Administrator

Administrator

በአማራ ክልል በከባድ መሳሪያ በታገዘ ጥቃት ንፁሃን መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

  ሁሉም ወገኖች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል


  በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና በታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ መንግስት እያካሄደ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን ተፅዕኖ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል፡፡
ከህግ ማስከበሩ ዘመቻ ጋር በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎና በሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና በታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ያመለከተው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት፣ አንፆኪያ ገምዛ፣ ማጀቴና አርማኒያ አካባቢ በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መፈፀሙንና በዚህም ሳቢያ በሲቪል ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክቷል፡፡
ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት መዘጋቱን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ በክልሉ ያሉ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት የክልል ልዩ ሃይሎችን እንደገና የማዋቀሩን ውሳኔ በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን መርተዋል አስተባብረዋል የተባሉ ወጣቶችና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት ለሲቪል ሰዎች ላይ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ጉዳት አድርሷል ያለው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ችግሩን በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱና ግጭቶችን ከሚያባብሱ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አድርጓል፡፡
በአካባቢዎቹ ስለተፈፀሙ ጥቃቶችና ስላደረሱት ጉዳቶች መንግስት አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥና በማንኛውም ሁኔታ የሚፈፀሙ እስራቶች ህግን መሰረት ያደረጉና ከአድልዎ ነፃ መሆናቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡


“ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት አሽቆልቁላለች”

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባለፈው ረቡዕ በተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልትና እስር አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት አደጋ ውስጥ መውደቁን የጠቆሙት ዶ/ር ዳንኤል፤ በዚህ ወቅት ቢያንስ 8 ጋዜጠኞች እስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ም/ቤት ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መሰረት እንዲኖረው፣ መንግሥት፣ ህገ-መንግስታዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።የሚዲያ ነፃነት ለሰብአዊ መብቶች መከበር መሰረት መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ከአራት ዓመት በፊት የታየው የነፃነት ዝንባሌ በሂደት አደገኛ ወደሆነ ሁኔታ መለወጡን አመልክተዋ፡፡ “በወቅቱ የታየውን የሚዲያ ነፃነት ዝንባሌ ተከትሎ የተሻሻለው የሚዲያ አዋጅ ትልቅ ለውጥ የታየበት ቢሆንም በርካታ ክፍተቶች ታይተዋል” ብለዋል- ኮሚሽነሩ።የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ባለፈው ረቡዕ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በመላው ዓለ ም የተከበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤትም ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ማክበሩ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2022 የሚዲያ ነፃነት ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበታል ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በመላው አገሪቱ ቢያንስ 29 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው እንደነበር አስታውሷል።
ባለፈው ረቡዕ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለማስታወስ ከደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ተቋም ጋር መግለጫ የወጣው አነስቲ፤ በዚያው ዓመት የትግራይ ባለስልጣናት አምስት ጋዜጠኞችን “ከጠላት ጋር በመተባበር” በሚል መክሰሳቸውን አንስቷል።
በመላው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሚገኙ ባለስልጣናት፣ የሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባዎችን ለማፈን ሲሉ በጋዜጠኞችና በፕሬስ ነፃነት ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ተባብሰዋል ብሏል- መግለጫው።ይህ በእንዲህ እንዳለ “ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደር” በቅርቡ ባወጣው የፕሬስ ነጻነት መጠቆሚያ ኢንዴክስ መሰረት፤ በኢትዮ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ነው የተመለከተው።ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም በፕሬስ ነፃነት ኢንዴክስ፣ ከ180 አገራት 114ኛ ደረጃ ላይ የነበረች ሲሆን በ2023 ዓ.ም 130ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠችው- ከ180 አገራት።

እናት ባንክ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበትና ዳጎስ ያለ ሽልማት የሚያስገኝ “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ይህን ያስታወቀው ሀሙስ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ስለ እናቱ የሚሰማውን ስሜት በA4 መጠን ወረቀት ከ3 ገፅ ባልበለጠና ባላነስ ፅፎ መወዳደር ይችላል ተብሏል፡፡
በፅሁፍ ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ ክብር፣ አክብሮትና ውለታ ግጥም ባልሆነ ነገር ግን በወግ፣ በደብዳቤ ቅርፅ የሚገልፅበትና ለእናቴ የሚልበት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን የባንኩ የማርኬቲንግ ፕሮሞሽንን የደንበኛ አገልግሎት ዳይሬክተር ወ/ሮ አክሊል ግርማ ተናግረዋ፡፡የመወዳደሪያ መስፈርቱና የውድድሩ ዳኝነት በቋንቋና በፅሁፍ ተግባቦት ሰፊ ልምድ ባላቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች የተዘጋጀና የሚከናወን እንደሆነም ሀላፊዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የፎክሎር ባለሙያና መምህር ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር) እና ደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎሮስ ተ/አረጋይ በአማካሪነት የሚሳተፉበት ይሄው “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር፤ ለጊዜው በአገሪቱ የስራ ቋንቋ በአማርኛ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎች 50 በመቶ የቅርፅ ጉዳዮች፣ 50 በመቶ ደግሞ የይዘት ጉዮች በድምሩ 100 ነጥብ እንዲይዙ ተደርገው መዘጋጀታቸውም  ታውቋል፡፡
ተወዳዳሪዎች ለውድድር የሚያቀርቡት ፅሁፍ ከዚህ ቀደም በሌሎች የህትመት እና ኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ያልቀረቡ ወጥ እና አዲስ መሆን ያለበት ሲሆን ፅሁፍ ግልጽና ተነባቢ እንዲሆን በኮምፒዩር ተተይቦ በ12 ፎንት የፊደላት መጠንና በ1.5 የህዳግ መስመር መቅረብ እንዳለበትም ተብራርቷል፡፡ በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች ስማቸውንና አድራሻቸውን ለውድድር በሚያቀርቡት ወረቀት ላይ መፃፍ እንደሌለባቸው የተገለጸ ሲሆን  ፅሁፉን አሸገው የሚያቀርቡበት ፓስታ ላይ ብቻ መፃፍ እንዳለባቸው ታውቋል የማስረከቢያ ጊዜው ከሚያዚያ 26 ቀን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ተወዳዳሪዎች የመወዳደሪያ ጽሁፋቸውን በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የእናት ባንክ ቅርንጫፍ በአካል ሄደው ማስገባት ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን በሁሉም አካባቢ እናት ባንክ ተደራሽ ባለመሆኑ Lenate @ enatbankssc.comየኢሜል አድራሻን በአማራጭነት መጠቀም ይቻላል ተብሏል፡፡ በውድድሩ ከ1-3 የወጡ አሸናፊዎች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት የሚበረከትላቸው ሲሆን አሸናፊዎች የሚሸለሙትን የገንዘብ መጠን የባንኩ ሃላፊዎች ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ አሸናፊ ፅሁፎችን ባንኩ ለተለያየ ጉዳይ ሊጠቀምባቸው ይችላል የተባለ ሲሆን ውድድሩ ማንኛውም እናቱን የሚወድ ሀሳቡን የሚገልፅበት እንጂ ፕሮፌሽናል የስነ ፅሁፍ ወድድር አለመሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪዎች በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
“ለእናቴ” የተሰኘው ይሄው ውድድር በየዓመቱ አይነቱን እየቀያየረ የባንኩ አንድ መለያ ሆኖ እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡ እናት ባንክ ማህበረሰቡ ከሚወዳደርበት በተጨማሪ የባንኩ ሰራተኞች ብቻ የሚወዳደሩበት መርሃ ግብርም እንደሚኖረው ተብራርቷል፡፡ እናት ባንክ በአሁኑ ወቅት ከብር ሁለት ቢሊዮን በላይ የተከፈለ ካፒታል ባለቤት ሲሆን ከ60 በመቶው በላይ ድርሻ የሴቶች መሆኑንና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች 137 ቅርንጫፎችን ከፍቶ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ ያብራሩት የባንኩ ሃላፊዎች፤ ባንኩ በተለይም ለሀገራችን ባለውለታ እንቁ ሴቶች በስማቸው ቅርንጫፍ እየከፈተ ስራውን መቀጠሉ ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡


ግዙፍ የካፒታል ኢንቨስትመንትና የዕድገት ማስፋፊያ  ዕቅዶችንም ይፋ አድርጓል

ጤና የምግብ ዘይት፣555 የጽዳት መጠበቂያ፣ ኦራ የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙና፣ሼፍ ሉካ ፓስታና አኳሴፍ የተፈጥሮ ማዕድን ውሃ የመሳሰሉ በርካታ ታዋቂ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች በማቅረብ የሚታወቀው 54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ. የቢዝነስ ግሩፕ፣ ስያሜውን ወደ ሳማኑ መቀየሩን አስታውቋል፡፡
የቢዝነስ ግሩፑ አዲሱን ስያሜውን ያበሰረው፣ ባለፈው ረቡዕ በሃያት ሬጀንሲ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ በዚህ መግለጫ፤ ግዙፍ የካፒታል ኢንቨስትመንትና የወደፊት የዕድገት ማስፋፊያ ዕቅዶችንምኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡ መግለጫውን  የሰጡት የ54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሚ/ር ጆአኪም ኢቡዌት፣ የኩባንያው  ማርኬቲንግ ማናጀር ወ/ሮ ዳርቻ መኮንንና  የኩባንያው ማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተር አቶ ኢዩኤል ሸዋንግዛው በጋራ በመሆን ነው፡፡
ኩባንያችን  ጥራታቸውን የጠበቁ የደንበኞች ምርቶችን በማቅረብ ይታወቃል ያሉት ግሩፕ ማርኬቲንግ ማናጀሯ ወ/ሮ ዳርቻ መኮንን፤ “ከምርት እስከ ገበታ ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚል መርህ ነው የምንከተለው” ብለዋል፡፡
“ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ማቅረብ ዋና ዓላማችን ነው” ሲሉም አክለዋል፤ወ/ሮ ዳርቻ መኮንን፡፡ ባለፉት ዓመታት ኩባንያቸው በስኬትና በዕድገት ጎዳና ላይ ሲጓዝ መዝለቁን የገለጹት ግሩፕ ማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተሩ አቶ ኢዩኤል ሸዋንግዛው በበኩላቸው፤ በእነዚህ ዓመታት የተደረጉ የፋብሪካና ማምረቻ ማስፋፊያዎች፣ የተገነቡ አዲስ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም ራሳቸው ማምረት የጀመሯቸው ለድርጅቱ የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ በቅርቡ ኖርፈንድ ከተባለው ታዳጊ አገሮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ የኖርዌይ ኢንቨስትመንት ፈንድ የ21 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ኢንቨስትመንት አዲስ የኤክስፖርት ፋብሪካ ለመገንባትና ከገበሬዎች ጋር በቀጥታ አብሮ በመሥራት የአግሮ ፕሮሰሲንግ አቅሙን ለማስፋት እንዲሁም  በኢትዮጵያ ለምግብነት የሚውል የዘይት ምርትን ለማሳደግ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡
 “በዚህ ኢንቨስትመንትና ተጨማሪ የንግድ ማስፋፊያ ዕቅዶች ምክንያት፣ 54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ  የኮርፖሬት ስያሜውን ወደ ሳማኑ መቀየሩን በደስታ ያበስራል” ብሏል፤ ኩባንያው  ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ፡፡ ‘ሳማኑ ፕራውድሊ ኢትዮጵያን - ሳማኑ በኩራት የኢትዮጵያውያን’ የሚል ነው አዲሱ ሙሉ ስያሜ፡፡ የሳማኑ አርማ መነሻ ተደርጎ የተወሰደው ከህይወት ምንጭ ‘አባይ ወንዝ’ እና ሣ ከሚለው የአማርኛ ፊደል መሆኑን የሚያብራራው መግለጫው፤ዲዛይኑ የሳማኑን ኢትዮጵያዊ መሰረት ለማጠናከር ያለመ ነው ይላል -ይህም ከፍተኛ ጥራት ያለው የፍጆታ እቃዎችን በማምረት ግንባር ቀደም ኢትዮጵያዊ በመሆን ለዕድገትና መስፋፋት ያለውን ጠኝካራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ በመግለጽ፡፡
የሳማኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚ/ር ጆአኪም ኢቡዌት በሰጡት መግለጫ፤ “ስለመጪው ጊዜ በጣም ደስተኞች ነን፤ ይህ አገሪቱ ያላትን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብትና ተሰጥኦ በመጠቀም የኢትዮጵያውያንን ህይወትና ኑሮ ለማሻሻል ራዕያችንን የምናጎለብትበት መንገድ ነው” ብለዋል፡፡
ከውጭ የተገኘውን ኢንቨስትመንትም በተመለከተ ሲናገሩ፤”አዲሱና ከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን ቆይታ በማጠናከር ለሰፋፊው የልማት መንገድ አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያግዘናል፡፡ ቀዳሚ ሂደቶችን ወደ ኋላ በማቀናጀት  የኢትዮጵያን ግብርና በሚያዳብርበት ወቅት የተዋቀረ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ለማምረት ያስችላል፡፡” በማለት አብራርተዋል፡፡“ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እያደረግንና የማምረት አቅማችንን እያሰፋን ባለንበት በዚህ ወቅት የኩባንያችንን ስያሜና ምልክት መቀየር ለድርጅታችን ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ “ግባችን በአገር ውስጥ የሚመረቱና የኢትዮጵያ ኩራት የሚሆኑ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ማቅረብ ነው” ብለዋል፡፡



የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በባሕር ዳር፣ በጅግጅጋ እና በሃዋሳ ከተሞች ያካሄደውን ግልጽ የምርመራ መድረክ (National Inquiry/Public Inquiry) ተከትሎ፣ በአዳማ ከተማ ከሚያዝያ 17 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አራተኛውን ግልጽ የምርመራ መድረክ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡
በመድረኩም በተለይ የዘፈቀደ እስርን፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስርና በእስር ወቅት ተከስተዋል ስለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎችና ምስክሮች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች እንዲሁም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተሰጡ ምላሾችን ማዳመጡ ተጠቁሟል፡፡
 ለአብነት ተመርጠው ከቀረቡት 18 አቤቱታዎች መካከል:- ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የታሰረን ሰው ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ የፍርድ ቤት የዋስትና መብት ትእዛዝ አለማክበር ይገኙበታል ተብሏል።
በተጨማሪም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጸዳጃና ሕክምና የማግኘት መብትን አለማክበርና ጭካኔ የተሞላበትና የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በቀረቡት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል እንደሚገኙበት ኮሚሽኑ አመልክቷል፡
የግልጽ ምርመራ መድረክ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ስልት መሆኑን ኢሰመኮ ጠቁሟል፡፡
“አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ መድረክ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፤ የሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባሕርይ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም ያካትታል፡፡” ብሏል፡፡
 ለግልጽ ምርመራው በኦሮሚያ ክልል ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር ወይም የምርመራና ክትትል ግኝቶች ያሏቸው አካላት ይህንኑ እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ፣ መቀመጫውን በውጭ ሀገር ያደረገ Oromo Legacy Leadership & Advocacy Association/OLLAA የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የየበኩላቸውን መረጃዎችና ትንተናዎች በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ማስገባታቸው የታወቀ ሲሆን፤ በግልጽ ምርመራ መድረኩም ላይ በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዋና ዋና ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል ተብሏል፡፡
ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተን ደርሰንበታል ያሉትን መረጃዎች በመድረኩ አቅርበው የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እንዲያውሉና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡
 “በኦሮሚያ ክልልና በተለያዩ ዞኖች በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽንና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ለቀረቡት አቤቱታዎችና ተፈጽመዋል ለተባሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም የፍትሕና  የጸጥታ ተቋማቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም ለመብት ጥሰቶቹ መነሻ ምክንያት የሆኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታም አስረድተዋል::” ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው፡፡በአዳማ ከተማ የተካሄደውን ግልጽ ምርመራ መድረክ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እና የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ መርተውታል፡፡
የዝግጅቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የመርማሪ ኮሚሽነሮች ሰብሳቢ ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ባደረጉት ንግግር፤ “በግልጽ የምርመራ መድረኩ ተጎጂዎች፣ ባለግዴታዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር መቻላቸው እንዲሁም ለወደፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በሁሉም አካላት በኩል ለመደጋገፍ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚያበረታታ ነው፡፡” ብለዋል፡፡


ግሪን ቴክ ፤ላለፉት ሦስት ወራት በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት  ያሰለጠናቸውን 25 ተማሪዎች ባለፈው ማክሰኞ ፣ ቃሊቲ ቶታል በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መ/ቤት አስመረቀ፡፡
25ቱ ተመራቂዎች  በዘርፉ የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ሲሆኑ ፤ሥልጠናው የተሰጠው ከኤስኦኤስ የህጻናት መንደር ጋር በመተባበር  ነው  ተብሏል፡፡
ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የግሪን ቴክ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ኢንጂነር ቅደም ተስፋዬ፤” በዘርፉ ተቀጣሪዎች ሳይሆን ሥራ ፈጣሪዎች እንድትሆኑ ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ሰልጣኞቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የአምስት ቀናት የሥራ ፈጣሪነት (entrepreneurship) ሥልጠና እንደሚሰጣቸውም ተነግሯል፡፡
በአገራችን  በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም እንደሌለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ያሁኖቹ ተመራቂዎች የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ናቸው ብለዋል፡፡በዕለቱ የተመረቁት ተማሪዎች በኤሌክትሪካልና መካኒካል ኢንጂነሪንግ በድግሪና በማስተርስ ድግሪ ደረጃ ትምህርት የወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ግሪን ቴክ በአጠቃላይ 300 ወጣቶችን በኤሌክትሪክ መኪና ቴክኒሽያንነት  ለማሰልጠን ያቀደ ሲሆን፤ 27 ወጣቶች በሥልጠና ሂደት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ግሪን ቴክ ኢትዮጵያ፤ በአገራችን የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆኑና ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጡ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክና በሶላር ቻርጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ይህ መጽሐፍ አማርኛ ምን ያህል ባለጸጋ እንደሆነ ፣ በአንጻሩ ሥነ-አመክንዮ አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ሥራ ነው :: በአማርኛ ቋንቋ ከተጻፉ ፣ ትውልድን ብዙ ከጠቀሙ አንጋፋ መጻሕፍት መካከል ይህ አንዱ ነው የሚል እምነት አለኝ :: "
ዓለሙ ፊጤ ( ዶክተር )
University Of Michigan America
ስለመጽሐፉ አስተያየት የሰጡ

 ሸበተ መሰለኝ!
               (በድሉ ዋቅጅራ)


        ሸበተ መሰለኝ፣ እውቀትም አረጀ፤
ጡት ተጣባውና፤
አበልጅ ሆኑና፤
ከድንቁርና ጋር፣ በወግ ተወዳጀ፡፡
ብርሃኑ ጠፋ፣ አይኑ ደነገዘ፤
መቅኒው በረዶ ሆነ፣ በቁሙ ፈዘዘ፡፡
ይኽው እውቀት ጃጅቶ፤
ከድንቁርና ላይ፣ በሊዝ ቦታ ገዝቶ፤
ጎጆ ቀለሰና፣ መስሎ ጎረቤቱን፤
ፀሐዩን ይሞቃል፣ እያሻሸ ሪዙን፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር!
‹‹የት ይደርሳል›› ስንል በወጣትነቱ፤
እዚህ እቅርባችን፣ ይኽው ተመልከቱ፤
እውቀት ተመፃድቆ፤
ማወቁን አድምቆ፤
ህፀፁን ደብቆ፤
ከድንቁርና ጋር፣ ከጠላቱ ታርቆ፡፡
ደባልነት ገባ፣ አብሮ ቤት ቀለሰ፤
አንዱ ሲገነባ፣ አንዱ እያፈረሰ፡፡
ውሃ እያፈሱ፤
ጤፍ እየቆጠሩ፤
ውሃ እየወቀጡ፤
ባንድ ተቀመጡ፡፡
ይብላኝ ለዚች ሀገር!
የሀገር ጥሪት ነጥፎ፤
የሕዝብ ሀብት ባክኖ፤
የእድሜ ሻማ ነዶ፤
ስልጣኔ ብሎ፤ ፈረንጅ ሀገር ሄዶ፤
ሩቅ… ባህር ማዶ፤
የተገኘን እውቀት፤
ወይም
እዚሁ ሀገር ውስጥ፣ ኮሌጅ ተኮልጆ፤
የተገኘው እውቀት፤
ይኽው ተመልከቱ…
ከውጭ ሲመለስ፣ ከኮሌጅ ሲወጣ፤
ቦቃ በግ ሰውቶ፤
ዛፍ ቂቤ ቀብቶ፤
ንፍሮውን በትኖ፣ እጣኑን አጢሶ፤
ይኽው ተመልሶ፣
ተንበርክኮ ሽቅብ፣ ቱፍታ ይቀበላል፤
መርፌውን ሰክቶ፤
ከድንቁርና ጋር እውቀት ይማማላል፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር!
እውቀትም እንደ ሰው፣
ያለ እድሜው አረጀ፤
ከጠላቱ ጋራ፣ በወግ ተወዳጀ፡፡
አያት ድንቁርና፣ ለምለም አስጨብጠው፤
ለጋ የጊደር ቂቤ፣ ግንባሩን ቀብተው፤
በአምሳላቸው ቀርጸው፣
አውራ ጣት አጠቡት፡፡
ልጃቸውም ሆነ፣ አባት አያት ሆኑት፡፡
ከዚያማ ጋለቡት፣
ሉጋም አበጅተው፣ ለህሊናው መግቻ፤
ለራዕዩ መቀጨት፣ ለህልማቸው መፍቻ፡፡
ለእኩይ እጣ ብሎት፣
 እውቀትም አርጅቶ፤
ይኸው ተመልከቱ፤ ደጅ ተጎልቶ፤
ከድንቁርና ጋር፣ እሳት እየሞቀ፣
እውቀት ተጃጅሎ፡፡
ለአድባር ይሰዋል፤
ለአውልያ ይሰግዳል፤
ያማል፣ ያማል፣ ያማል፣
እውቀት ተጃጅሎ፤
የኦክስፎርድ ዲግሪ፤
ያለማያን ካባ፣ ግርግዳው ላይ ሰቅሎ፡፡
ይብላኝ ለዚች ሀገር!
ይብላኝ ለኢትዮጵያ!
እውቀት ድንቁርና ለተወዳጁባት፣
አንዱ ሲገነባ፣ ሌላው ለሚንዳት፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር፡፡
(1989- ፍካት ናፋቂዎች)




 ቢዝነስ አዋቂው ዊሊያም ሪግሊ

                  ለ8.5 ሚ. አሜሪካውያን መስቲካ በነጻ አስቀምሷል
                     ዋሲሁን ተስፋዬ


       ዊሊየም ሪግሊ፤ በአሜሪካን ፔንስልቫንያ የተወለደና ፡  እስካሁንም በአለም ላይ ቁጥር አንድ ተሻጭ ማስቲካዎች መሀከል አንዱ የሆነው የሪግሊ  ባለቤት ነው ።
በልጅነቱ በአባቱ የሳሙና ፋብሪካ ውስጥ በትርፍ ጊዜው ይሰራ ነበር ፡ እድሜው 13 አመት ሲሞላ ደግሞ ፡ በአባቱ ኩባንያ የሚመረተውን ሳሙና እየተረከበ መሸጥ ጀመረ ። በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ አመታት እንደሰራ   በወቅቱ የነበሩትን የሳሙና ፋብሪካዎች በልጦ ለመገኘት አንድ ዘዴ ማሰብ ጀመረ ።
ይህ ዘዴ አነስ ያለ የቤኪንግ ፓውደር መስሪያ ማሽን በመግዛትና በማምረት ፡ የሱን ሳሙና ለሚገዙ ሰዎች ፡ አንድ ቤኪንግ ፓውደር በነጻ መስጠት ነው ።
 በዚህ መልኩ ሳሙናውን መሸጥ ሲጀምር፣ የሳሙናው ገበያ በሚገርም ሁኔታ ጨመረ ። ሆኖም  ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ፣ ሰዎች ሳሙናውን የሚገዙት በስጦታ መልክ፣ በነፃ ለሚያገኙት ቤኪንግ ፓውደር ሲሉ እንደሆነ አወቀ ።
ልክ ይህን እንደተረዳ፣ ወዲያውኑ ግዙፍ ማሽን ገዝቶ ፡ በሰው ዘንድ ተወዳጅ መሆን የጀመረውን የቤኪንግ ፓውደር ምርት በሰፊው ማቅረብ ጀመረ ።
በወቅቱ ቤኪንግ ፓውደር የሚያመርቱ ብዛት ያላቸው ካምፓኒዎች ስለነበሩም፣ የገበያ ፉክክሩን ለማሸነፍ ፡ ማስቲካ የሚያመርት ማሽን ገዝቶ፣ ቤኪንግ ፓውደር ለሚገዛ ሰው  አንድ ማስቲካ  መስጠት ሲጀምር. ..በነጻ ለሚሰጠው ሪግሊ ማስቲካ ሲባል፣ ቤኪንግ ፓውደሩ እንደ ጉድ መሸጥ ጀመረ ። ቢዝነስ አዋቂው ዊሊያም ሪግሊ ይህን እንደተረዳ። የቤኪንግ ፓውደር ማምረቱን በመተው፣ ሙሉ ለሙሉ ማስቲካ በማምረት ስራ ውስጥ ገባ። ምርቱ ተወዳጅ ሆኖ በመላው አሜሪካ ቆይቶም ፡ በመላው አለም ታዋቂ ብራንድ ሆነ።
እንግዲህ፤ ከላይ ባየነው አጋጣሚ ምክንያት የተፈጠረው ሪግሊ፣ ከአመታት በኋላ ዛሬ ላይ አመታዊ ሽያጩ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ አልፏል።
 ቢዝነስህን ወይም  ሥራህን አሻሽለህ ለመስራት ባሰብክ ቁጥር፣ ሥራህ  ወይም ቢዝነስህ  ያሻሽልሀል፡፡ .እዚህ ላይ ሳንጠቅስ የማናልፈው፣ ዊሊየም ሪግሊ፣ ይህን የማስቲካ ካምፓኒ ሲጀምር ፡ ማስቲካውን ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ዘዴ እስካሁንም ይወራለታል ።
 ይህ ሰው ማስቲካ ማምረቱን በሰፊው እንደጀመረ ሰሞን  ....ለ8.5 ሚሊዮን አሜሪካውያን ሪግሊ ማስቲካን እንዲቀምሱ በነጻ ልኮላቸው ነበር ። ይህ የማስተዋወቅ ዘዴውም  ውጤታማ የሆነው ወዲያውኑ ነበር ።

____________________________________________

                      እያረሩ መሳቅ--?

 
         “… በነዳጅ ማደያ ዙሪያ ያለው የመኪና ሰልፍ ያስደነግጣል። ወደ አንዱ ባለ መኪና ጠጋ አልኩና ጠየቅኩት...
“ምነው ነዳጅ የለም እንዴ?”
“ኧረ አለ”
“ታዲያ ይኼ ሁሉ ሰልፍ ምንድነው?”
“የነዳጅ  ቀጂው ስልክ ዘጋበት”
“ምን ዘጋበት?”
“የስልኩ ቻርጅ አለቀበት” ሳቄ ደርሶ ድቅን አለ።
ይኸውልህ እንግዲህ፣ ያልተጠና አሰራር እንዲህ ያለ ችግር ይፈጥራል። የነዳጅ ቀጂ ስልክ ቻርጅ ማለቅም እንቅስቃሴ ይገድባል?
(Jony Zewde በገፃቸው ካሰፈሩት)




        ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነሕ በመደመር አፍሪካ የስነ ጥበብ ስፍራ ታላቅ አውደ ርዕይ “Reflections on the I Ching በሚል  ርዕስ አዘጋጅቷል። ከ70 በላይ ስዕሎች ለህዝብ እይታ ይቀርባሉ ። ለስነጥበብ ስራዎቹ  “The Complete I Ching : The Definitive Translation by Taoist Master Alfred Huang” የተባለው መፅሐፍ  መነሻ ሆኗል።
ሰዓሊ ዳዊት መፅሐፉን በመጥቀስ እንደገለፀዉ፤ ኤግዚብሽኑ “የገነት፤ የመሬትና የሰው ልጅ ትልቅነት...ገነት፤ መሬትና የሰው ልጅ የሚግባቡበት አስተሳሰብ “ ይንፀባረቅበታል። ብሏል፡የሰዓሊ ዳዊት ሙሉነህ Reflections on the I Ching ታላቅ  አውደርዕይ፣  በመደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራ ሰኞ ሚያዝያ 23 ላይ በይፋ ተመርቆ በመከፈት፣ በቋሚነት ጎብኝዎችን የሚያስተናግድ ይሆናል። በስነጥበብ ስፍራው በሚገኘው የከተማችን ግዙፍ የስዕል አዳራሽ Yellow hall እና በአስደናቂው የስነጥበብ ዱንካን ubntu dome ከ70 በላይ ስዕሎች ይቀርባሉ ።ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነህ በስነጥበብ ሙያው ከ28 ዓመታት በላይ ሰርቷል።  አፈርን ቀለም ባደረገ ምርምርና ጥናትም ተሳክቶለታል። ለስዕል ስራዎቹ ከኢትዮጵያ የተሰበሰቡ አፈርና ድንጋይ ተፈጭተው ቀለማት ሆነዋል። ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹‹አለ የስነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት›› በግራፊክ አርት በ1987 ዓ.ም በዲግሪ የክብር ተመራቂ ነው፡፡
 በአዲስ አበባ ከተማ  የስዕል ስቱድዮዎችን በግል እና በቡድን መስርቶ በመንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡  ከ25 በላይ ኤግዚብሽኖችን  ለዕይታ አብቅቷል።



Page 6 of 647