
Administrator
ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ
እስቲ ስለ ሞት እናውጋ
አቈልቊዬ ፡ ባይ ፡ መሬቱን ፡
ቈስሎ ፡ አገኘሁት ፡ እግሬን ፡
ምን ፡ አሳዘነኝ ፡ ለእግሬ ፡ ቊስል ፡
ስሄድ ፡ እኖር ፡ ይመስል፡፡
(ከብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል
ሞት በስሙ ኗሪ ነው፡፡ ሶምሶን ሹሩባው ላይ ሀይል እንዳለው ሁሉ ሞትም ሀይሉ ስሙ ላይ ነው፡፡ ደህና ስም አጥፊ አጥቶ ይህ ሁሉ ዘመን ፋነነብን እንጂ፡፡ አንዳንድ ዘመን አለ ሞት ስሙ የሚገንበት፡፡ ሞት ስሙ ሲገን ለሞት የብልፅግና ወቅት ነው፡፡ ይሄንንም የኛን ዘመን የሞት የልምላሜ ዘመን ነው እላለሁ፡፡ ከተፈጥሮ ግብሩ በዘለለ በሰዎችና በተፈጥሮ ክስተቶች እየታገዘ ስሙን በየሜዳው የፃፈበት ለሰው የመከራ፣ ለሞት የተድላ ወቅት ነው፡፡ ሞትን መረሳት እንደሚገድለው እናምናለን፡፡ ምክንያቱም በስሙ ያለ ነዋ፡፡ ካልተጠራ ይሞታል፡፡
የዚህ ፅሑፍ አላማ፣ ሞት ቅጥራችንን እየዞረው ከሚኖር ከዚህ ዘመን ሰው ጋር፣ እንደው ሞታችን እርግጥ ቢሆን እንኳ፣ ሞትን እንዴት ባለ መንገድ ነው ማስተናገድ ያለብን የሚለው ላይ ለመምከር ነው፡፡ መቼም ከላይ የገባንባት መተከዣ መዲና ሳትገልጠን አትቀርም የሚል እምነት አለን፡፡አንድ እየተባለለት ነው አጥርም የሚወድቅ፣ እናም፣ እስኪ ሞትን ለመጣል ባንችል ለመነቅነቅ አንዳንድ ጉዳዮችን እንይ፡፡
ፈራና አሁንስ፣ ፈራን አቦ! ፈረንጆቹ አስቦኩን፡፡ እንዴት ያሉ ውለታ ቢሶች ሆነዋል አንተ፣ A living dog is better than a dead lion. ከሞትክ አትረባም ማለታቸው ነው አይደል? ቁርጣችንን ንገሩን እንጂ ጎበዝ! ይሄ በአንበሳ የሰማነው ጉዳይ ሰውም ላይ ይሰራ ይሆን? ከሞተው ሰውስ ድመቱ ትሻላለች፣ ቢያንስ ከአዋኪ አይጥ ታሳርፋለች ማለት ይሆን? ጉርብትናውስ? ፍቅሩስ? ፅዋውስ በአንድ ሽክና አፍ ገጥመን የጠጣነው? ሞት ሲመጣ ሁሉ ገለባ ነው ማለት ነው? በቃ በቃ ሁሉ እንዲሁ ባክኖ ቀሪ ነው? ይህ ማለት አንበሶቹ የታሪክ ጀግኖቻችን ውኃ በላቸው ማለት ነው? ወይስ ለነሱ ሲሆን የትርጉም ማሻሻያ እናደርጋለን? ኸረ ፈራን ጎበዝ! ኸረ የዚህን የሞት ነገር አንድ በለን ክንዴዋ!
አንድ!
ሞት የእግዜር እንግዳ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በስነ ፍጥረት ባህሪው እንግድነት ስላለበት በእንግዳ የሚጨክን አንጀት የለውም፡፡ (እንስሳት ምድር ላይ በመንፈላሰስ በአምስት ቀን ይቀድሙን የለም ወይ፣ ያ ማለትስ የእንስሳት ሀገር ሰው ነን ማለት አይደለም ወይ፣ ነው እንጂ ጎበዝ እየተማመንን)
አያ ሞት እንግዳ ነው ብለናል፡፡ በር ይቆምና ‹‹ የመሸበት የእግዜር እንግዳ ›› ይላል፡፡ አቤት ድምፁ እንዴት ያስፈራል፡፡ ፍርሃት ደግሞ ሞት የሚገባበት ቀዳዳ ነው፡፡ ሰው ይሄን ሲሰማ፣ አንድም በፍርሃት ሁለትም በብድር መላሽነት በር ይከፍታል፡፡ ሞት ይገባል፡፡ ሲገባ ያኔ የሞት እንግድነት ያበቃል፡፡ ምክንያቱም ዐይን ያወጣ ባለጌ ነዋ፡፡ ሰዎች ሆይ ሞትን ከደጅ መልሱት፡፡ በራፋችሁ ቆሞ ሲለምን እንዲህ በሉት፣
‹‹… ቦታውን ሁሉ ሕይወት ሞልቶታል፣ ለሞት የሚሆን ስርፋ የለም ››
ፃድቁ ላዖ ሱም ረቡዕ በሚፀለይ ውዳሴው ይህንኑ ነው ያለው (መቼም ስሙ ሲነሳበት እንዴት ብሽቅ እንደሚል፣ አያ ሞት)
‹‹… He who knows how to live can walk abroad
Without fear of rhinoceroses or tiger.
He will not be wounded in battle.
For in him rhinoceroses can find no place to thrust their horn,
Tigers no place to use their claws,
And weapons no place to pierce.
Why is this so?
ምክንያቱም፣ He has no place for death to enter. ››
ከበር የመለስነው ሞት፣ በር ገንጥዬ እገባለሁ ካለስ አንልም? ካለማ አንድም ዘራፍ ብሎ መነሳት አንድም ከነመኖሩ መርሳት፡፡ ዘራፉ ይቆየንና ከነመኖሩ መርሳት ይቻላል ወይ? የሚለውን እንይ፡፡ the denial of death ስልታዊ ማፈግፈግ ነው፡፡ ልክ ጲላጦስ እጁን ታጥቦ ኢየሱስን እንዳስገደለው ያለ፡፡ ለሞት ጀርባ መስጠት፡፡ እኔ ጋ አይደለም የመጣው አልያም እኔ የለሁበትም ብሎ ማለት፡፡
የሞትን ሕልውና አለማወቅ እና ሞትን መካድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እስኪ በተናጠል ለማየት እንሞክር፡፡ አንደኛ፣ ሞት ብሎ ነገር መኖሩን ጭርሹን አለማወቅን አስመልክቶ ፍሩውድ ያለውን እናንሳ፣ ፍሩውድ ያለው ይህን ነው፡፡
‹‹… እንዲያውም ልንገርህ፣ The conscious ጭርሹኑ does not know death or time, in man’s physiochemical, inner organic recesses he feels immortal. ››
ይህ ማለት፣ ደጅ ቆሞ ‹‹ ቤቶች ›› ሲል፡፡
‹‹ ማን ነው? ›› (ማለት፣ ተነስተህ ከመክፈትህ በፊት፡፡)
‹‹ እኔ ነኝ ›› (ስሙን አይናገርም? ሌባ)
‹‹ አንተ ማን ነህ? ስም የለህም? ›› (ጎበዝ! ደግ አደረግህ)
‹‹ ሞት ነኝ ››
‹‹ ሞት ምንድን ነው? አውሬ ነው? ሰው ነው? ካለዛሬም ስምህን ሰምቼው አላውቅ›› ብሎ ማለትን ይመስላል፡፡
ሞትን መካድ ላይ እንምጣ፣ ለዚህ ማሳያ ተመሳሳይ ምሳሌ እንጠቀም፡፡
ሞት ደጅ ይቆምና በር እየቀጠቀጠ ‹‹ቤቶች›› ሲል፡፡
‹‹እዚህ አይደለም የተንኳኳው፣ ጎረቤት ካለ ቤት ነው›› ብሎ በማሰብ ምንም እንደሌለበት ሰው ፊትን ወደ ግድግዳ መልሶ ለጥ ማለት፡፡ ሞትን የምንክደው መኖሩን ካወቅን በኋላ ነው፡፡ እዚህ ጋር ነው ከፍሩውድ ጋር ልዩነት የሚፈጠረው፡፡
ሞት ባዳ ነው፡፡ ሞት ከሰው ወገን ስላልሆነ፣ ለሰው አይራራም፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀልስ ምን አሉ የሞትን ነገር ታዝበው ‹‹… የሰው እንግዳ ሲመጣ፣ ግባ ይሉታል ብላ ጠጣ፣ ያንት መላክተኛ የመጣለት፤ ይዋል ይደር የለበት ›› ሞት ክፉ እንግዳ ስለሆነ ውለታውን በክፋት ነው የሚመልሰው፡፡ እርሱ ከፍቶ ባይሆን እንኳ፣ ውጤቱ ለእኛ ስለሚከፋ እጁ እስኪገነጠል ቢያንኳኳ እንኳ፣ የኛ በር እንዳልተንኳኳ ማመን እስከሚቻለን ድረስ መፅናትን መለማመድ፡፡ እውነት ማን ይሙት! የትኛዋ ልጃገረድ ናት የምጥ ስቃይን ከወላድ የምትጋራ? ስሜቱን፡፡ ምጥ እንዲያም ብታውቅ እንጂ ሕመሙ አይሰማትም፡፡ ሞትስ እንደ ውልደት አይደለም ወይ? ሕመሙን ሆነ ደስታውን እስካልቀመስነው መች ይሰማናል፡፡ አይሰማንም፡፡ ሰውም እንዲሁ ነው፤ ስለ ሞት ያለው ግምት፡፡ ከጎረቤቱ ጥል ባይሆን እንኳ ሞትን በማሻገር፣ አንዱ ቀሪና ቀባሪ እርሱ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡
ጋሽ ቤከርም ይህንኑ ነው ያሉት፣
‹‹… at heart one doesn’t feel that he will die, he only feels sorry for the man next to him. ››
ሌላው ጥያቄ፣ እንዴት ነው ሞት ላይ ዘራፍ የሚሉት? እና፣ ዘራፍ ያሉት ጠላት በዘራፍ አልበረግግ ቢልና ይልቁን ዘሎ ቢያንቅ ምን ያደርጋሉ? የሚለው ነው፡፡
ነገሩን ሁለት ቦታ ከፍለን ለማየት እንሞክር፡፡
ታግሎ ማሸነፍና፣ ታግሎ መሸነፍ፡፡ ታግሎ መሸነፍን፣ በታሪክም በዓይናችን ብሌንም ዐይተን በተማርነው መሰረት የሁላችን ሊባል ቁጥሮች ለጎደለን ለ99ኞቹ ትተን ፣ ታግሎ ማሸነፍን ለአንዱ እንሰጣልን፡፡
ዘጠኝ ሞት መጣ ሲሉት፣ አንዱን ግባ በሉት አላ፡፡
አንዱ ማን ነው?
እዚህ ጋ ጋሽ ቤከርን በድጋሚ ወደ’ዚህ ለመጥራት እንገደዳለን (ለማይረባ ነገር አመላለስንዎት አይደል ጋሼ… ይቅርታ)
‹‹ The hero was the man who could go into the spirit world, the world of dead, and return alive. ››
ሆድህ ገብቼ ደም ሳይነካኝ እወጣለሁ እንደማለት ያለ ነው ነገሩ፡፡ ይሄ ከሞት ግብግብ እግረ መንገዱን ሽልማት የሚገኝበት ነው፡፡ ሽልማቱ ደግሞ ጀግንነት ነው፡፡ ሞት ያልተፈራበት ዘመን አለ ቢሉ፣ ሰው አልነበረም ያኔ ብለን ለመጠየቅ እንደፍራለን፡፡ ስፓርታ ልጆቿን ለክብር ሞት መውለዷስ? ብትሉ፣ ሰው ሕይወቱን በትፍስህት ለሞት አያጫትም፣ ቢሳካለት እንኳ ሞትን ተሻግሮ ማየት አልቻለም፤ እንላለን፡፡ ሁሉም ሕይወት ሞት ፊት ኢምንት ነው፡፡ ያንን ማወቅ ለፈለገ ለእገሌ እሞታለሁ ያለ ጀግና አንገት ላይ ሰይፍ ያስደግፍ፡፡ ያኔ ጉራውና ትምክህቱ ለነፍሱ ቦታ ትለቃለች፣ ነፍስ ደግሞ ፈሪ ናት፡፡ ነፍስ የታሰረችበት ግድግዳ ነው ስጋ ማለት፡፡ ነፍስ ስጋን መሽጋ የምትኖር የሌላ ዓለም ዜጋ ናት፡፡ ድንገት የዜግነት ማጣሪያ ሲደረግ ትበረግጋለች፣ በስጋው እንጂ በነፍሱ ጀግና የሰው ዘር የለም፡፡ እንዲያው ልቡ ጀግኖለት እንደ ስፓርታውያኑ ወጠጤዎች ሞትን በድፍረት ቢጋፈጥ እንኳ ተመልሶ ገድሉን ለማፃፍ የሚሆን እድል አላገኘም፡፡ ካርል ዩንግ ይሄን የጀግንነት ጉዳይ ስነልቦናዊ ፍካሬ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ሰው የራሱን ሞት ከማሸነፍ በዘለለ በሌሎች (የሞት አገልጋይ ተደርገው በተመሰሉ monsters and force of evil) ላይ በመዝመትና እነሱን በማሸነፍ ጭምር ነው ይለናል፡፡ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ አይደል ተረቱስ፣ እሱን ባይሆን መልዕክተኞቹን በመጠፍጠፍ የሰው ልጅ ንቀቱን አሳይቷል፡፡ ይሄን እምነት ለማሳየት በየጫካው እየዞሩ፣… እነማ አትሉም?
‹‹ እነ ሄርኩለስ፣ እነ ዳዊት፣ እነ ጊዮርጊስ፣ ጊለጋሜሽ፣ ሲጉርድ፣ ዘንዶና አንበሳ በጥፊና በቴስታ ሲዘርሩ፣… ክርስቶስ መጣና ታዲያ፣…
… አያይ እንደዚያ አይደለም፣… አንዱና ትልቁ (ጉልቤው) ሌላውን (ደካማውን) እየበላና እየገደለ መኖር ሥርዓተ ተፈጥሮ ነው፡፡ ማሸነፍ ያለብን ሞትን ነው፡፡ don’t kill the messenger፣… የቱ ሞኝ ነው ኮምፒውተሩን ቫይረስ ሲያጠቃው፣ ቫይረሱን ፀረ- ቫይረስ በማስረጨት ፈንታ አውጥቶ የሚወረውር? የቷስ ቂል ናት ስንት ፈዋሽ ፀበል (ቡሩክ ካህን) ባለበት ሀገር ቤቴ ሰይጣን ገባ ብላ ቤቷን ጥላ ብርር የምትል? ይሄ ሞኝነት ነው፡፡ ሞት ግድግዳ ነው፡፡ ግድግዳውን ማፍረስና መተላለፊያ ማበጀት ነው ያለብን፣ እኔ ያንን ነው ያደረግሁት፡፡ ››
ያለውን አደረገ፡፡ ይሄን ጀግንነት ያለተቀናቃኝ በምልዓት የተቆጣጠረው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ የሰው ልጆች ጀግና ነው፡፡ ኢየሱስ ሞት ላይ ተረማምዶ ከማለፍ በላይ የጀግንነቱን ዜና በራሱ ጆሮ ለመስማት ችሏል፡፡ ከኢየሱስ ትንሳዔ ወዲህ ሞት እምብዛም ያልተፈራበት ዘመን ሆነ፡፡ ሰዎች እየሞቱ እያየ እንኳ ከሞት ባሻገር ስላለው ሕይወት ማወቁ ሰውን አፅናናው፡፡
ሞት ምን አለ ይሄን ጊዜ?
‹‹ ተበላሁ! ››
ሞት ይሄን ማለቱ በሀገር ተሰማ፡፡ ሀገሬው ሞት ይሄን ማለቱን ሲሰማ የድል ድግስ ደገሰ፡፡ (ኸረ ዘፈን ያወጡም አሉ አሉ፣… ሞትዬ ሞትነት፣ ሞት’ለም ሞቱካ፣… አሃሃሃ፣… እንዲህ ያለው ፈሪ፣ ልፍስፍስ ነህ ለካ፣… ሆሆይ ናና…) በየድግሱ ሞት ላይ ተቅራራ፡፡ የኢየሱስ ትንሳዔ ለሰዎች፣ ሞት ማለት ከገቡበት የማይወጡበት እንዳልሆነ መልመጃ ሆነ፡፡ ይሄን ጊዜ ጋሽ ቤከር ሰልፍ አሳብሮ ገባና እንዲህ አላ፣
‹‹ when we see a man bravely facing his own extinction we rehearse the greatest victory we can imagine. ››
ሰው በየመቅደሱ፣ በየእድሩ፣ በየዛፉ ጥላ፣ በየጨብሲ ቤቱ፣ ጠረጴዛ በጡጫ እየመታ ጥርሱን እያፋፋቀ ተማማለ፡፡ አንዱ ጎበዝ ብድግ ይልና መሃላውን ይመራል ሌላው እየተከተለ እሱ ያለውን ይላል፡፡
‹‹ ከእንግዲህ በኋላ፣… ሞት ሆይ እግር ብላ፣… If I am like my all powerful father, I will not die. ››
ኦስትሪያዊው ዶክተር ዊልካልም ሪችም ይሄን መሃላ Character armor ብሎ ጠራው፡፡
እንበልና (በእንበልና ገብተው የእውነትን ቦታ ያገኙ ስንቶች እንዳሉ መረጃው ቢኖረንም) ቅድመ ክርስቶስ የነበረው የሰው ልጅ ሞትን ሲፈራው የነበረው፣ ሞት የሙከራ ዕድል ስለማይሰጥ ነው እንበል፡፡
በምሳሌ እንየው፡- ከ’ለታት በአንዱ ቀን፣… እንዲያው አንዱ ጥጋብ ልቡን ንፍት ያደረገው ወጠጤ፣ በሰላም ኑሮውን እየኖረ ካለበት ድንገት ብድግ ብሎ የሞትን ነገር ቢያጣጥል፣ አጣጥሎም ባይቀርና ካልገጠምኩት ሞቼ ልገኝ ቢል፡፡
‹‹ የታባቱንስና ደግሞ! አሁንስ ለማንም ጠቋራ (መቼም ፈረንጅ ይመስላል እንደማትሉኝ) መንቦቅቦቅ ሰለቸኝ ››
ብሎ ቢገጥመውና ሞት በአንድ ቃሪያ ጥፊ ጥሎት ያንን የመሰለ መኳንንት ሙትት ብሎ ቢቀር፡፡ እሱኮ ሀሳቡ የነበረው፣ ሞት ቢያሸንፈው ከንግዲህ ኋላ አንገቱን ሰብሮ ሊኖር፣ እንደሁ አድባር ቀንታው ሞትን ቢያሸንፈው ጊዮርጊስ እንደረገጠው ድራጎን ያለ ምስል፣ ሞትን ከእግሩ ስር ረግጦ የሚያሳይ ሀውልት አደባባይ አቁሞ ለመኖር ነበር፡፡ ሞት ግን አሰራሩ እንደዚያ አይደለም፣ ከተጣሉት ለእርቅና ለሽምግልና የሚሆን ጊዜ አይሰጥም፡፡ እንዲያው ዝግት ያለ ነገር ነው፡፡ ይህ እንዴት ማለት ነው? ለነገ የሚሆን እቅድ ይዘህ ከአልጋ ትወጣና ነገን ብትጠብቅ ብትጠብቅ ሳይመጣ ቢቀር፣ ይሄም በቀላል እንግልጣርኛ
‹‹ any schoolboy can do experiments in the physics laboratory to test various scientific hypothesis. But man, because he has only one life to live, cannot conduct experiments to test whether to follow his passion [compassion] or not. ››
ኩንዴራ ከላይ ያለንን ሰምተን ‹‹ ልክ ብለሃል ›› ብለን ብዙም ሳንርቅ ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ እንገባለን፡፡ አጣብቂኙ የመጣው ከታሪክ ነው፡፡
ቅድመ ክርስቶስ ያለው የሰው ልጅ ሞት የመጨረሻ አለመሆኑ ጠፍቶት ነው? የሚል፡፡ ‹‹እህሳ?›› ስንል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው ብሎ ይጀምራል አጣብቂኙ፣
‹‹ ዛሬ አይምሰላችሁ፣ ጥንት የሄለናውያንን ፍልስፍና የሚያራምዱ የዜኖ ደቀመዛሙርት የሆኑት ስቶይክሶች፣ ቡድሂስቶች፣ ሂንዱሂስቶች ሁሉ ሳይቀር ሞት ለሰው ልጅ የመጨረሻው እንዳልሆነና Infinite (የሰው ልጅ የቁጥር እውቀቱ አገልግሎት እስከሚያጣበት) ጊዜ ተደጋግሞ ተወላጅ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ››
የአጣብቂኙን ነገር ችላ ለማለት ‹‹ የድሮ ሰው ምኑ ይታመናል ›› ብለን ልናጣጥል ስንጀምር፣ የድሮ ሰዎች አምላክ ከድህረ ክርስቶስ ሰዎች ነብይ አስነሳብና፡፡ እንደ ኒቼ ባሉ ባለ ጎፈሬ ሙስታሾች ስል ምላስ ሊያስገርፈን፡፡ ኒቼ ተነሳ ያንን ዞማ ፅዕሙን እያስተኛ፣
‹‹ የድሮ ሰው ምናምን እያልክ ነገር ከምታጣጥል ካሽ አውጣና መፅሐፌን ግዛኝ፣ እዛ ላይ ስለ Eternal recurrence የፃፍኩትን ታገኛለህ፣…››
ታዲያ እንዲህ ከሆነ ነገሩ የዛን ዘመን ሰው ሞትን ለምን ፈራ? ተብሎ ሲጠየቅ፣ እኛም መላምትን ለፈጠረ አምላክ ገለተ ጢሎሲ! እያልን መመልመት እንጀምራለን፡፡
መላምት 1፡- በዚህኛው ዓለም ያስኮረፉት ሞት (የድሮው ሞት ደግሞ ተበቃይ ነው) በሌላኛው ሕይወት ሲያገኛቸው መከራቸውን እንዳያበዛው በመስጋት፡፡ ማን ያውቃል ሞትም የTalien principle ተከታይ እንደሆነ? የናቀውን በንቀት፣ የተሳፈጠውን በስፍጠት የሚመልስ እንደሆን? ሞት ሲሳፈጥ ደግሞ አሟሟት በማክበድ ነው ሲባል ሰምተናል፣ ሲያደርግ ባናይም፡፡
መላምት 2፡- ድግግሙ ቅልሽልሽ ስላለው፡፡ አልያም ምን የመሰለው ከበርቴ አሳማ ሆኜ ብመለስስ ከሚል ከንቱ ስጋት?
ደግሞ ሞትን መፍሪያ ምክንያት ጠፍቶ ነው? እንዲያው ስታደክሙን እንጂ፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ታዲያ ሰው ምን በጀው? ብለን ከአፋችን ሳንጨርስ አጋፋሪሻ በቅሎአቸውን እየኮለኮሉ ከተፍ፡፡ በግራ ይሁን በቀኝ እጃቸው መፈክር ይዘዋል፡፡
‹‹ ሞትን ሽሹት! ›› የሚል የተፃፈበት፡፡
ጨዋታን ጨዋታ አይደል የሚያነሳው፣ ለመሆኑ አጋፋሪ ሞትን ሲሸሹ ነው ሲያባርሩ የሰነበቱት? ብሎ መጠየቅ አይከፋም፡፡ ምክንያቱም ሞት ሁሉ ሀገሩ ነዋ፡፡ ይልቅ አጋፋሪ በፍርሃትም ይሁን በግብታዊነት ሞትን በንቃት ይከታተሉት ነበር፡፡ ንቃታቸው ሞትን ከጉያቸው አልለየውም፡፡ ባሰቡት ቁጥር ሞት ቅርባቸው እንዲገኝ ሆነ፡፡ ለመሸሽ ባሉት ልክ እየቀረቡት በአንፃሩ ሞት ያለቀጠሮ እንዳያስቱት ብሎ ሲሸሽ እንደኖረ አድርገንም ማሰብ ይገባል፡፡ ይባስ ብለን፣ አጋፋሪ ሞትን ሳይሆን ሙታንን ነበር ሲሸሹ የነበሩት ብንልስ? ለምን አንልም ለምለም አንደበት እስካለን፡፡
እናም በስተመጨረሻ፣… ጋሽ ኩንዴራ The stupidity of people comes from having an answer for everything ብሎ እፍኝ ስላሳከለን መልስ ኪሳችን ቢኖርም ታላቅ የመታዘዝ ባሕል እድሜው እንዲረዝም ሲባል ጠይቀን እንወጣለን፡፡
1. ከሚከተሉት ምርጫዎች መካከል እንደው ይሄ ለኔ ይበጀኛል ያላችሁት ላይ አክብቡ?
ሀ. ቤቴን በሕይወት ሞልቼ ለሞት የሚሆን ቦታ ማሳጣት
ለ. ሞትን ታግዬ ማሸነፍ
ሐ. ከነመኖሩ ርስት አድርጌው መኖር
መ. እንደ አጋፋሪ መሸሽ
ሠ. መልሱ እዚህ የለም
ረ. እዚህ ከሌለ የት ነው?
(በስተመጨረሻም፣ በእኚህ ከላይ በጥቂቱም ቢሆን በጠቀስናቸው ግለሰቦች (በላዖ ዙ፣ በኤርነስት ቤከር፣ በፍሩውድና በአጋፋሪ) ሕይወት ውስጥ ስለተፈከረው ሞት ለመጨዋወት የያዝነውን የመንደርደሪያ ሀሳብ ዳግም የምንመለስበት ስለሚሆን፣ አትጥፉ ለማለት ነው፡፡)
የምስጋና ተዓምራዊ ሃይል!!
ለማሰብ እጅግ አስከፊ ከነበረ ሁኔታ ውስጥ በምስጋና ኃይል፣ ህይወታቸውን ሙሉ በሙሉ የለወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አውቃለሁ። ፈጽሞ ተስፋ የሌለው የሚመስል የጤና ጉዳይ፣ ተአምር የሚያሰኝ ውጤት አምጥቷል።
ሥራቸውን ማከናወን ያቃታቸው ኩላሊቶች እንደገና ሲያንሰራሩ፤ የታመሙ ልቦች ሲፈወሱ፤ የታወሩ አይኖች ሲበሩ አይቻለሁ። የተበጠሱ የግንኙነት ክሮች ተቀጥለው ወደ ሰመረ ግንኙነት መቀየራቸውን አውቃለሁ- በምሥጋና ተዓምራዊ ሃይል!!
አለቀለት የተባለ ጋብቻ ሲታደስ፤ የተራራቁ የቤተሰብ አባለት እንደገና ሲገናኙ፣ የወላጆችና የልጆች ግንኙነት እንደ አዲስ ሲገነባና መምህራን ተማሪዎቻቸውን ሲለውጡ ሁሉ አውቃለሁ።
በምስጋና አማካኝነት፣ ቤሳ ቤስቲን ያልነበራቸው ድሆች ባለጠጋ ሲሆኑ፣ የከሰረ ንግዳቸውን እንዲንሰራራ ሲያደርጉ፤ እድሜ ልካቸውን ከገንዘብ ጋር ግብግብ ገጥመው ሲንጠራወዙ የነበሩ፣ የተትረፈረፈ ሀብት ሲፈጥሩ አይቻለሁ።
አንዳንዶቹም እንዲያውም፣በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ከጎዳና ተዳዳሪነት ወጥተው ባለሥራና ባለመኖሪያ ቤት ሆነዋል። በድብርት ውስጥ የነበሩ ሰዎች አስደሳችና የተሳካ ህይወት መቀዳጀታቸውን አውቃለሁ። በጭንቀትና በተለያዩ የአዕምሮ ህመሞች ሲሰቃዩ የነበሩ ሰዎች፣ በምስጋና አማካኝነት ፍጹም የአዕምሮ ጤናቸው ተመልሶላቸዋል።
ሁሉም የዓለም አዳኞች፣ ምስጋናን ተጠቅመውበታል። ምክንያቱም ምስጋና እጅግ ላቅ ካሉት የፍቅር መገለጫዎች አንዱ መሆኑን ያውቃሉና። ምስጋናቸውን ባለማጓደል ሲያደርሱ፣ ህጉን በትክክል ጠብቀው እየኖሩ መሆናቸውንም ያውቃሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዱን ተአምራት ከመፈጸሙ በፊት፣ “አመሰግናለሁ” ይል የነበረው ለምን ይመስላችኋልሃል?
የሰዎች ውለታ በተሰማችሁ ቁጥር ፍቅርን እየሰጣችሁ ነው። የሰጣችሁት ደግሞ ተመልሶ ይሰጣችኋል። ሰዎችን ስታመሰግኑ ይሁን ለመኪናችሁ፣ ለአዲሱ ቤታችሁ፣ ለዕረፍት ጊዜያችሁ ወይም ለምትጠልቅ ጀንበር (Sun Set) አሊያም ለተበረከተላችሁ ስጦታ ወይም ደግሞ ለገጠማችሁ አስደሳች ክስተት ምስጋና ስታቀርቡ፣ ለእነዚህ ነገሮች ፍቅር እየሰጣችሁ በመሆኑ በአጸፋው የበለጠ ደስታን፣ የበለጠ ጤንነትን፣ የበለጠ ገንዘብን፣ የበለጠ አስደሳች ሁኔታዎችን፣ የበለጠ አስደናቂ ግንኙነቶችንና የበለጠ ምቹ አጋጣሚዎችን ታገኛላችሁ።
(ተአምራዊ ኃይል - The Power)
“ሰው ብቻ አትሁኑ”
ሰው ብቻ አትሁኑ፤ ‹ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው?› ብዬ ሳስብ፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው፤ እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፤ እንደ እንስሳ።
...ታላቁ ሊቅ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል … ‹ሰው እግዚአብሔር ሲለየው፤ ጠባዩ እንደ አራዊት፤ አመጋገቡ እንደ እንስሳ፣ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሔር ሆኖ ይቀራል›። በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው፤ ጥሪ የማይቀበል...እኔ በዕውነቱ ከተማው ፈርሶ እየተሰራ ነው እየተባለ ዐይናማዎቹ ሲያወሩም ሲያስወሩም እሰማለው። ፈርሶ መሰራት ያለበት ግን የሰዉ አስተሳሰብ ነው።... የሰው አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሰራ፤ የተሰራ ከተማ ይፈርሳል። ጃፓንና ቻይና ሀገራቸውን ያለሙት መጀመሪያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው።
ቤታችሁ ገብታችሁ እንድታጤኑት ነው። … እንደምታዩኝ እኔ ዐይነ ስውር ነኝ። ቀላል አይደለም.... እንኳን ዘወትር ዓይን አጥቶ አንድ ቀን መብራት ሲሄድ፣ ስንት እንደምታማርሩ ታውቅታላችሁ። እኔ ግን ዓይኔ ባለማየቱ አንድ ቀን እንኳን አልቅሼ አላውቅም። ከሞት ወዲያ መብራት አለ። ከመቃብር በላይ መብራት አለ።
... ወደ መቃብር ሲወርድ ማንም ዓይነ ስውር ነው። ማንም ዐይኑ እያየ የተቀበረ የለም። ተስፋችን ግን ምንድን ነው? ከሞት ወዲያ ሕይወት አለ። ከሞት ወዲያ ብርሃን አለ...አንዳንድ ጊዜ እመኛለሁ። የማይረባ ነገር ስናይ (ዓይናችንን) የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር... መልካም ነገር እስክናይ ድረስ ለጊዜው የሚያጠፋ ቆጣሪ ቢኖር።
…አሁን እንደው ጆሮ በካርድ የሚሰራ ቢሆን ሐሜት እንሰማ ነበር? የምንፈልገውን (ብቻ) አውርተን ስዊች ኦፍ እናደርገው ነበር። ችግሩ ብዙ ነው፡፡ ስንት ዞማ ጸጉር ይዞ አስተሳሰቡ የከረደደ አለ።
(መጋቤ ሐዲስ እሸቱ)
የ”ኦፕራ ሾው” የምንጊዜም ተወዳጅ እንግዳ!
ጥቁር አሜሪካዊቷ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ በአሜሪካ ከምንም ተነስተው፣ በራሳቸው ጥረትና ትጋት ቢሊየነር መሆን ከቻሉ እንስቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ ፎርብስ መጽሄት እንደሚጠቁመውም፤ የኦፕራ ወቅታዊ የተጣራ የሃብት መጠን 2.46 ቢ. ዶላር ይገመታል፡፡
ኦፕራ ለ25 ዓመታት ገደማ በስኬት በመራችውና ከፍተኛ ተወዳጅነት በነበረው “ኦፕራ ሾው” ላይ ለ35 ሺ ሰዎች ገደማ ቃለ-ምልልስ ማድረጓን በከራት ትናገራለች፡፡
በቅርቡ ለኦፕራ ቃለ-ምልልስ ያደረገላት አንድ ጋዜጠኛ፤ “የኦፕራ ሾው የምንጊዜም ተወዳጅ እንግዳ ማን ነው?” ሲል ጠይቋት ነበር፡፡
የዚህን ጥያቄ መልስ ለመመለስ ኦፕራ፣ በዝነኛው የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ኒኮላስ ክሪስቶፍ፣ የተጻፈውንና ያነበበችውን አንድ መጽሐፍ መጥቀስ ነበረባት፡፡ የታሪኩ ባለቤት አንዲት የዚምቧቡዌ ልጃገረድ ናት - ተዓምረኛ ልጃገረድ! ተወልዳ ያደገችው፤አግብታ የወለደችው እዚያው ዚምቧቡዌ ነው፡፡ ቴራይ ትባላለች፡፡
ቴራይ በልጅነቷ ከወንድሟ ጋር ት/ቤት ለመግባት ሳትታደል ነው ያደገችው፡፡ አባቷ ወንድ ልጃቸውን ት/ቤት እየላኩ፣ እሷ ግን ቤት ውስጥ ቀርታ እንድታገለግል ፈረዱባት፡፡ የሚያስገርመው ደግሞ ት/ቤት እየዋለ ለሚመጣው ወንድሟ፣ የቤት ሥራ የምትሰራለት እርሷ ነበረች - ትምህርቱ እየከበደው፡፡
ቴራይ ገና በህጻንነቷ ነበር ባል እንድታገባ የተገደደችው - በ11 ዓመቷ ግድም፡፡ በ18 ዓመት ዕድሜዋ የአምስት ልጆች እናት ነበረች፡፡ ልጅነቷን ሁሉ የሰጠችው ለሚስትነትና ለእናትነት ነው ቢባል ፍጹም እውነት ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር ሄይፈር የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የምትሰራ አንዲት ሴት ወደ እነ ቴራይ መንደር ጎራ ያለችው፡፡ ስለ ቴራይ በጥልቀት ካወቀች በኋላ፤”ህልምሽ ምንድን ነው?” ስትል ጠየቀቻት። ከባድ ጥያቄ ነበር፤ ለቴራይ፡፡ ከዚያ ቀን በፊት ይሄንን ዓይነት ጥያቄ ተጠይቃ አታውቅም፡፡ በመጨረሻም፣ ከሄይፈር የመጣችው ሴት፣ ህልሟን በወረቀት ላይ እንድታሰፍር ትመክራታለች፡
ቴይራም በተባለችው መሰረት፣ በብጣሽ ወረቀት ላይ ማሳካት የምትፈልገውን ግብ ትጽፍና፣ በትንሽዬ ጣሳ ውስጥ በመክተት፣ አንድ ትልቅ ድንጋይ ሥር ትደብቀዋለች፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቴይራ ራሷን ያገኘችው፣ ከአንድ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ድግሪ ስትመረቅ ነው፡፡
በርግጥም የመጀመሪያ ግቧ አድርጋ የጻፈችው፣ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪዋን ማግኘት ነበር። ወደ ዚምባቡዌ ተመልሳ ሁለተኛ ግቧን በብጣሽ ወረቀት ጽፋ እዚያው ድንጋይ ሥር ወሸቀችው። የማስተርስ ድግሪዋን ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ነበር -ሁለተኛው ግቧ፡፡ ይህንንም አሳካች። ሁለተኛ ድግሪዋን ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተቀበለች። አሁንም ወደ ትውልድ መንደሯ በመመለስ፣ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን ግቧን ጻፈች። በዚህ ጊዜ ደግሞ የዶክትሬት ድግሪዋን ለማግኘት ነበር ያለመችው። ባለፈው ዓመት ታዲያ ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲ የፒኤችዲ ድግሪዋን አጠናቃ፣ ዶ/ር ቴራይ ለመባል በቅታለች፡፡
ቴራይ በልጅነቷ የተከለከለችውን ትምህርት፣ እስክትጠግብ ድረስ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተማረች፡፡ ትምህርት ሀ ብላ የጀመረችው እጅግ ዘግይታ በ18 ዓመቷ ቢሆንም፣. እስከ ዶክትሬት ድግሪዋ ከመማር ያገዳት ምንም ነገር የለም፡፡ኦፕራ የዚህችን ወጣት አስደማሚ ታሪክ አንብባ ከጨረሰች በኋላ ነው፣ለቃለመጠይቅ ያፈላለገቻት፡፡ሆኖም በመላው አሜሪካ ተፈልጋ አልተገኘችም። በመጨረሻም አገሯ - ዚምባቡዌ እንዳለች ለማረጋገጥ ተቻለ፡፡
ኦፕራ አውሮፕላን ተሳፍራ፣ ባህር ተሻግራ ዚምባቡዌ ገባች፡፡ በታሪክ ብቻ የምታውቃትን ወጣት በአካል ተዋወቀቻት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በ”ኦፕራ ሾው” ላይ ቃለመጠይቅ ያደረገቻት።
ኦፕራ ዊንፍሬይ ቴራይን፤”የምንጊዜም ታላቅ እንግዳዋ” ያለችበትን ምክንያት ስትገልጽ፤ “እኔ ለ25 ዓመት በእያንዳንዱ ፕሮግራም ላይ ለተመልካቾቼና ተሳታፊዎቼ ስነግራቸውና ስመክራቸው የኖርኩትን ነው፣በዚህች ወጣት ታሪክ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ያገኘሁት፡፡
ሁሌም ትችላላችሁ- ሙከራችሁን ቀጥሉበት፤ ፈጽሞ አታቋርጡ እያልኩ ነው ሳስተምር የኖርኩት፡፡” ብላለች፡፡በዚምባቡዌ የተወለደችውና በገዛ አባቷ የትምህርት ዕድል የተነፈገችው ቴራይ፤ ዘግይቶም ቢሆን ህልሟን አሳክታለች - በሙሉ ልብ፣ በጥልቅ መንፈስ፣ በቁርጠኝነትና በዲሲፕሊን ተሞልታ!!
ሥራ ፈጣሪዎቹ ወንድማማቾች
“ሰው ከተሰማራ እንደ የስሜቱ ከዋለበት ስፍራ አይቀርም ማፍራቱ” ይባላል። ሁለቱ ወንድማማቾች ፍፁም ዘካሪያስ እና ነብዩ ዘካሪያስ፣ ለዚህ አባባል ሁነኛ ምሳሌዎች ናቸው።
ፍፁም ዘካሪያስ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ታህሳስ 26 ቀን 1979 ዓ.ም ተወለደ። ቅድመ መደበኛ ትምህርቱን በስድስት አመቱ፣ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው የሠ/ማ/ጉ የአፀደ ህፃናት ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ፣ መደበኛ ትምህርቱን በአቃቂ አድቬንቲስት ሚስዮን ት/ቤት ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በFTS ት/ቤት በከፍተኛ ውጤት አጠናቆል። ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትሪካል አርት የትምህርት ክፍል በመግባት፣ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።
ሆኖም በንግድ ስራ ላይ ባለውጥልቅ ፍላጎትና ጉጉት ምክያንት፣. የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን በማቋረጥ በወላጆቹ የሆቴል ንግድ ሥራ ላይ ተሰማራ። በኋላም ስለ ንግድ ስራ አዳዲስ ሃሳቦችንና የዘመኑን በቴክኖሎጂ የታገዘ የንግድ ስራ ክህሎት ለመቅሰም በማሰብ ወደ አውሮፓ ተጓዘ፡፡ በኔዘርላንድ፣ ቤልጅየም ፣ ኒውዘርላንድ ፣ ጀርመንና ሌሎች አገራትም በመዘዋወር ሁኔታዎችን ሲያጠና ቆይቶ፣ የተለያዩ መረጃዎችንና የቢዝነስ ሃሳቦችን በመያዝ ወደ አገሩ ተመለሰ።
ወንድሙ ነብዩ ዘካሪያስም፣ በአዲስ አበባ፣ በ1983 ዓ.ም ጳጉሜ 4 ቀን ተወለደ። የቅድመ መደበኛ ትምህርቱን የአሁኑ አቃቂ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የሠ/ማ/ጉ የአፀደ ህፃናት ትምህርቱን አጠናቀቀ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ቴዎድሮስ ፣ ሌስፔራንስ ት/ቤት፣ ቃሊቲ በሚገኘው ብሔራዊ ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳሪስ በሚገኘው አይጎዳ (school of Igoda ) ት/ትቤት በ2002 ዓ.ም አጠናቋል፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ም፣በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት በመማር በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል።ከዚያም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በንብረት ክፍል ውስጥ ተቀጥሮ ለአጭር ግዜ ካገለገለ በኋላ፣ ከወንድሙ ፍፁም ዘካሪያስ ጋር በመሆን ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቅሏል።
ወደ ንግዱ ዓለም የተሳቡት ገና በልጅነታቸው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በእናታቸው ስም በተሰየመው ሮሚ ሆቴል ንግዱን መለማመዳቸውን ይናገራሉ። ከፍ ሲሉም በግል ብንቀሳቀስ ይሻላል በማለት ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል። ከዓመታት በፊት አስቀድመው የዳቦ ቤት ንግዱን ሲያከናውኑ የቆዩት ወንድማማቾች በሃገራችን ያልተሰራ ምን አለ ብለው ቆም ብለው ማሰብ ጀመሩ ።
መኪናዎች በድንገት በመንገድ ላይ ሲበላሹ በፍጥነት እርዳታ የሚሰጥ በማይገኝበት በሃገራችን ለአሽከርካሪዎች የሚሆን መላ አልነበረም ቢኖርም ከእንግልት የሚያድንበት አንዳችም ስልት አልነበረም። በባህር ማዶ አቅንተው የነበሩት ፍፁም እና ዘካሪያስ ግን ይህንን እንግልት ለማስቀረት የመንገድ ዳር የመኪና ብልሽት የእርዳታ ሰጪ ድርጅትን ለመፍጠር ተነሱ እናም ኑሃ የመንገድ ዳር የመኪና ብልሽት እርዳታ ሰጪ ድርጅትን ፈጠሩ። 1915 ዓ.ም በአሜሪካ ሃገር የተጀመረው ይህ አገልግሎት በሌሎችም ዓለም ሃገራት እንዲሁም በእንዲሁም በእዚው በአህጉራችን አፍሪካም ኬንያ ፣ በደቡብ አፍሪካም ልምዱ ያለ ነው።
ከ100 ዓመት በሃላ ወደ ሃገራችን አምጥተነዋል። እኛ የፈጠርነው አዲስ ያለውን የመንገድ ፍሰት ችግር ይሄን ችግር ሊቀርፍ የሚችል ምንድነው ብለን ይሄ ነው በውስጣቸን የመጣው ሲልም አክሎ ተናግሮዋል። አንድ ስራ ሲጀመር ከባድ ቢመስልም በሃላ በሂደቱ እየተማሩ ብዙ መለወጥ እንደሚቻል ያምኑ ነበር።
ዘመኑ ቲክኖሎጂ ያደገበት እንደመሆኑ መጠን የመኪና የመኪና መንገድ ዳር ብልሽት የሚያመጣውን እንግልት ለማስቀረት ይህን ተቋም እውን ለማድረግ በርካታ ትግሎችን አድርገዋል። የፊልድ መካኒኮች በየአቅራቢያው መኖራቸውን የሚገልጡት መስራቾች በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን መተግበሪያውን ከplay store በማውረድ ወይም በአጭር የመስመር ቁጥራቸው 6516 ላይ በሚጠሩበት ሰዓት መካኒኮቹ ፈጣን አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል። የክፍያ ሂደቱም በወር 275ብር በ ሶስት ወር 825 በስድስት ወር 1500 ብር እና በአንድ አመት 3,000 ብር ጥቅል እንዳላቸው ከመስራቹ አንዱ የሆነው ነብዩ ዘካሪያስ ተናግሩዋል።
በስራ አለም ውስጥ ማንኛውም ከባድ ነገር በትዕግስት ካለፉት የሚቻል ነው ብለው ያምናሉ። የመንገድ ፍልሰቱን ሚዛናዊ የሚያደርገው የኑሃ ፕሮጀክት ባሳለፍነው መጋቢት 20/2015 በተመረቀበት እለት አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴን ጨምሮ ታላላቅ እንግዶች ታድመው የወጣቶቹን ጥረት አድንቀዋል። ኢ/ር አሰፋ መዝገቡ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የሰሩ ባለሙያ ሲሆኑ የኑሃ ሰዎችንም በማማከር ሙያዊ እውቀታቸውን አካፍለዋል። ኢንስፔክተሩም አንድ ተሽከርከሪ መንገድ ላይ ቆሞ ረጅም ጊዜ ሲቆይ አደጋ ማስከተሉ የማይቀር መሆኑን ገልጠው አገልግሎቱ እጅግ ጠቀሜታ ያለው መፍትሄ አምጪ ነው ብለዋል።
በሌሎች ሃገራት ኢንሹራንሶች በፕራይም ጥቅላቸው ውስጥ በማካተት ሰዎች አገልግሎቱን የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ የሚገልጠው ነብዩ ይሄንን ካየን በሃላ ወደ እኛ ሃገር በማምጣት እርሱንም አርቅቀን በምን መንገድ መሆን እንዳለበት ከውንድሜ ጋር ተወያይተን ከጨረስን በሃላ መተግበሪያውን ለማበልጠግ ስድስት ወር ገደማ አቆይቶናል ሲል ገልጠዋል።
በዚህ አምስት አመት ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞች እና በሌሎች ክልል ከተሞች እንደሚስፋፋ እንዲሁም ደግሞ ከሁለት ወር በሃላ ሌላ ይፋ የሚያደርጉት የስራ ዘርፍ እንዳለ ገልጠዋል።
ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ
በእውቀቱ ስዩም)
ማዳበርያ
እንደ ድሮው ብዙ የሰውነት እንቅስቃሴ አላደርግም፤ ሲነሽጠኝ፥ በሁለት ሳምንት አንድ ቀን ዢም ( gym) እሄዳለሁ፤ ወደ አዳራሹ እንደገባሁ አሰልጣኙ ሳያየኝ ፥ ኮቴየን “ ሳይለንሰር “ ላይ አድርጌ፥ ወደ ጥግ ሄድኩና የመጨረሻውን ሚጢጢ ዳምቤል አነሳሁ፤ ዳምቤሉ ከማነሱ የተነሳ ሁለት ራስ ያለው ትልቅ ቢስማር ነው እሚመስለው! ብዙም አልቆየም፤ የሆነ ድርብ ጭቆና የሚያህል መዳፍ ትከሻዬ ላይ ወደቀ፤ ዞር ስል አሰልጣኙ ነው፤ እኔን ለማሰልጠን ሳይሆን ለማሰቃየት የተመደበ ነው እሚመስለኝ::
“ብረት ከማንሳትህ በፊት ማሟቂያ ስራ” ሲል አዘዘኝ::
“ ምን ልስራ?”
ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በሁዋላ እንዲህ አለ፥
“ግራ እግርህን አንስተህ ፥ በማጅራትህ በኩል አሳልፈህ ተረከዝህን ሳም! “
እንደጀመርኩ አካባቢ ከጂሙ ሁለት ጊዜ በዊልቼር እየተገፋሁ ወጥቻለሁ::
ሰባት ፑሽአፕ ሰራሁና ሰባት ደቂቃ ከመስታወቱ ፊትለፊት ቆምኩ፤ እዚህ ጂም መምጣት ከጀመርሁ ወዲህ ለውጥ አለ፤ አንገቴ ዙርያ ሲክስ ፓክ አውጥቻለሁ፤ ጥቂት ቆይቶ፥ አሰልጣኙ “ ስኳት” አሰራኝ! ጂም ሄደህ ለማታውቅ አንባቢ፤ “ስኳት” ማለት ሽንት ቤት ልትቀመጥ ፈልገህ ቁጢጥ ማለት ከጀመርክ በሁዋላ ሽንት ቤቱ መበላሸቱን አይተህ ሀሳብህን ፥ቀይረህ ከመንገድ ስትመለስ ማለት ነው::
“ ስኳት ቢቀረብኝስ “ አልኩት የተንሸራተተ ዲስኬን ወደ ቦታው እየመለስኩ::
“ የግድ አስፈላጊ ነው” አለኝ አሰልጣኙ፤
“ምን ያደርግልኛል!”
“ እግርህንና መቀመጫህን ያዳብረዋል”
“ እግሬን ከመቀመጫዬ ነጥሎ እሚያዳብር ስፖርት የለም?”
“ የለም!“ አለኝ ኮስተር ብሎ፤” ተያያዥ ስለሆኑ አብረው ነው እሚዳብሩት!“
ስተክዝ እንዲህ ብሎ አጽናናኝ፤
“ አትጨናነቅ! መቀመጫህን ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚቀጥለው አመት ሌላ ስፖርት እንሰራለን”
እንቅስቃሴን ስጨርስ ገላዬን ታጠብኩ፤ ከዛ ብብቴን ወይባ ታጠንኩ፤ በአስር አመት ወደ ወጣትነቴ የተመለስኩ መሰለኝ! የሸሚዜን ሦስት ቁልፎች ፈታሁና ሩብ ደረቴን ለብርድና ለህብረተሰቡ እይታ አጋለጥኩት፤ ከ”ሮዛ” የሞዴል ማሰልጠኛ ለሻይ እረፍት የወጡ ኮረዶች፤ “He is out of my league” በሚል አይነት እሚያዩኝ መሰለኝ፤ በዚህ ቅርጽ ላይ ትንሽ ዝነጣ ልጨምርበት ብዬ፥ እግሬን በስታይል ፥ ጎተት አያደረግሁ መራመድ ጀመርኩ፡፡
ግቢያችን በር ላይ ስደርስ ፥ ዘበኛው በአዘኔታ ከንፈራቸውን አስጩኸው መጠጡና ፥
“ሪህ ነው ልጄ?”
ፍቅር ለቆሸሸው
ፍቅር ለቆሸሸው
ተስፋ ለሟሸሸው
ቀን በእድል ደመና
ሳይነጋ ለመሸው
የሳቅን ውብ ኪነት
ሀዘን ላበላሸው...
እንባ ወዴት ወዴት
ወዴት ነው ‘ሚሸሸው?
ልብ ለጠበበው ልብ ለጨነቀው
ሳግ ለተጋለበው፣ እልህ ለታመቀው
ሕይወት ለመረረ፣ ቅስም ለደቀቀው
ከዐይኖች የሚፈልቀው
ፈልቆ የሚርቀው?
እንባ አያሌው ሞኙን፣ ማነው ያታለለው?
ልብህን ሽሽና፣ ነፃ ላውጣህ ያለው
ካይን አርያም ቁልቁል፣ ወዳፈር የጣለው
በመራቅ መፍትሄ...
በመራቅ ስርየት፥ ያለ ያስመሰለው?
ፍቅር ለቆሸሸው
ተስፋ ለሟሸሸው
ቀን በእድል ደመና
ሳይነጋ ለመሸው
የሳቅን ውብ ኪነት
ሀዘን ላበላሸው...
እንባ አያሌው ሞኙ...
ወዴት ነው ‘ሚሸሸው?
(ረድኤት አሰፋ)
ሳህሉ ቢጠፋ አብረን በላን
ከእለታት አንድ ቀን አንድ አንበሳ፣ አንድ ነብር፣ አንድ ጅብ እና አንድ አህያ ችግር ገጥመዋቸው ተሰባስበው ሁኔታውን ለመገምገም ይቀመጣሉ፡፡ የውይይታቸው ርዕስ ‹‹አገሩን ለምን ድርቅ መታው? ዝናብ ለምን አቆመ? ምግብስ ለምን እጥረት ገጠመን?›› የሚል ነበር፡፡ በተደጋጋሚ፤ ‹‹እንዲህ እየተሰቃየን እስከ መቼ እንቆያለን? ያለ ምግብስ በባዶ ሆድ እንደምን ይዘለቃል?›› ይሉ ጀመር፡፡
ከመካከላቸው አንዱ አንድ ሀሳብ ሰነዘረ፡፡
‹‹ምናልባት እኮ ከእኛ መሀል ሀጥያት የሰራ ይኖር ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚሀር ለቅጣት የፈረደብን ፍርጃ ሊሆን ይችላል፡፡ አይመስላችሁም?›› ሲል ጠየቀ፡፡
‹‹እውነት ነው›› አለ ሌላኛው፡፡ ‹‹ምናልባት ሁላችንም የሰራነውን ሀጥያት ብንናዘዝና እግዚያብሄርን ይቅርታ ብንጠይቅ ይሻላል፡፡›› በሚል ሀሳብ ሁሉም ተስማሙና አንበሳ ኑዛዜውን ማሰማት ጀመረ፡፡
‹‹ወንድሞቼ በጣም የሚፀፅተኝን አንድ ሀጥያት ፈፅሜያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ወይፈን መንደር ውስጥ አግኝቼ፣ ወገቡን በክርኔ ሰብሬ አንድም አጥንት ሳላስቀር በልቼዋለሁ፡፡ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡››
ሌሎቹ እንስሳት ኑዛዜውን ካዳመጡ በኋላ የአንበሳን ሀይለኝነት ስለሚያውቁና ስለሚፈሩ እራሳቸውን በአሉታ ነቀነቁና፤
‹‹የለም አቶ አንበሳ፤ በጭራሽ ጥፋት አልፈፀምክም፡፡ የሰራኸው ስራም ምንም ሀጥያት የለበትም! እግዚሀር እንድትፈፅም የሚፈልገውን ተግባር ነው ያከናወንከው›› አሉት፡፡
ቀጥሎ ነብሩ ተናዘዘ፤
‹‹ወንድሞቼ፤ በጣም አዝናለሁ፤ እጅግ የሚፀፅተኝን አንድ ሀጥያት ሰርቻለሁ፡፡ ይኸውም አንድ ቀን አንድ ሸለቆ ውስጥ አንድ ከከብቶች ተነጥሎ የሚንከራተት ፍየል አግኝቼ፣ ቁጥቋጦ ውስጥ አድፍጬ ቅርጭምጭም አድርጌ በልቼዋለሁ፡፡ ለዚህም እግዚሀርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› አለ፡፡
ሌሎቹ እንስሳት የነብርን የአደን ችሎታ አድንቀው ሲያበቁ፤ ‹‹በጭራሽ ሀጥያት አልፈፀምክም አቶ ነብር፡፡ እንዲያውም ያንን ፍየል ባትበላው ኖሮ እግዚሀር ይቆጣ ነበር›› አሉት፡፡
ቀጥሎ ተራው ያያ ጅቦ ነበር ‹‹እኔ ሀጥያተኛ ነኝ ወንድሞቼ›› ሲል ጀመረ፡፡ ‹‹አንዴ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ገብቼ አንዲት ዶሮ አግኝቼ ቅርጥፍጥፍ አድርጌ በልቻታለሁ››
እንስሳቱም፤ ‹‹ይሄ በጭራሽ ሀጥያት አደለም፡፡ እንዲያውም እግዚሀር ደስ የሚለው ሁለት ሦስቱን ብትበላቸው ነበር›› አሉት፡፡
ለመጨረሻ አህያ ኑዛዜዋን አሰማች፡-
‹‹ከእለታት አንድ ቀን ጌታዬ ጭነት ጭኖብኝ እየነዳኝ ሳለ፤ አንድ ጓደኛውን አግኝቶ ቆም ብሎ መጨዋወት ጀመሩ፡፡ እኔ ሆዬ የመንገዱ ዳር ዳር እያልኩ አጎንብሼ እዚያ ያገኘዋትን ትንሽ ሳር ስግጥ ቆየሁ፡፡ ይሄንን ሀጥያት ሰርቻለሁ ወንድሞቼ፡፡ ለዚህም እግዚሀርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› አለች፡፡
ሌሎች እንስሳ አህያን ተመለከቷት። አህያን የሚፈራትም ሆነ የሚያደንቃት ማንም የለም፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ሁሉም እራሳቸውን ነቀነቁና፤
‹‹ይሄ በአለም ላይ ከተሰሩ ሀጥያቶች ሁሉ እጅግ በጣም የከፋው ነው፡፡ በሀገራችን ላይ ለሚደርሰው ስቃይና መከራም ዋናው ምክንያት ያንቺ ሀጥያት ነው፡፡ ቀንደኛዋ ሀጥያተኛም አንቺ ነሽ!›› በሚል ወነጀልዋት፡፡
ስለዚህም አንበሳ፣ ነብርና ጅብ ዘለው አህያይቱ ላይ ሰፈሩባት፡፡ አንድም አጥንት ሳያስቀሩ ተቀራመቷት፡፡ ሚስኪኗ አህያ በዚህ ሁኔታ ተሰዋች፡፡
***
ለግፍ ከዚህ ወዲያ ምሳሌ የለም፡፡ ሀይለኛ ይፈራል፡፡ ሀይለኛ ይደነቃል ሀይለኛ የሰራው ስራ ሁሉ እንደ ትክክል ይወሰድለታል፡፡ ሀጥያት መፈፀሙም ቢታወቅም እንደ ፅድቅ ስራ ይቆጠርለታል፡፡ ውይይቶች እና ግምገማዎች ሁሉ የሱን ንፅህና፣ የእሱን ብፅእና የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ደካሞች የሀይለኞች ሲሳይ እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡ ደካሞች ምንም አይነት ቅን አገልገሎት ቢሰጡም፣ ምንም አይነት ሸክም ቢሸከሙም ድካማቸው ሁሉ እንደ ከንቱ ተቆጥሮ እንዲያውም ሀጥያተኛ ነው ተብሎ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ የሰሩትን መልካም ነገር ሁሉ እንደ ሀጥያት ይናዘዛሉ፡፡ ከዚያም ይሰዋሉ፡፡ ከዚህ ወዲያ ጭቦኛ ስርአት የለም፡፡ ከዚህም ወዲያ ግፍ አይኖርም፡፡ በሀገራችን ሀይለኞች ተፈጥረው አይተናል። ሀይለኞች ደካሞች ላይ ግፍ ሲፈፅሙም አይተናል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ፤ ዲሞክራሲም፤ ሰላምም፤ እድገትም ሊመጣ እንዳልቻለና እንደማይችልም ተገንዝበናል፡፡ አስገራሚው ነገር፤ ደካሞች ሁሉ ከተሰዉት ደካሞች አለመማራቸው ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር፤ ደግሞ ሀይለኞች ሁሉ ከሌሎች ሀይለኞች ታሪክ አለመማራቸው ነው፡፡
ሀይለኞቹ፤ ‹‹ከዚህም ወዲያ አኩሪ ድል የለም›› ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው፡፡ ምናልባትም የደካሞቹ ከተሰውት አለመማር ሳይሆን አይቀርም። በግፍ የሚገኝ ማናቸውም ነገር የኋላ ኋላ ግፍ መሆኑ መረጋገጡም አይቀርም፡፡ የኋላ ኋላ ማስጠየቁ አይቀርም፡፡ እስከ ዛሬ በታሪክ የታየውም ይኸው ሀቅ ነው፡፡
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ታስሮ የነበረ አንድ እብድ፣ ጠዋት መናገር የጀመራትን አንድ አረፍተ ነገር ቀኑን ሙሉ ሲደጋግማት ይውል ነበር፡፡ ሰው የማይረዳለት ስለሚመስለው ይሆናል፡፡ ወይም በሌላም እብደታዊ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከነዚህ ከሚደጋግማቸውም አባባሎች መካከል፤ ‹‹ሞኝ ያስራል ብልጥ ይማራል›› የሚል ነበረበት፡፡ ግፍ የሚፈራ ሞኝ ነው፡፡ ግፍ የተሰራበት ደግሞ ከተማረ ብልጥ ነው፤ ማለት ነው፡፡ ዋናው ማማሩ ነው፡፡ ግፍ የሚፈፅም ሹም፣ አለቃ፣ የአለቃ ቀኝ እጅ፣ ቡድን፣ ፓርቲ ወይም መንግስት ይዋል ይደር እንጂ የእጁን ያገኛል፡፡ መጨረሻው አያምርም፡፡ ‹‹የሚደርቅ ውሀ ውሻ ይበላል›› እንደሚባለው በትንሽ በትልቁ ማኩረፍ፣ መቆጣት፣ ዘራፍ ማለት፣ ማስፈራራት እና ‹‹እርምጃ እወስዳሁ!›› ማለትን ይደጋግማል፡፡በአንድ አገር ጭቦና እኩይ ተግባር፣ ሙስናና ዘረፋ ከበረከተ ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት ግድ ይሆናል፡፡ አንዱ በቀኝ የተናገረው ለሌላው ግራ ይሆናል፡፡ መደማመጥ ይጠፋል፡፡ ባለ አንድ አቅጣጫ መንገድ (one way road) እንዲሉ፣ በዚህ በኩል ብቻ ሂዱ ማለት ይበዛል፡፡ ጉዞ ሁሉ ‹‹የተከለከለ መንገድ›› የሚል ፅሁፍ እና መፈክር ይበረክትበታል፡፡ ህዝብ እራስ አቀፍ (Self-censorship) ስርአትን ያዘወትራል፡፡ አለቃው የሚናገረው ለምንዝሩ ካለመግባቱም ሌላ አለቃ እና አለቃ እንኳ በአንድ ልሳን መነጋገር ይሳናቸዋል፡፡ ‹‹መልካም ጋብቻ ይሁንልህ!›› ቢለው ‹‹እግዜር ነው እንዲህ ያደረገኝ!›› ይላል፤ እንደተባለው የወላይታ ተረት መሆኑ ነው፡፡ አዩ ሌላ ወዮ ሌላ ነውና የተዘበራረቀ አሰራር ይሰፍናል፡፡ አቃጅና ፈፃሚ በተለያየ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ ይገኛል የተባለው ውጤት፤ እናፈራለን የተባለውን ፍሬ፣ ወይ ጥሬ ይሆናል ወይ ይረግፋል፡፡ለዚህ ጥፋት ወይም ሀጥያት ደግሞ ባለተራ፤ ‹‹ይሰዋል››፡፡
ከቶውንም ዲሞክራሲያውነት የጎደለው እና ጭቦ የበዛበት ስርአት ካለ ግልደፅነት ዘበት ነገር ነው፡፡ ግልፀኝነት ከሌለ ደግሞ የሚሰራው ከማይሰራው፣ ግፈኛው ከቀናው፣ አምራቹ ከአውዳሚው፤ ሀቀኛውና አዋቂው ከአስመሳዩና ከደንቆሮ የሚለይበት ሚዛን ይጠፋል፡፡ ሚዛን አለ ቢባል እንኳ ይሸቅባል፡፡ አዳዲስ ኮሚሽን፣ ባለስልጣን፣ ኮሚቴ ይበዛል፡፡ ‹‹በኮሚቴ ቢወስን ኖሮ ሙሴ ቀይ ባህርን አያቋርጥም ነበር›› እንደተባለው ቁርጥ ያለ እቅድ፣ ቁርጥ ያለ መመሪያ፣ ዕቅጩነት ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማግኘት ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ መልካም ውጤት ሲጠፋ ተጠያቂ ይፈጠራል፡፡ በአድሎ ይፈረዳል፡፡ ‹‹ፋቂ ቆዳ መፋቅ ቢያቅተው ውሻ ይሰድባል›› እንዲል መፅሀፉ፤ አንደኛው ወገን ላይ ሀጥያቱም፤ ይደፈደፋል፤ ይደመደማል፡፡
የኢ-ዲሞክራሲያዊነት፣ የመልካም-አስተዳደር (good Governance ) እጦት፣ የፖለቲካ ቡድኖች ገዢ ተገዢነት ሹኩቻ፣ ወዘተ አንዱ እና ዋነኛው ምንጫቸው አለመተማመን ነው - ‹‹ከጀርባው ምን ይኖር ይሆን?›› የሚል ስጋት እና ጥንቃቄ። ‹‹ያጎረሰኝ እንዲያንቀኝ ፈልጎ ሊሆን ይችላል!›› የሚል አመለካከት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ የጎሽ ሂደት ቀለል አድርገን ስንመለከተው እንግዲህ ወትሮውንም በፖለቲካው ጨዋታ ላይ የተሰለፉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ከዋና ተጫዋቾች ይልቅ ተለዋጮች (Bench እንዲሉ መፅሀፈ ካምቦሎጆ) የበዙባቸው መሆኑንና በአለመተማመን የሚጋዙ መበርከታቸውን እናስተውላለን፡፡ አለቃ አለቃን፣ ባለስልጣን ባለስልጣንን፣ ቡድን ቡድንን፣ ፓርቲ ፓርቲን የሚጠራጠርበት ሁኔታ ካለ ለማናቸውም እንቅስቃሴ ልባዊ አንድነት አይኖርም ማለት ነው፡፡ አብሮ መጋዝ ይቻላል እንጂ በአንድ ልብ ለመጓዝ አይቻልም፡፡ የይስሙላ እንጂ የልብ አንድነት አይኖርም፡፡ ቢቸግር ነው እንጂ ከአንድ ገበታ አይቆርሱም ማለት ነው፡፡ ‹‹ሳህን ቢበዛ አብረን በላን›› ማለት እንግዲህ ይሄው ነው፡፡
መጪው የህማማት ጊዜ ከራሳችን ጋር የምንጋገርበት፤ በጥሞና የምናሳልፍበትና ሃጢያታችንን የምንናዘዝበት ያድርልን። በተለይ ደግሞ ለፖለቲከኞቻችንና መሪዎቻችን።
ቅቱ ጥቅስ
‹‹ዛፍ ላይ ወጥቼ ልግደልህ፣ መሬት ሆኜ?›› ቢባል
‹‹ዛፍ ላይ ወጥተህ›› ብሎ መለሰ፡፡
‹‹ለምን?›› ቢለው፤
‹‹ዛፍ እስክትወጣ በህይወት እቆያለሁ…››
የወላይትኛ ምሳሌያዊ አነጋገር
በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ስም በተደራጀ ማህበር ሲሚንቶ ሲያከፋፍሉ ነበር የተባሉ ተከሳሾች ተቀጡ
በአቶ ሺመልስ አብዲሳ ስም በህገወጥ መንገድ በተደራጀ ማህበር ሲሚንቶ ሲያከፋፍሉ ነበር በተባለ ተከሳሾች ላይ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተሰጠ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ሽገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ትናንት በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ እንደተገለፀው ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ስም ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በህገ-ወጥነት በተደራጀው ማህበር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ የሚወጣ ሲሚንቶ በማውጣት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል። ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከመረመረ በኃላ በመዝገቡ ከተከሰሱ ተከሳሾች መካከል በስምንቱ ላይ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰኗል፡፡የቅጣት ውሳኔው ከተላለፈባቸው ተከሳሾች መካከል የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ባለሙያ አቶ አዲሱ አንጋሳ የሚገኙበት ሲሆን የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላም ከተከሳሾቹ መካከል ይገኙበታል፡፡
ፍርድ ቤቱ የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ባለሙያ በነበረው ተከሳሽ አቶ አዲሱ አንጋሳ ላይ የሃያ አመት ፅኑ እስራትና የሁለት መቶ ሺብር የገንዘብ ቅጣት የወሰነባቸው ሲሆን በክልሉ የቀድሞ የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላ ላይ ደግሞ የአምስት አመት ፅኑ እስራትና 10ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች እጅ ላይ የተገኙ 8ሺ ኩንታል ሲሚንቶ እና ከ565 ሺ ብር በላይ ገንዘብ እንዲወረስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
‹‹አዲስ አበባን ለማወቅ እሮጣለሁ›› ታላቅ የጎዳና ላይ ሩጫ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ከተማን ለማስተዋወቅ ያለመና ከከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በትብብር የተዘጋጀ የጎዳና ላይ ሩጫ ሊካሄድ ነው፡፡ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም የሚካሄደውና ኤም ጆይስ ኢቨንትስት ማርኬቲንግ ከአሀዱ ግሎባል ኔትወርክ ጋር ያዘጋጀው ይኸው የጎዳ ላይ ሩጫ በርካታ፤ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን የረመዳንን ፆም ምክንያት በማድረግ የአስር ቀና የአፍጥር ግብዣ፤ ፋሲካን በማስመልከት የምሳ ግብዣ እንዲሁም የጎዳ ላይ ሩጫና የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን ዛሬ አዘጋጆቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። በመስቀል አደባባይ ተጀምሮ እዚያው መስቀል አደባባይ በሚያበቃው የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ20ሺ እስከ 30ሺ ሰው ይሳተፍበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡