Administrator

Administrator

“ማስተር ፕላኑ ልማትን ያሻሽላል፤ በረብሻ የተሳተፉ ይከሰሳሉ” - መንግሥት

     “የአዲስ አበባና የፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን” ላይ፣ ሰሞኑን በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች  በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ፣ ሶስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ የክልሉ ፖሊስ በበኩሉ፤ በረብሻው የተሳተፉ ሰዎች ይከሰሳሉ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እጅ አለበት ብሏል፡፡
አምና ተመሳሳይ ግጭትና ተቃውሞ ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ “ማስተር ፕላኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በዙሪያው የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን እንዲጠቀለል የሚያደርግ ነው፤” የሚለው ተቃውሞ ከሰሞኑ እንደገና ተሰንዝሯል፡፡ “የከተሞቹ የአስተዳደር መዋቅር በማስተር ፕላኑ አይቀየርም” የሚለው መንግስት በበኩሉ፤ መሰረተ ልማትን በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ሲል ቆይቷል፡፡
“የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በዙሪያው ወዳሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች እየሰፋ መጥቷል” በማለት የሚከራከረው ኦፌኮ፤ “ማስተር ፕላኑን አንቀበልም፤ መሬታችን አጥንታችን ነው፤ አንነቀልም” በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች (ግንጪ፣ ደንቢዶሎ፣ ዲላላ፣ ወሊሶ፣ መደወላቡ፣ ሀረማያ፣ አይራ ጉይሶና በሌሎችም) ለተነሳው የተማሪዎች  ተቃውሞ፤ መንግስት ሰላማዊ ምላሽ መስጠት አለበት የሚለው ኦፌኮ፤ እየደረሰ ላለው ጉዳት መንግስት ኃላፊነቱን ይወስዳል ብሏል፡፡
እስር፣ ድብደባና ግድያ እየተፈጸመ፣ መሆኑን በማውገዝ፤ መንግሥት ይህን ድርጊት በአስቸኳይ ማቆም አለበት ብሏል- ኦፌኮ፡፡ “የአዲስ አበባ ወሰን፤ ከ1987 ዓ.ም በፊት  ወደነበረበት መመለስ አለበት፤ ከወሰን አልፈው የተከናወኑ ግንባታዎች በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ስር መተዳደር አለባቸው” ሲልም ፓርቲው ጠይቋል፡፡ የከተሞች ፕላን የፌደራል መንግስት ጉዳይ አይደለም ያለው ኦፌኮ፤ ማስተር ፕላኑ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ይጻረራል ብሏል፡፡  
ለልማት ተብሎ ከመሬታቸው የሚነሱ ገበሬዎች የህንፃዎች ጠባቂ እየሆኑ ነው ያሉት የኦፌኮ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ገበሬዎቹ የባለሀብትነት ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡  
ዓለም ባንክ ማስተር ፕላኑን መደገፍ የለበትም ያለው ኦፌኮ፤ ባንኩ እጁን ያንሳ ሲል ጠይቋል፡፡ የፈረንሳይዋ ሊዮን ከተማ አስተዳደር ለማስተር ፕላኑ ድጋፍ በመስጠትም አሁን ለተፈጠረው ችግር አስተዋጽኦ ስላደረገ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል ብሏል - ኦፌኮ፡፡  
የመንግስት በደልና ግፍ ካልቆመ፣ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ስጋት ላይ ይጥላል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደሚገደድ ተናግረዋል፡
“በአዲስ አበባ ዙሪያ፣  በኦሮሚያ ላይ ሰፊ የመሬት እና የባህል ወረራ ተካሂዷል  ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ከ25 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ አካባቢ የነበሩ 28  የገበሬ ማህበራት ዛሬ የሉም ብለዋል፡፡ መንግስት በርካሽ የካሳ ክፍያ ከገበሬዎች መሬት እየወሰደ  በሚሊዮን ብሮች በጨረታ ይሸጣል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ሱሉልታ አካባቢ ገበሬዎች በ50 ሺህ ብር ካሳ ይፈናቀላል ብለዋል፡፡
ሰኞ እለት በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ከፖሊስ ጋር በተነሳ ግጭት በርካታ ተማሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ትምህርት ተስተጓጉሎ ሰንብቷል፡፡  ዩኒቨርስቲው በበኩሉ፣  በተቃውሞ ምክንያት ትምህርት ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቋረጠና የግቢው ሁኔታ እንደተረጋጋ ገልጿል፡፡
ተቃውሞው በበርካታ ከተሞች በሚገኙ ዩንቨርስቲዎችና ት/ቤቶች የተስፋፋ ሲሆን ፣ በአንዳንዶቹ  አካባቢዎችም  ነዋሪዎች እንደተሣተፉበት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር በበኩሉ፤ በረብሻው የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን በመግለፅ ተቃዋሚዎችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ማስተር ፕላኑ የፌደራል ስርአቱን አይጥስም ያለው መስተዳድሩ፤ የኦሮሚያ መሬትንም ቆርሶ ለሌላ አካል አይሰጥም ብሏል፡፡  ሁከት የሚሹ ሃይሎች፤ ለማስተር ፕላኑ የተሣሳተ ትርጉም ሰጥተውታል፣ በዚህም ለጠፋው ህይወትና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ ናቸው ብሏል መስተዳድሩ ፡፡
ባለፈው አመት በዩንቨርስቲዎችና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ማስተር ፕላኑን ተመሳሳይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ፤ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት 10 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

ከቡድኑ ጋር ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ፣ ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ነበር
  በሴካፋ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን ልኡካን የመሩት የክለቡ ማናጀር ዊሊስ ዋሊያውላ፤ ስድስት የቡድኑ ልኡክ አባላት ለአስር ቀናት አርፈውበት ለቆዩት “እንዳለ እና ቤተሰቡ ቸርቺል ሆቴል መከፈል የነበረበትን 41 ሺህ 154 ብር መክፈል ባለመቻላቸው፣ ከሆቴሉ እንዳይወጡ ታግደው ከቆዩ በኋላ ከትናንተ በስቲያ ተለቀቁ፡፡
የኬንያው ብሄራዊ ቡድን “ሃራምቤ ስታርስ” ከሩብ ፍጻሜ ውድድሩ ውጭ ሆኖ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ወደ አገሩ ቢመለስም፣ ዊሊስ ዋሊያውላ ግን ከቡድኑ ጋር የመጡት ስድስት ተጨማሪ የልኡካን ቡድን አባላት በሆቴሉ የቆዩበትን ወጪ መክፈል ባለመቻላቸው ከሆቴሉ እንዳይወጡ ታግደው ከቆዩ በኋላ፣ የኬንያ የስፖርት ሚኒስቴር ክፍያውን በመፈጸሙ ትናንት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን “ሲቲዝን ቲቪ” የተባለው የአገሪቱ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡ የቡድኑ መሪ የሆቴሉን ዕዳ ሳይከፍሉ ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ፓስፖርታቸውን ተቀምተው ነበር ያለው ዘገባው፤ የኬንያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የልኡካን ቡድኑን ለመሩት ለእኒሁ ግለሰብ ወጪውን እንዲሸፍኑ 250ሺህ የኬንያ ሽልንግ መላኩን ጠቁሟል፡፡
የሴካፋ አዘጋጆች፤ ኬንያ 20 ተጫዋቾችንና አምስት የልኡካን ቡድን አባላትን ብቻ እንድትልክ ቢያስታውቁም፣ የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን 23 ተጫዋቾችንና የልኡካን ቡድን አባላትን በመላኩና ተጨማሪ ስድስት አባላት በመኖራቸው የገንዘብ እጥረቱ ሊከሰት እንደቻለ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

       ለችግር ተጋላጭ በሆኑ እናቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት  አድርጎ የሚሰራው መሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት፤ ጉለሌ ክ/ከተማ መቀጠያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 350 ሺህ ብር በማውጣት ምንጭ አገልብቶ የንፁህ መጠጥ ውሃ አጎልግሎት የሚያበረክተውን ፕሮጀክት፤ የፊታችን ሰኞ ረፋዱ ላይ ያስመርቃል፡፡ የጎለበተው ምንጭ ለአምስት ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥም የድርጅቱ መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት አዛገ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የደረቅ ቆሻሻ  አወጋገድ፣ የውሃ አቅርቦትና የንፅህና አጠባበቅ ፕሮጀክትን በሚደግፈው “ሲቪል ሶሳይቲ ስፖርት ፕሮግራም” ድጋፍ የተሰራ ሲሆን በተለይ በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የውሃ እጥረት የሚንገላቱ እናቶችና ህፃናትን እፎይ ያሰኛል ብለዋል፤ ወ/ሮ መሰረት፡፡
የአካባቢው ህዝብ በጉልበት፣ በእውቀት በጥበቃ ስራና በቁፋሮ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ይህ እገዛ ባይገኝ ኖሮ ፕሮጀክቱ 900 ሺህ ብር ይወስድ ነበር ብለዋል፡፡

- በውጭ አገራት ወታደራዊ ካምፖችን እንደማታቋቁም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ነበር
- ለመርከቦቼ ነዳጅ መሙያና ለጦር መኮንኖቼ መዝናኛ ላደርገው ነው ብላለች

   በውጭ አገራት ወታደራዊ ካምፖችን የማቋቋም ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ የቆየችው ቻይና፣ የሎጅስቲክስ ማዕከል ነው ያለችውን የመጀመሪያውን ወታደራዊ ካምፕ በጅቡቲ ለማቋቋም ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተነጋገረች እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ወታደራዊ ካምፑ ለቻይና የባህር ሃይል መርከቦች የነዳጅና የሌሎች ሎጅስቲክሶች አቅርቦት የማሟላትና አገሪቱ በኤደን ባህረ ሰላጤ በምታከናውናቸው የጸረ-ስለላ ተልኮዎች ላይ ለተሰማሩ የጦር መኮንኖችና መርከበኞች በመዝናኛ ማዕከልነት የማገልገል አላማ ይዞ እንደሚቋቋም የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡
ወታደራዊ ካምፑ መቋቋሙ የቻይና የጦር ሃይል አለማቀፍ ግዴታዎቹን እንዲወጣ እንዲሁም አለማቀፍና ክልላዊ ሰላምና መረጋጋትን በማስጠበቅ ረገድ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ  የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል፡፡
የቻይና የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማቲክና ወታደራዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ፣ አገሪቱ ለረጅም ጊዜያት ስትከተለው የኖረችውን በሌሎች አገራት ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያለማድረግ ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተዳፈረችው እንደሆነ ያሳያል ብሏል ዘገባው፡፡
በቅርቡ በማሊ በተከሰተውና 19 ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የሽብር ጥቃት፣ 3 ቻይናውያን መሞታቸውን ተከትሎ፣ ቻይና ጽንፈኛ ቡድኖች በአፍሪካ አገራት የሚያደርሱትን ጥቃት ለመታገል ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ዜጎቿ የሞቱባት ቻይና ከጸረ-ስለላ ተልዕኮ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በማሊና በሌሎች የአፍሪካ አገራት በተሰማሩ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ወታደሮቿን ማሰማራቷን ያስታወሰው ዘገባ፣ በጅቡቲ ከዚህ ቀደም የተቋቋሙ የአሜሪካ ጥምር ግብረ ሃይልና የፈረንሳይ ወታደራዊ ካምፖች እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡

   ሰሜን ኮርያ የአገሪቱ ወንዶች ጸጉራቸውን ከ2 ሴንቲ ሜትር በላይ እንዳያሳድጉ የሚከለክል ትዕዛዝ ያስተላለፈች ሲሆን የመዲናዋ ባለስልጣናት ጸጉራቸውን ከዚህ በላይ ያሳደጉትን ዜጎች በቁጥጥር ስር እያዋሉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን በሚታወቁበት የጸጉር ስታይል አሳጥረው እንዲቆረጡ እያስገደዱ መሆኑ ተዘገበ፡፡
ዘ ቴሌግራፍ፣ ቾሱን ኢቦ የተባለው የደቡብ ኮርያ ጋዜጣ ሰሞኑን ያወጣውን ዘገባ ጠቅሶ እንዳለው፣ የመዲናዋ አስተዳደር የፒንግያንግ ነዋሪ የሆኑ ወንዶች ጸጉራቸውን በኪም ጆንግ ኡን ስታይል በመቆረጥ፣ለፕሬዚዳንቱ ያላቸውን ክብር እንዲያሳዩ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
የከተማዋ ባለስልጣናት ያሰማሯቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተቆጣጣሪዎች፣ መቀስ ይዘው በየቦታው እየተዘዋወሩ፣ረጃጅም ጸጉር ያላቸውን ወንዶች አሳጥረው ማስተካከል መጀመራቸውም ተነግሯል፡፡
የከተማዋ ሴቶችም ቢሆኑ የጸጉር አሰራራቸውን የፕሬዚዳንቱ ሚስት የሆኑት ቀዳማዊት እመቤት ሪ ሶል ጁ፣ በሚያዘወትሩት የጸጉር አሰራር መልክ እንዲያስተካክሉ ታዝዘዋል ብሏል ዘገባው፡፡

ከ5 አመታት በኋላ ከ30 ዜጎቿ አንዱ ሚሊየነር ይሆናል
   ዌልዝ ኢንሳይት የተባለው አለማቀፍ የኢኮኖሚ መረጃ ተንታኝ ተቋም፣ ሲንጋፖር በመጪዎቹ አምስት አመታት በየአመቱ በአማካይ 37 ሺህ 600 ያህል ተጨማሪ አዳዲስ ሚሊየነሮችን ታፈራለች ተብሎ እንደሚገመትና በ2020 የፈረንጆች አመት ከ30 ሲንጋፖራውያን አንዱ ሚሊየነር ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጹን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ይህ የአዳዲስ ሚሊየነሮች ቁጥር በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ሚሊየነሮችን ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭ አገራት ወደ ሲንጋፖር የሚገቡትንም ይጨምራል ያለው ዘገባው፣ ሲንጋፖር በአሁኑ ወቅት በድምሩ 806 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የተጣራ ሃብት ያካበቱ 154 ሺህ ያህል ባለ ከፍተኛ ገቢ ዜጎች እንዳሏትና እነዚህ ሚሊየነሮች ከአጠቃላዩ የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር 3 በመቶ ያህሉን እንደሚይዙም ጠቁሟል፡፡
ወደ አገሪቱ የሚጎርፉና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ህንዳውያንና ቻይናውያን ሚሊየነሮች ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በሲንጋፖር የቀጠለው የፋይናንስ ገበያ መሟሟቅ፣የግል ባንኮች መስፋፋታቸውና የላቀ ጥራት ያለው የአኗኗር ዘዬዋ፣ ከፍተኛ ሃብት ያላቸውን በርካታ የተለያዩ አገራት ዜጎች ወደ አገሪቱ መሳባቸውን ይቀጥላሉ መባሉንም አስታውቋል፡፡

   እስካለፈው ጥቅምት በነበሩት አስራ ሁለት ወራት የተመዘገበው አለማቀፍ አማካይ የሙቀት መጠን በታሪክ ከፍተኛው እንደሆነና ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ የቀረው የፈረንጆች አመት 2015 በአለማችን እጅግ ሞቃቱ አመት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአለም የሜቲሪዮሎጂ ድርጅት ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከ2011 እስከ 2015 የነበረው የአምስት አመታት ጊዜ፣ በአለማችን ታሪክ እጅግ ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ የድርጅቱ ተመራማሪዎች የዘንድሮው የአለማችን አማካይ የሙቀት መጠን ከፍተኛ ሊሆን የቻለው የሰው ልጅ የሚፈጥረው የአለም የሙቀት መጠን በመጨመሩና የኤል ኒኖ ክስተት ባደረሱት የከፋ ተጽዕኖ ሳቢያ ነው ማለታቸውን ጠቁሟል። በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት በአለማችን የበካይ ጋዞች ልቀት መጠን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ያለው የአለም የሜቲሪዮሎጂ ድርጅት፣ የውቅያኖሶች የሙቀት መጠንም እስካሁን ከተመዘገቡት መጠኖች ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው አመት በርካታ የአለማችን አገራት በታሪካቸው ከፍተኛውን የሙቀት መጠን አስተናግደዋል ያለው ዘገባው፣ ቻይና ባለፉት 12 ወራት አይታው የማታውቀውን ሙቀት እንዳሳተናገደች ጠቁሞ፣ አፍሪካም በአመቱ ከፍተኛውን ሙቀት እንዳስመዘገበች አውስቷል፡፡

   መኖሪያቸውን ለንደን ባደረጉት ደራሲ ኤርሚያስ ሚካኤል (ሕርይቲ) የተፃፈው “የሚበርድ ፀሐይ” የተሰኘ የግጥም መድበል፤ ነገ ጠዋት ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ትንሷ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የተፃፉ 78 ግጥሞችን አካትቷል፡፡ በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን የግጥም ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ታዳሚያን በኮሜዲ ዝግጅቶች እንደሚዝናኑም የዝግጅቱ አስተባባሪ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንት የፕሬስ ስራዎች ድርጅት ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡

Saturday, 28 November 2015 14:11

የዘላለም ጥግ

(ስለ ጦርነት አስከፊነት)
• ኦ ሰላም! በስምሽ ስንት ጦርነቶች ታወጁብሽ።
አሌክሳንደር ፖፕ
• ጦርነት ጀብዱ አይደለም፡፡ በሽታ ነው፡፡ እንደ
ታይፈስ ዓይነት በሽታ፡፡
አንቶይኔ ሊ ሴይንት አክሱፔሪ
• ጦርነት እንደ ወንጀል መቆጠር አለበት፤
ቀስቃሾቹም እንደ ወንጀለኞች መቀጣት
አለባቸው፡፡
ቻርለስ ኢቫንስ ሁግስ
• ሰዎች አሁን ጦርነትን ማጥፋት ካልተሳካላቸው፤
ስልጣኔና የሰው ልጅ አከተመላቸው፡፡
ሉድዊግ ቮን ሚሴስ
• ጦርነት ለተሸናፊው ብቻ ሳይሆን ለአሸናፊውም
ጭምር ጐጂ ነው፡፡
ሉድዊግ ቮን ሚሴስ
• “እማዬ፤ ጦርነት ምንድን ነው?” ብሎ የሚጠይቅ
ህፃን ለመውለድ አልማለሁ፡፡
ኢቭ ሜሪያም
• አሜሪካ በ ሁሉም ነ ገር የ ዓለም መ ሪ መ ሆን
አለባት የሚለውን ሃሳብ ማስወገድ አለብን፡፡
ፍራንሲስ ጆን ማክኮኔል
• ጦርነቶችን የሚጀምሩት ወታደሮች አይደሉም፤
ፖለቲከኞች ናቸው፡፡
ጀነራል ዊሊያም ዌስትሞርላንድ
• ሰላም ከማስፈን ይልቅ ጦርነት መፍጠር በጣም
ቀላል ነው፡፡
ጆርጅስ ክሌሜንስዩ
• ጦርነት የፖሊሲ ክስረት ነው፡፡
ሃንስ ቫን ሲክት
• የታላላቅ መንግስታት ኃላፊነት ማገልገል እንጂ
ዓለም ላይ መግነን አይደለም፡፡
ሃሪ ኤስ. ትሩማን
• ለወታደራዊ ጀግንነት ትኩረት መስጠት
የፍልስፍና ድህነትን አመልካች ነው፡፡
ሄንክ ሚድልራድ
• በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤
በጦርነት ዘመን አባቶች ልጆቻቸውን
ይቀብራሉ፡፡
ሔሮዱተስ

Saturday, 28 November 2015 14:09

የጸሐፍት ጥግ

(ስለ ፕሬስ)


• አንድ ሚሊዬነር 10 ጋዜጦች ስላሉት የፕሬስ
ነፃነት የተቀዳጀን ይመስለናል፡፡ 10 ሚሊዮን
ሰዎች ግ ን ም ንም ጋ ዜጦች የ ላቸውም - ይ ሄ
የፕሬስ ነፃነት አይደለም፡፡
አናስታስ ማኮያን
• በሌሎች አገራት ፕሬሱ፣ መፃህፍትና
ማናቸውም ዓይነት የሥነጽሑፍ ሥራዎች
ሳንሱር የሚደረጉ ከሆነ፣ እነሱን ነፃ ለማውጣት
ጥረታችንን እጥፍ ማድረግ አለብን፡፡
ፍራንክሊን ዲ. ሩስቬልት
• ሌላ ቦታ እንደተናገርኩት፤ ነፃ ፕሬስ አንድን
አገር ጠንካራና የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ
ያግዛል፤ እኛን መሪዎችንም የበለጠ ውጤታማ
ያደርገናል፤ ምክንያቱም ከፍተኛ ተጠያቂነትን
ይፈልጋል፡፡
ባራክ ኦባማ
• በእኔ አስተያየት፣ የዲሞክራሲ የማዕዘን ድንጋይ
ነፃ ፕሬስ ነው እሱ - ነው የማዕዘን ድንጋዩ፡፡
ሚሎስ ፎርማን
• ነፃ ፕሬስ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን
እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ግን
ያለ ነፃነት ፕሬሱ መጥፎ ከመሆን ውጭ ፈጽሞ
ሌላ አማራጭ የለውም፡፡
አልበርት ካሙ
• ነፃ ፕሬስ የተከበረ ፕሬስ መሆን አለበት፡፡
ቶም ስቶፓርድ
• የፕሬስ ነፃነት የተረጋገጠው የፕሬስ ውጤት
ባለቤት ለሆኑት ብቻ ነው፡፡
ኤ.ጄ ላይብሊንግ
• ፕሬሱን መገደብ ህዝብን መስደብ ነው፤
የተወሰኑ መፃሕፍት እንዳይነበቡ መከልከል
ነዋሪዎች ሞኞች ወይም ባሪያዎች ናቸው ብሎ
ማወጅ ነው፡፡
ክላውዴ አድሬይን ሄልቬቲየስ
• ጋዜጠኝነት የተደራጀ ሃሜት ነው፡፡
ኤድዋርድር ኤግልስቶን
• የዲሞክራሲ ጫጫታ ደስ ይለኛል፡፡
ጄምስ ቡቻናን
• ሚዲያ የባህላችን የነርቭ ሥርዓት ነው፡፡
ጌሪ ማልኪን