Administrator

Administrator

- በግለሰቡ ላይ የደረሱ የመብት ጥሰቶች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ጠይቋል
- የዞን ዘጠኝ ጦማርያንን ሽልማት ለመቀበል ወደ ፓሪስ ሊጓዝ ነበር

    ተቀማጭነቱን በፈረንሳይ ያደረገው ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተሰኘ አለማቀፍ ተቋም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ከእስር ከተለቀቁት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች አንዱ የሆነውን ዘላለም ክብረት፤ ከአገር እንዳይወጣ መከልከሉ እንደሚያሳስበው አስታወቀ፡፡
የዞን ዘጠኝ ጦማርያን በዘንድሮው የሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት “የሲቲዝን ጆርናሊስት” ዘርፍ አሸናፊ ሆነው መመረጣቸውን ያስታወሰው ተቋሙ፣ ዘላለም ክብረት ጦማርያኑን ወክሎ ሽልማቱን ለመቀበል ባለፈው ሰኞ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ሊሄድ ሲል፣ በኢትዮጵያ መንግስት የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ፓስፖርቱን በመቀማት ወደ አውሮፕላኑ እንዳይገባ መታገዱን ገልጿል፡፡ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫው፡፡
የኢሚግሬሽን ባለስልጣናቱ ዘላለምና ሌሎች የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ከዚህ በፊት ታስረው መቆየታቸውን በምክንያትነት በመጥቀስ ከአገር መውጣት አትችልም እንዳሉት የጠቆመው ተቋሙ፣ በጦማሪው ላይ የተጣለውን የጉዞ እገዳ በተመለከተ በአዲስ አበባና በፓሪስ ከሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ገልጿል፡፡“በዘላለም ክብረት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ ያልጠበቅነው ነው፤ አስደንግጦናል፡፡ ከእስር በተፈታበት ወቅት እንቅስቃሴውን የሚገድብ ምንም አይነት ክልከላ አልተጣለበትም፣ የተቀሩት የዞን ዘጠኝ አባላትም ባለፈው ጥቅምት ከተመሰረተባቸው የሽብር ክስ ነጻ ተደርገዋል፤ ፓስፖርቱን የተቀማበት ምክንያት አልገባንም፣ የሚመለከታቸው አካላት የተጣሱትን የዘላለምን መብቶች በአፋጣኝ  እንዲያስከብሩ እንጠይቃለን” ብለዋል የተቋሙ የአፍሪካ ዴስክ ሃላፊ ክሊ ካን ስራይበር፡፡ ዘላለምፓስፖርቱን በተቀማ ማግስት ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ በተሰጠው መመሪያ መሰረት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማምራቱን፣ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝና ምርመራው እስካልተጠናቀቀ ድረስም ፓስፖርቱየማይመለስለት እንደተነገረው ተቋሙ በመግለጫ አስታውቋል፡፡


“በህገ መንግሥቱ የተደነገገውን የሳንሱር ክልከላ
የሚተገብር ውል ነው” አሳታሚዎች

   ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፤ ጋዜጣ አሳታሚዎች እንዲፈርሙ ያዘጋጀው የህትመት ውል በህገመንግስቱ የተደነገገውን የሳንሱር ክልከላ የሚተገብር ነው ሲል የተቃወመው ዋቢ የግል ፕሬስ አሳታሚዎች የዘርፍ ማህበር፤ ጉዳዩን መንግስት በአጽንኦት እንዲመረምረው በደብዳቤ ማመልከቱን አስታወቀ
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በበኩሉ፤ የተዘጋጀው ውል ከሳንሱር መቅረት ህግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብሏል፡፡
ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በማተሚያ ቤቱ ለሚጠቀሙ የጋዜጣ አሣታሚዎች ህዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ፤ የተወሰኑ አሣታሚዎች ማተሚያ ቤቱ ያወጣው ደንብ ላይ የጋራ ውይይት እንዲደረግ በጠየቁት መሠረት በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጐ ድርጅቱ ከአሣታሚዎቹ በተነሱ ነጥቦች ላይ ተገቢ ማብራሪያ የሰጠ ቢሆንም አሣታሚዎች እስካሁን ድረስ ውሉን እንዳልፈረሙ ጠቁሞ፣ እስከ ህዳር 30 ቀን 2008 ዓ.ም ውሉን ፈርመው እንዲልኩ አሳስቧል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በውሉ ጉዳይ መወያየቱን ያስታወቀው የአሣታሚዎቹ ማህበር፤ ድርጅቱ ውል እንፈራረም ማለቱ ተገቢ መሆኑንና እንደሚያምንበትም ገልፆ፤ ነገር ግን በውሉ ከተዘረዘሩት አንቀፆች ውስጥ በህገመንግስቱ አንቀፅ 29 የተነሳውን ቅድመ ምርመራን የሚቃረን አንቀፅ በመካተቱ ውሉን ለመፈረም እንቸገራለን ብሏል፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት በንኡስ አንቀፅ 3 በተራ ቁጥር ሀ፤ “የቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው” የሚለውን የጠቀሱት አሳታሚዎቹ፤ የብርሃንና ሠላም ውል ይሄን ህግ የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡
ማህበሩ የተቃወመው የውሉ አንቀፅ 10ኛ ቁጥር 1፤ “አታሚው በአሣታሚው እንዲታተም የቀረበለት የጽሑፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው” የሚለውንና በአንቀፁ ቁጥር 2፤ “አሣታሚው የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል” የሚለውን ነው፡፡
ማህበሩ በውሉ ውስጥ የተካተቱትን እነዚህን ሁለት ንኡስ አንቀፆች እንደማይቀበልና ከውሉ መውጣት አለባቸው ብሎ እንደሚያምን ጠቁሟል፡፡
ለመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በላከው ደብዳቤም፤ እነዚህ የውል አንቀፆች በህገ መንግሥቱ የተከለከለውን ቅድመ ምርመራን የሚተገብሩ ስለሆነ መንግስት ጉዳዩን በአጽንኦት መርምሮ አንቀፆቹ ከውሉ እንዲወጡለት ጠይቋል፡፡
ማህበሩ ለብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በላከው ደብዳቤ፤ ቀደም ሲል በተካሄዱ ውይይቶች ላይ እነዚሁ አንቀፆች እስካልተወገዱ ድረስ ውሉን ለመፈረም እንደማይችሉ መግለፃቸውን በማስታወስ፣ በድጋሚ ፈርሙ የሚል ማሳሰቢያ መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ቀጣይ ውይይት እንዲካሄድም ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
በማተሚያ ድርጅቱ የተዘጋጀው ውል ለፊርማ ከቀረበ ወደ 4 ዓመት ገደማ ሲሆነው አሳታሚዎችና ማተሚያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ ውይይት ቢያደርጉም በውሉ ላይ ሙሉ ለሙሉ መግባባት አልቻሉም፡፡
የማተሚያ ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ በበኩላቸው፤ የተዘጋጀው ውል አለማቀፍ ባህሪ ያለው መሆኑ ታምኖበት ሁሉም የመንግሥት ማተሚያ ድርጅቶች ተወያይተውበት ተግባራዊ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
አሳታሚዎቹ የተቃወሙት አንቀፅ፤ “አገርን የሚያፈርስ ዘገባ ካለ አላትምም” የሚል ነው ያሉት አቶ ተካ፤ እንደ አንድ የመንግሥት ተቋም፣ የህዝብንና የሀገርን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለብንና በህግም ስለምንጠየቅ ውሉን ለማስፈረም እንገደዳለን ብለዋል፡፡ “ውሉ በህገ መንግሥቱ ከተደነገገው የሣንሱር መቅረት ህግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ሌሎች የመንግሥት ጋዜጦች ውሉን ፈርመው አገልግሎት እያገኙ ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የግል ፕሬስ ባለቤቶችም ጉዳዩን የፖለቲካ ፍላጎት ማንፀባረቂያ ሊያደርጉት አይገባም ብለዋል፡፡
“አሁንም ያለ ውል መስራታችን ተገቢ አይደለም፤ ውሉን በተመለከተ ያቀረቡትን ቅሬታ የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ይመክርበትና ይወስናል፤ ከመንግሥት የሚሰጥ አቅጣጫ ካለም እናያለን” ብለዋል፤ አቶ ተካ አባዲ፡፡

   የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ሴት አውሮፕላን አብራሪዎች ብቻ ከአዲስ አበባ ወደ ታይላንድ ባንኮክ የደርሶ መልስ በረራ ከትናንት በስቲያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ዋና አብራሪም ሆነ ረዳት አብራሪ፣ ቴክኒንና የበረራ በቦይንግ 767 አስተናጋጆቹ እንዲሁም ተቆጣጣሪዎች ሙሉ በሙሉ ሴቶች ብቻ የሆኑበትን በረራ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደው “ቀጣይነት ላለው ልማት ሴቶችን ማብቃት” በሚል መርህ ነው ተብሏል፡፡በበረራው ወቅት ቲኬት ቆራጮች፣ የበረራ ደህንነት ባለሙያዎችና የደንበኞች እቃ ጫኞች ጭምር ሙሉ ለሙሉ ሴቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን ተሳፊሪዎቹ ግን አብዛኞቹ ወንዶች እንደነበሩ ታውቋል፡፡
በቦይንግ 767 የተከናወነውን በረራ በዋና አብራሪነት ካፒቴን አምሣለ ጓሉ በረዳት አብራሪነት ሠላም ተስፋዬ መርተውታል፡፡አየር መንገዱ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት በሚያከብርበት ዋዜማ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ማከናወኑ ታላቅ ስኬት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ፤ ከአየር መንገዱ ሠራተኞች 30 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡በሌላ በኩል የወንዶች የበላይነት የገነነበት እንደሆነ በሚነገርለት የዚምባቡዌ አየር መንገድ ባለፈው ማክሰኞ  ሙሉ በሙሉ በሴቶች የተመራ የአገር ውስጥ በረራ ከመዲናዋ ሀራሬ ወደ ቪክቶሪያ ፏፏቴ ማድረጉ ታውቋል፡፡ቦይንግ 737 – 200 አውሮፕላን በሀራሬ ሰማይ ላይ ያበረሩት ካፒቴን ቺና ማቲምባና ካፒቴን ሲምቢ ጴጥሮስ ሲሆኑ ዋና አብራሪዋ ካፒቴን ማቲምባ ከበረራው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠችው አስተያየት፤ “ታሪክ ሰርተናል” ብላለች፡፡ ረዳት አብራሪዋ ሲምቢ በበኩሏ፤ “እንዲህ ያለውን ታሪካዊ በረራ በማከናወኔ እድለኛ ነኝ” ስትል ስሜቷን ገልፃለች፡፡የሁለቱን እንስቶች የተሳካ በረራ ያደነቁት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን፤ አየር መንገዳቸው የሴቶችን ድርሻ የበለጠ ለማስፋት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡በዚምባቢዌያኑ እንስቶች ኩራት እንደተሰማው የገለፀው አለማቀፉ የሴት አብሪሪዎች ማህበር፤ በአለም ላይ ካሉ አብራሪዎች የሴቶቹ ድርሻ 6 በመቶ ብቻ መሆኑን አመልክቶ፣ አገራት በዘርፉ በርከት ያሉ ሴት ባለሙያዎችን ማፍራት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡

    ባለፈው ሳምንት በደብረብርሃን ከተማ የተመረቀው ግዙፍና እጅግ ዘመናዊ የተባለው ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣ ጥረት ኢንዶውመንት ዱዌት - ቫሳሪ ከተባሉ ሁለት የእንግሊዝ ኩባንያዎች ጋር በእኩል 50፣ 50 የአክሲዮን ድርሻ የተቋቋመ ፋብሪካ ነው፡፡ የዛሬ 20 ዓመት የተቋቋመው ጥረት ዳሽን ቢራ ፋብሪካን ጨምሮ ተመጋጋቢ ፋብሪካዎችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማቋቋሙ ስኬታማ አድርጎታል ተብሏል፡፡ጥረት የዛሬ 15 ዓመት በጎንደር ከተማ ዳሽን ቢራ ፋብሪካን መሰረተ፡፡
እዚያው ጎንደር ከተማ ለቢራ ፋብሪካው ብቅል የሚያቀርብ የብቅል ፋብሪካ በባህርዳር ከተማ፣ ለቢራ ፋብሪካው የጠርሙስ ሳጥን የሚያመርት ተክራሮት የተባለ ፋብሪካ፣ በኮምቦልቻ ቆርኪ የሚያመርት ዋሊያ ቆርኪና ጣሳ ፋብሪካ አቋቋመ፡፡
ከውጭ አገር የሚገዙ ዕቃዎችን አምባሰል የንግድ ድርጀት ያቀርባል፡፡ ወደብ ላይ የደረሱ ዕቃዎችን ክሊራንስ በለሳ ያከናውናል፡፡ ዕቃዎቹን ከወደብ አንስቶ ወደ አገር ውስጥ የሚያጓጉዘውና በየፋብሪካው የሚያደርሰው ደግሞ ጥቁር አባይ የተባለው የትራንስፖርት ድርጅት ነው፡፡
 ጥቁር አባይ የዳሽን ፋብሪካ ምርቶችንም ለደንበኞች ያደርሳል ብለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ታደሰ ካሳ፡፡ በክብር እንግድነት ተገኝተው ፋብሪካውን የመረቁት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ እጅግ ዘመናዊ በሆኑ መሳሪያዎች የተደራጀው ዳሽን ቢራ ፋብሪካ የአገራችን የግል ድርጅቶች፣ ከዓለም አቀፍ ታዋቂ ድርጅቶች ጋር በመጣመር ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የኢንዱስትሪ አመራር እውቀትና ክህሎት ለመጎናፀፍ በሚያስችል ደረጃ ላይ መሆናቸውን ያመለክታል አርሶ አደሮችንም ምርታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም፣ ፕላስቲክ፣ ቆርኪና ጠርሙስ አምራች ከሆኑና በደቡብ አማራ ክልል ከተገነቡ ተቋማት ጋር የምርት ትስስር የፈጠረ እንደሆነ ጠቅሰው፣ “ቢራ በማምረት ላይ ብቻ ሳይወሰን የአገራችንን ባህል በዓለም ደረጃ በማስተዋወቅ የአርሰናል ታዋቂ ተጫዋቾችን ሳይቀር እስክስታ ያስወረደ ቢራ ፋብሪካ ነው” በማለት ዳሽን ቢራ ፋብሪካን አሞካሽተዋል፡፡
ፋብሪካው ግብር በመክፈል አርአያ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ቤልጂየምና ቻይና ከሚገኙት የቢራ ፋብሪካዎች ቀጥሎ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ሦስተኛው ቢራ ፋብሪካ ነው ያሉት የዳሽን ደብረብርሃን ፋብሪካ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ መኮንን፤ ግንባታው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ መውሰዱን፣ የፋብሪካው አጠቃላይ ወጪ 3 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 2 ቢሊዮን ብር ለመሳሪያዎች ግዢ፣ 1 ቢሊዮን ብር ለውጭና ለአገር ውስጥ አማካሪዎች፣ ለግብአት አቅርቦትና ለሥራ ማስኬጃ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው፣ በ2 ሚሊዮን ሄክቶሊትር (1 ሄክቶሎትር 100 ሊትር ነው) ወደ ገበያ እንደሚገባና ትንሽ ማሻሻያ ተደርጎለት 3 ሚሊዮን ሄክቶሊትር እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር አሁን የጎንደር ፋብሪካ ከሚያመርተው 1.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ጋር በአጠቃላይ 4.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር ቢራ በዓመት ያመርታል ብለዋል፡፡
 አቶ ደሳለኝ፣ ፋብሪካው 40 ሺህ ኩንታል ብቅል መያዝ የሚችሉ 8 የሳይሎን፣ 4ሺህ 800 ሄክቶ ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸው 12 የጥንስስ ጋኖች፣ ቢራው ወደ ሙሌት ከመሄዱ በፊት የሚቆይበት እያንዳንዳቸው 2 ሺህ 400 ሄክቶ ሊትር የሚይዙ 5 ታንኮች እንዳሉት ጠቅሰው፣ በሰዓት 45 ሺህ ጠርሙሶች የሚሞሉ ሁለት መስመሮች፣ (90 ሺህ) በሰዓት 100 ሊትር የሚሞላ የድራፍት መሙያ ማሽን እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ በግንባታ ወቅት 1200 የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያየ የሥራ መስክ የተሳተፉ ሲሆን፣ በ245 ቋሚና በ450 ጊዜያዊ ሠራተኞች ሥራ እንደሚጀምር የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

   በአይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለውና ሰባት የአፍሪካ አገራት የሚካፈሉበት አፍሪካ ሰርከስ አርትስ ፌስቲቫል ከህዳር 17 እስከ 19 ቀን 2008 ዓ.ም በኦሮሞ ባህል ማዕከል ይካሄዳል፡፡
ፍካት ሰርከስ በሚያዘጋጀው በዚህ የሰርከት ፌስቲቫል ላይ ከግብፅ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከማዳጋስካር፣ ከሴኔጋል፣ ከደበብ አፍሪካና ከዛምቢያ የተውጣጡና ስምንት ያህል በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በፌስቲቫሉ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን ከ85 በላይ የሰርከስ ባለሙያዎች ካተታቸውን አዘጋጆቹ በጣይቱ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከሰርከስ ትርኢቱ በተጨማሪ ከህዳር 21-22 ቀን 2008 ዓ.ም አውደ ርዕይ እና የልምድ ለውውጥ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲዝ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

  በቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት ኃይለሥላሴ ዘመን ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንጋፋው ብሔራዊ ቴአትር ቤት፣ የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር ዱብ ዱብ እያለ ነው፡፡ በእርግጥ በ60 ዓመት ጉዞው ቴአትር ቤቱ ብቻውን አይደለም አንጋፋ የሆነው፡፡ በርካቶችን በጥበብ አንግሷል፡፡ ቴአትር ቤቱን በለጋ ዕድሜያቸው የተቀላቀሉ በርካታ ታዳጊዎችን፤ በጥበብ አሽቶና ሞርዶ፣ ለአንጋፋነትም  አብቅቷቸዋል፡፡  የክብር ካባ አጥልቆላቸዋል፡፡ የዝና መጎናጸፊያ ደርቦላቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ቀደምት ተቀጣሪዎች ታዲያ ለብሔራዊ ቴአትር ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ወደር የለሽ ነው፡፡ ፍቅር ብቻ ግን አይደለም፤ጥልቅ አክብሮትም ጭምር እንጂ፡፡ አስገራሚው ነገር፣ብዙዎቹ አርቲስቶች በቴአትር ቤቱ በትንሹ ለ30 ዓመታት ቢያገለግሉም  በገቢ ረገድ ጠብ ያለላቸው ነገር የለም፡፡ በ100 ብር ደሞዝ ተቀጥረው፣ከ30 ዓመት አገልግሎት በኋላ - 200 ብር ባልሞላች ገንዘብ ጡረታ የወጡ አሉ፡፡ ማንም ግን ብሔራዊ ቴአትርን ሲወቅስ አይሰማም፡፡ ምሬት የሚባል የለም፡፡ ፍቅር ብቻ፡፡ መወድስ ብቻ፡፡ አድናቆት ብቻ፡፡ አክብሮት ብቻ፡፡ ጥልቅ ስሜት ብቻ፡፡ ጥበባዊ መንፈስ ብቻ፡፡ ብሔራዊ ቴአትርና አርቲስቶቹ በአስማት ክር የተሰፉ ይመስላሉ፡፡ ተዓምር ነው፡፡ሰሞኑን ደግሞ ሁሉንም አርቲስቶች በቴአትር ቤቱ ውስጥ እንዲመሽጉ ያደረጋቸው አንድ ትልቅ ጉዳይ ተፈጥሯል፡፡ ብሔራዊ ቴአትር የተመሰረተበት የ60ኛ ዓመት ክብረ በዓል፡፡ እነሱም ታዲያ ልደቱን ሊያደምቁለት የጥበብ ልምምድ ላይ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ማህሌት ኪዳነወልድ፤የቴአትር ቤቱን  በዓል ምክንያት በማድረግ፣በብሔራዊ ቴአትር ከ30 እስከ 40 ዓመት ያገለገሉ 5 አንጋፋ አርቲስቶችን በአጭር በአጭሩ አነጋግራለች፡፡

አርቲስት አልማዝ ኃይሌ
ብሔራዊ ቴአትር መቼ ነው  የተቀጠርሽው?
የተቀጠርኩት በ1958 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጡረታ እስክወጣ ድረስ ወደ 40 ዓመታት ገደማ በብሔራዊ ቴአትር ሰርቻለሁ፡፡
ደመወዝሽ ስንት ነበር?
(ሳ….ቅ….) ስቀጠር 100 ብር ነበር፤ሲቆራረጥ 96 ብር ከ25 ሳንቲም ይደርሰኛል፡፡ ያው ጡረታ ስወጣ ግን --- 200 ብር እንኳን አልደረሰም ነበር፡፡
ብሔራዊ ቴአትርን እንዴት         ትገልጭዋለሽ?
ለኔ ትልቅ ዩኒቨርሲቲዬ ነው ዩኒቨርሲቲ እንኳን 40 ዓመት አያስተምርም፡፡ በ20 ዓመቴ ገብቼ፣ በ55 ዓመቴ ስወጣ፣ ትልቅ ልጅ ሆኜ ነው የወጣሁት፡፡ አሁንም ለበዓሉ የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ልምምድ ላይ ነኝ፡፡
እስቲ የማይረሳ ገጠመኝሽን ንገሪኝ ...
ለንጉሡለጃንሆይ፣ትርኢት እያሳየን ሳለ ውስጥ ልብሴ ወደ ታች ወርዶ፣ መድረክ ላይ ስወጣ፣ ጓደኞቼ፤“አልምዬ ውስጥ ልብስሽ … ውስጥ ልብስሽ…” ያሉኝን ፈጽሞ አልረሳውም፡፡

**********
አርቲስት ወይንሸት በላቸው
ብሔራዊ ቴአትር የገባሽው መቼ ነው?
በ1959 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጡረታ እስከወጣሁበት 1992 ድረስ ለ33 ዓመታት በቴአትር ቤቱ
አገልግያለሁ፡፡አሁንም ለ60ኛ ዓመት በዓሉ ልምምድ ላይ ነኝ፡፡
ደሞዝሽ ስንት ነበር …
ስትቀጠሪ?
ስቀጠርማ … በ100 ብር ነው … ብቻ
ጡረታዬ ላይ 500 ደርሻለሁ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ለአንቺ ምን ትርጉም አለው?
በደስታ መስራቴና የቤቱ ፍቅር ትዝታዬ ነው፡፡ እንደ ቤቴ ነው
የማየው፡፡ ሁለተኛ ቤቴ በይው፡፡ እኔ’ንጃ ምን
ልበልሽ… ፍቅሩ በጣም ይጎዳል፡፡ ደም ስር ውስጥ ስለሚገባ ከውስጥ
አይወጣም፡፡ የማይረሳሽ ገጠመኝ…
ውይ ብዙ አሉ፤ ግን አላስታውስም፡፡

****************************
አርቲስት መራዊ ስጦት
ለስንት ዓመት ነው በብሔራዊ ቴያትር ያገለገልከው?
ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ ለ43 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡
27ቱን ዓመት በኦርኬስትራ ኃላፊነት ነው የሰራሁት፡፡
መጀመርያ ስትቀጠር ደሞዝህ ስንት ነበር?
እኔ በ120 ብር ነው የተቀጠርኩት ያው ግን ---- ምን ታረጊበታለሽ በ8 ብር የጣሊያን ጫማ ገዝተሸ ታደርጊያለሽ፡፡ እኔ ጡረታ ስወጣ 700 ብር ደርሼ ነበር፡፡ አሁን በኔ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰራው የ6ሺ እና የ7ሺ ብር ደሞዝተኛ ነው፡፡ ጊዜው ተቀይሯል፤ መስዋእትነቱን የከፈልነው እኛ ነን፡፡ በእርግጥ ደሞዙ በማደጉ ከሁሉም በላይ ደስተኞቹ እኛ ነን፡፡ ዛሬ ዘፋኞች በሚሊዮኖች ብር የሚደራደሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ለአንተ ምንህ ነው ?
ብሔራዊ ቴአትር ለኔ የጥበብ መቅደሴ ነው፡፡ ከጡረታ በኋላ እንኳን ጠዋት 2፡30 ላይ ብሔራዊ ቴያትር፣ማታ ደግሞ ማርያም አታጭኝም፡፡ ብሔራዊ ቴአትር ቤትን በጣም እወደዋለሁ፡፡ በጣም አከብረዋለሁ፡፡ መጥፎ ነገር ሳይ እበሳጫለሁ፤ጥሩ ሳይ ደስ ይለኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ቲያትር ቤቱ እንደ ናይጄሪያና ሌሎች አገራት ከ4ሺህ -5ሺህ ተመልካች የሚይዝ አዳራሽ ሰርቶ ማየትን እመኛለሁ፡፡
እስቲ በሙያህ ያለህን ትውስታ ንገረኝ?
እንግዲህ ከነበርነው 13 የኦርኬስትራ አባላት የቀረነው 5 ነን፤ አሁን 80 ዓመቴን ይዣለሁ፡፡ በሙያዬ ዓለምን ዞሬያለሁ፡፡ ብዙ ትውስታዎች አሉኝ፡፡ ከሁሉም በላይ የስራ ፍቅር ነበረኝ፤ የሰራሁት ስራ ካልተወደደ እራቴን አልበላም ነበር፡፡


*******************
አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ

በብሔራዊ ቴያትር ለምን ያህል ጊዜ
አገለገልክ?
ከተመሰረተ ጀምሮ ጡረታ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ ለ40 ዓመታት ያህል አገልግያለሁ፡፡
የደሞዝ ጉዳይ እንዴት ነበር …
መጀመሪያ ስትቀጠር?
ያው ስቀጠር በ120 ብር ነበር፤ በኋላ636 ብር ደርሼ ነው ጡረታ የወጣሁት
ብሔራዊ ቴአትርን እንዴት ትገልፀዋለህ?
እድገት ላይ ያለ ቴአትር ቤት ነው፡፡ ሌላ እድገት እንጠብቃለን፤ ሌላ ብሔራዊ
ቲያትር እንደሚሰራ ሰምተናል፡፡ እደግ ተመንደግ ነው የምለው፡፡ በኪነጥበቡ
ብዙ እድገት አይተናል፤ ማንበብ የማይችሉትን ቲያትር አስጠንተናል፤
አሁን ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ሲሰጥ እያየን ነው፡፡
ተመስገን ነው እንግዲህ፡፡
ከመድረክ ገጠመኝ የማይረሳህ …
ከቴያትር ቤት ተወስጄ እስር ቤት
ገብቻለሁ፡፡ መድረክ ላይ ነስሮኝ፣ ነስሩ
አልቆምም ብሎ ፕሮግራም ተቋርጧል፡፡
ኧረ ብዙ ነው… ብዙ ብ….ዙ!!


*****************************

አርቲስት ሰለሞን ተካ


መቼ ነው ብሔራዊ የተቀጠርከው ?
በ1970 ነው፤ አሁንም ድረስ እየሰራሁ ነው፡፡
በስንት ብር ደሞዝ ሥራ ጀመርክ?
(ሳ…ቅ…) እንዴ --- ያኔ 100 ብር የኪስ ገንዘብ ብቻ ነበር የሚሰጠን፡፡ አሁን 2900 ብር ደርሻለሁ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ለአንተ ምንህ ነው?
ውይ… እኔ እንጃ፤ በቃ መንፈስ ነው ስሜት እንዴት ይገለፃል? መንፈስን ምን ብለሽ
ትገልጪዋለሽ? ለኔ ከቃል በላይ ነው፡፡
ውስጥን የማያርስ ደስታን ምን ልበልሽ?
በአፍሪካ የመጀመሪያው ቴአትር ቤት ነው፡፡ ህልሜ፤ብሔራዊ ቲአትር፣በዓለም ላይ አሉ ከተባሉ ቲያትር ቤቶች ጎን ተሰልፎ
ማየት ነው፡፡ የማይረሳህ የመድረክ ገጠመኝህ?
ሥራ እንደጀመርኩ አካባቢ፣ ያው ወጣትነትም አለ… እጩ ተዋንያን ተብዬ ተመረጥኩ፡፡ እኔ ቲያትርን ስፈልግ
ስፈልግ የምሰራው ነበር የመሰለኝ፤ በኋላም “ፍልሚያ” የሚባል ቲያትር ላይ አሽከር ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ እኔ ሆዬ
ቤቴ ተኝቼ መጣሁና፣ ትርኢቱን ቁጭ ብዬ ማየት ጀመርኩ፡፡ በኋላ አዘጋጁ አቶተክሌ፤ “ምን ትሰራለህ እዚህ?” ሲለኝ
“መስራት ነበረብኝ እንዴ?” ብዬው፤ ደሞዝ የተቀጣሁትን አልረሳውም፡፡

የሰላም ተምሳሌቷ አን ሳን ሱ ኪ፣ ህጉ ባይፈቅድላትም አገሯን ለመምራት ቆርጣለች

   ከአስር አመታት በላይ ወታደሩ በገነነበት አገዛዝ ስር የቆየችው ማያንማር ባለፈው እሁድ ታሪካዊና የአገሪቱን መጻይ ዕጣ ፋንታ ይወስናል የተባለለትን የፓርላማ ምርጫ አካሂዳለች፡፡ ወታደሩ አገሪቱ ወደተሟላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትገባ ያለው ፈቃደኝነትን ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዚህ ወሳኝ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ባለፈው ረቡዕ ይፋ ተደርጓል፡፡
በምርጫ ውጤቱ መሠረትም፣ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋና የሰላማዊ ትግል ተምሳሌት የሆነችው አን ሳን ሱኪ ያሸነፈች ሲሆን የምትመራው ፓርቲ “ናሽናል ሊግ ኦፍ ዲሞክራሲም”፣ በስልጣን ላይ ያለውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት “ቴን ሴን ፓርቲ ዩኒየን ሶሊዳሪቲ ዲቨሎፕመንት” ፓርቲን በሰፊ ልዩነት እየመራ እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡
ምርጫ ከተደረገባቸውና ጊዜያዊ ውጤቱ ከታወቀባቸው 40 በመቶ ያህል የፓርላማ መቀመጫዎች፣ ናሽናል ሊግ ኦፍ ዲሞክራሲ 90 በመቶ ያህሉን ማሸነፉን የዘገበው ቢቢሲ፣ እስካሁን ድረስም ምርጫ ከተካሄደባቸው 491 ያህል የሁለቱ ምክር ቤቶች መቀመጫዎች 163 ያህሉን ሲያሸንፍ፣ ገዢው ፓርቲ በበኩሉ፤ 10 ያህሉን ብቻ ማሸነፉ መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
ከአገሪቱ ፓርላማ 664 መቀመጫዎች መካከል ሩብ ያህሉ ለጦር ሃይሉ የተተወ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የአን ሳን ሱ ኪው ፓርቲ “ናሽናል ሊግ ኦፍ ዲሞክራሲ” አብላጫውን ድምጽ ይዞ አዲሱን የአገሪቱ ፕሬዚደንት መምረጥ የሚችለው ከቀሪዎቹ ወንበሮች ቢያንስ ሁለት ሶስተኛውን ወይም 329 ወንበሮችን መያዝ ሲችል ነው ብሏል፡፡
አን ሳን ሱኪ የምርጫው ውጤት ዘገየ እየተባለ መነገሩን ተከትሎ ባለፈው ማክሰኞ በስልጣን ላይ ላለው የአገሪቱ መንግስት በላኩት ደብዳቤ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል እስከ መጪው ሳምንት ድረስ ውይይት እንዲደረግና ብሄራዊ እርቅ እንዲፈጠር የጠየቁ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ዛው ታይ፣ ፓርቲውን ላገኘው ውጤት “እንኳን ደስ አለህ” ብለው፣ መንግስት ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑንና ይህን መሰሉ ውይይት ሊደረግ የሚችለው ግን፣ የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ከተገለጸ በኋላ እንደሆነ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በስልጣን ላይ ያለው የአገሪቱ መንግስትና አን ሳን ሱ ኪን ለአመታት በቁም እስር እንድትማቅቅ የፈረዱባት የመንግስቱ ታማኝ የጦር አበጋዞች ያወጡት ህገ መንግስት፣ አን ሳን ሱ ኪን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከመሆን እንደሚያግዳት የዘገበው ዘ ቴሌግራፍ በበኩሉ፣ እሷ ግን አሻንጉሊት ፕሬዚዳንት በመሾም ከበስተጀርባ ሆና አገሪቱን ለመምራት ማሰቧን አስታውቃለች፡፡
ይሄም የአገሪቱ የጦር አዛዦችን ክፉኛ አስቆጥቷል ተብሏል፡፡ የአገሪቱ ህገ መንግስት፤ ለፕሬዚዳንትነት የሚመረጠው ሰው የትዳር አጋሩ ወይም ልጆቹ የውጭ አገራት ዜግነት ያላቸው ከሆነ፣ ስልጣን መያዝ አይችልም የሚል ገደብ ማስቀመጡን ያስታወሰው ዘገባው፣ አን ሳን ሱኪ የቀድሞ ባለቤቷና ልጆቿ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ ፓርቲዋ ቢያሸንፍም እሷ ፕሬዚዳንት መሆን እንደማትችል ጠቁሟል፡፡
ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው ደግሞ፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል ሃላፊ ሚን ኡንግ ህሌንግ፤ የጦር ሃይሉ የምርጫው የመጨረሻ ውጤት መገለጹን ተከትሎ ከሚመሰረተው አዲሱ የአገሪቱ መንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለ15 አመታት ያህል በቁም እስር ላይ የቆየችውና በ2012 የፓርላማ ምርጫን ያሸነፈችው አን ሳን ሱ ኪ፣ ሰላማዊ ትግልን መርህ በማድረግ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበርና ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ ባደረገችው ተምሳሌታዊ ተግባር የ1991 የአለም የኖቤል የሰላም ሽልማትን መቀበሏ ይታወሳል፡፡

    የአሜሪካ መንግስት በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን የሽብር ቡድን የአልሻባብን ስድስት መሪዎች የሚገኙበትን ስፍራ ለጠቆመው ሰው ወይም ተቋም፣ 27 ሚሊዮን ዶላር በዎሮታ መልክ እንደሚሰጥ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
አሜሪካ ባለፈው አመት በሰነዘረችበት የድሮን ጥቃት የገደለችውን አህመድ አብዲ ጎዳኔን በመተካት፣ ቡድኑን በዋና መሪነት በማንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውን አቡ ኡባይዳህን በተመለከተ መረጃ ለሰጣት፣ ከፍተኛውን የ6 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እሰጣለሁ ማለቷን ዘገባው ገልጿል፡፡
በኬንያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተከሰተውና 148 ሰዎች በሞቱበት የቡድኑ የሽብር ጥቃት ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለትን ማሃድ ካራቴ ወይም አብድራህማን ሞሃመድ ዋርሳሜ የተባለ የቡድኑ አመራር፣ የቡድኑ የምልመላና የስልጠና ሃላፊ የሆነውን ማሊም ዳኡድ፣ የፋይናንስ ጉዳዮች ሃላፊውን ሃሰን አፍጎዬን፣ በአፍሪካ ቱሪስቶች ላይ በተሰነዘሩ የቡድኑ ጥቃቶች ላይ የተሳተፈውን ማሊም ሳልማንን እንዲሁም በኬንያ አዳዲስ የቡድኑ አባላትን በመመልመል ተሳትፏል ያለችውን አህመድ ኢማን አሊን በተመለከተ መረጃ ለሚሰጣት በድምሩ 27 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ብላለች አሜሪካ፡፡

Saturday, 14 November 2015 09:44

ስኳርና ቁጥር

* በዓለማችን በስኳር ህመም
የተያዙ ሰዎች - 387 ሚሊዮን
* በበሽታው በየዓመቱ
የሚሞቱ ሰዎች - 5 ሚሊዮን
* ከህመሙ ጋር በተያያዘ
የሚወጣ ወጪ - 550 ቢሊዮን
ዶላር
* ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤን
በመከታተል የስኳር ህመምን
መከላከል ይቻላል - 70 በመቶ
* በ2035 እ.ኤ.አ በዓለማችን
ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው
የስኳር ህመምተኛ - 600
ሚሊዮን
* እ.ኤ.አ በ1985 በዓለማችን
የነበረው የስኳር ህመምተኞች -
30 ሚሊዮን
* በዓለማችን በአንደኛው
ዓይነት የስኳር ህመም ብቻ
በየዓመቱ የሚያዙ ህፃናት
ቁጥር - 70ሺ

Saturday, 14 November 2015 09:42

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ታሪክ)
- የምፈጥረው እያንዳንዱ ታሪክ እኔን
ይፈጥረኛል፡፡ የምፅፈው ራሴን
ለመፍጠር ነው፡፡
ኦክታቪያ ኢ.በትለር
- እውነተኛ ታሪክ የምፅፍ ከሆነ ከራሴ
ስም ነው የምጀምረው፡፡
ኬንድሪክ ላማር
- አርቲስት አይደለሁም፡፡ ካሜራዬን
እከፍትና ታሪኬን እተርካለሁ፡፡
ታይለር ፔሪ
- ህይወቴ ድንቅ ታሪክ ነው - ደስተኛና
በድርጊቶች የተሞላ፡፡
ሀንስ ክሪስቺያን አንደርሰን
- አባቴ ታሪክ መተረክ ያውቅበታል፡፡
የተለያዩ ድምፆች በማውጣት እንድስቅ
ያደርገኝ ነበር፡፡
ሊሊ ኮሊንስ
- ትልቁ ነገር ድምፅህ እንዲሰማ፣ ታሪክህ
እንዲደመጥ ማድረግ ነው፡፡
ድዋይኔ ዋዴ
- ስሜትን ሰቅዘው የሚይዙና አይረሴ
የሆኑ ገፀባህሪያትን ለመፍጠር ተግተህ
ትሰራለህ፡፡ ሆኖም የማታ ማታ ዋናው
ነገር ታሪኩ ነው፡፡
ጄምስ ዳሽነር
- በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ሴት ገፀ ባህርይ
ስትኖር፣ ሁልጊዜ ያ ቀልቤን ይይዘዋል፡፡
ኦንግ ሊ
- አይገመቴ ሁን፡፡ እውነተኛና ቀልብ
ሳቢያ ሁን፡፡ ግሩም ታሪክ ተርክ፡፡
ጄምስ ዳሽነር
- ምንጊዜም ታሪክ ስፅፍ፣ ለወንዶችም
ለሴቶችም ማራኪ እንደሚሆን
አምናለሁ፡፡
ሱዛኔ ኮሊንስ
- ታሪክ መጀመሪያ፣ መካከልና መጨረሻ
ሊኖረው ይገባል፤ ነገር ግን የግድ በዚያ
ቅደም ተከተል መሆን የለበትም፡፡
ዣን ሉክ ጎዳርድ
- ሁሉም ገፀባህርያት ከማውቃቸው ሰዎች
የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው
ንሸጣ በኋላ ግን ለታሪኩ እንዲስማሙ
አርቃቸዋለሁ፡፡
ኒኮላስ ስፓርክስ
- ይሄንን ታሪክ ከዚህ ቀደም ሰምታችሁት
ከሆነ እንዳታቆሙኝ፤ ምክንያቱም
እንደገና ልሰማው እፈልጋለሁ፡፡
ግሮቾ ማርክስ
- ሴቶች፤ ስሜት ውስጥ ጠልቆ የሚገባ
የፍቅር ታሪክ የሚወዱ ይመስለኛል፡፡
ኢ.ኤል ጄምስ