Saturday, 01 October 2011 12:44

..ይቅርታ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም.....

Written by  በፍቃዱ አባይ
Rate this item
(4 votes)

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በዘመነኛ ስሙ ኢትዮ-ቴሌኮም በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በሐገራችን የሚሰጡ ማናቸውንም ግልጋሎቶች በብቸኝነት የሚሰጥም የሚነሳም ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ካለው ዘርፈ ብዙ ግልጋሎትና ጠቀሜታ አንጻርም ስሙ ግዘፍ ነስቶ ለዘመናት ዘልቋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰጠን ባለው ዘመን አመጣሽ የቴክኖሎጂ አቅርቦት መንስኤነት በዕለት ተዕለት ህይወታችን ላይ ከፍ ያለ ተጽእኖ ለመፍጠርም ተችሎታል፡፡ ለዚህም ነው ሰጪም ነሺም የሚሆነው (የፈጣሪን አልረሳሁም፡፡ ርዕሴ ስላልሆነ እንጂ) ዓለም በዘመነ መረጃ መነሾነት እየጠበበች ለመምጣቷ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም በዕለታዊ ህይወታችን አዛዥ ናዛዥ የሚሆነውም ከላይ በጠቀስኳቸው ማሳያዎች ምክንያት ነው፡፡

ቀደም ሲል ራሱ ተቋሙ ጭምር እንደ ብርቅ ያያቸው የነበሩ የመገናኛ ዘዴዎችን አሁን... አሁን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት መገልገላችን የማይቀር ሆኗል፡፡ በዚህ የተስማማንና እጃችንን ታጥበን ከተቋሙ ጋር የተጠቃሚነት የውዴታ ግዴታ ውል የገባን ከሆነ ደግሞ እንደ ደንበኛ ንጉስ የመሆን ክብር ባለቤት ባንሆን እንኳን በመሰረታዊነት ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት ከተቋሙ የምንጠብቀው አንደኛው ግዴታ ነው፡፡  
ተቋሙ የስምም ሆነ የአሰራር ለውጥ ከማድረጉ በፊትም ሆነ በኋላ እየሰጣቸው ካሉ አዳዲስና ነባር ግልጋሎቶች አንጻር በጠንካራ ሆነ በደካማ የምንነቅስለት ጉዳይ አጥቶ አያውቅም፡፡ ቀዳሚ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ለእናቱ በመሆኑ ነው፡፡ የምንሸሸግበት ሌላ ጥግ ስለሌለንም ጭምር፡፡ (እዚህ ጋር ድሮ በአማተር ክበባት ተውኔትን ለመተወን ስንነሳ ከምናደርጋቸው የድምጽ ልምምዶች አንደኛዋ ቃለ-መነባንብ ትዝ አለችኝ፡፡ እንዲህ ትላለች፡፡ ..ብሳሳትም ባልሳሳትም ንጉስ ነኝና መግዛት አለብኝ፡፡.. የኛና የቴሌ ጉዳይም እንዲያው ነው፡፡ ብንወቅስም ብናንቆለጳጵስም ያው አንድ ለእናቱን ነው፡፡ ስለሆነም በአዲሱ አመት ፊቴን ወደ እርሱ አዞርኩኝ፡፡ በራስህ አይን ግንድ ይዘህ እየዞርክ የቴሌን ጉድፍ... ካላላችሁኝ፡፡
ከሸጋው ልጀምር፡፡ በ2004 አዲስ አመት ተቋሙ በቅናሽ ዋጋ የሞባይል ቀፎና ሲም ካርድ ለተጠቃሚው ማቅረብ መጀመሩ፤ ለወር የሚቆይ የሲም ካርድ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉ፤ ተከታታይ ማስታወቂያዎችን በእጅ ስልኮቻችን በየዕለቱ መላኩ ሊነሱ የሚገባቸው ጥንካሬዎቹ ናቸው፡፡ ስራ አጥ በበዛበት ሐገር ከ8000 በላይ የቀድሞ ሰራተኞቹን ማሰናበቱ፤ የሽቦ አልቦ ግልጋሎቶች ጥራት መቀነስና መቆራረጥ ደግሞ ከተጠቃሽ ድክመቶቹ ውስጥ ናቸው፡፡ እኔም በአዲሱ ዓመት የሙዚቃ ያህል እየሰለቸኝም ቢሆን እየሰማኋቸው ካሉት አዲሱ የኢትዮ-ቴሌኮም የአገልግሎት ችግሮች መሐከል በተለይም በአንዱ ዙሪያ አጠነጥናለሁ፡፡
ከላይ የጽሑፌ ዋንኛ ርዕስ ያደረኩት ዐረፍተ ነገር የኢትዮ-ቴሌኮም የአዲሱ ዓመት አዲስ ስጦታ ብዬዋለሁ፡፡ ..ይቅርታ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም፡፡..  ይህን አዲስ ፈሊጥ (አብሻቂ መልዕክት) መስማት የጀመርኩት በአዲሱ ዓመት በመሆኑ ነው የአዲስ ዓመት ስጦታ ለማለት የተገደድኩት፡፡ ከዚህ በፊት የለመድኳቸው እና እንደ ቃለ-ተውኔት አጥንቼ የማነበንባቸውንና ሰርክ የማላመልጣቸውን የአገልግሎት መልእክቶች (የደወሉላቸው ደንበኛ ስልክ መልዕክት እያስተላለፈ ስለሆነ... ፤ የደወሉላቸው ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል...፤ መስመሮች ሁሉ ለጊዜው...) የመሳሰሉ መልዕክቶችን መስማትና የጥራት ችግሮችን የመገላገል አምሮቴ ሳይሳካ ተቋሙ ተጨማሪ ዕዳ መስጠቱ ቢያሳስበኝ ነው ለመጻፍ መነሳሳቴ፡፡
ለመሆኑ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮ-ቴሌኮም ደንበኛውን አሁን ማግኘት አትችልም ሲለኝ የኔን ደንበኝነትስ ከምን ቆጥሮት ነው? የምፈልጋቸውን ደንበኛ ለማግኘትስ ውሳኔ ማሳለፍ ያለበት አገልግሎት ሰጪው ወይስ ተፈላጊው ግለሰብ? ለመሆኑ የሐገሪቱንና የተቋሙን ህግ አክብሮ ለሚጠቀም ዜጋ (ደንበኛ) ከሰው ጋር በድምጽ መገናኘትን ለመከልከል ለኢትዮ-ቴሌኮም መብቱን ማን ሰጠው? ተቋሙ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻርስ ደንበኛን እንዳይገኝ መከልከል ከገቢ አንጻር፤ ሰዎች በፈለጉት ወቅት (ጊዜ) ከፈለጉት ግለሰብና ተቋም ጋር የመገናኘት መሰረታዊ መብትን ከመከልከል አንጻርና ከሙያዊ ስነ ምግባር አኳያ አባባሉ ምን ያህል አግባብነት አለው? የሚሉና ተጨማሪ ጥያቄዎችን በማንሳት መሞገት ይቻላል፡፡ እስኪ ከላይ ከተነሱት መሰረታዊ ጥያቄዎች አንጻር ጥቂቶቹን ብቻ ልነካካ፡፡  
ይህንን ግላዊ ምልከታዬን ሳነሳም ቀደም ሲል በተለይም በሞባይል አገልግሎት ላይ ይታዩ የነበሩ ችግሮች በአዲሱ አመራርና ድርጅት አማካኝነት ይቀረፋል፡፡ ተቋሙም የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል የሚለውን ቃል-ኪዳን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ትኩረቴም በአዲስ አበባ ያለውን ግልጋሎትና ችግሮችን ብቻ የተመለከተ ይሆናል፡፡
..ይቅርታ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን
ማግኘት አይችሉም፡፡..    
የአዲሱ ዓመት ስጦታ ያልኩት ይህ ገዳቢና ስሜትን የሚጎዳ አነጋገር በተቋሙ ሊታሰብበት የሚገባው ይመስለኛል፡፡ ለደንበኞች መልዕክትን በተገቢ፤ ግልጽና ሳቢ በሆነ መልኩ ማስተላለፍ ከአገልግሎት ሰጪዎች የሚጠበቅ ጥበብ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ2001 ዓ.ም የተጠቀመበት ቴሌቪዥንን የማስመዝገብ ግዴታ እንዴት ውጤታማ እንደሆነ ለማወቅ በወቅቱ በየመመዝገቢያ ስፍራ የነበረውን ወረፋ ማስታወሱ ብቻ ይበቃል፡፡ ለዚህ መሰሉ ውጤት መገኘት የመልዕክቱ አቀራረብ የነበረው ጉልበት ወሳኝ ነበር፡፡ ችግሩ አካሄዱ ቀጣይነት ስላልነበረው በስኬቱ መቀጠል አልተቻለውም፡፡ የኢ.ሬ.ቴ.ድን በምሳሌነት ማንሳቴ kxþT×-ቴሌ÷ም ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ራሱ ቴሌ የሞባይል ቀፎና ሲም ካርድን (GSM) ለማዳረስ የተጠቀመባቸውን ስልቶችና ዘዴዎች ላስተዋለ በርዕሱ ያነሳሁት አነጋገር (መልዕክት) ምንም እንኳን ይቅርታን ያስቀደመ ቢሆንም ተገቢነት እንደጎደለው ተሰምቶኛል፡፡ በተለይም .....ማግኘት አይችሉም!፡፡.. የሚለው መልዕክት ከትህትናው ይልቅ ትዕዛዝ ሰጪነቱ ያመዝናል፡፡ ለኔ ይህ መልዕክት ምንም እንኳን መረዋ ድምጽን በተላበሰች እንስት ቢደርሰኝም ቃናው .....ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ፈጽሞ የተከለከለ ነወ.. ከሚለው   የደርግ የኖረ ማሳሰቢያ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ (ከታላቅ አብዮታዊ ይቅርታ ጋር፡፡) እናም xþT×-ቴሌ÷ም ቢያስብበት ምን ይለዋል? ያስብበት አላልኩም፡፡ አባባሉ ትዕዛዝ እንዳይሆንብኝ ፈርቼ ነው፡፡
ደንበኛን ከደንበኛ ማበላለጥ  
በአንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውስጥ ግልጋሎት የሚያገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች በእኩልነት መታየት አለባቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ደንበኛውን አሁን ማግኘት አይችሉም ሲባል ግን የመብትም ጥያቄ ይጭርብኛል፡፡ የፈለኩትን ደንበኛ ማግኘት እንደማልችል የሚነገረኝ ደዋይም (ደንበኛም) የዚህ ድርጅት ደንበኛነቴን መሆኔን የዘነጋ ስለመሆኑም ይነግረኛል መልዕክቱ፡፡ በተጨማሪም ደንበኛውን አሁን ማግኘት እንደማልችል የነገረኝ ተቋም፤ ተፈላጊውን ደንበኛ መቼ ላገኝ እንደምችል ግን አይነግረኝም፡፡ አሁን ማግኘት አይችሉም ለማለት ድፍረቱና እውቀቱ ካለው ተቋም አማራጭንም ሊያቀርብልኝ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አሁን ማግኘት አይችሉም የሚለው ቃና ነጻነትን አልሰጠኝም፡፡ በአንድ ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ማድሊን ኦልብራይት፤ በስልጣን ዘመናቸው ልጆቻቸውን ሊያገኙአቸው ፈልገው ስልክ በሚደውሉ ወቅት ከቢሮአቸው የሚመጣላቸው መልስ ሁልጊዜም ልጆቹን ያበሳጫቸው ነበር፡፡ የስልክ መልዕክት ተቀባዮቹ .....ይቅርታ ልጆች፤ እናታችሁን አሁን ማግኘት አትችሉም፡፡.. ይሏቸው እንደነበርና ይህም ለልጆቻቸው መልካም ስሜትን ይሰጣቸው እንዳልነበር እና ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ግን ይህንን መሰሉን መልዕክት መስማት በማቆማቸውና ጊዜያቸውን ለቤተሰባቸው ጭምር መስጠት በመቻላቸው  ልጆቻቸው መደሰታቸውን መናገራቸውን ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ዓለምን ለሚመሩ እናት ልጆች እንኳን መልዕክቱ ምን ያህል ይጎረብጣቸው እንደነበር ማመዛዘን ለሚመለከተው ተቋም የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስገርመኝ ሌላው ጉዳይ አጠገብ ላጠገብ ሆነንም ብንደዋወል ማግኘት አትችሉም መባላችን ነው፡፡ (እባክዎ ላፍታ ጋዜጣውን ያስቀምጡና ሞባይሎን በመደወል ይሞክሩት፡፡ ሐሳብ ከኔ፤ ሒሳብ ከራስዎት መሆኑን እንዳይዘነጉ) እኔ ግን በሁኔታው ተገርሜ ሳስብ ማግኘት የማንችለው ደንበኛውን ሳይሆን ራሱ አገልግሎት ሰጪውን ይመስለኛል፡፡ ጥራትን ተላብሶ ቀልጠፍ ብሎ ምን ልታዘዝ የሚል ታማኝ አገልጋይ መሆን ውድ በሆነባት ሐገሬ፣ xþT×-t½l¤÷ምን መካሪ ሳያስፈልገው አልቀረም፡፡
የገቢ ማነስ ተጽዕኖ  
ይህንን አላስፈላጊና አሰልቺ መልዕክት ደጋግሞ የሚያደምጥ የተቋሙ ደንበኛ በድርጅቱ የገቢ መጠን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ሞባይል ስልክን ቀላል፤ ተመራጭና ሳቢ ከሚያደርጉት አማራጮች አንደኛው ለፈጣን ግልጋሎት ምቹ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ደንበኛ ይህንንና መሰል አላስፈላጊ መልዕክቶችን በተደጋጋሚ መስማቱ በተጠቃሚነቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድርና ወደ ሌላ የመገናኛ ስልት አማራጭ እንዲያዘነብል ይመራዋል፡፡ (ወደ ሌላ ተቋም መቼም አልልም፡፡) ደንበኛው አገልግሎት በሚሰጠው ተቋም ላይ እምነቱንና ፍላጎቱን ማጣቱ ደግሞ ለተቋሙ ከገቢ የማይወዳደር ተጨማሪ ጥቅም ያሳጣዋል ብዬም አስቤያለሁ፡፡ ገቢውን ከፍ አድርጎ ወጪውን ለመቀነስ በሚል ሰበብ ከስምንት ሺህ ብር በላይ ነባር ሰራተኞቹን ለቀነሰ ድርጅት ደግሞ ገቢን የሚቀንሱ አማራጮችን መቀነስ ለነገ የማይለው ምርጫው ይመስለኛል፡፡
ለማሳያነት ከላይ ያተኮርኩባቸው አብይና ንዑስ ሐሳቦቼ ላይ ማተኮሬ በሞባይል አገልግሎት ላይ ብቻ ያየኋቸውን ችግሮች ለመጠቆም በሚል ቀና አስተሳሰብ ብቻ ነው፡፡ የተቋሙ መልካም ጅምሮች እንዳሉ ሆነው ከሞባይል ባልተናነሰ በኢንተርኔት (CDMA, DIAL UP) በተለምዶ Wireless ተብለው በሚጠሩት ተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይም የሚታዩት ችግሮች ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ የመስመር መቆራረጥ፤ ምንም አይነት ምላሽ ያለመስጠት፤ ደዋዩ ምንም አይነት የጥሪ ድምጽ (tone) ሳይሰማ የስልክ መነሳት፤ የስልክ ግንኙነቱ በደቂቃዎች የተወሰነ መሆን (ብዙው ጊዜ ሁለት ደቂቃ ብቻ) የኔትዎርክ መጨናነቅ... ወዘተ በተያያዥነት የሚነሱ፤ ሲነሱ የሰነበቱ፤ አሁንም መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች ናቸው፡፡  
ያም ሆኖ ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ተጠቃሽ ችግሮቹ ተወግደው ዳግም ብዕራችንን ስናነሳ ውዳሴያችን በርክቶ ወቀሳችን ይቀንስ ዘንድ የመጪው አዲስ አመት አዲስ ስጦታችን ይሆን ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል?

 

Read 5930 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 12:47