Administrator

Administrator

በጋና 208 የመንግስት መኪኖች የገቡበት ሳይታወቅ ጠፍተው መቅረታቸው መረጋገጡን ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ከአሁን በኋላ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ለባለስልጣናት አገልግሎት የሚሰጡ አዳዲስ መኪኖች እንዳይገዙና አሮጌዎቹ ጥቅም መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የወጣባቸው ቪ ኤይት እና ፕራዶ የመሳሰሉ ውድ መኪኖች የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ ባስተላለፉት ውሳኔ፣ የህዝብ ሃብት እየባከነ በመሆኑ ከአሁን በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡ አዳዲስ መኪኖች አይገዙም ብለዋል፡፡
ስልጣኑን የለቀቀው መንግስት 707 የመንግስት መኪኖችን ለአዲሱ የአገሪቱ መንግስት ማስረከቡን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአዶ መንግስት ስልጣን መያዙን ተከትሎ በተደረገ የሃብት ቆጠራ 234 መኪኖች መጥፋታቸው መረጋገጡንና የተወሰኑት በፍለጋ ሲገኙ የተቀሩት 208 መኪኖች ግን አሁንም ድረስ እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳይታወቅ የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸውን ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ፖሊስና ጉምሩክን ጨምሮ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ግለሰቦችን በአባልነት የያዘ ልዩ ግብረ ሃይል አዋቅሮ የጠፉትን መኪኖች የማፈላለግና ከጉዳዩ ጋር ንክኪ ያላቸውን የቀድሞም ሆነ የአሁኑ የጋና መንግስት ባለስልጣናትን በቁጥጥር ስር አውሎ፣ ለህግ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝም ዘገባው ገልጧል፡፡

ካርሎስ ቀበሮው በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀውና ከአለማችን ቀንደኛ ገዳዮች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ኢሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝ፣ ከ43 አመታት በፊት በፓሪስ በሚገኝ የገበያ ማዕከል በፈጸመው አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ባለፈው ማክሰኞ ለ3ኛ ጊዜ የዕድሜ ልክ እስራት ቅጣት እንደተጣለበት አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1974 የተከሰተውንና 2 ሰዎች ለሞት፣ 34 ሰዎች ደግሞ ለመቁሰል አደጋ የተዳረጉበትን የቦምብ ጥቃት ፈጽሟል በሚል ክስ ተመስርቶበት ፓሪስ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበውና ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሎ የተከራከረው ካርሎስ፤ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ተጨማሪ የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበት ዘገባው ገልጧል፡፡
ካርሎስ ችሎቱ ከመሰየሙ ከሰዓታት በፊት፣ “ይህ እጅግ የሚገርምና ከአራት አስርት አመታት በፊት ተፈጸመ በተባለ ወንጀል ላይ የሚከናወን ወለፈንዲ የሆነ የፍርድ ሂደት ነው” በማለት ችሎቱን ያጣጣለ ቢሆንም፣ የዕድሜ ልክ እስራት ፍርዱ መወሰኑንና ይህን ተከትሎም ጠበቆቹ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ማስታወቃቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ከ23 አመታት በፊት በፈረንሳይ ልዩ ሃይል ክትትል በካርቱም በቁጥጥር ስር የዋለው ቬንዙዋላዊው አደገኛ ገዳይ ካርሎስ በ1970 ዎቹ እና 80 ዎቹ በፈጸማቸውና ባስፈጸማቸው በርካታ የግድያ ወንጀሎች ለሁለት ጊዚያት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ከዚያ ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ የ67 አመቱ ካርሎስ፣ ከሳምንታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ሙያህ ምንድን ነው በሚል ከችሎቱ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “ብቁ አብዮተኛ” ሲል ምላሽ የሰጠ ሲሆን ዕድሜውን ሲጠየቅም፣ “17 ነው፤ ደስ ካላችሁ 50 አመት ጨምሩበት” ሲል ማላገጡን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ውይይት ይደረጋል
እናት የማስታወቂያ ድርጅት፣ የጀርመን የባህል ማዕከልና ወመዘክር በትብብር በሚያዘጋጁት የንባብ ፕሮግራም ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ‹‹ቤት ያጣው ቤተኛ››የተሰኘው የዮናስ ጎርፌ መፅሀፍ ላይ በወመዘክር አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡ በዕለቱ የውይይት የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርበው የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀፍሬ ስብሀት እንደሆነ የገለፀው እናት የማስታወቂያ ድርጅት ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ጋብዟል፡፡

በምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን የተዘጋጀውና “የማንነት ዜማ” የተሰኘው የኪነ ጥበብ ምሽት የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡ በምሽቱ የበገና ድርደራ፣ የዋሽንት፣ የክራር፣ የመሰንቆና የመለከት ጨዋታዎች ለታዳሚ እንደሚቀርብም አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ምሽት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ ወግና ዲስኩር የሚያቀርቡ ሲሆን ገጣሚ ነቢይ መኮንን ወግ ያቀርባል ተብሏል፡፡ በዚህ የባህል፣ የትውፊትና የጥበብ ምሽት ላይ ፍላጎት ያለው እንዲታደም አዘጋጁ ጋብዟል፡፡

በ2016 የኖቤል ሽልማት በስነጽሁፍ ዘርፍ አሸናፊ የሆነውና ስራ ስለበዛብኝ ሽልማቱን ለመቀበል አልችልም በማለት በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ሳይገኝ የቀረው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ደራሲ ቦብ ዲላን፣ ከወራት ማንገራገር በኋላ ሰሞኑን ሽልማቱን ለመቀበል መስማማቱ ተዘግቧል፡፡
ባልተለመደ ሁኔታ ስለ ሽልማቱ ምንም አይነት አስተያየት ሳይሰጥ በመቆየቱና ሽልማቱን ባለመቀበሉ ብዙዎችን ሲያነጋግር የቆየው ቦብ ዲላን፤ አሸናፊነቱ በይፋ ከታወጀ ከአምስት ወራት በኋላ ስቶክሆልም ወደሚገኘው የኖቤል ተቋም በማምራት ሽልማቱን ለመቀበል መወሰኑን ቢቢሲ ገልጧል፡፡
የ75 አመቱ ቦብ ዳይላን በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ በስቶክሆልም ሁለት የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እንደሚያቀርብ የጠቆመው ዘገባው፣ እግረ መንገዱን  የ900 ሺህ ዶላር ሽልማቱን ይቀበላል ተብሏል፡፡
በተቋሙ ህግ መሰረት የኖቤል ተሸላሚ የሆነ ሰው በአንድ ዩኒቨርሲቲ በእንግድነት ተጋብዞ ትምህርት ካልሰጠ የሽልማት ገንዘቡን እንደማያገኝ ያመለከተው  ዘገባው፤ ዲላን ግን በአካል ተገኝቶ ለማስተማር እንደማይችል ጠቁሙ ይሄም ሆኖ ግን ትምህርቱን በቪዲዮ ቀርጾ ለማስተላለፍ ማቀዱን ገልጧል፡፡
ዲላን በኖቤል የስነጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያው አሜሪካዊ የዘፈን ግጥም ደራሲ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ በ1993 በስነጽሁፍ ዘርፍ ከተሸለመው የረጅም ልቦለድ ደራሲው ቶኒ ሞሪሰን በመቀጠል በዘርፉ ለሽልማት የበቃ አሜሪካዊ መሆኑንም አስታውሷል፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን፤ አመሻሹ ላይ አንድ የተራበ ተኩላ የሚበላ ነገር ባገኝ ብሎ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር፣ ድንገት አንድ ግቢ ውስጥ የህፃን ልጅ ድምፅ ይሰማል፡፡ ግራ ቀኝ ቃኝቶ ማንም በአካባቢው እንደሌለና እንደማይታይ አረጋግጦ፤ ቀስ ብሎ ኮሽታ ሳያሰማ ወደ ግቢው ይገባል፡፡ ወደ መስኮቱ ተጠጋና ከቤት ውስጥ የሚሰማውን ድምፅ በጥሞና ማዳመጥ ይጀምራል፡፡
ህፃኑ አሁንም እያለቀሰ ነው፡፡ እናትየው ልታባብለው ትሞክራለች፡፡
‹‹ማሙሽዬ ዝም በል፤ ነገ የማረግልህን አታውቅም፡፡ ከረሜላ፣ ብስኩት፣ እገዛልሀለሁ፡፡ ግን ማልቀስህን ካቆምክ ነው፡፡ እሺ?›› ማሙሽ አልተበገረም፡፡ ብስኩቱም ከረሜላውም ሊያማልለው አልቻለም፡፡
እናት ትዕግሥቷን ጨረሰችና፤
‹‹እንግዲህ ዋ! ውጪ ላለው ተኩላ ነው የምወረውርህ!›› አለችው፡፡
ተኩላ ይሄን ሲሰማ ልቡ ጮቤ ረገጠች፡፡
‹‹አሃ ልጁን ሊወረውሩልኝ ነው፡፡ እራቴን የምበላው ላገኝ ነው ማለት ነው!›› አለ፡፡ በፀጥታ መጠበቁን ቀጠለ፡፡
መስኮቱ ሥር ሆኖ ኮሽ ባለ ቁጥር እየቋመጠ ቀና ይላል፡፡ ምንም የለም፡፡ በጊዜ ለማይለካ ጊዜ በረሀብና በጉምዥት እያዛጋ ጠበቀ፡፡ ልጁ አልተወረወረለትም፡፡
እየመሸ ሲሄድ ልጁ እየተረጋጋላት ሲመጣ፤ እናትየዋ፤
‹‹ጎበዝ የኔ ልጅ!! ያ ተኩላ ቢመጣ በጭራሽ ልጄን አልሰጠውም፡፡ አንተ ፀባይ ያለህ ቆንጅዬ ልጅ ነህ፡፡ በል እንዲሞቅህ ቢጃማህን ድርብርብ አድርገህ አልጋህ ውስጥ ግባና ለጥ በል፡፡ እሺ የእኔ ቆንጆ?››
ልጁም፤
‹‹እሺ እማዬ ለጥ እላለሁ!›› አለና ተኛ፡፡ ተኩላው በጣም ተናደደ፡፡
‹‹በጣም የሚያሳዝነው እነዚህ ሰዎች ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብዬ ልቤን ማውለቄ! ከእንግዲህ የዚያ ቤት ሰዎች የሚናገሩትን አንድም ቃል አላምንም!›› ብሎ ግቢውን ለቅቆ ወጣ!
*   *   *
ተጨባጭና ላም አለኝ በሰማይ ተስፋን መለየት፣ ካሮትና ዱላን ማወቅ፣ ዋናና አቋራጭ መንገድን ልብ ማለት ዋና ነገር ነው፡፡ አገኛለሁ ተብለው የሚጠበቁና የማይጠበቁ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ሰጪዎች በዋዛ የማይለቋቸው፣ ተቀባዮች ሲመኙዋቸው የሚኖሩ አያሌ ጉዳዮች እንዳሉ አለመርሳት ነው፡፡ ልጅ ራበኝ ብሎ ማልቀሱ፣ የፈለገውን ካልሰጣችሁኝ ብሎ ማልቀሱ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ እናት ማባበሏና እንዲተኛ ማድረጓ ግን የእናትነት ኃላፊነትና ፍቅር ነው፡፡ ህዝብ የሚጠይቃቸው ነገሮች አያሌ ናቸው፡፡ አንዳንዴ አልቅሶ ይጠይቃል፡፡ አንዳንዴ ጮኾ ይጠይቃል። አንዳንዴ በምሬት ይጠይቃል፡፡ ሁሉንም ጥያቄዎች እንደየጠባያቸው መልስ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የራሱና ራሱ ነጥቆ የሚወስዳቸው እንደ ሰብዓዊ መብቶችና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያሉ ቁልፍ ነገሮች መኖራቸውን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ህዝቡ ራሱም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የእኔ ነው የሚለውንና ጎደለብኝ የሚለውን ለይቶ ማወቁ ነው ጥያቄዎችን እንዲያነሳ የሚያደርገው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ተቋማት፣ የሙያ ተቋማት፣ ፓርቲዎች፤ አጋዥ ኃይላት ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ በወግ በወግ ሆነው፣ “ጋን በጠጠር ይደገፋል” የሚሉና በጥበባዊ ስልት የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ተግተው የሚረዱ መሆን አለባቸው፡፡
መግባባትን፣ መቻቻልን፣ ዕርቅን፣ ትዕግሥትን፣ የጊዜ አጠቃቀምን ማወቅ አለባቸው፡፡ በመንግሥት በኩል ህዝብ ምሬት ደረጃ እስኪደርስ፣ የኑሮ ውድነቱ አንገፈገፈኝ እስኪል፣ ቸል ብሎ ማየት ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎችን አለመገንዘብ ነው፡፡ ሁኔታዎችን አለመገንዘብ ኋላ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልና ዋጋም እንደሚያስከፍል ልብ ማለት የልባሞች ክህሎት ነው፡፡
በሀገራችን ውስጥ የምናካሂዳቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አብዮቶች የተሣሠሩ ካልሆኑ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ እንደገና ይበተናሉና፡፡ የሁሉም ግብ አገርን ማዘመን ነው፡፡ ይህም የህዝብ ህይወት የተሻለ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
ዳንኤል ለርነር የተባለ ፀሐፊ፤ ስለ ዝመና ሲናገር፤ “ዝመና እጅግ መልከ - ብዙ ሂደት ሲሆን በሁሉም የሰው ልጅ ሀሳብና እንቅስቃሴ ውስጥ ያለና ተጠቃሽ ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹ ፍሬ ጉዳዮቹ፡- ከተማዊነትን ማበልፀግ (urbanization) ኢንዱስትሪያዊነት፣ ዓለማዊ ይዞታን ማሳደግ፣ ዲሞክራሲን ማስፋፋት፣ ትምህርትን ማራባትና የሚዲያ ተሳትፎን ማጎልበት ሲሆኑ፤ ቁም ነገሩ ግን ሁሉም የሚያድጉት ከተጣመሩና ከተሳሰሩ መሆኑ ላይ ነው” ይለናል፡፡ ዝምድናቸውና ሰምሮ - ተጓዥነታቸውን በትጋት መከታተል ያሻል፡፡
የእነዚህን ፍሬ ጉዳዮች ዕድገት ማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ ህዝብን አምኖ የህዝብን ተሳትፎ በእያንዳንዳቸው ውስጥ በአስተማማኝ መንገድ ማሳየት ሲቻል ነው፡፡ እንደ ድሮው ዘመን ፖለቲካዊ ንትርክ፤ “ሥርዝ ያንተ፣ ድልዝ የእኔ፣ እመጫት የእሷ፤ ሆያ - ሆዬ የሰፊው ህዝብ!” ብለን የምናልፈው ነገር አይደለም፡፡ ህዝብን ሳይዙ ጉዞ “እንሥራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” እንደሚባለው ዓይነት ነው። በየዘመኑ በተደጋጋሚ “ህዝብን ማገልገል” ፣ “ህዝባዊነት”፣ “ህዝባዊ ተሳትፎ”፣ “ዲሞክራሲያዊ አሳታፊነት”፣ “አረንጓዴ ዘመቻ”፣ “የኢኮኖሚ አብዮት”፣ “የባህል አብዮት” ወዘተ … ሲባል እንሰማለን። የዚህ ሁሉ መቋጫ ግን አንድ ጥያቄ ነው፡፡ “በተግባር አለ ወይ? አፍአዊ ነው ልባዊ?” የሚለው ነው። የሀገራችን ዕውነታ አብዛኛውን ጊዜ አሉታዊ መልስ እንዳለው ነው የሚያመላክተን፡፡ ወረቀት ላይ እንጂ መሬት ላይ የለም፡፡ ለምን ተብሎ ሲጠየቅ፤ በርካታ ምክኖችን መደርደር ቢቻልም አንዱ ዐቢይ ምክን ሐቀኛ ተግባሪ መጥፋቱ ነው! የወሬ ሰው መብዛቱ ነው፡፡ ለታይታና ለአደባባይ እይታ አለሁ አለሁ ባዩ መበርከቱ ነው! ደስኳሪው ከአንድ ቦይ እንደሚፈስ ውሃ የሚለፈለፍ ንግግር ሚዲያውን መሙላቱ ነው! ሁሉን መነካካት፣ ስለ ሁሉም ማውራት፤ በተጨባጭ  ምንም ፍሬ አለመያዝ… እየተለመደ መጥቷል፡፡ የለብ - ለብ ፖለቲካ፣ የለብ ለብ ኢኮኖሚ፣ የለብ ለብ ቢሮክራሲያዊ ዘመቻ ተጠናውቶናል፡፡ “ተሸክመዋል እንዳይባል በብብታቸው፣ ፈጭተዋል እንዳይባል ግማሽ ቁና” የሚለው ተረት የሚያስረዳን ይሄንኑ ነው!  

“በፓርቲያችንእንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ይፈጥርብናል”
አቶ አበበ አካሉ
(የ”ሰማያዊ” የውጭ ግንኙነት ኃላፊ)

የፓርቲ ስብሰባ ላይ ሆነን ነው የመረጃ ቋቶቻችንን ከፍተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለ4 ወራት መራዘሙን ያየነው፡፡ በጣም ነበር ያዘነው፡፡ መንግስት በሀገሪቱ ምንም አይነት ችግር የለም እያለ በሚዲያዎች እየነገረን፣ አዋጁን በድጋሚ ለ4 ወር ማራዘሙ ሀገሪቱ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ያሳያል፡፡ ሁሉም ነገር ተረጋግቷል፤ሰላም አለ፤በተባለበት ሰአት አዋጁን ማራዘም ለሀገሪቱም አይጠቅምም፤የፖለቲካ ምህዳሩንም ያጠባል፡፡ ለወደፊት የሚታሰሩ ሰዎችም ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ ሰላም ሰፍኗል እያሉ አዋጁን የማራዘም ጉዳይ እንዴት እንዳዩት እኛ አናውቅም፡፡ ሰላም ነው ከተባለ ማራዘሙ ተገቢ አይደለም፡፡
የአዋጁ መራዘም በፓርቲያችን እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋትና ስጋት ይፈጥርብናል፡፡ በየክልሉ ተንቀሳቅሰን የፓርቲውን ስራ መስራት አለብን፣ ከህዝብ ዘንድ መድረስ አለብን፡፡ ይሄን ለማድረግ እንዴት ፍቃድ እናገኛለን፡፡ ይሄ በጣም ይከብዳል። በጣም ያሳስበናል፡፡ ፓርቲያችን በዚህ ጉዳይ ተሰብስቦና መክሮበት አቋሙን በመግለጫ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡

=================================

“የአዋጁ መራዘም ለኔ አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው”

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ ሊቀመንበር)

የአዋጁ መራዘም ለኔ አስደንጋጭ ነው፡፡ የስጋታችንን ደረጃ የበለጠ እያጠለቀው ነው፡፡ እነሱ ተሃድሶአችንን እያጠለቅን ነው እንደሚሉት ሁሉ የኛም ስጋት እንዲሁ ደረጃው እየጠለቀ ነው ያለው፡፡ ይሄ አዋጅ መፍትሄ አይሆንም፡፡ እነሱ ህዝብን አስገድዶ እየገዙ መኖር የሚለውን የቻይናዎች ፍልስፍና ነው እየተከተሉ ያሉት፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ያላቸው ህዝቦችን በምታስተናግድ ሀገር ላይ የዚህ ዓይነት አካሄድ በብሶት ላይ ብሶት፣ በምሬት ላይ ምሬት ይፈጥራል። ህዝቡን ለማስከፋት ምክንያት መጨመር ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ በዚህ ሀገር በጣም አሳዛኙ አጋጣሚ ነው፡፡ የዚህ አይነቱ እርምጃ ለኛ አይነቱ ሀገር የሚሆን አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ራዕይ እንዳጡና ምን ያህል ፍርሃት ውስጥ እንዳሉ ነው የሚያሳየው፡፡
4 ወር እኮ አሁንም ያልቃል፡፡ ከዛ ምን ይፈጠራል? 6 ወር ምንም ሳይሰራ አይደለም እንዴ ያለቀው፡፡ መፍትሄው ይሄ አይደለም፤ ዝም ብሎ ድብብቆሽ እንደሚጫወቱ ህፃናት መሆን ነው፡፡ እኔ ብዙም የፖለቲካ ጥበብ አላየሁበትም። ህዝቡ በነፃ ሃሳቡን ገልፆ መንቀሳቀስ ሲችል እኮ ነው መንግስት የህዝብን ሀሳብ መረዳት የሚችለው፡፡ በሀዘንና በምሬት አንገቱን ደፍቶ ውስጡ እየፋመ መኖሩ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ታምቆ የከረመ ነገር ፈንድቶ ሲወጣ ጉዳቱ ኃይለኛ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በብሶት ላይ ብሶት እየጨመሩ መሄድ የበለጠ ነገር ከማወሳሰብ ውጪ በሀገሪቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። የተወሰደውም እርምጃ አግባብ አይደለም፡፡ ህዝባችንም ትዕግስቱን አሳይቷል፡፡ ህገ መንግስቱ የሰጣቸው 4 ወር ጊዜ ካለቀ በኋላ ደግሞ ምን እንደሚፈበርኩ ለማየት የዚያ ሰው ያድርገን ነው የምንለው፡፡
በዚህ መሀል  የአባላቶቻችን መታሰር፣ የሰብአዊ መብት መጣስ ስጋታችን ያይላል ማለት ነው። ምን ተፈጥሮ ነው የሚያራዝሙት? ምን ስጋት ታያቸው? ከተፈለገም ችግር ባለባቸው ቦታዎች ብቻ ማራዘም ይቻል ነበር፡፡ አሁን አዲስ አበባ ምን ችግር ታየ? በሌሎች አካባቢዎችስ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤”80 ከመቶ በላይ ህዝብ እንዲራዘም ፈልጓል” ብለው ሲናገሩ፣ እንደ ሀገር መሪ ጥንቃቄ ማድረግ የለባቸውም እንዴ? የትኛው ድርጅት ነው ይሄን ያጠናው? ምናልባት ኢህአዴግ ካድሬዎቹን አነጋግሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ ማን ጠያቂ አለብኝ እየተባለ ነው ሁሉም ነገር የሚደረገው፡፡ እንግዲህ ሁላችንም ተስፋ ቆርጠን … ቆርጠን የዚህች ሀገር ነገር ምን እንደሚሆን ያስጨንቃል፡፡  

===================================


“አሁንም ቢሆን
የሚያስፈልገው የፖለቲካ መፍትሄ ነው”

ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

አዋጁን ማራዘም ባለፉት 6 ወራት ታይቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ውድቀት በድፍረት ማስቀጠል ነው፡፡ አጠቃላይ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ ወድቋል፡፡ ከእድገት አንፃር፣ ከGTP 2 አንፃር፣ ከጤናና ከትምህርት አንፃር-----በሌሎችም ዘርፎች ታስቦ የነበረው የእድገት እቅድ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር የማይቀየርበት ጊዜ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ አዋጁ ተራዘመ ማለት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በነበሩበት ደካማ አካሄድ ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ ሌሎች  መንግስትም ባለሀብቶችም የሚያካሂዷቸው ኢንቨስትመንቶች በሙሉ እየተጎዱ ነው የሚሄዱት፡፡
አሁንም ፖለቲካዊ መፍትሄ እስካልመጣ ድረስ 4 ወር ቢራዘም ምንም አይነት ለውጥ የሚያመጣ መስሎ አይታየኝም፡፡ ህዝቡ እስካሁን የጠየቃቸው ጥያቄዎች እየተመለሱለት አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶ ተብሎ እስከ ታች የወረደውን አካሄድ ለማየት ሞክረን ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋወሩ እንጂ የማያሰሩ ደንቦችና ህጎች ሪፎርም አልተደረጉም፡፡ ክፍተቶቹ እንዳሉ ናቸው፤አሁንም አልተዘጉም፡፡ ስለዚህ አዋጁ ለውጥ አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ለ4 ወር ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ አንድ ዓመት ራሱ በዚህ መንገድ ከቀጠለ ህዝቡ የበለጠ ወደ ሌላ አማራጭ እንዲያመራ በር እየከፈተ ነው የሚሄደው፡፡
 አሁን እንደምናየው በየመንደሩ ሚሊሻና ካድሬ የተለየ አስተሳሰብ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል እያሰረ ነው ያለው፡፡ ባለፉት ጊዜያት አንድም አባል ታስሮብን የማናውቅ ፓርቲ፣ አሁን በየወረዳዎቹ አባሎቻችን ታስረውብን ነው ያሉት፡፡ ይሄ የበለጠ ጥላቻን፣ ቅራኔንና ቂምን እየቋጠረ ነው የሚሄደው፡፡ ህብረተሰቡ አሁን ባለው አኳሃን የተሻለ አስተሳሰብ ይይዛል ብለን አናስብም፡፡ አሁንም ቢሆን የሚያስፈልገው የፖለቲካ መፍትሄ ነው፡፡ ውይይት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ውይይቱን ራሱ እናድርግ ስንል እንኳ ምን ያህል እየገፋን እንደሆነ እየታየ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እንዳለበት፣ የታሰሩ ሰዎች መፈታት እንዳለባቸው በአጀንዳ መልክ እንወያይበታለን ያልነው ሁሉ ዘግተውብናል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት ያለፉበትን የፖለቲካ ሂደት መገምገም አይከብደንም፡፡ በአጠቃላይ ስጋት እየጫሩ ነው ያሉት፡፡ እነሱም ይሰጋሉ፡፡ እንዳያሻሽሉ ግራ ገብቷቸዋል፡፡ እንዳያሳትፉን ደግሞ በመሃል ብዙ ሚስጥሮች ይወጣሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ለነሡ ስጋት ሆነው ነው የሚቀጥሉት፡፡
እንደሚታወቀው በሃገሪቱ ላይ የውጭ ምንዛሬ ጠፍቷል፡፡ ምንዛሬ ጠፋ ማለት ወጪ ገቢ ንግድ መስራት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ትላልቅ ባለሃብቶች በምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሠራተኛ እየቀነሱ ነው ያሉት፡፡ ምርት እየቀነሱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን ተብለው የተቋቋሙ ማዕከላት በገንዘብ እጥረትና በአዋጁ ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ  አገሪቱ በኢኮኖሚ ምን ያህል እየተጎዳች እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ይሄን ሁሉ ባለማሰባቸው አዋጁ መራዘሙ እስካሁን ከነበረው እጅግ የበለጠ እየጎዳን ነው የሚሄደው፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት የሚቻለው አዋጁን በማስቀጠልና በመዋሸት አይደለም፡፡ አንድ ታላቅ የሃገር መሪ የሆነ ሰው፤”82 በመቶ ህዝብ እንዲቀጥል ደግፎናል” ብሎ የሚናገርበት የውሸት አለም ላይ ነው ያለነው፡፡ መቼ ሄደው መረጃ ሰብስበው ነው? መቼ ህዝብ የሚናገረውን አደመጡ?... እንዲህ ያለ ሃሰተኛ መረጃ በአደባባይ መናገር እጅግ ያሳዝናል። መቼም አሁን ባለንበት ደረጃ አንቀርም፡፡ ተተኪው ትውልድም ቢሆን የለውጥ ጥያቄ አንግቦ ጥያቄ የሚያቀርብበት ጊዜ ሩቅ ይሆናል ብለን አናስብም፡፡
============================


‹‹አዋጁ መራዘሙ ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም››
ዶ/ር በዛብህ ደምሴ (የመኢአድ ፕሬዚዳንት


በሌላው አለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ችግር ያለበት ቦታ ላይ ብቻ ተለይቶ ነው የሚታወጀው፡፡  እንደኛ ሃገር እንደዚህ የተራዘመ አዋጅ አይጣልም፡፡ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማራዘም ይልቅ “ለምንድን ነው ህዝቡ በየክልሉ ብሶቱን የገለፀብኝ ?”፣ “ምንድን ነው የጠየቀው?” የሚለውን አጢኖ፣መልስ ለመስጠት ቢሞክር ነበር የሚያዋጣው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙ ተገቢ ነው ብዬ አልገምትም፡፡ መንግስት እንደ መንግስትነቱ ለህዝቡ ብሶት መልስ መስጠት እንጂ በጉልበትና በሃይል ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፡፡
ይሄ መንግስት ሁሉም እንደሚያውቀው ሠላም፣ እድገት እያለ ይናገራል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ሠላምም እድገትም ይፈልጋል፤ግን ሠላምና እድገት ሊመጣ የሚችለው ዝም ብሎ በምኞት ሳይሆን ህዝቡ ለሚጠይቀው ጥያቄ መንግስት ተገቢውን መልስ መስጠት ሲችል ብቻ ነው፡፡ በኔ እምነት አዋጁ መራዘሙ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል ብዬ አልገምትም፡፡
በአሁኑ ጊዜ የፓርቲያችን አባላትና አመራሮች ይታሰራሉ ይፈታሉ፡፡ እርግጥ ነው ለኮማንድ ፖስቱ አመልክተን የተፈቱልን አባላት አሉ፡፡ ግን በአጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴያችንን ገድቦታል። አባሎቻችን እንደ ልባቸው ተሰብስበው ውይይት ለማድረግ ተቸግረዋል፡፡

ጽላቱን የሚያውቁ ካህናት በምርመራው መካተት እንዳለባቸው ተጠቁሟል
• “ጥያቄውን ለሀገረ ስብከቱ እንዳናቀርብ ሥራ አስኪያጁ ያሳስሩናል” /ምእመናኑ

በጋምቤላና ደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የምትገኘው፣ የሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ዕድሜ ጠገብ ታቦት፣ የደረሰበት አለመታወቁን የከተማው ምእመናን የተናገሩ ሲሆን፤ በአቋራጭ መክበር በሚፈልጉ ስግብግቦች እጅ ሳይገባ አፋጣኝ ማጣራትና ምርመራ እንዲካሔድላቸው መንበረ ፓትርያርኩን ጠየቁ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ በ1941 ዓ.ም. መታነጿንና ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠ የኪዳነ ምሕረት ታቦትም እንዲገባ ካስደረጉ በኋላ፣ ሥርዓተ እምነታቸውን ሲፈጽሙባትና ሲማፀኑባት እንደኖሩ ምእመናኑ ጠቅሰው፤ ከየካቲት 24 ቀን ጀምሮ ግን ታቦቱ በመንበሩ ላይ እንደሌለ ከካቴድራሉ ካህናት መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
የታቦቱ/ጽላቱ/ በመንበሩ ላይ አለመኖር በመጀመሪያ ያረጋገጡት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ እንደነበሩና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ቄሰ ገበዙን እንደጠየቋቸው ያወሱት ምእመናኑ፣ ቄሰ ገበዙ፥ “እኔን ለምን ትጠይቁኛላችሁ? ሥራ አስኪያጁን ጠይቁ፤” የሚል ምላሽ በመስጠታቸው፣ “ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎብናል፤” ብለዋል፡፡ በቀጥታ ለጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዳያቀርቡ፣ “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ተጠቅመው ያሳስሩናል፤” ብለው እንደሚሰጉና ሁከት እንዳይቀሰቀስ ፍርሃት እንዳደረባቸው ምእመናኑ አልሸሸጉም፡፡
“ለምነን ያላፈርንባት፤ ችግራችንን ፈጥና የምትሰማን የኪዳነ ምሕረት ታቦት ጠፍታ እንዴት ዝም እንላለን፤ ብለን በአንድ ቦታ ተሰብስበን ከተመካከርን በኋላ በትዕግሥትና በሥርዓት ለሚመለከተው የበላይ አካል ማመልከትን መርጠናል፤” ያሉት ምእመናኑ፣ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ባለፈው መጋቢት 13 እና 14 ቀን፣ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሠራው ታቦት፣ የሀገርም ቅርስ መሆኑን ምእመናኑ ጠቁመው፣ በአቋራጭ የመክበር ምኞት በተጠናወታቸው ስግብግቦች እጅ ሳይገባ፣ በመንበረ ፓትርያርኩ መሪነት አስቸኳይ ማጣራትና ምርምራ እንዲካሔድላቸው ተማፅነዋል፤ ጽላቱ የሚቀመጥበት መንበር ባዶ መኾኑን የሚያሳይ በወቅቱ የተቀረፀ የቪዲዮ ምስል በአባሪነት ማቅረባቸውን ገልጸው፣ ጽላቱ በመንበሩ ላይ ተገኘ ቢባል እንኳ፣ ዕድሜ ጠገቡ ጽላት መሆኑን ለይተው በሚያውቁ ካህናት ታይቶ መረጋገጥ እንደሚኖርበት ጨምረው አሳስበዋል፡፡
አህጉረ ስብከቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፣ በክልሉ ተመድበው በሠሩበት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ 17 ብቻ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ወደ 53 ማደጉንና በደቡብ ሱዳን ጭምር መታነፃቸው ተገልጧል፡፡ ይህም የዋና ሥራ አስኪያጁን ሐዋርያዊ ትጋት ያመለክታል ቢባልም፣ በአገልግሎታቸው ቀጣይነትና አያያዝ ረገድ፣ ከአገልጋዮችና ምእመናን በርካታ ጥያቄዎች እየተነሡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ፣ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ በእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡



የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ይፃረራል፤ ያሉት የትግርኛ ቋንቋ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከሥርጭት እንዲታገድላቸውና እንዲወገድላቸው፣ የመቐለ ምእመናን የጠየቁ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በበኩሉ፣ “ትርጉሙ፣ በቤተ
ክርስቲያኗ ሊቃውንት የተሠራ ነው፤ ስሕተት አለው፤ የሚል እምነት የለንም፤” ብሏል፡፡
ከ40 በላይ የሆኑ ምእመናን የተፈራረሙበት ማመልከቻ፤ ለትግራይ አህጉረ ስብከት 4 ሊቃነ ጳጳሳት በግንቦት 2008 ዓ.ም ያቀረቡ ቢሆንም፤ ለጥያቄያቸው እስከ አሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ምዕመናኑ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ እና የወንጌላውያን ኅብረት አብያተ ክርስቲያናት አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ያሳተመው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ፤ “ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ በተፃራሪ፡- የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚክድ፣ የቅድስት ሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚያዛባ፣ ሥልጣነ ክህነትን የሚሽርና የማይቀበል፣ የቤተ ክርስቲያኗን ፊደልና ቁጥር አቆጣጠር የማይቀበል እንዲሁም፣ ቤተ ክርስቲያኗ የምትቀበላቸውን 81 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ጎን በመተው 66 መጻሕፍትን ብቻ ያካተተ በመሆኑ፣ እምነትን የሚያስክድ ነው፤ ይወገድልን፤” ብለዋል - ምዕመናኑ፡፡
መጽሐፍ ቅዱሱ ታትሞ በገበያ ላይ ከዋለ በኋላ፣ 92 በመቶ የሚሆነውን የክልሉን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ግራ እያጋባ መሆኑንም ምዕመናኑ በማመልከቻቸው ጠቁመዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ ይፃረራል፤ የተባለው ይኸው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደተለያዩ የከተማና እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዳይሰራጭና

ዳግመኛም እንዳይታተም እንዲታዘዝላቸው ምዕመናኑ ጠይቀዋል። የትርጉሙን ስሕተት የሠሩ አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑና ርምጃ

እንዲወሰድባቸው ምዕመናኑ አያይዘው ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጠቅላይ ጸሐፊ፣ መምህር ይልማ ጌታሁን፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በግልጽ የቀረበ

አቤቱታ እንደሌለ ገልጸው፣ አቤቱታ አቅራቢዎች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅሬታ አቅርበው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዩን እያየችው መሆኑን መረጃ

እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ትርጉሙ፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ሊቃውንት በጥንቃቄ የተሠራ መሆኑን የጠቆሙት መምህር ይልማ፣ “ሥራው ስሕተት አለው ብለን አናምንም፤

አለው ቢባል እንኳ ሊቃውንቱን ነው መጠየቅ ይችሉ የነበረው፤” ብለዋል፡፡ የትርጉም ሥራው፣ በሊቃውንት ተመርምሮ ፓትርያርኩ ባሉበት

ተመርቆ እንዲሰራጭ መደረጉንም መምህር ይልማ አስረድተዋል፡፡
“ትርጉሞች፣ በቤተ ክርስቲያን ፈቃድና ተሳትፎ የሚሠሩ ናቸው እንጂ፣ ማኅበሩ በራሱ ተነሣስቶ የሚያደርገው አይደለም፤” ያሉት መምህር ይልማ፤

እስከ አሁንም፣ የትርጉም ስሕተት አለበት፤ የሚል ጥቆማ ለማኅበሩ እንዳልቀረበ አስታውቀዋል፡፡ 

   በሚያዚያ ወር በጥቅል ‹‹ሶስታ ሃሴት›› የሚል ሰያሜ የተሰጣቸው 3 ተከታታይ ሩጫዎች ተዘጋጅተዋል

       በተባበሩት መንግስታት አብይ ስፖንሰርነት ‹‹ስለምትችል››  በሚል መርህ ከሳምንት በፊት ለ14ኛ ጊዜ የተካሄደው  የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ስኬታማ እንደነበር የውድድሩ አስተባባሪ  ዳግማዊት አማረ ለስፖርት አድማስ ገለፀች፡፡
11ሺ ተሳታፊዎች የነበሩት የጎዳና ላይ ሩጫው መነሻ እና መድረሻው በመደበኛው  አትላስ ሆቴል  መመለሱ ድምቀት ፈጥሯል ያለችው ዳግማዊት፤  ሩጫው ከመጀመሩ በፊት እና ካበቃ በኋላ የነበረው አጠቃላይ ድባብ ያማረ ነበር ብላለች፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ከ150 ዓመታት በፊት ስለነበረች የኢትዮጵያ ጀግና ሴት የተሰራው የቃቄ ውርድዎት  ቲያትር አንድ የተቀነጨበ ትዕይነት ለእይታ መቅረቡ፤ በሴቶች እየተዘወተረ የመጣው ታዋቂው የዙምባ ዳንስ ደስ የሚል ትርኢቶችን በመፍጠር ውድድሩን ማሟሟቁ፤ እንዲሁም ስለምትችል የሚለው መርህን በማንገብ የሴቶችን ስኬትና ሚና ለማክበር የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ስኬታማ እንደነበሩም አብራርታለች፡፡
በ5 ኪ.ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በዋናው የአዋቂ አትሌቶች ውድድር አስደናቂ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን በመሰረት ደፋር በባለቤቷ ቴድሮስ የሚንቀሳቀሰው የአዲዳስ  ዴፕሎፕመንት ፕሮጀክት ወጣት አትሌቶች ብዙም የውድድር ልምድ ባይኖራቸውም በአንደኛ እና  ሁለተኛ ደረጃ ውድድሩን በመጨረሳቸው ነበር፡፡ በ1ኛ ደረጃ የጨረሰችው የአዲዳስ ዴቨሎፕመንት አትሌት ደጊቱ አዝመራው ስትሆን ሌላዋ አጋሯ አበባ ተፈራ በሁለተኛ ደረጃ ተከትላ ገብታለች፡፡ ምህረት ተፈራ እና ብርሃን ምህረቱ ከሱር ኮንስትራክሽን 3ኛእና አራተኛደረጃ አግኝተዋል፡፡  በሌላ በኩል ከ35 ደቂቃ በታች 5 ኪሎሜትሩን ለሚጨርሱ  ስፖርተኞች ከሜዳልያ ሽልማት ባሻገር የአትሌት መሰረት ደፋር ፊርማ ያረፈበት 2000 ሰርተፍኬቶች ለሽልማት የቀረቡ ቢሆንም፤ በውድድሩ ላይ  ከ35 ደቂቃ በታች በመጨረስ የተሸለሙት 300 ብቻ ሆነዋል፡፡ በውድድሩ መነሻ ላይ በአንድ ጎዳና ላይ እጅብ ብሎ በመሮጥ የተፈጠረው  ግርግርና መጨናነቅ ብዙ ሴቶች ከ35 ደቂቃ በታች ውድድራቸውን እንዳይጨርሱ አድርጓቸዋል ብላለች፡፡ ዳግማዊት አማረ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  ፡፡ ከ30 በላይ ስፖርተኞችን ባሳተፈው የሴት ተምሳሌቶች  ውድድር የግሸን ፋርማሲ ባለቤት ወይዘሮ አማከለች ሉሉ ሲያሸነፉ በሁለተኛደረጃ የጨረሰችው ድምፃዊት ቤተልሄም ጌታሁን ወይም ቤቲ ጂ ነበረች፡፡ በአምባሳደርና የውጭ ዲፕሎማቶች ምድብ ደግሞ የስውድን አምባሳደር ባለቤት ሚስሪኮ ሜንሲያ  አሸንፈዋል፡፡    
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያዚያ 15  ጀምሮ  ባሉት ተከታታይ 3 እሁዶች የተለያዩ 3 ሩጫዎችን ማዘጋጀቱን ለስፖርት አድማ በላከው መግለጫ ያመለከተ ሲሆን ሶስቱ ተከታታይ ሩጫዎች በጥቅል ሶስታ ሃሴት (Triple Crown) የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል፡፡ የመጀመርያው ሚያዚያ 15 የሚካሄደውና በአጠቃላይ 4000 ተሳታፊዎችን የሚያስተናግደው የሃዋሳው 2009 ሲሲኢሲሲ ሃዋሳ ግማሽ ማራቶን ሲሆን ይህ ሩጫ በውስጡ የ21 ኪ.ሜ.፤ የ7ኪ.ሜ እንዱሁም የህፃናት ሩጫ የሚያካትት ይሆናል፡፡  ሁለተኛው ውድድር
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ህክምና ባለሞያዎች ማህበር ጋር በመሆን የሚያዘጋጀው አመታዊው ኤማ ሩጫ  ሚያዚያ 22 ቀን ለ2ኛ ጊዜ ሲካሄድ  5000 ተሳታፊዎች ይኖሩታል፡፡
በመጨረሻም ሚያዚያ 29 ላይ የአውሮፓ ቀንን አስመልክቶ የሚዘጋጀው የአውሮፓ ቀን የህፃናት ሩጫ ሲሆን እድሜያቸው ከ3 አመት በላይ የሆኑ 3000 ህፃናት ወንዶችና ሴቶችን  የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡