Administrator

Administrator

    ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት 6 ወራት በአገሪቱ ላይ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የምዕራብ መንግስታት፣በጥርጣሬና በስጋት ነው የተቀበሉት፡፡ የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረትም፤አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ያወጡት መግለጫ ከወትሮው የተለየ ነው፡፡  
አዋጁን በፅኑ የተቃወመው የአሜሪካ መንግስት በኤምባሲው በኩል ባወጣው መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ በመሰብሰብና ሀሳብን በነፃነት በመግለጽ መብት ላይ ገደብ የሚጥለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ፣ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረውን ሁሉን አሳታፊ የሆነ የለውጥ መነሳሳት የሚያቀጭጭ፣ ይሰፋል ተብሎ በተስፋ የሚጠበቀውን የፖለቲካ ምህዳርም የበለጠ የሚያጠብ ነው” ብሏል፡፡   
 “የተፈጠሩት ሁከቶችና ብጥብጦች የሰው ህይወትን እየቀጠፉ እንደሆኑና በዚህም መንግስት ጭንቀት ውስጥ መግባቱን እንገነዘባለን” ያለው ኤምባሲው፤“ሆኖም ለዚህ አይነቱ ችግር መፍትሄው  መብትን መገደብ ሳይሆን የበለጠ ነፃነትን መፍቀድ ነው” ብሏል -የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መውጣት አጥብቆ እንደሚቃወመው በመግለጽ፡፡
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ፤መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ ማሻሻያ በእጅጉ የሚጎዳ ነው ብሏል - በመግለጫው፡፡  
“አዋጁ መልካሙን ጅምር ሊያጠፋው ይችላል፤ከተቻለ የአጭር ጊዜያት ቆይታ ይኑረው” ሲልም ለመንግስት ምክር ለግሷል - ህብረቱ፡፡  
አዋጁ በሚተገበርባቸው ጊዜያት መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና መሰረታዊ መብቶች እንዲረጋገጡ የአውሮፓ ህብረት የጠየቀ ሲሆን ለሀገሪቱ ሁነኛ የፖለቲካ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ከተቃዋሚዎችና ከሀገሪቱ የፖለቲካ ተዋናዮች ጋር የሚደረግ  ውይይት ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ቤንት ቫን በሰጡት አስተያየት፤አዋጁ የሰብአዊ መብቶችን እንዳይገድብ ስጋት አለን ብለዋል፡፡ የአዋጁ የቆይታ ጊዜ ማጠር የሚችልበት ሁኔታም መመቻቸት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸው በበጎ የሚታይ ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን የመናገር፣ የመሰብሰብና ሃሳብን የመግለፅ መብቶች የሚገድብ በመሆኑ ያሳስበኛል” ያለው ደግሞ የእንግሊዝ መንግስት ነው፡፡  
አዋጁ ለአጭር ጊዜ ብቻ ይተገበራል የሚል ተስፋ አለኝ ያለው የእንግሊዝ መንግስት፤ “በዚህ ጊዜ ውስጥም ቢሆን መንግስት መሰረታዊ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች ያከብራል የሚል እምነት አለን” ብሏል፡፡ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅትም ሰዎችን በጅምላ ማሰርና ኢንተርኔትን ማቋረጥ ሊተገበር አይገባም” ሲል አሳስቧል - የእንግሊዝ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ፣ ፈጣንና ግልፅነት በተሞላው መንገድ የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ይመርጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ያለው መግለጫው፤ “ስለ ወዳጅነታችንም ለኢትዮጵያውያን እርዳታችን አይለይም” ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ከተለያዩ የዓለም ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ሰሞኑን ውይይት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤”አዋጁ ሀገሪቱ የገጠማትን የሰላምና መረጋጋት ችግር ለመፍታት የተዘጋጀ ነው፣ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህም የሀገሪቱ ሁኔታ መሻሻል አሳይቷል” በማለት የአዋጁን ጠቀሜታ ለዲፕሎማቶቹ አስረድተዋል፡፡   

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እረኛ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ፣ አንድ ሀሳብ መጣለትና ከፍ ወዳለው ኮረብታ ወጣ፡፡
ከዚያም፤ “ተኩላ! ተኩላ! በጎቻችንን ሊጨርስ መጥቷል፡፡ ቶሎ ድረሱ!” ሲል ለመንደሩ ህዝብ ጮኸ፡፡
መንደሬው ጦር ያለው ጦሩን፣ ቆንጨራ ያለው ቆንጨራውን፣ ዱላ የያዘ ዱላውን ይዞ እየሮጠ ኮረብታውን ወጥቶ ወደ ግጦሹ ሜዳ ሄደ፡፡
“የታለ፣ ተኩላው?” ብለው ጠየቁት፡፡
“ተኩላውማ ወደ እናንተ ስጮህ ሰምቶ ሸሸ!” አላቸው፡፡
መንደሬዎቹ አመለጠን ብለው እየተናደዱ ተመለሱ፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ ያ እረኛ እንደገና ወደ ኮረብታው ይመጣል፡፡
ከዚያም፤
“ተኩላ! ተኩላ! ያ ተኩላ በጎቻችንን ሊበላ መጥቷል፡፡ ድረሱልኝ!” አለ፡፡
መንደርተኞቹ፤
“ዛሬስ አያመልጠንም! በታችም በላይም መውጫ መግቢያውን እንዝጋበት፤ የትም አይጠፋም!” እያሉ በግሪሳ መጡ!”
እግጦሹ ሜዳ ሲደርሱ፤
“የታለ ተኩላው? ዛሬ አንምረውም!” አሉና ጠየቁት፤ እረኛውን፡፡
እረኛውም፤
“አይ ዛሬ እንኳን ማ ለችግሬ እንደሚደርስ፣ ማ እንደማይመጣ፣ ማ ለበጎቹ እንደሚጨነቅ፣ ማ እንደማይጨነቅ፣ ለመለየት ብዬ ነው እንጂ ተኩላው አልመጣም! አለና መለሰ፡፡
መንደርተኞቹ፤ እየተናደዱና በእረኛው እያማረሩ ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
በሶስተኛው ሳምንት በእርግጥም ተኩላው መጣ!
እረኛው እየሮጠ፣ እያለከለከ ወደ ተራራው ወጣ፡፡
“ተኩላ! ተኩላ! ዛሬ የምሩ ተኩላ መጥቷል፡፡ በጎቻችሁ እንዳይበሉ በነብስ ድረሱ!” አለ፡፡ ማን ይስማው? ማንም ሰው ሳይመጣ ቀረ! ተኩላው በነፃነት የሚችለውን ያህል በግ ቅርጥፍ አድርጎ በላና ሄደ፡፡
*        *      *
“ዋዛ ፈዛዛ ልብ አያስገዛ” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ውሸት ሆነው ሲደጋገሙ ዕውነት የሚመስሉ፣ ወይም የሚሆኑ አያሌ ነገሮች አሉ፡፡ በእርግጥ ደግሞ የሂትለር ዋና ፀሐፊ ጎብልስ፤ “አንድን ውሸት ደጋግሞ በመናገር ወይም በማስነገር ዕውነት ለማድረግ ይቻላል” የሚለውንም አንዘነጋም! ህብረተሰብ በእጅጉ ባልነቃበት አገር፤ ውሸትን ዕውነት ለማስመሰልም ሆነ ዕውነትን ውሸት ለማስመሰል መሞከር አያስገርምም! ፖለቲካ ብዙ የማስመሰል ጥበብ አለበት፡፡ ሀሳዊውን ፖለቲከኛ ከሀቀኛው መለየት የህዝብ ኃላፊነት ነው! በዘልማድ “እገሌ ክፉኛ ይቦተለካል” ማለት፤ ሸፋጭ ነው፣ ቀጣፊ ነው ማለት ነው፡፡ ምናልባት Politics is a dirty game የተባለው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእርግጥም ፖለቲካ አስቀያሚ ጨዋታ ነው፡፡ በፖለቲካ ይሉኝታ የለም። ያም ሆኖ በፖለቲካው በዚህ መንገድ ብሄድ ያዋጣኛል አያዋጣኝም ብሎ መጠየቅ፤ የብልህ እርምጃ ነው፡፡ ትላንት ያሉትን ሽምጥጥ አድርጎ መካድ ፖለቲካ ነው፡፡
ፖለቲካ ለሱ መፈጠርን ይጠይቃል፡፡ ምሁር ወይም የሙያ ሰው ለፖለቲካ አይሆንም፤ የሚባለው ከዚህ መሰረታዊ የፖለቲካ ባህሪ በመነሳት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በየትኛውም የፖለቲካ ጎራ እንሰለፍ፣ የሀገርና የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መቆም የሀቀኛ ፖለቲከኛ ተግባር መሆን አለበት፡፡
ከፖለቲከኝነት ጋር ሳይነጣጠል እጅ ለእጅ ተያይዞ የሚጓዝ አንድ አባዜ አለ - ሙስና! ይህ አባዜ በተለይ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ እንደ ማተብ የሚጠለቅ፣ እንደ ዳዊት የሚደገም የዕለት የሰርክ ፀሎት ነው! “የዕለት እንጀራዬን አታሳጣኝ” ወደ “የዕለት ሙስናዬን አታሳጣኝ” ተለውጧል! “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው ተረት፤ የባለስልጣኑ መሪ - መፈክር ሆኗል፡፡
በሙስና የተሰራው ህንፃ አፍ ቢኖረው ስንቱን ባጋለጠ ነበር፡፡ የታጠረም ሆነ ያልታጠረ አጥር አፍ ቢኖረው፣ ስንቱን ጉድ ባደረገ ነበር፡፡ ወገናዊነት መናገር ቢችል ኖሮ፣ ስንቱን ግፍ ባስረዳን ነበር፡፡ ዲሞክራሲ አፍ ቢኖረው ኖሮ፣ ስንቱን ሀሳዊ ዲሞክራት አፉን ባስዘጋ ነበር፡፡ ፍትህ ርትዕ አንቀፅ መጥቀስ ቢችል ኖሮ፣ ስንቱን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ባደባባይ ባጋለጠ ነበር፡፡ ሀገራችን ገና ብዙ መንገድ ይጠብቃታል። ማደግ ያለበት መለወጥ ያለበት፣ መቀልበስ ያለበት አያሌ ጉዳይ ይጠብቃታል፡፡ ይህን መፈፀም ያለባቸው ከየጎራው ያሉ አካላት በሙሉ ፈቃደኝነትና ቆራጥነት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አፋቸው ሌላ ልባቸው ሌላ የሚያስብ ከሆነ ግን “ጅብ፤ ጥጃ ጠብቅ” ቢባል፤ “ቢጠፋብኝስ?” አለ፤ እንደተባለው ይሆናል!  

  • አሁን የሚያስፈልገን የአስቸኳይ ጊዜ አንድነትና ፍቅር ነው
      • ማረሚያ ቤት መታረሚያ ቦታ እንጂ መሰቃያ መሆን የለበትም
      • የጋዜጠኝነት ሙያ እዚህ የደረሰው በጋዜጠኛው ብርታት ነው
      • የሽብርን አስከፊነት እኛ ኢትዮጵያውያን አሳምረን እናውቀዋለን

     ከሰሞኑ ከእስር ከተፈቱት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፤ለ7 ዓመት በእስር ቤት በነበረው ቆይታ፣ በጋዜጠኝነት ሙያው፣ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

     በሽብር ወንጀል ተጠርጥረህ የታሰርክበት አጋጣሚ እንዴት  ነበር?
የታሰርኩት ሰኔ 12 ቀን 2003 ዓ.ም ነው። ሁኔታዎች በጣም እየተወሳሰቡ የመጡበት ወቅት ነበር፡፡ ምናልባት በወቅቱ እፅፋቸው በነበሩ መጣጥፎች  ላይ በስፋት ፀረ ሽብር ህጉን እተች ነበር፡፡ ፀረ ሽብር ህጉ በጣም ከባድ መሆኑንና አሳሳቢ መሆኑን ለማመላከት የአቅሜን እጥር ነበር። ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ደግሞ እየተካረሩ የመጡበት ሁኔታም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት እንዲሁ የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል እገምት ነበር፡፡ በኋላ ሰኔ 12 ቀን የጋዜጣ ኤዲቶሪያል ስብሰባ ነበረኝ፡፡ ወደ ቢሮ ስሄድ ብዙ ሰዎች ይከተሉኝ ነበር፡፡ በወቅቱ የሆነ ችግር እንዳለ ገምቼ፣ እኔም ሁኔታውን በጥንቃቄ እከታተል  ነበር፡፡ በኋላ ወደ ኢንተርኔት ካፌ ገባሁና ሊሲፒጂኤ እና ለጋዜጠኛ ማህበራት ስለ ሁኔታው በኢ-ሜይል አሳወቅሁኝ፡፡ የጠረጠርኩት አልቀረም፣ እዚያው ኢንተርኔት ቤት እያለሁ፣ ብዙ የፌደራል ፖሊስ አባላትና ተሽከርካሪዎች መጥተው ያዙኝ፡፡ በወቅቱ በሁኔታው ተገርሜ ነበር፡፡ ምናልባት ሄሊኮፕተር ነው የቀረው እንጂ የተሽከርካሪና የፖሊሶችን ብዛት ላየ፣ አንድ በእጁ ብዕርና ወረቀት የያዘን ጋዜጠኛ ለመያዝ አይመስልም፡፡ እኔ በህይወቴ መሳሪያ የሚባል ነገር ነክቼ አላውቅም፡፡ ግን ሁኔታውን ለተመለከተ፣ መሳሪያ የያዝኩ ነበር  የሚመስለው። በኋላም ቤቴ ተፈተሸ፡፡ በሽብር ተጠርጥረህ ነው ተባልኩ፡፡ ይሄን ሲሉኝ፣ ቀልድ ነበር የመሰለኝ፤ በኋላ ቤቴ ተፈትሾ፣ ከ4 በማያንሱ ፌስታሎች፣ ወረቀቶችና የተለያዩ መንፈሳዊ ፊልሞች እንዲሁም ካሴቶች በሙሉ ተወሰዱ፡፡ እኔ ቤት ውስጥ ከመዝሙርና ከመንፈሳዊ ፊልሞች ውጪ ምንም የለም፡፡ እነሱም በኋላ ይሄን ሲረዱ፣ የወሰዱትን በሙሉ ለባለቤቴ መልሰውላታል፡፡  ይሄን የቤት ውስጥ ብርበራ ሲያደርጉ፣ እስከ ዛሬ ከህሊናዬ የማይጠፋው፣ ሁለት እጆቼ በካቴና ታስረው፣ ልጄ ሊጠመጠምብኝ እየሮጠ ሲመጣ፣ በድንገት እጄ ላይ ያለውን ሰንሰለት አይቶ፣ የደነገጠው ድንጋጤና መሸማቀቅ ነው፡፡ ልጄ በወቅቱ ፊቴን አያይም ነበር። ገና 2 ዓመቱ ነበር፡፡ ነገር ግን እጄን ነበር አተኩሮ ያይ የነበረው፡፡ ይሄ እስከ ዛሬ አዕምሮዬ ውስጥ የፈጠረው መጥፎ ጠባሳ አለ፡፡ ልጄ “ፍትህ”፤ በልጅነቱ ሳቂታና ተጫዋች ነበር፡፡ አሁን ግን  ዝምተኛና ብዙ የማይናገር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እኔን ለመጠየቅ ሲመላለስም በዝምታ ይመለከተኛል  እንጂ ብዙ አያናግረኝም ነበር፡፡
ማዕከላዊ ከገባህ በኋላ የምርመራ ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
ማዕከላዊ በነበረው ምርመራ ሁሉም ነገር ከመጀመሪያው ነው የሚጀመረው፡፡ አስበሃል ወይ? እያሉ ነው የሚጠይቁት፡፡ እነሱ አስቧል ብለው ለያዙት ሰው እንኳ በቂ መረጃና ማስረጃ የላቸውም። እኔ ለውጭ ሚዲያዎች ስሰራ ሙያዬን ጠብቄ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ለ8 ወራት ተጠልፈዋል የተባሉትን የስልክ ንግግሮች ለየትኛውም በጉዳዩ ላይ ጥናት ለሚሰራ አካል ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ መደበኛ የመረጃ ልውውጥ፣ ንግግሮችን ነው ሳደርግ  የነበረው፡፡ እነሱ መረጃ አምጣ እያሉ ድብደባ ፈፅመውብኛል፡፡ ብርሃን በሌለውና ሙቀት በሌለው ቤት ውስጥ ለ90 ቀናት እንድቆይ ተደርጌአለሁ፡፡ የኔ እንደውም በምርመራ ሂደት ዓይናቸውን ካጡት፣ የመራቢያ አካላቸውን ከተጎዱት የተሻለ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ እርግጥ ነው በድብደባ ብዛት ጆሮዬ ለረጅም ጊዜያት ደም ይፈሰው ነበር፡፡ ከዚያ በተረፈ ስነ ልቦናን የሚጎዱ፣ በብሄር ማንነት ላይ ያተኮሩ ዘለፋዎች ነበሩ፡፡ እኔ የማውቀው ሰው መሆኔን ነው፤ ግን ዘለፋው አዕምሮ ይጎዳ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ እንግዲህ በኋላ ላይ የሰጠውን ፍርድ ሰጥቷል፡፡
በአንተ የክስ ክርክር ላይ “ኦፕሬሽን” የሚል ቃል እንደ ማስረጃ ቀርቦ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ንገረን?
ጉዳዩ እንግዲህ አባታችን ታመው እኛ ጋ መጥተው ነበር፡፡ ሃገር ውስጥ ያለሁት ወንድ የቤተሰባችን አባል እኔ ብቻ ስለነበርኩ፣ ህክምናቸውን የምከታተለው እኔ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ እሳቸው ኦፕራሲዮን ተደርገው ከውጪ ወንድሜ ይደውልልኝና፤ ”አባታችን እንዴት ናቸው?” ይለኛል። እኔም፤ “አይ አሁን በቃ አታስብ፣ ኦፕሬሽኑን አድርጓል” አልኩት፡፡ ይሄ ቃል የሆነ ኦፕሬሽን ነው ተብሎ ነው፣ የምርመራው አካል ሆኖ የቀረበው፡፡ ሁኔታው ይሄን ይመስላል፡፡ አባታችንም እኔ እስር ቤት ሆኜ፣ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ሌሎችም በጣም የተዛቡ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ለዚህ ነው በጉዳዩ ላይ ጥናት ማድረግ ለሚፈልግ መረጃ መስጠት እችላለሁ ያልኩት፡፡ ሌሎች እንደ ማስረጃ የቀረቡብኝ ፅሁፎች ደግሞ አምኜባቸው፣ ሃሳቤን ይገልፁልኛል ብዬ የፃፍኳቸው፣ የምወዳቸው ፅሁፎች ናቸው፡፡ በወቅቱ ምንም ማድረግ ስለማይቻል፣ ፍ/ቤቱ በኛ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በአክብሮት ተቀብለነዋል፡፡
በወቅቱ የ14 ዓመት እስራት  ይፈረድብኛል ብለህ ጠብቀህ ነበር?
መሬት ላይ ያለውን ሃቅ እንገምግም ከተባለ፣ ሊከሰስ ይገባል ብባል እንኳ መከሰስ የነበረብኝ በሚዲያ አዋጁ መሰረት ነበር፡፡ በመረጃ ልውውጡ ወቅት ሀገሪቱን የሚጎዳ ነገር ተፈጽሟል ከተባለ እንኳ በሚዲያ አዋጁ ነበር ሊታይ የሚገባው። ነገሩን ለጥጠው በሽብር አዋጁ ነው የከሰሱኝ። የሽብርን አስከፊነት እኛ ኢትዮጵያውያን እናውቀዋለን፡፡ በሃይማኖትና በግብረ ገብ ተቀርፀን፣ በእዝነት እንድናድግ ሆነን ነው እኛ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችን የሚያሳድጉን፡፡ ይሄ ስነ ልቦና ለሽብር ያውም በገዛ ሀገር ላይ ሽብር ለመፈጸም በእጅጉ ሩቅ ነው፡፡ እኔም በወቅቱ በሽብር ተከሰሃል ስባል፣ ከፍተኛ ቅጣት ነው የጠበቅሁት፡፡ እርግጥ አንድም ምስክር አልቀረበብኝም ነበር፡፡ ተከላከል ስባልም ተከላክያለሁ፡፡ ግን ያው 14 ዓመት እስራት ተፈረደ። ፍርዱ ሲሰጥ አስገርሞኛል እንጂ አላስደነገጠኝም ነበር፡፡
የማረሚያ ቤት ቆይታህስ ምን ይመስላል?
እንግዲህ ማረሚያ ቤት የቆየሁት ለ7 አመታት ያህል ነው፡፡ በማረሚያ ቤት መቆየት ብዙ ነገር ለማሰላሰል፣ የጥሞና ጊዜ ለማግኘት ይረዳል። መከራዎች፣ እንግልቶችና መገፋቶች መልካም ነገር ነው የሚያወጡት፡፡ ወተት ሲናጥ ነው ቅቤ የሚወጣው፤ አበባ ሲረግፍ ነው ዛፍ ፍሬ ማፍራት የሚጀምረው፡፡ የማረሚያ ቤት ቆይታዬን በዚህ ነው የምገልፀው፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን ዝዋይ ነው ያሳለፍኩት፡፡ በወቅቱ ጉዳያችን በመላው ህዝብ ዘንድ ትኩረት ማግኘቱ፣ ብዙ ወገን ከጎናችን መቆሙን ስንሰማ፣ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለኛ እየተሟገተ መሆኑን ስንረዳ ተስፋችን ይለመልም ነበር፡፡ በአሉታዊ ጎኑ ደግሞ ምናልባት እኔ ጠንካራ ባለቤት ስላለችኝ ቤተሰቤ እንደነበረ ጠበቀኝ እንጂ በርካታ ቤተሰብ በዚህ ምክንያት ፈርሷል፡፡ እኔም ወላጅ አባቴን ማገዝ ስችል በመታሰሬ ሳላግዘው አጥቼዋለሁ፡፡
በማረሚያ ቤት ህክምና አናገኝም ነበር። በአንድ ወቅት እንደውም የኩላሊት ጠጠር ያመኝ ስለነበር እንድታከም ወደ ሆስፒታል ሪፈር ተፅፎልኝ፣ በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ተከልክያለሁ። ብዙ አስነዋሪ ነገሮች አሉ፡፡ በማረሚያ ቤት የብዙ ሰዎችን መከራ መመልከት ይቻላል፡፡ ድብደባዎች ይፈፀማሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር የሚሰማ አካል ካለ፣ ይሄ መመርመር አለበት፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በዘፈቀደ የሚቀጠቀጡበት ቦታ እስር ቤት ነው። ማረሚያ ቤት ማለት እኮ መታረሚያ ቦታ እንጂ መሰቃያ መሆን የለበትም፡፡ በድብደባ ብዛት የሞቱ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ በመፅሐፌ በዝርዝር ፅፌዋለሁ፡፡ ግን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተባለው ተቋም፣ ይሄን እንኳ ለማጣራት ጥረት ሲያደርግ አንመለከተውም፡፡ ራሳቸውን አጥፍተው ሞቱ የሚባሉ የኦነግ ተከሳሹን ኢ/ር ካሳሁን ጨመዳን ጨምሮ በርካቶች አሉ፡፡ ለምን ይሄ ጉዳይ አይጣራም? መጣራት አለበት፡፡ እኔ በብዛት ከእነ ጀነራል አሳምነው ፅጌ ጋር ከሌሎች እስረኞች ተገልለን ነው ታስረን የቆየነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አንችልም፣ የካፌ አገልግሎት አናገኝም። ከሌሎች እስረኞች ጋር እንድንገናኝ አይፈለግም ነበር፡፡
ለምንድን ነው እንደዚያ የሚደረገው?
ያው እኛን ለመጉዳት ነው፡፡ የማግለል ስራ ነው የሚሰራው፡፡ ስለ ምግቡ እንኳ ባናነሳው ነው የሚሻለው፡፡፡ እንጀራውና ወጡ ከምን እንደሚሰራ እንኳ አናውቅም፡፡ በጣም አቅምን የሚያዳክም ምግብ ነው፡፡ በአብዛኛው ያለ ምግብ ነው የኖርነው ማለት ይቻላል፡፡
እዚያው እስር ቤት ሆነህ ሁለት መፅሐፍትን አሳትመሃል፡፡ እንዴት ነው የተሳካልህ?
የሰው ልጅ አካሉ ቢታሰርም አዕምሮው ማሰብ አያቆምም፡፡ በተቻለኝ አቅም ተደብቄ ነበር የምፅፈው፡፡ የምፅፋቸውን ደግሞ ፖሊሶች የማያገኙት ቦታ እደብቃለሁ፡፡ አወጣጡ የራሱ መንገድ አለው፡፡ ያን መንገድ አሁን መግለፁ ብዙም አስፈላጊ አይሆንም፡፡ ሌሎችም ያንን መንገድ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በዚህ መልኩ ነው፣ መፅሐፎቼ ወጥተው የታተሙት፡፡
በማረሚያ ቤት ሳለህ፣ አብዛኛውን ጊዜህን እንዴት ነበር የምታሳልፈው?
በብዛት መፅሐፍት አነባለሁ፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ወደ ቤተ መፅሐፍት በጥበቃ ታጅበን እንሄዳለን፤ 5 ደቂቃ ይሰጠናል፡፡ በ5 ደቂቃ ውስጥ አንድ የምንፈልገውን መፅሐፍ መርጠን፣ ተመልሰን እንገባለን፡፡ ከዚያ ውጪ የምንፈልጋቸውን መጽሐፍት፣ ከውጪ በተለያየ መንገድ እናስገባለን። ሌላው ስፖርት በብዛት እንሰራለን፤ የፀሎት ጊዜም አለን፤ ስለተለያዩ ጉዳዮችም እንወያያለን፡፡ እስር ቤቶች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች መገኛ ናቸው። ከሁሉም ጋር እንወያያለን፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች ነበር  ጊዜያችንን የምናሳልፈው፡፡
የትኞቹን  ሚዲያዎች ትከታተሉ ነበር?
ያው ኢቲቪ አለ፡፡ ጋዜጦች አይገቡም፡፡ በመጨረሻ አካባቢ ደግሞ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በተለያየ መንገድ ግን መረጃዎችን ለማግኘት እንሞክር ነበር። እነ ኦሮማይን የመሳሰሉ መጻህፍት እኮ መግባት አይችሉም፡፡ ምናልባት ማስገባት የሚቻለው የተረት መጻህፍት ይመስለኛል፡፡  
እስር ቤት ሆነህ ሁለት ዓለማቀፍ ሽልማቶችን አግኝተሃል፡፡ በሽልማቶቹ ምን ነበር የተሰማህ?
እንግዲህ አንደኛው ሂውማን ራይትስ ዎች ያበረከተልኝ ሽልማት ሲሆን ሁለተኛው የሲኤንኤን መልቲ ቾይዝ አፍሪካ ዓመታዊ ሽልማት ላይ “የዓመቱ ጋዜጠኛ” በሚል የተሸለምኩት ነው፡፡ እነዚህ ሽልማቶች እኔ ከሌላው የበለጠ ስለሰራሁ የተሰጡኝ አይመስለኝም፡፡ ሽልማቶቹ ተምሳሌታዊ ናቸው፡፡ ሌላው አለም እየተከታተለን እንደሆነ ለማሳየት የተደረጉ ሽልማቶች ይመስሉኛል፡፡ ሽልማት ይሰጥ ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ 30 እና 40 ዓመት በጋዜጠኝነት የሰሩ የምናከብራቸው ጋዜጠኞች አሉ፡፡ እኔ በጋዜጠኝነት የቆየሁት ለ10 ዓመት ነው፡፡ ግን ሽልማቶቹን በአክብሮት እቀበላቸዋለሁ፡፡ ለኔ ከሁሉም በላይ ሽልማቴ፣ የኔን ጉዳይ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች የሚለግሱኝ ፍቅር ነበር፡፡ አስታውሳለሁ፣ በፊት ቢሮዬ እየመጡ፣ ጋዜጣ በነፃ የምሰጣቸው አንድ ጡረተኛ ሽማግሌ ነበሩ፡፡ እሳቸው ለባለቤቴ 20 ብር ሰጥተዋት፣ “ሙዝ ገዝተሽለት ሂጂ” ያሏት ነገር፣ ዛሬም ከህሊናዬ አልወጣም፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ሽልማት ለኔ የለም፡፡
በይቅርታ ለመፈታት ያመለከትክበት አጋጣሚ እንደነበር ሰምቼአለሁ፡፡ በእርግጥ ይቅርታ ጠይቀህ ተከልክለሃል?
ሁላችንም እንደምናስታውሰው፤ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች፣ ርዕዮት ዓለሙና እኔን በወቅቱ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው አቶ አንተነህ አብርሃም፣ የአለማቀፍ የጋዜጠኝነት ህብረት ተወካይና ሌሎች ሰዎች መጥተው አነጋገሩን፡፡ እኛ እንድትፈቱ ነው የምንፈልገው፣ መንግስት ሊፈታችሁ ይፈልጋል። ለምን ነገሮችን እዚህ ጋ አንቋጭም የሚል ሃሳብ አቀረቡ፤ ሁለቱ ስዊድናዊያንና እኔ ይሄን ተቀብለን የይቅርታውን ሰነድ ሞላን፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ፣ ”የጥቁርና ነጭ ደም አይለያይም” ብለው ነበር፤ በኋላ ግን ነጮቹን በመፍታት እኔን በማቆየት እንደሚለያይ አሳይተውናል፡፡ ነጮቹን ወዲያው ለቀቋቸው፣ እኛን አቆዩን፡፡ አሁን ግን “ይቅርታ አድርገንላችኋል፣ ትቀበላላችሁ አትቀበሉም” የሚል አማራጭ ነው ያቀረቡልን፡፡ እንቀበለዋለን ብለን ወጥተናል፡፡
በዚህ መንገድ ከእስር  እፈታለሁ የሚል ግምት ነበረህ?
መቼ እና እንዴት የሚለውን መገመት ባልችልም በመሃል እንደምፈታ ተስፋ አደርግ ነበር፡፡ በኛ ጉዳይ ተመሳሳይ ፍርድ የተፈረደባቸው ሲፈቱ ሳይ፣ ተስፋ አደርግ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ ተገማች አይደለም፡፡ ተገማች አለመሆኑ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን አይነት የአፈታት መንገድ አልገመትኩም፡፡
በእስር ላይ ሆናችሁ ሀገሪቱ ባለፉት 3 ዓመታት ያሳለፈችውን ፖለቲካዊ ቀውስ በተመለከተ ምን ያህል መረጃ ታገኙ ነበር?
መረጃዎችን በደንብ እንከታተል ነበር፡፡ በተለያየ አማራጭ እያንዳንዷን ነገር እናገኝ ነበር፡፡ ከፖሊሶችም ቢሆን መረጃ የምናገኝበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡
እንደ ጋዜጠኝነትህ፣ የሀገራችንን የጋዜጠኝነት ሙያ እንዴት ትገልፀዋለህ?
 የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ በብዙ ጎታች ነገሮች ወደ ኋላ እየተጎተተ፣ ጥርሱን ነክሶ ወደፊት ለመግፋት የሚሞክር ነው፡፡ የሀገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ እዚህ የደረሰው፣ አሰሪ ሁኔታዎች በመኖራቸው ሳይሆን በጋዜጠኛው ብርታት ነው፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች ብዙ ይጥራሉ፡፡ የግሉ ሚዲያ ደግሞ በመከራ ውስጥ ያለ ነው፤ ይሄን ተቋቁሞ ወደፊት ለመግፋት የሚውተረተር ነው፡፡ በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ጋዜጠኞች፣ ምስኪን ጋዜጠኞች ነን፡፡ በብዙ ፈተና እና ትግል ውስጥ ነው የምናልፈው። እኔ ለምሳሌ በሙያዬ ስንቀሳቀስ፣ ከ5 ጊዜያት በላይ ታስሬያለሁ፣ ታግቻለሁ፡፡ ሂደቱ እጅግ ፈታኝና በምስቅልቅሎሽ የተሞላ ነው፡፡ ወደ ኋላ በሚጎትቱ አሰራሮች፣ ደንቦችና ስልታዊ ደባዎች የተጠፈረ የሙያ መስክ ቢኖር ጋዜጠኝነት ነው፡፡ እስካሁን ያለፍንበት ሂደት የመገፋፋት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የሚኖረውን ሂደት አላውቅም፡፡ የተሻለ ነገር እንዲመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?
አሁን ብዙ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉ፡፡ ጫፍ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሃይማኖታዊ በዓል ሲያከብሩ ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡ ብዙ ምስቅልቅል ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ በነዚህ መሃል ደግሞ የነበሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ነፃነት፣ ዲሞክራሲ ፈልጓል፡፡ አሁን  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይሆን አስቸኳይ ውይይት ነበር የሚያስፈልገን። የአስቸኳይ ጊዜ አንድነት፣ ፍቅር ነው የሚያስፈልገን። ሰራዊት ማሰማራት ሳያስፈልግ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅር ማስተካከል ይቻላል፡፡ እውነተኛ የሀገር ሽማግሌዎች ስራቸውን መስራት አለባቸው፡፡ ኢህአዴግ በአውራ ጣቱ ቆሞ ሳይሆን ቁጭ ብሎ ነው መወያየት ያለበት፡፡ ዶ/ር መረራ እንዳሉት፤ ሁለቱም ወገኖች መቀራረብ አለባቸው። መፍትሄው ያለው ሁለቱም ጋ ነው፡፡ ነገር ግን ፈለግንም አልፈለግንም ከእንግዲህ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ ማበቡ አይቀርም፡፡ የዲሞክራሲ ፀሐይ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ይሄ የብሄር ማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት መቆም አለበት፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ዝዋይ እያለሁ፣ ማረሚያ ቤት ድረስ እየመጡ የሚጠይቁኝ አደይ፣ ትርሃስ የሚባሉ እናቶች ነበሩ፡፡ ከልባቸው ጠይቀውኝ፣ መርቀውኝ ነበር የሚሄዱት፡፡ እኛን እነዚህ የፍቅር እናቶች ናቸው ዘር ሳይለዩ ያሳደጉን። ወንበር ላይ የተቀመጡ ሰዎች በሰሩት ስህተት፣ ሌሎች መጎዳታቸው ተገቢ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የለውጥ ጊዜ ስለሆነ፣ ሁሉንም ነገር ቆም ብሎ ማሰብ የግድ ይላል፡፡  
የወደፊት እቅድህ ምንድን ነው?
እኔ በጋዜጠኝነት ሙያዬ የተሻለ ነገር ለማድረግ ነው የምጥረው፡፡ አንድ ሰው ባዳበረው ሙያ ነው መጓዝ ያለበት፡፡ አንድን በባህር ውስጥ የለመደ ዓሳ፣ በሰማይ ብረር ብንለው አይሆንም፡፡ የኔም እንደዚያው ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያዬ ቀጥዬ፣ አስተዋፅኦ ማበርከት እፈልጋለሁ፡፡
በተረፈ ከጎኔ የቆሙ የሰው ዘሮችን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያንም እግዚአብሔር እንዲባርካት፣ እንዲጠብቃት፣ ያጣነውን መደማመጥ እንዲሰጠን እመኛለሁ፡፡     

  በኢትዮጵያ የተፈጠረው አለመረጋጋትና የሠላም እጦት እንዳሳሰበው የጠቆመው የአፍሪካ ህብረት፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያንና መንግስት ለሠላምና መረጋጋት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር ሙሣ መሃመት ፋኪ ከትናንት በስቲያ ለመገናኛ ብዙሃን ባሠራጩት መግለጫ፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዋንያን ሠላምና መረጋጋትን ከሚነሣ ድርጊት መታቀብ አለባቸው ብለዋል፡፡
“መንግስትና የሃገሪቱ ህዝብ ችግሩን በመግባባት እንደሚፈቱት እምነት አለኝ” ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል መግባቱንም ህብረቱ በአዎንታ እንደሚቀበለው አስታውቀዋል፡፡
“የኢትዮጵያ መረጋጋት ለህዝቧ፣ ለቀጠናውና ለመላው አፍሪካ በእጀጉ አስፈላጊ ነው” ያሉት ሙሣ ፋኪ፤ መንግስትና ሁሉም የሃገሪቱ ባለድርሻዎች በሃላፊነት ስሜት እንዲንቀሣቀሱ አሳስበዋል፡፡

 “የወጣው መስፈርት አንድን ግለሰብ ታሳቢ ያደረገ ነው”
       “በ4 ወር እንኳን አንድ ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ ያሉም ቢተባበሩ ሥራው አያልቅም”

   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሦስት ሳይቶች የሚገኙ 40/60 ቤቶችን የአሉሙኒየም በርና መስኮት ከነመስታወቱና ከነሙሉ ገጠማ ስራው እንዲሰራለት ያወጣው የ1 ቢሊዮን ብር ጨረታ ሠነድ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በጨረታው ሠነድ ላይ የወጣው መስፈርት ለአንድ ድርጅት የወገነ፣ የወቅቱን የምንዛሬ እጥረት ያላገናዘበና በአጠቃላይ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ነው ሲሉ  በአልሙኒየም አስመጭነትና ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ለአንድ ግለሰብ እንዲመች ሆኖ የተሰናዳው የጨረታ ሠነድ እንኳን በ4 ወር በ4 ዓመት በአንድ ድርጅት ተሰርቶ  ሊያልቅ ቀርቶ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ በአልሙኒየም ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ቢተባበሩ እንኳን ሥራው እንደማያልቅ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ ባወጣው የጨረታ ሠነድ ተጫራች ድርጅቶች የአልሙኒየም ክምችት (ስቶክ) እንዲኖራቸውና ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ መጠየቁን የገለፁት ድርጅቶቹ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ድርጅቶች ቶሎ ቶሎ እቃውን እያስገቡ ማከማቸት እንደማይችሉ፣ አንድ ዕቃ ታዝዞ እስኪገባ የሚፈጀውን ጊዜ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሠነዱን በዚህ መልኩ ማዘጋጀታቸው አንድን ድርጅት ለመጥቀም ሆን ብሎ የተሰራ ሴራ ነው ሲሉ ያማርራሉ፡፡
ከደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ ሠርተፍኬት አቅርቡ መባሉን በተመለከተም፤ “እኛ እቃውን ከውጭ የምናስመጣ እንደመሆናችን ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የሚሰጠን ሠርተፍኬት እንደሌለ ይታወቃል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከውጭ አገር የሚሰጥ ተመጣጣኝ ሠርተፍኬት እንዲያቀርቡ አለመጠየቃቸውም ሆን ተብሎ ተፎካካሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የተሰራ በመሆኑ ሠነዱን ቢገዙም በጨረታው እንደማይሳተፉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የጨረታው ሠነድ አንድ ድርጅትን ለመጥቀም ታስቦ ለመውጣቱ ምን ማረጋገጫ አላችሁ በሚል ከአዲስ አድማስ ለተነሳው ጥያቄ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲመልሱ፣  ታሳቢ የተደረገው ድርጅት ከውጭ በሚመጣ አልሙኒየም ተረፈ ምርት ሪሳይክል እያደረገ የሚያመርት በመሆኑ ክምችትም የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች ሠርተፍኬትም እንዳለው ይታወቃል በአጠቃላይ የታዘዘው የአልሙኒየም አይነትና ቀለም ሳይቀር ለዚሁ ድርጅት የታሰበ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ከአምስት ዓመታት በፊት በክራውንና በሰንጋ ተራ ለተገነቡ ቤቶች ተመሳሳይ የ1 ቢሊዮን ብር ጨረታ ወጥቶ ይሄው ድርጅት ማሸነፉንና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያላጠናቀቀው ሥራ እንደነበር ገልፀው፤ ጭራሽ እነዚህን ቤቶች በአራት ወር (በ120 ቀናት) አንድ ድርጅት በጥራትና በፍጥነት ያጠናቅቃል ማለት ዘበት ነው ብለዋል፡፡
የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በአራት ወር አልሙኒየም በሮች ከነመስታወታቸው ተገጥመው እንዲጠናቀቁለት ጨረታ ያወጣባቸው ሦስት ሳይቶች ሲሆኑ፤ እነዚህም ሳይት አንድ ቦሌ ቡልቡላ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ሳይት 15 ባለ 15 ወለል (G+15)  ቤቶች፣ በሳይት ሁለት ቦሌ በሻሌ 22 ባለ 15 (G+15)፣  15 ባለ 13 ወለል (G+13)፣ 21 ባለ 9 ወለል (G+9) ቤቶች፣ በሳይት ሦስት ደግሞ ቦሌ አያት፡- 16 ባለ 15 ወለል (G+15)፣   34 ባለ 13 ወለል (G+13)፣ 10 ባለ 8 ወለል (G+8) ቤቶች ሲሆኑ እነዚህን ብሎኮች በ120 ቀናት የአልሙኒየም በር ከነመስታወቱ ለመግጠም አልሙኒየሙ በካሬ ተባዝቶ፣ ለ120 ቀናት ሲካፈል ድርጅቱ በቀን 3637 ካሬ ሜትር አልሙኒየም መስራት እንዳለበት የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ በህልምም በእውንም የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ጠንካራ የሚባል ድርጅት በቀን ከ30 ካ.ሜ በላይ አልሙኒየም ቆርጦ አስተካክሎ፣ መስታወት ገጥሞና ሠርቶ ማጠናቀቅ እንደማይችል የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይሄ በቤት ችግር እየተሰቃየ መቶ ፐርሰንት ከፍሎ በጉጉት ለሚጠብቀው ህዝብ ተጨማሪ መዘግየትን እንደሚፈጥር ገልፀው፤ ኢንተርፕራይዙ እነዚህን ሕገ-ወጥ አሰራሮች በጥሞና ተመልክቶ፣ የጨረታ ሠነዱን እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡ ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነም መብታቸውን በህግ እንደሚያስከብሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡  
የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ኃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተደጋጋሚ ቢሮአቸው ብንመላለስም ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ የሚሰጥ ባለመገኘቱ የኢንተርፕራይዙን ሀሳብ ማካተት አልቻልንም፡፡

በጦርነትና የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ አደገኛና አስቸጋሪ ህይወት እየገፉ የሚገኙ የአለማችን ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ከ357 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ሴቭ ዘ ችልድረን ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዓለማቀፍ ሪፖርት ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡
በጦርነትና በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ ከሚገኙት የአለማችን ህጻናት፣ ግማሽ ያህሉ ወይም 165 ሚሊዮን የሚደርሱት ከፍተኛ ግጭት በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ውስጥ እንደሚኖሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ህጻናት ለዚህ ችግር በመጋለጥ ረገድ ቀዳሚነቱን እንደሚይዙና አፍሪካውያን ህጻናት እንደሚከተሉ በመግለጽ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከሚኖሩ አምስት ህጻናት፣ ሁለቱ ግጭት ወይም ጦርነት በሚከናወንበት አካባቢ በ50 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ እንደሚኖሩ አመልክቷል፡፡
በርካታ ህጻናት በጦርነትና በግጭት ቀጠናዎች ውስጥ እንደሚገኙባቸውና ለህጻናት እጅግ አደገኛ ናቸው ተብለው በሪፖርቱ ከተጠቀሱት የአለማችን አገራት መካከል ሶሪያ ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ አፍጋኒስታንና ሶማሊያ በተከታታይነት ተቀምጠዋል፡፡
በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የማቁሰል ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ እንደመጡ የዘገበው ዘ ኢንዴፔንደንት፤ የተባበሩት መንግስታት በማስረጃ አስደግፎ የሚመዘግባቸው መሰል ጥቃቶች ቁጥር ባለፉት ሰባት አመታት ውስጥ በ3 እጥፍ ማደጉንም አስታውሷል፡፡
በግጭቶችና በጦርነቶች ሳቢያ ከመኖሪያ አካባቢያቸው እየተፈናቀሉ ለተለያዩ ስቃዮችና እንግልቶች የሚዳረጉ የአለማችን ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ከ65 ሚሊዮን በላይ የዓለማችን ህጻናት ምንም አይነት ቋሚ የመኖሪያ ቤት እንደሌላቸው አመልክቷል፡፡

   የአገሪቱ መሪ፤ ሚኒስትሮች ከባልደረቦቻቸው ጋር ፍቅር እንዳይጀምሩ አስጠንቅቀዋል

   ከሰሞኑ ይፋ ከተደረገባቸው የወሲብ ቅሌት መረጃ ጋር በተያያዘ፣ አገራዊ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆኑት የአውስትራሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ፤ የፓርቲ መሪነትና የሚኒስትርነት ስልጣናቸውን ይለቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተዘገበ ሲሆን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልኮም ተርንቡልም፤ ሚኒስትሮች ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመው ከተገኙ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ፣ በቅርቡ የ24 አመት ትዳራቸውን በማፍረስ፣ የስራ ባልደረባቸው ከሆነች አንዲት ሴት ጋር በፈጠሩት የድብቅ የፍቅር ግንኙነት፣ ሴትየዋን ማስረገዛቸውን የሚያጋልጥ የወሲብ ቅሌት መረጃ ከሰሞኑ ይፋ መደረጉንና ጉዳዩ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ መሆኑን የዘገበው ዘ ቴሌግራፍ፤ ይህን ተከትሎም የአገሪቱ ፓርላማ ከትናንት በስቲያ ባደረገው ስብሰባ፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተከስተዋል ያላቸውን ሌሎች ተጨማሪ የሙስና ድርጊቶችን በመመርመር፣ ሚኒስትሩ ከስነምግባር ውጭ የሆነና ክብርን የሚያጎድፍ ጸያፍ ተግባር በመፈጸማቸው፣ በፈቃዳቸው ስራቸውን እንዲለቅቁ ወይም እንዲባረሩ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን አመልክቷል፡፡
“በምክትል ሚኒስትሩ ድርጊት እጅግ አዝኛለሁ፤ ይሄም ሆኖ ግን ከአሁን በኋላ ባለትዳርም ሆነ ወንደላጤ ማንኛውም ሚኒስትር፣ የስራ ባልደረባው ከሆነች ሴት ጋር በፍጹም የፍቅር ግንኙነት መመስረትም ሆነ አንሶላ መጋፈፍ አይችልም” ሲሉ በይፋ ያስጠነቀቁት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልኮም ተርንቡል፤ ድርጊቱ በቀጣይም እንደ አንድ ከባድ የስልጣን ብልግና ወይም የሙስና ወንጀል ተወስዶ እንደሚያስቀጣም አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን በአገሪቱ የሚኒስትሮች ስነምግባር ደንብ ውስጥ ከስራ ባልደረባቸው ጋር የፍቅር ግንኙነት በሚጀምሩም ሆነ በሚያማግጡ ሚኒስትሮች ዙሪያ የሚያትት ምንም አይነት አንቀጽ ባይኖርም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከአሁን በኋላ መሰል ድርጊት የፈጸመ ሚኒስትር፤ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቀው በማስጠንቀቅ፣ ድርጊቱን በግልጽ የሚያወግዙና ተገቢ ቅጣት የሚጥሉ ህጎችና መመሪያዎች በቀጣይ ወጥተው፣ ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተናግረዋል፡፡
24 አመታትን በትዳር አብረዋት ከዘለቋት ባለቤታቸው፣ አራት ሴት ልጆችን ያፈሩት የ50 አመቱ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የስራ ባልደረባቸው ከሆነች ሌላ ሴት ጋር በድብቅ እፍ ክንፍ ማለታቸውና ማስረገዛቸው ባለፈው ሳምንት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ የአገሪቱን ፖለቲካ ፓርቲዎችም ጨምሮ በርካታ ዜጎችን እያነጋገረ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡  

 ለወራት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ብዙ ሲወራለት የቆየው አዲሱ የሳምሰንግ ስማርት ፎን ምርት ጋላክሲ ኤስ9 በመጪው ሳምንት በባርሴሎና በሚካሄደው አለማቀፍ የሞባይል ትርዒት ላይ በይፋ ተመርቆ በገበያ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲሱ ጋላክሲ ኤስ9 የመሸጫ ዋጋው 739 ፓውንድ ያህል እንደሚሆን የዘገበው ቴክራዳር ድረገጽ፣ ሞባይሉ 6 ጊጋ ባይት ራም እንዳለውና 64 ጊጋ ባይት መረጃ መያዝ እንደሚችል እንዲሁም ባለ 12 ሜጋፒክስል ሁለት ካሜራዎች እንደተገጠሙለት አመልክቷል፡፡
ውሃንና ቆሻሻን የመከላከል አቅሙ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ የተነገረለት ኤስ9 ያለ ገመድ ቻርጅ መደረግ የሚችል እንደሆነም ዘገባው አስረድቷል፡፡
ኩባንያው ሞባይሉ በይፋ በተመረቀ በቀናት እድሜ ውስጥ ከደንበኞች የግዢ ትዕዛዝ መቀበል እንደሚጀምርና በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ ምረቱን ለገዢዎች የማድረስ ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  በአፍጋኒስታን ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 በተካሄዱ ብጥብጦች፣ ከ10 ሺህ በላይ በሚሆኑ የአገሪቱ ንጹሃን ዜጎች ላይ የግድያ ወይም የመቁሰል አደጋ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአፍጋኒስታን በአመቱ 3 ሺህ 438 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን የጠቆመው ተመድ፤7 ሺህ 15 ያህል የሚሆኑትም ለመቁሰል አደጋ መዳረጋቸውን ያመለከተ ሲሆን በዜጎች ላይ ከተፈጸሙት ግድያዎች ወይም የማቁሰል ድርጊቶች መካከል ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት የተፈጸሙት በጸረ-መንግስት ሃይሎች በተደረጉ የቦንብ ጥቃቶች መሆኑንም አመልክቷል፡፡ በአመቱ በአፍጋኒስታን ንጹሃን ዜጎች ላይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች መካከል ታሊባን 42 በመቶ፣ አይሲስ 10 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው ያስታወሰው መግለጫው፤ በአሜሪካ የአየር ድብደባዎች ለሞትና ለመቁሰል አደጋ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥርም እያደገ ነው ብሏል፡፡
በ2017 የፈረንጆች አመት አፍጋኒስታናውያን ህጻናትና ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው፤በአመቱ 359 ሴቶች መገደላቸውንና 865 ሴቶች ደግሞ መቁሰላቸውን፤ 861 ህጻናት መገደላቸውንና 2 ሺህ 318 መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡

የደን ሽፋንን በተፋጠነ የዛፍ ተከላ በማሳደግ፣ የአየር ብክለትን ለመዋጋት ቆርጦ የተነሳው የቻይና መንግስት፤ ከስራ ገበታቸው ተሰናብተው የነበሩ 60 ሺህ ወታደሮችን መልሶ በመቅጠር በችግኝ ተከላ ስራ ላይ ሊያሰማራ ማቀዱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት በመደበኛ ውትድርና ሙያ ላይ ያገለግሉ የነበሩና ከስራ ገበታቸው የተሰናበቱት እነዚህ ወታደሮች፤ የቻይና መንግስት በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች ሊያከናውናቸው ባቀዳቸው ሰፋፊ የደን ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ በችግን ተከላ ስራ ላይ እንደሚሰማሩ የጠቆመው ዘገባው፤በተለይም የኢንዱስትሪ ጭሶችን በብዛት በማውጣት ከፍተኛ የአየር ብክለትን በሚያስከትሉ አካባቢዎች ብዛት ያላቸው ዛፎችን ለመትከል መታቀዱን አመልክቷል።
ቻይና በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ብቻ 84 ስኩየር ኪሎ ሜትር በሚሸፍን ቦታ ላይ በርካታ ዛፎችን የመትከል እቅድ ይዛ በስፋት እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ በደን ይሸፈናል ተብሎ የታቀደው ቦታ ስፋት ከአየርላንድ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን አስረድቷል።
 አገሪቱ የደን ሽፋኗን አሁን ከሚገኝበት 21 በመቶ፣ በመጪዎቹ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ ወደ 23 በመቶ ከፍ ለማድረግ ማቀዷንና የደን ሽፋኑ እ.ኤ.አ እስከ 2035 ድረስ 26 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡