Administrator

Administrator

 ናይጀሪያ አሸባሪው ቡድን ቦኮ ሃራም በነዳጅ ማጣሪያዎቿ ላይ በተደጋጋሚ ባደረሳቸው ጥቃቶች ሳቢያ በ2016 ከዘርፉ ማግኘት ከሚገባት ገቢ 100 ቢሊዮን ዶላር ያህል ማጣቷን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
    የሽብር ቡድኑ በአገሪቱ የነዳጅ ማምረቻ አካባቢዎች በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ሳቢያ የናይጀሪያ የነዳጅ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የነዳጅ ሚኒስትሩ ኤቢ ካቺክው ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በየዕለቱ የምታመርተው ነዳጅ በ1 ሚሊዮን በርሜል መቀነሱን ገልጧል፡፡
አገሪቷ ባለፉት 25 አመታት የከፋውን የኢኮኖሚ ድቀት ማስተናገዷንም የጠቀሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት የነዳጅ ምርቱን ለማሻሻልና ኢኮኖሚው እንዲያገግም ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡

 • በጥንካሬው ወደር አልተገኘለትም
                      • ከ17 አመታት በኋላ አሁንም ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ቀፎዎች አሉ

      ዓለማችን እጅግ በተራቀቁ ስማርት ፎኖች ከመጥለቅለቋ፣ ተች ስክሪን ሞባይል በልጅ በአዋቂው እጅ ከመግባቱ፣ ሞባይል ከመደዋወያ መሳሪያነት አልፎ እጅግ በርካታ ተግባራትን መፈጸሚያ ወሳኝ ቁስ ከመሆኑ በፊት፣ በቀዳሚነት ወደ ገበያ የገባውና እንደ ብርቅ ይታይ የነበረው፣ በጥንካሬው ዛሬም ድረስ አቻ እንደማይገኝለት የሚነገረው ኖኪያ 3310፤ እንደገና ወደ ገበያ ሊገባ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
    የዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎች ዘመን ጅማሬ ምልክት እንደሆነ የሚነገርለት ፈር-ቀዳጁ ኖኪያ 3310፤ በአለማችን የሞባይል ቀፎዎች ቴክኖሎጂ ታሪክ እጅግ ጠንካራውና ሃይል ቆጣቢው እንደሆነ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፣ የሞባይል ቀፎው ከ17 አመታት በኋላ በቅርቡ እንደገና ወደገበያ ሊገባ መሆኑን ገልጧል፡፡
   የተወሰነ ማሻሻያ ይደረግበታል የተባለው አዲሱ ኖኪያ 3310፣ በዚህ ወር መጨረሻ በሚከናወነው የአለም የሞባይል ኮንግረስ ላይ ለእይታ ይበቃል ያለው ዘገባው፤ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በገበያ ላይ እንደሚውልና የመሸጫ ዋጋው 59 ዩሮ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድቷል፡፡
   ኖኪያ 3310 እ.ኤ.አ በ2000 ለመጀመሪያ ጊዜ ተመርቶ ወደ ገበያ መግባቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ምንም እንኳን ኩባንያው ይህንን የሞባይል ቀፎ ማምረት ካቆመ 12 አመታት ቢቆጠሩም ከ16 አመታት በፊት የተመረቱና አሁንም ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ቀፎዎች እንዳሉ ገልጧል፡፡ ኖኪያ ኩባንያ ከሚታወቅባቸው ስኬታማ የሞባይል ቀፎዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ኖኪያ 3310 ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ በቀረበበት ወቅት በአለም ዙሪያ 126 ሚሊዮን ያህል እንደተሸጠ የተነገረ ሲሆን፣ የተሻሻለው አዲሱ ምርት ከሳምንታት በኋላ ለአውሮፓና ለደቡብ አሜሪካ አገራት ገበያ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡ ኩባንያው “ኖኪያ 215”ን የመሳሰሉ የቀድሞ ተወዳጅ የሞባይል ቀፎዎቹን
እንደገና አሻሽሎ በማምረት የገበያ ድርሻውን የማስፋት ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ዘገባው አብራርቷል፡፡

 የፊቱን ገጽታ፣ አለባበሱን፣ አነጋገሩን፣ ስሙንና አጠቃላይ ሁኔታውን ሆን ብሎ ከአዶልፍ ሂትለር ጋር
በማመሳሰል፣ በየጎዳናው ሲንቀሳቀስ የነበረው ኦስትሪያዊ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ፣ ለጨፍጫፊው ናዚ ክብር
ሰጥተሃል በሚል መከሰሱ ተዘግቧል፡፡ ሃራልድ ዜንዝ የሚለውን ወላጆቹ ያወጡለትን ስም ሃራልድ ሂትለር
ብሎ የቀየረው የ25 አመቱ ኦስትሪያዊ፤ ከጸጉር ስታይሉ አንስቶ፣ የጺም አቆራረጡንና አለባበሱን ከሂትለር ጋር
በማመሳሰል በየአደባባዩ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን የጠቆመው ቢቢሲ፤ ጨፍጫፊውን ሂትለርን አክብረሃል በሚል
መከሰሱን ገልጧል፡፡     ግለሰቡ በመጽሃፍት መደብሮች እየተዘዋወረ የሁለተኛው የአለም ጦርነትን የተመለከቱ መጽሃፍትንና መጽሄቶችን በብዛት መግዛት ያዘወትር እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፤ ሂትለር በተወለደበት ቤት አካባቢ በተደጋጋሚ ሲያንዣብብ መታየቱንም ጠቅሷል፡፡ ለሂትለር ክብር የሚሰጥ ድርጊት በአገሪቱ ህግ መሰረት ወንጀል መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው፤ በብዙዎች ዘንድ “ዳግማዊ ሂትለር” ተብሎ የሚታወቀው ግለሰቡም፣ በተደጋጋሚ መሰል ድርጊቶችን ሲፈጽም መቆየቱ በምርመራ በመረጋገጡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ፣ ክስ እንደተመሰረተበት አመልክቷል፡፡

 የደራሲ ሚካኤል መኮንን የአጭር ልቦለድ ስብስቦችን ያካተተ “የተጣሉ ፊደላት” የተሰኘ መፅሐፍ የፊታችን ሐሙስ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡
    አጫጭር ልቦለዶቹ በህይወት ፍልስፍና፣ በአገርና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው ተብሏል። ሰባት አጫጭር ልቦለዶችን የያዘው መፅሐፉ፤ በ242 ገጾች ተቀንብቦ፣ በ65 ብር ከ95 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡መጻህፍቱን ምስጋናው መፃህፍት መደብር እንደሚያከፋፍለውም ታውቋል፡፡

የ25 ስኬታማ የሥራ ፈጣሪዎች፣የቢዝነስ መሪዎችንና ምሁራንን አጫጭር አነቃቂ ታሪኮች የያዘው “5ቱ ገፆች” የተሰኘ መፅሐፍ የፊታችን ሀሙስ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል እንደሚመረቅ “ገበያ ኑ ቢዝነስ ፕሮሞሽንና ኮሚዩኒኬሽን” ገለፀ፡፡ የስኬት መፅሐፉን ፅፎ ለማጠናቀቅ ሰባት አመት እንደፈጀበት የተናገረው ሰለሞን ሹምዬ፤ መፅሀፉ ለኢንተርፕረኒሺፕ ትምህርት ማጣቀሻ ሆኖ እንደሚያገለገል ጠቁሟል።
   የመፅሐፉ መታሰቢያነት ለእናቱና ልጆቻቸውን በጥሩ ስነ-ምግባር ላሳደጉ እናቶች በሙሉ እንደሆነ የገለፀው ደራሲው፤ በዕለቱ እናቶች በሚገኙበት ‹‹እናቴ” የተሰኘና ኤልያስ መልካ ያቀናበረው ነጠላ ዜማ እንደሚለቅም ተናግሯል፡፡   ደራሲው ከዚህ ቀደም ‹‹ገመና›› የተሰኘ ረጅም ልቦለድና ‹‹ምስጢር›› የግጥም መድበል ለንባብ ማብቃቱ ይታወቃል፡፡

 ሠዓሊ ገነት አለሙ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 4 ከዚህ አለም በሞት ተለየች፡፡ ስርዓተ ቀብሯ ሰኞ የካቲት 6 በጴጥሮስ ወጳውሎስ የተፈጸመ ሲሆን የሠዓሊዋን ስራዎች ለዕይታ ክፍት ባደረገው አስኒ ጋለሪ ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ሠዓሊዋን በሚዘክሩ ስራዎች። ቁሶችና በተለያዩ ማስታወሻዎች ገነት አለሙን ይዘክራል፡፡
   ሠዓሊ ገነት አለሙ በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ሠዓልያን መሃከል በግንባር ቀደምትነት የምትታወስ ስትሆን በሃገር ውስጥና በውጪ ሃገራትም ስራዎቿን አሳይታለች፡፡ ገነት እ.ኤ.አ.በ2015 የፖሎክ-ክራስነር ሽልማትን መቀበል የቻለች ትጉህና ለሙያዋ ታላቅ መስዋዕትነትን የከፈለች ሠዓሊ ነበረች፡፡

    የወጣት ሰዓሊያን ሀይሉ ክፍሌና ታምራት ስልጣን የስዕል ስራዎች ለእይታ የቀረቡበት ‹‹ታሪክን ለዛሬ›› የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ፣ከትናንት በስቲያ ምሽት በድንቅ አርት ጋለሪ ተከፈተ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያተኩረው አውደ ርዕዩ፤የሰዓሊያኑን አመለካከት፣ ሀሳብና ድንቅ የአሳሳል ጥበብ የሚያንፀባርቁ በርካታ ስዕሎችም እንደቀረቡበትየቤተ-ሥዕሉ ማናጀር ኤዶም በለጠ ገልፃለች። አውደ ርዕዩ ለተከታዮቹ 24 ቀናት ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡   በተመሳሳይ አምስት ወጣት የሪያሊስቲክ ሰዓሊያን ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ‹‹ሀርመኒ›› የስዕል አውደርዕይ፤ባለፈው ቅዳሜ ከአትላስ አለፍ ብሎ በሚገኘው ኢሳያስ ያብዘር ጂምስቶንና አርት ጋለሪ ተከፍቶ እየታየ ነው፡፡ ሰዓሊ ዮሴፍ
አባተ፣ቴዎድሮስ ግርማ፣ዮናስ ደገፉ፣ አብይ እሸቴና መሀሪ ተሾመ በጋራ ከ25 በላይ ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ይሄው አውደርዕይ፤ ለአንድ ወር ያህል ለእይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

    የኢትዮጵያ ቪዥዋል አርቲስቶች ማህበር ከ60 በላይ አባላት የተሳተፉበትና የተለያዩ የስዕል አሳሳል ዘይቤዎች የተንፀባረቁበት ‹‹አርትፌር” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ባለፈው ረቡዕ በብሄራዊ ሙዚየም አቀረበ፡፡ የፊታችን ማክሰኞ ድረስ ለዕይታ ክፍት ሆኖ በሚቆየው በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ የአሳሳል ቴክኒኮች የሚታዩባቸው እጅግ በርካታ ስዕሎች የቀረቡ በመሆኑ በስፋት ለማየትም ሆነ ለመግዛት በቂ አማራጮች እንዳሉት አዘጋጆቹ ገልጸዋል። እንደዚህ አይነት አርት ፌሮች በሌላው ዓለም የተለመዱና ለአድናቂዎች አማራጭ የሚቀርቡበት አሰራር ቢሆንም በአገራችን እንዲህ አይነት የስዕል አውደ ርዕዮች የተለመዱ እንዳልሆኑ የተናገሩት አዘጋጆቹ፤ በቀጣይ እንዲለመድ በተከታታይ ለማዘጋጀት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

 59ኛው ታላቁ የግራሚ ሽልማት ባሳለፍነው እሁድ ምሽት በሎሳንጀለስ በደማቅ ስነስርዓት የተካሄደ ሲሆን፣ የሽልማት ስነስርዓቱን በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን ካሰራጯቸው ዘገባዎች በጥቂቱ ቆንጥረን  እንሆ እንበላችሁ!...

      የሁለቱ እንስቶች ፍልሚያ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ጉዳዩ በሁለት እንስት የአለማችን ሙዚቃ ከዋክብት መካከል የሚደረግ ፍልሚያ እንደሆነ ሲዘገብ ነበር የሰነበተው - የአዴል እና የቢዮንሴ፡፡
መንታ ልጆችን ማርገዟን በቅርቡ ይፋ ያደረገቺው ተወዳጇ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፤ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛ ነበር - ዘጠኝ ጊዜ ሽልማት በመታጨት፡፡ 25 በተሰኘው የሙዚቃ አልበሟ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል በበኩሏ፣ በአምስት ዘርፎች ታጭታለች፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው  የግራሚ ሽልማት ውጤት ታዲያ፣ እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል የአመቱ ምርጥ አልበም እና የአመቱ ምርጥ ሪከርድን ጨምሮ በታጨችባቸው አምስት ዘርፎች፣ በሁሉም አሸናፊ መሆኗን በማብሰር የፍልሚያው ባለድል መሆኗን አረጋግጧል፡፡
ተፋላሚዋ ቢዮንሴ፤ ማሸነፍ የመታጨትን ያህል አልቀናትም፡፡ ከታጨችባቸው ዘጠኝ ግራሚዎች በእጇ ማስገባት የቻለቺው ሁለቱን ብቻ ሆኗል፡፡
የተጧጧፈው የአልበም ሽያጭ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ውጤት እሁድ ምሽት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የተሸላሚ ድምጻውያኑ የሙዚቃ አልበሞች ሽያጭ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተዘግቧል፡፡
የአምስት ሽልማቶች አሸናፊዋ አዴል የሙዚቃ አልበም የሆነው 25 ሽያጭ፣ ማሸነፏ ይፋ በተደረገ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ በ150 በመቶ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን” ሄሎ” የተሰኘው ነጠላ ዜማዋ ዳውንሎድ የተደረገበት መጠንም በ308 በመቶ ያህል ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የተላለፉ ሙዚቃዎች፣ እሁድ ዕለት ዳውንሎድ የተደረጉበት መጠን፣ በ207 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ ሙዚቃዎቹ በድምሩ 178 ሺህ ጊዜ ዳውንሎድ መደረጋቸውን ጠቁሟል፡፡
26 ሚሊዮን ተመልካች
በሲቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ የተላለፈውን የዘንድሮውን የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት በአለም ዙሪያ የሚገኙ 26 ሚሊዮን ያህል ተመልካቾች እንደተመለከቱትና ይህ ቁጥር ከአምናው በ1 ሚሊዮን ያህል እንደሚበልጥ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
የዘንድሮው ግራሚ በኤቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከተላለፈውና 34 ሚሊዮን ሰው ከተመለከተው፣ የአምናው የአካዳሚ ሽልማት ስነስርዓት ቀጥሎ በታሪክ ሁለተኛው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ፣ በቴሌቪዥን የተከታተለው የሽልማት ስነስርዓት ነው ተብሏል፡፡
ያልተለመደ ፖለቲካዊ ድባብ
የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ከወትሮው በተለየ መልኩ፣ ፖለቲካዊ ድባብ ያንዣበበበት እንደነበር ተነግሯል፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱን በመድረክ አጋፋሪነት የመራው ጄምስ ኮርዴን፤ ስነስርዓቱን የከፈተው በራፕ መልክ ባቀረበው ፖለቲካዊ ሽንቆጣ ነበር - “ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስካሉ ድረስ፣ መጪውን ነገር ማወቅ አንችልም!...” በማለት፡፡
ጄኔፈር ሎፔዝ በበኩሏ፤ በዚያው ምሽት የምርጥ አዲስ አርቲስት ዘርፍ ተሸላሚውን ይፋ ለማድረግ ወደ መድረክ በወጣችበት አጋጣሚ ባደረገቺው አጭር ንግግር፣ አሁን በምንገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ፣ ድምጻችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ ነው ብላለች፡፡ የሪከርዲን አካዳሚ ፕሬዚዳንት ኒል ፖርትኖው ደግሞ፣ ሙዚቃ ህዝብን አንድ በማድረግ ረገድ ያለውን ብርቱ ሃይል በተመለከተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሌሎች በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የታደሙ የአለማችን ድምጻውያንና ዝነኞችም በሙዚቃዎቻቸውና ባቀረቧቸው ንግግሮች፣ ፖለቲካዊ ቃና ያሏቸውን የተለያዩ መልዕክቶች ማስተላለፋቸው ተነግሯል፡፡

Sunday, 19 February 2017 00:00

የፍቅር ጥግ

 - አንገቴ ላይ አልማዝ ከማጠልቅ ይልቅ ጠረጴዛዬ ላይ ፅጌረዳ ቢኖር እመርጣለሁ፡፡
  ኢማ ጎልድማን
- ሽቶና አበቦችን እወዳለሁ፡፡
  ዶናቴላ ቨርሳቼ
- መፋቀር እርስ በርስ መተያየት ብቻ አይደለም፤ ወደ ተመሳሳይ አቅጣጫ መመልከትም ነው፡፡
  አንቶይኔ ዲ ሴይንት ኤክሱፔሪ
- ፍቅር የዳበሰው ሰው በጨለማ ውስጥ አይጓዝም፡፡
  ፕሌቶ
- ፍቅር ቀድሞ ያልነበሩ በሮችንና መስኮቶችንም እንኳን ያስከፍታል፡፡
  ሚኞን ማክላውግህሊን
- ለአንቺ ያለኝን ፍቅር በሙሉ ለመሸከም መቶ ልቦች በጣም ያንሳሉ፡፡
  ያልታወቀ ደራሲ
- ፍቅር ሁለት ሰዎች የሚጫወቱትና ሁለቱም የሚያሸንፉበት ጨዋታ ነው፡፡
  ኢቫ ጋቦር
- ፍቅር የስሜቶቻችን ግጥም ነው፡፡
  ሆኖሬ ዲ. ባልዛክ
- ነይና ልቤ ውስጥ ኑሪ፤ ኪራይ አትከፍይም፡፡
  ሳሙኤል ላቨር
- አፍቅሪኝ፤ ያኔ ዓለም የእኔ ትሆናለች፡፡
  ዴቪድ ሪድ
- ፍቅር ማለት አብሮ መጃጃል ነው፡፡
  ፓውል ቫለሪ
- ሰዎች ስለወደዱን ብቻ ለምን ጅሎች ናቸው ብለን እናስባለን?
  ኤማ አታ አይዱ
- እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ ይሄ ነው የህንድ የመጨረሻ መልዕክት
  ኢ.ኤም. ፎ ርስተር
- ፍቅር ለየት ያለ በሽታ መሆኑን ሁሉም ሰው ማወቅ አለበት፡፡
  ደብሊው.ሲ.ሃንዲ
- ፍቅር ምስጢር መሆኑ ያበቃ ዕለት፣ ደስታነቱ ያከትማል፡፡
  አፍራ ቤህን
- ፍቅር ልክ እንደ ኩፍኝ ሁላችንም ሊወጣልን ይገባል፡፡
  ጄሮሜ ኬ. ጄሮሜ