Administrator

Administrator

 - አምና 72ኛ የነበሩት ትራምፕ፣ ዘንድሮ 2ኛ ሆነዋል - ከ74 የአለማችን ሃያላን፣ አፍሪካውያን 2 ብቻ ናቸው

    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት 74 ሰዎች የተካተቱበትን የ2016 የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ፣ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሴስ እና የአሜሪካ የፌደራል ሪዘርቭ ሃላፊ ጃኔት የለን እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ፣ የአልፋቤት ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ላሪ ፔጅ፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ አምና 72ኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ትራምፕ፣ በሚገርም መሻሻል ዘንድሮ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፣ አምና በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአንጻሩ ዘንድሮ ወደ 48ኛ ደረጃ አሽቆልቁለዋል፡፡ በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ውስጥ ሁለት አፍሪካውያን ብቻ የተካተቱ ሲሆን፣ 44ኛ ደረጃን የያዙት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ ከአፍሪካውያን መካከል ቀዳሚው ሃያል ሰው ሲባሉ፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ 68ኛ ደረጃን በመያዝ ሁለተኛው ሃያል ሰው ሆነዋል፡፡
በፎርብስ የአመቱ ሃያላን ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስማቸው የተካተተ ግለሰቦች ቁጥር 11 እንደሆነ የጠቆመው መጽሄቱ፣ ከእነዚህም መካከል የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ እና የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮዲሪጎ ዱሬቴ እንደሚገኙበት ገልጧል፡፡ ፎርብስ መጽሄት የአመቱን የአለማችን ሃያላን የመረጠባቸው መስፈርቶች በብዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ብቃት፣ የፋይናንስ አቅም፣ የተጽዕኖ ወሰን ስፋትና አቅምን የመጠቀም ብቃት የሚሉ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡

- ቱርክ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዋትዛፕን ዘግታለች

      የጀርመን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ቶማስ ኦፐርማን ፌስቡክ ሃሰተኛ ዜናዎችን በአፋጣኝ ከድረገጹ ላይ የማያስወግድ ከሆነ በአንድ ሃሰተኛ ዜና 500 ሺህ ዩሮ ቅጣት እንዲጣልበት የሚያስገድድ ህግ እንዲወጣ ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል። ፌስቡክ ግለሰቦችንና ተቋማትን ተጠቂ የሚደርጉ ሃሰተኛ ዜናዎችንና መረጃዎችን በተመለከተ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች በአግባቡ ተቀብሎ አፋጣኝ እርምጃ እየወሰደ አይደለም ያሉት ኦፐርማን፤ ይህን እንዲያደርግ የሚያስገድድ ህግ መውጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ፌስቡክ መሰል ሃሰተኛ ዜናዎችንና መረጃዎችን በተመለከተ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ተቀብሎ፣ በ24 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከማህበራዊ ድረገጹ ላይ የማይሰርዝ ከሆነ፣ እስከ 500 ሺህ ዩሮ የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት ይገባል ብለዋል፡፡ በመሰል ዜናዎችና መረጃዎች ተጠቂ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማትም ከፌስቡክ ካሳ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
ፖለቲከኛው ያቀረቡት የቅጣት ሃሳብ፣ አገሪቱ በመጪው የፈረንጆች አመት 2017 ልታካሂደው ያሰበቺው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት ሊረበሽ ይችላል በሚል የጀርመን መንግስት በድረገጾቹ ላይ ጥብቅ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ የያዘው አቋም አካል ነው ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ባለፈው ሰኞ በቱርክ የሩስያ አምባሳደር አንድሪ ካርሎቭ በጥይት መገደላቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዋትዛፕን መዝጋቱን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡

   - ከ26 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ 45 ያህል ቆስለዋል - የ92 አመቱ ሙጋቤ በቀጣዩ ምርጫም ይወዳደራሉ

      የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ዘመን ገደባቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት አለማሳየታቸው የቀሰቀሰው ከፍተኛ ተቃውሞ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት የፈጠረ ሲሆን  የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከ26 በላይ ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ቆይታ ባለፈው ማክሰኞ ቢያበቃም እስከ 2018 በስልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ በፓርቲያቸው ከተገለጸ በኋላ  የአገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የጠሩት ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ግጭት ማምራቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በርካታ ተቃዋሚዎች ባለፈው ማክሰኞ የገዢውን ፓርቲ ቢሮ ማቃጠላቸውን ተከትሎ፣ በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት መከሰቱንና የጸጥታ ሃይሎች ቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ በርካታ ዜጎችን ማሰራቸውን ገልጧል፡፡
በመዲናዋ ኪንሻሳ የተጀመረው ተቃውሞው ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተስፋፋና ውጥረቱ እየተባባሰ መምጣቱን ያመለከተው ዘገባው፤ ተመድ 45 ያህል ተቃዋሚዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መቁሰላቸውን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁንና በአገሪቱ የተሰማራው የተመድ የሰላም አስከባሪ ሃይልም ግጭቱ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳያመራ መስጋቱንና ውጥረቱን ለማርገብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡
አሜሪካ ፕሬዚዳንት ካቢላ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ተነሳሽነት አለማሳየታቸው አሳዝኖኛል ማለቷን የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ ባለፈው ወር ላይ ምርጫ መደረግ ቢገባውም የምርጫ ኮሚሽኑ ሰበብ አስባብ በማብዛት ምርጫውን ማራዘሙ ካቢላን በስልጣን ላይ ለማቆየት የታሰበ ሴራ ነው የሚል ቁጣ መፍጠሩንም ገልጧል፡፡
ከ2001 አንስተው አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት የ45 አመቱ ጆሴፍ ካቢላ፣ በህገመንግስቱ በተደነገገው መሰረት ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደር የማይችሉ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን 74 አባላት ያሉት የሽግግር መንግስት በማቋቋም እስከ 2018 ድረስ አገሪቱን በመምራት ለመቀጠል አቋም መያዛቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከ36 አመታት በላይ ዚምባብዌን የመሩትና አገሪቱን ወደከፋ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስላስገቧት ስልጣን ይበቃቸዋል የሚል ጫና ከውስጥም ከውጭም የበረታባቸው የ92 አመቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ ከአንድ አመት በኋላ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ፓርቲያቸው አስታውቋል፡፡ ሙጋቤ በ2018 ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ተቃዋሚ ሃይሎች የፓርቲውን ውሳኔ በማውገዝ አገሪቱን ወደ ከፋ ስራ አጥነት፣ የገንዘብ ቀውስና የኢኮኖሚ ድቀት ያስገቧት ሙጋቤ ስልጣን የሚይዙ ከሆነ የከፋ ቀውስ ይከተላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ፓርቲያቸው ዛኑ-ፒኤፍ ከሰሞኑ ባደረገው ጉባኤ ላይ በፓርቲው የወጣቶች ክንፍ፣ ሙጋቤ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው የአገሪቱ መሪ ሆነው ይቀጥሉ የሚል ሃሳብ መነሳቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ባለፉት አመታት የሙጋቤን አምባገነናዊ ስርዓት በማውገዝ ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው ሲያሰሙ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ የተሸነፉትና ስልጣናቸውን እንዲለቁ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ጫና ሲደረግባቸው የሰነበቱት የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜህ፤ የማንም ጫና ከስልጣኔ አያስለቅቀኝም ሲሉ በድጋሚ በአቋማቸው መጽናታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ ከፈጣሪ በቀር ስልጣኔን ሊያስለቅቀኝ የሚችል አንዳች እንኳን ምድራዊ ሃይል የለም በማለት እቅጩን ተናግረዋል፡፡

  በሰሃራ በረሃ ውስጥ በሚገኘውና አልጀሪያንና ሞሮኮን በሚያዋስነው ተራራማ አካባቢ ከ37 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሰኞ ማለዳ ላይ ያልተጠበቀ በረዶ መጣሉን የእንግሊዙ ሜትሮ ጋዜጣ  ዘግቧል፡፡ በረዶው ለአንድ ቀን ያህል ከቆየ በኋላ መቅለጡን የጠቆመው ዘገባው ፤ በሰሃራ በረሃ በረዶ ሲጥል ይህ በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ በማስታወስ ክስተቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዞ የመጣ ሊሆን እንደሚችል መነገሩንም ገልጧል፡፡
ከዚህ በፊት በሰሃራ በረሃ በረዶ ጥሎ የነበረው እ.ኤ.አ በ1979 ወርሃ የካቲት ላይ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በወቅቱ የጣለው በረዶ ለግማሽ ሰዓት ያህል ቆይቶ መቅለጡን በመጠቆም፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ግን አንዲትም የበረዶ ቅንጣት በበረሃው ክልል ውስጥ ታይታ እንደማትታወቅም አክሎ ገልጧል፡፡

ታዋቂው የድረገጽ ኩባንያ ያሁ፣ ከ1 ቢሊዮን በላይ የያሁ አካውንቶች የኢንተርኔት መረጃ ዘራፊዎች ከሶስት አመታት በፊት የፈጸሟቸው የሚስጥራዊ መረጃ ዝርፊያ ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ያሁ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ እ.ኤ.አ በ2013 በተፈጸሙ ጥቃቶች ከአንድ ቢሊዮን በላይ የድረገጹ ተጠቃሚዎች ስም፣ የስልክ ቁጥር፣ ሚስጥራዊ የይለፍ ቃል፣ የኢሜይል አድራሻ እና ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎች በዘራፊዎች ተሰርቀዋል፡፡ የኢንተርኔት ዘራፊዎች የተጠቀሱትን ሚስጥራዊ መረጃዎች ቢዘርፉም፣ የባንክና የክፍያ መረጃዎችን አለመዝረፋቸውን ኩባንያው አክሎ ገልጧል፡፡ ያሁ ባለፈው መስከረም ባወጣው መረጃ፣ በ2014 ላይም 500 ሚሊዮን ያህል አካውንቶች የመሰል ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን እንዳስታወቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ኩባንያው ሰሞኑን ባወጣው መግለጫም የያሁ ተጠቃሚዎች ከመሰል አደገኛ የመረጃ ዘረፋዎችና ጥቃቶች ራሳቸውን ለመጠበቅ፣ የአካውንቶቻቸውን ሚስጥራዊ የይለፍ ቃሎችና የደህንነት ማረጋገጫ ጥያቄዎች እንዲቀይሩ ኩባንያው አሳስቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በካሊፎርኒያ ያደረገው ያሁ፣ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጠቆመው ዘገባው፣ ዘራፊዎች የፈጸሙበት ጥቃት ቨሪዞን የተባለው ተቋም ያሁን ለመግዛት በጀመረው ድርድር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚል ስጋት መፈጠሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

 - ታዋቂ ድምጻውያን በበዓለ ሲመቱ ላይ አንዘፍንም ብለዋል
                        - ለመዝፈን ቃል የገባችው አንዲት ድምጻዊት ብቻ ናት

     ታዋቂዋ ድምጻዊት ሴሌን ዲዮን ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ወር በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ በሚከናወነው በዓለ ሲመታቸው ላይ የሙዚቃ ስራዎቿን እንድታቀርብ ያቀረቡላትን ግብዣ አልቀበልም ማለቷ ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ በበዓለ ሲመት አዘጋጆቻቸው በኩል ለሴሌን ዲዮን በክብር ግብዣ ቢያቀርቡላትም፣ ድምጻዊቷ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝታ ለመዝፈን ፈቃደኛ አለመሆኗን እንደገለጸች ዘራፕ ድረገጽ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡ ከሴሌን ዲዮን በተጨማሪ የትራምፕን ግብዣ አልቀበልም ያሉ ሌሎች አለማቀፍ ዝናን ያተረፉ ድምጻውያን መኖራቸውን የጠቆመው ድረገጹ፤ ከእነዚህም መካከል ኤልተን ጆን፣ ጋርት ብሩክስና አንድሪያ ቦሴሊ እንደሚገኙበት ገልጧል፡፡
አንዳንድ ድምጻውያን ፈቃደኝነታቸውን በመግለጽ በበዓለ ሲመቱ ላይ ለመዝፈን ቀጠሮ ቢይዙም፣ የትራምፕ ተቃዋሚ የሆኑ አድናቂዎቻቸው ባደረጉባቸው ጫና ሳቢያ ከሰሞኑ ሃሳባቸውን እንደቀየሩ የጠቆመው ዘገባው፤ አብዛኞቹ ድምጻውያን ግብዣውን ያልተቀበሉት በበዓለ ሲመቱ ላይ ተገኝተው በመዝፈን ለትራምፕ ፕሬዚዳንትነት እውቅና መስጠት ባለመፈለጋቸው ነው መባሉንም ጠቅሷል፡፡
በበዓለ ሲመቱ ላይ እንዲዘፍኑ ግብዣ ከተደረገላቸው ድምጻውያን መካከል እስካሁን ድረስ በፕሮግራሙ ላይ እንደምትገኝ ለአዘጋጆቹ ማረጋገጫ የሰጠቺውና በዝግጅቱ ላይ የአሜሪካን የህዝብ መዝሙር ለመዘመር ቀጠሮ የተያዘላት የ16 አመቷ ታዳጊ ድምጻዊት ጃኪ ኢቫንቾ ብቻ ናት ተብሏል፡፡

ለጋዜጦች፣ መጽሃፍት፣ መጽሄቶች፣ ደረሰኞች--- ህትመት የሚሆኑ ወረቀቶችን ያመርታል

     “ፒዩርውድ ፐልፕ ፔፐር ኤንድ ፓኬጂንግ” ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ በአንድ ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ግዙፍ የወረቀትና የማሸጊያ ካርቶን ማምረቻ ፋብሪካ በዱከም አካባቢ ሊገነባ መሆኑን በተለይ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያውያን፣ በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በቻይናውያን ባለሃብቶች የጋራ ጥምረት የተቋቋመው ኩባንያው፤ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙንና በኦሮምያ ክልል በዱከም ከተማ አካባቢ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ዞን፣ ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል 68 ሄክታር ቦታ መረከቡን በመጠቆም፣ የፋብሪካው ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመርም ገልጧል፡፡
ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ማምረት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ፋብሪካው፤ ዘመኑ የደረሰበትን የማምረቻ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥራት ያላቸው የተለያዩ አይነት ምርቶችን በማምረት በስፋት ለገበያ እንደሚያቀርብ ኩባንያው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ቀዳሚ ትኩረቱን የሚያደርገው ከውጭ አገራት ጥቅል የመጸዳጃ ቤትና የህትመት ወረቀቶችን እያስመጡ በጥሬ እቃነት ለሚጠቀሙ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች የተለያዩ አይነት ጥቅል ወረቀቶችን በማቅረብ ላይ እንደሆነ የጠቆሙት የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አቶ ማሂር ኢስማኤል፤ ፋብሪካው በአመት 32 ሺህ 500 ቶን ያህል የተለያዩ አይነት የንጽህና መጠበቂያና የህትመት ወረቀቶችን እንዲሁም የማሸጊያ ካርቶኖችን የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለ700 ያህል ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥር የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ ፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርትንና ጥቅም ላይ የዋሉ ወረቀቶችን መልሶ በጥሬ እቃነት የሚጠቀም በመሆኑ ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡ ለንጽህና መጠበቂያና ለመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ከሚውሉ ለስላሳ ወረቀቶች በተጨማሪ ለጋዜጦች፣ ለመጽሃፍት፣ ለመጽሄቶች፣ ለደረሰኞች፣ ለቀን መቁጠሪያዎችና ለሌሎች የህትመት ስራዎች የሚውሉ የተለያዩ አይነት ወረቀቶችን እንዲሁም የማሸጊያ ካርቶኖችን እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበው ፋብሪካው፤ ለአገር ውስጥ የወረቀት አምራቾች ጥቅል ወረቀቶችን የማቅረብ እቅድ እንዳለውም ተነግሯል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የወረቀት ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን ባለመቻሉ፣ አገሪቱ የወረቀት ምርቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ አገራት እየገዛች ለመጠቀም ተገድዳ መቆየቷን የጠቆሙት አቶ ማሂር፤ የዚህ ግዙፍ ፋብሪካ መገንባት ለወረቀት ግዢ የሚወጣውን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በማዳን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

Saturday, 24 December 2016 12:46

የፖለቲካ ጥግ

- ፖለቲካ ከፊዚክስ የበለጠ አስቸጋሪ ነው፡፡
     አልበርት አንስታይን
- ፖለቲኞች የትም ቦታ አንድ ናቸው፡፡ ወንዝ በሌለበትም እንኳን ድልድይ ለመገንባት ቃል ይገባሉ፡፡
     ኒክታ ክሩስቼቭ
- እውነት በአብላጫ ድምፅ አይወሰንም፡፡
     ዱግ ግዊን
- ኮንሰርቫቲቭ፤ምንም ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ መደረግ እንደሌለበት የሚያምን ሰው ነው፡፡
     አልፍሬድ ኢ.ዊጋም
- አንዳንድ ሰዎች ለመርሃቸው ሲሉ ፓርቲያቸውን ይለውጣሉ፤ ሌሎች ደግሞ ለፓርቲያቸው ሲሉ መርሃቸውን ይለውጣሉ፡፡
    ዊንስተን ቸርቺል
- ፖለቲካ ጨዋታ ሳይሆን ከባድ ሥራ ነው፡፡
    ዊንስተን ቸርቺል
- ለአሜሪካ ነፃነት ትልቁ አደጋ ህገ መንግስቱን ችላ የሚል መንግስት ነው፡፡
    ቶማስ ጀፈርሰን
- ሁሉም ሰዎች ሲፈጠሩ ተመሳሳይ ናቸው - ከሪፐብሊካኖችና ዲሞክራቶች በስተቀር፡፡
    ግሮቾ ማርክስ
-የማታ ማታ የምናስታውሰው የጠላቶቻችንን ንግግር ሳይሆን የወዳጆቻችንን ዝምታ ነው፡፡
    ማርቲን ሉተርኪንግ
- በፖለቲካ፣ ምላሽ ያልተሰጠው ውሸት፣ በ24 ሰዓት ውስጥ እውነት ይሆናል፡፡
   ዊሊ ብራውን
- በፖለቲካ ውስጥ አለመሳተፍ ከሚያስከትላቸው ቅጣቶች አንዱ ካንተ ባነሱ ሰዎች መተዳደርን ነው፡፡
   ፕሌቶ
- በዝግታ እራመዳለሁ፤ ነገር ግን ፈፅሞ ወደ ኋላ አልራመድም፡፡
    አብርሃም ሊንከን
- ልጆቼ ሂሳብና ፍልስፍና የማጥናት ነፃነት እንዲያገኙ፣ እኔ ፖለቲካና ጦርነት ማጥናት ይኖርብኛል፡፡   
   ጆን አዳምስ

Sunday, 25 December 2016 00:00

የፍቅር ጥግ

- ወዳጆች ፍቅራቸውን የሚያሳዩት በደስታ ጊዜ አይደለም፤ በመከራ ጊዜ ነው፡፡
     ዩሪፒዴስ
- ፍቅር የሚባለው የሌላው ሰው ደስታ ከራስህ ደስታ ሲልቅብህ ነው፡፡
    ኤች.ጃክሰን ብራውን ጄአር.
- ሁሉንም ውድድ፤ጥቂቶችን እመን፤ በማንም ላይ ክፉ አትስራ፡፡
    ዊሊያም ሼክስፒር  
- ህይወትን ከወደድካት፣ መልሳ እንደምትወድህ ተገንዝቤአለሁ፡፡
    አርተር ሩቢንስቴይን
- በፍቅር ለመውደቅህ ስበትን ሰበብ ማድረግ አትችልም፡፡
    አልበርት አንስታይን  
- አንዳንዴ ልብ ለዓይን የተሰወረውን ያያል፡፡
    ኤች. ጃክሰን ብራውን ጄአር  
- አንድ ሰው የሚፈቀረው ስለተፈቀረ ነው፡፡ ለማፍቀር ምክንያት አያስፈልግም፡፡
    ፓውሎ ኮልሆ
- ህይወት መዝሙር ነው - ዘምረው፡፡
 •  ህይወት ጨዋታ ነው - ተጫወተው፡፡          
 • ህይወት ፈተና ነው - ተጋፈጠው፡፡
 • ህይወት ህልም ነው - እውን አድርገው፡፡
 • ህይወት መስዋዕት ነው - ሰዋው፡፡
 • ህይወት ፍቅር ነው - አጣጥመው፡፡
     ሳይ ባባ
- የድሮ ነገሮች ሁሉ እወዳለሁ - የድሮ ጓደኞች፤ የድሮ ዘመን፣ የድሮ ባህርይ፣ የድሮ መፃህፍት፣ የድሮ ወይን ጠጅ፡፡
    ኦሊቨር ጎልድስሚዝ  
- ፍቅር አንደ ቫይረስ ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜ በማንም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡
    ማያ አንጄሎ  
- ፍቅር እውነተኛ እጣ ፈንታችን ነው፡፡ የህይወትን ትርጉም ለብቻችን አናገኘውም። ከሌሎች ጋር ሆነን እንጂ፡፡
    ቶማስ ሜርቶን
- ሰዎች ይወዱኛል፡፡ ደግሞ ታውቃላችሁ… በጣም ስኬታማ ነኝ፡፡ ሁሉም ይወደኛል፡፡
    ዶናልድ ትራምፕ  
- በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያለ ፍቅር ኖረዋል፤ አንድም ሰው ግን ያለ ውሃ አልኖረም፡፡
   ደብሊው.ኤች.ኤዩደን
- የተገኘነው ከፍቅር አብራክ ነው፤ ፍቅር እናታችን ናት፡፡
    ሩሚ  

Sunday, 25 December 2016 00:00

የዘላለም ጥግ

(ዝነኞች በመሞቻቸው ሰዓት የተናገሩት)

· ‹‹የመጨረሻ ቃል የሚያስፈልገው በህይወት ሳሉ በቅጡ ሳይናገሩ ለቀሩ ጅሎች ነው፡፡››
      ካርል ማርክስ (ፈላስፋ)  
· ‹‹ከሸክላ የተገነባች ሮም አገኘሁ፤ እምነበረዷን ሮምን ትቼላችሁ እሄዳለሁ፡፡››
      አጉስተስ ቄሳር
   (የመጀመሪያው የሮማ ንጉስ፣ ለህዝቡ የተናገረው)
· ‹‹ለመሞት ቅንጣት ታህል አልፈራሁም።››
      ቦብ ማርሊ (ሙዚቀኛ)  
· ‹‹እግዚአብሔርንና የሰው ልጅን አስቀይሜአለሁ፤ ምክንያቱም ሥራዬ ሊኖረው የሚገባው የጥራት ደረጃ ላይ አልደረሰም››  
     ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ  (ፈልሳፊና ሰዓሊ)
· ‹‹ዛሬ ማታ እሄዳለሁ››
     ጄምስ ብራውን (ሙዚቀኛ)
· ‹‹ሁሉም ደስተኛ ነው? ሁሉም ሰው ደስተኛ እንዲሆን እሻለሁ፡፡ እኔ ደስተኛ መሆኔን አውቃለሁ››
    ኢቴል ባሪሞር (ተዋናይት)
· ‹‹አሁን ልተኛ ነው፤ ደህና እደሩ››
    ሎርድ ጆርጅ ባይሮን (ፀሐፊ)
· ‹‹መግባት አለብኝ፤ ጉሙ እየገለጠ ነው››
    ኢሚሊ ዲክንሰን (ገጣሚ)  
· ‹‹እዚያ በጣም ውብ ነው››
   ቶማስ አልቫ ኤዲሰን (ፈልሳፊ)  
· ‹‹አዎ ከባድ ነው፤ ኮሜዲ የመስራት ያህል ግን አይከብድም››   (መሞት ከባድ እንደሆነ ተጠይቆ የመለሰው)
    ኢድመንድ ግዌን (ተዋናይ)
· ‹‹ጥቁር ብርሃን ይታየኛል››
    ቪክቶር ሁጎ (ፀሐፊ)  
· ‹‹ንግስት ነኝ፤ ነገር ግን ክንዶቼን የማንቀሳቀስ ሃይል የለኝም››
    ሉይስ (የፐርሽያ ንግስት)
· ‹‹ምስኪን ነፍሴን ጌታ ይርዳት››
    ኤደጋር አላን ፓ (ፀሐፊ)
· ‹‹ምንም ያልተበረዘ 18 መለኪያ ውስኪ ገልብጫለሁ፤  ይሄ አዲስ ክብረ ወሰን ይመስለኛል….››
    ዳይላን ቶማስ (ገጣሚ)

Page 5 of 307