእይታ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ በየአመቱ ከ600 በላይ ፊልሞችን በማሰባሰብ የተመረጡ 60 ፊልሞችን ለእይታ ሲያበቃ መቆየቱን አስታውሶ፤ ባለፉት አመታት ከ400 በላይ ፊልሞችን ለእይታ ማብቃቱን ጠቁሟል፡፡

የትምህርት አሰጣጡ በአገራችን የተለመደውን የመማር ማስተማር ሂደት የሚያስቀር ነው ተብሏል
                 
      ጅማ ዩኒቨርሲቲ ኔዘርላንድ ውስጥ ከሚገኘውና በዓለም ታዋቂ ከሆነው ስኩል ኦፍ ማኔጅመንት ጋር በመተባበር በአግሪ ቢዝነስ አለም አቀፍ እውቅና ያለው የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት ሊጀምር ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ሰሞኑን ባካሄደው የምክክር ጉባዔ ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ በተለያዩ መ/ቤቶች በአግሪ ቢዝነስ ማኔጅመንት የሥራ መስክ ላይ ተቀጥረው ለሚሰሩ ባለሙያዎች ትምህርቱን ይሰጣል፡፡ ትምህርቱ በዓይነቱ የተለየና በአገራችን የተለመደውን የመማር ማስተማር ሂደት የሚያስቀር እንዲሁም ችግሮችን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ፣ ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን ይህንኑ የአግሪ ቢዝነስ ማስተርስ ፕሮግራም አስመልክተው ሲናገሩ፣ ፕሮጀክቱ በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የአግሪ ቢዝነስ ማኔጅመንት ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የሚል እምነት የተጣለበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በኔዘርላንድ ኤምባሲ አስተባባሪነት የአግሪካልቸር ምሩቃን ሆነው ሥራውን የሚሰሩት ባለሙያዎች፤ የማኔጀመንት እውቀቱና ልምዱ ስለማይኖራቸው ትክክለኛ ማናጀር መሆን አልቻሉም፡፡ ስለዚህም ይህ ፕሮግራም እነዚህ ባለሙያዎች የሚጎድላቸውን በመሙላት፣ በዘርፉ ብቃት ያላቸው ሙያተኞች እንደሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ወንዳፈራሁ የዳሰሣ ጥናቱን ጠቅሰው እንደተናገሩት፣ በእርሻው ዘርፍ የአግሪ ቢዝነሱን ሥራ የሚሰሩት አግሪካልቸር ባለሙያዎች ሲሆኑ እነሱም ሳይንሱን በሚገባ ያውቁታል፤ የማኔጅመንቱን ሥራ ግን በብቃት  ማከናወን ወይንም ሥራውን ማዘመን አልቻሉም፤ ይህም የእርሻ ውጤቶች ከአገር ውስጥ ገበያ አልፎ ለውጪ አገር ገበያ እንዲቀርቡና የውጪ ምንዛሪ እንዲያስገኙ በማድረጉ በኩል ሰፊ ክፍተት እንዲኖር  አድርጎታል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍም በመደገፍ ረገድ እነዚህ ባለሙያዎች ቁልፍ ሚና አላቸው ያሉት ዶክተሩ፤ ክፍተቱን ለመሙላትና በዘርፉ የተሟላና በቂ ዕውቅና ያለው ባለሙያ ለማፍራት፣ ይህ ፕሮግራም ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባለሙያዎችን ወደተለያዩ አገራት በመላክ አጫጭር ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ የማድረጉ አሠራር ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን የገለፁት ዶክተሩ፤ ይህ አሠራር ግን ውጤታማ አለመሆኑንና ሰልጣኞቹ ወደ ስራቸው ሲመለሱ ወደቀደመው አሠራራቸው እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የአግሪ ቢዝነስ ማኔጅመንት ማስተርስ ፕሮግራም የትምህርት አሠጣጥ ከዚህ ቀደም ከተለመደው የተለየና የአገሪቱን መሰረታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ችግሮች ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ስልጠናና ትምህርት እንደሚሆንም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ትምህርትና ስልጠናው በአገሪቱ ላይ ባሉ ቁልፍ ችግሮች ላይ የተመሰረተ ሆኖ ለእነሱ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችል ዕውቀትና ልምድ የሚያስጨብጥ ነው›› ብለዋል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው በኢንዱስትሪው የበርካታ ዓመታት ዕውቀትና ልምድ ያላቸው የአገር ወስጥና የውጪ አገር ሙሁራን ምሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በመጪው መስከረም ወር ከ30-40 በሚደርሱ የመጀመሪያ ባች ተማሪዎች ትምህርቱ እንደሚጀመር የተናገሩት ፕሮጀክት አስተባባሪው፤ ትምህርቱ የሚሰጠው የአግሪካልቸር ባለሙያዎች ለሆኑና በሙያቸው እየሰሩ ለሚገኙ ሙያተኞች እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡ የመማሪያ ቦታ ለጊዜው አዲስ አበባ በሚገኘው የዩኒቨርስቲው  የሳተላይት ካምፓስ እንደሚሆንና በቀጣይ ሥራው ወደሚገኝበት ቦታ ላይ በመሄድ የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በሁለት ዓመት የሚጠናቀቀው ትምህርቱ በአግሪ ቢዝነስ የማኔጅመንት፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚክስ ባህርይ ያላቸው 18 ኮርሶችን ያካተተ እንደሆነም ዶክተሩ ገልጸዋል፡፡ ለትምህርቱ አጠቃላይ ክፍያ 5000 ዶላር ይደርሳል የሚል ግምት እንዳላቸው የጠቆሙት ዶክተሩ፤ ሴት ተማሪዎች የአጠቃላይ ክፍያውን ሶስት አራተኛውን ብቻ ከፍለው የሚማሩበት ዕድል ይመቻቻል ብለዋል፡፡

 በወንጀል ምርመራ ታሪኮች ላይ ያተኮሩ 16 ያህል ልቦለድ መፅሀፍትን የደረሱትና በ79 አመታቸው ከዚህ ኣለም በሞት የተለዩት ደራሲ ይልማ ሃብቴስ የቀብር ስርአታቸው ረቡዕ ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በአስኮ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
  ደራሲ ይልማ ከልቦለዶቹ መፅህቶቸው በተጨማሪ ሰባት ያህል የቴሌቪዥን ድራማዎችን በመድረስና በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ ከቴሌቪዥን ድራማዎቻቸው “ያልተከፈለ እዳ” ተጠቃሽ ሲሆን ከመፅሐፍቶቻቸው መካል የመጀመሪያ ድርሰታቸው የሆነውን “የላታደለች በሰው ሰርግ ተዳረች” ጨምሮ የቤቱ መዘዝ፣ ከቀብር መልስ፣ ሌላው እጅ፣ ደም
የነካው እጅ፣ ሣይናገር የሞተ እና የአበቅየለሽ ኑዛዜ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ደራሲ ይልማ ሀብተየስ ከደራሲነታቸው ባሻገር
የላብራቶሪ ምርመራ ባለሙያ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ትውልዳቸውም አዲስ አበባ በ1930 ዓ.ም ሲሆን ትምህርታቸውን በሊሴ ገ/ማርያም ተከታትለዋል፡፡

Saturday, 22 April 2017 12:52

ሪፎርም ወይስ አብዮት?

  የመጽሐፉ ርዕስ፡- ሪፎርም ወይስ አብዮት?
                                    ደራሲ፡- አቶ ሞላ ዘገዬ
                                   የገጽ ብዛት፡- 94
                                     ዋጋ፡- ብር 40.60   

      መግቢያ
እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ አገራዊ ፈተና ገጥሞናል። በአገራችን በበርካታ አካባቢዎች የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ እነዚህ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ከመፈታት ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ እየወሰዱት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ለጊዜው ነገሮች የተረጋጉ ቢመስሉም፣ ለገጠሙን አገራዊ ፈተናዎች የሚበጅ ዘላቂ መፍትሔ ካልተፈለገ በስተቀር የተዳፈነው እሳት አስቀያሚ መልክ ይዞ እንደሚመጣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ውስጥ መሆናችን በራሱ የሚናገረው ብዙ ነገር አለ፡፡
በበኩሌ ለሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ የሆነ፣ በተለይ ደግሞ የጉዳዩን ባለቤት (ሕዝቡን) ያሳተፈ ሐቀኛና ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀ በስተቀር፣ አገራችን ወደከፋ ሁኔታ ልትገባ ትችላለች የሚል ከፍተኛ ስጋት አለኝ።
 ብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው የሕዝብ ልዩነቶች፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና በድሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው የሀብት ክፍፍል መራራቅና በብዙሃኑ ሕዝብ ዘንድ የሚስተዋለው የከፋ የኑሮ ውድነት፣ በወጣቱ አካባቢ የሚታየው ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነትና ተስፋ ማጣት፣ በአገራችን የሰፈነው መረን የለቀቀ ሙስናና ሕዝብ ያማረረ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ያለንበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና አስቸጋሪነት እርስ በርሳቸው እየተመጋገቡ፣ ችግሮች መፈታት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ ያሰጋል። በመንግሥት በኩል መሠረታዊ የሆነውን ችግር ወደ መልካም አስተዳደር ችግር ለማውረድ የሚደረገው የተለመደው አካሔድ ጨርሶ መፍትሔ አይሆንም፤ ሕዝብንና አገርን ውድ ዋጋ ያስከፍላል። ዜጎች መሠረታዊ ጥያቄ ሲጠይቁ፣ ጥያቄውን በቅንነት ተመልክቶ ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ፣ ሁሉንም የሕዝብ ጥያቄዎች ወደ አገልግሎት አሰጣጥና ወደ ዳቦ ጥያቄነት ማውረድ ሕዝብና መንግሥት ይበልጥ የሚለያይ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄ በኃይል ለመፍታት መሞከሩና የፖለቲካ ብልጣብልጥነቱም ቢሆን ችግር ይቀፈቅፍ እንደሆነ እንጂ ፈጽሞ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡  
በአገራችን ለወራት በዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን አጥተናል፤ ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት ተከስቷል፤ በኢትዮጵያውያን መካከል አለመተማመንና መጠራጠርን የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ታይተዋል፤ የቱሪዝም ዘርፉ ተቀዛቅዟል፤ በተቃውሞው ወቅት በተለያዩ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ጉዳት መድረሱ በአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዕድገት ላይም ያለ ጥርጥር ቀላል ያልሆነ ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡ ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡  
በዚህች ለውይይት መነሻነት እንድታገለግል በቀረበች ትንሽ መጽሐፍ፣ አገራችን የገጠሟትን ፈተናዎች ለማለፍና አሳታፊና ፍትሐዊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት፣ የመንግሥትና ገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የሁሉም (የተደራጁም ያልተደራጁም፣ በአገር ውስጥም በውጭም የሚኖሩ) ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ለማብራራት ተሞክሯል። ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የመፍትሔው አካል ለማድረግና ለአገራችን የፖለቲካ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ የሕገ መንግሥት ሪፎርም ሒደት ትልቅ ዕድል የሚሰጥ አጀንዳ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ዝቅ ብዬ እንደማስረዳው፣ የሕገ መንግሥት ሪፎርም፣ በተለይም የሪፎርም ሒደቱ፣ አንኳር አንኳር የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ለውይይት ቀርበው ሰፊ ውይይትና ምክክር የሚደረግበት፣ በኅብረተሰቡና በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ክፍፍል የፈጠሩ አገራዊ ጉዳዮች ወደ አደባባይ ወጥተው ጠንካራ ክርክር የሚደረግበት፣ በሕገ መንግሥት ደረጃ ሊደነገጉ የሚገባቸው ወቅታዊ ጉዳዮች የሚቀርቡበትና የሚፈተሹበት፣ ከዚህ ቀደም የተከሰቱና በፖለቲከኞችና በኅብረተሰቦች መካከል ቂምና ቁርሾ የፈጠሩ ጉዳዮች ተነስተው በሰከነ ሁኔታ ውይይት የሚካሄድበትና የታሪክ ቁስሎች እንዲሽሩ የሚደረግበት፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚተዳደርበትን ሰነድ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያመነጭበት ሒደት ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ የሕገ መንግሥት ሪፎርም ሒደት በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባው መስተጋብር ለውይይት የሚቀርብበት፣ የአገረ መንግሥትና የኅብረተሰብ ግንኙነት (state-society relation)፣ እንዲሁም የሲቪሉ ሕዝብና የአገር መከላከያና የጸጥታ ኃይሉ ሁኔታ (civil-military relation) ምን መምሰል እንዳለበት ግልጽ በሆነ መልኩ ለሕዝብ ቀርቦ ውይይትና ክርክር የሚደረግበት እና መቋጫ የሚበጅበት ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡
“ማሻሻል” የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በአንጻሩ፣ ውሱን በሆኑ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ላይ መከራከርን እና አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮችን (ድንጋጌዎችን) ለሕዝበ ውሳኔ ማቅረብን የሚመለከት ጠባብ አድማስ ያለው ሒደት ነው፡፡ በዚህች ጽሑፍ “ማሻሻል” ከሚለው ይልቅ ሪፎርም የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል መጠቀሙን መርጫለሁ፡፡ ይኸውም በአገራችን በኅብረተሰቡ፣ በተለይ በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ያለው ቂምና ቁርሾ እንዲደርቅና ሕዝባዊ መሠረት ያለውና ሐቀኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ካስፈለገ፣ ሒደቱ የተወሰኑ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን በማሻሻል መወሰን የለበትም የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ስለሆነም የሕገ መንግሥት ሪፎርም ሒደት የአገራችንን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ሊያስተካክለው እንደሚችል ሰፋ ያሉና ለውይይት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን ከመዳሰስ አልፎ፣ “ይህ አንቀጽ እንዲህ ቢሆን፣ ያ አንቀጽ እንዲያ ቢደረግ” ወደሚል ዝርዝር የሕግና የሕገ መንግሥት ጉዳይ መግባት አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፡፡
የሕገ መንግሥት ሪፎርም ጥያቄ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ ሊሆን የሚገባው መሠረታዊ አጀንዳ ነው ብዬ ስለማምን፣ ይህች አነስተኛ ጽሑፍ በዚህ ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት እንዲጀመር ምክንያት ከሆነች ግቧን መታች ማለት ነው፡፡
ስለ ደራሲው በአጭሩ
አቶ ሞላ ዘገዬ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የክቡር ዘበኛ ሠራዊት አባል የነበሩ ሲሆን፣ በሠራዊቱ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ከተራ ወታደርነት እስከ መቶ አለቃነት ደርሰዋል፡፡ በየካቲት 66ቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ወቅት ንቁ ተሳትፎ ከነበራቸው መለዮ ለባሾች ውስጥ አንዱ የነበሩት ደራሲው፤ በአብዮቱ የመጀመሪያ ዓመታት የክቡር ዘበኛ ሠራዊትን ወክለው ለውጡን በማስተባበር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ በዚህ ተሳትፏቸው ምክንያት የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው፣ ኮርት ማርሻል ተቋቁሞ የሞት ቅጣት ከወሰነባቸውና ደርግ ሥልጣን እንደያዘ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈታቸው የፖለቲካ እስረኞች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለውጡን በሙሉ ልባቸው ደግፈው በብሔራዊ ባንክና በድሬደዋ አስተዳደር በለውጥ ሐዋሪያነት፣ በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር በፖለቲካ ኦፊሰርነት፣ በጨርጨር አዳልና ጋራ ጉረቻ አውራጃ እንዲሁም በጅጅጋ አውራጃ በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡ ደራሲው በሁለቱ አውራጃዎች፣ በተለይም የጅጅጋ አውራጃ በሶማሊያ ተስፋፊ መንግሥት ከደረሰበት ውድመት መልሶ እንዲቋቋም፣ የጅጅጋ ከተማን አስፓልት ሥራ ጨምሮ በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎችና ልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ በሠሩት ሥራ ታላቅ ኩራት ይሰማቸዋል፡፡
ባለፈው መንግሥት ውድቀት ማግስት በቀይ ሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከ8 ዓመት በላይ ከታሰሩ በኋላ፣ በግላቸው ተከራክረው በተጠረጠሩባቸው ሁሉም ወንጀሎች ነጻ የተባሉት ደራሲው፤ በትምህርት ዓለም፣ በምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ የተለያዩ አገሮች ከወሰዷቸው በርካታ የፖለቲካና የሥራ አመራር ሥልጠናዎች በተጨማሪ፣ ከአዲስ አበባና ለንደን ዩኒቨርሲቲዎች በሕግ ሙያ ሰልጥነዋል፡፡ ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ በጥብቅናና በሕግ ማማከር ሙያ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ደራሲው በየካቲት 66ቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት በንቃት በመሳተፋቸው የሚኮሩ ቢሆንም፣ በአብዮቱ ወቅት በተከሰተው ደም መፋሰስና አብዮቱ በአገር በቀል ዕሴቶች ላይ ባሳረፈው አሉታዊ ጫና በእጅጉ ይፀፀታሉ፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ያለፈው ያለመደማመጥና የመጠፋፋት ባሕል እንዲቀርና አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንዲገነባ፣ ይልቁንም አገር በቀል እሴቶች ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ይጽፋሉ፣ ባገኙት መድረክ ሁሉ ይናገራሉ፡፡

Page 1 of 330