Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 22 October 2011 12:15

ዓለም አቀፋዊው ሕዝባዊ አመፅ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አለማችን በአዲስ አይነት ሕዝባዊ አመፅና የለውጥ ማዕበል እየተናጠች ነው፡፡ 2011 ዓ.ም ገና ከመጥባቱ በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ ፕሬዝዳንት ቤን አሊን ካሰናበተ በኋላ ወደ ግብፅ በማምራት ለ30 ዓመታት ተደላድለው ይመሩ የነበሩትን ሙባረክንም ከስልጣናቸው አሽቀንጥሯቸዋል፡፡ ቀጥሎም በየመን፣ በባህሬን፣ በሶሪያ፣ በአልጀሪያ፣ በሊቢያ፣ በኳታር፣ በዮርዳኖስ፣ በኩዌትና በሌሎችም አረብ አገራት ሕዝባዊ አመፅ ተቀስቅሷል፡፡ የሊቢያ አማፂያን ከኮሎኔል ጋዳፋ ታማኞች ጋር ለስድስት ወራት ያህል በመዋጋት ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ አወዛጋቢ የሆኑት ጋዳፊም ከትናንት ወዲያ መገደላቸው ተገልጿል፡፡

በቃላቸው የማይገኙት የየመኑ መሪ አብደላህ ሳላህ በቅርቡ ስልጣን እንደሚለቁ መናገራቸው እውነት ከሆነ የመንም በሕዝባዊ አመፅ የተገኘውን ድል ማጣጣም ትጀምራለች፡፡ በሶሪያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ በየጊዜው በርካቶችን እየቀጠፈ ቢሆንም በሽር አል-አሳድን ለማውረድ የተጀመረው ተቃውሞ አሁንም ቀጥሏል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝባዊ አመፅ የተቀሰቀሰባቸውና አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙት የተቀሩት የአረብ አገራት መሪዎች ለሕዝባቸው የተለያዩ ማባበያና ድጐማ በማድረጋቸው ጋብ ሊልላቸው ችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአረቡ አለም ሕዝባዊ አመፅ በመካከለኛው ምስራቅ ብቻ አልተገታም፡፡ ከሰሞኑ፣ መላውን የአለማችንን ታላላቅ ከተሞች መሰረት ያደረጉ ተቃውሞዎች ቀስ በቀስ ከዓለም ጫፍ ወደ ሌላው የዓለም ጫፍ ተዳርሰዋል፡፡
ከኒውዮርክ እስከ ቶኪዮ፣ ከሜልቦርን እስከ ለንደን፣ ከጃካርታ እስከ ማድሪድና ባርሴሎና፣ ከሳንቲያጐ እስከ ሮም፣ ከቤጂንግ እስከ በርሊን፣ ከኒውዴሊ እስከ ቴላቪቭ ድረስ እንደ ወረርሽኝ ተዛምቷል፡፡ ባጠቃላይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስን ተከትሎ በተፈጠረ የኢኮኖሚ መናጋት፣ የበለፀጉ አገሮች መንግስታት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ ችሏል፡፡
ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው፣ ለውጥ መፈለግ የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጐት ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናትም ለውጥን ለማምጣት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ ከዛሬ 162 አመት በፊት የ1848 አብዮት በመባል የሚታወቀው የአውሮፓ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ፤ በይዘትም በቅርፅም አሁን ከተፈጠረው አብዮት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ልክ እንደ አሁኑ ዘመን የጊዜው አብዮት፣ የገንዘብ ዋጋ ግሽበትና የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር እንዲሁም የሸቀጥ ዋጋ መናር አይነተኛ መገለጫዎቹ ነበሩ፡፡ የዚያን ዘመን ነገስታት ጊዜ ያለፈባቸውና ያረጁ ሆነው ነበር፡፡ እንደ አሁኑ ዘመን ግንባር ቀደም የአመፁ ተሳታፊ በዋነኛነት ወጣቱ ትወልድ ሲሆን በጊዜው የነበረውን የመገናኛ ዘዴ ማለትም በገፍ የሚታተሙ ጋዜጦችን እንደ ዋነኛ መረጃ ይጠቀም ነበር፡፡
ነገር ግን የዘመኑ አመፅ በመልካም አልተደመደም የአማፂዎቹ ኃይል ከተጠናከረ በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተከፋፈሉ፡፡ ይባስ ብሎም እርስ በእርስ በተነሳ ግጭት ሳቢያ ተዳከሙ፡፡ ከዚያም ደብዛቸው ጠፋ ሠራዊቱ ደግሞ ከንጉሳዊያኑ ጋር ታማኝ ሆነው በመቆማቸው ሕዝባዊ አመፁን በተኑት፡፡ ነገስታቱም ትንሽ ቆይተው ራሳቸውን አጠናከሩ፡፡ ነገሩን አንድ የታወቁ የእንግሊዝ ታሪክ ፀሐፊ እንዲህ ገልፀውት ነበር፡፡ ታሪክ የመንገዱ ጫፍ ላይ ከወጣ በኋላ፣ ተመልሶ ወደ ነበረበት አሽቆለቆለ”
በሌላም በኩል እ.ኤ.አ ከ1967-68 ድረስ በምዕራብ አውሮፓ እና በምስራቅ አውሮፓ ሕዝባዊ አመፆች ተቀስቅሰው ነበር፡፡ በእርግጥ በዚያን ጊዜ አብዛኛው አውሮፓዊ ጥሩ ስራ ገቢ የነበረው ሲሆን፣ የፋይናንስም ሆነ የኢኮኖሚ ቀውሶች አልነበሩም “አናርኪስቶች” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የዚያ ዘመኖቹ ተቃዋሚዎች ለተቃውሟቸው ጠንካራ ራእይ እንዳልነበራቸው ይነገራል፡፡ በ1980ዎቹም ቢሆን በምስራቅ አውሮፓ የሶሻሊስት ሥርዓትን ለመናድ ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ አመፆች ተካሂደዋል፡፡
አሁን ደግሞ በ2011 ዓ.ም በዓለማችን ላይ ከዳር እስከ ዳር የተነሱት ተቃውሞዎች የዓለምን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ሊቀይሩ እንደሚችሉ የብዙዎች ግምት ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም በ82 አገሮች በ951 ከተሞች ውስጥ የተካሄዱት ዓለም አቀፍ ተቃውሞዎች በይዘታቸውም በአይነታቸውም እስካሁን በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ የሚበልጡ ናቸው፡፡
CNN ሰሞኑን ሰፊ ሽፋን በመስጠት እንደዘገበው፣ በየአገሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች፣ ኢኮኖሚውን በበላይነት በመቆጣጠር የአገሪቱን ሃብት ወደ ካዝናቸው በገፍ በሚያስገቡት ሃያላን ኩባንያዎች ላይ ቁጣቸውን አሰምተዋል ብሏል፡፡ በሁሉም አገሮች ተመሳሳይ የተቃውሞ ድምፅ እንደሚሰማ የገለፀው ሲኤንኤን፤ 1 በመቶ የሚሆኑት ኩባንያዎች ሀብትን ለራሳቸው ሲያጋብሱ፣ለ 99 በመቶ የምንሆን ብዙሃን ግን ገለልተኛ ተደርገናል የሚል ነው፡፡
በስራ ማጣትና በኑሮ መወደድ የተማረሩ አሜሪካዊያን ባለፈው ቅዳሜ ከዎልስትሪት ሕንፃ አንስተው እስከ ኒውዮርክ ስኩዌር ድረስ በእግር በመሄድ ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ “ለባንኮችና ለኩባንያዎች የሚደረገው ከፍተኛ ድጐማ ባዶ እጃችንን አስቀርቶናል”፣ “ኩባንያዎች አላስፈላጊ ትርፍ እንዲያጋብሱ ተደርጓል”፣ “የሃብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ አይደለም”፣ “ዩናይትድ ስቴትስ ተነሺ! (Wake up United States)” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ወጥተዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ በ59ኛው ጐዳና ላይ በሚገኘው የቢሊየነሩ ሩፐርት ሙድሮክ መኖሪያ ቤት ሲደርሱም፣ “ሚ/ር ሙድሮክ ይበቃዎታል”፣ ሃብትዎን ያካፍሉ በማለት በጩኸት ተናግረዋል፡፡
በለንደንም ቢሆን ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፡፡ በለንደን ቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል ፊት ለፊት የተሰበሰቡ እንግሊዛዊያን፣ 99 በመቶ የሚሆኑ ብዙሃን ስራ አጥና የስራ ዋስትና የሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ ጣታቸውን በባለሃብቶች ላይ ቀስረዋል፡፡ “ካፒታሊዝም መልካም ነገር አላደረገልንም” “ካፒታሊዚም አርጅቷል” “ካፒታሊዝም ፍትህን አላመጣም” የሚሉ መፈክሮች ተስተጋብተዋል፡፡
በለንደን ከወጡት ተቃዋሚዎች ውስጥ ፒተር ቫጉ ሃን የተባለ ተቃዋሚ ሲናገር፣ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘባችንን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ወስደውታል፡፡ እኛን ችላ ያለውን መንግስት ድምፃችንን በማሰማት እንቃወመዋለን በማለት ተናግሯል፡፡
በፈረንሳይም ቢሆን ቀላል የማይባል ተቃውሞ ተካሂዷል፡፡ አንዱ ተቃዋሚ ድምፁን ከፍ በማድረግ ሲገልፅ፤ የአገሪቱ መሪዎች ከሕዝቡ ጋር ለመነጋገርም ሆነ፣ ችግሩን ለማየት ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ የቱንም ያህል ለተቃውሞ ብንወጣ አሁንም እየሰማችሁን አይደለም፡፡ ነገር ግን የማትሰሙን ከሆነ አሁን የተከሰተው ብሶት እየቀጠለ በመሄድ አገሪቷ ወደ አለመረጋጋት እንደምታመራ እወቁ በማለት ለፈረንሳይ መሪዎች ድምፁን አሰምቷል፡፡
በዎልስትሪት የተነሳው ሕዝባዊ አመፅ ሮምንም ሲያሸብራት ውሏል፡፡ በሮም ፓርታሳንጆቫኒ አጠገብ በሚገኘው የአገር ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ ሕንፃውን በመክበብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጣሊያናዊያን ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡ በተለይም የተወሰኑ ተቃዋሚዎች፣ ቤንዚን የተሞሉ ጠርሙሶችን በሕንፃው ላይ ወርውረዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ መኪና ሲያቃጥሉና መስታዎቶችን ሲሰባብሩ ተስተውሏል፡፡ የሮም ፖሊሶች ጣልቃ በመግባታቸው በተፈጠረው ረብሻም፣ 70 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሷል፡፡ ሮም ከተማ በአንድ እግሯ የቆመች እስኪመስል የተነሳውን ሕዝባዊ አመፅ፣ የጣሊያን መንግስት መቆጣጠር እስኪሳነው ድረስ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር፡፡
የስፔኗ ማድሪድም ብትሆን በተቃውሞ ማዕበል ከተናጡት አገሮች አንዷ ነበረች፡፡ በማድሪድ፣ ከፕላዛ ዲ.ሲብሌስ እስከ ፓረታ ዲ.ሶል ሕንፃ ድረስ በኑሮ መወደድና በሥራ አጥነት የተማረሩ ስፔናዊያን፣ መንግሥት እየተመለከተን አይደለም በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ በማድሪድ ጐዳናዎች ላይ “በጥቂቶች መብታችን ተሰርቋል” የሚል አርማ የያዙ በርካታ ሰልፈኞች ጐዳናውን አጨናንቀውት ነበር፡፡ በማድሪድ የተቀጣጠለው ተቃውሞ ወደ ባርሴሎናም ተዛምቷል፡፡
ጀርመንም ብትሆን ሕዝባዊ ተቃውሞን ለማሰማት አልዘገየችም፡፡ በጀርመን የወጡት ሰልፈኞች በአገሪቱ የሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎች ላይ ቁጣቸውን አሰምተዋል፡፡ ጀርመናዊያን ለደረሰባቸው ችግር Gold Mansucks እና ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡ በጀርመን የነበረ አንድ ተቃዋሚ ሲናገርም “መንግስት ሕዝቡን ሊፈራ ይገባል እንጂ፣ ሕዝቡ መንግስትን ሊፈራ አይገባም” በማለት ተናግሯል፡፡ መቼም ጀርመን ጋር ቀልድ የለም መሰለኝ፣ የጀርመን ፖሊሶች ሚጥሚጣ የተሞሉ አስለቃሽ ጪስ ይዘው በመውጣት በሰልፈኞቹ ላይ ነስንሰውታል፡፡
በካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ በተካሄደ ተቃውሞ ደግሞ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች “1 በመቶ የሚሆኑት የታላላቅ ኩባንያ ባለቤቶችና አንዳንድ ባለስልጣናት ይታሰሩ” “ወጣቶችን ችላ ማለት ይቁም” እንዲሁም “99 በመቶ የምንሆን እኛ ፀረ ሞኖፖሊስት አቋም ይዘናል” የሚል መፈክር አሰምተዋል፡፡
ሕዝባዊ አመፅ ምን እንደሆነ የማታውቀው የስካንዴቪያዋ አገር ዴንማርክም ሕዝባዊ ተቃውሞን አስተናግዳለች፡፡ በዴንማርክ ኮፐንሃገን ከተማ 3000 የሚጠጉ ተቃዋሚዎችም “1 በመቶ የሚሆኑት ሞኖፖሊስቶች ሃብትን አለአግባብ አጋብሰዋል፡፡ 99 በመቶ የሚጠጉት በመካከለኛ ኑሮ የሚገኙት ዜጐች ግን ተዘንግተዋል” የሚል መፈክር አሰምተዋል፡፡
ሕዝባዊ አመፅ የተለመደባት ግሪክም ከሰሞኑ ተቃውሞ ጋር ተቀላቅላለች፡፡ በግሪክ የባህር ኃይል ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው፣ የመርከቦች እንቅስቃሴ ተቋርጧል፡፡ የአገሪቱ ገንዘብ ሚኒስቴር ሰራተኞችም በመንግሥት ላይ ቁጣቸውን ለመግለፅ የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል፡፡ የግሪክ ፖሊሶች በየጊዜው በሰልፈኞቹ የሚወረወረውን ድንጋይ ለመቆጣጠር ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው የሰለጠኑ ውሾችን ይዘው አድማውን ለመበተን ተገደዋል፡፡
ሕዝባዊ አመፁ ኢስያንና አውስትራሊያንም ጐብኝቷል፡፡ በታይላንድ፣ በቻይና፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በኢንዶኔዥያ፣ በኒውዝላንድ በጃፓንና በሌሎችም የኢስያ አገራት ተመሳሳይ ተቃውሞ ተካሂዷል፡፡
በኢንዶኔዥያ ጃካርታ ከተማ በተካሄደ አመፅ፣ ፊታቸው ላይ ማክስ ያጠለቁ ሰዎች፣ የአሜሪካ ኤምባሲን በመክበብ፣ “የአሜሪካን መንግስት የሚከተለው የኢምፔሪያሊዝም ሥርዓትለ መደምሰስ አለበት” በማለት በጩኸት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተቃዋሚዎቹ “ኢምፔሪያሊስቶች ዘራፊዎች፣ ጦረኞችና ወራሪዎች ናቸው” የሚሉ ተቃውሞዎችንም አሰምተዋል፡፡ በጃፓንና በኒውዝላንድም ተመሳሳይ ተቃውሞ ተካሂዷል፡፡
በቺሊ ሳንቲያጐ ከተማም ቢሆን “ኢምፔሪያሊዝም ይውደም” የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል፡፡ በሳንቲያጐ የሚገኙትን ግዙፎቹ የአሜሪካና የጀርመን ኩባንያዎችንም “ሆዳሞች” በማለት ተሳድበዋል፡፡
በሁሉም አገራት የሚገኙ ተቃዋሚዎች ያነሱት ጥያቄ ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን፣ ይኸውም ከሕብረተሰቡ 1 በመቶ ብቻ የሚሆነውን የሚወክሉት ሞኖፖሊስቶች ኢኮኖሚውን በበላይነት በመቆጣጠራቸው ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል (Fair Wealthy Distribution) እንዳይፈጠርና ስራ አጥነት እንዲስፋፋ አድርጐታል የሚል ነው፡፡ በአሜሪካ የተደመጠው “We are 99%” እና “Bank are Cancer” የሚሉ መፈክሮችም በብዙ አገሮች ተስተጋብቷል፡፡
በምዕራብ አውሮፓ አገራት በተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅ የተደናገጡት የአውሮፓ መሪዎች በቀጥታ የሰጡት ምላሽ አለመኖሩ የአውሮፓ መንግለስታት ግራ መጋባታቸውን የሚጠቁም ነው በማለት፣ ዓለም አቀፍ ፖለቲከኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን የቡድን 20 አገራት የፋይናንስ ሚኒስቴሮች ቅዳሜ እለት፣ በፓሪስ ተሰብስበው ባንኮችም ሆኑ ሌሎች ኩባንያዎች ተገቢ የሆነ የካፒታል አቅም እንዲኖራቸው እና የተረጋጋ የግሎባል ገበያ ለማምጣት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
በአሜሪካ ዎል ስትሪት አካባቢ የተነሱት ተቃዋሚዎች፤ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማድረግ የተንቀሳቀሱት አብዛኞቹ በሥራ ማጣትና በኑሮ መወደድ የተማረሩ መሆኑ ቢገለፅም፣ ለተቃውሞ እንዲወጡ ይበልጥ ያነሳሳቸው ግን የቱኒዚያውና ግብፁ ሕዝባዊ አመፅ ያመጣው ስኬት እንደሆነ አብዛኞቹ ተናግረዋል፡፡በሌሎች አገሮች የተካሄዱ ተቃውሞዎች ደግሞ ዎል ስትሪትን መሰረት አድርገው እንደ ነበር ተገልጿል፡፡ በተለይም በአውስትራሊያ ሜልቦርን የወጡት ሰልፈኞች፤ ከአሜሪካዊያን ተቃዋሚዎች ጋር ያላቸውን አንድነት ለማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሜልቦርን አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች ልክ በካይሮ ታህሪር አደባባይ እንደታየው ለመኝታ የሚያገለግሉ ልብሶችንና ምግቦችን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በሌላም በኩል በሰሞኑ የተካሄዱ ሕዝባዊ አመፆች ልክ እንደ ቱኒዚያና ግብፅ ተቃዋሚዎች ማህበራዊ ድረ ገፆችን ተጠቅመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች በ2011 ዓ.ም የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ሕዝባዊ አመፅ የክሊክሊቲዝም አብዮት ነው ብለውታል፡፡
የዊክሊክስ ድረ-ገፅ መስራች ጂሊያን አሳንጂ፣ ይህንን ሁሉ ያመጡት ስግብግብ የሆኑ ባለሀብቶችና አንዳንድ ፖለቲከኞች ናቸው በማለት ገልጿል በተጨማሪ አሳንጂ መሪዎች ለሕዝባቸው ድምፅ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡም ጠይቋል፡፡
በእርግጥም 2011 ዓ.ም አለማችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ጥያቄዎችና አመፆች የተናጠችበት ዓመት ነው፡፡ በእስራኤል መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በከፍተኛ የቤት ዋጋ መናር የተነሳ ተቃውሞ፣ በሕንድ በሙስና የተነሳ ተቃውሞ፣ በቻይና ሙስናና የተራራቀ የሃብት ክፍፍል፣ በአሜሪካ የስራ አጥነትና የስራ ዋስትና ማጣት እንዲሁም ባንኮች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ድጐማ እየተደረገላቸው ሌላው ሕብረተሰብ ችላ መባሉና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመፅ አስመልክቶ የአለማችንን የኢኮኖሚ ርዕዮት እና የካፒታሊዝም ስርዓት አጣብቂኝ ውስጥ መግባትና የወደፊቱን የዓለማችንን የኢኮኖሚ እጣ ፈንታ አስመልክቶ፤ በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር እንዲሁም Crisis Economics መፅሐፍ ተባባሪ ደራሲ የሆኑት ፕሮፌሰር ኖሩዌል ሮቢን ትንተና አቅርበዋል፡፡
ለስራአጥነት፣ ከስራ መፈናቀል እና የተራራቀ የሃብት ክፍፍል እንዲሁም የኑሮ መወደድና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ፕሮፌሰር ሮቢኒ ሲጠቅሱ፣ በዋነኛነት የግል ዘርፍ ኩባንያዎች በጣም እየበለፀጉ ሲሄዱ፣ ካፒታል ወደ እነርሱ ይሰበሰባል፣ በዚህን ጊዜ ተራው ሕብረተሰብ ያለው አቅም እየተዳከመ ይሄዳል፡፡ በተለይም እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ያለ ገደብ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት፣ ጤናማ ባልሆነ ፉክክርና ብልፅግናን ሲያገኙ፣ ሌለው ሕብረተሰብ ከጨዋታ ውጪ እየሆነ ይሄዳል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የቻይና እና የሕንድ ካላቸው የሕዝብ ቁጥር አንፃር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሠራተኞችን በርካሽ ዋጋ ለኩባንያዎች ተቀጥረው መስራታቸው በርካታ የምዕራባዊያን ኩባንያዎች ተነቅለው ወደዚያ ስፍራ እንዲንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠራተኛ ደሞዝ እንዲቀንስና የስራ እድሎችም እንዲታጡ አድርጓል ይላሉ፤ ፕሮፌሰር ሮቢኒ፡፡
ሮቢኒ ሲቀጥሉ፣ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ በአሜሪካ በሮናልድ ሬገን አስተዳደርና በእንግሊዝ በማርጋሬት ታቸር አስተዳደር ወቅት፣ ኒዮ-ሊበራሊዝም ማቆጥቆጥና መስፋፋት ገበያው ቁጥጥር እንዳይኖረው አድርጓል ይላሉ፡፡ አሁን የተፈጠረው ቀውስ ኒዮ ሊበራሊስቶች ያመጡት ጣጣ ነው በማለትም ይገልፃሉ፡፡ በ(Market Oriented Liberal Democracies) መሰረት የፋይናንስ ተቋማት ልቅ በሆነ የገበያ ስርዓት፣ ያለ ገደብ እንዳሻቸው እንዲንቀሳቀሱና ገበያውን እንዲመሩት በመደረጉ፣ የገንዘብ ቀውሱንና የምጣኔ ሃብት ድቀትን አስከትሏል በማለት ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪም በአሜሪካ በርካታ ባንኮች ቅጥ ያጣ ብድር መስጠታቸውና ያበደሩትን በወቅቱ መሰብሰብ አለመቻላቸው እንዲሁም በትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር በእዳ የተሰሩ ቤቶች ዋጋቸው ማሽቆልቆል እንደ ምክንያት ይጠቀሳል በማለት አብራርተዋል፡፡
በ19ኛው ክ/ዘመን የኖረው ታዋቂው ጀርመናዊው የፖለቲካ ፈላስፋ ካርል ማርክስም፤ ካፒታሊዝም ዛሬ በዓለም ላይ የተፈጠረውን ችግር እንደሚያመጣ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ ማርክስ፣ ፍሬድሪክ ኤንግልስ ከተባለው አጋሩ ጋር በመሆን “The Communist Manifesto” በተባለው መፅሐፍ ላይ የካፒታሊዝም ስርዓት ውልዶች በሆኑት ልቅ የሆነ የገበያ ስርአት፣ ግሎባላይዜሽን፣ ሞኖፖሊዝም ምክንያት የፋይናንስ ቀውስና የኢኮኖሚ ግሽበት እንደሚፈጠር ተናግሯል፡፡ ጥቂቶች ብቻ ወደ ካዝናቸው በሚያግበሰብሱት ሃብት ምክንያት የኑሮ መወደድና ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ሠራተኞች አደጋ ውስጥ እንደሚወድቁ ከዛሬ 150 ዓመት በፊት ምሁራዊ ትንቢቱን ገልፆ ነበር፡፡ፕሮፌሰር ሮቢኒ፣ መፍትሄ ያሉትንም ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ብዙሃኑን ሊጠቅም የሚችል የኢኮኖሚ ሞዴል መቅረፅና ጤናማ የገበያ ስርዓትን መዘርጋት እንዲሁም በባንኮችና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በገበያው ውስጥ የራሱን ድርሻ ሲወጣ፣ መንግስትም ተገቢ ባልሆኑ የገበያ እንቅስቃሴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም አዳዲስ የስራ መስኮችን ማስፋፋት እና ሰፊ የሃብት ልዩነቶችን ሊፈጥሩ የማይችሉ የእድገት ሞዴሎች ማስፋፋት ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን የ2011 ዓ.ም ሕዝባዊ አመፅ ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም በማለት አጠቃለዋል፡፡

 

Read 6423 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 12:27

Latest from