Administrator

Administrator

Monday, 30 January 2017 00:00

እኔ፣ ሽክናና ቅኝ ግዛት

  ‹‹ወታደሩን በምን ያህል መጠን እናጠናክረው? ለእናት አገራችን በአስቸኳይ አንድንደርስ፣ ይሄ ቀዳዳ ሳይከፈት…ነገር ግን በሕግ አንበይናለን፤ እናስፈፅማለን እንላለን…ገና ጦር ሜዳ ሄዶ ጠላቱን አይቶ መግደሉን ወይም መሞቱን ሳያውቅ ከመኪና ላይ በራሱ እየወረደ የሚሞት ወጣት ነው ያለው፡፡ ምንድን ነው ይሄ? ከኢትዮጵያ ነው እንዴ የበቀለው?...››
አሉ አሉ ጓድ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡፡
ከፍርሃታችን አለማፈራችን፡፡
ከእሳቸው በላይ እኔ አርሬአለሁ፡፡ ‹‹ምንድን ነው ይሄ ታለ? ከኢትዮጵያ ነው አንዴ የበቀለው?›› ብያለሁ፡፡ እሳቸው አጣለሁ ብለው ከሰጉት በላይ እኔ ሰግቻለሁ፡፡ ‹‹ፍቅራችንን በምን ያህል መጠን እናጠናክረው? ለሲፈን በአስቸኳይ እንድንደርስ፣ ይሄ ቀዳዳ ሳይከፈት…›› ብያለሁ፡፡
የቱ ቀዳዳ? መንግሥቱ እኛን የሚፈልጉን እንደ ጋሽ ሩፌ ጭቃ፣ ቀዳዳ ለመድፈን ነው እንዴ? እያነሱ ሊመርጉን፤ ትንሽ ሽንቁር ላይ ልክክ ስንል ‹‹ለእናት ሀገሩ አኩሪ መስዋዕትነት ከፍሎ…›› እንባላለን እንደ አባቴ፤ አይ ወንድ!
እነ ሸክና እኔ ቤት ሦስት ቀን አደሩ፡፡ ሽክና በእናቱ ሀገሩ እጅግ አድርጎ ተበሳጨ፤ በተለይ የጠጅ አቅርቦት ከተቋረጠ የኢትዮጵያን የሶስት ሺህ አመት ነፃነት ይገፍፋል፡፡
‹‹ተገዝተናል!›› ይላል ቀበኛ ያኘከው ጨርቅ በመሰለ ፊቱ ላይ ብስጭት እያስነበበ፡፡
ፈርተን የተሸሸግን ቢሆንም አንዳንዶች ይሄንን ሀሳብ በጀግንነት ይዋጋሉ፡፡
‹‹አሲዙ፣ እኔ እረታችኋለሁ›› ይላል ሸክና፡፡
ጨዋታ ሞቅ ሲል ሴቶቹ አብዮት ጠባቂ ከሚጠብቁበት ከዋርድያ ነቅለው ይመጣሉ፡፡
‹‹አንተ ምን ታሲዛለህ?›› ምንም እንደሌለው ያወቁ፡፡
‹‹እስክሞት ቀጥቅጡኝ›› ይላል፡፡
ሽክናን ለመምታት ሰበብ የሚፈልገው ሳኮ የመጀመሪያዋን ሃያ አምስት ሳንቲም ይጥላል፡፡
‹‹ይኸው፣ እዩ ደሞ!››
‹‹እንምርህም ግን››
‹‹አትማሩኝ››
‹‹ከሁለተኛ ፎቅ እንደመዝለል ይቆጠራል››
‹‹ንፋስ ይወስደዋላ››
ሣቅ!!
ሽክና ለውርርድ የቀረበውን ፍራንክ አይቶ ‹‹‹ለዚችማ ብዬ ውርርዴን አላበላሽም›› አለ፡፡
እልህ የያዛቸው ጨመሩ፡፡
‹‹አሁን ይቻላል! ስምንት ብርሌ ጠጅ በቂ ነው።››
‹‹በውርርዱ ካላሸነፍክ ተመላሽ ነው አትጠጣ››
‹‹ለሱ ግድ የለም፡፡›› አለና ቀጠለ፡፡ ‹‹እዚህ ሰፈር ያሉትን ስሞች ስነግራችሁ መዝግቡ››
‹‹እሺ›› መዝጋቢ ተመደበ
‹‹ሩፌ›› አለ
‹‹ሩፌ›› ተመዘገበ
‹‹ዎሌ፣ መዘገባችሁ? ቸሩ፣ ዶሪ፣ ሳኒ፣ መዘገባችሁ? ድገሙልኝ፤››
‹‹ሩፌ›› ሲሉ
‹‹ሩፍ ከሚለው እንግሊዘኛ ነው የተገኘው፡፡ ጣሪያዬ ማለት ነው››
‹‹ዎሌ››
‹‹ዎል ከሚለው እንግሊዝ ቃል የተገኘ ነው ወለሌ››
‹‹ቸሩ››
‹‹ቸር ወንበር ነው፡፡ ወንበሬ››
‹‹ዶሪ››
‹‹ዶር፤ በሪሁን ማለት ነው››
‹‹ሳኒ››
‹‹ሰን፣ ፀሀይ አይደል ፀሐዬ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች በዚህ ይታወቃል፡፡››
የሚስቀው ሳቀ፤ የሚናደደው ተከራከረ፡፡
‹‹በእንግሊዝ ቀኝ አልተገዛንም ካለች እንደ እኔ በማስረጃ ተከራከሩ››
‹‹ነው እንዴ? አንተ? እንግሊዝ ገዝታናለች?›› አለ ሳኮ፡፡ ‹‹ወይኔ የሙዜን አሰበሉኝ፣ ምን አሰዋሻቸው? ወይኔ የሻሜታዬን…››
ሽክና ጠጁን በሴቶቹ አስላከ፡፡
በሁካታ መካከል እናቴ ትመጣና አንዴ በግልምጫ ታነሳናለች፡፡ ‹‹እኔ እዚህ ነፍስና ስጋዬ ይቦጨቃል እናንተ ታወካላችሁ? እንዴት ያሉ ሀሳብ የለሾች!
ቻይና ስለእሷ የተጀመረው ወሬ እንዳይቀጥል ብቻ ለጥበቃ የተቀመጠች ይመስላል፡፡ ለመሳቅ ትሞክርና ሽክና ሲያያት ትኮሳተራለች፡፡ ያ ማር ነጋዴ ማን ይሆን? ከእኔ የባሰ ሳይፈርድበት አልቀረም፡፡ ማር የነካካ እጁን ወደኋላ አድርጎ ይሄኔ…
ምንጭ ፡- ‹‹በፍቅር ስም›› መፅሀፍ የተቀነጨበ
በደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ከተፃፈው

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሩት ነጋ ለምርጥ መሪ ተዋናይነት ታጭታለች

     ጋለሪያ ቶሞካ ለ22ኛ ጊዜ በሚያካሂደው የስዕል ትርኢት፤ “ነፃና ንፁህ” በሚል ርዕስ የሰዓሊ ይስሃቅ ሳህሌን የሥዕል ስራዎች ለእይታ አቀረበ፡፡የሥዕል ትርኢቱ በትናንትናው እለት የተከፈተ ሲሆን የህፃናትን አለምና ህይወት የሚገልፁ የተለያዩ ስዕሎች የተካተቱበት ነው ተብሏል፡፡ “እንደ ህፃናቱ አሳሳል በወፍራም መስመራት የተሰመሩ፤ በሰፋፊ ዝርግና ደማቅ ህብረ ቀለማት የተቀቡ ነፃ፣ ንፁህና የዋህ ኪነ ቅቦች ናቸው” ብለዋል ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፤ ስለ ሰዓሊው ሥራዎች ባሰፈሩት አስተያየት፡፡ “በህፃናት ዓለም ውስጥ መገኘት፣ ያንን ዓለም መተንተን፣ በህፃናት ህሊና ውስጥ የሚፈሱ ቀለማትን ማጫወት ደስ ይለኛል” የሚለው ሰአሊው፤ ከልጅነቱ ጀምሮ በኪነ ሥዕል ሙያ ራሱን ያዳበረ መሆኑ በሥዕል ትርኢቱ መግለጫ መፅሄት ላይ ተጠቁሟል።
ሰዓሊው ከዚህ ቀደም በፈረንሳይ የባህል ማዕከል፣ በብሄራዊ ሙዚየም፣ በብሄራዊ ቴአትርና በአስኒ ቤተ ሥዕል ስራዎቹን ለዕይታ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ “ነፃና ንፁህ”፤ ለሁለት ወራት ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡ ጋለሪያ ቶሞካ የሚገኘው ሳር ቤት ካናዳ ኤምባሲ ፊት ለፊት ነው፡፡

ከ14 በላይ መፃህፍት አሳትመዋል
     ቼምበር ማተሚያ ቤትን የመሰረቱትና በኢትዮጵያና በአፍሪካ ታሪኮች ላይ ያተኮሩ መፃህፍትን የፃፉት እንዲሁም ለትምህርት የሚሆኑ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተፃፉ ከ14 በላይ መፃህፍትን ያሳተሙት አቶ
አስፋው ተፈራ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ በኢትዮጵያ መፅሐፍ ቅዱስ ማህበር በፕሬዚዳንትነት፣ በአዲስ አበባና በምስራቅ አፍሪካ ላይንስ ክለብ በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ያገለገሉት አቶ አስፋው፤ ከህልፈታቸው በፊት 10 የሚደርሱ መፃህፍትን ለህትመት እያዘጋጁ እንደነበር ታውቋል፡፡ በብሔራዊ ዩኔስኮ በድርሰት ክፍል ኃላፊነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በህዝብ
አስተዳደር ምርምርና ክፍል ጥናት፣ እንዲሁም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በናይጄሪያ  በኢትዮጵያ  ኤምባሲ በዲፕሎማትነት የሰሩት አቶ አስፋው፤ የኢምፔሪያል ሆቴል መስራችና ባለቤትም ነበሩ፡፡ አቶ አስፋው ተፈራ ባደረባቸው ህመም በአገር ውስጥና በውጪ አገር ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው፣ ሰኞ ጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም ያረፉ ሲሆን የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም ባለፈው ረቡዕ በአማኑኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ አቶ አስፋው ተፈራ ባለትዳርና የ5 ልጆች አባት ነበሩ፡፡

Sunday, 29 January 2017 00:00

የቢዝነስ ጥግ

- ድሃ ሆነህ ብትወለድ ጥፋቱ ያንተ አይደለም፤ ድሃ ሆነህ ብትሞት ግን ጥፋቱ ያንተ ነው፡፡
    ቢል ጌትስ
- ሁሉንም እንቁላሎች በአንድ ቅርጫት ውስጥ አትክተት፡፡
     ዋረን በፌ
- ለገንዘብ አትስራ፤ገንዘብን ላንተ እንዲሰራልህ አድርገው፡፡
     ሮበርት ኪዩሳኪ
- በእውቀት ላይ የሚፈስ መዋዕለ ንዋይ ምርጥ ወለድ ይከፍላል፡፡
     ቤንጃሚን ፍራንክሊን
- ትምህርት የዕድል መወጣጫ መሰላል ብቻ አይደለም፤ የመጪው ጊዜአችን ኢንቨስትመንትም ጭምር ነው፡፡
     ኢድ ማርኬይ
- ኢንቨስተር ለመሆን የተሻለ ነገ እንደሚመጣ የምታምን መሆን አለብህ፡፡
     ቤንጃሚን ግራሃም
- ድሃ ሰው በሚሰጥህ ምክር ገንዘብህን ኢንቨስት አታድርግ፡፡
     የስፔናውያን አባባል
- ገንዘቤ በሙሉ ያለው በቁጠባ ሂሳብ ውስጥ ነው፡፡ አባቴ የአክሲዮን ገበያን ምናልባት 75 ጊዜ ያህል አስረድቶኛል፡፡ አሁንም ግን አልገባኝም፡፡
     ጆን ሙላኔይ
- በአክሲዮን ገበያ ላይ ኢንቨስት ማድረግን እየነቀፍኩ አይደለም፤ እኔ ኢንቨስተር ነኝ፡፡
     ግሬስ ናፖሊታኖ
- የሳምንቱን የዕረፍት ቀናት አልወዳቸውም፤ ምክንያቱም የአክሲዮን ገበያ የለም፡፡
     ሬኔ ሪቭኪን

 አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ባለፈው የአገሪቱ ምርጫ፣ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙ እንዲጣራ የሚያደርግ ትዕዛዝ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሁለት ግዛቶች በመራጭነት የተመዘገቡ አሉ፣ ህጋዊ ያልሆኑ መራጮች ተመዝግበዋል፣ በህይወት የሌሉ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል የሚሉትን ጨምሮ ከመራጮች ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ መጭበርበሮችን እንዲጣራ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በምርመራው የተገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም፣ የአገሪቱን የምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስርዓት የምናስተካክል ይሆናል ብለዋል ትራምፕ፡፡
ትራምፕ ተፈጽሟል የተባለውን መጭበርበር አጣራለሁ ይበሉ እንጂ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የምርጫ ሃላፊዎች በምርጫው ሂደት መጭበርበር መፈጸሙን የሚያመለክቱ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃዎች አለመቅረባቸውን ሲናገሩ መቆየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን መግለጫ ያወጡት ባለፈው ማክሰኞ በተደረገው የዋይት ሃውስ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቃል አቀባዩ ሻን ስፓይሰር፤” በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች በምርጫው ድምጻቸውን ሰጥተዋል” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ ትራምፕ የምርጫው ሰሞን ጀምሮ መጭበርበር መፈጸሙን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሲገልጹና “በምርጫው አምስት ሚሊዮን ያህል ህገ-ወጥ መራጮች ለሄላሪ ድምጻቸውን ሰጥተዋል” የሚል ክስ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሶ፣ ይህን ክሳቸውን የሚደግፍ ምንም አይነት ማረጋገጫ አለማቅረባቸውን ዘግቧል፡፡

   ኢትዮጵያ በሙስና ከ176 የአለማችን አገራት 68ኛ ደረጃን ይዛለች

     ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ አመታት በሙስና ክፉኛ በመዘፈቅ አለምን ስትመራ የዘለቀቺው ሶማሊያ፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016ም ቀዳሚነቷን ማስጠበቋን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም አስታውቋል፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የአመቱ የዓለማችን የሙስና ሁኔታ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ጥናቱ ከተሰራባቸው የአለማችን 176 አገራት በሙስና 68ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ጠቁሟል፡፡
ተቋሙ በአለማችን ከፍተኛ ሙስና የተንሰራፋባቸው አገራት በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፡- ደቡብ ሱዳንና ሰሜን ኮርያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ያገኙ ሲሆን  ሶርያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ጊኒ ቢሳኦ እና ቬንዙዌላ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የዓለማችን 176 አገራት መካከል ዴንማርክና ኒውዚላንድ እጅግ አነስተኛው ሙስና የሚታይባቸው ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ ፊንላንድና ስዊድን በሁለተኛና በሶስተኛነት መቀመጣቸውን ገልጧል። አነስተኛ ሙስና ያለባቸው የአለማችን አገራት ተብለው የተዘረዘሩት ቀሪዎቹ አገራት ደግሞ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ሲንጋፖር፣ ኒዘርላንድስ፣ ካናዳና ጀርመን ናቸው፡፡
ሙስና መጠንና ስፋቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም የአለማችን አገራት እንደሚታይ ያስታወሰው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፤ በርካታ የአለማችን አገራት ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በ2016 መሻሻል ከማሳየት ይልቅ የባሰ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

 የወቅቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ እና የማይክሮሶፍት መስራቹ አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ፣ በመጪዎቹ 25 አመታት ጊዜ ውስጥ የአለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ የጥናት ውጤት አመለከተ፡፡
የቢልጌትስ ሃብት በፍጥነት እያደገ መሄዱ ከቢሊየነርነት ወደ ትሪሊየነርነት ያሸጋግራቸዋል ቢባልም፣ በመዝገበ ቃላት ውስጥ ግን ትሪሊየነር የሚባል ቃል እስካሁን እንዳልሰፈረ ተዘግቧል። ኦክስፋም ኢንተርናሽናል ይፋ ያደረገው ይህ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ እ.ኤ.አ ከ2009 አንስቶ የሃብት መጠናቸው በአማካይ በ11 በመቶ እያደገ እዚህ የደረሰው ቢል ጌትስ፣ እድገቱ በዚሁ መጠን እየጨመረ ከቀጠለ እድሜያቸው 86 አመት ሲሞላቸው፣ የአለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 የቢል ጌትስ የሃብት መጠን 50 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የዘገበው ፎርብስ፤ በአስር አመታት ጊዜ ውስጥ የተጣራ ሃብታቸው ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016 ላይ 84.4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንም ገልጧል፡፡

  በተለያዩ ድረገጾች የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ዕቅድ አለው የሚል መረጃ በስፋት ሲሰራጭበት የከረመው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ መረጃው ሃሰተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ዙክበርግ በቅርቡ ባልተለመደ ሁኔታ ፖለቲካ ቀመስ አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ፣ ወደ ፖለቲካው አለም የመግባትና ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንዳለው የሚጠቁሙ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ መሰንበታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ግለሰቡ ግን ሰሞኑን ከአንድ ድረገጽ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ መረጃውን ማስተባበሉን ዘግቧል፡፡
“የሚወራው ነገር ሃሰት ነው፡፡ እኔ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ የለኝም፡፡ ሙሉ ትኩረቴን የማደርገው የፌስቡክን ማህበረሰብ በመገንባትና ከባለቤቴ ጋር ባቋቋምነው ቻን ዙክበርግ ኢኒሺየቲቭ የተሰኘ ድርጅት አማካይነት የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራት ላይ ነው” ብሏል ዙክበርግ፡፡
ዙክበርግ ለፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንደሌለው ያስታውቅ እንጂ፣ ወደ ፖለቲካ የመግባትም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የመስራት እቅድ ይኑረው አይኑረው በግልጽ ያለው ነገር እንደሌለ ዘገባው ገልጧል፡፡
ዙክበርግ ፕሬዚዳንት የመሆን እቅድ አለው የሚለውን ጭምጭምታ ያጠናከረው ደግሞ፣ የፌስቡክ ኩባንያ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በቅርቡ ባደረገው ማሻሻያ፣ ዋና ስራ አስፈጻሚው በፖለቲካዊ ምርጫ የመወዳደር መብት እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ ማስተካከሉ ነው ተብሏል፡፡

 አለማቀፉ ማህበረሰብ እየጨመረ ለመጣው የናይጀሪያ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ በመጪዎቹ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ 90 ሺህ ያህል የአገሪቱ ህጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል፡፡
በአገሪቱ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ተገቢውን ድጋፍ ባለማግኘት በአለማቀፍ ደረጃ ቀዳሚው እንደሆነ ያስታወቀው ተቋሙ፤አሸባሪው ቡድን ቦኮ ሃራም ከሚያደርሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ስደቶችና መፈናቀሎች የአገሪቱን 450 ሺህ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጠቂ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁሞ፣ ተገቢው ድጋፍ ካልተደረገ በመጪዎቹ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በየቀኑ በአማካይ 240 ህጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ቦኮ ሃራም በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው የሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰባት ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ከአነዚህ የአገሪቱ ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት እንደሆኑም አመልክቷል፡፡
የምግብና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችና ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ ቢሄድም፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ ተገቢ ምላሽ አልሰጠም ያለው ዩኒሴፍ፤መንግስታትና ለጋሾች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ በዓል ቀን፣ ባልና ሚስት አንድ እንግዳ ይመጣባቸዋል፡፡ የከበደ እንግዳ! ዶሮ ወጥ ተሰርቷል፡፡ በግ ታርዷል፡፡ ቤቱ በዓል በዓል ይሸታል፡፡ ስኒ ረከቦቱ ላይ ተደርድሯል፡፡ እጣኑ ቦለል ቦለል ይላል፡፡
እንግዳውና ቤተሰቡ ግብዣውን ለመብላት አኮብኩበዋል፡፡
ራቱ ተጀመረ፡፡ በመካከል “እ!እ!እ!” የሚል የትንሽ ልጅ የለቅሶ ድምፅ ይሰማል፡፡
እንግዳው፣
“ምንድን ነው ይሄ የሚሰማው ድምፅ?” ሲል ጠየቀ፡፡
አባት፤
“አይ፣ የእኛ ልጅ ነው ተወው” አለ፡፡
እንግዳውም፤
“እንዴት እተወዋለሁ? በዓመት በዓል እንዴት ከቤተሰቡ ይለያል? የት ነው ያለው አሳዩኝ” ብሎ ድርቅ አለ፡፡
እንግዳው፤
“እንዲያውም አልበላም” አለ፡፡
“ና ላሳይህ” ብሎ ወደ ጓዳ ወሰደው፡፡
ልጁ፤ ቆጡ ላይ ታስሯል፡፡
እንግዳው በጣም አዘነ፡፡
“ምን አድርጎ ነው እንዲህ ዓይነት ቅጣት የፈፀማችሁበት?”
አባት፤
“ምንም አላደረገም፣ ግን ከልምድ እንደምናውቀው፣ ከእንግዳ ጋር ገበታ ከቀረበ እጁ ባለጌ ነው!
ከእንግዳ ፊት ብድግ ያደርጋል፡፡ ብትቆጣውም አይሰማም” አለ፡፡
እንግዳው፣
“ኧረ በጣም ነውር ነው፡፡ ግዴለም፤ ይምጣ፣ ይምጣ፡፡ እናስተምረዋለን፤ ሥነ ስርዓት፡፡” አለና አግባባቸው፡፡
ልጁ ተፈቀደለትና ከእስር ተፈታ፡፡ ከቆጡ ወረደና ገበታ ቀረበ፡፡
የዶሮ ብልት በፈርጅ በፈርጁ ይቀርብ ጀመር፡፡
ልጁ ዕውነትም አደገኛ ኖሯል፡፡
እንግዳው ፊት የቀረበውን ሁለት የዶሮ እግር በተከታታይ እያነሳ ነጨ! ከዚያ የአባቱን የፈረሰኛ ብልት አነሳ! ይሄኔ ግራ የተጋባችው እናት በቁጣ፤
“ይሄን እንዲች ብለህ እንዳትነካ፤ ነግሬሃለሁ!” ብላ ለእንግዳው ሌላ ብልት ስታቀርብ፤ ልጁ ይሄ ሊመልሰው ነው? እጁን ሰደደ፡፡ ይሄኔ እንግዳው የልጁን እጅ ቀብ አድርጎ፣ ፈጥኖ አጠንክሮ ያዘና፤ ወደ ባለቤቶቹ ዞሮ፤ “እንግዲህ፣ ሸብ አድርጉልኝ ይሄን ልጅ!” አለ፡፡ ልጁም ከሶስት የዶሮ ብልት በኋላ፣ ሸብ ተደርጎ፣ ተመልሶ ቆጡ ላይ ሰፈረ!
*          *        *
ልማድ የልጅነት አባዜ አለው፤ አድጎ ተመንድጎም ራሳችን ላይ ፎቅ ሊሰራብን ይችላል። መላቀቅ ያለብን ብዙ ልማድ አለ! ይሄ ከባህላችን፣ ከማህበራዊ ኑሯችን፣ ከፖለቲካችንና ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ ስነ ልቦናዊ ግንኙነቱም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ ይሄን ወደ አገር ጉዳይ መንዝሮ ማየት ጉዳዩን በሚገባ መሰረት ያበጅለታል፡፡ እየተዘወተሩና እየተለመዱ የሚመጡ የአገራችን ጉዳዮች ውለው አድረው፣ ጎልበተው መታየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ትናንሽ ዕቅዶች ወደ ትላልቅ ፈቅዶች የሚያድጉት ትናንሾቹ በአግባቡ ሲፈፀሙ ነው፡፡ ለዚያ የጊዜ ስሌት፣ የዝርዝር አያያዝና የቁጥጥርና ግምገማ ሥርዓት በአግባቡ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ይህን ፈፃሚውና አስፈፃሚው አካል፣ የራሱ አቅልና ብስለት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የራስ አመለካከት ከአገር አመለካከት ጋር ይራራቅና ጣጣ የሚያመጣው፡፡ እያንዳንዱን ሰው ቀርፆ፣ ሰው ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ይህን የሚሠሩ ተቋማት እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ለዚህ ብሩህ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የሲቪል ማህበራት ቁጥርም፣ አቅምም በጣም ውስን ነው፡፡ ይህ የሆነው ፋይዳቸውን ከልቡ ያመነበት ወገን ባለመኖሩ ነው፡፡ ጊዜም ባይኖር ጊዜ ወስዶ፣ ለጥያቄው መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አማካዩ መንገድ ይሄው ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚው ድርድር ባሻገር የህዝብን አስተሳሰብ የሚያሰባስብ፣ ወደ ተግባር እንዲያመራም የሚያግዝ ኃይል ያስፈልጋል፡፡
‹‹ከእናንተ ሌላ እኛም አለንኮ›› የሚል የህብረተሰብን ክፍል ማን ይታደገው ማለት አለብን፡፡ በጥቁርና በነጭ መካከል ያለውን ግራጫ መስመር፣ ስፋቱን ስለማንገነዘብ ጠቀሜታውም የዚያኑ ያህል ይሳሳብናል፡፡ ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ፣ ለአንድ ዓመት አይነግሥ›› የሚለው አባባል፣ አበው ያለ ነገር አላሉትም፡፡ ለአመራሩ፣ ለገዢው ክፍል፣አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ በእርግጥ አማካሪ ሲባል በዕውቀት የረቀቀ፤ በልምድ የበለፀገና  ጊዜ ያስተማረው ሊሆን ይገባል! መንግሥት ሲቸኩል የሚያለዝበውም፣ ሲጠጥር የሚያልመው፤ ግትር ሲል የሚያላላው፣ አይዞህ ባይም፣ ገሳጭም፣ ነው የሚያሻው፡፡ የጥንት የጠዋቱ ገጣሚ ገሞራው፤ እንዳለው፡- ‹‹…ነገሩ አልሆን ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
 ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…›› የሚሉ በሳሎች ያስፈልጋሉ፡፡ በመደራደር ብዙ መንገድ መሄድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንድ ዕውነት መረሳት የለበትም፡፡ ማናቸውም ወገን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ገና ሶስተኛም ወገን ተጨምሮ አይበቃም ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው። ጉዳዩን መሠረታዊ የሚያደርገው የሀገራችን ችግር ስፋት ነው፡፡ የፍትሕ መጓደል፣ የዲሞክራሲ አለመብሰል፣ የሀብት አለመደላደል፣ የተቋማት ሥርዓት አለመሻሻል፣ መልካም አስተዳደር አለመታደል፣ ያልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ አጥተው መንሳፈፍ፣ ወዘተ ምኑ ቅጡ! ለዚህ ነው አገር ሙሉ ድርጅት ቢፈጠር እንኳ የአገር ቋት አይሞላም የምንለው!
እነዚህ ሁሉ በቅጡ ቢሰባሰቡና ኢኮኖሚውን ካቀረቀረበት ቢያቀኑት ድንገት ፎቀቅ እንል እንደሁ እንጂ ነገረ-ሥራችን እንኳ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነብን መቸገራችን የዕለት የሠርክ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ተራው ዜጋ ‹‹የምበላው ሳጣ፣ ልጄ ጥርስ አወጣ›› ቢል አይፈረድበትም! ኑሮው ከሥረ-መሠረቱ እናሻሽልለት! በዓል በመጣ ቁጥር የሚሰቀቀው አያሌ ነው! የእኛን መጥገብ ብቻ አንይ!! ይህንን ተደራዳሪዎቹ ወገኖች፣ እነሆ ወቅቱ መጥቷልና በምን መቀነቻ አጥብቀን እንያዘው ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ፀፀታችንን ሳይሆን ነገርአችንን እናስብ! የመሪዎችን ጉባኤ ስናስብም የአገራችንን መረጋጋት እንፈይድ!! 

Page 7 of 317