Saturday, 22 October 2011 11:29

የጣዕረ ሞቱ ጭምብል

Written by  ደራሲ - ኤድጋር አለን ፓ ተርጓሚ - አባድር ጀማል
Rate this item
(1 Vote)

በአንድ ወቅት በሆነች ሀገር ግዛት ውሥጥ ከላይ ወደ ታች፣ ከግራ ወደ ቀኝ እየተራወጠ ህዝቦቿን ዶግ አመድ የሚያደርግ ነፍሰ-በላ ጣዕረ-ሞት ተከሠተ፡፡ በሀገሪቷ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ዘግናኝ ፅልመተ-ሞት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ደም የጣዕረ-ሞቱ መገለጫ ምልክት ነው፡፡ እንደ ፍም እሳት የሚንበለበል ቀይ ሰቅጣጭ ደም የቀዩ ጣዕረ-ሞት መለያ አሻራው ነው፡፡ በቀዩ ጣዕረ-ሞት ቀንበር የተያዘ ሰው አሰቃቂ ለሆነ ህመም ይዳረጋል፡፡ ከራስ ቅሉ ውሥጥ ያለው አእምሮ ከየት እንደመጣ በማይታወቅ ወጀብ ይናጣል፣ ይናወጣል፡፡

አጥንቱ ሳይሰበር፣ ሥጋው ሳይሠነጠቅ ነቁጥ በሚያካክሉት የቆዳው ቀዳዶች ደም እንደ ምንጭ እየተፍለቀለቀ፣ እንደ ጅረት እየጐረፈ አሰቃቂ በሆነ ስቃይ ተቀፍድዶ ይንጨረጨራል፡፡ በመላው አካላቱ በተለይም በፊቱ ላይ የሚፈጠረው የረጋ የደም ልሥን ማንነቱን ሰልቦ የወዳጅን እርዳታ፣ የዘመድን ዋይ ዋይታ ከማግኘት ያርቀዋል፡፡ በመጨረሻም አካሉ ጠውልጎ ይወረዛና ይበሰብሳል፤ ደግሞም ይሄ ሁሉ የህመም ሂደት ተጀምሮ እስኪያልቅ የሚፈጀው ጊዜ ግማሽ ሰአት ብቻ ነው፡፡
ይህም ሆኖ ሀገረ ገዢው ልኡል ፕሮስፔሮ የችግሩ ጥልቀት ብዙም ያሳሰበው አይመስልም፡፡ ምንም ነገር እንዳልተከሠተ ሁሉ ጌታ ፕሮሥፔሮ እንደወትሮው ጤናማና ደስተኛ ይመስላል፡፡ ገሚሱ የሀገሬው ህዝብ በምህረት የለሹ ቀይ ጣዕረ-ሞት በትር ተቀጥቅጦ ሲረግፍ ልኡሉ እንደርሡ ያለ አንድ ሺህ ጤናማና ልበ-ብሩህ ሰዎችን መርጦ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ቤተ-መንግሥቱ አመራ፡፡
ቤተ መንግስቱ ከሠው የተለየ አፈንጋጭ ምርጫ ባለው ልኡል ፕሮሥፔሮ ንድፍ መሠረት የተገነባ፣ ያልተለመደ አይነት ዲዛይን ያለው ቤተ-መንግሥት ቢሆንም ውበቱና ግርማ ሞገሡ ላቅ ያለ ነው፡፡
ዙሪያውን በማይነቃነቅ ግምብ የተከበበ ሲሆን በረዥሙ ግምብ ላይ ደግሞ በወፋፍራም ብረቶች የተሰፋ አስተማማኝ በሮች አሉ፡፡
ወደ ቤተ-መንግስቱ የገቡት የጌታ ፕሮስፔሮ ጋሻ ጃግሬዎች፤ ከእነሱ ውጪ ማንም ሠው ወደ ቤተ-መንግስቱ እንዳይገባ፣ ከገቡትም ውስጥ ማንም እንዳይወጣ በማሠብ የበሮቹን መክፈቻና መዝጊያዎች በእሳት አቅልጠው ደፈኗቸው፡፡ አሁን ሁሉም ሰው በአስተማማኝ መዳፍ ውሥጥ ተደላድሎ ተቀምጧል፡፡ አሁን በሀገሪቷ ዙሪያ የተንሰራፋውን ቀይ ጣዕረ - ሞት መርሳት ይቻላል፡፡ አሁን ከውጪ ያለው አለም የራሡን ችግር በራሡ ይፈታ ዘንድ መተው ይቻላል፡፡ ጌታ ፕሮስፔሮና ጋሻ ጃግሬዎቹ ከእነሡ ውጪ ስላለው አለም እያሰቡ የሚብሰከሰኩ፣ በሀዘን የሚብሰለሰሉ ቂላቅሎች አይደሉም፡፡ ጌታ ፕሮስፔሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ አቅርቦላቸዋል፡፡ ምንም ያነሰ ወይም የጎደለ ነገር የለም፡፡ በቂ የሆነ ምግብ ቀርቧል፡፡ ሙዚቃ አለ፣ አታሞ ይደለቃል፣ ዳንኪራ ይረገጣል ወይኑም በላይ በላይ፣ ባናት ባናቱ ይጨለጣል፡፡ ውበት በመላ ቤተ መንግስቱ ውሥጥ እንደ ጅረት ፈሷል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁሉ ነገራት ያሉት ከቤተ-መንግስቱ ግድግዳ በመለስ ነው፡፡ በእርግጥ በቤተመንግሥቱ ግድግዳ ውስጥ እስካሉ ድረስ አስተማማኝ የሆነ ዋስትና አላቸው፡፡ ቤተመንግስቱን ከከበበው ግድግዳ ውጪ ያለው ነገር ግን አንድና አንድ ብቻ ነው - ቀይ ጣዕረ ሞት!
በዚህ መልኩ ለጥቂት ወራት ከዘለቁ በኋላ በአምስተኛ ወራቸው ማገባደጃ ላይ ወጣ ያለ ምርጫ ያለው አፈንጋጩ ልኡል ፕሮሥፔሮ ወዳጆቹን ለማስደሰት ለየት ያለ እቅድ አወጣና ድል ያለ የጭምብል ፓርቲ አዘጋጀ፡፡ ነገርየው እንግዳና ያልተለመደ ቢሆንባቸውም ተከታዮቹ በሙሉ ጭምብላቸውን አጥልቀው ከፓርቲው ታደሙ፡፡
የጭምብል ፓርቲው የተካሄደው በሰባት ክፍሎች ውስጥ ነበር፡፡ ክፍሎቹ የተሰሩት በተለመደው አይነት የቤተ-መንግስት ወግ በሮቹ ሲከፈቱ ሰባቱም ክፍሎች እንዲታዩ ተደርጎ አልነበረም፡፡ የክፍሎቹ አሰራር ትንሽ ለየት ይላል፡፡ በእያንዳንዱ ሀያ ወይንም ሰላሳ ያርድ ውስጥ አንዳንድ ኩርባ አለ፡፡ በክፍሎቹ ግድግዳ ግራ፣ ቀኝና መካከል ላይ ቀጥ ብለው የቆሙ መስኮቶች ተሰድረዋል፡፡ መስኮቶቹ ከመስታወት የተሰሩና ደማማቅ ቀለሞችን የተቀቡ ናቸው፡፡ በስድስቱ ክፍሎች ውስጥ ግድግዳዎቹና መስኮቶቹ ተመሳሳይ የሆነ ቀለም ተቀብተዋል፡፡
በስተምስራቅ የሚገኘው ክፍል አረንጓዴ ሲሆን መስኮቶቹም አረንጓዴ ቀለም አላቸው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ያለው ክፍል ደግሞ የወይን ጠጅ ቀለም ተቀብቷል፡፡ የሶስተኛው ክፍል ቀለም አረንጓዴ ሲሆን መስኮቶቹም አረንጓዴ ቀለም አላቸው - የአራተኛው ክፍል ቀለም ቢጫ - አምስተኛው ነጭ - ስድስተኛው ሀምራዊ ቀለም ተቀብተዋል፣ መስኮታቸውም እንደዛው፡፡ የመጨረሻውና ሰባተኛው ክፍል ሙሉ ለሙሉ ጥቁር ሲሆን በዚኛው ክፍል ውስጥ ያሉ መስኮቶች ከክፍሉ የተለየ ቀለም ተቀብተዋል፡፡ በሠባተኛው ክፍል ላይ ያሉ መሥኮቶች ፍም የሚመሥል ቀይ የደም ቀለም የተቀቡ ናቸው፡፡
ከሠባቱ ክፍሎች ውጪ በብረት እጄታ ውሥጥ የሚቀጣጠሉ እሳቶች አሉ፡፡ በደማማቅ ቀለማት የተንቆጠቆጡት ክፍሎች የእሳት ጮራ ሲንፀባረቅባቸው አሥደናቂ የሆነ ውበት ይፈነጥቃሉ፡፡ በመጨረሻው ጥቁር ክፍል ውሥጥ የሚፈጠረው ህብረ-ቀለም ግን በእጅጉ ይዘገንናል፡፡ የእሳቱ ጮራ በጥቁሩ ክፍልና ቀይ የደም ቀለም ባላቸው መስኮቶች ላይ ሲንፀባረቅ ለእይታ የሚቀፍ ድንግዝግዝ ቀለም ይፈጠራል፡፡ ወደ ክፍሉ ለሚገቡ ባለ ጭምብሎችም አስፈሪ የሆነ ገታን ያላብሳቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በጥቁሩ ክፍል ውሥጥ ከጥቁር እንጨት የተሰራ ግዙፍ ሰአት ቆሟል፡፡ እያንዳንዷ ሰአት በነጎደች ቁጥር ሰአቱ ቀዝቀዝ ያለ ቀፋፊ ድም ያሰማል፡፡ ልክ ሙሉ ሰአት ሲሞላ ደግም ለሁሉም ሰው ጉልህ ሆኖ የሚሰማ አስገምጋሚ ደውል ከጥቁሩ ሰአት ይመነጫል፡፡ የሰአቱን ሙሉነት የሚያበስረው ከባድ ደውል ሙዚቃ መሰል ጥኡም ዜማ ቢኖረውም በአድማጮቹ ልብ ላይ የሚፈጥረው ጥልቅ የሆነ እንግዳ ስሜት አለ፡፡ የሠአቱ አሥገምጋሚ ደውል በተሠማ ቁጥር ዝግጅቱን በማራኪ ዜማ ሲያደምቁ የቆዩት የሙዚቃ ቡድን አባላት ጨዋታቸውን አቁመው በሠአቱ ድም ይመሰጣሉ፡፡ ዳሌያቸውን ሲወዘውዙ የነበሩ ዳንኪራ ረጋጮች፤ እጅ ወደ ላይ የተባሉ ይመሥል ባሉበት ጠውልገው በመንፈሥ ይነጉዳሉ፡፡ ሲንጫጩ የቆዩ ነፍሶች፤ ሁሉ ነገር አለማቸውን ረስተው በሀሳብ ሰረገላ ይንሳፈፋሉ፣ በትዝታ ባህር ውስጥ ሠጥመው ይሟሟሉ፡፡
ደስተኛ የነበሩ ፊቶች ይገረጣሉ፡፡ ከጥቁሩ ሠአት የሚወጣው ልብ አንሠፍሥ ደውል ቀስ በቀስ ሲከስም፣ የደውሉ ርዝራዥ የገደል ማሚቶው ከቤቱ ድባብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠፋ ቤቱ ፀጥ ረጭ ይላል፡፡ ከዚያም ሁሉም በአንድ ላይ ያስካኩና ከዚህ በኋላ ወደ ሠአቱ ደውል እንደማይሳቡ እየተማማሉ ይነጋገራሉ፡፡ ሆኖም ስልሳ ደቂቃዎች አልፈው ከጥቁሩ ሰአት የሚመነጨው አብረክራኪ ድም ሲሠማ ሁሉን ነገር ረሥተው በያሉበት ቀና እንዳሉ ይቀራሉ፡፡
ይህም ሆኖ ጌታ ፕሮስፔሮ ያዘጋጀው የጭምብል ፓርቲ ከሞላ ጎደል አስደሳች ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ የልኡሉ ምርጫዎች ባብዛኛው ወጣ ያሉና ከብዙሀኑ ምርጫዎች ያፈነገጡ ናቸው፡፡ ነፍሡን የሚያስደስተው ባልተለመዱና እንግዳ በሆኑ ነገሮች ነው፡፡ ሀሳቦቹ ሁሉ ድፍረት የተሞላባቸውና በአደጋ የታጀሉ ናቸው፡፡ ብዙዎች ልኡሉ አእምሮው ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነበት ቀውስ ውስጥ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ሆኖም የእርሡ ተከታዮች ሠውዬውን በቅርበት መመልከትና በጥልቀት ማጤናቸው የግድ ነው፡፡
ፓርቲው በአመዛኙ አስደሳች ቢባልም በጥቂቱ የሚከነክኑ ገታዎች ነበሩት፡፡ አንድ ሺህ ባለ ጭምብሎች በክፍሎቹ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሲቦርቁ ቆዩ፡፡ የክፍሎቹን ቀለማት በላያቸው ላይ እያንፀባረቁ በሙዚቃ ድግስ ተምነሸነሹ፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ሙዚቃው እንቅስቃሴያቸውን ተከትሎ የሚፈሥ እንጂ እነሡ የሙዚቃን ምት እያነፈነፉ የሚወዛወዙ አይመስልም ነበር፡፡ ሆኖም ልክ የጥቁር ሠአት ደውል ሲሰማ ከደውሉ ድም ውጪ ያለው ነገር ሁሉ ፀጥ ረጭ ይላል፡፡ እንቅስቃሴዎች ጭጭ ሙጭጭ ብለው ይጠፋሉ፡፡ ተወዛዋዦች ወደ በረዶነት የተቀየሩ ይመስል በያሉበት ቀዝቅዘውና ደርቀው ይቀራሉ፡፡ ልክ የደውሉ ድም እንደጠፋ ደግሞ ደርቀው የቀሩ ሙት አካላት ሁሉ በድጋሚ ነፍስ ዘርተው አሸሼ ገዳሜያቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ቤቱ በሁካታና በውበት ይደምቃል፡፡ ባለጭንብሎቹ በየክፍሉ እየተዘዋወሩ ጌታቸው ባዘጋጀላቸው የደስታ ባህር ላይ ይዋኛሉ፡፡ በስተምዕራብ በኩል ከሚገኘው የመጨረሻ ክፍል ውስጥ ግን ከጥቁሩ ሰአትና የእያንዳንዱን ሰኮንድ ማለፍ ከሚያበስሩት ቀዝቃዛ ድምፆች በቀር ምንም ነገር የለም፡፡ ወደዚኛው ክፍል ለመግባት የሚደፍር ባለጭምብል ማግኘት ከነአካቴው አይታሰብም፡፡ የክፍሉ ጥቁረትና ቀይ የደም ቀለም ያላቸው መሥኮቶች የሚረጩት ዘግናኝ ብርሀን፣ በባለጭምብሎቹ ልብ ላይ ከፍተኛ የፍርሀት ስሜት ያሳድራሉ፡፡ በዛ ላይ ወደዚህ ክፍል የሚገባ ባለጭምብል በእያንዳንዷ ሰኮንድ ውስጥ ከጥቁሩ ሰአት የሚመነጨውን ሰቅጣጭ ድም ማስተናገድ ይኖርበታል፡፡ የሰአቱ ድም ስጋውን፣ ደሙንና አጥንቱን አልፎ ከመቅኖው ጋር ይዋሀዳል፡፡ ስለዚህ ከክፍሎቹ በስተመጨረሻ ወደሚገኘው ጥቁር ክፍል ዝር የሚል አካል የለም፡፡ የተቀሩት ስድስት ክፍሎች ግን በሠዎች ተጨናንቀዋል፡፡ በነዚህ ክፍሎች ውሥጥ ሞቃት የሆነ ማራኪ የህይወት ምት ከነጣፋጭ ለዛው ይደመጣል፡፡
በዚህ መልኩ ጭፈራው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ዘለቀና ልክ ከሌሊቱ ስድሥት ሰአት መሆኑን የሚያበስረው ገዝጋዥ ደውል ከጥቁሩ ሠአት ሲፈነዳ፣ ሙዚቃውም ታዳሚውም በያሉበት ቀጥ አሉ፡፡ ይሄኛው ደውል ከዚህ ቀደም ከተሠሙት ሁሉ የተለየና የምሽቱን ድባብ ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ነበር፡፡ ፀጥ ረጭ ባሉት ክፍሎች ውሥስ አስራ ሁለት የደውል በትሮች አቃጨሉ፡፡ የታዳሚዎች ልብ ከደውሎቹ እኩል ደለቁ፣ እኩል ደም ረጩ፡፡ በጥልቅ፣ ተመሥጥኦ ቀልጠው በሟሙት ነፍሶች ውስጥ እልፍ አእላፍ የሀሣብ ሰንሰለቶች ገደብ የለሽ በሚመሥለው የጊዜ ልኬት ላይ ነገሡ፡፡ የመጨረሻው የደውል በትር እስትንፋሡ ነጥፎ፣ ፀጥታ ከመሥፈኑ በፊት ውሥብስብ የሆነው የገደል ማሚቱ በስፍራው ላይ ተስተጋባ፡፡ በእርግጥ ይህን ጊዜ ነበር በርካቶች እስካሁን ያላስተዋሉት እንግዳ ባለጭምብል ከመካከላቸው መጋደሙን ልብ ያሉት፡፡ የመጨረሻውን ደውል ተከትሎ በቤቱ ውሥጥ የተስተጋባው የገደል ማሚቱ በፈጠረባቸው ሠመመን ውስጥ ሠጥመው ያንን ለአይን የሚቀፍ፣ ለመንፈስ የሚጨንቅ ፍጡር በልባቸው መነር አበክረው ተመለከቱት፡፡ የባለ ጭምብሉን ማንነት ለማወቅ እርስ በእርሳቸው አንሾካሾኩ፣ ተጠያየቁ፡፡ ጫጫታና ጉሩምሩምታ አዳራሹን ናጡት፡፡ ቀስ በቀስ የመገረምና የመደመመ ከዚያም የፍርሀትና የስጋት፣ በመጨረሻም አሰቃቂ የሆነ የህመምና የሥቃይ ሥሜት በስፍራው ላይ ተንሰራፋ፡፡
እስካሁን ሲገለ በነበረው አይነት አስደሳች ድባብ ላይ እንደዚህ አይነት ውዥንብር መዝራት የሚችል ፍጡር፣ ፍፁም ልዩ የሆነ ፍጡር እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡ መቼም ሰው ሆኖ ስሜት የሌለው ፍጡር አይኖርም፡፡ የሠው ልጅ ያሻውን ያህል ግድ የለሽ ቢሆን እንኳ፣ ከተነኩ ሥሜቱን የሚያገነፍሉ የተወሠኑ የልብ አውታሮች ይኖሩታል፡፡ እነዛ ህይወትንም ሆነ ሞትን እንደ ቀልድ የሚቆጥሩ ብኩኖች እንኳን አንዳንድ የማይቀልዱባቸው ነገሮች አሏቸው፡፡ ለነዛ በሁሉ ነገር ላይ ማፌዝና ማላገጥ ለሚችሉ ደንታ ቢሥ ቀላጆችም ቢሆን እንደዚህ አይነቱ ነገር ከንፈርን አሥፈልቅቆ ጥርስን የሚያስፈታ ጉዳይ አይደለም፡፡
የእውነት ለመናገር ጌታ ፕሮሥፔር በፓርቲው ላይ ተከታዮቹ ያሻቸውን አይነት ልብስ እንዲለብሡና የመረጡትን አይነት ጭምብል እንዲያጠልቁ ፍቃድ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ሥፍራ ላይ የተከሠተው እንግዳ ፍጡር የለበሠው ልብስና ያጠለቀው ጭምብል ግን ገደብ የለሹን የጌታ ፕሮሥፔሮን ፍቃድ የተሻገረ ነው፡፡ ሠውዬው ያለቅጥ ከመርዘሙና ከመቅጠኑም ባሻገር ልክ ሊቀበር እንደተዘጋጀ የተገነዘ ሬሳ፣ ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በጨርቅ ተሸፍኗል፡፡ በፊቱ ላይ ያጠለቀው ጭምብል አጠገቡ ቀርበው የተመለከቱት አይኖች ሊለዩት እስኪያዳግታቸው ድረስ ገፁን ሙሉ ለሙሉ የሙት ሠው ፊት አስመስሎታል፡፡ ይህም ይሁን… ምንም አይደል፣ ታዳሚያኑ ይህንን ሁሉ ሊታገሡ ብሎም ሊቻቻሉ ይችላሉ፡፡ እነሡን እረፍት የነሳቸው አንድ ነገር ነው፡፡ ሠውዬውን ሲመለከቱ የቀዩ ጣዕረ-ሞት ምስል ድቅን እያለባቸው ተረብሸዋል፡፡ የእንግዳዉን ሠው ልብስ የደም ጠቃጠቆ አጥልቶበታል፡፡ ፊቱም ፍም የሆነ ቀይ አጋንንት መስሏል፡፡
“ይህንን ዘግናኝ ፍጡር በሠዎች መካከል በዝግታና በሙሉ ልብ ሲንቀዋለል ያየው ጌታ ፕሮስፔሮ፤ መጀመሪያ በፍርሀት ከዚያም በቁጣ ሥሜት ተንቀለቀለ፡፡ “የማን ነው ደፋር?! “ ጌታ ፕሮሥፔሮ በፍርሀትና በንዴት መካከል ሆኖ አምቧረቀ
“ይዛችሁ ጭምብሉን አውልቁልኝ! እስኪ ማንና ምን እንደሆነ እናያለን! “ በሁለት ስሜቶች ፍጭት ተቀፍድዶ አዘዘ፡፡ በጥቂት ጋሻ ጃግሬዎች የተከበበው ጌታ ፕሮሥፔሮ፤ ከበስተምስራቅ ከሚገኘው ሠማያዊ ክፍል ውስጥ ሆኖ የሚያጮሃቸው የድም ጅራፎች፤ በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ግልና ጉልህ ሆነው ይስተጋቡ ነበር፡፡ በእርግጥ የአዛዡ ድም እንደተሰማ ሠዎች ሠብሰብ ብለው ወደ እንግዳው ፍጡር ሲተሙ ታይተው የነበረ ቢሆንም ከአጠገቡ እንደደረሡ ግን ሠውዬው ላይ እጅ ለመሠንዘር በቂ ድፍረት ያለው ልብ ጠፋ፡፡
እንግዳው በጌታ ፕሮሥፔሮ እልፍኝ ውሥጥ ለሠሥ እያለ ሲያዘግም፣ ሁሉም ሠው ወደ ኋላ ሽሽት እያለ አሳለፈው፡፡ ማንም ሰው ሳያቆመው ፍፁም በሆነ ዝግታ፣ በተለካና በተጠና አረማመድ ሠማያዊውን ክፍል እየለቀቀ ወደ ወይን ጠጁ ክፍል አመራ፡፡ ከወይን ጠጁ ክፍል ከደረሠ በኋላ ወደ አረንጓዴው፣ ከዚያም ወደ ቢጫ ወደ ነጭ በነጩ ክፍል ውሥጥ አድርጐ ከሀምራዊው ክፍል ደረሰ፡፡ ይህን ጊዜ ነበር ጌታ ፕሮሥፔሮ መላ አካሉ በቁጣ ነዶ፣ ሥለቱን ከጉያው መዞ በስድሥቱ ክፍሎች ቁልቁል እየተንደረደረ፣ ከጥቁሩና ከሀምራዊው ክፍል ድንበር ላይ ወደ ደረሰው እንግዳ ፍጡር የቀረበው፡፡ ሁሉም ሠው በአርድ አብረክርክር ፍርሀት ስለተሸበበ፣ አንድም ሠው ጌታውን ለመከተል አልደፈረም፡፡ ጌታ ፕሮሥፔር ሥለቱን እንደደገነ ከባለ ጭምብሉ ጎን ሊደርስ ሶሥት ወይንም አራት ጫማ ሲቀረው፣ በራስ ቅሉ ውሥጥ የፍርሀት መርዝ ሰንቅሮ አካልን የሚያደርቅ የሠይጣን ጉማጅ ከፊት ለፊቱ ተደንቅሮ ጠበቀው፡፡ በድንጋጤ ደንዝዞ ከደረቀው የጌታ ፕሮስፔሮ በድን አካል ውስጥ አሰቃቂ የሆነ ሠቅጣጭ የስቃይ ድም ተሠማ፡፡ አብረቅራቂው ስለት ከመዳፉ ተንሸራቶ እየተብለጨለጨ በጥቁሩ ወለል ላይ ወደቀ፡፡ በደቂቃዎች ብልጭታ ውስጥ የጌታ ፕሮሥፔሮ ሙት አካል የሥለቱን አቅጣጫ ተከትሎ በጥቁሩ ወለል ላይ ተዘረረ፡፡
ይህንን የተመለከቱት የልኡሉ ተከታዮች ከሌጣ ፍርሀት የመነጨ ድፍረታቸውን አሰባስበው፣ በጥቁሩ ክፍል ውስጥ ከግዙፉ ሠአት ጥላ ስር በድን መሥሎ ወደ ተገተረው ፍጡር ተመው ጠንካራ መዳፋቸውን ሊያወርዱበት ተራወጡ፡፡ ሆኖም በሬሳ መገነዣ ከተጠቀለለውና ሙት መሠል ጭምብል ካጠለቀው አካል መሠል ነገር ውስጥ ምንም አይነት አካል አለመኖሩን ሲረዱ የጣዕር እንባቸውን አነቡ፡፡ ሞት ሳይበላቸው በህይወት እያሉ ለራሳቸው ሙሾ አወረዱ፡፡ ባልጠበቁት መንገድ ባላሰቡት ሠአት በዚህ ውድቅት ሌሊት ቀዩ ጣዕረ-ሞት እንደመጣባቸው ተገነዘቡ፡፡
ቀስ በቀስ፣ አንድ በአንድ፣ በጥቁሩ ወለል ላይ እየተንጠባጠቡ፤ በቀዩ ጣዕረ-ሞት ቁጣ ሁሉም በድን ሆነው ቀሩ፡፡ የጥቁሩ ሠአት እስትንፋሥም ከመጨረሻው ሟች ነፍሥ ጋር አብሮ ተቋጨ፡፡ ድቅድቁ ጨለማና ቀዩ ጣዕረ-ሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሁሉም ላይ ለሁሌም ነገሡ፡፡

 

Read 4686 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:38