Administrator

Administrator

  ከዘመናችን የአለም ታላላቅ የሂሳብ ሊቃውንት አንዷ እንደሆነች የሚነገርላት እና የሂሳብ የኖቤል ሽልማት ተብሎ የሚታወቀውን የፊልድስ ሜዳል ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያዋና ብቸኛዋ የአለማችን ሴት የሆነቺው ኢራናዊቷ መሪየም ሚርዛካኒ በጡት ካንሰር ህመም በ40 አመቷ ማረፏ ተዘግቧል፡፡ ላለፉት ለአራት አመታት ያህል በጡት ካንሰር ስትሰቃይና ህክምናዋን ስትከታተል የቆየቺው ኢራናዊቷ የስታንፎርድ የሂሳብ ፕሮፌሰር መሪየም ሚርዛካኒ ባለፈው ቅዳሜ ለህልፈተ ህይወት መዳረጓን ሜይል ኤንድ ግሎብ ዘግቧል፡፡ መሪየም ሚርዛካኒ ኮምፕሌክስ ጂኦሜትሪ እና ዳይናሚክ ሲስተምስ በተባሉ ዘርፎች ባፈለቀቻቸው እጅግ ገራሚ ግኝቶቿ የሂሳብ የኖቤል ሽልማት ተብሎ የሚታወቀውንና በመስኩ የላቀ አስተወጽኦ ላበረከቱ ላላላቅ ተመራማሪዎችና መምህራን የሚሰጠውን የፊልድስ ሜዳል ሽልማት እ.ኤ.አ በ2014 ማግኘቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ መምህርት ሆና ስታገለግል መቆየቷንም አመልክቷል፡፡
በቴህራን በሚገኘው ሻሪፍ ዩኒቨርሲቲ እና በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን የተከታተለቺው መሪየም፣ የኢራን አለማቀፍ የሂሳብ ኦሎምፒያድ ሽልማት አሸናፊ ከመሆኗ በተጨማሪ የተለያዩ በርካታ አለማቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቷንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 በአለማችን የተለያዩ አገራት የሚገኙ 12.9 ሚሊዮን ህጻናት ምንም አይነት የክትባት አገልግሎት አለማግኘታቸውንና ይህም ክትባት ያላገኙ ህጻናትን ለከፉ በሽታዎች ያጋልጣል ተብሎ እንደሚሰጋ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣውና የ194 የአለማችን አገራትን የክትባት ሽፋን ደረጃ በሚያሳየው ሪፖርት እንዳለው በአመቱ ከአለማችን 10 ህጻናት አንዱ ምንም አይነት ክትባት ያላገኘ ሲሆን፣ በ8 የአለማችን አገራት ከሚገኙ ህጻናት በ2016 አመት የክትባት አገልግሎት ያገኙት ከግማሽ በታች ናቸው፡፡
አነስተኛ የህጻናት ክትባት አገልግሎት ካለባቸው የአለማችን አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የክትባት አገልግሎት መስፋፋት ለመቻሉ ፖሊዮን የመሳሰሉ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰቱ ሰበብ ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡
ተጨማሪ 6.6 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናትም ዲቲፒ የተባለውን የክትባት አይነት ለመጀመሪያ ዙር ከወሰዱ በኋላ፣ ቀሪ ሁለት ዙር ክትባቶችን ሳያገኙ መቅረታቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ክትባት በአለማችን ተቅማጥንና ቲታነስን ጨምሮ በተለያዩ የበሽታ አይነቶች ሳቢያ በየአመቱ ሊከሰቱ ይችሉ የነበሩ 3 ሚሊዮን ያህል የህጻናት ሞቶች እንዳይከሰቱ እያደረገ ይገኛል ያለው ሪፖርቱ፣ ባለፉት 10 አመታት በአገራት መካከል ያለው የክትባት ሽፋን ልዩነት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ በአለማቀፍ ደረጃ የተሟላ የጤና አገልግሎት አቅርቦትን ለማሟላት የተያዘውን የዘላቂ ልማት ዕቅድ ግብ ለማሳካት፣ በየአመቱ 371 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ መመደብ እንደሚያስፈልግ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
መንግስታት፣ ለጋሾችና በጎ አድራጊዎች በየአመቱ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ መድበው ከሰሩ እስከ 2030 ድረስ 97 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን በበሽታ ለህልፈተ ህይወት ከመዳረግ ሊያድኑ እንደሚችሉ የጠቆመው ድርጅቱ፣ ለአብዛኞቹ አገራት ይህን ያህል ገንዘብ መመደብ አዳጋች በመሆኑ ለጋሾች ድጋፋቸውን መስጠት እንደሚኖርባቸውም አመልክቷል፡፡

    • የበቆጂ አትሌቶች ለኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት 10 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፅፈዋል፡፡ 15 የዓለም አትሌቲክስ ሪከርዶች አስመዝግበዋል፡፡ እንዲሁም ከ34 በላይ        የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡
    • ጥሪዎች ለበቆጂ ሯጮች ትንሳዔ ከጋዜጠኛ፤ ከከንቲባ ፤ ከእውቅ አሰልጣኞች…
    • በመላው ኢትዮጵያ ትልልቅ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡ በቆጂ ግን የረባ ስታድዬምና የመሮጫ ትራክ የላትም፡፡ ለምን ?
    • አትሌቲክስ ኢንቨስትመንት ነበር… ግን የታላላቅ አትሌቶች መቆጠብ፤ የበቆጂ የተሰጥኦ አካባቢነት መዘንጋት

     ባለፉት 25 ዓመታት በታላላቅ የዓለማችን የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ለኢትዮጵያ የላቁ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ቆይተዋል፡፡  ትውልዳቸው በአርሲ  አሰላ፣ በቆጂና ሌሎች የገጠር ከተሞች ናቸው፡፡ በረጅም ርቀት  10ሺ  እና 5ሺ ሜትር፤ በመካከለኛ ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ዓለምን ተቆጣጥረዋል፡፡ በማራቶንና በጎዳና ላይ ሩጫዎች በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶችም የገነኑ  ናቸው፡፡
አንድ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ የሯጮች ከተማ በሚል በሰራው የፎቶ ቡክሌት የበቆጂ ጉብኝቱን አስመልክቶ  ‹‹…. የዓለማችንንን ምርጥ ማራቶን ሯጮች የልደት ምስክር ወረቀቶች ቢመረመሩ በቆጂ ተደጋግማ ትጠቀሳለች…›› በሚል መፃፉን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በ10ሺ ሜትር የአፍሪካን ፈር ቀዳጅ ድል ያስመዘገበችው ደራርቱ ቱሉ፤ በዓለም አትሌቲክስ የረጅም ርቀት ንጉስ ለመባል የበቃው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ10ሺሜ፤ በ5ሺ ሜትር የማይሰበር ክብረወሰን የያዘው ቀነኒሳ በቀለ፤ በኦሎምፒክ ማራቶን ልዕልቷን ወደ አገራቸው የመለሱት ገዛሀኝ አበራና ፋጡማ ሮባ እንዲሁም ቲኪ ገላና፤ ፤ የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ የተባለች ባለከፍተኛ ውጤት ባለቤት ጥሩነሽ እና የዘመኑ ምርጥ ፕሮፌሽናል ኢትዮጵያዊ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ፤ ፈጣኑ የኢትዮጵያ አትሌት መሃመድ አማን  ሌሎችም ከአርሲዎቹ የገጠር ከተሞች ተገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ በኦሎምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በዓለም አገር አቋራጭ፣ በአፍሪካ ሻምፒዮና፤ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች ከ67 በላይ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ ሰብስበዋል፡፡  
ከአዲስ አበባ በ230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው በቆጂ በተለይ የምትነሳ ናት፡፡ ደራርቱ ቱሉ በጣዕሜ ፤ ፋጡማ ሮባ በመራሮ፣  ጥሩነሽ ዲባባ በጨፋ፣ ቀነኒሳ በቀለና፣ ታሪኩ በቀለ፣ ቲኪ ገላናና፣ እልፍነሽ ዓለሙ በሌሙ፣ የተወለዱባቸው የገጠር መንደሮች ናቸው፡፡ የበቆጂን ዙርያዋና ከበዋታል።  የበቆጂ አትሌቶች ለኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት 10 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፅፈዋል፡፡  15 የዓለም አትሌቲክስ ሪከርዶች አስመዝግበዋል፡፡ እንዲሁም ከ34 በላይ የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎችን ሰብስበዋል፡፡
 በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ የቱርክ ጋዜጠኛ እንደጻፈው በቆጂ እንደ  አገር በመቆጠር በዓለም የአትሌቲክስ መድረክ ምን ያህል የገዘፈች መሆኗን በንፅፅር መመልከት ይቻላል፡፡  ባለፉት 25 ዓመታት በኦሎምፒክ መድረክ ከ60ሺ ነዋሪዎች ከሚገኙባት በቆጂ የወጡ አትሌቶች የሰበሰቧቸው ሜዳልያዎች  1.2 ቢሊዮን ህዝብ ያላት ህንድ በሁሉም ስፖርቶች በኦሎምፒክ ከሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎች የሚበልጥ፤ 247 ሚሊዮን ህዝብ ካላት ኢንዶኔዥያ በእጥፍ የሚልቅ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለናሙና ያህል ብቻ የዲባባ እህትማማቾች በኦሎምፒክ መድረክ ያገኟቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት 22 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሶሪያ እና 28 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሳውዲ አረቢያ በድምር ከሰበሰቡት የሚበልጥም ነው፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በዓለም ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክ እና በዓለም አገር አቋራጭ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ የሰበሰበችው የወርቅ ሜዳልያ ብዛት 179 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ፓኪስታን እንኳን አላስመዘገበችውም፡፡
በዚህ ከፍተኛ ስኬት የኢትዮጵያ ክብር በዓለም አትሌቲክስ በወርቃማ ቀለም እንዲሰፍር ሆኗል፡፡ በቆጂን በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅ የሯጮች ምድርም  አድርጓታል።
የአትሌቶቹ ውጤታማነት ላይ በየጊዜው በአትሌቲክስ ባለሙያዎች ምርምሮች እየተደረጉባት ይገኛል፡፡  በመላው ዓለም በሚሰራጩ ትልልቅ ሚዲያዎች  በተደጋጋሚ የምትጠቀስ ከተማ መሆኗም ቀጥሏል፡፡ በየጊዜው ልዩ ዘጋቢ ፊልሞች ተሰርተውላታል፡፡  በተለያዩ ጊዜያት ስለሚወጡባት ታላላቅ አትሌቶቿ፤ ስለመልክዓምድሯ፤ ስለአየር ንብረቷ፤ ስለ አትሌቶች አኗናር፤ ስልጠና እና የእለት ተዕለት ህይወት በስፋት እየተወሳ ነው፡፡  
ጥሪ ከጋዜጠኛው
በ1ኛው «አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» የጎዳና ሩጫ መነሻነት… በቆጂን በአትሌቲክስ ለማልማት
የታላላቅ  አትሌቶች መገኛ በሆነችው በቆጂ ከተማ  ለመጀመሪያ ጊዜ  የ5ነ ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ «አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» በሚል መርህ ከወር በፊት ተዘጋጅቶ ነበር። ከበቆጂ 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ  በተካሄደው ውድድር ከአምስት ሺ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲሁም አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ የከተማዋ የሩጫ ባህል ሆኖ የ5ኪ ሜትር ውድድሩ በአትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን ተሳታፊው ህዝብም  ችግኝ ይዞ በመሮጥ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫው ጭላሎ ሚዲያ ፕሮሞሽን በተባለ ድርጅት የተዘጋጀ ነው፡፣፡ ጭላሎ በበቆጂ ገዝፎ የሚታይ ልዩ ግርማ ሞገስ ያለው ተራራ ነው፡፡ የድርጅቱ ባለቤት   ጋዜጠኛ እና ገጣሚ አንዱዓለም ጌታቸው ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው በቆጂ ላይ ነው፡፡ ስለበቆጂ ልጆች አስተዳደግ እና የሩጫ ባህል ለስፖርት አድማስ ሲገልፅ‹‹ እንደማንኛውም የከተማዋ ተወላጅ ልጅነቴን ያሳለፍኩት በእረኝነት ነው ፡፡ ቤተሰብ  ሲልክህ ሮጥ ብለህ  ይባላል፡፡ ወደ ተላክበት የምትሮጠው ብዙ ርቀት ነው። ሽርካ የተባለች የገጠር ከተማ ወደ የሚኖሩ አያቶቼ ቤት ስላክ አስታውሳለሁ፡፡ 3 ሰዓታት ይወስድብኛል፡፡ አብዛኛውን እየሮጥኩ ነበር የምሸፍነው፡፡ ስለዚህ ሩጫ የልጅነት ህይወታችን አካል ነው፡፡ የከተማዋ ባህል ሆኖ አድገንበታል፡፡ …የሁሉ መነሻ  ከ25 ዓመታት በፊት የደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ፈርቀዳጅ ድል ማስመዝገቧ ነበር። ያኔ በቆጂ የነበረ ትውልድ በሙሉ ሯጭ መሆንን ተመኘ፡፡›› ብሏል።
አንዱዓለም እነ ቀነኒሳ፤ የዲባባ እህትማቾችና ሌሎችም ምርጥ አትሌቶች በተማሩበት ትምህርት ቤት ስለነበረው የሩጫ ትጋት እና ፍቅር ትውስታ አለው፡፡ በተለይ በእረፍት ሰዓት በተማሪዎች መካከል ይደረጉ የነበሩ ውድድሮች ናቸው። በቆጂ ዛሬም ድረስ ሩጫን  ባህሏ ያደረገች  ልዩ ከተማ ናት። በትምህርት ቤቶች ብቻ አይደለም፡፡ በከተማዋ ዙርያ ገብ በሚገኙ ጫካዎች፤ የተንጣለሉ መስኮች እና ጋራዎች ልምምድ እና ስልጠና የተለመዱ ትእይንቶች ናቸው፡፡
ጋዜጠኛ አንዷለም ምንም እንኳን ገና በታዳጊነቱ የሩጫ ህልም ቢኖረውም ብዙ አልገፋበትም፡፡ በከተማዋ ሚኒ ሚዲያዎች ግን ስለ በቆጂ ታላላቅ አትሌቶች ገድል በመዘገብ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ አድልቶ ነበር፡፡ በከተማዋ ከአትሌቲክስ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ለማከናወን ሲተጋ  ቆይቷል፡፡ ‹‹ በቆጂ የስሟን ያህል ትኩረት አላገኘችም፡፡ በስፖርት መሰረተ ልማቶች እጅግ ኋላ ቀር ናት፡፡ ስለዚህም ይቆጨኛል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ በገነነ የሯጮች ምድር  ሁለገብ ስታድዬም፤ የማሰልጠኛ ማዕከልና የመሮጫ ትራክ አለመኖሩ ተገቢ አይደለም፡፡ የዛሬ አስር ዓመት  የኢትዮጵያ አትሌቶች ሙዚዬም በከተማዋ ሊገነባ መሰረት ተጥሎ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ይህን ለመቀየር ነው የበኩሌን ጥረት ማድረግ የጀመርኩት፡፡›› በማለት የተነሳበትን ዓላማ ለስፖርት አድማስ አስረድቷል፡፡
ስለዚህም አንዷለም ጌታቸው ለከተማዋ ባደረበት ቁጭት የጎዳና ላይ ሩጫውን ለማዘጋጀት እንዲወስን አድርጎታል፡፡ ጭላሎ ሚዲያ የተባለ ድርጅቱን ካቋቋመ በኋላ በመጀመርያ ለ2009 የገና በዓል የአትሌቶች መንደር በሚል ልዩ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጀ፡፡ በቆጂ ማናት የሚለውን ጥያቄ መልስ ለመስጠት በተዘጋጀው በዚህ ልዩ ስነስርዓት እንደመዝናኛ የሙዚቃ ከንሰርት ከማዘጋጀቱም በላይ እነ ኃይሌ፤ ገዛሐኝ አበራ እና ሌሎች ትልልቅ አትሌቶች በክብር እንግድነት የተሳተፉበት ነበር፡፡ ከዚህ ተመክሮው በኋላ እንዷለም የመጀመርያውን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በከተማዋ ሊያስተናግድ ችሏል። የአትሌቶች መገኛ የሆነች ታሪካዊ ከተማ እንዴት ስፖርተኛ ህዝቧን የሚያሳትፍ ውድድር አይኖራትም በሚል ቁጭት በቀረፀው ፕሮጀክት ነው፡፡«አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» በሚል መርህ በስኬት የተካሄደውን የጎዳና ላይ ሩጫ በየዓመቱ ለመቀጠል እንደሚፈልግ ያሳወቀው አንዷለም፤ በተለይ በአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችን ታላላቅ አትሌቶች የተገኙባት በቆጂ ከተማ ተጎጂ መሆኗን ለዓለም ለማሳወቅ የሚያስችል ፈርቀዳጅ ሃሳብ በመሆኑ ውጤታማነቱን ያመለክታል ብሏል፡፡
አትሌቲክስ ስታድዬም በሚል ስያሜ ያልተሟላ መሰረተ ልማት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ትራክ የሌለው አጥር የለሌለው የበቆጂ ስታድዬም፡፡ በሌላ በኩል የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልም በተሟላ ግንባታና መሰረተ ልማት የሚንቀሳቀስ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በትኩረት ተገንብተው የሚንቀሳቀሱ አለመሆናቸው ከባድ ቁጭት የሚፈጥርብኝ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የውጤት መውረድ እና የላቀ ብቃት ያላቸው አትሌቶች በተተኪነት የማፍራት እድል የተበላሸው ከእነዚህ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ይመስለኛል፡፡›› በማለት አንዷለም ጌታቸው ለበቆጂ ከተማ የሚሰማውን ቁጭት ይገልፀዋል። በርግጥ የበቆጂ አትሌቶች ከስታድዬሙ እና ከማሰልጠኛ ማዕከሉ ይልቅ በተፈጥሯዊ መልክዓ ምድሮችን መስራት ይመርጣሉ ግን የስፖርት መነሰረተ ልማቶች መገንባት አለባቸው፡፡

ጥሪ ከከንቲባው
ለኢትዮጵያ ሆነ ለአፍሪካ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ  አትሌቶችን ለማፍራት
 የበቆጂ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ተስፋዬ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት  1ኛው «አረንጓዴ ልማት ለአረንጓዴ ጎርፍ» የጎዳና ላይ ሩጫው የበቆጂን 80 ዓመት ከመዘከሩም በላይ ከውድድሩ ጎን ትልልቅ አጀንዳዎች በማንገብ በመከናወኑ አስደስቶናል ይላሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የሚደረግ ዘመቻን ለማፋፋም፤ በአትሌቲክስ እየተንሰራፋ የመጣውን የዶፒንግ ችግር ተመለከተ የግንዛቤ እና የማስተማርያ መድረክ ለመፍጠር እንዲሁም ዜግነታቸውን የሚቀይሩ አትሌቶች እየበዙ መምጣታቸውን ተቃውሞ ለውጥ ለመፍጠር የሚደረጉ  ጥረቶችን ያስተዋወቅንበት መድረክ ስለሆነ በማለትም ማስረጃቸውን አቅርበዋል፡፡
‹‹በቆጂ የማትነጥፍ የአትሌቲክስ ስኬት ምንጭ ሆና እንድትቀጥልና ተከታዮችን ለማፍራት ታላላቅ አትሌቶች ያላቸው ምሳሌነት አስተዋፅኦ ቢኖረውም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡›› የሚሉት ከንቲባው ‹‹አትሌቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል ሰርተዋል ብሎ የከተማው መስተዳድርም ሆነ ህዝቡ አያምንም፡፡ ከተማዋ ጥሩ ስታድዬም፤ የልምምድ ማዕከል እንኳን የላትም፤ ይህ ደግሞ መቀየር አለበት ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በከተማው መስተዳድር፤ በወጣቶችና ስፖርት፤ በአትሌቲክስ ፌደሬሽንነና በሌሎች ባለድርሻ አካላት የተከናወኑ ጅምር ተግባራት መኖራቸውን አያይዘው የጠቀሱት ከንቲባው በቆጂ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ስታድዬም እንዲሁም የልምምድ እና ማሰልጠኛ ማዕከል መገንባት ለኢትዮጵያ ሆነ ለአፍሪካ ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡
‹‹ታላላቆቹ አትሌቶች በስፖርቱ ካገኙት ክብር እና አንፃር እንዲሁም በኢኮኖሚ ካላቸው አቅም ጋር ተያይዞ በቆጂ ላይ ብዙ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ይህን አስመልክቶ በየጊዜው ውይይት እያደረግን ቆይተናል፡፡ የአትሌቶችን ተግባራዊ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በከተማው አስተዳደር በኩል ለአትሌቶቹ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ሰርተናል፡፡ በአሰላ ከተማ የንግድ ማዕከል፤ ሆቴል የሰሩ አሉ፡፡ የከተማው መስተዳድር ከዚህ በፊት ለተለያዩ የልማት ስራዎች ይሆናል በሚል መሬቶችን ለአትሌቶች ሰጥቶ ነበር፡፡ ታላላቆቹ አትሌቶች በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የምንሰራቸው የግንባታ ስራዎች እስኪጠናቀቁ ግዜ ስጡን ብለው ስለነበር እንጅ። አትሌቶች ለእኛ አምባሳደሮቻችን ምልክቶቻችን ናቸው። የከተማው መስተዳድር አብሯቸው ለመስራት ይፈልጋል። እነሱም ፍላጎት እንዳላቸው እናውቃለን፡፡›› ብለዋል የበቆጂ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ተስፋዬ፡፡
የከተማው መስተዳድር በተለያዩ ክለቦች፤ በግብረሰናይ ተቋማት የተያዙ የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች እንደሚከታተል የከተማው ከንቲባ ተናግረው፤  የኦሮምያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሚያንቀሳቅሰው የበቆጂ ማሰልጠኛ ማዕከልም በመንግስት በጀት ተገንብቶ ከተለያዩ ስፍራዎች ተሰጥኦ ያላቸውን አትሌቶች በመመልመል በቂ ስልጠና በመስጠት እየሰራ መሆኑን፤ የብዙ ቀደምት አትሌቶች ዛሬም ቢሆን ዋና መገኛዎች ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው በዚያም ሰፊ ተግባር ለማከናወን እንቅስቃሴ አለ የሚሉት ከንቲባው በአጠቃላይ ግን በተሟላ ጥራት እና ብቃት እየሰራን ስላልሆንን ይህን በከፍተኛ ንቅናቄ ለመቀየር ትኩረት አድርገናል ብለዋል፡፡
ይቀጥላል

-------------------------------------------------
                          
                         የአፍሪካ ዋንጫን በቻይና ወይም በአሜሪካ የማዘጋጀት ሃሳብ ቀርቧል

      የ2023 የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድርን በቻይና፣ በአሜሪካ ወይም በኳታር ለማዘጋጀት እና ከአህጉሪቱ ውጭ የሚገኙ 3 አገራት ብሄራዊ ቡድኖችን በውድድሩ ለማሳተፍ የሚያስችል ምክረ ሃሳብ በአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ስብሰባ ላይ መቅረቡ ተዘግቧል፡፡
ካፍ የአፍሪካ የአግር ኳስ ዋንጫን የገንዘብ አቅም ለማጠናከርና ውድድሩን የበለጠ ሳቢነት ያለው ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር ባለፈው ማክሰኞ እና ረቡዕ በሞሮኮ ባካሄደው ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ ምክረ ሃሳብ፣ የ2023ን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያዘጋጁ ቻይናን፣ አሜሪካን ወይም ኳታርን የመጋበዝ አማራጭን ያቀረበ ነው፡፡ የገንዘብ አቅምን ማጠናከርንና የአፍሪካ ዋንጫን አለማቀፋዊ ማድረግን ግቡ ያደረገ ነው የተባለው ምክረ ሃሳቡ፣ በመገናኛ ብዙሃን በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ በበርካታ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ትችት እየተሰነዘረበት ይገኛል፡፡
ሃሳቡ በካፍ ተቀባይነት የማግኘቱ ዕድል ጠባብ መሆኑን የዘገበው ጋና ሶከር ኔት ድረገጽ፣ የ2023 የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ ተራውን ለጊኒ ቀደም ብሎ መስጠቱንም አስታውሷል፡፡

  • የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት እስከ 3 ሺህ ዓመት ይዘልቃል
                                        • ለሁሉም ቤተ-እስራኤላውያን እስራኤል አገራቸው፤ ቤታቸው ናት
        ተወልደው ያደጉት በደቡብ ጎንደር አምቦ በር በተባለች የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ በህጻንነታቸው እንደ ማንኛውም ገጠር ተወልዶ እንዳደገ ልጅ፤ ቤተሰቦቻቸውን እንጨት በመልቀም፣ ውሃ ከምንጭ በመቅዳትና በመላላክ እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ መብራት እንኳን በሌለበት የገጠር ቀበሌ ያደጉት የዛሬዋ እንግዳችን፤ በ16 ዓመት ዕድሜያቸው ወደ እስራኤል በማቅናት ከአገራቸውና ቀዬአቸው ርቀው፣ በሂብሩ ቋንቋ ትምህርት በመጀመራቸው የገጠማቸውን ፈተና
አጫውተውናል፡፡ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ክብርት አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያ፤ የዛሬ ሳምንት ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ፣ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር፡፡ ለተመራቂዎችም የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡ በስፍራው የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በአምባሳደሯ
ትውልድና እድገት፣ በእስራኤል ቆይታቸው ስለተጋፈጧቸው ፈተናዎች፣ ለአምባሳደርነት እስከመድረስ ስላበቋቸው የጥንካሬ ምስጢሮች፣ ስለ ኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት፣ በቤተ- እስራኤሎች የኑሮ ዘይቤና የመብት ጥሰቶች ዙሪያ (እጅግ በተጣበበ ሠዓታቸው) አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያን አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-

      ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ዩኒቨርስቲ ተከፍቶ፣ እርስዎም የክብር እንግዳ ሆነው፣ ተማሪዎችን ሲያስመርቁ ምን ተሰማዎት?
እምም. . . በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እንዲያውም ልንገርሽ… ከተመራቂዎቹ በላይ እኔን ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም እኔ እዚህ በማድግበት ጊዜ ዩኒቨርስቲ ቀርቶ ብዙ የትምህርት ዕድል አልነበረም፡፡ ደስታዬን እጥፍ ያደረገው አንቺ እንዳልሽው እዚህ አካባቢ ተወልጄ አድጌ፣ በዚህ ሀገር ወግና ባህል ታንፄ፣ ከዚያም ወደ እስራኤል አገር ሔድኩኝ፡፡ በወቅቱ ት/ቤት ስገባ የመማሪያ ቋንቋው እንኳን እንግሊዝኛ አልነበረም፤ ሂብሩ ነበር፡፡ አንዳንዴ መምህራን ሲያስተምሩ  አይገባኝም ነበር፡፡ መጀመሪያ በአማርኛ ጽፌ፣ ከዚያ ወደ መኝታዬ እሔድና ያንን ጽሑፍ ወደ እንግሊዝኛ እቀይራለሁ፡፡ ከዚያ ነው በስንት ልፋት ወደ ሂብሩ የምቀይረው፡፡ እኔ በእንደዚያ ዓይነት አስቸጋሪና ፈታኝ ጊዜ ነበር ያለፍኩት፡፡ ያንን ችግር የተጋፈጥኩት መማር ስለነበረብኝ ነው፡፡  
ተምረው ትልቅ ደረጃ ለመድረስ የነበረውን ህልም ከየት ነው የታጠቁት?
እኛ ቤተሰቦቻችን ያሳደጉን “ጠንክራችሁ ከተማራችሁ ትልቅ ደረጃ ትደርሳላችሁ፤ ለአገራችሁም ኩራት ትሆናላችሁ” በሚል ምክር ነበር፡፡ ይህንን ተከትዬ አስቸጋሪ ፈተናዎችን አልፌ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ ይህንን ስንቅ ያስታጠቁኝ ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡ ሌላውም ወጣት ምንም ፈተና ቢገጥመው፣ ዓላማ ካለው የፈለገበት መድረስ ይችላል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ዛሬ በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ይህቺን አገር የሚለውጡ ብዙ ራዕይ ያላቸው ተማሪዎች በአካባቢያቸው፤ በራሳቸው ቋንቋና በወገኖቻቸው ተምረው ተመርቀዋል፡፡ እኔም ተወልጄ ባደግሁበት አካባቢ፣ ያውም ዩኒቨርስቲ ተከፍቶ፣ እኔም እዚህ ደርሼ፣ በክብር እንግድነት ተጋብዤ ተማሪዎችን ስመርቅ፣ ከእነርሱ በላይ መደሰቴ ለዚህ ነው፡፡ አሁንም የምመክረው፣ ዓላማ ካላችሁ የትም ትደርሳላችሁ፤ እኔን ተመልከቱ የሚል ነው፡፡ በምረቃው ላይ ያስተላለፍኩትም መልዕክት ይሔው ነው፡፡
እንደሚያውቁት በተለይ በገጠሩ የአገራችን ክፍል፣ ሴት ልጅ ያለ ዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን ትጋፈጣለች፤ ዛሬ እነዚህን ፈተናዎች አልፋ ከተመረቁት 2653 ተማሪዎች፣ አጠቃላይ ብልጫ ያመጣችውን  ወጣት የሸለሙት እርስዎ ነበሩ --
እጅግ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ይገርምሻል እኮ ስሟ እንደኔው በላይነሽ ነው፡፡ ይሔ የሚያሳየው የራሷን ጥረትና ትግል እንዲሁም የዓላማ ፅናት ነው። አየሽ እኔም የገጠሩን አስተዳደግ አልፌበታለሁ፤ አውቀዋለሁ፡፡ ፈተናዎችን ተጋፍጠው ለዚህ የሚበቁ ልጆችን ሳይ ልቤ ይነካል፡፡ ደስታዬ ከልክ ያልፋል፡፡ አየሽ ነገ ይህቺ ልጅ የአገር መሪ ልትሆን ትችላለች፡፡ ዛሬ ያገኘችው ክብር፣ አድናቆትና ምርቃት ለበለጠ ክብርና ኃላፊነት እየገፋፋት ይሔዳል፡፡ ለሌሎች አቻዎቿም ምሳሌ ትሆናለች፡፡ ወደ ኋላም መሔድ አትፈልግም፡፡ ይህቺ ልጅ አገሪቷ በልጆቿ ተስፋ እንዳላት አመላካች ናት፡፡ ስላገኘኋት፤ ስላየኋት በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
እስቲ ስለ አስተዳደግዎ በጥቂቱ ያንገሩኝ ?
ከጎንደር 25 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በሚገኝ መንደር ነው የተወለድኩት፡፡ በጣም ጥሩ ጥሩና ጠንካራ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት። ትምህርትም የጀመርኩት እዚያው ሰፈር ውስጥ በነበረ ት/ቤት ነው፡፡ የእስራኤል ጂው (ቤተ እስራኤል) ከሆነ ቤተሰብ ነው የወጣሁት፡፡ አባቴ የታወቁ ትልቅ የሃይማኖት መሪ ነበሩ፤በተለይ አርብ አርብ መጽሐፍ ቅዱስ እየተነበበ፣ እንማራለን፡፡ በእኛ ሃይማኖት አርብ አርብ መሰብሰብ አለ፡፡ እራት የሚበላው በአንድ ላይ ነው፡፡ ከዚያ ለሕይወታችን የሚጠቅመንን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ አባታችን ያስተምሩን ነበር፡፡
ከያኔው የአባትዎ ትምህርት ይበልጥ ውስጥዎ የቀረውን ሊነግሩኝ ይችላሉ?
አንዳችን ሌሎችን እንደ ራሳችን ወድደን ስለመኖር፣ ተካፍለን ስለ መብላት፣ አካባቢያችንንና ሕዝቡን ስለ መውደድ፣ በአጠቃላይ ስለ አንድነትና ስለ ፍቅር ስንማር ነው ያደግነው፡፡ መማር ብቻም ሳይሆን ቤተሰብም ይህንን በተግባር ሲያደርግ ዓይቼ ነው ያደግሁት፡፡ እንዲያውም አባቴ ‹‹የእኛ ቤት እንደ አብርሃም ቤት ነው›› ይሉ ነበር፡፡ እነዚህ ትምህርቶችና ምክሮች አሁን ላለሁበት ደረጃ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የልጅነት ጊዜዬንም ከቤተሰቤ ጋር በደስታ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ይሔ ሁሉ አሁንም ትዝ ይለኛል፡፡
እስራኤል ምንድን ነው ያጠኑት?
በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በአፍሪካ ጥናቶች  ነው የመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪዬን የሰራሁት፤ በኋላ ፒኤችዲ ልሰራ ስል የሆኑ ሰዎች ‹‹ለምን አትሞክሪም፤ ዲፕሎማት መሆን ትችያለሽ›› የሚል ሃሳብ ሲያመጡ፣ ማስተርሴን እየሠራሁ ጥናትና ምርምር ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ምክንያቱም፤ የሠዎቹ ሃሳብ ወደ ውስጤ ሰርፆ ነበር፡፡ ከዚያ ዲፕሎማት መሆን አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ፡፡ ዲፕሎማት ከሆንኩ በኋላ ግን ወደዚህ እመጣለሁ ብዬ ያሰብኩት አሁን በመጣሁበት ወቅት አልነበረም፡፡ ለምን ብዙ ልምዶችን መቅሰም እንዳለብኝ አምን ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ ያው እንደሚታወቀው የዛሬ አምስት ዓመት አምባሳደር ሆኜ መጣሁ፤ ይሄው እየሠራሁ ነው፡፡
በአንድ ወቅት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተቋርጦ እንደነበርና መልሶ መቀጠሉን ሠምቻለሁ፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በአሁኑ ወቅት ምን ይመስላል?
ኢትዮጵያና እስራኤል በአሁኑ ወቅት ያላቸው ግንኙነት እጅግ በጣም በጣም የጠበቀ ነው። ግንኙነታቸው እስከ 3 ሺህ ዓመት ይዘልቃል፡፡ ከንጉሥ ሰሎሞንና ከንግሥት ሣባ ጊዜ ጀምሮ ማለት ነው፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም ጦርነት ስለነበረ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች፡፡ ግንኙነቱ እንደገና እ.ኤ.አ በ1989 ታደሰ። ግንኙነቱ ከታደሠ በኋላ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጥቶ፣ አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክቱ ነገሮችን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
የአገራቱ ግንኙነት ትልቅ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ከሚያመላክቱት አንዱ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ሲሆን ባለፈው ወርም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤልን መጎብኘታቸው የአገራቱን የጠበቀ ግንኙነት ያመለክታል፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽም፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከ3ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ አገራት ሕዝብ የተሳሰረ በመሆኑ፣ ይህን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሕዝብ ለሕዝብ፣ ዩኒቨርስቲ ለዩኒቨርስቲ፣ ሆስፒታል ለሆስፒታል ትስስር መፍጠር አለብን፡፡ እስራኤል ስፋቷና የሕዝቧ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም ትልቅ አገር ናት፡፡ በጠላት የተከበበች ብትሆንም በዕውቀት፣ በሥራና አገር በመውደድ የጠነከሩ ሕዝቦች ስላሏት አሁንም ትልቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ናት፡፡
ከዘመቻ ሠለሞን ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ በርካታ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል መሔዳቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከአኗኗር፣ ከሠብዓዊ መብት አያያዝ አኳያ የሚሰሙ ቅሬታዎች አሉ፡፡ እስቲ በዚህ ላይ ማብራሪያ ይስጡኝ?
የኢትዮጵያውያን ይሁዳዎች (ቤተ እስራኤላዊያን) በእስራኤል የሚኖሩት በጣም በጥሩ ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንድ ችግር ያለባቸውም አሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ ሚድያው የሚያሳየውን ካጤንሽው ብዙ ጥሩ ነገር አያሳይም፡፡ አንድ ነገር ሲነሳ ነው ሔደው ያንን ብቻ ለመናገር የሚፈልጉት፡፡ እኛ አንደኛ የጀርባ ታሪካችንን (background) ማየት አለብን። አብዛኞቹ ቤተሰቦቻችን አርሰው፣ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ፣ እጅግ የምንኮራባቸው ገበሬዎች ናቸው፡፡ እዚያ አገር ስትሔጂ ቴክኖሎጂው፤ የባህሉ ጫና አለ፡፡ ያንን ሁሉ አልፈን፣ በዚህ አጭር ጊዜ ትልልቅ ቦታ የደረሱ ልጆችን ማየት መቻላችን፣ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ እርግጥ ቀደም ሲል ከጠቀስኳቸው ነገሮች፤ ጫናዎች አንፃር አንዳንድ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ እነርሱን የማለፍ ብልሀት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ሁሉም ቤተ-እስራኤላዊያን፣ እስራኤል አገራቸው፤ ቤታቸው ናት። ሁሉም መብት አላቸው፡፡ እንደውም ለኢትዮጵያ ቤተእስራኤላዊያን መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማስትሬት ወይም ዶክትሬት ዲግሪያቸውን እስኪሰሩ  ድጋፍ አይለያቸውም። ቤት መግዛት ቢፈልጉ 80 በመቶውን ወጪ የሚሸፍነው የእስራኤል መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤሎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከራሺያ የመጣው ቤተ-እስራኤላዊ ተምሮ፣ ቴክኖሎጂውን አውቆ ነው፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ የኖርነው ደግሞ የኖርንበት ሥርዓት ሌላ ነው፡፡ ስለዚህ መደገፍ አለብን፡፡ ያንን ለማስተካከል የእስራኤል መንግሥት እየሠራ ሲሆን  ሌሎች በዚሁ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችም አሉ፡፡ ነገሮች በሒደት መቶ በመቶ ጥሩ ይሆናሉ፡፡


አለቃ ገብረ ሃና ከዕለታት አንድ ቀን መንገድ እሄዳለሁ ብለው ይነሳሉ፡፡
“ማዘንጊያ” ይላሉ ሚስታቸውን
“አቤት” ይላሉ ሚስት
“መንገድ ልሄድ አስቤያለሁ”
“ወዴት?”
“ወደ ቆላ ወርጄ የታመመ ጠይቄ፣ የተጣላ አስታርቄ እመለሳለሁ!”
“እንግዲያው ባዶ ሆድዎን አይሄዱም፤ ቆይ ቁርስ ደርሷል፡፡”
“ባዶ ሆዳችንን አደል የተፈጠርን?”
“ቢሆንም ወንድ ልጅ የሚገጥመው ስለማይታወቅ ባዶ ሆዱን አይወጣም”
“ሴትስ የሚገጥማት ታጣለች ብለሽ ነው? ካልሽ እንግዲህ ቶሎ አቅርቢልኝና ፀሃዩ ሳይገርር ልነሳ”
ወ/ሮ ማዘንጊያ ጉድ ጉድ ብለው ቁርስ አቀረቡና አብረው በልተው ተሰነባብተው ተለያዩ፡፡
አለቃ ቆላ ወርደው የታመመ ጠይቀው፣ የተጣሉትን ሁለት ሰዎች ሊያስታርቁ ግቢያቸው ሲደርሱ ጭራሽ ተጋግለው ቡጢ ሊቀማመሱ ግራ ቀኝ ሲሉ ያያሉ፡፡ ከሰዎቹ አንደኛው የተማረና አዋቂ የሚባል ነው፡፡
ሌላኛው ምንም ያልተማረና መሀይም ነው፡፡
መሀይሙ የተማረውን፡
“አንተ ደንቆሮ! ዶሮ ራስ!” ይለዋል፡፡
“አፍህን ዝጋ ነግሬሃለሁ!” ይላል የተማረው
“ደንቆሮ! ደደብ! ቆርቆሮ!” ይላል መሀይሙ፡፡
“ምንም ልሁን አፍህን ካልዘጋህ ዋጋህን ታገኛለህ!”
አለቃ፤
 “ተው እንጂ፤ ተው አይሆንም!” ይላሉ ሊገላግሉ መካከል ገብተው፡፡
መሀይሙ አሁንም፤ “ደንቆሮ! አለቃ፤ ይሄኮ ደደብ ነው!” ይላል፡፡
አለቃ፤ ሁለቱንም በተለያየ አቅጣጫ ገፍተው ይለያዩዋቸዋል፡፡
ይሄኔ አንድ መንገደኛ ድንገት ይደርሳል፡፡ አለቃ ያውቃቸዋል፡፡ ወደሳቸው ቀረብ ብሎ፤
“አለቃ ምን እያደረጉ ነው?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡
አለቃም፤
“ስድብ ቦታውን ስቶብኝ፤ ቦታ ቦታው እየመለስኩ ነው!” አሉ፡፡
*   *   *
በሀገራችን ቦታውን የሳተ ብዙ ነገር አለ፡፡ ዲሞክራሲ ቦታውን ስቷል፡፡ ዲሞክራቱ አፉን ዘግቶ ተቀምጦ ሐሳዊ - ዲሞክራቱ ከጣራ በላይ ይጮሃል፡፡ የተማረው ፀጥ ብሎ መሀይሙ ያለ እ ኔ ማን አለ ይላል፡፡ “ምሁሩ ስፒከር ነገር የለው፣ መሀይሙ ባለ አምፕሊፋየር ነው፤” እንደተባለው ነው፤ ይሄ ክፉ እርግማን ነው፡፡
የሀገራችን ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት
ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት!”
ይለናል፡፡ ቋንቋ ለቋንቋ ከመጠፋፋት ይሰውረን፡፡ ቋንቋ ለቋንቋ ካልተደማመጥን፣ ቋንቋ  ለቋንቋ ካልተግባባን ለፍትሕ አንመችም፡፡ ቋንቋ ለቋንቋ ካልተናበብን ለሃይማኖት፣ ለጐሣ፣ ለእርስ በርስ ግጭት እንዳረጋለን፡፡
ተወያይተን መፍታት የምንችላቸውን ነገሮች፣ ተጋጭተን ወይም ተዋግተን ካልፈታን ብለን ያዙኝ ልቀቁኝ እንላለን፡፡ ከዚህ እርግማን ይሰውረን፡፡ አንድን ነገር ባንድ ጥሞና መፈፀም ሲገባን፣ ሁለት ሶስት ነገር ካልፈፀምን ብለን ስንራኮት አንዱንም ሳንጨብጥ እንቀራለን፡፡
“ራስ ሴላስ መስፍነ ኢትዮጵያ” የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይለናል፡-
“ዐባይን ከምንጩም ከመድረሻውም በአንድ ጊዜ ለመጨለፍ አይቻልም፡፡
የእናትየው አበባ ሳይረግፍ ልጅ እንቡጥ ትታቀፋለች፡፡ አባትየው ዓለምን ለመተው ዝግጁ ሳይሆን  ልጅ እውስጥ ገብቼ ልፈትፍት ይላል፡፡ በአንድ ጊዜ ደግሞ ለሁለት ትውልድ ቦታ የለም!”
አባት ታጋይ ቦታውን ለመልቀቅ ዝግጁ ሳይሆን ተተኪ ትውልድ ቦታውን ልውረስ ይላል እንደ
ማለት ነው፡፡ መተካካት ቀላል የማይሆነው ለዚህ ነው፡፡ ወጉ እንጂ ግብሩ ሩቅ ነው፡፡ የ60ዎቹ ዓመታት ታጋዮች (ዛሬ ያሉትን ያሸነፉትንም ጨምሮ) በየትኛውም መልኩ ተደራጅተው ይታገሉ የነበሩት ጊዜው የፈቀደውን ያህል ብስለት ነበራቸው፡፡ ትምህርቱ፣ ዕውቀቱ፣ ቅን ልቦናው ነበራቸው፡፡ ትግላቸው ዛሬ አቁሟል? ወይም ነገም ይቀጥላል? የትላንቱ ታሪክ የት ጋ ቆሞ አዲሱ ታሪክ የት ጋ ጀመረ? ታሪክ ተመራማሪዎች ይፈትሹት፡፡ አንድ ዕውነት ግን አለ፡፡ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ጨምሮ፣ ያ የዱሮው አስተሳሰብ ዛሬ፤ ሁሉም ላይ፣ ጥላውን ያጠላባቸዋል፡፡ የትግል ልምዳቸው ያው የትላንትናው ነው፡፡ “የነቃ፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ ኃይል ያሸንፋል!” ነው የሁሉ ነገር መፍትሔያቸው፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ ዛሬ ቋንቋ ለቋንቋ መግባባት ያቃተው፡፡ ከንግግር ከውይይት ይልቅ ጦር መነቅነቅ ይቀናናል (Not the word but the sword እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ፡፡)
ያደግነው በህቡዕ ትግል (Clandestine Struggle) ውስጥ ነውና በሁሉም ወገን ያለን ፖለቲከኞች፤ በሰላም አገርን እናስብ ሲባል የባቢሎንን ግንብ እንደምንገነባ ሁሉ ቃል ለቃል መግባባት እርም ይሆንብናል፡፡ ፅንፍ መለየት (Polarization) ብቻ መፍትሄ ይመስለናል፡፡
ለሀገር ስንል ግማሽ መንገድ እንኳ አብረን እንሂድ መባባል ሽንፈት ይመስለናል፡፡ ገጣሚው እንዳለው፤ “ከዋሸህ ሽምጥጥ፤ ከመታህ ድርግም!” የሚል ፅንፈኛ መርህ ብቻ ሆኗል የሚገዛን! ትላንት ያልነውን ዛሬ ለመሻር ከቶም ዐይናችንን አናሽም፡፡ ለእለት ፖለቲካ እስከበጀን ድረስ መካድና መካካድ አይገደንም። ዋሽተን ማጣፊያው ሲያጥረን “ፖለቲካ እኮ ነው!” እንላለን፡፡ የመዋሸት ሊቼንሳ አለን እንደማለት፡፡ መንግስትም፣ ፓርቲም፣ ተቃዋሚም፣ ደጋፊም ይሄ ሊቼንሳ ያለው ነው የሚመስለው፡፡ አገር ያጠፋው አገር አለማሁ ይላል፡፡ ሙሰኛው የፀረ ሙስና ህግ አውጪ ይሆናል፡፡ ግፈኛው ስለ ፍትሕ ይሰብካል፡፡ መሀይሙ የተማረውን ቀጪ ተቆጪ ይሆናል፡፡ ቦታ ቦታው ያልተመለሰ አያሌ ወንጀለኛ በናጠጠባት አገር ዕድገት ማምጣት ከባድ ፈተና ነው፡፡ መንግሥት ይዋሻል ወይ? ሙሰኛ አለ ወይ? ፓርቲ ይሰርቃል ወይ? ወዘተ ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም፡፡ መልሱ፤ “አያ፤ የብሳና ዛፍ ይሸብታል ወይ?” ቢለው “ለዛፍ ሁሉ ያስተማረው ማን ሆነና ነው” አለው፤ የሚለው ተረት ነው፡፡

- አንድ የፓርላማ አባል በወር 10, 640 ዶላር ይከፈለዋል
- የግል ቤትና መኪና መግዣ የ257,400 ዶላር ብድር ይሰጠዋል
የኬንያ መንግስት የሰራተኞች ክፍያ ወጪውንለመቀነስ ሲል የፓርላማ አባላትን ወርሃዊ ደመወዝ  በ15 በመቶ ለመቀነስ ማቀዱን የዘገበው ቢቢሲ፤የአገሪቱ የፓርላማ አባላት ከፍተኛ ደመወዝ ከሚያገኙ የአለማችን ህግ አውጪዎች ተርታ ኬንያ የፓርላማ አባላትን ደመወዝ
በ15% ልትቀንስ ነው እንደሚሰለፉ ዘግቧል፡፡የኬንያ የፓርላማ አባላት በወር 7 ሺህ 200 ዶላር ደመወዝ ያገኙ እንደነበር ያስታወሰው
ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት የያዘው አዲስ እቅድ ደመወዛቸውን በ15 በመቶ ከመቀነሱ በተጨማሪ፣በየሰበብ አስባቡ ያፍሱት የነበረውን ዳጎስ ያለ ውሎ አበልና ጥቅማጥቅም እንደሚያሳጣቸውም ገልጧል።አዲሱ ውሳኔ የመንግስት ባለስልጣናትን ደመወዝና ጥቅማጥቅሞች በከፍተኛ ሁኔታ
የሚቀንስ ነው ያለው ቢቢሲ፤ ከዚህ ቀደም የወር ደመወዛቸው ከ16 ሺህ ወደ 14 ሺህ ዶላር ዝቅ የተደረገባቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም በአዲሱ ህግ ሌላ ቅናሽ እንደሚደረግባቸው አመልክቷል፡፡በአገሪቱ አማካይ ወርሃዊ ገቢ 150 ዶላር ብቻ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ የሚመለከተው የአገሪቱ ኮሚሽንም የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመገምገምና የፓርላማ አባላቱ ይህን ያህል ገንዘብ ማግኘታቸው አግባብ አለመሆኑን በማመን ቅናሽ እንዲደረግበት መወሰኑን ጠቅሶ፣ የደመወዝ ቅናሹም በመጪው ነሃሴ ወር መጀመሪያ የሚካሄደውን ብሄራዊ ምርጫ ተከትሎ ተግባራዊ ይደረጋል መባሉን አስረድቷል፡፡የኬንያ የፓርላማ አባላት ከ7 ሺህ 200 ዶላር ደመወዝ በተጨማሪ ከሚያገኙዋቸው ጥቅማጥቅሞች መካከልም፣ የ67 ሺህ 400 ዶላር የግል መኪና መግዣ ብድር፣ ለቤት መግዣ የሚውል የ190 ሺህ ዶላር ብድር፣ ለመንግስት ስራ የሚውል የ48 ሺህ ዶላር መኪና፣ እንዲሁም የ3 ሺህ 440 ዶላር ወርሃዊ የትራንስፖርትና የመኪና ጥገና ወጪ አበል እንደሚገኙበት ዘገባው ዘርዝሯል፡፡


    “ከግብር እና ከሞት ማንም አያመልጥም” ይሉ ነበር አሜሪካኖች፡፡ ቱጃሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ “ላወቀበት ብዙ መንገድ አለ” ይላሉ። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የ916 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው በማሳየት ለ18 አመታት ያህል ይህ ነው የሚባል የፌደራል ታክስ እንዳልከፈሉ ይነገራል፡፡ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት በሚወዳደሩበት ወቅትም “የግብር ህጉን ክፍተቶች (loopholes) በመጠቀም አያሌ ረብጣዎችን ከግብር አድኛለሁ” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል፡፡ “ችግሩ የኔ ሳይሆን የህጉና የህግ አውጭዎቹ ነው፡፡” በማለትም ጣታቸውን ወደ ተፎካካሪያቸው የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተን ቀስረው ነበር፡፡ በመሰረቱ ግብር ማጭበርበር (tax evasion) እንጂ ከግብር ማምለጥ (tax avoidance) ወንጀል አይደለም፡፡
በግብር ጉዳይ በመንግስትና በዜጎች መካከል እሰጥ አገባዎችን ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ መንግስት ከግብር ብዙ ገቢ ለመሰብሰብ ሲጥር፣ ዜጎች በበኩላቸው፣ ከግብር ለማምለጥ ሲታትሩ፣ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በግብር ጉዳይ በዜጎችና በመንግስት መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ብዙ ዙፋኖች ተነቃንቀዋል፡፡ ትላልቅ ግዛቶች (empires) ወድቀዋል፡፡ ለግብፅ፣ ለሮምና ለስፔን ሰፋሪ ግዛቶች (empires) መፍረስ አንዱ ምክንያት በግብር ምክንያት የተቀሰቀሱ አመፆች እንደሆኑ ይነገራል።
ብሪታኒያ ከአትላንቲክ ማዶ ካለው ሰፊው ርስቷ የተቀነሰችው፣ የአሜሪካም አብዮት የፈነዳው በግብር ምክንያት በተፈጠረ እሰጥ አገባ መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በስኳር ላይ የተጣለው ግብር፣ የቴምብር ቀረጥና በሻይ ላይ የተጣለው ታክስ በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩትን ሰፋሪዎች አስቆጣ፡፡ በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ ሳንወከል በሚወጡ የግብር ህጎች መገዛት የለብንም (No taxation without representation) አሉ፡፡ በዚህ ሰበብ የተለኮሰው የአመፅ እሳት፤ ብሪታኒያን አንገብግቦ አስወጣት፤ ሰፋሪዎቹም ነፃ የአሜሪካን መንግስት መሰረቱ፡፡
የፈረንሳይ አብዮትም የፈነዳው ሀገሪቷ የተቆለለባትን ግዙፍ ዕዳ ለመክፈል ዜጎቿ ላይ የጫነችው እጅግ የበዛ ግብር የህዝቡን ቁጣ በመቀስቀሱ ነው፡፡ ከበርቴው ከግብር ነፃ ሲሆን፣ ገበሬውና የሰራተኛው መደብ በተጫነባቸው ከፍተኛ ግብር ክፉኛ ማቅቀዋል፡፡ ይህ ፍትሐዊነት የጎደለው የግብር ስርዓት፤ የፈረንሳይን አብዮት አስነስቶ፣ ሉዊስ 16ኛም ስልጣኑን ብቻ ሳይሆን ህይወቱን አጣ፡፡ ለእንግሊዝ አብዮት አንዱ መነሻም በግብር ምክንያት የተነሳ ብሶት ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በግብር ምክንያት በርካታ ንትርኮችና አለመግባባቶች በመንግስትና በዜጎች መካከል ተፈጥረዋል፡፡ ሰሞኑን በመዲናችን አዲስ አበባ በደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሚሰማው ብሶት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን የሚወጡት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን (ኢገጉባ) በቀን ገቢ ላይ ተመስርቶ በሚወስነው የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ይህ በግምት ላይ ተመስርቶ የሚከፈል የደረጃ “ሐ” ግብር፣ የአፈፃፀም ችግሮች ብቻ ሳይሆን ይህን ለመወሰን የመጡት የግብር ህጎችም የራሳቸው ክፍተቶች አሉባቸው፡፡
በተሻሻለው የግብር አዋጁ መሰረት የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ ማለት አመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከ500 ሺህ ብር በታች የሆኑ ግለሰቦች ናቸው፡፡ የትኛውንም ያህል መጠን የሚያገኙ ድርጅቶች ግን እንደ ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ ይቆጠራሉ፡፡ በቀድሞው የግብር አዋጅ ደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ ማለት አመታዊ ገቢያቸው ከ100 ሺህ በታች የነበሩት ናቸው፡፡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግብር የሚከፍሉት አማካይ የቀን ገቢያቸው ተገምቶ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን (ኢገጉባ) ባስቀመጠው ቀመር መሰረት ነው፡፡ ደረጃ “ሐ” ለግብር አሰቸጋሪ (hard - to - tax) የሚሆኑ የስራ ዘርፎች የተሰባሰቡበት መደብ ነው፡፡ በዚህ መደብ ላይ የጣለው ግብር ምንጊዜም ከውዝግብ ርቆ አያውቅም፡፡
ከዚህ መደብ ሥር ያሉ ግብር ከፋዮችን የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ ማድረግ ለግብር ከፋዮቿም ሆነ መንግስት ግብርን ለመሠብሠብ የሚያደርገውን ወጪ በእጅጉ ያበዛዋል፡፡ ለዚህም ነው በቀን ገቢ ግምት ላይ የተመሠረተ ግብር እንዲከፍሉ የሚደረገው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ይህን ግብር ለማስፈፀም የወጡት አዲሱ የገቢ ግብር ደንብ ሠንጠረዥም ሆነ መመሪያ ቁጥር 123/2009 ችግሮች ይታዩባቸዋል፡፡ ለተፈጠረው የትመና ችግርም የየራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡
የአዲሡን የግብር አዋጅ መውጣት ተከትሎ፣ አዲስ የግብር ደንብ ተረቅቆ በዚህ ወር ይወጣል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ ረቂቅ ደንብ ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የተሰማሩባቸውን የንግድ ዘርፎች ይዘረዝራል፡፡ ይህ ሠንጠረዥ ከጌሾና ብቅል ንግድ ጀምሮ እስከ ጀበና ቡና ንግድ ድረስ በአጠቃላይ ዘጠና ዘጠኝ የንግድ ዘርፎችን አካቶ ይዟል፡፡
ይህ ዝርዝር በሃገሪቱ ውስጥ ብሎም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎችን ያጠቃልላል ብሎ ማሠብ አይቻልም፡፡ ይህ የግብር ሰንጠረዥ የንግድ ሚኒስቴር ከተዘጋጀው የንግድ ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ከሚጠቀምበት የንግድ ስራ ፍቃድ መስጫ መደቦች መመሪያ (Ethiopian standard industrial classification) ጋር ቢጣጣም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይህ የንግድ ሥራ ፍቃድ መስጫ መደቦች መመሪያ የራሡ የሆኑ ክፍተቶች ቢኖሩትም፣ ከሞላ ጎደል በሃገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ የንግድ ስራዎችን ያካተተ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በግብር ደንቡ ባለው ሠንጠረዥ ላይ ብቻ ተመስርቶ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብርን መሠብሰብ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል፡፡
ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የሚከፍሉት የግብር  መጠን የሚወሠነው የግብር ከፋዩን የቀን ገቢ መጠን ሊያሳዩ የሚችሉ አመላካቾችን (indicators) በመጠቀም ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ አመለካከቶች (indicators) ሙሉ ለሙሉ ተጨባጭ (objective) ናቸው ማለት አይቻልም። የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት የሚጠቀምባቸው መለኪያዎች ሙሉ ለሙሉ ተጨባጭ ካለመሆናቸው በተጨማሪ ገቢ በመገመት ሂደቱ ላይ የገማቾች የተለያየ ህላዓዊ ፍርድ (Subjectivity) ሲታከልበት በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያሉ ግብር ከፋዮች የተለያዩ መጠን ያለው ግብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ይህ የቀን ገቢ መጠን ላይ የተመሠረተ ግብር በተቻለ መጠን ህሊናዊ ፍርድን (Subjectivity) እስካላስቀረ ድረስ እና ሳይንሳዊነትን እስካልተላበሠ ድረስ ኢ-ፍትሐዊ (in-equitable) ግብር መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡
ችግሩን የከፋ ያደረገው ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የቀን ገቢ ላይ የተመሠረተ ግብር ትመና የተካሔደው ከስድስት አመታት በፊት 2003 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ በነዚህ ስድስት አመታት ውስጥ የገቢያቸው መጠን የጨመረ የሚጠበቅባቸውን ግብር ሳይከፍሉ፣ የገቢያቸው መጠን ያሽቆለቆለ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው፤ ያልተገባ ግብር ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ‹‹ጭራሽ ከመቅረት ዘግይቶ መድረስ ይሻላል›› እንደሚባለው፤ ከስድስት አመታት በኋላም ቢሆን የግብር ክለሳ መካሔዱም አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን፤ በትመና ሥራው ላይ የተሠማሩ ሰዎችን በዘመቻ ካሠለጠነ በኋላ የትመና ሥራውንም በዘመቻ እንዲሠሩ ማድረጉ፣ እውነተኛ ገቢን እንዲሁም ግብርን ማንፀባረቅ አለመቻሉ፤ ቅሬታንም መፍጠሩ የሚያስገርም አይደለም፡፡
የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብ ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ በመያዝ የተወሰነባቸውን የቀን ገቢ እንዲሁም በዚያ ላይ የተጣለውን ግብር የማስቀየር (rebut) የማድረግ ዕድሉ በህግ ተደንግጎ ቢሠጣቸው ችግሩን በተወሠነ መልኩም ቢሆን መቀነስ ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ዕድል የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋይን የሒሳብ መዝገብ እንዲይዝ ያበረታታዋል፡፡ የያዙትን የሒሳብ መዝገብም በማየት ከደረጃ ‹‹ሐ›› ወደ ደረጃ ‹‹ለ›› እና ደረጃ ‹‹ሀ›› የተሸጋገሩ ግብር ከፋዮችን በቀላሉና በማያሻማ ሁኔታ መለየት ይቻላል፡፡ በአሁን ሰአት በደረጃ ‹‹ሐ›› ያሉ ግብር ከፋዮች ወደ ሌሎች የግብር ደረጃዎች መሸጋገራቸውን ግብር ሠብሣቢው መሥሪያ ቤት እንዴት እንደሚመዝን ማሠብ በራሡ ትልቅ ጥያቄ ያጭራል፡፡
ግብርን መደበቅ፣ በገቢ ትመና ወቅትም እቃዎችን መሰወር፣ ህፃናትን በሱቆች ላይ አስቀምጦ መሔድ፣ ሱቅ ዘግቶ መጥፋት እና የመሣሠሉት ችግሮች የሚፈጠሩት በግብር ከፋይ ዘንድ የግብርን ጥቅም ካለመገንዘብ በተጨማሪ ፍትሐዊ ያልሆነ ግብር መጫኑ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ተገቢነት የሌለውን ከፍተኛ ግብር በመፍራት ሱቁን ዘግቶ ቢጠፋ ምንም አያስገርምም፡፡
በገቢ ግብር ደንቡ ሠንጠረዥ ላይ የተቀመጠው አማካይ የትርፍ (Profitability rate) መቶኛ  በራሱ እንዴት እንደተወሠነ ግራ አጋቢ ነው፡፡ በሠንጠረዡ ላይ ያሉ የንግድ ዘርፎች አይከስሩም የማለት አንድታም ያለው ይመስላል፡፡ በደረጃ ‹‹ሐ›› ሥር ያሉ ግብር ከፋዮች እንደማንኛውም ነጋዴ የሚያጋጥማቸውን ትርፍም ሆነ ኪሣራ የረሳው ይመስላል፡፡
ይልቁንም በዚህ መደብ ያሉ አነስተኛ ግብር ከፋዮች የገጠማቸውን ኪሣራ በሒሳብ መዝገብ የሚያስረዱበት እድል ቢፈጠርላቸው፣ ኪሣራቸውንም እንዲያሸጋግሩ ቢፈቀድላቸው በርካታ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ በመያዝ፤ አሁን የተፈጠረውን ችግር መቀነስ ይቻላል፡፡ መንግስት ከአፈፃፀም ችግሮች በተጨማሪ የህጉንም ግድፈቶች በማየት የግብር ከፋዩን ቅሬታ ሊፈታ ይገባል፡፡

“መንግስት የእንቦጭን ጉዳይ እንደ ብሄራዊ አጀንዳ ቢይዘው ጥሩ ነው”
ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ 11 ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቋል
በአገሪቱ ግዙፍ የምርምር ማዕከል እያስገነባ ነው

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 6536 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ያስመረቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ ቀዳሚ ነው የተባለ የቴክኖሎጂ ምርምርና ፈጠራ ማዕከል ግንባታም እየተጠናቀቀ ነው ተብሏል፡፡ ዘንድሮ 11 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋወቀው ዩኒቨርሲቲው፤ ስድስቱን በቀጥታ
ለተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶች አስተላልፏል፡፡ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ፕሮጀክቶችንም ተወዳድሮ በማሸነፍ እየሰራ እንደሚገኝ
የጠቆመ ሲሆን በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጤና ተቋማት የመረጃ አያያዝን ለማዘመን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የ3.5 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት መፈጸሙን አመልክቷል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የሚከበር ግዙፍ የትምህርት ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ባደረገው እንቅስቃሴ፣ ለከተማዋ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የ16 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በነዋሪው ዘንድከፍተኛ ተወዳጅነትን ላተረፈው ፋሲል ከነማ (አፄዎቹ) የስፖርት ክለብም የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ለከተማው ነዋሪዎች ያስገነባው ግዙፍ የሪፈራልሆስፒታልም ከዩኒቨርሲቲው ሰናይ ተግባራት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፓርትመንት በበኩሉ፤ በእንቦጭ አረም ከፍተኛ የመድረቅ ስጋት የተጋረጠበትን የጣና ኃይቅን
ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተርና የመካኒካል ኢንጅነሪንግ መምህር አቶ ሰለሞን መስፍን፤እንቦጭ አረምን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረትና በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡


 እንቦጭ አረምን ለማጥፋት እያደረጋችሁት ካለው ጥረት እንጀምር----
በጣና ላይ የተከሰተውን እንቦጭ አረም፣ በሰው ኃይል በእጅ ለማንሳት መሞከር የማይቻል ነው። የግዴታ ማሽን ያስፈልጋል፡፡ በቪክቶሪያ ኃይቅ ላይ ተከስቶ የነበረን እንቦጭ አረም ለማንሳት ጥቅም ላይ የዋለው ማሽን ነው፡፡ ከተንሳፋፊ ጀልባ ጋር ተገጣጥሞ የሚሰራ ማሽን ነው አረሙን ሊያነሳ የሚችለው፡፡ የጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውን ይህን አረም ለማንሳትም  በራሳችን ተነሳሽነት፣ በዩኒቨርሲቲው የምህንድስና ክፍል ውስጥ አንዱን ማሽን ገጣጥመን እያጠናቀቅን ነው፡፡ ለዚሁ አረም ማጥፊያነት ብቻ ነው ይህ ማሽን የተሰራው፡፡
ማሽኑ እንዴት ነው አረሙን ለማጥፋት ጥቅም ላይ የሚውለው?
ከፊት ባለው (አካፋ መሰል) አካሉ ተንሳፋፊውን አረም እየጎተተ፣ ወደ ውስጥ በመቀረጣጠፍ ያስገባዋል፡፡ መሃል ላይ ባለው የማሽኑ ክፍል ደግሞ አረሙ ይፈጫል፣ የተፈጨው ተመልሶ ውሃው ላይ አይጣልም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ አረሙ በስሩም፣ በግንዱም የመራባት አቅም ስላለው፣ በቋት ተጠራቅሞ ከኃይቁ አካባቢ በራቀ ቦታ ላይ ይጣላል፡፡ በሌላው ሀገር መሰል አረምን ለማጥፋት ስራ ላይ የሚውሉ ማሽኖች፤ የተፈጨውን  አረም የማጠራቀሚያ የራሳቸው ቋት የላቸውም፡፡ ወደ ሌላ ጀልባ በመገልበጥ ነው የሚያጠራቅሙት፡፡ እኛ ግን ማሽኑ የራሱ ቋት እንዲኖረው አድርገን ነው የሰራነው፡፡
የዚህ አረም የጉዳት መጠን እንዴት ይገለጻል?
 አረሙ በባህሪው ከመሬት ጋር የሚገናኝ ስር የለውም፤ ዝም ብሎ ውሃው ላይ ነው እየተራባ የሚንሳፈፈው፡፡ በዚህ ሂደት ውሃውን እየመጠጠው በማድረቅ፣ ደረቅ መሬት እየፈጠረ ይሄዳል፡፡ በአሁን ወቅት የሃይቁን ዳርቻ ብንመለከት፣ በዚህ መንገድ አረሙ መሬት ፈጥሯል፡፡ አረሙ በባህሪው ውሃ ይወዳል፡፡ ውሃውን ደግሞ ቀድሞ ከነበረው ሦስት እጥፍ ነው የትነት መጠኑን የሚያሳድገው፡፡ ለዚያም ነው ሃይቆችን ሙሉ ለሙሉ የሚያደርቀው፡፡ ለምሳሌ ከአፍሪካ ታላላቅ ወንዞች አንዱ በሆነው ዛምቤዚ ወንዝ ላይ የተፈጠረው እንቦጭ አረም፣ የኃይል ማመንጫ ኃይሎች ሁሉ እንዲዘጉና እንዲቋረጡ አድርጓል፡፡ ለኛም የህዳሴ ግድብ ይሄ አረም ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ምክንያቱም በቀላሉ እየተንሳፈፈ ከዚህ ወደ ግድቡ መሄድ የሚችል ነው፡፡ ወደፊት ፕሮጀክቱ ሲጀምር ፈተና ነው የሚሆንበት፡፡
አረሙ የጤና ችግርም ያመጣል፡፡ በባህር ትራንስፖርት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ የዓሳ ሀብት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ዓሳዎች እንዳይራቡ ያደርጋል፡፡ የኦክስጅን ዝውውሩን ስለሚገታ መራባት አይችሉም፡፡ ለዓሣ አጥማጆችም ፈተና ነው የሚሆንባቸው፤ መረባቸውን መዘርጋት አይችሉም፡፡
አረሙ ከስሩ ሊጠፋ የሚችለው ምን ቢደረግ ነው?
አረሙን ማጥፋት አይቻልም፤ እንዳይስፋፋ ማድረግ ነው የሚቻለው፡፡ እኛ በሰራናቸው ማሽኖች ነው አረሙን መግታት የሚቻለው፡፡ እኛ የሰራነው አንድ ማሽን ነው፤ ነገር ግን አሁን በጎንደር አዋሳኝ ብቻ የተከሰተውን አረም ለማስወገድ ተመሳሳይ ስድስትና ሰባት ያህል ማሽኖች ያስፈልጋሉ። ምናልባት በባይሎጂካል መንገድ አረሙን የሚመገቡ ጢንዚዛዎችን በማምጣት በረዥም ጊዜ መስፋፋቱን መቀነስ ይቻል ይሆናል፤ ግን ይሄ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የኛ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር ሳሙኤልም በፈንገስ አረሙን መቋቋም የሚችል ንጥረ ነገር ለማዘጋጀት ሞክሯል፡፡ እነዚህ ምርምሮች በላብራቶሪ ሙከራ ደረጃ ውጤታማ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመስክ ላይ በሚገባ መሞከር ያስፈልጋል። ሌሎች ሀገሮች ኬሚካልም ይጠቀማሉ፡፡ የኛ ግን ሃይቅ እንደመሆኑም ብዝሃ ህይወትን ስለሚጎዳ ኬሚካል መጠቀም አይቻልም፡፡
ግን አረሙ ከየት ነው የመጣው?
 አመጣጡ ላይ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ምክንያት እስካሁን አልቀረበም፡፡ መጀመሪያ የታየው መገጭ ወንዝ ላይ ነው፡፡ ግን ወደ ሀገር ውስጥ እንዴት እንደመጣ አይታወቅም፡፡ በእርግጥ ከኛ ቀድሞ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ በተለይ በቪክቶሪያ ሃይቅ ባለቤት ሀገሮች ነው የገባው፡፡ ግን ወደኛ ሀገር እንዴት እንደመጣ አይታወቅም፡፡ አንዳንዴ ከከተማ የሚመጡ ፍሳሾች እንዲህ አይነቱን አረም የመፍጠር እድል አላቸው፡፡ ከጎንደርም ሆነ ከሌሎች ከተሞች የሚለቀቁ ፍሳሾች ከጣና ሃይቅ ጋር መገናኘት የለባቸውም፡፡ ግን መነሻው ይሄ ፍሳሽ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጥናትና ምርምሮች መካሄድ አለባቸው። በዋናነት የአረሙ መነሻ ደቡብ አሜሪካ ነው፡፡ አረሙ አበባ ያወጣል፡፡ በደቡብ አሜሪካ ይሄን አበባ ለቤት ማስዋቢያና ጌጣጌጥ ይጠቀሙበት ነበር። አሁን ይሄ አረም በዓለም ላይ ካሉ አስር አስከፊ አረሞች አንዱ ነው፡፡
በጣና ላይ የተከሰተው አረም በፈረንጆቹ 2014/15፣ 44 ሺህ ሄክታር መሸፈኑን የሚያመለክት መረጃ አለኝ፡፡ አረሙ ደግሞ ከ12 እስከ 18 ቀናት ውስጥ ራሱን በእጥፍ የማባዛት ባህሪ አለው፡፡ ይሄ በጣም አደገኛ ባህሪው ነው፡፡ እኛ ሀገርም ሆነ ሌሎች ሀገሮች ላይ ይሄ አረም ሃይቆችን አድርቋል። ጣና ላይም ይሄ የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለም። ይሄን ጉዳይ ቢቻል መንግስት እንደ ብሔራዊ አጀንዳ ቢይዘው ጥሩ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውና ጥቂት የመንግስት አካላት ብቻቸውን ሊወጡት አይችሉም። ሌላ የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይሄን ጉዳይ የሚከታተል አካል በመንግስት ተቋቁሞ ቢሠራ መልካም ነው፡፡
የሰራችሁት ማሽን ምን ያህል አረም በቀን ያፀዳል?
 በሰዓት እስከ 5 ቶን ማስወገድ የሚችል ነው። አረሙ ውሃ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ማሽኑ ውሃውን እየጨመቀ ነው የሚፈጨው፡፡ ይሄን ማሽን የሚያንቀሳቅሱ ባለሙያዎችም አሉን፡፡ ሐምሌ መጨረሻ ላይ ማሽኑ ወደ ሀይቁ ተወስዶ ይሞከራል፡፡ ወደ ስራም ይገባል፡፡ ተጨማሪ ማሽን ይመረት ከተባለም ጨምረን እናመርታለን፡፡ አረሙን ለማጥፋት በሰው ኃይል ቢሞከር ውጤቱ እምብዛም ነው፡፡ አወጋገዱም አስተማማኝ አይደለም፡፡ አረሙ መልሶ ችግር እንዳይፈጥር በአግባቡ መወገድ አለበት፡፡
ታዲያ የተፈጨው አረም ሲጣል መልሶ ችግር አይፈጥርም?
የተለያዩ ሀገሮች ይሄን አረም ከሀይቁ ወይም ከውሃ አካሉ ካስወገዱት በኋላ ለተለያየ ነገር ይጠቀሙበታል፡፡ ከአረሙ ባዮጋዝ፣ ሜቴን ጋዝ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከአረሙ ከሰልን ተክቶ ሊነድ የሚችል ብሪኬት መስራት ይቻላል፡፡ ኬንያዎች በቅርቡ ለዱባይ ማዳበሪያ ፋብሪካ ኤክስፖርት አድርገዋል፡፡ ለማዳበሪያ ምርት ይሆናል፡፡ ኬንያዎች ከኩባንያው ጋር ውል ገብተው፣ እየፈጩ ኤክስፖርት በማድረግ ገቢ እያገኙበት ነው፡፡ ቡና እና ሻይ ኤክስፖርት አድርገው ካገኙት ገቢ በላይ ከዚህ አረም አግኝተዋል፡፡ ለዚህ ነው መንግስት በዚህ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አለበት የምለው፡፡ በቅርቡ አስራ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ነው ከውጭ ያስገባነው፡፡ ይሄን ከሸጠልን ኩባንያ ጋር ለምን አረሙን ለመሸጥ አንዋዋልም? ይሄን መንግስት ማሰብ አለበት፡፡ ትልቁ ነገር ይሄን አረም ማስወገድ ቢሆንም የተወገደውን በዚህ መልኩ ለሀገር ጥቅም ማዋል ይቻላል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ምርምሮችና ፈጠራዎች ላይ እየተሳተፈ ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 38 የሚደርሱ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ተመርተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አዳዲስ ፈጠራዎችም አሉን፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች እኛ ጋር መቅረት የለባቸውም፤ ስራ ላይ መዋል አለባቸው የሚል እቅድ ይዘን ወደተጠቃሚዎችም እያደረስን ነው፡፡ በቅርቡ አራት የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ወደ ተጠቃሚዎች አድርሰናል፡፡ ለምሳሌ በቱሪዝም ጉዳይ የጀርመንና የአማርኛ ቋንቋ መተግበሪያ (Application) ሰርተናል፡፡ በተለይ ለአስጎብኚዎች ይሄ መተግበሪያ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ በአንድሮይድ ስልኮች ላይ በቀላሉ የሚጫን፤ ጀርመንኛን ወደ አማርኛ፣ አማርኛን ወደ ጀርመንኛ ቋንቋ የሚቀይር መተግበሪያ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን ለአስጎብኚዎች፣ ለዞኑ ቱሪዝም መምሪያ አስረክበናል፡፡ ሌላው የሰሜን ጎንደርና የደቡብ ጎንደርን የጉብኝት ቦታዎችና አንዳንድ ሆቴሎችን መገኛ የያዘ ዲጂታል ካርታ አዘጋጅተን አስረክበናል፡፡ ይህ ካርታ በህትመትም ይገኛል፡፡
የጎንደር፣ ላሊበላና አክሱምን የሚያገናኝ ካርታም በኛ የጂአይኤስ ባለሙያዎች ተሰርቷል፡፡ ይሄ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ከማስተዋወቅ አንፃር ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቱሪስቶች፤ ያለ ሰው እርዳታ ህንፃዎችን፣ ቤቶችን፣ ሆቴሎችን በአጠቃላይ የሚፈልጓቸውን ቦታዎች በቀላሉ ማግኘት የሚያስችላቸው የአሰሳ (Navigation) መተግበሪያ፣ የኛ ተማሪዎች ሰርተው ለጎንደር ከተማ አስተዳደር አስረክበናል፡፡
በፀሐይ ኃይል ብቻ የሚሰሩ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችንም ሰርተናል፡፡ በባዮ ጋዝና በሜቴን የሚነዳ መኪና ሰርተናል፡፡ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎቹ አሁን ሙከራቸው ተጠናቆ፣በኩባንያ ደረጃ መመረት ነው የሚቀራቸው፡፡ የሚያመርቱ ኩባንያዎች መፈጠር አለባቸው፡፡ እነዚህ ከመጡ እኛ ቴክኖሎጂውን ለማካፈል  ዝግጁ ነን፡፡ እኛም ራሳችን ይሄን የሚያመርት ኩባንያ መፍጠር አለብን፡፡ ሌላኛው ለተጠቃሚዎች ያደረስነው ቴክኖሎጂያችን፣ የላፕቶፕ ባትሪን የተመለከተ ነው። ብዙ ጊዜ የላፕቶፕ ባትሪ ውድ ከመሆኑም በላይ ሲያረጅ ያለው አማራጭ መጣል ብቻ ነው፡፡ እኛ ግን አያገለግልም የተባለውን ባትሪ በቀላሉ እየሞላን ወደ አገልግሎት መመለስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው የፈጠርነው፡፡ ለወደፊት እዚሁ ማምረት የሚቻልበት ሁኔታም እየተሰራ ነው፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ ዘንድሮ የ106 የዩኒቨርሲቲው መምህራንን ላፕቶፖች ባትሪ ሞልተናል፡፡ የዚህ ፈጠራ ባለቤት ዩኒቨርሲቲውና የሰሩት ግለሰቦች ናቸው፡፡
ቴክኖሎጂውን ከዩኒቨርሲቲ ውጪ ላሉ ተጠቃሚዎች እንዴት ልታደርሱ አስባችኋል?
 ለህብረተሰቡ ማድረስ ጀምረናል፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኙ 20 ሥራ አጥ ወጣቶችንና ከዞኑም ወደ 28 ሥራ አጥ ወጣቶች፣ በድምሩ 48 ሥራ አጥ ወጣቶችን አሰልጥነን ወደ ስራ እንዲገቡ አድርገናል። ጎንደር ከተማ ላይ በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ያረጁ የላፕቶፕ ባትሪዎችን የሚሞሉ ወጣቶች አሉ። አንድ ባትሪ ከ1400 ብር በላይ ነው የሚሸጠው፡፡ ወጣቶቹ ግን በ500 ብር ነባሩን አዲስ አድርገው፣ ደንበኛው መልሶ እንዲጠቀምበት እያደረጉ ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ይውላል ተብሎ የሚታሰበውን የንፋስ ሀይል፣ ለከርሰ ምድር ውሃ ማውጫነት የሚያውል ቴክኖሎጂ አዘጋጅተናል፡፡ ሰሜን ደባርቅና ዳባት አካባቢ ከፍተኛ የንፋስ ፍጥነት አለ፡፡ አምባጊዮርጊስ አካባቢ በንፋስ ኃይል የሚሰራና 120 ሜትር ጥልቀት ውስጥ ያለን ውሃ ወደ ገፀ ምድር የሚያፈስ ፓምፕ ሰርተናል፡፡ እሱን በቅርቡ እናስመርቃለን፡፡ ይህ ከከርሰ ምድር የወጣ ውሃ ንፁህ ስለሆነ ለመጠጥም ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ለመፍጠሪያነት ይውላል፡፡
እኛም ለመስኖ ልማት የሚውል ሃይቅ ለመፍጠር አቅደን፣ ገበሬዎች የሚበዙበትን አካባቢ መርጠን ነው ፓምፑን የተከልነው፡፡ ውሃውን ለመስኖ እንዲጠቀሙ አቅደን ነው ይሄን ያደረግነው። ሁሉንም መጥቀስ ጊዜ ይወስዳል እንጂ እንደዚህ ያሉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ 38 የቴክኖሎጂ ሽግግሮችና ፈጠራዎችን አዘጋጅተናል፡፡
የ3D ማተሚያ ማሽን፣ ዶክመንቶችን የማጠራቀሚያ አፕሊኬሽን፣ የፍ/ቤት ጉዳዮችን መከታተያ መተግበሪያ አፕሊኬሽን ሰርተናል፡፡ የፍ/ቤት መከታተያ መተግበሪያው በተለይ የሀገራችንን የፍ/ቤት አሰራር ለማዘመን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ባለጉዳዮች በቀጥታ ቀጠሮአቸውን እንዲከታተሉ ከማድረጉም ባሻገር በአንድ ጉዳይ ላይ ዳኞች ቢለዋወጡ እንኳ ቀጣዩ ዳኛ የቀድሞው ከቆመበት እንዲቀጥል በቀላሉ መረጃ የሚሰጠው ይሆናል፡፡
ከግብርና ጋር በተያያዘ ምርታማ ዘሮችን የማላመድ፣ ወተትን ከቅቤ በቀላሉ የሚለይ ማሽንም ሰርተናል፡፡ በቅርቡ ከተጠቃሚዎች ጋር ርክክብ እናደርጋለን፡፡ እስከ ሐምሌ 30 ሁሉም የተጠናቀቁ የምርምር ስራዎቻችንን ለተጠቃሚዎች የማድረስ እቅድ ነው የያዝነው፡፡ ለ2010 ደግሞ ሌሎች እቅዶች ይዘናል፡፡ ፓተንት ያገኘንባቸውን ቴክኖሎጂዎች በርካታ ኩባንያዎች  እንድንሸጥላቸው እየጠየቁን ነው፡፡ ለወደፊት በተገቢው መንገድ እንዲያገኙት ይደረጋል፡፡
አሁን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከላችሁ አነስተኛ ነው፡፡ ለወደፊት ምን ታስቧል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ግዙፍ የሚባለውን የወርክሾፕና የፈጠራ ማዕከል እየገነባን ነው፡፡ ግንባታውም በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በርካታ የምርምር ማዕከሎችን የያዘ ግዙፍ የምርምር ማዕከል ነው፡፡ በሀገራችን የእንስሳት ህክምና ሆስፒታል የለም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግን ይሄን እውን ለማድረግ የእንስሳት ህክምና ሆስፒታልም እየገነባ ነው፡፡    



ቀን አንዲት ድመት አንድ አውራ ዶሮ ታይና አድፍጣ ልትበላው ትፈልጋለች፤ በእርግጥ ልትበላው አይገባትም በህጉ፡፡ አውራ ዶሮው በመሠረቱ፤ ድመት አውራ ዶሮ የመብላት ባህል የላትም በሚል በቸልተኝነት ግቢው ውስጥ እየተጐማለለ ይዝናናል፡፡ አመሻሽ ላይ ነው፡፡
በመጨረሻ ድመቷ ዘልላ ከመያዙዋ በፊት፤ ምክንያት እንደሚያስፈልጋት አሰበችና እንዲህ አለችው፤
“እንደምን ውለሃል አያ አውራ ዶሮ?”
አውራዶሮም፤ “ደህና ነኝ፡፡
እንደምን ውለሻል እመት ድመት”
እመት ድመትም፣
“ሌሊት ሌሊት እየጮህክ ሰዎችን ከእንቅልፋቸው እየቀሰቀስክ እስከ ዛሬ ስትረብሽ ከርመሃል፡፡ ከእንግዲህ ግን ይሄ አጉል የምትጮኸው ነገር ያበቃል፡፡ አሁን እርምጃ ልወስድብህ ነው” አለችው፡፡
አውራ ዶሮው፤ እመት ድመት እንደተሳሳተች በመገመት፤
“እመት ድመት ሆይ በጣም ተሳስተሻል፡፡ እኔ የምጮኸው ሰዎች ማለዳ እንዲነሱና እንዲነቁ፣ የዕለት ሥራቸውን በጠዋት እንዲጀምሩ፤ በዚህም ኑሯቸውን ለማስተካከል እንዲችሉ እንጂ ለመረበሽ አይደለም፡፡ እንዲያውም እኔ ባልኖር በትክክል ጊዜን ለማወቅ አይችሉም ነበር” አለና ተከላከለ፡፡
እመት ድመት ግን በግትርነት፤
“ሰዎች ጊዜውን ለማወቅ ቻሉም አልቻሉም፣ እኔ እራቴን ሳልበላ ማደር የለብኝም” ብላ ዘላ ቀጨም አደረገችው፡፡
* * *
የማናቸውም ጥሩ ምክንያት መኖር አንዴ በልቡ ለመብላት ያሰበን ሰው ከማድረግ አያግደውም፡፡
“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ይሏታል” የተባለው ተረት የተገላቢጦሽ ሆነ ማለት ነው፡፡
ህዝብን ተሳታፊ የማያደርግ እንቅስቃሴ ዘላቂ አይሆንም፡፡ አመራር ሁሉ ሀቀኛ ተመሪ ያገኝ ዘንድ ግድ ነው፡፡
ተሳታፊነት በውዴታ እንጂ በግዴታ የሚሆን አይደለም፡፡ የህዝብ ቀዳሚ አብሪ ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱን ያልያዘ (መያዝም ቢሉ በውዴታና ከልብ) ለውጥ የሚያቆጠቁጥ አይሆንም፡፡ ቻይናዎች “ጀልባ ማንቀሳቀስ ከፈለግህ ወደ ወንዙ መቅረብ አለብህ” የሚሉት በአግባቡ ለመቅዘፍ እንዴት እንደሚቻል ልብ እንድንል ነው፡፡
መሪና ተመሪ ልባዊ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሪና ተመሪ የአዕምሮ አቅም መመጣጠን (Congruence of wavelength) ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሪና ተመሪ የአቋም መጣጣም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሪና ተመሪ ከጌታና ሎሌ ግንኙነት የተላቀቁ መሆን አለባቸው፡፡ መሪና ተመሪ የመተካካት ባህል ሊኖራቸው ይገባል እንጂ አይተኬ - ነኝ (indispensable) የሚል ሰው የሚኖርበት መሆን የለበትም፡፡
በተለይም ተመሪው ወይም ተከታዩ “መሪዬ ከሌለ ወዴት እደርሳለሁ?” የሚል ሥጋት ያለው ከሆነ፤ አንድም መሪው ብቸኛና አይተኬ ነኝ እንዲል ይገፋፋዋል፤ አንድም ደሞ ተመሪው ራሱን ለተተኪነት እንዲያዘጋጅ፤ በቆመበትና ባለበት ሁኔታ ያግተዋል፡፡ ቻይናዎች እንደሚሉት “ከዶሮዎች መካከል ያለች ፒኮክ በቀላሉ ትለያለች” ማለት ነው፡፡
መሪው አይተኬ ሆነ ማለት ይኼው ነው፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ መሪ አይተኬ ነኝ ብሎ ሲያስብ ብዙ ዓይነት ባህሪያትን ያንፀባርቃል፡እኔ ያልኩት ምንጊዜም ልክ ነው ከሚል ተነስቶ፤ እኔ ያልኩት ካልተፈፀመ ሞቼ እገኛለሁ፤ ይላል፡፡ ያጠናውን፣ የፃፈውን የተናገረውን በሀገሩ ላይ ይፈትናል፡፡ ወይም ይፈትሻል፡፡ ኢኮኖሚው በእጁ ይወድቃል፡፡ በየጉዳዩ ላይ ቅድመ ፍርድ ይሰጣል፡፡ “ስታሊን እንደንስ” ሲል ማን ቁጭ ብሎ ያያል” ይላል ክሩስቼቭ። እሱ ሲስቅ አገር ይስቅ ዘንድ፣ እሱ ሲቆጣ አገር ይቆጣ ዘንድ ግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አሁን አሁን የእኛን ሙሰኞች ከሙስና እንዲፀዱ ማድረግ “ውሻን አይጥ መያዝ ማስተማር” ዓይነት ከባድ ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡ ሌባ ያዝ ተብሎ የተላከው፤ ራሱ ሲሰርቅ ይገኛል፡፡ ሲሰርቅ ተይዞ እሥር ቤት የገባው፤ ሌላ ዓይነት ሌብነት ተምሮ ይወጣል “ሞኝ ያስራል ብልጥ ይማራል” የተባለው ዓይነት፡፡
የሙስና ዲግሪ የሚሰጥ ቢሆን፤ በመሬት፣ በቤት፣ በቢሮክራሲ፣ በቴክኖክራሲ፣ በሌበር - አሪስቶክራሲ፣ በብሔር - አሪስቶክራሲ የሚሸለሙ ስንቶችን አፍርተን ነበር - ባይልልን ነው እንጂ፡፡
“የመጨረሻው ድህነት በህይወት ውስጥ ምንም ምርጫ ማጣት ነው፡፡”ይሉናል፤ የፈረንጅ ፀሐፍት፡፡ ወይም ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለን፤ “ማጣት፤ በነብስህ ጫፍ ሩቅ አልመህ ሁሉን መሳት” ማለት ነው፡፡
በየጉዳዩ ላይ ምርጫ ያጣ ህዝብ እጅግ ደሀ ህዝብ ነው፡፡ ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ገዛ ኢኮኖሚው፣ ስለ መናገር ነፃነቱ፣ ስለ ቤት ንብረቱ አማራጭ የሌለው፤ የዓለም ባንክ ባልደነገገው መንገድ የድህነት ምርኮኛ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን፡፡ በየአቅጣጫው ዙሪያ ገባውን በችግር ማጥ የተወረረ ህዝብ ያልታደለ ነው፡፡ ያም ሆኖ እንደ መኮንኑና እንደ ጄኔራሉ ውይይት፤ የታሪክ ምፀት ባለቤት መሆኑ ባይቆጭ ያንገበግባል፡፡
መኮንኑ - “ኧረ ዙሪያውን ተከበናል፤ ጄኔራል?” ሲል
ጄኔራሉ - “አሪፍ ነዋ በፈለግነው አቅጣጫ እንተኩሳለን” አለ አሉ፡፡
አዎንታዊነት? ጨለምተኝነት? ትራጆ - ኮሜዲ? ወይስ ፋርስ? ዞሮ ዞሮ ምፀት ነው፡፡

አሐዱ ኤፍኤም 94.3 ሬዲዮ ጣቢያ የሙከራ ስርጭቱን የጀመረ ሲሆን ከሐምሌ 15 ቀን 2009 በኋላ መደበኛ ፕሮግራሞቹን እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ጣቢያው በይፋ ስርጭት መጀመሩን አስመልክቶ የሬዲዮ ጣቢያው የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን  ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫና የጉብኝት ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፤ከስምንት ዓመታት አድካሚና እልህ አስጨራሽ ሥራ በኋላ ጣቢያው የብሮድካስቲንግ ፈቃድ አግኝቶ ተቋቁሟል፡፡  
የኤዲስቴይለር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ በሆነው ኤዲስቴይለር ሚዲያ ሴንተር ውስጥ የተቋቋመው ይኸው የሬዲዮ ጣቢያ፤የኢትዮጵያውያን ድምፅ በመሆን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለማስታወስና ለማስተዋወቅ እንዲሁም ማህበራዊና ባህላዊ ህይወትን ለማጠናከር እንደሚሰራም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡  
የኤዲስቴይለር ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ በላይ በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት፤ ጣቢያው እንደ ስሙ በመረጃ፣ በቴክኖሎጂና በአቀራረቡ ቀዳሚ ሆኖ አድማጮቹን ቀዳሚ ለማድረግ ይተጋል፡፡ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች በማደራጀትም የተቋቋመበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይሰራል፡፡ ጣቢያው በሚዲያው ዘርፍ የልዕቀት ማዕከል (Center of Excellence) የመሆን ራዕይ እንዳለውም ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የሬዲዮ ጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤የሬዲዮ ጣቢያው በአገሪቱ የሚገኙትን የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ቁጥር በአንድ ከፍ ከማድረግ በዘለለ የራሱን ቀለምና መልክ ይዞ በማህበረሰቡ አኗኗርና አስተሳሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል፡፡
የአሐዱ ሬዲዮ ዋና አዘጋጅ አቶ ካሣ አያሌው ካሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ጣቢያው በረቀቁ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና በዘመናዊ ስቱዲዮ የተደራጀ ከመሆንም ባለፈ በሙያው ልምድ ባካበቱና ለሙያቸውና ለሚያገለግሉት ህዝብ ክብር ባላቸው ሙያተኞች የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፤ ጋዜጠኛው ራሱ የቴክኒኩንም ሥራ እየተቆጣጠረ ፕሮግራሞችን የሚሰራበት አዲስ አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ገልፀዋል፡፡
ጣቢያው ከሬዲዮ ስርጭቱ በተጨማሪ የድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን እያደራጀ እንደሚገኝና ድረ ገፁ የአሐዱ ሬዲዮንን መሰረታዊ ባህርያት ተከትሎ፣ ከድምፅ ባሻገር መረጃዎችን በፅሁፍ፣ በፎቶና በቪዲዮ አስደግፎ እንደሚያቀርብና የሬዲዮ ስርጭቱንም በኢንተርኔት በቀጥታ እንደሚያስተላልፍ ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሙከራ ስርጭት ላይ የሚገኘው የሬዲዮ ጣቢያ፤ከመጪው ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ ስርጭቱን እንደሚጀምርም ተገልጿል፡፡