Saturday, 24 September 2011 10:21

ጥበብና ..የቋንጃ ቆራጮቹ.. ዘመን

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ..ታሪካዊ ተውኔት.. ታተመ፡፡ አራት ታሪካዊ ተውኔቶቹ በአንድ ላይ ሆነው ነው የታተሙት፡፡ በአቡነ ጴጥሮስ፣ በዘርአይድረስ፣ በአፄ ምኒሊክና በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የፃፋቸው ናቸው፡፡ የመሐፉ መታተም የዘገየ ዜና ቢሆንም፣ እሱን ተንተርሶ የሰማሁት ነገር አዲስ ሆኖ አስደምሞኛል፡፡ ከአንድ አዛውንት ደራሲ ጋር (ስማቸውን ያልጠቀስኩት ስላላስፈቀድኳቸው ነው) ስንጨዋወት ነው ይሄን የነገሩኝ፡፡
ፀጋዬ ገብረመድህን በአፄ ቴዎድሮስ ህይወት ላይ የተንተራሰው ተውኔቱ ታይቶ የተወደደለት ሰሞን ነው፡፡ ወረፋው ለጉድ ነበር፡፡ ያየው የሚያወራው ሁሉ ለትንግርት ሆነ፡፡ ይሄንን ልብ ያሉት የወቅቱ ጥቃቅን ባለሥልጣናት (የጀርባ ሥማቸው ቋንጃ ቆራጭ ነው) አቅማቸው የሚመጥነውን ጥቃቅን ስብሰባ አደረጉ፡፡ የስብሰባ አጀንዳው የፀጋዬ ብዕር በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የፈጠረው ፀዳል በአፄ ኃይለሥላሴም እንዲደገም ነገሮችን ማመቻቸት ነበር፡፡

..እህስ? ምን ትላላችሁ?.. አሉ የጥቃቅን ባለሥልጣኖች ጥቃቅን ስብሰባ መሪ፡፡
..ጥሩ ነውጂ - ጥሩ ነው - ይበል.. አሉ ለታች እንጂ ለላይ በማይሰማ ጥቃቅን ድምፃቸው፡፡ በዚህ መካከል አንድ ሸርማማ-ሸረመም ግልገል ባለስልጣን ጥርጣሬአቸውን xnsù:-
..ፀጋዬ አፄ ኃይለሥላሴ የተባለውን ቴአትር በመፃፉ ቅሬታ የለኝም፡፡ እንደውም ከኛ እስኪመጣ ፀጋዬ መጠበቅ አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን.....
..እ? የምን ነገር ግን ነው?..
..ነገር ግን እሱ አያርፍም፣ መቼም እንደምታውቁት ደፋር ነው፡፡ አንዳች ምሥጢራዊ ነገር ጨምሮ ንጉሱን ቢያስቆጣብንስ?..
..ለካ ይሄም አለ?.. አሉ የጥቃቅን ባለሥልጣኖቹ አውራ፡፡ ..በሉ ዘዴ ፈልጉ - እንዴት እናርግ?..
..ለምን ከኢዩኤል ዮሐንስ ጋር ተጣምረው አይፉትም?..
..ጥሩ ሀሳብ፣ ጥሩ! ይሄው ነው ዘዴው!..
በዚሁ ተስማምተው ፀጋዬ እንዲቀርብ ላኩበት፡፡ መጣ
..መቼም.. አሉ ሰብሳቢው ..መቼም በአፄ ቴዎድሮስ ላይ የፃፍከው ቴአትር አገር ያደነቀው ሆኗል እኛም ወደነዋል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ተሰብስበን ስንጨዋወት በነካ እጅህ ግርማይነታቸውን የሚመለከት ..አፄ ኃይለሥላሴ.. የተሰኘ ቴአትር እንድትደርስ ተስማምተናል፡፡ ረዳት ኢዩኤል ዮሐንስን መድበንልሃል፡፡..
መቼም እንቢ አይል፡፡ እንቢ ቢል ፀቡ ከኛ ጋር ሳይሆን ከእሳቸው ከጃንሆይ ጋር ይሆናል ብለው የደመደሙት ሰብሳቢ ..ጨርሻለሁ.. ሊሉ ሲሉ...
..ጥሩ ነው.. አለ ፀጋዬ፡፡ ..ጥሩ ነው፡፡ ርእሱንም ጥሩ መርጣችኋል፡፡ (የሽርደዳ ነበር - ተሰብሳቢዎቹም ገብቷቸዋል) መቼም እንደምታውቁት እኔ የምፈው ተውኔት (theatre of cruelity) የተሰኘውን የግሪኮች ዘውግ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ገፀ ባህሪው ከባድ ጠላት ያስፈልገዋልና ርእሱን ባወጣ እጃችሁ የጃንሆይን ቀንደኛ ጠላት ምረጡልኝ - ማነው?..
ተሰብሳቢዎቹ ተፋጠጡ፡፡ ልጅ እያሱ እንዳይሉ ታሪኩ ሌላ ሊሆን ነው፡፡ አፄው ስሙ እንዲነሳ የማይፈልጉት ነው፡፡ በላይ ዘለቀ? እንደዚያው! ታከለ ወልደሀዋርያት? እንደዛው! ታዲያ ማን?
..ተወው - ተወው፣ ሌላ ቀን ጠርተንህ እንነግርሃለን.. አሉ ሰብሳቢው፡፡ አልጠሩትም፣ ሊጠሩትም አይችሉም፡፡ በዚሁ ቀረ፡፡
ውሉን ያስጨበጡንን አንጋፋ ደራሲ አመስግነን የነገር ዳንቴላችንን እንተርትር፡፡ ለመሆኑ እነዚያ ..ቋንጃ ቆራጮች.. ቋንጃ ለመቁረጥ ስንት ደራሲ እና የጥበብ ሰው ፊታቸው አቁመው ይሆን? ደግሞምኮ ቋንጃ ቆራጭ የተፈነገለ ባሪያ ለማምለጥ ዳር-ዳር ሲል ነው፤ የቋንጃ ቆረጣ ሥራውን የሚያከናውነው፡፡ እናስ? ደራሲውና የጥበብ ሰው ሁሉ ቋንጃ ቆራጭ ፊት የሚቀርበው ያገነገነ ባሪያ በመሆኑ ነው? የማን ባሪያ? የንጉሱ? የልዑላኑ? የመሣፍንቱ? የባለስልጣናቱ?... ፀጋዬምኮ ያልተገባ ነገር እንደተጠየቀ አልሆነም፡፡ ቋንጃ ቆራጮቹ ቋንጃውን የመቁረጥ መብት እንዳላቸው ተቀብሎ በተጠየቅ ነው ያመለጣቸው፡፡ በተጠየቅ ባያመልጥስ ኖሮ? ብዕሩን እንደማሲንቆ እየከረከረ ልቡ ያልገባውን ሊያሞግስ? ከዚህ በኋላ ያለው የሥጋ ነፃነት ምኑ ነው? ነፍሱ ተፈንግሎ ቋንጃው አልተቆረጠም ማለት እንችላለን?
የደራሲ ተቀዳሚ ግብአቱ ነፃነቱ ነው፡፡ ነፃነቱ የሚገለፀው በአካል ወደአሰኘው አካባቢ በመንቀሳቀስ አይደለም፡፡ በአእምሮ፣ በሐሳብ፣ በምናብ... ላይ ገደብ እንዳያርፍ በመከላከል ነፃነቱን ያስከብራል፡፡ ደራሲ የእግር ቋንጃ የለውም፡፡ የምናብ፣ የአእምሮና የሐሳብ እንጂ፡፡ ጥንታዊቷ ግሪክ ገናናነቷ በሮማዎች ተድሶ ዜጐቿ ያለ ጠባቂ ሲበተኑ በባሪያ ፈንጋዮች ባለቤት እንደሌለው እሸት እየተሸመጠጡ ተሸጠዋል፡፡ ከአንጡራው ግሪክ ባሻገር የተማሩት ሳይቀሩ ተፈንግለው ለሮማውያን ተቸብችበዋል፡፡ ሆራስ የተሰኘው ሮማዊ ባለቅኔ (ከክ.ል.በፊት 65-8) ስለዚሁ ጉዳይ እንዲህ ብሎ IÐL:-
“The more finely trained, particularly the Greek Slaves, were with the ‘City families’, in other words, lived in the town house. Not only cooks, scribes, musicians, pedagogues, actors, but even physicians, author and philosophers were held as slaves.”
(በተገቢው የሰለጠኑ በተለይም ግሪካዊዎቹ ባሮች ከከተሜ ቤተሰቦች ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ ምግብ አብሳዮች ብቻ ሳይሆኑ ቁም ፀሐፊዎች፣ ሙዚቀኞች፣ መምህሮች፣ ተዋንያኖች ሌላው ቀርቶ ሐኪሞች፣ ደሪሲዎችና ፈላስፎች በባርነት ተይዘው ነበር፡፡)
ሆራስ እንደሚነግረን ከሆነ፤ በዘመኑ በባርነት የተፈነገሉ ደራሲያንና ፈላስፎች የነበሩበት ሁኔታ እንደ ድቅ የሚቆጠር ነው፡፡ እንደሌሎቹ ባሮች በጥቃቅን ሥራ ላይ አይሰማሩም፡፡ ባሪያ አሳዳሪዎቹ ጠንቅቀው የሚያውቋቸው ከመሆኑም በላይ የአቻ ወዳጅነትም ነበራቸው፡፡ እንደ መካሪ-ዘካሪም ይቆጠራሉ፡፡ ለፍልስፍናና ለድርሰት ሥራቸው የሚፈልጉት ሁሉ ይሟላላቸዋል፡፡ ባሪያ አሳዳሪው የአካላቸው እንጂ የአእምሯቸው፡ የሀሳባቸው፣ የምናባቸው ገዢ አልነበረም፡፡
እነ ፀጋዬ ገብረመድህን ያለፉበት የድርሰት ዘመን ግን ..ባሪያ.. ከተባሉት ግሪካውያን የከፋ ሆኖ ይታየናል፡፡ በአካል ባሪያ አይደሉም፣ ሥጋቸውን የገዛ የለም፤ ነፍሳቸው ግን ተፈንግላ የባሪያ አሳዳሪው ንብረት ተደርጋለች፡፡ የደራሲው አእምሮውቖ ሐሳቡና ምናቡ በቋንጃ ቆራጮቹ ሥለት ሥር ነው፡፡
ፀጋዬ ገብረመድህን ..አፄ ኃይለሥላሴ.. የተሰኘውን የቋንጃ ቆራጮች ንስ በዘዴ ቢያጨነግፍም ከጥቃቅኖቹ (ለሱ ትልቅ ከሆኑት) ባለሥልጣኖች ባላንጣነት አትርፎ ነበር፡፡ የጥቃቅኑ ስብሰባ መሪ የነበሩት ሰው ፀጋዬን አድብተው ከመጠበቅ ውጭ አፉ ውልፍት ብሎ ከጃንሆይ ጋር የሚጋጭበትን ሁኔታ ሲያመቻቹ ቆይተው ነበር - ይባላል፡፡ እኚህ ባለሥልጣን ከመሳፍንቱ ወገን ባይሆኑም በትዳር ጭራቸውን ከዙፋኑ ጋር ለማቆላለፍ ሞክረዋል፡፡ ሚስታቸው በዘመኑ አጠራር ..ሞጃ.. ናቸው፡፡ አንድ ቀን ፀጋዬን መንገድ ያገኙትና አፉን እንዲያድጠው የተሙለጨለጨ ጥያቄ ያቀርቡለታል፡፡
..ፀጋዬ ለምንድነው ሞጃዎችን የምትጠላው?..
ፀጋዬ ምኑ ሞኝ? ..ሞጃዎችን አልጠላም.. አላቸው፡፡ ..ሞጃዎችን አልጠላም፡፡ እጣቢያቸውን ግን አልወዳቸውም፡፡..
..ማነው እጣቢያቸው?.. አላሉም፡፡ ያውቁታል፡፡ አጥጋቢ መልስ እንዳገኙ ሁሉ ተሰናብተውት ሄዱ፡፡
ወደ ደራሲና ፈላስፋ ፈንጋዮቹ ሮማውያን እንመለስ “Foundations of Christianity” የተሰኘ መሐፍ ላይ እንደቀረበው ሮማውያን የልሂቃኑን ባሮች ሥራ ዘርፈዋል፡፡ “Rome’s greatest thinkers and poets were almost all of them plagiarists” (የሮም ታላላቅ አሳቢያንና ባለቅኔዎች ሁሉም ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ በጥበብ ስርቆሽ ላይ የተሰማሩ ነበሩ፡፡)
ዘመኑ ሮማዊዎቹን የጥበብ ዘራፊዎች አላቸው እንጂ ያኔ እንደዚያ አልነበረም የሚሉ አሉ፡፡ ባሪያው ያመረተውና ያፈራው ብቻ ሣይሆን ልቦናውን አንቅቶ የሰራውም ጥበብ የባሪያ አሣዳሪው ስለነበር በዚያው መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የጥበብ ስርቆሽን ከሌላው ምዝበራ ሁሉ የከፋ አድርገው የሚመለከቱ በዚህ አይስማሙም፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ግድ የላቸውም፡፡ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ አንድ ወቅት ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
..እንደሰውና እንደ ገጣሚ ሳስብ ህብረተሰቡ ጋ መድረሱ ብቻ ያስደስተኛል፡፡ ከዚህ ውጭ ጥያቄ የለኝም፡፡ ከዚህ በኋላ ምናልባት በስሜ ማድረግ ካለብኝ፣ አጥፍቼ ከሆነ ልቀጣበት ካልሆነ በስተቀር ጭብጨባ ፈልጌ ከሆነ በእውነቱ ትክክለኛ ገጣሚ አይደለሁም፡፡ ...ግጥሞቼን ማንም ሰው በባለቤትነት ሊወስዳቸው ሁሉ ይችላል፡፡ መፈለጌ በቃኝ እኔ፤ ሥራዎቹ መፈለጋቸው በቃኝ፡፡..
ወደ ቋንጃ ቆራጮቻችን እንመለስ፡፡
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን yቋንጃ-ö‰ôcÜ ሥራ ከነፃ መሰል ባሪያው ወደ ህቡዕ ባሪያ አሳዳሪው የጥበብ ሽግግሩ እንዲሰልጥ ማድረግ ነው፡፡ ምሥጋና አከል ቴአትር እንዲፃፍ ከማስገደድ አልፈው፤ ..የባሪያ - አሳዳሪው.. ቀልብ ያረፈበት የጥበብ ሥራ በበረከትነት እንዲሰጥ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ አንድ ጊዜ አፈወርቅ ተክሌ የሥዕል ኤክዚቢሽን ከፍቶ አፄው፣ ልዑላኑ፣ መሣፍንቱና ክቡር ሚኒስትሮችን ይጋብዛል፡፡ ከነዚህ ጐብኚዎች ጀርባ ከማይጠፉት ቋንጃ-ቆራጮች መካከል አንዱ ወደ አፈወርቅ ጠጋ ብሎ፤
..ልዑሉ ይሄን ስዕል ወደውታልና አበርክትላቸው.. ይላል፡፡
..ከወደዱት ይግዙት እንጂ አላበረክትም.. የአፈወርቅ ምላሽ ነበር፡፡ ይህን የሰማ ቋንጃ ቆራጭ ሁሉ ..ጉድ!.. አለ፡፡ ነገር ግን የአፈወርቅ ደረጃ ከእነሱ ከፍ ያለ ስለነበር ወሬ ለማወሻከት አላመቻቸውም፡፡ አፈወርቅ ቀድሞ ተዘጋጅቶባቸው ነበር፡፡ ከቋንጃ ቆራጮቹ ለመገላገል አንድ ዘዴ ዘይዶ ነበር፡፡ እላይ ካሉት ..ባሪያ አሳዳሪዎች.. ጋር ቀጥታ ግንኙነት መፍጠር፡፡ ቋንጃ ቆራጮቹ ..ለሥራ.. የሚመቻቸው ግንኙነት የሌለው ደራሲ፣ ሰዓሊ ሆነ ሌላ የጥበብ ሰው ሲያገኙ ነው፡፡ አፈወርቅ ሳይዙት ዘለላቸው፡፡ አመለጣቸው፡፡

 

Read 3558 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:23