Saturday, 29 December 2012 08:35

ሊፋን በየዓመቱ ሁለት የረድኤት ድርጅቶችን ሊረዳ ነው

Written by  መታሠቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

ከአንድ መኪና ሽያጭ 300 ብር እሰጣለሁ ብሏል
ሊፋን ሞተርስ ሁለት አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶችን ለአንድ ዓመት በቋሚነት ለመርዳት መዘጋጀቱንና ከፈረንጆች አዲስ አመት ጀምሮ ከሚሸጡ መኪኖች ከእያንዳንዳቸው ላይ 300 ብር ለድርጅቶቹ መርጃ እንደሚያውል አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ በየዓመቱ ሁለት ሁለት በግብረ ሠናይ ተግባራት ላይ የተሰማሩ በጐ አድራጊ ድርጅቶችን እየመረጠ ለአንድ ዓመት እርዳታ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

በዚሁ መሠረትም ለቀጣዩ አንድ አመት ሜሪጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅትን እና ሜቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ድርጅትን ይረዳል፡፡ ኩባንያው ለእነዚህ ሁለት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በዓመት ውስጥ ከሚሸጣቸው መኪኖች በእያንዳንዱ መኪና 300 ብር ሂሣብ ለመርዳት የተዘጋጀ ሲሆን በዓመት ውስጥም ከ300ሺህ ብር በላይ ግብረሰናይ ተቋማቱ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡ 
የሁለቱ አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶች መስራችና ሥራ አስኪያጆች እንደተናገሩት፤ በአገራችን በርካታ እናትና አባታቸውን አጥተው ለጐዳና ህይወት የተዳረጉ ህፃናት፣ ጧሪና ቀባሪ አጥተው እጅግ አስከፊ ህይወት የሚመሩ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መኖራቸውን አመልክተው፣ ሁሉም አቅሙ በፈቀደውና በቻለው መጠን የእነዚህን ወገኖች ህይወት ለመለወጥና ለችግራቸው ደራሽ ለመሆን መሥራት አለበት ብለዋል፡፡ ኩባንያው ለአንድ ዓመት ለድርጅቶቹ ለመስጠት ላሰበው እርዳታና ድጋፍ አመስግነው ጉዳዩ የሁሉም ዜጋ ሐላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል በ2002 ዓ.ም የተቋቋመና በአሁኑ ወቅት ከ140 በላይ የአዕምሮ ህሙማንና አረጋውያንን በመርዳት ላይ የሚገኝ በጐ አድራጊ ድርጅት ሲሆን ሜሪጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ደግሞ እናትና አባት የሌላቸውን ህፃናትንና አቅመ ደካማ አረጋውያንን በመንከባከብ ለረዥም ዓመታት ሲሰራ የቆየ በጐ አድራጊ ድርጅት ነው፡፡

Read 3360 times