Administrator

Administrator

  በጀርመኑ የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) እና ሲኤንኤፍኤ በተሰኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት እገዛ በአርሲ ዞን ሁሩታና ሳጉሬ ወረዳዎች፣ከ60 ሺ ዩሮ በላይ በሆነ ወጪ፣ ዘመናዊ የግብርና ግብአቶች ማስፋፊያ ማዕከላት ተገነቡ፡፡
ሰሞኑን የተመረቁት እነዚህ የግብርና ማዕከላት፣ ዘመናዊና ጥራት ያላቸው የሰብል ዘሮችን፣ የአረም መከላከያ መድሐኒቶችና የእንስሳት ህክምና ምርቶችን በሰለጠኑ ሠራተኞችና በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ለአርሶ አደሮች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
ማዕከላቱን የተራድኦ ድርጅቶችና የአካባቢው ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች በእኩል መዋጮ ያስገነቧቸው ሲሆን ከአገልግሎት ሽያጭ የሚሰበሰበው ገቢም ለወጣቶቹ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡ አንድ ማዕከል ለ25 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች እንደሚያገለግል የተጠቆመ ሲሆን ማዕከላቱ ግብአቶችን ከማቅረብ ጐን ለጐን፣ለአርሶ አደሮች የምክርና ስልጠና አገልግሎት እንደሚሰጡ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጧል፡፡    

 የ“ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ የሽፋን ፎቶ በ400 ሺህ ብር ተሽጧል

    በቅርቡ በገበያ ላይ የዋለው “እስኪ ልየው” የተሰኘው የድምጻዊት ሄለን በርሄ የሙዚቃ አልበም ባለፈው ሳምንት አርብ ምሽት በማማስ ኪችን በተከናወነ ልዩ ፕሮግራም የተመረቀ ሲሆን፣ በእለቱ በይፋ ተመርቆ ለእይታ የበቃውና በአልበሙ ውስጥ ከተካተቱት 14 ሙዚቃዎች አንዱ የሆነው የ“ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ ፎቶ ግራፍ ለጨረታ ቀርቦ በ400 ሺህ ብር ተሽጧል፡፡
ኡቡንቱ አርት ማኔጅመንት እና ንጉስ ኢንተርቴንመንት በጋራ ያዘጋጁትና የካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ምሽት ወሎ ሰፈር በሚገኘው ማማስ ኪችን በተከናወነው የአልበሙ የምረቃ ፕሮግራም ላይ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የድምጻዊቷ አድናቂዎችና ተጋባዥ እንግዶች የታደሙ ሲሆን፣ ድምጻዊቷ አዳዲስና ቆየት ያሉ ተወዳጅ ሙዚቃዎቿን በአስገራሚ ብቃት በማቀንቀን ታዳሚውን ስታዝናና አምሽታለች፡፡
ድምጻዊት ሄለን በርሄ፣ በአዲሱ አልበም ውስጥ የተካተተውን የኔ ቆንጆ የተሰኘ ተወዳጅ ዜማ ያበረከቱላትን ታዋቂውን የዜማ ደራሲና የማንዶሊን ተጫዋች አቶ አየለ ማሞን ጨምሮ ለአልበሙም ሆነ ለሙዚቃ ክሊፑ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን በተደጋጋሚ ስታመሰግን አምሽታለች፡፡
ምነው ሸዋ ኢንተርቴንመንት ፕሮዲዩስ ያደረገውና 350 ሺህ ብር ያህል ወጪ እንደተደረገበት የተነገረለት እንዲሁም ከ50 በላይ ተዋንያን የተሳተፉበት “ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ በምሽቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ለእይታ በበቃበት ቅጽበት፣ በዩቲዩብ ድረገጽ የተለቀቀ ሲሆን፣ የፕሮግራሙ ታዳሚያን አድናቆታቸውን በሚገርም ሁኔታ ሲገልጹ ተስተውለዋል፤ በዩቲዩብም ብዙ ተመልካቾች እያዩት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የ“ፊታውራሪ” የሙዚቃ ክሊፕ የሽፋን ፎቶ ግራፍ በምሽቱ ለጨረታ የቀረበ ሲሆን፣ የድምጻዊቷ አድናቂዎችና በዝግጅቱ ላይ የታደሙ የሙዚቃ አፍቃሪያን ፎቶግራፉን በእጃቸው ለማስገባት ረጅም ፉክክር ካደረጉ በኋላ፣ በስተመጨረሻም 400 ሺህ ብር ያቀረቡት የማማስ ኪችን ባለቤት ጨረታውን አሸንፈዋል፡፡
በአልበሙ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ጸደኒያ ገብረ ማርቆስ፣ ጌትሽ ማሞ፣ ዳግማዊት ጸሃዬና አስገኘው አሽኮ (ዴንዳሾ)ን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ ድምጻውያን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚያን አቅርበዋል፡፡

 “የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሕያው መሆን አለበት”

     የክራርና የዋሽንት መምህርና የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ መስራች የነበሩት አርቲስት መላኩ ገላው በሰማንያ ዓመት ዕድሜያቸው አሜሪካ ውስጥ አርሊንግተን - ቨርጂንያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አርፈዋል።
አርቲስት መላኩ ገላው በጣልያን የወረራ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 1929ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ገላው ተክሌና ከእናታቸው ከእማሆይ ትኩነሽ ተሰማ በላስታ ላሊበላ ተወለዱ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የተፀነሰው የሙዚቃ መሳሪያ የመጫወት ፍቅር ከልጅነት ባለፈ በ1956 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲና የኦርኬስትራ ኢትዮጵያን በመቀላቀል በክራርና በዋሽንት ተጫዋችነት፣ ከዚያም ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በሁለቱም ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በመምህርነት ከ28 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
በተለይ በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ከተስፋዬ ለማ፤ ከአሜሪካዊው መሲንቆ ተጫዋች ቻርለስ ሳተን እና ከአርቲስት ጌታ መሳይ አበበ ጋር በመሆን የባህል አምባሰደርነታቸውን በዓለም ለማስመስከር ችለዋል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትም የባህል የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት በማይበረታታበት ጊዜ የራሳቸውን የማስተማር ልምድ በመጠቀም ትምህርቱን መስጠት እንደጀመሩና መሰረት እንደጣሉ ተማሪዎቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ ታላላቅ የሚባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎችን እንደ ጥላሁን ገሠሠ፤ ብዙነሽ በቀለ፤ ሂሩት በቀለንና ሌሎች አንጋፋ ድምፃውያንን በዋሽንትና በክራር በማጀብ የሙያ ድርሻቸውን የተወጡ ባለሙያ ነበሩ፡፡ ለአርቲስት ጌታ መሳይ አበበም “የሽምብራው ጥርጥር” የሚለውን የሙዚቃ ድርሰት በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባውን የአገው ባህላዊ ሙዚቃንም በልዩ መልክ በማጀብ የዋሽንት ችሎታቸውንም አስመስክረዋል፡፡
ኑሯቸውን በአሜሪካ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ በግላቸው በርካቶችን ክራር በማስተማር የቆዩ ሲሆን በአቶ ተስፋዬ ለማ በተቋቋመው ሙዚየም ውስጥ የባህል ሙዚቃ መሳሪያዎችን በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ከማበርከታቸውም በተጨማሪ ከቀድሞ የሙዚቃ አጋሮቻቸው ከተስፋዬ ለማ፤ ቻርለስ ሳተን እና ጌታ መሳይ አበበ ጋር በመሆን “ዞሮ ገጠም” የሚል ሙዚቃን በመስራት ለባህል ሙዚቃ ህዳሴ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 ለባህል የሙዚቃ መሳሪያ ዕድገት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የፊደል ዕድሜ ዘመን ተሸላሚ ክብርን አግኝተዋል፡፡ “የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ሕያው መሆን አለበት” የሚለውን ጽኑ አቋማቸውን ህይወታቸው እስካለፈችበት ጊዜ ድረስ ሌሎችን በማስተማርና በተለይም ሙያውን ለልጆቻቸው በማውረስ ታላቅ ታሪክ የሰሩ የባህል ሙዚቃ አምባሳደር ሆነው አልፈዋል፡፡
አርቲስት መላኩ ገላው ባለትዳርና የ7 ልጆች አባት ሲሆኑ 12 የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 3 ቀን 2010 ዓ.ም በአርሊንግተን ቨርጂኒያ ቤታቸው በ80 ዓመት ዕድሜያቸው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አስክሬናቸውም በመጪው እሁድ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚሸኝ ሲሆን ቀብራቸውም የፊታችን ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010ዓ.ም በፈረንሳይ ደብረ ፀሀይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከቀኑ በ9ሰዓት እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቻቸው የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡

  “አዝማሪና ውሃ ሙላት” በተሰኘው የደራሲ ከበደ ሚካኤል ግጥም ውስጥ የምናቃቸው ዝነኛ መስመሮች ለዛሬ የመረጥናቸው ናቸው፡፡

        አዝማሪና ውሃ ሙላት
        አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
        የወንዝ ውሃ ሞልቶ
                ደፍርሶ ሲወርድ
        እዚያው እወንዙ ዳር
                እያለ ጐርደድ
        አንድ አዝማሪ አገኘ
                ሲዘፍን አምርሮ
        በሚያሳዝን ዜማ
            ድምፁን አሳምሮ፡፡
        “ምነው አቶ አዝማሪ
        ምን ትሠራለህ?”
        ብሎ ቢጠይቀው፤
        “ምን ሁን ትላለህ፣
        አላሻግር ብሎኝ
        የውሃ ሙላት
        እያሞጋገስኩት
        በግጥም ብዛት
        ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ”
        “አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
        ነገሩስ ባልከፋ
        ውሃውን ማወደስ
        ግን እንደዚህ ፈጥኖ
        በችኮላ ሲፈስ
        ምን ይሰማኝ ብለህ
        ትደክማለህ ከቶ
        ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
        እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ
        ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”

        ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
        መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
በተደጋጋሚ ሀገራችን ባለፈችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ የተገነዘብነው ዋና ነገር ገዢው “ያቀድኩትን ልተግብርበት እረፉ”፤ ሲል፤ ተገዢው “ኧረ ይሄ ነገር አልተሟላልኝም እያለ ሲያማርር፤ በመሀል ውዱ ጊዜ ማለፉ ነው፡፡ የጠፋው ጊዜ ከሰነበትን በኋላ ተመልሶ መፀፀቻችን ይሆናል፡፡ የተወሳሰበው ችግር መፍትሄ ማግኘት ቀርቶ የባሰ የተወሳሰበ ሆኖ ይገኛል፡፡ የባሰ ምስቅልቅሉ ይወጣል፡፡ መፍትሄ መስጠት ያለባቸው አካላት የውስጥም የውጪም ግፊትና ውጥረት ስላለባቸው፤ ሌሎች ችግሮችን ማስተናገድ አልሆነላቸውም። ቢወተወቱ አያዳምጡም፡፡ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም” የሚለው ተረት የበለጠ ይገልፀዋል፡፡ ለማደግም ሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው መደማመጥ ነው። ሁሉንም ነገር ዐይኔን ግንባር ያድርገው ብለን አንችለውም፡፡ ካለመደማመጥ በተጨማሪ የሚደረገውንም ሆነ የተደረገውን አላውቅም፤ ማለትና መስማትም ማየትም እምቢ ካልን፣ ጉዟችን የዕውር የድንብር ይሆናል፡፡
ጊዜ እየረፈደ ከመጣ በኋላ ሁኔታውን ለመቀልበስ ብንሞክር ፍሬ-አልባ ሙከራ ይሆናል። ዛሬም ዐይናችንን ከፍተን ቆም ብለን እናስብ፡፡ ውጥረት ውስጥ ከመግባታችን በፊት የውጥረቱን መፈጠሪያ ቧንቧዎች እንዝጋ፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን እናዳምጥ። ሀገራችን ከእንግዲህ ተጨማሪ ችግር የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም፡፡ ካልተጠነቀቅን ሀገርም እንደ ሰው ተሰባሪ ናት፡፡ የ1966ን አብዮት አንርሳ፡፡ ገዢዎች መግዛት ሲያቅታቸው፣ ተገዢዎች አንገዛም ሲሉ፣ ሀገር ለአብዮት የበሰለ ሁኔታ ላይ እንደደረሰች አንዘንጋ፡፡ ሲመሽ ጉሮሮ ለጉሮሮ ከመተናነቅ፣ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር ነው፤ ወደ መፍትሄው የሚያስጠጋን። እስከ መቼ “ዴሞክራሲያችን ለጋ ስለሆነ ነው” እያልን ምክንያት እንሰማለን? እስከ መቼ “የመልካም አስተዳደር ችግር ነው” እያልን እንዘልቀዋለን? እስከ መቼስ “የፍትህ ሰጪ አካላት የአፈፃፀም ችግር አለ” እያልን እንጓዛለን? የድህነት ችግርስ እስከመቼ ነው ቁልፍ ነው እየተባለ የምንቀጥለው? ከሃያ በላይ ዓመታት ተጉዘን፣ ምንም ለውጥ አለማምጣታችን፣ የሚያሳፍረን ጊዜ አይመጣምን? ዛሬም መብራት ይጠፋል፡፡ ዛሬም ውሃ ይጠፋል፡፡ ዛሬም ኔትዎርክ ይቸግራል፡፡ ዛሬም ኑሮ አዘቅት ውስጥ እየከተተን ነው፡፡ እነዚህ የብሶትና የምሬት ምንጮች እስከ መቼ እንደተጫኑብን ይኖራሉ? እናስብ! ምንጣፉ ከእግራችን ስር ተስቦ እስኪወሰድ አንጠብቅ! “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” ከአርባ ዓመት በኋላ መድገም አሳፋሪ ይሆናል፡፡ “ፋታ ስጡኝ”  ለማለትም ጊዜ የለም! የነካነው ሁሉ ወርቅ ይሆናል ብለን እንደ ሚዳስ አስማት (Midas Touch) የምናስብበት ጊዜ አልፏል፡፡
“እስቲ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”
የሚለውን ዛሬም ማስተዋል ይበጃል፡፡ መልካም ጊዜ ይመጣ ዘንድ ሁላችንም እንመኛለን!   

የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አለመሻሻል
የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መሻሻል ከማሳየት ይልቅ የበለጠ እየተበላሸ መጥቷል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ለረጅም ጊዜ ችግሮች ተገቢውንና ቀጣይነት ያለው መልስ ያለማግኘታቸው ያመጣው ድምር ውጤት ነው፡፡ ማህበረሰቡ በተለያየ መንገድ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችም አሉት፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ አፋጣኝ መልስ ያለማግኘት፣ ትኩረት ማጣት፣ በቂ ክትትል አለመኖር አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች እርባና ቢስ እንደሆኑ ተደርጐ መቆጠሩ ማህበረሰቡ መጨረሻ ላይ በራሱ መንገድ መፍትሄ እንዲፈልግ ነው ያስገደደው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መገለጫው፣ ማህበረሰቡ በዚህ መልኩ የራሱን ጥያቄ አንግቦ ጐዳና ወጥቶ፣ መንግሥትን በቀጥታ መታገል ሳይገባው፣ በወኪሎቹ በኩል የሚታገልበትና ጥያቄዎቹን የሚያቀርብበት መንገድ ነው፡፡ ይሄ አሁን በኢትዮጵያ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት ተቃውሞ መሪ የለውም፡፡ የተደራጀ ጥያቄ የለውም፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ለመቆጣጠር የተወሳሰበና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ እያየን ያለነውም ይሄንን ነው፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ለችግሮቹ ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ያለው ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ብቻ በማስቀመጥ ነው፡፡ አግባብ ያለው መልስ እየሰጠ አይደለም፡፡ ስር ነቀል ለውጥ አካሂዶ ጥያቄዎቹን በዘላቂነት የመመለስ ስራ አይደለም እየተከናወነ ያለው፡፡ ዝም ብሎ እግር በእግር እየተከታተለ ነው፣ ትንንሽ መልሶችን  ለመስጠት እየሞከረ ያለው፡፡ ይሄ ህዝቡን አያረካም፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ አሁን ተጨባጭና ቀጥተኛ ምላሽ ነው የፈለገው፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ዛሬውኑ መልሱን አምጣ ነው እያለ ያለው፡፡ ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ ላሉት የፖለቲካ ጥያቄዎች ትእግስት ነበረው፤ ምክንያቱም ሀሳብን በነፃነት መግለፅ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት፣ የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ለአብዛኛው ህዝብ የልሂቃኑ ጥያቄ መስሎ ነበር የሚታየው፡፡ በዚህ ምክንያት ማህበረሰቡ ህይወቱን እስከ መሰዋት ሊሄድ አይችልም ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ሲከማቹ የቆዩት ችግሮችና ጥያቄዎች፣ አግባብ ያለው አፈታት ባለማግኘታቸው፣ ማህበረሰቡ ታግሶ ታግሶ፣ የራሱን አማራጭ ሊወስድ ችሏል፡፡ የተጠራቀሙ ጭቆናዎችና ፍረጃዎች ናቸው ለዚህ ያበቁት፡፡

ብሄር ተኮር ጥቃቶች   
ከብሄር ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ውዝግቦች ለረጅም ጊዜያት ህብረተሰቡ ውስጥ ሲብላሉ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ከመብላላት አልፈው ዋነኛ ችግር ሆነዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚች አገር፣ አንዱ ብሄር አንዱን እንዲያጠቃው የሚፈቅድ ማህበረሰብ ፈፅሞ የለም፡፡ በሌላ በኩል፣ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ይሄ የብሄር ጉዳይ ያልተነሳበትና ያለመግባባት መንስኤ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ በወቅቱ አግባብ ያለው ውይይት ተደርጐ መልስ ቢሰጠው ኖሮ፣ ዛሬ ተመልሶ አይከሰትም  ነበር፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው፣ አስቀድሞ መተግበር ነበረበት፡፡ በወቅቱ እነዚህ ነገሮች ባለመታከማቸው ዛሬ ላይ ፈጠው ወጥተዋል፡፡ ከዚህ ችግር  ለመውጣት አሁንም ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ሁነኛ የግጭት አፈታት ስልት መነደፍ አለበት፡፡ እርግጥ ነው ከህዝባችን ታሪክ ስንነሳ፣ የብሄር ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ግጭቶች ሲኖሩም፣ ከድንበርና ከግጦሽ መሬት የባለቤትነት ጥያቄ አያልፍም፡፡ አሁን ግን ትንሽ ነገሮች የተቀየሩ ይመስላል፡፡
 ባለፉት 27 ዓመታትም አንዱ አንዱን ሲጨቁን፣ ሲበድል፣ ሲበዘብዝ እንደነበር ነው ሲተረክ የተኖረው። አንዱ አንዱን በጥርጣሬና በጥላቻ እንዲያይ ተደርጐ ነው፣ የማህበረሰቡ ቀደምት ግንኙነቶች ሲተረኩ የኖሩት፡፡ ታዲያ ከዚህ ተረክ ምን በጐ ፍሬ ነው የሚጠበቀው፡፡ ማህበረሰቡ “እገሌ ሀብትህን ሲበዘብዝ ነበር” ሲባል ነው የኖረው። በዚህ የተነሳ  አንዱ በሌላው የአገሪቱ ክፍል ሰርቶ ሲኖር፣ እንደ ሀብት በዝባዥ ነው የሚታየው። ንብረቴን ዘረፉኝ ነው፤ ብሶቱ፡፡ እንግዲህ ካለፉት ዓመታት ተረኮች ያተረፍነው ይሄንን ነው፡፡ ችግሩ የበለጠ አድማሱን ሳያሰፋና የአገሪቱን ህልውና ሳይፈታተን በጊዜ እልባት ማግኘት አለበት፡፡

የፖለቲከኞች መፈታትና ፋይዳው
እነዚህ ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት እስር ቤት የገቡ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች መፈታት በእርግጥም ህዝቡ የበለጠ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡ መንግሥት እነዚህን ሰዎች በመፍታቱ ብቻ ለህዝቡ ጥያቄ በቂ መልስ ሰጥቻለሁ ብሎ ካሰበ በእጅጉ ተሳስቷል፡፡ ምክንያቱም የእስረኞች መፈታት ጉዳይ ከህዝቡ ጥያቄዎች አንዱ እንጂ ዋነኛ ግብና ዓላማ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ማህበረሰቡ እንዲፈቱ ታግሎላቸዋል፡፡ ስለዚህ መፈታታቸው እንደ አንድ ድል ነው የሚቆጠረው፤ ግን የጥያቄዎች ሁሉ መልስ አይሆንም፡፡

የህግ የበላይነትና ሰብአዊ መብት
የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ጥያቄው የህግ የበላይነትን ማስከበር ሲባል በምን መንገድ የሚለው ነው፡፡ የህግ የበላይነትን በሌላ የህግ ጥሰትና ጥፋት ለማስከበር ጥረት የሚደረግ ከሆነ ውጤት አያመጣም፡፡ መንግሥት ደግሞ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲጥር፣ የማህበረሰቡን የህግ ንቃተ ህሊና ማገናዘብ አለበት፡፡ መፍትሄው የህይወት ማጥፋት ሳይሆን አጥፊዎችን በህግ ጥላ ስር ማዋል ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ የበለጠ ጥፋት የሚያስከትል ከሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ችግሮችን የመፍታት አቅም ከሌለው፣ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ህብረት ፈጥሮ መፍታት ነው የሚበጀው፡፡ እስካሁን ይሄን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህ በኋላም ይሄን ለማድረግ ጊዜ አለው፡፡ ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ በመነጋገር፣ ተከታታይ የመትሄ ሀሳቦችን ማመንጨትና ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አለመሻሻል
የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መሻሻል ከማሳየት ይልቅ የበለጠ እየተበላሸ መጥቷል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ለረጅም ጊዜ ችግሮች ተገቢውንና ቀጣይነት ያለው መልስ ያለማግኘታቸው ያመጣው ድምር ውጤት ነው፡፡ ማህበረሰቡ በተለያየ መንገድ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችም አሉት፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ አፋጣኝ መልስ ያለማግኘት፣ ትኩረት ማጣት፣ በቂ ክትትል አለመኖር አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሚነሱ ጥያቄዎች እርባና ቢስ እንደሆኑ ተደርጐ መቆጠሩ ማህበረሰቡ መጨረሻ ላይ በራሱ መንገድ መፍትሄ እንዲፈልግ ነው ያስገደደው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ መገለጫው፣ ማህበረሰቡ በዚህ መልኩ የራሱን ጥያቄ አንግቦ ጐዳና ወጥቶ፣ መንግሥትን በቀጥታ መታገል ሳይገባው፣ በወኪሎቹ በኩል የሚታገልበትና ጥያቄዎቹን የሚያቀርብበት መንገድ ነው፡፡ ይሄ አሁን በኢትዮጵያ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት ተቃውሞ መሪ የለውም፡፡ የተደራጀ ጥያቄ የለውም፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ለመቆጣጠር የተወሳሰበና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ እያየን ያለነውም ይሄንን ነው፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ለችግሮቹ ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ያለው ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ብቻ በማስቀመጥ ነው፡፡ አግባብ ያለው መልስ እየሰጠ አይደለም፡፡ ስር ነቀል ለውጥ አካሂዶ ጥያቄዎቹን በዘላቂነት የመመለስ ስራ አይደለም እየተከናወነ ያለው፡፡ ዝም ብሎ እግር በእግር እየተከታተለ ነው፣ ትንንሽ መልሶችን  ለመስጠት እየሞከረ ያለው፡፡ ይሄ ህዝቡን አያረካም፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ አሁን ተጨባጭና ቀጥተኛ ምላሽ ነው የፈለገው፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ዛሬውኑ መልሱን አምጣ ነው እያለ ያለው፡፡ ከዚህ በፊት ማህበረሰቡ ላሉት የፖለቲካ ጥያቄዎች ትእግስት ነበረው፤ ምክንያቱም ሀሳብን በነፃነት መግለፅ የመደራጀት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት፣ የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ለአብዛኛው ህዝብ የልሂቃኑ ጥያቄ መስሎ ነበር የሚታየው፡፡ በዚህ ምክንያት ማህበረሰቡ ህይወቱን እስከ መሰዋት ሊሄድ አይችልም ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሮች ተቀይረዋል። ሲከማቹ የቆዩት ችግሮችና ጥያቄዎች፣ አግባብ ያለው አፈታት ባለማግኘታቸው፣ ማህበረሰቡ ታግሶ ታግሶ፣ የራሱን አማራጭ ሊወስድ ችሏል፡፡ የተጠራቀሙ ጭቆናዎችና ፍረጃዎች ናቸው ለዚህ ያበቁት፡፡

ብሄር ተኮር ጥቃቶች   
ከብሄር ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ውዝግቦች ለረጅም ጊዜያት ህብረተሰቡ ውስጥ ሲብላሉ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ከመብላላት አልፈው ዋነኛ ችግር ሆነዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚች አገር፣ አንዱ ብሄር አንዱን እንዲያጠቃው የሚፈቅድ ማህበረሰብ ፈፅሞ የለም፡፡ በሌላ በኩል፣ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ይሄ የብሄር ጉዳይ ያልተነሳበትና ያለመግባባት መንስኤ ያልሆነበት ጊዜ የለም፡፡ በወቅቱ አግባብ ያለው ውይይት ተደርጐ መልስ ቢሰጠው ኖሮ፣ ዛሬ ተመልሶ አይከሰትም  ነበር፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው፣ አስቀድሞ መተግበር ነበረበት፡፡ በወቅቱ እነዚህ ነገሮች ባለመታከማቸው ዛሬ ላይ ፈጠው ወጥተዋል፡፡ ከዚህ ችግር  ለመውጣት አሁንም ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ሁነኛ የግጭት አፈታት ስልት መነደፍ አለበት፡፡ እርግጥ ነው ከህዝባችን ታሪክ ስንነሳ፣ የብሄር ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ግጭቶች ሲኖሩም፣ ከድንበርና ከግጦሽ መሬት የባለቤትነት ጥያቄ አያልፍም፡፡ አሁን ግን ትንሽ ነገሮች የተቀየሩ ይመስላል፡፡
 ባለፉት 27 ዓመታትም አንዱ አንዱን ሲጨቁን፣ ሲበድል፣ ሲበዘብዝ እንደነበር ነው ሲተረክ የተኖረው። አንዱ አንዱን በጥርጣሬና በጥላቻ እንዲያይ ተደርጐ ነው፣ የማህበረሰቡ ቀደምት ግንኙነቶች ሲተረኩ የኖሩት፡፡ ታዲያ ከዚህ ተረክ ምን በጐ ፍሬ ነው የሚጠበቀው፡፡ ማህበረሰቡ “እገሌ ሀብትህን ሲበዘብዝ ነበር” ሲባል ነው የኖረው። በዚህ የተነሳ  አንዱ በሌላው የአገሪቱ ክፍል ሰርቶ ሲኖር፣ እንደ ሀብት በዝባዥ ነው የሚታየው። ንብረቴን ዘረፉኝ ነው፤ ብሶቱ፡፡ እንግዲህ ካለፉት ዓመታት ተረኮች ያተረፍነው ይሄንን ነው፡፡ ችግሩ የበለጠ አድማሱን ሳያሰፋና የአገሪቱን ህልውና ሳይፈታተን በጊዜ እልባት ማግኘት አለበት፡፡

የፖለቲከኞች መፈታትና ፋይዳው
እነዚህ ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት እስር ቤት የገቡ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች መፈታት በእርግጥም ህዝቡ የበለጠ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡ መንግሥት እነዚህን ሰዎች በመፍታቱ ብቻ ለህዝቡ ጥያቄ በቂ መልስ ሰጥቻለሁ ብሎ ካሰበ በእጅጉ ተሳስቷል፡፡ ምክንያቱም የእስረኞች መፈታት ጉዳይ ከህዝቡ ጥያቄዎች አንዱ እንጂ ዋነኛ ግብና ዓላማ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ማህበረሰቡ እንዲፈቱ ታግሎላቸዋል፡፡ ስለዚህ መፈታታቸው እንደ አንድ ድል ነው የሚቆጠረው፤ ግን የጥያቄዎች ሁሉ መልስ አይሆንም፡፡

የህግ የበላይነትና ሰብአዊ መብት
የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ ሃላፊነት ነው፡፡ ጥያቄው የህግ የበላይነትን ማስከበር ሲባል በምን መንገድ የሚለው ነው፡፡ የህግ የበላይነትን በሌላ የህግ ጥሰትና ጥፋት ለማስከበር ጥረት የሚደረግ ከሆነ ውጤት አያመጣም፡፡ መንግሥት ደግሞ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲጥር፣ የማህበረሰቡን የህግ ንቃተ ህሊና ማገናዘብ አለበት፡፡ መፍትሄው የህይወት ማጥፋት ሳይሆን አጥፊዎችን በህግ ጥላ ስር ማዋል ነው፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ የበለጠ ጥፋት የሚያስከትል ከሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ችግሮችን የመፍታት አቅም ከሌለው፣ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ህብረት ፈጥሮ መፍታት ነው የሚበጀው፡፡ እስካሁን ይሄን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህ በኋላም ይሄን ለማድረግ ጊዜ አለው፡፡ ወደ ህብረተሰቡ ቀርቦ በመነጋገር፣ ተከታታይ የመትሄ ሀሳቦችን ማመንጨትና ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡

 119 እስረኞች ክሳቸው ተቋረጠ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣ ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞና ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ፅጌ ይገኙበታል

     የሚኒስትሮች ም/ቤት ከትላንትናው እለት ጀምሮ የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን ለ6 ወራት እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው በህዝባዊ አመፅና አድማ፣ የመንግሥትና የግል ንብረቶች ውድመትና የሰው ህይወት መጥፋትን ለማስቀረት ነው ተብሏል፡፡ አዋጁ ከ15 ቀናት በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል 119 እስረኞች በትላንትናው እለት ክሳቸው የተቋረጠ ሲሆን 56 የግንቦት 7 አባላት ተብለው የተጠረጠሩ እንዲሁም 41 የኦነግ አባላት ተብለው የተጠረጠሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉት መካከል ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ፣ ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞና ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ፅጌ ይገኙበታል፡፡

 የፊፋ ዓለም ዋንጫው ከ50 በላይ ሀገራትን ሲያካልል ወደ ኢትዮጵያ በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ በኮካ ኮላ ኩባንያ አማካኝነት መምጣቱ ለስፖርት አፍቃሪው ትልቅ ክብር ነው፡፡ የታላቁ የስፖርት መድረክ አካል የመሆን እድልን ይፈጥራል፡፡ ለአሸናፊ የሚበረከት ዋንጫ በቅርበት ለማየት መቻል በህይወት አንዴ የሚመጣ እድል ነው።   በኢትዮጵና በአፍሪካ ቀንድ የኮካ ኮላ ብራንድ ማናጀር የሆኑት ወ/ት ትዕግስት ጌቱ “የዓለም ዋንጫውን ወደ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ማምጣት በመቻላችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግር ኳስ ስፖርት ላለው የማይሞት ፍቅር የሰጠነውን እውቅናና ክብር የሚያሳይ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ “እግር ኳስ በባህል፣ በሀይማኖት እና ፖለቲካ ሳይገደብ ህዝቦችን አንድ የማድረግ ሀይል አለው፡፡ ኮካ ኮላ ይህንን የፊፋን አለም ዋንጫ የመመልከት የተለየ አጋጣሚ ለኢትዮጵያውን መፍጠሩ ትልቅ ስኬት ነውም” ብለዋል፡፡ ኮካ ኮላ በዓለም ግዙፉ የመጠጥ ካምፓኒ ሲሆን ወደ 500 የሚደርሱ የተለያዩ የመጠጥ ብራንዶችን ከ200 ሀገራተ በላይ ለሚገኙ ለደንበኞቹ ያደርሳል፡፡ ከሁለት መቶ በላይ የሆኑ ሀገራት የሚገኙ ተጠቃሚዎቻችንን በቀን በ1.7 ቢሊዮን መስተንግዶዎች በማዝናናት ላይ ይገኛል፡፡
ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ሊሚትድ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ስለ ዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ጉብኝት መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የእግረ ኳስ አፍቃሪዎች ተወዳጁ ዋንጫ ወደ ሀገሪቱ በሚመጣ ወቅት ለመመልከት የሚችሉባቸውን የለተያዩ እድሎች ያመለከተ መግለጫ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ከሱዳን ቆይታው በኋላ ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ የካቲት 17 ቅዳሜ ጠዋት ሲደርስ አዲስ አበባ ኤርፖርት ታላላቅ ባለስልጣናት፣ ሚኒስትሮች እና የኮካ ኮላ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሀላፊዎች በተገኙበት የደመቀ አቀባበል ይደረግለታል፡፡ በመቀጠልም በብሄራዊ ቤተመንግስት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዋንጫውን የሚረከቡት ስነ ስርዐት የሚከናወን ሲሆን፣ ከቤተ መንግስት ቆይታው በመቀጠል የዓለም ዋንጫው ለጋዜጣዊ መግለጫ ወደ ሂልተን ሆቴል የሚያመራ ይሆናል፡፡ ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ የፎቶ ፕሮግራም የሚኖር ሲሆን፣ በዚህ ስነ ሰርዐትም ጋዜጠኞች ከዋንጫው ጋር የማስታወሻ ፎቶ መነሳት የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በሁለተኛ ቀን እሁድ፣ የካቲት 18፤ 2010 ዓ.ም የፊፋ አለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ቆይታ መላው የስፖርተ አፍቃሪ ህዝብ ከፊፋ የአለም ዋንጫ ጋር የማይረሳ ቀን የሚያሳልፉበት አስደሳችና አዝናኝ ውሎ በግዮን ሆቴል ይካሄዳል፡፡
የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ
የዓለም ዋንጫ በፊፋ ዋና አዘጋጅነት በ1930 እ.ኤ.አ ላይ በደቡብ አሜሪካዋ ኡራጋይ መካሄድ ከመጀመሩ ሁለት ዓመት በፊት የውድድሩ  ደንብ ሲቀረፅ ለአሸናፊ ለየት ያለ የክብር ዋንጫ እንዲሸለም ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡  ይህንኑ የዋንጫ ሽልማት በጥሩ ዲዛይን እንዲሰራ ታላቁና ከባዱ ታሪካዊ ኃላፊነት ለፈረንሳዊው ቀራፂ አቤል ላፍሌዌር ተሰጠው፡፡ ፈረንሳዊው ቀራፂም የተሰጠውን የታሪክ አደራ ባግባቡ በመወጣት አስደናቂዋን ዋንጫ አዘጋጅቶ ሊያቀርብ ቻለ፡፡ የፊፋ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ፈረንሳዊው ጁሊየስ ሪሜት መታሰቢያ ሆና ‹የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ› ተባለች፡፡
የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ለዓለም ዋንጫ አሸናፊዎች ከ1ኛው የዓለም ዋንጫ አንስቶ መሸለም ከጀመረች በኋላ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈራርቀውባታል፡፡ 1ኛው የዓለም ዋንጫ በኡራጓይ በ1930 እ.ኤ.አ ላይ ተካሂዶ ተጀምሮ እስከ 1938 እ.ኤ.አ በፈረንሳይ እስከ ተዘጋጀው 3ኛው የዓለም ዋንጫ ሶስተኛው ሻምፒዮና ከዘለቀ በኋላ 2ኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ፡፡  በዚያ ወቅት የፊፋ ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት ጣሊያናዊው ዶ/ር አሪኖ ባራሲ ውድድሩ በተቋረጠባቸው 12 ዓመታት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በኃላፊነታቸው ስር ሆና በአደራ ያስቀመጧት ነበረች፡፡ ጣልያናዊው የዓለም ዋንጫዋን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወራሪ ኃይሎች ዘረፋ ለመጠበቅ ሲሉ በጫማ ሳጥን ውስጥ አኑረዋታል፡፡ በአንድ አጋጣሚ በቤታቸው ፋሽቶች ፍተሻ ሲያደርጉ አልጋ ስር በመደበቅም አትርፈዋታል፡፡
በ1966 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በጊዜው የውድድር አዘጋጅ በነበረችው እንግሊዝ ያጋጠማት አስደንጋጭ ታሪክም ነበር፡፡ ለዓለም ዋንጫው መስተንግዶ ማሟሟቂያ ይሆናል ተብሎ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ለጉብኝት ቀርባ ከነበረችበት የኤግዚቢሽን ማዕከል በመጥፋቷም ነበር፡፡ ያን ጊዜ የዋንጫዋ መጥፋትና መሰረቅ ከታወቀ በኋላ  በዋናው የውድድር መድረክ ላይ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር ስጋት ሆኖ ነበር፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ግን ለኤግዚቢሽን ቀርባ ከነበረችበት ግዙፍ ህንፃ ብዙም ሳይርቅ የሚገኝ ትልቅ ዛፍ ስር መሬት ውስጥ በጋዜጣ ተጠቅልላ እንደተቀበረች ተገኘች። ለሕዝብ እይታ ቀርባ ከነበረችበት ስፍራ የጠፋችው ባልታወቁ ሌቦች ተሰርቃ ነበር፡፡ አንዲት ብልህ ውሻ ግን ከጌታዋ ጋር ስትንሸራሸር ዛፍ ስር የሚገኘውን መሬት ምሳ የተቀበረችውን ዋንጫ አግኝታለች፡፡ ለእንግሊዝና ለእግር ኳሱ አለም ታላቅ ውለታን ያደረገችው ውሻዋ ፒክልስ ትባል ነበር፡፡
በ1970 እ.ኤ.አ በሜክሲኮ ተደርጎ እስከ ነበረው 8ኛው የዓለም ዋንጫ የዓለም ሻምፒዮናነቱን ብራዚል ለሶስተኛ ጊዜ በማሸነፏ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የዘላለም ንብረት አድርጋት ነበር፡፡ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በታላቁ የስፖርት መድረክ ህልውናዋ ያበቃው በ1983 እ.ኤ.አ ላይ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዩዲጂኔሮ በዘራፊ ወሮበሎች ከተሰረቀች በኋላ ነበር። በወቅቱ ዋንጫዋን የሰረቁት ወሮበሎች ሌብነታቸው እንዳይነቃ  በማለት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን በፍም እሳት አቀለጧት እናም ወደ ሌላ ቅርፅ እንደቀየሯት በመላው ዓለም ተወስቶ ነበር፡፡ ብራዚል በዚህ ዘመን ዋንጫዋን ለሶስት ጊዜ ለማሸነፍ በመቻሏ ለዘላለም ማስቀረት የምትችላትን ኦርጅናል የጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫ ማጣቷ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋን ያስደነገጠ ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ የብራዚል ወሮበሎች የታሪክ ሌብነት የብራዚልን የዓለም ዋንጫ ስኬት ያሰናከለው ቢመስልም፤ በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፊፋ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ተመሳሳይ የጁሊየስ ሩሜት ዋንጫ እንዲሰራ ተደርጎ ምትኳ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ተበርክቷል፡፡
ኦሪጅናሏ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በመጠኗ አነስተኛ ነች፡፡ 35 ሴ.ሜ ቁመት ያላት ስትሆን እስከ 3.8 ኪ.ግ. የክብደት መጠን ነበራት፡፡ የዋንጫዋ አብዛኛው ክፍል የተቀረፀው በጠራ የብር ማዕድን ሲሆን ዙሪያዋን በተወሰነ የወርቅ ለምድ የተለበጠች ነበረች፡፡ የዋንጫዋ መሰረት ሰማያዊ ቀለም የነበረው ሲሆን በከፊል የከበረ ድንጋይ Lapis Lazuic  ከተባለ ማዕድን የተሰራ ነው፡፡ በዋንጫዋ ታችኛው ክፍል ያሉት አራት ጎኖች ዙሪያቸውን በወርቅ የተለበጡ ሲሆን ስፍራው የአሸናፊዎች ዝርዝር እንዲሰፍርበት የተዘጋጀ ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫ በጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ሽልማትነት ከ1930-70 እ.ኤ.አ የተካሄደች ሲሆን በዋንጫዋ ታችኛው ክፍል በሚገነው በዚሁ የወርቅ ለምድ ላይ በእነዚያ ጊዜያት በውድድሩ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ ዘጠኝ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖችም ስም ተቀርጾ ሰፍሮበታል፡፡  ብራዚል በ1958, 1962, 1970፣ ኡራጋይ በ1930, 1950፣ ጣሊያን በ1934, 1938፣ ምዕራብ ጀርመን በ1954 እና እንግሊዝ በ1966 እ.ኤ.አ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን አሸንፈዋል፡፡
አዲሷ የፊፋ ዓለም ዋንጫ
አዲሷ የፊፋ የዓለም ዋንጫ በ1970 እ.ኤ.አ ላይ ሜክሲኮ ባዘጋጀችው 9ኛው የዓለም ዋንጫ ብራዚል የዓለም ሻምፒዮናነቱን ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፍ በመቻሏ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የዘላለም ንብረቷ በማድረግ ከሰረቀች በኋላ የተፈጠረች ናት፡፡ ፊፋ የውድድሩን አዲስ የዋንጫ ሽልማት ለማዘጋጀት ውሳኔ ከላይ ከደረሰ በኋላ፤ የዓለም ዋንጫን ሽልማት በመቅረፅ ከ7 ሀገራት የተውጣጡ ቀራፂዎች የሰሯቸው 53 የተለያዩ ዲዛይኖች ለውድድር ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም የፊፋ ኮንግረስ ባሳለፈው ውሳኔ የጣሊያኑን ቀራፂ ሲልቪዮ ጋዚንጋን የዋንጫ ቅርፅና የስራ ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በዚህ መሠረት በ1974 እ.ኤ.አ በተከናወነው 10ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ አዲሷንና ዛሬ ድረስ የዘለቀችውን የዓለም ዋንጫ ለታላቋ የስፖርት መድረክ ለማቅረብ በቃ፡፡  አዲሲቷ የፊፋ የዓለም ዋንጫ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ንብረት ሆኖ ለዘላለም የምትቆይ ናት፡፡ ፊፋ በመተዳደሪያ ደንቡ እንደሚያመለክተው ዋንጫዋን ያሸነፈ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሰራችውን ሽልማት ለተወሰኑ የፌሽታ ሰሞናት ጠብቆ እንዲያቆይ ቢፈቀድለትም ኦርጅናሌዋን ዋንጫ አስረክቦ በፊፋ የተዘጋጀውን ተመሳሳይ ዋንጫ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ አዲሷ የዓለም ዋንጫ ሽልማት ዛሬም ድረስ ከውድድሩ ጋር አብራ እንደቆየች ትገኛለች፡፡ የዓለም ዋንጫዋ 36 ሴ.ሜ ርዝማኔ ሲኖራት የተሰራችው 4 ሺህ 970 ግራም ክብደት ከሚመዝን 18 ካራት ንፁህ ወርቅ ነው፡፡ የዋንጫዋ የታችኛው ክፍል በከፊል የከበረ ድንጋይ ከሆነው ማልቺይት ከተባለ ማዕድን የተለበጠና የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚሁ የዋንጫው ክፍል ላይ በ2014 እኤአ እስከተከናወነው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ድረስ በሻምፒዮናነት ታሪክ የሰሩ አገራት ተቀርፀው ሰፍረውበታል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናዎቹ ዝርዝር የሚፃፍበት ይኸው ቦታው እስከ 2030 እ.ኤ.አ ለሚያሸንፉ ብሔራዊ ቡድኖች ቦታ እንዳለው ቢታወቅ የዓለም ዋንጫ 100ኛ ዓመት ሲከበር አዲስ ዲዛይን ሊሰራ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የአሁኗን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ  በድል ሊስማት የቻለው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አምበል ፍራንዝ ቤከን ባወር ነበር፡፡ በ1974 እ.ኤ.አ በተካሄደው በዚህ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የተደረገው በሆላንድና በአዘጋጇ ምዕራብ ጀርመን መካከል ነበር፡፡ ጀርመንም ይህችኑ ዓለም ለመጀመርያ ጊዜ ያሸነፈች የአውሮፓ አገር ሆናለች፡፡ በ1978 እ.ኤአ ላይ ደግሞ በሞናሞናታል ስታድዬም ቦነስ አይረስ ከተማ ላይ ይህችኑ ዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ተቀዳጅታ የመጀመሪያዋ ደቡብ አሜሪካ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡
ጣሊያናዊው ቀራፂ ሲሊቪዮ ጋዚንጋ የሰሯት የፊፋ ዓለም ዋንጫ በታሪኳ በርካታ የዓለማችንን ታላላቅ ከተሞችን በሻምፒዮኖቹ እና በአዘጋጆቹ አገራት አማካኝነት ጎብኝታለች፡፡ ቦነስ አየረስ፤ ሳንቲያጎ፤ ማድሪድ፤ ሮም፣ ሎስ አንጀለስ፣ ፓሪስ፣ ዮክሃማ፤ በርሊን፤ ጆሃንስበርግና ሪዮዲጄኔሮ ይገኙበታል፡፡ የዓለም ዋንጫ ሽልማት የእግር ኳስ ስፖርትን ዓለም አቀፋዊነትና ታላቅ ውበት ተምሳሌት ተደርጋ የተቀረፀች ዋንጫ መሆኗን ቀርፂዋ ሲልቪዮ ጋዚንጋ ይናገራሉ፡፡ ስለ አንዱ የዓለም ዋንጫ ትዝታቸው ሲናገሩ “ጣሊያናዊ እንደመሆኔ” ስኳድራ አዙራ የተባለውን ብሔራዊ ቡድናችንን እደግፋለሁ፡፡ ስለዚህም በ1982 እ.ኤ. በሳንቲያጎ በርናባኦ ስታድዬም ማድሪድ ከተማ ውስጥ የጣሊያን ቡድን ዋንጫውን በማንሳት የፈፀመው ገድል ምንጊዜም አልዘነጋውም፡፡ ግብ ጠባቂው ዲኖ ዞፍ በጣሊያናዊ የተሠራቸውን ይህችን ዋንጫ ሲያነሳ በጣም ኮርቻለሁ። ዓለም ዋንጫዋ በገጽታዋ ጣሊያንን ብታንፀባርቅ አይደንቅም” ብለው ነበር፡፡ ከ1974 እ.ኤ.አ ወዲህ የአሁኗን የፊፋ የዓለም ዋንጫን ሶስት ጊዜ በመውሰድ ግንባር ቀደም የሆነችው ጀርመን (በ1974 ፤ በ1990ና በ2016 እ.ኤ.አ) ላይ በማሸነፍ ነው፡፡ ሁለት እኩል ያሸነፉት ደግሞ ብራዚል (በ1994 እና በ2002 እ.ኤ.አ) ፤ (ጣሊያን በ1982 እና በ2006 እ.ኤ.አ)  እና  አርጀንቲና (በ1978 እና በ1986 እ.ኤ.አ) ላይ ሲሆን፤እንዲሁም  ፈረንሳይ በ1998ና ስፔን በ2010 እ.ኤ.አ የዓለም ዋንጫዋን እኩል አንዴ በሻምፒዮናነት አንስተዋል፡፡
የዓለም ዋንጫ ዋጋዋና የመስተንግዶ ገቢዋ
ሲልቪዮ ጋዚንጋ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩት ከዓመት በፊት ሲሆን፤ የሰሯትን የዓለም ዋንጫ እንደ ልጄ የምቆጥራት የስነ ጥበብ ውጤት ናት ብለው ነበር፡፡ በ1971 እ.ኤ.አ ላይ ዲዛይን አድርገው እንደጨረሷት የዋንጫዋ ዋጋ እስከ 50 ሺህ ዶላር ይገመት ነበር፡፡ ዘንድሮ በወቅታዊው ዋጋ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ተተምኗል። በነገራችን ላይ የዓለም ዋንጫን የሚያህል ታላቅ የስፖርት መድረክ በማዘጋጀት በአማካይ ከ5-9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው የዋንጫዋን ውድ ስጦታነት ያመላክታል፡፡
በ2002 እ.ኤ.አ ላይ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ 17ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 9 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2006 እ.ኤ.አ ላይ ጀርመን 18ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 12 ቢሊዮን ዶላር፤ በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል 20ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ  እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫን ለ32 አገራት አዘጋጅቶ ለአሸናፊው የሚሸልም አገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ 30 ቢሊየን ዶላር እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል፡፡ ዓለም ዋንጫውን በሚያዘጋጅበት 4 ዓመታት ውስጥ ደግሞ እስከ 4 ሚሊየን ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡
የዓለም ዋንጫም ዋጋ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር መተመኑን የሚስተካከል ሌላ የስፖርት ሽልማት የለም። ከእግር ኳሱ ዓለም ውድ ዋጋ ያለው ሽልማት ተብሎ ቢጠቀስ የዓለማችን አንጋፋው የክለቦች ውድድር የሆነው የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ነው፡፡ ለ5 የተለያዩ ጊዜያት የተቀረፀው ይሄ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ እስከ 420 ሺ ፓውንድ ያወጣል፡፡ የዓለማችን ቁጥር 1 የክለቦች ውድድር የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ከ1992 እ.ኤ.አ አንስቶ ለሻምፒዮኖቹ የሚበረከት ነው፡፡ ምንም እንኳን በቴሌቪዥን ስርጭት መብት፣ በስታድየም ገቢ፣ በስፖንሰርሺፕ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ቢያገኝም ዋንጫው ግን ያን ያህል አያወጣም፡፡ በብር ተለብጦ የተሰራው የእንግሊዝ ፕሮሚር ሊግ ዋንጫ ማልቻለት የተባለ የከበረ ማዕድን መሰረት የሆነለት ነው፡፡ 104 ሴ.ሜትሮች የሚረዝምና 25 ኪ.ግ የሚመዝን ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተለበጠበት ብር በዋጋ ቢተመን ከ10 ሺ ዶላር አይበልጥም፡፡ በ1967 እ.ኤ.አ ላይ የተሰራው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ 71 ሴ.ሜትር የሚረዝምና 7.5 ኪ.ግ ክብደት ያለው ሲሆን፤ በምንም አይነት ዋጋ አልተተመነም፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ደንብ መሰረት ማንም ቀርፆ የመሸጥ መብት የለውም፡፡  

 ከ5 ሺ ብር እስከ 10 ሺ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል
 
    ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እውቅናን በማግኘት በቃላዊ ሂሳብ ስሌት፣ በሶሮባንና በሁለንተናዊ የአዕምሮ ዕድገት ላይ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችንና የሂሳብ ስሌት ውድድሮችን ሲያካሂድ የነበረው “ማይንድ ፕላስ ማትስ” ተቋም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የሂሳብ ትምህርት ጥያቄና መልስ ውድድር ያካሂዳል፡፡
ውድድሩ በአራተኛ፣ በስድስተኛ፣ በስምንተኛ፣ በ10ኛና በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል የሚካሄድ ሲሆን ከአማራ የባህር ዳር፣ ከኦሮሚያ የአሰላና አዳማ፣ ከትግራይ የመቐለ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ ተማሪዎች እንደሚሳተፉና በመጀመሪያው ዙር 10ሺህ ያህል ተማሪዎች ለውድድር ቀርበው እንደነበር “ማይንድ ፕላስ ማትስ” ገልጿል፡፡ እስካሁንም ከአዲስ አበባ 3126፣ ከመቀሌ 1569፣ ከባህር ዳር 659፣ ከአሰላ 300፣ ከአዳማ 300 ከድሬደዋ 450 በድምሩ 6404 ተማሪዎች ክልላቸውን ወክለው የሚቀርቡ ሲሆን በየክፍል ደረጃቸው 15 ተማሪዎች ለመጨረሻው ዙር ቀርበው፣ የአሸናፊዎች አሸናፊ የመለየት ስራ እንደሚሰራም ተቋሙ ገልጿል፡፡
የፈተናዎቹ ጥያቄዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታንት ዩኒቨርሰቲ መምህራን በጥንቃቄ የተዘጋጁ መሆናቸውንም ተቋሙ ጨምሮ ገልጿል፡፡ በውድድሩ 1ኛ ለሚወጣ 10 ሺህ ብር፣ 2ኛ ለሚወጣ 7 ሺህ ብር፣ በ3ኛነት ለሚያሸንፍ የ5 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን የገለፀው “ማይንድ ፕላስ ማትስ”፤ የመጨረሻውና የሽልማቱ ሥነ ስርዓት በእለተ ፋሲካ በተመረጠ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ እንደሚተላለፍ አስታውቆ፣ ውድድሩ መካሄዱም ሆነ በቴሌቪዥን ቀጥታ መተላለፉ ሌሎች ተከታይ ተማሪዎችን በማነቃቃት፣ በሂሳብ ትምህርት ላይ ፍላጎት እንዲያድርባቸውና ለውድድር ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋልም ተብሏል፡፡

በአንዱአለም አባተ (የአፀደ ልጅ) የተሰናዱት “ንጉስ ዘርዓ ያዕቆብና ሌሎች ግለ - ወጎች” እና “የህሊና መንገድና ሌሎች ልቦለዶች” የተሰኙ መፅሀፎች ሰኞ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚመረቁ የምርቃቱ አዘጋጅ መገዘዝ መልቲ ሚዲያና ቴአትር ፕሮሞሽን አስታወቀ፡፡ በዕለቱ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “ንጉስ ዘርዓ ያዕቆብና ሌሎች በተሰኘው መፅሀፍ ላይ ልዩ ዳሰሳ የሚያቀርቡ ሲሆን ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ ደግሞ መፅሀፉ ለቴአትር ትምህርትና ለደራሲያን ያለውን ፋይዳ ለታዳሚው ያካፍላሉ ተብሏል፡፡ በአ.አ.ዩ የጋዜጠንነትና ተግባቦት መምህር የሆኑት ዶ/ር ተሻገር ሽፈራው ደግሞ “የህሊና መንገድ እና ሌሎችም” በተሰነው መፅሀፍ ላይ ዳሰሳ እንደሚያቀርቡም ታውቋል፡፡ “ንጉስ ዘርዓ ያዕቆብ” የተሰኘው መፅሐፍ ደራሲው በመረጣቸው ተሪካዊያን ግለሰቦች ላይ በመመርኮዝና በተውኔታዊ አቀራረብ ያሰናዳቸው ታሪኮች የተካተቱበት ሲሆን ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮችም በፍትህ፣ በእውነት፣ በበቀል፣ በክህደትና በቃል ኪዳን ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ታሪኮቹ ምናባዊ ልብ ወለድ ቢሆኑም ከታሪክና ከቅዱሳት ድርሳናት ዋናውን የትረካ ጭብጥ ይዘው በመነሳታቸው በስነ - ፅሁፍ ዓለም “ንቡር ጠቃሽ” ከሚባለው የስነ ፅሁፍ ዘውግ ይመደባልም ተብሏል፡፡ በ124 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ60 ብርና በ15 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡ ደራሲው “የህሊና መንገድ እና ሌሎም አጫጭር ልቦለዶች” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍም ለንባብ አብቅቷል፡፡ በዚህ መፅሀፍ ውስጥ በተለያየ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 13 ያህል አጫጭር ልቦለዶች ተካተውበታል፡፡ በ118 ገፆች የተመጠነው መፅሐፉ በ50 ብርና በ10 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡