ለመሆኑ ጥሬ ሥጋ /በተለያዩ መልኩ/ መብላት በአገራችን መች ተጀመረ? ደራሲ አለማየሁ ነሪ ..ኢትዮጵያ ሲሳይ.. በሚል ርዕስ በ1998 ዓ.ም ባሰሙት መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ የሚከተለውን መልስ አኑረዋል፡-
..ከክርስቶስ ልደት 29 ዓመት በፊት የሮማው ንጉሥ አውግስቶስ ቄሣራ አገራችን ኢትዮጵያን በሰሜኑ በኩል በጦር ወርሮ ለመግባት የጦር እንደራሴው የነበረ ጄኔራል ከመላኩ በፊት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥሬ ሥጋ ቢበላ እንደነውር ይቆጠርበት፣ የነበረ ብቻ ሳይሆን በፍፁም የተከለከለም እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ በጦርነቱ ወቅትም ዘማች ሠራዊት ምግቡን ለማብሰል እሳት በሚያነድበት ስፍራ የሚወጣውን ጭስ በመመልከት የጠላት ሠራዊት አስከፊ አደጋ እያደረሰ በወገን ላይ ጉዳት ማመዘኑ፣ የወቅቱ ኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎች ደረሱበት፡፡ በጭሱ ሳቢያ የሚደርሰው ሽንፈትም እጅግ ስለበዛ ሥጋ ለማብሰያ እሳት እንዳይቀጣጠል፣ ጭስ እንዲቀር፣ የኢትዮጵያ ጦርም ጥሬ ሥጋ እንዲበላ እንደታዘዘ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥሬ ሥጋ መብላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ባህል ሆኖ መለመዱን.. የዕድሜ ባለፀጎች ይናገራሉ፡፡
ጥሬ ሥጋን መብላት በአገራችን በዚህ መልኩ ከተጀመረ በኋላ በተለይ ከጉራጌ ብሔረሰብ ባህላዊ ምግቦች አንዱ ከመሆን አልፎ በኢትዮጵያ የባህል ምግቦች ውስጥ ቀድመው ከሚጠሩት መሐል የሚገኘው ክትፎ፤ በተለይ በመስቀል በዓል ወቅት በጉራጌዎች ቤት እንደ ምግብ ይበላል ሳይሆን እንደ ውሃ ይጠጣል በማለት የሚገልፀው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ ነው፡፡
ምንጭ - (የዴንጌሳት በዓልን አስመልክቶ በ2004 ዓ.ም ከወጣው ..ዴንጌሳት መስቀል በጉራጌ.. የተሰኘ አነስተኛ መሄት ኤዲት ተደርጐ የተወደሰ)