Administrator

Administrator

Saturday, 27 July 2019 14:30

የተፈጥሮ ጥግ


 • ዛፍ የሚተክል ከራሱ ባሻገር ሌሎችንም የሚወድ ሰው ነው፡፡
ዶ/ር ቶራስ ፉለር
• ሰው ዛፍ የሚተክለው ለራሱ አይደለም፤ ለቀጣዩ ትውልድ ነው፡፡
አሌክሳንደር ስሚዝ
• ዛፍ ለመትከል ተመራጩ ጊዜ የዛሬ 20 ዓመት ነበር፡፡ ሁለተኛው ተመራጭ ጊዜ ደግሞ አሁን ነው፡፡
ዳሬል ፑትማን
• ዛፎች ለሰው ልጆች መንፈስ ሰላምን ያጎናጽፋሉ፡፡
ኖራ ዋልን
• ዛፎችን እንጂ የጦር ሰራዊትን አታሳድግ፡፡
ያልታወቀ ሰው
• ማደግ ያለብህ እንደ እንጉዳይ ሳይሆን እንደ ዛፍ ነው፡፡
ጃኔት ኤርስኪን ስቱዋርት
• ጥበባችን ሁሉ የተጠራቀመው በዛፎች ውስጥ ነው፡፡
ሳንቶሽ ካልዋር
• ዛፍ ብሆን ሰውን የምወድበት አንዳችም ምክንያት አይኖረኝም ነበር፡፡
ማጊ ስቲፍቫተር
• ዛፍ የሚተክል ሰው፤ እሱ ተስፋን ይተክላል::
ሉሲ ላርኮም
• መጥፎ ጋዜጦችን ለማውጣት ጥሩ ዛፎችን ያወድማሉ፡፡
ጄምስ ጂ.ዋት
• እንደ ዛፍ ሁን፡፡ ዛፍ ቅንጫፉን ለሚቆርጡትም ጭምር ጥላ ይሆናል፡፡
ስሪ ቻይታንያ


Saturday, 27 July 2019 14:28

የግጥም ጥግ

  ቤት

     ቤት የለህም ወይ ብለው ይጠይቁኛል
     አገር የሌለው ቤት ምን ያደርግልኛል?
          2010

        ውጊያ

    እግዝአብሔር አሸነፈ ሦስት ሆኖ ገብቶ
    ሰይጣን ግን ድል ሆነ ብቻውን ተዋግቶ
       2011 ሰኔ ዳዊት ጸጋዬ

Saturday, 27 July 2019 14:27

የዘላለም ጥግ


   • በግላችን ጠብታ ነን፡፡ በአንድ ላይ ግን ውቅያኖስ ነን፡፡
ዩኖሱኬ ሳቶር
• አንድነት ባለበት ምንጊዜም ድል አለ፡፡
ፑቢሊየስ ሳይረስ
• በአንድነት ውስጥ ጥንካሬ አለ፡፡
ኤዞፕ
• የነፃነት መሰረቱ አንድነት ነው፡፡
ኦሊቨር ኬምፐር
• አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት ማለት አይደለም፡፡ የዓላማ አንድነት ነው፡፡
ፕሪስኪላ ሺረር
• አንድነት ሲፈጥሩ ደካሞች እንኳ ጠንካራ ይሆናሉ፡፡
ፍሬድሪክ ቮን ሺለር
• ዓላማው ለጥፋት የሆነ ጊዜ አንድነት አደገኛ ነው፡፡
ሊቪ ዛካርያስ
• አገራችንን የምንወድ ከሆነ፣ የአገራችንንም ሰው መውደድ አለብን፡፡
ሮናልድ ሬጋን
• ይህችን አገር ለሁላችንም ምቹ የመኖርያ ሥፍራ ካላደረግናት በስተቀር፣ ለማናችንም ምቹ መኖርያ አትሆንም፡፡
ቲዮዶር ሩስቬልት
• አገራችንን እንድንወድ ዘንድ፣ አገራችን የምትወደድ መሆን አለባት፡፡
ኤድመንድ ቡርኬ
• የሥነ ጽሑፍ ማሽቆልቆል፣ የአገር ማሽቆልቆልን ያመለክታል፡፡
ጆሃን ዎልፍ ጋንግ ቮን ገተ
• ታላቅ አገርና ታላቅ ህዝብ ለመሆን፣ ታላላቅ ነገሮችን መስራት አለብህ፡፡
ሆመር ሂካም
• ታላቅ አገር የምንፈልግ ከሆነ፣ ራሳችንን መለወጥ የግድ ነው፡፡
ኮሪ ቡከር

Saturday, 27 July 2019 14:26

አስገራሚ እውነታዎች

(ስለ ዛፍ)

 • ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ዛፍ፣ አዲስ ከተተከለ ዛፍ፣ በ70 እጥፍ ገደማ የአየር ብክለትን ያስወግዳል፡፡
• አንድ ጤናማ ዛፍ፣ እስከ 10ሺ ዶላር ዋጋ ያወጣል፡፡
• ዛፎች የሚሰጡት ጥላና ነፋሻማ አየር፣ አመታዊ የአየር ማቀዝቀዣና ማሞቂያ ወጪን በ2.1 ቢሊዮን ዶላር ይቀንሳል፡፡
• 20 ሚሊዮን ዛፎችን በመትከል፣ ምድርና ሕዝቧ 260 ሚሊዮን ቶን ተጨማሪ ኦክስጂን ያገኛሉ፡፡ እነዚሁ 20 ሚሊዮን ዛፎች፤ 10 ሚሊዮን ቶን
ካርቦንዳይኦክሳይድን ከከባቢው ላይ ያስወግዳሉ፡፡
• አንድ ዛፍ፣ በህይወት ዘመኑ፣ አንድ ቶን ካርቦንዳይኦክሳይድ ከከባቢው ላይ መሳብ ይችላል፡፡
• ዛፎች ዘና ያደርጋሉ፤ ጭንቀት ይቀንሳሉ፤ የልብ ምት መጠንን ዝቅ ያደርጋሉ፡፡
• ዛፎች ባሉባቸው የገበያ ማዕከላት፣ ሸማቾች፣ የበለጠ ገንዘብ ለማውጣት ፈቃደኞች ናቸው፡፡ በዛፎች በተከበቡ የገበያ ማዕከላት ውስጥ ለረዥም ጊዜ ለመቆየት ፈቃደኛ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡
• ለሥራ በሚመላለሱበት መንገድ ላይ እንዲሁም በቢሮአቸው መስኮቶች ዛፎችን የሚመለከቱ ሠራተኞች የበለጠ ምርታማ ናቸው፡፡
• ዛፎች የንብረትን ዋጋ ከፍ ያደርጋሉ:: በዛፎች የተከበቡ መኖሪያ ቤቶች፣ ዛፍ ከሌላቸው ቤቶች እስከ 25 በመቶ በላቀ ዋጋ ይሸጣሉ፡፡
• በህንፃዎች ዙሪያ በተገቢው ሥፍራ የተተከሉ ዛፎች፣ ለአየር ሁኔታ መቆጣጠሪያ የሚያስፈልገውን ወጪ እስከ 50 በመቶ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡
• የዛፎች ዕይታ ባለበት ሆስፒታል ህክምና የሚወስዱ ህሙማን፣ በፍጥነት ድነው ይወጣሉ፡፡ በህክምና ቆይታቸውም ብዙ መድሃኒቶችን አይጠቀሙም፡፡
• አንድ አማካይ መጠን ያለው ዛፍ፤ በዓመት አራት አባላት ላሉት አንድ ቤተሰብ በቂ የሆነ ኦክሲጅን ያመነጫል፡፡Saturday, 27 July 2019 14:24

ከአዋቂዎች አንደበት


•  ያልተማሩ ምሁራን ያቆዩዋትን አገር፣ የተማሩ መሃይማን አያፈርሷትም፡፡
ታዬ ቦጋለ - የታሪክ ምሁር
(ጦቢያ)
•  በ3ሺ ዓመት ታሪካችን እንዲህ ዓይነት ፈተና ገጥሞን አያውቅም፡፡
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ
(ድርና ማግ የኪነ ጥበብ ምሽት)
• ኢትዮጵያ አንድ ስትሆን እንኳን ታቦቱ ጠንቋዩ እፎይ ብሎ ያድራል፡፡…
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ
(ድርና ማግ የኪነ ጥበብ)
•  እኛ የምንፈልገው ማንነታችንን ሳይሆን አንድነታችንን የሚያስመልስልን ነው፡፡
ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ
(ዶንኪ ቲዩብ)
•  አገራችንን የገደላት የፍልስፍና ድህነት ነው::…
አንዳርጋቸው ጽጌ
(ጦቢያ)
• በኛ አገር ሁለት ዓይነት መፈናቀል ነው ያለው፡፡ አፈናቃዮች ከአዕምሯቸው፤ ተፈናቃዮች ከኑሮአቸው ነው የተፈናቀሉት::…
መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ
(ድሬ ቲዩብ)
•  ኢትዮጵያዊ ቁጣውን በአድዋ፣ ጥበቡን በላሊበላ፣ ትዕግስቱን በአክሱም… እየገለፀ የኖረ የሚገርም ሕዝብ ነው፡፡…
ፓስተር ዮናታን
(ድሬ ቲዩብ)
•  እኛ አገር ያሉትን አክቲቪስቶች:: አክቲቪስት አልላቸውም፡፡… እኔ ማይክሮዌቭ አክቲቪስት ነው የምላቸው:: ማይክሮዌቭ የቀዘቀዘውን አሙቆ የሚያቀርብ ነገር ነው… የቆረፈደ፣ የቆየ፣ ያረጀ ታሪክ አሙቀው… በድሮ ለቅሶ አዲስ ድንኳን ሕዝቡን አስተክለው እያስለቀሱት ነው… በድሮ ለቅሶ አዲስ ድንኳን ተክለናል::…
ፓስተር ዮናታን
(ድሬ ቲዩብ)
• በኢትዮጵያ ላይ የኖሩና ለኢትዮጵያ የኖሩ መካከል ልዩነት አለ፡፡ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያ ላይ የኖርን ነን፤ ለኢትዮጵያ የኖርን አይደለንም ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ለምሳሌ  በኢትዮጵያ ላይ የኖርኩ ነኝ:: ለኢትዮጵያ የኖሩት በጎ ነገር ሰርተው ያለፉት መሪዎቿ፣ ነፃነት የተዋደቁት አርበኞችና ወታደሮቿ ናቸው፡፡…
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
(አንድ አፍታ ቲዩብ)
• አሁን ያሉትን አክቲቪስቶች ከአስለቃሾች ለይቼ አልመለከታቸውም ሀሳብ ቢኖራቸው የሚበጀው፣ የሚጠቅመውና የሚያፋቅረው ላይ ነበር መስራት ያለባቸው…    
ዮናስ
(ቴዴል ቲዩብ)

Saturday, 27 July 2019 13:55

የፍኖተ ሰላም ዩፎዎች!!

“ባህር ዳር እንደገባሁ ባጃጅ ተሳፈርኩ ባጃጅ ማለት ከብዙ ጨርቅና ትንሽ ብረት የተሰራች ለአቅመ ተሽከርካሪነት ያልደረሰች…”ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም ከአፍሪካ መዲና (አንዳንዶች የአፍሪካ ዋና መሽኛ ይሏታል) አዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ሲሄድ ከተማዋን እንደበርሃ አንበጣ በባጃጅ ተወርራ ሲመለከት የተናገረው ነበር፡፡
ወዳጄ በዕውቀቱ ስዩም በባህር ዳር የባጃጅ ቁጥር መብዛት ቢገረምም ለኔ ይበልጥ አስገራሚ የሆነብኝ ግን በፍኖተ ሠላም ጐዳናዎች ላይ እንደ ሮኬት ሲወነጨፉ የሚውሉት ባጃጆች ቁጥር ነው፡፡ ፍኖተ ሠላም በግምት ከ50ሺህ የማይበልጥ ነዋሪና አንድ ባለ አንድ መስመር የአስፋልት መንገድ ብቻ ያላት ቢሆንም የባጃጆች ቁጥር ግን ይገርማል፡፡
የባጃጅና የሶስት ቁጥር ዝምድና ይገርመኛል፡፡ ባጃጅ በሶስት ጐማዎች የምትሽከረከር እጅግ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ስትሆን የተሰራችውም ከብረት፣ ከጨርቅና ከጐማ መሆኑ፣ እንዲሁም በውስጧ ሶስት ተሳፋሪዎችን ብቻ ማቀፍ መቻሏ የባጃጅንና የሶስት ቁጥርን ዝምድና ያጠናክርብኛል፡፡ በአንዳንድ የሀገራችን ከተሞች (አዲስ አበባን ጨምሮ) ከሶስት ተሳፋሪዎች በላይ በመጫን የባጃጅንና የሶስት ቁጥርን ዝምድና ለማፍረስ የተነሱ ቢመስልም በፍኖተ ሠላም ግን ይህ አይሰራም ከሶስት ሰው በላይ በባጃጅ ማሳፈር ነውር ነው፡፡
ከተማዋ አንድ አስፋልት የዋና ጐዳና መስመርና ጥቂት ከኮብልስቶን (የህወሓት ትምህርት ፖሊሲ ያፈራቸው ወጣቶች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው “ገንዘብ የሚያፍሱበት የስራ መስክ” ይሉታል ኮብልስቶንን) የተሰሩ መንገዶች ቢኖራትም ባጃጆች ግን በዚህች ብቸኛ ጐዳና እና ገባር መንገዶች ላይ ከጋማ ከብቶች፣ መንገዳቸውን ከማይጠብቁ እግረኞች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ጋር እየተጋፉም ቢሆን ያለመታከት ሲበሩ ይውላሉ፡፡ እዚህ ላይ አንድ የታዘብኩትን ሁነት ላክል፡፡
በአዲስ አበባ ብዛት ያላቸው ሰዎች መንገድ ዳር ቁመው ከታየ ታክሲ ወይም ሌላ የትራንስፖርት አገልግሎት እየጠበቁ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በፍኖተ ሠላም ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝብ ያለምንም ምክንያት የከተማዋን ብቸኛ የአስፋልት መንገድ በሆል ቆሞበት የነበሩ ቋሚዎች ወደ መሀል በመግባት ያለከልካይ መሀል አስፋልት ላይ ቆመው ወሬያቸውን በኩራት ሲደልቁ ለተመለከተ፤ መንገዱ የተሰራው ለመኪና ነው ወይስ ለእግረኞች የወሬ መኮመሪያ ብሎ እንዲጠይቅ ያስገድደዋል፡፡ ያም ሆኖ በመኪና አደጋ ህይወቱ የሚያልፍ ሰው አለመኖሩን ስሰማ ገርሞኛል፡፡ ይበልጥ የሚገርመኝ ደግሞ የፍኖተ ሰላም ጎረቤት የሆነችው የአዊ ብሔረሰብ ዞን መናገሻዋ ኮሶ በርና ሌሎች የአዊ ብሔረሰብ ዞን ትንንሽ ከተሞች ሳይቀሩ የመንገድ ላይ ህግ በማክበር ከኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆናቸው ነው፡፡ ፍኖተ ሰላም ከጐረቤቷ መማር አልቻለችም ማለት ነው ወይም በዘመኑ ህወሓት ወለድ የፖለቲካ ቋንቋ “ፍኖተ ሰላም ከጐረቤት አገር የልምድ ልውውጥ መውሰድ ይቀራታል” ማለት እንችላለን!!
ፍኖተ ሰላም ከመሄድ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በባህር ዳር የባጃጅ ትራንስፖርት የመጠቀም ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ የተሳፈርኩባት ባጃጅ ሌሎች ሁለት ሰዎች እንዲሳፈሩላት በሯን ከፍታ ተሳፋሪ ብትፈልግም ድርሽ የሚል ጠፍቶ ለረጅም ደቂቃዎች መጠበቅ ግድ ብሏት ነበር፡፡
ጥበቃው ሲሰለቸኝ በኔ ጉትጎታና ተጨማሪ ክፍያ ለመክፈል ፍላጐት በመግለጼ እኔኑ ይዛ በረረች እንጂ ሌሎች ሁለት ሰዎች በመጠበቅ ውላ ባለማደሯ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም፡፡ አንዳንድ የባህር ዳር ቧልት አዋቂዎች “አንድ ባጃጅ አንድ ተሳፋሪ ካገኘ ሌሎች ሁለት ባጃጆች ከፊትና ከኋላ ሆነው ያን እድለኛ ባልንጀራቸውን እንደ አምባሳደር አጅበው ይሄዳሉ” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡
በፍኖተ ሰላም ግን እንደዚህ አይነት የተሳፋሪ ድርቅ የለም፡፡ በአጭር አገላለጽ የፍኖተ ሰላም ባጃጆች ለደቂቃም ጾም የለባቸውም፡፡ ተሳፋሪ ለመሳፈር ባጃጆችም ደንበኞቻቸውን በፍጥነት ለማገልገል ቃለ መሃላ የፈጸሙ ይመስላሉ፡፡
(ደራሲና ጋዜጠኛ ይርጋ አበበ በላቸው “ኢካቦድ”
በሚል ርዕስ ካወጣው መጽሐፍ የተቀነጨበ፤)


• ጠንካራ እምነት ያለው ተቃዋሚ ደስይለኛል፡፡
ፍሬድሪክ ዘ ግሬት
• የላቀ ሥራ ብዙውን ጊዜ ጠንካራ ተቃውሞ ይገጥመዋል፡፡
ድዋይት ኤል.ሙዲ
• ተቃውሞ እውነተኛ ወዳጅነት ነው፡፡
ዊሊያም ብሌክ
• ለናንተ ኢ-አማኒ ነኝ፤ ለእግዚአብሄር ታማኝ ተቃዋሚ ነኝ፡፡
ውዲ አለን
• ለሶሻሊዝም የሰላም ትርጉም፣ የተቃዋሚ አለመኖር ነው፡፡
ካርል ማርክስ
• በመንግስት ውስጥ ስትሆን ተቃዋሚህን መኮንን አለብህ፡፡
ማሂተር ሞሃመድ
• ተቃዋሚ ያለህ መሆኑ ብቻ ታላቅ መሪ አያደርግህም፡፡
ማርኮ ሩቢዮ
• ተቃዋሚህን ፈጽሞ አሳንሰህ መመልከት የለብህም፡፡
ጆን ስካርሌት
• አንዳንዴ ለተቃዋሚ እውቅና መስጠት አለብህ፡፡
ጋውታም ጋምብሂር
• ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መጨረሻቸው ወህኒ ቤት ሲሆን ጤናማ አይደለም፡፡
ቪታሊ ክሊትስችኮ
• በዲሞክራሲ ውስጥ ጤናማ ተቃውሞ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ናቪን ፓትናይክ
• ተቃዋሚዎች ከፊት ለፊትህ ያለውን መቀመጫ ይይዛሉ፤ ጠላቶች ግን ከኋላህ ነው የሚቀመጡት፡፡
ዊንስተን ቸርችል

Saturday, 27 July 2019 14:20

የወቅቱ ጥቅስ

‹‹የአማራ ሕዝብ እንደ ጨቋኝ ሆኖ የተሳለውን ትርክት የማንቀበለው ለፖለቲካ ትርፍ ብለን አይደለም፤ ትርክቱ በተጨባጭ የተሳሳተ ስለሆነ ነው፡፡››
(አቶ ሙስጦፌ ሞሃመድ ኡመር፤ የሶማሌ ክልላዊ ፕሬዚዳንት፤ በባህር ዳር ‹‹የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት›› ላይ ከተናገሩት…)

Monday, 29 July 2019 00:00

የአድማስ ትውስታ

ከአዘጋጁ፡-

        ጋዜጣችን አዲስ አድማስ የተመሰረተችበትን 20ኛ ዓመት ከጥቂት ወራት በኋላ ታከብራለች:: የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ ቅዳሜ
ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር ለአንባብያን የደረሰው፡፡ ወደ 20ኛው ዓመት በዓላችን በሚያዳርሱን ጥቂት ወራት “የአድማስ ትውስታ” በሚል በሰየምነው በዚህ አዲስ ዓምድ፤ ከቀድሞ ዕትሞች እየመረጥን ጊዜውንና ጋዜጣችንን እናስታውሳችኋለን፡፡

                    የዲሞክራሲ እጥረት ወይስ ጥሰት? (ለዜጐቻችን ህይወት ቅድምያ እንስጥ!)
                            አልአዛር ኬ

          በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ ጉዳዮች የተነሳ ብጥብጥ ተከስቶ የሰዎች ህይወት ሊጠፋ ስለብጥብጡ መንስኤና ስለ ሰዎቹ ህይወት መጥፋት ሳይሆን ህይወታቸው ስለጠፋው ሰዎች ቁጥር በፓርላማዋ ክርክር የምትገጥም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር በአለም ለመኖርዋ እጠራጠራለሁ፡፡ ይህ አባዜአችን መቼ እንደሚለቀን አይታወቅም፡፡
ያለፈውን ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ በገጠመን የፖለቲካ ቀውስ በርካታ ዜጐች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ መንግስት የሞቱት ዜጐች ቁጥር በአስሮች የሚቆጠር ነው ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ የለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው በሚል በፓርላማ ክርክር ተደርጐበት ነበር፡፡ በኋላ ላይ አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ የራሱን ማጣራት አድርጐ ሟቾቹ 193 ሲቪሎችና 6 ፖሊሶች ናቸው ብሎ ሪፖርቱን ሲያቀርብ መንግስት በፊት የገለፀው ቁጥር በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ባለመደገሙ ቅር ሲለው ተቃዋሚዎች ደግሞ እኛ ያልነው ቁጥር ልክ ቢሆንም ባይሆንም መንግስት የጠቀሰው ቁጥር ብቻ እንኳን ልክ አልሆነም በሚል የትክክለኝነት ስሜት ተሞልተው አይተናቸዋል፡፡ የሰው ህይወት ክብር በሌለበት፣ የዜጐች ደህንነት ሁለተኛ አጀንዳቸው በሆነበት ሀገር እንዲህ አይነቱ ክርክር በፓርላማ መካሄዱ ብዙም አያስገርምም፡፡
ነገር ግን በከፍተኛ የሀላፊነት ስሜት በፖለቲካ ጉዳይ የተነሳ ዜጐች የማይሞቱበትና አካላቸውን የማያጐድሉበት ስርአት እንዴት አድርገን እንገንባ በሚል አንድም አይነት ውይይት ለማድረግ አለመፈለግ ግን የሀገራችን ትልቁ እርግማን ነው፡፡
የሞቱብንን የቀብርን፣ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሞቱብንም የምናውቅ እኛ፤ የቆሰሉብንን ያስታመምንና በምንና እንዴት ሆነው እንደቆሰሉብንም የምናውቀው እኛ፤ የቆሰሉብንን ያስታመምንና በምንና እንዴት ሆነው እንደቆሰሉብንም የምናውቀው እኛው ሆነን፤ አንድ ኮሚቴ አጣራሁ ብሎ ብሎ ቢነግረን የምንመዝነው እቤታችን ጓዳ ካለው እውነተኛ የራሳችን ሪፖርት ጋር ነው፡፡
ባለፈው በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው የፓርላማ ውይይት ግርምቱ ሳይጠፋብን አሁን በቅርቡ በዚሁ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በፓርላማ የተካሄደው ውይይት ሌላ አስገራሚ ነገሮች ነበሩት፡፡
በአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ የፓርላማው የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፣ በሁከቱ ወቅት የተከሰተው የሰብአዊ መብት አያያዝ እጥረት ላይ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፣ በቀጣይም ትምህርት ተወስዶበት ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው:: የደረገው ውይይት ግን ከላይ የተጠቀሰው ሃሳብ በተግባር እንደማይውል ያረጋገጠ፤ በፖለቲካ አያያዛችን ወደፊት በተአምርም ቢሆን መራመድ እንደማንችል ያሳየ ነበር፡፡
በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የተደነገገው የዲሞክራሲ እጥረት፣ የዲሞክራሲ ጥሰት በሚለው ቃል ይተካልን በሚል በተቃዋሚዎች የቀረበው ሃሳብ ውሳኔው መንግስትን አጥፊ ነው ብሎ ስላልጠቀሰ የዲሞክራሲ ጥሰት ተፈጽሟል ቢባል በዘወርዋሬ መንግስትን ያመለክታል ከሚል ሃሳብ የመነጨ ይመስለኛል:: የዲሞክራሲ ጥሰት ሆነ እጥረት ተከስቷል ተብሎ በፈለገው አይነት አገላለጽ ቢፃፍ የሞቱትና የቆሰሉት ወገኖቻችን በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደሞቱና እንደቆሰሉ እኛው ዋነኛ ባለቤቶቹ ጠንቅቀን ስለምናውቅ የቃላት አተካራው ጠብ የሚል ነገር የለውም፡፡
ነገር ግን ከኢህአዴግ ወገን የቀረበው ሙግት ከምንሠራው ስህተት መቸም ቢሆን ትምህርት ለመቅሰም ዝግጁነት እንደሌለን የሚያሳይ ነው:: አንድ የኢህአዴግ ተወካይ የተከበሩ የፓርላማ አባል፤ ነገሩን ያስረዱት፡፡ “እጥረት በባህሪው ጉድለት እንዳለ ያሳያል፤ የተሟላ ነገር የለም የሚል ነው፡፡ ጥሰት የሚለው ቃል ተመጣጣኝ አይደለም፤ ገደብ አልፏል በሚል ይቀመጥልኝ ተብሎ በሌላ መልኩ የቀረበ ስለሆነ እጥረት በሚለው ይቀመጥ እንላለን” በሚል ነው፡፡ እኒህ ተወካይ ያው የድርጅታቸው ነገር ሆኖባቸው የተናገሩት እንጂ የህዝቡን ስሜት ለመረዳት ሞክረው አሊያም በቀናነት ገምተውት ቢሆን ኖሮ ከዚህ የተሻለ ነገር ሊያቀርቡ ወይም ያቀረቡትን ከማቅረብ ይቆጠቡ ነበር ብዬ አስባለሁ:: መንግስት የዲሞክራሲ እጥረት አለብኝ ማለቱ እኔ የምፈልገውን ያህል ዲሞክራሲን አላሰፈንኩም እንጂ የቻልኩትን እየሰራሁ ነው፤ ለማለት እንደሆነ ይሁንለት እንበል፡፡ ነገር ግን 193 ዜጐች ህይወታቸውን ያጡት በምን ዓይነት ችግር እንደሆነ እኛ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ዲሞክራሲ ያጥራቸዋል ሳይሆን በግልጽ ይጥሳሉ እየተባሉ በየጊዜው የሚወገዙት ሀገሮች በፖለቲካዊ ብጥብጥ 193 ዜጐቻቸው የማይሞቱባቸው እነሱ ከመላእክት ጋር እየሰሩ ይሆን?
በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት አያያዛቸው ለዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ደፍሮ የሚከራከርላቸው ሰው መቼም ብዙ እንደማይገኝ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ በመቶ የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎቻቸውን የማይገድሉት ስለ ሰማይ ቤቱ ህይወታቸው ስለሚያስቡ ይሆን? ግብፅ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኡጋንዳ ወዘተ…መሪዎቻቸው በስልጣናቸውን በተቃውሞ ቀልድ አያውቁም፡፡ ግን በመቶ የሚቆጠሩ ዜጐቻቸውን ሲፈጁ አይታዩም፡፡ ሞትና ፍጅት እኛ ሀገር ቀልድ የሆነበት ምክንያት ግን በእጅጉ ያስገርማል፡፡
መንግስት በጊዜው የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በወሰደው እርምጀ የ193 ዜጐች እልቂት ተከስቷል፡፡ ይህ እርምጃ ገደብ ያለፈ እርምጃ ነው:: ተብሎ በመንግስት በኩል እንዲታመን መሞትና መቁሰል የነበረባቸው ዜጐች ስንት ሺ መሙላት ነበረበት፡፡ ነገሩ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ያ ሁኔታ መንግስት እንደተመኘውና እንዳደረገው ተመጣጣኝ ነው ተብሎ መወሰኑ ለኢህአዴግ የልቡን አድርሶለት ይሆናል፡፡ የህዝቡን ስሜትና ልብ ግን ከቶም አያሽርለትም፡፡
የእውነተኛው ሪፖርት ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለቀባሪው አረዱት እንደተባለው ተመጣጣኝ ነው አይደለም፤ አጥሯል የለም ተጥሷል በሚል ለማሳመን እንዲያው ደከመ እንጂ ዋነኛው ትኩረቱ ሊሆን የሚገባው ከዚህ ስህተት ምን ተምሬአለሁ፤ ወደ ፊትስ እንዴት መራመድ አለብኝ የሚሉትን ጉዳዮች ነበር፡፡
ኢህአዴግ የዲሞክራሲ ጥሰት አልፈፀምኩም፤ የዲሞክራሲ እጥረት እንጂ በማለት በተወካዮቹ አማካሯነት መከራከሩ “ሞኝ በሞኝነት ሃሳቡ ለራሱ ይራቀቃል” የሚለውን የአይሁዶች አባባል ያስታውሳል፡፡
ጥሰት ፈጽመሀል አለመባል ከተጠያቂነት ነፃ ያደርገው ከመሰለው ላመነበት የዲሞክራሲ እጥረትና ዲሞክራሲ ላጠረበት ህዝብ የሚከሰው በምንድን ነው? ለዚህስ አልጠየቅም ሊል ይሆን? ለበርካታ አመታት ዲሞክራሲን ካላሰፈንን ወይም የዲሞክራሲ ግንባታችንን ካላሟላን እንደሀገር የመቀጠላችን ጉዳይ አጠያያቂ ነው፤ ዲሞክራሲ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳያችን ነው ብሎ ኢህአዴግ አስረግጦ ሲያስረዳን ኖሮአል፡፡ ታዲያ አሁን የዲሞክራሲ እጥረት ተከስቶብኛል ማለቱ በራሱ ማስጠንቀቂያ መሠረት የሀገሪቱን ህልውና ወደየት እየወሰደ ነው?
የኢህአዴግ አጋር ድርጅት አባል የሆኑ አንድ የተከበሩ የፓርላማ አባል፤ “መቻቻል፣ ዲሞክራሲን ማስፋትና ካለፈው ስህተት መማር ይጠቅማል”  ብለዋል፡፡
እኒህ የተከበሩ ሰው ስለ ኢህአዴግና ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን ግልጽ አቋም በደንብ ስለምናውቅ እንዲህ ያለ ሃሳብ መሰንዘራቸው አሪፍ ነገር ነው፡፡
በእርግጥም መቻቻልና ዲሞክራሲን ማስፋት፣ ካለፈ ስህተትም መማር ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ ነገር ነው፡፡
እነዚህን ቅዱስ ሀሳቦች በተግባር ለመተርጐም ደግሞ አጥፊ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ቢጠይቅ፣ የበደለውን ቢክስ ከባላንጣው ጋር እርቅ ቢያደርግ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ቢያደርግ በእነዚህ አይነት አሰራሮች ዘመን ባጠገበችው ሀገራችን ይበልጥ ያተርፋል፡፡
ይህን ሃሳብ ኢህአዴግ በአባሉና በተወካዩ የተከበሩ የፓርላማ አባል በኩል የመለሰው “አገርን ከባለ ብጥብጥና አደጋ ለመታደግ ስለሆነ የተወሰነው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ብሎ ባስቀመጠበት ሁኔታ፤ አጥፍታችኋልና ይቅርታ ጠይቁ፤ ጐድታችሁአልና ካሳ ክፈሉ የሚል ነገር ማስቀመጥ ተገቢነት ያለው አይመስለኝም” በሚል ነው፡፡ እኒህ ሰው እንደ ኢህአዴግ አባልነታቸው ሳይሆን እንዲያው በሰውነታቸው ብቻ አስበው መልስ የሚሰጡ ቢሆን የ193 ሲቪል ዜጐችን መገደል ምን ይሉት ይሆን?
እንደ ኢህአዴግ የእርቅ፤ የይቅርታና የካሳን ጉዳይ ፈጽሞ ሊቀበል የማይችልባቸው ሁለት መሠረታዊ ባህሪዎች እንዳሉት ይሰማኛል፡፡ አንደኛው፡- እንዲህ ማድረግ ለጠላቶች መንበርከክና መሸነፍ ነው ብሎ ከህዝብ አንፃር ሳይሆን ከፓርቲ አንፃር ብቻ ከማየት ባህሪው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ጠላቶች ብቻ እንጂ እኔ ስህተት ፈፃሚና አጥፊ አይደለሁም፤ ከሚለው አስተሳሰቡ ነው፡፡ ድሮ ንጉሱ እኔ ከዙፋኔ ከወረድኩ ኢትዮጵያ ያልቅላታል ይሉ ነበር እንደሚባለው፤ እኔ ካልመራሁዋት ይህቺ አገር የምጽአት ቀኗ ነገ ይሆናል ብሎ ከሚያስብ ድርጅት፤ እንዲህ ያለ አቋም መንፀባረቁ ብዙም አስገራሚ ነገር አይደም፡1 እንደ ሀገር መሪ ድርጅት ኢህአዴግ፤ ለኛም ለራሱም ሲል ከስህተት መማሩን ሊያሳየንና ከህዝብ ጋር እልህ መጋባቱን ማቆም ይገባዋል፡፡ አስራሁለተኛው ሰአት ሲመጣና ጊዜ ሲመሽ የሁሉም ማረፊያ ያው ህዝቡ ነው፡፡ ያኔ እንዲህ ያልኩት እንዲህ ያደረኩት ተገድጄ ነው፤ ተሳስቼ ነው ብዙም አያዋጣም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ የኢህአዴግ ስህተትና የኢህአዴግ ድክመት በምንም ነገር ቢሆን እነሱን የተሻሉና እንከን አልባ እንደማያደርጋቸው ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡ ለሁሉም ችግሮች ኢህአዴግን ብቻ መርገም ኢህአዴግን ብቻ ማውገዝ ለህዝብ ጥቅም አያመጣም፡፡
ህዝብና ታሪክ ሁሉን እንደ የእጅ ስራው ብቻ ነው የሚመዝነው፡፡ የመንግስት ስልጣን አለመጨበጥ ከጥፋት ነፃ አያደርግም፡፡ በድጋፍ አብሮ ተሰልፎ ህይወቱን ለሰጠ ህዝብ፤ ካሳው ህብረት፣ አንድነትና የተሻለ ስራን እንጂ ለግል ስልጣን ያለ እረፍትና እፍረት መሿኮት ከቶም መሆን የለበትም፡፡
ለማጠቃለል በሀገራችን ፓርላማ፣ ዜጐች በፖለቲካ የተነሳ የማይሞቱበትና የማይቆስሉበት ስርአት እንዴት በህብረት እንገንባ በሚል ጉዳይ ላይ ውይይት ሲደረግ ማየት እናፍቃለሁ፡፡ ለትንሽ ለትልቁ ጉዳይ ይዋጣልን እያልን ጦርና ዘገር ሰባቂ ጀግኖች ሆነን ያተረፍነው ነገር ቢኖር የዜጐች ህልፈትን ብቻ ነው፡፡ አምላክ ይርዳን!!   

 የእውቁ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ይርጋ አበበ አለባቸው ‹‹ኢካቦድ፣ የተዛቡ አገራዊ ትርክቶችና ፍሬያቸው›› መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ጀምሮ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ በዋናነት ታላላቅ የፖለቲካ ወጎችን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን፣ የልጅነት ጊዜን፣ እንዲሁም ዋዛና ቁም ነገር የያዙ ነገር ግን አስተማሪ የሆኑ ትርክቶችን የያዘ ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
አሁን በሕይወት በሌለችው ሰንደቅ ጋዜጣ፣ በአሀዱ ሬዲዮና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በተለይም በፖለቲካ ትንታኔ ጽሑፎቹና በስፖርት ዝንባሌው የሚታወቀው ጋዜጠኛ ይርጋ አበበ ‹‹የዘመኑ ተመስገን ገብሬ›› የሚያሰኘውን ከእድሜውና ከኖረው በላይ አንብቦና አንሰላስሎ የጻፈውን መጽሐፍ እነሆ በረከት ስለማለቱ አንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርታኢ ጥበቡ በለጠ በመጽሀፉ ጀርባ ባስቀመጠው ማስታወሻ አስፍሯል፡፡ በ187 ገፅ የተቀነበበው መጽሐፉ በ67 ብር ከ83 ሳንቲም ለገበያ የቀረበ ሲሆን ጃፋር መጻህፍት መደብር በዋናነት እያከፋፈለው ይገኛል::

Page 12 of 447