“ቆንጆዎች” የሥዕል ኤግዚቢሽን ሐሙስ ይከፈታል
የሠዐሊና መምህር ዘርዓዳዊት አባተ የሥዕል ስራዎች የሚቀርቡበት አውደርዕይ የፊታችን ሃሙስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም እንደሚከፈት ተገለፀሰዓሊው የሚያቀርቡት የሥዕልና ቅርጻቅርጽ አውደርእይ እስከ ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ሠዐሊው ካሁን ቀደም ለአስራ ሰባት ጊዜ ያህል አውደርእዮችን ያዘጋጀ ሲሆን ያሁኑን አውደርዕይ የሀገር ባለ ውለታ ጀግኖችን በማሰብ እንዳዘጋጀው ተናግሯል፡፡
“ሴት የላከው” ፊልም በድጋሚ ይመረቃል
በደራሲ ኢንጂነር ግርማይ ኃይል ተፅፎ የተዘጋጀው “ሴት የላከው” የ97 ደቂቃ ፊልም ባለፈው ማክሰኞ የተመረቀ ሲሆን በእለቱ በነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል መዋዥቅ የተነሳ ፊልሙ ሙሉ በሙሉ ባለመታየቱ በድጋሚ እንደሚመረቅ ቶኔቶር ፊልም ፕሮዳክሽን አስታወቀ፡፡ በእለቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር መሰል ችግር ስላልነበር ሙሉ ፊልሙን አሳይተናል ያሉት የፕሮዳክሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግርማይ ኃይሌ፣ፊልሙ በታየባቸው ሶስት ቦታዎች ግን በኤሌክትሪክ ሃይል መዋዠቅ የተነሳ ለ58 ደቂቃ ብቻ ለማሳየት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
“የእማዋዬ እንባ” ረዥም ልብወለድ ለንባብ በቃ “አነበብካት” እየተነበበ ነው
የደራሲ ገስጥ ተጫኔ ስድስተኛ የልቦለድ ሥራ የሆነው “የእማዋዬ እንባ” ለንባብ በቃ፡፡ “የመከራ ዘመን ወግ” የሚል ስያሜ የነበረው መፅሃፉ፣ባለሙያዎች አስተያየት ከሰጡ በኋላ ያሁኑ ርዕስ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበርና በብርሃንና ሰላም ድርጅት የሕትመት ተዘዋዋሪ ሂሳብ የጋራ አስተዳደር የታተመው መጽሐፉ፣278 ገፆች ያሉት ሲሆን በ45 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
ቢዮንሴ እና ሌዲ ጋጋ ነጠላ ዜማ ሊያወጡ ነው
ታዋቂዎቹ አቀንቃኞቹ ቢዮንሴ ኖውልስ እና ሌዲ ጋጋ ከሶስት ዓመት በኋላ በጋራ ነጠላ ዜማ ሊያወጡ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ አርቲስቶቹ ለሚሰሩት አዲስ ነጠላ ዜማ ስቱድዮ መግባታቸውን የዘገበው “ዘ ዋየር”፤ ተመሳሳይ የጆሮ ጌጦችን ማድረግ መጀመራቸውንና ይሄንኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲያሰራጩ መቆየታቸውን አመልክቷል፡፡ ነጠላ ዜማው በቀጣይ ወር ለገበያ እንደሚበቃ የሚጠበቀው የሌዲ ጋጋ ‹‹አርት ቶፕ› የተሰኘ አዲስ አልበም መሪ ዜማ እንደሚሆንም ታውቋል፡፡ ሁለቱ የፖፕ ሙዚቃ ንግስቶች ከሶስት ዓመት በፊት “ቴሌፎን” በተባለው ነጠላ ዜማ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው የነበረ ሲሆን በሌዲ ጋጋ ግጥም በተሰራው “ቴሌፎን” የተሰኘ ዜማ ላይ ቢዮንሴ በአጃቢነት አቀንቅናለች፡፡ ዜማው በመላው ዓለም 7.4 ሚሊዮን ዲጂታል ቅጂዎች እንደተሸጡ ይታወቃል፡፡
የጀምስ ቦንድን ፊልም የሰራው ኤምጂኤም ከኪሳራ እየወጣ ነው
ከሁለት ዓመት በፊት በኪሳራ የመሸጥ አደጋ አንዣቦበት የነበረው ኤምጂኤም የፊልም ስቱዲዮ ከኪሳራ እያገገመ እንደሆነ “ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር” ዘገበ፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት የመጨረሻ ሶስት ወራት ላይ ለእይታ የበቃውና ከቢሊዮን ዶላር በላይ ያስገባው ሃያ ሶስተኛው የጀምስ ቦንድ ፊልም “ስካይ ፎልስ” የኤምጂኤም ስቱዲዮን ከኪሳራ ለማውጣት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተገልጿል፡፡
በአዲሱ ዓመት ምርጥ ፊልሞች ይጠበቃሉ
በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በርካታ ምርጥ ተዋናዮችን ያሳተፉ ምርጥ ፊልሞች የዓለም ሲኒማዎችን እንደሚያጥለቀልቁ ተገለፀ፡፡ አክሽን ፊልሞች፤ በ3ዲ በድጋሚ የተሰሩ እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልሞች ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በተከታታይ እንደሚለቀቁ ይጠበቃል፡፡ ከፊልሞቹ መካከልም ብሩስ ዊልስ የሰራው “ጂአይ ጆ ሪታሊዬሽን”፣ የቶም ክሩዝ “ቶፕ ገን” እና የስፒልበርግ “ጁራሲክ ፓርክ” በአዲስ መልክ በ3ዲ፤ “አይረን ማን ሶስት” እና “ስታር ትሬክ ኢንቱ ዳርክነስ› ይጠቀሳሉ፡፡
‹‹ሌስ ሚዝረብልስ›› ከሙዚቃዊ ድራማ ፊልሞች በገቢ ተሳክቶለታል
በዩናይትድ ኪንግደም የተሰራው እና ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ መታየት የጀመረው ‹‹ሌስ ሚዝረብልስ›› የተባለው ሙዚቃዊ ድራማ በሰሜን አሜሪካ በዘርፉ ከፍተኛውን ገቢ እንዳስገባ ዘ ጋርድያን ዘገበ፡፡ ‹‹ሌስ ሚዝረብልስ›› ለእይታ በበቃ በ13 ቀናት በሰሜን አሜሪካ ብቻ 100 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት አዲስ ክብረወሰን እንዳስመዘገበ ታውቋል፡፡
ለምሩፅ ገቢ ማሰባሰቢያ ይካሄዳል
ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ህይወት ለመደገፍ የፊታችን ሐሙስ በሸራተን አዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጀ፡፡
ከመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ከባለሃብቶችና ከተለያዮ ባለሙያዎች የተዋቀረ አንድ ኮሚቴ ከቢ.ኤም.ዲ ፕሮሞሽን ጋር ገቢ ማሰባሰቡን ሲያስተባብር ቆይቷል፡፡ በሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ የሚካሄደውን ፕሮግራም በ450ሺ ብር አቶ አብነት ገ/መስቀል ብር ስፖንሰር ማድረጋቸው ሲገለፅ ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ ክቡር ዶ/ር ሼህ መሀመድ አሊአል-አላሙዲን፤ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ አትሌቶችና የሚመለከታቸው አካላት በሚገኙበት ልዩ ዝግጅቱ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለችበት 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 1 ሳምንት ቀረው
በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የዛሬ ሳምንት በጆሃንስበርግ ሶከር ሲቲ ስታድዬም ደቡብ አፍሪካ ከኬፕቨርዴ በሚያደርጉት ጨዋታ የሚጀመር ሲሆን ዘንድሮ በቡድኖች መካከል ተመጣጣኝ ፉክክር እንደሚታይ ተጠብቋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ5 ከተሞች በሚገኙ አምስት ስታድዬሞች ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እስከ 53.3 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ሽያጭ ከ340ሺ በላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በ200 አገራት የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን ከ700 በላይ የሚዲያ ተቋማት ፈቃድ አግኝተው ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ለውድድሩ ሽፋን ለመስጠት ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሰኞ ከቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በኳታር ዱሃ ላይ 1-1 የተለያየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ከታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ጋር አዲስ አበባ ላይ ሶስተኛውን የወደጅነት ጨዋታ አደረገ፡፡
በ2012 የፊፋ ክዋክብት ምርጫ የ“ምድብ 3” ሚና ምን ይመስላል
በሳምንቱ መጀመርያ ፊፋ የ2012 የእግር ኳስ ኮከቦችን በየዘርፉ የሸለመ ሲሆን ሊዮኔል ሜሲ ለአራተኛ ጊዜ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ በመመረጥ የመጀመርያው ተጨዋች ሆነ፡፡
ሊዮኔል ሜሲ የወርቅ ኳሱን ሊሸለም የበቃው የፊፋ አባል አገራት የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና አምበሎች ከሰጡት ድምፅ 41.6 በመቶውን በማሸነፍ ነው፡፡ክርስትያኖ ሮናልዶ በ23.6 በመቶ እንዲሁም ኢኒዬስታ በ10.91 በመቶ ድምፅ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ወስደዋል፡፡ የስፔን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቪሰንቴ ዴልቦስኬ የ2012 ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ሲመረጡ በ2012 የዓለም እግር ኳስ ምርጥ 11 ቡድንን የስፔኑ ላሊጋ አምስት ከሪያል ማድሪድ፤ አምስት ከባርሴሎና እንዲሁም 1 ከአትሌቲኮ ማድሪድ በማስመረጥ ተቆጣጥሮታል፡፡