Saturday, 22 October 2011 11:25

በ16 ዓመቱ የቁጠባ (የባንክ) ሂሳብ ከፍቶ በ26 ዓመቱ የሁለት ፋብሪካ ባለቤት የሆነ ወጣት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

አንድ ታዳጊ በ16 ዓመቱ የቁጠባ (የባንክ) ሂሳብ ከፈተ የሚል ነገር መስማት የተለመደ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፤ የቁጠባ ሂሳብ ሳይኖራቸው የሚሞቱ በርካታ ሰዎች አሉና! ወሬውን ሲሰሙ፣ ምናልባት የመጀመሪያ ጥያቄዎ፣ የት አገር የሚል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ እዚሁ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ምናልባት የሀብታም ልጅ ከሆነ ወላጆቹ ለወደፊት የኮሌጅ ትምህርቱ (በውጭ አገር ሀብታም ወላጆች ለልጆቻቸው የኮሌጅ ትምህርት፣ ሕክምና፣ ትዳር፣…እያሉ በስማቸው የቁጠባ ሂሳብ ስለሚከፍቱ) በስሙ የቁጠባ ሂሳብ ከፍተውለት ነው ብለው አስበው ይሆናል፡፡ ግን አይደለም፤ ከድሃ ቤተሰብ ነው የተወለደው፡፡ የቁጠባ ሂሳቡን የከፈተው ራሱ፣ ውሃ በሳንቲም ሸጦና በአንድ ብር የሻወር አገልግሎት ሰጥቶ ነው ቢባሉ፤ በባንክ አሠራር፣ አንድ ሰው በስሙ የቁጠባ ሂሳብ መክፈት የሚችለው 18 ዓመት ሲሞላው እንደሆነ ስለሚያውቁ እንዴት በማለት ግር ሊልዎት ይችላል - ግን እውነት ነው፡፡

የያኔው ታዳጊ ዛሬው የ26 ዓመት ወጣት የሁለት ፋብሪካዎች ባለቤት መሆኑን ብንነግርዎትስ? የሚያጠግብ እንጀራ . . . ይላሉ ወይስ ኧረ እንዲህ ዓይነት ቀልድ ተውን ይላሉ፡፡ ምንም አይጠራጠሩ፤ እያጫወትኩዎት ያለው ነገር እውነት ነው፤ ወጣት ቢኒያም በደዊ መሐመድ፤ ሁለተኛ ፋብሪካውን መስከረም 20 ቀን 2004 ዓ.ም አስመርቋል፡፡  
ወጣት ቢኒያም፣ ተወልዶ ያደገው፣ የተማረውና ሥራ የጀመረው በአዳማ (ናዝሬት) ከተማ ነው፡፡ ሁለቱን ፋብሪካዎች የተከለውም እዚያው አዳማ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፋብሪካ የዘይት ሲሆን፤ በቅርቡ የተመረቀው ደግሞ የኤክስፖርት (የቅባትና ጥራጥሬ) እህሎች አበጥሮና አሽጐ ለውጭ አገር ገበያ የሚያቀርብ ነው፡፡
ጥራጥሬና የቅባት እህሎች እያበጠረ አሽጐ ወደ ውጭ የሚልከው ፋብሪካ ዛብሎን ትሬዲንግ በመባል ይታወቃል፡፡ የዘይት ፋብሪካው ደግሞ ፊሶን በመባል ይጠራል፡፡ ዛብሎን፣ ከቅባት እህሎች በዋነኛነት ሰሊጥና ኑግ ይልካል፡፡ ሱፍ፣ ኦቾሎኒ (ለውዝ) እና የጉሎ ፍሬም የሚላኩ ምርቶች ናቸው፡፡ ከጥራጥሬ ደግሞ ቀይና ዥንጉርጉር ቦሎቄ፣ አተር፣ ሽምብራ፣ ምስርና ማሾ (ትናንሽ ፍሬ ያለው አረንጔዴ እህል) ይልካል፡፡ ዛብሎን በግንባታ ሂደት ላይ በነበረበት ጊዜ እንኳን ምርቶቹን ወደ አሜሪካ፣ ህንድ፣ መካከለኛ ምስራቅ፣ ኔዘርላንድስ፣ ዮርዳኖስ . . . በመላክ ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስገኝቷል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በ10 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተው ዛብሎን ትሬዲንግ፤ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 30 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ መላክ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ምርቶችንም ከውጭ ያስገባል፡፡ ኤ4 ወረቀቶች፣ ብረታ ብረቶች፣ ሜታል ሺት፣ ላሜራ፣ ፌሮ፣ ፓልም የምግብ ዘይት፣ ቀላልና ከባድ የጭነት መኪኖች፣ . . .ይጠቀሳሉ፡፡
ለመሆኑ ወጣት ቢኒያም እንዴት በዚህ ዕድሜው ለደረሰበት ስኬት በቃ? ሌላው ይለው እንደሆነ እንጂ እሱ ተሳክቶልኛል የሚል እምነት የለውም፡፡ “እኔ መሥራቴ ነው እንጂ ስኬቴ አይታየኝም፡፡ ሰው ተሳክቶልሃል ይለኛል፡፡ እኔ ግን ምንም አይመስለኝም፡፡ ወጣት ነኝ፤ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብኝ ነው የማምነው” ይላል፡፡
በ12 የሥራ ዓመታት ውሃ ከመሸጥና የሻወር አገልግሎት ከመስጠት (ከምንም ነገር) ተነስቶ ማለት ይቻላል፤ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር እያንቀሳቀሰ እራሱንና አገርን መጥቀም፤ ለዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠር ቀላል ስኬት አይደለም፡፡ ለመሆኑ ምሥጢሩ ምን ይሆን? ነገሮችን አክብዶ ያለማየት፣ ዓላማና ግብ ይዞ መንቀሳቀስ፣ ጠንክሮ መሥራት፣ በስንት ፈተናና ድካም ያገኟትን ሳንቲም ቆጥቦ መያዝ (እንደ አልባሌ ነገር ያለማጥፋት) ወደ ስኬት ጐዳና ሊያደርሱ እንደሚችሉ ይናገራል - ቢኒያም፡፡
ዛብሎን ትሬዲንግ ከመመረቁ አንድ ሳምንት በፊት መስከረም 12 ቀን 2004 ዓ.ም 26ኛ የልደት በዓሉን ያከበረው ወጣት ቢኒያም፤ በልጅነቱ፣ አባቱ የተለያዩ ነገሮችን እየነገዱ ቤተሰቡን ሲያስተዳድሩ እያየ ነበር ያደገው፡፡ በዚህ የተነሳ፣ እሱም ፍራክ ለማግኘት በ14 ዓመቱ ከ7ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ሳንቲም ሊያስገኙ በሚችሉ እንደ ውሃ መሸጥ፣ የሻወር አገልግሎት፣ . . . ያሉ ጥቃቅን ነገሮችን አሁን በፈረሰውና ግንብ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ መሥራት እንደ ጀመረ ያስታውሳል፡፡
ታዳጊው ቢኒያም፣ ትምህርቱን ያቋረጠው ድህነትን ታግሎ ለማሸነፍ ስለሆነ፣ እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ፓስቴ በመብላት ወይም ቢስክሌት በመጋለብ. . . ያገኛትን ሳንቲም አያባክንም ነበር፡፡
ያለ በቂ ምክንያት ከቢኒያም እጅ አምስት ሳንቲም አትባክንም - ትጠራቀማለች እንጂ! ሥራ ከጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላ በ16 ዓመቱ ከ10 ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ2001 ዓ.ም ወደ ሕብረት ባንክ ሄዶ የቁጠባ ሂሳብ መክፈት እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ የባንኩ ሠራተኞች፣ በታዳጊው ሐሳብ ቢገረሙም “ዕድሜህ አይፈቅድልህም” ብለው አላባረሩትም፡፡ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ መስጠት ስለማይችሉ ወደ ሥራ አስኪያጇ ወስደውት ምን እንደፈለገ ነገሯት፡፡ ሥራ አስኪያጇ የሰማችውን ማመን አልቻለችም፤ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ቢኒያምን ጠየቀችው፡፡ እሱም እውነቱን እንደሆነ ፍርጥም ብሎ መለሰላት፡፡ ዓላማና ቁርጠኝነት እንዳለው ከሁኔታው ተረዳች፡፡ የዚያን ታዳጊ ሞራል ከመግደል ይልቅ ማበረታታት ጥሩ መሆኑን ስላመነች፣ “የሚያስጠይቅ ነገር ከመጣ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ” በማለት የቁጠባ ሂሳብ እንዲከፍት ፈቀደችለት፡፡ ቢኒያም፣ ሐሳቡ በመሳካቱ በጣም ተደስቶ በኪሱ በነበረው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ (1,250) ብር ሂሳብ ከፈተ፡፡ ከዚያም ያገኘውን ገንዘብ በየጊዜው እየወሰደ ማጠራቀሙን ተያያዘው፡፡
በዚያን ወቅት አባት ብቻ በሚያመጡት ገቢ ቤተሰቡን ማስተዳደር አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እናት የቤተሰባቸውን ገቢ ለመደጐም ወሰኑ፡፡ ከዚያም በአንድ አነስተኛ መሳሪያ፣ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ዘይት መጭመቅ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን እንደጠበቁት አልሆነላቸውም፡፡ መንቀሳቀሻ ገንዘብ አጠራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ፣ ገንዘብ ያበድረኛል ብለው ወደተማመኑት ሰው ሄደው ብድር ጠየቁ፡፡ ሰውዬው ግን ችግራቸዉን ሊፈቱላቸው አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ አዝነው ክፉኛ ቆዘሙ፡፡ ቢኒያም፣ እናቱ እንደዚያ አዝነው ማየቱ ሰላም አልሰጥህ አለው፡፡ ስለዚህ ባንክ ያጠራቀመው ገንዘብ ስላለ አውጥተው እንዲጠቀሙበት ነገራቸው፡፡ ያኔ የተጠራቀመው ገንዘብ 25ሺህ ብር ያህል ደርሶ ስለነበር፣ አንዴ 15ሺህ ብር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ 10ሸህ ብር አውጥቶ ሰጣቸውና እየረዳቸው አብረው መሥራት ጀመሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ቤተሰቡ ውስጥ የበለጠ መተማመንና መተሳሰብ ተፈጠረ፡፡ በእንዲህ ዓይነት እየተደጋገፉ ሲሰሩ እንደቆዩ፣ ቢኒያም፣ አንድ የዘይት ፋብሪካ እንደሚከራይ ሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ እናቱን “አብረሻቸው የምትሠሪያቸውን ሰዎች አውቃቸዋለሁ፡፡ እህል በዱቤ ስጡኝ ብላቸው አይከለክሉኝም፡፡ ስለዚህ ፋብሪካውን ተከራይቼ ለብቻዬ ልሥራ” በማለት አማከራቸው፡፡ እናቱ በሐሳቡ ቢስማሙም ሁለቱንም ማንቀሳቀስ የሚችል በቂ ገንዘብ አልነበረም፡፡ ስለዚህ መኖሪያ ቤታቸውን በዋስትና አስይዘው 300ሺህ ብር በስሙ ተበደሩለት፡፡ እሱም ዕዳውን በየወሩ እየከፈለ ዕድሜው 20 ዓመት ሲሆን ከመንግሥት በሊዝ በገዛው መሬት ፊሶን የምግብ ዘይት ኮምፕላክ ፋብሪካ በ1ሚ ብር ካፒታል (በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 10 ሚሊዮን ብር ደርሷል) ከፈተ፡፡ እዚያው ግቢ ውስጥ አንድ መኝታ ክፍል፣ ሳሎን፣ ማዕድ ቤትና ለቢሮ የሚሆን ትንሽ ክፍል ሠርቶ ከቤተሰቡ ቤት ወጥቶ መሥራት ጀመረ፡፡ እዚያው ግቢ ውስጥ እየኖረ ሌት ተቀን ሲሠራ ቆይቶ አንድ የነበረውን የዘይት መጭመቂያ መሳሪያ አምስት እንዳደረሰው ይናገራል፡፡ ከዚያም እስከ ዲላ፣ ይርጋጨፌና ጂማ ድረስ እየሄደ የገበያ ጥናት በማድረግ የራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች የሚጨምቁትን ዘይት ጭምር በበርሜል እየሞላ ያከፋፍል ጀመር፡፡ ከዓመት በኋላ ከአዳማና ከናዝራዊ ዘይት ፋብሪካዎች ቀጥሎ የተሻለ የተባለለት ትልቅ የዘይት መጭመቂያ መሳሪያ ከቻይና ገዝቶ ለየት ያለና በአዳማ ያልተለመደ የጥጥ ፍሬ ዘይት ማምረት እንደጀመረ ይናገራል፡፡ ለመሆኑ ወጣቱ ባለሀብት እንዴት ከዘይት ሥራ ወደ ኤክስፖርት ንግድ ገባ? በ 2000 ዓ.ም መጨረሻ ገደማ ብዙ የቅባት እህል ምርት ነበረው፡፡ ለምን ይህንን ምርት አበጥሬ ወደ ውጭ አልክም የሚል ሀሳብ መጣለት፡፡ ከዚያም ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተመካክሮ ሀሳቡን ስለደገፉት መጀመሪያ የቅባት እህሎችን፣ በመቀጠልም ጥራጥሬ በአነስተኛ መሳሪያ እያበጠረ መላክ እንደጀመረ ገልጿል፡፡ ደንበኞቹ ግን በጥራቱ ደስተኞች አልነበሩም፣ ቅሬታ ነበራቸው፡፡ “አንተ የላከውን እህል እንደገና በማበጠር ለተጨማሪ ወጪና ለጊዜ ብክነት እየተጋለጥን ነው፡፡ ለምን በተሻለ መሳሪያ አበጥረህ፣ ጣጣውን የጨረሰ ንፁህ እህል አትልክልንም” የሚል ወቀሳ በየጊዜው ያሰሙ እንደነበር ቢኒያም ያስታውሳል፡፡ ደንበኞች በሚፈልጉት የጥራት ደረጃ ለማቅረብ፣ አንዱን ምርት አራትና ከዚያም በላይ ጊዜ ማበጠር ያስፈልጋል፡፡
ይህ አሠራር ደግሞ የተፈለገውን ምርት በተፈለገው የጥራት ደረጃና ጊዜ ማቅረብ አላስቻላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ፣ ለምን የተሻለ ማበጠሪያ አንገዛም? ደንበኞቻችንስ ለምን የመጀመሪያ ምርጫቸው እንዲያደርጉን አንሠራም? በማለት ተነሳስተው 12 ዓይነት የቅባትና የጥራጥሬ እህሎችን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ (99.7 በመቶ) ማበጠርና ማሸግ የሚችል ትልቅ መሳሪያ ከቱርክ ገዝተው መትከላቸውን ተናግሯል፡፡ መሳሪያው በቀን 12ቶን ወይም 1ሺህ 200 ኩንታል ምርት የማበጠርና የማሸግ አቅም ያለው ዘመናዊ መሳሪያ ነው፡፡
ቢኒያም፣ ከሥራው ጋር ትስስር ወዳለው የእርሻ ዘርፍ የመግባት ሐሳብ አለው፡፡ ጥፍጥሬ መፍጨት የሚችል መሳሪያ ስላለው በጥጥ እርሻ ለመሰማራት ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል፡፡ ጥጡን ለአገር ውስጥ ወይም ለውጭ ፋብሪካዎች ለማቅረብ፣ ጥፍጥሬውን ደግሞ ጨምቆ ዘይት ለማምረት፡ የቅባት እህሎችንም እሴት (ቫሊዩ) የመጨመር ሐሳብ አለው፡፡ ለምሳሌ፣ ሰሊጥን እንዳለ ጥሬውን ከመላክ፣ ፈትጐ የላይኛውን ሽፋን በማንሳት ወይም በዳቦ ቅቤነት አዘጋጅቶና እሴት ጨምሮ የመላክ ሐሳብ አለው፡፡ ቢኒያም የራሱንም ሆነ የሌሎች ድርጅቶች ምርት ጅቡቲ ወደብ ለማድረስና ሸቀጥ ወደ መሃል አገር ማመላለስ የሚችል “ዛብሎን የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት” የተሰኘ እህት ኩባንያም አለው፡፡ ወጣት ቢኒያም ከ7ኛ ክፍል ያቋረጠውን ትምህርት በማታው ክፍለ ጊዜ ተከታትሎ ከኮሌጅ በማኔጅመንት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ አሁን ደግሞ የዲግሪ ትምህርቱን ለመቀጠል እየተዘጋጀ ነው፡፡ ቢኒያም ትዳር የመሠረተ ሲሆን ሁለት ሴት ልጆች አፍርቷል፡፡ ወጣቱ ባለሀብት በሁለቱ ፋብሪካዎች ለ40 ቋሚና ለ30 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ሥራ በሚኖርበት ጊዜ የሠራተኞች ቁጥር 126 እንደሚደርስ ታውቋል

 

Read 6399 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:28