Administrator

Administrator

    የመጀመሪያው የአክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች ሆነን ሳለ፣ ይህ ስልጣኔ መስፋት ሲገባው እንዴት ፈረሰ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት “የጠፋው አዳም” የኪነ ጥበብ ምሽት፣ የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 እስከ ምሽት 1፡45 በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡
በውይይቱ ላይ ከሚሳተፉት ምሁራን መካከል የዘርዓያዕቆብ ዘጠነኛ የልጅ ልጅ የሆኑት ሊቀ ጠበብትና ሳይንቲስት ገ/ማሪያም ማሞ፤ ስልጣኔያችን ለምን ፈረሰ፣ እንዴት ፈረሰ፣ ማንስ አፈረሰው? በሚለውና በምርምር በደረሱባቸው ሰባት ምልክቶች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ እንደሚሰጡ የሁነቱ አዘጋጅ አቶ ቤዛ ሁነኝ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ ሊቀ ጠበብቱና ሳይንቲስቱ
ገ/ማሪያም ማሞ በበኩላቸው፤በአክሱም ስልጣኔ ላይ ባደረጓቸው ምርምሮችና ግኝቶች እንዲሁም ስልጣኔው እንዲቀጥል ምን መደረግ አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ በዚህ ውይይት ለመታደም መግቢያው 70 ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡ 

  በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ኮንሰርት ታቀርባለች

    የድምፃዊት ሄለን በርሄ “እስኪ ልየው” የተሰኘ አልበሟና “ፊት አውራሪ” ለሚለው ዘፈኗ የተሰራው ቪዲዮ ክሊፕ የፊታችን አርብ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ፣ ወሎ ሰፈር በሚገኘው ማማስኪችን ይመረቃል፡፡
በምሽቱም ድምጻዊት ሄለን “ፊታውራሪ”ን ጨምሮ የተለያዩ ዘፈኖቿን የምታቀርብ ሲሆን ሌሎች ድምፃዊያንም እንደሚያቀነቅኑ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የድምጻዊቷ ማናጀር አቶ በረከት ተሾመ እንደገለጹት፤ ድምጻዊቷ ከአብይ ፆም በኋላ በአዲስ አበባና በክልሎች ትልልቅ ኮንሰርቶችን የምታቀርብ ሲሆን በቀጣይም በውጭ አገራት ተመሳሳይ ኮንሰርቶች የማቅረብ እቅድ አላት፡፡  
በአንድ የዘፈን አልበሟ ተቀባይነት፣በአንድ የዘፈኗ ቪዲዮ ላይ አነጋጋሪ ስሆነው አልበሟና ስለተሰማራችበት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአዲስ አድማስ ለቀረበላት ጥያቄ በሰጠችው ምላሽ፣ አልበሟ ጥሩ ተቀባይነት ማግነቱን፣ በህፃናት ካንሰር ከUNDP ጋር በሴቶች ዙሪያ እንደምትሰራ የገለፀች ሲሆን አለባበሷ በቪዲዮው ዳይሬክተር ስንታሁ ሲሳይ ትዕዛዝ መለበሱን ገልፃ “በዚህ አለባበስ ህዝቡንም ሆነ ሚዲውን አስቀይሜ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብላለች፡፡

 በክላስ አክት ፊልም ፕሮዳክሽን እየተሰራ ዘወትር እሁድ ከምሽቱ 1፡30 የሚቀርበው “ትርታ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነገ ምሽት በፋና ቴሌቪዥን እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡  
የድራማው ደራሲ  ሶፎንያስ ታደሰ ሲሆን ዳይሬክተሩ ልዑል ተፈሪ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በድራማው ላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የሚሳተፉበት ሲሆን ከነዚህም መካከል፡- ኤልሳቤጥ መላኩ፣ አላዛር ሳሙኤል፣ ጌታቸው ስለሺ፣ ዲበኩሉ ታፈሰ፣ እታፈራሁ መብራቱ፣ ዝናቡ ተስፋዬ፣ አበበ ባልቻ፣ ፍሬው አበበ፣ ናርዶስ እንግዳ፣ ያፌት ሄኖክ፣ ሜሮን እንግዳና ሌሎችም እንደሚተውኑበት አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡   
ወንጀል ነክ ልብ አንጠልጣይ ዘውግ ያለው ድራማው፤ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በ1950ዎቹ ዓመታት በአንድ ዘመናዊ ነጋዴና በአንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ድራማው በታሪክም ሆነ በምስል ጥራቱ ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነም አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ መንገድ ላይ ይገናኛሉ፡፡
አዋቂ፡- እንደምን ውለሃል ወዳጄ
አላዋቂ፡- እግዚሃር ይመስገን እንዴት ከርመሃል?
አዋቂ፡- እኔ ደህና ከርሜያለሁ፡፡
አላዋቂ፡- ይሄ ምሁር ነኝ ባይ ጉረኛ ሁሉ ሰፈር ውስጥ አላስቀምጥ አለን እንጂ እኛማ ደህና ነን፡፡
አዋቂ፡- እንዴት ነው ያስቸገረው?
አላዋቂ፡- አሃ አንተም ጀመርከኝ እንዴ?
አዋቂ፡- የማላውቀውን እንድታሳውቀኝ ብዬ እኮ ነው፡፡
አላዋቂ፡- ደህና፡፡ አሁን ወዴት እየሄድክ ነው?
አዋቂ፡- ወደ ገበያ
አላዋቂ፡- እንግዲያውስ አብረን እንሂድ- ግን አዋቂ ነኝ ብለህ እንዳትፈላሰፍብኝ
አዋቂ፡- እኔ እንደውም ካልጠየቅኸኝ አላስቸግርህም፡፡
ተስማምተው መንገዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ጥቂት እንደሄዱ አንድ አጥር ላይ ያለ አውራ ዶሮ አጠገብ ይደርሳሉ፡፡ አውራ ዶሮው ይጮሃል። ይሄኔ አላዋቂው፤
“ይሄ አውራ ዶሮ እዚህ ሲጮህ፣ የዚህ ዓይነት ሌላ አውራ ዶሮ መንግሥተ-ሰማይ ውስጥ ይጮሃል” አለ፡፡
አዋቂው፡- መንግሥተ-ሰማይ ንፁህ ነው፡፡ እንደ ዶሮ ያለ ባለ ኩስ እዚያ ሊኖር አይችልም፡፡
አላዋቂው፡- አይ አውራ ዶሮ‘ኮ ሲጮህ፤ አፉን ወደ ገነት ቂጡን ወደ ሲዖል አድርጎ ነው፡፡
አዋቂው፡- ሲዖል‘ኮ የሰውን እርጥብ ሥጋ እንኳን ያነዳል፡፡ የዶሮ ላባ ካገኘማ ወዲያው ነው አቀጣጥሎ የሚያጋየው!
አላዋቂው መሟገቻ ነጥብ አጣ፡፡
አላዋቂው፡- ኦዎ! እኔ ምንቸገረኝ- ያባቴ ዶሮ አደለ ቢያንበገብገው!
*    *    *
የአንድ አገር አንዱ መልካም ገፅታዋ አዋቂዎቿን መንከባከቧና ከእነሱም በቂ ምክር መቀበሏ ነው። ያልተማረ አላዋቂ እየገነነ፣ የተማረ አዋቂ እየኮሰሰ በሄደ ቁጥር የሀገር እድገት ቁልቁል ይሆናል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ የፊደል ሠራዊት እስከ ደርግ የመሀይምነትን ጥቁር መጋረጃ መቅደጃ መሠረት ትምህርት ድረስ የተለፋው አላዋቂነትን ለመቀነስ ነው፡፡ ብዙ ተጉዘንበታል፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ዛሬም ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ ጥረቱን መቀጠል ተገቢ ነው፡፡ አላዋቂነት በእርግጥ የመማር ያለመማር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሳይማር በቂ ብስለት ያለው ሰው ብዙ አለ፡፡ ተምሮ በዘር፣ በሃይማኖትና በቀለም አባዜ ውስጥ የሚዳክር አያሌ ሰው አለ፡፡ ተምሮ እንዳልተማረ እያደር የሚደነቁር፣ እንደ ሽንቁር እንሥራ የሚያፈስ በርካታ ምሁር አለ፡፡ አስተዳደግ፣ አካባቢ ተፅዕኖ፣ የአቻ ዕድሜ ግፊት፣ የማህበረሰቡ የዕድገት ደረጃ፣ የግብረገብነት ጥልቀት ወዘተ … የማንነቱ መቀረጫ ሊሆኑ ይችላሉ። የሃገራችን የዕድገት አካሄድ በማንነት መለኪያ አንፃር በተለይ አሥጊ አካሄድ ላይ ያለ ይመስላል። የሚያባብስ እንጂ የሚያሻሽል በሌለበት ሁኔታ ከገባንበት እዘቅት የመውጣት ዕድል እየጠበበ እየመጣ ነው፡፡
ይህንን ጠንቅቆ የተረዳና የራሱን ጠጠር ጥሎ ለመሻሻል አስተዋፅዖ የሚያደርግ ማንኛውም ዜጋ፤ የለውጡ ሞተር አካል ይሆናል፡፡ በተለይ ወጣቱ ዐይኑን እንዲከፍት ይጠበቅበታል፡፡ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድ ከግዴለሽነትና ከተመልካችነት ወጥቶ፣ ወደ ተዋናይነት መሸጋገሩ አይቀሬ ነው! በየትኛውም ዘመን የነበረው ወጣት፤ ቀስ በቀስ ነው ለአገር አሳቢ እየሆነ የመጣው፡፡ ግብአቶቹ አያሌ ናቸው፡፡
በንጉሡ ጊዜ የነበረው ወጣት ወደ አብዮቱ የለውጥ ሂደት እስኪገባ ድረስ የሃያና የሰላሳ ዓመት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፏል፡፡ አብዮተኛ ሆኖ የተፈጠረ ወጣት ኖሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም የ1966 ዓመተ ምህረቱ አብዮት ከመፈንዳቱ ዋዜማ “የጆሊ - ጃኪዝም” ዘመን ነበር፡፡ ቤል ቦተም (ቦላሌ-ከታቹ በጣም ሰፊ)፣ ሰፊ ቀበቶ፣ አፍሮ ፀጉር፣ ህልሙም ውኑም ሴት ጠበሳ፤ ጭሳ ጭሱን በየጥጉ ያከናውን የነበረ ትውልድ ማቆጥቆ የጀመረበት ሰዓት ነበር፡፡ እንደ ዛሬው “ሀንግ” ባይሆንም፣ የግሩፕ ፀብ ጣራ ነክቶ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ያ ሁሉ የተዛነፈ ጉዳይ ላይ የነበረውን ወጣት አብዮት ዋጠውና የለውጡ ሞተር ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡ መረሳት የሌለበት ከሞላ ጎደል የጥቂት የነቁ ወጣቶች መንቀሳቀስ ብቻ እንደነበር ነው፡፡ Change is an incremental process ለውጥ አዳጊ ሂደት ነው እንደ ማለት ነው፡፡ የሁሉም ወጣት ዐይን በአንድ ጊዜ አይከፈትም፡፡ ለውጥን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ማየት ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ትውልድ ቸኩሎ ለጥቅም ሲቆም ብዙ አገራዊ ጉዳዮችን ሊዘነጋ መቻሉ አይታበልም፡፡ ታላላቆች ታናናሾችን ለመግራት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ መናናቁ የትም አያደርስም። ምንም ያልተማሩ ወላጆች፤ ልጆቻቸውን ለፍሬና ለወግ ማዕረግ ያበቁት ከእኔ የተሻለ ልጅ ላፍራ ብለው ነው! የጊዜ ገደብ አመለካከታችን መቀየር አለበት - የአንድ ጀንበር ድል የለምና፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅድ፣ ከትዕግሥትና ከሆደ - ሰፊነት ጋር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው! ለዚህ ደግሞ ቁልፉ ዲሲፕሊን ነው፡፡ ያለ ዲስፕሊን እንኳን ዓመታት ሳምንታት መዝለቅ አይቻልም፡፡ ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ፤ የሀገራችን የጋዜጣ ሥርዓት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ተብለው ተጠይቀው - “40 ዓመት ይበቃል” ማለታቸውን አንርሳ፡፡ ሩቅ የሚያይ አዕምሮና የቅርቡን በአግባቡ የሚራመድ እግር ያስፈልጋል፡፡ የየዕለቷን ድል በማጠራቀም ከጉራ በፀዳ ንቃት መንቀሳቀስ ያሻል። ይህ ሁሉ የዲሲፕሊኑ አካል ነው፡፡ የእስከዛሬው መንገድ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” ነበር። ይህ እንዳይደገም ሁሉም የቀደምት ተዋንያን “በእኛ ይብቃ” ይበሉ፡፡ ወይም በዘመነኛው አባባል “አፉ በሉን” ይበሉ፡፡ ስህተትን አለማረም ለስህተት ደረጃ ማውጫ ካልሆነ በቀር ለማንም አይበጅም። ለተረካቢው ትውልድ የምንሰጠው የጠራ ታሪክ አይኖርም፡፡ ተረካቢውም ትውልድ ታሪክን መርማሪ፣ አመክንዮ የሚገባው፣ ከነችግሩ የነገን ብሩህነት የሚያይ፣ ትችትና ማጥላላትን ዋናዬ የማይል፣ ትምህርትን መሬት አውርዶ የት እደርስበታለሁ የሚል፣ እኔ ካልተለወጥኩ አገር አትለወጥም ብሎ የሚያስብ፣ ግብረገብነትን የዕለት ተዕለት ህይወቱ ለማድረግ የሚጣጣር፣ ከፖለቲከኝነት ይልቅ ሰው ለመሆን የሚተጋ፣ የሚማረው ከሁሉም በፊት ለራሱ መሆኑን የሚያውቅ፣ ትውልድ እንዲሆን ከመመኘት አልፈን የምናግዘው፣ የምናበረታታው፣ የምናማክረው ዜጎች መኖር አለብን፡፡ ወጣቱም ከማፈንገጥ ይልቅ አዳማጭ፣ ከአጉራ - ዘለልነት ይልቅ አደብ መግዛትን የሚመርጥ፣ ከሞቅ ሞቅ ይልቅ ላቅ ጠለቅ ማለትን የሚወድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” ይሆናል፡፡ ከዚያ ይሰውረን!!      

  ለረጅም ዓመታት የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ብዙ መከራ ሲደርስባቸው መቆየቱን የገለፁት የቁጫ ማህበረሰብ ተወካዮች፤ የማንነት ጥያቄያችን፣ መከራና እንግልታችንን እያባባሰው ነው ብለዋል። በቅርቡ የቁጫ ተወላጅ በሆነው የሶሲዎሎጂ ባለሙያው ሀብታሙ ሃ/ጊዮርጊስ የተፃፈውን በቁጫ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን “የቁጫ ታሪክ እስከ 2007” የተሰኘ መፅሀፍ ሲያነቡ የተገኙ የማህበረሰቡ አባላት፣ ቤታቸው እየተበረበረና ለተለያዩ ጥቃቶች እየተጋለጡ መሆኑን ባለፈው ሳምንት አቤቱታ ለማሰማት ወደ አዲስ አበባ የመጡ ተወካዮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በቅርቡ ይካሄዳል ለተባለው የህዝብና ቤት ቆጠራ የተመለመሉ ቆጣሪዎች፤ “በሚሞላው ፎርም ላይ ብሄር በሚለው ቦታ “ቁጫ” የሚል እንዳትፅፉ፤ ታብሌቱ ላይ ክፍት አድርጋችሁ እለፉ” የሚል ትዕዛዝ በአመራሮች እየተሰጣቸው ነው ብለዋል አቤቱታ አቅራቢዎቹ፡፡
በቆጣሪነት የተመረጡ የቁጫ ተወላጅ ወጣቶች፣ ከቆጣሪነት እየተሰረዙ እየወጡ እንደሆነም በመግለፅ፤ ይህ የቁጫ ህዝብ ላይ የሚደርሰው እንግልትና ስቃይ ፍጹም ህገ-ወጥ በመሆኑ አጥብቀን እንቃወማለን ብለዋል፡፡
የቁጫ ተወላጅ ምሁራንና ባለሀብቶች፣ የማህበረሰቡ የማንነት ጥያቄ እንዲመለስ በተደጋጋሚ በሚያነሱት ጥያቄ ለድብደባ፣ ለእስራትና ለተለያዩ ጥቃቶች ሲጋለጡ መቆየታቸውን ያወሱት የማህበረሰቡ ተወካዮች፣ የተወላጆቹ ስቃይ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባሱ የትውልድ ቦታቸውን ጥለው፣ ቤተሰባቸውን በትነውና ስራና ንግዳቸውን ትተው ለስደት መዳረጋቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከ1980ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ማህበረሰቡ እንደማህበረሰብ እውቅና ሊያሰጠው የሚችላቸውን በርካታ መስፈርቶች ቢያሟላም፣ ስልጣንና ወንበራቸው እንዳይነቃነቅ የፈለጉ የአካባቢው አመራሮች፤ በማህበረሰቡ ላይ ጫና በማሳደር፣ ያልሆነ ማንነት እንደጫኑበት ቀጥለዋል ይላሉ፡፡
የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያ (ሶሲዎሎጂስት) እና የቁጫ ተወላጅ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ሃ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የቁጫ ማህበረሰብ ሲጠይቅ የኖረው የማንነት ጥያቄ አለመመለሱ ሳያንሰው፣ ስለ ማንነቱ የተፃፈ ታሪክ ማንበቡ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ፣ ቤቱ እየተበረበረና እየተሸማቀቀ የሚኖርበት ምክንያት መቆም አለበት ብለዋል፡፡ ማህበረሰቡ እስከዛሬ በማንነት ጥያቄ ብቻ ቤቱ ሲቃጠል፣ ንብረቱ ሲወድም፣ ት/ቤቶች እየተዘጉ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ሲስተጓጎሉና አፋቸውን ባልፈቱበት ቋንቋ በግድ ሲማሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ አሁን ግን ጭቆናው ጣሪያ ነክቶ፣ የራሱን ታሪክ እንዳያነብ፣ የመቁጠር የመቆጠር መብቱን እንዳይጠቀም በማድረግ፣ ህገ-መንግስቱን የሚፃረር ስራ እየተሰራ መሆኑን በምሬት ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡ ከዓመታት በፊት ጀምሮ የማንነቱን ጥያቄ ለክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤትና ለፌደሬሽን ምክር ቤት በተዋረድ ሲያቀርብ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ፤ ጉዳዩ ፌደሬሽን ምክር ቤት ቢደርስም ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱን በመግለፅ፤ አሁንም ሽማግሌዎቹ ከማህበረሰቡ ተወክለው አዲስ አበባ በመምጣት፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ለማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና በተዋረድ ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የማህበረሰቡ ጥያቄ እንዲመለስና እንግልትና ስቃዩ በአስቸኳይ ቆሞ፣ የመቁጠር መቆጠር መብቱ እንዲከበር ጠይቀዋል - ተወካዮቹ፡፡
የቁጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳማ ሻራ የቁጫ ታሪክ የያዘ መፅሃፍ በማንበባችን ስቃይ እየደረሰብን ነው የሚለውን አቤቱታ በተመለከተ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ “ተፃፈ የተባለው መፅሀፍ፣ እንደ መፅሀፍ የማይቆጠርና በውስጡ ወንጀሎችን የያዘ ነው፤ መፅሀፉን አንብበሀል ተብሎ የተንገላታም የተጠየቀም የለም፤ ሶዶ ላይ በይፋ ሲሸጥ ነበር” ብለዋል፡፡ የቤትና ህዝብ ቆጠራውን በተመለከተም፤ ብሄሩን እንዳይሞላ የታገደ ከተመረጠበት የቆጣሪነት ስራ የተሰረዘም እንደሌለ ገልፀው፤ ማህበረሰቡን ወከልን ብለው አዲስ አበባ የመጡት አቤቱታ አቅራቢዎችም ተቀባይነት የሌላቸው በመሆናቸው ጉዳዩን ወረዳው ድረስ መጥታችሁ ማጣራት ትችላላችሁ” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል - ዋና አስተዳዳሪው፡፡

“ምስጋናዬና ፍቅሬ ከልብ ነው”
ከአራት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነው የሙዚቃ ድግሴ እጅግ ባመረ መልኩ ተጠናቋል። የባህርዳር ህዝብ ወደ ከተማዋ ስገባ ካደረጉልኝ አቀባበል ጀምሮ፣ በቆይታዬ ወቅት ባሳዩኝ ፍቅርና ክብር እንዲሁም መስተንግዶ ልቤ ተነክቷል - እወዳችኋለሁ! የዝግጅቱ ዕለት ስቴዲየም ተገኝታችሁ የታደማችሁ በሙሉ በተለይም ደግሞ ከሩቅ አካባቢዎች፣ ከአራቱም ማዕዘን መጥታችሁ ኮንሰርቱን ለተካፈላችሁ ሁሉ ምስጋናዬና ፍቅሬ ከልብ ነው።
የሙዚቃ ስራዎቼን ማቅረብ ከጀመርኩ ጊዜ አንስቶ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የማይገባኝን ሁሉ እንዳደረገልኝ በድጋሚ በመመስከር፣ ሁሌም በፍፁም ታማኝነት፣ እናንተን እንደማገለግል ሳረጋግጥ በታላቅ ኩራት ነው።
እግዜር ያክብርልኝ!
አመሰግናለሁ ባህር ዳር!
አመሰግናለሁ ኢትዮጵያ!
(ከቴዲ አፍሮ ፌስቡክ)
 እጅግ ከብዙ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ በማስታወቂያ ብቻ ተገድቦ ያልቀረው፤ “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የብላቴናው የሙዚቃ ኮንሰርት፣ እውን ሆኖ፣ በስኬት ተጀምሮ በስኬት ተጠናቋል። የኮንሰርቱ አዘጋጆች /በተለይም ቴዲ አፍሮ/ ከሙዚቃ ኮንሰርቱ አንድ ቀን ቀደም ሲል፣ በወልድያ ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞና እሱንም ተከትሎ፣ በሞቱት ሰዎች ምክንያት ፕሮግራሙ እንዲሰረዝ ብዙ ዓላማ ከነበራቸው “አዛኝ ቅቤ አንጓቾች” በኩል የተከፈተውን ፕሮፓጋንዳ፣ እንዳላየ ለማለፍ ተገደዋል። ሁሉን እሰማለሁ ካልክ ከሁሉም አትሆንም፤ ወዳጄ።
በዛሬ ጊዜ የላፕቶፓቸውን ኪ-ቦርድ፣ ለነገርና ለቦይኮት ያቀባበሉ የዘመናችን ተዋጊዎች ዘንድ አድመኝነት እንጂ ማስተዋል ብሎ ነገር የለም። ይህን የሙዚቃ ድግስ ለማዘጋጀት አርቲስቱና ተባባሪዎቹ ብዙ ድካምና መከራ ከፍለው ባህር ዳር በተገኙበት፣ የመድረክና ተያያዥ ውድ ዝግጅቶች በተጠናቀቁበት፣ ብዙ የብላቴናው አድናቂዎች ከመላው ኢትዮጵያ ባህር ዳር በታደሙበት፣ እጅግ ብዙ ትኬቶች ተሽጠው ባለቁበት--- 11ኛው ሰዓት ላይ የአባ ምን ገዴ ልጆች፤ የራሳቸውን መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን አንድም ሳያዛንፉ እየከወኑና ጠቆር ያለ ማኪያቶኣቸውን እየላፉ፣ በሚነካኩት ሞባይላቸው፣ በድፍረት የኮንሰርቱን መሰረዝ ጠይቀዋል።
ሁኔታው ወዳጄ ናቲ ማን፣ ከወር ገደማ በፊት ያጫወተኝን እንባ አስጨራሽ ገጠመኙን አስታወሰኝ። ናቲ መኪና አልባ ተከራይን ፈልጎ ማግኘት በሚቸግርበት አንድ የሸገር ኮንዶሚኒየም ብሎክ ነበር እሚኖረው። የኮንዶሚኒየሙ ግቢ ሁሌም በጊዜ፣ በተከራዮቹ መኪና ጥቅጥቅ ብሎ ይሞላል። አንድ ቀን ናቲ ወደ ግቢው ሲገባ ከፊቱ ሌላ ባለ መኪና ቆሟል። የብሎኩ ዘበኛ፣ ሰውየውን፣ የግቢው መኪና ማቆሚያ ስለሞላ መኪናውን ውጭ እንዲያሳድራት በማመናጨቅ እጁን እያወናጨፈ ነገረው። ይሄኔ ሰውየው መስኮቱን ዝቅ አድርጎ፣ ዘበኛውን በመጥራት እንዲህ አለው፡-
“እንደው የአስር ብር ኮንጎ ጫማህን ውጭ እማታሳድር ሰውዬ፣ አፍህን ሞልተህ የሚሊዮን ብር መኪናን ውጭ አሳድር ስትል አይቀፍህም?”
መቼም ምን ለማለት እንደፈለግሁ፣ ይገባችኋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ቴዲ አፍሮ እጅግ በበዛ መሬት አንቀጥቃጭ የህዝብ ፍቅር ታጅቦ ድግሱን ከውኗል። ድግሱም፤ “Bahir Dar, are you ready?!” ከሚለው ከብዙ ናፍቆት በኋላ ከተሰማው የብላቴናው ድምፅ፣ ሶስት አራት ሰዓት ቀድሞ በኢትዮጵያዊነት ቀለማት እጅግ አሸብርቆ ቆይቷል። ከፍቅርና አንድነት ግምጃ ተራቁተን ባዶ በቀረንበት በዚህ ዘመን፣ እንደ ኢትዮጵያዊ፤ የቀረን አስተሳሳሪ ምልክት፣ አንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑን ስታይ ሆድ ይብስሃል። እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖርና እንደ ኢትዮጵያዊ መዘመርን ለተጠሙ ወገኖች ሁሉ ግን ምሽቱ በቀላሉ እሚረሳ ሆኖ አላለፈም።
በተለይም ወደ ስታዲየሙ በተወሰኑ ወጣቶች አማካኝነት፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ሲገባ የተሰማው የህዝብ ድጋፍና ጭፈራ ልብን አብዝቶ እሚያሞቅ ነበር። ጭብጨባና ድጋፉን ተከትሎም፤ “ኦሮሚያ! ኦሮሚያ!” የሚለው የቀመር የሱፍ ዜማ፣ በታዳሚው አንደበት በጋራ ተዚሟል። ወዲያው ከመድረኩ የአሊ ቢራ ሙዚቃ ተከፍቶ በአንድነት ተጨፍሮበታል።
እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው ኮንሰርት፣ ወደ ሁለት ሰዓት አቅራቢያ፣ ከብዙ ጥበቃ ትዕግስትና ፈተና በኋላ የተናፋቂውን “ሰው!” ድምፅ ማሰማቱ አልቀረም።
“Bahir Dar, are you ready?!”
ወዳጄ፤ ልክ እንደኔ የመሬት መንቀጥቀጥን በህይወትህ አይተህ እማታውቅ ከሆነ፣ በዚህች ሰአት በዚህች ቦታ ባለመገኘትህ ልታዝን ይገባሃል። ቃላት በማይገልፀው ጩኸት፣ ሆታ፣ ግፊያና አጀብ፤ ብላቴናው እጅግ ያሸበረቀ ደማቅ መስቀል፣ ከፊቱ ያተመ ቲ-ሸርት ለብሶ፣ “አፍሪካዬ!” እያለ ወደ መድረኩ መጣ። እዚህ ጋ ዝም ብል ነው የሚሻለው፡፡ ምክንያቱም የሆነውን፣ የተሰማውን፣ የተደረገውን --- በቃላት ልገልጸው አልችልማ። አዝናለሁ!!
ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች የብላቴናውን የሙዚቃ ድግሶች ታድሜአለሁ። ሁሉም ጋ አርቲስቱ ከህዝቡ የሚበረከትለት ድጋፍና ፍቅር ልክ የለውም፡፡ የእሁዱ ግን ይለያል፡፡ ቴዲ፤ ወደፊትም ይሄን በመሰለ የህዝብ የፍቅር ባህር ውስጥ ሰምጦ፣ መዝፈኑን እጠራጠራለሁ። እያንዳንዱ ሙዚቃ ሲጠናቀቅ በምትገኘው ፋታ መሃል፤ ”ቴዲ አንደኛ! ቴዲ የአንድነት መንፈስ!” የሚል የአድናቂዎች ሙገሳ ይንቆረቆርለት ነበር፡፡ አርቲስቱም በመሽኮርመምና በመደነቅ፣ ለተበረከተለት የፍቅር ሙገሳ፣ ምስጋናውን ሲያቀርብ አምሽቷል። አንዴ ደግሞ፤ “ዕድሜና ጤና ለቴዲ!” እያለ ህዝቡ ሞቅ ያለ ጭፈራውን አስነካው፡፡ ቴዲም በበኩሉ፤ ”ረጅም ዕድሜ ለሁላችን!” ሲል በአጸፋው መርቋል።
የባህርዳሩ ኮንርሰት በሙዚቃ ጥራት በኩልም ሊመሰገን የሚገባው ነበር። አቡጊዳ ባንድ፤ የሳክስፎን ትራምፔትና መሲንቆ ተጫዋቾችን እንደ አዲስ ጨምሮ ተገኝቷል። ከሮቤልና አበራ በተጨማሪም ሌላ ሶስተኛ የሊድ ጊታር ተጫዋች ነበረው፡፡ ሩፋኤል ያልተገኘበት ከበሮ፣ በሁለት ወጣቶች ሲደለቅ አምሽቷል። ባንዱ የስቱዲዮን “ኢፌክት” ለማምጣት በተጠጋ ውጤታማ “አኪውሬሲ”፣ ሙዚቃውን ሲጠበብበት  አምሽቷል። ብላቴናው፤ “አፍሪካ”፣ “ግርማዊነትዎ” እና “ጥቁር ሰውን” ከበፊት አልበሞቹ ላይ እንዲሁም “ኢትዮጵያ”፣ “ሰምበሬ”፣ “ማር እስከ ጧፍ”፣ “አናኛቱ”፣  “ያምራል”፣ “ታሞልሻል”፣ “እማ ዘንድ ይደር”፣ “ቴዎድሮስ” እና “ማራኪዬ”ን ከአዲሱ አልበሙ ተጫውቷል። በተለይ “አናኛቱ፣ ሰምበሬ፣ ኢትዮጵያ፣ ማር እስከ ጧፍና ቴዎድሮስ”ን ሲጫወት፣ የህዝቡ የዝማሬና አንድነት መንፈስ ለጉድ ነበር።
/Some awkward moments:)
ኮንሰርቱ በሁለት ምዕራፍ የተከወነ ነበር። በመሃል ቴዲና ባንዱ ለእረፍት ሲወርዱና በድንገት የዲጄው የሙዚቃ ግብዣ በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ሲቋረጥ፣ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፆች ከተለያዩ የስታዲየሙ ክፍሎች መስተጋባት ጀመሩ። እንዲህ ያለውን የተቃውሞ መንፈስ፣ ብዙም የፈለጉት እማይመስሉት የአርቲስቱ የቅርብ ሰዎች፣ በተለይም ማኔጀሩ አቶ ጌታቸው፣ ወደ መድረኩ ጫፍ ወጥቶ፣ ዲጄውን ሲቆጣው ተስተውሏል። “በሙዚቃ ያዝልን” አይነት ነው፤ ነገሩ። ይህ ትዝብት ግን ከመድረኩ በቅርብ ርቀት የተገኘ ያንድ ታዳሚ አረዳድ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ ያም ሆኖ፣ የተቃውሞ ድምፆችን ማየል ከመድረክ ጀርባ (ባክስቴጅ) ሆኖ የሰማው አርቲስቱ፤ በተለመደ የሃይል መልዕክቱ እዛው ሆኖ፣ ትህትናን ባጀበ ድምፅ “ፍቅር ያሸንፋል!!!” ሲል አረጋግቷል። ቴዲ ዘፋኝ ብቻ እንዳልሆነ ለመመስከር፣ እንዲህ ባሉ አስጨናቂ ገጠመኞች መሃል መገኘትን ይጠይቃል።

ነገረ ጃ ያስተሰርያል
የጃ ጣጣ ሌላ የመድረክ ላይ ድራማ አሳይቶን አልፏል። ህዝቡ ከመጀመርያው አንስቶ በእያንዳንዱ የሙዚቃ ፋታ መሃል፣ “ጃ ያስተሰርያል”ን ሲጠይቅ ነበር ያመሸው። አርቲስቱ ወደ መጨረሻ፣ ዝግጅቱን በ“ጥቁር ሰው” ሊዘጋ በሚሰናዳባት ሰዓት ላይ ግን የህዝቡ ጥያቄ አይሎ፣ ግጥሞች ከፍ ባለ ድምፅ በዜማ ይሰሙ ጀመር።
ግርማዊነታቸው ከዚህ ሰረገላ
ወደ ዋገን ወርደው ሲተኩ በሌላ...
ከዚህ በኋላ የሆነው … አስፈሪ፣ አስደንጋጭ፣ በተወሰነ መልኩም አስቂኝ ነበር።
ቴዲ ህዝቡን ጠየቀ።
“ያስተሰርያል ይዘፈንላችሁ?”
ህዝቡ ከባህር ዳር ጎንደር ድረስ በሚሰማ ሃይለኛ ድምፅ “አዎ” አለ። ብላቴናው፤ ፊቱን አዙሮ ከጊታር ተጫዋቾቹ ጋር አጭር ምክክር አድርጎ ሲያበቃ፣ ወደ ህዝቡ ዞረና፡-
“እዘፍንላችኋለሁ” አለ።
በዚህ መሃል ሁኔታውን ከዳር ሆኖ ሲመለከት የቆየውና በቁጣና ብስጭት አቅሉን የሳተው የአርቲስቱ ማናጀር መድረክ ሰብሮ ገባ። ”እናንተ ናችሁ አማክራችሁ ዝፈን ያላችሁት!?” በሚል እየተጨቃጨቀ ይመስላል፡፡ ቴዲ አፍሮም ፈገግ እያለ፣ ጭቅጭቁን እንደኛው በዝምታ ነበር የታደመው፡፡
ለሰዓታት ሰላምና ፍቅር ሰፍኖበት የዘለቀው መድረክ፤ ከመቅጽበት ዝምታና ውጥረት ሞላው፡፡ በዚህ መሃል ህዝቡ፤ “ቴዲ አይፈራም!” እያለ መጮህ ጀመረ።
ቴዲም ወደ ህዝቡ በመዞር፤
“እኔ ፈርቼ አላውቅም!” መለሰ፡፡
ሌላ ሆታ፣ ሌላ ጭፈራ። አቶ ጌታቸው ቁጣና ብስጭቱን አራግፎ ከመድረክ ወረደ። አርቲስቱም፤ ጃ የፍቅር፣ የይቅርታና የእርቅ መልዕክት መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን ማንም እንዲከፋው ስለማይፈልግ ኮንሰርቱን በ“ጥቁር ሰው” መዝጋቱ እንደሚሻል በትህትና አስረድቶ፣ ዝግጅቱን በባልቻ ከውኖ ህዝቡን አመስግኖ፣ ከበዛ ድጋፍና ፍቅር ጋር ታጅቦ ከመድረክ ወርዷል።
(ከEil jah ፌስቡክ)


    የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ ተከትሎ፣ታስረው የነበሩ ከ2ሺ በላይ ዜጎችን መፍታቱን አስታወቀ፡፡ በትላንትናው ዕለት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት መግለጫ፤2 ሺ 345 እስረኞች  በምህረት መፈታታቸውን የተናገሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺ 568 ያህሉ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው እንደነበሩ  ገልጸዋል፡፡
መንግስት አገሪቱን ለማረጋጋትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ መግለጹን ተከትሎ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 500 የሚደርሱ እስረኞች የተፈቱ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል እርምጃም የዚሁ ውሳኔ አካል እንደሆነ ታውቋል፡፡

ቀበሮ መሞቻዋ ደርሶ በዱር አራዊት ፊት ትናዘዛለች፤ አሉ፡፡
“ወዳጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ ከዚህ ዓለም መሰናበቴ ነው፡፡ ስለዚህ ጥቂት ቃላት ልናገር፤ አያ አንበሶ ጉልበት ባታበዛ ጥሩ ነው፡፡ እሜት ጦጢትም ብልጣ ብልጥነቱን አታብዢው! ዝንጀሮ ወሬ እያቀባበልክ፣ የዱር አራዊቱን እርስ በርስ አታባላቸው፡፡
ከርከሮ ቀን አመቸኝ ብለህ፣ አቅመ ደካሞችን አታጥቃ፡፡
ነብር አንዴ ሰሶችን፣ አንዴ የሜዳ አህዮችን፣ አንዴ ፍየሎችን እንዳፈተተህ እያሳደድክ መብላትህን ጋብ አድርገው፡፡
ድብ ማድባትህን ተው!
ዱኩላ አመሻሹ ላይ የቤት እንስሳት ለማጥቃት መውጣትህን አቁም፡፡
ጅብ ለአህዮች ብታዝን ጥሩ ነው፡፡ ታቀብ!
ዝሆን ሳታንቀላፋ ወዳጆችህን ተግተህ ጠብቅ፡፡
ጎሽ ልጄን ለማዳን በሚል ሰበብ፣ ሌሎችን መውጋት፣ ዘዴው የተበላ ዕቁብ ስለሆነ ማንንም እንደማታታልል ዕወቅና ተቆጠብ….
በዚህ ዓይነት ስለ ሁሉም ማስረዳቷን ስትቀጥል፣ ድንገት አውሬዎቹ ሁሉ አጉረመረሙባት!
አንበሳ ከሁሉ በላይ ተቆጣ፡፡
ነብር ሊያንቃት ተቁነጠነጠ፡፡
ዝሆን መሬቱን ይጭር ገባ፡፡
ጎሽ በንዴት ዛፍ እየታከከ፣ ቀበሮን ዘሎ ሊወጋ አሰፍስፏል!
ሁሉም ሊወነጨፉባት እንደሆነ እመት ቀበሮ ስለተገነዘበች፡-
“ጎበዛዝ አውሬዎች ሆይ! እንደው ለጊዜው ተንፍሰን እንሙት ብለን ነው እንጂ የተባላችሁትን እንደማትፈፅሙት‘ኮ እናውቃለን!” አለችና፣ ክልትው ብላ ወድቃ ቀረች!!
* * *
የሚፈልገውን ለማለት የሚችል፣ የታደለ ህዝብ ነው! የሚፈልገውን መመገብ የሚችል የታደለ ህዝብ ነው! የትም ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችል የታደለ ህዝብ ነው፡፡
“ደብዳቤ ቢፅፉት እንደቃል አይሆንም
እንገናኝና ልንገርሽ ሁሉንም”
ለማለት የሚችል የታደለ ህዝብ ነው!
የጠየቀው የሚፈፀምለት የታደለ ህዝብ በመሆኑ ያስቀናል፡፡ ያለ ደጅ-ጥናት፣ ያለ መጉላላት፣ ያለ ድህነት ህይወቱን የሚመራ ህዝብ እጅግ ያስቀናል!
በአገሩ የመጣ ማናቸውም ነገር የሚቆጨው፣ የሚያንገበግበው ምሁር ያለው ህዝብ፣ የተቀደሰ ነው! ለዕድገቱ የሚበጅ ዓይነት ትምህርት የሚማርና ሁሌ ከአትሮንሱ ግርጌ የሚገኝ ህዝብ የታደለ ነው! ይጭነው አጋሠሥ፣ ይለጉመው ፈረስ ያለው ህዝብ ማንንም ያስቀናል!
“ከአገር እኖር ብዬ
ልጅ አሳድግ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ!”
ሳይል፣ ሳይሳቀቅ፣ ሳይገፋ የሚኖር ህዝብ፣ አምላክ የመረቀው ህዝብ ነው!
“ለመቶ ሃምሣ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ፤ አለቀ በላዬ!”
የማትል ምስኪን እናት ያለችው አገር፣ ዕድለኛ አገር ነው! ፍትሑ የተስተካከለ፣ ዲሞክራሲው ያልተበረዘ፣ አስተዳደሩ ያልተዛባ፣ ጤናው የተጠበቀ፣ ልማቱ የሚያኮራ፣ የማይዋሽና የማይዋሽበት ህዝብ፤ ተስፋው የሚለመልም፣ የተመኘው የሚፈፀምለት ህዝብ ነው! አገራችንና ህዝቧ እንዲህ ያለ ፀጋና ባለፀጋነት ትጎናፀፍ ዘንድ፤ የሁላችን ትጋትና ርብርብ፣ የሁላችን የመንፈስ ፅናት፣ የሁላችን የባህል ትሥሥር ሊኖር ይገባል!
አገርና ህዝብ የማሳደግ ጉዞ መቼም ቢሆን አጭር ሆኖ አያውቅም፡፡ አልጋ በአልጋም አይደለም! የምንከፍለው ግብር ተመጣጣኝ ጥቅምና ዕድገት እናገኝ ዘንድ ነው! የምንሄድበት መንገድ እንዲገነባልን፣ የምንገለገልበት መብራትና ውሃ እንዲኖረን፣ ልጆቻችንን የምናስተምርበት ት/ቤትና የምናሳክምበት ሆስፒታል እንዲኖረን ነው ከደሞዛችን፣ ከንግዳችን፣ ከምርታችን ቆጥበን ግብር የምንከፍለው! “እኔ ግብር ከፋይ ነኝ!” ብለን እንድንኮራ ነው ልፋታችን! በእርግጥም “አገሬ ምን ትሠራልኛለች” ማለት ብቻ ሳይሆን፣ “እኔ ለአገሬ ምን እሠራለሁ?” ማለት የሚቻለው ያኔ ነው! ለዚህ አርቆ ማስተዋል፣ አስቦ መራመድ ወሳኝ ነው! ከስሜት ይልቅ ብስለት አያሳጣን የሚባለውም ለዚህ ነው! ለስሜታዊነት፣ ለምሬት፣ ለትኩሳት፣ ለእዚህም እዚያም መነሳሳት የሚገፋፋ መመሪያዎችን፣ አዋጆችንና እርምጃዎችን በላይ በላዩ ከማከል በፊት ቆም ብሎ ማሰብን ብንለምድ መልካም ነው፡፡ በየትኛውም ወገን ያለን የሀገራችን ሰዎች ከስሜት ይልቅ ብስለት አያሳጣን ብለን የምናይበት መንገድ እንሻ!!

Saturday, 27 January 2018 11:52

‹‹…ጤናማ እናትነ ት….››

 እናት ሁሉም ነገር ነች፡፡ እናት መፍትሔ ነች፡፡ እናትነት ዘመን የማይሽረው መቼም የማይቀየር ነገር ነው፡፡ እናትነትን ምንጊዜም …ምንም አያደበዝዘውም። -
ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ
ከላይ የምትመለከቱት ፎቶግራፍ በፊስቱላ ሕመም ምክንያት ሲሰቃዩ የነበሩ ወጣት ሴት ልጆች እና ከሕመሙ ጋር ለረጅም አመታት አብረው የኖሩ አረጋዊት ሴት ታክመው በመዳናቸው የሚያሳዩት የደስታ ሳቅ ነው። የሐምሊን ፊስቱላ መስራች ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን በታካሚዎቹ መካከል ምስላቸው ይታያል፡፡
በዚህ እትም የምናስነብባችሁ የፊስቱላ ታካሚዎች ከሆስፒታሉ ከወጡ በሁዋላ የሚያርፉበት በታጠቅ አካባቢ የሚገኘው የደስታ መንደርን የስራ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመንደሩ ካነጋገርናቸው ባለሙያዎች መካከል ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ  የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ይገኙበታል። ወ/ሮ በለጥሻቸው የደስታ መንደር ምን ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡አንዲት ታካሚ የነገረችንን ታነቡ ዘንድ እነሆ፡፡
‹‹….እኔ እንደተዳርኩ ነበር በአመቱ ያረገዝኩት። ስዳር የአስራ አምት አመት ልጅ ነበርሽ ብለውኛል። ታዲያ በአመቱ ልጅ ተረገዘ፡፡ የመውለጃ ቀኔ ሲደርስ ግን ጭንቅ ሆነ፡፡ በአካባቢዬ የነበሩ የልምድ አዋላጅ እንደገናም በዘመናዊው የማዋለድ ተግባር ሰልጥነዋል ተብሎ ተጠርተው መጡ፡፡ እንግዲህ እሳቸው ተጠርተው የመጡት በሁለተኛው ቀን ነበር፡፡ እሳቸውም አይተው …አ.አ.ይ ቀላል አይመስለ ኝም፡፡ ነገር ግን ልሞክር ብለው አንድ ቀን አደርኩ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ቅርብ ወደሆነው ጤና ጣብያ በሸክም በቃሬዛ ወሰዱኝ፡፡ ታዲያ የተረገዘው ልጅ ሞቶ እኔም እንዳልሆን ሆኜ ተገላገልኩ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ወደቤቴ ተመልሼ ሳለሁ ዝም ብሎ ልብሴ ይበሰብሳል። ሽንትም አይይዘኝም፡፡ የሚበላ የሚጠጣ ሲሰጡኝ ታዲያ ሽንቴ እየበዛ እንዲያውም እየሸተተ አስቸገረ፡፡ እኔም ለሁለት ወር ከተሰቃየሁ በሁዋላ በቃኝ አልበላም አልጠጣም አልኩኝ፡፡ ለምን ቢሉኝ … የሆንኩትን ነገርኩዋቸው፡፡ የአራስነት መስሎኝ እንጂ የሚፈሰው ፈሳሽ ሽታው አስቸግሮኛል አልኩዋቸው፡፡ እንዲያው በሰው ፊት ልቁም ወይም ልቀመጥ …ብቻ ስነሳ ልብሴ በስብሶ በእግሬ ላይ ሽንት ፈስሶ ይገኛል፡፡  ባለቤቴም ወደቤተሰቦቼ ዘንድ መለሰኝ፡፡ የባህል ሕክምናው… ጸበሉ… ሁሉም አልቀረኝ። አንዱም መፍትሔ አልሆነም፡፡ ውሎ አድሮ ግን የሐምሊን ፊስቱላ ሐኪሞች ወደኛም መንደር ደርሰው ነበርና ለሕክምና አመጡኝ፡፡ በ2001/ዓ/ም እንደመጣሁ ታከምኩ፡፡ ለሁለት አመት ከሆስፒታል ከቆየሁ በሁዋላ ወደደስታ መንደር በ2003/ዓ/ም ተዛወርኩ፡፡ አሁን በካፌው ስራ ሰልጥኜ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ወደአገሬም እንዳልመለስ ከሕክምናው መራቅ አልችልም፡፡ አሁን ግን ቤት ተከራይቼ ስራዬን እየሰራሁ ይኼው እኖራለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን ሽንቴንም በላስቲክ ከረጢት አድርገውልኝ ከሰው ጋር እውላለሁ፡፡…››
የታካሚ ምስክርነት
ደስታ መንደር ማለት በፊስቱላ የተጎዱ ወገኖች ዘለቄታዊ  የሆነ እገዛ የሚያገኙበት …እራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትን ሙያ የሚቀስሙበት …ከህብረተሰቡ ጋር ተመልሰው ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን የተለያየ የእደጥበብ ትምህርት የሚማሩበት ተቋም ነው፡፡ ይህ ቦታ በመንግስት ስር ይተዳደር የነበረ ሌላ ተቋም የነበረ ሲሆን በሁዋላ ግን ለዶ/ር ካትሪን ሐምሊንና ለሆስፒታሉ በተለይም የፊስቱላ ሕመማቸው በቀላሉ ለማይድንላቸው ሴቶች የተሰጠበት አላማ ከፊስቱላው ጋር ሲኖሩ በምን ሁኔታ እራሳቸውን ደግፈው መኖር አለባቸው ለሚለው ነበር፡፡ አሁን ግን የታካሚዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ እና በዘላቂነት ለማኖር ከፍተኛ በጀት በማስፈለጉ ምክንያት በዘላቂነት ማኖር አልተቻለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማህበራዊውም አቅጣጫ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡት ታካሚዎች ወደየመጡበት ህብረተሰብ ቢመለሱ የበለጠ ሊጠቀሙ እንዲሁም ሞራላቸው ሊታደስ ይችላል የሚል እምነት ስላለ አስፈላጊው ሕክምና ከተደረገላቸው እና ለመቋቋም የሚያስችላቸው በቂ እውቀት ካገኙ ወደመጡበት አካባቢ በመውሰድ ማቋቋም ይሻላል ወደሚለው ዝንባሌ መሄድ ግድ ሆኖአል፡፡ ስለዚህም ደስታ መንደር ጠንከር ያሉት ታካሚዎች እየተመረጡ ወደሀገራቸው በመሄድ ጤናቸውን ጠብቀው የራሳቸውን ስራ እየሰሩ እንዲኖሩ የሚበቁበት ማእከል ሆኖአል፡፡  ደስታ መንደር የተባለበትም ምክንያት በቆይታቸው ወቅት እስኪያገግሙ ድረስ ደስ እያላቸው ስለሚታከሙ ነው፡፡
ወ/ሮ በለጥሻቸው በመቀጠል እንደገለጹት ከ100 %ታካሚዎች መካከል 4% እና 5 % የሚሆኑትን ታካሚዎች በቀዶ ሕክምና ምንም እንከን ሳይወጣለት ለማዳን እንደማይቻል ሐኪሞች ይመሰክራሉ፡፡ ስለዚህም  ወደመንደሩ የሚላኩት የፊስቱላ ታካሚዎች ከ2-3 ወር ወይንም እስከ አመት ድረስ ሊሆን በሚችል ጊዜ ከፍ ያለ የህክምና ስራ የሚደረግላቸው እና እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከራሳቸው ጋር በመመካከር በዘላቂነት ሽንትን በውጭ ሰውነታቸው በኩል ከልብሳቸው ስር በሚንጠለጠል የላስቲክ ከረጢት  እየተቀበሉ በዘላቂነት እንዲኖሩ የሚመቻችላቸው ናቸው፡፡  ስለዚህም እነዚህ ሴቶች በተፈጥ ሮአዊው መንገድ ሽንታቸውን ማስወገድ የማይችሉ ሲሆን በሚሰጣቸው የላስቲክ  ከረጢት ግን እየተ ቀበሉ በሚኖሩበት ጊዜ ከአሁን ቀደም በሕመም በነበሩበት ጊዜ የነበረው ከማህበረሰቡ መገለል እንዲሁም የጤና እውክታ እና ማህበራዊ ጫና በማይደርስባቸው ሁኔታ እራሳቸውን በመቆጣጠር እና በአቅራቢያ ቸው በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና ክትትላቸውን በማድረግ በጥሩ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲቀጥል አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል፡፡ ከእነዚህ ሴቶች መካከል ድጋሚ ትዳር የሚመሰርቱም አሉ፡፡ በእርግጥ ሽንትን ለማስወገድ የሚጠቀሙበት የላስቲክ ከረጢት የሚመጣው ከውጭ ሀገር ሲሆን እስከአሁን የሚሰጣቸው ግን ከሆስፒታሉ ነው፡፡ አጠቃቀሙም አንዱ ከረጢት ምናልባት ለሶስት ወይም አራት ጊዜ ያህል ሲሆን ከዚያ ባለፈ የሚጣል ነው፡፡ ታካሚዎች በዚህ ሁኔታ የወደፊት ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ በቅድሚያ አስፈላጊው የምክር አገልግሎት ተሰጥቶአቸው ተስማምተው እንዲወስኑ ይደረጋል፡፡
ከዚህ ውሳኔና የቀዶ ሕክምና በሁዋላ ግን ለሶስት ወር በደስታ መንደር ተቀምጠው በቅርብ የህክምና ክትትል እያደረጉ በምን ሁኔታ መገልገል እንዳለባቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ ለኑሮ የሚያግዙ ትምህርቶችን እንዲወስዱ ይደረጋል። በደስታ መንደር ቆይታቸው በጤና በተመሳሳይም ወደፊት እራሳቸውን በምን መንገድ ችለው ወደ ትውልድ መንደራቸው ቀረብ ብለው መኖር ይችላሉ የሚለውን በጥናት በመመስረት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። ሀሳቡ የሚጀምረው ከእነሱ ጋር በመመካከር ሲሆን በአካባቢያቸው ምን ቢሰሩ ያዋጣቸዋል? የሚለው ከግንዛቤ ይገባል፡፡ አነስተኛ ቢሆንም ለስራ መነሻ የሚሆናቸው ገንዘብም ይሰጣቸዋል፡፡
አቶ ጉቱ ሰቦቃ በደስታ መንደር ለሶስት ወር ያህል ከቆዩ በሁዋላ ወደየመንደራቸው ወይንም አካባ ቢያቸው የሚሄዱ ታካሚዎች ከሄዱ በሁዋላ ያለው የኑሮ ሁኔታቸው ምን ይመስላል የሚለውን ክትትል እና ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሕመሙ በዚህ አካባቢ ተብሎ የማይወሰን በሁሉም ክልል የሚፈጠር እንደመሆኑ ታካሚዎች ወደመንደራቸው የሚሰማሩትም በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡ ስለዚህም ወደመጡበት ማህበረሰብ ተመልሰው ኑሮአቸውን እንዲጀምሩ …ተቋርጦ የነበረውን ሕይወት እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡ ሕመሙ ሲገጥማቸው ትዳራቸው የመፍረስ… ንብረታቸው የመበተን አደጋ የሚደርስበት በህብረተሰቡ ዘንድ መገለል እና የማህበራዊ ውም ሆነ ኢኮኖሚያዊው ኑሮአቸው ስለሚ ቋረጥ ይህ ድርጅት ወደአካባቢያቸው ሲመልሳቸው እነዚህ ነገሮች መቶ በመቶም እንኩዋን ባይሆን በተቻለ መጠን ሴቶቹ እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን መንገድ በመፈለግ እንዲቋቋሙ በማድረግ ነው፡፡ ይህ ስራ የሚሰራው ከባለድርሻ አካላት ጋር ነው፡፡ ስራ መስሪያ ቦታ ማግኘት አለባቸው፡፡ የገበያ ትስስር እንፈጥራለን የሚል ቃል ኪዳን ስናገኝ ገንዘብ እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚሰሩት ከሴቶች ጉዳይ ቢሮ… ከሀይማኖት ተቋማት … በቅርብ ከሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር በትብብር እንሰራለን፡፡ እነዚህ ሴቶች ተቋቁመው ስራ ከጀመሩ በሁዋላ በተወሰኑ ጊዜያት ከቤታቸው ድረስ እየሄድን እውነት በአይን የሚታይ ነገር አለ ወይ ? ተግባሩ ከምን ደርሶአል? የሚለውን ክትትል እናደርጋለን፡፡
ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ የደስታ መንደር ስራ አስኪያጅ በስተመጨረሻው የገለጹት አንዲት ሴት ልጅ ተድራ ልጅ ለመውለድ ስትደርስ ጀምሮ ያለው ጥንቃቄ በአካባቢው የሚኖር ሰው ሁሉ ኃላፊነት መሆ ኑን ነው፡፡ የትዳር ጉዋደኛ …ቤተሰብ እንዲሁም የመንደር …አካባቢው ሰው ሁሉ ስለዚያች ልጅ መጨ ነቅ አለበት፡፡ ችላ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አንዲት እናት ደህና ሆነች ማለት ሰፈር ጎረቤቱ… ቤተሰቡ… ዘመድ አዝማዱ ሁሉ ደህና ነው ማለት ስለሆነ ነው፡፡
እናትነት ዘመን የማይሽረው መቼም የማይቀየር ውድ ነገር ነው፡፡ እናትነትን ምንጊዜም …ምንም አያደበዝዘውም፡፡


               “ትራምፕ የልቡን ስለሚናገር እወደዋለሁ” - የኡጋንዳው መሪ ዮሪ ሙሴቬኒ

   የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ናህማት፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በአፍሪካውያን ላይ አስጸያፊ ንግግር ማድረጋቸው አግባብነት የሌለውና የአገራቱ መሪዎች በጋራ የሚያወግዙት ነው ቢሉም፣ የኡጋንዳው መሪ ዮሪ ሙሴቬኒ በአንጻሩ፣”ትራምፕ ምን ይሉኝ ሳይል የልቡን ስለሚናገር እወደዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ” በማለት በዘለፋው አለመቀየማቸውን ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ በቅርቡ አፍሪካውያንንና ሃይቲያውያንን በሚመለከት አስጸያፊ ንግግር ማድረጋቸው በተመድ ሳይቀር መነቀፉን ያስታወሰው ኒውስ 24፤ የህብረቱ ሊቀመንበርም ከትናንት በስቲያ ከአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ፣ ዘለፋው አፍሪካውያንን ያስከፋና የጥላቻ ንግግር ነው፤ ህብረቱም አጥብቆ ያወግዘዋል ያሉ ሲሆን  ህብረቱ በማካሄድ ላይ ያለውን ጉባኤ ሲያጠናቅቅ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
የኡጋንዳው መሪ ዮሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው፣ ትራምፕ አፍሪካውያንን በተመለከተ ያለውን አመለካከትና ስሜት ሳይሸፋፍን እቅጩን ስለሚናገር እወደዋለሁ፤ እኛ አፍሪካውያን ያለብንን ድክመት ለመናገር ቃላት አይመርጥም፣ አካፋን አካፋ ይላል በማለት በትራምፕ ንግግር አለመቀየማቸውን ገልጸዋል ብሏል ዘገባው፡፡