Administrator

Administrator

   በጨዋታ ላይ ሆነው ሳላቸው ሳይመጣባቸው ሆን ብለው በተቀናቃኝ ቡድን ተጫዋች ላይ ወይም በውድድር ሃላፊዎች ላይ የሚያስሉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲባረሩ በአለማቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ መወሰኑን ስካይ ስፖርትስ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
ፌዴሬሽኑ ሆን ብለው የሚያስሉ ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጡ የሚያስገድድ አዲስ ህግ ያወጣው የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በማሰብ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ዳኞች ሆን ብለው በቅርብ ርቀት ከሚገኝ ተጫዋች ፊት የሚያስሉ ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ እንዲያባርሩ መልዕክት ማስተላለፉንም አመልክቷል፡፡
ዳኞች ሳላቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገው የሚያስሉትን በቀይ ካርድ ከማባረር እንዲታቀቡ እንዲሁም ተጫዋቾች መሬት ላይ ምራቃቸውን እንዳይተፉ እንዲመክሩም ፌዴሬሽኑ ያወጣው አዲስ ህግ ያዝዛል፡፡

  ታዋቂዎቹ የማህበራዊ ድረ ገጾች ፌስቡክና ትዊተር ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭተዋል በሚል በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድረ ገጾች ላይ የእገዳ እና መረጃ የማንሳት እርምጃዎችን እንደወሰዱ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች በትራምፕ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የወሰኑት ህፃናት የበሽታ መከላከል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ለኮሮና ቫይረስ አይጋለጡም የሚል የተሳሳተና አደገኛ መረጃ በማሰራጨታቸው መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱ በፌስቡክና ትዊተር ላይ አድርገውት የነበረው መረጃ በኩባንያዎቹ በአፋጣኝ እንዲነሳ መደረጉንም አመልክቷል፡፡
ትዊተር ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የለቀቁትን የተሳሳተ መረጃ የያዘ አጭር ቪዲዮ እስኪያነሱት ድረስ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚጠቀሙበትን ይፋዊ የትዊተር ገፃቸውን ማገዱን ያስታወቀ ሲሆን ፌስቡክ በበኩሉ፤ በትራምፕ ገጽ ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ ከበሽታ መከላከል ጋር በተያያዘ ሀሰተኛ መረጃ የያዘ እንዲሁም የመተዳደሪያ ደንብና ፖሊሲውን የሚጥስ በመሆኑ መረጃውን ማንሳቱን አስታውቋል፡፡

   የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው አለም ከ1 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተጎጂ ማድረጉን የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ አለማችን ከኮሮና ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት የከፋ አጠቃላይ ቀውስ ሊገጥማት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
በአለም ዙሪያ በሚገኙ ከ160 በላይ አገራት ከኮሮና ስጋት ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና በዚህም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች ተጎጂ መሆናቸውን የጠቆሙት ጉቴሬዝ፣ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም 250 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደነበሩ ማስታወሳቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል።
የአለማችን አገራት መንግስታት ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው አንገብጋቢ ጉዳይ ተዘግተው የቆዩ ትምህርት ቤቶችን መክፈት መሆኑን ዋና ጸሃፊው ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡


   ኮሮና ቫይረስ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በመላው አለም በየ15 ሰከንዱ አንድ ሰው ወይም በየቀኑ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝና፣ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ህንድ እና ሜክሲኮ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ19.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ713 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስነበበው ወርልዶ ሜትር ድረገጽ፣ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 12.3 ሚሊዮን ያህል መድረሱን አስታውቋል፡፡ የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 5 ሚሊዮን የደረሰባትና ከ162 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት አሜሪካ፤ ከአለማችን አገራት በተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር ቀዳሚነቱን የያዘች ሲሆን፣ ብራዚል በ2.8 ሚሊዮን ተጠቂዎችና በ95 ሺህ ሟቾች በሁለተኛነት ትከተላለች፡፡ ህንድ በ1.9 ሚሊዮን ተጠቂዎች፣ ሜክሲኮ በ50 ሺህ ያህል ሟቾች ከአለማችን አገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ድረገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ቫይረሱ ከገባባቸው 188 የአለማችን አገራትና ግዛቶች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ወይም 126 አገራት የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ሪፖርት ማድረጋቸው የዘገበው ሮይተርስ፣ በ80 በመቶ የአውሮፓ እንዲሁም በ70 በመቶ የእስያ አገራት የቫይረሱ ስርጭት እያደገና እየተስፋፋ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
ባለፉት 5 ወራት በአለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ መጨመሩን የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፣  ከየካቲት መጨረሻ እስከ ሃምሌ ወር አጋማሽ በነበረው ጊዜ በቫይረሱ ከተጠቁ 6 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 15 በመቶው ወጣቶች መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከአፍጋኒስታን አጠቃላይ ህዝብ አንድ ሶስተኛው ወይንም 10 ሚሊዮን ያህሉ በኮሮና ቫይረስ ሳይያዝ እንዳልቀረ በጥናት ማረጋገጡን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሙከራ በማድረግ ላይ ከሚገኘው ጆንሰን ጆንሰን ኩባንያ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ለመግዛት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈጸሙንና በቀጣይም 200 ሚሊዮን ተጨማሪ ክትባቶችን ለመግዛት ማቀዱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜናም፤ ሩሲያ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመጭው ጥቅምት ወር ለዜጎቿ ለመስጠት ማሰቧን ባለፈው ሳምንት ማስታወቋን ተከትሎ፣ የአለም የጤና ድርጅት ሩሲያ ክትባቱን ለማምረትና ለዜጎቿ ለመስጠት አለም አቀፍ መመሪያዎችን መከተል አለባት ሲል ዕቅዱን መቃወሙን ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ድቀት ማድረሱንና የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ በ11.9 በመቶ መቀነሱን የዘገበው ቢቢሲ፣ የስፔን ኢኮኖሚ ታይቶ የማይታወቅ የ18.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና የፈረንሳይ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትም በሁለተኛው ግማሽ አመት የ13.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስረድቷል፡፡
በመላው አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ ወደ 10 ሚሊዮን የተጠጋ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥርም 22 ሺህ ያህል መድረሱን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ 530 ሺህ ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ደቡብ አፍሪካ፤ በአህጉሪቱ በተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚውን ስፍራ የያዘች ሲሆን ግብጽ በ95 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ45 ሺህ፣ ጋና በ39 ሺህ፣ አልጀሪያ በ33 ሺህ ተጠቂዎች እንደሚከተሉ ተነግሯል፡፡ በአፍሪካ በቂ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እየተደረገ አለመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት እያፋጠነው እንደሚገኝ የዘገበው ሮይተርስ፣ በአህጉሪቱ ከተደረጉት 9 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በ10 አገራት መደረጋቸውን አመልክቷል:: ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ ሞሮኮ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ሞሪሺየስ እያንዳንዳቸው ከ200 ሺህ በላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎችን ማድረጋቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ሶስት ሚኒስትሮች ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በተረጋገጠባት ጋምቢያ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ሃሙስ ለ21 ቀናት የሚቆይ የሰዓት እላፊና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱ የተነገረ ሲሆን፣ በሞዛምቢክም ከትናንት ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ አዲስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ተነግሯል፡፡
በደቡብ አፍሪካ 24 ሺህ ያህል የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን አልጀዚራ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ ያስነበበ ሲሆን ቢቢሲ በበኩሉ፤ በደቡብ ሱዳን 78 ያህል የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውንና አንዱ ለሞት መዳረጉን ዘግቧል፡፡

 ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤ “በግጥም ሃሳብን ለመግለጽ” በሚል ርዕስ የፃፉትን ታሪክ ወደ ስድ ንባብ ስንቀይረው የሚከተለውን ስነ ተረት ይመስላል፡፡
አንድ ገጣሚ ያጋጠመውን እንዲህ ሲል ተረከ፡-
የሚተርከው ለአንድ ፈላስፋ ነው፡፡
“ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ንጉስና ንግስቲት ቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ይኖሩ ነበረ፡፡ እስካሁን ልጅ አልወለዱም፡፡ መንግሥቱን የሚመራና ዙፋኑን የሚወርስ ልጅ ለማፍራት ይፈልጋሉ፡፡ ውለው አድረው አንድ ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ሰፈርተኛው ባለሥልጣን ንጉሣዊ ቤተሰብ የተለያዩ የውጭ ሀገር እንግዶች ሁሉ ተገኙ፡፡ እንኳን ማርያም ማረችሽ ለማለት የመጡ ናቸው፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ሙገሳና እንኳን ደስ አልዎት ብለው ለንጉሡ ደስታቸውን ለመግለጽ ተዘጋጅተው የመጡት አያሌ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ “በሉ የልጁን፣ የልዑሉን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ምኞታችሁን ተናገሩ፡፡” አሉ ንጉሡ፡፡
ሳይንቲስት ተነሳና “ይሄ ልጅ ሃኪም ይሆናል” አለ፡፡
ሰው ሁሉ አጨበጨበ፡፡
ቀጥሎ የቤተክህነቱ ሹም ተነሱና “ይሄ ልጅ ጳጳስ ይሆናል” አሉ፡፡
ሰው ሁሉ በጭብጨባ ደስታውን ገለፀ፡፡
ሌላው ሰው ተነሱና “ይሄ ልጅ ያለጥርጥር ጀነራል የአገራችን የጦር መሪ ነው የሚሆነው፡፡”
ሰው ከሁሉም የበለጠ ጭብጨባ አሰማ፡፡
ሌላው የመጨረሻው ሰው ተነሳና የተለየ ነገር ተናገረ፡፡
እንዲህ አለ፡- “ሁላችሁም ያላችሁት ሊሆን የሚችልና ልዑላችንም ያለጥርጥር ሊካንበት እድሉ ሰፊ የሆነ ነገር ነው፡፡ እኔ የምለው ግን ምንም ቢባል ምንም ከመሆን የማይቀር ነው፡፡”
ሁሉም “ንገረና ምንድነው ከመሆን የማይቀረው ያልከው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
የመጨረሻው ሰው ሲመልስም፤ “ይሄ ልጅ አንድ ቀን ይሞታል” አለ፡፡
በቤተ መንግሥት የነበረው ሰው ሁሉ ከፋው፡፡ ተቆጣ፡፡
ሟርተኛ አለው - አንዱ፡፡
ጥቁር ምላስ አለው - ሌላው፡፡
“ይሄ ሰው የመንግሥታችንና የንጉሣችን ጠላት ነው አሉ” ሌሎቹ፡፡
“ይሄን ሰው ሁለተኛ አይኑን እንዳናይ፤ ሠፈራችን እንዳይመጣ፤ ሠይጣን ዲያብሎስ” እያሉ ጥንብ እርኩሱን አወጡት፡፡ ሌላም ሌላም እርግማን አወረዱበት፡፡ አንዳንዶቹ ለጠብ ተጋበዙ፡፡ ጥቂቶቹ በዱላ አነከቱት፡፡
“ፈላስፋ ሆይ! ያጋጠመኝ ይህ ነው፤ አየህ እኔ ሀቀኛ ሰው ስለሆንኩኝ መዋሸት አልፈልግም፤ እውነት ተናግሬ ደግሞ መቀጥቀጥ አልሻም፤ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም አንተ በኔ ቦታ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ፈላስፋውም “ወዳጄ፤ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥምህ “ኦሆሆ! አሀሀ!” እያልክ መውጣት ብቻ ነው” አለው፡፡
*   *   *
ከጉዳይ ሁሉ ክፉ አላስፈላጊ መስዋዕትነት መክፈል ነው፡፡ ከድርድር ሁሉ ክፉ አስቀድሞ ባለቀ ጉዳይ ላይ መነታረክ ነው፡፡ በዘመናዊ አነጋገር በተበላ እቁብ ላይ መጨቃጨቅ ነው፡፡ ጉንጭ አልፋ ክርክር ጊዜን፣ ንብረትንና አቅምን ከማባከን የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ እንደ ፈረንጆቹ አባባል፤ “riding dead horse” (በሞተ ፈረስ መጋለብ ነው፡፡) የእነግብጽ አካሄድ ይሄን ይሄንን ያጠቃልላል፡፡ ሃገራችን “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” ብላ መልካምና ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ጥበብን የተላበሰ ጉዞ አካሂዳለች፡፡ ሚስጢር በወጉ ካልተጠበቀ የባቄላ ወፍጮ ነው በማለትም ተገቢ ጥንቃቄ አድርጋለች፡፡ ማስፈራሪያና ፕሮፓጋንዳ ሳይበግራትም አፀፋውን እየመለሰች የመጀመሪያ የውሃ ሙሌቷን በስኬት ተወጥታለች፡፡ ገና ግን በጥበብ ፣ በብልሃት፣ በፖለቲካ ብስለት፤ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ እንዳትሆን አድርጋ መጓዝ ይጠበቅባታል፡፡ ትዕግስት አስፈላጊ መሆኑን የማወቃችንን ያህል፣ ፍርሃት እንዳልሆነም በቅጡ እናውቃለን፡፡
የውሃ ሙሌት ብቻ ሳይሆን የልብ ሙሌትም ያስፈልጋል፡፡
“ወባህነ”
“ወከመ ዘኢነኢባህነ ኮነ” አለች ይላል፤ ውሻ፡፡ ይላል የግዕዙ ትርጓሜውም፡-
“ጮህን ጮህን
እንዳልጮህን ሆንን”   
ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን የጮህንላቸውን ፍሬ ጉዳዮች አለመርሳት ተገቢ ነው፡፡
“የረጋ ወተት ቂቤ ይወጣዋል” ብለናል፡፡
ቆራጥነትና ሃሞተ መራር መሆን ያስፈልጋል ብለናል፡፡
“ኧረ ምረር ምረር ምረር እንደ ቅል
አልመርም ብሎ ነው ዱባ እሚተከል” ብለናል፡፡
ህግን ተንተርሶ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ መጠነ ሠፊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንርሳ፡፡
“ነገሩ አልቆም ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር” ብለናል፡፡
የሞላና የጐደለውን፤ የጠጠረና የላላውን ለይቶ የፖለቲካ ጥብቅነትን መጠበቅ ያሻናል፡፡
“ከሚጋልብ ፈረስ፣ መንገድ የምታውቅ ታሪክ ትሻላለች” ብለናል፡፡
“ከጥንት ጀምረን እኛ እንደምናውቀው
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው” ብለናል፡፡
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ” ብለናል፡፡
ጅማሮዎቻችንን እናጢን፡፡ የቀሩንን እናስላ፡፡
“ያረፈ የሊጥ ሌባ…” ተባብለናል፡፡
በመጨረሻም “እማማ ሰነፏን” እናስታውሳለን፡፡
እማማ ሰነፏ ምርጥ ባለሙያ ጠላ ጠማቂና ሻጭ ናቸው፡፡ ጠላቸው በጣም ጣፋጭ ነው፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ግቢያቸው ከአፍ እስከ ገደፉ ይሞላል፡፡
ታዲያ እድሜ ልካቸውን በሳምንታት አንድ ቀን ይጠምቁና፤ ያቺ ቀን ስታልፍ ደሞ የጠላው ጊዜ እስኪደርስ ለጥ ብለው ይተኛሉ፡፡ ለዚህ ነው እማማ ሰነፏ የተባሉት፡፡ አድናቂያቸው ጠላ ጠጪም ቶሎ ቶሎ ደጋግመውና አሳምረው ጥመቁ አይልም፡፡ እሳቸውም ተፎካካሪ ይመጣብኛል ብለው አይሰጉም፡፡ ወይም በርከት አድርገው የመጥመቅ እቅድ የላቸውም፡፡
ከእማማ ሰነፏ የምንማረው ነገር አለ፡፡ ለአንድ ሰሞን ብቻ የሚደረግ ዘመቻ ምንም ያማረ ቢሆን፤ ከዚያ መታቀብ ከዘላቂ ልማት ጋር ይጋጫል፡፡ የመጀመሪያው የግድቡ ውሃ ሙሌት በአያሌው ተደንቋል፡፡ ከዘላቂ ግብ አኳያ ግን ብዙ መንገድ ይቀረዋል፡፡
ችግኝ ተክለን፤ ቀጥሎስ? ማለት አለብን፡፡
ግድብ ሞልተን ቀጥሎስ? ማለት አለብን፡፡
እጃችንን ታጥበን ጭንብል አጥልቀን ተራርቀን…ቀጥሎስ? ማለት አለብን፡፡
…ቁጥጥርና ግምገማስ መቼ እናድርግ ማለት አለብን፡፡ ዲሞክራሲውስ ምን ያህል አደገ? ጐለበተ? ምን ያህል ከሌሎች የእድገት ጉዳዮቻችን ጋር ተሰናሰለ? ጐረቤቶቻችንስ ምን ሂደት ላይ ናቸው? የካሮትና የአርጩሜ ነገር እንዳይሆን፡፡
“Carrot and Stick” ሥርዓታችን እና መርሀችን የት ድረስ ሥራ ላይ ዋለ? ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችንስ የት ድረስ ሥራ ላይ ዋሉ? ትኩረትን በሰፊው የሚሹ ብዙ ጥያቄዎች አሉን፡፡ ተረካቢው ትውልድም ሆነ አስረካቢው አንጋፋ አቃጅ፣ አትጊ፣ አነቃቂና ውጤት ናፋቂ እንዲሆን፤ ሌት ተቀን ንቃትና ትምህርት ወደ ህዝቡ እንዲዘልቅ፣ ጥርት ባለ መንገድ፣ ዛሬ የወቅቱ ጥያቄያችን ነው፡፡ አንድን ግብ ለማሳካት ድካምና መስዋዕትነት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንቅፋት በሚያጋጥመን ሰዓት ዘላቂውን ግብ እያሰብን፣ ትናንሾችን ችግሮች በትዕግስት ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ አይጢቱን ለመምታት አብረን ምጣዱን እንዳንሰብረው፡፡ “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” ማለት አለብን፡፡

Friday, 07 August 2020 16:32

የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ-19

Friday, 07 August 2020 16:32

የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ-19

Page 13 of 499