Saturday, 24 September 2011 10:24

የ..እንጀራ ሚኒማይዝ ምጣድ.. ውጣ

Written by  (ወግ - እምባው ገ/ዮሐንስ)
Rate this item
(0 votes)

..እንጀራ ከመከራ..፣ ..ለእንጀራ ተሰደደ..፣ ..በእንጀራዬ መጣ..፣ ..ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም.. (ምነው ቢሉ በወጥ ጭምር እንጅ)፤ ..ይህችም እንጀራ ሆና ሚጥሚጣ በዛባት.. ወዘተ፡፡ ስለ እንጀራ ጠይቀው ስለ እንጀራ የሚመልሱ ብሒሎች በዝተውብኝ  ቢገርመኝ ነው ለእናንተም ማመላከቴ፡፡ እስኪ እናንተም ሌሎች የእንጀራ አባባሎችን አስሱና ምርጫችሁን በ600 የሞባይል ቁጥር ..ቴክስ ሜሴጅ.. ላኩልኝ፡፡ ሁለት ብር እንደሚያስከፍልና ትርፍ እንደማገኝበት አልደብቃችሁም፡፡ ለጊዜው ግን የከፋቸው ጐበዛዝትና ቆነጃጅት ..ግዙዎች..፤ ወንዝ ባይደርሱ ምንጭ፤ እሱም ቢቀር ውሀ በገበቴ ሲሻገሩ የሚያንጐራጉሩበትን ወይም የሚያንገራግሩበትን ግጥም ተመልከቱ፡፡

..እሄዳለሁ በቃ ነገር አላበዛም
እንጀራ ነው እንጅ ሰውን ሰው አይገዛም..
ያኔ የባሪያ ንግድ ላይ አመጽ ተለኩሶ የጐዳና ላይ ነውጥ በተቀሰቀበት ሠሞን የተገጠመ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁንም ከዚህ አስከፊ ግፍ ገና ነፃ ያልወጡ የአለም ሕዝቦች ካሉ፤ ይህንን ለነፃነት ንቅናቄ በመዝሙርነት የሚታጭ ግጥም ወደ ሀገራቸው ቋንቋ አስተርጉመው መጠቀም እንደሚችሉ ሳበስራቸው በታላቅ ደስታ ነው፡፡ በመጀመሪያ የሀሳቡ አፍላቂ ባለ መብት ለሆንኩት ለእኔ ክፍያ መፈፀም እንዳይረሱ ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡ (ጐበዝ እዚህች ላይ የኢንተርፕረነርሺፕ ፖቴንሻሌን ልብ እያላችሁ)፡፡ ግጥሟን በዘመናዊ መንገድ ማሻሻልም ይቻላል፡፡
..እመጣለሁ ኪዮስክ ዱቤም አላበዛም፡፡
እንጀራን ነው እንጅ ሰውን ሰው አይገዛም..  
(..አዛማጅ ስህተት የራሴ..) እያልኩ እንጀራዬን አበስላለሁ፡፡
ወሬያችን ስለ እንጀራ ነው፡፡ የዘይቱንና ጋዙን ወጭ እያሰላን ላለመጨነቅ ብቻ ሳይሆን፤ ለዛሬ ወጋችን አስፈላጊ ባለመሆኑ ጭምር የወጡን ጉዳይ ትተን ስለ ግዥ እንጀራ ጥቂት እንወጋወጋለን፡፡
በቾክና ብላክቦርድ፤ በብላክቦርድና ቾክ መደባትና ቀለማት፤ ...በቆራጣ ካርቶን ላይ ወደቀኝ ወደ ግራ ዘመም ብሎ በዶላር እስኪርብቶ፤ ...በነጭ ወረቀት ላይ ሠረዝ ንቅሳት መስለው በእርሳስ የተከተቡ፣ የተቀቡ ናቸው ማስታወቂያዎቹ፡፡ (ጐበዝ ይቅርታ እነ ባለ ታቱ እኔ እናንተን ለመንካት ብዬ አይደለም፡፡) በየአጥሩ ሰንሰል ላይ፤ በግቢ መዝጊያ ቆርቆሮ ላይ፣ ብቻ በተገኘበት ሁሉ ወልገድገድ ብለው የቆሙ፣ ..የሚበላ እንጀራ አለ.. የሚሉ የወል ስም ማስታወቂያዎችን እንተዋቸው፡፡
..እገሌ እንጀራ፣ እገሊት እንጀራ፣ እንትን እንጀራ፣ ምንትስ እንጀራ.. የሚል ስም ወጥቶላቸው፤  ማስታወቂያቸው ላይ የእንጀራ ፎቶ ተጨምሮላቸው... መቼም እንጀራው በምትሀት ተልቆ መሆን አለበት፡፡ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያህል ክብ ምጣድ ወደየት ተገኝቶ ያን ያህል እንጀራ ይጋገራል? በዚህ ላይ በሊጥ ፋንታ ከወተት የተጋገሩ የሚመስሉት የእንጀራ ምስሎች፤ ለስም ማውጫነት ከሚዘጋጅ የድፎ ዳቦ ምስሎች በብዙ እጅ አጣጥፈው ወፍረውና ተልቀው ከስያሜአቸው ጋር የአዲስ አበባን ማዕዘናት አጥለቅልቀዋል፡፡
እንዲያው እናንተም ታዝባችሁ ይሆን ወይስ እንደእኔ ጧትና ማታ ፌስታል አንጠልጥሎ የደረቅ እንጀራ ሻጮችን ጉበን ዓምባር ከማስገጨት ነፃ ወጥታችኋል? ወይም የሆድ ነገር የኔን ሆድ ብቻ ቆርጦት እንደሆነ... (አይ ጐበዝ ማነህ አንቲባዮቲክ ነገር ውሰድበት ያልከኝ? ለእኔ እኮ ስጋ ቤቶችና ፎቶ ቤቶች እኩል ባለውለታዎቼ ናቸው፡፡ ሁለቱም ጥሩ ጥሩ ስጋና ጥሩፎቶዎች ሰቅለው ያሳዩኛልና)፡፡ እና የእንጀራ ስያሜና የእንጀራ መጠን እንዴት እንደማይገናኙ በማየት፤ ለአንዳንዶቹ የራሳችንን ተዛማጅ የፈጠራ ስሞች ሰይመን እንመለከታለን፡፡ (የማንንም መብት ላለመንካትና በገዛ እጄ የእለት እንጀራዬን የሚሸጥልኝ አጥቼ ፆም እንዳላድር ጭምር)፡፡
መጀመሪያ የምናገኘው ..እናት እንጀራ..ን ነው፡፡ የ..እናት እንጀራ.. ባለ ከለር ማስታወቂያ ላይ፤ የትልቅ ነጭ እንጀራ ፎቶ አይተን ስንሄድ፤ የፎቶው ጥላ የሚመስል ጥቁርና በዚያ ላይ ከእንጀራ ላይ የተጠበቀች ክብ ሚኒ እንጀራ ይገጥመናል፡፡ ስያሜው ..የእንጀራ.. የሚል መነሻ ቅጥያ ያሰፈልገዋል - ..የእንጀራ እናት እንጀራ..፡፡
..ጥጋብ እንጀራ.. በበኩሉ ገና ማስታወቂያውን እንዳዩት ..ስንቱን ያጠግብ ይሆን?.. የሚል ጥያቄ ያስነሳል - ውፍረቱና ስፋቱ፡፡ በአካል ስትገናኙ ግን፤ የሚያጠግብ ሳይሆን ጠግበው የሚበሏት ሆና ያገኟታል - ..ጠባብ እንጀራ.. ብትባል ይስማማታል፡፡
..ማኛ እንጀራ..ን ደግሞ ግዙ፡፡ ..ልጅ የቆላው ቡና.. በመሠለ ከለሩ፤ ፈንጣጣ እንደወጋው ፊት ጣል ጣል ከማለቱ በቀር አይኑ ተደምጥጦ ልሙጡን መቅረቡ፤  ከመጠኑ ማነስ ጋር ሲታይ፤ ..መናኛ እንጀራ.. ለመባል እንኳን ብዙ ይጐድለዋል፡፡
ጐልማሳው ላጤ ከስራ እንደወጣ እግረ መንገዱን ወደ ኪዮስክ ጐራ ብሎ በመጠኗና በጥቁረቷ ከምጣዱ የማሰሻ ጨርቅ የማትሻል ደረቅ እንጀራውን በስስ ፌስታል አስጠቅልሎ በጉያው ሸጐጥ ሲያደርግ ልጅነቱ ፍክ ይለዋል፡፡ ያ መልካሙ ልጅነት ከነሚያምረው ወዙና ከነውበቱ ብቻ ሳይሆን፤ በዋናነነት መሐረቤን ያያችሁ ከሚለው ጨዋታው ጋር ይታወሰዋል፡፡ (ጐበዝ ያንተ የልጅነት ትውስታ ..በኖህ መርከብ.. ወለሎች ላይ እየተሯሯጥክ ኩኩሉ መጫወት ነው ለምትሉኝ አልፈርድባችሁም፡፡ ምክንያቱም የተወለድኩት ራሱ የጥፋት ውሀ ከደረቀ በኋላ መሆኑን ባለማወቃችሁ ነው)፡፡
የልጅነት ነገር ከተነሳ አይቀር፤ የልጆች ተወዳጅ የሆነ የ..እንቆቅልሽ.. ጨዋታ ሊመጣ ይችላል፡፡
..እንቆቅልህ?..
..ምን አውቅልህ?..
..የዘንድሮ እንጀራ ድፍንነቱ በምን ያስታውቃል?..
..በማጥገቡ..
..አይደለም..
|T¶WN በመሙላቱ..
..አይደለም..    
..እሺ አገር ስጠኝ?..
..አድአን ሰጥቼሀለሁ..
..አድአ ገብቼ ምን አጥቼ፤ ማኛ ጤፍ በልቼ ለማንኛውም መልሱ ..በክብነቱ ብቻ.. ነው፡፡
ያወገዙት ነገር ውስጥ ገብቶ መዘፈቅ ይሆንብኛል ብዬ ነው እንጅ፤ ከላይ ጠቆም ያረግሁዋችሁ የ..ኢንተርፕረነር ፖቴንሻሌን.. ተጠቅሜ በአጭር ጊዜ የምከብርበት ዘዴ ብልጭ ብሎልኝ ነበር፡፡ ምን መሠላችሁ? ከዚያችው ከፈረደባት ሀገረ ቻይና ባለማስቀመጫ ሲኒዎች በብዛት አስወጥቼ፤ ሲኒውን ለብቻ ለነጋዴዎች አስረክባለሁ፡፡ ማስቀመጫውን ደግሞ ለእንጀራ ሻጮች በምጣድ ፋንታ እቸበችባለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን ለሚሸጡት እንጀራ የሚሆን ምጣድ ገበያ ላይ ስለሌለ፤ በሸክላ ሽራፊ እየጋገሩ ሲቸገሩ ማየት አልፈልግም፡፡ (ጐበዝ፤ ያፋጠጣችሁኝ መስሏችሁ፤ ..አያ ጅሎ የአከምባሎውስ ጉዳይ?.. ብትሉኝ፤ እሱንም ቀድሜ አስቤበታለሁ፡፡ ለእሱም ሌላ የሲኒ ማስቀመጫ ነው ምላሹ)
እንዲያውኮ፤ ለሀሳብ መነሻ እንጅ ፌርማታና መድረሻ አለመኖሩ ግርም ይለኛል፡፡ በዚህም መሠረት ነገር ነገርን ይስባል እንዲል መጽሐፍ (ቢዝነስ ቢዝነስን እንደሚጐትተው በ..ሎው ኦፍ አትራክሽን.. ተጽፏል)... አሁን ምን ትዝ አለኝ መሠላችሁ? የእንጀራው ማስቀመጫ፡፡ መቼም የደረቅ እንጀራ መሸጫ ቤቶች አቅብጧቸው ለእንጀራ ማስቀመጫነት መሶብን እንጠቀማለን ቢሉ ጉዳዩ ከ..ዶሮን በጋን.. አልፎ ..መርፌን በሳንሳ.. መሆኑ ነው ጉዳዩ፡፡ እና ድሮ እናቶች ..አዲስ.. እና ..የሱዳን ሽቶ..አቸውን ከጌጣጌጥ ጋራ የስለት ሳንቲሞችን ጨምረው የሚያስቀምጡበት የጌጥና የክብር ዕቃ ምን ነበር? እዎ ሙዳይ (ጐበዝ እዚህች ላይ በልጅነትህ የእናትህን ኮቴ እያደባህ አስልተህ ሙዳያቸውን እየከፈትክ ስትመነትፍ፤ ቅጽል ስምህ ..ሙዳይ አስደንግጥ.. ነበር የምትሉኝን የስም ማጥፋት አልቀበለውም)፡፡ እና በዚህ አይነት በሲኒ ማስቀመጫ ለተጋገረ እንጀራ ..ከሙዳይ.. የተሻለ ማስቀመጫ ወዴት ይገኛል? በእግረ መንገዱም እንጀራ ከጉልትና ከኪዮስክ ወጥቶ ፒያሳ ..ብር..ና ..ወርቅ.. ቤቶች ውስጥ ..ካራት.. ወጥቶለት በግራም መሸጥ ይጀምር ይሆናል፡፡ (ጉድ በል የባህር ዳሩ)
ለጊዜው ግን ከስራ ወጥቶ እግረ መንገዱን እንጀራውን አስጠቅልሎ በጉያው ሻጥ ያደረገው ላጤ ጐልማሳ፤ አሁንም ስለ ግዥ እንጀራ ይወራረዳል - ከሆዱ ጋር ለሆዱ በሆዱ፡፡ ..እንዲያው መቶው እንጀራ ቢከመር ከላይ በኩል አፍጥጬ ባየው፤ በዘጠና ዘጠኙ እንጀራ ስር፤ የመጀመያውን እንጀራ አይኑ ቁልጭ እንዳለ አየዋለሁ? አላየውም? አየዋለሁ? አላየውም?..... እያለ ይወራረዳል፡፡
እንጀራን በትዝታ መነጽር የኋሊት ስንቃኘው ..ያኔ፣ ጥንት ጥንት፣ ያኔ.. ለመባል በማይበቃበት ዘመን፤ ..ካሲና.. እና ..እንጐቻ.. የሚባሉ እንጀራ መሰል ነገሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ፣ ዛሬ በተደረገው የኢኮኖሚ ሽግሽግ እንጀራ በእነሱ መጠን አቋርጦ ቁልቁል ሲወርድ ..ካሲና.. እና ..እንጐቻ.. ግን ዛሬ በመብልነት ባይገኙም፤ በስማቸው ላይ መጠነኛ ለውጥ ተደርጐበት፤ ..ካሲና.. ወደ ..ከከሲና.. ዘፈንነት ሲሻሻል፤ ..እንጐቻ.. ደግሞ ..እንጐቻ - ወግ.. ተብሎ ለአንድ የድርሰት ዘርፍ መጠሪያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡
የደረቅ እንጀራ ሽያጭ ጉዳይ፤ ለ..ደረጃ መዳቢ.. እሩቅ ቢሆንም፤ ለ ..ደረጃ አዳሪ.. ሁሉ የእለት ጉዳዩ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ ለምን የተሠራበት ጥሬ ዕቃ እላዩ ላይ አይለጠፍበትም? ምክንያቱም አንዳንድ እንጀራኮ የግድ መጠቅለያ ፌስታሉ ላይ እንደ አረቄ ሁሉ መለጠፍ ያለበት ነው - ..የሎሚ እንጀራ.. ተብሎ፡፡ (ደግሞ ይህንን ስላችሁ፤ ገና ለገና ሠፈሬን የምታውቁ፤ ለካስ በጠረኑም ቢሆን እንዲደርስህ ብለህ ነው ..መካኒሳ.. ..መሬሳ.. ፋብሪካው ጥግ ፈልገህ የተከራየኸው ትላላችሁ፡፡ የ..እህል ውሃ.. ጉዳይ ሆኖብኝ ብቻ ነው ብዬ እመልሳለሁ)
ስለ ደረቅ እንጀራ ገዥ ደንበኞች ስናስብ አዛውንቷ የደረቅ እንጀራ ደንበኛም ከ..ኩል ማን.. እንጀራ የገዙትን እንጀራ እያጣጠፉ፣ እያገላበጡ... ደግሞ ድንገተኛ ንጥሻቸው ከሰሀኑ ላይ አፈናጥሮ ከአፈር እንዳጨምርባቸው አፋቸውን በእጃቸው እያፈኑ በማጉተምተም፤ ..ወይ እንጀራና ጊዜ! ኩርማን እንጀራ! እውነትም የኩርማን እንጀራ.. እያሉ ቢያሳቅሉ ማን ይፈርድባቸዋል? ትዝታቸውን አጠንጥነው የኋላውን ወደፊት ሲስቡትም... ..ጉድ እኮ ነው! በእኛ በሞኞቹ ጊዜ፤ ሦስቱን በአራት ፍራንክ በየጉልቱ እንሸጠው የነበረው እንጀራኮ፤ ሊጡን ለማዞር በምጣዱ ዙሪያ የሚያሶመሱም ብርቱ ፈረስ የሚያስፈልግ ነበር የሚመስለው፡፡ ዛሬማ ሊጥ መቀባትና ምራቅን ቢቅ ማድረግ እኩል ሆነው አረፉት..... ይላሉ፡፡
እኒህ አዛውንት ስለ እንጀራ በሆዳቸው ከመለፍለፍ አልፈው በጭንቅላታቸው  መፈላሰፍ ይቃጣቸዋል - እንዲያው ሀሳቤን ከመዝገቡ አያስገባብኝና፤ እሱ ባለቤቱ አልሽ አይበለኝና፤ እንዲያው ሀሳቤን ከመዝገቡ አያስገባብኝና፤ አሁን እኔ ይህችን በአፌ አድርጌ ..በላሁ.. ነው እምል ወይስ ..ቆረብኩ..?
ይህንን ሁሉ ..ካነሳን ከጣልን.. በኋላ በእንጀራ ግዢና ሽያጭ ጉዳይ ላይ ግራ ቀኝ ማትሮ ሚዛናዊ ለመሆን ያህል፤ መቼም ..የጤፍ ዋጋ እንዳበደች ኳስ በየሰአቱ ሽቅብ በሚጐንበት ሁኔታ..፤ እንደ ጥንቱ ዘመን ..ውሻ በቁልቁለት የማይጐትተው.. እንጀራ ማቅረብ አይጠበቅብንም የሚለውን የእንጀራ ሻጮች ..እሮሮ.. ማድመጡ ተገቢ ነው፡፡ ቢሆንም ..ጥራጥሬ.. እንደ ጥንቱ ዘመን ለ..ሠንጋፈረስ.. እራትነት ብቻ ባይፈረድበትም እንኳ፤ ንፍሮና ቆሎን አሳብሮ ከ..እንጀራ.. ጋር ለመዛመድ ከ..ጤፍ.. ጋር የዘር ሐረጉ አይፈቅድለትም፡፡ ለዛሬው የጤፍ እንጀራን በተመጣጣኝ መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እየተመኘሁ፤ እኔም የእንጀራ ደምበኞቼ ..እንጀራ ጨርሰናል.. ብለው ኪዮስካቸውን ሳይዘጉብኝ ፌስታሌን አንጠልጥዬ  መብረሬ ስለሆነ፤ እዚህች ላይ ለአዲሱ ዘመን ..የእንጀራ ሚኒማይዝ.. ምጣድ ውጣ
የ..እንጀራ ማክሲማይዝ.. ምጣድ ግባ....
ተባብለን እንሠነባበታለን፡፡

 

Read 4615 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:30