Administrator

Administrator

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር በአገራችን ሥር የሰደደ አብሮ የመሥራት ባህል እንዳለ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በርግጥም ኢትዮጵያውያን እንደ አብሮ መብላት ሁሉ አብሮ በመሥራትና በመተጋገዝ ክፉ ቀንን የማለፍ  ልማድ እንዳላቸው አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ አብሮ ለመስራትና ለመተጋገዝ አስኳል ከሆኑት ማህበራዊ እሴቶቻችን መካከል እድርና መሰል ቀደምት ማህበራዊ ተቋማት ይገኙበታል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት፤ የሰው ልጆች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት የተመሳሰለና የተሳሰረ  እንደመሆኑ መጠን፣ በተናጠል መኖር የማይቻል ነገር ነው፡፡  በአገራችን ያሉ ዕድሮችም የዚሁ እውነት ነፀብራቆች ናቸው፡፡ ስለ ዕድሮች ታሪካዊ አመጣጥ እስካሁን በተመራማሪዎች ዘንድ ስምምነት ላይ ባይደረስም፣ ዕድሮች በአገሪቷ የቆዳ ስፋት ልክ የተሰራጩና ዛሬ ላይ ምናልባትም በጣም ሩቅ የሆኑ አካባቢዎች ካልሆኑ በቀር ዕድር የሌለበትን መንደር ማሰብ አዳጋች ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የዕድሮች ምክር ቤት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በከተማዋ ብቻ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው 7,5ዐዐ ዕድሮች ይገኛሉ፡፡  
እነኚህ ማህበረሰቡ ይሁነኝ ብሎ የሚያቋቁማቸው የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ዓይነታቸው ቢለያይም (ለምሣሌ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ወዘተ) ተብለው ቢሰየሙም በቀደመው ጊዜ የሁሉም ዓላማ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይኸውም “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” እንዲሉ፣ አባላት በራሳቸው ወይም በቤተሰባቸው ላይ እክል ሲገጥማቸው ፈጥኖ በመድረስ፣ የገንዘብ ድጎማ በማድረግ፣ በጉልበት በማገዝና በማፅናናት ሀዘንተኞቹ የገንዘብ ችግር ሳይገጥማቸው ሀዘናቸውን ረስተው፣ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማበረታታት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ በሚኖርበት ወይም በሥራ ቦታ አካባቢ ከሚገኙ እድሮች አባል ካልሆነ በአባልነት እንዲታቀፍ ይበረታታል፡፡ ስለዚህም ቢያንስ የአንድ ዕድር አባል መሆን የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ መቼስ የዕድሮችንና የዕድርተኞችን ምንነት ለዚህ ፅሁፍ አንባቢ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ስለሚሆን በዚሁ ይበቃናል፡፡ እናስ እጅ ከምን?
በአሁኑ ወቅት በርካታ እድሮች ከዘመኑ ጋር ዘምነው፣ ዓላማቸውንና ተደራሽነታቸውን አሳድገውና አስፋፍተው፣ ህብረታቸውን አጠናክረው በተለያዩ የልማት ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ፣ በአባላቶቻቸው ብቻ ሳይገደቡ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችንም ተደራሽ በማድረግ፣ ጉልህ የሆነ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሚና ሲጫወቱ ይስተዋላሉ፡፡ ለእድሮቹ የቀደመ አቋም መለወጥ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ ኤችአይቪ/ኤድስ ለመከላከልና ተያያዠ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአገራችን ኤችአይቪ/ኤድስ ተስፋፍቶ በርካታ ህይወት ይቀጥፍና የአልጋ ቁራኛ ያደርግ በነበረበት በዚያ አስከፊ ወቅት የችግሩ ሰለባ የሆኑትን ግለሰቦችና ቤተሰቦች የአካባቢያቸው ዕድሮች በሞት ብቻ ሳይሆን በህይወት ሊደርሱላቸው ቆርጠው ተነሱ፡፡ በዚያ አጋጣሚ ገርበብ ብሎ የተከፈተው የዕድሮች በር፤ ዛሬ በሰፊው ተከፍቶ ለበርካታ የልማት ሥራዎች እልፍኝ ሆነኗል፡፡
ይህ ክስተት መንግሥትን ጨምሮ የበርካታ ተቋማትን ዐይን በመሳቡ አለንላችሁ ባይም በዚያው ልክ ጨምሯል፡፡ የእድሮች ዋነኛ የልማት መሣሪያ የመሆን አቅማቸውም በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን እንደ ሳንድራ ጆሀንሰን (2ዐ1ዐ) ያሉ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሰረት፤ አያሌ ቁጥር ያላቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እድሮችንና መሰል ማህበራትን ለልማት አንቀሳቅሰዋል፡፡
ለአብነትም ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢ/ህ/ማ/ል/ድ) በተለይም ከ1990ዎቹ ጀምሮ ከማንም በላይ ማህበረሰባቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁትን ዕድሮችና ማህበራትን ወይም የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማትን ሁነኛ አጋሮቹ በማድረግ በርካታ የማህበረሰብ ልማት ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በተለይ ከ1996 ዓ.ም ወዲህ ኢ/ህ/ማ/ል/ድ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር የበርካታ ማህበረሰብ ምሥርት ተቋማትን (ዕድሮች፣ የዕድሮች ህብረት፣ አፎሻ፣ የሴቶች ማህበራት፣ የአካባቢ ተወላጆች ማህበራት፣ ወዘተ) ተቋማዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጠናከር ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ በምላሹም ተቋማቱ የማህበረሰባቸውን ችግር በመፍታት በተለይም ህፃናትን ጨምሮ ለችግር የተጋለጡትን የህብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ ኑሮዋቸውን የማሻሻልና ብቁ ዜጋ የማድረግ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡  
እስከዛሬም ድረስ ኢ/ህ/ማ/ል/ድ በ22 የተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ወደ 885,ዐዐዐ የሚጠጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከሚወክሉ ከ142 የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ጋር በመተባበር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙት እነኚህ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት፣ በኢ/ሕ/ማ/ል/ድ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አማካኝነት በየጊዜው ጠቃሚ የሆነ የገንዘብና የቴክኒክ እገዛ ያገኛሉ፡፡ ቴክኒካዊ እገዛው ሥልጠና፣ የልምድ ልውውጥና ክትትልን የመሳሰሉ የአቅም ልማት ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡
በአጠቃላይ የኢህማልድ ፕሮጀክቶች ተቋማቱ የአሠራር ሥርዓታቸውን ከማዘመን ጎን ለጎን በራሳቸው ፕሮጀክት ቀርፀው በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ በማስቻል ትልቅ ጠቀሜታ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ድጋፍ ተቋማቱ ከፍተኛ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማሻሻል የሚያስችል አቅም እንዲገነቡ ለማገዝ፣ በተለይም የመኖሪያ አካባቢዎችን ለህፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት ምቹ ለማድረግ እንዲተጉ ለማበረታታት የታለመ ነው፡፡ በምላሹም  እያንዳንዱ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋም እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መፍትሄ በማስቀመጥ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
በርካታ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ሕጻናት ትምህርታቸውን ያለ ችግር መከታተል ችለዋል፤ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ መረጋጋትም አግኝተዋል፡፡
በርካታ ወጣቶች እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ማስተዳደር ችለዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ በአካባቢው ላሉ ሌሎች ወጣቶች አርአያ በመሆን ተነሳሽነትን ፈጥረዋል፡፡
የገቢ ማስገኛ ሥራ ውስጥ የገቡ ብዛት ያላቸው የህጻናቱ አሳዳጊዎች በራሳቸው ገቢ ማግኘት ጀምረዋል፤ ልጆቻቸውንም ያለችግር ለመመገብና ለማስተማር በቅተዋል፡፡
የሴቶችን የልማት ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው
ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን፤ ወርሀዊ የገንዘብ ድጎማና እንደአስፈላጊነቱም የመኖሪያ ቤት ጥገና ተደርጎላቸዋል፡፡
ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በጤና፣ በግልና በአካባቢ ጥበቃ፣ በልጆች አስተዳደግ ወዘተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሌላም ሌላም ሌላም፡፡
ለዋቢነት ይሆን ዘንድ በሀዋሳ ከተማ ከሚገኙ አጋር ማህበራት እንዱን እንዘክር፤ በሀዋሳ ከተማ ዳካ ቀበሌ የሚገኘው የሴራሚክስ አካባቢ ነዋሪዎች መረዳጃ ዕድር ልማት ማህበር በ1988 ዓ.ም
እንደተለመደው ሁሉ አባላት ዕክል ሲደርስባቸው ለማቀባበር፣ ለማስተዛዘንና መጠነኛ የገንዘብ ድጎማ ለማድረግ ተቋቋመ፡፡ ይህ ዕድር ከኢ/ህ/ማ/ል/ድ ጋር አጋርነት በመፍጠር ወደልማት ከገባ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጠሯል፡፡ በኢ/ህ/ማ/ል/ድ ለዕድሩ አመራሮች የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠትና በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ዕድሮች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ በማመቻቸትና እንዲሁም ተገቢው የአሰራር ለውጥ ማሻሻያ እገዛ በማድረግ  አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ ተደርጓል፡፡
“የኢሕማልድ ፕሮጀክት ማህበረሰባችንን አስተዋወቀን፡፡ ከችግሩ ጋር አብረን እየኖርን ችግሩን አናውቀውም ነበር፡፡” የሚሉት ከሴራሚክ እድር አመራር አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋማርያም ደሳለኝ፤ “ይገርማችኋል በቀን አንዴ እንኳ መብላት የማይችሉ እዚሁ እስራችን ነበሩ፤ በተደረገላቸው ድጋፍም ከፍተኛ መሻሻል አሳይተዋል፡፡ ዛሬ በፕሮጀክቱ የታቀፉት የህብረተሰብ ክፍሎች በህይወታቸው ላይ ጉልህ የሆነ መሻሻል እያሳዩ ነው፡፡ የእነሱን ለውጥ በማየትም ሌሎች የአካባቢያችን ነዋሪዎች ተስፋቸው እያንሰራራ ነው”  በማለት በተደምሞ ስሜት ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋማርያም ገለፃ ከሆነ፤ ከኢ/ሕ/ማ/ል/ድ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ህፃናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ፣ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ፣ የዘወትር አልባሳት፣ የስፖርት አልባሳት በመስጠት እንዲሁም ለአሳዳጊዎቻቸው መሠረታዊ የንግድ ሥራ ክህሎት ሥልጠና እና ለንግድ ሥራ መነሻ የሚሆን መጠነኛ የገንዘብ ድጎማ በማድረግ፣ ህፃናቱ ያለ ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችለዋል፡፡ በተጨማሪም ዕድሩ በተለያዩ የህፃናት አስተዳደግ፣ በጤና፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ ለችግር የተጋለጡ ህፃናትና አረጋውያን እንክብካቤ እንዲሁም የማህበረሰብ ግልጋሎትና መልካም ሥነ-ምግባር በመሳሰሉ ርዕሶች ላይ ከ5ዐዐ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አስተምሯል፤ ግንዛቤያቸውንም አዳብሯል፡፡  ማህበረሰባቸውን ከችግር ለማውጣት ቆርጠው የተነሱት የዕድሩ አመራሮች፤ አባላቶቻቸውን በማሳመንና በማነሳሳት ከመደበኛ ወርሃዊ መዋጮ በተጨማሪ ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ለተጋለጡ ህፃናት እንዲሁም ጧሪ ቀባሪ ላጡ አረጋውያን መደገፊያ የሚሆን መዋጮ ጀምረዋል፡፡ እሰየው የሚያሰኝ ትልቅ እመርታ፤
“አሁን ትምህርቴን ለመቀጠል ድጋፍ አግኝቻለሁ፡፡ ዋናው ትኩረቴም እሱ ነው፡፡ የትርፍ ጊዜ የጥናት ፕሮግራም እየተከታተልኩ ውጤቴን አሻሽላለሁ፡፡ ወደፊት ሀኪም ሆኜ ኤችአይቪ/ኤድስ እና ሌሎች ህመሞችን ለመዋጋት እመኛለሁ፡፡” የምትለን ደግሞ የ1ዐ ዓመቷ ታዳጊ፤ ፀደይ አበራ (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሟ መቀየሩን ልብ ይሏል) ናት፡፡ ወላጆቿን በኤችአይቪ/ኤይድስ ምክንያት ያጣችው ይህች የባህር ዳር ከተማ ታዳጊ የቀን ጨለማ ውስጥ በነበረችበት ሰዓት “ጎህ ለሁሉም” የተሰኘው በአካባቢዋ የሚገኝ የማህበረሰብ ልማት ማህበር እንደደረሰላት ታወሳለች፡፡ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች፣ አልባሳት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የንፅህና  ቁሳቁሶችና የህይወት ክህሎት ሥልጠናዎች ማህበሩ ከኢ/ሕ/ማ/ል/ድ ባገኘው ድጋፍ አማካኝነት ለፀደይ ካበረከታቸው ድጋፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ፀደይም በአንደበቷ እንዳስረገጠችው፤ ተስፋዋ ለምልሞ በትምህርቷም መሻሻልን እያሳየች ነው፡፡
የአምስት ልጆች እናት የሆኑት የ4ዐ ዓመቷ ወይዘሮ መሪማ መሀመድ፤ በቡታጅራ ከተማ የቀበሌ ዐ5 ነዋሪ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ወይዘሮ መሪማ እንጀራ ጋግሮ በመሸጥ ልጆቻቸውን ያሳድጉ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረባቸውን ችግር ሲናገሩ፤ ለጤፍ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስለማይኖራቸው ሁልጊዜ በብድር ነበር የሚሠሩት፡፡ “ከሀብታም ገንዘብ ለመበደር እኮ ወይ ቤት ሊኖር ይገባል ወይ ተያዥ የሚሆን ሌላ ሀብታም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ድሀ በተለይም የእኔ ቢጤዎቹ ሴቶች በጣም እንቸገር ነበር” ይላሉ ወይዘሮዋ፡፡ ሆኖም በነፀብራቅ የሴቶችና ህፃናት የልማት ማህበር ሥር ከታቀፉ በኋላ ወይዘሮ መሪማ ለችግራቸው መፍትሄ አገኙ፡፡ ከነፀብራቅ በተቀበሉት የንግድ ሥራ ክህሎት ሥልጠናና ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር አማካኝነት የእራሳቸውን ንግድ በመጀመር፣ ልጆቻቸውን ማስተማር በአጠቃላይም ቤተሰባቸውን ያለችግር ማስተዳደር ችለዋል፡፡
የ23 ዓመቱ የቢሾፍቱ ከተማ ወጣት ተስፋሁን አበራ ታሪክ ደሞ እንዲህ ነው፡፡ ተስፋሁን ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነበር አባቱን በሞት የተነጠቀው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ እናቱም ታመው አልጋ ላይ ዋሉ፡፡ ስለዚህ ተስፋሁን ከእናቱና ከእህቶቹ ጋር በድህነት ሕይወቱን እንዲገፋ ተገደደ፡፡ “ስላሳለፍኩት ውስብስብ ህይወት ምንም የሚያውቁት ነገር ሳይኖር ሰዎች ሥራ በማጣቴ፣ እንደ ዕድሜ እኩዮቼ ዩኒቨርሲቲ ባለመግባቴ ይኮንኑኝ ነበር፡፡ ስለዚህ እኔም እራሴን የተረገምኩ አድርጌ እቆጥር ነበር፡፡” ይላል ተስፋሁን የቀድሞውን ሲያስታውስ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋሁን በትጋት የልማት ማህበር በመታቀፍ፣ የኮምፒዩተርና የመረጃ ቴክኖሎጂ ሥልጠና ወሰደ፡፡ ሥልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላም በፎቶግራፍ ማንሳትና እጥበት ሥራ በቋሚነትና በትርፍ ጊዜ በመሠማራት ጠቃሚ ገቢ ለማግኘት በቅቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ዛሬ የእራሱ ስቱዲዮ ያለው ሲሆን ወደፊትም ኢንተርኔት ካፌ ለመክፈት አቅዷል፡፡ ዛሬ ከእራሱና ከቤተሰቡ አልፎ ለሌላም ለመትረፍ ያስባል፡፡ “አሁን አንገቴን ቀና አድርጌ መሄድ እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም በጎረቤቶቻችን ዘንድ ጠንካራ ሠራተኛ ተብዬ ተቀባይነትን አግኝቻለሁ፡፡ ወደፊትም ችግረኛ ህፃናትንና ሴቶችን ለመደገፍ እምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡” ብሏል፡፡
ባጠቃላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ልማት ፊታቸውን በማዞር፣ የሕብረተሰባቸውን ችግር ለመፍታት ደፋ ቀና የሚሉት የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት፣ ነባራዊውን ሁኔታ ለመረዳት የበለጠ ቅርብ ስለሆኑ በነሱ አማካኝነት በርካታ ተጠቃሚዎችን በቀላሉ መለየትና መድረስ እንደሚቻል አያጠያይቅም፡፡ ማህበራቱም የአካባቢያቸውን ህብረተሰብ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት  ትልቅ ራዕይ እንደሰነቁ በተለያዩ ጊዜያቶች አስመስክረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ራዕያቸውን እውን ለማድረግ  የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለዘለቄታው እራሳቸውን እንዲችሉ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢ/ህ/ማ/ል/ድ በየዓመቱ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት መልካም ተሞክሮ ቀንን በማክበር፣ ተቋማቱ እርስበርስ እንዲተዋወቁ፣ ልምድ እንዲለዋወጡ፣ እንዲሁም ከመንግስትና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር  መልካም ትብብርና ትስስር እንዲፈጥሩ ልዩ መድረክ እያመቻቸላቸው ይገኛል፡፡ ዘንድሮም ሰኔ 23 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የድርጅቱ “ጄክዶ ኦፖርቹኒቲ ፎር ቼንጅ” የሥልጠና ማዕከል የመንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት “የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት አጋርነት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡ ዝግጅቱ ማህበራቱ የስራ ውጤቶቻቸውን በትዕይንትና በድምጽ የሚያስተጋቡበት፤ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተውጣጡ 6ዐ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት በማህበረሰብ ልማት ዘንድ ላደረጉት አስተዋፅኦ ዕውቅና የሚሰጥበት፤ ከዚህ በተጨማሪ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ልዩ ሽልማት የሚበረከትበት የማህበራቱ ዝግጅት ነው፡፡
የእንደዚህ ያለ ውጥን ዋና መልእክት፤ የማህበራትን ልማታዊ ፋይዳ በማጉላት ተገቢውን እገዛና ትብብር ለማህበራቱ መሻት ነው፡፡ ስለሆነም ከግለሰብ እስከ ተቋም፤ ከልጅ እስከ አዋቂ…. እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ በአንድነት በመተባበር እንደ ማህበረሰብ ምስርት ተቋማት ያሉ የህብረተሰብ አጋዦችን ማገዝ ከተቻለ፣ የማህበረሰብን ችጋር ማባረር ብሎም ከሥልጣኔና ከብልፅግና ማማ ላይ መውጣት ይቻላል፡፡  በመተባበር የማይናድ የችግር ጋራ፣ በመተጋገዝ የማይገፈፍ የችጋር ደንቃራ፤ ተቀናጅቶ በመስራት የማይቀረፍ ልማታዊ ፈተና የለምና ሁሉም ያብር፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!” ነውና ብሂሉ፡፡

ባለፈው ረቡዕ ሁለት ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች

ሰሜን ኮርያ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለባትን እገዳ በመጣስ ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ሁለት አደገኛ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት በፈጸመው ድርጊት አለማቀፍ ተቃውሞ  ገጥሞታል፡፡
የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር ጄን ናካታኒ፤የሚሳኤል ሙከራዎቹ ሰሜን ኮርያ ወታደራዊ አቅሟን በማሳደግ ደቡብ ኮርያን፣ ጃፓንንና ሌሎች አካባቢዎችን ለመምታት የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ማምረቷን የሚያሳዩ እንደሆኑ ጠቁመው፣ እያደገ የመጣው የሰሜን ኮርያ ወታደራዊ ሃይል  ለአገራቸውም ሆነ ለአካባቢው አገራት ከፍተኛ አደጋ ነው ማለታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፤ ድርጊቱ የጸጥታው ምክር ቤትን እገዳዎች የጣሰ ህገወጥ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፣ አገራቸው ከአሜሪካና ከደቡብ ኮርያ ጋር በመተባበር ለድርጊቱ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቀዋል፡፡
የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልንበርግ በበኩላቸው፤ሰሜን ኮርያ ሚሳኤሎቹን ማስወንጨፏን በጽኑ እንደሚቃወሙት ጠቁመው፣ አገሪቱ መሰል ጸብ አጫሪ ድርጊቶችን ከመፈጸምና የባለስቲክ ሚሳኤል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሚሳኤሎችን ከማስወንጨፍ እንድትቆጠብ አስጠንቅቀዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፤የሰሜን ኮርያን ድርጊት አስጊና ጸብ አጫሪ በመሆኑ በጽኑ እንቃወመዋለን፤ ራሳችንንም ሆነ ጃፓንና ደቡብ ኮርያን የመሳሰሉ አጋሮቻችንን ከመሰል ስጋቶች ለመከላከል የያዝነው ጽኑ አቋም አሁንም እንደጸና ነው ብለዋል፡፡


Saturday, 25 June 2016 12:12

የዘላለም ጥግ

- በጥበብ መፅሃፍ ውስጥ የመጀመሪያው
ምዕራፍ ሃቀኝነት ነው፡፡
ቶማስ ጄፈርሰን
- እውነቱን የምትናገር ከሆነ ምንም ነገር
ማስታወስ አይኖርብህም፡፡
ማርክ ትዌይን
- ስለ ራስህ እውነቱን የማትናገር ከሆነ፣ ስለ
ሌሎች እውነቱን ልትናገር አትችልም፡፡
ቪርጂንያ ውልፍ
- በመጠራጠር ወደ ጥያቄ እናመራለን፣
በመጠየቅ ወደ እውነቱ እንደርሳለን፡፡
ፒተር አቤላርድ
- እውነት ነፃ ያወጣሃል፤ መጀመሪያ ግን
አሳርህን ያበላሃል፡፡
ጄምስ ኤ. ጋርፊልድ
- እውነት ጫማዋን ስታጠልቅ፣ ውሸት
የዓለምን ግማሽ ልትጓዝ (ልታዳርስ)
ትችላለች፡፡
ቻርለስ ስፐርጊዮን
- የትምህርት ግብ ዕውቀትን ማስፋፋትና
እውነትን ማሰራጨት ነው፡፡
ጆን ኤፍ.ኬኔዲ
- አብዛኞቹ ቀልዶች መራር እውነትን
ይገልፃሉ፡፡
ላሪ ጌልባርት
- ተፈጥሮን መርምር፣ ተፈጥሮ የእውነት
ጓደኛ ናት፡፡
ኢድዋርድ ያንግ
- ለሰዎች ሃቁን የምትነግራቸው ከሆነ
አስቂኝ ሁን፤ ያለበለዚያ ይገድሉሃል፡፡
ቢሊ ዋይልደር
- ህይወት ሞትን እንዲህ ስትል ጠየቀችው፡
- “ለምንድነው ሰዎች እኔን የሚወዱኝ፤
አንተ ግን የሚጠሉህ?”
ሞትም መ ለሰላት፡- “ ምክንያቱም አ ንቺ
ውሸት ነሽ፤ እኔ ደግሞ መራር እውነት
ነኝ”
ያልታወቀ ተናጋሪ
- እውነቱን ተናገር፤ አሊያም ሌላ ሰው
ይናገርልሃል፡፡
ስቴፋኒ ክሌይን
(ስለ እውነት



ከ65.3 ሚ የአለማችን ስደተኞች፣ ግማሽ ያህሉ ህጻናት ናቸው
   በአለማችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ስደተኞች ብዛት በታሪክ ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገቡ ሲሆን እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2015 መጨረሻ  በስደተኝነት የተመዘገቡ፣ ጥገኝነት የጠየቁ ወይም በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 65.3 ሚሊዮን መድረሱን ተመድ አስታወቀ፡፡የአለማችን ስደተኞች ቁጥር በ2014 ከነበረበት የ10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጸው የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን፣ በአለማችን ከሚገኙ ስደተኞች መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት የሶርያ፣ የአፍጋኒስታንና የሶማሊያ ዜጎች መሆናቸውን ጠቁሞ 10 ሚሊዮን ስደተኞች ያሏት ሶርያ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች ብሏል፡፡በአለማችን ከ113 ሰዎች መካከል አንዱ ስደተኛ እንደሆነ የጠቆመው ኮሚሽኑ፤በፈረንጆች 2015 በአንድ ደቂቃ 24 ያህል ሰዎች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ መገደዳቸውንና ግማሽ ያህሉ የአለማችን ስደተኞች ከ18 አመት በታች የሚገኙ ህጻናት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ዓምና ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን በላይ እንደነበር ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤በርካታ ስደተኞችን በመቀበል ከአለማችን አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ቱርክ መሆኗንና በአገሪቱ 2.5 ሚሊዮን ያህል የሌሎች አገራት ስደተኞች እንደሚገኙ ገልጧል፡፡

   ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት አያሌ የቅኝ ግዛት ወረራዎች ሙከራ ቢደረግባትም አያት ቅድመ አያቶቻችን ባደረጉት ተጋድሎ፣ታፍራ የተከበረች ኢትዮጵያን ተረክበናል፡፡ ከእነዚያ አኩሪ ድሎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ለአፍሪካውያን ጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ በአርአያነት የሚጠቀሰው የአድዋ ጦርነት ነው፡፡ ጣልያኖች እጅግ ዘመናዊና የሰለጠነ ጦር እየመሩ ቢመጡም በዳግማዊ ሚኒሊክ የሚመራውና ከአልደፈርም ባይነት ወኔ በቀር ዘመናዊ ሊባል የሚችል ጦር መሳሪያ ያላነገበው የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ጣልያኖችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ ጦርነቱን በድል አጠናቋል፡፡
እንደምናውቀው ከቅኝ ግዛት ማክተም በኋላ ምዕራባውያን ሀገራት ከአፍሪካውያን ጋር ልዩ ልዩ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በመፍጠር ለሀገራቸው ገጽታ ግንባታ ጠቃሚ ነው ብለው የሚያምኑትን ተግባራት ያከናውናሉ፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና ወታደራዊ ትብብሮች ይሳተፋሉ፡፡
ዛሬ የትምህርት ትብብር ላይ እናተኩርና ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅኝ ግዛት ማክተም በኋላ ብዛት ያላቸው ኢንተርናሽናል ኮሚዩኒቲ ት/ቤቶች ተከፍተዋል፡፡
የአሜሪካን አይ ሲ ኤስ፣ የእንግሊዙ ሳንድ ፎርድ፣ የፈረንሳዩ ሊሴ ገ.ማርያም፣ የጀርመኑ ጎቴ ኢንስቲትዩት እንዲሁም የጣልያን ት/ቤት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ት/ቤቶች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ባላቸው ስምምነት፣ በሀገራቸው የትምህርት ስርአት መሰረት ትምህርት የሚሰጡ ቢሆንም በሀገሪቱ ካሌንደር  የሚከበሩ ሀገራዊም ሆነ ሀይማኖታዊ በአላትን የማክበር ግዴታ ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ መሬቱ የኢትዮጵያ ነውና፡፡ አለም አቀፍ ተቋማትና የውጭ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን ሀገራዊ በዓላት ማክበር ይጠበቅባቸዋል! በዚህ መሰረት አብላጫዎቹ ኤምባሲዎችና ት/ቤቶቻቸው በዓላትን ያከብራሉ! ት/ቤቶቻቸውን ይዘጋሉ፡፡ ያም ሆኖ፤ የኢጣልያን ኮሙኒቲ ት/ቤት፣ የአድዋ ድል በዓል በሚከበርበት የካቲት 23 አንድም ቀን ዘግቶ እንደማያውቅ፣ እንዲሁም ከሌላው ቀን በተለየ በዚያ እለት ከት/ቤት የቀረ ተማሪን የተለየ ቅጣት እንደሚቀጣ አንድ ልጁን እዚያ የሚያስተምር ወዳጄ ቢነግረኝ፣ጉዳዩ ከንክኖኝ ነው ይህን ትዝብት ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡
ኧረ ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ይሄንን ያውቁ ይሆን? እነዚህ ሰዎች እኮ ያንን ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሆነውን ታላቅ ድል በዘመናት ሂደት ከኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ አደብዝዞ ለማጥፋት ተግተው እየሰሩ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በቅርቡ 75ኛ ዓመት የድል በዓል አራት ኪሎ አደባባይ ላይ በተከበረበት ወቅት የኢጣልያ አምባሳደር ተገኝተው ይህንኑ ሀሳብ ሲያጠናክሩ በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ ጎበዝ … የጀግንነታችን አሻራ ያረፈበት አኩሪ የድል ቀናችንን ጣልያኖቹ ሲክዱትና ሲያናንቁት መመልከት ለማንም ኢትዮጵያዊ የማይዋጥና የሚያንገበግብ በመሆኑ፣የሚመለከተው የመንግስት አካል ጉዳዩን በቸልታ ሊያየው አይገባም እላለሁ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል ነው ነገሩ፡፡
-ከሙሉጌታ ጅኒ

ምክንያቱና ሰበቡ ምንድነው?

    በእንግሊዝ ፓርላማ ከ99% በላይ መቀመጫ በመያዝ የሚታወቁ አራቱ አውራ ፓርቲዎች፤ ለወትሮው በአይነ ቁራኛ የሚተያዩ ብርቱ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡ በትናንቱ ምርጫ ግን እርስ በርስ አልተፎካከሩም፡፡ ያለወትሯቸው ለአንድ ዓላማ በጋራ ለሁለት ወራት ቀስቅሰዋል፣ “እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መፈናቀል የለባትም” በማለት፡፡
የገዢ እና የተቃዋሚ ፓርቲ ዋና ዋና መሪዎች፣ እንዲህ ተባብረው ቢቀሰቅሱም፣ አልተሳካላቸውም፡፡ አብዛኛው እንግሊዛዊ፣ የመሪዎቹን ቅስቀሳና ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን ትቶ፤ በትናንቱ ምርጫ፣ “ከአውሮፓ ህብረት ለመገላገል” ወስኗል - 51 በመቶ ያህሉ መራጭ፡፡
ዋና ዋናዎቹ የፓርቲ መሪዎች ብቻ አይደሉም የተሸነፉት፡፡ የእንግሊዝ ብሄራዊ ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት … የማስጠንቀቂያ መዓት ሲያዥጎደጉዱ ከርመዋል፡፡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ከለቀቀች፣ ኢኮኖሚዋ በ6% ያሽቆለቁላል፤ ፓውንስ ስተርሊንግ ይረክሳል፤ ዋጋ ይንራል፤ የዜጎች ገቢ በ3ሺ ዶላር ይቀንሳል … ማስፈራሪያው ስፍር ቁጥር የለውም፡፡
ከአውሮፓ አንጋፋ መሪዎች በተጨማሪ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም፣ እንግሊዛውያንን አስፈራርተዋል፡፡ “በንግድና በኢንቨስትመንት ዙሪያ፣ ቅድሚያ ሰጥተን የምንደራደረው ከአውሮፓ ህብረት ጋር ነው፤ እንግሊዝ ከህብረቱ ከወጣች ውራ ትሆናለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል ኦባማ፡፡
ይሄ ሁሉ የማስፈራሪያ ውርጅብኝ ውጤት አላስገኘም፡፡ በተለይ ደግሞ፤ የአገሪቱ አንጋፋ ፓርቲዎችና ዋና ዋና መሪዎች፣ እንዲህ ተሰሚነት ማጣታቸው አስገራሚ ነው፡፡ እነማን እንዳሸነፉ ደግሞ ተመልከቱ፡፡ ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ያፈነገጡ የተወሰኑ ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም  ለዓመታት በፓርላማ አንዲት ወንበር ለማግኘት ያቃተው ፓርቲ… እነዚህ ናቸው “ከአውሮፓ ህብረት መገላገል አለብን” በማለት ሲቀሰቅሱ የነበሩት፡፡ እናም፣ ነባሮቹ አውራ ፓርቲዎችና መሪዎች ተሸንፈው፣ ድል የአፈንጋጮች ሆነ፡፡
በምርጫው ሽንፈት ማግስት፣ ዳቪድ ካሜሮን፣ ከጠቅላይ ሚንስትርነት እና ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ መሪነት ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
ተቃዋሚያቸው የሌበር ፓርቲ መሪም፣ ከሃላፊነታቸው እንዲወርዱ፣ ከራሳቸው ፓርቲ ፖለቲከኞች ጥያቄ ተነስቶባቸው፣ አፋፍ ላይ ደርሰዋል፡፡
ይበልጥ አስገራሚ የሚሆነው ግን፤ ሌሎች የአውሮፓ አገራትም በተመሳሳይ አስደንጋጭ ማዕበል እየተናጡ መሆናቸው ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት፣ በጣሊያን ከተሞች በተካሄዱ ምርጫዎች፤ በተለይ በዋና ከተማዋ በሮም እንዲሁም በቱሪን፣ ነባሮቹ ፓርቲዎች አሸናፊ አልሆኑም፡፡ እስከዛሬ ስልጣን በወጉ ያልቀመሰ ፓርቲ ነው ገንኖ የወጣው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በኦስትሪያ ለ60 ዓመታት ስልጣን ላይ ሲፈራረቁ የነበሩ ሁለት ነባር ፓርቲዎችም፣ ተዘርረዋል፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ፣ የሁለቱ ነባር ፓርቲዎች ድርሻ 80% ያህል ነበር፡፡ ባለፈው ወር በተካሄደው ተመሳሳይ ምርጫ ግን፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ የሁለቱ ነባር ፓርቲዎች ድርሻ ቁልቁል ወርዶ ተፈጥፍጧል፡፡ ከ11% የበለጠ ድምፅ ስላላገኙ፣ በማጣሪያው ከምርጫ ተሰናብተዋል፡፡
በተቃራኒው ስልጣን ቀምሰው የማያውቁ … በጭራሽ ከስልጣን አጠገብ ደርሰው የማያውቁ … በአንድ ወገን ከኢንቨስትመንት ይልቅ ድጎማን የሚያወድሱ የሶሻሊዝም ግርፍ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ዘረኝነትን የሚያናፍሱ የፋሺዝም ግርፍ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ብልጫ አግኝተዋል፡፡
በግሪክም፣ ነባሮቹ ፓርቲዎች ተሸንፈው፣ የሶሻሊዝም አራጋቢዎች ስልጣን ይዘዋል፡፡ በስፔንም እንዲሁ፣ አምስት ዓመት ያልሞላቸው ፓርቲዎች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመግነናቸው፣ ነባሮቹ ፓርቲዎች፣ የፓርላማ አብላጫ ወንበር መያዝ አልቻሉም፡፡ ምን ይሄ ብቻ! የአየርላንድ ነባር ፓርቲዎች፣ ተመሳሳይ ፅዋ ተጎንጭተዋል፡፡ ፊንላንድና ዴንማርክም እንዲሁ፣ ነባር ፓርቲዎችን በሚያናጋ ማዕበል ተመትተዋል፡፡ በጀርመን ዘንድሮ በተካሄደ የክልሎች ምርጫ፣ ከአምስት ዓመት በፊት ያልነበረ አዲስ ፓርቲ፣ ከነባሮቹ የበለጠ ድምፅ ሲያገኝ ታይቷል፡፡ በፈረንሳይም እንዲሁ፡፡ ….
እንደ ነባሮቹ ፓርቲዎች ሁሉ፣ ነባሩ የኢኮኖሚ ስርዓትም እየተንገራገጨ ነው፡፡ መንግስታት በየጊዜው የድጎማ መዓት ይፈለፍላሉ፡፡ ከዜጎች ገቢ ግማሽ ያህሉን ታክስ እየቆረጡ ይወስዳሉ፡፡  ይህም  አልበቃቸውም፡፡ መረን የተለቀቀ ወጪያቸውን ለመሸፈን፣ መንግስታት በትሪሊዮን ዶላሮች ብድር ተዘፍቀዋል፡፡ እንዲህ በመንግስታት ጣልቃ ገብነት የተቀየጠው የአውሮፓ የኢኮኖሚ ስርዓት፣ ከቀውስ መውጣት አቅቶታል፡፡ ከመንፏቀቅ ያለፈ እድገት ማስመዝገብ ተስኖታል፡፡ስራ አጥነት፣ ከ10% በታች አልወርድ ብሏል፡፡
ነባሮቹ ፓርቲዎች፣ ቅይጥ ኢኮኖሚያቸውን ለማሻሻልና የነፃ ገበያ ስርዓትን ለማስፋፋት አልቻሉም፡፡ ተሰሚነታቸውም ከኢኮኖሚው ጋር ተዳክሟል፡፡
ችግሩ ምንድነው? በነባሮቹ ምትክ፣ በምድረ አውሮፓ እየገነኑ የመጡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፣ ከቀድሞዎቹ የባሱ እንጂ የተሻሉ አይደሉም፡፡ በተጨማሪ የታክስ ጫናና በተጨማሪ የድጎማ ብክነት፣ ኢኮኖሚን የሚያዳክሙ የሶሻሊዝምና የፋሺዝም ግርፍ ናቸው - እንደ አሜሪካውያኑ በርኒ ሰንደርስ እና እንደ ዶናልድ ትራምፕ፡፡

ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፌ ስቡክ የሰመረላቸው የመንግስት ባ ለስልጣናትና ተ ቋማት ጥ ቂት ናቸው ብሏል

   ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ላይ ባደረገው የናሙና ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን በፌስቡክ በኩል የሚያስተላልፏቸው የጥላቻ መልዕክቶችና አስተያየቶች መጠን፣ ከተጠቃሚዎች ብዛት አንጻር እጅግ አነስተኛ ሆኖ እንዳገኘው አስታወቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያውያንን የፌስቡክ አጠቃቀም በተመለከተ ለሁለት አመት ያህል ያከናወነውና ሰሞኑን ይፋ ያደረገው “መቻቻል” የተሰኘ ርዕስ ያለው ይህ ጥናት፤ በናሙናነት ከተወሰዱት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አስተያየቶች መካከል ብሄርን፣ ዜግነትን፣ ሃይማኖትን ወይም ጾታን መሰረት በማድረግ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን የሚያገልሉ የጥላቻ መልዕክት ያዘሉት 0.7 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ ገልጿል፡፡
በ2007 ዓ.ም ከየካቲት እስከ ሃምሌ በነበሩት ወራት ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከሰጧቸው አስተያየቶችና መልዕክቶች ውስጥ 13 ሺህ ያህሉን በናሙናነት ወስዶ የተነተነው ጥናቱ፣ አደገኛ ወይም ጠብ አጫሪ ተብለው ከተመደቡት የፌስቡክ አስተያየቶችና መልዕክቶች መካከል 21.8 በመቶ የሚሆኑት የፖለቲካ ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ እንደሆኑና ሃይማኖትና ብሄር 10 በመቶ እና 14 በመቶ ያህል ድርሻ እንዳላቸውም ገልጧል፡፡
በጥናቱ የጥላቻ አስተያየቶችንና መልዕክቶችን አስተላልፈዋል ከተባሉት ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መካከል 92 በመቶ ያህሉ፣ ትክክለኛ ማንነታቸውን ደብቀው በሃሰተኛ የፌስቡክ ስም የሚጠቀሙ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የመንግስት ተቋማት ፌስቡክን እንደ አንድ የመረጃ ማሰራጫ መንገድ ለመጠቀም ሙከራ እያደረጉ ነው ያለው ጥናቱ፤ ይሄም ሆኖ ግን ተጽዕኖ መፍጠርና ተሰሚነት ማግኘት የቻሉት በጣም አነስተኛ ናቸው ብሏል፡፡
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያከናወነው ይህ ጥናት፤ ከ2007 የካቲት እስከ ሃምሌ ባሉት ወራት፣ በ1ሺህ 55 የፌስቡክ ገጾች ላይ የተሰጡ ከ13 ሺህ በላይ አስተያየቶችና መልዕክቶችን በናሙናነት ወስዶ መተንተኑ ተገልጧል፡፡

     ከብራዚልና ከሜክሲኮ ዋና ከተሞች፣ ከካልታና ከኢዝላማባድ … ከሃጋሪና ከፖላንድ እንዲሁም ከዩክሬንና ከማሌዥያ ዋና ከተሞች ይልቅ፣ የአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት ይከፋል፡፡ ከካናዳ ኦታዋ እና ጊታሞና ሞንትሪያል፤ ከጀርመን ሊፕዚግ እና ኑርንበርግ ከተሞች ጋር ሊነፃፀርም፣ የኑሮ ውድነት በአዲስ አበባ ይከብዳል፡፡ ሜርሰር የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው አመታዊው የዓለማችን ከተሞች የኑሮ ውድነት ደረጃ፣ መዲናችን አዲስ አበባ 143ኛ ደረጃን መያዟን አስታወቀ፡፡
ተቋሙ ለ22ኛ ጊዜ በ209 የዓለማችን አገራት ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ ተመስርቶ ይፋ ያደረገው የዘንድሮ ሪፖርት እንደሚለው፣ በአለማችን ከሚገኙ ከተሞች ለመኖር ከፍተኛ ወጪን በመጠየቅ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘቺው ሆንግ ኮንግ ስትሆን የአንጎላ መዲና ሉዋንዳና የስዊዘርላንዷ ዙሪክ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ዝቅተኛ ወጪን የሚጠይቁ የዓለማችን ከተሞች ተብለው የተዘረዘሩት ደግሞ የናሚቢያዋ ዊንድሆክ፣ የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውንና የካይሬጊስታኗ ቢሽኬክ ሲሆኑ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ከተሞች የአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ያለባት ከተማ ናት ያለው ሪፖርቱ፤ የኮንጎዋ ኪንሻሳና የቻድ ርዕሰ ከተማ ጃሜና ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አብራርቷል፡፡
ተቋሙ የከተሞችን የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የአልባሳትና የመሳሰሉትን ከ200 በላይ የሚሆኑ ምርቶችና አገልግሎቶች ዋጋ እና ሌሎች ተያያዥ የፋይናንስ ሁኔታዎችን በመገምገም የየከተሞችን የኑሮ ውድነት ደረጃ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭት እንዲቋረጥ አድርጓል ተብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሰኞ ዋጃሌ በተባለቺው የኢትዮ-ሶማሊላንድ የድንበር ከተማ አምስት የሶማሊላንድ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር አውሎ ማሰሩንና አራቱ ከቆይታ በኋላ ሲለቀቁ አንደኛው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ዳስላን ሬዲዮ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞቹን ከማሰር ባለፈ፣ ሆርን ኬብል የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ ያስተላለፈው ዘገባ ተገቢ አይደለም በሚል ታይኮም ለተባለው የሳተላይት ተቋም ባቀረበው ቅሬታ፤ጣቢያው በአካባቢው ያሰራጭ የነበረው ፕሮግራም እንዲቋረጥ ማድረጉንም ሶማሊላንድ ኢንፎርመር ዘግቧል፡፡
ጋዜጠኞቹ በዋጃሌ ከተማ በተዘጋጀ ሃሰተኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ በኋላ በመንግስት ልዩ ሃይል ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ወደ ጂግጂጋ ከተማ ተወስደው እንደታሰሩ የጠቆመው ዘገባው፣ አራቱ ሲፈቱ ሆርን ኬብል ቲቪ የተባለው የሶማሊላንድ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ባልደረባ፣ጋዜጠኛ ሙክታር ኑር ግን አሁንም በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን ያሰረበት ምክንያት ግልጽ አይደለም ያለው ዘገባው፤ሶማሊላንድና ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ረገድ ተባብረው ሲሰሩ እንደነበርና ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ የታሰሩ የአገሪቱ ጋዜጠኞች በሃርጌሳ በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁሞ ሌሎች ጋዜጠኞችም በኢትዮጵያ በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውሷል፡፡የሶማሊላንድ ጋዜጠኞች ማህበር፣ ናሽናል ዩኒየን ፎር ሶማሊ ጆርናሊስትስ እና ሶማሊ ኢንዲፔንደንት ሚዲያ ሃውስስ አሶሴሽን የተባሉት የጋዜጠኞች ማህበራት፣ድርጊቱን የፕሬስ ነጻነት ጥሰት ነው በማለት ያወገዙት ሲሆን በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሙክታር ኑር፣ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቅ ጠይቀዋል፡፡

“ከ7 ወር በኋላ ከድርቅና ተረጂነት ዜጎች ይላቀቃሉ” መንግስት

   የበልግና የክረምቱ ዝናብ በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ በድርቅ የተጎዱ ዜጎች በመጪው ጥር 2009 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ከተረጂነት ይላቀቃሉ የተባለ ሲሆን በግብርና ላይ የሚሰሩ አለማቀፍ ተቋማት በበኩላቸው፤ መንግስት ለግብርናው በቂ ዝግጅት አላደረጉም ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ የክረምቱ ዝናብ በሚፈለገው መጠን እየዘነበ መሆኑን የጠቀሰው በአፍሪካ ግብርና ላይ ትኩረቱን ያደረገው የአርካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት የተሰኘው ተቋም፤ መንግስት እርዳታ በማቅረብ ላይ ብቻ በመጠመዱ የዘር አቅርቦቱን ቸል ብሎታል ብሏል፡፡ የዘር አቅርቦቱ እጥረት እያጋጠመው ነው ያለው ተቋሙ፤ ይህም የድርቁን ችግር ሊያራዝመው ይችላል ብሏል፡፡
የብሄራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኮሚሽነር በበኩሉ፤ ከ7 ወር በኋላ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ከድርቅ ተረጂነት ትላቀቃለች ተብሎ እንደሚጠበቅና የድርቁን ወቅታዊ ችግርና የተረጅዎችን ሁኔታ የሚያጠና ቡድን ወደየአካባቢዎቹ መላኩን ጠቁመዋል፡፡
“እስካሁን የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ከ10.2 ሚሊዮን አልዘለለም” ያሉት ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ፤ የበልጉ ዝናብ ምን ያህል ተረጅዎችን ከተረጅነት አላቀቀ የሚለውን ቡድኑ ካጠና በኋላ የተረጂዎች ቁጥር አሁን ካለበት ሊቀንስ ይችላል ብለዋል፡፡ የበልግና የክረምቱን ዝናብ በአግባቡ ተጠቅሞ የሚሰራው ስራ ቀጣዩን ሁኔታ ይወስነዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ወደ 15 ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ የተሰጋው ግን እስካሁን አልደረሰም ብለዋል፡፡
የመንግስት ሙሉ ትኩረት የእርዳታ ስራው ላይ መሆኑ የተገኘውን ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ክፍተት እየፈጠረ ነው ያለው የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት በበኩሉ፤ ዝናቡ ትርጉም የሚኖረው አርሶ አደሮች በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ ነው፤ ይህ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ እየተስተዋለ አይደለም ብሏል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የክረምቱን ዝናብ ለመጠቀም “በዘር ሳይሸፈን የሚቀር መሬት መኖር የለበትም” በሚል አቋም፤ የዘር አቅርቦቱን ባለው አቅም ሁሉ እያቀረበ መሆኑን እምብዛም እጥረት ሊያጋጥም አይችልም ብሏል፡፡