Administrator

Administrator

እነሆ መፅሀፍ መደብር፣ ሊትማን ቡክስና ክብሩ መፅሀፍት መደብር በመተባበር በየወሩ መጨረሻ ባሉት ቅዳሜና እሁድ የሚያዘጋጁት የመፅሀፍ ሂስ ጉባኤና አውደ ርዕይ የዛሬ ሳምንት ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው ትራኮን ህንፃ ላይ ይከፈታል፡፡
“ሀሳብን በሀሳብ መፈተን” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ የሂስ፤ ጉባኤና አውደ ርዕይ ላይ “የአለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ ገብረ-መሲህ ድርሰቶች (የኦሮሞ ታሪክ ከ1500-1900) የተሰኘው መፅሐፍ ለሂስ የተመረጠ ሲሆን መፅሀፉ በ19ኛው ክ/ዘመን ከተፃፉ መፅሀፍቶች መካከል የአገራችንን የ400 ዓመታት ታሪክና በተለይም የኦሮሞን ህዝብ ታሪክና ባህል በስፋት የሚያስቃኝ ነው ተብሏል  ለሂስና ለውይይት የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ሥነ-ጥበባት መምህር አቶ አበባው አያሌው እንደሆኑም የአውደርዕዩ ዝግጅት አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ገልፀዋል፡፡ ቅዳሜና እሁድ አውደርዕዩን የሚጎበኙ የመፅሀፍት እቁብን ጨምሮ ከ25 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸው መፅሀፍት መግዛት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

 ማይና ፕሮሞሽን ኢንተርቴይንመት ከኢትዮጵያ ሆቴል ጋር በመተባበር የሚያካሂደው 11ኛው “ህበረት ትርኢት” የኪነ - ጥበብ ምሽት የፊታችን አርብ ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ይካሄዳል፡፡
 ዝግጅቱ አጭር ኮሜዲ፣ ግጥም በጃዝ፣ ወግ፣ ሙዚቃና ስታንዳፕ ኮሜዲ የሚያካትት ሲሆን በዚህ ደማቅና የመማሪያ መድረክ ላይ ፍላጎት ያለው እንዲሳተፍ አዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል፡፡

 የሩሲያ ፌዴሬሽን ኤምባሲ ብሄራዊ የአንድነት ቀንን በማስመልከት የአዲስ አበባን እና የሳንት - ፔተርስቡርግን እህትማማች ከተማነት ምክንያት በማድረግ ዛሬ ከቀኑ 8፡45 ጀምሮ በሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል (ፑሽኪን አዳራሽ) ከሩሲያ የመጡ ሙዚቀኞች የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ፡፡
ከሩሲያ ሴንት ፒተርስቡርግ በመጡ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች በሚቀርበው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የኢትዮጵያ ታላላቅ ሙዚቀኞች፣ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህራን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሩሲያ ዜጎችና ሩሲያ የተማሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡ ዛሬ በድምቀት ይካሄዳል የተባለው ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት፤ የሁለቱን ከተሞች እህትማማችነት ከማጉላቱም በላይ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የታለመ እንደሆነም የሩሲያ የሳይንስ የባህል ማዕከል የላከው መግለጫ ያመላክታል፡፡

- አንጌላ መርኬል ለ7 ተከታታይ አመታት 1ኛ ደረጃን ይዘዋል
          - አምና 2ኛ የነበሩት ሄላሪ ክሊንተን፤ ዘንድሮ 65ኛ ደረጃን ይዘዋል
          - ግማሽ ያህሉ ሴቶች አሜሪካውያን ናቸው

     ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2017 የአለማችን 100 ኃያላን ሴቶችን ዝርዝር ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን ላለፉት ስድስት አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የዘለቁት የጀርመን መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬል ዘንድሮም ቀዳሚነታቸውን አስከብረዋል፡፡
በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ ለአራተኛ የስልጣን ዘመን የአገሪቱ መራሄ መንግስት መሆናቸውን ያረጋገጡት መርኬል፤ በአመታዊው የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ሲካተቱ የዘንድሮው ለ12ኛ ጊዜያቸው መሆኑን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የአንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በዘንድሮው ዝርዝር የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር የማይክሮሶፍቱ መስራች ባለቤት የሆኑትና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ የተባለውን የበጎ ምግባር ተቋም ከባለቤታቸው ጋር አቋቁመው በመምራት ላይ የሚገኙት ሚሊንዳ ጌትስ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ የፌስቡኳ ሼሪል ሳንበርግ በአራተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ የጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሜሪ ባራ አምስተኛነቱን ይዛለች፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ኃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 100 ሴቶች በቢዝነስ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በፖለቲካ፣ በበጎ ምግባር፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች መስኮች ስኬትን የተጎናጸፉ፣ ሃብት ያካበቱ፣ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉና ተሰሚነትን ያተረፉ ናቸው ተብሏል፡፡ ከአመቱ 100 ኃያላን የአለማችን ሴቶች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት አሜሪካውያን መሆናቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ ሚሼል ኦባማ ዘንድሮ ከዝርዝሩ ሲወጡ፣ በምርጫ የተሸነፉት ሄላሪ ክሊንተን አምና ከነበሩበት የ2ኛነት ደረጃ በሚገርም ሁኔታ አሽቆልቁለው፣65ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን አመልክቷል፡፡
ዘንድሮ 23 የአለማችን ሴቶች በአዲስ ገቢነት የኃያላኑን ዝርዝር መቀላቀላቸው የተነገረ ሲሆን፣ 19ኛ ደረጃን የያዘቺው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ከእነዚህ ሴቶች አንዷ መሆኗም ታውቋል፡፡

 ከሰሞኑ ሌላ የሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው ተብሏል

     ሰሜን ከኮርያ በቅርቡ ያደረገቺው ስድስተኛው የኒውክሌር ሙከራ ባስከተለው የመሬት መንቀጥቀጥና የዋሻ መደርመስ አደጋ ሳቢያ ከ200 በላይ የኒውክሌር ጣቢያው ሰራተኞች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የጃፓኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ የአሻይ ዘገበ ሲሆን የሰሜን ኮርያ መንግስት ግን ሃሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
አገሪቱ ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ፑንጌሪ ከተባለውና በሰሜን ምዕራብ ግዛቷ ከሚገኘው የኒውክሌር ጣቢያ ካደረገቺው የኒውክሌር ሙከራ ጋር በተያያዘ በጣቢያው ዋሻ ውስጥ በሬክተር ስኬል 6.3 የመሬት መንቀጥቀጥና ፍንዳታ መፈጠሩንና 100 ያህል ሰራተኞችን ወዲያውኑ መግደሉን የዘገበው ሮይተርስ፤ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በደረሰ ሌላ አደጋም ሌሎች ከ100 በላይ ተጨማሪ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ መነገሩን አመልክቷል፡፡
የሰሜን ኮርያ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባሰራጨው ዘገባ፤ መረጃው መሰረተ ቢስና አገሪቱ በኒውክሌር ፕሮግራም ላይ እያስመዘገበች ያለውን እመርታ ለማጠልሸት ሆን ተብሎ የተሰራጨ ወሬ ነው በማለት ማስተባበሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜናም የደቡብ ኮርያ የስለላ ተቋም፣ ሰሜን ኮርያ በቅርቡ ሌላ የሚሳኤል ሙከራ ልታደርግ በዝግጅት ላይ መሆኗን የሚያመላክት መረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
የስለላ ተቋሙ በሰሜን ኮርያ የሚሳኤል ፕሮግራም ተቋማት አካባቢ አዲስ ሙከራ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተጧጧፈ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡


    ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ የሚገኘው የሞዛምቢክ መንግስት፣ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የህዝብ ገንዘብ ወጪ በማድረግ አለማቀፍ ብራንድ የሆኑ 45 እጅግ ዘመናዊ የቅንጦት መኪኖችን ለባለስልጣናት ማመላለሻ ለመግዛት ጫፍ ላይ መድረሱንና ይህም የአገሪቱን ዜጎችና የሲቪል ማህበራትን በከፍተኛ ሁኔታ ማስቆጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት መርሴድስ፣ ቶዮታ ላንድክሩዘር፣ ፎርድ ሬንጀር፣ ሃዩንዳይና ፔጆን ጨምሮ በአለማቀፍ የመኪና ገበያ የላቀ ስም ያላቸው ኩባንያዎች ምርቶች የሆኑ 45 አዳዲስ ሞዴል መኪኖችን ለመግዛት ስምምነት አድርጎ ክፍያ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም በማህበራዊ ድረገጾችና በተለያዩ መድረኮች ተቃውሞ እንደገጠመው አመልክቷል፡፡
የመንግስት ባለስልጣናትን ለማንሸራሸር የታሰቡትን እነዚህን የቅንጦት መኪኖች ለመግዛት የተመደበው ገንዘብ፤ በዘንድሮው አመት ለአገሪቱ የአደጋ መቆጣጠር ተቋም ከተያዘው በጀት በእጅጉ እንደሚበልጥና የከተማ ድህነትን ለመቀነስ ከተያዘው በጀት በጥቂቱ እንደሚያንስም ተዘግቧል፡

 የከተማው ስፋት የኒውዮርክ ሲቲን 33 እጥፍ ያክላል ተብሏል

    ሳዑዲ አረቢያ 26 ሺህ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና ከኒውዮርክ ሲቲ 33 እጥፍ ያህል የቆዳ ስፋት የሚኖረውን ኒኦም የተሰኘ እጅግ ግዙፍ ከተማ፤ በ500 ቢሊዮን. ዶላር ወጪ ልትቆረቁር መዘጋጀቷን ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች፡፡
በሰሜን ምዕራባዊ የሳዑዲ ግዛት የቀይ ባህርን ዳርቻ ታክኮ የሚቆረቆረው አዲሱ ከተማ ኒኦም፤ ለኑሮ፣ ለንግድና ለመዝናኛ በአለማቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ተመራጭ ከተማ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን የዘገበው ሮይተርስ፤ ከተማው የሚቆረቆርበት ስፍራም ለእስያ፣ አውሮፓና አፍሪካ አገራት በቀላሉ ተደራሽ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ራዕይ 2030 የተባለውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደተሻለ ለውጥ በማሸጋገር ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን የመፍጠር ግብ ያስቀመጠው ዕቅድ አካል የሆነው ይህ ግዙፍ ከተማ፤የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን አስታውቀዋል፡፡
ከተማው እጅግ የተዋበ፣ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የተሟላ፣ ሙሉ ለሙሉ በታዳሽ ሃይል አቅርቦት የሚሰራ እንደሚሆንና ራሳቸውን የቻሉ በጣም ሰፋፊ የቢዝነስና የኢንዱስትሪ ዞኖች አንደሚኖሩት የጠቆመው ዘገባው፤ የግንባታው የመጀመሪያ ምዕራፍ በ2015 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመትም አመልክቷል፡፡
የአለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች የሆነቺው ሳዑዲ አረቢያ፣ የነዳጅ ዋጋ ከቀነሰበት ከ2014 አንስቶ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝና የፋይናንስ እጥረት መታየቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከልም ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለማስከፈል ማቀዱ እንደሚገኝበትም አክሎ ገልጧል፡፡

ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ሶስት ወራት፣ የደቡብ ኮርያው የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ በታሪኩ ከፍተኛው የሩብ አመት ትርፍ የሆነውን የ9.8 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ሲያስመዘግብ፣ የማህበራዊ ድረገጹ ፌስቡክ በበኩሉ፤ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉ በሳምንቱ መጀመሪያ ተዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ በሩብ አመቱ ያገኘዋል ተብሎ ከተገመተው ትርፍ በእጅጉ የላቀ ትርፈ ማስመዝገቡን የዘገበው ኤቢሲ ኒውስ፤ የሩብ አመት ሽያጩም ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው በ30 በመቶ ብልጫ በማስመዝገብ፣ 55.1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል፡፡ የአለማቸን ቁጥር አንድ የስማርት ፎን አምራቹ ሳምሰንግ፣ በአለማቀፍ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የሚሞሪ ቺፕስ ሽያጩ ጋር በተያያዘ በትርፋማነት አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የሚሞሪ ቺፕስ ምርቱን የበለጠ ለማስፋፋት ባለፈው አመት ብቻ 29.5 ትሪሊዮን የደቡብ ኮርያ ዎን ወጪ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
ፌስቡክ በበኩሉ፤ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ4.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን ትርፉ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገበው ጋር ሲነጻጸር የ80 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሩብ አመት አስመዘግበዋለሁ ብሎ ካቀደው ገቢ የ47 በመቶ ብልጫ ያለው የ10.33 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን ከዚህ አጠቃላይ ገቢው 98 በመቶ ያህሉን ያገኘው ከድረ-ገጽ ማስታወቂያ አገልግሎቱ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

 የኦስካር እጩው ታዋቂ የሆሊውድ ዳይሬክተርና የፊልም ጸሃፊ ጄምስ ቶባክ፣ ጾታዊ ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሶብናል በሚል በይፋ ክሳቸውን የሚያቀርቡ ሴት ተዋንያን ቁጥር 238 መድረሱን ሎሳንጀለስ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ሃርቬ ዊኒስተን የተባለው ታዋቂ የፊልም ፕሮዱዩሰር፣ “ጾታዊ ትንኮሳና የአስገድዶ መድፈር ጥቃት አድርሶብናል” በማለት ከ40 በላይ ሴት ተዋንያን ባለፉት ሳምንታት በአደባባይ ክሳቸውን ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ “እኔም” የተሰኘና “ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶብኛል” የሚሉ ሴቶች ድርጊቱን ያወገዙበት ዘመቻ፣ በማህበራዊ ድረገጾች ተጧጡፎ መቀጠሉን ያስታወሰው ዘገባው፤በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ደግሞ ሌላኛው ታዋቂ የሆሊውድ ዳይሬክተር ጄምስ ቶባክ፣”ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሞብናል” የሚሉ በርካታ ሴት ተዋንያን ወደ አደባባይ እየወጡ ሲሆን ጉዳዩ ዓለማቀፍ ትኩረት እየሳበ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
“ዘ ፒክ አፕ አርቲስት”ን ጨምሮ በርካታ ተወዳጅ ፊልሞችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ዳይሬክተሩ፤በተለይ ጀማሪ ተዋንያንን ወደ ፊልሙ አለም ለማስገባት የተለያዩ ጾታዊ ትንኮሳዎችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን እንደሚያደርስባቸው የሚገልጹና “የጥቃቱ ሰለባ ነን” በሚል ምስክርነታቸውን የሚሰጡ የሆሊውድ ሴት ተዋንያን ቁጥር 238 መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የ72 አመቱ ዳይሬክተር ከተዋንያኑ የቀረበበትን ክስ፣ “መሰረተ ቢስ ውንጀላ” በማለት ያጣጣለው ሲሆን በእንዲህ አይነት ነውር ላይ ተሰማርቶ እንደማያውቅ መግለጹንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የፊልም ባለሙያው የጾታ ትንኮሳና ጥቃት ሰለባ ነን በሚል በይፋ ክሳቸውን ካቀረቡት ታዋቂ የሆሊውድ ሴት ተዋንያን መካከል፡- ጁሊያና ሙር፣ ሳሪ ካሚን፣ ስታር ሪናልዲ እና ቴሪ ኮን እንደሚገኙበትም ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡

እስካሁን 50 ሺህ አስሯል፤ 110 ሺህ ከስራ አባርሯል

    ባለፈው አመት ከተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ከ50 ሺህ በላይ ዜጎቹን ያሰረውና 110 ሺህ ያህሉንም ከስራ ገበታቸው ያባረረው የቱርክ መንግስት፤ከትናንት በስቲያ በተጨማሪ 121 የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀድሞ ሰራተኞች ላይ የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ሀሙስ እለት የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው 121 ቱርካውያን፣ ከዚህ ቀደም ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ጋር ንክኪ አላችሁ በሚል ከስራ ገበታቸው ያባረራቸው እንደሆኑ የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ፖሊስ በ30 ያህል ግዛቶች ግለሰቦቹን አድኖ ለመያዝ ዘመቻ መጀመሩን አመልክቷል፡፡ ግለሰቦቹ በሚስጥር መልዕክት መላላክ በሚያስችል የሞባይል አፕሊኬሽን አማካይነት ከመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሾችና ከግብረ አበሮቻቸው ጋር ይገናኙ ነበር መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የቱርክ መንግስት ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ ከሆነውና “የመፈንቅለ መንግስቱ ፊታውራሪ” ከሚላቸው ጉሌን ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የሚጠረጥራቸውን ዜጎቹን በጅምላ ማሰሩ በአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና መንግስታት ሲያስተቸው መቆየቱንም አስታውሷል፡፡

Page 3 of 363