Administrator

Administrator

የአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት የከተማዋ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የጣለውን ዕግድ ለማስነሳት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት አስታውቋል። ቀደም ሲል ምክር ቤቱ ዕግዱን ለማስነሳት በተለያዩ መንገዶች ያደረጋቸው ጥረቶች እንዳልተሳኩ ገልጿል።
ባለፈው ረቡዕ ታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ም/ቤቱ ባወጣው መግለጫ፣ “የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን በመፍታት ረገድ ደብዳቤ ከመጻፍ ያለፈ ውጤታማ ሚና አልተጫወተም” ብሏል። አክሎም፣ በሂጃብ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የመቀመጥ ዕድል እንደተነፈጋቸው አስታውቋል።ምክር ቤቱ በማብራርያው፣ የአክሱም ከተማ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለብሰው እንዳይማሩ የተደረገው ክልከላ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ የሰው ልጆችን መብት የሚጋፋ መሆኑን አንስቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችግሩን ለመፍታት ብዙ አማራጮች መሞከራቸውም ተጠቅሷል።
“ክልከላው እንዲነሳ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ያልተሳካ ሽምግልና እና መተግበር የማይችል ደብዳቤ ከመፃፍ የዘለለ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የለም” ሲል ምክር ቤቱ ስሞታውን አትቷል። በአክሱም ከተማ የሚገኘው ትምሕርት ቤት አንዳንድ አመራሮች ከራሳቸው የሃይማኖት ፍላጎትና የትምህርት መብት አተያይ በመነሳት ተማሪዎች ወደ ትምሕርት ገበታቸው እንዳይመለሱ ማድረጋቸውን ምክር ቤቱ ጠቁሟል።በሂጃብ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የመቀመጥ ዕድል እንደተነፈጋቸው የከሰሰው ከፍተኛው ምክር ቤት፤ ዕገዳው የሙስሊም ተማሪዎችን መብት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት የጣስ ድርጊት ነው በማለትም ምክር ቤቱ ዕገዳውን አውግዞታል። ምክር ቤቱ ጉዳዩን ሁሉም ትግራዋይ እንዲያወግዘው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ “ከቀናት በፊት በአቋም መግለጫችን እንደጠቀስነው ‘ክልከላው በአፋጣኝ ዕልባት ካልተሰጠው፣ በሕግ እንጠይቃለን’ ባልነው መሰረት ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስደነዋል” ብሏል።
የትምህርት ቢሮው ችግሩን በጥቂት ቀናት ውስጥ ካልፈታ፣ ቀጣይ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።በተያያዘ ዜና፣ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት፣ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ትምሕርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት፣ ትዕዛዝ የሰጡና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ድርጅቱ ባለፈው ዓርብ ታሕሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአዲስ አድማስ በላከው አጭር ሪፖርት፣ በተማሪዎቹ ላይ የተጣለውን ዕግድ ተከትሎ፣ የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ለአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምሕርት ጽሕፈት ቤት  የጻፈው ደብዳቤ ለችግሩ ግልጽ መፍትሔ የሚሰጥ አለመሆኑን ጠቅሶ፣ “ችግሩ እስከ አሁን እንዲቀጥል አስተዋጽዖ አድርጓል” በማለት ነቅፏል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 25 ላይ የተደነገገውን የዕኩልነት መብት፣ የሃይማኖት፣ የዕምነትና የአመለካከት ነጻነት መብት አንቀጽ 27ን ጨምሮ፣ ልዩ ልዩ መመሪያዎች መጣሳቸውን አትቷል። ድርጅቱ፣ የትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ትምሕርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት፣ ትዕዛዝ የሰጡና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ወደ ትምሕርት ገበታ በአፋጣኝ እንዲመለሱ በማድረግ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፎርም እንዲሞሉ እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን በገና ዋዜማና በበዓሉ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ የዞኑ ነዋሪዎችና አንድ የመንግሥት ሃላፊ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ። ጥቃቱን የፈጸሙት አዋሳኝ ከሆነው የምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጎርካ ወረዳ፣ ከሬዳ እና ጀሎ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፣ ታሕሳስ 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት ሁለት በግብርና ስራ ሲተዳደሩ የነበሩ ዜጎች ተገድለዋል። ነዋሪዎቹ አያይዘውም፣ አርሶአደሮቹ የተገደሉት በጥይት ተደብድበውና አካላቸው ተቆራርጦ መሆኑንም አብራርተዋል።ሟቾቹ አርሶአደሮች አንታዮ ዦላና አድማሱ አሰፋ የተባሉ ሲሆን፣ ታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የቀብር ስነ ስርዓታቸው መፈፀሙን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። አክለውም፣ “አቶ አንታዮ ዦላ የተገደሉት ታሕሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 11:30 ኬረዳ ቀበሌ ውስጥ ነው። ገዳዮቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ከምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ጋላና ወረዳ፣ የተለያዩ የጦርና ስለታማ መሳሪያዎች ታጥቀው ወደ ኮሬ ዞን ዘልቀው ገብተው ነው። የቡልቶ ጃልደሳ ታጣቂዎች ናቸው።” ብለዋል።“በዚሁ ቀበሌ ጥቃት ከመፈጸም ባሻገር፣ የቤት እንስሳትን ዘርፈዋል” ያሉት ነዋሪዎቹ፣ “አድማሱ አሰፋ ደግሞ ታሕሳስ  29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 6:30 ገደማ ጄሎ ቀበሌ ውስጥ ተገድሏል ” ሲሉ ገልጸዋል። ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ከምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች ጥቃት እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
የዞኑ የሕዝብ ተወካይ የሆኑት አቶ ዘናነም አዱላ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፣ ከ2009 ዓ.ም. አንስቶ ጥቃት መፈጸሙን አጽንዖት ሰጥተው፣ ከ300 በላይ ዜጎች ሕይወታች እንደተቀጠፈ ተናግረዋል። ከባድ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ በታጣቂዎቹ ሲፈጸም መቆየቱን ገልፀዋል።“መንግስት የሕዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ቸልተኝነት አሳይቷል። ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም” የሚሉት የሕዝብ ተወካዩ፣ “ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ክፍተት አለ” በማለት ያስረዳሉ። በምዕራብ ጉጂ በኩል አልፎ ወደ ዲላ እና ሃዋሳ ለመጓዝ የሚያስችለው መንገድ መዘጋቱን ጠቁመው፣ ይህም በዞኑ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ከመፍጠሩ ሌላ፣ ከመስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጥቃቱ እንዳገረሸ ጠቅሰዋል።አቶ ዘናነም ግጭቱን ለዝርፊያና የኮንትሮባንድ ንግድ የሚጠቀምበት ሃይል እንዳለ የተናገሩ ሲሆን፣ ስለዚሁ ሃይል በግልጽ ከማብራራት ተቆጥበዋል። ታጣቂዎቹ ከብቶችና ሌሎች የቤት እንስሳት እንደሚዘርፉም ተናግረዋል።
የኮሬ ዞን ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ትግሉ ዘብዶስ የጥቃቱን መደጋገም አንስተው፣ “ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋር የጸጥታ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
 ይሁንና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለመግለጽ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

Friday, 10 January 2025 21:24

25ኛው የብር ኢዮቤልዩ

ወይዘሮ ፈለቀች ለማ እባላለሁ፡፡ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የአስራ አንድ ልጆች እናት ነኝ፡፡ በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ ትምህርት የጀመርኩት በቄስ ትምህርት ቤት ነው፤ ከዚያም በመንግሥት ትምህርት ቤት ገብቼ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማርኩ በኋላ በሀገሩ ባህልና ወግ መሠረት በጣም በልጅነቴ ተዳርኩ፡፡ ሆኖም ያኔ ሲንጀር ካምፓኒ የሚሰጠውን የዲዛይን ትምህርት ጨርሼ ከተመረቅሁ በኋላ፣ በጅማ የሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን፣ ሴቶች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የልብስ ስፌትና ጥልፍ ስልጠና በመስጠት እናስመርቅ ነበር።

አዲስ አድማስ ከመጀመሩ በፊት ባለቤቴ ሁሌም ጋዜጣና መፅሔት እንዲሁም መጻሕፍት እየገዛ ያመጣ ስለነበር፣ ንባብ የቤታችን ባህል ሆኗል፡፡ በኋላም አዲስ አድማስ ቅዳሜ መውጣት ሲጀምር ልጆቹም በዚያው ቀጠሉበት፡፡ እኔም ጋዜጣውን ማምጣት እንዳይረሱ ሁሌም አስታውሳቸዋለሁ፤ በጣም የሚወደድ ጋዜጣ ስለሆነ ምንጊዜም እንዲያልፈኝ አልፈልግም፡፡

አዲስ አድማስን ለብዙ ዓመታት አንብቤአለሁ፤ ወደፊትም አነባለሁ፡፡ ጋዜጣውን እንዳገኘሁ መጀመሪያ የማነበው የነቢይ መኮንንን (ነፍሱን ይማረውና) ርዕስ አንቀጽ ነው፤ ሁለተኛ የማነበው ደግሞ የዮሐንስ ሰ.ን ጽሁፍ ነው፡፡ እኔ ከልጆቹ ቀድሜ ካነበብኩ ጥሩ የምላቸውን ጽሁፎች እንዲያነቡ እጠቁማቸዋለሁ፡፡ ሁሉም አምዶች ሳምንቱን ሙሉ የሚነበቡ ናቸው፡፡ በእኔ በኩል፣ አዲስ አድማስን በድረ ገፅ አላነብም፤ለዕድሜዬ አይሆንም፤ በዚያ ላይ ጋዜጣው ሁሌም በእጄ ነው።

በአዲስ አድማስ ላይ በርካታ አስገራሚና አስደማሚ ታሪኮችን አንብቤአለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ሁሌም የማይረሳኝ፣ ኮፊ አናን ኢትዮጵያ በነበሩ ጊዜ የቤት ውስጥ ረዳታቸው የነበሩትን ሴት ተመልሰው ሲመጡ ሊያገኟቸው ፈልገው፣ ሴትየዋ በቀጠሮው ሰዓት ባለመድረሳቸው ሳይገናኙ መቅረታቸውን የሚያትተው ታሪክ ነው፡፡ የቀጠሮ ሰዓት የማያከብር ሰው ስለሚገርመኝ ይሆናል፣ ይሄ ታሪክ ሁሌም ትዝ የሚለኝ፡፡

በእርግጥ የማነበው ጋዜጣ ብቻ አይደለም፤ መፅሔቶች የታሪክና የሀይማኖት መጻሕፍትንም አነባለሁ፡፡ ዜናም አያመልጠኝም፡፡ ማንበብ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዕውቀትን ያስታጥቃል፡፡ መረጃን ከሰው አፍ ከመስማት አንብቦ መረዳት የተሻለ ነው፡፡

የአዲስ አድማስ ፀሐፊዎችና አዘጋጆች፣ ከአንባቢዎቻቸው ቀድመው መገኘት አለባቸው፤ በሁሉም ረገድ ሊበረቱ ይገባል፡፡ ጋዜጣው አምዶቹን መጨመር እንጂ መቀነስ የለበትም፤ የተቀነሱ አምዶች ስላሉ የጎደሉትን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻ እንኳንም ለአዲስ አድማስ 25ኛ ዓመት አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ መልካም የሥራ ዘመን ይሁንላችሁ።

• በስሙ አደባባይ ለመሰየምና ሐውልት ለማቆም ከከተማ
አስተዳደሩ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ተብሏል

ከ60 ዓመታት በላይ በተወዳጅነት ያቀነቀነው “የትዝታው ንጉስ” ማህሙድ አህመድ፣ በነገው ዕለት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በአድናቂዎቹ በክብር ከመድረክ ይሸኛል።

ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ የመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ጆርካ ኢቨንትስ ኦርጋናይዘር እና ዳኒ ዴቪስ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ የስንብት ኮንሰርቱ ለጋሽ ማህሙድ በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ ነው። በኮንሰርቱም ላይ ተወዳጆቹ ድምጻዊያን ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ አደም መሐመድ፣ ወንዶሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) እና ዜና ሃይለማሪያም ታላቁን አርቲስት አጅበው ያቀነቅናሉ ተብሏል።

አርቲስቶቹ ከጋሽ ማህሙድ በተረፈው ሰዓት ታዳሚን ለማስደሰትና፣ አንጋፋውን ሙዚቀኛ በክብር ለመሸኘት በከፍተኛ ደረጃ እየተዘጋጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጋሽ ማህሙድም “አሳድጎ ለዚህ ክብር ያበቃኝን አድናቂ፣ በተቻለኝና አቅሜ በፈቀደው መጠን በመጫወት አስደስቼ ለመሰናበት ተዘጋጅቻለሁ” ያለ ሲሆን፤ “ሁላችሁም መጥታችሁ ብትሸኙኝ ደስታውን አልችለውም” ሲል ሁሉም እንዲታደም ጥሪ አቅርቧል።


ጋሽ ማህሙድን አጅበው የሚያቀነቅኑት ለምን ወንዶች ብቻ ሆኑ፣ ሴት አቀንቃኞች ለምን አልተካተቱም? በሚል ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ለቀረበው ጥያቄ፣ ከስንብት ኮንሰርቱ አዘጋጆች አንዱ የሆነው ዳኒ ዴቪስ በሰጠው ምላሽ፤ " አስቴር አወቀ እንድትሳተፍ ፈልገን ጋብዘናት ነበር፤ ወደ ውጪ በመውጣቷ ልትገኝ አልቻለችም፤ እኛም የፈለግነው እሷን ነበር፤ አልሆነም" ብሏል።

የአንጋፋውን ሙዚቀኛ የጋሽ ማህሙድ አህመድን የህይወት ታሪክ የሚተርክ መፅሐፍ በትላንትናው ዕለት የተመረቀ ሲሆን፤ በስሙ አደባባይ ለመሰየምና ሐውልት ለማቆም ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል።

“መጻሕፍት ሻጮች ህይወትን ይታደጋሉ”


ጄምስ ፓተርሰን በዓለም ዝናው የናኘ እጅግ ታዋቂና ትጉህ አሜሪካዊ ደራሲ ነው። የ77 ዓመቱ ፓተርሰን እ.ኤ.አ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ 200 ገደማ ረዥም ልብ ወለዶችን ጽፎ ለህትመት ያበቃ ሲሆን፤ መፃህፍቱ በዓለም ዙሪያ ከ425 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሸጠውለታል። 1 ሚሊዮን ያህል ኤሌክትሮኒክስ መፃሕፍት (e-books) በመሸጥም የመጀመሪያው ደራሲ ነበር፡፡
ፓተርሰን እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም በፎርብስ የከፍተኛ ተከፋይ ደራሲያን ሰንጠረዥን በመቆጣጠር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዘልቋል- በ95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ። አጠቃላይ ገቢው ደግሞ ከአሰርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ 700 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር፡፡
ሚሊየነሩ አሜሪካዊ ደራሲ ከተወዳጅ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ ባሻገር የመጻሕፍት ሻጮች አለኝታም ነው፡፡ የመፅሐፍ ኢንዱስትሪውን የጀርባ አጥንት በመደገፍ ይታወቃል - የግል የመፃሕፍት መደብሮችን።
በዚህ የፈረንጆች በዓል ሰሞን በመላው አሜሪካ በሚገኙ 600 የግል መፃህፍት መደብሮች ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች በአጠቃላይ የ300ሺ ዶላር የበዓል ቦነስ አበርክቷል - በነፍስ ወከፍ 500 ዶላር!
“መፃህፍት ሻጮች ህይወትን ይታደጋሉ- አራት ነጥብ!” በማለት ለABC ኒውስ የተናገረው ደራሲው፤ “በዚህ የበዓል ወቅት ለእነሱም ሆነ ለትጋታቸው ዕውቅና መስጠት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።” ብሏል።
ለዓመት በዓል የገንዘብ ስጦታው የታጩት የ600 መፃሕፍት መደብር ሠራተኞች አንድም ራሳቸው ያመለከቱ አሊያም በመደብር ባለቤቶች፣ በደራሲያን ወይም በደንበኞች የተጠቆሙ ናቸው ተብሏል- በትጋትና ታታሪነታቸው።
“የሚስተር ፓተርሰንን የገንዘብ ልግስናና የልብ ቸርነት እናደንቃለን። ሁላችንም ሚስተር ፓተርሰን ለግል መፃሕፍት ሻጮች ለሚያደርጉት የማያቋርጥ ድጋፍ ምስጋናችን ወደርየለሽ ነው፡፡” ብለዋል፤ የአሜሪካ መፃህፍት ሻጮች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊሰን ሂል በመግለጫቸው፡፡
“መፃሕፍት ሻጮች በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚጫወቱትን ወደር-የለሽ ሚና መገንዘባቸውና መሸለማቸው ከምንም ነገር የላቀ ነው” ሲሉም አክለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈፃሚው።
ደራሲው ለመፃሕፍት ሻጮች የ500 ዶላር የበዓል ቦነስ ሲያበረክት ያሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ላለፉት አስርት ዓመታት ሲያደርገው የቆየው የልግስና ተግባር ነው፡፡ ሥነ-ፅሁፍን በማሳደግና ንቁ ማህበረሰቦችን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ በማመን፣ የግል የመፃሕፍት መደብሮችንም ያለማቋረጥ በመደገፍ ይታወቃል፤ በአገረ አሜሪካ፡፡
በመጋቢት ወር ላይ ፓተርሰን ለመፃሕፍት ሻጮች የሚከፋፈል 600ሺ ዶላር እንደሚያበረክት የአሜሪካ መፃሕፍት ሻጮች ማህበር አስታውቆ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ2020 ደግሞ በመላው አሜሪካ ለሚገኙ የግል መፃሕፍት መደብሮች 500ሺ ዶላር ለግሷል- ሥራቸውን እንዲያሳድጉና እንዲነቃቁ።
“ዋይት ሐውስ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪንና ትላልቅ ቢዝነሶችን ከውድቀት መታደግ ያሳስበዋል - ያንን እረዳለሁ። እኔ ግን በመላ አገሪቱ ዋና ጎዳናዎች እምብርት ላይ የሚገኙ የግል የመፃሕፍት መደብሮች ህልውና ያሳስበኛል።” ብሏል ፓተርሰን በሰጠው መግለጫ።
“የምናሰባስበው ገንዘብ የመፃሕፍት መደብሮችን በጣም በምንፈልግበት በዚህ ወቅት ህያው እንደሚያደርጋቸው ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲልም አክሏል፤ ደራሲው።
ጄምስ ፓተርሰን እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም ለአሜሪካ የግል የመፃሕፍት መደብሮች 1 ሚሊዮን ዶላር ለግሶ ነበር- ለእያንዳንዳቸው 15ሺ ዶላር የሚከፋፈል። ባለፉት ዓመታት ደራሲው ለመፃሕፍት መደብሮችና መጻሕፍት ሻጮች ብቻ ሳይሆን ለቤተመጻህፍት ባለሙያዎችና ለመምህራንም የበዓል ቦነስ ሲያበረክት ቆይቷል።
የመፃሕፍት መደብሮችንና መፃሕፍት ሻጮችን በገንዘብ ከመደገፍና ከማገዝም በተጨማሪ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መፃሕፍትን ለት/ቤቶች ቤተ-መፃሕፍት ለግሷል። የህፃናት መፃሕፍትንም በመፃፍ የሚታወቀው ደራሲው፤ ህፃናት የንባብ ባህል እንዲያዳብሩም በትጋት ይሰራል። “ህፃናት በለጋ ዕድሜያቸው የማንበብ ልማድ ካላዳበሩ ለውጭው ዓለም ባዕድ ከመሆናቸውም ባሻገር በራስ መተማመን ይጎድላቸዋል፤ ስለዚህ የግድ ማንበብ አለባቸው፤ ይህን ማድረግ ደግሞ የኛ የወላጆች ሃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡” ይላል- ፓተርሰን።
ጄምስ ፓተርሰን የበኩር ስራውን ለንባብ ያበቃው እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም ሲሆን፤ ርዕሱም “The Thomas Berryman Number” ይሰኛል። ከሌሎች በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ መካከልም፡- Alex Cross, Michael Bennet, Women’s Murder Club እና Maximum Ride የተሰኙት ልብወለዶች ይጠቀሳሉ። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ልብወለዶቹም ወደ ፊልም ተቀይረውለታል፡፡

 

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ፤
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፤
በምሉእ ፍቅሩ ሰውን ከባርነት ወደ ነጻነት ለመመለስ በሥጋ ሰብእ የተወለደው ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓመተ ምሕረት የልደት በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለዘሠምሮ ለሰብእ፤ ክብር በሰማያት ለእግዚአብሔር ይሁን›› በምድርም እጅግ ለወደደው የሰው ልጅ ሰላም ይሁን” (ሉቃ ፪÷፲፬)
ይህ ቃለ ሰላም በጌታችን ዕለተ ልደት የተነገረ ነው፣ ቃሉ የተነገረው እንዲሁ እንደ ተራ ነገር ሳይሆን በቃለ መዝሙር እየተደጋገመ ነው፡፡ የተዘመረውም በምድራውያን ደራሲዎች ሳይሆን በሰማያውያን መላእክተ እግዚአብሔር ነው፣ የያዘው መልእክትም ሰማያውያንና ምድራውያንን ሁሉ ያካለለ ነው፡፡ የመልእክቱ ገዢ ሓሳብም አምላክ ከሰውነታችን ጋር ባለመለያየት፣ ባለመጠፋፋት፣ ባለመቀላቀል፣ ባለመዋዋጥ፣ ባለመለዋወጥና ያለባዕድና አንድ አካል፣ አንድ ክዋኔ፣ አንድ ጠባይ ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾኣልና እግዚአብሔር ይክብር ይመስገን፡፡ የተዋሕዶውም ምስጢር ሰላምን ያሰፍናልና እግዚአብሔር ሰውን በእጅጉ መውደዱ ከዚህ ተዋሕዶ ዓውቀናል የሚል ነው፡፡
በእርግጥም እግዚአብሔር ሰውን ለመውደዱ ከዚህ የበለጠ ማሳያ ወይም ማስረጃ የለም፤ እንከን የለሽ ንጹህ አምላክ የእኛን ኃጢአተኛ ሰውነት አካሉ አድርጎ ተወለደ ሲባል ላስተዋለው ሰው ምንኛ ቢወደን ነው የሚለው ጥልቅ አድናቆትን ያጭራልና ነው፡፡ይህ ብቻም አይደለም በዚህ ነገረ ተዋሕዶ ምክንያት ሰውነታችን አምላክ ሆኖ በመንበረ ጸባኦት እንዲቀመጥ መብቃቱ የድኅነታችንና የክብራችን ከፍታ ምን ያህል አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደደረሰ መንፈሳችን በአንክሮ ይረዳዋል፡፡ድምር ውጤቱም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ፍጹምና አስተማማኝ ሰላም መፈጠሩን ያስረዳናል፤ ሰማያውያኑ መላእክተ እግዚአብሔር በመዝሙራቸው ያበሰሩን ይህንን የምስራች ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ እግዚአብሔር በእጅጉ ይወደናል ስንል እንዲሁ ከሜዳ ተነሥተን ኣይደለም፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ሳይጸየፈን ሰውነታችንን በረድኤት ወይም በኅድረት ያይደለ በኩነት ተዋሕዶ ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ ስላደረገው ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ፍጹምና ምሉእ ፍቅሩ ሰውነታችንን በመበረ ጸባኦት ኣስቀምጦ መላእክት ሳይቀሩ ፍጥረታትን በሙሉ እንድንገዛ አድርጎናል፤ ምክንያቱም መላእክት በዕለተ ልደት የዘመሩለት በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለሆነ ለቤተ ልሔሙ ሕፃን እንጂ ለመለኮት ብቻ ኣይደለምና ነው፡፡ የዕለተ ልደት መዝሙር ዛሬም በሰማያትም ሆነ በምድር በተዋሕዶ ሰውም ኣምላክም የሆነ አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመለክበታል፣ ይመሰገንበታል፡፡የሰማዩና የምድሩ ዕርቅ ወደ ኋላ ላይመለስ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ተከናውኖኣል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰውም አዋጭ ምርጫ ይህ ዕርቅ ተጠብቆ እንዲኖር ነው፣ ያለ ዕርቅ ሰላም ሕይወት የለውምና፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የእግዚአብሔር ክብርና ሰላም በእጅጉ የተሳሰሩና የተቆራኙ ናቸው፤ እኛ እግዚአብሔርን ካከበርነው፣ ካዳመጥነው፣ ከታዘዝነውና ከተከተልነው ሰላም አለ ማለት ነው፡፡ ለሱ ካልታዘዝንና እሱን ካላከበርን ግን ዘላቂ ሰላምን ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ ምክንያቱም ሰላምን ጨምሮ መልካም ነገር ሁሉ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነውና፡፡ ዛሬ በሁሉም የዓለማችን ማዕዘን የሚታየው የሰላም መደፍረስ እግዚአብሔርን ካለማክበራችንና ለሱ ካለመታዘዛችን የተነሣ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ዓለም ከእግዚአብሔር ቃል ርቃ ለመሄድ በእጅጉ እየኳተነች ነው፤ በዚህ እኩይ ተግባርዋ ደግሞ እግዚአብሔር ለስጋትና ለጉስቁልና አሳልፎ እየሰጣት ነው፡፡ እግዚአብሔር በምስጢረ ሥጋዌው ቢታረቃትም ዕርቁን ማክበር አቅቶአታል፤ ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ ቸል ብላ የምታደርገው ሩጫ የትም ሊያደርሳት እንደማይችል ብታውቅና በንስሓ ብትመለስ እግጅ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የእግዚአብሔር ቃል “እናንተስ ከማይጠፋ ዘር ተወለዳችሁ” ብሎ ተስፋውን እንደነገረን ምድባችን ከማይጠፋ ዘር እንዲሆን ክርስቲያኖች የሆን ሁላችን በአእምሮ ጐልብተን፣ በሥነ-ምግባር ኣምረን፣ ጤናማ ሕይወትን ልንመራ ይገባናል፡፡
የአምላካችንን በዓለ ልደት ስናከብር ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ፍቅርን፣ ነገረ ዕርቅንና ነገረ ሰላምን በማኅበረሰባችን የማሥረጽ አጀንዳ ይዘን ልናከብር ይገባል፡፡
ጠቡ ፣ ጥላቻው፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ለወንድሜ ከማለት ይልቅ ለኔ ለኔ ማለቱ ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን ኣላየንም፡፡ አሁንም ወደ ልባችን እንመለስና በፍቅር፣ በዕርቅና በእኩልነት፣ በስምምነትና በወንድምነት ወደሚገኝ አንድነት እንምጣ፤ የልደቱ መዝሙር ያስተማረን ይህና ይህ ብቻ ነውና፡፡ በሌሎቹ ክፍለ ዓለማት እንደሆነው ሁሉ በሀገራችን የተከሠተው አላስፈላጊ ግጭት ብዙዎችን አሳጥቶናል፤ ብዙዎችንም ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ሜዳ ላይ ፈሰው የሰቆቃ ኑሮ እንዲገፉ አድርጎብናል፡፡ የሀገር ሀብት እንዲወድም ሆኖአል፤ ልጆቻችን ምናለ ከእንግዲህ ወዲህ ቢበቃንና ምድሪቱን የሰላም አየር እንድትተነፍስ ብንፈቅድላት፤ ይህ የወቅቱ የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ መልእክትና ጥሪ ነው፡፡
በመጨረሻም፡-
በዓለ ልደት የእግዚአብሔር በዓል ነውና፣ እግዚአብሔር በምድራችን ሰላምን ያወርድ ዘንድ ካለን ከፍለን ለተፈናቃዮች፣ ለነዳያን እና ለአካል ጉዳተኞች በመለገስ በዓሉን በመንፈሳዊ ደስታና በሰላም እንድናከብር አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤
መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ
ተክለሃይማኖት
ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
እየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጆች እና በአምላክ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ በምህረት፣ በይቅርታ እና በታላቅ ፍቅር ወደ ምድር መምጣቱ ሰላምን እና ፍቅርን ለምድር እንዲሁም አብሮነት እንዲጎለብት ምሳሌ ለመሆን ነው::
ስለዚህ በዓሉን ስናከብር የእየሱስ ክርስቶስን ምሳሌነትን በመከተል የሰላም እሴቶችን እየገነባን፣ ፍቅራችንን ይበልጥ እያጎለበትን እንዲሁም አብሮነታችንን እያጠናከርን ሊሆን ይገባል::
በዓሉን ስናከብር ያላቸው ለሌላቸው ማዕድ በማጋራት ፍቅር፣ መተሳሰብና አብሮነት በሚገለጽበት መልክ እንዲሆን ጥሪ እያቀረብኩ፣ የሰላም እና የደስታ በዓል እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
Page 6 of 753