Administrator

Administrator

ኤኤችዋን ኤንዋን (AHINI) የተባለው አዲሱ ጉንፋን መሰል ኢንፍሌዌንዛ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተቀስቅሶ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት በጥር ወር ብቻ በተደረገ ቅኝት፣ 32 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸውንና ከእነዚህ መካከልም አራቱ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ዳዲ ጂማ ተናግረዋል፡፡
ወቅትን ጠብቆ የሚቀሰቀስ ጉንፋን መሰል በሽታ እንደሆነ የተነገረለት የኢንፍሎዌንዛ በሽታ፤በፍጥነት ከሚዛመቱ በሽታዎች መካከል የሚመደብ ሲሆን ተገቢው ህክምና ካልተደረገለትም ለሞት ሊያጋልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
እንደ ማንኛውም የጉንፋን በሽታ በትንፋሽና ከአፍንጫ በሚወጣ ፈሳሽ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ የህዝብ ትራንስፖርቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና ሰዎች በስፋት የሚሰባሰቡባቸው ሥፍራዎች በሽታውን በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ለማስተላለፍ ምቹ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በሽታው በተለይም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትንና ከስልሣ አምስት አመት በላይ የሆናቸውን ሰዎች እንዲሁም ነፍሰ ጡር ሴቶችን በይበልጥ ያጠቃል፡፡ አንድ ሰው ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ እያለ ምንም አይነት የህመም ስሜቶች ሳይኖሩት በሽታውን ሊያስተላልፍ እንደሚችልና ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከ5-7 ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች እንደሚተላለፍ ዶ/ር ዳዲ ተናግረዋል፡፡
 በስኳር፣ በደም ግፊት፣ በልብና የኩላሊት በሽታዎች መያዝ ለኢንፍሉዌንዛ ይበልጥ ተጋላጭ  የሚያደርግ ሲሆን ሁለቱ በአንድ ላይ በቀላሉ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡ በጉንፋን መሰሉ ኢንፍሎዌንዛ የተያዘ ሰው ከመደበኛው የጉንፋን በሽታ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ትኩሳት፣ ሳል፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ መከርከርና የጡንቻ መገጣጠሚያ ህመሞች፣ የአፍንጫ ፈሳሾችና ማስነጠስ የበሽታው ዋንኛ ምልክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በታዩ ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ኤኤችዋን ኤንዋን የተባለው ኢንፍሌዌንዛ፤ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ሲሆን በዓለም በየዓመቱ ከ3-5 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙና ከ500ሺ በላይ የሚሆኑት በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከአለም ጤና ድርጅት የተኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በላብራቶሪ ምርመራ የተገኙት የኢንፍሎዌንዛ በሽታ ናሙናዎች አሜሪካ አገር ወደሚገኘው “ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል” (CDC) መላካቸውንና ይህም የተደረገው በሽታው በየጊዜው ባህርይውን ስለሚለዋውጥ፣ ለተጨማሪ ምርመራ እንደሆነ ዶ/ር ዳዲ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የአለም ጤና ድርጅት፤አለም አቀፍ የጤና ሥጋት እንደሆነ የጠቆመው የዚካ ቫይረስ በአገራችን መከሰቱን የሚያረጋግጡ መረጃዎች እስከ አሁን አለመገኘታቸውንና አገሪቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን የገለፁት የሥራ ኃላፊዎች፤ የቫይረሱን መኖር አለመኖር ለማረጋገጥ የሚያስችል ኬሚካል ከውጪ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ቫይረሱ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ እንደነበር የሚያሳዩ ፍንጮች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡  

  በወተት ውስጥ የሚኘውን የአፍላቶክሲን ኤም 1 ይዘት ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ መጀመሩን “ብሌስ አግሮ ፉድ ላብራቶሪ” አስታወቀ፡፡
በከብቶች መኖ ላይ የሚገኘውንና ከብቶች ከተመገቡት በኋላ በሚሰጡት የወተት ምርት ላይ ዓይነቱን ቀይሮ የአፍላቶክሲን ኤም 1(Aflatoxin M1) የሚሆነውን እንዲሁም ካንሰር የማምጣት አቅም አለው የተባለውን መርዛማ ንጥረ ነገር ይዘት ለማወቅ የሚያስችል የላብራቶሪ ፍተሻ መጀመሩን የገለፀው ድርጅቱ፤ ይህም ወተት አምራች ገበሬው በቅርቡ በተፈጠረው የመረጃ መዛባት ሳቢያ ያጣውን የገበያ ዕድል መልሶ ለማግኘት ያስችለዋል ብሏል፡፡
 ምርመራው፤ ሸማቹ ማህበረሰብ ደረጃውን የጠበቀ የወተት ምርት ለማግኘት የሚያስችለው  እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ የላብራቶሪ ፍተሻው የተጀመረው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የወተት አቀናባሪዎች በጠየቁት መሰረት መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ ቀደም ሲል የላብራቶሪ ፍተሻው የሚከናወነው ወደተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት በመላክ እንደነበር አስታውሶ፣ አዲሱ አሠራር ይህንን ለማስቀረት ያስችላል ብሏል፡፡  

 ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአህጉሪቱ በትልቅነቱ ሊጠቀስ የሚችል የህፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ሊገባ ነው፡፡
በአለርት ማዕከል ግቢ ውስጥ ይገነባል የተባለው ይኸው የህፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተሟላና በሙያው በብቃት በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የተደራጀ እንደሚሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ተናግረዋል፡፡ የሆስፒታሉ የግንባታ ሥራ በቀጣዩ አመት እንደሚጀመርም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የአለርት ማዕከል በ1.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የእናቶች ህክምና መስጫና ማዋለጃ ማዕከል ባለፈው ማክሰኞ መርቀው የከፈቱት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ፤ ማዕከሉ መንግስት የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያደርገው ርብርብ አንዱ አካል የሆነውን የጤና ተቋማትን የማስፋፋት ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው እናቶች በማዕከሉ ተገቢውን ክብካቤና የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ዋንኛ ሥራው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የማዋለጃ ማዕከሉ፤ የቅድመ ወሊድ ክትትል፣ የማዋለድ አገልግሎት፤ የድህረ ወሊድ ክትትል፣ የማህፀን ቀዶ ህክምና፣ የቤተሰብ ምጣኔና የክትባት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን 22 የመኝታ አልጋዎች፣ 5 የማማጫ አልጋዎች፣ ሁለት የኦፕሬሽን ማድረጊያ ጠረጴዛዎች ያሉትና የሪከቨሪ ስክራብ ሩም የተሟሉለት መሆኑም ታውቋል፡፡

በደራሲ አቤል ወርቁ ደመቀ የተፃፈው “የፍቅር ደረሰኝ” የተሰኘ መፅሀፍ ዛሬ ከረፋዱ 3፡30 ላይ ፒያሳ በሚገኘው አዲስ ብድርና ቁጠባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ የዘመናችንን ፍቅር አጉልቶ ያሳያል የተባለው መፅሀፉ ታሪኮቹን መስሎ ሳይሆን ሆኖ እንደፃፋቸውና ገፀ ባህሪያቱን እንደቀረፃቸው ደራሲው በመግቢያው ጠቁሟል፡፡ በ140 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ40 ብር የሚሸጠው መፅሀፉ ዛሬ ደራሲያን ሀያሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት ይመረቃል ተብሏል፡፡

የሰዓሊ ሮቤል ብርሃኔ ከ50 በላይ የሥዕል ስራዎች ለእይታ የሚቀርቡበት “The Voice Within” (የራስ ድምፅ) የተሰኘ የስዕል ትርኢት የፊታችን ማክሰኞ ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ይከፈታል፡፡ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያልም ተብሏል፡፡
ሰዓሊ ሮቤል ብርሀኔ፤ በዓሉ የስዕል ትርኢት ሲያቀርብ አራተኛ ጊዜው ሲሆን ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር ከ20 ጊዜ በላይ በውጭና በአገር ውስጥ ለእይታ አብቅቷል፡፡ ሥዕሎቹ፤ ሰዎች ህሊናቸው እርስ በእርሱ ሲጋጭባቸው መልሱ በገዛ ህሊናቸው ውስጥ እንደሚገኝና ግጭቱም ከኋላ ታሪካቸው ጋር የተሳሰረ መሆኑን አጉልተው ያሳያሉ ተብሏል፡፡

በደራሲ መላኩ ደምለው የተፃፈው “ብልጭታ” የግጥም መድበል የፊታችን አርብ ከቀኑ 9፡00 እስከ 11፡30 ሰዓት በቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በፍቅር፣ በማህበራዊና በስነ-ልቦና ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 89 ግጥሞችን የያዘው መጽሐፉ በ104 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ የመጽሐፉ፤ ሽያጭ ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለኩላሊት እጥበት ማህበር ድጋፍ እንደሚውልም በመጽሐፉ ላይ ተገልጿል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የንዋይ ጦርነት”፣ “ውብ ያለመልክ” እና “ነጭ ለባሽ” የተሰኙ ረጅም ልቦለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፤ የፍቅረኞች ቀንን አስመልክቶ “የፍቅር ቀጠሮ” የተሰኘ ፕሮግራም ነገ በዋሺንግተን ሆቴል ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡
ፕሮግራሙ በኢትዮ ኤቨንትስ አስተባባሪነት፣ “ኢስት አፍሪካን ታይገር ብራንድስ” ከዋሺንግተን ሆቴል ጋር በመሆን አዘጋጅተውታል ተብሏል፡፡
በምሽቱ ታዋቂ ድምፃውያን የሚያቀነቅኑ ሲሆን ጥንዶቹ በቀይ ምንጣፍ ስነስርአት አቀባበል ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡ በተለያዩ አዝናኝ ውድድሮች ላይ ለሚያሸንፉ ጥንዶችም የተለያዩ ሽልማቶች መዘጋጀታቸው ተጠቅሷል፡፡
በዲጄ ኪንግስተን የሚመራ የሙዚቃ ዝግጅት እንዲሁም የኮሜዲያን ፕሮግራም የሚቀርብ ሲሆን ለፍቅረኞቹ ራትና ወይንም መሰናዳቱን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
ፕሮግራሙ በቀጥታ በብስራት ኤፍኤም ሬዲዮ እንደሚተላለፍ የገለፀው የኢትዮ ኤቨንት ስራ አስኪያጅ አቶ ማናዬ እውነቱ፤ መግቢያ ለጥንዶች 1ሺህ ብር፣ ለነጠላ 500 ብር እንደሚከፈል ታውቋል፡፡

በደራሲ ተስፋ በላይነህ የተፃፈውና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያተኩረው “ትንሳኤ ናፋቂዎች መልእክት ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች” የተሰኘ መፅሀፍ የፊታችን አርብ ከ10 ሰዓት ጀምሮ ጎንደር ከተማ በሚገኘው ላንድ ማርክ ሆቴል ይመረቃል፡፡ አንጋፋው ደራሲና ሀያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፤ በሥፍራው ተገኝቶ በመፅሀፉ ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ እንደሚያደርግ የምረቃ አስተባባሪው “ግጥም በመሰንቆ” ገልጿል፡፡ በ302 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ69 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የሚንከራተቱ ኮከቦች” የተሰኘ መፅሀፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

ሰባክያኑ፡-
እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን በለሷን በልተው ከተሳሳቱ በኋላ አዳምንም ጠርቶ፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ … ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ …” ብሎ ረገማቸው፡፡ የእግዚአብሔርን እርግማን እንዴት ያለው ምድራዊ ሃይል ወደ ምርቃት ሊለውጠው ይችላል?
ክርስቶስም አለ፤ “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። … እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡” እንግዲህ ፈጣሪን ከመከተል የበለጠ ጣዕም ፍጡራንን ወይም የፍጡራኑን የእጅ ስራ በመከተል ሊገኝ አይችልም፡፡ እናም ታላቁን ዓላማ (ክርስቶስን መከተል) እንኳ በተድላና በደስታ በተሞላ መንገድ ሳይሆን መስቀሉን ይዞ ቀራንዮን እንደ መውጣት በሚያስቃስት መከራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
የ“ከመቅጽበት … ባለጸግነት” ሰባክያን ግን “የለም የለም (የምን “ጥረህ ግረህ” ብላ) በኛ መንገድ ሁሉ ነገር ቀና፣ ጉዞው የተሳካ፣ ህይወትም ጣፋጭ ብቻ ናት … ከእርስዎ የሚጠበቀው አምነው መሰለፍና በስርዎም ማሰለፍ ብቻ ነው … ከዚያማ ምኑ ቅጡ …” ይሏችኋል፡፡
ስብከቱ፡-
የ“ከመቅጽበት … ባለጸግነት” ሰባክያን ስብከት ተወዳዳሪ የለውም፡፡ “ለቸርነቱ ወደር የለውም! ጨለማን በብርሀን የሚገልጥ፣ ክረምትና በጋን የሚያፈራርቅ፣ ከዘመናችን ላይ ይህቺን ቀን ቀድሶ የሰጠን …” ብለን የምናመልከው አምላክ ሰባክያን እንኳ በሰላም ስብከታቸው መሐል “ወዮላችሁ!” ይላሉ፡፡ የ“ከመቅጽበት … ባለጸግነት” ሰባክያን ግን ክፉ ከአፋቸው አይወጣም፡፡ በከንቱ ስለሚደክሙት “መከታ”፣ ባለማወቅ ስለሚኖሩት “መምህራን”፣ በድህነት ለሚቆራመዱትም “መጽዋቾች” ሆነው በምድር ላይ ገነትን ቁልጭ አድርገው ይስሏታል፡፡ ይቺን ስብከት “ከልባቸው” የሰሙ፤ ሥራ ማለት በከንቱ መድከም፣ ደሞዝ ከብናኝ ያነሰች ኢምንት፣ ይሉኝታም አላዋቂነት እንደሆነ አምነውና ተጠምቀው ይወጣሉ፡፡አንደበተ ርቱአኑ መድረክ ይዘው ይሄን ስብከት ሲሰብኩ፣ አፉን ከፍቶ የማይሰማቸው የለም፡፡ ጭራሽ በተጨባጭ ስሌት እያጣቀሱ፣ ይሄን የህልም እንጀራ ፈትፍተው ሲያጎርሷቸው በጎዳናው ሰተት ብለው ይገባሉ፡፡ ቁጥሩን ይህ ነው የማይባል ብር ከተሰቀለበት የሚያወርዱበት ረጅም እጅ እንደተሰጣቸውና ያሻቸውን የሚያደርጉበት ቀንም ቅርብ መሆኑን በጽኑ ያምናሉ፡፡ (በቃ ገቡበታ!)
የሰባክያኑ አይነቶች፡-
ያው እምነቱ አንድ ይሁን እንጂ ስብከቱ በሁለት መልክ ይሰጣል፡፡ አንደኛው “የቅን አሳቢዎቹ” ሲሆን እነርሱም “ኑ አብረን እንደግ” የሚል መርህ አላቸው፡፡ ትዕዛዛቸውም፤ “እናንተ የሰጠናችሁን ተልዕኮ አንግባችሁ እየለቀማችሁ አምጧቸው፣ እነርሱም የኛን መልክ ይዘው ይወጣሉ” ነው፡፡ የነገሩ ፍሰት እንደ ተላላፊ በሽታ ይመስላል፡፡ አንዱ በሽተኛ ጤነኛውን ይለክፋል፣ ያ ጤና የነበረው አንዴ ከተለከፈ ደግሞ ሌሎቹን ለመልከፍ ያነፈንፋል፣ ከተሳካለት ሌላ ለክፎ የሱ ቢጤ ለካፊ አድርጎት ቁጭ ይላል … እያለ እያለ ይቀጥላል፡፡
ሁለተኞቹ ደግሞ “መካሪዎች” ናቸው፡፡ ተመካሪው ማር ማር የሚል ምክራቸውን ሲሰማ ደሙ ይፈላል፡፡ (ከልጅነት ጀምሮ የተማረው) ያ ሁሉ ትምህርት፣ እኒያ ሁሉ መምህራን … በከንቱ ዘመኑን እንደፈጁት ይገባዋል፡፡ “እህ!” ብሎ የሰማት ይቺ የደቂቃ ምክር ከተወለደ ጀምሮ ሰምቶት የማያውቀውን “እውነት” ፍንትው አድርጋ ታሳየዋለች፡፡ (አጃኢብ!!! ይላል፡፡)
የስብከቱ ጽንሰ ሐሳብ፡-
ስብከቱ እንዲህ ይላል፡፡ የንግድ ሸሪክ ልታፈሩ ወይም ገንዘብ ልታጠራቅሙ አስባችሁ ይሆናል፡፡ እንደ ወትሮው በእውር ድንብር አትሂዱ … እንዲህ አድርጉ፡፡ መጀመሪያ አንድ በሉ (“አንድ” ደግሞ ቀላል ናት)፡፡ ለምሳሌ የንግድ ሸሪክ ከሆነ በቃ ራሳችሁን አንድ ብላችሁ ቁጠሩ፤ ወይም ገንዘብ ለማጠራቀም ከሆነ፣ ዛሬ አምስት ሳንቲም ቆጥባችሁ ጀምሩ (በጣም ቀላል)፣ ከዚያም ቀጥሎ ሁለት አድርጉት (የቀደመውን እጥፍ ማለት ነው)፣ (ቀጥሉ) አራት፣ ስምንት፣ አስራ ስድስት፣ ሰላሳ ሁለት … እያለ ይቀጥላል፡፡
(ማለትም) “የንግድ ሸሪክ ከሆነ እናንተ ሁለት ታፈራላችሁ፣ ከዚያ የፈሩት ሁለቱ ደግሞ (ሌሎች) ሁለት ሁለት ያፈራሉ፣ እነዚህ አራቱ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ሲያፈሩ … ስምንት ይሆናል፣ አስራ ስድስት፣ ሰላሳ ሁለት፣ ስድሳ አራት … እያለ ይቀጥላል፡፡ ወይም ገንዘብ መቆጠብ ከሆነ በመጀመሪያው ቀን ከቀላሉ አምስት ሳንቲም ጀምሩ፣ ከዚያ አስር፣ ሃያ፣ አርባ፣ ሰማኒያ ሳንቲም፣ ብር ከስልሳ፣ ሶስት ብር ከሃያ፣ በስምንተኛው ቀን ስድስት ብር ከአርባ እያለ ይቀጥላል፡፡ ከዚያማ አመት ሳይሞላ (አላሙዲንን ተውትና) ቢል ጌትስን ጫማ ጠራጊያችሁ ልታደርጉት ትችላላችሁ” ይላሉ፡፡ (አሰፋፈሩ እንደየድርጅቱ ዓይነት በሁለት ወይም በአራት ቅርንጫፍ የሚንሰራፋ ይሆናል)
እውነት ነውን?፡- እንደሚባለው ከሆነ፤ ምንም ጥርጥር የሌለው እውነት ነው፡፡
እንዲህ ሆነ (ታሪክ)፡-
አንድ ንጉስ ወታደሮቹን ድል ወደናፈቀበት የፍልሚያ አውድማ ይልካል፡፡ ይህ ፍልሚያ በቀላሉ የሚጠናቀቅ አልነበረም፡፡ እናም “አሸንፍ ይሆን?” እያለ እየሰጋ መቼም ገና ለገና “እሸነፋለሁ” ብሎ እጅ መስጠት የሞት ሞት ነውና “ያበጠው ይፈንዳ” ብሎ ይዘምታል፡፡ እጅግ ድንቅ በሚባል ጀግንነት አንዱ ጎበዝ ጠላቱን ድባቅ መትቶ ንጉሱ የናፈቁትን ድል እያብለጨለጨ ይዟት ከተፍ ይላል፡፡
በቃ ደስታና ፈንጠዝያ ሆነ (እልልታው ቀለጠ)፡፡ ታዲያ ከድል ማግስት የድሉን ፋኖ መሸለምና ማወደስ ወግ ነውና፡፡ “ኑ ወዲህ” ብለው ሀገሬውን ባደባባይ ይሸክፉታል፡፡ ሰው (ሁሉ) ጢም አለ፡፡
በዚህ ጠጠር ቢጣል መሬት በማይነካበት የሰው ስጥ መሃል ንጉስ ሆዬ ማማ ላይ ወጡና÷ “ያገሬ ህዝብ ሆይ÷ ጠላታችንን ምልክቱ እንኳ እንዳይገኝ አድርገን አውድመናልና ደስ ይበልህ!!!” አሉ፡፡ ((ጨብጨብጨብ…. እልልልልልልል …)) “ዛዲያ … እንዲህ ያለውን እንደ ማር የሚጣፍጥ የድል ዜና ለመስማት ካበቁን ጀግኖች መሃል አውራውን ዛሬ በእናንተ ፊት ልሸልመው ተሰናድቻለሁ … ” ((ጨብጨብጨብ…. እልልልልልልል …ጨብጨብጨብ…. እልልልልልልል …ጨብጨብጨብ…. እልልልልልልል …))
ያ ድል አድራጊ ጀግና ወታደርም ሊሸለም ወደ ማማው ወጣ፡፡ እጅም ነስቶ ቃላቸውን ሲጠብቅ ንጉስም “ለእንዲህ ያለው ባለድል እኔ ይሄን ያንን አልልም ያሻውን እሰጣለሁ … ብቻ እሱ የከጀለውን ይጠይቅ፡፡ ሲያሻው ገንዘብ፣ ካሻው ስልጣን፣ አይ ካለም የግዛቴን ክፍል … ወይ ደግሞ …” አሉ፡፡ ሰው “ወይ ደግሞ …” የምትለውን ፤ “በቃ ልጃቸውን ሊድሩለት ነው፣ አልጋ ወራሽ ሆነ ማለት ነው” ብሎ ተረጎመው፡፡ እሱም የሚመርጠውን ለመተንፈስ ጉሮሮውን ጠራርጎ ተሰናዳ፡፡
“ንጉስ ሆይ!!!” ብሎ የቼዝ መጫወቻዋን (ባለ ስልሳ አራት ሳጥን (square) ዝንጉርጉር ጥቁርና ነጭ ሰሌዳ) ከጉያው አውጥቶ “ንጉስ ሆይ!!! እኔ የምፈልገው በዚህ ሰሌዳ ላይ በመጀመሪያዋ ሳጥን አንድ ፍሬ ስንዴ፣ በሁለተኛዋ ሳጥን ሁለት ፍሬ ስንዴ፣ በሶስተኛዋ ሳጥን አራት ፍሬ ስንዴ፣ በአራተኛዋ ሳጥን ስምንት ፍሬ ስንዴ … እያደረጉ እጥፍ እጥፉን እያስቀመጡ ከጨረሱ በኋላ፤ ያንን አጠራቅመው እንዲሰጡኝ ነው” አለ፡፡ ሰው በሳቅ ፍርስ አለ፡፡ ንጉሱ ግን ብስጭት ብለው፤ “እኔ ደህና ነገር የሚፈልግ እንደሆነ ብዬ ነበር፣ እንዲህ ያለ ገልቱ መሆኑን መች አውቄ … እውነት እላችኋለሁ ልጅህን ዳርልኝ ቢል እንኳ እምቢ አልልም ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው … አንድ ቁና እንኳ የማይሞላ ስንዴ ጠየቀኝ … እኔማ ቃሌን አላጥፍም ሂዱና ቆንጥራችሁ ስጡት” አሉ፡፡
አሽከሮቹም ስንዴውን ሊሰፍሩ ወደ ጓዳ ገቡ፡፡ ነገር ግን ንጉሱ እንዳሉት ስንዴው እንቅብ የማይሞላ ቁንጥር አልሆነም፡፡ አይደለም የንጉሱ የአገሬው ስንዴ ተጭኖ ቢመጣ የፋኖውን ስፍር (የጠየቀውን) ሊሆን አይችልም፡፡ ንጉሱ ይሄን ሲሰሙ በህዝባቸው ፊት “ቃሌን አላጥፍም” ያሏት ንግግር ውሃ እንደበላት ተረዱ … “ቃለ አባይ ሊያስብለኝ አይደል” አሉና “በሉ እሱን ሰው አጥፉልኝ” ብለው አዘዙ፡፡ ስንት የታጨለት ጀግና ሰው፤ በድሉ ማግስት ተቀልቶ ተገደለ፡፡
ንጉሱ የዚህን ጀግና የስንዴ ጥያቄ መመለስ አቅቷቸው እስከ ማስገደል የደረሱት (የስንዴው ስፍር) ምን ያህል ቢሆን ነው?
ከመቅጽበት … ባለጸግነት - ኔትወርክ ማርኬቲንግ
በዚች መከራ በበዛባት ምድር ላይ፣ ሰው ጠብ እርግፍ ብሎ ላቡን አንጠፍጥፎ (ያውም ከተሳካለት) የዕለት እንጀራውን በሚበላባት እሾሃማ መሬት ላይ የገነትን በር አስጮልቆ የሚያሳይ ቀዳዳ ማለት ኔትወርክ ማርኬቲንግ ነው፡፡ በስብከቱ (በኔትወርክ ማርኬቲንግ) ሙቀት አጮልቆ (ማርና ወተት የሚፈስባትን ስፍራ) ያየ ሰው፣ ጮማ ቆርጦ በላዩ ላይ የማር ጠጁን እንደለበሰ ወዝ በወዝ ሆኖ እያንጸባረቀ ከቢሯቸው ይወጣል፡፡ ደሞዝን ስጋ ለብሳ ፊቱ ቆማ ቢያገኛት በጥፊ አጠናግሮ ያባርራት ነበር፡፡አዎ! አካሄዱ እንደሚባለው የሚፈስ ከሆነ እውነት ነው፡፡ ያው ሂደቱ አንድ ሰው ሁለት ሰዎችን በስሩ አስገብቶ ከገዙት (ከተገለገሉት) ተጠቃሚ ይሆናል፣ ሁለቱ ደግሞ ሁለት ሁለት ሰዎችን ሲያስገቡ ዋናውን በአራት ሰዎች እንዲጠቀም ያደርጉታል፣ እነሱ ደግሞ ሌሎች አራት ሰዎችን ይጠብቃሉ፣ አራቱ ሲገቡ ደግሞ ሁለት ሁለት አስገብተው ስምንት ጫፎች ይሆናሉ … በዚህ የላይኛው ሰውዬ ጉርሻ እያደገ፣ ከወረትም አልፎ ቅርስ ሆኖ ቁጭ ይላል … ነው አካሄዱ፡፡
ከላይ ከተቀመጠው (በእጥፍ እያደገ መሄዱ) በተለየ መልኩ በአራት ሰው (ቅርንጫፍ) ወይም ከዚያም በላይ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል … ዞሮ ዞሮ በርቢ (exponentially) አካሄድ እንደ ዛፍ ስር ቅርንጫፉን እያበዛ መቀጠል ነው ስልቱ፡፡
ታዲያ በዚህ መንገድ የሚሰላ ስንዴ እንዲሰጡት የጠየቀው ጦረኛ፤ በንጉሱ ትዕዛዝ እንዲቀላ መደረጉ የስንዴው ስፍር ምን ያህል ቢሆን ነው?
መነሻው አንድ ቢሆንም እጥፍ እየሆነ ስለሚያድግ፣ በ  ሃይለ ቁጥር እየረባ የሚሄድ ይሆናል፡፡ ይህም የመጀመሪያው   ሲሆን ሁለተኛው ፣ ሶስተኛው  እያለ ይቀጥላል፡፡ በዚህም መሰረት እንደ ሰውየው (ወታደሩ) ጥያቄ የመጨረሻው (ስልሳ አራተኛው ሳጥን - (የመጀመሪያው ከ  ስለጀመረ))  ይሆናል፡፡ ይህም ማለት  የስንዴ ፍሬዎች ነው (ቁጥሩን ማንበብ እንኳ ያቅታል)፡፡ በአጠቃላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያለውን ስንሰበስበው  ይሆናል፡፡ እንግዲህ ንጉሱን ያሳፈረ፣ ጠያቂውንም ያስገደለውን  ፍሬ ስንዴ በሚገባን መጠን እንዲህ ቀይረን እንየው፡፡
ወደ ክብደት ስንቀይረው ይህ የስንዴ ክምችት  ሜትሪክ ቶን ይመዝናል፣ ተከማችቶ በአንድ ላይ ቢቆለል ደግሞ ከዓለማችን ትልቁ ተራራ ኤቨረስት የላቀ ግዝፈት ይኖረዋል፡፡ ዓለማችን በዓመት ከምታመርተው ምርት (የሩዝ) ጋር ስናነጻጽረው ደግሞ  እጥፍ ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ይህን ያህል ስንዴ ማከማቸት ቢፈለግ እንኳ አንድ ሺ ዓመታትን ይወስዳል ማለት ነው፡፡
ይህ መጠን ነው እንግዲህ ንጉሱን ድልን ባለመጣላቸው ጀግና ላይ እንዲጨክኑ ያደረጋቸው፡፡ ቃሌን እጠብቃለሁ ያሉት ሀገረ ገዥ፣ መሳቂያ መሆናቸውን ሲያውቁ የከፋውን እርምጃ በወዳጃቸው ላይ ሰነዘሩ፡፡
ታዲያ ይሄን አንገት የሚያስቀላ ስሌት ወደ ጎን ጥለው … የኛዎቹ “ምሁራን” በኩራት “አምስት ሳንቲም ብላችሁ ብትጀምሩ የትና የት ትደርሳለችሁ” ይላሉ፣ “ነጋዴዎቹም” ብድግ ብለው “በስራችሁ ሁለት ሰው አድርጋችሁ … አጥምቃችሁ ልቀቋቸው ምድርን ይሞላሉ … እናንተም የናጠጠ ሀብታም ትሆናላችሁ” እያሉ ይሰብካሉ፡፡ (የ  ፍሬ ስንዴን ጉዳይ አልሰሙ ይሆናል፡፡)
ሌላው ነገር “በዚህ ስርዓት ውስጥ ያሉት ተመልሰው በመግባት ለስርዓቱ ቀጣይነት አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ” ይላሉ፡፡ ማለትም የሚሸጥም ከሆነ መልሰው ራሳቸው ገዢ ሊሆኑ፣ አገልግሎትም ከሆነ ድጋሚ ተጠቃሚ እየሆኑ የስረኞቹን ሰው ፈላጊዎች ከመናበዝ ማዳን ይችላሉ ይሉናል፡፡ (አንዳንዶቹ ተመልማዮች “ገንዘብ የለንም” ሲሉ “ግዴለም የአንተን እኔ እከፍላለሁ … ብቻ አምነህ ሰው መሰብሰቡ ላይ በርታ …” እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡)ይሄ በጭራሽ ሊሳካ የማይችል ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ ያሉት ሁሉ ተደምረው ከታችኞቹ በአንድ ያንሳሉና፡፡ ለምሳሌ ከ  ቀጥሎ  ይመጣል፣ ይህም ማለት አንድ ሰው ሁለት ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ራሴ መልሼ ልግባ ቢል እንኳ አንድ ሌላ ሰው ይጎድለዋል፡፡ ከ  ቀጥሎ  ይሆናል (በሁለቱ ስር ሁለት ሁለት ሰዎች ሲገቡ)፤ ከላይ ያሉት ሶስቱ መልሰን እንግባ ቢሉም አንድ ሌላ ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ በ  ሰዎች ስርም  ሰው መግባት አለበት፡፡ ከላይ ያሉት ሲደመሩ  ብቻ ይሆናሉ፡፡ እናም በአጠቃላይ ከታች እንዲገቡ የሚፈለጉት (ሰዎች) ብዛት ሁልጊዜ ከላይ ካሉት ድምር በአንድ ይበልጣል፡፡
በመሆኑም በፍጹማዊ (absolute) እድገት ደረጃው ስርጭቱ እንዲሄድ ማድረግ ተጨማሪ አዲስ አባላትን መጠየቁ የግድ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የዓለም ህዝብ በሙሉ ይሳተፍበት ብንል እንኳ ሰላሳ ሶስት ደረጃዎችን ሳይሄድ ቀጥ ይላል፡፡ ምክንያቱም  ይሆናል፡፡ የዓለማችን ህዝብ ብዛት ደግሞ ከዚህ ያነሰ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ግማሾቹ የመጨረሻዎቹ ጫፎች ስለሚሆኑ የሰው መጠቀሚያ መሆን እንጂ ለነሱ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡
በአጠቃላይ ከሁለት ነጥቦች አንጻር የኔትወርክ ማርኬቲንግን መኮነን ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ከሚገኘው አገልግሎት አንጻር ነው፡፡ በእርግጥ ኔትወርኩ (ስርዓተ መረቡ) አገልግሎትን በቀላሉ ለማስፋትና ብዙዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹ ነው (ከስርጭት አንጻር)፡፡ ነገር ግን የስርዓተ መረቡ ዓላማ ከአዲስ ተመልማዮች የሚገኘውን ገንዘብ በመጠቀምና ከፍሎ በማቃመስ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ገሚሶቹ (የመጨረሻው ጫፍ ላይ ያሉት) መስዋዕትነቱን ከፍለው አጨብጭበው ይቀመጣሉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ስርዓት ውስጥ የተቀላቀሉት ለወሰዱት ቁስ (አገልግሎት) ከሚገባው በላይ ከፍለው በኋላ በሚሰጠው ጉርሻ ማካካስና ብሎም መክበር ነውና፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስርጭቱ እየሰፋ ሲመጣ ወደ ኋላ የተቀላቀሉት አባላት ተመልማይ ፍለጋ የሚማስኑት መማሰን እየከፋ ይመጣል፡፡ እየቆየም (መሳካት ስለማይችል) ይደርቃል (ይቆማል)፡፡  
ሌላው ነገሮች በልፋትና በድካም ሳይሆን እንዲሁ የሰውን ድካም በመውሰድ ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን ስራ ፈትነትንና ስራ ጠልነትን በማስፋፋት አልሞ አዳሪውን ያበረክታል፡፡ ሰርቶ ማግኘት የሚባለውን ነገር አስቀርቶ፣ “እገሌ በኔ ስር ቢገባ .. እገሊት በኔ ስር ብትገባ …” እያሉ ማሰብ ይሆናል ነገሩ፡፡ (ለሀገር የሚፈይዱትም ነገር አይኖርም፡፡) በተለይ በኔትወርክ ማርኬቲንግ ስም የሚሰራጩት ነገሮች ያልተፈተሹ ከሆኑና ሀገሪቱ ለሌላ ልታውለው የሚገባውን የውጪ ምንዛሬ በከንቱ ካፈሰሱ ከብክነትም በላይ ወንጀል ይሆናል፡፡
ከመቅጽበት … ባለጸግነት - “የሚታመኑትን” ስንከተል
ከመቅጽበት ባለጠግነት (ጥምር ቃሉ) “ከመቅጽበት” እና “ባለጸግነት” የሚሉትን ሁለቱን ትርጓሜዎች ያዝላል፡፡ “ከመቅጽበት” ማለት ካይን ጥቅሻም በበለጠ ፍጥነት የሚለውን ፍቺ ሲወክል፣ “ባለጠግነት” ማለት ደግሞ ሁሉ የተሟላለት፣ ቸገረኝ አጣሁ የሚለው የሌለው፣ የሞላው የደላው እንደማለት ነው፡፡
“ከመቅጽበት ባለጸግነት” አጣሁ ነጣሁ ስትል በኖረችው ሀገራችን፣ ረሃቡም ጦርነቱም (ሄድ መለስ) እያለ ሲደቁሳት በከረመችው የኛ ምድር፤ በአንደበተ ርቱዕው (ኔትወርክ ማርኬቲንግ (የትስስር ግብይት) ወይም MLM ወይም ያሻቸውን ይበሉት …) መሰበክ ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ የዚህ ዕምነትም ተከታዮች በስብከታቸው፤ በዚች ባላደገች ሀገር ሳይሰሩ መብላት እንደሚቻል፣ ሳይደክሙ መበልጸግም እንዳለ ያስተምሩናል፡፡
በጽንሰ ሐሳቡ (በሒሳብ) መሰረት (ምናልባት ከሰው ልጅ አዝጋሚነት አንጻር) ፍጥነቱ ከመቅጽበት ላይሆን ይችላል እንጂ ባለጸግነቱን ስሌቱ ያመጣዋል፡፡ (ልብ በሉ ስሌቱ ብቻ ነው የሚያመጣው፡፡) ይሁን እንጂ የስሌቱ አካሄድ (አጨማመር) በኃይለ ቁጥር አሰላል ስለሚቀመር የመጠኑ ልኬት በምድራችን ፈጽሞ እውን መሆን የማይችል ነው፡፡ የ“ከመቅጽበት ባለጸግነት” “እምነት” ተከታዮችና ሰባክያኑ ግን ይሄን እውነት ዘለው ስሌቱን በ“ይሆናል” እያነበነቡ ብዙዎችን አሳምነው ያጠምቃሉ፡፡
ለምሳሌ አንድ ህጻን በአንድ ዓመት ውስጥ ያደገውን መጠን (በቁመት) ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታትም በዚያው መጠን ይቀጥላል ብሎ ማሰብ፤ በሒሳቡ መሠረት በ20ኛው ዓመት፣ በ30ኛው … በ100ኛው ቁመቱ ስንት መቶ ወይም ስንት ሺ እንደሚደርስ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ተፈጥሮ ቁመትን እንዳሻን እንዳናዘልግ ታግደናለች፡፡ሒሳብ ማለት - ውሸት፣ መደመርና ማብዛትም - ቅጥፍና፣ ማስላት ደግሞ - ቅዠት ካልሆነ በስተቀር፤ የስሌቱን ውጤት ከዓለማችን (ከሀገራችን) እውነት ጋር ስናዛምደው የ“ከመቅጽበት ባለጠግነት”ን ከንቱነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ለምሳሌ (በዚሁ በ“ከመቅጽበት ባለጠግነት” ቅዠት) የአፍሪካ ሀገራትን እናስተሳስር ብንል፡፡ (ያው ኢትዮጵያ (የኛ ስለሆነች) እንድታድግ ከላይ እናደርጋትና) ኢትዮጵያ ሰብካ ጅቡቲንና ኬንያን በኔትወርኩ ውስጥ አስገባች ብንል፡ በ 1 ስር 2 ተገኙ ማለት ነው፡፡ በ2ቱ ስር 4፡፡ በ4ቱ ስር 8፡፡ በ8ቱ ስር 16 ይልና፤ በመጨረሻ በ16ቱ ስር 32 ሀገራትን ስንፈልግ የአፍሪካ ሀገራት አልቀው 32 አልሞላ ይሉናል፡፡ ምክንያቱም ከላይ ያሉት 1 + 2 + 4 + 8 + 16 = 31 ናቸውና፤ ከ54ቱ የአፍሪካ ሀገራት የቀሩት 23 ብቻ ይሆናሉ፡፡
እናም አስራ ስድስቱ ሀገራት ሃያ ሶስቱን ለመቀራመት ሲራወጡ ቀውጢ የሆነ ጦርነት ሊፈጠር ነው፡፡ በስተመጨረሻ ያሉት (ፈላጊዎች) ያልተያዘ የአፍሪካ ሀገር አጥተው ቁጭ ይላሉ፡፡ ምናልባትም መስዋዕት የሆኑትም እነ አንጎላ ከሆኑ … አንጎል ሆነው መቅረታቸው ነው ማለት ነው፡፡
ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ተተግብሮ ካላየነው አናምንም ብሎ መሟገት፤ ክፍት የቤንዚን በርሜል አጠገብ ተቀምጦ “ክብሪት ብንለኩስ ይነዳል ወይስ አይነድም” እያሉ እንደ መሟገት ይሆናል፡፡ መንደዱን በእውን አይቶ (ነዶ) ከማረጋገጥ ይልቅ አለመንደዱን ሳያዩ አምኖ፣ ከመለኮስ መቆጠብ ሕይወት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በደመነፍስ መወሰን ሳይሆን ካለመሆኑ በፊት አለመሆኑን ማወቅ ማለት ነው፡፡ የትምህርትና የሳይንስ ጥቅሙም ይሄው ነውና፡፡
“ከመቅጽበት ባለጠግነት” በምናውቃት እከካም ምድር ላይ “ገነትን” በአንጸባራቂ ቀለም አጠገባችን ስሎ፤ ተስበው የሚስቡትን በማፍራት የሚመለክ “ሃይማኖት” ነውና፤ ተዘፍቀው የሚዘፍቁ ደፋር ሰባክያን በፊታውራሪነት ይመሩታል፡፡ ለዚህም ደህና የመስበክ ልምድ ይፈልጋልና፤ ቀድሞ (በሌላ መድረክ) ተደማጭነት የነበራቸው የሃይማኖት ሰባክያንና ታዋቂ ግለሰቦች በመሪነት ተሳትፈውበት፤ ደፋ ቀና ብለው የማያገኙትን ረብጣ ገንዘብ ተንጋለው መቁጠርም ጀምረዋል፡፡
ይሄንንም ዝርፊያ “በሌለንበትም ጊዜ እንኳ ትርፉ ተቆልሎ ጠብቆናል” እያሉ በኩራት ሲያወሩት፤ የሚያፈራ ዛፍ ተክለውና ኮትኩተው ያሳደጉ ወይም የማይደርቅ ምንጭ የቆፈሩ ያህል በመኩራራት ነው፡፡
ነገር ግን “ጉልበት አይፈጠርም አይጠፋምም፤ ካንዱ ወደ ሌላው ይሸጋገራል እንጂ፡፡” የሚለው የፊዚክስ ነባር ህግ እዚህም እንደሚሰራ አላስተዋሉ (ወይም ክደውት) ይሆናል እንጂ፤ አንዱ ሳይሰራ ሲበለጽግ፣ ሌላው ደግሞ የደከመበትን ፍሬ ሳያገኝ እንደሚራቆት ግልጽ ነው፡፡
ዘርቶ ያጨደም ሆነ ቆፍሮ ማዕድን ያወጣ የመሬትን ወዝ ይጠቀማል እንጂ (ከሌላ) ከየትም አይፈጥረውም፡፡ መሬት ደግሞ አርሰንና ዘርተን፣ የዕለት እንጀራችንን ልንጎርስባት የተለገሰችን የማዕዳችን ናትና በወጉ ማምረት ተገቢም ልክም ነው፡፡ ለዚህም ነው “የላባችንን ወዝ በላን” እንጂ “የመሬትን ሀብት ዘረፍን” የማንለው፡፡ የሰውን ድካም ቁጭ ብሎ መጉረስ ግን ስጋውን ቆርሶ እንደመብላት ይቆጠራል፡፡
እናም እንዲህ ያለውን ንጥቂያ ልዩ መልክና ቁመና ሰጥቶ ለማስፋት ጠንሳሾቹ የተጠቀሙት ዘዴ አለ፡፡ አንደኛው መስቀል ይዘውና ኪታቡን አንግበው ሰማያዊውን መንግስት ሲሰብኩ የነበሩትን በመጥለፍ የዚህም “ሃይማኖት” ሰባክያን አድርጎ ማሰማራት ነው፡፡ በየመድረኩ ጣፋጭ አንደበታቸውን ሲሰማ የኖረ (የዋህ) ህዝብ እንዴት ብሎ “አልቀበልም” ይበላቸው? በቃ! ሁሉም ተከትሏቸው ነጎደ፡፡ እነርሱም ያን ሁሉ ሰው እያራቆቱ ለራሳቸው የሞቀ ለብሰው ብቅ እያሉ “ይሄው አትራፊ ነው አላልናችሁም፣ እነሆ ያገኘነው ዳጎስ ያለ ጉርሻ …” እያሉ በድፍረት ቁለቅለቱን ተያያዙት፡፡
ሌላው አስገራሚ ስልት ደግሞ፤ “ፈጣሪ ይመስገን” እያለ ቆሎውን ቆርጥሞ ወደ ስራው የሚሰማራውን ሰው ማስጋት ነው፡፡ “የለም በዚህ አኳኋንህ አመትም መቆየትህን እንጃ?” ሲሉት የኛ ሰው ብርክ ያዘው፡፡ “ጉዳዩን ከትርፍም ባለፈ የህልውና ጉዳይ ነው” እያሉ ሲለፍፉበት ደንጋጩ በዛ፡፡ “ሽንትና ሰገራ ብቻ ቆሻሻህን አያወጣልህም፤ የሚያስፈልግህ ሌላ ነገር አለ” አሉ፤ “አጥንትህ እንደ ሸንበቆ ተሰጥሮ ማለቁ አይቀርም … እናም ካሁኑ አስብበት” እያሉም ሲወተውቱት፤ ጤነኛ ነኝ ብሎ ያስብ የነበረው ሰው ሁሉ ራሱን እንደ በሽተኛ እየቆጠረ በነሱ ፈውስ ሊድን ተመዝጋቢ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ የዚህ ስልታቸው አጠቃላይ ይዘት “ተፈጥሮ በራሷ እንከን አለባትና …” የሚል ነው፡፡ ጠበቅ አድርገው ሲይዟቸው ደግሞ “እንከን እንዲኖራት ያደረገነው እኛው ነን” ይሉና “ያው ምርቶቹ ግን ችግሩን ይቀርፉታል” ይላሉ፡፡
እነዚህ የሚጠሯቸው ማዕድናት “ለጤና አስፈላጊ ናቸው” ሲሉ፤ የጤናችን ጠበቃዎች በሆኑት ሐኪሞች በኩል ሄደን ማረጋገጫ እንዳንጠይቅ “የለም የለም መድኃኒት ሳይሆኑ ምግቦች ናቸው” ብለው ይታጠፋሉ፡፡
እናም ወትሮ በምናምናቸውና “ለኢትዮጵያውያን ምግባቸውን ሰጠኋቸው” የሚለውን ቃል ሲሰብኩ በነበሩት አንደበት በኩል ዘልቀው “የለም፤ ለኢትዮጵያውያን ምግብን አልሰጠም፣ ለቻይና እንጂ፤ እነዚህን ምርቶች ካልወሰድን ደግሞ የሚጎድለን ነገር አለና አስቡበት …” አሰኟቸው፡፡
ለ“ከመቅጽበት ባለፀግነት” “የሚታመኑትን ስንከተል” የምናገኛቸው እነዚህ ነገሮች እውነት ተጨማሪ ምግቦች ናቸውን? እንጀራችንስ የማያሟላቸው ናቸው? ጎደሎ ነገርን ስንመገብ የኖርን ሰዎች ነበርን እንዴ? ወይስ …


Saturday, 13 February 2016 11:06

የዘላለም ጥግ

(ስለ እግዚአብሔር)

- እግዚአብሔር ህመማችንን የምንለካበት
ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡
ጆን ሌኖን
- እግዚአብሔር ረቂቅ ነው፤ ተንኮለኛ ግን
አይደለም፡፡
አልበርት አንስታይን
- እግዚአብሔር ራሳቸውን የሚረዱ ሰዎችን
ይረዳል፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን
- ከእግዚአብሔር ጋር አወራለሁ፤ ሰማዩ ግን
ባዶ ነው፡፡
ሲልቪያ ፕላዝ
- በእግዚአብሔር አላምንም፤ ግን ይናፍቀኛል፡

ጁሊያን ባርነስ
- እያንዳንዱ ሰው በራሱ መንገድ ወደ
እግዚአብሔር ዘንድ ይምጣ፡፡
ሔነሪ ዋርድ ቢቼር
- ከሰው ልጅ መፍትሄዎች ይልቅ
የእግዚአብሔር እንቆቅልሾች የበለጠ
ያጠግባሉ፡፡
ጂ.ኬ. ቼስቴርቶን
- እግዚአብሔር ዛሬ የ86ሺ 400 ሰከንዶች
ስጦታ አበርክቶልሃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ
አንዱን ሰከንድ “ተመስጌን” ለማለት
ተጠቅመህበታል?
ዊሊያም አርተር ዋርድ
- እግዚአብሔር ወንጌልን በመፅሃፍ ቅዱስ
ላይ ብቻ አልፃፈም፤ በዛፎች፣ በአበቦች፣
በደመናውና በክዋክብቶችም ላይ ጭምር
እንጂ፡፡
ማርቲን ሉተር
- እግዚአብሔር ሁለት እጆችን ሰጥቶናል፡፡
አንደኛውን ልንቀበልበት፣ ሌላኛውን ደግሞ
ልንሰጥበት፡፡
ቢሊ ግራሃም
- እግዚአብሔር ዓለምን ለመፍጠር ውብ
የሂሳብ ስሌት ተጠቅሟል፡፡
ፖል ዲራክ
- እግዚአብሔር ሰዎች ከሚያስቡት በላይ
ትልቅ ነው፡፡
ጂሚ ዲን
- እግዚአብሔር ቁማር አይጫወትም፡፡
አልበርት አንስታይን
- እግዚአብሔር ትላልቆቹን ክብደቶች
የሚያንጠለጥለው በትናንሾቹ ሽቦዎች ላይ
ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን