Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62

ከጥቅምት 28 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ የቆየው “ከለርስ ኦፍ ዘ ናይል” ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በአስር ዘርፎች ሽልማት በመስጠት ባለፈው እሁድ ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ተጠናቀቀ፡፡ ብሉ ናይል ፊልም እና ቴሌቪዥን አካዳሚ ከኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ጋር ባዘጋጁት ፌስቲቫል፤ 58 ፊልሞች ተሳትፈው ሽልማቱ ተሰጥቷል፡፡ በተለያዩ ዘጠኝ ዘርፎች ከስድስት የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች እና ፊልሞች “ምርጥ” በመባል ዋንጫ ሲሸለሙ የፌስቲቫሉን ትልቁን ሽልማት “ዘ ግራንድ ናይል አዋርድ“ የናይጄርያው ፊልም አሸንፏል፡፡

በወይዘሮ የውብማር አስፋው የተፃፈውና በሴቶች የትጥቅ ትግል ሚና ላይ የሚያተኩረው “ፊኒክሷ ሞታ ትነሳለች” መፅሐፍ በሚዩዚክ ሜይ ዴይ ኢትዮጵያ የመፃሕፍት ንባብና የውይይት ክበብ ለውይይት ይቀርባል ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በአምስት ኪሎው ብሔራዊ ቤተመዘክር የሚካሄደውን የሦስት ሠዓት ውይይት የሚመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ምሁር ዶር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው፡፡

ላለፉት አስር ዓመታት በየዓመቱ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል የዘንድሮ ዝግጅቱን ማቅረብ ጀመረ፡፡ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴ፣ በጣሊያን የባህል ተቋም እና በጎተ የጀርመን የባህል ተቋም እየቀረቡ ያሉት ፊልሞች ከተለያዩ የአውሮፓ ሐገራት የተውጣጡ ሲሆኑ በነፃ ለሕዝብ እየቀረቡ ናቸው፡፡ባለፈው ሰኞ “The Entrepenur” የተሰኘ የጣሊያንን ፊልም በጣሊያን የባህል ተቋም በማሳየት የተጀመረው ፌስቲቫሉ፤ የፖላንድ፣ የፊንላንድ፣ የፈረንሳይና የዴንማርክ ፊልሞች ያሳየ ሲሆን ዛሬ በ11 እና በ1 ሰዓት የአየርላንድ እና የኔዘርላንድ ፊልሞች በጣሊያን የባህል ተቋም ያሳያል፡፡ 

ፀሐፊው የሐገር ባለውለታ ያሏቸው ኢትዮጵያውያን ታሪኮች የተካተቱበት “ያልተዘመረላቸው” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በመጽሐፉ ታሪካቸው ከተፃፈላቸው መካከል ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ፣ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ሮማነወርቅ ካሳሁን፣ አቤ ጉበኛ፣ ወርቁ ማሞ፣ ደበበ ሰይፉ እና ገብረክርስቶስ ደስታ ይገኙበታል፡፡ በፍፁም ወልደማርያም የተዘጋጀው ባለ 273 ገፆች መጽሐፍ ዋጋው 45 ብር ነው፡፡

“የአባታችን ጓዳ” በሚባል ድርጅት ለሚረዱ ህፃናት ገቢ ማሰባሰቢያ “ዋትስ አውት” ያዘጋጀው ባዛር ትናንት ተከፈተ፡፡ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ክፍት ሆኖ በሚቆየው ባዛር፤ ልዩ ልዩ የጌጣ ጌጥ እና የእደ ጥበብ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ 25 ድርጅቶች ይሳተፉበታል፡፡ “የአባታችን ጓዳ” የተባለው የበጎ አድራጎት ተቋም በየቀኑ ከ150 በላይ ህፃናትን በመመገብ የሚሰራ ነው፡፡ ባዛሩ ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአበባ ግርማይ ወልደ ሥላሴ የተፃፈው “መውስቦ” የትግርኛ ልቦለድ መፅሐፍ ለንባብ የበቃ ሲሆን በመጪው ረቡዕ አዲስ አበባ በሚገኘው ራስ ሆቴል ከቀኑ 10፡30 እንደሚመረቅ ፀሐፊዋ አስታወቁ፡፡ መጽሐፉ ነሐሴ 15 ቀን ሊመረቅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በእለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በማረፋቸው ምርቃቱ ተሠርዟል፡፡ የዛሬ ሁለት ወር በመቀሌው “ሚላኖ ሆቴል” የተመረቀውና በድጋሚ በራስ ሆቴል የሚመረቀው የትግርኛ ልቦለድ፤ 200 ገፆች ያሉት ሲሆን ለሀገር ውስጥ በ40 ብር ለውጭ ሐገራት ደግሞ በ8 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡

ሲድኒ ሼልደን “The Sands of Time” በሚል በእንግሊዝኛ የፃፈው መጽሐፍ በሙሉ ቀን ታሪኩ “ጦሰኛው ማፍያ” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ሰሞኑን ለሽያጭ ቀርቧል፡፡ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ያሳተመውን ልብ ሰቃይ ልቦለድ እያከፋፈለ ያለው ዩኒቲ መፃሕፍት መደብር ነው፡፡ መጽሐፉ ካሁን ቀደም “እጣ ፈለግ” ተብሎ መተርጎሙ ይታወሳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በሰውነት ማጎልመሻ ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ተንተርሶ የተዘጋጀው “በዘመናዊ አሰራር ሰውነትን መገንባት” መጽሐፍ ለንባብ የበቃ ሲሆን በ30.50 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ከመጽሐፉ ገፆች አብዛኞቹ በሥዕላዊ መግለጫዎች የተሸፈነውን መፅሐፍ ያዘጋጀው ኤፍሬም ታዬ ነው፡፡

ባክስትሪት ቦይስ ከሰባት ዓመታት መራራቅ በኋላ በድጋሚ የሙዚቃ ቡድናቸውን በማቀናጀት መስራት ጀመሩ፡፡ ለ20 ዓመታት አብረው የሰሩት “ባክስትሪት ቦይስ” ሰባተኛ አልበማቸውን በመስራት ላይ ሲሆኑ በ2013 ለገበያ እንደሚበቃ አስታውቀዋል፡፡ በ1990ዎቹ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ እውቅና የነበራቸው “ዘ ባክስትሪት ቦይስ” ሰሞኑን “ክሪስማስ ታይም ኤጌን” የተባለ አዲስ ነጠላ ዜማቸውን ለቅቀዋል፡፡ የሙዚቃ ቡድን አባላቱ ለአዲሱ አልበም ስራ በለንደን በሚገኝ መኖርያቸው መሰባሰባቸውን የገለፀው “ዲጂታል ስፓይ” የሚሰሯቸው ሙዚቃዎች ልዩ የሙዚቃ ስልቶችን በማቀናበር እንደሚሆን እንደተናገሩ እና የራፕ እና የሮክ ስልት እንዳልሆኑ ማስታወቃቸውን አትቷል፡፡

የ18 ዓመቱ ጀስቲን ቢበር እና የ20 ዓመቷ ሴሊና ጎሜዝ ከሳምንት በፊት የፍቅር ግንኙነታቸውን በማቋረጥ መለያየታቸውን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ ባለፈው ሳምንት ሴሊና ጎሜዝ በሁለቱ መካከል የነበረው ግንኙነት እጅግ እየተወሳሰበ መምጣቱንና ጀስቲን ቢበር ለፍቅራቸው እንደማይታመን መጠርጠሯን በመግለፅ ለመለያየት ቀድማ መወሰኗን “ዘ ፒፕል” መጽሔት ዘግቧል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሆሊውድን ትኩረት ስቦ የቆየው የሁለቱ ታዳጊዎች የፍቅር ግንኙነት ንፋስ የገባበት በስራቸው ፕሮግራም አለመጣጣም ሳይሆን አይቀርም ብሏል - “ኢኦንላይን” ባሰራጨው መረጃ፡፡

ቶኒ ብራክስትን የተዘፈቀችበት የ50 ሚሊዮን ብር እዳ ንብረቷን እያሸጠባት መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ከ1989 ጀምሮ በሙዚቃ ሙያዋ ያሳለፈችው ሙዚቀኛዋ ፤ በዘፈን ደራሲነት፣ በፕሮዱዩሰርነትና በተዋናይነት ከፍተኛ ስኬት እና ክብር ያገኘች ስትሆን 6 የግራሚ፤ 7 የአሜሪካን ሚዩዚክ አዋርድ እና 5 የቢልቦርድ ሽልማቶችን ሰብስባለች፡፡