Saturday, 24 September 2011 10:18

እባብና መሰላሉ

Written by  ሌሊሣ
Rate this item
(2 votes)

መጀመሪያ ጨዋታ መሆኑን
መተማመን አለብን፡፡ ለነገሩ እናንተ ባታምኑበትም፤ እኔ     እስካመንኩበት ድረስ - ጉዳዬ አይደለም፡፡ እኔ አጫዋቹ ነኝ - ፀሐፊው፤ እናንተ የጨዋታው ተመልካቾች ናችሁ - አንባቢያን፡፡ ገፀ - ባህሪው ተጫዋቹ ነው፡፡ ገፀ - ባህሪውን በመረጥኩለት ጨዋታ ውስጥ እንዲጫወት ያደረኩት፣ መጫወቻዬ ስለሆነ አይደለም፡፡ ገፀ ባህሪው ጨዋታውን እንዲያሸንፍ እፈልጋለሁ፡፡ ማሸነፍ የሚቻል ጨዋታ መስራቴን የማረጋግጠው በገፀባህሪው ድል አማካይነት ስለሆነ፡፡
***

እስጢፋኖስ ህይወትን ማስተካከል እንደሚቻል ያምናል፡፡ የተወለደው ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ ነው፡፡ ህይወትን ማስተካከል የሚቻለው ስህተት ባለመስራት እንደሆነ ያምናል፡፡ እምነቱ በህይወቱ ላይ ሰርቶ ስላየው ማመን ብቻ ሳይሆን ማወቅ ከጀመረ ቆይቷል፡፡
እናቱ ከልጅነቱ ጀምሮ የምትነግረው ነገር እያደገ ሲሄድ ሳይሆን ልጅ በነበረበት ወቅት ነበር የተሰማው፡፡ ..የተማረና የበላ.. ወድቆ አይወድቅም ትለዋለች፡፡ ሰሌዳ ላይ የተፃፈለትን ተማረ፤ ትሪ ላይ የቀረበለትን እንክት አድርጐ በላ - አደገ፡፡ መሰላል አከለ፡፡
ዩኒቨርስቲ ውጤት መጥቶለት ሲገባ በውጤቱም ሆነ በገባበት በር አልተደነቀም፡፡ አልተገረመም፡፡ አልደነገጠም፡፡ በደንብ እስካጠና ውጤቱ የሚያደርሰው ሥፍራ ለእሱ ግልጽ ነበር፡፡ ያልተዘራ አይበቅልም፡፡ እንደ ሜዳ አበቦች ሳይዘራ የሚበቅል ነገር የሰው ልጅን አይጠቅምም ብሎ ያስባል፡፡ ትምህርቱን በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆ ስራ ያዘ፡፡ ሁሉም ነገር ከፊቱ ዝግጁ ሆኖ ቀረበለት፡፡ የተባበሩት መንግስታት መስሪያ ቤት ውስጥ የምትሰራ አብሮ የተማራትን፤ ባህሪዋ እና ፍላጐቷ ከእሱ ጋር የሚጣመረው ሉላን አገባ፡፡ ህይወት ለጥ እንዳለ መስክ ከፊትለፊቱ ተዘርግቷል፡፡ ሚስቱን ጠዋት ስሞ ይወጣል፡፡ ማታ ከስራ መልስ ስሟት ይገባል፡፡ ሉላም በባህሪዋ እንደሱ ናት፡፡ ሁለቱ አንድ ሆኑ፡፡ ውጭ እና ውስጦች፣ አንድ ሆነው የተበየዱ፣ አንደኛው ሲያልቅ ሌላኛው የቱ ጋር እንደሚጀምር የማይታወቅ የጉንጉን ገመዶች፡፡ የጉንጉኑን ጥንካሬ በአገማመዱ መገመት ይቻላል፡፡
(እዚህ ላይ ትረካውን ወይንም ጨዋታውን ቆም እናድርግና የጨዋታውን አይነት እና ህጉን ልንገራችሁ፡፡ ገፀ ባህሪው (እስጢፋኖስ) በየደቂቃው እና በየቀኑ ሁለት አይነት አማራጭ ይገጥመዋል፡፡ አንደኛው አማራጭ ..መሰላል.. ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ እንደ መልካም እድል ከፍ የሚያደርገው፣ የሚያሳድገው... ወደላይ መወጣጫ፡፡ ሁለተኛው፤ እባብ ነው፡፡ ዝቅ የሚያደርገው፣ ቁልቁል የሚጥለው፣ ሲኦል የሚከተው የሚገድለው መውረጃ፡፡ ከሁለቱ አማራጮች አንዱን መውሰድ የገፀ ባህሪዎቹ ፋንታ ነው)
***
እስጢፋኖስ ከልጅቱ ጀምሮ ስሙን አሳጥረው ሲጠሩበት አይወድም፡፡ ..እስቲቭ.. ..እስጢፎ.. ሲሉት ደስ አይለውም፡፡ እንዲታረሙም ያደርጋል፡፡ እራሱን አሳጥሮ መሆን... ወይንም በአቋራጭ አድርጐ ወደተሻለበት መድረስ አይፈልግም፡፡ በአቋራጭ የተደረሰ ቦታ ማስመለሱ እንደማይቀር... ስህተትን ማስተካከል የሚቻለው ስህተት ባለመስራት እንደሆነ ያውቃል፡፡
..ሀኪም ማየት አለብን.. አለችው ሉላይ፤ አንድ ምሽት፡፡ እራት በልተው ጨርሰው ሳሎን ቤት ሶፋ ላይ የኬብል ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ነበር፡፡ እስጢፋኖስ ከቅርብ አመታት ወዲህ ቴሌቪዥን እያየ ወይን የመጐንጨት አመል አዳብሯል፡፡ ..ለልብ ጥሩ ነው ትንሽ ጠጪ.. ይላታል ሉላን፡፡ ፊቷን ታጨማትራለች፡፡ የሚመር ምንም ነገርን ወደ አፏ ማስገባት አትወድም፡፡ መጥፎ ሰውን ራሱ ስትገልጽ ..ይመርራል.. ብላ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ሁሉ ..ስኳር - ስኳር.. ይላል፤ በሉላይኛ፡፡
መጠጡን አንዴ ከተጐነጨ በኋላ እስጢፋኖስ ፊቱን አኮሳተረ፡፡ መነጽሩን በአንድ ጣቱ ወደላይ ከፍ አደረገ፡፡ እጁን ደረቱ ላይ አጣመረ፡፡
|TN> ብንታገስ አይሻልም.. አላት፤ በንግግር ቁም ነገር፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የነበረው ልፊያ... ከሀኪም ወሬ ጋር በኖ ጠፍቷል፡፡ እስጢፋኖስ የቢቢሲን ዜና ብቻ ነው ማድመጥ የሚፈልገው፡፡ ሉላ ዜና የሚባል ነገር አይጣፍጣትም፡፡ ወይን እና ዜና የእስጢፋኖስ ናቸው፡፡ ፊልም እና ቸኮላት የሉላይ፡፡
***
ዶክተሩ ጉሮሮውን አፀዳ፤ ወንበሩ ላይ ለጠጥ ብሎ መነጽሩን ወደ ግንባሩ ከፍ አደረገ፣ በጣቶቹ አይኖቹን አሻሸ፡፡ እስጢፋኖስ የራሱን መነጽር በጣቱ ወደላይ ገፋ አደረገ፡፡
..ሌላ ምርመራ እናድርግ...፡፡ ይሄኛው ውጤት ከበፊቱ ምንም ለውጥ የለውም፡፡ እናንተ ሙከራችሁን ቀጥሉ.. አለ ዶክተሩ፡፡ የበፊቱን የምርመራ ውጤት ለባልና ለሚስቱ እየሰጣቸው፡፡ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ቀናት አለፉ፡፡ ወራት፡፡
ለጥ ያለው ሜዳ እና ለምለሙ የህይወታቸው መስክ መገርጣት የጀመረ መሰለው እስጢፋኖስN፡፡ የሉላ ልብ በሆነ ነገር እንደ ድንጋይ ከብዶ እንደተጫነ ለራሷ ይታወቃታል፡፡ ውበቷ የሆነ ሻሽ አስሯል፡፡ የቸኮላቱ ጣዕም የማያጣፍጠው ምሬት ወደ አፏ ይመጣል፡፡ አሮጌ ሳንቲም  የሚል ዝገት፡፡
እስጢፋኖስ ስሙ የከበደው መምሰል ጀመረ፡፡ ጫን አድርጐ የሚረግጠው መሬት እና በራስ መተማመን የተሞላው እርምጃው በተሰባበረ ጠርሙስ ላይ እንደምትሮጥ አይጥ ሹልክ ይልበታል፡፡ መነሩን በአንድ ጣቱ ወደ ላይ ከፍ ያደርጋል፡፡
..ምንድነው ማድረግ ያለብኝ.. ብሎ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ..በዚህ አመት ልጅ መውለድ ነበረብን፤ ምንም ስህተት አልሰራንም እስካሁን፡፡ ሁለታችንም ዝግጁ ነን፤ ጤነኞች ነን፤... ምንድነው ችግሩ... መፍትሄውስ?..
..የአንተ የዘር ፍሬን የሴቴው እንቁላል ሊቀበለው አልቻለም... በአርቴፊሻል መንገድ የዘር ፍሬውን ከእንቁላሉ ጋር ለማዋሃድ ያደረግነው ሙከራም አልተሳካም.. አለ ሀኪሙ፡፡ ...የማህፀን ኪራይን እንድታስቡ ለመምከርም ቢሆን... የአንተ የዘር ፍሬ እና የእሷ መጀመሪያ መዋሀድ ቢችሉ ነበር.. አለና ሀኪሙ መቀመጫው ላይ ለጠጥ አለ፡፡ መነሩን ግንባሩ ላይ ሰክቶ አይኖቹን በጣቶቹ አሻሸ፡፡ ቀና አለ፡፡
..እንደዚህ አይነት ኬዝ በመድሃኒት መለወጥ ካልተቻለ በአመጋገብ ይለወጣል፡፡ እነዚህን ተጨማሪ ዝርዝሮች ፋርማሲ ጠይቁ.....
ከወር በኋላ እንዲመለሱ ቀጠሮ ሰጥቶ ሰደዳቸው፡፡ እስጢፋኖስ እና ሉላ ለመመካከር ተቀመጡ፡፡
.....የሌላ ሰው ዘር ፍሬ መሞከር አንችልም..
እስጢፋኖስ ላለማሰብ ሲሸሸው የነበረው ጥያቄ ነው፡፡ ስህተት መስራት አይፈልግም፡፡
..የሌላ ሰው ዘር የሌላ ሰው ልጅ ነው.. ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ የሚለው ተረት ትዝ አለው፡፡ የድሮ ሰው እንዳትለው ፈርቶ ሳያወጣው ዋጠው፡፡
..ልጆች የፈጣሪ ፀጋ ናቸው፤ በእኛ በኩል ይመጣሉ እንጂ የእኛ ናቸው ለማለት ግን አይቻልም..
..ምን ማለትሽ ነው? ከየት ያመጣሽው ሳይንስ ነው?... ብዙ ፊልም ማየት እንግዲህ ችግሩ ይህ ነው..
..አንተም ከቢቢሲ ያመጣኸውን ዘገባ... ሳይንስ ምናምን ለምን ትለኛለህ? ይሄኔ እግዜርን ብታምን ልጅ ባልከለከለን..
..ሉሌ ምን ነክቶሻል? እንደተማረ ሰው አስቢ እንጂ..
.....ልጅ እፈልጋለሁ... እፈልጋለሁ!... ልጅ የማትሰጠኝ ከሆነ... በቃ..
..በቃ ምን... እፈታሀለሁ?!... ነው ወይንስ ከሌላ እወልዳለሁ?..
የወይን ጠርሙሱን አንስታ ፊቱ ላይ ረጨችበት፡፡ ወደ ፎቅ ቤቱ መኝታ ክፍላቸው ሮጠች፡፡ ተከተላት፡፡ በሩን ስትቆልፍ ደረሰ፡፡ መነሩን በጣቱ ከፍ አድርጐ ወደ ሳሎን ተመለሰ፡፡ ሪሞት ኮንትሮሉን አንስቶ ቻናሉን ወደ ቢቢሲ ዜና ለወጠው፡፡
** *
ሴት ፊቷን ከባሏ እና ከቤቷ አቅጣጫ ወደ ውጭ ስታዞር ሁኔታዋ ላይ ያስታውቃል፡፡ እስጢፋኖስ ስሙን አሳንሰው ..እስቲፍ.. እያሉ ሲጠሩት ማስጣል አልቻለም፡፡ ...ወሬ ይነፍሳል፡፡ ...የሉላ መልክ የራሱን ይመስል እንደነበር የተገነዘበው ፊቷ መቀየር ሲጀምር ነው፡፡ ፊቷ የሌላ ሰውን መምሰል ጀመረ፡፡ እሱ የሚወዳቸውን ልብሶች ትታ ሌላ ሰው የሚወዳቸውን መልበስ ጀመረች፡፡ ጠረኗ ቀንሶ... ሽቶዋ ጠነከረ፡፡ ...ስራ የምትገባበትን ሰአት አስረፍዳ ወደቤቷ መመለሻዋን አራቀች፡፡ ...እሱ የሚጣፍጥ ነገር መውደድ ሳይጀምር ሉላ የሚመር ነገር መውደድ ተማረች፡፡ ሰክራ ስትመጣ ሊያስቆማት አልቻለም፡፡ በህይወቱ ስህተትን በማረም አያምንም፡፡ ስህተትን ማረም የሚቻለው ባለመስራት ብቻ ነው ይላል፤ በደነዘዘ አእምሮ በሚያወራ የወይን ስካር...፡፡
...ወሬ ይነፍሳል፡፡ ይሄዳል ተመልሶ ለመንፈስ ይመጣል፡፡ እስጢፋኖስ... ይቃጠላል፡፡ ...ለጥ ያለው መስክ ተራራ ሆነበት፡፡ ተራራውን ገለል ለማድረግ የቡልዶዘር ትእግስት ያስፈልጋል፡፡ ስህተት የሌለው ትእግስት... እያለ ያስባል፡፡ ...የሰማውን ወሬ ለማረጋገጥ ሄዶ አያውቅም፡፡
አንድ ጠዋት ብቻዋን ከምትተኛበት የመኝታ ክፍል ሊያነጋግራት ሄደ፡፡ አልጋ ለይተዋል፡፡
..ራሴን ነፃ አውጥቻለሁ.. አለችው፡፡
..ምን ማለት ነው? ከእኔ ነው ነፃ ያወጣሽው... ከትዳር... ወይስ?..
በሩን ፊቱ ላይ ወርውራ ዘጋችበት፡፡
ስህተት ላለመስራት ሲባል እጅን አጣምሮ ማየት መፍትሄ እንዳልሆነ ገባው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግን አያውቅም፡፡...ድፍን ሲልበት አማራጮች ሁሉ ጀአንድ የበቆሎ ራስ ላይ ያለ አንድ ዘለላ ሆኑበት፡፡
- የሀገር ሽማግሌ ሰብስቦ ማናገር (የሀገር ሽማግሌ የት እንደሚገኝ አያውቅም)
- ሉላን ከአልጋው ጋር አስሮ ማስቀመጥ
- እግሯ ስር ተንበርክኮ ማልቀስ
- ለእናት እና አባቷ መንገር (እናት እና አባቷ በስተርጅና አሜሪካ ገብተዋል)   
ሉላ ለብዙ ቀን ጠፋች፡፡ እስጢፎ/እስቲቭ ጓደኞቿን ሲጠይቅ ዋለ፡፡ ላንጋኖ መሄዷን ሰማ፡፡ ስለ ተተኪው ሰውዬ...ማንነት ለመስማት ከዚህ በፊት አይፈልግም ነበር፡፡ አሁን ግን ጠየቀ... አጠያየቀ፡፡ በመሳሪያ አያምንኧ ያደገው የመሳሪያ ሀገር ቢሆንም፡፡  መሳሪያ አፈላልጐ ገዛ፡፡ ወደ ላንጋኖ መኪናውን አስነስቶ ነጐደ፡፡      
***
የተባለው ሆቴል ደረሰ፡፡ ብዙ አማራጭ አለው...
•ውሽማውን እና ሚስቱን መክሯቸው ወደ ቤቱ መመለስ
•ውሽማውን ገንዘብ ሰጥቶ እንዲተዋት ማድረግ (ውሽምዬው ብርም ሽጉጥም አለው)
•ለሚስቱ የቸኮላት ሽልማት ማበርከት
ውሽማውን ፍቅር ሲሰሩ ቀጥሎ ከተከራየው አልቤርጐ ሆኖ ማዳመጥ
•ሚስቱን መፍታት
ውሽማውን
***
ሚስቱን መፍታት አእምሮውን መፍታት እንደሚሆን ጥርጣሬ የለውም፡፡ ሉላዳይ የመጀመሪያ ሚስቱ ብቻ ሳትሆን የመጀመሪያ ፍቅሩም ናት፡፡
የበሩን መዝጊያ ገንጥሎ ሲገባ፣ ሉላ እና ሰውዬው... እስጢፋኖስ እና ሉላን በቀድሞው ዘመን ይመስላሉ፡፡ ተቃቅፈዋል፡፡ ለእስጢፋኖስ ተራራ የሆነበት ህይወት ለእነሱ ለጥ ያለ አረንጓዴ መስክ እንደሆነ በአይናቸው ነፀብራቅ ማወቅ ቻለ፡፡ የእስጢፋኖስ ተራራ ሲገፋ የቆየው ግሬደር (ትዕግስቱ) ተስፋ ቆረጠ፡፡ ንዴት ከተራራው ውስጥ በርቅሶ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ተራራው በንዴት ተበታትኖ ጠፋ፡፡ ለጥ ያለ ሜዳ ተከሰተ፡፡ የተከሰተው ግን ለምለም መስክ ሳይሆን ለጥ ያለ በረሃ ነው፡፡
መሳሪያውን መዞ አወጣ፡፡ አሁንም ብዙ ምርጫ አለው፡፡ ብዙ ብዙ፡፡ ስህተትን ማረም የሚቻለው ባለመስራት ብቻ ነው ይል ነበር እስጢፋኖስ የሚባል አንድ ሰው በመሰላሉ ወደላይ በሚወጣባቸው የከፍታ ዘመኖቹ፡፡ በእባቡ ተውጦ ወደ መቀመቅ ከመውረዱ በፊት፡፡

 

Read 4600 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 11:52