Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 12:34

የገጣሚነት ጣጣ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ስለ ፍላጐት 
1/ በክፍል ውስጥ እየተማርኩ ወረቀት ላይ ስሞነጫጭር ብዙ ጊዜ በመምህሮቼ እጅ ከፍንጅ እየተያዝኩ የዘለፋ እና የወቀሳ ቅጣቶች ተፈጻሚ ሆነውብኛል፡፡
2/ ታክሲ ላይ ወይም አውቶብስ ውስጥ ወይም መንገድ ላይ ድንገት በሚፈነዳ አስበርጋጊ ድምጽ የማደንቃቸውን ገጣሚዎች ግጥም ሳነበንብ ያለምንም ህጋዊ ፈቃድ የሰው ሰላም በማናጋት ሙከራ ተገምቼ ግልምጫዎችን አስተናግጃለሁ፡፡
3/ የመንግስት ሰራተኛ እያለሁ አማርኛ ቋንቋ አስተምር ነበር፡፡ የተማሪዎችን ክፍለ ጊዜ ድርሰት በማንበብ ማባከኔ በልዩ አጣሪ ኮሚቴ ጥልቅ ምርመራ እና ፍተሻ ተደርጐ ስለደረሰበት በተማሪ፣ በወላጅ እና ወዘተረፈ ፊት እንደ ስጋ ከብት ተገምግሜያለሁ፡፡
4/ በ1996ቱ የመምህራን ኮንፍረንስ ላይ የተኮማተሩ የመምህራን ፊቶችን መፍታቴ፤ የተሰላቹ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችን ልቦና ማደሴ፣ በመምህራን ጉሮሮ ውስጥ የተንጐረጐሩ ነጠላ ዜማዎችን በይፋ መዝፈኔ ይህንንም ሳደርግ ኪነትን እንደ መሳሪያ መጠቀሜን የወረዳው ካቢኔ ባደረገው ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ስላረጋገጠ የካቢኔው ሰብሳቢ ከአስተዳደሩ የተበረከተልኝን የማባረሪያ ደብዳቤ ለግሶኛል፡፡
“ወንሕነሰ ተንሣእነ ወረታዕነ፡፡ እኛ ግን ተነስተን ፀንተንም ቆምን፡፡”

ትንሽ ስለግጥም
ግጥም ምንድን ነው? ቅኔስ? ዜማ፣ ምት፣ ለዛ፣ ውበትስ? በመዋሸት እና በመቅጠፍ፤ በመሳቅ እና በምፀት፤ በራዕይ እና በቅዠት፤ በሙገሳ እና ውደሳ ምን መለያየት አለ? ማወቅ እና አለማወቅስ ምን ያመሳስላቸዋል?
ግጥም ወዳጅ መሆን እና መግጠም ሌላ ናቸው፡፡ መጥበብም መጠበብም፡፡ ጥበብ ሕይወት ተስፋ እምነትና ፍቅር በሚስጥር ይመራሉ፡፡ የነዚህን መምሪያ ሚስጥር ማወቅ እና ያወቁ መምሰል ግን ለየቅል ናቸው፡፡
እስቲ ግጥምን በኩራዝ እንመስል፡፡ እኔ ከየት እንደተሰለፍኩ አላውቅም፡፡ ሁለት ወገን ግን አያለሁ፡፡ አንደኛው ወገን ኩራዙን በመቅረዙ ላይ ለማንገስ፤ አንደኛው ከመቅረዙ አውርዶ ለመከስከስ የሚፋተጉ፡፡ አቅሜ ቢፈቅድ ኩራዙን መቅረዙ ላይ ለማንገስ እመኛለሁ፡፡ ለመከስከስ ለሚማስኑት ደግሞ ማዘን አለብኝ፡፡ “ወሎሙ በሙስናሆሙ ዐስበ ዓመጻ፡፡ (ለከንቱ ማስተማራቸው ደሞዝ ይቀበላሉና”፡፡ የሰራሁት ቢያስችለኝ ይህንን ማህበር መቀላቀል አልፈልግም፡፡

ችሎታን በሚመለከት
ከኩነኔ ጽድቅ ይሻላል፡፡ ከውሸትም እውነት፡፡ ግጥም እወዳለሁ እችል እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ ይችን መጽሐፍ ይዤ /የቅርቦቹን ብቻ ልጥራ/ በእነጌትነት እንየው፤ ነቢይ መኮንን፤ አበባው መላኩ፤ በድሉ ዋቅጅራ ...ጐዳና ስገባ እፍረት ነው ኩራት ነው ለእኔ?
እንዲህ ማለት ግን እችላለሁ፡፡
ፀጋየ ገ/መድህን፤ ዮሐንስ አድማሱ፤ ሰሎሞን ዴሬሳ፤ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው...ግጥምን ለማሳደግ እየጣሩ፣ አዲስ አመጣጥ አገጣጠም አስተሳሰብ የሚፈበርኩ ናቸው፡፡ እኛ ግን እነሱን እንድንተካ ተስፋ ከቆረጥን እንድንመስላቸው እንፀልይ፡፡
ጥንትም የነበርን እኛ አሁንም ያለን እኛ
እንዴት ያን ሁሉ ወኔ ለደዌ ሰጥተን እንተኛ
እንዳለ ገጣሚ አበባው መላኩ
(“ደም የተፋ ብዕር” በሚል በደሳለኝ ስዩም ከወጣው የግጥም መድበል መግቢያ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጐበት የወጣ)

 

Read 6303 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:37