Administrator

Administrator

  ከእንግሊዝ አምባሳደር ጋር በእስረኞችና በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል

    በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ወደ መደበኛ የፓርቲ ሥራቸው ለመመለስ መወሰናቸውን የገለጹ ሲሆን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ከሆኑት ሱዛን ሞርሄድ ጋር መወያየታቸውም ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ባወጣው መረጃ፤ አምባሳደሯ በወቅቱ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር መወያየታቸውን ጠቁሟል። ውይይቱን በተመለከተ ለአዲስ አድማስ ያብራሩት ዶ/ር መረራ፤ ስለ ማረሚያ ቤቶች የእስረኞች አያያዝ፣ ስለ ወቅቱ የሀገሪቱ ሁኔታና ወደፊት ሊሆን ስለሚገባው ጉዳይ ከአምባሳደሯ ጋር በስፋት መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ የሰው ህይወት መቅጠፍን የሚያስከትል ግጭት ሳይፈጠር፣ በሰላማዊ መንገድ በሚያሰማበት ሁኔታ ላይ በትኩረት ተወያይተናል ብለዋል - ዶ/ር መረራ።
በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ከሆኑት አምባሳደር ቫግ ነር ጋር መወያየታቸውን  መዘገባችን  ይታወሳል፡፡
ከእስር በተለቀቁ ወቅት በፖለቲካ ትግላቸው ይቀጥሉ እንደሆነ አለመወሰናቸውን የተናገሩት ዶ/ር መረራ፤ በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የሊቀ መንበርነት ሥራቸው ለመቀጠል መወሰናቸውን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ከአደአ በርጋ ህዝብ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት፣ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ወደ አካባቢው በተጓዙበት ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ የአድናቆት አቀባበል እንዳደረጉላቸው የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡   
በተመሳሳይ ዶ/ር መረራ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በአምቦ ከተማ፣ተቀራራቢ ቁጥር ያለው ህዝብ ደማቅ   አቀባበል እንዳደረገላቸው ይታወቃል፡፡

  53 ኢትዮጵያውያን ከሞዛምቢክ እስር ቤት ወጥተዋል

    የኬንያ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ግዛቴ ገብተዋል ያላቸውን 29 ኢትዮጵያውያን፣ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ጠዋት ያሰረ ሲሆን በሌላ በኩል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሞዛምቢክ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠዋል ተብለው የታሰሩ 53 ኢትዮጵያውያንን ማስፈታቱን  አስታውቋል፡፡
ፓስፖርትና አስፈላጊ የጉዞ ሰነዶች ሳይኖራቸው፣ ከሞያሌ በጭነት መኪና በመጓጓዝ ላይ ሳሉ ሩዋራካ በተሰኘች የኬንያ ግዛት ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት 29 ኢትዮጵያውያን፣ አላማቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ መሻገር እንደነበር  የኬንያው ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ  ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የተሻለ ስራ ፍለጋ ከሀገራቸው መሰደዳቸውን መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በእስረኞች ማቆያ እንዲገቡ ተደርጎም፣ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አመልክቷል፡፡
ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ የመኪናው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋለ ሲሆን የኬላ ጠባቂ ፖሊስ ላይም ምርመራ እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ፍ/ቤት ከቀረቡ፣ በህገ ወጥ መንገድ የሀገሪቱን ግዛት በማቋረጥ ወንጀል ተከሰው፣ እስከ 1 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድባቸው እንደሚችል ታውቋል፡፡  
በሌላ በኩል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በተመሳሳይ የሞዛምቢክን ድንበር በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠው ደቡብ አፍሪካ ሊገቡ ሲሉ በሞዛምቢክ ፖሊስ ተይዘው ታስረው የነበሩ 53 ኢትዮጵያውያንን፣ ከፍተኛ ድርድር በማድረግ ማስመለሱን አስታውቋል፡፡ ከወራት በፊትም በተመሳሳይ፣ በዛምቢያ እስር ቤት የነበሩ 150 ኢትዮጵያውያንን በማስፈታት፣ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ማድረጉን ሚኒስቴሩ መግለፁ ይታወሳል፡፡    

  እኔ ቀድሜ የተረጎምኩትን “The power of Now” የተሰኘ መጽሐፍ ተርጉመው፣ የ100 ሺህ ብር ኪሣራ አድርሠውብኛል ያሉት ተርጓሚ በፍ/ቤት የ194 ሺ ብር ካሣ እንዲከፈላቸው ተወሠነ፡፡
ከሳሽ ደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፍትሃ ብሄር ችሎት ሚያዚያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ባቀረቡት የክስ አቤቱታ፤ በኤክርሃቶ ቶል፣ “The power of Now” በሚል የተፃፈውን መፅሐፍ “የአሁንነት ሃይል” በሚል ወደ አማርኛ ተርጉመው ለአንባቢያን ማቅረባቸውን ይሁን አንጂ እሳቸው በማያውቁትና ፍቃዳቸው ሳይጠየቅ አቶ ብስራት እውነቱ የተባሉ ደራሲ “የአሁኑ ሃይልነት” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ቋንቋ በመመለስ ኪሣራና ጉዳት እንዳደረሰባቸው ጠቁመዋል፡፡
በዚህ የክስ አቤቱታ፤ አቶ መኮንን ፋንታሁን መፅሃፉን እንዲተረጉም በማድረግና በአሣታሚነት እንዲሁም ፋር ኢስት ትሬዲን ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ደግሞ በአታሚነትና በመሸጥ፣ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘታቸውና ጉዳት አድራሽ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ፣ የራሳቸውን መልስ ለፍ/ቤት ያቀረቡ ሲሆን አንደኛ ተከሣሽ የሆኑት አቶ ብስራት እውነቱ፤ የመፅሃፍ ባለመብትና ደራሲ ሄክሃርት ቶል እንጂ ከሣሽ አይደሉም ስለዚህ የፈጠራ ባለመብት አይደሉም፤ የሚል መልስ የሠጡ ሲሆን ሁለተኛ ተከሳሽ በበኩላቸው፤ ከሣሽ ራሳቸው የዋና ደራሲውን ፈቃድ ሣያገኙ ነው የተረጎሙት፤ በዚህም የመፅሃፍ ባለመብት ሆነው ክስ ማቅረብ አይችሉም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 3ኛ ተከሳሽ (ማተሚያ ቤቱ በበኩሉ፤ እኔ ስራዬን የመፅሐፉን ይዘት ማንበብ ሣይሆን ማተም ብቻ ነው የሚል ምላሽ ሠጥተዋል፡፡
ከሣሽ በበኩላቸው፤ በፍሬ ጉዳይ ላይ ባቀረቡት መከራከሪያ፤ የትርጉም ስራ እራሱን የቻለ ፈጠራ በመሆኑ በቅጅና ተዛማጅ አዋጅ ቁጥር 410/96 መሠረት ጥበቃ አለው፤ ሲሉ አንቀፅ ጠቅሠው ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ፍ/ቤቱ፤ ከሣሽ “መፅሃፉን እኔ ስለተረጎምኩት ሌላ ሠው ሊተረጉመው አይችልም” ብለው አንቀፅ በመጥቀስ ያቀረቡትን መከራከሪያ ተቀባይነት እንደሌለው፤ ነገር ግን ተከሣሾችም ከሳሽ መፅሀፉን በመጀመሪያ መተርጎማቸውን ማመናቸውንና ይዘቱም ተመሣሣይነት እንዳለው ከግምት በማስገባት፣ በጉዳዩ ላይ ውሣኔ ሠጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱ ባሣለፈው ውሣኔ፣ 1ኛ እና 2ኛ ተከሣሽ ጥፋተኛ በመሆናቸው፣ በከሳሽ ደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ ላይ ላደረሡት ቁሣዊ ጉዳት 94 ሺህ አንድ መቶ አርባ ብር (94,140) እንዲሁም በከሳሽ ላይ ለደረሰው የሞራል ጉዳት ብር አንድ መቶ ሺህ (1000,000) በድምሩ አንድ መቶ ዘጠና አራት ሺህ አንድ መቶ አርባ ብር (194,140) ብር እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡ 3ኛ ተከሳሽ (ማተሚያ ቤቱ) በከሳሽ ላይ ላደረሠው ቁሣዊም ሆኖ ሞራላዊ ጉዳት ሃላፊነት የለባቸውም ብሏል - ፍ/ቤቱ፡፡

   *ዋና ዳይሬክተሯን ተክተው ይሰራሉ ተብሏል

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ፣ በአለማቀፍ ተቋማት የረጀም አመታት የከፍተኛ አመራርነት ልምድ ያላቸውን ኢትዮጵያዊውን አቶ ደረጀ ወርዶፋን የተመድ የስነ-ህዝብ ፈንድ የፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አድርገው መሾማቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው፤በቅርቡ የስነ-ህዝብ ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙትን የፓናማ ተወላጇን ናታንያ ካኔም ተክተው እንደሚሰሩም ነው የተገለጸው፡፡
በተለያዩ አለማቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የስራ ሃላፊነቶች ላይ ከ28 አመታት በላይ የዘለቀ ስኬታማ አመራር በመስጠት የካበተ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊው አቶ ደረጀ፣ በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን ናታሊያ ካኔምን እንደሚተኩ ተመድ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአለማቀፉ ኤስኦኤስ የህጻናት መንደር፣ የምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ አለማቀፍ ክልላዊ ዳይሬክተር የሆኑትና 4 ሺህ 500 ያህል ሰራተኞችን በስራቸው በማስተዳደር ላይ የሚገኙት አቶ ደረጀ፣ ብቃት ባለው አመራር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ፈተናዎችን በመቋቋም፣ በአብዛኛው አፍሪካን ተደራሽ ያደረጉ በርካታ ስራዎችን በስኬታማነት እንዳከናወኑ መግለጫው አስረድቷል፡፡
አቶ ደረጀ ከዚህ ቀደምም አሜሪካን ፍሬንድስ ሰርቪስ ኮሚቴ በተባለው ተቋም በክልላዊ ዳይሬክተርነት፣ በኡጋንዳ የኦክስፋም ሃላፊ፣ በሴቭ ዘ ችልድረን በምክትል የፕሮግራም ዳይሬክተርነትና በሌሎች ታላላቅ ተቋማት በከፍተኛ የስራ ሃላፊነቶች ላይ በማገልገል ብቃታቸውን ማስመስከራቸውን አስታውሷል፡፡
ኢትዮጵያዊው አቶ ደረጀ ከኦክስፎርድ ብሩከስ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በማስተርስ፣ በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በሶሻል ፖሊሲ ኢን ዲቨሎፒንግ ካንትሪስ በማስተርስ መመረቃቸውንና፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በቢዝነስ ማኔጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን መግለጫው አክሎ ገልጧል፡፡  

  “አንቺም አባዎራ እኔም አባዎራ
                   ግራ ገባው ቤቱ በማ እንደሚመራ…”

   በኬንያ ከወራት በፊት በተካሄደው የድጋሚ ምርጫ ያሸነፉት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በይፋ ቃለ መሃላ ፈጽመው አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት መምራት ከጀመሩ ከወራት በኋላ፣ እነሆ ያልተጠበቀ ነገር ባለፈው ማክሰኞ በመዲናዋ ናይሮቢ ተከናወነ፡፡
ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ካስደገሙ በኋላ፣ ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉት የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ፤ ባለፈው ማክሰኞ ናይሮቢ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውን ሰብስበው፣ “የታላቋ ኬንያ ሪፐብሊክ  ፕሬዚዳንት ነኝ” ሲሉ በማወጅ ቃለ መሃላ ፈጸሙ፡፡
የያዘውን ስልጣን በድንገት መነጠቁ ያስደነገጠውና ጉዳዩ ወደ ከፋ ግጭት እንዳያመራ ያሰጋው የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት፤ የጎንዮሹ ቃለ መሃላ አገርን የሚያፈርስ፣ክፉ ድርጊት በመሆኑ እንዳይካሄድ ብሎ ቢያስጠነቅቅም፣ ራይላ ኦዲንጋ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው፣ መጽሃፍ ቅዱሳቸውን ከፍ አድርገው ይዘው፣ መሪነታቸውን አወጁ። ሁለተኛ ፓርላማ ማቋቋማቸውንም በድፍረት ተናገሩ፡፡
ህጋዊው የኡሁሩ መንግስት. የኦዲንጋን የጎንዮሽ በዓለ ሲመት በቀጥታ ስርጭት ለህዝቡ ለማድረስ እየተዘጋጁ የነበሩትን ኬቲኤን፣ ኤንቲቪ እና ሲቲዝን ቲቪ የተባሉ ሶስት ታላላቅ የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ስርጭት አቋርጧል፡፡
የኡሁሩ መንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹን መዝጋቱን ተከትሎ፣ ባለፈው ሃሙስ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ተሰይሞ ጉዳዩን ካጤነው በኋላ፣ ለ14 ቀናት ያህል በጉዳዩ ዙሪያ ቀጣይ ምርምራ አድርጎ እስከሚጨርስና የመጨረሻ ብይን እስኪሰጥ ድረስ፣ የመንግስት ውሳኔ ተሽሮ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ስርጭታቸውን እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
የኡሁሩ መንግስት ግን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብሮ፣ ጣቢያዎቹን ለመክፈት ፍላጎት አለማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ የአዲሱ ፕሬዚዳንት ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም የአገሪቱ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚጥስ ነው፣ በማለት የመንግስትን እርምጃ ማውገዛቸውን አመልክቷል፡፡
የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሁነኛ ምላሽ እስካልሰጠ ድረስ፣ ኬንያ በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ከፋ ብጥብጥና ቀውስ ልታመራ እንደምትችል የሚናገሩት የመብት ተሟጋቾች፤ ሁለቱም ሃይሎች አገሪቱን ወደ ጥፋት ከማምራት እንዲቆጠቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ስራ ፈትተው ከሚቀለቡ 6 ሺህ ወታደሮች፣ የተወሰኑት በግድ እረፍት ይወጣሉ

   ፕሬዚዳንቱ ወጪን ለመቀነስ ሲሉ ለሰሞኑ የህብረቱ ስብሰባ፣ የግል አውሮፕላናቸውን ትተው፣ በመደበኛ አውሮፕላን ነበር የመጡት
ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት የገጠመው የናሚቢያ መንግስት፤ወጪን ለመቆጠብ በሚል ሚኒስትሮችን፣ ምክትል ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት ሃላፊዎችን ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ባለስልጣናት ወደ ውጭ አገራት እንዳይሄዱ መከልከሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ማንኛውም የአገሪቱ ባለስልጣን ለስብሰባ፣ ለስልጠናና ለሌሎች ጉዳዮች ከአገሪቱ ውጭ የሚያስወጣው ጉዞ ካለ በአፋጣኝ እንዲሰርዝ መንግስት መመሪያ ማስተላለፉን የጠቆመው ዘገባው፤ የጉዞ ክልከላው ቢያንስ እስከ ወሩ መጨረሻ ተግባራዊ ሆኖ እንደሚቆይና ይራዘማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡ በውጭ አገራት ጉዞ ሳቢያ ለባለስልጣናት ከፍተኛ ወጪ ማውጣት እንዲቆም ያሳሰቡት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሀጌ ጌንቦ፤ በሰሞኑ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅትም የግል አውሮፕላናቸውን ትተው፣ የህዝብ ማመላለሻ መደበኛ አውሮፕላን መጠቀማቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የናሚቢያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በማዕድን ኤክስፖርት ገቢ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የአለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ ኢኮኖሚዋን ክፉኛ እንደጎዳውና የፋይናንስ እጥረት የገጠመው የአገሪቱ መንግስት መሰል ወጪዎችን ለመቀነስ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስረድቷል።
ስራ ፈትተው በጦር ካፕሞች ለሚኖሩ የጦር ሃይሉ አባላት ደመወዝ በአግባቡ መክፈልም ሆነ የእለት ምግብና ውሃን ጨምሮ የተለያየ ወጫቸውን መሸፈን ያቃተው የአገሪቱ መንግስት፣ ከሰሞኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን የአመት እረፍት ለማስወጣትና በእረፍት ላይ ለሚገኙትም ተመልሰው እንዳይመጡ መመሪያ ለመስጠት መወሰኑን ዘ ናሚቢያን የተባለው የአገሪቱ የግል ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መከላከያ ሚ/ር ለ2018 የበጀት አመት 5.6 ቢሊዮን የአገሪቱ ዶላር እንደተመደበለት ያስታወሰው ዘገባው፣ አገሪቱ 15 ሺህ ያህል ወታደሮች እንዳሏትና 6 ሺህ ያህሉ ስራ ፈትተው በጦር ካምፖች ውስጥ እንደሚኖሩ መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

  በየቀኑ 50 ሚሊዮን ሰዓታት ፌስቡክ ላይ ይጠፋሉ

    ታዋቂው የማህበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017፣ የመጨረሻው ሩብ አመት፣ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የ4.3 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱንና ይህም ካለፈው የሩብ አመት ትርፍ፣ በ61 በመቶ ብልጫ እንዳለው ኩባንያው ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኩባንያውን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግን ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፤ ፌስቡክ በተጠቀሰው የሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 12.7 ቢሊዮን ዶላር ያገኘ ሲሆን፣ የወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ቁጥርም 2.13 ቢሊዮን ያህል ደርሷል። ፌስቡክን በሞባይል የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር ማደጉ በሩብ ዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ እንዲያገኝ አስችሎታል ያለው ዘገባው፤ በየዕለቱ ፌስቡክን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥርም 1.4 ቢሊዮን መድረሱን አስረድቷል፡፡
ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየተሻማና ስራ እያስፈታ ነው በሚል የሚሰነዘርበትን ትችት በማጤን፣ በሩብ አመቱ ተጠቃሚዎች በየቀኑ ፌስቡክ ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ መውሰዱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአንድ ቀን ውስጥ ተጠቃሚዎች በፌስቡክ ላይ የሚያጠፉትን አጠቃላይ ድምር ጊዜ ወደ 50 ሚሊዮን ሰዓታት ዝቅ ማድረጉን አስታውሷል፡፡
በአዲሱ የፈረንጆች አመት የዓለማችን የዲጂታል ማስታወቂያ ገበያ ውስጥ 266 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ይንቀሳቀሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ በዚህ ገበያ ውስጥ ፌስቡክ 18.4 በመቶ ያህል ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚገመት አመልክቷል፡፡

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የፓስፖርት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ በ140 የተለያዩ ክፍት የስራ ቦታዎች ላይ ሴቶችን ቀጥሮ ለማሰራት ባወጣው ማስታወቂያ፤ ከ107,000 በላይ አመልካቾች መቅረባቸውን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በድንበር አካባቢ መስሪያ ቤቶች መስራት ለሚፈልጉ ስራ ፈላጊዎች የወጣው የክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ፤ በድረ ገጽ አማካይነት በተሰራጨ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ107,000 በላይ አመልካቾች መቅረባቸው ያስደነገጠውና መስተንግዶው ከአቅሙ በላይ የሆነበት ዳይሬክቶሬቱ፤ በአፋጣኝ ማስታወቂያውን ማንሳቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያው ቢያንስ ሁለተኛ ደረጃን ያጠናቀቁና ከ25 እስከ 35 አመት በሚገኘው የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አመልካቾችን ብቻ መጋበዙን የጠቆመው ዘገባው፤ በሳኡዲ አረቢያ የሴቶች ስራ አጥነት 33 በመቶ ላይ እንደሚገኝም አስታውሷል፡፡

   (ጾታዊ እኩልነት ለመፍጠር)

    የካናዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከ37 አመታት በላይ በድምቀት ሲዘመር በዘለቀውና “ኦ… ካናዳ” የሚል ርዕስ ባለው የአገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር ውስጥ የሚገኙትን ጾታዊ እኩልነትን ያላማከሉ ቃላት ለመቀየር የቀረበለትን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከሰሞኑ አጽድቆታል፡፡
በካናዳውያን መካከል ጾታን መሰረት ያደረገ ልዩነት የሚፈጥርና ሁሉንም ዜጎች ያማከለ መሆን ሲገባው ለወንዶች ያደላ ነው በሚል ከ8 አመት በፊት ጀምሮ ቅሬታ ሲቀርብበትና ሲያነጋግር ቆይቷል ይላል ቢቢሲ - በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተዘጋጀው የአገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር ግጥም ውስጥ የሚገኘውን አንድ ነጠላ ሃረግ፡፡
“በሁሉም ወንድ ልጆችሽ ፈቃድ…” የሚለው ይህ የብሄራዊ መዝሙሩ ግጥም አካል የሆነ ሃረግ፣ “በእናት ካናዳ ጉዳይ የሚያገባቸው ወንድ ልጆቿ ብቻ ናቸው” የሚል የተዛባና ጾታዊ እኩልነትን ያላማከለ መልዕክት ያዘለ በመሆኑ፣ ቃላቱ ተቀይረው ከጾታ ክፍፍል በጸዳ ሌላ ስንኝ ይተካ በሚል የቀረበውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ፣ በጉዳዩ ላይ ድምጽ የሰጠው ምክር ቤቱ፣ የስንኙ ሁለት ቃላት እንዲቀየሩና “በሁላችንም ፈቃድ” የሚል ትርጉም እንዲሰጥ ወስኗል፡፡
“ኦ ካናዳ” የሚለው የአገሪቱ ብሄራዊ መዝሙር በይፋ ስራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1980 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶ በነበሩት ዓመታትም፣ “ወንድ ልጆችሽ” የሚለውን አገላለጽ የያዘው ይሄው አነጋጋሪ ሃረግ እንዲቀየር የሚጠይቁ የውሳኔ ሃሳቦች ለ12 ጊዜያት ያህል ለምክር ቤቱ ቀርበው እንደነበርና ሁሉም ሳይጸድቁ መቅረታቸውን አስታውሷል፡፡

    የመጀመሪያው የአክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች ሆነን ሳለ፣ ይህ ስልጣኔ መስፋት ሲገባው እንዴት ፈረሰ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት “የጠፋው አዳም” የኪነ ጥበብ ምሽት፣ የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 እስከ ምሽት 1፡45 በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሚሳተፉት ምሁራን መካከል የዘርዓያዕቆብ ዘጠነኛ የልጅ ልጅ የሆኑት ሊቀ ጠበብትና ሳይንቲስት ገ/ማሪያም ማሞ፤ ስልጣኔያችን ለምን ፈረሰ፣ እንዴት ፈረሰ፣ ማንስ አፈረሰው? በሚለውና በምርምር በደረሱባቸው ሰባት ምልክቶች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ እንደሚሰጡ የሁነቱ አዘጋጅ አቶ ቤዛ ሁነኝ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ ሊቀ ጠበብቱና ሳይንቲስቱ
ገ/ማሪያም ማሞ በበኩላቸው፤በአክሱም ስልጣኔ ላይ ባደረጓቸው ምርምሮችና ግኝቶች እንዲሁም ስልጣኔው እንዲቀጥል ምን መደረግ አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ በዚህ ውይይት ለመታደም መግቢያው 70 ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡ 

Page 4 of 378