Administrator

Administrator

 በመላ አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል

ባለፈው ሳምንት ሁለት የፋይናንስ ሚኒስትሮችን ከሃላፊነታቸው ያነሱት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያደቅ ተግባር እየፈጸሙ ነው በሚል ባለፈው ረቡዕ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ያሰሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በአገሪቱ ሙስና ተስፋፍቷል፣ በገዢው ፓርቲ የስልጣን መተካካት ላይ አግባብ ያልሆነ ተግባር ተፈጽሟል በሚል ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ረቡዕ ዕለት ጆሃንስበርግ ውስጥ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱና በመንግስት የሚከናወኑ የሙስና ድርጊቶችን የሚገታ ጠንካራ ንቅናቄ እንደጀመር መጠየቃቸውን አስታውቋል፡፡
በዕለቱ ከጆሃንስበርግ በተጨማሪ በመላ አገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በኬፕታውን በተከናወነው ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ዙማ ከስልጣን መውረድ አለባቸው የሚል መፈክር ሲያሰሙ መዋላቸውን ጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የቀድሞውን የአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ናላላ ኔኔን ከሃላፊነታቸው ማንሳታቸው ከፍተኛ ትችት እንዳስከተለባቸውና ውሳኔያቸው የገበያ ቀውስ መፍጠሩንም አስታውሷል፡፡

- ላለፉት 12 አመታት የሚገዳደራትአልተገኘም
- ለኑሮ የማትመቸዋ የአለማችን የመጨረሻዋ አገር ኒጀር ናት

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በየአመቱ ይፋ በሚያደርገው ሂዩማን ዲቨሎፕመንት ኢንዴክስ ሪፖርት ውስጥ ለኑሮ ምቹ የሆኑ የአለማችን አገራት ዝርዝርን ላለፉት 11 አመታት በቀዳሚነትን ይዛ የዘለቀችው ኖርዌይ፣ ዘንድሮም በቀዳሚነት መቀመጧን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
አማካይ የህይወት ዘመን፣ ትምህርት፣ ገቢ እና የኑሮ ደረጃን በመስፈርትነት በማስቀመጥ የአለማችንን አገራት እየገመገመ ደረጃ የሚሰጠው ተቋሙ፤ ኖርዌይ በሁሉም መስፈርቶች ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ዘንድሮም ለኑሮ ምቹዋ አገር ለመሆን መብቃቷን አስታውቋል፡፡
በኖርዌይ አማካይ የህይወት ዘመን 81.6 አመት ሲሆን ጠቅላላ አመታዊ ብሄራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋም 64ሺህ 992 ዶላር መድረሱንና ይህም በተቋሙ ጥናት ከተካተቱት 188 ያህል የአለማችን አገራት በቀዳሚነት እንዳስቀመጣት  ዘገባው ገልጧል፡፡ ከኖርዌይ በመቀጠል እስከ አምስተኛ ደረጃን የያዙት የአለማችን አገራት አውስትራሊያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክና ኒዘርላንድስ ናቸው ተብሏል፡፡
ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ አምስት የአለማችን አገራት የተባሉት ደግሞ ኒጀር፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኤርትራ፣ ቻድ እና ብሩንዲ ናቸው፡፡

    በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በጐልማሶችና ማህበረሰብ ልማት ትምህርት ክፍል መምህርና የትምህርት ክፍሉ ሃላፊ በሆኑት በአቶ ያዴሳ ቶሎሳ ወዬሳ የተዘጋጀውና በትምህርት በምርምርና በአተገባበር ሂደቶች ላይ ትኩረት አድርጐ የተሰናዳው “አጠቃላይ የትምህርት እና የስራ ላይ ምርምር ዘዴዎችና አተገባበር” የተሰኘ መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ በማንኛውም ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች፣ ለመመረቂያ ጽሑፍ ዝግጅትና በማንኛውም የስራ መስክ በተግባራዊ የስራ ላይ ምርምር ለተሰማሩ እንዲሁም ሊሰማሩ ለሚሹ ባለሙያዎችና መምህራን እንደ ማጣቀሻ ማኑዋል ሆኖ እንደሚያገለግልም ተጠቅሷል፡፡ በሁለት ክፍሎች የተዘጋጀውና በርካታ ምዕራፎችን ያካተተው መጽሐፉ፤ በ204 ገጾች የተመጠነ ሲሆን በ80 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡  

የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስትና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር በሆኑት ዶ/ር ሞገስ አየሁ የተፃፈውና በአዕምሮ ህመምና ህሙማን ህይወት ላይ ትኩረቱን ያደረገው “ድፍርስ” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡
በ18 ክፍሎች የተዘጋጀው ይኸው መጽሐፍ፤ ስለ አንጐል መታወክና መንስኤዎቹ፣ ስለ አዕምሮ ህመም ምንነት፣ አዋቂና ህፃናት ላይ ስለሚከሰት የአዕምሮ ህመም፣ ስለ ኦቲዝምና ሌሎች ከአዕምሮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጥልቅ ትንታኔን ይዟል፡፡ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ አስተያየቱን ያሰፈረው ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፤ “ዶክተሩ የፃፉት ይህ መጽሐፍ የሚጠቅመው ለአዕምሮ ህሙማንና ለአሳታሚዎች ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ኪናዊ ስራ ለሚሰሩ ገጣሚያን፣ ልቦለድ ደራሲያንና ፊልምና ቴአትር ለሚሰሩም የጥበብ ሰዎች ግብአት የሚሆን ነው” ብሏል፡፡ በ184 ገጾች የተሰናዳው መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ75 ብር፣ ለውጭ አገራት በ20 ዶላር ይሸጣል። 

በደራሲ ዘውዱ አበጋዝ ተተርጉሞ በተሻለ አሰፋ የተዘጋጀው “ቆንጆዎቹ” የተሰኘ ቲያትር ከ15 አመታት በኋላ ወደ መድረክ የተመለሰ ሲሆን ዛሬ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ለተመልካች ይቀርባል፡፡
በስደት ህይወት ላይ የሚያጠነጥነውና የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል ይዳስሳል የተባለው ይኸው ቲያትር፤ የ2፡15 ርዝማኔ እንዳለው ታውቋል፡፡ በቲያትሩ ላይ ወለላ አሰፋ፣ ትእግስት ግርማ፣ ሰለሞን ሐጐስ፣ ይገረም ደጀኔና ሕሊና ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች አንጋፋ ተዋንያን ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

Saturday, 19 December 2015 10:42

አሴዋ ሁሌም በልባችን ነህ!!

አይረሴ ራዕይ
እኛማ እንቆጥራለን
ዛሬም ሙሉ ሳቅክን
ያልተሸራረፈ ሙሉ ፈገግታህን
እንዳቀፍን አለን በየምላዳችን የነገ ሰብልህን
አሴ ኩራ ኩራ፣ ባለህበት ኩራ
ብርሃኑ ያዘምራል፣ ያሳብህ ተራራ
ዓመቱማ ያልፋል ወደፊት ገፍትሮን
ዘመኑ ቢሸብት፣
አይረሴ ራዕይ፤ ነጭ ፀጉር የለው
ከቶ መች ይረሳል
ህልምህ የወይን ጠጅ ሲነጋ ይበስላል፡፡
የነበረህና የነበረን ሀሳብ፣ እያደር ይጠራል፡፡
ስምህ ማዘርዘሩ፣ መንፈስህ መብቀሉ
ዕምነት ፍልስፍና ውልና ፈትሉ
ዕውቀትና ትጋት ብርሃን ፊደሉ
ሩቅ እንዳሰብነው ሩቅ ነው ገድሉ
ዛሬም አለ ቃሉ፣
ያውም በርቶ ፈክቶ፣ እስከማዕዘኑ፡፡
አውቃለሁ ታውቃለህ
የመከረኛ አገር መከሯ እስኪገባ
መከራ መብዛቱ
ዕውን ቢሆን እንኳ
ራዕይህ አለ ምስክር ይቆማል፤ ቀኑ ለመንጋቱ፡፡
አይቆምም ጉዟችን ባይቆምም ሥጋቱ
አይደለም ራዕይ ብሳና ዛፍ ግንድ
ሽበት አይወርሰውም፤ የዕድሜ ዘመን ግርድ
አይረሴ ራዕይ የቸገንክበትን
የፍል ዕውቀት እርሻ፣ የዓለም አሂዶህን
ታያለህ ማሳውን፡፡
አሴ ኩራ ኩራ
ብርሃን ያዘምራል ያሳብህ ተራራ
የራዕይ ተራራ !!
(ለአቶ አሰፋ ጎሳዬ ሙት አመት መታሰቢያ)
ነ.መ


Saturday, 19 December 2015 10:32

ቁጣ ማለስለስ

አጨሳለሁ!...ማለቴ የሠርጌ እለት ማጨስ እፈልጋለሁ፡፡
አንሙት ጓደኛዬ ሰሞኑን ከመካኒክነት ስራው ጋር ተያያዥነት ያለው ቁጣ ማለስለስ የሚል ስልጠና ወስዷል፡፡ በዚህ ስልጠና መሰረት ቁጣዬ እንዳይነድ ልተገብር ስለሚገባኝ የተለያዩ የቁጣ ማለስለሻ ዘዴዎች ነግሮኛል፡፡ ከዘዴዎቹ መሃከል ማጨስ ይገኝበታል፡፡
የሠርጌ እለት ለትዳር ጠይቄያቸው “እምቢ” ያሉኝ አስራ አንድ ሴቶች ድንገት በአይኔ ላይ ድቅን ቢሉ ቁጣዬ መንደዱ አይቀርም፤ በጣም ነው ያረዘሙብኝ ይሄን ጐዳና፡፡ ንግስት እልፍኝ እስኪደርስ የሚደረደሩ አሳላፊዎች መሆናቸው በገባኝና “እለፍ!” ከማለታቸው በፊት አሳልፉኝ ብዬ በጠየቅኩ፡፡
ብቻ እነርሱ ድንገት ትውስ ካሉኝ ቁጣዬ ሊነድ ስለሚችል ለስለስ ለማድረግ የአንሙቴን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብኛል፡፡ በክብር ከሚጠራው ታዳሚ ፊት ቁጣዬን ለማለስለስ ብዬ ማስቲካ አላኝክም፡፡ ረዘም ያለ የእግር ጉዞ ማድረግ በጭራሽ አይታሰብም፤ ያለኝ አማራጭ ማጨስ ነው፡፡ ምን? ሲጃራ…አላደርገውም! እሺ ሊነድ የሚችለው ቁጣዬን እንዴት ላለስልሰው?
ምን አስጨነቀኝ ከዚህ ሁሉ ሙሽራይቱን ባጨሳትስ!? ቁጣ የእሳት አመድ ስለሆነ ታምቆ ይቆያል፡፡ ጠንካራ ሲሆን ሃይለኛ ችግር ይፈጥራል፡፡ በስራ፣ በፍቅርና በእለተ ተእለት ግንኙነት መሃከል ጣልቃ እየገባ ይበጠብጣል፡፡ በተጨማሪም ቁጣ የእሳት ፍም ስለሆነ አልፎ ወደ ትዳሬ ከዘለለ ጥሩ አይመጣም፡፡ ለትዳር ጠይቄያቸው እንቢ ባሉኝ አስራ አንዱ ሴቶች የተፋፋመው ቁጣዬ፣ ወደ ትዳሬ ተላልፎ ቤቴ ሲነድ ማየት አልሻም፡፡
***
“ዢያኛ…ኩኛ” ቁጣ ምንድነው? ቁጣ ምን ያመጣል?
ቁጣ ውስጣችሁ ሲኖር፤ እንዲሁ ይታወቃችኋል፡፡ ምቾት አይሰማችሁም፤ በሆነ ባልሆነው ትረበሻላችሁ። ደረታችሁ ጥብቅ፣ ልባችሁ ምትት…ምትት፣ ጡንቻዎቻችሁ ውጥርጥር፣ እግሮቻችሁ ድክም፣ ላብና ራስ ምታት ይፈራረቅባችኋል፡፡ ጩሁ ጩሁ፣ እቃ ስበሩ ስበሩ፣ ሰው ተማቱ ተማቱ፣ ተሳደቡ ተሳደቡ፣ አልቅሱ አልቅሱ፣ ተጋፉ ተጋፉ ይላችኋል፡፡ ለራስ በቂ የሆነ ጊዜ አለመስጠት ለቁጣችሁ መንደድ መነሻ ይሆናል፡፡ መዳረሻው ደግሞ ይከብዳል፡፡ ሃይለኛ ቁጣ ሲነድ “ምን ይሻለኛል…ልፈንዳ ይሆን? ልብረር ይሆን?” ያሰኛል፡፡
በተለይ እናትና አባት ሲጣሉ ተወርውሮ ከግድግዳ እየተጋጨ የሚሰባበረውን የቤት እቃ ሲለቃቅም ያደገ ልጅ ቁጣን መቆጣጠር ይከብደዋል፡፡ ንዴት ሁኔታዎችን ሲያባብስ እንጂ የማንንም ችግር ሲፈታ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ “ማሂቲያ” ይሄን መረዳታችሁን ቁጣን ለማለስለስ ያግዛችኋል፡፡
“ምን አይነት ቆሻሻው ነህ?”
“ልታሞኘኝ ትፈልጋለህ እንዴ?”
“ግድ የለሽ!”
“እረፊ!...ልጐዳሽ እችላለሁ”
“ይሄ አካባቢ በጣም አስጠልቶኛል”
ተቃራኒ የሆኑ አስተሳሰቦችን እንድንከተል ጫና ስለሚያሳድሩብን እንዲህ አይነት ንግግሮችን ልናስወግድ ይገባናል፡፡ “የሚወራው መጥፎ ነገር ሁሉ እኔን በማስመልከት ነው” ብለን ልናስብ አይገባም፡፡ አለበለዚያ በተወራው ሁሉ መታመማችን ነው፡፡ ስለ እኛ በጐ በጐውን ከሚናገሩ ሰዎች ልንርቅ አይገባም፡፡
“ሚፊቺሚ” “እኔ ፍፁም ነኝ!” ይሄ አስተሳሰብ ፍፁም ቁጠኛ እንድትሆኑ በአያሌው ይተባበራችኋል፡፡ የሰው ፍፁም የለውም! ወይ ማግኘት አልያም መሞት የሚባል ነገር አይሰራም፡፡ ማግኘት ካላገኙም እንደገና ለማግኘት መኖር፡፡ ለምን ትቸኩላላችሁ? ሞት እንደው ሳትጠሩትም ቢሆን መምጣቱ አይቀርም፡፡
“ዩኒ ሚት” ቁጣን ለማንደድ መንገድ ጠራጊ የሆኑትን ተቃራኒ አስተሳሰቦች እንዴት ማስወገድ እንደምትችሉ ላሳያችሁ…
የሆነ ሰው አፍጥጦ ሲመለከታችሁ “ለምን እንዲህ አፍጥጦ ያየኛል? ይሄኔ በሆዱ ሲያስጠላ እያለኝ ነው” እያላችሁ ከማሰብ “አፍጥጦ እያየኝ ነው፤ነገር ግን ምን እያሰበ እንደሆነ አላውቅም” ማለት ይሻላችኋል፡፡ “ለምንድነው ጣል ጣል የሚያደርጉኝ?” ከማለት “አንድ ቀን ውድድድ…ያደርጉኛል” ብሎ ማሰብ፡፡ “ስለ እኔ ምንም ግድ አይሰጣትም፤ የሆነች ግድ የለሽ!” ከምትይ “በራሷ ጉዳይ በጣም ስለተወጣጠረች ረስታኛለች” ማለቱ አይበጅሽም ወይ?
“እኔ ቁጣ የለብኝም፤ ቁጣዬ የሚነደው ሰዎች ተልካሻ የሆነ ነገር ሲያደርጉ ሳይ ነው” የምትል ከሆነ፡፡ ከውጪ መጥቶ ይስፈርብህም ከውስጥህ ይንደድብህም ንዳድ እንደው ንዳድ፤ ቁጣም እንደው ቁጣ ነው፡፡
“ሺን ሹአ” ቁጣ ሲነድ ከማይሆን ቦታ ይጥላችኋልና ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ፡፡ ቁጣዬ ሲነድ መቆጣጠር ይከብደኛል ከምትሉ ቀድሞ መንገድ ጠራጊ የሆኑትን ጉዳዮች መቀናነስ ይጠቅማል፡፡ ለራሳችሁ በቂ ጊዜ ከመስጠት አትቦዝኑ፡፡ አቅሙ ካላችሁ “ዮጋ” ብትማሩ መልካም ነው፡፡ ካልሆነም ስሜቱ ሲሰማችሁ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ቴሌቪዥን ማየት (ከዜና በስተቀር)፣ ማስቲካ ማኘክ፣ ማሽላ ማፈንዳት (ፈንዲሻ) ወይም የፈነዳውን መብላት፣ ፎቶ መነሳት (እየሳቃችሁ ቢሆን ይመረጣል) እና እየደጋገማችሁ ምስር ክክ! ምስር ክክ! ማለት ወዘተ…፡፡
“ሁጂን ቹኣ?!” ሚስቴ በጩኸት…”ከስራ የምትወጣው ስንት ሰአት ላይ ነው?!” ስትለኝ “ቲሞቻሚሽ” “ቆይ መጣሁ ማሬ” እላትና ከነደደው ቁጣዬ ለመለስለስ ሽንት ቤት ገብቼ ለሁለት ሰአታት ያህል በረዥሙ አየር አስባለሁኝ፡፡ ለስልሼ ስጨርስ ተመልሼ እሄድና “ሁሻቺ” “ለምን እንዲህ ብለሽ ጠየቅሽኝ? እስቲ ቁጭ በይና ባነሳሽው ሃሳብ ዙሪያ እንወያይበት” ብዬ እርሷንም አለሰልሳታለሁኝ፡፡
ቁጠኛ ብሆን ገና ጥያቄውን ከማንሳቷ “ሺን ሲሺ ፒካ ሲኦ!” “ለምን አስፈለገሽ? በመሃከላችን መተማመን ጠፋ ማለት ነው?” እያልኩ አፍ አፏን እላታለሁኝ፡፡ እሷም እየጮኸች መልስ ትሰጠኛለች፤ቤታችን በአንድ እግሩ ቆመ ማለት አይደለም? “ላሼ ላሼ” የራስን ብቻ ማዳመጥ ሳይሆን መደማመጥም ያስፈልጋል፡፡
በፈጠራችሁ “እኔ መቼም ቢሆን ተወዳጅ ሰው ልሆን አልችልም!” አትበሉ፡፡ “ሁዋል ሲኛ” ሰው አንደኛ የሚወድላችሁ ነገር ቢኖር እራሳችሁን መውደዳችሁን ነው! የማትወዱት ማንነታችሁን ማንም አይወድላችሁም!
“ሲሞ ሺሞ ሺኝ” በትውልዳችሁ እርግማን እንዳይመጣ ሌሎችንም መውደድና መንከባከብ ተማሩ፡፡ የጥቁር ህዝቦች እናት ምድር ኢትዮጲስ፤ የበኩር ልጆቿ ሌሎችን ልክ እንደራሳቸው መውደድና መንከባከብ ሊማሩ አልቻሉም፡፡ በእነርሱ ምክንያት አምላክ ተቆጥቶ ረግሟት እስከ አሁን ድረስ ክፉኛ ተጐሳቁላለች፡፡ በቀደመው ዘመን ምድሪቱን ከገነት የሚፈሱ ወንዞች ያጠጧታል፤ከእርሷ ዘንድ የሚወለዱት ሁሉ በክርታዝ ጥቅል ነው፡፡ ከሽሉ ውስጥ የደም ጠብታ አይገኝም፤ ንፁህ ውሃ ብቻ! በአምላክ አብዝታ የተወደደች የሰው ዘር መገኛ፡፡
“ላይሙ ዣቲዬ” ታዲያ እንዲህ ሆነ፡፡ በየሜዳው ታርደው የሚጣሉት እንስሳት ደም ነፍስ ወደ ሰባተኛው ሰማይ አብዝቶ ጮኸ፡፡ በተለይ የአንዲት ላምና የበግ ግልገል ደመ-ነፍስ፡፡ አምላክም…
“ከጠይሟ መሬት ዘንድ እሪታ በረከተ፤ የአንዲት ላምና የበግ ግልገል ከደመ ነፍሳቸው “የበደል ወናፋችን ሞላ፤ ፍረድልን!” የሚል እሪታ ከሁሉም አይሎ ይሰማኛል፡፡ እስቲ ወርደህ የጠይሚቱ ልጆች የሆኑት ሀበሻትና ሙካሪብን ጠርተህልኝ ተመለስ!” አለው ለመልዐኩ፡፡
በመልዐኩ መልእክት አድራሽነት ሀበሻትና ሙካሪብ አብረው እንዲመጡ ቢጠሩም፣ ሙካሪብ አዲስ ለሚሰራው ጐጆ ማጣበቂያ እንዲሆነው በማሰብ የሰጐን እንቁላሎችን እየሰባበረ ስለነበር ሳይሄድ ቀረ፡፡ ሀበሻት ብቻውን መጥቶ ከአምላክ ፊት ቆመ…
“የኢትዮጲስ ልጆች፤ ስለምንድን ነው የላሚቱንና የበግ ግልገሉን ቆዳ ደመ - ነፍሳቸው ሳይወጣ በፊት ከላያቸው የላጣችሁት?” አምላክ ሀበሻትን ጠየቀው፡፡
“ወደ ፑንት ወረድንና ግብር አድርሰን ስናበቃ፣ በቅባት የራሱት መዳፎቻችንን ለማፅጃ የሚሆነን እንስሳ በዙሪያችን አላገኘንም፡፡ እናም ከሙካሪብ ተማክረን ከአምባው ላይ ሳር ስትግጥ ያገኘናትን ላም ቆዳዋን ላጥንላት፡፡ ከማረዳችን ቀድመን ቆዳዋን ስናነሳባት፤ ስታጠባው የነበረ እንቦሳዋ ሲጮህ በአንድ ጥፊ ፀጥ አሰኘሁት፡፡ እሜዳው ላይ ተንፈራፈረ፤ ድፍት ሳይል አልቀረም፡፡ እርሱን እርሳው፡፡ አሀሀሀሀ! ይገርምል አምላክ፤ ላሚቱን ልጠን ስናበቃ ግልጥ አላለልን መሰለህ። ለካንስ የላሚቱ ቆዳ ልስላሴው መዳፍ ለመጥረግ አይበጅም ኖሯል፤ አሀሀሀ…” እያስካካ መለሰለት፡፡
ሀበሻት ቀጠለ….”ለጥቆ ካለው ቀዬ እልፍ እንዳልን ማለፊያ ጠጉር ያለውን ግልገል በግ ስናገኝ ቆዳውን ገፈፍንለትና መዳፎቻችንን አፀዳን፡፡ ጨዋታ ይዞን ስለነበር ከነ ነፍሱ፤ በህይወት እያለ ቆዳውን መግፈፋችን ትዝም አላለን፡፡ በኋላ ላይ እንደ ላሚቱና እንደ እንቦሳዋ እርሱም ተደፋ” አለው፡፡
አምላክ “ስለምን ቆዳቸውን መላጥ አስፈለገ? እንደ ከዚህ ቀደሙ እጆቻችሁን እንስሶቹ በህይወት ሳሉ በላያቸው አትጠርጉም ነበር ወይ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሀበሻት “ኤዲያ፤ ኖሩ አልኖሩ ምን አባታቸው ይሰራሉ?! ሲል መለሰለት፡፡
“ሺን ሲሺ ፒካ ሲሜ ቱዪ ሾማ ኦኦ!!! ኦ!!! ኦ!! ኦ!...”
በሙካሪብና ሃበሻት ግድ የለሽነት የአምላክ ቁጣው ነደደ…
“ሳይሞቱ፤ በህይወት እያሉ ቆዳቸው ይላጥ፡፡ ሁለቱም ከጉልበታቸው የሚወጣ፤ ዘራቸው በሙላ ቆዳ ቢስ ይሁን!” ሲልም ተራገመ፡፡
ከዛን ጊዜ ጀምሮ አትችሉም፡፡ ምንም እንኳን ከገነት እየወጡ ምድሪቱን የሚያረሰርሱት ወንዞች እስከ አሁን ቢኖሯችሁም፤ የምትዋለዱት የመንፈሳችሁ ቆዳ እንደተላጠ ነውና ስትነካኩ ክፉኛ ያማችኋል፡፡ ለቻይና ሊትረፈረፍ የሚችል የተፈጥሮ ገፀ በረከት ለእናንተ ግን አልበቃችሁም! እስቲ ተዋደዱ? አትችሉም፡፡ ከተዋደዳችሁ መተቃቀፍ አይቀርም፤ መተቃቀፍ ደግሞ የመንፈሳችሁ ቆዳ ስለተነሳ ለእናንተ በሽታ ነው፤ ደዌ፡፡ ስትነካኩ ክፉኛ ያማችኋል!
“ሙኣ ሙኣ!...ሙኣ” “ሲካ ማቼ??...ሲካ…ማቼ??”
እንዴ…ለምን? ለምን?...ለምን አትሉም? አይበቃም! አይበቃም! አይበቃችሁም ወይ? ይህ ብሶት የሚወልደው የአፍሪካውያን ጩኸት መቼ ነው የሚሰማው? በዚህች ምድር ላይ የወንድማማቾች ጥላቻ እስከ መቼ እድሜውን እያራዘመ ይኖራል?
እረኡኡኡኡ…ኡኡኡኡ “እባክህን እባክህን ስለ ፍቅር እረደን??? እረረ!! ደ!!ደ!! ንንን!!” “እረደን” በሉት። “ማኦቲኛ” …ምህረቱን አውርዶላችሁ አሳርዱትና፤ ሳትላጡ ከነመንፈሳችሁ ቆዳ ለመተቃቀፍ ምቹ እየሆናችሁ…ደጋግማችሁ ተወለዱ፤ ዳግም በፍቅር መንፈስ ተወለዱ እንጂ?!
*   *   *
ቁጣ ማለስለስ ከተባለው ትምህርት ላይ ቀንጨብ አድርጐ ይሄን ገራሚ ታሪክ ያወጋኝ አንሙቴ ሲሆን፣ ያስተማራቸው ደግሞ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ የከፍተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ቻይናዊ ነው፡፡
ኤዲያ፤ ቻይና ተናገረ አልተናገረ ምን አባቱ ይሰራልኛል?!
ሲጀመር የቻይናዊና የኢትዮጵያዊ ቁጣ መሃል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የቻይኖቹ ቁጣ ቀሰስተኛ፤ የሚነደውም ቀስ በቀስ ነው፡፡ ድህነታቸው ላይ ቁጣቸው ነዶ ሰላሳ አመት ሙሉ ሲጐተት ከርሞ ነው ትቷቸው የሄደው፡፡ የእነርሱን አይነት ቁጣ ኑሮዬን እቆጣዋለሁ፡፡
እንደነርሱ ቁጣው ድህነት ላይ አልነደደም እንጂ ኢትዮጵያዊ ድህነቱን ቢቆጣ በአምስት አመት ችግር ድራሹ ይጠፋ ነበር፡፡ አመሉ መሬት ነው! ኮሶ ኮሶ እስከሚለው ድረስ እጅግ ካላስመረሩት፤ የአበሻ ቁጣው አይነድም፡፡
ይቅርበት ኮሶ እንዳታቀምሰው! ኢትዮጵያዊን ነካክተህ መሬት የሆነ ሸጋ አመሉን ካስጣልከው፤ እምር ብሎ ይነሳብሃል! እምር ብሎ ከተነሳ በኋላ ምኑን ልንገርህ? ከቁጣው ንዳድ ብዛት…ከቁጣው ንዳድ ብዛት፤ አህያ ብትሆን እንኳን ክንፍ አውጥተህ ትበራለህ!
ጣልያንን ያበረርነው በቁጣችን፣ ከሰው ሀገር ገብተን የኮሪያን “ኮሚውኒስት” ያበረርነው በቁጣችን፤ መንግስቱ ሃይለማርያምን ያበረርነው በቁጣችን፣ ኤርትራንም ያበረርናት በቁጣችን፡፡ የኢትዮጵያዊ ቁጣው የነደደ እለት ፈጣሪ በኮባ ቅጠል ሸብልሎ ይሰውረኝ፡፡
አወይ እዳ፤ እንግዲህ የሠርጌ እለት ቁጣዬ የሚነድ ከሆነ ሠርገኛውን ከነድንኳኑ ማብረሬ ነው፡፡ እሺ ቁጣዬ በምን ይለስልስ? “ሙሽራይቱን በጥፊ ማጨስ” የሚለው ሃሳብ አልተዋጠልኝም፤ በስንት ዳዴ አግኝቻትማ አላጨሳትም፡፡
እምምም…ወ-ተ-ት …አሹ…ወተት!
ከሙሽሪትና ከእኔ ፊት የሚደረደረው ጠላና ጠጅ አጠገብ በብርሌ ተደርጐ ወተት ቢቀመጥልኝስ? ወተት እንኳንስ ቁጣ መርዝ ያረክስ የለ፡፡ የምን ቁጣ ማለስለስ፤ ስለ ቁጣ ማለስለስ በተማረው መሰረት አንሙቴ የራሱን ቁጣ ማለስለስ ይችላል፡፡ እኔ ግን የሠርጌ እለት ልክ እንደ አያት ቅድመ አያቶቼ፤ ከወተቱ እየተጐነጨሁ ቁጣዬን አረክሰዋለሁ!
ምርጥ ሃሳብ…አሹ ዳይሊጋዳ!
(“ክብሪት” ከተሰኘው የይግረም አሸናፊ
የልብወለድና ወጎች
ስብስብ መጽሐፍ የተወሰደ ከገጽ 40-47 - 2007)


- በየሄድኩበት ሁሉ ጥቁር ካልሲ ይጥሉብኝ ነበር
- “መድሃኒት እየሰረቀ ይሸጣል” ብለው አስወርተውብኛል

አዲስ አበባ ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ የዕድሜያቸውን ግማሽ ያሳለፉት በውጭ አገራት ነው፡፡ በማህበረሰብ ጤና የማስተርስ ዲግሪ
ይዘው ለንደን በሚገኝ አንድ ትልቅ ሆስፒታል ውስጥ በሲኒየር ነርስነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ አቶ ሄኖክ አያሌው ላለፉት
አራት ዓመታት “በወሮበሎች ስውር ደባ” (Gung stocking) ሲሰቃዩ እንደቆዩና በተለያዩ የራሳቸው ጥረቶች ከችግሩ ነፃ መውጣታቸውን
ይገልፃሉ፡፡ የወሮበሎች ደባ፤ አንድ ግለሰብ በወሮበሎቹ ስሙ ከጠቆረና “ብላክ ሊስት” ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ውድመት እንዲያመራ
የሚያደርግ ስርዓት ነው ይላሉ አቶ ሄኖክ፡፡
በወሮበሎቹ ወጥመድ ውስጥ የገባሁት በእንግሊዝ አገር ሳለሁ በተዋወቅኋት ዮዲት ጉዲት የተባለች ሴት ሰበብ ነው የሚሉት የታሪኩ
ባለቤት፤ ከእሷ ጋር ባለመግባባት ከተለያዩ በኋላ በወሮበሎቹ ጥቃት መከራቸውን ማየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ “የወንበዴዎቹ ዓላማ
ያጠመዱትን ሰው ስም በማጥፋትና በማጠልሸት በብቸኝነት፣ በጭንቀትና በፍርሃት ማሸበር ነው ይላሉ አቶ ሄኖክ፡፡ በተከበርኩበት
ትልቅ ሆስፒታል ውስጥ “መድኃኒት እየሰረቀ ይሸጣል” ብለው አስወርተውብኛል ያሉት የታሪኩ ባለቤት፤ በየሄድኩበት ሁሉ ጥቁር ካልሲ
ይጥሉብኝ ነበር… በማለት የደረሰባቸውን ያስረዳሉ፡፡ ባለፈው አራት ዓመት የደረሰባቸውን ስቃይም፣ “የዲያስፖራው ስውር ደባ” በተሰኘ
መፅሃፋቸው ተርከውታል፡፡ መፅሀፉ “The Jaws of Evil” በሚልም ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ባለፈው ሳምንት ከአማርኛው ጋር
ተመርቋል፡፡ የ49 ዓመቱ ጐልማሳ አቶ ሄኖክ አያሌው “የወሮበሎች ስውር ደባ” በሚሉት ጉዳይ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት
ዮሴፍ ጋር ተከታዩን ሰፊ ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡


ከአገር የወጡት መቼና እንዴት ነው?
እኔ ከአገር የወጣሁት በደርግ ስርዓት ማብቂያ አካባቢ ነው፤ በፈረንጆቹ 1990 መጀመሪያ ላይ ማለት ነው፡፡ ወደ 25 ዓመት ገደማ አልፎኛል፡፡ የወጣሁበት ዋናው ምክንያትም በወቅቱ በነበረው ብሔራዊ ውትድርና ለመሄድ ባለመፈለጌ ነው፡፡ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ በቀጥታ ወደ ፖላንድ ሄድኩኝ፣ እዛ አንድ ሳምንት ከቆየሁ በኋላ ወደ ስዊድን አመራሁ፡፡ ለ11 ዓመታት በስዊድን ከቆየሁ በኋላ ሌላ አንድ አመት በተለያዩ አገራት ማለትም ጀርመን አሜሪካና ሌሎች አገራት ተዘዋውሬ ካየሁ በኋላ እንግሊዝ ገባሁ፡፡ ይኸው አሁን በለንደን መኖር ከጀመርኩኝ 14ኛ ዓመቴን እያገባደድኩኝ ነው፡፡
በለንደን ምን እየሰሩ ይኖራሉ? ምንድን ነው ያጠኑት?
ስዊድን የቆየሁት በትምህርትም በስራም ነው፡፡ እንግሊዝም እንደዛው፡፡ በማህበረሰብ ጤና የማስተርስ ዲግሪ አለኝ፡፡ ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የ“Intensive care unit” (የፅኑ ህሙማን ክፍል እንደማለት) ሲኒየር ስፔሻሊስት ነርስ ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
እስቲ የወሮበሎች ስውር ደባ (Gung stocking) ምን ማለት እንደሆነ ያብራሩልኝ?
ጋንግ ስቶኪንግ (የወሮበሎች ደባ) ማለት በጉዳዩ ዙሪያ በታተሙ የተለያዩ መጽሐፍት ላይ እንደተገለፀውና እኔም በህይወቴ ደርሶ እንደተረዳሁት፣ አንድ ግለሰብ በወሮበሎቹ ስሙ ከጠቆረና “ብላክ ሊስት” ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ውድመት እንዲያመራ የሚያደርግ ስርዓት ነው፡፡
“የዲያስፖራው ስውር ደባ” በተሰኘው መፅሀፍዎ ላይ እንዳነበብኩት፤ ወሮበሎች የተባሉት አካላት ያጠመዱት ሰው ባለበት ሁሉ ይገኛሉ፡፡ ግለሰቡ አገር ቢቀይርም ይከተሉታል፡፡ ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? የወሮበሎቹ ሥራ ሳይንሳዊ ነው ወይስ ምትሃታዊ?
ጋንግ ስቶኪንግ ከሌሎቹ ደባዎች ወይም የማጥቂያ ስልቶች ለየት የሚለይበት የራሱ ባህሪ አለው፡፡ አንደኛ ህጋዊ ያልሆኑ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በሌላ በኩል እነሱ ብቻ አጥቅተው አይተውሽም፡፡ የራስሽ ወዳጅ ዘመዶች፣ የስራ ባልደረቦችሽ፣ ቤተሰብሽ… ብቻ ሁሉም ያንቺ የሆነ ሁሉ በአንቺ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ያደርጉሻል። ይህን የሚያደርጉት በአንቺ ላይ ያልሆነ ወሬ ፈጥረው በማስወራት ነው፡፡ ከዚያ ሁሉም አንቺን ይጠረጥርሻል። በአይነቁራኛ ይመለከትሻል፡፡ ብቻ የሆነ ፍርሃት፣ ብቸኝነት፣ ጭንቀት… ዙሪያሽን እንዲከብሽ ያደርጉሻል። ይህን ሲያደርጉ ምንም አይነት ማስረጃ ላለማስቀረት ይጥራሉ፡፡ ከዚያ ካለፈ በጣም ትንሽ ማስረጃ ብቻ ይተዋሉ፡፡ ይህን ሴራቸውን ፖሊስ ጣቢያ ሄደሽ ክስ ብትመሰርቺ፣ መጽሐፍ ልፃፍና ሌላውን ላስተምር ብትይ በመረጃና በማስረጃ ማስደገፍ ስለማትችይ ዝም ብለሽ ከመሰቃየት ውጭ የምታመጭው ነገር የለም፡፡
ሳይንሳዊ ነው ወይስ ምትሀታዊ ላልሺው፤ ወሮበሎቹ ለደባቸው የሚጠቀሙት የስነ - ልቦና መጽሐፍትን ነው። ምንም ምትሀት የላቸውም፤ በአማርኛው መጽሐፌ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ እነሱ ሰው ምን ቢደረግ ጭንቀትና ፍርሀት ሊገጥመው እንደሚችል ትልልቅ የስነ ልቦናና የህክምና ተመራማሪዎች የፃፏቸውን መጽሐፍት በማንበብ ነው ሽብራቸውን የሚፈጥሩት፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ በተለይ ኢትዮጵያዊያን የሚያዳምጣቸው ስለሌለ የባሰ ችግር ውስጥ እየገቡ ነው፡፡
ጉዳዩ ቅድም እንዳልሽው ልክፍት፣ ምትሀት ወይም ድግምት ስለሚመስል በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ይህንን ችግር ሲናገሩ ተለክፏል፣ ተደግሞበታል፣ ቡዳ በልቶታል… እየተባሉ ፀበል ይወሰዳሉ፤ ከዚያ ሲያልፍም ጠንቋይ ቤት ይወስዷቸዋል፡፡ “ኧረ አላበድንም ጤነኛ ነን” ሲሉ “ይኼው ያስለፈልፈዋል” እየተባሉ ብዙ ችግር ይደርስባቸዋል፡፡ ይሄ በችግር ላይ ችግር፣ በስቃይ ላይ ስቃይ ነው የሚሆንባቸው፡፡ በአገራችን አንድን ነገር ደጋግሞ ሰው ደጃፍ ላይ መጣል ለምሳሌ ዶሮ እያረዱ በተደጋጋሚ ሰው በር ላይ መጣል፣ ወፍ እያረዱ ሰው ሳሎን ውስጥ በተደጋጋሚ መጣል ድግምት ነው እየተባለ እንደሚያብዱት አይነት ነው፤ ግን ይሄ ከዚያ ይለያል፡፡
ልዩነቱ ምንድን ነው?
እኔ በህይወቴ ደርሶ እንዳየሁት፤ ያ ታርዶ በተደጋጋሚ የሚጣለው ዶሮ ወይም ወፍ አይደለም ሰዎቹን የሚያሳብዳቸው፤ ድግግሞሹ ብቻ ነው፡፡ ዶሮው ወይም ወፉማ በቃ የሞተ ነው፡፡ የሚጣሉት ነገሮች ባይደጋገሙና አንዳንድ ጊዜ ብቻ ቢሆን ኖሮ አያሳብዱም ነበር፡፡ ወሮበሎቹም አንድ ሰው ራሱን እንዲያጠፋ፣ እንዲያብድ፣ እንዲወድም ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ባጠመዱት ሰው ላይ ፍርሃትና ሽብር ለመልቀቅ አንድን ነገር በተደጋጋሚ ማድረጋቸው ነው፡፡
በመጽሐፉ ላይ እንደጠቆሙት፤ እርስዎን የሚያሸብሩት በጥቁር ካልሲ ነበር?
አዎ ነገሩ እስኪገባኝና እስክነቃባቸው ድረስ በመኝታ ቤቴ፣ በመታጠቢያ ክፍሌ፣ በቢሮዬ መሳቢያና በምቀይረው ጫማ ውስጥ እንዲሁም መኪናዬ ላይ ጥቁር ካልሲ ይጥሉ ነበር፡፡ ይሄ በጣም ያስፈራል ይዘገንናል። የምትይዢ የምትጨብጪው ይጠፋሻል፡፡ ልትዝናኚ ሌላ ቦታ ብትሄጂም እዛ ቦታ ቀድሞ ጥቁር ካልሲ ይጠብቅሻል።
በሌላ በኩል ለረጅም ጊዜ ፓስወርዴ ጠፍቶኝ ስባዝን ነበር፤ በኋላ ስልኬ በእነርሱ እንደተጠለፈ አወቅሁኝ፡፡ ኢንተርኔት የምትጠቀሚ ከሆነ ፓስወርድሽን ሰብረው በመግባት ከአንቺ ጓደኞች ጋር እንደ አንቺ ሆነው ኢ ሜይል ይደራረጋሉ፤ ምስጢርሽን ይወስዳሉ፤ ፌስ ቡክ ላይ ገብተው ካንቺ ጓደኞች ጋር ያወራሉ፡፡ ብቻ የሚሳናቸው ነገር የለም፡፡ እኔ እስኪ አገር ልቀይር ብዬ ጀርመን ስሄድ የማርፍበት ቦታ ቀድሞ ጥቁር ካልሲ ተጥሎ ነበር፡፡ ስዊድንም ስሄድ የማርፍበት የጓደኛዬ ቤት በር ላይ ይሄው ካልሲ ተጥሎ ጠበቀን። ይሄ ላልነቃበት ሰው ከድግምትስ በላይ አይሆንም እንዴ?
ወሮበሎቹ የሚያጠምዱት ማንን ነው? ምክንያታቸውስ ምንድን ነው?
በማንኛውም ሁኔታ፣ በየትኛውም ጊዜ፣ የትኛውም ሰው ወጥመድ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ ከምክንያቶቹ አንዱና ዋናው ከወሮበሎቹ ከራሳቸው ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር የተጣላ ካለ ይጠመዳል፡፡ በፆታዊ ግንኙነት ሴቷ በቃኝ ብላ ወንዱ መቀጠል ከፈለገም ያስጠቁራታል፡፡
ለእርስዎ ወጥመድ ውስጥ መግባት ምክንያት የሆነችውና በመጽሐፉ ውስጥ ዮዲት ጉዲት በሚል ከተገለፀችው ሴት ጋር እንዴት ተገናኙ? እንዴትስ ለወጥመዱ ምክንያት ሆነች?  
እኔና ዮዲት ጉዲት በሶስተኛ ሰው ነው የተገናኘነው። እኔም እሷም በማናውቃት ሴት አማካኝነት ተገናኘን። እኔ በወቅቱ ትዳር ለመመስረትና ቤተሰብ ለማበጀት እፈልግ ስለነበር ዮዲትም ባል ትፈልጋለች ተብሎ ነው የመጣችው፡፡ ነገር ግን እሷ ትዳር ሳይሆን የመኖሪያ ፈቃድ ነበር የምትፈልገው፡፡ እሷ መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራት በህገ ወጥ መንገድ ለንደን ውስጥ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ከተቀራረብን በኋላ ብዙ ነገሮች ምቾት አልሰጡኝም። በአጠቃላይ እኔ የምፈልገው አይነት ስብዕና ያላት ሴት ባለመሆኗ ግንኙነቱን ለማቋረጥ ተገደድኩኝ፡፡ እሷ አለመፈለጓ ስላሳመማት ልትበቀለኝ ፈለገችና አስጠቆረችኝ፡፡
ለካስ የወሮበሉቹ አባል ነበረች፡፡ ይህን እርምጃ ከመውሰዷ በፊት “አንተ ካልወደድከኝና ልታገባኝ ካልፈለግህ ቢያንስ መኖሪያ ፈቃድ እንዳገኝ ፈርምልኝ” የሚል ጥያቄ ሁሉ አቅርባልኝ ነበር፡፡ እኔ እንዲህ አይነት ህገ -ወጥ ስራ ባለመፈለጌ እዚህ ችግር ውስጥ ገባሁ። ከዚያ በኋላ ያየሁትን መከራና ስቃይ መጽሐፉ ላይ አንብበሽዋል፡፡ በጣም ተከብሬ በምሰራበት ሆስፒታል ውስጥ “ሄኖክ መድሀኒት እየሰረቀ ይሸጣል”  ብለው አውርተውብኝ ስሸማቀቅ ኖሬአለሁ፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ ንፅህናሽን ለማስረዳት ብትሞክሪ ሰሚ የለሽም፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ ስቃይ ደርሶብኛል፡፡
ለዮዲት ጉዲት ብፈርምላት ወይም ባገባት ኖሮ ከዚህ ወጥመድ ነፃ እሆን ነበር ብለው ያስባሉ?
በፍፁም! የባሰ አዘቅት ውስጥ፣ የባሰ ችግር ውስጥ እገባ ነበር፣ በህይወት መቆየቴንም እጠራጠራለሁ። በጣም አደገኛ ሰው ስለመሆኗ በተዋወቅንባቸውና ስለሷ ለማወቅ በሞከርኩባቸው ጥቂት ጊዜያት ለመረዳት ችያለሁ፡፡
በመስሪያ ቤት መድሃኒት ይሰርቃል በሚል ከተወነጀሉ በኋላ ነፃነትዎን ለማወጅ “Lie detective” በተባለ መሳሪያ 17 ሺህ ብር ከፍለው በመመርመር፣ እውነቱ ተረጋግጦ በሚሰሩበት ሆስፒታል ተቀባይነትን እንዳገኙ በመፅሀፉ ገልፀዋል፡፡ ሌሎች የችግሩ ሰለባዎች ታዲያ ለምን ይህን ዘዴ አይጠቀሙም?
ትክክል ነው፤ ቴክኖሎጂው መጥፎም በጐም ጐኖች አሉት፡፡ ለመጥፎ ከተጠቀምሽው መጥፎ ይሆናል፤ ለመልካም ከተጠቀምሽው እንደዚሁ። እኔም አለመታመኑ ሲበዛብኝ፣ የሚሰማኝም ሳጣ ነው ወደ መሳሪያ ምርመራው የሄድኩት፡፡ በዛ ነው ነፃ የወጣሁት። እኔ ነርስ እንደመሆኔ የስራና የውጭ ካልሲዬ የተለያየ ነው፡፡ ሆስፒታል ስገባ ከውጭ አድርጌ የገባሁትን ጫማና ካልሲ አውጥቼ፣ የሆስፒታሉን ሳደርግ ያወለቅሁት ውስጥ ጥቁር ካልሲ ይጨምራሉ። ይሄንን ሳመለክት አይሰሙኝም፡፡ ተከብሬ በኖርኩበት ሆስፒታል ውስጥ የመድሃኒት ሌባ ተብዬ ሁሉም ሲጠቋቆሙብኝ፣ በቃ ወደ ዲቴክቲቭ ምርመራ ሄድኩኝ። ውጤቱ “ነፃ ነው” አለ። ይህንን ለሆስፒታሉ የበላይ አካል አቀረብኩ። በጣም ጉድ  ተባለ፡፡
ከዚያ በኋላ ሆስፒታሉ ለእኔ ጥበቃና ክትትል ማድረግ ጀመረ፡፡ ከዚያም አልፎ በስራ ቦታዬ፣ በምቀመጥበት ወንበር አካባቢ “ሲሲ ቲቢ” የተባለ ሳያቋርጥ በተከታታይ የሚቀርፅ ቪዲዮ ካሜራ ተገጠመ። በዚህ ካሜራ በተገኘ ውጤት አራት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ደባ ሲሰሩ ተገኝተው ከስራ ሲባረሩ፣ በከባድ ማስጠንቀቂያም የታለፉ አሉ፡፡ እጃቸው ረጅም ነው ወሮበሎቹ፡፡
ሌሎቹ ለምን ይህን መሳሪያ አይጠቀሙም ለተባለው አንደኛውና ዋናው ምክንያት የችግሩን መንስኤ አለማወቃቸው ነው፡፡ እንዳልኩሽ ችግሩ ሲደጋገምባቸው እየተሸበሩ እየፈሩ ብቸኛ እየሆኑ ስለሚሄዱ ከሰው ጋር ለመመካከርና መፍትሔ ለማግኘት እድል አያገኙም፡፡
ቀደም ሲል  ወሮበሎቹ ደባውን ሲሰሩ ከቻሉ ምንም አይነት መረጃ ላለማስቀረት ካልሆነም ትንሽ መረጃ ብቻ ይተዋሉ፤ ይህ ደግሞ ተበዳዮች ፍትህ እንዳያገኙ ያደርጋል ብለውኛል፡፡ እርስዎ መጽሐፍ ለመፃፍ የሚያስችል መረጃ እንዴት ማሰባሰብ ቻሉ?
እኔ ነገሮች ሲደረጉ ቪዲዮ እንድቀርፅ፣ የሰው ማስረጃ እንዳሰባስብ፣ ፎቶ እንዳነሳና ሌሎች መረጃዎችን እንዳሰባስብ፣ መጽሐፍ ጽፌም ሌሎች እንዲማሩበት ለማድረግ የቻልኩት ችግሩ ምን እንደሆነ ቀድሜ በማወቄ ነው፡፡ በወሮበሎች ወጥመድ ውስጥ መውደቄን ስላወቅሁኝ ነው፡፡ ሌሎቹማ ስለማያውቁት ፖሊስ ጣቢያ ሄደው “እንዲህ እያደረጉኝ ነው፤ እንዲህ እየሆንኩኝ ነው” ብለው ሲያመለክቱ “መረጃ አምጡ” ይባላሉ። ይህን ማድረግ አይችሉም፤ እንደውም እንደ አዕምሮ በሽተኛ ነው የሚታዩት፡፡ የወሮበሎቹም ዓላማ ይሄው ነው፤ ተዓሚነትን ማሳጣት፡፡ የመጽሐፉ ዋና አላማም የችግሩ ተጠቂዎች መንስኤውን አውቀው ከችግሩ እንዲወጡ፤ ችግሩ ያልደረሰባቸውም አጠቃላይ የችግሩን ምንነት አውቀው፣ ችግሩ ሲመጣ እንዲከላከሉ ክትባት እንዲሆናቸው ነው፡፡
በመኖሪያ ቤትዎ፣ በሚሄዱባቸው ሆቴሎች፣ በመስሪያ ቤትዎና በሌሎችም ቦታዎች በርካታ ጥቁር ካልሲዎች ተጥለውበታል፡፡ በመጨረሻ ካልሲዎቹን አጥበው መጠቀም እንደጀመሩ ነው በመጽሐፉ የገለፁት። እንዴት ደፈሩ?
እንዳልኩሽ መጀመሪያ ጥቁር ካልሲ ሲጥሉብኝ እበረግግ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ለመድኩት፤ ስለዚህ በጣም በሙቅ ውሃና በኬሚካል አጥቤ መጠቀም ጀመርኩኝ፤ እንደውም አድርጌው ቢያዩኝ እላለሁ። ካልሲው ምንም የለውም፤ በቃ ካልሲ ነው፤ ስለዚህ እኔም ላበሳጫቸው ብዬ ነው የማደርገው፡፡ በቃ ምንም አልሆንኩም፡፡
“የዲያስፖራው ስውር ደባ” የተሰኘው መጽሐፍዎና “The Jaws of Evil” በሚል ወደ እንግሊዝኛ የተመለሰው መፅሃፍ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሆቴል ተመርቀዋል። የመፃህፍቱ መተርጎምና መመረቅ ፋይዳው ምንድን ነው?
“የዲያስፖራው ስውር ደባ” የተፃፈው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ ዓላማውንም ቀደም ብዬ ነግሬሻለሁ። አሁንም ብዙ ኢትዮጵያኖች በችግሩ እየተሰቃዩ ነው። መጽሐፉን ያስመረቅኩት ይበልጥ ችግሩ ትኩረት እንዲያገኝ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የችግሩ ተጠቂዎች ቀን አለ፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር በርሊን ጀርመን ውስጥ ተከብሯል፡፡ እኛ አገር እንኳን ቀኑ ሊከበር ችግሩ በቅጡ የታወቀ አይመስለኝም። በእኔ መጽሐፍ ላይ እንዳየሽው ጥቂቶች በተወሰነ ደረጃ ችግሩን አውቀውት የደረሰባቸውን ምስክርነት አንብበሻል፡፡ በመጽሐፍ ምረቃው ላይም የደረሰባቸውን  ስቃይ ሲናገሩ ሰምተሻል። እኔም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት ለበጐ አድራጐት ስራ መጥቼ አላስቆም አላስቀምጥ ሲሉኝ፣ ፖሊስ ጣቢያ ብሄድ እንደ እብድ ነው ያዩኝ እንጂ የሰማኝ የለም፡፡ ስለዚህ በመጽሐፉ ምረቃ እለት የተገኙ ሚዲያዎች የችግሩን ስፋት ለሰው እንዲያስገነዝቡ፤ ሰዎችም መጽሐፉን አግኝተው እንዲያነቡ ለማድረግ ነው፡፡ ወሮበሎች መጽሐፉ እንዳይመረቅ ሁለት ጊዜ አዳራሽ ተከራይቼ አስከልክለውኛል፡፡ ስለዚህ ህዝብም መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡
መጽሐፉን የሚችል ገዝቶ፣ የማይችል በማንኛውም መልኩ እኔን ቢያገኘኝ በነፃ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ እስካሁን ወደ 600 መጽሐፍት በነፃ ሰጥቻለሁ፡፡ በችግሩ ውስጥ ያለ ሰው ካለም ቀርቦ ቢያማክረኝ ከተሞክሮዬና ከልምዴ በማካፈል፣ ከችግሩ እንዲወጣ ለማገዝ ፈቃደኛ ነኝ፡፡
በመጽሐፉ ላይ ስሞት ኩላሊቴ፣ ልቤ፣ ሌላውም የሰውነት ክፍሌ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ይሰጥልኝ፤ የቀረው አካሌ ለምርምር ይዋል ብለው ቃል ገብተዋል። በህይወት እያሉም በየጊዜው ደም እንደሚለግሱ ገልፀዋል። ደግነትዎ በጣም አልበዛም?
 (በጣም እየሳቁ) ደግነት በጣም በዛ አይባልም፡፡ ደግ ከሆኑ በጣም ደግ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ለነገሩ ይሄን ሁሉ የገለፅኩት እንዲህ “ህጋዊና ሰላማዊ ሰው ሆኜ ነው ይሄ ሁሉ የደረሰብኝ” ለማለት እንጂ ይህን አደረግሁ ብዬ ጉራ ለመንዛት አይደለም፡፡
ሌላው በወሮበሎች የሚጠመደው ግለሰብ እንደኔው ዓይነት ሰላማዊ ሰው ነው፤ የሚለውን ለማስረዳት ፈልጌ ነው፡፡ በመጽሐፌ ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች በፊት የወሮበሎቹ አባል ሆነው ሲያጠምዱ የነበሩ አሁን ራሳቸው የተጠመዱ አጋጥመውኛል፡፡ ስለ ልብና ኩላሊቴ ቃል የገባሁት ስዊድን በስደት እንደገባሁና መንጃ ፈቃድ ላወጣ ስል ነው፡፡ እዚያ አገር መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ስትሄጂ፤ ስትሞቺ ኩላሊት፣ ልብ፣ አይን መስጠት ትፈልጊ እንደሆነ ፎርም ይቀርብልሻል፤ እኔም ያኔ ነው ቃል የገባሁት፡፡ ወደ ለንደን ስመጣም በዚያው አቋሜ ነው የፀናሁት፡፡ ደምም በቁሜ ሆኜ ለመለገስና የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ ቃል በገባሁት መሰረት እየለገስኩ እገኛለሁ፡፡
በመጨረሻ የሚናገሩት ካለ …
ከሁሉ በፊት ፈተናዬን ተጋፍጦ ጦርነቴን ያሸነፈልኝን የሄኖክን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ በስራዬ ከጐኔ የነበሩትን ሁሉንም አመሰግናለሁ፡፡ በመጨረሻም ወሮበሎች የያዙት ሥራ፤ አርጅተው ሲደክሙ ስንቅ የማይሆናቸው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ከህሊናችሁ ታረቁ እላለሁ፡፡ የተጠቂ ቤተሰቦችም ልጆቻችሁ፣ እህትና ወንድሞቻችሁ የሚሏችሁን ስሟቸው፡፡ አዳምጧቸው፤ አዋቂ ቤት፤ ጠንቋይና ባለዛር ቤት እየወሰዳችሁ ችግር አትደርቡባቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ለችግሩ ትኩረት ይስጥ እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡      

Saturday, 19 December 2015 10:28

የጸሐፍት ጥግ

ስለ ሽልማት)

ሽልማት ለእኔ ምንም ማለት አይደለም፡፡
የእኔ ሽልማት ሥራዬ ነው፡፡
ካታሪን ሄፕበርን
- የምፈልገው የኖቤል ሽልማት ነው፤ 400ሺ
ዶላር የሚገመት ነው፡፡
ክላዩስ ኪንስኪ
- የኖቤል ሽልማት በሚከፍታቸው በሮች
ብዛት በእጅጉ ትገረማላችሁ፡፡
ኢሊ ዊስል
- ሽልማቶች ለማሸነፍ ብዬ አይደለም
ፊልሞችን የምሰራው፡፡ ፊልሞችን የምሰራው
ፊልሞችን ለመስራት ብዬ ነው፡፡
ኖርማን ጄዊሰን
- በእርግጥም በዓለም ላይ ታላቅ ከሚባሉት
የሥነ-ፅሁፍ ሽልማቶች አንዱ የሆነውን
“Booker” በማሸነፌ በእጅጉ ክብር
ይሰማኛል፡፡
ሪቻርድ ፍላናጋን
- ብዙ ሽልማቶችን አግኝቻለሁ፤ ነገር ግን
ይሄ የመፃፍ ሂደቱን በማቅለልም ሆነ
በማክበድ ረገድ ምንም ልዩነት የሚያመጣ
አይመስለኝም፡፡
ሩት ሬንዴል
- ለማናቸውም ዓይነት ሽልማቶች ዋጋ
አልሰጥም፡፡
ዴቪድ ሆክኔይ
- ከሁለቱ የህይወት ዋነኛ ሽልማቶች፡- ውበትና
እውነት፤ የመጀመሪያውን በአፍቃሪ ልብ
ውስጥ ሁለተኛውን በሰራተኛ እጅ ውስጥ
አግኝቼዋለሁ፡፡
ካሊል ጂብራን
- ዓለም ጀግና ልብና የተሳለ ጎራዴ ላላቸው
ወገኖች አንፀባራቂ ሽልማቶችን ማበርከቷን
ትቀጥላለች፡፡
ኤፍ.ኢ. ስሚዝ
- የትምህርት ቤት ውስጥ ሽልማቶችን
አልወድም ነበር፡፡ ፈተናዎችንም እንደዚያው፡
፡ ከ ዚያም የ መጀመሪያ ድ ግሪና ሁ ለተኛ
ድግሪን ጠላሁ፡፡ እኒያን የጠላሁበት ምክንያት
መፈተንን፣ መ ውደቅን ወይም በ ማንም
በሀሰት መወደስን ስለማልወድ ነው፡፡
ቢሊ ቻይልዲሽ
- ጌጥም ይሁን አሻንጉሊት ደስታን
የሚያጎናፅፈው ሽልማቱ አይደለም፤
ሽልማቱን ለማሸነፍ የሚደረገው ጥረት
እንጂ፡፡
ኤድዋርድ ጂ. ቡልዌር-ሊቶን
- ሔነሪ ኪሲንጀርን የኖቤል የሰላም ሽልማት
በሸለሙበት ወቅት ፖለቲካዊ ምፀት ዘመኑ
አልፎበት ነበር፡፡
ቶም ሌህረር
- በ20ዎቹ ዕድሜዬ መጀመሪያዬ ላይ ረዥም
ልብወለድ ፃፍኩ፤ ከዚህም የሁለተኛ ደረጃ
ሽልማት አሸነፍኩ፡፡ በመቀጠልም አጭር
ልብወለዴ ታተመ እናም 50 ዶላር አገኘሁ፡፡
ይሄም ትልቅ ነገር ነበር፡፡
ሱ ሚለር

ከዕለታት አንድ ቀን አያ አንበሶ ታሞ እቤት ዋለ፡፡ ምግብ የሚያመጣለት በማጣቱ ወዳጁን ቀበሮን ይጠራና “ወዳጄ ቀበሮ፤ እባክህ ወደ ጫካው ሂድና ወጣቱን አጋዘን ጥራልኝ። የአጋዘን ልብና አንጐል አምሮኛል” ይለዋል፡፡ ቀበሮም የአያ አንበሶን ቃል ለመፈፀም ወደ ጫካው ይሄድና አጋዘንን ያገኘዋል፡፡ ከዚያም፤
“የመጣሁት አንድ የምሥራች ይዤልህ ነው፡፡ አያ አንበሶን የዱር አራዊትን ንጉሥ ታውቀዋለህ፡፡ ታሞ ሊሞት ተቃርቧል፡፡ አንተን መንግሥቱን እንድትወርስ ሊሾምህ ይፈልጋል፡፡ መቼም የነገሥክ ጊዜ በመንግሥትህ አትረሳኝም፡፡ አሁን ወደሱ መመለሴ ነው። ብልህ ከሆንክ አብረኸኝ ና” አለው፡፡
አጋዘን በዜናው በጣም ማለለ፡፡ ምንም ሳይጠራጠር ወደ አያ አንበሶ መኖሪያ ሄደ፡፡ አጋዘኑ ገና እንደገባ፤ አያ አንበሶ አጋዘኑን ለመያዝ ተወረወረ፡፡ ሆኖም በጣም ከመወርወሩ የተነሳ ጆሮውን ብቻ ጨርፎት መሬት ላይ ወደቀ፡፡ አጋዘን አምልጦ ሄደ፡፡ ቀበሮው በድን ሆኖ ቆመ፡፡ አንበሳ በጣም ተናደደ፡፡ በዚያ ህመሙ ላይ ረሀብ ሊገለው ደርሷል፡፡ ስለዚህም ቀበሮን እንደገና ለመነው፡፡
ቀበሮም፤ “አሁን እንኳ እሺ እሚለኝ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ልሞክር” ብሎ ወደ ጫካው ሄደ፡፡ አጋዘኑ ከቁስሉ ለማገገም ሲሞክር ያገኘዋል፡፡
አጋዘን፤ “አንት የማትረባ ልታስገድለኝ ነበር! በቀንዴ ወግቼ ሳልገድልህ ድራሽህ ይጥፋ!” አለው፡፡
ቀበሮው ግን በሀፍረተ - ቢስ ግትርነት፤
“ምን ዓይነት ፈሪ ነህ? አንበሳ እኮ ሊጐዳህ አላሰበም፡፡
አንዳች ንጉሣዊ ሚስጥር በጆሮህ ሹክ ሊልህ መሞከሩ ነበር፡፡ አንተ ግን እንደደነገጠች ጥንቸል ሮጠህ ሄድክ፡፡
አያ አንበሶን በጣም አስከፍተኸዋል፡፡ መቼም አንተን ትቶ ተኩላን የሚሾመው አይመስለኝም፡፡ ዕውነት ሀሞት ካለህ መጥተህ መንግሥትህን ተረከብ፡፡ ምንም የጉዳት ነገር አታስብ፡፡ ብቻ በመንግሥትህ የእኔን ውለታ እንዳትረሳ” አለው፡፡
አጋዘኑ ለሁለተኛ ጊዜ ጓጓ፡፡ ወደ አያ አንበሶ በረት መጣ፡፡ አሁን ግን አያ አንበሶ አልተሳሳተም፡፡ በቀጥታ አጋዘን ላይ ሰፈረበት፡፡ አንበሳ ከአጥንቱ ጋር ሲታገል፤ ቀበሮ ቀልጠፍ ብሎ የአጋዘኑን ልብ መነተፈና ዋጠው፡፡
አንበሳ አጥንቱን ቆረጣጥሞ ልቡን ቢፈልግ የለም፡፡
“አንተ ቀበሮ ልቡ የታለ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ቀበሮም፤
“አያ አንበሶ፤ ወደ አንበሳ መኖሪያ ሁለት ጊዜ የመጣ ሞኝ አጋዘን ምን ልብ ይኖረዋል ብለው ነው?” ሲል መለሰ፡፡
*   *   *
አንድን ስህተት ሁለቴ ከመሳሳት ይሰውረን! “ትላንትና ማታ ወደ ቤትህ ስትገባ እንቅፋት ሆኖ የመታህ ድንጋይ ዛሬ ማታም ደግሞ ከመታህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ” ይላሉ ቻይናዎች። በየጊዜው እንቅፋት የሚሆኑብን ብዙ ሳንካዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ወሳኙ ጉዳይ ግን እንዴት ልናልፋቸው እንችላለን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ መንገድ አስቦ፣ አቅዶ፣ ተዘጋጅቶ፣ በሰከነ መላ ተወያይቶ መፍታትና መገላገል ነው፡፡ ይህም ግልፅነትና ጉዳዩን ቁልጭ አድርጐ በሁለት ዓይን ማየትን፤ የግድ ይጠይቃል፡፡ ይሄ በፈንታው ተጠያቂነትን ይወልዳል፡፡ “የእምዬን እከክ ወደ አብዬ ልክክ” ከማድረግ ያድነናል፡፡ ሁለተኛና ከባዱ መንገድ ደግሞ ችግርን በኃይል ለመፍታት መሞከር ነው፡፡ ይሄኛውም ቢሆን ግን በአቦ ሰጡኝና በዘፈቀደ ይሁን ከተባለ ሥርዓት አልባ ሁኔታን ሊያስከትልና ስሜታዊነትን ሊያሰፍን ይችላል፡፡ አያሌ ፀፃች ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ አንድ ፈላስፋ፤ “ከፀፀቶች ሁሉ የከፋ ፀፀት የሚፈጠረው፣ አብዛኛውን ጊዜ፤ ከስሜታዊነት ነው” ይለናል፡፡ ነገሮችን ረጋ ብሎና ሰክኖ ማየት መለኝነት ነው፡፡ የሚያልፉ የማይመስሉና በቀላሉ ሥጋት ላይ ሊጥሉን የሚችሉ ክስተቶችን አደብ ገዝተን፣ አስልተን ማስተዋል ትርፉ ብዙ ነው፡፡ ዋጋ ከመክፈልም ያድነናል፡፡
ሀገራችን፤
“የዘንድሮ ጉዴ ለኔም ገረመኝ
አንዱን ስለው አንዱ፣ አንዱ ባሰብኝ…”
የሚለው ዘፈን የሚመለከታት ይመስላል፡፡ የዲሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰብዓዊ መብት፣ የጤና፣ የድርቅ ወዘተ. ያልተፈቱ አያሌ ችግሮች እያሉን፣ ባለቤት የሌላቸው ሌሎች ችግሮች እንደ አዲስ ይመነጫሉ፡፡ የበለጠ ችግር የሚሆነው ደግሞ ወዴት እንደሚያመሩ አለመታወቁ ነው፡፡ “አይጢቱ ድፍን ቅል ውስጥ ገብታ ወለደች” አለው፡፡ “በምን ገብታ” ቢለው “ጉዱ ምን ላይ ነው?!” አለው አሉ፡፡ ጉዱ ምን ላይ ነው የሚያሰኙ አያሌ ጉዳዮች አሉን፡፡ የመሬት ሽንሸናና ሽያጭ ሙስና አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ ሰፊው ህዝብ “እማሆይ የተበላ ማሽላ ይጠብቃሉ” ዓይነት እስኪሆን ድረስ፤ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡
የበላ የበላው ደግሞ ሽፋን እየፈለገ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” ሆኗል፡፡ ኪሱን ካደለበ፣ ፎቁን ከገነባ፣ በርካታ ደብተሮች ከያዘ በኋላ “አገር አደጋ ላይ ወድቃለች!” እያለ መልሶ ሰው ያደነቁራል፡፡ የዋሃን የዚህን ሽፋን መጫወቻ ይሆናሉ፡፡ አገሩ ባለቤት - አጥና ተጠያቂ አካል የሌለው መስሏል፡፡ በሁሉም ረገድ “ግርግር ለሌባ ያመቻል” ሆኗል ነገሩ። ዘዴና መንገድ ማስላት ግዴታችን ነው፡፡ ነገሮችን ሁሉ ያንድ ወገን ጉዳይ አድርጐ አለመመልከት አንዱ መንገድ ነው፡፡ አቋራጩንና የብልሁን መንገድ ማየት ጥልቅ ዓይን ይፈልጋል እንጂ ጨርሶ አዳጋች ነው ማለት አይደለም፡፡ ያልተደራጀ ኃይል፣ ኃይል አይደለም፡፡ ዋናው አስተውሎትና ትኩረት ግን “መንገድ የምታውቅ አይጥ፣ ፈረስ ትቀድማለች” የሚለው የወላይታ ተረት ቢሆን መልካም ነው!