Administrator

Administrator

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሹም ባለሥልጣን እሥር ቤት ይገባል፡፡
እንደገባ ወደተመደበለት ክፍል ሲደርስ፣ እሥረኛው ሁሉ በሱ ላይ መጠቋቆም   ጀመረ፡፡
አንደኛው - እንዴ ይሄንን‘ኮ አውቀዋለሁ፤ የናጠጠ ሀብታም ነው!
ሁለተኛው - እኔ ደግሞ አንቱ የተባለ ሹም መሆኑን ነው የማውቀው!
ሶስተኛው - ጐበዝ አትጃጃሉ! የናጠጠ ሀብታምም፣ አንቱ የተባለ  ሹምም  እንዳይሆን ምን ያግደዋል? እንዲያውም በዛሬ ጊዜ የሚበዙት    ሹሞች ሀብታሞች   ናቸው፡፡
አራተኛው - ቀስ እያለች ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም መጣች በለኛ!
አንደኛው - እንዴታ!
ስድስተኛው - እኔ እምለው ወንድሞቼ፣ ከዚህ ሁሉ ፍልስፍና ለምን ራሱን   አንጠይቀውም?
ሁሉም - ውነቱን ነው፣ ውነቱን ነው!
አንደኛው - ጋሼ
እንግዳው እሥረኛ - አቤት የኔ ልጅ
አንደኛው - ምን አድርገዋል ብለው ነው ወደዚህ ያመጡዎት?
እንግዳው እሥረኛ - ኮርቻ ሰርቀሃል ነው የሚሉኝ
አንደኛው - ለኮርቻ? እዚህ ከባድ እሥር ቤት ለኮርቻ ብለው አመጡዎት?
እንግዳው እሥረኛ - ምን እባክህ አንድ የማትረባ በቅሎ ከሥሩ አለች!
***
በሀገራችን ሌባው በጣም በዝቷል፡፡ ሁሉም ስለኮርቻው እንጂ ስለ በቅሎዋ አያወራም! የሚታሠረው እንጂ ስለ በቅሎዋ አያወራም! የሚታሠረው በርካታ የሀገር ገንዘብ ሰርቆ ይሁን እንጂ ምንም እንዳልነካ አድርጐ ደረቱን የሚነፋ መዓት ነው፡፡ የሀብት ዘረፋው ሳያንስ በሥልጣን የሚባልገው ሥፍር ቁጥር የለውም፡፡ ሥልጣን ወደ ኃላፊነት ሳይሆን ወደ ሀብት፣ ወደ መሬት መከፋፈል፣ ወደ ዘመድ መጠቃቀሚያ፣ ወደ ፍትሕ ማዛቢያ፣ ወደ ምዝበራ መረብ ማስፋፊያ፣ ወደ ህገ ወጥ ፎቅ መገንቢያ ካመራ፤ ወደ ልማት ሳይሆን ወደ ጥፋት እየሄድን ነው ማለት ነው፡፡ ውሎ አድሮ ሁሉም የበታች እንደ ቁንጩዎቹ የድርሻዬን ልውሰድ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡
ከባለሥልጣን የሚመሳጠረው አቀባባይም እኔም የድርሻዬን ማለቱም አይቀሬ ነው፡፡ በኮሚሽን የሚተዳደረው ሰው፤ ከዋናዎቹ ገዢና ሻጮች የተሻለ የሚያገኝበትን መንገድ ስለሚያሰላ ህገ-ወጥ ንግዱ እንዲፋፋም፣ የተለያዩ ወገኖች ገብተውበት የዘረፋ መረቡ እንዲሰፋ፣ ማድረጉን ይያያዘዋል፡፡ አንዱ ህገ ወጥ ተብሎ ሲታሰር ግን መረቡ አይነካም፡፡ ሀገራችን እስከወሲብ ድረስ የተወሳሰበ ሙስና እያስተናገደች መሆኑ ይነገራል፡፡
ይህንኑ ሙስና ምሁሩም መሀይሙም፣ ህገ አስፈፃሚውም አላዋቂውም አድናቆቱን እየገለፀና ወሬውን በመንዛት እየተባበረ ሀገራችን ወደ አሳዛኝ ፈተና እየገባች ነው!
የብዝበዛው መረብ ክሩ እየበዛ ሲሄድ ፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው! ምነው ቢሉ ሌብነቱን እንዳይከላከሉ፣ በእጅ በአፍ የሚባሉ ፖለቲከኞች ይኖራሉና! ከንቲባዎች፣ የወረዳ ሊቃነ መናብርት፣ የማህበራት መሪዎች፣ ህግ አስፈፃሚዎች፣ ትላልቅ የክልል ሹማምንት ከትንሽ እስከ ትልቅ የቅሌት መዝገብ ላይ ሠፍረው ወደ ወህኒ ሲጋዙ፣ ወደ ዘብጥያ ሲወርዱ አይተናል፡፡
ገናም እናያለን፡፡ የብዝበዛው መረብ እስካልተበጣጠሰ ድረስ! በመሬት ስፋት የማይለካ፣ በፎቅ ርዝመት የማይወሰን፣ በቀረጥ ነፃ ብቻ የማይቆም የህሊና መቆሸሽና ተዛማች የሌብነት በሽታ እንደ ዘር - ደዌ መናኘቱ፤ የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ - ርትዕ፣ የዕድገት ሀገር ትሆናለች የምትባለውን ሀገራችንን፤ ህልውናዋን ጭምር የሚፈታተኑ ከተላላኪ እስከ መመሪያ አስፈፃሚ የሌብነት ባለድርሻ አካላት የሆኑባት የዘረፋ መናኸሪያ እንዳትሆን፣ ከባድ እንቅስቃሴ ትሻለች፡፡
ራሱ እየሰረቀ ሌላውን ማማት ፋሺን እየሆነ ነው፡፡ እራሱ እየገረፈ እንደ ጅራፉ የሚጮኸው እየባሰ ነው፡፡
ከሥጋ ቤት እስከ ኦፊስ ባር ሲመካከርና ሲመርብ (Weaving corruptive networks) የሚያመሸው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡
ሌብነት “ቢዝነስ” የሚል የማዕረግ ስም ከወጣላት በጣም ቆየ! አንዴ በሥልጣኑ፣ አንዴ በንግድ ውስጥ እጃቸውን እየነከሩ ያሉ በርካታ ናቸው - “የሌሊት ወፍ ገብሪ- አይጥ ነኝ፤ አይጥ ገብሪ የሌሊት ወፍ ነኝ” ማለት ይሄው ነው!   

Saturday, 24 October 2015 10:13

“ዝክረ አርቲስት አልጋነሽ

አንጋፋዋ የጥበብ ባለሙያ አልጋነሽ ታሪኩ ለ50 ዓመታት የሰራቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቿ የተዘከሩበት የኪነጥበብ ፕሮግራም ከትላንት በስቲያ ጠዋት በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ተከናወነ፡፡
 በእለቱ የአርቲስቷ ስራዎች፣ የጥበብ አጀማመሯ፣ በኪነጥበቡ ያሳለፈቻቸው ፈተናዎችና ስኬቶቿ የተወሱ ሲሆን የተለያዩ የኪነ - ጥበብ ዝግጅቶችም ቀርበዋል፡፡
 በዚህ ፕሮግራም  ላይ የአርቲስቷ የሙያ ጓደኞች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የኪነጥበብ አፍቃሪያን፣ የባህልና ቱሪዝም ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመው ነበር፡፡  

• ተልዕኮዬ የጃንሆይን ትምህርት ለዓለም ማሰራጨት ነው
• Ethiopia is calling - የሚለውን እንዴት አቀነቀነው?

    ጃማይካውያን ለኢትዮጵያና ለቀድሞው ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያላቸው ከአምልኮ ያልተናነሰ ፍቅርና ክብር በእጅጉ የሚያስደንቅ ነው፡፡
የሬጌ አቀንቃኙ ሲዲኒ ዊን ሳልማንም፤ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ እንዲሁም በጃንሆይ ፍቅር በእጅጉ መማረኩን ይገልፃል፡፡ ተልዕኮዬ የአባባ ጃንሆይን
መልእክት ለዓለም ማሰራጨት ነው ይላል፡፡ ከፍቅሩ ብዛት እምነቱን ሳይቀር ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቀይሯል፡፡ በቋሚነት የሚኖረውም እንደ
ሁለተኛዋ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም፣ በሚቆጥራት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊት ሚስት አግብቶ ልጆች አፍርቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 የኒውዮርክ መንትያ ህንፃዎች በአልቃይዳ በተመቱ ጊዜ “Babilon is falling Ethiopia is calling” (ባቢሎን እየፈረሰች ነው፤
ኢትዮጵያ እየተጣራች ነው እንደማለት) የሚል ዘፈን ማቀንቀኑን ይናገራል፡፡ የዛሬ 14 ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ፣ የእረፍት
ስሜት እንደተሰማው ይገልፃል፡፡ እንዴት? ምን ዓይነት እረፍት? ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ፍቅርና ቁርኝት ምስጢሩ ምንድነው? አርቲስት ሲዲኒ ሳልማን
ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ሁሉንም በስፋት አውግቷታል፡፡ በ20 ዓመቱ ከጃማይካ ወደ አሜሪካ የተሻገረበትን ምክንያት በመግለፅ
የሚጀምረው አቀንቃኙ፤ ስለህይወቱና ሙያው በተለይም አዲስ ስለሚያወጣው የሙዚቃ አልበሙ ይነግረናል፡፡



ለምን ነበር ወደ አሜሪካ የሄድከው?
በዚያን ጊዜ እናትና አባቴ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ አሜሪካ በመሻገራቸው ነው እኔም  ከቤተሰቤ ጋር የሄድኩት፡፡ እዚያ እንደሄድኩ የኮሌጅ ትምህርት ጀመርኩኝ፡፡ በብሩክሊን ከተማ ብሩክሊን ኮሌጅ ውስጥ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አጠናሁ፡፡ ድምፅና ጊታር ያጠናሁት ግን  በሞንሮው ኮሌጅና ኢሮኖቲካስ ኮሌጅ በመሳሰሉት ውስጥ ነው፡፡…
በስንት ዓመትህ ነው ማንጐራጐር የጀመርከው?
የ12 አመት ልጅ ሆኜ ጃማይካ ውስጥ በትምህርት ቤት የተሰጥኦ ውድድር ላይ ተሳተፍኩ፡፡ በማመልክበት ቤተ-ክርስቲያንም እዘምር ነበር፡፡ በዚያን ሰዓት ድምፅህ አሪፍ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰጡኝ ነበር፡፡ በፕሮፌሽናል ደረጃ መዝፈን የጀመርኩት ግን ኒውዮርክ ውስጥ ነው፡፡ ከኮሌጅ ምርቃቴ በኋላ ማለት ነው፡፡ ከዚያም እምነቴን ወደ ኦርቶዶክስ ቀየርኩኝ፡፡ ሃይማኖቴን ኦርቶዶክስ ካደረግሁ በኋላ በሙሉ አቅሜና ችሎታዬ ስለ ኢትዮጵያና ፍትህ ስለተነፈጉ ድሆች ለመዝፈን ወሰንኩና መዝፈን ጀመርኩኝ፡፡
እምነትህን ለምንድነው ወደ ኦርቶዶክስ ሃየማኖት የቀየርከው?
በአባባ ጃንሆይ ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ለሰው ልጆች ስላላቸው ፍቅር በልጅነቴም እሰማ ነበር፡፡ ወደ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ከኢትዮጵያዊያን ጋር የመገናኘት እድል ስለገጠመኝ የበለጠ ሰው ወዳድነታቸውን፣ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን አክብሮት በተግባር ለማየት ቻልኩ፡፡ እንደምታውቂው ምዕራባዊያን ሁሌ ወከባ፣ ሁሌ ለአለማዊ ነገር ግርግር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ለመኖርና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ለመሆን በቃሁ፡፡ የኢትዮጵያ ባህልና እምነት የህይወት ልምዴ አንዱ አካል እንዲሆን መረጥኩ፡፡
“Babilon is falling Ethiopia is calling” የሚለውን ዘፈን ያቀነቀንከው ለዚህ ነው?
አዎ፡፡ ግን ይሄ አልበም የተሰራው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2001 ዓ.ም ኒውዮርክ ውስጥ የሚገኙት ሁለት መንትያ የቢዝነስ ህንፃዎች በአልቃይዳ በተመቱ ወቅት ነው፡፡ የሚገርምሽ የኔም የስራ ቦታ እነዚያ ህንፃዎች ውስጥ ነበር፡፡ በቃ እንደዛ ህንፃዎቹ ተመትተው ሲወድቁ “Babilon is falling Ethiopia is calling” የሚለው ዘፈን መጣልኝ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያኖች ይህን ዘፈን ያውቁታል፡፡ ከዚያም አልበሙ እንደወጣ (ከ14 አመት በፊት ማለት ነው) ሰሞን ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማህ ስሜት ምን ነበር?
እዚህ እንደመጣሁ የተሰማኝ እረፍት ነው፡፡ ምንም እንኳን ለአገሪቱ አዲስ ብሆንም እረፍት ተሰምቶኛል፡፡ ምክንያቱም በኖርኩበት ኒውዮርክ ሁሌም ወከባ ነው፤ ያለሽን 95 በመቶ ጊዜ የምታሳልፊው በስራ ነው፡፡ ለመኖር… ለቤት ኪራይ… ለሶሻል ሴኪዩሪቲ… ለሁሉም መስራት አለብሽ፡፡ ይህን ሁሉ ለማሟላት ገንዘብ ያስፈልግሻል፡፡ አሜሪካ ውስጥ አንድ ቀን እንኳን ስራሽን አጣሽ ማለት ውው….ው በቃ ህይወትሽ ተመሳቀለ ማለት ነው፡፡ እኔም በዚህ ህይወት ውስጥ ስለኖርኩ ስልችት ብሎኝ ነበር፡፡ እዚህ ስመጣ አዲስ ህይወት… እረፍት… ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያን በክርስቶስ ፍቅር ውስጥ ተረጋግቼ የመኖር ፍላጐት አደረብኝ፡፡ በቃ ኢትዮጵያ እንደገባሁ እረፍት ነው የተሰማኝ፡፡
ህዝቦቹም እንግዳን እንደ ህፃን ልጅ በፍቅር ነው የሚንከባከቡት፡፡ አየሩም… ሁሉም ነገር ለእኔ በጣም ተስማሚ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቼ አማርኛ መናገር ስጀምር፣ እየሳቁ ያበረታቱኝና ሞራል ይሰጡኝ ነበር፡፡ ብቻ ኢትዮጵያ ፍቅር… የፍቅር አገር ናት፡፡ ከዚህ ፍቅር ደግሞ እኔ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ፡፡ ኢትዮጵያን እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደባት ቅዱስ አገር፣ እንደ ኢየሩሳሌም ነው የማያት፡፡ ለእኔ ሁለተኛዋ ኢየሩሳሌም ናት ማለት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ኢየሩሳሌም እስራኤል ውስጥ ጦርነት አለ፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በሰላም በኩል ከኢየሩሳሌም ትበልጣለች፡፡
ኢየሩሳሌም ኖረህ ታውቃለህ?
በፍፁም! ኢየሩሳሌምን በመፅሀፍ ቅዱስ ነው የማውቃት፡፡ ነገር ግን በፍፁም የምረሳት አገር አይደለችም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዋናው ስራህ ምንድን ነው? ሙዚቃ? ንግድ ወይስ?
ዋናው የእኔ ተልእኮ የመፅሃፍ ቅዱስን ትምህርት፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅርና መልእክት መስበክና ማሰራጨት ነው፡፡ የአባባ ጃንሆይን መልእክትና ትምህርት ለዓለም ማሳወቅ ነው፡፡ አባባ ጃንሆይ የአለም ህዝቦች ፣ በዘርና በቀለም ሳንለያይ በፍቅር እንድንኖር አስተምረውናል፡፡ የእኔም ዋና ስራ እነዚህን ነገሮች ማስተማር ነው፡፡ ትምህርቱን የማስተላልፈው ደግሞ በሙዚቃ ነው፡፡ ስለዚህ ዋና ስራዬ ሙዚቃ ነው ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊት አግብተህ ሁለት ልጆች ማፍራትህን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለትዳርህ አጫውተኝ?
ልክ ነው ሚስቴ ኢትዮጵያዊት ናት፡፡ ለይላ ትባላለች፡፡ ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ሴት ልጆችን ከእሷ ወልጃለሁ፡፡ ምስጋናዬ ሲዲኒ እና መባፅዮን ሲዲኒ ይባላሉ፡፡ ምስጋናዬ ዘጠኝ አመቷ ሲሆን መባፅዮን የአራት አመት ልጅ ናት፡፡ በኑሮዬ፣ በልጆቼና በትዳሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
እስቲ ስለ ባለቤትህ ለይላ እና ስለተገናኛችሁበት አጋጣሚ አጫውተኝ…
ባለቤቴ ለይላ መኩሪያ ትባላለች፡፡ የተገናኘነው ናዝሬት ውስጥ ነው፡፡ እኔ ገና አዲስ አበባ እንደመጣሁ ኑሮዬን ለማመቻቸትና ስራ ለመስራት ወዲህ ወዲያ እያልኩ ሳለ ነበር ያገኘኋት፡፡ ናዝሬት አንድ ዝግጅት ነበረኝ፤ እዚያ ለስራ ስሄድ የፕሮግራሙ አደራጅ ነበረች፡፡ በዚያን ጊዜ የአዳማ ወጣቶች ልማት ላይ የመስራት ፍላጐት እንዳላት ነገረችኝ፡፡ እኔም ሻሸመኔ ውስጥ የሆነ ድርጅት አለን፤ ራስታዎች የምንሳተፍበት፡፡ አዳማና ሻሸመኔ ደግሞ ሁለቱም የኦሮሚያ ክልሎች እንደመሆናቸው ብዙ የልማት ስራዎችን አብረው ይሰራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አዳማና ሻሸመኔ ላይ ፌስቲቫሎች ተዘጋጀና እኔም በበጐ ፈቃደኝነት ስራዎቼን አቀረብኩኝ፡፡ ላይላ ባላት አቅም አገሯንና ህዝቧን ማገልገል የምትወድ ጐበዝ ሴት ናት፡፡ እንዲህ ተቀራርበን ነው ያገባኋት፡፡ ለይላ ለእኔ ጥሩ ሚስት ናት፡፡
የባለቤትህ ዋና ሙያ ምንድን ነው?
እሷ የተዋጣላት ማናጀር ናት፡፡ በማኔጅመንትና በእንግዳ አቀባበልና አያያዝ ዘርፍ ነው የተመረቀችው፡፡ አዳማ ትልቅ ሆቴል ውስጥ በስኬታማ ማናጀርነት ለረጅም ጊዜ ሰርታለች፡፡ አሁን ደግሞ በሙዚቃና ኢንተርቴይንመንት ዘርፍ ትልልቅ ዝግጅቶችን ታሰናዳለች፡፡
የመጀመሪያ ሚስትህ ናት ወይስ ከዚያ በፊት ትዳር ነበረህ?
አሜሪካ እያለሁ ሌላ ሚስት ነበረችኝ፤ ከእሷ ሁለት ትልልቅ ሴት ልጆች አሉኝ፡፡
“The Ultimate Challenge” (ታላቁ ፈተና) የተባለው ሁለተኛ አዲስ አልበምህ … ምን ላይ ደረሰ?
“ታላቁ ፈተና” አልበሜ አልቋል ግን አልተለቀቀም፡፡ በመጀመሪያ የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን ነጠላ ዜማ ለቅቄያለሁ፡፡ በመቀጠል ሶስት ነጠላ ዜማዎችን እለቅና ከዚያ በኋላ ታህሳስ ወር ላይ ሙሉ አልበሙ ይለቀቃል፡፡
“ታላቁ ፈተና” የተሰኘውን ነጠላ ዜማ በለቀቅህ ጊዜ የዘፈኑ መነሻ አባባ ጃንሆይ እ.ኤ.አ በ1963 በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ጀኔቫ ውስጥ ያደረጉት ንግግር እንደሆነ ገልፀህ ነበር…
ልክ ነው፡፡ አባባ ጃንሆይ ዓለምን ትልቅ ፈተና እንደገጠማት፣ በፍቅር መኖር ሰላምና አብሮነት እየጠፋ፣ የሰው ልጅ ፈተና ውስጥ መውደቁን ተናግረው ነበር፡፡ መነሻው ያ ንግግር ነው፤ እሳቸው ኢትዮጵያ የራሷ ባህል፣ ፈሪሀ እግዚአብሄር፣ መዋደድና መፋቀር ያላት አገር እንደሆነች በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ እኔም እዚህ ላይ አፅንኦት ሰጥቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ዋናው ስራዬ በሙያዬ ፍቅርና አንድነትን መስበክ ነው ብዬሻለሁ፡፡
በእሳቸው ንግግር መነሻነት ቦብ ማርሌይም ያቀነቀነ ይመስለኛል፡፡ ያንተ በምን ይለያል?
ትክክል ነው፤ ቦብ በዚህ ላይ መዝፈኑን አስታውሳለሁ፡፡ እሱ የቆዳ ቀለም፣ የአይን ቀለም… ልዩነት የአለምን ህዝብ መለያየት የለበትም፤ ሁሉም የአለም ህዝብ እኩል ነው… የሚለውን ነው ማስተላለፍ የፈለገው፡፡ የእኔም ከዚህ ብዙ አይለይም፡፡ አሁንም ታላቅ ፈተና የሆነው ይኸው በዘር፣ በቆዳ ቀለም መከፋፈል… የሰው ልጅ አንድነትን ያለመቀበል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ እግዚአብሄርን በማመንና በእግዚአብሄር ፍቅር ውስጥ ሊፈታ የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ልቡን ወደ ፈጣሪ በማዞር፣ እርስ በእርስ መዋደድ እንዳለበት ነው ጃንሆይ በአፅንኦት የተናገሩት፡፡ እኔም በዚህ ላይ ነው ያተኮርኩት፡፡ ትንሽ ልዩነት ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ አባባ ጃንሆይ በንግግራቸው መጨረሻ፤ “ልባችሁን ክፈቱና ሌሎችን በፍቅር ተቀበሉ፤ ያን ጊዜ ታላቁ ፈተና ያበቃል” ነበር ያሉት፡፡
ባለፈው ወር የአልበምህን መምጣት ለማስተዋወቅና “ታላቁ ፈተና” የተሰኘ ነጠላ ዜማህን ለማስመረቅ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ኮንሰርት አዘጋጅተህ ነበር፡፡ የታዳሚው አቀባበል እንዴት ነበር?
በኮንሰርቱ ያገኘሁት ምላሽና የሰዎች አስተያየት ከጠበቅሁት በላይ አሪፍ ነበር፡፡ አልበሜ ውጤታማ እንደሚሆን አመላካች ኮንሰርት ነው፡፡
ከኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ጋር የመስራት እድል ገጥሞሃል?
ኦ…ው በጣም በጣም ከብዙዎች ጋር ሰርቼአለሁ፡፡
ለምሳሌ …?
ለምሳሌ ከፀሃዬ ዮሐንስ ጋር ሰርቻለሁ፤ “ሳቂልኝ ሳቂልኝ” የሚለውን ዘፈኑን ካስታወስሽ “ቆንጅዬ ደህና ነሽ” እያልኩኝ ፊቸሪንግ ሰርቻለሁ፡፡ መድረክ ላይ ከጆኒ ራጋ (ዮሐንስ በቀለ) እንዲሁም ከሃይሌ ሩት ጋር ሰርቻለሁ፡፡
ከብዙ ዓመታት በፊት ከቴዲ አፍሮ ጋር ሻሸመኔ ውስጥ አብረን ሰርተናል፡፡ በሻሸመኔ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚማሩበትና እኛ የምንረዳው ት/ቤት አለ፡፡ “ጃማይካ ራስተፈሪያን ደቨሎፕመንት ኮሚዩኒቲ” የሚባል ት/ቤት ነው፤ ወደ 800 ያህል ተማሪዎች አሉት፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በትምህርታቸው መቶ በመቶ ውጤታማ ናቸው፡፡
 በጥሩ ሁኔታ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፤ ሻሸመኔ ብትሄጂ ብዙዎቹ ወጣቶች በትክክልና በአጥጋቢ ሁኔታ እንግሊዝኛ ይናገራሉ፡፡ ሌላው አካባቢ ይሄንን አታይም፡፡ ለማንኛውም እኔና ቴዲ አፍሮ በጋራ ኮንሰርት አዘጋጅተን፤ ለዚህ ት/ቤት አቅርበናል፡፡ ከጋሽ መሐሙድና ከሌሎችም ትልልቅ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ክብርና ደስታ ይሰማኛል፡፡
እስቲ ኢምፔሪያል ማጀስቲክ ስለተባለው የሙዚቃ ባንድህ ንገረኝ…
ኢምፔሪያል ማጀስቲክ ባንድ ከተለያየ አለም በተውጣጡ ሙዚቀኖች የተዋቀረ ባንድ ነው፡፡ አብዛኞቻችን የተገናኘነው ሻሸመኔ በተደረገ የራስተፈሪያን ኮሚዩኒቲ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ መጀመሪያ እኔ፣ ጁዳ፣ አልተን፣ ዛብሌን የተባልን ሰዎች ነን ያቋቋምነው፡፡
ዋና ዋናዎቹ የባንዱ ሰዎች እኛ ነን፡፡ ከዛ በፊት ሌሎችም ሰዎች ነበሩ፤ ግን በቋሚነት ባንዱ ውስጥ የሚሰሩ አልነበሩም፡፡
ስንት አይነት የሬጌ ስልቶች አሉ?
አር ኤንድ ቢ ሬጌ አለ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጪ አንቺ ሆዬ፣ ባቲ፣ ትዝታ፣ አምባሰል ስልት ሬጌዎች አሉ፡፡ “ታላቁ ፈተና” የተሰኘው አልበሜም በነዚህ አራት የሙዚቃ ስኬሎች የተሰራ ነው፡፡
በአልበሜ ትዝታ ማይነር አንቺሆዬ፣ ባቲ ማይነር ተካተውበታል፡፡ ከበሮና ዋሽንትንም በተለያዩ ሙዚቃዎች ውስጥ አስገብቻለሁ፡፡ የጃማይካ ሬጌ ላይ ደግሞ ድራምና የሬጌን ስሜት የሚፈጥሩ መሳሪያዎችን አካትቻለሁ፡፡
በአልበሙ ላይ አማርኛ ዘፈኖች የሉህም?
“Ethiopia is calling” የተባለው የመጀመሪያ አልበሜ ላይ ሁለት የአማርኛ ዘፈኖች ነበሩ፡፡  “ስላሴ የነፍስ ዋሴ” እና “ኢትዮጵያ የኔ መመኪያ” የተሰኙ እንደውም “ስሜን የማታውቁ ካላችሁ፣ ሲዲኒ ሳልማን እባላለሁ ልንገራችሁ” እያልኩ ነው የዘፈንኩት፡፡
በአሁኑ አልበሜ ላይ አማርኛና እንግሊዝኛ እየደባለቅሁ እንጂ ብቻውን አማርኛ አልዘፈንኩም፡፡ ወደፊት ሙሉ በሙሉ የአማርኛ አልበም አወጣለሁ፡፡ ምክንያቱም የአማርኛ ቋንቋ ችሎታዬ እያደገ ነው፡፡ እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል አይደለም የሚባለው... (በሚያስቅ አማርኛ)፡፡
ከኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በጣም የምትወደው ምንድን ነው?
ለእኔ አንደኛ ዶሮ ወጥ ነው፤ ሽሮም ነፍሴ ነው፤ አልጫና ጥብስም እወዳለሁ፡፡ ዶሮና ሽሮ ወጥ ግን ለእኔ በጣም ተወዳጅ ምግቦች ናቸው፡፡
ሻሸመኔ የሚገኘው “Twelve Tribes of Israel” የተባለው ድርጅታችሁ አሁንም አለ?
አለ፡፡ እኔ በ2001 እ..ኤ ሀምሌ ነው ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣሁት፡፡ የመጣሁትም ይሄ ድርጅት ጋብዞኝ ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ለመኖር አፈልግ ሰለነበር በድርጅቱ ግብዣ ሀምሌና ነሐሴን እዚህ ቆይቼ ሁሉንም ነገር ካጠናሁ በኋላ መስከረም ላይ የሆነ ፕሮግራም ስለነበረኝ ለንደን ሄጄ፣ ከዚያ ወደ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ነው ጠቅልዬ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት፡፡
 “ትዌልቭ ትራይብስ ኦፍ እስራኤል” በእየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ራስ ተፈሪያን ያቋቋሙት የእምነት ድርጅት ነው፡፡ አሁንም አለ፡፡
አሁን የት ነው የምትኖረው?
እዚሁ አዲስ አበባ ሰሚት ነው የምኖረው፡፡ ሻሸመኔ መኖሪያ ቤት ሰርቻለሁ፤ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡ ሻሸመኔ አለ ያልኩሽ “ጃማይካ ራስተፈሪያን ዴቭሎፕመንት ኮሙዩኒቲ” ት/ቤት ውስጥም አልፎ አልፎ አስተምራለሁ፡፡
    በገቢ በኩል ይሄም ያግዘኛል፡፡ ሚስቴ ጐበዝ ሰራተኛ ናት፤ በጣም ደስተኛ ህይወት እየኖርኩኝ ነው፡፡    

Saturday, 24 October 2015 10:09

የዝነኞች ጥግ

(ስለ ኢንተርኔት)

- ኢንተርኔትን በተመለከተ አንድ ትልቅ
ችግር አለብኝ፡፡ ይኸውም በውሸታሞች
የተሞላ መሆኑ ነው፡፡
ጆን ላይዶን
- የማስታወቂያ የወደፊት እጣ ፈንታ
በኢንተርኔት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ቢል ጌትስ
- ዛሬ እርሻ የተለየ መልክ ይዟል -
ገበሬዎቻችን GPS እየተጠቀሙ ነው፡
፡ የመስኖ ሥራችሁን በኢንተርኔት
መቆጣጠር ትችላላችሁ፡፡
ዴቢ ስታብናው
- ሰዎች ስለግል ህይወታቸው ለማውራት
በጣም ፈቃደኞች አይደሉም፤ ወደ
ኢንተርኔት ስትመጡ ግን የበዛ
ግልፅነታቸውን ታያላችሁ፡፡
ፓውሎ ኮልሆ
- ኢንተርኔት ለሰው ልጅ ብዙ ያልተነገሩ
ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡ ከኢንተርኔት ብዙ
ለመጠቀም ከፈለግን እንደራሳችን ሃብት
ልንቆጥረው ይገባል፡፡
ሚሼል ቤከር
- የመጨረሻ ቃል፡- ስለ ኢንተርኔት ዕውቀት
የለኝም፡፡ ኮምፒዩተር የለኝም፡፡ በ74
ዓመት ዕድሜዮ እሱን የመማር ትዕግስት
አይኖረኝም፡፡
ዴቪድ ዊልከርሰን
- ሰዎች ኢንተርኔት ላይ በሚያጠፉት የጊዜ
መጠን እገረማለሁ፡፡
ጄ.ኤል.ፓከር
- ኢንተርኔትን እፈራ ነበር፤ ለምን? ቢሉ
መተየብ አልችልም ነበር፡፡
ጃክ ዌልሽ
- ኢንተርኔትን ልታምኑት አትችሉም፡፡
ኒኮሌቴ ሼሪዳን
- ኢንተርኔት አገራዊ ድንበር የሚባል ነገር
አያውቅም፡፡
ኢላን ዴርሾዊትዝ
- በአሁኑ ጊዜ እንግሊዝኛ መናገር የማይችልና
ኢንተርኔት መጠቀም የማይችል ሰው እንደ
ኋላቀር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
አል - ዋሊድ ቢን ታላል
የዝነኞች ጥግ

እኛንም የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል




 

Saturday, 24 October 2015 10:05

የፀሐፍት ጥግ

• የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ስለ ሳንባ
ነቀርሳ በፃፍኩት ድርሰት ተሸልሜአለሁ፡፡
ወጉን ጽፌ ሳጠናቅቅ በሽታው
እንደነበረብኝ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
ኮንስታንስ ቤከር ሞትሌይ
• በፅሁፌ ውስጥ ብዙ የወግ አላባውያንን
ለመጨመር እሞክራለሁ፡፡
ራይስዛርድ ካፑስቺኒስኪ
• የእኔ ጉብዝና መጽሐፍ አንብቦ ሂሳዊ
መጣጥፍ መፃፍ ላይ ነው፡፡
ሪቨርስ ኩኦም
• ወግ ነፍሴ ነው፡፡ ልሰራበት የምወደው
ዘውግም ነው፡፡
ሜግሃን ዳዩም
• በ1980 ዓ.ም የ11ኛ ዓመት ልደቴን
ከማክበሬ ጥቂት ቀደም ብሎ የመጀመሪያ
ወጌን በእንግሊዝኛ ፃፍኩኝ፡፡
ፓንካጅ ሚሽራ
• አዕምሮዬን ለማጽዳት ወግ እጽፋለሁ፡፡
ልቤን ለመክፈት ልብወለድ እጽፋለሁ፡፡
ታዪዬ ሴላሲ
• የምፅፋቸውን የግል ወጐች በተመለከተ
ማንም እንደማያነባቸው ራሴን
አሳምኘዋለሁ፡፡
ዳኒ ሻፒሮ
• አብዮት የእራት ግብዣ ወይም ወግ
መፃፍ ወይም ስዕል መሳል አሊያም ጥልፍ
መጥለፍ አይደለም፡፡
ማኦ ዜዶንግ
• ልብወለድ መፃፍ አይመቸኝም ነበር፡፡
እኔ የምወደው ከረዥም ልብወለድ ይልቅ
የግል ወጐችን ነበር፡፡
አላይን ዲቦ ቶን
• የወግ ዋናው ነገር ሁኔታዎችን መለወጥ
ነው፡፡
ኢድዋርድ ቱፍቴ
• ወጐችን ወይም ፅንሰ ሃሳብ መፃፍ
አልወድም፡፡
አድሪያን ሚሼል


Saturday, 24 October 2015 10:04

የመንግሥት ጥግ

 ሥራ ለመፍጠር የግሉ ሴክተር ያስፈልገናል፡
፡ መንግስት ሥራ መፍጠር የሚችል ቢሆን
ኖሮ ኮሙኒዝም በተሳካለት ነበር፡፡ ግን
አልሆነለትም፡፡
ቲም ስኮት
- የቅርቡን ብቻ ማሰብ የመልካም መንግስት
ትልቁ ጠላቱ ነው፡፡
አንቶኒ አልባኔዜ
- መንግሥት ማለት እኛ ነን፤ እናንተና እኔ፡፡
ቴዎዶር ሩስቬልት
- ዲሞክራሲ ለእያንዳንዱ ሰው የራሱ ጨቋኝ
የመሆን መብት ያጎናፅፈዋል፡፡
ጄምስ ረስል ሎዌል
- ሰዎች መላእክት ቢሆኑ ኖሮ መንግስት
የሚባል አያስፈልግም ነበር፡፡
ጄምስ ማዲሰን
- ገንዘብ ሊገዛው የሚችል ምርጥ መንግስት
አለን፡፡
ማርክ ትዌይን
- ዓለም ህግ በማውጣት አትድንም፡፡
ዊሊያም ሆዋርድ
- መንግስት ምርት ቢሆን ኖሮ፣ እሱን መሸጥ
ህገወጥ ይሆን ነበር፡፡
ፒ.ጄ. ኦ‘ሮዩርኬ
- እያንዳንዱ አገር የሚገባውን መንግስት
ያገኛል፡፡
ጆሴፍ ዲ ማይስትሬ
- መንግስት የሰሃራ በረሃን እንዲያስተዳድር
ኃላፊነት ቢሰጠው፣ በ5 ዓመት ውስጥ የአሸዋ
እጥረት ይፈጠር ነበር፡፡
ሚልተን ፍራይድማን  

Saturday, 24 October 2015 10:01

የዘላለም ጥግ

ስለ እውነት)
- ሦስት ነገሮች ለረዥም ጊዜ ተደብቀው ሊቆዩ
አይችሉም፡- ፀሐይ፣ ጨረቃና እውነት፡፡
ቡድሃ
- በጥበብ መፅሀፍ ውስጥ የመጀመሪያው
ምዕራፍ ሃቅ ነው፡፡
ቶማስ ጀፈርሰን
- ዓለም ሁሉ ውሸት በሚናገርበት ወቅት፣
እውነት መናገር አብዮታዊ ተግባር ነው፡፡
ጆርጅ ኦርዌል
- እውነቱን የምትናገር ከሆነ ምንም ነገር
ማስታወስ አይኖርብህም፡፡
ማርክ ትዌይን
- በመጠራጠር ወደ ጥያቄ እናመራለን፤
በመጠየቅ እውነቱ ላይ እንደርሳለን፡፡
ፒተር አቤላርድ
- የሙጥኝ ብሎ የማይለቅ ብቸኛ እውነት
ክህደት ነው፡፡
አርተር ሚለር
- ትክክለኛውን ነገር ለመስራት ከፈለግህ
እውነቱን እወቅ፡፡
ቶማስ ሁክስሌይ
- እውነት ያለ ነገር ነው፤ የሚፈጠሩት ውሸቶች
ብቻ ናቸው፡፡
ጆርጅስ ብራኪው
- ከሚጠቅም ውሸት ይልቅ የሚጎዳ እውነት
ይሻላል፡፡
ቶማስ ማን
- ጥርጣሬ ሲገባህ እውነቱን ተናገር፡፡
ማርክ ትዌይን
- ብርሃን የእውነት ተምሳሌት ነው፡፡
ጄምስ ረስል ሎዌል
- እውነት በአንድ ሺ የተለያዩ መንገዶች ሊገለፅ
ይችላል፤ ሁሉም ግን እውነት ናቸው፡፡
ስዋሚ ቪቬካናንዳ
- ከፍቅር፣ ከገንዘብና ከዝና ይልቅ እውነትን
ብትሰጡኝ እመርጣለሁ፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶሪዩ
- ለህፃናት እውነት እውነቱን ንገሯቸው፡፡
ቦብ ማርሌይ
- ነፍስን የሚያረካ ነገር ቢኖር እውነት ብቻ
ነው፡፡
ዋልት ዊትማን

ወደ ጋምቤላ ሲጓዝ የነበረ ሌላ አውሮፕላንም ጎማው በመውለቁ ተመልሶ ማረፉ ተነግሯል

ትላንት ማለዳ ከአየርላንድ ደብሊን አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ዋሽንግተን በመብረር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET500 ቦይንግ 787-800 አውሮፕላን በግራ ሞተሩ ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ብልሽት ጉዞውን አቋርጦ ወደ መነሻው መመለሱንና ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ማረፉን አየርመንገዱ አስታወቀ፡፡
የቴክኒክ ብልሽቱን ሰበብ ለማወቅ በአየርመንገዱ የቴክኒክ ባለሙያዎችና በጂኢ ኢንጂነርስ ባለሞያዎች ትብብር ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝም የጠቆመው አየር መንገዱ፤ አውሮፕላኑ ተቀይሮ ጉዞው ወደ ዋሽንግተን መቀጠሉን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ጉዞው በመስተጓጎሉ ሳቢያ በመንገደኞች ላይ ለተፈጠረው መንገላታትም ይቅርታ ጠይቋል፡፡
አይሪሽ ሚረር በበኩሉ፤ አውሮፕላኑ ከደብሊን አውሮፕላን ጣቢያ ተነስቶ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ከተጓዘ በኋላ በገጠመው የቴክኒክ ብልሽት ሳቢያ አንደኛው ሞተሩ ጠፍቷል መባሉን ጠቁሞ፣ ከ300 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ እንደነበርም ትናንት ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ ባለፈው ሰኞ በበረራ ቁጥር ET -150 ከቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ተነስቶ ወደ ጋምቤላ በመብረር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦምባርዲየር Q-400 አውሮፕላን፤ አንደኛው ጎማው ወልቆ በመውደቁ ሳቢያ ተመልሶ ለማረፍ መገደዱን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 55 መንገደኞችና 4 የበረራ ቡድን አባላት ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡  

የ300 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተበይኖበታል

የ“ሎሚ” መፅሄት አሳታሚ የነበረው ዳዲሞስ ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ኃላ/የተ/የግል ማህበር እና ስራ አስኪያጁ አቶ ግዛው ታዬ፤ ከ800 ሺህ ብር በላይ ታክስ በማጭበርበርና በሌሎች ተያያዥ 14 ክሶች፣ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ በይኖበት፣ የ18 ዓመት ፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡
ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ ግዛው ታዬ፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ክሱ እስከተመሰረተበት ጊዜ ድረስ ለ5 ዓመታት ሂሳቡ ኦዲት አልተደረገም የሚለው የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፤ ሁለቱም ተከሳሾች የተለያዩ የታክስ ማጭበርበሮችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል ይላል፡፡
 የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰወርም ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ መንግስትን ከ800 ሺህ ብር በላይ ማሳጣታቸውን የክስ መዝገቡ ይገልፃል፡፡
ተከሳሽ በሚያሳትመው “ሎሚ” መፅሄት፤ ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳትና ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ወንጀል ተከሶ በ50 ሺህ ብር ዋስ ከተለቀቀ በኋላ መሰወሩ የተጠቀሰ ሲሆን ይሄኛውም የፍርድ ሂደት ተከሳሹ በሌለበት እንደታየ ታውቋል፡፡
ተከሳሽ በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ክስ በአካል ቀርቦ መከላከል ባለመቻሉም፣ ፍ/ቤቱ በሌለበት የ18 ዓመት እስርና የ100ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ያስተዳድረው በነበረው ድርጅት ላይ የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

• በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም በብዙኃን መገናኛ ስለሚተላለፉ ትምህርቶች ይወስናል

   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀጣይ ህልውና እየተፈታተኑና የምእመናኗን ፍልሰት እያባባሱ ናቸው በተባሉ፤ የ“ተሐድሶ ኑፋቄ” እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተገለጸ፡፡የቅዱስ ሲኖዶሱ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት የተጀመረ ሲሆን በምልአተ ጉባኤ የተሠየመው አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በቀረፃቸውና በምልአተ ጉባኤው በጸደቁ የመነጋገርያ ነጥቦች ለቀናት እንደሚመክር ታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ያካተተውና ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን የያዘው አርቃቂ ኮሚቴ፣ ለምልአተ ጉባኤው ካቀረባቸው ከ15 ያላነሱ አጀንዳዎች መካከል፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሰርገው በመግባት  አስተምህሮዋን፣ ሥርዐቷንና ትውፊቷን ውስጥ ለውስጥ በመበረዝ ጉዳት አስከትለዋል የተባሉ  “የተሐድሶ ኑፋቄ” አራማጆች ጉዳይ አንዱ ሲሆን የእንቅስቃሴውን ችግር የተመለከቱ ጥናቶችና መረጃዎች በጥልቀት ይፈተሹበታል፤ ተብሏል፡ከቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ቀደም ብሎ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ የተካሔደው የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ ባወጣው መግለጫ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተወገዘውን “የተሐድሶ ኑፋቄ”ን ተጽዕኖ ለመቋቋምና የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት በቂና መጠነ ሰፊ በሆነ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምእመናንን በእምነታቸው ለማጽናት የጋራ አቋም ይዟል፤ ለተፈጻሚነቱም በልዩ ልዩ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች የሚያስተምሩ መምህራንን በጥራትና በቁጥር ማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቱን ዘመኑ በሚፈቅዳቸው ሚዲያዎች በመታገዝ ለመላው ዓለም ማዳረስ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሚዲያዎቹ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራስዋን ድምፅ የምታሰማባቸውና ማዕከላዊነታቸውን የጠበቁ መሆን እንደሚገባቸው በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱም በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በመተላለፍ ላይ ስለሚገኙ ትምህርቶች ከምእመናን ሲቀርቡ የቆዩ አቤቱታዎችን በአጀንዳው በማካተት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተጠቁሟል፡፡የ“ተሐድሶ ኑፋቄ” አራማጆች፣ አስተምህሮዋን ከመፃረር ባሻገር በአንዳንድ የሀገር ውስጥና የውጭ አካባቢዎች፣ ማዕከላዊውን አስተዳደሯን የሚፈታተን “ገለልተኛ አስተዳደር” በመፍጠር ምእመናኗን እያደናገሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና ለችግሩ አስተዋፅኦ እንዳለው በጋራ አቋሙ የገለጸው አጠቃላይ ጉባኤው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ህልውና ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ መዋቅሯን የሚያጠናከርና የሕግን የበላይነት የሚያረጋግጥ አስቸኳይ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል ተብሏል፡፡ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን በወሳኝ መልኩ በመቅረፍ አደረጃጀቷና አሠራሯ ዘመኑን በሚዋጅ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የአሳታፊነት መርሕ ላይ ለመመሥረት ያስችላሉ የተባሉ ዐበይት ውሳኔዎች በቅዱስ ሲኖዶሱ ሲተላለፉ ቢቆዩም ተግባራዊነታቸው የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ተነግሯል፡፡ ያልተተገበሩ ውሳኔዎቹን በዝርዝር ይገመግማል የተባለው ምልአተ ጉባኤው፣ ተፈጻሚነታቸውን በመከታተል መዋቅራዊ ለውጡን የሚያረጋግጥ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊያቋቋም እንደሚችልና በቀጣይነትም ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር የሚያጠና ኮሚቴ እንደሚሠይም ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጾች የተመለከቱ ደንቦችን በተጣጣመ መልኩ የሚያወጣ አካል እንደሚሠየም የተጠቀሰ ሲሆን የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው የአዲስ አበባ ልዩ መተዳደርያ ደንብና ከባድ ቀውስ ፈጥረዋል የተባሉት የአስተዳደር ችግሮቹ በአጀንዳነት አብሮ እንደሚታይ ተገልጧል፡፡