Administrator

Administrator

Saturday, 26 October 2019 12:09

ማን ምን አለ?

 * ‹‹…እኛ አገር ኢትዮጵያዊነት የምትባል በጣም ድንቅ መርከብ አለች፡፡ ጠንካራ፡፡ ብርቱ:: ውብ የሆነች፡፡ ይህች መርከብ እየተንሳፈፈች ባለበት፣ የዛሬ ዓመት ከበረዶ ግግር ጋር ልትጋጭ ብላ፣ ልትሰጥም ብላ፣ በአስደናቂ የእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት እንደምንም ብላ አምልጣ አልፋለች፡፡ ከዚያም ያንን የበረዶ ግግር ካለፈች በኋላ ዓመቱን በሙሉ አንድ ጊዜ የብሔርተኝነት ግግር በፊቷ ሲቆም፣ ሌላ ጊዜ የመፈናቀል የበረዶ ግግር በፊቷ ሲቆም፤ አንዴ ወደ ቀኝ እያለች፣ እንደገና ወደ ግራ እያለች፣ ደሞ እየታጠፈች… ብዙ የበረዶ ግግሮችን አልፋ ዛሬ እዚህ ደርሳለች፡፡ ነገር ግን ዛሬም እቺ ኢትዮጵያዊነት መርከብ ከፊቷ የበረዶ ግግር አለ፡፡ ዛሬም ማለፍ ያለባት የበረዶ ግግሮች አሉ፡፡… ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን ሊያድን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው!››
     ዶ/ር ወዳጄነህ መሃረነ (‹‹አንዳፍታ›› ዩቲዩብ)
* ‹‹…የተባለውን በሙሉ ሰምቻለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስምና ክብር የሚገባው ለእኔ ነው ብዬ በፍጹም አላምንም፡፡ ክብሩን ሁሉ እግዚአብሔር ይውሰድ…››
     ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ (የሰላም ሚ/ር ለሰላም የኖቤል ሽልማት  ዕውቅና ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት)
* ‹‹…ታሪክ፣ እምነትና ጎሳ ቢኖር፣ የሚያመሳስላቸው ነገር ምርጥ ምሽጎች መሆናቸው ነው፡፡…››
    ፈላስፋና ፀሐፊ መሃመድ አሊ (ኢቲቪ መዝናኛ)
* ‹‹…ዶ/ር ዐቢይ ለዘመናት የሄድንበትን የመበቃቀል ስህተት፣ በአዲስ መንፈስ በይቅርታ እንሻገር ሲል፣ እንደ ማንኛውም ዜጋ እኔም ደስ ብሎኝ ይሄን ሀሳብ ተቀብያለሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ የሆነው ኢትዮጵያ የሄደችበትን የመከራ ዘመን በማሰብ አንድ ቦታ ላይ እንዘጋዋለን የሚል (እንደ አንድ ዜጋ) እምነት ስለነበረኝ ነው፡፡ አሁን ያሉትን ሁኔታዎች ስንመለከት፣ በብሔር-ተኮር ፖለቲካ ጎራ ያሉ ሀይሎች ጫፍ እየወጡ፣ ኢትዮጵያዊ የሚለውን የዜግነት ሀሳብ እየገፉ፣ ዜጎች እንደ ልባቸው እንደ ዜጋ የሚኖሩበትን እያፈረሱ… የመገፋፋትና የማፈናቀል… ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ሊታረም የሚችልበትን መንገድ… እንደ አንድ ዜጋ በግሌ ሞክሬአለሁ፡፡ ሊሰሙኝ የሚችሉ ባለሥልጣናትን ‹‹ምን እያደረጋችሁ ነው›› ብዬ ጮሄአለሁ፡፡ አዝናለሁ፤ ይሄን ስናገር ግን… ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡ ያሰብነው ጋ እየሄድን አይደለም፡፡ ለውጡ ሃዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው…››
   አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ (ለአማርኛው ቢቢሲ ከሰጠው ቃለ ምልልስ)

ከዕለታት አንድ ቀን የቆላና የደጋ ገበሬዎች ነበሩ፡፡ ሁለቱም በችግርና በጉስቁልና ሲኖሩ ሳለ፣ አንድ ቀን አንደኛው፣ ሳር ቤቱን ትቶ፣ ቆርቆሮ ቤት ቀየረ፡፡ አጥሩም በአዲስ መልክ ታጠረ፡፡
የጥንት ግጥም የሚቀጥለውን ይላል፡-
አልኩሃ ምን ትሆን?
እኔም እናትህ ነኝ አንተም ልጄ ብትሆን
ይቺን ጨቅላ መጽሐፍ የምታነብ ሁሉ
አደራ ስለ እኔ ማሪያም ማሪያም በሉ
ከሃያ ስድስቱ ወንዶች ፊደላት
አርግዣለሁና መዝገበ ቃላት
ስንት እልፍ አበው ናቸው አርግዘው የሞቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ
ለትምህርት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ
        * * *
ዛሬ ርዕሰ አንቀፁን በግጥም ያቀረብነው፣ ትንሽ ወዝ እናክልበት ብለን ነው!
ሁላችንም በጋራ ከተንቀሳቀስን የጋራ ግብ ይኖረናል!
ፊት ለፊት እንሂድ!
እንቅፋት አንፍራ!
ትላንትናን አበክረን እንይ!
‹‹ነገም ሌላ ቀን ነውን›› አንዘንጋ!
ያመለጡን ዕድሎች አያሌ ናቸውና ሀሳቡን ብቻ እናብሰልስለው፡፡
ሁኔታዎችን እያጤንን መንገዳችንን ልብ እንበል፡፡   
ብዙ መጓዛችንን እናስተውል፡፡
ገና ብዙ እንደምንጓዝ አይጥፋን፡፡
ዞሮ ዞሮ መንገዱ ረዥም ነው!
ለዳገት የጫነው፣ ሜዳ ላይ እንዳይደክም ጉልበታችንን እናክም!
ወዴት እንደምንሄድ በትክክል እንወቅ!
ደጋግመን ያልነውን ዛሬም እንበለው፡-
እኔ መች ፈልጌ ሕይወት ያለችግር
መንፈሴስ መች ሽትቷ ራሷ ግር
ለታላቁ አላማ አለው መልካም ዕድል
ሕይወቴ ትሞላ ትሁን የትግል ድል!
… የሁላችን ሂደት የሁላችን ዕድል
የሚል ነው አንድ አካል
አይበቃም ያሉት ሰው ተርፎ እንዴት ይገኛል?
ከሚለው አያልፍም ሁሉም ገፁ አንድ ነው
ዓለም እንደዚህ ነው
አገር እንደዚህ ነው
ሰፈር እንደዚህ ነው
ሕይወት ይህ ብቻ ነው!
በአዲሱ  ዘመን፤ በጎ በጎው ሁሉ ለአገራችንና ለህዝቦቿ!!

ቅድሚያ በዓለም እጅግ የተከበረውን የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፍዎ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ልገልጽ እወዳለሁ። የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ፤ እርስዎ በኢትዮጵያና በጎረቤት አገራት መካከል ሰላም ለማስፈን ባደረጉት ጥረት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣና ያለ ቅድመ ሁኔታ ከኤርትራ መንግስት ጋራ በመገናኘት የእርቅ ተነሳሽነት ጠቅሶ፣ ለእነዚህ ስራዎችዎ እውቅና በመስጠት የዓመቱ የኖቤል የሰላም  የኖቤል ተሸላሚ መሆንዎን ይፋ አድርጓል፡፡
የአገራችን መሪ ለዚህ ከፍተኛ ሽልማትና እውቅና መብቃቱ ሁላችንንም ሊያስደስተን ሲገባ፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወገኖችዎ ግን የደስታው ተቋዳሽ እንዳንሆን የሚያደርጉን፣ እርስዎንም በተሰጠዎት ዓለማቀፍ እውቅና ልክ እውቅና ከመስጠት የሚያግዱን ቅሬታዎች አሉ፡፡ ይህ የተሸለሙት ሽልማት እንደእነ ማህተመ ጋንዲ ያሉ ታላላቅ የዓለማችን ሰዎች ያገኙት ሽልማት ነው። እርስዎም  እንደነዚህ ታላላቅ ሰዎች ይሆኑ ዘንድ  ምኞታችን ነው። የእነኚህ ታላላቅ ሰዎች አንዱ መለያ ባህርይ ለሰብዓዊነት ያላቸው ከፍተኛ እይታና ከጊዜያዊ ነዋያዊና የስልጣን ጥቅም ይልቅ ዘላቂ የሆነ ለሰው ልጅ የሚበጅ እሳቤ ያላቸው መሆናቸው ነው። በዚህም ምክኒያት ከቂመኝነትና ከበቀልኝነት የፀዱ ናቸው።
ክቡርነትዎም በዚህ በተሰጠዎ ዓለማቀፍ እውቅና ደረጃ ራስዎን ከፍ አድርገው ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን የደስታው ተካፋይ ሊያደርጉ የሚችሉበት እድል አለ። አብዛኞቻችን የትግራይ ብሄር ተወላጆች፣ እርስዎ ወደ ስልጣን  ከመጡ ወዲህ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ብሄር ተወላጆች እስር ቤት በመግባታቸው፣ ለውጡ ለኛ ሳይሆን እኛ ላይ እንደመጣ እንድንቆጥረው ተገድደናል። በተለይም እንደ ቀድሞ የስራ ባልደረባዎ እንደእነ ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ያሉ ወጣት ምሁራን እንዲሁም ወታደራዊ መሪዎች እንዲሁም ነጋዴዎች በእርስዎ ትእዛዝ መታሰራቸው እጅግ አሳዝኖናል። በዚህም ሳቢያ  በመላው ዓለም የምንገኝ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ‘ወፍሪ ሓርነት’ በሚል መሪ ቃል፣ እስረኞቻችን እንዲፈቱ ትግል ለመጀመር በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን። ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾችን ለማስተባበርም ስራው እየተጀመረ ነው። ከነዚህ ተግባራት አንዱ ራሱ የኖቤል ኮሚቴው ላይ ጫና ማሳደርንም ሊያጠቃልል ይችላል።  
የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሽልማቱን ሊሰጥዎት ከወሰነባቸው ምክኒያቶች አንዱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታትዎ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል። ታዲያ እርስዎም ይህን ከፍተኛ የሰብእና መለኪያ የሆነ እውቅናና ሽልማት በሚመጥን መልኩ፣ ራስዎን ከጊዜያዊ እልህና በቀለኛነት በማፅዳት፣ ወደ ስልጣን ሲመጡ የገቡልንን የይቅርታና የፍቅር ቃል ወደ ተግባር ይለውጡ ዘንድ እማፀንዎታለሁ።
ዛሬ በፖለቲካ ለውጡ ምክኒያት እስር ቤት የሚገኙ የትግራይም ሆነ የሌላ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን በምህረት ከእስር ቢለቅቁ፣ ለዚህ ሽልማት ያበቃዎትንና በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ተስፋ የጫሩበትን የይቅርታና የፍቅር ቃልዎን ተግባራዊ ማድረግዎን ያሳያል። የተሰጠዎት የሰላም የኖቤል ሽልማትም ሁላችንንም በእኩል ያስደስታል፡፡ እናም ክቡርነትዎ ከምንከፋፈልና ከምንሸናነፍ፣ በእርስዎ ይቅርታ አድራጊነት ሁላችንም እናሸንፍ። የትግራይንም ሆነ የሌሎች ብሔር የፖለቲከኛ እስረኞች ይፍቱ!
በመጨረሻም መልዕክቴን በደንብ በሚገልፁልኝ በቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ስንኞች ሃሳቤን እቋጫለሁ።
ለለውጥ ያጎፈረው ዙፋን ላይ ሲወጣ
እንደ አምናው ባለቀን ያምናውን ከቀጣ
አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ
ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ ምህረት አስተምረን አንድ አድርገን መልሰህ  
በድጋሚ እንኳን ደስ ያለዎ!
መርስዔ ኪዳን
ከሜኔሶታ ሃገረ ኣሜሪካ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Saturday, 19 October 2019 14:18

የስኬት ጥግ

• መንግስትን በማሳደግ ኢኮኖሚውን
አታሳደውገውም፡፡
ሮበርት ሜትካልፌ
• ኢኮኖሚውን የሚመራው መንግስት
መሆን የለበትም፡፡
ኪውይኮ ካንሴኮ
• በጥበብ፣ ኢኮኖሚ ሁሌም ውበት ነው፡፡
ሔንሪ ጄምስ
• ማንም ኢኮኖሚውን በእርግጠኝነት
ሊተነብይ አይችልም፡፡
ጃሚ ዲሞን
• ጠንካራ ኢኮኖሚ የሚጀምረው፣
ከጠንካራና በወጉ ከተማረ የሰራተኛ
ሃይል ነው፡፡
ሊል ኦዌንስ
• ሴቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ሲሳተፉ
ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
ሂላሪ ክሊንተን
• ወደ ጨረቃ መጓዝ የፊዚክስ ጉዳይ
አይደለም፤ የኢኮኖሚ እንጂ፡፡
ጆን አር.ፕላት
• በኢኮኖሚ ብልፅግና ውስጥ ፈጠራ
መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡
ማይክል ፓርተር
• ጥሩ ኢኮኖሚ ማለት ጥሩ ፖለቲካ ነው፡፡
ፖል ኪቲንግ
• ኢኮኖሚ ሁሉም ቦታ አለ፡፡ ኢኮኖሚን
መረዳት የተሻሉ ውሳኔዎችን ለመወሰንና
ደስተኛ ሕይወትን ለመምራት ያግዛል፡፡
ታይለር ኮዌን
• ዓለም የሚመራው በሃብታሞች ነው፤
የሚገነባው ግን በድሆች፡፡
አሚት ካላንትሪ
• የሃያ አንደኛው ክ/ዘመን የማህበራዊ
ፍትህ ንቅናቄ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡
ዌንዴል ፒርስ
• የኢኮኖሚ ዕድገትን ዕውን ለማድረግ፣
የግብር ጫናን መቀነስ አስፈላጊ ነው፡፡
ቦብ ሻፈር
(ስለ ኢኮኖሚ


Saturday, 19 October 2019 14:17

የዘላለም ጥግ

• የዓለም ሰላም ከውስጥ ሰላም ይጀምራል::
ዳላይ ላማ
• ውስጣዊ ሰላም ከሌለ፣ ውጭያዊ ሰላም
አይኖርም፡፡
ጌሺ ኬልሳንግ ጂታሶ
• የስኬት መለኪያ፤ ደስታና የአዕምሮ ሰላም
ነው፡፡
ቡቢ ዳቭሮ
• ሰላም የሚመነጨው ከውስጥ ነው፡፡
ከውጭ አትፈልገው፡፡
ቡድሃ
• ሰላም በሃይል ሊጠበቅ አይችልም፤ እውን
ሊሆን የሚችለው በመግባባት ብቻ ነው::
አልበርት አንስታይን
• በዚህ ዓለም ላይ ከአዕምሮ ሰላም የሚልቅ
ሀብት የለም፡፡
ያልታወቀ ሰው
• የአዕምሮ ሰላም ያለው ሰው፤ ራሱንም
ሌሎችንም አይረብሽም፡፡
ኢፒኩረስ
• ሰላም ከፈገግታ ይጀምራል፡፡
ማዘር ቴሬዛ
• የመምረጥ ነፃነት ያለው ሕዝብ፣ ሁሌም
የሚመርጠው ሰላምን ነው፡፡
ሮናልድ ሬጋን
• ከራስህ ጋር ሰላም ስትፈጥር፣ ከዓለም ጋር
ሰላም ትፈጥራለህ፡፡
ማሃ ግሆሳናንዳ
• ሰላምን ከነፃነት ልትለየው አትችልም፤
ማንም ቢሆን ነፃነቱን እስካላገኘ ድረስ
ሰላሙን አያገኝም፡፡
ማልኮልም ኤክስ
• ወደ ሰላም የሚያደርስ መንገድ የለም፤
ራሱ ሰላም ነው መንገዱ፡፡
ኤ.ጄ. ሙስቴ
• ሰላም የጦርነት አለመኖር አይደለም፤
የፍትህ መስፈን ነው፡፡
ሐሪሰን ፎርድ


Saturday, 19 October 2019 14:09

አንድነት ያለ ብዝኃነት

 የአንድና የብዙ ጉዳይ፣ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው፡፡ የአንድና የብዙ ሁኔታ፣ የአያሌ ጠቢባን፣ የበርካታ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው:: አንዳንዶቹ በአሐዳዊው፣ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ፡፡
ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን?
አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን? በደስታም ሆነ በኃዘን ጊዜ፣ በሰላምም ሆነ በጭንቅ ወቅት፣ ተፈጥሮን እየቃኙ ወደ ልብ ጓዳ መግባት ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ለአንድና ለብዙ ምሥጢርም ሐይቁን መመልከት፣ የወፎችን ዝማሬ ማዳመጥ፣ በእጽዋት፣ በእንስሳትና በሰማዩ ውበት መማረክ ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ ብዝኃነትንም፣ አንድነትንም አጣምራ ይዛለችና፡፡ ምን የመሰለ ኅብረ ቀለም፣ ምን የመሰለ ኅብረ ዜማ፡፡ የሷን ምሥጢር ማድነቅና ከእርሷ መማር የሚታክተው የሰው ልጅ ግን ያስተክዛል፤ ያሳዝናል፡፡ ሲተባበርና ሲስማማ ድንቅ ተአምር የሚሠራው የሰው ልጅ፣ ለምን ይሆን የሚከፋፈለው? ብዝኃነቱ ነው የሚያጣላው ወይስ ሌላ ምሥጢር ይኖር ይሆን? የሰው ልጅ በጸጥታ ከራሱ ጋር መሟገት፣ ወደ ህሊናውም ዞር ብሎ እራሱን መጠየቅ ይገባዋል፡፡ መፍትሔ የሚገኘው በመረጋጋት፣ በማዳመጥና በማሰላሰል፣ ከውሱኑ እውቀት በላይ ያለውን እውነት በመፈለግ ነው፡፡
ብዝኃነት ያለ ኅብረት አታምርም፤ ብዝኃነት ተብላ መጠራትም አትችልም፤ ወይም አይገባትም፡፡ ይልቁንም “አለመተዋወቅ”፣ “መራራቅ” በሚሉ ቃላት ብትገለጽ ይሻላል:: አንድነት ያለ ብዝኃነት፣ አንድነት ተብላ ልትጠራ ያስቸግራል፡፡ ብዝኃነት የሌላት ወይም ያልነበራት አንድነት ትርጉም የላትም፡፡ ከመጀመሪያው ወይም ከወዲሁ አንድንና አንድ ወጥ ለሆነ ነገር፣ አንድነት የሚባል ቃል ፍች የለውም፡፡ ወደ አንድነት ለመምጣትም ሆነ አንድ ለመሆን ቢያንስ ሁለት መሆን ያስፈልጋል፡፡ ብዙ መሆንም ያሻል፡፡ ብዝኃነት ውበት ሊሆን የሚችለው ከአሐዳዊነት ሲሻገር ነው፡፡ ከቃየልና ከአቤል ታሪክ የኤሳውና የያዕቆብ ታሪክ ያስደስታል፡፡ የዮሴፍና የወንድሞቹ መጨረሻ ያጽናናል፡፡ የቃየልንና የአቤልን ታሪክ ከመድገም የኔልሰን ማንዴላን ራእይ መድገም ይሻላል፡፡
ችቦ በደንብ ደምቆ እንዲያበራ ብዙ እንጨቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እንጨቶች ኅብረት ሲኖራቸው እሳቱ ይደምቃል፡፡ የእሳቱ ውበት ሌሎችን ይሰበስባል፡፡ ይማርካል! እንጨቶቹ ሲለያዩ ግን እሳቱ ቀስ እያለ ይጠፋል፡፡ ብዝኃነት ያለ አንድነት ይበርዳል፡፡
አንድነት ያለ ብዝኃነት ያፍናል፡፡ ብዝኃነትና አንድነት ሲተቃቀፉና ሲሳሳሙ ደስ ያሰኛል:: አንድነትና ተስፋ ሲነግሱ፣ ብዝኃነት ቦታ አይጠበውም፤ ሀብትም አያንስም፤ መካፈልና መተሳሰብ ስላሉ አይርብም፡፡ አንድነትና ተስፋ ሲነግሱ፣ ሕይወት ትርጉም ይኖራታል፡፡ ጊዜም ይበረክታል፡፡ እኔ እኔን ለመሆን፤ እሱ እሷ፣ አንተና አንቺ ታስፈልጉኛላችሁ፤ ያለ አንተ፣ ያለ አንቺ፣ እኔ፣ የውሸት ጣዖት ነው የምሆነው፡፡ ያለ አንተና ያለ አንቺ፣ እኔ እራሴን ማወቅ አልችልም፡፡ ሰው ሰራሽ መስታወት ስለ ውጫዊ ገጽታዬ፣ ጊዜያዊ መረጃ ሊሰጠኝ ይችላል፡፡ አንተና አንቺ ግን ወደ ውስጤ ዘልቄ እንድገባ ታደርጉኛለችሁ፡፡ አንተና አንቺ ግን የፈጣሪ ሥራ በመሆኔ የሚገኘውን ጸጋና ሞገስ ታዩልኛላችሁ፣ ታሳዩኛላችሁ፡፡ መስታወቱ ሊወደኝ አይችልም፡፡ አንተና አንቺ ማፍቀርንና መፈቀርን ታስተምሩኛላችሁ፡፡ ኃላፊነትን ታለብሱኛላችሁ፡፡
የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት፣ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ወገን ወይም ማኅበር አልለየም፡፡ በዚህም ልዩ መልእክት አስተላለፈ፡፡ እጅግ ልዩ መልእክት! ጠላትንም መውደድ፡፡ ብዝኃነትን እያከበረ አንድነትን አወደሰ፡፡ እንዲሁም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ማንነትና ስለ አባልነት ድንቅ ትምህርት አስተማረ:: ብዙኃነትንና አንድነትን ከማንነት ጋር አስተዋወቀ፡፡ ብዝኃነትን ሲያከብር አንድነትን አልተወም፡፡ አንድነትን ሲያውጅ፣ ብዝኃነትን አልጨፈለቀም:: እነኚህን ሁለት እውነቶች እንዴት ማያያዝ እንደሚቻል ያሳየበትን መንገድ ማጤን ልብ ይሏል፡፡ የእሱ መፍትሔ ለብዙ ፈላስፋዎች፣ ለምድር ጠቢባን ምንኛ በጠቀመ፡፡ “ማንነቴ በአባልነቴ አይወሰንም፤ ማንነቴ ከአባልነቴ ይበልጣል” አለ::
አይሁዳዊነት፣ ግሪካዊነት፣ ሮማዊነት፣ ወንድነትና ሴትነት የብዝኃነት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ አይሁዳዊው ልክ እንደ ግሪካዊው፣ ግሪካዊውም እንደ አይሁዳዊ መኖር አያስፈልገውም፡፡ እያንዳንዱ የራሱ ውበት አለው፡፡ ክርስቶሳዊ ኅብረት ግን የበለጠ ያስውባቸዋል፡፡ በግል ከነበራቸው ውበት የበለጠ ውበት ያጐናጽፋቸዋል፡፡ ምጡቁ ከወዲሁ የነበረውን አያጠፋውም፡፡ ይልቁንም ያሳድገዋል፤ ፍጹምም ያደርገዋል፤ “ማንነቴ አይሁዳዊነቴ ብቻ ነው፣ ግሪካዊነቴ ብቻ ነው” ማለት ማንነትን መወሰን ነው፡፡ ያለውን ውበት ማገድ ነው፡፡ የሰው ልጅ “እኔ” ሲል ጤነኛ “እኔ” እና ጤነኛ ያልሆነ “እኔ” እንዳለ ማወቅ ያስፈልገዋል፡፡ “እኛም” ሲል፣ ጤነኛ “እኛ” እና ወደ ጥፋት የሚወስድ “እኛ” እንዳለ ማጤን ይገባዋል፡፡ ከአባልነት የመጠቀ አንድነት ሲኖር ነው ውበትን መቃኘት፣ አንድነትን ማጣጣም፣ ሰላምን ማስፈን፣ ብልጽግናን ማምጣት የሚቻለው፡፡ ---
(ከዮናስ ዘውዴ ከበደ “ሔምሎክ”
መጽሐፍ የተቀነጨበ)


ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ከሚገኙት 700 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት መካከል 149 ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት በቂ ምግብ እንደማያገኙና የመቀንጨር ችግር ተጠቂ መሆናቸውን ተመድ ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ ሰሞኑን ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፤ 149 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት ተገቢውን ምግብ ባለማግኘታቸው ሳቢያ የአእምሮና የተክለ-ሰውነት እድገት ውስንነት ያለባቸውና ለተለያዩ የጤና ችግሮች የተጋለጡ ሆነዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ከሆናቸው አጠቃላዩ የአለማችን ህጻናት መካከል ግማሹ ለእድገትና ለጤንነት እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ቪታሚኖችንና ሚኔራሎችን እንደማያገኙም የተቋሙ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት የመቀንጨር ችግር ተጠቂ ከሆኑባቸው የአለማችን አገራት መካከል የመን ተጠቃሽ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ ዕድሚያቸው ለትምህርት ካልደረሰ የአገሪቱ ህጻናት መካከል 46 በመቶ ያህሉ የመቀንጨር ችግር ተጠቂ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
በአለማችን 800 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቋሚነት የርሃብ ሰለባ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ ሁለት ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአንጻሩ ከሚገባው በላይ ብዙ መጠን ያለውና ለጤና ተስማሚ ያልሆነ ምግብ በመመገብ ሳቢያ ለከፍተኛ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ለልብ ህመምና ለስኳር በሽታ እንደተጋለጡ አመልክቷል፡፡
ከአምስት እስከ አስራ ዘጠኝ አመት የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ የከፍተኛ የሰውነት ክብደት ተጠቂ ዜጎች ብዛት አሜሪካ ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን እንደምትይዝ የጠቆመው ሪፖርቱ፤በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አሜሪካውያን መካከል 42 በመቶ ያህሉ የችግሩ ተጠቂዎች መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የአገሪቱ ፖሊስ በከተሞች እየተስፋፋ ያለውን የወንጀል ድርጊት በ2 ቀናት ውስጥ እንዲያጠፋ መመሪያ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ግድያና ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎች መስፋፋታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒም፣ ፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች በጋራ በመምከር በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ወንጀሎቹን ማስቆም የሚችሉበትን እቅድ በአፋጣኝ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አመልክቷል፡፡
ወንጀለኞችን በሙሉ በሁለት ቀናት ውስጥ ማጥፋት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ሙሴቬኒ፤ ዜጎች በወንጀለኞች ሲዘረፉና ሲገደሉ እያዩ ዝም የሚሉበት ጊዜ እንዳበቃ ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ መኖሪያ ቤቶችንና ድርጅቶችን ሰብረው እየገቡ በገጀራና በሌሎች መሳሪያዎች እያስፈራሩ ዝርፊያ የሚፈጽሙ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ እጅግ በርካታ ዜጎች በወንጀለኞቹ ቢዘረፉና ቢገደሉም የአገሪቱ ፖሊስ ይህ ነው የሚባል እርምጃ ሳይወስድ በመቆየቱ ሲወቀስ እንደነበርም አስታውሷል፡፡


 ከአሜሪካ መንግስት የተጣለበት ማዕቀብ ክፉኛ ያንኮታኩተዋል ተብሎ ተሰግቶለት የነበረው የቻይናው የሞባይል አምራች ኩባንያ ሁዋዌ፣ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ገቢው በ24 በመቶ ማደጉን አስታውቋል፡፡
ሁዋዌ ኩባንያ ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ብሉምበርግ እንደዘገበው፣ ኩባንያው እስካለፈው መስከረም ወር በነበሩት ያለፉት ዘጠኝ ወራት 185 ሚሊዮን የሞባይል ስልኮቹን ለአለማቀፍ ገበያ በማቅረብ 86.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡
ሁዋዌ ከሞባይል ሽያጭ በተጨማሪ እጅግ ፈጣኑን የ5ጂ ኔትወርክ በስራ ላይ ለማዋል የሚያግዙ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ለመሸጥ 60 ያህል የሽያጭ ስምምነቶችን በአለም ዙሪያ ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር መፈጸሙን የጠቆመው ዘገባው፤ ያም ሆኖ ግን የአሜሪካ ማዕቀብ የኩባንያውን አጠቃላይ አመታዊ ገቢ ክፉኛ ይጎዳዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ሁዋዌ ባለፈው አመት የአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የሞባይል አምራችነት ስፍራን ከአሜሪካው አፕል ኩባንያ መረከቡን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተግቶ በመስራት የሳምሰንግን ቦታ በመረከብ የአለም ቁጥር አንድ የሞባይል አምራች ኩባንያ የመሆን ግብ ቢያስቀምጥም፣ የአሜሪካ ማዕቀብ ግቡን እንዳይመታ እንቅፋት ይፈጥርበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክሎ ገልጧል፡፡

Saturday, 19 October 2019 13:20

በተስፋ የተሞላ ማነቃቂያ

 ‹‹ትችላላችሁ፤ እንደምትችሉ አምናለሁ››


            እኔ ከአባቴና ከእናቴ ቤት ስወጣ 13 ዓመቴ ነው፡፡ ያሳደገኝ እግዚአብሔር ነው፡፡ እናንተንም እግዚአብሔር ያሳድጋችኋል፡፡ (አሜን ይላሉ ልጆቹ) ግን የእምነት ሰው መሆን አለባችሁ:: እንደምታድጉ እንደምትለወጡ ካመናችሁ… በጣም ብዙ ወጣቶች በጣም ብዙ ታዳጊዎች አላችሁ መለወጥ ማደግ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ሃይስኩል የጨረስኩት፣ መጨረስ ከሚገባኝ ጊዜ በስድስት በሰባት ዓመት ዘግይቼ ነው:: ይቻላል ከወሰናችሁ፡፡ ዋናው የናንተ ውሳኔ ነው፡፡ በኛ በኩል ዛሬ እንድትመጡና እንድታዩ የፈለግነው በኋላ በክፍያ ሲሆን፣ ፕሮቶኮል ሲበዛ፣ እንደናንተ ዓይነት ሰዎች፣ እውነተኛ አገር የሚወዱ፣ አገር የሚጠብቁ፣ ለጊዜው ብቻ እጅ ያጠራቸው ሰዎች የማይገቡበት ሥፍራ እንዳይሆን ነው፡፡ እናንተን ካላካተተ የኢትዮጵያ ሃብት መሆን አይችልም፡፡ እናንተም ኢትዮጵያው ናችሁ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚያማምሩ የሃብታሞች ብቻ ሳይሆን የሌላቸውም ጭምር ስለሆነች…፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ቢያንስ ከ4ሺ እስከ 5ሺ የሚጠጉ የጐዳና ልጆችን ከጐዳና በማንሳት ማደሪያ ቦታ እንዲኖራቸው እየሰራን እንገኛለን፡፡ እስካሁን ተናግረን አናውቅም፤ ምክንየቱም ሁሉም ሲያልቅ ስለሚያምር ነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ እንጨርሳለነ:: አልጋ፣ ፍራሽ፣ አንሶላ የሚያግዙን ሰዎች ካገኘን በኋላ በዚህ ዓመት ከ4ሺ -5ሺ የጐዳና ልጆች እናነሳለን፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እያልን ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ብዙ አይደላችሁም፡፡ 30ሺ -40ሺ የሚሆን ነው አዲስ አበባ ያለው:: ማደሪያ ካገኛችሁ ትናንሽ ሥራ ሰርታችሁ፤ ራሳችሁን የምትመግቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እናንተ አካባቢ ክሊኒክ ኖሮ፣ ቢያማችሁ እንኳን የምትታከሙበት ቢያንስ ማታ ማታም ቢሆን የምትማሩበት ነገር እንዲመቻች የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ እናንተ ግን በመደራጀት አሁን ከተማ ውስጥ አበባ ዛፍ እየተከልን ስለሆነ ያንን በመንከባከብ ብቻ… ውሃ በማጠጣት… በመኮትኮት የዕለት ምግባችሁን የምትሸፍኑበትን መንገድ ማመቻቸት የከተማውም የመንግስትም ሥራ ይሆናል፡፡ ከናንተ የሚፈለገው ሱስን መጠየፍ፣ ሌብነትን መጠየፍ፣ ጥላቻን መጠየፍ… ወስኖ መቀየርና ለአገር ኩራት መሆን ነው፡፡ ያንን ደግሞ ትችላላችሁ፡፡ እኛ ከጐናችሁ ነን፡፡ ትችላላችሁ… አምናለሁ እንደምትችሉ!!...››
(ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት የጎዳና ልጆች አንድነት ፓርክን በጎበኙበት ወቅት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)  


Page 8 of 456