Administrator

Administrator


    እውን የመሆኑ ጉዳይ ሲያነጋግር የሰነበተውንና በመጪው ማክሰኞ ሊካሄድ ቀን የተቆረጠለትን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ጁን ኡን ታሪካዊ ውይይት የምታስተናግደው ሲንጋፖር፤ ውይይቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉት ቀናት ለደህንነት ስትል በአየር ክልሏ በሚካሄዱ የበረራ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ እንደምታደርግ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የአቪየሽን መስሪያ ቤት ባለፈው ረቡዕ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በአካባቢው አገራት የጸጥታ ስጋት የፈጠረ ሲሆን ለደህንነት ሲባል በሲንጋፖር የአየር ክልል ለሶስት ቀናት ያህል የበረራ እንቅስቃሴ ገደብ መደረጉ ከእስያ ዋነኛ የአየር በረራ መስመሮች አንዱ በሆነው በዚህ አካባቢ የበረራዎች መስተጓጎል ይፈጥራል መባሉን አመልክቷል፡፡
በእነዚህ ቀናት ወደ ሲንጋፖሩ የቻንጊ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የሚያቀኑ አውሮፕላኖች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው የጠቆመው ዘገባው፤ የተወሰኑ የማኮብኮቢያ መስመሮችን ብቻ እንዲጠቀሙ እንደተነገራቸውና  ለጸጥታና ደህንነት ስትል በሁለቱ መሪዎች ቆይታ ህዝቡ ድርሽ የማይልባቸው በርካታ ቦታዎች መለየታቸውንም አመልክቷል፡፡


     ለእኩልነት በቁርጠኝነት የሚሰራ መንግስት እውን እናደርጋለን የሚል አቋም የያዙት አዲሱ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፤ 64 በመቶ ሴቶች ያሉበት ካቢኔ ማዋቀራቸውንና በቁልፍ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ሴቶችን መመደባቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረጉት የካቢኔያቸው አባላት ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 17 አባላት መካከል አስራ አንዱ ሴቶች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አዲሱን ካቢኔ ባለፉት 45 አመታት የስፔን ታሪክ፣ የሴቶች አብላጫ የታየበት ያደርገዋል ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ባለፈው ቅዳሜ ቃለመሃላ ፈጽመው ስልጣን መያዛቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ታዋቂ የአገሪቱ ሴቶችን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ በኢኮኖሚ ሚኒስትርነት፣ በፍትህ ሚኒስትርነት፣ በጤና ሚኒስትርነትና በሌሎች ወሳኝ ሃላፊነቶች ላይ መሾማቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ፡
ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራጆይ ከሾሟቸው ሚኒስትሮች ውስጥ የሴቶቹ ድርሻ 36 በመቶ ብቻ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤አዲሱ መንግስት ለሴቶች ወሳኝ የስልጣን ቦታዎችን መስጠቱ በብዙዎች ዘንድ ተደናቂነት እንዳተረፈለትም አክሎ ገልጧል፡፡

 በጦር ሜዳ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ10 ዓመታት በ246 በመቶ ጨምሯል

    የዓለማችን ሰላም ባለፉት አስር ዓመታት እያሽቆለቆለ መምጣቱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 ብቻ የአለማችን አገራት በግጭቶች ሳቢያ በድምሩ 14.8 ትሪሊዮን ዶላር ማጣታቸውን አይኢፒ የተባለው የጥናት ተቋም አመለከተ፡፡
ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው የጥናት ተቋም፣ ባለፈው ረቡዕ ለ12ኛ ጊዜ ይፋ ያደረገው አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ አመላካች ሪፖርት እንደሚለው፤ በአለማችን በጦር ሜዳዎች ላይ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አስር አመታት በ246 በመቶ ያደገ ሲሆን ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአንጻሩ በ203 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 በአለማችን 92 አገራት፣ የሰላም ሁኔታ ላይ ማሽቆልቆል የታየ ሲሆን ሶርያ፣ አፍጋኒስታንና ደቡብ ሱዳን በከፍተኛ ሁኔታ ሰላም የራቃቸው አገራት ናቸው ተብሏል፡፡
በአመቱ የ71 የአለማችን አገራት ሰላም መሻሻል ታይቶበታል ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ በ2017 የፈረንጆች አመት 104 የአለማችን አገራት፣ የመከላከያ ወጪያቸውን ከኢኮኖሚ ወጪዎች ያነሰ ማድረጋቸውንና 115 አገራት ደግሞ ወታደራዊ የሰው ሃይላቸውን መቀነሳቸው  በመልካም ተሞክሮነት ጠቅሶታል፡፡
በአለማችን በአመቱ ከፍተኛውን ሰላም ያስተናገዱት የአለማችን አገራት፤ አይስላንድ፣ ኦስትሪያና ፖርቹጋል መሆናቸውን የጠቆመው ተቋሙ፤ በአፍሪካ ሰላማቸውን በጥሩ ሁኔታ ያሻሻሉ አገራት፤ ጋምቢያ፣ ላይቤሪያና ብሩንዲ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

    ከዕታት አንድ ቀን፤ አንድ አንቱ የተባሉ፣ የደሩና የኮሩ የጥንት አርበኛ ፊታውራሪ፣ በአንድ የገጠር ከተማ ይኖሩ ነበር፡፡ እኒህ ሰው ጠላትን ባባረሩ ማግሥት የጀግንነት ተግባራቸው አልጠቅም ብሏቸው፤ ወደ ጫካ ወጣ ይሉና አደን ላይ ይሰማራሉ፡፡ ከርከሮ ካገኙ ከርከሮ፣ አውራሪስ ካገኙ አውራሪስ…ብቻ ያገኙትን የዱር እንስሳ አድነው ገድለው፣ ቢያጡ ቢያጡ ጅግራም ቢሆን ገድለው ወደ ቤት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ይኼን ሁሉ ግዳይ ጥለው ቤተሰብ እንዲሰበሰብ ይደረግና በጋራ ገበታ ተቀርቦ ይበላል፡፡
ታዲያ እግረ መንገዳቸውን የእያንዳንዱን የሚታደን የዱር እንስሳ ባህሪ ያብራራሉ፡፡
“ነብር ስታድኑ፤ ይሄን ይሄን ጥንቃቄ አድርጉ… ከርከሮ ከሆነ አቁስሎ መተው አደገኛ ስለሆነ የገባበት ገብታችሁ መጨረስ አለባችሁ- ግሥላ ከከርከሮ ይብሳል… አልመህ መተኸውም አደገኛ ነው…” እያሉ በዝርዝር የታዳኞቹን አውሬዎች ባህሪና ጠባይ በደንብ ይገልፃሉ፡፡
ቤተሰቡም ጥያቄ ካለው እየተብራራለት ቁልጭ ያለ መግለጫ ያገኛል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ገበታም የማይቀርብ፣ ማብራሪያም የማያዳምጥ፣ ሞገደኛና አባያ ልጅ አለ፡፡
ፊታውራሪ፤
“ያ፤ ካብ- አይገባ-ድንጋይ፣ ልጄ ዛሬ የት ሄዷል?” ይሉና ይጠይቃሉ፡፡
ቤተሠቡም፤
“በተደጋጋሚ ወደ ማዕዱ ቅረብ ብንለው አሻፈረኝ አለንኮ! በልመናም ሞከርነው፣ በጄ አላለንም። አሁንማ ጭራሽ ሁላችንንም አኩርፎ ቁጭ አለ!”
ፊት አውራሪም፤
“ተውት…ልጅ ሲያኮርፍ ምሳው ራቱ ይሆናል!” አሉ፡፡
ዕውነትም እንዳሉትም አልቀረ፣ ማታ ራበኝ አለና ቀን የተቀመጠውን በላ!
* * *
ህብረተሰብን በለውጥ-ወዳድ እና በለውጥ-ጠል ከፍሎ ማየት የሚቻል መስሎ አይታይም ነበር። የዚህ መሠረታዊ ምክኑ በእርምት-እንቅስቃሴ (Rectification)፣ እደሳ (Reform) እና ሥር ነቀል ለውጥ (Radical Change) መካከል፤ በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃም ሆነ በአተገባበር መልኩ፣ የተወሰነ መቀራረብና መለያየት በመኖሩ ነው፡፡ በሀገራችን ቁርጥ ያለ፣ እንደ አብዮት ያለ ለውጥ እስካሁን የተለመደ ቅላፄና ዜማ ያለው ሆኖ በማየታችን፤ ከፅንፍ ፅንፍ ጥግ የያዘ መልክ (Polarized feature) በመሆኑ የምናወጣቸው ቅፅሎች፤ የምንሰነዝራቸው አቃቂሮች፣ የምንቀልማቸው ውዳሴዎች ጥርት ያሉ ቃላትን የተሸከሙ ነበሩ፡፡ ግልፅ ማብራሪያ ይሰጥበት ነበር፡፡ አድሃሪ፣ ተራማጅ፣ አስመሳይ፣ አድር ባይ፣ መሀል-ሠፋሪ፣ ወግ-አጥባቂ፣ ውዥንብር ፈጣሪ፣ ወዘተ በሚል ቅጥ-ባላቸው ቃላት እንገለገል ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ቀዳማይ እና ድሃራይ የተሰኘው የኮርቻ ፊትና ኋላ በአብዮት ውስጥ፤ ወደ ፊት የመቅደምና ወደ ኋላ የመቅረት ባህሪ መገለጫ ሆነውን ነበር፡፡ ዛሬ የተያያዝነው ለውጥ ባህሪ ግን ፅንፈኝነት የሚያስተናግድ አይመስልም! እንደ ትራንስፎሜሽን ያለው ፅንሰ-ሀሳብ የዋዛ ክስተት አይደለም፡፡ ውጣ ውረዱ ብዙ ነው፡፡ ሂደቱ ረዥምና ጠመዝማዛ ነው! ጀሌነትና መንገኝነት ፋሺን (ዘዬ) የነበረበት ዘመን፤ ዛሬ ቀለሙ የፈዘዘ ነው! አፌ- ጮሌነት፣ ጤፍ የሚቆላ ምላስ ያለው አራዳ ጊዜ፣ ሁሉን ባፌ አመራዋለሁ ተብሎ የሚኩራሩበት ወቅት እያከተመ ይመስላል፡፡
ዛሬ በዐይናችን በብረቱ የምንመሰክረው፣ የምናውቀው ነባር ሥርዓት ቀስ በቀስ እየተናደ፣ መድረሻው በቁርጥ ወዳልታወቀ ግብ እየተጓዝን እንደሆነ ነው! እዚህ ላይ አንዳች ጥብቅ ጉዳይ መንፈሳችንን ሰቅዞ ይይዘናል፡፡ እስካሁን በፕሮግራም፣ በፖለቲካ ተጋግሮ፤ እንደ ንብርብር አለት ሁሉ በቀላጤ፣ በመመሪያ፣ በፈጣን ማስታወሻ ተደርቶ፣ ሥርዓቱን ለመመርመር እንኳ “በበላይ አካል”፣ “በሚመለከተው አካል፣” “በመዋቅሩ አቅጣጫ መሠረት”፣ “በግምገማ እንደ ተቀመጠው” ወዘተ በሚሉ ጠንካራ የቱሻ ገመዶች የተተበተበ የቢሮክራሲ ቀይ-ጥብጣብ (bureaucratic red-tape) የበዛበት ቅጥ-አምባሩ የጠፋ “የእኔ ብቻ አውቅልሃለሁ” ሥርዓት፤ አንኳር በአንኳር እየተናደ መሆኑን እያስተዋልን ነው! ይህ አንዱ የወቅቱ ገፅታ ሲሆን፣ ሌላው ገፅታው የሚሆነው የመልሶ መገንባቱ ሂደት ነው! ድሮ በነበረው ሥርዓተ-ፈርሳታ ወቅት፤ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም፤ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው” የሚል መፈክር እንደነበር ልብ እንላለን፡፡
በዓለም ላይ የማፍረስ-መገንባትን ሂደት ያልቀመሰ ሥልጣኔ የለም! ከታዋቂው የአሜሪካን የርስ በርስ ውጊያ ጀምሮ፣ “ከእንግዲህ አንራብም!” ብለው እስከተነሱት አውሮፓውያን ድረስ፤ ፈርሰው ራሳቸውን የገነቡበትን ታሪክ አንብበናል፡፡ በተራችን ራሳችንን በመንፈም በአካልም የምንገነባበት ወቅት መከሰቱ የተስፋ ምሥራች ነው! በኢትዮጵያ አያሌ የለውጥ ነፋስ ያመጣቸውን አጋጣሚዎች በንዝህላልነት፣ በእልህ፣ እኔ የሌለሁበት አይሳካም የማለት ስሜት እና የነገን ራዕይ በብስለት ካለማጤን ዕድሉን አጥተናል፡፡ ከእንግዲህ ዐይናችንን እንክፈት አጋጣሚዎችን መዝለል የፀፀት እናት ነው!
(missed opportunities are mother of regretion) ይባላል፡፡ በተደጋጋሚ ፀፀት ውስጥ መውደቅ የለብንም! የመጣውን የለውጥ መንፈስ ላለመጋራት ማፈንገጥ፣ እምቢተኝነትን መቀፍቀፍና ማኩረፍ ነገ ያስከፍለናል፡፡ “ልጅ ሲያኮርፍ ምሣው ራት ይሆነዋል” የሚለው የአበው ብሂል፣ ይኸንኑ የሚመክረን ነው! ልብ ያለው ልብ ይበል!!

 · ዶ/ር ዐቢይ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አደንቃለሁ
  · የማረምያ ቤት ሰዎች፣ እየተደረገ ያለው ለውጥ የገባቸው አይመስለኝም

     ፍቅረማርያም አስማማው ይባላል፡፡ የ31 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከገባ አምስት አመት እንዳስቆጠረ ይናገራል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከ“ሠማያዊ” ፓርቲ የጀመረው የፖለቲካ ተሣትፎው፤ እስከ “አርበኞች ግንቦት 7” ፍለጋ አድርሶታል፡፡ የማታ ማታም ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ክስ ሊመሰረትበት ችሏል፡፡ ወጣቱ፤ ከፓርቲ የፖለቲካ ተሣትፎው እስከ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ክስና እስር ድረስ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አውግቶታል። በምርመራ ወቅት የገጠመውን ሥቃይም ይገልጻል። እንዴት ወደ
ፖለቲካ ህይወት እንደገባ በመግለፅ ፍቅረማርያም እንዲህ ታሪኩን ይጀምራል፡-


   ከ2005 ዓ.ም በፊት ምንም አይነት የፖለቲካ ተሣትፎ አልነበረኝም፡፡ በኋላ ግን የማያቸውና የምሰማቸው ነገሮች፣ ውስጤን ወደ ፖለቲካው ይገፋፉኝ ጀመር፡፡ ዳር ላይ ቆሞ፣ “ፖለቲከኞች ብቁ አይደሉም፤ አይረቡም” እያሉ መተቸት ተገቢ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ እምነት በመነሣትም፣ እስቲ ፓርቲዎች ውስጥ በመሣተፍ፣ ሁኔታውን ልየው ብዬ በመወሰን፣ ወደ ፓርቲ ፖለቲካ ገባሁ፡፡ በወቅቱ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ተብለው የሚታመኑት ፓርቲዎች፡- አንድነት፣ ሠማያዊና መኢአድ ነበሩ፡፡ እኔም ሁሉንም ካጠናሁ በኋላ ሠማያዊ የተሻለ ሆኖ ስላገኘሁት ፓርቲውን ተቀላቀልኩኝ፡፡ ወጣቶችም ስለሆኑ ተግባብቶ ለመስራት ጠቃሚ ነው በሚል ነበር የመረጥኩት፡፡
በሽብር የተፈረጀውን “ግንቦት 7” ለመቀላቀል ጉዞ ጀምረህ ነበር---?
ሠማያዊ ፓርቲ ውስጥ ሆኜ ብዙ ነገሮች እመለከት ነበር፡፡ እነዚህ በግልፅ የሚታዩ፣ ለሠላማዊ ትግል አመቺ ያልሆኑ ሁኔታዎችን እንዴት ነው መቋቋም የሚቻለው፣ የሚለው በውስጤ ይፈጠርብኝ ነበር። በሠላማዊ መንገድ ስንታገል እስር፣ ድብደባና ወከባ ይፈጸማል፡፡ ስርአቱ ይሄን የሚፈፅመው በምርጫ ሣይሆን በደምና በአጥንት የተገነባ መሆኑን ተረዳው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በምርጫ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ እውነተኛ ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ስረዳ፣ አሁን በስርአቱ ቁንጮ ላይ የተቀመጡ ሰዎች፣ ወጣቶች ሆነው ያደረጉትን ነገር ማድረግ እችላለሁ በሚል፣ “ግንቦት 7”ን ኤርትራ ሄጄ ለመቀላቀል ወሠንኩ፡፡ እነሡ በግንቦት 20 ውስጥ ተደብቀው፣ ሌላ ሰው ግን እነሱ ያደረጉትን ማድረግ እንደማይችል ነበር የሚያስቡት፤ ስለዚህ በዚህች ሃገር ላይ የምፈልገውን ለውጥ ለማግኘት፣ እኔ በመረጥኩት መንገድ መታገል አለብኝ ብዬ ነው ያመንኩት፡፡ እኔ እንኳን ነፃነቱን ባላገኝ፣ልጆቼ የልጅ ልጆቼ፣ ይህ ጭቆና እንዳይጫንባቸው ማድረግ ይገባኛል በሚል ቁርጠኝነት ነው፣ ከዚህ ውሣኔ ላይ የደረስኩት፡፡ የትጥቅ ትግሉ የመጨረሻው አማራጭ በመሆኑ፣ ወስኜ ወደዚያው ጉዞ ጀመርኩ፡፡  
ለእኔ “ግንቦት 7” አሸባሪ የተባለበት ሂደት አሣማኝ አልነበረም፡፡ ድርጅቱ ለኔ የነፃነት ታጋይ ነው፡፡ በዚህ መነሻ ነው የመጨረሻው የመታገያ አማራጭ ያደረግሁት፡፡ በውስጡ የተሠባሠቡት ሰዎች ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ የሚሉ እንጂ አንድም ቀን በኢትዮጵያ ላይ ሞትን ደግሠው አያውቁም፡፡
እንዴት ነበር ወደ ኤርትራ ጉዞ የጀመራችሁት?
ከዚህ ከአዲስ አበባ ነው የተነሣነው፣ በየብስ ትራንስፖርት ባህርዳር …. ጎንደር እያልን እስከተያዝንበት ማይካድራ ድረስ 6 ቀን ነበር የፈጀብን። ጉዟችን በህዝብ ትራንስፖርት ነበር፡፡ ትልቅ ጥንቃቄ ይጠይቅ ስለነበር ነው፣6 ቀን የፈጀብን፡፡ በኋላ ትግራይ ውስጥ የምትገኘው ማይካድራ ስንደርስ፣ በደህንነቶች ተያዝን።
ኤርትራ ለመድረስ ምን ያህል ይቀራችሁ ነበር?
ብዙ አይደለም፡፡ እርግጥ ከማይካድራ እስከ ኤርትራ ልንሄድ የነበረው በእግራችን ነው፡፡ እኛን ለማሻገር የተስማማው ልጅ፣ ቢበዛ የአንድ ሠዓት የእግር መንገድ ርቀት ቢቀረን ነው ብሎን ነበር። እንግዲህ ደህንነቶች የያዙንም የእግር ጉዞውን ለመጀመር በተሰናዳንበት አጋጣሚ ነው፡፡ በወቅቱ ልንያዝ እንደምንችል በመገመታችን፣ ተይዘን ከተከሰስን ሌሎች እንደሚሉት፣ “ወደ ሱዳን ወይም ወደ ሌላ ሃገር ስደት ልንወጣ ነው አንልም፤ በግልፅ “ግንቦት 7”ን ልንቀላቀል ነው እንላለን” ብለን ተነጋግረን ነበር፡፡ ከኔ ጋር በወቅቱ ኢየሩሣሌም ተስፋው፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድ እና አሸጋጋሪያችን ልጅ ነበረ፡፡ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ተስማምተን ስለነበር፣ ደህንነቶቹ ይዘውን፤ “የት ልትሄዱ ነው?” ሲሉን፤ ኤርትራ አልናቸው፤ “ምን ልታደርጉ?” አሉን፤ “ግንቦት 7ን ልንቀላቀል” አልናቸው፡፡
ከዚያስ ---?
ከተያዝን በኋላ አንድ ሁለት ቀን ሁመራ አካባቢ የሚገኝ የደህንነት ቢሮ አቆዩን፤ ጎንደር ሁለት ቀን አደርን፡፡ ከዚያ አዲስ አበባ አምጥተው፣ ማዕከላዊ አስገቡን፡፡ በወቅቱ እኛ አምነንላቸው ስለነበር፣ ድብደባና ግብግብ አልገጠመንም፡፡ በምርመራ ወቅትም፣ በግልጽ “ግንቦት 7ን ልንቀላቀል ነው” ስላልናቸው፣ ብዙ ጫና አላደረጉብንም፡፡
ፍ/ቤትስ የነበረው ሂደት ምን ይመስላል?
ለፍ/ቤቱም ድርጊቱን መፈፀማችንን አምነናል። “ያው ወጣቶች ነን፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሠዎች፤ ግፍ ይፈፅማል ያሉትን ስርአት ለማስወገድ የወሠዱትን አማራጭ ነው እኛም የወሠድነው፡፡ እኛም ለሃገራችን፣ ለወገናችንና ለራሣችን የምንፈልገውን ዲሞክራሲያዊ ስርአትና ፍትህ ለማምጣት ስንዘምት ነው የተያዝነው” የሚል ቃል ነው ለፍ/ቤት ያስረዳነው፡፡ ሌላው ሠላማዊ የተባለው አማራጭ፣ የውሸት ስለሆነ፣ የወሠድነው አማራጭ ትክክል ነው ብለን ተናገርን፡፡
ፍ/ቤቱ ክሳችሁን ተከላከሉ ሲለንም፣ የቀድሞ ታጋዮችንና እነ ጀነራል ሣሞራ የኑስን፣ እነ አቶ አባይ ፀሃዬን፣ እነ አቦይ ስብሃትን ነበር በምስክርነት የጠራነው። በሃገሪቱ ያለው ስርአት ያለበትን ደረጃ ከዲሞክራሲና ከፍትህ አንፃር እንዲያስረዱም ምሁራንን አዘጋጅተን ነበር፡፡ ፍ/ቤቱ ለምስክሮቻችን መጥሪያ ከላከልን በኋላ ማረሚያ ቤቱ መጥሪያውን ወሠደብንና እንዳንከላከል ተደርገን ተፈረደብን፡፡ እኔ አራት አመት፣ ብርሃኑ ተ/ያሬድ አምስት አመት፣ ኢየሩሳሌም ተስፋው ደግሞ አራት አመት ከአምስት ወር እንዲሁም ወደ ኤርትራ ሊያሻግረን የነበረው ደሴ አራት አመት ከአምስት ወር ነው የተፈረደብን፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታህ ምን ታዘብክ?
እኔ በማረሚያ ቤት ስቆይ የተረዳሁት፣ ወደ ኤርትራ ተሻግሬ፣ “ግንቦት 7”ን ለመቀላቀል የወሠንኩት ውሣኔ ትክክል እንደነበር ነው፡፡ በፊት ማረሚያ ቤት ሲባል፣ አጥፊዎች ከስህተታቸው ታርመው፣ መልካም ዜጋ ሆነው የሚወጡበት ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን በኋላ ማረሚያ ቤቶቻችን የስነ-ምግባር ቦታ አለመሆናቸውን ተረዳሁ፡፡ ሰዎች ይዘረፋሉ፣ ይደበደባሉ፣ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ይፈፀምባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ አስተማሪ ሳይሆን ሰዎችን ወዳልሆነ መንገድ የሚመራ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለምሣሌ አንድ ጊዜ ግቢ ውስጥ ረብሻ ተነስቶ፣ “ረብሻውን አስነስታችኋል” ተብለን፣ በካቴና አስረውን፣ መሬት ላይ አስተኝተው፣ ሲደበድቡን ነበር የዋሉት፡፡ በዚህ ድብደባ አንድ ልጅ እዚያው ነው ደም የተፋው፡፡ ህክምና ባለማግኘቱም ከ12 ቀናት ቆይታ በኋላ ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል፡፡ በማረሚያ ቤት ሙስና ህጋዊ ነው የሚመስለው፡፡ ገንዘብ ያለው ጥሩ ሁኔታ ሊገጥመው ይችላል፡፡ በዚያ ላይ “እኛ ይሄን ስርአት ያቆምነው እንዳንተ ነጭ ጤፍ እየበላን አይደለም” በሚል  የስነ ልቦና ጉዳት ይደርስብን ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ሥርአቱን የበለጠ እንዲጠላ የሚያደርግ ነው። ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስፈን የወደቁ ጓዶቻቸውን ረስተው፣ ጭቆናን ነው ለኛ የተረፉት፡፡ ይሄ ያሣዝናል። አሁን እነዚህ ሰዎች ከስህተታቸው ተምረው፣ በሃገሪቱ እየተጀመረ ያለውን የለውጥ ተስፋ ሊደግፉ ይገባል፡፡ መለወጥ አለባቸው፡፡ ህዝቦቿ የሚዋደዱባት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሠፈነባት፣ ሁሉም ዜጋ እኩል የሆነባትን ሃገር መገንባት እንድንችል እድል ሊሠጡን ይገባል። የዚህ ለውጥ አጋዥ መሆን ያለባቸውም ለራሣቸው ሲሉ ነው፡፡
በቂሊንጦ ቃጠሎ ከተከሰሱት ውስጥ አንዱ ነበርክ። በእርግጥ በቂሊንጦ ቃጠሎ ተሣትፈሃል?
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከመቃጠሉ ሁለት ሣምንት በፊት፣ እኔ ወደ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ተልኬ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ግን የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደሮች፤ እኔን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎችን “እስረኛ ታሳምፃላችሁ” በሚል ከሌሎች እስረኞች ለብቻ ነጥለው፣ ዞን 4 የሚባል ቦታ አስረውን ነበር፡፡ በእዚህ ቦታ እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋዬ ነበሩ፡፡ በኋላ እኔ ወደ ዝዋይ ተላኩ፡፡ እዚያ ደግሞ እነ ጀነራል አሣምነው ፅጌ የታሠሩበት ልዩ ጥበቃ የሚባል ቦታ ነው የገባሁት፡፡ ዝዋይ ሆኜ ነው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተቃጠለው፡፡ በወቅቱ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የነበረው እስረኛ በእጅጉ የሚበደል በመሆኑ በየጊዜው ያማርር ነበር፡፡ ቃጠሎ ከደረሠ በኋላ በተለያዩ መድረኮች መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ነገሮች ሲነገሩ፣ መንግስትን ከተጠያቂነት ለማዳን ሁላችንንም ከያለንበት ሠብስበው ነው ክስ ያዘጋጁልን። ለምሣሌ ዶ/ር ፍቅሩ  ማሩ፤ ከቃጠሎ አንድ ቀን በፊት ሣንባቸውን ታመው ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡ ግቢ ውስጥ በስኳር ህመም ስለሚታወቁ፣ ክሡ ሲዘጋጅ፣ “ቸኮሌት ሆን ብለው በልተው ስኳራቸው ሲነሣባቸው ነው ሆስፒታል የገቡት” ብለው ነበር፡፡ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል ነው - ክሣቸው፡፡ ዶክተሩ ግን፣ ሆስፒታል የገቡት በሣንባ ህመም ነበር፡፡
የናንተስ ክስ  ምን ነበር?
ያው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን አቃጥለው፣ በር ላይ በሚጠብቋቸው 60 አውቶቡሶች ተሳፍረው፣ “ግንቦት 7”ን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ፣ ሌሎች ደግሞ በሞያሌ አድርገው አልሸባብን ለመቀላቀል አስበው ነበር በሚል ነው የተከሰሰነው፡፡ 60 አውቶቡስ ይሄን ኦፕሬሽን ለማሣካት እንደተዘጋጀ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ገንዘብ ለዚህ እንዳወጡ፣ እኛም እንደተደራጀን ተደርጎ ነው ክሡ የቀረበው፡፡ በተጨማሪም የማረሚያ ቤት ሃላፊዎችንና ውስጥ ያሉ በተለምዶ “አስጠጪዎች” የሚባሉ ከማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ታሣሪዎችን ገድለን ለመውጣት እንዳቀድን ጭምር ነው ክሡ፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ አስጠጪ ከሚባሉት በአደጋው የሞተው አንድ ሠው ነው፡፡ ሌሎቹ በተለያየ ሽብር ክስ የነበረባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄ አሳዛኝ ነበር። የኔ ክስ አንዱ፣ “እኛ ዝዋይን ለማቃጠል ተዘጋጅተናል፤ እናንተ ቂሊንጦን አቃጥሉ” የሚል ደብዳቤ ፅፈሃል የሚል ነበር፡፡ “ይሄ ሲሆን ደግሞ መጀመሪያ አቅደህ ነው ወደ ዝዋይ የሄድከው” የሚል ነገር ነው ያመጡት። የቀረቡብኝ ምስክሮችም፤ “በብዛት ከአማራ ልጆች ጋር ተሰብስቦ ይቆማል፣ መፅሐፍ ያነባል፣ የይስማዕከ ወርቁን ዴርቶጋዳ--” በማለት ነው የመሰከሩት፡፡
በምርመራ ወቅት ምን የተለየ ነገር አጋጠመህ?
በአዲስ አበባ በቆመው የቀይ ሽብር ሠማዕታት መታሠቢያ ሃውልት ላይ “አይደገምም” ተብሎ የተፃፈውን በኛ ላይ ደግመውታል፡፡ የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽንም ምርመራ አድርጎ፤ በደሎች መፈፀማቸውን ለፍ/ቤት አቅርቧል፡፡ ከአካላዊ ጥቃቱ ባለፈ ባልዋልንበት ባላደረግነው ነገር፣ ክሡ እጃችን ላይ ሲደርስ፣ የተቃጠለ ሬሣ ፎቶ ስናይ ስነልቦናችን መንፈሣችንን በእጅጉ ነው የተጎዳው፡፡ ጉዳቱ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገለፅ አልነበረም፡፡ የብዙ ሰው አዕምሮ ስለተጎዳ ነበር ፍ/ቤት ውስጥ እንደዚያ አይነት ንትርክና እሠጣ ገባ የነበረው፡፡ ከአካላዊ ጉዳቱም በላይ ነው የመንፈስ ጉዳቱ፡፡
ሌሎች ደግሞ በዚህ ተጠርጥራችኋል ተብሎ ጥቅምት 4 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ሸዋ ሮቢት ነው የተላኩት፡፡ በወቅቱ የገባሁ ቀን ማታ አሠቃቂ የስቃይ ጩኸት እሠማ ነበር፡፡ በኋላ እኔንም ወደ ምርመራ ወሠዱኝ፡፡ “ሰው ገድለሃል” አሉኝ፡፡ “ይሄን አላደረግሁም” አልኳቸው…በቃ ገልብጠው አስረው ደበደቡን፡፡ ይሄ አልበቃ ሲላቸው፣ የአንድ እግሬ አውራ ጣት በትንሹ መሬት እንዲነካ አድርገው፣ ሌላውን እግሬን ወደ ጎን ወጥረው፣ ሁለት እጆቼን ወደ ላይ ወጥረው አስረው ሲደበድቡኝ ነበር፡፡ ይሄ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ደብድበውኝ ሲደክማቸው አውርደው አሣረፉኝ፡፡ በኋላ አንድ መርማሪ፣ “ፍቅረ ማሪያም ሞኝ አትሁን፤ ይሄ ከላይ የመጣ ስለሆነ የሚሉህን እሺ ብለህ ተቀበል!” አለኝ፡፡ “ይሄ እኔ የማላምንበት ነው” አልኩ፡፡ ግን በቃ የሆነ ነገር መዝገብ ላይ ጽፈው፣ በማናይበት ሁኔታ፣ እያስፈራሩ ያስፈርሙን ነበር። የሆነውን ነገር ያለ አማራጭ ነው የተቀበልኩት፡፡ እጄ ከአልጋ ጋር ታስሮ ነበር የማድረው፣ ሽንት ቤት፣ ሻወር  ቅንጦት ነበር፡፡ እጆቼ በካቴና ነበር ታስሮ ውሎ የሚያድረው። ለሁለት አጋጥመውም ያስሩናል፡፡ ሽንት ቤት ስንጠቀም፣ አንዱ ቆሞ ነበር የሚያስጠቅመው። በቃ በደንብ ነው ያጠቁን፡፡ እኔ ስለዚህ ነገር ሣወራ በእጅጉ አዝናለሁ፡፡
ክሣችሁ በመጨረሻ እንዴት ተቋረጠ?
የቃጠሎው ክስ የተቋረጠው፣ የውሸት ክስ እንደሆነና እንደማያዋጣቸው ስላወቁ ነው፡፡ በምርመራ ወቅት በሚገርም ሁኔታ “ማንን ገድልሃል” ሲባል ተጠያቂ፣ እከሌን ሲል  “አይ እሡ በህይወት አለ” ይባል ነበር… ይደርስብን ከነበረው ድብደባ ለመዳን፣ በቃ ስሙን የማላውቀውን ሰው ነው የገደልኩ እንድንል ይደረግ ነበር፡፡ ለአስራ አንድ ሰው ሞት ተጠያቂ ነህ ተብሎ የነበረ ልጅ፤ በኋላ ሁለት ሰዎች በህይወት ስለተገኙ ተብሎ፣ ሁለቱ ሰዎች ተቀንሠውለታል፡፡ ይሄን ይመስል ነበር ጉዳያችን፡፡ በዚህ ምርመራ በደረሠብን ድብደባ፣ አብዛኞቹ በእጅጉ ተጎድተው መሄድ፣ መቀመጥ፣ መራመድ አቅቷቸው ነበር፡፡ ለመናገር የሚከብዱ አሠቃቂ በደሎች ናቸው የተፈፀሙብን፡፡ ብልቱ የተኮላሸ፣ እግሩ ከጥቅም ውጪ የሆነ ሁሉ አለ፡፡
አሁን በአገሪቱ ላይ እየታየ ስላለው የለውጥ ነፋስ ምን ትላለህ?
እርግጥ እኛ ከእስር ወጥተናል፤ ግን ዛሬም አብረውን የተከሠሱ ሠዎች ከእስር አልወጡም። ሌሎችም መፈታት ያለባቸው አሉ፡፡ በተረፈ ዶ/ር አብይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል ውጤት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የትግል ጥያቄ ተከትለው እየሄዱ ነው ያሉት፡፡
አሁንም ግን በፊት የነበረው የኢህአዴግ ጉልበተኛነት በማረሚያ ቤት አለ፡፡  እውነቱን ለመናገር፣ የማረሚያ ቤት ሰዎች ሃገሪቱ ለይ እየተደረገ ያለው ለውጥ የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር አብይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄን ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አደንቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንደ ሃጢያት በሚታይበት ሃገር ላይ እሣቸው ይሄን ሃሣብ አጉልተው መምጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ አሁን የሚታየው ነገር ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ፈጣሪ ከረዳን የተሻለ ነገር ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

• “ሥራቸው የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፡፡ የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤”
• “ሃይማኖት በመንግሥት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለው ሚዛን ያስፈልገዋል፤”



    የሃይማኖት ተቋማት በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ፣የሞራል አስተማሪነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከእንግዲህ መንግሥታቸው  በተቋማቱ ውስጥ የሚፈጸምን ዘረፋና ሌብነት በቸልታ እንደማያልፈው አስጠነቀቁ፡፡
“ሃይማኖት በመንግሥት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፤”የሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ትክክለኛ መርሕ ቢኾንም፣ የሃይማኖት ተቋማት የሚሰበስቡት መባ እና ዘካ የሕዝብ ሀብት እስከኾነ ድረስ መንግሥት አጠቃቀሙን የመቆጣጠር ርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ገንዘብ የሕዝብ ሀብት እንደኾነና በየትኛውም ዓለም ኦዲት እንደሚደረጉ የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፣ትንሽ የሌብነት ምልክት ካዩ ፈቃዳቸውን እስከመቀማት እንደሚደርሱ አስረድተዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ከመሬት ጀምሮ ለመንግሥት ለሚያቀርቡት ጥያቄ ባለሥልጣናቱ በእኩልነት ምላሽ መስጠት የሚገባቸውን ያህል፣ በአጸፌታው የመንግሥት ጥያቄ “ምከሩ፤ ገሥጹ፤ ሰላም አምጡ” በማለት ብቻ እንደማይወሰንና እንደማይቀጥል አስረድተዋል፡፡ “በዕለት ተዕለት የሃይማኖት ሥራ መንግሥት አይገባም፤ በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ሃይማኖት አይገባም፤ ግን ደግሞ ቀይ መሥመርና ድንበራችን ሁሌ የቆመና የማይገናኝ አይደለም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አጠቃላይ መርሑ ትክክል ቢኾንም ዘወትር እንደማይሠራና ሚዛን እንደሚያስፈልገው አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣“የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ሥራቸው፣የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፤ የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤ የለባቸውም፤ አላግባብ መባ እየሰበሰቡ ምን ላይ እንዳዋሉት የማይታወቅ ከኾነ ከእነርሱ የሚጠበቀው የሞራል ልዕልና ይጠፋና የሚያስተምሩትም ምእመን ሌባ ይኾናል፤”በማለት በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ እንዲሁም ሃይማኖት በጥበብና በዕውቀት በባለሥልጣናት ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በመጠቀም፣ መንግሥትን በተግባር ለማስተማር ቀዳሚውን ድርሻ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ፣ በሼራተን አዲስ የተካሔደውን 4ኛውን ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማትን ከተደራጁ ሌቦች ለመከላከልና ለማጠናከር የሚደረገው ትግል፣ በመንግሥት ብቻ ከዳር የማይደርስ በመኾኑ፤ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሲቪል ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ዘርፎ መክበርንና ሰርቆ አለማፈርን የሚያበረታታውን ባህልና አስተሳሰብ እያወገዙና እያጋለጡ በምሳሌነት በመዋጋት ለሕዝቡ ትምህርት እንዲኾኑ ጠይቀዋል - “እስኪ ምሳሌ ኾናችሁ ተገኙ፤ምሳሌ ኾናችሁም ታገሉ፤የሠራችሁትንም ለትምህርት እንዲኾን ለሕዝብ አሳዩ፡፡”

 ግጥም በጃዝ የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ የ “ደብተራው” አጭር ተውኔት አንደኛ ዓመት ክብረ በዓልን ያከብራል፡፡
በዚህ ምሽት ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከተላለፉት የ “ደብተራው” ተውኔቶች የተመረጡ ክፍሎች ተቀናብረው ለተመልካች የሚቀርብ ሲሆን፤ አንድ አዲስ የ “ደብተራው” ተውኔትም ይቀርባል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ገጣሚ በድሉ ዋቅጀራ (ዶ/ር)፣ በእውቀቱ ስዩም፣ አርቲስት ጌትነት እንየውና ሙአዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የተመረጡ የጥበብ ስራዎቻቸውን ለታዳሚያኑ ያቀርባሉ፡፡
የመግቢያ ዋጋ 100 ብር ሲሆን ትኬቱ በጃፋር መፅሐፍት መደብር (ኮሜርስ ተወልደ ህንፃ) እንዲሁም ዮናስ መፅሐፍት መደብር (ብሔራዊ ትያትር በረንዳ) ይገኛል፡፡ በዕለቱም ራስ ሆቴል በሚገኘው፣ ጦቢያ ግጥምን በጃዝ ቢሮ ማግኘት እንደሚቻል አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡


Saturday, 02 June 2018 11:58

ሴት ስትሆን

ሴትነት ምንድን ነዉ;
ብለህ የሰጠሀኝ ከባድ የቤት ስራ
መልሱ እኔንም ከብዶኝ ቃላት እመርጣለሁ
ሀሳብ አወጣለሁ ሀሳብ አደራለዉ
ሴትነት ምንድን ነዉ;
ሲመስለኝ
በሴትነት ጥልቅ ዉስጥ እጅግ የተለየ ሁለት
አለም አለ
እሷ
ከሁለቱ መካከል ከድንበሩ ስፍራ
ለሁለት ተወጥራ የምትኖርበት
ከሁለት የደቀለ ሶስተኛ አለም አላት::
ሌላ እንዴት ነበረ ሴትነት ትርጉሙ;
ሴትነት መንፈስ ነዉ፡፡
ልክ ... እርኩስ ደግ ብለህ እንደምትፈርጀዉ
እንደምትለምነዉ… ወይ እንደምታበረዉ
አማትበህ አርባ ክንድ
እንዲህ ነዉ ቅኝቱ ሴትነት ሲነጋ ሴትነት ቀን
ሲረፍድ፡፡
እንጂ ሴት ህይወት የላትም
ወይ ቀድሞ አልተሰጣትም
ወይንም ስጦታዋን ኋላ ነፍገዋታል
ትኖር ትምሰል እንጂ እስትንፋስዋ የታል::
ዉስጧ የነገሰዉ በአይን የሚታየዉ…
የሌላ ሰዉ አጥንት፤ የሌላ ሰዉ ስጋ፤ የሌላ ነፍስ
ነዉ::
እጆቿ ሲቆርሱ አፍዋ ቢከፈትም
የገባዉ ካንጀቷ ይበተናል የትም::
ስትባክን ብትታይ ቀንሌት በጎዳና
ስታመላልስ ነዉ ሌሎችን ተጭና::
ብቻ ይህ ሴትነት ባህል ካረቀቀዉ፤ አባባል
ካነጸዉ ቁንጽል ትርጉም ዉጪ
ሴትን ሆነዉ ሲያዩት
በስጦታ ሲሰጥ ፤ በነፍስ ሲገባ ብቻ የሚገለጥ
ብዙ አንድምታ ያለዉ
ዉስብስብ ቅኔ ነዉ፡፡

Saturday, 02 June 2018 11:57

የግጥም ጥግ


 የአንዳንድ ቀን ግጥሞች
መዓዛ
አንዳንዴ
መክተቢያ ቀለሙን በጅ ባልያዙበት
ማስፈሪያ ወረቀት በማይገኝበት
ጭው ያለ በረሀ
ቀን እየጠበቁ በዉልብታ መጥተው
ዉብ ሆነው ለመግጠም በሀሳብ ተፀንሰው
ሳይደምቁ ሳይሰፍሩ
መልሰው ላይመጡ ቀልጠው የሚቀሩ
በጅ ያልተጨበጡ ያልታዩ ያልጠሩ
ብቻ … ቀልብ የሚያሸፍቱ
የሚያቁነጠንጡ
ስሜት የሚያነጥሩ
የአንዳንድ ቀን ግጥሞች
የምናብ ስንኞች፡፡

 ለህጻናት ምቹ አገራት፡- ሲንጋፖር፣ ስሎቬኒያ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን

   በመላው አለም ከሚገኙት ህጻናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወይም 1.2 ቢሊዮን ያህሉ የድህነት፣ ግጭት ወይም ጾታዊ መድልኦ ሰለባዎች መሆናቸውን አለማቀፉ የረድኤት ተቋም ሴቭ ዘ ችልድረን፤ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአለማችን አንድ ቢሊዮን ህጻናት በድህነት በተጠቁና 240 ሚሊዮን ህጻናት ግጭት ባለባቸው አገራት ይኖራሉ ያለው ሪፖርቱ፤ 575 ሴት ህጻናት ደግሞ ጾታዊ መድልኦ በተንሰራፋባቸው አገራት ውስጥ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡
ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአለማችን ህጻናት ድሃ በመሆናቸው፣ በጦርነት አካባቢዎች በመኖራቸውና ሴት በመሆናቸው ሳቢያ የከፋ ህይወት እየመሩ ይገኛሉ ያለው የተቋሙ ሪፖርት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የጉልበት ስራና የምግብ እጥረትም የአለማችንን ህጻናት ክፉኛ እየፈተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
ሴቭ ዘ ችልድረን በ175 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው ሪፖርት፤ ምንም እንኳን ካለፈው የፈረንጆች አመት ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት፣ የህጻናት የችግር ተጋላጭነት ቢቀንስም፣ በ40 አገራት ግን ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡
ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ለድህነት፣ ግጭትና ጾታዊ መድልኦ የተጋለጡባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት ሁሉም ከአፍሪካ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ ኒጀር፣ ማሊና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡ ለህጻናት ምቹ የተባሉት የአለማችን አገራት በአንጻሩ ሲንጋፖር፣ ስሎቬኒያ፣ ኖርዌይና ስዊድን ናቸው፡፡