Administrator

Administrator

የአለማችን ቢሊየነሮችን የሃብት ደረጃ በማውጣት በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤ የ2018 የፈረንጆች ዓመት የአለማችንን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን የ112 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያስመዘገቡት የአማዞን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።
ቤዞስ አምና ከነበራቸው አጠቃላይ ሃብት ዘንድሮ የ39.2 ቢሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሪ ማስመዝገባቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ በአንድ አመት ውስጥ ይህን ያህል የሃብት ጭማሪ በማስመዝገብ በታሪክ የመጀመሪያው የአለማችን ባለጠጋ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ባለፉት 24 አመታት ውስጥ ለ18 ጊዜያት የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ሆነው የዘለቁት የማይክሮሶፍቱ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ ዘንድሮ 90 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ይዘው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያሉ ሲሆን የታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ መስራች ማርክ ዙክበርግ በ71 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አምስተኛው የአለማችን ቢሊየነር ሆኗል፡፡
የአመቱ የተጣራ ሃብታቸው 3.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የተነገረላቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አምና ከነበሩበት የሃብት ደረጃ በ222 ደረጃዎች ዝቅ ብለው 766ኛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አለማችን ዘንድሮ ከመቼውም በላይ በርካታ ቢሊየነሮችን ማፍራቷን የጠቆመው ፎርብስ፤አምና 2 ሺህ 43 የነበረው የቢሊየነሮች ቁጥር ዘንድሮ ወደ 2 ሺህ 208 ከፍ ማለቱንና የአለማችን ቢሊየነሮች ጠቅላላ ሃብት ድምር አምና ከነበረበት የ7.7 ትሪሊዮን ዶላር ጭማሪ በማድረግ ዘንድሮ 9.1 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጧል፡፡
ከሙስና ጋር በተያያዘ ባለሃብቶቿን ስታስር የከረመቺውን የሳኡዲ አረቢያ ባለሃብቶች በዘንድሮው የባለጠጎች መዝገብ ውስጥ አለማካተቱን ያስታወቀው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤ ባለፈው አመት በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተው የነበሩ 10 የሳኡዲ ቢሊየነሮችን ስም ከዝርዝሩ መፋቁን አመልክቷል፡፡
ከሳኡዲ የሙስና ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ከተፋቁት ባለጠጎች መካከል አምና 18.7 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት የነበራቸው ልኡል አልዋሊድ ቢን ታላል እና 8.1 ቢሊዮን ዶላር የነበራቸው ሼክ ሙሀመድ ሁሴን አል አሙዲን ይገኙበታል፡፡

 

እንግሊዝ ናይጀሪያውያን እስረኞችን ወደ አገራቸው ልካ የእስር ጊዜያቸውን እንዲጨርሱ ለማድረግ፣በአገሪቱ ግዙፍ ወህኒ ቤት የምታስገነባበት 700 ሺህ ፓውንድ ያህል በጀት መያዟን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ እንግሊዝ ኪሪኪሪ በሚባለውና በሌጎስ የሚገኘውን የናይጀሪያ ትልቁን ወህኒ ቤት ለማስፋፋት ማቀዷን የጠቆመው ዘገባው፤ ሁለቱ አገራት ከ4 አመታት በፊት በፈጸሙት እስረኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት መሰረት እስረኞች ወደ አገራቸው ገብተው እንዲታሰሩ የማድረግ ሃሳብ መያዙንም አመልክቷል፡፡
በ2016 የፈረንጆች አመት ብቻ 320 ናይጀሪያውያን በተለያዩ የወንጀል ክሶች ቅጣት ተጥሎባቸው በእንግሊዝ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የእስር ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፤ በእንግሊዝ ከሚገኙ የሌሎች አገራት እስረኞች ናይጀሪያውያን 3 በመቶውን እንደሚሸፍኑም አስታውሷል፡፡

ከአመታት በፊት በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፍ የነበረው የአሜሪካው ኩባንያ ብላክቤሪ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቼን የቅጂ መብት በመጣስ ተጠቅሞብኛል ሲል በታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ኩባንያ በፌስቡክ ላይ ክስ መመስረቱ ተነግሯል፡፡
ፌስቡክ ፈጠራዎቼን በመስረቅ በዋትሳፕና በኢንስታግራም አፕሊኬሽኖቹ ላይ ተጠቅሞብኛል ሲል ክስ የመሰረተው ብላክቤሪ፤ከአመታት በፊት አብረን ልንሰራ ተስማምተን ነበር፣ ውሉን አፍርሶ ፈጠራዎቼን ተጠቅሞብኛል ብሏል- ቢቢሲ እንደ ዘገበው፡፡
ብላክቤሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽያጩ እየቀነሰና ተወዳዳሪነቱና ተወዳጅነቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከ2 አመታት በፊት ስማርት ፎን ማምረት ማቆሙን የጠቆመው ዘገባው፤ባለፈው አመትም በኖክያ ላይ ተመሳሳይ የቅጂ መብት ጥሰት ክስ መስርቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡

አንድ በወታደሮች ካምፕ የመዝናኛ ክበብ ዙሪያ የተፃፈ ሐተታ የሚከተለውን ቀልድ ነጥቧል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ የመኮንኖች ክበብ ውስጥ ከተራ ወታደር እስከ ጄኔራሎች ድረስ እየተዝናኑ ሳሉ፣ የዕንቆቅልሽ መሰል ጥያቄና መልስ ተጀመረ፡፡
የጨዋታ መሪው፤
“ለመሆኑ ወሲብ (የአልጋ ላይ ግንኙነት) ስንት ፐርሰንቱ ፍቅር ነው? ስንት ፐርሰንቱስ ሥራ ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
መኮንኖቹ እንደየ ማዕረግ ደረጃቸው ይመልሱ ጀመር፡-
ጄኔራሉ:- “ዘጠና ከመቶው ፍቅር፣ አሥር ከመቶው ሥራ ነው” አሉ፡፡
ኮሎኔሉ፡- “በእኔ ግምት ሰማኒያ ከመቶው ፍቅር ነው፡፡ ሃያ ከመቶው ሥራ ነው፡፡” አሉ፡፡
ሻለቃው ቀጠሉ፡- “ለእኔ እንደሚሰማኝ ደግሞ ወሲብ ሰላሳ በመቶው ሥራ፤ ሰባ በመቶው ፍቅር ነው”
ሻምበሉ ደግሞ፤
“እኔ በበኩሌ አርባ በመቶው ሥራ ነው እላለሁ፡፡ ስልሳ በመቶው ግን ፍቅር ነው፡፡”
መቶ አለቃው ጥቂት ስሌት ሠርተው፤
“እኔ ደግሞ ወሲብ ሃምሳ በመቶው ፍቅር፣ ሃምሳ በመቶው ሥራ ነው እላለሁ”
አለ፡፡
ሃምሳ አለቃው ተነሳና፣
“የእኔ ከሁላችሁም ይለያል፡፡ ወሲብ አርባ በመቶው ፍቅር፤ ስልሳ በመቶው ሥራ ነው” አለ፡፡
አሥር አለቃው፤
“ሰላሳ በመቶው ፍቅር ነው፡፡ ሰባ በመቶ ደግሞ ሥራ ነው” አለ፡፡
ይሄኔ ተራ ወታደሩ እጁን አወጣ፡፡
ዕድል ተሰጠው፡፡
“እኔ ከሁላችሁም አልስማማም፤ ለእኔ ወሲብ መቶ በመቶ ፍቅር ነው” አለ፡፡
ጄኔራሉም፣ ኮሎኔሉም፣ ሻለቃውም አጉረመረሙ፡፡
“እኮ ምክንያትህን አስረዳና?” አሉት፡፡
ተራ ወታደሩም፤
“ጌቶቼ፤ ወሲብ ሥራ ቢኖርበት ኖሮ ለእኛ ትተውልን ነበር!”
* * *
አስተሳሰባችን የልምዳችን፣ የትምህርታችን የተፈጥሮአችን ተገዢ ነው፡፡ ልምዳችን የቅርብ የሩቁን የማስተዋልና በትውስታችን ቋት ውስጥ የማኖር ውጤት መዳፍ ሥር ያለ ነው፡፡ ትምህርታችን ትምህርት የሚሆነው ወደ ዕውቀት መለወጥ ሲጀመር ነው! ዕውቀታችን ወደ የብልህ-ጥበብ (wisdom) የሚለወጠው አንድም በዕድሜ፣ አንድም የሚዛናዊ አመለካከት ባለቤት ስንሆን ነው! ሚዛናዊነት የጎረኝነት (Positionality) ተቃራኒ ነው፡፡ የወገናዊነት ፀር ነው! ወገናዊነት የኢ-ፍትሐዊነት መቆፍቆፊያ ሰንኮፍ ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊነት ከማናቸውም ህገ-ወጥ ድርጊት ጋር፤ አንዱን-ሲነኩት-ሌላው ይወድቃል ዓይነት ግንኙነት አለው፡፡ (Domino-effect እንደሚባለው፡፡) ለችግሮች የምንሰጠው አጣዳፊ መፍትሔዎች ወዴት ያደርሱናል? ብሎ መጠየቅ ትልቅ መላ ነው፡፡ “የፊተኛውን ባልሽን በምን ቀበርሽው- በሻሽ፤ ለምን- የኋላኛው እንዳይሸሽ” የሚለውን ማውጠንጠን አለብን፡፡ በየለውጡ ውስጥ የአንድ የአገራችንን ገጣሚ ስንኞች ሥራዬ ብሎ ማዳመጥ ጠቃሚ ነው፡-
“ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ከምሮ እየናደ፣ ንዶ እየከመረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ
ጀመረ”
መውጫ መውረጂያችን በሥጋት የታጠረ ከሆነ፤ ከመረጋጋት ጋር እንራራቃለን፡፡ ያለ ሥጋት የምንጓዘው ለህሊናችን ታማኝ የሆንን እንደሆነ ነው! በስሜታዊነት ምንም ዓይነት ድርጊት መፈፀም የለብንም፡፡ ፅንፈኛ ሆነንም ማሰብ የለብንም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አሉታዊነትን
(Negativism) በፍፁምነት ማስወገድ አለብን፡፡ ለረዥም ጊዜ ሰቅዞ የያዘንን ሁሉ፣ በተቃውሞ በጋራ ከመጠርነፍ ዕምነት የግድ መላቀቅ ይኖርብናል፡፡ ነጋዴውን ሌባ ነው ብሎ አስቦ መጀመር፣ ባለሙያውን ከእኛ ጋር ካልሆነ ባለሙያ አይደለም ብሎ ማሰብ፣ ሰውን አላግባብ መፈረጅ፤ የእኔ ቦይ ውስጥ ካልፈሰስ የተሳሳተ ሰው ነው ብሎ መገምገም… እኒህና እኒህን መሰል አካሄዶች ሁሉ ከፀፀት አያፋቱንም!
ዛሬም ነገረ-ሥራችንን እንመርምር፡፡ ማህበረሰብ ለአመክንዮ እንጂ ለመላምት/ለግምት መጋለጡ ደግ አይደለም፡፡ ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ አሊያም ፓርቲያዊ ግልፅነት (Transparency) ወደድንም ጠላንም አስፈላጊ ነው! አለበለዚያ ዳፍንተኝነት (Obscurantism) ይወርረናል፡፡ ህብረተሰብ የሀገሪቱ አካሄድ ውሉ እንዳይጠፋበት ማድረግ ያለበት አመራሩ ነው፡፡ አመራር ተመሪውን አይከተልም፡፡ ያ ከሆነ ጭራዊ እንቅስቃሴ ወይም የድሃራይ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል- Tailist movement እንዲል መጽሐፍ፡፡ ደራሲ በተደራሲ ከተመራ፣ ገጣሚው በአጨብጫቢ-ታዳሚ ከተመራ፣ ዋናው ባለሙያ በበታቹ ተፅዕኖ ውስጥ ከወደቀ፣ መሪው በተመሪው እጅ ከተያዘ የመንተብ- decadence አንድ ድረጃ ነው! ከዚህ ተከትሎ ምርጫ ማጣት ይመጣል፡፡ የሚፈልገው ነገር ሁሉ ጭጋግ ውስጥ ይወድቅና አጥርቶ ማየት ይሳነናል፡፡ የቱን ልያዝ ዓይነት ድንግዝግዝ ውስጥ እንጨፈቃለን፡፡
ያኔ ነው እንግዲህ “ከሞትና ከህይወት የቱ ይሻልሃል?” ቢባል ሲያስብ ዘገየ፤ የሚለው ተረት ጎልቶ የሚነበበው! ከዚህ ይሰውረን!!

 

በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት በመስጠትና የሰሉ ሂሳዊ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ ሰሞኑን መታሰራቸው ታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህሩና ጦማሪው አቶ ስዩም ተሾመ የመታሰራቸው ጉዳይ ከትናንት በስቲያ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተነገረ ሲሆን ስለ ሁኔታው ለማወቅ ወደ ቅርብ ወዳጃቸው በመደወል መታሰራቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ስዩም ተሾመ፤ ሐሙስ ጠዋት 4 ሰዓት ገደማ ወሊሶ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፀጥታ ኃይሎች መወሰዳቸው የታወቀ ሲሆን ምንጮች በኮማንድ ፖስቱ ሳይታሰሩ እንዳልቀረ ቢገምቱም ለማረጋገጥ ግን አልተቻለም፡፡
በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችቶችን በድፍረት በመሰንዘር የሚታወቁት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ፤በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ጋር በተያያዘ ትንተናዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች በመስጠት ትኩረት ስበው ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 2025 ለማሳካት ለያዘችው ሁሉንም ዜጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ የሚውል የ375 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ ማግኘቷ ታውቋል፡፡
ከዓለም ባንክ ሰሞኑን የተገኘው የገንዘብ ብድር በተለይ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ውስጥ ለአንድ ሚሊዮን የገጠር ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ለተያዘው እቅድ አጋዥ ይሆናል ተብሏል። በአጠቃላይ የ5 ዓመቱ ፕሮጀክት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅም ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል የማምረት አቅም እንዳላት በመግለጫው የተጠቆመ ሲሆን ፕሮጀክቱም በቁርጠኝነት ከተሰራ ስኬታማ ይሆናል ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ ካላት ሃይድሮ ኤሌክትሪክ አቅም ባሻገር ከፀሐይ፣ ከንፋስና ከጂኦተርሚናል ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም እንዳላት የዓለም ባንክ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት 10 ዓመታት ውጤታማ የኤሌክትሪክ ማዳረስ ፕሮግራም ዘርግቶ በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞችንና መንደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተመልክቷል- በመግለጫው፡፡

ከግንባር ቀደም ዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ዎርልድ ሬሚት፣ ኒውዮርክ የሚገኙ 9 ሺህ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በፈጣንና ዝቅተኛ ዋጋ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ ጊዜ ውድ በሆነበት የአሜሪካ (የውጭ አገር) ኑሮ፣ ደንበኞች ወደ አንድ ተቋም (ባንክ ወይም ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች) በአካል መሄድ ሳይኖርባቸው በማንኛውም ቦታና ሰዓት፣ የድርጅቱን ድረ - ገፅ ወይም ሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ ይችላሉ ብሏል፡፡
ዎርልድ ሬሚት በኒውዮርክ ግዛት የሚኖሩትን ጨምሮ ከ50 በላይ በሚሆኑ አገራት የሚኖሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዜቶች የሚልኩትን ገንዘብ፣ እዚህ ያሉ ገንዘቡ የተላከላቸው ሰዎች በመላ አገሪቷ ከሚገኙ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ቅርንጫፎች እንዲወስዱ ከባንኩ ጋር መዋዋሉን ገልጿል፡፡
የገንዘብ አስተላላፊው ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ኃላፊ ሻሮን ኪንያንጁይ፣ በዎርልድ ሬሚት በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች ከፍተኛ ዕድገት እያሳዩ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችም ሆኑ ተቀባዮቹ ከዎርልድ ሬሚት ጥራት ያለው አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ማረጋገጣችንን እንቀጥላለን፡፡ ኒውዩርክን ያካተተ አገልግሎት መጀመርና የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደ መረባችን መግባት ወደ ኢትዮጵያ ሃዋላ ለሚልኩ ሰዎች መልካም ዜና ነው ብለዋል፡፡
በወጣት ሶማሊያዊ ኢንተርፕረነር እስማኤል አህመድ እ.ኤ.አ በ2010 የተመሰረተው ዎርልድ ሬሚት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ የጀመረው በተመሰረተ በዓመቱ በ2011 እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫው፣ ኒውዮርክ በመጨመሩ አሜሪካ የዎርልድ ሬሚት ትልቁ የገንዘብ መላኪያ ገበያ እንደምትሆንና ኩባንያው በ2017 ከአሜሪካ የሚላከው ገንዘብ 200 ፐርሰንት ዕድገት ማሳቱን አመልክቷል፡፡ ዎርልድ ሬሚት ከFacebook, spotify, Netfliy እና Slack እንዲሁም ቀዳሚ ኢንቨስተሮች ከሆኑት Accel እና TCV 200 ሚሊዮን ዶላር ማግነቱን ገልጿል፡፡ ዋና መ/ቤቱ በለንደን ሲሆን የአሜሪካ ዋና መ/ቤት በዴንቨር፣ ክልላዊ ቢሮዎች ደግሞ በካናዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በፊሊፕንስ፣ በጃፓን፣ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ እንዳሉት መግለጫው አመልክቷል፡፡

“የእስረኞች መለቀቅ በበጎ የሚታይ ነው፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግን አሳሳቢ ነው” - የተመድ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

በሁከትና ብጥብጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን የገለጸው ኮማንድ ፖስቱ፤ በሀገሪቱ አሁን የሚደረገው ተቃውሞ የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ መምጣቱንና የመንግስት ስልጣን በሃይል ለመያዝ የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለው አስታውቋል፡፡
ከሰኞ የካቲት 26 እስከ ረቡዕ የካቲት 28 በኦሮሚያ በተለይ ከአዲስ አበባ አምቦ ነቀምት ባለው አቅጣጫ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወሊሶ ጅማ መስመር፣ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ተዘግተው መሰንበታቸውን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ጠቁመው፤ በአድማ የሰነበቱ ከተሞች ከረቡዕ አንስቶ በአብዛኛው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
የንግድና የትራንስፖርት አድማ በተደረጉባቸው የኦሮሚያ ከተሞች በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና ፋብሪካ መቃጠሉን የጠቆመው ኮማንድ ፖስቱ፤ በ17 የፀጥታ ኃይሎችም ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ፣ የሆስፒታልና የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ፤ ከአድማና ተቃውሞው ጋር ተያይዞ በተለያዩ ከተሞች 6 ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
በሰሞኑ የሀገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፤ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይል ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸው፣ እንቅስቃሴውም የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ አራት ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን፣ 10 ያህል ተሽከርካሪዎች መጎዳታቸውን የተናገሩት አቶ ሲራጅ፤ የቀበሌና ወረዳ ጽ/ቤቶች እንደተቃጠሉም ገልፀዋል፡፡ የንብረት ዘረፋና ከጸጥታ ሃይሎች ላይ መሳሪያ የመቀማት ሙከራ መደረጉ የተጠቆመ ሲሆን በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተነግሯል፡፡ ህብረተሰቡ መንግስት ተዳክሟል በሚል የሚናፈሰውን አሉባልታ ማመን እንደሌለበት የገለጹት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፤ መንግስት እንዳሁኑም ተጠናክሮ አያውቅም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያግዛል በሚል የጀመረውን የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት እርምጃ እንደማይገታ ያስታወቁት አቶ ሲራጅ፤ በሌላ በኩል ኮማንድ ፖስቱ ከህብረተሰቡ የሚደርሱትን ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ እንዲሁም በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከየት አካባቢና ምን ያህል እንደሆኑ አልጠቀሱም፡፡
በንግድና ትራንስፖርት የማቆም አድማ ላይ የሰነበቱት አብዛኞቹ የኦሮሚያ ከተሞች ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን በቡራዩና አዳማ አካባቢ ደግሞ በአድማው የተሳተፉ ነጋዴዎች “ህግ አላከበራችሁም” በሚል ንግድ ቤቶቻቸው እንደታሸጉባቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በወልቂጤ ከተማ ሲካሄድ የነበረው አድማ ቆሞ ከሐሙስ ጀምሮ መደበኛ እንቅስቃሴ መቀጠሉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ሰኞ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያው፤ ዜጎቹ ከአዲስ አበባ ውጪ እንዳይጓዙ ያሳሰበ ሲሆን ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በሚገኙ ከተሞች የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውንም አስታውቆ ነበር፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዞይር ራድ አል ሁሴን ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው 37ኛው የኮሚሽኑ መደበኛ ስብሰባ፤ የዓለም ሀገራት የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በቃኙበት ሪፖርታቸው፤ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከ7 ሺህ በላይ እስረኞችን መልቀቋ በበጎ የሚታይ ተቀባይነት ያለው እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፤ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችና ለውጥ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በእውነተኛና ሁሉን ያሳተፈ ውይይትና የፖለቲካ ሂደት ነው ብሏል - የኮሚሽኑ ሪፖርት፡፡
መንግሥትም በቅርቡ በተፈፀሚ የዜጎች ግድያ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን አጣርቶ ለህግ እንዲያቀርብ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል በሪፖርታቸው፡፡

አሜሪካ- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ሩሲያ- በኒውክሌር ማብልያ፣ አረብ ኤምሬትስ- በወደብ አጠቃቀም አተኩረዋል ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ የሦስት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ተቀብላ አስተናግዳለች። የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ የአሜሪካና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች፡፡ ሳምንቱ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው ብለዋል- የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ። ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በንግድ፣ በኢንቬስትመንት፣ በፀጥታና ደህንነት ጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ መወያየታቸውም ታውቋል፡፡ የተባበሩት አረብ ኢምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን፤ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በወደብ አጠቃቀምና እንዲሁም በሰራተኞች አያያዝና ልውውጥ ላይ ሲነጋገሩ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በዋናነት በፀጥታና ደህንነት፣ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ እንዲሁም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በኒውክሌር ግንባታ፣ በኢንቨስትመንት መወያየታቸው ተጠቁሟል፡፡ ረቡዕ አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሠን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚያሳስባቸውና መንግስት የቆይታ ጊዜውን ያሣጥረዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ከቲለርሠን ጋር በቀጠናዊ ፀጥታና ሠላም፣ በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትብብር እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ላይ መነጋገራቸውን ገልፀዋል፡፡ የሠው ህይወት እየቀጠፈ ባለው የፀጥታ ችግር ተነጋግረናል ያሉት ቴለርሠን፤ የዜጎች መብትን ከመገደብ ይልቅ የበለጠ የሚረጋገጥበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ሽግግርን እንደግፈዋለን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሠላማዊ የስልጣን ሽግግር በለጋነት ለሚገኘው የሃገሪቱ ዲሞክራሲ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ በሃገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስታቸው በእጅጉ እንደሚያሣስበው የጠቀሡት ቲለርሠን፤ አሣሣቢ የሚያደርገውም በመሠረታዊ የሠብአዊ መብቶች ላይ ገደብ ስለሚያበጅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይም የሠብአዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው፣ የህግና ስርአት መከበር አስፈላጊ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃዎችን ከመውሠድ እንዲቆጠቡ ተነጋግረናል ብለዋል-ቲለርሰን፡፡ በሃገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች አስፈላጊ መሆናቸውን እንዲሁም፣ ገደቦችን ከማበጀት ይልቅ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር የሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት ጠቃሚ መሆኑን መነጋገራቸውንም አስታውቀዋል። ዜጎችም ለዲሞክራሲ መረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ሂደትን የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ፣ አመፅ ብቻውን መፍትሄ እንደማይሆን በመረዳት፣ በሃገሪቱ የተሻለውን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “ሃገሪቱ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ እንረዳለን” ያሉት ቲለርሠን “ዜጎች ሠላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረብ አለባቸው፤ መንግስትም መብትን ከመገደብ ይልቅ የበለጠ ማስፋት ነው ያለበት” ብለዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቆይታም እንደሚያጥር ተስፋ አደርጋለሁ ያሉት ቲለርሠን፤ “በቆይታው ወቅትም በዜጎች ላይ የሠብአዊ መብት ጥሠት ሊያስከትል ይችላል” የሚለውን ስጋት በሚያስወግድ ሁኔታ ሊተገበር እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡ አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚደረገውን ዲሞክራሲን የማሣደግ ሒደትም እንደምትደግፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ለምን መረጡ? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኛ የቀረበላቸው ቲለርሠን፤ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት 100 ዓመታትን የዘለቀ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም በተለይ በአካባቢ የፀጥታ ጉዳይ ኢትዮጵያ አጋር መሆኗን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ለጋ ዲሞክራሲ ማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ነው ብለዋል፡፡ በቆይታቸውም በዲሞክራሲ ጉዳይ፣ በፀጥታና ደህንነት፣ በኢኮኖሚያዊና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ዙሪያ በሠፊው መነጋገራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ ወታደሮቿን በሠላም አስከባሪነት በመላክ ለቀጠናው ሠላምና ደህንነት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ እንዲሁም ስደተኞችን ተቀብላ ማስተናገዷ ከፍተኛ ዋጋ የሚሠጠው መሆኑን ቲለርሠን በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡ በሣምንቱ መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የዩናይትድ አረብ ኢምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በዋናነት በሁለቱ ሃገራት መካከል ለወደፊቱ በሚኖረው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ወደ ሃገሪቱ አቅንተው ደህንነታቸው ተጠብቆ በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውና መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም አስታውቀዋል፡፡ በተመሣሣይ ከወራት በፊት የጉብኝት ፕሮግራም የተያዘላቸው የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሠርጌ ላቭሮቭም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅትም ሩሲያ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ በኢትዮጵያ ለመገንባት የተስማሙ ሲሆን ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ163 ሚሊዮን ዶላር እዳ ስረዛ ማድረጓም ታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ የአሜሪካ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጉብኝት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ሳምንቱ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው ብለዋል፡፡ የሩሲያና የአሜሪካ አምባሳደሮች በአንድ ሆቴል ማደራቸውን ጠቁመው፤ በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣታቸውም ጉዳይ “የተለየ ምስጢር የለውም፤ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው” ብለዋል። ከተባበሩት አረብ ኤምሬት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተደረገ ውይይት፤ የሶማሊያን ሉአላዊነት በማይነካ መልኩ ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ የ17 በመቶ ድርሻ ኖሯት፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ጋር ለመጠቀም ስምምነት ላይ መደረሱን ዶ/ር ወርቅነህ አስታውቀዋል፡፡ “የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በዋናነት ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ሊጠይቁ አይደለም የመጡት፤ መደበኛ ዲፕሎማሲውን የማጠናከር ስራ ሊሰሩ ነው ጉብኝት ያደረጉት” ያሉት ዶ/ር ወርቅነህ፤ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ውይይትም የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ጉዳይ እንዲሁም ኒውክሌርን ለሰላማዊ ጉዳይ በማዋል ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን አስረድተዋል፡፡

 • “ኮማንድ ፖስቱ የተለጠጠ ሥልጣን ተሰጥቶታል”
    
   ለ6 ወር የሚተገበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ2/3ኛ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን የአዋጁን ድንጋጌዎች ተላልፎ የተገኘ እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል ተብሏል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በ346 ድጋፍ፣በ88 ተቃውሞና በ7 ድምጸ ተአቅቦ ጸድቋል ተብሎ ነበር፡፡ ሆኖም በኋላ ላይ በተሰጠው መግለጫ፤አዋጁ በ395 የድጋፍ ድምጽ ጸድቋል በሚል ተስተካክሏል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተቃወሙት በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ተመራጭ የፓርላማ አባላት መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ፤ የአዋጁን አስፈላጊነት ባብራሩበት ንግግራቸው፤ በዋናነት አዋጁ ትኩረት ያደረገው የፀጥታ ችግሮችን ከመሰረቱ ማድረቅ ላይ ነው ብለዋል፡፡ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ አድማሳቸው እየሰፋ መጥቷል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት፣ በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውሮ የመኖርና ሃብት አፍርቶ የመጠቀም መብትን የሚገድቡ እንቅስቃሴዎች ተበራክተዋል፣ አሳሳቢ ደረጃም ደርሰዋል ብለዋል፡፡
አሁን እየተከሰቱ ያሉ ሁከቶች ኃይል የተቀላቀለበት የሰው ህይወት የሚቀጠፍበት፤ ብሄርን መነሻ በማድረግ ዜጎችንም የሚያፈናቅል ሆኗል ተብሏል። በሌላ በኩል በከተሞች ህገ ወጥ የመሬት ወረራዎች መበራከታቸውንም አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡
አዋጁም እነዚህን ችግሮች ከምንጩ ለማድረቅ ታቅዶ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ከዚህ ቀደም ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለየ ሁኔታ በዋናነት የሚተኮረው የሁከት ጠንሳሾችና አቃጆች ላይ ይሆናል ተብሏል፡፡
ሌላው አዋጁ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሚደረግን ጥረት ማገዝ ላይ ይሆናል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስታዲየሞችና የሃይማኖት ተቋማት የመሳሰሉት አካባቢ የሚፈጠሩ ሁከቶችን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ህገ ወጥ የመሬት ወረራንና ግንባታን እንዲሁም የኢንቨስተሮችን መሬት በህገ ወጥ መንገድ መውሰድን መከላከል ላይ አዋጁ ያተኩራል ተብሏል፡፡
በአዋጁ ማብራሪያ ላይ አስተያየትና ጥያቄ ያቀረቡ በርካታ የምክር ቤት አባላት፤ በተለይ በአዋጁ አፈፃፀም ላይ በየደረጃው ያሉ የክልል የአስተዳደር አካላት ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል ያሉ ሲሆን በተለያዩ አንቀፆች ላይም ማሻሻያዎችን ጠይቀዋል፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን የፓርላማ ተመራጭ ባቀረቡት አስተያየት፤ በነቀምት ከተማ ተከስቶ ከነበረው ግጭትና ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የዞኑ ም/አስተዳዳሪና የነቀምት ከተማ ከንቲባ መታሰራቸውን በመጥቀስ፤ በዚህ አዋጅ አስተዳደሮች ሰለባ ከመሆን ይልቅ አብረው መስራት ቢችሉ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
አንድ አባልም አዋጁ ለ6 ወር ከሚፀና ወደ 3 እና 4 ወር ዝቅ ቢል የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከመስጋት አንፃር አዋጁ በህዝቡ ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው የገለፁ አንድ የምክር ቤት አባል “ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ሊቋረጥ ይችላል” የሚለው ድንጋጌም በመገናኛ ብዙኃን ህልውና ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል” ብለዋል፡፡
እኚሁ የምክር ቤቱ አባል፤ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተመለከቱ ጉዳዮች በመደበኛ ህግ ሊታዩ ይችላል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
“ኮማንድ ፖስቱ የተለጠጠ ሥልጣን ነው የተሰጠው” ያሉ ሌላው የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፤ “ኮማንድ ፖስት ከመሬት ጋር ምን አገናኘው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በህዝባችን ላይ ስጋት የፈጠረው የተለጠጡ መብቶች ለኮማንድ ፖስቱ መሰጠቱ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፤ በአሁኑ ወቅት ሁከትና ብጥብጥ እየተጠራ ያለው በማህበራዊ ሚዲያ መሆኑን በመጥቀስ፤ መገናኛ ዘዴዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ ለኮማንድ ፖስቱ ካልተፈቀደ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትርጉም አይኖረውም ብለዋል፡፡
ከመሬት ጋር በተያያዘ በመደበኛ ህግ፣ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን የክልልና የፌደራል አስተዳደሮች ማስቆም ባለመቻላቸው በአዋጁ መካተቱን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ “ህግና ስርዓት የለም በሚል መሬት የሚወረርበትና ህገ ወጥ ግንባታ የሚከናወንበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ብለዋል፡፡
“የኢንቨስተሮች መሬትን መቀማትም በህግና በስርአት መሆን አለበት ከዚህ ውጪ ያለ እርምጃ በቸልታ አይታለፍም” ብለዋል - ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፡፡
አዋጁ፤ “የወንጀል ተጠያቂነትን” ባስቀመጠበት አንቀፁ፤ “መደበኛ ህግ የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ የተመለከቱ ከአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችና መተባበር ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል” ይላል፡፡   


=========

ከጋዜጣው አዘጋጅ፡-  በፓርላማ የተገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ፤አዋጁ በ346 የድጋፍ ድምጽ መጽደቁን የዘገበ ሲሆን በኋላ ላይ የፓርላማው ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የድጋፍ ድምጹ 395 ነው በሚል ማስተካከያ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም በጋዜጣው ላይ 390 የድጋፍ ድምጽ የሚል የቁጥር ስህተት ተፈጥሯል፡፡ ለዚህም ውድ አንባቢያንን ይቅርታ ልንጠይቅ እንወዳለን፡፡
   

Page 10 of 389