Administrator

Administrator

•    ፖሊስ አደጋውን እያጣራሁ ነው ብሏል
በትላንትናው ዕለት በታላቁ አንዋር መስጊድ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ በ5 ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲደርስ በ19 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ ፖሊስ ቦንቡን የወረወረውን ግለሰብ ለመያዝ ክትትል እያደረገመሆኑን አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስቴር አቶ ጌታቸው ረዳ አደጋውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ፍንዳታው የአካል ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው የሞተ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ጉዳቱ የደረሰባቸው ዜጎችም ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ በሚገኙ የህክምና ማዕከላት ተወስደው እርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል ተብሏል፡፡
ትላንት ምሽት የብሔራዊ  የመረጃና የደህንነት አገልግሎትና የፖሊስ ግብረ ሃይል በሰጡት መግለጫ፤በመርካቶ ታላቁ መስጊድ የጁምአ ጸሎት አድርሰው ሲወጡ በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ የተወረወረው ቦንብ በ5 ሰዎች ላይ ከባድና በ19 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ማድረሱን የገለጸ ሲሆን ፖሊስ ቦንቡን የወረወረውን ግለሰብ ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 05 December 2015 15:57

ማስተካከያ

     ቅዳሜ ህዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም በቅፅ 16 ቁጥር 828 የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ከሳሽም ምስክርም ሆኖ ፍ/ቤት ቀረበ” በሚል ርዕስ በወጣው ዘገባ፤ “ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን በሙሉ ካዳመጠ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከሉ በማለት ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጥሯል” የሚለው፣ “ምስክሮችን ካደመጠ በኋላ ፍ/ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጥሯል” በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ እየገለፅን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

         ህንድ ባለፉት ከ100 በላይ አመታት ከተመዘገቡት የዝናብ መጠኖች ከፍተኛው የተባለውን ሃይለኛ ዝናብ ባለፈው ረቡዕ በደቡባዊ ክፍሏ ያስተናገደች ሲሆን ዝናቡ ባስከተለው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ክፉኛ መመታቷን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ታሚል ናዱ በተባለው የአገሪቱ ግዛት የዘነበው ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የግዛቱ መዲና በሆነችው ቼናይ፣ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውንና አውሮፕላን ማረፊያውም ስራ ማቋረጡን ገልጧል። በአካባቢው ወሩን ሙሉ ይዘንባል ተብሎ ከሚጠበቀው አማካይ የዝናብ መጠን በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ዝናብ በ24 ሰዓታት ውስጥ መዝነቡንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
በህንድ አራተኛዋ ትልቅ ከተማ የሆነችው ቼናይ፣ ከአገሪቱ ዋነኛ የመኪና አምራችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከላት አንዷ እንደሆነች ዘገባው ጠቁሞ ከተማዋ ጎርፉ ባስከተለው የመብራት መቋረጥ እንቅስቃሴዋ ሙሉ ለሙሉ መገታቱን አስረድቷል። የጎርፍ አደጋው ያስከተለውን ጥፋት ለማከምና ተረጂዎችን ለማቋቋም አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ግብረ ሃይል ተቋሙሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

 ፖሊሶችና የመንግስት ባለስልጣናት ይከተላሉ
                     - በአመቱ ከ75 ሚ በላይ የ28 አገራት ዜጎች በሙስና ገንዘብ ከፍለዋል
    በአፍሪካ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በ2015 በሙስና ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዙት፣ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ባለጸጎችና የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎች መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣው አመታዊ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ በአህጉሪቱ ከባለጸጎች በመቀጠል በሙስና ሁለተኛውንና ሶስተኛውን ደረጃ የሚይዙት የፖሊስ መኮንኖችና የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡
በ28 የአፍሪካ አገራት ላይ በተሰራው በዚህ ጥናት፣ ከ43 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ቃለመጠይቅ እንደተደረገላቸው የጠቆመው ዘገባው፤በዚህም ሙስና በአህጉሪቱ ክፉኛ መስፋፋቱንና በአመቱ ከ75 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን ከፖሊስ ወይም ከፍርድ ቤት ቅጣት ለመዳንና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉላቸው ለማስቻል፣ በሙስና መልክ ገንዘብ እንደከፈሉ ተደርሶበታል ብሏል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የአፍሪካ አገራት በአመቱ የከፋው ሙስና የተመዘገበው በላይቤሪያ ሲሆን፣ ካሜሩን፣ ናይጀሪያና ሴራሊዮን ይከተላሉ ተብሏል። ከምስራቅ አፍሪካ አገራትም ኡጋንዳና ኬንያ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ተነግሯል፡፡
በላይቤሪያ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው የአገሪቱ ዜጎች መካከል 69 በመቶ የሚሆኑት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሉ ለስራ ሃላፊዎች ገንዘብ በሙስና መልክ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቦስትዋና እና በሞሪሺየስ 1 በመቶ ያህሉ ሰዎች ብቻ ሙስና እንደሰጡ የገለጸው ዘገባው፤በጥናቱ ከተዳሰሱ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አነስተኛውን ሙስና ሰርተው የተገኙት የሃይማኖት መሪዎች መሆናቸውን ገልጧል፡፡ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ድህነትን ከማባባስ በተጨማሪ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዳይሟሉ ያግዳል ያለው ተቋሙ፤በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆች አመት ስልጣናቸውን ያለአግባብ በሚጠቀሙ አካላት ሳቢያ ክፉኛ የተጎዱት ሙስና መስጠት አቅም የሌላቸው አፍሪካውያን ድሆች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

        የቀድሞው የጊኒ ፕሬዚዳንት ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ፤ ከሁለት አመታት በፊት በኢትዮጵያ በኩል ወደ አሜሪካ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ከ64ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ደብቀው ማሸሻቸውን ባለፈው ማክሰኞ በኖርዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳመኑ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ በወቅቱ ዋሽንግተን በሚገኘው ዱሌስ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ፣ ከ10 ሺህ ዶላር በታች እንደያዙ በመናገር ቀሪውን ገንዘብ በሻንጣቸው ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ መሞከራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ይህ ድርጊታቸው በጥበቃ ሃይሎች ተደርሶበት ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጧል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ለፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቃላቸውን በሰጡበት ወቅትም፣ በቋንቋ ችግር ምክንያት በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ያለውን የጉምሩክ አሰራር በአግባቡ መረዳት አልቻልኩም ብለው ሊያመልጡ መሞከራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር እንዳለው፤ የ51 አመቱ ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴን ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት በመጪው የካቲት በሚሰየም ችሎት በግለሰቡ ላይ እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት ቅጣት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሴኩባ ኮናቴ በጊኒ የ50 አመታት ታሪክ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በተባለውና እ.ኤ.አ በ2010 በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣን እንደለቀቁ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የአፍሪካ ህብረት የጸጥታ ሃይል ጄኔራል ኮማንደር ሆነው ሲያገለግሉ እንደቆዩ ጠቁሟል፡፡

 - በዱባይ በበኩሏ ጤናማ
             አኗኗር የሚከተሉትን ልትሸልም ነው
    የጂያንግሱ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውና በምስራቃዊ ቻይና የምትገኘው የናንጂንግ ከተማ የቆሸሹ መኪኖችን ሲያሽከረክሩ የተገኙ ሾፌሮችን በገንዘብ የምትቀጣበትን አዲስ አሰራር ተግባራዊ ልታደርግ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከተማዋ ገጽታዋን ለመገንባት የጀመረችው እንቅስቃሴ አካል የሆነው ይህ የቅጣት መመሪያ እንደሚለው፣ አካላቸውና ጎማቸው የቆሸሸ መኪኖች 16 ዶላር፣ የታርጋ ቁጥራቸው በቆሻሻ የደበዘዘ ወይም ህጋዊ ፍቃድ የሌለው ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው መኪኖች እስከ 320 ዶላር የሚደርስ ቅጣት ይጣልባቸዋል ይላል፡፡
ኒጃንግ ዴይሊ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ አዲሱን መመሪያ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ ቻይናውያን የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች “የእኛ መኪና ለቆሸሸ፣ መንግስትን ምን ጥልቅ አደረገው” ሲሉ የከተማዋ አስተዳደር ያቀደውን የቅጣት አሰራር ክፉኛ እየተቹት እንደሚገኙ ዘገባው ገልጧል፡፡
አንዳንዶቹ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎችም የቅጣት አሰራሩን መንግስት ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲል የቀየሰው ተገቢ ያልሆነ ስልት ነው ሲሉ መተቸታቸው ተነግሯል፡፡ዱባይ በበኩሏ! ነዋሪዎቿን ንቁና ጤናማ እንዲሆኑ ለማበረታታት በማሰብ የሲኒማ መግቢያ ትኬትና ነጻ የጂምናዚየም አባልነት መታወቂያ ልትሰጥ ማቀዷን ገልፍ ኒውስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የዱባይ የጤና ባለስልጣን መስሪያ ቤት ያወጣው አዲስ የማበረታቻ ዕቅድ እንደሚለው፣ አዘውትረው ጤናማ ምግብ የሚመገቡና የሰውነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በየጊዜው በድረገጽ አማካይነት የሚሰጡት ሳምንታዊ ውጤት ተመዝግቦ የማበረታቻ ሽልማቱን ያገኛሉ፡፡
69 በመቶ የዱባይ ነዋሪ የሆኑ አዋቂዎች ከመጠን ያለፈ የውፍረት ችግር ተጠቂ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከተማዋ ከዚህ በፊትም ክብደታቸውን ለመቀነስ የቻሉ ነዋሪዎቿን ወርቅ የምትሸልምበት አሰራር ተግባራዊ አድርጋ እንደነበር አስታውሷል፡፡

    አይሲስ ትዊተር በተባለው ታዋቂ የማህበራዊ ድረ ገጽ አማካይነት የሽብር እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት የሚያግዝ የፕሮፓጋንዳ ስራ የሚሰሩና ለሽብር ቡድኑ አዳዲስ አባላትን የሚመለምሉ ከ300 በላይ አሜሪካውያን አምባሳደሮች እንዳሉትና አብዛኞቹም ሴቶች እንደሆኑ ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የጽንፈኝነት ጥናት ፕሮግራም ተመራማሪዎች፣ በአሜሪካ የሚኖሩ የአይሲስን አላማ የሚያቀነቅኑ ግለሰቦች በተለይም ትዊተር በተባለው ማህበራዊ ድረገጽ አማካይነት የፕሮፓጋንዳና የምልመላ ስራቸውን እንደሚያከናውኑ የገለጹ ሲሆን ምንም እንኳን ትዊተር፣መሰል አካውንቶችን በተደጋጋሚ ቢዘጋም የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ግን አልቀነሰም ብለዋል፡፡ ትዊተር ከአይሲስ ጋር ንክኪ አላቸው ብሎ የሚገምታቸውን አካውንቶች እየተከታተለ ቢዘጋም፣ ተጠቃሚዎቹ በሰዓታት እድሜ ውስጥ አዲስ አካውንቶችን በመክፈት፣ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ያህል የተከታይ ቁጥር እያገኙ ነው ብለዋል አጥኚዎቹ፡፡
ተጠቃሚዎቹ በዋናነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከሽብር ጋር በተያያዙ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩና የሽብር ቡድኖች በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጽሟቸውን የሽብር ጥቃቶችም ሲደግፉና ሲያደንቁ እንደተገኙ ዘገባው ገልጧል፡፡

     በተለያዩ ተክሎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ፀረ አረም ኬሚካሎች ያለቀናቸው ለሚወለዱ ህፃናት መንስኤ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት አመለከተ፡፡ በአሜሪካ አገር አንድያን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ ድርጅቱ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ በናይትሬት የበለፀጉ ፀረ አረም ኬሚካሎችና  ማዳበሪያዎች ህፃናት ያለቀናቸው እንዲወለዱና ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲጋለጡ እያደረጉ ነው፡፡ ነፍሰጡር  ሴቶች በተለይም በእርግዝናቸው የመጨረሻ ወራት ለፀረ አረም ኬሚካሎችና ማዳበሪያዎች በስፋት የሚጋለጡ ከሆነ፣ በሆዳቸው በያዙት ፅንስ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር የመፍጠራቸው ዕድል ሰፊ ከመሆኑም በላይ ልጃቸውን ያለቀኑ ለመውለድ ይገደዳሉ ብሏል - ዘገባው፡፡

        የቴሌኮም መሰረተ ልማት አቅራቢው ዜድቲኢ ኩባንያ፤ በኢትዮጵያ በሁለት አይነት መስኮች ተሰማርቷል፡፡ ሞባይል ስልኮች አምርቶ ያቀርባል። በሌላ በኩል የኔትወርክ ዝርጋታ ያከናውናል። በአሜሪካ ገበያ በስማርት ስልኮች የገበያ ድርሻ ኩባንያው በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡  በአውሮፓና በእስያም ቢሆን ድርሻው ሰፊ ነው፡፡ በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ ኩባንያው በስማርት ስልኮች ያለውን የገበያ ድርሻ እያሰፋ ሲሆን ከ6 ያላነሱ የተለያዩ ሞዴል ስማርት ስልኮችን ወደ ገበያ አስገብቷል፡፡
አላማችን በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የስማርት ስልኮች ፍላጎት ጥራት ያላቸውን ስልኮች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ነው የሚሉት የኩባንያው ተርሚናል ቢዝነስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር  ሣም ዊ፤ ኩባንያው በሀገሪቱ በኔትወርክ ዝርጋታ ውስጥ እየተሳተፈ በመሆኑ ስማርት ስልኮቹ በኔትወርክ አይታሙም፤ ከፍተኛ የኔትወርክ ጥራት አላቸው ይላሉ፡፡ ዜድቲኢ በኢትዮጵያ የስማርት ስልኮች ፋብሪካ ለማቋቋም በሂደት ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
አብዛኛው ሰው ዜድቲኢን ከዚህ ቀደም የሚያውቀው የCDMA፣ 1x ከመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ጋር በተገናኘ ሲሆን በስማርት ስልኮች ግን እምብዛም የተሰማራ አልነበረም፡፡ ጥራት ያላቸውን የዜድቲኢ ምርቶች ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሰብ፣ ኩባንያው የስማርት ስልክ ዘመናዊ ምርቶቹን ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል፤ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፡፡
በአትሌቲክስ የበርካታ ሪከርዶች ባለቤት የሆነው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ደግሞ እነዚህን የኩባንያውን ምርቶች በማስተዋወቅ የዜድቲኢ አምባሳደር ሆኖ እየሰራ ነው፡፡ ኃይሌ ምርቶቹን ተጠቅሞባቸው ጥራታቸውን በሙከራ ካረጋገጠ በኋላ አምባሳደር እንደሆነ የጠቀሱት ሚ/ር ሣም፤ ኩባንያው ይሄን ያደረገው በምርቶቹ ጥራት ስለሚተማመን ነው ይላሉ፡፡ በተለይ ምርቶቹ በኔትወርክ በኩል ያላቸው ጥራት በገበያ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኙ አድርጓል የሚሉት ሚ/ር ሣም ሁሉም ምርቶች በአማራጭነታቸውም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። ምርቶቹ ከፋብሪካ ከመውጣታቸው በፊት ጥብቅ ፍተሻና ሙከራ ተደርጎባቸው ጥራታቸው እንደሚረጋገጥም ገልፀዋል፡፡
ዲዛይናቸው ለአያያዝና ለእይታ እንዲያመቹና ማራኪ እንዲሆኑ ተደርገው የተዘጋጁ ሲሆን የውስጥ ጥራታቸውም አስተማማኝ ነው ይላሉ ዳይሬክተሩ። Grands 52 የተሰኘ ሰፊ ስክሪን ያለው የ4ጂ ተቀባይ ስልክ የኢትዮጵያን  ገበያ ከተቀላቀሉት ስማርት ፎኖች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን ምርቶቹ ተቀባይነት እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዜዲቲኢ በአሁን ወቅት አዳዲስ ምርቶቹን በኢትዮጵያ ገበያ በሰፊው እያስተዋወቀ ሲሆን አትሌት ኃይሌ የምርቶቹ አምባሳደር ሆኖ መስራቱ ውጤታማ እያደረገው መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ እቅድ ያለው ኩባንያው፤ ከሁለት ኢትዮጵያውያን አንዱ የዜድቲ ምርት ተጠቃሚ እንዲሆን ጠንክሮ ይሰራል ያሉት ሚ/ር ሣም፤ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የመሸጫ መደብሮችን ለመክፈት እቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚቋቋመው የስማርት ፎኖች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለኢትዮጵያውያን የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በኢትዮጵያና በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቹን የሚያቀርብበትን እድል ለኩባንያው ይፈጥርለታል ተብሏል፡፡
ኩባንያው ከቢዝነስ ጐን ለጐን በኢትዮጵያ የተለያዩ ማህበራዊ ተሳትፎዎች ላይም የተሰማራ ሲሆን በቅርቡ የተከናወነውን “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ”ን የወርቅ ደረጃ ስፖንሰር ሆኗል፡፡ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተዘጋጀውን የስፖርት ኤክስፖም በዳይመንድ ደረጃ ስፖንሰር አድርጓል። ኩባንያው በቀጣይ በኢትዮጵያ ጥራት ያለው ኔትወርክ ከመዘርጋት ባሻገር  ደረጃቸውን የጠበቁ እጅግ ዘመናዊ ስማርት ፎኖችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ፣ ከሁለት ኢትዮጵያውያን የሞባይል ተጠቃሚዎች አንዱ የዜድቲኢ ምርት ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡


      የኢትዮ-ኮርያ የቢዝነስ ፎረም የተካሄደ ሲሆን ከኮርያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኩባንያዎች ለመጡ 40 ያህል የኢንዱስትሪው ኃላፊዎች በኢትዮጵያ በዘርፉ ስላለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ከትናንት በስቲያ በካፒታል ሆቴል የተካሄደውን የቢዝነስ ገለጻ ከኮርያ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከኮርያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን፣ ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ከኮርያ የንግድ ም/ቤትና ከ17 የኮርያ ኩባንያዎች የተውጣጡ የቢዝነስ ልዑካን ተከታትለውታል፡፡
የፎረሙ ዓላማ በሁለቱ አገር ኩባንያዎች መካከል ያለውን ትብብር ከፍ ለማድረግ፣ አዳዲስ የቢዝነስ አማራጮችን መፍጠር፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በስትራቴጂያዊ ትብብርና በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ የቢዝነስ ጉባኤዎች ማካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጨርቃጨርቅና  አልባሳት፣ ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ … ኢንቨስትመንት አመቺ መሆኗን የጠቀሱት የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ በቦሌ ለሚ ተሰርቶ አገልግሎት ከጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ፣ በሀዋሳ፣ በመቀሌ፣ በኮምቦልቻ፣ በባህርዳርና በጅማ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑነ ገልጸዋል፡፡
6.000 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተጋመሰ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚኖራት፣ በአሁኑ ወቅት ለጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል መሸጧን፣ ለሱዳንና ለኬንያም ለመሸጥ መዋዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳላት የጠቀሱት የኮርያ የልማት ስትራቴጂ ተቋም የፕሮግራም ኦፊሰርና የልማት አማካሪ ዶ/ር ሊ-ጃ-ሁን፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥቅም የሚታፈስባት አገር ናት፡፡ ለምሳሌ 200 ሺህ ዶላር ኢንቨስት ብታደርግ ሰባት እጥፍ ጥቅም ታገኛለህ፡፡ ይህ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ስለዚህ በቀላል ኢንዱስትሪ ጀምሮ ወደ ትልቅ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የኮርያ የጨርቃጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት እየሰሩ ያሉት በባንግላዴሽ፣ በጓቲማላ፣ … እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ሉጃ-ሁን፣ ወደዚህ የመጡት በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት መሬት፣ በቀላሉ የሚሰለጥንና በርካሽ የሚሰራ የሰው ኃይል አላት፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ሲሆን ችግሮችም አሉ፡፡ ዋናው ችግር የሎጂስቲክስ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መናር ነው። ከጅቡቲ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር መስመር ከወር በኋላ ሥራ ሲጀምር ይህ ችግር እንደሚቃለል እርግጠኛ ነኝ በማለት አስረድተዋል፡፡