Saturday, 08 October 2011 09:44

ደስተኛው ልዑል

Written by  ትርጉም ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

ተረት - ተረት
ረጅም አምድ ላይ የቆመ እና ከተማውን ቁልቁል የሚመለከት የደስተኛ ልዑል ሐውልት አለ፡፡ ሐውልቱ ከላይ እስከ ታች በንፁህ የወርቅ ቅጠል የተለበጠ ነው፡፡ ዓይኑም በሁለት ደማቅ እንቁ የተሰራ ነው፡፡ የሻምላው እጀታም በአልማዝ የተለበጠ ነው፡፡ ይህን ሐውልት ብዙዎች ያደንቁታል፡፡ «ሐውልቱ እንደ ነፋስ አቅጣጫ ጠቋሚ ውብ ነው ´ አለ፤ ለኪነጥበብ ሥራዎች አድናቆት ያለው ሰው የሚል ዝና ማግኘት የሚፈልግ አንድ ከንቱ የከተማ ምክር ቤት አባል፡፡ «ሆኖም ለህዝብ የሚሰጠው ጠቀሜታ ብዙ አይደለም ´ ሲል አከለ፤ የተግባር ሰው ያልሆነ ዋዘኛ የሚል ወቀሳ እንዳይከተለው በመሥጋት፡፡ ሆኖም ሰውየው ጨርሶ ዋዘኛ የሚባል አልነበረም፡፡

“ለምን እንደ ደስተኛው ልዑል አትሆንም “ አለች አንዲት እናት፤ ጨረቃን አውርዱልኝ እያለ ለሚያለቅስ ልጇ፡፡  “ደስተኛው ንጉስ ምንም ነገር አምጡ ብሎ አያለቅስም፡፡ “
“በምድር ላይ ደስተኛ የሆነ ሰው መኖሩን በማወቄ ደስ ብሎኛል “ ሲል አጉተመተመ፡፡ አስደናቂውን ሐውልት ሲመለከት የነበረው የተበሳጨ ሰው፡፡
“መላአክ ይመስላል “ አሉ ደማቅ ቀይ ካባና እና ፀአዳ ነጭ ጋወን ያደረጉት የበጎ አድራጎት ህፃናት ከቤተክርስቲያን ሲወጡ፡፡
“እንዴት አወቃችሁ? “ አለ የሂሳብ መምህሩ፡፡  “ለመሆኑ መላአክ አይታችሁ ታውቃላችሁ? “
“እንዴ አ በህልማችን አይተን እናውቃለን “ ሲሉ መለሱ ህፃናቱ፡፡ የሂሳብ መምህሩ ፊቱን አኮሳትሮ እና አጨፍግጎ ተመለከታቸው፡፡ የልጆቹ ህልመኛነት ስላናደደው፡፡
አንድ ቀን ማታ በከተማው ላይ አንዲት ትንሽ ገዴ ሲበር ታየ፡፡ ጓደኞቹ ከስድስት ሳምንታት በፊት ወደ ግብፅ ሄደዋል፡፡ እርሱ ግን ወደኋላ ቀረ፡፡ የቀረውም ከአንዲት ውብ ሸንበቆ ጋር ፍቅር ይዞት ነው፡፡ ሸንበቆዋን ያገኛት በፀደይ ወር መግቢያ ላይ በወንዙ ተፋሰስ አንድ ትልቅ ቢራቢሮ እያሳደደ ሲበር ነው፡፡ በሸንበቆዋ ቀጭን ወገብ ቀልቡ ጠፍቶ ሊያናግራት ቆም አለ፡፡
“ውዴ ላድርግሽ? “ አለ ግርግር ሳያበዛ ፍቅሩን መግለፅ የፈለገው ትንሹ ገዴ፡፡ ሸንበቆዋም ዝቅ ብላ እጅ ነሳችው፡፡ እርሱም ዙሪያ ዙሪያዋን እያለ በረረ፡፡ በክንፎቹ ውሃውን እየነካ ብርማ የውሃ ሞገድ እና ነመምቴ እየፈጠረ፡፡ የገዴ የፍቅር ማግባቢያ ዘዬው ይሄው ነው፡፡ እንዲህ እያደረገ የበጋው ወራት አለፈ፡፡
“ይህ አስቂኝ ፍቅር ነው “ አለ ሌላ ትንሽ ገዴ በረብሻ ድምፅ እየጮኸ፡፡  “ገንዘብ የላትም ዘመዶቿ ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡ “ በእውነትም ወንዙ በሸንበቆ የተሞላ ነበር፡፡ እናም የመኸር ወቅት ሲገባ ገዴዎቹ በሙሉ አካባቢውን ለቀው ተሰደዱ፡፡
እነሱ ከሄዱ በኋላ አፍቃሪው ገዴ ብቸኝነት ተሰማው፡፡ የጀመረው የፍቅር ህይወትም ያሰለቸው ጀመር፡፡  “እርሷ እንደሆን አትናገር አትጋገር “ አለ፡፡  “ደግሞ ዝም ብላ የምትሽኮረመም ባለጌ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ምክንያቱም ዘወትር ከንፋሱ ጋር ስትቀብጥ አያታለሁ፡፡ “ በርግጥም ንፋስ በነፈሰ ጊዜ ሁሉ ሸንበቆዋ እጅግ ባማረ ሞገስ ለንፋሱ እጅ ትነሳለች፡፡  “በተጨማሪም ከቤት መውጣት የማትወድ ናት “ ሲል ቀጠለ፡፡  “እኔ ደግሞ መጓዝ መሄድ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህ ሚስቴም መጓዝና መሄድ የምትወድ መሆን ይኖርባታል፡፡ “
“ከኔ ጋር ትሄጃለሽ? “ አላት ገዴው በመጨረሻ፡፡ ሆኖም ሸንበቆዋ ራሷን ወዘወዘች፡፡ እርሷ ከቤቷ ጋር ፍፁም የተቆራኘች ናት፡፡
“እስከዛሬ ስትጫወችብኝ ቆይተሻል “ ሲል ጮኸ፡፡  “አሁን ወደ ፒራሚዶቹ መሄዴ ነው፡፡ በይ ደህና ሁኚ “ አላትና በረረ፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲበር ውሎ ሲመሻሽ ከአንድ ከተማ ደረሰ፡፡  “እንግዲህ የት አረፍ ብዬ ልደር? “ አለ፤  “ከተማዋ ደህና ዝግጅት ያላት እንደሆነች ተስፋ አደርጋለሁ “፡፡
ከዚያም ከረጅም አምድ ላይ የቆመ አንድ ሐውልት አየ፡፡
“በቃ እዚያ ሄጄ አድራለሁ “ አለ፤ “ንጹህ አየር እንደልብ የሚገኝባት ጥሩ ቦታ ነች፡፡” ስለዚህ ወደ ሐውልቱ በሮ ከደስተኛው ልዑል እግሮች መሀል አረፈ፡፡  “በወርቅ የተሰራ መኝታ ቤት አለኝ “ አለ ዝቅ ባለ ድምፅ ለራሱ፡፡ አካባቢውን እየቃኘና እንቅልፉን ለመለጠጥ እየተደላደለ፡፡ ሆኖም ጭንቅላቱን በክንፉ ሽጉጥ እንዳደረገ ትልቅ የውሃ ጠብታ ወደቀበት፡፡  “ምን ያለ ጉድ ነው “አለ፤  “በሰማይ እንኳን አንድም ደመና አይታይም፡፡ ይኸው ከዋክብቱ ሲንቦገቦጉ ይታያል፡፡ ግን ዝናብ ይወርድብኛል፡፡ በሰሜን አውሮፓ ያለ የአየር ጠባይ እኮ በጣም አስቀያሚ ነው፡፡ ያቺ ሸንበቆ ዝናብን አብዝታ ትወድ ነበር፡፡ ግን ለሌላ የማታስብ ስግብግብ በመሆኗ ነው “
ደግሞ ሌላ ወፍራም ውሃ ጠብ አለበት፡፡
“ከዝናብ የማይከልለኝ ከሆነ የሐውልት ጥቅሙ ምንድን ነው? “ አለ፤  “በደንብ የሚሞቅ የጭስ ማውጫ ቀዳዳ መፈለግ ይሻለኛል “ አለና ለመብረር ወሰነ፡፡
ግን ክንፉን ዘርግቶ ከመብረሩ በፊት ሦስተኛ ጠብታ አረፈበት፡፡ ቀና ብሎ አየ፡፡ የሆነውን ነገር አየ፡፡ ምን ይሆን የታየው?
የደስተኛው ልዑል አይኖች በዕንባ ጢም ብለዋል፡፡ ሞልተውም በወርቃማ ጉንጮቹ ኩልል እያሉ ይወርዳሉ፡፡ በጨረቃ ብርሐን ፊቱን ሲያዩት እጅግ ያማረ ነው፡፡ ስለዚህ ትንሹ ገዴ አዘነለት፡፡
“ማነህ አንተ? “ አለ
“እኔ ደስተኛው ልዑል ነኝ “
“እና ለምን ታለቅሳለህ? “ ሲል ጠየቀ ገዴው፤  “አካሌን በእንባ አራስከው እኮ “
“በህይወት ሳለሁና የሰው ልብ በነበረኝ ጊዜ “ ሲል መለሰ ሐውልቱ፤  “እንባ ምን እንደነበረ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም ሀዘን ሊገባ ከማይችልበት ከሳንሶቺ ቤተመንግስት የምኖር ሰው ነበርኩ፡፡ ቀን ቀን ከጓደኞቼ ጋር ባትክልቱ ሥፍራ ስጫወት እውላለሁ፡፡ ማታ ማታ በትልቁ እልፍኝ እደንሳለሁ፡፡ የአትክልቱን ሥፍራ ከከበበው ረጅም ግንብ ባሻገር  ምን አለ ብዬ ጠይቄ አላውቅም፡፡ በዙሪያዬ ያለው ነገር ሁሉ ውብ እና አስደሳች ነበር፡፡ ባለሟሎቼ እና ተከታዮቼ ደስተኛው ልዑል እያሉ ይጠሩኛል፡፡ በእውነትም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ የሥጋ ፈቃድ አለመጉደል ደስታ ከሆነ፡፡ እንደዚህ ሆኜ ኖሬ እንደዚሁ ሞትኩ፡፡ እናም አሁን ስለሞትኩኝ እዚህ ከፍ ካለ ቦታ ላይ አቆሙኝ፡፡ ይኸው አሁን በዚህ ከተማ ውስጥ ያለው አስቀያሚ የመከራ ህይወት ሁሉ ይታየኛል፡፡ ልቤ ከብረት የተሰራ ቢሆንም ከማልቀስ ግን አላዳነኝም፡፡ ከማልቀስም በቀር ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ “
“ምን! ይሄ ግዑዝ ወርቅ አይደለም እንዴ?” አለ ገዴው ፡፡ አስተያየቱን ጮኽ ብሎ ለመናገር ትህትና ገድቦታል፡፡
“እዚያ ማዶ “ አለ ሐውልቱ ለጆሮ በሚጥም ሙዚቃዊ ድምፅ፤  “እዚያ ማዶ የአንድ ድሃ ሰው ቤት አለ፡፡ ከቤቱ መስከቶች አንዱ ክፍት ነው፡፡ በዚያ የተከፈተ መስኮት ከጠረጴዛ አጠገብ የተቀመጠች አንዲት ሴት ትታየኛለች፡፡ ፊቷ ምጥጥ ያለና የተጎሳቀለ ነው፡፡ እጇ የቀላ እና ሸካራ ነው፡፡ ልብስ ሰፊ ስለሆነች እጇ በመርፌ የተወጋጋ ነው፡፡ የንግስቲቱ ደንገጡር በሚቀጥለው የዳንስ ዝግጅት ላይ የምትለብሰውን የሀር ጋዎን በአበባ ጌጥ እየጠለፈች ነበር፡፡ ከአንድ ጥግ ያለው አልጋ ላይ ትንሽዋ ልጇ ታሞ ተኝቷል፡፡ ኃይለኛ ትኩሳት አለው፡፡ እናም እናቱን ብርቱካን ስጪኝ ይላታል፡፡ ነገር ግን እናቱ ከወንዝ ውሃ በቀር ሌላ ልትሰጠው የምትችለው ነገር የላትም፡፡ ስለዚህ እያለቀሰ ነው፡፡ ገዴ - ገዴ ትንሹ ገዴ ከሻሞላዬ እጀታ ያለውን አልማዝ ወስደህ ትሰጥልኛለህ? እኔ እግሬ ከአምዱ ስለተጣበቀ መንቀሳቀስ አልችልም፡፡ “
“አይ! ዘመዶቼ ወደ ግብፅ ሄደዋል፡፡ እኔንም ይመጣል እያሉ ይጠብቁኛል “ አለ ገዴው፡፡  “በአሁኑ ሰዓት ጓደኞቼ በአባይ ወንዝ ላይ - ታች ይበራሉ፡፡ ከሎተስ አበባዎችም ጋር ያወራሉ፡፡ ወደ ታላቁ ንጉስ መቃብር ሄደውም ይተኛሉ፡፡ ንጉሱ በአማረ የሬሳ ሳጥን ውስጥ ሆኖ በዚያ ይገኛል፡፡ በቢጫ የሀር ጨርቅ ተጠቅልሏል፡፡ በማድረቂያ ቅመምም ደርቋል፡፡ በአንገቱም አካባቢ ፍዝ አረንጓዴ የከበረ ድንጋይ አለ፡፡ እጆቹም እንደጠዘለ ቅጠል ናቸው፡፡
“ገዴ፣ ገዴ፣ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “ከእኔ ጋር አንድ ሌሊት አታሳልፍም፡፡ ዛሬን አትላላከኝም “ ይኸውልህ - ልጁ በጣም ተጠምቷል፡፡ እናቱም በጣም እዝናለች፡፡ “
“አይ እኔ ልጆች አልወድም “ ሲል መለሰ ገዴው  “ባለፈው ጊዜ፤ በባህሩ አካባቢ ስኖር ሳለ ሁለት ባለጌ የወፍጮ ፈጭታው ልጆች ነበሩ፡፡ እነሱም በየጊዜው ድንጋይ ይወረውሩብኝ ነበር፡፡ በእርግጥ መትተውኝ አያውቁም፡፡ እኛ ገዴዎች በዚህ አንጠረጠርም፡፡ ደግሞም የእኔ ዘመዶች ፈጣን - ከተፎ - ተፌ በመሆን ዝና ያላቸው ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ፤ የልጆቹ አድራጎት የብልግናቸው ማሳያ ነው፡፡ “
ደስተኛው ልዑል አዘነ፡፡ ትንሹ ገዴም ቅር አለው፡፡  “ሀገሩ በጣም ይቀዘቅዛል “ አለ፤  “የሆነ ሆኖ ለአንድ ምሽት እዚህ አድሬ መልዕክትህን አደርስልሃለሁ፡፡
“አመሰግናለሁ፡፡ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፡፡
እናም ትንሹ ገዴ አልማዙን ከልዑሉ ሻምላ ነቅሎ በመንቆሩ ይዞ ከተማውን ቁልቁል እያየ በረረ፡፡በነጭ እብነበረድ የተሰሩ መላዕክት ባሉበት ቤተክርስትያን አቋርጦ በረረ፡፡ በቤተመንግስቱ አግድሞ ከነፈ፡፡ በዚያ ሲያልፍ የዳንስ ሁካታ ሰማ፡፡ አንዲት ልጃገረድ ከወዳጅዋ ጋር ከሰገነቱ ስትወርድ ተመለከተ፡፡  “ከዋክብቱ አያምሩም? “ አለ ወዳጅዋ፤  “የፍቅር ኃይልስ ምንኛ ታላቅ ነው “
“መቼም ቀሚሴ ለታላቁ መንግስታዊ ድግስ እንደሚደርስልኝ ተስፋ አለኝ “ አለች፡፡  “ካባዬ ላይ አበባ እንዲጠለፍበት ለሰፊ ሰጥቼ ነበር፡፡ ግን ጥልፍ ሰፊዋ በጣም ሰነፍ ሴት ነች “
ባህሩን አቋርጦ ከነፈ፡፡ በዚያም በመርከቦች ተራዳ የተንጠለጠሉ ፋኖሶችን አየ፡፡ በድሆች መንደር አቋርጦ ነጎደ፡፡ አዛውንት አይሁዶች አገኘና ሲማቱና በመዳብ ሚዛን ገንዘብ ሲመዝኑ ተመለከተ፡፡ በመጨረሻም ከድሃዋ ቤት ደርሶ ወደ ውስጥ አየ፡፡ ልጁ በጭንቀት ከአልጋው እየተገላበጠ ይወራጫል፡፡ እናትዬው በጣም ደክሟት ስለነበር እንቅልፍ ወስዷታል፡፡ ገዴው በመስኮቱ በኩል ዱብ አለና አልማዙን ጠረጴዛ ላይ ካለው የጣትዋ ቤዛ አጠገብ አስቀመጠ፡፡ ከዚያም በልጁ አልጋ ዙሪያ በቀስታ እየበረረ በክንፉ የልጁን ግንባር አራገበለት፡፡  “አቤት አሁን በረድ አልኩ “ አለ ልጁ  “አሁን በቃ ሊሻለኝ ነው “ አለና የጣፈጠ እንቅልፍ ውስጥ ገባ፡፡ገዴው ወደ ደስተኛው ልዑል በረረ፡፡ ያደረገውንም ነገረው፡፡  “በጣም ይገርማል “ አለ ገዴው፤  “አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ቢሆንም እኔ ሙቀት ይሰማኛል፡፡ “
“ይህ የሆነው ጥሩ ሥራ ስለሰራህ ነው፡፡ “ አለ ደስተኛው ንጉስ፡፡ ትንሹ ገዴ ያስብ ጀመር፡፡ በኋላም እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ገዴው ሁሌም ማሰብ ሲጀምር እንቅልፉ ይመጣል፡፡
ሲነጋ ወደ ወንዝ ወርዶ ገላውን ታጠበ፡፡  “እንዴት ያለ ትንግርት ነው “ አለ አንድ የአዕዋፍ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ድልድዩን አቋርጦ ሲሄድ ገዴውን ተመልክቶ፡፡  “ገዴ በክረምቱ! “ አለ፡፡ እናም ለአንድ ጋዜጣ ረጅም ደብዳቤ ፃፈ፡፡ ሁሉም የፕሮፌሰሩን ቃል ይጠቅሰው ጀመር፡፡ ደብዳቤው ምንም በማይገባቸው ቃላት የታጨቀ ስለነበር ሁሉም ይጠቅሱት ጀመር፡፡
“ዛሬ ምሽት ወደ ግብፅ እሄዳለሁ “ አለ ገዴው፡፡ ስለ ጉዞው በማሰብ በእጅጉ ተደስቶ ነበር፡፡ ከመሄዱ በፊት በከተማው የሚገኙትን ሀውልቶች በሙሉ ጎበኘ፡፡ ለረጅም ጊዜ ከቤተክርስቲያኑ የደውል ቤት ጉልላት አናት ላይ ተቀምጦ ቆየ፡፡ ሲያልፍ ሲያገድም የሚያዩት ድንቢጦች ሁሉ እየተንጫጩ፤  “ምን አይነት ደስ የሚል እንግዳ ነው “ ሲባባሉ እየሰማ በራሱ ኩራት ተሰማው፡፡መሽቶ ጨረቃ ብቅ ስትል ወደ ደስተኛው ልዑል በረረ፡፡  “ወደ ግብፅ የምትልከኝ ነገር አለ? “ አለ፤  “አሁን ወደ ግብፅ ጉዞ ልጀምር ነው፡፡ “
“ገዴ፣ ገዴ፣ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “አንዲት ሌሊት ከኔ ጋር አታሳልፍም? “
“አይ እኔ ግብፅ ይጠብቁኛል እኮ “ አለ ገዴው፡፡  “ነገ ጓደኞቼ ሁሉ ወደ ሁለተኛው ፏፏቴ ይበራሉ፡፡ ጉማሬዎቹም በቄጤማዎቹ መሀል ይጋደማሉ፡፡ አማልክት ሜምኖን ከታላቁ የጥቁር ድንጋይ ዙፋኑ ይቀመጣል፡፡ ሌሊቱን ሁሉ ከዋክብቱን ሲመለከት ያድራል፡፡ የማለዳ ኮከብ ስታበራ አንድ የደስታ ጩኸት ጮኾ ፀጥ ይላል፡፡ ተሲያቱ ላይ ቢጫ የመሰለ ቀለም ያላቸው አንበሶች ውሃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ ይወርዳሉ፡፡ አረንጓዴ የከበረ ድንጋይ የመሰለ ዓይን አላቸው፡፡ ግሳታቸውም ከፏፏቴው ጩኸት ገንኖ ይሰማል፡፡
“ገዴ፣ ገዴ፣ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “በከተማው ዳርቻ በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ አንድ ወጣት ይታየኛል፡፡ በወረቀት የተሞላ ጠረጴዛ ላይ ተደፍቷል፡፡ አጠገቡ በተቀመጠ ዋንጫ ውስጥም የጠወለገ አበባ አለ፡፡ ፀጉሩ ቡኒ እና ጥቅልል ያለ ነው፡፡ ከንፈሩ እንደ ሮማን ቀይ ነው፡፡ አይኑ ትልቅና ቡዝዝ ያለ ነው፡፡ አንድ ተውኔት ፅፎ ለመጨረስ እየታገለ ነው፡፡ ግን ብርዱን አልቻለውም፡፡ የረሃብ ጠኔ ጥሎታል፡፡
“ከአንተ ጋር አንድ ሌሊት አሳልፋለሁ “ አለ መንገደኛው ገዴ፡፡  “እና አንድ አልማዝ ልውሰድለት? “
“አይ አልማዝ የለኝም “ አለ ልዑሉ፤  “አሁን የቀሩኝ አይኖቼ ናቸው፡፡ አይኖቼ ከውድ እንቁ የተሰሩ ናቸው፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት ከህንድ የመጡ ናቸው፡፡  “ከዓይኖቼ አንዱን አውጣና ውሰድለት፡፡ ለጌጥ ሰሪው ሸጦ ምግብ እና እንጨት ገዝቶ ተውኔቱን ይጨርሳል፡፡”
“ውድ ልዑል “ አለ ገዴው፤  “ያን ላደርግ አልችልም “ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፡፡
“ገዴ፣ ገዴ፣ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “እንዳዘዝኩህ አድርግ፡፡ “
ስለዚህ ገዴው ከልዑሉ ዓይን አንዱን አወጣ፡፡ ከዚያም ወደ ፀሐፊው ጎጆ በረረ፡፡ ጣሪያው ቀዳዳ ስለነበር ወደ ውስጥ ለመግባት አልተቸገረም፡፡ በአንዱ ቀዳዳ ሾልኮ ወደ ክፍሉ ገባ፡፡
ወጣቱ ፀሐፊ የገዴውን ክንፍ ጅግጅግታ ላለመስማት ጆሮውን በእጆቹ ደፈነ፡፡ ከዚያ አይኑን ገልጦ ሲመለከት ከጠወለገው አበባ ላይ እጅግ ያማረ እንቁ አየ፡፡
“አዎ በሥራዬ አድናቆት ማግኘት ጀመርኩ ማለት ነው “ አለ፤  “ይህ እንቁ ከአድናቂዬ የተላከ መሆን አለበት፡፡ አሁን ተውኔቱን መጨረስ እችላለሁ “ ብሎ በእጅጉ ተደሰተ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ገዴው ወደ ባህሩ ዳርቻ ወረደ፡፡ ከአንድ ትልቅ መርከብ ተራዳ ሆኖ መርከበኞች ትላልቅ ሳጥኖችን በገመድ እያሰሩ  “ሆ-ጳ!” እያሉ ይጮኻሉ፤ እያንዳንዱን ሳጥን ሲያነሱ፡፡
“ነገ ወደ ግብፅ እሄዳለሁ “ አለ ገዴው፡፡ ግን ማንም ልብ ያለው አልነበረም፡፡ ጨረቃ ብቅ ስትል ተመልሶ ወደ ደስተኛው ልዑል በረረ፡፡
“እንግዲህ ልሰናበትህ መጣሁ፡፡ ደህና ሰንብት “ አለ፡፡  “ገዴ፣ ገዴ፣ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “አንዲት ተጨማሪ ሌሊት ከኔ ጋር
አታድርም? “
“ወቅቱ ክረምት እኮ ነው “ አለ ገዴው፤  “አሁን አጥንት ዘልቆ የሚነካ ብርድ ይመጣል፡፡ በግብፅ ፀሐይዋ አረንጓዴ ዘንባባዎችን ታሞቃለች፡፡ በጭቃ ላይ ተጋድመው ፣ ቁልጭ ቁልጭ እያሉ ዙሪያቸውን በሚዩት አዞዎች ላይ ሙቀቷን ታወርዳለች፡፡ አሁን ጓደኞቼ በቤአልቤክ ቤተመቅደስ ጎጇቸውን እየሰሩ ነው፡፡ ክፍት ቀይ እና ነጫጮቹ ዳክዬዎች እነሱን እያዩ ይዳራሉ፡፡ ውድ ልዑል አሁን ተለይቼህ ልሄድ ግድ ነው፡፡ ግን እስከመቼም አልረሳህም፡፡ ወደ ፊት በበጋ ወቅት ስመጣ ዛሬ ለተቸገሩት በሰጠሃቸው ፈንታ ሁለት ውብ ፈርጦችን አመጣልሃለሁ፡፡ እንቁዎቹ ከፅጌሬዳ የቀሉ ይሆናሉ፡፡ አልማዞቹም ከታላቁ ባህር የደመቀ ሰማያዊ ይሆናሉ፡፡
“እዚያ ከአደባባዩ በታች “ አለ ደስተኛው ልዑል፤  “እዚያ አንዲት ልጃገረድ ቆማለች ጓደኛዋም ከቦዩ ውስጥ ጥላት ሁሉም በጭቃ ተጨማልቀዋል፡፡ አባቷ ይሄን ቢያይ ይቆጣታል፡፡ ወደ ቤትም ገንዘብ ይዛ ካልገባች ይገርፋታል፡፡ ስለዚህ እያለቀሰች ነው፡፡ ጫማም ሆነ ካልሲ የላትም፡፡ ከትንሽ ጭንቅላቷ የምታስረው ሻሽ የላትም፡፡ ሌላኛውን ዓይኔን አውጣና ወስደህ ስጣት፡፡ እንዲያ ካደረክ አባቷ አይመታትም፡፡ “
“ለአንድ ተጨማሪ ሌሊት ከአንተ ጋር እሆናለሁ “ አለ ገዴው፤  “ነገር ግን ዓይንህን ላወጣ አልችልም እሱን ካወጣሁ ጨርሶ እውር ትሆናለህ “፡፡
“ገዴ፣ ገዴ፣ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “እንዳዘዝኩህ አድርግ “
ስለዚህ የልዑሉን ዓይን አወጣ፡፡ ያንንም በመንቆሩ ይዞ ቁልቁል እየተምዘገዘገ በረረ፡፡ በልጃገረዲቱ አጠገብ ሽው ብሎ ከንፎ ጌጡን ከእጇ ላይ ጣል አደረገላት፡፡  “እንዴት የሚያምር ብርጭቆ ነው “ አለች ትንሽዋ ልጃገረድ፡፡ እየሳቀች ወደ ቤቷ ከነፈች፡፡
ይሄን አድርጎ ገዴው ወደ ልዑሉ ተመልሶ ሄደ፡፡  “አሁን አንተ ታውረሃል “ አለው፤  “ስለዚህ ለዘላለሙ ካንተ ጋር እሆናለሁ፡፡ “
“አይ ትንሹ ገዴ “ አለ ምስኪኑ ልዑል፤  “ወደ ግብፅ መሄድ ይኖርብሃል፡፡ “
“እዚሁ ካንተ ጋር እኖራለሁ “ አለ ገዴው፤ ከዚያም ከእግሩ ስር ተኛ፡፡
በማግስቱ ገዴው ከልዑሉ ትከሻ ላይ ተቀምጦ ዋለ፡፡ በተለያየ ቦታ ሲሄድ ያጋጠመውን ነገር ሁሉ አጫወተው፡፡ በአባይ ወንዝ ዳርቻ እረጅም ሰልፍ ሰርተው የሚቆሙት ጋጋኖዎች ዓሣን እንዴት እንደሚያጠምዱ አጫወተው፡፡ የምድርን ያክል ዕድሜ ስላላት፣ በበረሃ ስለምትኖረው፣ ሁሉን አዋቂ ስለሆነችው ሲፊንክስ፤ በእጃቸው መቁጠሪያ ይዘው በግመሎቻቸው አጠገብ በቀስታ ስለሚራመዱ ነጋዴዎች፤ የጥቁር እንጨት መልክ ስላለው እና መስታወት የመሰለ ድንጋይ ስለሚያመልከው ስለጨረቃው ተራሮች ንጉስ፤ በዘንባባ ዛፎች ውስጥ ስለሚተኛው ስለትልቁ አረንጓዴ እባብ እና ለእባቡ የማር ቂጣ ስለሚመግቡት ሃያ ቀሳውስት፤ ትላልቅና ሰፋፊ በሆኑ ቅጠሎች ላይ ተቀምጠው በሰፊው ሃይቅ ላይ ስለሚቀዝፉት እና ሁልጊዜም ከቢራቢሮ ጋር ጦርነት ስለሚገጥሙት ድንክዬ ሰዎች፤ ሲያወራለት ዋለ፡፡
“ውድ ትንሹ ገዴ “ አለ ልዑሉ፤  “ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ነግረኸኛል፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያስገርመው የሰው ልጆች ስቃይ ነው፡፡ እንደ ችግር ግራ አጋቢ እንቆቅልሽ የለም፡፡ ትንሹ ገዴ በዚህች በእኔ ከተማ ላይ ዳር እስከዳር ብረርና በዚያ ምን እንዳየህ ንገረኝ፡፡ “
ገዴው ትልቁን ከተማ እያካለለ በረረ፡፡ በዚያም ለማኞቹ በበራቸው ተቀምጠው ሳለ ሐብታሞቹ በውብ ቤቶቻቸው ሆነው ሲደሰቱ ተመለከተ፡፡ ጨለማ በወረሳቸው ጠባብ መንገዶች ሲበር በረሃብ ፊታቸው ነጭ የሆነ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ህፃናት በጥቁሩ ጎዳና ወድቀው ተመለከተ፡፡ በድልድዩ ካለው ቅስት ስር ብርዱን ለመከላከል ተቃቅፈው የተኙ ሁለት ህፃናት ልጆችን አየ፡፡  “እንዴት እርቦናል “ አሉ፡፡ ንግግራቸውን የሰማው ዋርድያም እዚህ መተኛት አይቻልም ብሎ አስነሳቸውና በዝናብ ውስጥ መጠጊያ አጥተው ዞሩ፡፡ከዚህ በኋላ ገዴው ተመልሶ ወደ ልዑሉ በረረና ያየውን ሁሉ ነገረው፡፡
“እኔ ገላዬ በሙሉ በንፁህ ወርቅ ቅጠል የተሸፈነ ነው “ አለ ልዑሉ፤  “እያንዳንዷን ቅጠል እያነሳህ ለድሆቹ ስጥልኝ፡፡ ሰዎች ወርቅ ደስታን የሚሰጣቸው ይመስላቸዋል “ አለ፡፡
ገዴው፤ ደስተኛው ልዑል አስቀያሚና ግራጫ ድንጋይ እስኪመስል ድረስ እያንዳንዷን የወርቅ ቅጠል እያነሳ ለድሆቹ ሰጠ፡፡ እያንዳንዷን ቅጠል እያነሳ ወስዶ ለድሆች በሰጠ ቁጥር የገረጣው የድሆቹና የህፃናቱ ፊት ፅጌሬዳ አበባ ይመስላል፡፡ ይስቃሉ፡፡ በጎዳናም ይጫወታሉ፡፡  “አሁን ዳቦ አለን እያሉ ይጮኻሉ፡፡ “በረዶ ዘነበ፡፡ ከበረዶውም በኋላ አመዳይና ውርጭ ወረደ፡፡ ጎዳናዎቹም ብር የፈሰሰባቸው መሰሉ፡፡ ደማቅና አንፀባራቂ ሆኑ፡፡ የበረዶው ግግር ከብርጭቆ ድንጋይ የተሰራ ጩቤ መስሎ ከየቤቱ ክፈፍ ተንጠልጥለው ይታያሉ፡፡ ሁሉም ባለ ፈር ልብስ ለብሶ ይንቀሳቀሳል፡፡ ትናንሽ ህፃናትም ደማቅ ቀይ ኮፍያ አድርገው በበረዶው ላይ እየተንሸራተቱ ይጫወታሉ፡፡ ምስኪኑ ትንሽ ገዴ ቅዝቃዜው እየጠናበት ነው፡፡ ነገር ግን በጣም የሚወደውን ልዑል ጥሎ መሄድ አልፈለገም፡፡ ወደ አንድ ዳቦ ጋጋሪ ቤት እየሄደ ጋጋሪው ሳያየው ከበር የወደቁ የዳቦ ፍርፋሪዎችን እየለቀመ በመብላት እና ክንፉን በማወዛወዝ ሙቀት ለማግኘት ተጣጣረ፡፡ በመጨረሻም ሞት እንደመጣበት አወቀ፡፡ አሁን የቀረው ጉልበት ወደ ልዑሉ ትከሻ ለመብረር የሚያስችል ብቻ ነበር፡፡  “ደህና ሁን ውድ ልዑል “ ሲል አጉረመረመ፡፡  “እጅህን እንድስም ትፈቅድልኛለህ? “
“ትንሹ ገዴ በመጨረሻ ወደ ግብፅ ለመሄድ በመነሳትህ በጣም ደስ ብሎኛል “ አለ ልዑሉ፤  “እዚህ ረጅም ጊዜ ቆየህ፡፡ እኔ በጣም እወድሃለሁ፡፡ እጄን ሳይሆን ና ከንፈሬን ሳመኝ፡፡ “
“አሁን ወደ ግብፅ አይደለም የምሄደው “ አለ ገዴው፡፡  “አሁን የምሄደው ከሞት ቤት ነው፡፡ ሞት የእንቅልፍ ወንድም ነው፡፡ አይደለም እንዴ? “ እናም የደስተኛውን ልዑል ከንፈር ሳመና ሞቶ ከእግሩ ሥር ወደቀ፡፡ በዚያች ቅፅበት በሀውልቱ ውስጥ እንግዳ የሆነ የመንቃቃት ድምፅ ተሰማ፡፡ ከባድ ሐዘን የደረሰበት ልብ ለሁለት ተሰነጠቀ፡፡ አደገኛ ውርጭ የፈሰሰበት ቀን ነበር፡፡
በማግስቱ ጠዋት የከተማው ከንቲባ ከሁለቱ አማካሪዎቻቸው ጋር ሆነው በዚያ ግድም ባለ አደባባይ ይሄዱ ነበር፡፡ የደስተኛው ልዑል ሐውልት ከቆመበት አምድ አቅራቢያ ሲደርሱ ወደ ላይ ቀና ብለው ተመለከቱ፡፡  “ኤዲያ ደስተኛው ልዑል ጨርሶ አስቀያሚ ሆኗል “ አሉ፡፡
“ጨርሶ አስቀያሚ ሆኗል! “ አሉ ሁሌም ከንቲባው ያሉትን መድገም የሚወዱት የከተማው ምክር ቤት አባላት፡፡ ያን ብለውም ሐውልቱን ለማየት ቀና አሉ፡፡
“የሻምላው ጌጥ ወድቋል፤ አይኑም ወጥቷል፤ አሁን ወርቃማነቱ ጠፍቷል “ አሉ ከንቲባው፤  “አሁንማ የኔ ቢጤ መስሏል፡፡ “
“አዎ የኔ ቢጤ መስሏል “ አሉ የከተማው ምክር ቤት አባላት፡፡
“ደግሞ እግሩ ሥር አንድ የወደቀ ወፍ አለ “ ሲሉ አከሉ ከንቲባው፡፡  “ወፎች ወደዚህ ከተማ ገብተው መሞት እንደማይችሉ የሚያዝ አዋጅ ልናወጣ ይገባል “ የከንቲባው ፀሐፊ የተናገሩትን ቃል በማስታወሻው መዘገበ፡፡ የደስተኛው ልዑል ሀውልት ወረደ፡፡  “ይሄ ነገር ውበቱ ስለረገፈ ጠቃሚነቱም አለፈ “ አሉ በዩኒቨርስቲ የአርት ፕሮፌሰር የሆኑት ሰው ዕዕ ከዚያም ከብረት ማቅለጫ ከውር አስገብተው አቀለጡት፡፡ የከተማው ከንቲባም በቀለጠው ብረት ምን ሊሰራ እንደሚገባ ለመነጋገር ስብሰባ ተቀመጡ፡፡  “ሌላ ሐውልት መስራት ይገባናል “ አሉ፤  “ይህም ሐውልት የኔ ሐውልት ይሆናል፡፡ “ “የኔ ሐውልት “ አሉ፤ የከተማው ምክር ቤት አባላት በሙሉ፡፡ በዚህም ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ እኔ እስከሰማኋቸው ድረስ ጭቅጭቃቸው አላባራም፡፡
“እንዴት ያለ እንግዳ ነገር ነው!” አለ የማቅለጫ ፋብሪካው ሰራተኞች ተቆጣጣሪ፡፡  “ይሄ የተሰነጠቀ ከብረት የተሰራ ልብ በከውር ውስጥ አይቀልጥም እርሱን ወዲያ መጣል አለብን፡፡ “  የሞተው ገዴ ከወደቀበት ቆሻሻ ሥፍራ ወረወሩት፡፡
“በዚህ ከተማ እጅግ ውድ የሆኑ ሁለት ነገሮችን ፈልገህ አምጣልኝ “ አለ እግዚአብሄር ከመላዕክቱ ለአንዱ፡፡ መላአኩም የተጣለው ልብ የተሰራበትን ብረትና የሞተውን ገዴ ወስዶ ሰጠ፡፡
“በትክክል መርጠሀል “ አለ እግዚአብሄር፡፡  “ይህ ትንሽ ወፍ በገነት መስክ ለዘለዓለም ይዘምራል፡፡ ደስተኛው ልዑልም በእኔ የወርቅ ከተማ ገብቶ ሲያመሰግነኝ ይኖራል “
ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ፡፡ ለኛም እንዲህ የሚያስብ መሪ አያሳጣን፡፡

 

Read 5076 times Last modified on Monday, 10 October 2011 06:02