Administrator

Administrator

 አንዳንድ ዕውነቶች ሲያረጁ ተረት ይመስላሉ፡፡ ትምህርትነታቸው ግን ዘመን - ተሻጋሪ ነው፡፡ ባለፈው ዘመን አንድ ሰው ጐረቤቱን በፖለቲካ ሰውነት (በመንግሥት ወጋኝነት) ይጠረጥረዋል፡፡ በጣም ስለሚፈራውም  ግራ ቀኙን እያጣራ ነው መንገድ የሚሄደው፡፡ ሲወጣ ሲገባ ባየው ቁጥር እየተሸማቀቀ ነው የሚያልፈው፡፡ ጐረቤትዬው ኮስታራ ነው፡፡ ግን ሰው ቀና ብሎ አያይም፡፡ ልጆቹ ከልጆቹ ጋር ሊጫወቱ ሲመጡ፤ “እናንተ ልጆች አርፋችሁ ቤታችሁ ተቀመጡ፡፡
ኋላ ጣጣ ታመጡብኛላችሁ!” እያለ ይቆጣቸዋል፡፡ የልጆቹ ኳስ ጐረቤትየው ግቢ ከገባ፤ ጭንቅ ነው። “ይሄዋ እንደፈራሁት መዘዝ ልትጐትቱብኝ ነው!” ብሎ ያፈጥባቸዋል፡፡ ሚስት ትሄድና ኳሱን ታመጣለች፡፡ ጐረቤታሞቹ ሚስቶች ቡና ይጠራራሉ፡፡
ይሄኛው ባል፤ “ኋላ ነግሬሻለሁ፡፡ አፍሽን ሰብስበሽ ተቀመጪ፤ ምን ፍለጋ ቡና እንደሚጠሩሽ አይታወቅም” እያለ ያስጠነቅቃታል፡፡
 “ኧረ እኛ ምንም የፖለቲካ ነገር አናወራም፡፡ ሞኝ አደረከን እንዴ” ትለዋለች ሚስት፡፡
ባል፤  “አሄሄ አይምሰልሽ! ዛሬ ሣር - ቅጠሉ የሰው አፍ ጠባቂ ነው፡፡ ይቺ ሴትዮ እያዋዛች እንዳታወጣጣሽ!”
ሚስት፤
“ቆይ፤ መጀመሪያ ነገር፤ እኔ ምን አለኝና ነው እምታወጣጣኝ? ምን የደበቅኩት ፖለቲካ አለኝ?”
ባል፤
“እኔ አላውቅልሽም ወዳጄ! ብቻ ጠንቀቅ ነው!” ይላትና ይወጣል፡፡
አንድ ቀን እዚሁ ጐረቤት ጠበል ተጠሩ፡፡
ሚስት ለባሏ፤
“ጠበል ተጠርተናል ጐረቤት፡፡ እንሂድ?”
ባል፤ “አልሄድም” ይላል፡፡
ሚስት፤ “አክብረው ጠርተውሃል ምናለ ብትሄድ” ብላ ትሞግተዋለች፡፡
ባል፤ “አልሄድም ብያለሁ አልሄድም”
“እሺ፤ ለምን ቀረህ ቢሉኝ ምን እመልሳለሁ?”
“ትንሽ አሞት ተኝቷል በያቸው በቃ” አለ ቆጣ ብሎ፡፡
 ሚስት ሄደች፡፡ ባል ቀረ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ አጋጣሚ ሆኖ ባል ወደ ሥራ ሊሄድ ውይይት ላይ ተሳፍሯል፡፡ ጫፍ በሩ ጋ ነው የተመቀመጠው፡፡
ጐረቤትየው በዛው ታክሲ ሊሳፈር ይመጣል፡፡ ሳያስበው እግሩን ረግጦት ይገባል፡፡
ይሄኔ ባል ወደ ሰውዬው ዞር አለና፤
“ወንድሜ፤ የከፍተኛ ሊቀመንበር ነህ እንዴ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
“አይደለሁም” ይለዋል ጐረቤትዬው፡፡
“የቀበሌ ሊቀመንበር ነህ?”
“አይደለሁም”
“የአብዮት ጥበቃስ?”
“አይደለሁም”
“እሺ ካድሬ ነህ?”
“አይደለሁም”
“ታዲያ ምናባክ ያራግጥሃል? ና ውጣ ከፈለክ ይዋጣልን!”
“ኧረ ወዳጄ እኔ ምንም ጠብ ውስጥ የምገባ ሰው አይደለሁም፡፡ አሁን የጠየከኝን ሁሉ አንተ ነህ ብዬ ስንት ዘመን ስሰጋና ስፈራህ ኖርኩኮ!” አለው፡፡
*    *    *
ጥርጣሬ ቤቱን የሠራበት ማህበረሰብ ደስተኛና በተስፋ የተሞላ አይሆንም፡፡ መጠራጠርና መፈራራት ባለበት ቦታ ግልጽነት ድርሽ አይልም፡፡ አሜሪካዊው የንግድ ሰው ማክዳግላስ፤ “ጭምት ነብሶችን ትናንሽ ጥርጣሬዎች ለውድቀት ይዳርጓቸዋል፡፡ ጠባብ አመለካከት ያለው፤ ፍርሃት የወረረውና አመንቺ ህብረተሰብ ሽንፈቱን ያረጋገጠ ነው” ይለናል፡፡
“ጠርጥር” የሚል ዘፈን በሚያስደስተው ህብረተሰብ ውስጥ እርግጠኝነትን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ይሄ ሥር ከሰደደ ደግሞ መድሐኒት አይገኝለትም፡፡ “በሽታው ሥር-የሰደደ ከሆነ ሞቱንም መዳኑንም መተንበይ አስተማማኝ አይደለም” ይለናል የግሪኩ የህክምና አባት፤ ሒፖክራተስ፡፡
ጥርጣሬ የበዛበት ማህበረሰብ አገር ለመገንባት አስተማማኝ ኃይል አይሆንም፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማበልፀግ ይከብደዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ድርጊት ጀርባ አንድ ጥርጣሬ እየኖረን ወደፊት መራመድ አይቻልም፡፡ ግልፅነት ከሌለ ዴሞክራሲ ደብዛው ይጠፋል፡፡ ኢፍትሐዊነት ይነግሣል፡፡ ሙስና ያጥጣል። ሚስጥራዊነት ያይላል፡፡ በመጨረሻም፤ “በልቼ ልሙት!” መፈክር ይሆናል!! በሀገራችን ታሪክን እንኳ በጥርጣሬ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የተዘመረላቸው አሉ፡፡ ያልተዘመረላቸው አሉ፡፡ እየተዘመረላቸው የማይታወቁ አሉ፡፡ ለምሳሌ የሰላሌው ጀግና አቢቹ፡፡ አዶልፍ ፓርለሳክ እንደፃፈው፤ “ይቺ አንድ ፍሬ ደጃዝማች! ከኛ በላይ ጀብዱ እየሰራች መሆኑን እንሰማለን!” አሉ አሉ ጃንሆይ፤ ስለ አቢቹ ሲናገሩ፡፡
“አቢቹ ነጋ ነጋ …. ቆሬን ሲወራኒኒ ለቺቱ ነጋ ነጋ …… አምቱን ሲላሊኒ”
“አቢቹ ሰላም ሰላም አቢቹ እሾህ አይውጋህ አቢቹ ክፉ አይይህ አቢቹ ዐይን አያይህ” እንደማለት ነው፡፡
 ይህ የተዘፈነው ለአቢቹ ነው፡፡ ዛሬም ይዘፈናል፡፡ ግን አቢቹን ሰው አያውቀውም “ዛሬ አዝማሪው ሳይቀር ስለራሶች ጀግንነትና ስለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅነት፤ ማንጎራጎሩን ርግፍ አድርጎ ትቶታል…” ይለናል፤ ያው ፀሐፊ፡፡ ልብ ያለው ግን የለም፡፡ ምናልባት የነገሥታቱ
ጀግኖች እንዲወደሱ ሆን ተብሎም ታሪክ ተጋርዶ ይሆናል፡፡ ይሄም ያው ጥርጣሬ ነው፡፡
ስለ መሪዎች ትተን ስለ ህዝብ ወይም ስለ ህዝባዊ ጀግኖች እንዘምር ነው ነገሩ፡፡ ያልነቃ ህብረተረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል፡፡ በዕውቀትና በትምህርት ያልዳበረ ማህበረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል። የማይተማመኑ ፖለቲከኞች ያሉትና የሚመሩት ማህበረሰብ ተጠራጣሪነቱ ያይላል፡፡ በዚህ ላይ ከፖለቲካው ሥርዓት ጋር አለመግባባት ከተጨመረበት ጨርሶ ማበድ ነው፡፡ “ማሰብም ሊገታ ይችላል” እንዳለው ነው ፤ቲዮዶር አዶርኖ-የጀርመኑ ፈላስፋ፡፡ “አንበሳና የበግ ግልገል አብረው ሊተኙ ይችላሉ፡፡ ችግሩ የበግ ግልገሏ እንቅልፍ አይኖራትም” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ እንደተጠራጠረች መንጋቱ ነው ማለታቸው ነው፡፡
ከጥርጣሬ የምንወጣው ዕውነቱን በማወቅ ነው፡፡ መረጃዎች በቀጥታ ሲደርሱ ነው፡፡ መረጃ ሲጠራ ዕውነት ማየት ይጀመራል፡፡ ካልጠራ ጎሾ ያጎሸናል፡፡ የተማሩ ያስተምሩ፡፡ የነቁ ያንቁ፡፡ ያወቁ ያሳውቁ፡፡ “አውራ ዶሮ ራሱ ሳይነቃ ሌላውን አይቀሰቅስም” የሚባለውን ልብ እንበል፡፡

   ጥናቶች ምን ይላሉ?
   የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ተጠሪነቱ ለህዝብ እንደራሴዎች ነው፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ሚዲያ አልሆነም የሚሉ ትችቶችና ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ በ10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ኢቢሲን ጨምሮ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ወገንተኛ መሆን እንዳልቻሉ አመልክቶ
ነበር፡፡ ከሰሞኑም ኮርፖሬሽኑ ያሉበትን ችግሮች የሚቀርፍ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያደርግ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ታዟል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ችግሮች ምንድን ናቸው? ለምን የህዝብ አመኔታ ማግኘት ተሳነው? እንዴትስ ተሻሽሎ የህዝብን ቀልብ መግዛት ይችላል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህራንን አነጋግሮ አስተያየታቸውን
እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡
    
              “የአመለካከት ለውጥ ካልመጣ በቀር ሚዲያው ብቻ አይቀየርም”
               እንግዳወርቅ ታደሰ (በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

     ኢቢሲ እድሜ ጠገብና ግዙፍ ተቋም በመሆኑ በአሁን ውቅት በዘርፉ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራንን ትኩረት የሳበ ሆኗል፡፡ በርካቶች ጥናት ሰርተውበታል፡፡ እኔም ከነዚህ ጥናቶች ተነስቼ ነው አስተያየቶችን የምሰጠው፡፡
በአጠቃላይ ይህ የሚዲያ ነፃነት ችግር የአፍሪካ ሀገራት ችግር ነው፡፡ ደግሞ ከህትመቱ ይልቅ ብሮድካስት ሚዲያው ላይ ችግሩ ይጠነክራል። ጥናቶች ይሄን ያሳያሉ፡፡ የብሮድካስት ሚዲያ ያልተማረውን የህብረተሰብ ክፍልንም ስለሚያዳርሱና ለጠንካራ የሀሳብ መንሸራሸሪያነት ምቹ ስለሆኑ መንግስታት የበለጠ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጉባቸዋል፡፡ የኛም ሀገር ሁኔታ እንዲሁ ነው፡፡ ለምሳሌ የሬዲዮን ጉዳይ ብቻ ነጥለን ብንመለከተው፣ የአፍሪካ መሪዎች ሬዲዮንን በእጅጉ ይፈልጉታል፤ ስለዚህ ለማንም አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም። ይሄን ባህሪ ደግሞ የወረሱት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነው፡፡ እኛ ሀገር ጣሊያን 5 ዓመት በቆየበት የወረራ ጊዜ እንኳን ይህቺን ልምድ ነው ትቶ ያለፈው፡፡ ሳንሱር ማድረግና ሬዲዮውን ለፕሮፓጋንዳ ጥቅም ማዋል የመሳሰሉ ልምዶችን ትቶልን ነው ያለፈው፡፡
የሀገራቱ መንግስታትም ሚዲያን የሚያስፋፉት ከራሳቸው ሁነቶች ጋር በማስተሳሰር ነበር፡፡ ለምሳሌ ቴሌቪዥን የተጀመረው ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጋር በተገናኘ ነበር፡፡ ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ነበር እንጂ በእርግጥም ህዝባችን ሚዲያ ያስፈልገዋል ከሚል መነሻ አልነበረም፡፡ ይሄ ሁኔታ እያደገ መጥቶ ነው አሁን ያለው ችግር ላይ የጣለን፡፡ ጥናቶችም የሚያሳዩት ይሄንን ነው፡፡ አሁንም ጡንቻና አቅም ያለው አካል ሚዲያውን ለመሳሪያነት ይጠቀመዋል። የፕሮፓጋንዳና ፖሊሲ ስርፀት የሚሰራው ሚዲያውን አንቆ በመያዝ ነው፡፡
አንድ ኖርዬአዊ አቢሲ ላይ ያጠናው ጥናት አለ። በጥናቱ ላይ ሌሎች የመንግስት መገናኛ ብዙኃንም ተካተውበታል፡፡ ግለሠቡ በዚህ ጥናቱ፤ ላይቤሪያና ኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛታቸው መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይጠቅሳል፡፡ ሚዲያዎቻቸው የሃገር ውስጥ ጉዳዮችን በስፋት እንደሚዘግቡ ያስቀምጣል፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገሮች ግን የትኩረት አቅጣጫቸው ከውጭ ሚዲያዎች የሚቀዳ ነው ይላል፡፡ ግን ይሄም ቢሆን ሚዲያው ነፃ እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ ከፍተኛ ክፍተት ያለውም አመራሩ ላይ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት እንዳለ ይገልፃል፡፡ እኔም ራሴ ጥናቴን የሰራሁት በዚህ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እንዴት ነው ነፃነት አላችሁ ወይ ብዬ ስጠይቅ፣ “ወቅቱ ክፉ ካልሆነ ነፃ ነን፤ ጠንካራ  ጉዳይ ከተነሣ ግን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ይኖራል” የሚል መልስ ነው ያገኘሁት፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት እንዴት ነው ‹‹ሪፎርም›› ይደረግ የሚባለው? አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቹ አመራሮች የሙያ ብቃትና ችሎታ ያንሣቸዋል። ታማኝ በመሆናቸው ብቻ ወደ አመራርነት ስለሚመጡ ብዙም ለውጥ አያመጡም፡፡ ኢቢሲ ሙያን የመረዳት ውስንነትና በራስ የመተማመን ችግር ያለበት አመራር እንዳለው ጥናቶች በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ አመራሩ ከገዥው መደብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ዋናው ችግርም ይሄ ነው፡፡
ጋዜጠኞቹን ስናይ ሁለት መልክ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለሙያው ብቻ ይተጋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የዚህ ባህሪ የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል በየክፍሉ  የተመደቡ ኤዲተሮች /አዘጋጆች/ አመዳደብም ተፅዕኖ እንደሚያደርግ ግልፅ ነው፡፡ አዘጋጅ ሆነው የሚቀመጡ ሰዎች ብቃት ወሳኝነት አለው፡፡
እኔ አጠቃላይ የአመለካከት ለውጥ ካልመጣ በስተቀር ሚዲያው ብቻ ይቀየራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኔ ለማስተምራቸው ልጆች የምነግረው ወገንተኛ እንዳይሆኑና ሙያውን እንዲያከብሩ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ የኛ ጋዜጠኞች መጀመሪያ በኢኮኖሚ አቅማቸው በሁለት እግራቸው መቆም ይፈልጋሉ፡፡

------------

                     “የኢቢሲ ጋዜጠኞች ነፃነታቸውን ማስከበር አለባቸው”
                       ሄኖክ ንጉሴ (በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር

      ኢቢሲ የጋዜጠኝነትን ንድፈ ሀሳብ ከመከተል አኳያ ብዙ ችግር አለበት፡፡ በ2008 እ.ኤ.አ የመንግስት ሚዲያ ልማታዊ ጋዜጠኝነት እንደሚከተል ታውጆ ነበር፡፡ ኢቢሲም ይሄን እንዲከተል ነው የተባለው። ግን ከልማት ጋዜጠኝነት አተገባበሩ ጋር በተያያዘ ብዙ ጉድለትና ክፍተት አለበት፡፡ አንደኛ የልማት ጋዜጠኝነት በተለያዩ ሀገራት የተለያየ አተረጓጎምና አተገባበር ነው ያለው፤ ቁርጥ ያለ መርህ የለውም። መንግስታት በራሳቸው አካሄድ እንዲተረጉሙት መንገድ የሚከፍት ነው፡፡
ለምሳሌ የፊሊፒንስ መንግስት የልማታዊ ጋዜጠኝነትን በራሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመተርጎም፣ ያንን ለጋዜጠኞች በመስጠት እንዲመሩበት ያደርጋል። የኛም ሀገር እንዲህ ያለ ባህሪ ነው ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ ለባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት በር ይከፍታል፡፡ ጋዜጠኛውን ነፃነት የማሳጣት ነገሮች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡ ኢቢሲም የዚህ ችግር ተጠቂ ሆኖ ነው የምናየው፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ለእንደዚህ ያለ ጣልቃ ገብነት የተጋለጠ ነው፡፡
ኢቢሲ ለፓርላማው በሰጠው ማብራሪያ ጣልቃ እየተገባብኝ ነው ማለቱም ከዚህ አንፃር የሚፈጠር ነው፡፡ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፅንሰ ሀሳብን ለመተግበር ከተፈለገ በራስ ብቻ ከመተርጎም ይልቅ ምሁራንን በሚገባ አነጋግሮ፣ ጋዜጠኞችንም አማክሮና በሚገባ አሰልጥኖ ወደ አሰራር ማምጣት ቢቻል  ውጤታማ ለመሆን ይቻል ነበር፡፡
ለኔ በዋናነት በኢቢሲ የሚታየኝ ችግር የልማታዊ ጋዜጠኝነት ፅንሰ ሀሳብን አዛብቶ ተርጉሞ የመተግበር ነገር ነው፡፡ እኛ በቅርብ ጊዜ በመንግስት ሚዲያዎች ላይ ያከናወንናቸው ጥናቶች ሳይቀሩ የመንግስት ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት እንዳለ ያረጋግጣሉ። ጋዜጠኛው ነፃ እንዲሆን አልተደረገም። ነፃነት ደግሞ ለጋዜጠኛ ዋናው መርህ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ አሁን እየተተገበረ ነው የሚባለው የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሞዴል በድጋሚ ለውይይት  ሊቀርብ ይገባል፡፡
የልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ያቀጭጫል የሚሉ ክርክሮች አሉ። በእርግጥም ይሄን በኛ ሃገርም እየተመለከተነው ነው፡፡ አንድ ባለስልጣን በዚህ ደረጃ ጣልቃ ገብነት ካለው የምርመር ጋዜጠኝነትን ለመስራት አስቸጋሪ ነው ማለት ነው፡፡
ኢቢሲ ውስጥ ባለስልጣናት ጣልቃ እንዳይገቡ የሚገድብ ህግ መኖር አለበት፡፡ ሌላው አቢሲ የህዝብን ፍላጎት አዳምጦ የመዘገብ ባህል ማዳበር አለበት፡፡ ያን ጊዜ ነው ኢቢሲ የህዝብ ነው የሚባለው፡፡ ግጭት ሲኖር የመንግስት ጥቅም እንጂ የህዝብ ጥቅም ሲንፀባረቅበት አይታይም። መነሻቸው የመንግስት ምላሽ ነው እንጂ የህዝብ ቅሬታ አይደለም፡፡ ይሄ ሁሉ የሚስተካከለውና ጣቢያው በተግባር የህዝብ የሚሆነው ነፃነቱን ሲያረጋግጥ ነው፡፡
በሌላ በኩል የኢቢሲ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ከባለስልጣናት ጣልቃ ገብነትም ሆነ ከሌሎች አካላት ለመከላከል የሙያ ማህበር ሊመሰርቱ ይገባል። በአጠቃላይ የሙያው ማህበራት መጠናከርና የራሳቸውን ነፃነት ማስከበር አለባቸው። የጋዜጠኝነት ትልቁ መርህ ነፃነት ነው፡፡ ነፃነትን የምታመጣው በጋራ ሆኖ በመንቀሳቀስ ነው፡፡
አንድ በቅርቡ የተጠና ጥናት፤ በመንግስት ሚዲያዎች ያሉ ጋዜጠኞች የፓርቲ አባላት እንደሆኑና ሙያዊ ጉዳዮችን ሲነጋገሩ፤ ከፓርቲያቸው አሸማቃቂ ትችቶች እንደሚደርስባቸው ያትታል፡፡ ስለዚህ ለሙያው ሳይሆን ለድርጅታዊ መርህ ታማኝ መሆንና እንጀራዬን አጣለሁ ብሎ የመስጋት ችግር እንዳለ ያመላክታል፡፡ ስለዚህ የሙያ ማህበራት መቋቋምና መጠናከር አለባቸው፡፡ ከጣልቃ ገብነትም ራስን ለመከላከል አንዱ መሳሪያ ነው፡፡

---------------

                   “በህዝብ ተአማኒነት ያጣ ሚዲያ እንደሌለ ነው የሚቆጠረው”
                   በለው አንለይ (በሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

      በአንድ ሀገር ውስጥ የዲሞክራሲ ስርአት ለመገንባት፤ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ሙስናን ለመከላከል፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በሀገራችን በመንግሥት ስር በርካታ መገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን ከፓርቲ ፍላጎት ነፃ ሆነው እንዲሰሩ ቢደረግ የተጠቀሱትን ህዝባዊ አገልግሎቶች መስጠት ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢቢሲ ህዝብ የሚፈልገውን ማድረግ አልቻለም፡፡ “የብዝኃነትና የህዳሴ ድምፅ” የሚል መሪ ቃል ባለቤት ቢሆንም ተግባሩ መሪ ቃሉን በትክክል የሚገልፅ አይመስለኝም፡፡
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ንፁስ አንቀፅ 5፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችንና ሀሳቦችን ለማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ እንዲሰራ ይደረጋል ነው የሚለው፡፡ እንግዲህ ኢቢሲም የተመሰረተበት አላማ ይሄው ነው፡፡ በህገ መንግስቱ ኢቢሲ የህዝብ መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። ጥያቄው እንደ ህዝብ መገናኛ ብዙኃንነቱ የህዝብ ሆኗል ወይ የሚለው ነው። እንደ መሪ ቃሉ የብዝኃነት ድምፅ መሆን ችሏል ወይ? ጣቢያው የህዝብ ፍላጎቶችን እያንፀባረቀ አይደለም፡፡ ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት እንደሚነገረው፤ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ተከታትሎ ለህዝብ ማጋለጥ ያለበት ደግሞ የህዝብ የተባለው ኢቢሲ ነው፡፡ እኔ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፤ እስካሁን ኢቢሲ አጋልጦት የታሰረ ወይም ከስልጣኑ የተባረረ ባለስልጣን አናውቅም፡፡ ምናልባት መንግሥት ራሱ ባለሥልጣን ካሰረ በኋላ ነው ከስር ከስር የሚዘግበው እንጂ አስቀድሞ አጋልጦ ሲያቀርብ አላየሁም፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሙከራ ሊኖር ይችላል እንጂ በተግባር በሚገባ ሲውል አናይም፡፡ ይሄ የሚያሳየው የፓርቲ ወገንተኝነት እንደሚያጠቃው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የህዝብ ተአማኒነትን ያሳጣዋል፡፡ እንዲህ ያለ ተአማኒነትን ያጣ ሚዲያ ደግሞ እንደሌለ ነው የሚቆጠረው፡፡ ለአንድ ሚዲያ ተአማኒነትን ከማጣት በላይ የሚጎዳው ነገር የለም፡፡
አሁን ኢቢሲ እንደሚመራበት ጋዜጠኝነት፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ብቻ ነው ብልን ከተረጎምነው ትልቅ አደጋ አለው፡፡ ይሄ ኢቢሲ ከተመሰረተበት የህገ መንግስቱ አላማ ጋርም ይጋጫል፡፡ ጋዜጠኝነት ልማታዊ ጋዜጠኝነት ብቻ አይደለም፡፡ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ቁንፅል ነው፡፡ በኛ ሃገር ልማታዊ ጋዜጠኝነት ለመንግስት እንዲጠቅም ተደርጎ ነው የተተረጎመው፡፡ ጋዜጠኝነት ማለት ሃሳብን መግለፅ ማለት ነው፡፡ ሃሳብን መግለፅ ደግሞ ስለ ልማት ብቻ ማውራት አይደለም፡፡ ይሄ የሚዲያን ታሪካዊ ሚና ወደ ጎን ገሸሽ የሚያደርግ ነው፡፡
ኢቢሲ የህዝብ ሚዲያ እንዲሆን ከተፈለገ ብዙ መድከም ሳያስፈልግ ህገ መንግስቱ ላይ ያለውን ነገር ወደ ተግባር ማውረድ በቂ ነው፡፡ ብዝኃነት ስንል የአስተሳሰብ ብዝኃነትም ስለሆነ የተቃዋሚ ድምፆች እንዲሰሙ ማድረግ የመሳሰሉትን በሙሉ ሽፋን መስጠት አለበት፡፡ይህን ለማድረግ ይሄ ሚዲያ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች መመራት አለበት፡፡ ሁለተኛ በፓርቲና በመንግስት መካከል ያለው ልዩነት በግልፅ መታወቅ መቻል አለበት፡፡
ፓርቲ የራሱን ሚዲያ መመስረት መቻል አለበት። መገናኛ ብዙኃንን የፓርቲ፣ የህዝብ/የመንግስት ወይም ነፃ ሚዲያ ብለን በሶስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ መንግስታዊ/ ህዝባዊ ሚዲያ የምንለው ሙሉ ነፃነት ሊኖረው ይችላል፡፡ የፓርቲ ሚዲያ ግን የፓርቲው አቋም ብቻ የሚንፀባረቅበት ነው የሚሆነው፡፡ ከፓርቲ አመለካከት ውጪ ከሆነ ፓርቲው የራሱን እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር የኛ ሃገር ችግር የፓርቲና የመንግስት/ህዝብ ሚዲያ ልዩነት ጠርቶ አለመቀመጡ ነው፡፡ ይሄ መስመር ከጠራ ብቻ ነው ኢቢሲ ትክክለኛ የህዝብ ሚዲያ መሆን የሚችለው፡፡

-------------

                “የጋዜጠኞች ገለልተኛ አለመሆን ትልቁ ችግር ነው”
                አስማማው አዲስ (በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ጋዜጠኝነት መምህር)

      በቅርቡ የምሁራንንና የሚዲያዎች ግንኙነት ላይ ያተኮረ አንድ ጥናትእያጠናሁ በነበረበት ወቅት ኢቢሲ ተአማኒነቱን ማጣቱን ከጥናቴ ውጤት ተገንዝቤአለሁ፡፡ ለጣቢያው ተአማኒ አለመሆን ዋናው መንስኤ ደግሞ የጋዜጠኞች ከመንግስታዊ አካል ተፅዕኖ ነፃ አለመሆን ነው፡፡ ሁለተኛው ሚዲያው የሚመራበት ፍልስፍና ችግር ነው። ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው የሚለው፡፡ ግን ይሄ በትክክለኛው ትርጉም አልተያዘም፡፡ በመሰረቱ ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሶስት ይከፈላል፡፡ አንደኛው Pro-process የሚባለው ነው፡፡ ይሄ ለሂደቱ ድጋፍ ማድረግ የሚል መርህን ያነገበ ነው፡፡ ከመንግስት ጋር በመሆን ለመንግስት ስትራቴጂዎች አስተዋፅኦ ማድረግ የሚል ነው፡፡  
መንግስት የሚሰራውን ከስር ከስር እየተከታተሉ መዘገብ ማለት ነው፡፡ ሌላኛው የልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ Pro-participation የሚባለው ነው፡፡ ይሄ ዜጎች መብታቸው እንዲከበር አተኩሮ የሚሰራ መርህ ነው፡፡ ሌላኛውና ሶስተኛው Pro-government የሚባለው ነው፡፡ ይሄኛው በመንግስት ፖሊሲ ጥላዎች ስር ሆኖ የመንግስትን ፖሊሲዎች ማስፈፀም ነው፡፡ የኛ ሀገር ሚዲያ በዚህ ስር ያለ ይመስለኛል፡፡ ይሄ በራሱ የጣቢያው ችግር ነው፡፡
በሌላ በኩል የጣቢያው ፕሮግራም ይዘቱ አሰልቺ ነው፡፡ ተደጋጋሚና አታካች ናቸው፡፡ ጣቢያው የጋዜጠኞች የእውቀትና የክህሎት ችግር አለበት፡፡ ይሄን ነው ጥናቴ ያመላከተኝ፡፡ ለዚህ ነው ከምሁራን ጋር እንዳይሰራ የሆነውም፡፡ በጣቢያው ላይ ያለበቂ ጥናትና ምርምር የሚቀርቡ ፕሮግራሞችም በርካታ መሆናቸው በጥናቴ ተመላክቷል፡፡ ይሄ ነው በህዝብ ዘንድ ለትችት የሚዳርገው፡፡
በጋዜጠኝነት ውስጥ ቀላሉ መርህ “እውነትን መናገር” የሚለው ነው፡፡ ይሄ በኛ ሀገር ገና አልመጣም። የባለስልጣናት ጉዳይ እንጂ ህዝብ ጋ ያለ እውነትን ለማግኘት ጥረት አይደረግም፤ የህዝብ እውነታም ሲቀርብ አይስተዋልም። ሌላው የፕሮፓጋንዳ ተጠቂ መሆን ወይም ለፕሮፓጋንዳ ማስተላለፊያነት የተመቻቸ መሆኑ ነው፡፡ ገለልተኝነት ማጣት ሌላው ትልቁ ችግር ነው፡፡ ጋዜጠኞች ከባለስልጣናት ራሳቸውን አለማግለላቸው ይባስ ብሎ ከነሱ ጋር እጅና ጓንት መሆን ይታያል፡፡ ኃይልና ስልጣን ላላቸው ሰዎች ተገዢ የመሆን ነገር ይታያል፡፡ ለህሊና ተገዥ ያለመሆን ችግር በስፋት እንደሚታይ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ አንዳንዴ ባልተፃፉ የጋዜጠኝነት መርህና ህግ ሁሉ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ጣቢያው ልማታዊ ጋዜጠኝነት እከተላለሁ ካለ፣ በሚገባ መርሁን መተግባር አለበት፡፡ ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ ያለበትን ደረጃ ለመግለፅ የሚሰራ ዘገባ፤ ከጊዜው የዘገየ ከሆነ ለምን ዘገየ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ጣቢያው በአጠቃላይ መሻሻል ከፈለገ፣ ጋዜጠኞች ሙሉ ነፃነት ማግኘት አለባቸው። ተቋሙም ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ መቻል አለበት፡፡

--------------

                     ‹‹ኢቢሲ አለቃው ህዝብ ነው››
                      ተሻገር ሽፈራው (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር)

     የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሚመሩት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወጣጡ የቦርድ አባላት ነው፡፡ የቦርድ አባላቱ ከሚዲያዎቹ ህዝቡ ፍትሃዊ የሆነ ዘገባ እንዲቀርብለት፣ በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል፣ የዲሞክራሲ ባህልን እንዲያሣድግ የመሣሰሉ ጉዳዮችን የመከታተል ሃላፊነት አለባቸው፡፡
ይሄ በማቋቋሚያ ደንቦችም ተደንግጓል፡፡ ሚዲያዎቹ የህዝብና ሃብት መሆናቸው፣ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ህዝብን አሳታፊ እንዲሆን በድንጋጌዎቹ ተቀምጠዋል፡፡ አሁን ዋናው ችግር እየታየ ያለው ይሄን ወደ ተግባር መለወጡ ላይ ነው፡፡
በተግባርና በሙያ መርሀ መካከል ያለውን ክፍትት መሙላት ከተቻለና መርሆዎቹ መሬት ከወረዱ እነዚህ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅባቸውን ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ ትልቁ ችግር ይሄ እየተፈፀመ አለመሆኑ ነው፡፡ለምሳሌ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንደተጨባጭ ሁኔታ ትክክለኛና ፍትሃዊ የዜና ሽፋን ማግኘት መብቱ ቢሆንም በተግባር እየታየ ያለው ከተማ ተኮር ወይም ባለስልጣናት ላይ የሚያተኩር ዘገባ ነው የሚቀርበው፡፡ ህዝብ ስለእያንዳንዱ ነገር ማወቅ አለበት፤ ይሄ እየሆነ አይደለም፡፡
በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ መሆን አለበት ስንል የውይይት መድረክ ያዘጋጃል፡፡ በዚህም ሃሣብ ከላይ ወደታች ብቻ ሳይሆን ከታችም ወደ ላይ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ይሄ እስካሁን አልተሠራም። አሁን ግልፅ ልዩነት ያለው በአዋጆቹና በተግባር መካከል ነው፡፡ ያንን ማቀራረብ ከተቻለ ነው የሚፈለገው ለውጥ የሚመጣው፡፡
ኢቢሲ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተጠሪ ሲሆን አለቃው ህዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተግባር ስናየው የመንግስት ቢሮዎች ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት ከፍተኛ ተፅዕኖ ይታይባቸዋል። ከነዚያ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ መረጃዎች ናቸው እንጂ በሚዲያው በኩል ከፍተኛ ግምት ሊሠጣቸው የሚገባው፡፡ እነሱን የሚገዳደር ነገር መምጣት የለበትም፡፡ ኢቢሲ ከመንግስት አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ተፅዕኖ ወጪ መሆን አለበት፡፡ አለቃው ህዝብ ነው፤ ስለዚህ ህዝብ ነው የሚቆጣጠረው እንጂ አስፈፃሚ አካሉ አይደለም፡፡
ዋናው ኢቢሲ እንዲሻሻል ከተፈለገ፤ ሙያዊ ነፃነቱን፣ የጣቢያውን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ማክበር ነው፡፡ ኤዲተሮች/አዘጋጆች ራሳቸውን ከተፅዕኖ ነፃ አውጥተው፣ የተሠጣቸውን የሙያ ነፃነት መርህ በድፍረት ከተገበሩ ነው ሚዲያው የህዝብ መሆን የሚችለው፡፡

     የኢቢሲው ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ጋር ካደረገውና ባለፈው ሳምንት በእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ይቀርባል ተብሎ ከተዋወቀ በኋላ በድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች ውሳኔ ሳይተላለፍ ቀርቷል ከተባለው ቃለመጠይቅ ጋር በተያያዘ በፈቃዱ ስራውን መልቀቁን አስታወቀ፡፡
ላለፉት 4 አመታት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያገለገለው ጋዜጠኛ ብሩክ፣ ከድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ጋር በስራዎቹና በግል ህይወቱ ዙሪያ ያደረገው ቃለ መጠይቅ እንዳይተላለፍ መታገዱ ከፈጠረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ በተቋሙ ውስጥ ለመቀጠል የሚያስችል ሞራላዊ አቅም እንደሌለው በመጥቀስ፣ ስራውን በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ መወሰኑን ትናንት ለድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ ገልጧል፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ በተያዘለት ፕሮግራም አለመተላለፉ ብዙዎችን ያሳዘነና ያስቆጣ ጉዳይ ሲሆን፣ ጋዜጠኛውም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከህሊናው ጋር እየታገለ ስራውን መቀጠል ስለማይችል፣ በገዛ ፈቃዱ ስራውን ለመልቀቅ መወሰኑን በፌስቡክ ገጹ ላይ ትናንት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
“ጉዳዩ አንድን የኪነጥበብ ሰው የማቅረብና ያለማቅረብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የጋዜጠኝነት ልዕልናንም የሚጋፋ ጭምር እንጂ፤ ብዙዎች መስዋዕትነት የከፈሉለትን ሙያ ክብር ለመስጠት ስል ስራዬን የመልቀቅ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ” ብሏል፤ ጋዜጠኛው በዚሁ መረጃው፡፡
ከስራ ለመልቀቅ ሰበብ የሆነውን የቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ በተመለከተ በቅርቡ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ የጠቆመው ጋዜጠኛው፤ ላለፉት አራት አመታት በድርጅቱ በነበረው የስራ ቆይታ መልካም ጊዜ ማሳለፉን በማስታወስ፣ ለድርጅቱ ሰራተኞችና በተለያዩ መንገዶች ከጎኑ ለነበሩ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ጋዜጠኛው በቴዲ አፍሮ መኖሪያ ቤት በመገኘት ከድምጻዊው ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ባለፈው እሁድ በመዝናኛ ፕሮግራም ይተላለፋል የሚለው መረጃ በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት ተሰራጭቶ ብዙዎች ዕለቱን በጉጉት እንዲጠብቁት ቢያደርግም፣ ቃለ መጠይቁ እንዳይተላለፍ መወሰኑን የሚገልጽ ሌላ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ደግሞ ጉዳዩ በድምጻዊው አድናቂዎች ዘንድ በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ቅሬታንና ቁጣን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡
“ኢትዮጵያ” የተሰኘውን አምስተኛ የሙዚቃ አልበሙን በቅርቡ ካወጣው ቴዲ አፍሮ ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ በተመለከተ በማህበራዊ ድረገጾች ከሚሰራጩ መረጃዎች በስተቀር የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አመራሮችም ሆኑ የዝግጅት ክፍሉ ሃላፊዎች በይፋ ያስታወቁት ነገር የለም፡፡


“እምነትና ውኃ እንጂ ቅብዐ ቅዱስም ሜሮንም አልነበረም፤ ሰውዬውም አልቀባኝም”
ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሹመታቸው በፊት ጉዳዩ እንዲጣራ አዝዟል
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመጪው ሐምሌ፣ 16 ኤጲስ ቆጶሳትን ትሾማለች

   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በመጪው ሐምሌ ወር ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙ 16 መነኰሳትንና ቆሞሳትን የመረጠ ሲሆን፤ ከተሿሚዎቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር አባ ኃይለማርያም መለሰ፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ከሃይማኖቱ ውጭ ከኾኑ ሌሎች የእምነት መሪዎች ጋራ “ቅብዓ ቅዱስ ተቀባብተዋል” በሚል የቀረበባቸውን አቤቱታ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ አስተባበሉ፡፡
የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባላት የኾኑ የወንጌላውያን አብያተ እምነት መሪዎች በተገኙበት፣ ባለፈው የካቲት 22 ቀን፣ በአዲስ አበባ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የተካሔደው መርሐ ግብር፣ በሚያሳስቡ የጋራ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር የተዘጋጀ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንጂ፣ የቡራኬና ቀኖናዊ እንዳልነበረ፣ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሳተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያ (ኢኦተቤ-ቴቪ) በሰጡት ማስተባበያ ተናግረዋል፡፡
የመርሐ ግብሩ ጭብጥ፥ “ውኃ ለኹሉም ፍትሐዊ በኾነ መንገድ” በሚል በወርኃ ጾሙ፣ ንጹሕ ውኃ በተለይ ከሰሃራ በታች ላለው ክፍለ አህጉር በፍትሐዊ መንገድ እንዲዳረስና ውኃ ወለድ በሽታዎች እንዲወገዱ ለማሰብ እንደተዘጋጀና ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱም መገኘታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ ሥነ ሥርዓቱን የመሩትም፣ መርሐ ግብሩን እንዲያስተባብሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ በመወከላቸውና በኅብረቱ ተከታታይ መርሐ ግብር ቤተ ክርስቲያኒቱ ተረኛ በመኾኗ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
“ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክዬ፣ ውኃ በእጅጉ አስፈላጊ የእግዚአብሔር ስጦታ ስለመኾኑ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈረውንና በሀገራችን ክርስቲያናዊ ትውፊት በጠበልና በእምነት የሚሰጠውን ፈውስ ተናግሬአለሁ፤” ያሉት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፤ “የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን የምትመራው የኅብረቱ አባል ቤተ ክርስቲያን፣ በመነካካትና በተግባር የምትፈጽማቸው ምልክታዊ መገለጫዎች (symbolic action) አሉ፤ እኔም ተበጥብጦ ከቀረበው ውኃና እምነት በጣቴ ጠቅሼ በተሳታፊዎቹ ግንባር ላይ በትእምርተ መስቀል ምልክት አድርጌያለሁ፤ ይህም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በእምነትና በሥርዓት የሚመስሏት ሌሎች እኅት አብያተ ክርስቲያናትም፣ በመሰል መርሐ ግብሮች ላይ የሚያደርጉትና የተለመደ ነው፤” ብለዋል፡፡
ለሥነ ሥርዓቱ የቀረበው፣ “ቅብዓ ቅዱስ እና ሜሮን ነው፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት ደግሞ በእምነት ከተለዩና ከተወገዙ ሰዎች ጋራ ይህ አይደረግም፤ መርሐ ግብሩም በቤተ መቅደስ ውስጥ መከናወን አልነበረበትም፤” በሚል ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም እንደቀቡና እንደተቀቡ የሚያሳዩ ምስሎችና ትችቶች በማኅበራዊ ድረ ገጽ በስፋት መሰራጨታቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ “ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጅ በፍጹም አልቀባኝም” ሲሉ ተቀብተዋል መባሉን አስተባብለዋል፡፡
“ቅብዓ ቅዱስም ቅብዓ ሜሮንም አልነበረም፤ እነርሱም አይቀበሉም፤ አይፈልጉም፤” ያሉት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ በምስሉ ላይ የሚታየው ሰው ጣቱን ወደ ግንባራቸው ሲያስጠጋ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት የተሾመ ካህን ሌላ ሰው ሊነካውና ሊባርከው እንደማይችል በሹክሹክታ እንደነገሩትና ጣቱን እንደመለሰ ገልጸዋል፡፡  
ሥነ ሥርዓቱ ከተካሔደ ወራት ማስቆጠሩን ያስታወሱት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ ምስሉን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ያሰራጩት ሰዎች፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩ ከኾነ፣ በወቅቱ እንዲብራራላቸው ሊጠይቋቸው ይችሉ እንደነበር ጠቅሰው፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳትን እስከሚመርጥበት ሳምንት በማዘግየትና ከሢመተ ጵጵስናው ጋራ በማገናኘት በድረ ገጽ ማስፋፋታቸው፥ “ግላዊ ጥቅምና ተልእኮ እንዳላቸው ያሳያል፤ እኔን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ክብር ነው የነኩት፤“ ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፤ ለሹመቱም የተመረጡት፣ በቅርበትና በሓላፊነት ላይ ስላሉ ሳይሆን በፈቃደ እግዚአብሔር እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የኤጲስ ቆጶስ ተሿሚው ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም ይህን ይበሉ እንጂ፣ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን መርሐ ግብር ሙሉ በሙሉ የሚያሳይ ቪዲዮ፣ ለሊቃነ ጳጳሳት እና ለሊቃውንት ቀርቦ እንዲጣራ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከትላንት በስቲያ አዝዟል፡፡ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም በኤጲስ ቆጶስነት ቢሾሙም ተመልሰው የሚያገልግሉት ምእመኑን በመኾኑ፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር እንዲሁም የሕዝቡን ኅሊና ነጻ ለማድረግ ሲባል፣ የተነሣው ጥያቄ ከበዓለ ሢመቱ በፊት ምላሽ ማግኘት እንዳለበት፣ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሊቃነ ጳጳሳት ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ተችዎች በበኩላቸው፡- ‹‹አጣርቶ መምረጥ ወይስ መርጦ ማጣራት?›› ሲሉ በዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም ምርጫ ታይቷል ያሉትን የቅደም ተከተል ግድፈት ተችተዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የአራቱ ጉባኤያት መምህርነት ከሚታወቁት ሌላው ዕጩ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ዕዝራ ሐዲስ ጋራ ጎንደርን በመወከል ተወዳድረው፣ ሁለቱም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን እኩል 18 ድምፅ በማግኘታቸው በተጣለው ዕጣ ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል የተባሉት አባ ኃይለ ማርያም፣ በነገረ መለኰት የዶክትሬት ዲግሪ እንዳላቸውና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደኾኑ ተገልጿል፡፡
ግንቦት 2 ቀን የጀመረውን የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት ያጠናቀቀው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎች የሚሾሙ 16 ኤጲስ ቆጶሳትን ከትላንት በስቲያ ኃሙስ የመረጠ ሲኾን፤ ሢመተ ጵጵስናው፣ በመጪው ሐምሌ 9 ቀን እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡ ተሿሚዎቹ፣ ከ31 ተጠቋሚ መነኰሳትና ቆሞሳት መካከል፣ በክህነትና በምንኵስና ሕይወት፥ በትምህርት ዝግጅትና በአገልግሎት ልምድ በአስመራጭ ኮሚቴ ተለይተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደቀረቡና በምሥጢራዊ ድምፅ አሰጣጥ እንደተመረጡ ታውቋል፡፡
ከሢመተ ጵጵስናው በፊት ተሿሚዎቹ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን እየፈተኗት በሚገኙ ዐበይት ወቅታዊ ጉዳዮችና እንደ አባትነታቸው የሚጠበቅባቸውን በተመለከተ፣ የአንድ ወር ሥልጠና እንደሚሰጣቸው፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡



· የህግ የበላይነት ከሌለ ዘመናዊ መንግሥት አይገነባም
            · የዳኝነት ተቋም ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት
            · ፍትህ ሊያገኝ ወደ ፍ/ቤት የመጣ ሰው ሊንገላታ አይገባም
               አቶ ሞላ ዘገየ (የህግ ባለሙያ)

       የህግ የበላይነት ሲባል ምን ማለት ነው? በኛ ሃገርስ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል ወይም እየተረጋገጠ ነው ለማለት የሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሷል?
የህግ የበላይነት ማለት በኔ እምነት በአንድ ሃገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ከህግ በታች መሆናቸውንና በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያመላክት ፅንሠ ሀሳብ ነው። ይሄን ስርአት መገንባት ዜጎች በሃይለኞች በተለይ ከምንም በላይ ሃይል ባለው መንግስት እንዳይጠቁ ዋስትና ይሠጣል፡፡ ያለ ህግ የበላይነት  ዘመናዊ  የመንግስት ስርአት አይገነባም። የህግ የበላይነት ከሌለ ዘመናዊ መንግስት የለም፡፡ በየትኛውም ሃገር መንግስት በህግ ካልተገደበ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ የፈላጭ ቆራጭ ምንጩም ይሄው ነው። ስለዚህ የህግ የበላይነት ማለት ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡
የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ደግሞ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ አንዱ ፍ/ቤት ነው፣ ከፍ/ቤት ጋር ደግሞ አቃቤቢ ህግ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት፣ ጠበቆች እንዲሁም ሚዲያ መኖር አለባቸው፡፡ ፍ/ቤት በህገ መንግስቱ የተደነገገ ነፃነት አለው፡፡ አሁን ጥያቄው በእርግጥስ በተግባር ነፃነቱ ተከብሯል ወይ የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ህገ መንግስቱ መሬት ላይ ወርዷል ወይ? በኔ እምነት ይሄ አልተተገበረም፡፡
ይሄን በምሳሌዎች ሊያብራሩት ይችላሉ?
በሚገባ! ለምሣሌ እስከ ዛሬ ዳኞች እንዴት ነው የሚመለመሉት? የዳኞች አመላመልና አሿሿም ግልፅነት ይጎድለዋል፡፡ ሊሆን ይገባዋል ብዬ የማምነው አንድ ዳኛ የሚሆን ሰው መመልመል ያለበት በግል ነው፡፡ ለዳኝነት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች በግልፅ ወጥተው እነዚህ መለኪያዎች በአደባባይ በሚዲያ ጭምር ማስታወቂያ ወጥቶ፣ እነዚህን መለኪያዎች አሟላለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ አመልክቶ፣ በየደረጃው ተጣርቶ፣ መመዘኛውን የሚያሟሉ ጥቂቶች ብቻ ተመርጠው፣ አግባብ ባለው አካል አማካኝነት ለፓርላማ ቀርበው መሾም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለምሳሌ አንድ እጩ በተማረበት ት/ቤት፣ በሚኖርበት ሰፈር በግልፅ ፎቶግራፉ ተለጥፎ፣ ዜጎች በሰውየው ላይ አስተያየት መስጠት አለባቸው፡፡ ዜጎች በግልፅ በሰውየው ላይ ባህሪውን፣ አስተዳደጉን፣ ስነምግባሩን በተመለከተ አስተያየታቸውን ሊሠጡ ይችላሉ፡፡
በዚህ መንገድ መመልመሉ ሰውየው ላይ ህዝብ እምነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ሌላው የእድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ዳኝነት ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ በከፍተኛ ፍ/ቤት የሚሾም ሰው ከማንም የፖለቲካ ስልጣን የተለየ ከባድ ሃላፊነት ነው ያለበት፡፡ ከማንኛውም ባለስልጣን በተለየ የመጨረሻውን ፍርድ የሚሠጥ ዳኛ፣ የሞት ፍርድና ንብረትን የሚያሳጣ ፍርድ የሚወስን ዳኛን እንዲህ በቀላሉ መመደብ አይገባም። ባህሪ፣ እድሜ፣ የስራ ልምድ ተደማምረው ነው ዳኛ መሾም ያለበት፡፡ አሁን ባለው አሠራር ይሄን ልምድ አላይም፡፡ ግልፅ አይደለም፡፡
የእድሜ ጉዳይ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው?
ለምሳሌ በ20ዎቹ ውስጥ ያለን ሰው በዳኝነት አስቀምጦ፣ የትዳር ጉዳይ እንዲዳኝ ቢቀርብለት እንዴት ነው የሚዳኘው? ምን ልምድ አለው? አላገባም! አያውቀውም፤ እንዴት ነው ነገሮችን የሚገነዘበውና የሚያመዛዝነው? ይሄን ስል ስለ ትዳር ለመወሠን ሁሉም ዳኛ ማግባት አለበት ማለቴ አይደለም፡፡ እድሜ ለማመዛዘን ወሣኝነት አለው፡፡ እድሜ የልምድ ጥርቅም ነው፡፡
ሌላው አንድ አዲስ ወጣት ዳኛ፤ መጀመሪያ በረዳት ዳኝነት መስራት አለበት፡፡ ይሄን ስል አንዳንድ ከእድሜያቸው በላይ የበሠሉ ወጣት ዳኞች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ በኔ እምነት አንድ ሠው በዳኝነት መንበር ላይ ተቀምጦ ውሣኔ ለመስጠት፣ እድሜው ከ30 አመት በታች መሆን የለበትም ባይ ነኝ፡፡ 30 ዓመት የኖረ ሰው የህይወት ልምድ ይኖረዋል። በ30 ዓመቱ በረዳት ዳኝነት ተሹሞ በትንሹ ለ3 እና 4 ዓመት ቢሠራና በ35 አመቱ የዳኝነት ሃላፊነት ቢወስድ፣ የቀረበለትን ጉዳይ አመዛዝኖ መርምሮ መወሰን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እድሜን ሣነሳ ለእኔ የሚያሳስበኝ የማገናዘብ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ በጥብቅና ስራ 28 አመቴ ነው እና ብዙ የምታዘባቸው ነገሮች ስላሉ ነው ይሄን የምለው፡፡
በሌላ በኩል ዳኞች በግልጽ መስፈርት ይለዩ የምልበት ምክንያት ደግሞ ይሄ አሁን ገለልተኛ አይደሉም የሚለውን ሃሜት ያስቀረዋል፤ እስካሁንም በግልፅ ቢሠራ የፍትህ አካሉ ለዚህ ሃሜት አይዳረግም ነበር፡፡
የዳኝነት ተቋሙ አሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህል ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ነው ብለው ያስባሉ?
ይሄ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የዳኝነት ተቋም ነፃነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይሄን ማረጋገጡ የሚታየው ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ነው፡፡ እኛ ሀገር ዳኝነቱ ነፃነት የለውም የሚለው ሃሜት የበረከተው በሚታዩ ነገሮች መነሻነት ነው፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች ዳኞች ነፃነታቸውን የሚያስጠብቅ የሙያ ማህበር አላቸው፡፡ እኛ ሀገር የለም፡፡ ይሄ ማህበር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ማህበሩ ከምን ይጠብቃቸዋል ከተባለ አንደኛ በህሊናቸው ተመርተው ህግን መሰረት አድርገው በሰጡት ውሳኔ የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመከላከል ያስችላቸዋል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጥቅማጥቅማቸውን ለማስከበር ይረዳቸዋል፡፡
ዳኞች የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ከተፈለገ ይህ የሙያ ማህበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዳኛ ህግን መሰረት አድርጎ ውሳኔ ለመስጠት ከውሳኔው በኋላ በስራዬ፣ በህይወቴ፣ በቤተሰቤ ምንም ነገር አይደርስብኝም የሚል መተማመን ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ በራስ መተማመን ሊፈጠር የሚችለው በማህበር ተደራጅቶ፣ ራሱን መከላከል ሲችል ነው፡፡ ይሄ አሁን ባለው ሁኔታ እኛ ሀገር የለም። የህግ የበላይነትን ለማምጣት ከሆነ ጥረቱ አሁንም አንድ ገለልተኛ የሆነ ኮሚሽን በአስቸኳይ ተቋቁሞ የእስከ ዛሬውን የዳኞችን አሰራር የሚገመግምና አጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን ችግሮች የፈተሸ ሪፖርት ማቅረብ አለበት፡፡ ነፃ የሆነ የማንኛውም የፖለቲካ ተፅዕኖ የሌለበት፣ ይህ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ ዳኝነቱ ነፃ የሚወጣበትን መፍትሄ የሚያፈላልግ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት አቅርቦ በፖለቲካ ተፅዕኖ ስር የወደቀው የዳኝነት ስርአቱ ነፃ የሚወጣበት መፍትሄ መበጀት አለበት፡፡ የዳኝነት ተቋሙ በህገ መንግስቱ መሰረት በነፃነት ስራውን ሰርቷል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል ወይ የሚለው  የሁልጊዜ ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ የሚችለው ይህ ገለልተኛ ተቋም የሚያቀርበውን የምርመራ ሪፖርት መነሻ አድርጎ ሊወሰዱ በሚችሉ እርምጃዎች ብቻ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ችግሩን ከእነ መፍትሄው ማቅረብ አለበት። አሁን ሁሉም ሰው ያሉትን ችግሮች በራሱ እይታ ነው የሚተረጉመው፡፡ ሊቋቋም ይገባዋል ብዬ የማምነው ገለልተኛ ኮሚሽን፤ የዳኞች አሿሿምን፣ የፖሊስ አሠራርን፣ የአቃቤ ህግ አሰራርን፣ የጠበቆች አሠራርን፣ የማረሚያ ቤት አሰራርን፣ በጥልቀት የሚፈትሽና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ የሚያወጣ መሆን አለበት፡፡ ይሄ በአስቸኳይ ካልተፈፀመ ስለ ህግ የበላይነት የሚነሡ ጥያቄዎች ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡
ብዙዎቹ የሃገሪቱ ችግሮች የሚመነጩት’ኮ በሃገራችን የህግ የበላይነት ባለመኖሩ ብቻ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የለም ማለት ደግሞ ፍትህ የለም ማለት ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ይህቺን ሃገር ያስተዳደሩና የገዙ መንግስታት አንዱ ትልቁ ችግራቸውና ድክመታቸው እንዲሁም ሊወቀሡበት የሚገባቸው ከፓርቲና ከመንግስት ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን አለመፍጠራቸው ነው፡፡ አሁንም እነዚህ የሉም። ምናልባት ሙከራዎች ሊደረጉ ይችላሉ እንጂ ነፃ ተቋማት የሉም፡፡
ከዚህ በመነሣት ነው የሃገራችን ችግር የህግ የበላይነት አለመኖር ነው የምለው፡፡ የህግ የበላይነት የሌለው ደግሞ የፍትህ ተቋማት ከፖለቲካ ነፃ ሆነው መስራት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ በዚህ በሚቋቋመው ኮሚሽን አማካኝነት መጣራት አለበት። ደህንነቱን ከፖለቲካ ጫና ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ የፍትህ አካሉ ለምንድን ነው ተደጋግሞ የሚወቀሠው የሚለው በአፋጣኝ የመጨረሻ ምላሽ ማግኘት አለበት።
ሰሞኑን 7ኛው የፍትህ ሣምንት መሪ ቃል፤ ‹‹የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሠላምና ለህዝቦች አንድነት›› ይላል፤ ይሄ አስገራሚ ነው፡፡ ይሄንን ማረጋገጥ ያለበት ገለልተኛ ኮሚሽን ነው፡፡
ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው ዳኛ የተከበሩ ሲባል ከርሞ፣ አንድ ቀን ደግሞ ጠበቃ የሚሆነው። ይሄ ስህተት ነው፡፡ አንድ ጊዜ በዳኝነት ወንበር ላይ የተቀመጠ ሰው የሚሞተው እዚያው በዳኝነቱ ወንበር ላይ ነው እንጂ ዳኛ ሆኖ ወደ ጠበቃ መምጣት ለፍትህ አሠጣጡም ተገቢ አይሆንም፡፡ ፍትህ ይዛባል። አላማቸው ጠበቃ መሆን ስለሆነ ፍትህ ይዛባል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳኝነት ኑሮ መሻሻል አለበት። ዳኛ ስለሚበላውና ቤተሠቡን ስለሚመግበው መጨነቅ የለበት፡፡ ሁሉም ሊሟላለት ይገባል፡፡ ሃሳቡ በሙሉ ዳኝነቱ ላይ መሆን አለበት፡፡ እኛ ሃገር ግን የምንታዘበው፤ የሞት ፍርድ የፈረደ ዳኛ፣ ከሰው ጋር ታክሲ ተጋፍቶ ሲሳፈርና በእግሩ ሲሄድ ነው፡፡ ይሄ መሆን የለበትም፡፡ የዳኞች ኑሮ በእጅጉ መሻሻል አለበት፡፡
እርስዎ እንደ ጠበቃ በዳኞች አካባቢ የሚታዩ ጉድለቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
በጣም ጠንቃቃና ችሎቱን ስነስርአት የሚያስይዙ ጎበዝ ዳኞች ያሉትን ያህል ዳኛ ይሁኑ ባለጉዳይ የማይለዩ፣ በአለባበሳቸውም ዳኛ የማይመስሉ ሰዎችም አሉ፡፡ በነገራችን ላይ በፍ/ቤቶች የአለባበስ መመሪያ መኖር አለበት፡፡ እኔ ከምታዘበው ነገር ከኔ ጀምሮ ችሎት ስንቆም ከረባት አናስርም፡፡ ይሄ ስህተት ነው። የአለባበስ መመሪያ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ በፍ/ቤት ስንቆም “የተከበሩ … ጌታዬ” የምንለው እኮ ግለሰቡን አይደለም፤ ተቋሙን ነው፡፡ እዚያ ተቋም ውስጥ ያለ ሰው ደግሞ ይሄን ክብር የሚመጥን ሆኖ መቅረብ አለበት፡፡ ሌላው ሳልናገር የማላልፈው በፍ/ቤቶች ያለው የመፀዳጃ ቤት ችግር፣ የካፍቴሪያ ችግር ነው። ዳኞቻችን ወደድንም ጠላንም ክብር ይገባቸዋል፤ በፓርላማ የተሾሙ የተከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄንን ክብራቸውን የሚመጥን አገልግሎት ነው በስራ ቦታቸው ማግኘት ያለባቸው፡፡ የላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጠው ልንመለከታቸው አይገባም። እኔ እንኳ ስለዚህ ነገር መናገር ከጀመርኩ ከዓመት በላይ ሆኖኛል፤ ግን ሰሚ የለም፡፡ ከፍ/ቤት በላይ ምን የሚከበር ተቋም ሊኖር ይችላል! የለም ስለዚህ ፍ/ቤቶች የሚገባቸውን ክብር የሚመጥን አደረጃጀትና አገልግሎት መስጫዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ሌላው የዳኞች ስነ ምግባር መታሰብ አለበት። አንዳንዶች ያመናጭቃሉ፣ ያልተገባ ንግግር ይጠቀማሉ፣ ሰዎችን ስሜታዊ ያደርጋሉ፤ እንዲህ ያሉ ዳኞች ሊታረሙ ይገባቸዋል፡፡
ሌላው በተደጋጋሚ የሚታየው ችግር የአሰራሮች አለመስተካከል፣ ደንበኞችን ማጉላላታቸው ነው። ከመቅረፀ ድምፅ ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ይቅረብ ይባልና የቀጠሮ ምልልስ ይፈጠራል፤ ይሄ ለፍትህ አሰጣጡ ተግዳሮት ነው፡፡ ሌላው የምታዘበው ነገር ባለጉዳይና ጠበቃ የሚመካከሩበት ቦታ የለም፡፡ ይሄ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ፍ/ቤት አካባቢ የመመካከሪያ ቦታ ሊኖር ይገባል። በአጠቃላይ የፍ/ቤት ግቢዎች ለፍትህ አሰጣጡ አመቺ የሆኑ ነገሮች ተሟልተው የሚገኙባቸው አይደሉም፡፡ ይሄ አሳሳቢ ነው፡፡
ሌላው የፍ/ቤት ሰራተኞች ደንበኞች የማመናጨቅ፣ የመገፈታተርና የተለያዩ ችግሮች ይፈጥራሉ፤ ይሄ መታረም ያለበት ነው፡፡ ፍትህ ሊያገኝ ወደ ፍ/ቤት የመጣ ሰው ሊንገላታ አይገባውም፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት አጠቃላይ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ ሰብሳቢው የዱር አራዊት ሁሉ ሊቀመንበር አያ አንበሶ ነው፡፡ ስብሰባው እንዲኖር ያዘዘው ግን የሁሉም የበላይ የሆነው አምላክ ነው፡፡
አራዊቱ ሁሉ ንቅል ብለው ከጫካው መጥተዋል፡፡ አያ አንበሶ በነብሮ አማካኝነት የምዝገባ ቁጥጥር እንዲደረግ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የስብሰባ መቆጣጠሪያ ላይ ሁሉም ተገኝተው ኤሊ ግን አልመጣችም፡፡ የኤሊን መቅረት ለማጣራት የተወሰኑ አራዊት ተሰማሩ፡፡ ዝንጀሮና ጦጣ አንድ ላይ አገኟት፡፡
“እመት ኤሊ”
“አቤት”
“ከስብሰባው በመቅረትሽ የዱር አራዊት ሁሉ ተቀይመውሻል፤ ማንን ተማምና ነው? እያሉ ነው!”
“እኔ የተማመንኩት ተፈጥሮን ነው፡፡ እዚህ የድንጋይ መከላከያ ዋሻ ውስጥ ሆኜ ማን ይነካኛል?” አለች፡፡
“እሺ ይሄንን መልስሺን ለአምላክ እንነግራለን!” ብለዋት ይሄዳሉ!
አምላክ የኤሊን ነገር ሲሰማ “ትምጣና ፍርዷን ትስማ” አለ፡፡
ኤሊ የግዷን እየተንጓፈፈች መጣች፡፡
አምላክም፤
“ለፈፀምሺው ከፍተኛ ድፍረት አንድ ከባድ ፍርድ ይገባሻል፡፡ በዚህም የዱር አራዊት ሁሉ ትምህርት ሊያገኙ ይገባል፡፡ በዚህ መሰረት እመት ኤሊ ከዛሬ ጀምሮ እሸሸግበታለሁ ያልሺውን ድንጋይ ለብሰሽ ኑሪ! ይህ ህግ የማይሻር የማይለወጥ ይሁን” አለ፡፡
ብዙዎቹ የዱር አራዊቶች የፍርድ ማቃለያ ጠየቁላት፤ አንዳንዶቹ፤ “አውቃ ሳይሆን ተሳስታ ነው” አሉ፡፡
ከፊሎቹ፤
“የድንጋይ ዋሻ የመጨረሻው መጠለያዋ መስሏት ነው” አሉ፡፡
ሌሎቹ፤ “ስለ አምላክ ታላቅነት ያላት ዕውቀት ውሱን በመሆኑ ነው” አሉና ተማፀኑ፡፡ አምላክ ግን “ትምህርት ማግኘት አለባት” አለ፤ ኮስተር ብሎ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኤሊ ዕድሜ ልኳን ድንጋይ እንደለበሰች ትኖራለች፡፡
*   *   *
በዚህም ሆነ በዚያ ከህግ መሸሽ ያስጠይቃል፡፡ ያስቀጣልም፡፡ ይግባኝ የሌለው ከባድ ቅጣት! ታስቦ፣ ወንጀል ልፈፅም ተብሎ፣ ሁነኛ ጥፋት ተደርጎ የተፈፀመ ድርጊት ነው! ማጣፊያው የሚያጥረውም ለዚህ ነው!
የየትኛውም ወገን የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት ትልቁን ስዕል (The Bigger Picture) ማየት እንደሚችሉ የገባቸው አይመስሉም፡፡ ብዙ ግትር የሚመስሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንኮታኩተዋል! ያሉ ሲመስላቸው የሉም፡፡ ተፅዕኖ ያሳደሩ ሲመስላቸው ዜሮ ግፊት ብቻ (Zero degree pressure) ነው ያላቸው፡፡ የመግባባት አቅማቸው ደካማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሁኔታዎችን ጠንቅቆ አውቆ የመጠቀም ዘዴ ከቶም የእነሱ ባለመሆኑ ነው፡፡ የድንጋይ ምሽግ ይዣለሁ ብሎ መተማመንና ማን ይነካኛል ማለት “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚለውን የጠዋት ተረት እየናቁ መውደቅ ነው፡፡ በወገናዊነት መረብ (በኔትዎርክ) አገር አይገነባም፡፡ ምክንያቱም ኔትዎርኩን ለመበጣጠስ ደፋ-ቀና ሲባል ሊሰራ የሚገባው ቁልፍ ቁልፍ ሥራ ሳይከናወን ይቀራል፡፡ አገር ወደ ኋላ ትቀራለች፡፡ የጉዳዮችን ቅደም ተከተል ማበጀት አንዱ ወሳኝ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህም ብልህነትን ይጠይቃል፡፡ የህዳሴው ግድብ ዐቢይ ራዕይ መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ ሆኖም ከሥሩ መከናወን ያለባቸውን ሌሎች ቁልፍ ተግባራት የምንሸፍንበት ወይም ድክመታችንን  ላለማሳየት ጭምብል የምናጠልቅበት (masking one’s own weaknesses) ዘዴ መሆን የለበትም፡፡ በየአደባባዩ መሪ መፈክሮችን በማስገርና ጠላቶቻችን ያልናቸውን በማውገዝ፣ የራሳችንን ጥፋት ለመከለል መሞከር አንድ ቀን መጋለጡ አይቀሬ ነው፡፡ (They shout at most against the vices they themselves are guilty of እንዲሉ ፈረንጆቹ) የቡድነኝነትም ሆነ የመንገኝነት ስሜት ለሀገር አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ግብዓት አይፈጥሩም፡፡ ይልቁንም የገነባነውን ይሸረሽራሉ፡፡
ዶ/ር  አበራ ጀምበሩ፤ ‹‹ብቸኛ ሰው›› ጽሁፋቸው ላይ ፀሐፌ ትዕዛዝ ተፈራ ወርቅ ኪዳነወልድ ቅሬታቸውን ሲገልጡ፤ ‹‹የሥራ ቅንነት፣ ትጋትና ግለት እየቀዘቀዘ መሄድ፤ ተረስቶና ሞቶ የነበረው የቤተ - መንግሥት ተንኮል እንደገና ነፍስ ዘርቶ፣ ለብዙ መልካም ስራዎች እንቅፋት መሆኑ፣ የወገን የመከፋፈል መንፈስ በብዙ ሰዎች ማደሩ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ለመማር ዝግጁ ከሆንን አሁንም ጊዜ አለ፡፡ ውሃ ወቀጣውን እንተው፡፡ ሁልጊዜ የእነ እገሌ ጥፋት ነው ማለትን በርትተን እናስወግደው፡፡ ራሳችንን ለማዳን ኳሱን ወደ ሌሎች በመወርወር የተሻለ ፍሬ አናፈራም፡፡ ይልቁንም የወረወርነው ቀስት መልሶ ወደ ራሳችን ይመለስና ይወጋናል- ቡመራንግ (Boomerang)፡፡ አዳዲስ ሹማምንት ሥልጣን ላይ በተቀመጡ ቁጥር በአሮጌዎቹ ባለሥልጣናት ላይ እንከንና አቃቂር በማውጣት፣ የራስን ንፁህነት ለማሳየት መጣጠር ለጊዜው የዋሐንን ይማርክ እንደሆን እንጂ ዘላቂ የልማት መሳሪያ አይሆንም፡፡ ውስጣችን ከፊውዳላዊ አስተሳሰብ ሳይፀዳ ዲሞክራሲያዊነትን፤ ብሎም ፍትሐዊነትን ከዚያም ልማታዊነትን ማፍራት አይቻልም፡፡ በዘመነ በዛንታይን፣ የሮማን መንግሥት የካቶሊክ ስርዓት ፀሐፍት ሲተቹ፤ “The Holy Roman Empire is neither Holy nor Roman nor an Empire” ይሉ ነበር፡፡ ቅዱስ ሮማዊ ግዛት ተባለ እንጂ ቅዱስም አልነበረም፡፡ ሮማዊም አልነበረም፡፡ ግዛትም አልነበረውም ማለታቸው ነው፤ በስላቅ! ከውሃ ወቀጣው ግምገማ መውጣት አለብን፡፡ አዲስ አመለካከት እናምጣ፡፡ ለአስተሳሰብ ፈጣሪዎች (Thinkers) ዕድል እንስጥ፡፡ አለበለዚያ አሮጌው አመለካከት አረንቋ ውስጥ እንደተቸከልን እንቀራለን፡፡ ‹‹አንድን ግንድ አሥር ዓመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም›› የሚባለው ለዚህ ነው!

 በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች አገሮች ቅድመ እርግዝና የጤና ምርመራ አልተለመደም። ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት የሚቆጠረው ደግሞ ቅድመ እርግዝና ምርመራ ሊደረግ ይገባዋል የሚለው እውቀት በብዙዎች ዘንድ አለመኖሩ ነው።
                ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ የ
                ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
      ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና መምህር ለዚህ እትም እንግዳ ናቸው። እሳቸው እንዳሉትም ሴቶች እርግዝናን ሲያስቡ አስቀድመው ሊዘጋጁባቸው  ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ዋናው የጤና ጉዳይ ነው። አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት ሙሉ የጤና ምርመራ ብታደርግ እጅግ በጣም ጥሩ እርምጃ ይሆናል። ነገር ግን ይህንን የሚያደርጉት እናቶች በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በአደጉት አገሮች ጭምር በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከዚህም ምክንያቶች አንዱ ከ50% በላይ እርግዝ ናዎች ሳይታቀዱ የሚከሰቱ መሆኑ ነው። ለእርግዝና እቅድ ሳይያዝለት የሚከሰት ሲሆን ደግሞ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ መሆኑ እሙን ነው። በጤናው ፣በማህበ ራዊው ፣በኢኮኖሚው ጭምር ከእርግዝና ቀጥሎ ምን ሊደረግ ነው? የሚለው እርግዝና መኖሩ ከታወቀ በሁዋላ የሚደረግ ምክክር መሆኑ የተለመደ ነው። ነገር ግን ይህ በከፊል እናቶች በሰላም የእርግዝና ጊዜያቸውን ጨርሰው እንዲወልዱ ሲችሉ ብዙዎች ደግሞ የተለያዩ ችግሮች እንዲገጥማቸው ያደርጋል።
ዌብ ሜድ የተሰኘው ድረገጽ እንደሚያመለክተው ከእርግዝና በፊት የጤና ምርመራ ማካሄድ ለሚወለደው ልጅ ከመወለዱ በፊትና ከተወለደ በኋላም ለሚኖረው ጤናማ የሆነ ሕይወት እጅግ ጠቃሚ ነው። እርግዝናው ከተፈጠረ በሁዋላ የተለያዩ የጤና ችግሮች መኖራቸው ቢታወቅ ከጽንሱ ጋር በተያያዘ የእናትየውንም ሕይወት ውስብስብ ችግር ላይ ይጥላል።
ጤናን በተመለከተ ለእናትየው የሚደረገው ቅድመ ምርመራ እና ለሴትየዋ ከሚደረግላት ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
ሴትየዋ እርግዝናውን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ሆና እስከመጨረሻው ድረስ በሰላም ትደርሳለች ወይ የሚለውን አስቀድሞ ለማወቅ ይረዳል።
እርግዝና ሲመጣ ቀድሞ የነበሩ የጤና ጉዳዮች ካሉ እነዚያን ሕመሞች ተቆጣጥሮና አስተካክሎ ለእናትየውም ሆነ ለጽንሱ ችግር እንዳይገጥማቸው ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳል።
ቅድመ እርግዝና ባሉ ሕመሞች ምክንያት የሚወሰዱ መድሀኒቶች ከእርግዝናው ጋር አብረው መቀጠል የማይችሉ ከሆነ እነዚያን መድሀኒቶች ለማስተካከል ይረዳል። ብለዋል ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ።
ብዙ ጊዜ እርግዝና ለምን ሳይታቀድ ይከሰታል የሚል ጥያቄ ሲነሳ በተለይም ባልና ሚስት ከሆኑ መቼም ይምጣ መቼ ...ትዳር የመሰረትነው ልጅ ለመውለድ ስለሆነ ስጋት የለብንም ሊሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ጋብቻ የፈጸሙ ሰዎች ሁሉ መውለድ አለባቸው ከሚል ድምዳሜ የሚደረስበት ሁኔታም ይታያል። አንዳንዶች በተለይም በኢትዮጵያ ማርገዝ ልቻል አልቻል ሳላውቅ ምርመራ ምን ያደርጋል የሚባልበት ሁኔታም ይስተዋላል። እንዲያውም አንዳንዶች እርግዝናው ገፍቶ እስኪታወቅ ድረስ ወደሐኪም ቤት መሔድ የማይፈልጉም አሉ። ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም እንደ ዶ/ር ድልአየሁ። ስለዚህ ሳያቅዱ መውለድ ባይለመድ እና ከእርግዝና በፊት ቅድመ እርግዝና ማድረግ ተገቢ መሆኑን ቢያውቁ ሁሉም ሴቶች ቅድመ እርግዝና የጤና ምርመራ ሳያደርጉ ማርገዝን አይደግፉም።
የተለያዩ ሕመሞች እርግዝናን ከዳር አድርሶ ልጅ ለመቀበል ሳያበቁ ወይ ጽንሱ እንዲቋረጥ አለዚያም በእናትየው ሕይወት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ስለዚህም ቅድመ እርግዝና የህክምና ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የህመም አይነቶች የሚከተሉት የተወሰኑት ናቸው።
የስኩዋር ሕመም፡-
አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት የስኩዋር ሕመም ካለባት እና ስኩዋሩ በጥሩ ቁጥጥር ላይ ባለበት ሁኔታ ካላረገዘች የሚያመጣው ተጽእኖ አስከፊ ነው። ከስኩዋሩ ጋር በተገናኛ ጽንሱ ላይ ሊከሰት የሚችለው የአፈጣጠር ጉዳቶች ሁሉ አስቀድሞውኑ ቁጥጥርና ክትትል ከተደረገ ይቀንሳል።
ደም ግፊት፡-
አንዲት እናት የደም ግፊትዋ ጥሩ ቁጥጥር ላይ እያለ ካረገዘች ጽንሱም ላይ ሆነ እራስዋ ላይ ችግር የመፈጠሩ አጋጣሚ በጣም ይቀንሳል። አንዳንድ የደም ግፊት መድሀኒቶች በእርግዝና ጊዜ የማይመከሩ ሲሆን እነዚህ መድሀኒቶች በተለይም የመጀመሪያዎች የእርግዝና ሳምንታት ላይ ጽንሱ ላይ ችግር ያመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ ቀድማ ለምርመራ ከቀረበች ግን ሁኔታዎች ሊስተካከሉ ይችላሉ።
የደም መርጋት፡-
የደም መርጋት ችግር ያለባቸው እናቶች ከሚወስዱዋቸው መድሀኒቶች ውስጥ የተወሰኑት በተለይም የመጀመሪዎች የእርግዝና ወራት ላይ ባይወሰዱ ይመከራል። ይህንን በአስፈላጊ መድሀኒት ለመለወጥ መወሰን የሚቻለው ግን እናትየው ቅድመ እርግዝና ምርመራ ለማድረግ ወደሆስፒታል ከሄደች ነው።
ቅድመ እርግዝና ምርመራ ማድረግ ተገቢ የሚሆንባቸው ሌሎችም ብዙ ሕመሞችና የሚወሰዱ መድሀኒቶች አሉ። ለምሳሌም እንደልብ ሕመም ያሉት የእናትየውንም ሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የታወቁ እና ከፍተኛ የህክምና ክትትል የሚደረግባቸው ሕመሞች ያሉአት ሴት እነዚህ ሕመሞች ያሉበት ደረጃ ስለመስተካከላቸው የሐኪም የይሁንታ መልስ እስኪያገኙ ድረስ እርግዝናው እንዳይከሰት ለማድረግ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ሁኔታም ይኖራል።
ዌብ ሜድ የተሰኘው ድረገጽ እንደሚገልጸው ቅድመ እርግዝና የጤና ምርመራ በሚደረግበት ወቅት እናቶች ለሐኪማቸው ሊመልሱት የሚገባ የተለያየ ጥያቄ ይነሳል።
ከስነተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዘ ጥያቄ፡-
የመጀመሪያው ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ነው። ለመሆኑ የወር አበባ መቼ እንደሚመጣ የምታውቅበት ቀን መቁጠሪያ አዘጋጅታለች?
ስትጠቀም የነበረው የእርግዝና መከላከያ አይነት ምንድነው?
ከአሁን ቀደም በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፍ በሽታ ታማ ታውቃለች?ወይንስ? የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት አለባቸው።
ከእርግዝና ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች ፡-
ከዚህ በፊት የነበረው እርግዝና በምን ሁኔታ ተቋጨ? ተወልዶአል አልተወለደም? ውርጃ ነበረ? ...ወዘተ
ከዚህ በፊት ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ጊዜ ፣ከወሊድ በሁዋላ ተፈጥሮ የነበረ የመንፈስ ጭንቀት አለ?ወይንስ?
ከዚህ በፊት የተወለደ ልጅ ካለ የጤናው ጉዳይ ምን ይመስላል? የጤና እክል አለ?ወይንስ?
የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። እነዚህ ችግሮች ትክክለኛውን መልስ ካገኙ በድጋሚ እንዳፈጠሩ ጥረት ይደረጋል።
የጤና ሁኔታ ጥያቄዎች፡-
በጤና ጉዳይ የሚነሱ ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። ነገር ግን ዋና ዋናዎቹ አስም ፣የደም ግፊት ፣ስኩዋር ፣የልብ ሕመም ፣የደም መርጋት የመሳሰሉት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን ቀደም የተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ካሉ እና ከማደንዘዣ ጋር የተገናኘ አለመስማማት ከነበረ አስቀድሞ መታወቅ አለበት።
ሕክምና በሚደረግበት ወቅት ከሚሰጡ መድሀኒቶች አለመስማማት መኖር አለመኖሩም መረጋገጥ ይገባዋል። ከአሁን ቀደም ከምትወስዳቸው መድሀኒቶች ውስጥ የትኞቹ አለመስማማት ወይንም አለርጂክ እንደፈጠረባት ታውቆ ወደእርግዝናው ከመግባትዋ በፊት የሚስማማት መድሀኒት ካልተለወጠላት ወይንም መጠኑ ዝቅ ወይንም ከፍ ማለት የሚገባውም ከሆነ አስቀድሞ ካልተስተካከለ ለጽንሱ አስጊ ሊሆን ይችላል።
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች ጥያቄዎችን ከእርግዝና በፊት ለሐኪሙ ማስረዳት የእናትየውንም ሆነ የጽንሱን ሕይወትና ሙሉ ጤነኛነት ለማረጋገጥ ያስችላል።

  በደቡብ ሱዳን ለአራት አመታት ያህል በዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ በአገራቸው እና ከአገራቸው ውጪ የተፈናቀሉ የአገሪቱ ህጻናት ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ በታህሳስ ወር 2013 በተቀሰቀሰውና ይህ ነው የሚባል ዘላቂ መፍትሄ ሳይገኝለት ለአመታት በቀጠለው የእርስ በእርስ ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች ወደ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና  ሱዳን እንዲሰደዱ ማድረጉን  የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ ስደተኞች መካከልም ከ62 በመቶ ወይም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን ገልጧል፡፡
የእርስ በእርስ ጦርነቱ ሌሎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ህጻናትንም በአገራቸው ውስጥ ከመኖሪያ ስፍራቸው ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅትና የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ማስታወቃቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
የእርስ በእርስ ግጨቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን መገደላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የተፈናቀሉ አጠቃላይ ዜጎች ቁጥርም 3.5 ሚሊዮን እንደሚደርስ አስታውቋል፡፡

መዝናኛው ኢንዱስትሪ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ያቀደቺው ሳኡዲ አረቢያ፣ በአይነቱ ልዩ የሆነና የላስ ቬጋስን ያህል ስፋት ይኖረዋል የተባለውን ግዙፍ የመዝናኛ ከተማ ግንባታ ከስድስት ወራት በኋላ እንደምትጀምር መነገሩን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከመዲናዋ ሪያድ በስተደቡብ አቅራቢያ በሚገኝ 334 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ስፍራ ላይ የሚቆረቆረውና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ የሚደረግበት ይህ ልዩ የመዝናኛ ከተማ፤ ለነዋሪዎችና ለውጭ አገራት ጎብኝዎች የተለያዩ የመዝናኛ፣ የስፖርትና የባህላዊ ትርዒቶች አገልግሎት እንደሚሰጥ ዘገባው አስታውቋል፡፡
እጅግ ማራኪ ፓርኮች እንደሚኖሩት የተነገረለት ይህ ግዙፍ መዝናኛ ከተማ፣ አለማቀፍ ተፈላጊነት እንደሚኖረውና ለአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ አዳዲስ የገቢ አማራጮችንና የኢኮኖሚ መስኮችን በማስፋፋት ኢኮኖሚዋን ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ አቅዳ እየሰራች እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ የዚህ ጥረት አንዱ አካል የሆነው የግዙፍ የመዝናኛ ከተማ ግንባታ ፕሮጀክት በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

  የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በተለያዩ ብሄራዊ፣ አህጉራዊና አለማቀፍ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲያንቀላፉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚያሰራጩና በታላቁ መሪያችን ላይ የሚያላግጡ ሰዎች ተሳስተዋል፣ ሙጋቤ በስብሰባዎች ላይ አይናቸውን ገርበብ ስለሚያደርጉ ያንቀላፉ ይመስላሉ እንጂ በጭራሽ አይተኙም ሲሉ የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ አስተባብለዋል፡፡
“ታላቁ መሪያችን አይኖቻቸው የብርሃን ጨረሮችን የመቋቋም አቅም ስለሌላቸው በተደጋጋሚ አይኖቻቸውን ገርበብ ስለሚያደርጉና ጎንበስ ስለሚሉ ያንቀላፉ ይመስላሉ እንጂ፣ ብዙዎች በማህበራዊ ድረገጾች እንደሚያብጠለጥሏቸው ስብሰባቸውን አቋርጠው አያንቀላፉም” ሲሉ የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ፣ ሄራልድ ለተባለው የአገሪቱ መንግስት ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ እርጅና ተጫጭኗቸው አቅም ቢከዳቸውም በቀጣዩ አመት በሚካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ታጥቀው መነሳታቸውንና ስልጣናቸውን እንደዋዛ ለማንም እንማያስረክቡ ያስታወቁት የ93 አመቱ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፤ ሰሞኑን ለአይን ህክምና ወደ ሲንጋፖር ማቅናታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሙጋቤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ እና የአረብ-አፍሪካ ጉባኤን ጨምሮ በበርካታ አህጉራዊና አለማቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ እንቅልፍ ወስዷቸው የሚያሳዩ አስቂኝ ፎቶግራፎችና የቪዲዮ ምስሎች በተለያዩ ድረገጾች ላይ በስፋት ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡