Administrator

Administrator

82ኛው “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” ረቡዕ ይካሄዳል
 82ኛው ዙር “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በራስ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ ግርማ ተፈራ - ሙዚቃ፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙ - ትረካ፣ ሽመልስ አበራ - መነባንብ፣ ጌዲዮን ወ/ዮሐንስ - ዲስርና በኃይሉ ገ/እግዚአብሄር ወግ የሚያቀርቡ ሲሆን ትዕግስት አጀመ፣ አብረሃም አስቻለው፣ ውብአለም ተስፋዬና ናትናኤል ጌቱ ግጥሞቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

 በስራ ፈጠራና በካይዘን ፅንሰ ሀሳብ ላይ ተመስርተው ባሰናዷቸው መፅሐፍት የሚታወቁት ዶ/ር አቡሽ አያሌውና እንድሪስ አራጋው “የኢንተርፕረነርሺፕ ሀሁ” የተሰኘ መፅሐፍ አዘጋጅተው ለገበያ አቀረቡ፡፡ መፅሐፉ፤ “የራስህን ቢዝነስ ለመጀመር አሁኑኑ ተነስ” በሚል ከንግድ ሀሳብ ፈጠራ እስከ ንግድ ሀሳብ እቅድ አነዳደፍ ድረስ በተግባር የተዋቀረ ትምህርት ይሰጣል ተብሏል፡፡
አንድ ሰው እንዴት ውጤታማ ቢዝነስ መጀመር ይችላል፣ በፍጥነት ገበያን ሰብሮ ለመግባት ምን መደረግ አለበት፣ የቱን አይነት የንግድ ህጋዊ አመሰራረቶች ቢመርጥ ይጠቀማል በሚሉትና መሰል ጉዳዮችም ላይ ሰፊ ሃሳብና አማራጭ ያቀርባል ተብሏል፡፡ በ330 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ175 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

   በኢንተሌክችዋል አለም አቀፍ ት/ቤት አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረውና ከ1 መቶ በላይ ት/ቤቶች የተውጣጡ 1 ሺህ ተማሪዎች የተሳተፉበት የሂሳብ ውድድር፤ አሸናፊዎችን በመሸለምና በኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ተጠናቀቀ፡፡
ት/ቤቱ ከ1ኛ - 3ኛ የወጡ ተማሪዎችን እንደየክፍል ደረጃቸው ከ2 ሺህ እስከ 1 ሺህ ብር እና የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ሸልሟል፡፡ ለአሸናፊ ተማሪ ት/ቤቶችም ዘመናዊ ፕሪንተርና ኮፒ በአንድ ላይ የያዘ ማሽን በሽልማት አበርክቷል፡፡ ውድድሩ ዘንድሮ ከ6ኛ - 8ኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች መካከል ለስምንተኛ ጊዜ መካሄዱም ተገልጿል።
በዚህ ውድድር የግልና የመንግሥት ት/ቤቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ የሂሳብ ውድድሩን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ እቅድ እንደነበራቸው የት/ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ቅርንጫፍ መምህርና ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ካሳሁን አስራደው ተናግረዋል፡፡ ውድድሩ በየዓመቱ መካሄዱ የተማሪዎቹን የሂሳብ ትምህርት ፍላጎትና ችሎታ ያሳድጋልም ተብሏል፡፡

  በዶ/ር አማረ ተግባሩ የተፃፈው “ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሐፉ በ1960ዎቹ መጨረሻ በዋናነት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እንዲሁም የመኢሶን መሪ በነበረው ኃይሌ ፊዳ ህይወት፤ ፖለቲካዊ ሚና እንዲሁም አጠቃላይ አብዮታዊ እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ነው ተብሏል፡፡
ስለ ኃይሌ ፊዳ ጨዋነት፣ አስተዋይነት፣ አርቆ አሳቢነትና ረቂቅነት የሚያወሳው መፅሐፉ፤ ለዛውን፣ ልዩ ፍቅሩንና ሥጦታውንም በተባ ብዕርና ባማረ ቋንቋ ይገልጽልናል ተብሏል፡፡ “የድህረ ዘውድ ኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጋ ነፃነትና እኩልነት የሚያረጋግጥ፤ የደሀውንና የተበደለውን ወገን ዕድልና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ አቅጣጫ ከቀየሱት ወጣቶች ግንባር ቀደም የሆነው ኃይሌ ፊዳ ነውና ይህን መልካም ማስታወሻ ስላበረከተልን የዶ/ር አማረ ተግባሩ ባለውለታ ነን …” ብለዋል ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በመፅሐፉ ጀርባ ባሰፈሩት አስተያየት፡፡ በ236 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በ111 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡  

  አሜሪካ 610 ቢ. ዶላር፣ ቻይና 228 ቢ. ዶላር፣ ሩስያ 66.3 ቢ. ዶላር አውጥተዋል

    የአለማችን አገራት ለወታደራዊ ጉዳዮች የሚመድቡት በጀትና አመታዊ ወጪ እየጨመረ መምጣቱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለማችን በድምሩ 1.739 ትሪሊዮን ዶላር ለወታደራዊ ጉዳዮች ወጪ መደረጉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲቲዩት የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አለማቀፍ ወታደራዊ ወጪ በ2016 ከነበረበት የ1.1 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ይህም ለሰላም አማራጮች ትኩረት መነፈጉን የሚያመለክት አደገኛና አሳሳቢ ክስተት ነው ተብሏል፡፡
በ2017 የፈረንጆች አመት ከፍተኛውን ወታደራዊ ወጪ ያወጡት ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሩስያና ህንድ ናቸው ያለው ተቋሙ፤እነዚህ አገራት በአመቱ በአለማችን ከተደረገው አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ 60 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍኑም አመልክቷል፡፡
አሜሪካ በአመቱ ከአለማችን አገራት ከፍተኛውን የ610 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ወጪ በማውጣት ቀዳሚነቱን መያዟን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ይሄም ሆኖ ግን ወጪው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ባለበት መቀጠሉንም አክሎ ገልጧል፡፡ ላለፉት ከ20 በላይ አመታት ወታደራዊ ወጪዋን ከአመት አመት እየጨመረች የመጣቺው ቻይና፤በ2017 የፈረንጆች ዓመትም ወጪዋን በ5.6 በመቶ በማሳደግ፣ በድምሩ 228 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን የተቋሙ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ ሩስያ እ.ኤ.አ ከ1998 ወዲህ ወታደራዊ ወጪዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ቀንሳለች ያለው ተቋሙ፤ የአገሪቱ ወጪ በ2016 ከነበረበት በ20 በመቶ ቅናሽ በማሳየት፣ በ2017 የፈረንጆች አመት 66.3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ቅናሹ ከአለማችን አገራት ከፍተኛው መሆኑንም አመልክቷል፡፡

“ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት የሚገባቸው ታላቅ ሰው ናቸው!” - የደቡብ ኮርያው መሪ

      የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮርያ ልሳነ-ምድር ሰላምን ለማስፈን ላደረጉት ጥረት እውቅና ሊሰጥ ይገባል ያሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ ፕሬዚዳንቱ ለመጪው የፈረንጆች አመት 2019 የታላቁ የኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት እንዲቀርቡ ለሽልማት ተቋሙ በላኩት ደብዳቤ መጠየቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት የሆኑት እነዚሁ 18 ፖለቲከኞች ባለፈው ረቡዕ በኖርዌይ ለሚገኘው የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በላኩት ደብዳቤ፣ ትራምፕ በኮርያ ልሳነ ምድር ጦርነት እንዲያበቃ፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውልና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ፣ የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
ሪፐብሊካኑ ትራምፕ ለኖቤል ሽልማት በዕጩነት እንዲቀርቡ ለተቋሙ ጥያቄውን ያቀረቡት የደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄኢን፤”ትራምፕ የኖቤል ሽልማት የሚገባቸው ታላቅ ሰው ናቸው” ሲሉ ባለፈው ሰኞ በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ መሆኑንም የጠቆመው ዘገባው፤የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም በ2009 የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውን አስታውሷል፡፡
በተቋሙ ህግ መሰረት፤ ለኖቤል ሰላም ሽልማት ዕጩዎችን የሚያቀርቡት፣ የአገራት ብሄራዊ ህግ አውጪ ተቋማት አባላት፣ ፕሮፌሰሮችና ከዚህ ቀደም ተሸላሚ የነበሩ ግለሰቦችና የመሳሰሉት ብቻ ናቸው ያለው ዘገባው፤ተቋሙ ለሪፐብሊካኑ ጥያቄ ምን አይነት ምላሽ እንደሰጠ አለመታወቁን ጠቁሟል፡፡
የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ ለዘንድሮው ሽልማት 330 ዕጩዎችን መመዝገቡን ያመለከተው ዘገባው፤አሸናፊዎቹም በመጪው ታህሳስ ወር ላይ ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡

   የሞ ኢብራሂም ሽልማትን ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው

   የሞ ኢብራሂም ተቋምን የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑት የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፤ ባለፈው ሳምንት ከተቋሙ በሽልማት መልክ ያገኙትን 5 ሚሊዮን ዶላር የአገራቸውን ሴቶች የማብቃት አላማ ያለው ማዕከል ለማቋቋም እንደሚያውሉት አስታውቀዋል፡፡
ለሁለት ተከታታይ የስልጣን ዘመናት አገራቸውን የመሩትና ከወራት በፊት ስልጣናቸውን ያስረከቡት የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፤ አገሪቱን ለአመታት ከዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት እንድታገግም ለማድረግ በተጫወቱት ቁልፍ ሚናና በአመራር ብቃታቸው ለዘንድሮው የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን የዘገበው ሲኤንኤን፤ ባገኙት የሽልማት ገንዘብ በስማቸው የተሰየመ የሴቶችና የልማት ማዕከል እንደሚያቋቁሙ መናገራቸውን አመልክቷል፡፡
“የአገሬ ሴቶች የለውጥ ሃዋርያ፣ የሰላም ጠባቂና የእድገት ቀያሾች እንዲሆኑ ለማገዝ ራሱን የቻለ ማዕከል የማቋቋምና ሴቶችን የማብቃት ስራዬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ” ሲሉ የቀድሞዋ መሪ የ79 አመቷ ሰርሊፍ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል። በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ፣ አገራቸውን በተጨባጭ ያሳደጉ፣ ህጉ የሚፈቅድላቸውን የስልጣን ገደብ አክብረው በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ያስረከቡ አፍሪካውያን መሪዎችን የሚሸልመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ በነበሩት አመታት ሽልማት ሳይሰጥ መቆየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም የሆነው መስፈርቱን የሚያሟላ አፍሪካዊ መሪ ሊያገኝ ባለመቻሉ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በሱዳናዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ሞ ኢብራሂም እ.ኤ.አ በ2006 የተቋቋመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ ከመሪዎች በተጨማሪም የአፍሪካ አገራትን የመልካም አስተዳደር ሁኔታ 88 ያህል መስፈርቶችን በመጠቀም እየገመገመ ደረጃቸውን በየአመቱ ይፋ እንደሚያደርግም አመልክቷል፡፡

    ከሳምንታት በፊት በጠባቂያቸው 119 ላፕቶፖችን የተዘረፉት የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ አሁን ደግሞ ጉሹንጎ ሆልዲንግስ በተባለው ተቋማቸው ተቀጥሮ በሚሰራ የሂሳብ ባለሙያ 10 ሺህ ዶላር ያህል መዘረፋቸውን አፍሪካን ኒውስ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
ፒተር ቢሂቢ የተባለውና ዝርፊያውን ፈጽሟል የተባለው የድርጅቱ ሰራተኛ፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት መቅረቡን የጠቆመው ዘገባው፤ በ100 ዶላር ዋስትና የተለቀቀው ግለሰቡ በመጪዎቹ ሳምንታት ተገቢው የፍርድ ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡
ይህ የዝርፊያ ወንጀል ከተፈጸመ ከቀናት በፊትም ጠባቂያቸው የነበረ አንድ የአገሪቱ ወታደር ከሮበርት ሙጋቤ 119 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን በመዝረፍ መሰወሩንና በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ ተጠርጣሪው ግን “ላፕቶፖቹን ሙጋቤ ናቸው በስጦታ መልክ የሰጡኝ” ሲል መከራከሩንና ከሰሞኑም እርግጥም ሰጥተውት እንደሆነ ራሳቸው ሙጋቤ ምስክርነት ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።

 የታንዛኒያ መንግስት 900 ዶላር በመክፈል የጡመራ ፈቃድ ሳያወጡ ሲሰሩ ያገኛቸውን ጦማሪዎች፤ የ2 ሺህ 200 ዶላር እና የ1 አመት እስር ቅጣት እንደሚያስተላልፍባቸው ከሰሞኑ ማስታወቁን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለፈው መጋቢት ወር በስራ ላይ ባዋለው አዲስ የድረገጽ ይዘት መመሪያ መሰረት፣ ተመዝግበው ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ያላገኙ ጦማሪዎች፤ ከዛሬ ጀምሮ በህገወጥ መንገድ ሲሰሩ ከተገኙ የተጠቀሰው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
ጦማሪያኑ አብረዋቸው የሚሰሩ ባለአክስዮኖችን፣ ካፒታላቸውን፣ ዜግነታቸውን፣ የሙያ ብቃታቸውን፣ የታክስ የምስክር ወረቀታቸውንና የመሳሰሉትን መረጃዎች ለሚመለከተው አካል እንዲያስመዘግቡና 900 ዶላር ከፍለው ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው የሚያስገድደው መመሪያው፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጥስ፣ ኢ-ፍትሃዊ እርምጃ በሚል በአገሪቱ ጦማርያንና አክቲቪስቶች መተቸቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

    ኤችአይቪ ቫይረስ በሚያስከትለው የአቅም መዳከም የተነሳ በመውለድ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶችን ጤንነት የሚፈታተንና እንዲሁም ቫይረሱ ወደ ቤተሰብ የመተላለፍ እድሉን ስለሚጨምር ወደ ፊት ልጅ ለመውለድ የሚኖራትን ፍላጎት ሊፈታተነው ይችላል፡፡ ስለዚህም ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ መጠቀም ያልተፈለገ እርግዝናን ከመከላከሉም ባሻገር ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ የሚኖ ረውን መተላለፍ ይቀንሳል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው እውነታ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ንጹህ አዲስና ዶ/ር እስክንድር ከበደ ካደረጉት ጥናት የተወሰደ ነው፡፡ ጥናቱ የተደረገው በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ፤ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል እና ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በእርግዝና ወቅት ክትትል ከሚደረግበት ክሊኒክ ነው፡፡ በሶስቱ ሆስፒታሎች በአመት እስከ 12.000/አስራ ሁለት ሺህ እናቶች የሚወልዱ ሲሆን ጥናቱ የተደረገውም April-August/2016/ ድረስ ነው፡፡
የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለ ሴቶች እርግዝናን በእቅድ ወይንም በፕላን እንዲያ ደርጉ የሚመክረውን ጥናት ለማድረግ በጥናቱ የተካተቱ ሴቶች በሙሉ ቫይረሱ ያለባቸው ሲሆኑ በተጠቀሱት ሆስፒታሎች የእርግዝና ክትትል በማድረግ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ቫይረሱ በደማቸው ቢኖርም በምጥ ላይ የነበሩ ወይንም ጽንስ በማቋረጥ ላይ የነበሩ እና የተረ ገዘው ልጅ ሞት የገጠማቸውን እናቶች ጥናቱ አላካተተም፡፡ በጥናቱ የተካተቱት እናቶች 183/ሲሆኑ በተለይም 173/እናቶች 94% የሚሆኑት ለጥናቱ ጠቃሚ መረጃን በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡   
ሰውነት ሕመምን እንዲቋቋም የሚያስችለውን አቅም የሚፈታተነው ኤችአይቪ ቫይረስ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛውን የስርጭት ቁጥር የያዘ ሲሆን ከዚህም ሴቶች 58% የሚሆነውን በቫይረሱ የመያዝ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ የኤችአይቪ ስርጭት በህጻናቱም በኩል ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከፍ ያለ ቁጥር የተመዘገበበት ሲሆን በአለም በአመት በአዲስ በቫ ይረሱ ከሚያዙት 98% የሚሆኑት በዚሁ ክልል የሚኖሩ ናቸው፡፡
እርግዝናን በእቅድ መፈፀም በተለይም በደማቸው ውስጥ የኤችአይቪ ቫይረስ ላለባቸው ሴቶች እጅግ አስፈላጊ ከሚሆንበት ምክንያት አንዱ ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሲሆን ከፕላን ውጭ የሚደረገው ግን በጣም አደገኛና የተጸነሱትን ልጆችም ከቫይረሱ ለመጠበቅ የማያስችል የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡
ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ ዘዴን መጠቀም አቅምን ያገናዘበና ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ እንዲሁም የእናቶችን እና የህጻናቱን ጤንነት እና ሕይወትን ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ዘዴ ነው፡፡ ኮንዶምን መጠቀም ኢንፌክሽንን ከመተላለፍ የሚያግድ ጠቃሚው መንገድ ነው፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት /20-43% የሚሆኑ ቫይረሱ በደማቸው ያለ እናቶች ብቻ የቤተሰብ እቅድ ዘዴን የሚጠቀሙ መሆኑ ተረጋግጦ አል፡፡ በተደረገው ጥናት ውጤት መሰረትም 14/ሚሊየን/አስራ አራት ሚሊየን የሚሆኑ ያልታ ቀዱ እርግዝናዎች በየአመቱ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ይከሰታሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያ ያዘ በተደረገው ዳሰሳ የተገኘው ምላሽ እንደሚያሳየው ከሆነ ያገቡ እና የተማሩ እንዲሁም በከ ተማ የሚኖሩ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሴቶች በተሻለ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል የሚያ ደርጉ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ሴቶቹ በራሳቸው ሕይወት መወሰን የማይችሉ ፤ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ (ድህነት) ያላቸው ፤ዝቅተኛ የሆነ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎት ካለ እና የቤተሰብ ቁጥራቸው ከፍ እንዲል የሚፈልጉ ከሆነ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት የማያሳዩ ናቸው፡፡
እንደውጭው አቆጣጠር በ2011/በተደረገው ጥናት በአዲስ አበባ 43.3% የሚሆኑ ቫይረሱ በደ ማቸው ያለ እናቶች ልጅ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሲሆን በጥናቱ ከታቀፉት ውስጥ 71.5% የሚሆኑት በቅርብ እንደሚወልዱ ተናግረዋል፡፡ መልስ ከሰጡት 26.8% የሚሆኑት ጥናቱ በሚ ካሄድበት ወቅት እርጉዝ የነበሩ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በተደረገው ጥናት እንደታየው ከሆነ ሴቶች በምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩ ሲነገራቸው ወዲያውኑ ልጅ እንዳይኖራቸው የሚወስኑ ብዙ ሲሆኑ በኬንያ ደግሞ አብዛ ኞቹ ማለትም 87% የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ እናቶች ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን ፕሮግራም በፈቃደኝነት እንደሚሳተፉና ወደፊትም ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ስላሳዩ በዚህም ወደ 59% የሚደርስ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ፈቃደኝነት እና ተግባር ታይቶ አል፡፡
በኢትዮጵያ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና በጋንዲ ሆስፒታል በውጭው አቆጣጠር በ2013/ በተደ ረገው ጥናት የታየው ያልተፈለገ እርግዝና ቫይረሱ በደማቸው ባለባቸው ሴቶች 56.3% ሲሆን ቫይረሱ በደማቸው የሌለባቸው ሴቶች ግን 29.5% ማለትም በግማሽ ያህል የቀነሰ ነበር፡፡
አስፈ ላጊውን መከላከያ ያለማግኘት ምክንያት ተደርገው የሚወሰዱት፤
በጉዳዩ ዙሪያ ማለትም ስለመከ ላከያዎቹ አገልግሎት ትንሽ ወይ ንም ጭርሱኑ እውቀት አለመኖር፤
አገልግሎቱን ለማግኘት አለመቻል ፤
በኤችአይቪ እና በቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎት መካከል ቅንጅት አለመኖር፤
የአድሎና መገለል ፍራቻ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ እናቶች ኮንዶምን ስላለመጠቀም የሰጡት መልስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
እኔ እርጉዝ ነኝ፡፡ ስለዚህ ኮንዶም መጠቀም አያስፈልገኝም፡፡
ባለቤቴ በኮንዶም መጠቀም የሚባለውን ነገር በፍጹም አይደግፈውም፡፡አይወድም፡፡
ፍቅረኛዬ ወይንም በወሲብ የምገናኘው ሰው እኔ ቫይረሱ በደሜ ውስጥ እንዳለ አያውቅም።
በኮንዶም ወሲብን መፈጸም ስሜትን ስለሚቀንስ አላደርገውም፡፡
ምክንያቱ ባይገባኝም አልወደውም፡፡
ሌሎች፡-
ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ያልተፈለገ እርግ ዝናን መከላከል ወይንም ተገቢውን የጊዜ እርቀት በመጠቀም ልጆችን ማፍራት እንዲሁም ምን ያህል ልጅ በቤተሰብ መወለድ አለበት የሚለውን መወሰን ነው፡፡
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በጥናቱ ከተካተቱት በደማቸው ኤችአይቪ ቫይረስ የሚገኝባቸው ሴቶች መካከል እርግዝናቸው የታቀደ መሆኑን ያረጋገጡት 113/ሲሆኑ 60/ዎቹ ግን ካለእቅድ ማርገዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለባለቤቶቻቸው ኤች አይቪ መረጃ ሲመልሱም 83/የሚሆኑት ቫይረሱ በባላቸው ደም ውስጥ እንዳለ ሲመሰክሩ 34/የሚ ሆኑት ደግሞ ነጸ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን 56/የሚሆኑት ሴቶች ባላቸው ኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ ይኑር አይኑር የሚያውቁት ነገር የለም፡፡
ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ከሚያስችሉ መከላከያዎች በተለይም ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቢጠቀሙ የሚመከረው ኮንዶም ነው፡፡ ይህንን በተመለከተም ቫይረሱ በደምሽ ውስጥ መኖሩ ከታወቀ በሁዋላ ኮንዶም መጠቀም ጀምረሻል ወይ ለሚለው ጥያቄ አልጠቀምም ያሉ /71/ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ያሉ /55/ናቸው፡፡ በተከታታይ እጠቀማለሁ ያሉ ግን /47/ያህል ናቸው፡፡ ኮንዶምን በእርግዝናው ወቅት ትጠቀማላችሁ ወይ ለሚለው ደግሞ አዎን የሚል ምላሽ የሰጡ /45/ ሲሆኑ አልጠቀምም ያሉት ግን 126/ናቸው፡፡
ባጠቃላይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት መሰረት ከተገኘው ውጤት በመነሳት የደረሱበት ድምዳሜ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ትውልድን ለማፍራት እንዲ ቻል፤ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ሴቶች በተገቢው መንገድ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል እንዲ ችሉ ፤እንዲሁም የኢንፌክሽን መተላለፍ እንዳይኖር ተገቢው ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ምክርና አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል፡፡     

Page 8 of 394